Monday, 07 November 2011 13:23

በሚዩዚክ ሜይዴይ (ውይይቱን እንደታዘብኩት)

Written by  እንድሪያስ
Rate this item
(0 votes)

ባለፉት ሰባት ዓመታት በየ15 ቀኑ እሁድ እሁድ ከ170 በላይ የሥነ - ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ውይይት ያካሄደው “ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የንባብና የውይይት ክበብ” ባለፉት ጥቂት ወራት ታሪክ ቀመስ መጻሕፍትን ብቻ የሙጥኝ ብሎ ነበር፡፡ “ቄሳርና አብዮት”፣ “ጃገማ ኬሎ”፣ “የሀበሻ ጀብዱ”፣ “ደቂቀ እስጢፋኖስ” እና “ትዝታ ዘ አለቃ ለማ” የተሰኙትንና በክበቡ ውይይት የተካሄደባቸውን መጻሕፍት በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በታዳሚዎች ተደጋጋሚ ውትወታና “እስቲ አሁን ደግሞ ፊታችንን ከፍተኛ ተነባቢነትን ወዳገኘ ወጣት ደራሲ እንመልስ” በሚል እሳቤ ይመስላል የደራሲ መሐመድ ሱልማን “ፒያሳ ማሕሙድ ጋ ጠብቂኝ” የተሰኘው ተወዳጅ መጽሐፍ ያሳለፈነው እሁድ ተረኛ የሆነው፡፡

ውይይቱ ከሚጀምርበት ስምንት ደቂቃዎች ቀድሞ አዳራሹ ሞልቶ መቀመጫ ጠፋ፡፡ ሰዓት አክብረው የመጡትም መሬት ላይ ተቀምጠውና ቆመው ውይይቱን ለመታደም ተገደዱ፡፡ አዳራሹ ውስጥ ካለው ሰው እኩሌታ የሚሆኑ ታዳሚዎች በቦታ እጦት ተመለሱ፡፡ 
አዳራሹ ጢም ብሎ መፈናፈኛ ስለጠፋና ሙቀቱ ስለበረታ በስተቀኝ ጥግ የሚገኘው የጀርባ በር ተከፈተ፡፡ “የቡና ቤት ሥዕሎች”፣ “አውዳመት”፣ “የሌሊት ድምፆች” እና “አዜብ” በተሰኙት መጻሕፍቱ የምናውቀው አንጋፋው ደራሲና የወግ ፀሐፊ መስፍን ሀብተማርያም ለውይይቱ የሚሆነውን የዳሰሳ ጽሑፍ ለማቅረብና መጽሐፉን ለመሔስ ቦታውን ያዘ፡፡ የሚዩዚክ ሜይዴይ አወያይ በፍቃዱ አባይ፤ ደራሲው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነት ስለሚያገለግል ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በውይይቱ ላይ መገኘት እንዳልቻለና ለዚያም ይቅርታ መጠየቁን ገለፀ፡፡
እንደወትሮው፣ ጋሽ መስፍን ዳሰሳውን ከረጅም ጊዜ የቅርብ ጓደኞቹ ጋር የሚያወራ ያህል በቀልድ፣ በቧልትና በፌዝ እያዋዛ ነበር ያቀረበው፡፡ ደራሲው መሐመድ ሱልማን “ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ” በሚለው ሰፊ ምዕራፍ ስር በተለምዶ “የፒያሳ ልጆች” የሚባሉትንና የሱ ዘመነኞች የሆኑትን አለማየሁ እሸቴ፣ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርና ሌሎችን ጠቅሶ ከነሱ ጋር የማይጠፋውን መስፍን ሀብተማርያምን አለማካተቱ እንዳስከፋው በአሽሙር ገልጾ አዳራሹ ውስጥ የነበረውን ሰው በሳቅ አንከትክቷል፡፡
ጋሽ መስፍን በአሁኑ ጊዜ የሚያነባቸው አብዛኞቹ ወጐች እንደማያስቁት ገልጾ መሐመድ ሱልማን በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ያካተታቸው ወጐችና መጣጥፎች ግን በተደጋጋሚ እንዳሳቁትና እንዳፍነከነኩት አልሸሸገም፡የደራሲውን አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች፣ ውብ የቋንቋ ብቃትና ለየት ያለ አቀራረብም ወዶታል፡፡ በዚህ ረገድ የወደዳቸውን አናቅጽም፡፡ ከመጽሐፉ የተለያዩ ምዕራፎች መርጦ አንብቧል፡፡ አሁን ላለንበት የጥድፊያና የሩጫ ዓለም ከድርጊት ድርጊት ወይም ከሀሳብ ሀሳብ በፍጥነት የሚያሸጋግሩን አጫጭር ዓረፍተ ነገሮች ተመራጭ መሆናቸውንና ደራሲውም ይህን በተገቢው መንገድ መጠቀሙን አወድሷል፡ ደራሲው ለፊደላትና ለሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ያደረገውን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሁም በአጠቃላይ የአርትኦት ሥራው ላይ ያሳየውን ጭንቀትና ጥበት አድንቋል፡፡ ሆኖም ጋሽ መስፍን “ራስጌ ላይ በጨለማ መደብ ላይ እንዲያርፍ የተደረገው የገጽ ቁጥርና የመጽሐፉ ርዕስ እንደኔ ያሉ አዛውንቶችን የማየት ችግር ያላገናዘበ ነው፡፡ ከ50 ዓመት በላይ ላለነው ሰዎች ሊታሰብልን ይገባ ነበር” ሲል ቅሬታውን በፌዝ መልክ ገልጿል፡፡
ከቆይታ በኋላ አወያዩ በፍቃዱ አባይ፤ ታዳሚዎች ለጋሽ መስፍን ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉ አልያም ስለመጽሐፉ ያላቸውን ማንኛውም አስተያየት መስጠት እንደሚችሉ ያቀረበውን ግብዣ ተከትሎ፣ በርካታ ታዳሚዎች ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡ አንዱ ታዳሚ ጋሽ መስፍን ደራሲው በድፍረት፣ በገለልተኝነትና በብስለት ስለፃፋቸው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ምዕራፎች ምንም አለማለታቸውን ነቅፏል፡ጠያቂው አያይዞም ደራሲው ሙስሊም እንደመሆኑ በመጽሐፉ ውስጥ ከእምነቱ የበቀሉ ቱባ ቃላትና ዘዴዎችን ቢጠቀም መጽሐፉ ለኢትዮጵያ ሥነ - ጽሑፍ ዕድገት የበለጠ አዎንታዊ አበርክቶት ይኖረው እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ከጋሽ መስፍንና ከውይይቱ ታዳሚዎች ለደራሲው የተቸረው አድናቆትና ውዳሴ ያሰጋው ሌላ ታዳሚ “ደራሲው ከፍተኛ የሥነ - ጽሑፍ ተሰጥኦና ብዙ የመሥራት እምቅ ኃይል ቢኖረውም ገና በመጀመሪያ ሥራው ይህን ሁሉ ውዳሴ ማቅረብ ደራሲውን ማጥፋት አይሆንም?” የሚል መልዕክት ያዘለ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የ67 ዓመቱ ጋሽ መስፍን የመርሳት ችግር ሳያገኛቸው አልቀረም፡፡ የመሐመድ ሰልማን መጽሐፍ ውስጥ አንድ ምዕራፍ የተሰጠው “የጀሚላ መዳፎች” ታሪክ ማጠንጠኛ ወሎ ሰፈር ሆኖ ሳለ ፒያሳ አድርገው ተናግረዋል፡፡ ይኼም በአዳራሹ ከሚገኙ ታዳሚዎች ትዝብት ውስጥ ጥሏቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ስለተደጋገመበት ይመስላል አንዱ ስሜታዊ ታዳሚ “ጋሽ መስፍን በርግጥ መጽሐፉን አንብበኸዋል ወይስ አንብበህ ረስተኸዋል...” ሲል የጠየቀው፡፡ ጠያቂው አያይዞም “አደይ መቀሌ”፣ “በኤርትራ ሙዚቃ የምትደንስ ከተማ፣ “ከአዲግራት እስከ ዛላንበሳ” የሚሉትና ሌሎች ጽሑፎቹን ደራሲው በገለልተኝነትና ሚዛናዊ ስሜት እንዲሁም በጥናት ላይ ተመሥርቶ መሥራቱን አድንቋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አርኪቴክት ገብረመድህን በበኩሉ፤ መሐመድ ሰልማን ስለ ፒያሳ የፃፈ የመጀመሪያው ሰው እንዳልሆነ በመግለጽ እነ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ፍቅሩ ኪዳኔና ሌሎችም በመሐመድ ዓይነት ዕይታና አቀራረብ ባይሆንም ስለ ፒያሳ እንደፃፉ ገልጿል፡፡ ሐሳቡን በመቀጠልም ልክ ደራሲና ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገላጋይ ስለ አራት ኪሎ ጽፎ የፈረሰውን ሰፈር “አጥቢያ” በተሰኘው መጽሐፉ ዘላለማዊ እንደማድረጉ የመሐመድም “ፒያሳ መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ” ተመሳሳይ የሰነድነት ፋይዳ አለው ብሏል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ መጽሐፉ ይህን ዘመን ቁልጭ አድርጐ እንዳሳያቸው ገልፀዋል፡፡ ደራሲው በዚህ መጽሐፉ አሁን ያለንበትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እውነታ በድፍረት፣ በከፍተኛ አስተውሎትና በገለልተኛ ዕይታ እንዳንፀባረቀ ተናግረዋል፡፡
ወደ ውይይቱ ማሳረጊያ አካባቢ ደራሲውን ከጳውሎስ ኞኞ አማተር የጋዜጠኞ ማኅበር የሥነ-ጽሑፍ ተሳትፎው ጀምሮ በቅርበት የሚያውቀው ወዳጁ፤ ይህ መጽሐፍ የደራሲው የመጀመሪያ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ለወሰዱት በሰጠው እርማት ደራሲው ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ያደረሳቸውንና ያዘጋጃቸውን መጻሕፍት ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ ደራሲ “ዳሰሳ ዘ ኃይማኖት” የሚል መጽሐፍን ከአንድ የሥራ አጋሩ ጋር በጋራ፣ ሦስት የእንግሊዝኛ ንግግር መማሪያ መጻሕፍትን በግል እንዲሁም አንድ የአረብኛ ቋንቋ አጋዥ መጽሐፍን በግል ጽፎና አዘጋጅቶ ለአንባብያን እንዳቀረበ ገልጿል፡ ከ”ፒያሳ ማሕሙድ ጋ ጠብቂኝ” በፊት አምስት መጻሕፍትን ለሕትመት አብቅቷል ማለት ነው፡፡
አወያዩ በፍቃዱ አባይ፤ መጽሐፉ አሁን ስድስተኛ እትም ላይ መድረሱንና እስካሁን አርባ ሺህ ኮፒ ያህል መሸጡን ገልጿል፡፡ እኔም በግሌ ከመጽሐፍ አዟሪዎች፣ መሬት ላይ መጻሕፍት ዘርግተው ከሚሸጡ ነጋዴዎች እንዲሁም ብሔራዊ ጀርባ ከሚገኙ መጻሕፍት መደብሮችና አከፋፋዮች ጠይቄ ባገኘሁት መረጃ፤ የመጽሐፉ ገበያና ተፈላጊነት አልቀነሰም፡ ሁሉም በገበያው ደስተኛ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ “መጽሐፍ እየፃፉ መኖር አስቸጋሪ ነው” የሚሉ የቆዩና ስር የሰደዱ አባባሎች በበርካታ ፀሐፍት ስኬት ውድቅ ሲሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡ ሕይወታቸውን በመጻሕፍት ላይ የመሠረቱ ነጋዴዎችና ፀሐፍትም እየተበራከቱ ነው፡፡ አንባቢውም እንደፍላጐቱ በሚፈልገው ዘርፍ የሚፈልገውን መጽሐፍ እያገኘ ነው፡፡ አሳታሚዎች የአንባቢውን ፍላጐት የተረዱ ይመስላሉ፡፡
የመሐመድ ሱልማን ስኬት ወደ ሥነ-ጽሑፉ ዓለም ለመምጣት ፍላጐቱ ላላቸው በርካታ ወጣቶች ጥሩ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ የኅብረተሰቡን የንባብ ባህል ለማዳበር የሚተጋው ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመጻሕፍት ንባብና ውይይት ክበብ፤ ባሳለፍነው እሁድ ያካሄደውን ውይይት በጨረፍታ የቃኘሁበትን ጽሑፌን በዚህ ላብቃ፡፡ ቸር እንሰንብት!

 

Read 3317 times Last modified on Monday, 07 November 2011 13:31