Sunday, 31 March 2024 20:13

የአውሮፕላን ላይ ወግ (Ichigo ichie – one time, one meeting!)

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(1 Vote)

ከአስር ሰዓት በላይ የሚፈጀውን የቻይና በረራ በራሴ ላይ ላለማክበድ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ በምሽት ተነስተን ለሊቱን እስከ ንጋት ስለምንጓዝ በበረራ ላይ ግማሹን ለሊት ለመተኛትና ግማሹን  ደግሞ እያነበብኩ ለመሄድ ስላቀድኩ መጽሐፌን ሸክፌያለሁ፡፡ ጥሩ እቅድ ነበር፡፡
አውሮፕላኑ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ግን አልተሳካልኝም፡፡
በረራ ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ አብዛኛው ሰው እንቅልፉን ይለጥጠው ጀመር፡፡ እኔ አነቃቂ ጭስ እንዳጨሰ ሰው እየተቁለጨለጭኩ በሌሎች መቅናት ሆነ ስራዬ፡፡ መፅሐፉንም ቢሆን  ሃሳቤን ሰብስቤ ማንበብ አቃተኝ። ግራ ገባኝ፡፡ ሲደካክመኝ ብቻ አንድ አስር ደቂቃ እንቅልፍ መሳይ ሸለብ አድርጎኝ ብነቃ አንገቴን በህመም ውስጥ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ትራስ ስላልነበረኝ አንገቴ ተጣሞ ነበር፡፡ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ አንገቴን እያሻሸሁና ዙሪያዬን እየቃኘሁ ተወዘፍኩ፡፡
ከጎኔ ያለው ቻይናዊ መሳይ ሰውዬ ችግሬ የገባው ይመስል ትንንሽ አይኖቹን ጨፈን በማድረግ ፈገግታውን ለገሰኝና እየተንጠራራ ሊያዋራኝ ሞከረ፡፡ ፈጠን ፈጠን በሚል እንግሊዝኛ፡፡
‹‹ትራስ መሳይ የአንገት ድጋፍ ላውስህ?›› ሲል ጠየቀኝ፤ በአንገቱ ዙሪያ ያደረገውን ደንገል እያሳየኝ፡፡
‹‹አመሰግናለሁ፡፡ የእርስዎን ወስጄማ እንዴት? …›› አልኩ ግራ እንደገባኝ፡፡ (ለነገሩማ ወሬው ሁሉ በ‹ዩ› እና ‹ዩርስ› … ስለሆነ እርስዎ እየተባባልን እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ቢሆንም ሽማግሌውን  አክብሬ ማውራቴን ልንገራችሁ ብዬ ነው፡፡ )
‹‹ረጅም ጉዞ ስለሆነ ትራስ መያዝ ነበረብህ፡፡ የበረራ ልምድ የለህም?›› አለኝ በጥርጣሬ፡፡
‹‹የለኝም፤ የአገር ውስጥ በረራዎችም ግፋ ቢል ከአንድ ሰዓት በላይ ስለማይወስዱ አያስቸግሩም፡፡››
‹‹ገባኝ፡፡ ከልምድ ነው ብዙ ነገር የሚገኘው። ልምድ ያሰለጥናል፣ ልምድ ጥበበኛ ያደርጋል፡፡ አንድ የአገሬን ሰዎች ብልሃት ልንገርህ፡፡ በነገራችን ላይ ስሜ ካዙኪ ይባላል፡፡ ሰላም ወይም ብርሃን ማለት ነው፡፡ 69 አመቴ ነው፡፡ ጃፓናዊ ነኝ። በርግጥ እናቴ ቻይናዊ አሜሪካዊት ስለሆነች መልኬ ብዙ ሰው ግራ ያጋባል፡፡ አባቴ ከቶኪዮ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በገጠር ቀበሌዎች ውሃ ከጥልቅ በመቆፈር የተሰማራ የግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ ነው የማገለግለው። ከአገሬ ጡረታ ወጥቻለሁ፡፡›› አለና ፈገግ ሲል የበለዙ ጥርሶቹንና የሚያፍን የአፍ ጠረኑን ተጋፈጥኩት። ሰውየው አጠር አድርጎ የህይወት ታሪኩን ነገረኝ ማለት ነው፡፡
ቻይኖችና ጃፓኖች ሲቀላቀሉ ካዙኪን ይመስላሉ ብዬ እየተገረምኩ አየሁትና፣ በጨዋ ደምብ ስሜን ነገርኩት፡፡ አብይ እባላለሁ፡፡ ለጥቄም በእንግሊዝኛ ፊደል ስሜን ፅፌ እያሳየሁ ተዋወኩት፡፡
‹‹ስምህን የት እንደሰማሁት እንጃ እንጂ የማውቀው አይነት ስም ነው …››
‹‹ይሆናል … ›› አልኩና እኔም ፈገግታውን ተካፈልኩ፡፡ በሰዓታት ውስጥ ያገኘኋት የመጀመሪያ ፈገግታዬ ነበረች፡፡ ለእኔ ፈገግታ ውድ፣ ፊትን አጨፍግጎ መዋል ደግሞ ልምድ ነው፡፡
‹‹ልምድ ጥበበኛ ያደርጋል ነበር ያልከኝ?! … ›› ስል ወደ ጨዋታችን ተመለስኩ፡፡
‹‹… እ … አዎ ልክ ነህ! ልምድ ሲዳብርና ከራስ እውቀት ተገምዶ ሲመነጭ ይበልጥ ብልሃተኛ ያደርጋል ነው የምልህ፡፡ ጃፓኖች አሳ በጣም እንደሚወዱ መቼም ታውቃለህ፡፡ እናም ጃፓን ውስጥ አሳ የሚወደደው ትኩስ ሲሆን ነው። ከፍሪጅ የከረመ አሳ ማንም አያደንቅም። ታዲያ በድሮ ጊዜ የሰው ቁጥርም አነስተኛ ስለነበረ ከአቅራቢያ ካለው ወንዝና ውቅያኖስ እየተጠመደ በትኩሱ ይቀርብ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሰውም እየበዛ፣ የአሳዎቹም ቁጥር እየቀነሰ በመሄዱ አሳ አጥማጆቹ በውቅያኖሶቹ ላይ እየራቁ ማጥመድ ግድ ሆነባቸው፡፡ እየራቁ ሲሄዱ ደግሞ ለቀናት በውሃው ላይ ሰንብቶና ያገኙትን አሳ ሰብስቦ መምጣት ሆነ፡፡ መሰንበት ከተጀመረ ደግሞ አሳዎቹ ይበላሻሉ፣ ስለዚህ ጀልባዎቹ ላይ ትልልቅ ማቀዝቀዣዎችን መግጠም ተጀመረ፡፡
በርግጥ አሳዎቹን በማቀዝቀዣ አቆይቶ ማምጣትም የፈላጊዎቹን ቁጥር እንዲቀንስ አደረገ፤ ስለዚህ ሌላ አማራጭ መምጣት ነበረበት፡፡ ጀልባዎቹም በጣም እያደጉ ነውና በላያቸው ላይ ትንንሽ ሰው ሰራሽ ውሃማ ኩሬዎች (ትልልቅ ገንዳዎች) በማድረግ አሳዎቹ እንደተጠመዱ፣ ከመረቡ ወደ ገንዳዎቹ ገልብጦ ለቀናት በህይወት እንዲቆዩ ማድረግ ተጀመረ … ››
‹‹ድንቅ! …›› አልኩ ሳይታወቀኝ
‹‹…በዚሁ አላበቃም’ኮ፡፡  እንዲህ ማድረጉ ጥሩ ዘዴ ነበር፡፡ ሆኖም ጀልባዎቹ እየራቁና በውሃው ላይ ብዙ ቀናት በቆዩ ቁጥር ወደ ገንዳው የተጨመሩት አሳዎችም ከቀናት የኩሬ የዋና ቆይታ በኋላ መድከም፣ መደበርና ፍሬሽ ጣእማቸውን ማጣት እንዲሁም ጥቂቶቹ መሞት ጀመሩ፡፡ ይህ ደግሞ ለአጥማጆቹ  ሌላ ተጨማሪ ችግር ሆነ፡፡ ያልሞቱትም አሳዎች ጣዕም ተቀየረ።››
‹‹… እና ምን አደረጉ ታዲያ? ….››
ከትንሽዬ የፈገግታ ርችት ቀጥሎ እንዲህ አለኝ … ‹‹ቀላል መፍትሔ ተገኘ፡፡ በኩሬው ውስጥ ከሚከተቱት አሳዎች ጋር ጥቂት ትንንሽ ሻርኮችን አብረው ይጨምራሉ፡፡ ሻርኮቹ አሳዎቹን ለምግብነት ስለሚፈልጓቸው በኩሬው ውስጥ ልባቸው እስኪጠፋ ያሯሩጧቸዋል። ስለዚህም አሳዎቹ ለማምለጥ ሲሯሯጡ ከርመው ከነነፍሳቸው ፍሬሽ ጣዕም ይዘው ለገበያ መቅረብ ጀመሩ፡፡ ታዲያ ይህ ልምድ የሚሰጥህ ጥበብ አይደለምን?››
‹‹ነው’ንጂ!…›› አልኩ በእርካታ። ‹‹ስለተዋወቅንና ይህንን ስላጫወትከኝ አመሰግናለሁ፡፡›› አልኩት ከልቤ፡፡
‹‹ኢቺጎ ኢቺ - one time, one meeting! ይላሉ የኔ አገር ሰዎች፡፡›› (ያገኘሃትን አንዲት የህይወት አጋጣሚ ማድነቅና ማክበር አለብህ፤ ድጋሚ ላይገኙ ይችላሉና ለማለት ነው፡፡)
‹‹ኢቺጎ ኢቺ! … ግሩም ድንቅ አባባል፡፡ አጭርና ግልፅ!›› አልኩ በለሆሳስ፡፡
ሽማግሌው ካዙኪ ደንገል የአንገት ትራሱን አቀበለኝና፣ እንደልጅ እንጣጥ ብሎ ተነስቶ ወደ መታጠቢያ ቤት አመራ፡፡ እኔ በአንገቴ  ዙሪያ ትራሴን አስደግፌ ትንሽ እፎይታ አገኘሁ፡፡ ልምድ ማጣት አልኩ በልቤ፡፡ አይኔን ከደን አድርጌ፤ ድጋሚ አውሮፕላን ላይ የምወጣ ከሆነ ግን … ስል ከምናቤ ጋር ተነጋገርኩ፡፡
ሽማግሌው ተመልሶ መጥቶ ኖሮ ከአጠገቤ ቆሞ ሰውነቱን እያፍታታ፤ ‹‹እንቅልፍ ያዘህ እንዴ?›› ሲል በለሆሳስ ጠየቀኝ፡፡
‹‹.. በፍጹም! .. ›› አልኩ ፈገግ ብዬ አይኖቼን ‹ቷ›  አድርጌ እየገለጥኩ፡፡  
‹‹ሌላ የአገርህ ወግ ልንገርህ?››
‹‹ደስ ይለኛል!›› አልኩ ለመስማት እየጓጓሁ፡፡
‹‹…መንዝ አካባቢ አንድ ሽማግሌ በአስተርጓሚ ያጫወቱኝ ነው፡፡ ረጅም የእግር መንገድ እየተጓዝን ነበር፡፡ እናም ሽማሌው እንዲህ ሲሉ የመንገድ ወሬ አመጡ፡፡ አንድ ገበሬ አራት አህዮች ጭኖ ወደ ከተማ ይጓዝ ነበር፡፡ ጠጋ ብዬ ወዴት እየተጓዘ እንደሆነ ጠየኩት፡፡ እርሱም ወደገበያ ሲል መለሰልኝ፡፡
‹አህዮችህ ምን ተጭነዋል?›      ‹የመጀመሪያው አህያ የተጫነው ትዕቢትና ጉረኝነት ነው፡፡ ›
‹እሱን ደግሞ ማን ይገዛል?› ስል በመገረም ጠየኩት፡፡
‹ፈላጊዎቹና ገዢዎቹማ በብዛት የተማርንና የተመራመርን ነን የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡› ሲል መለሰልኝ
‹ሁለተኛውስ?›
‹ሁለተኛው አህያ  የተጫነው ማጭበርበርና ተንኮል ነው፡፡›
‹የእርሱስ ፈላጊዎች እነማን ናቸው? ›
‹እርሱን አምጣልን ያሉኝ ስግብግብ ነጋዴዎችና ስራ ፈቶች ናቸው፡፡› ሲል በፈገግታ መለሰና ጨዋታውን ቀጠለ፤ ‹ሦስተኛው አህያ የተጫነው ቅናት ነው፡፡ የእርሱ ፈላጊዎች ደግሞ እርስ በእርሳቸው የሚቀናኑ ሃብታሞች ናቸው። መቼም አንዱ አንዱን ለማጥፋት እንቅልፍ የላቸውም፡፡ የመጨረሻውን አህያ ግን የጫንኩት በልዩ ትዕዛዝ ነው› ብሎ በሳቀ ተርገፈገፈ፡፡
‹ምን ይሆን? › ስል በጉጉት ጠየኩ፡፡
‹አራተኛውን አህያ እንዲህ እስኪጨነቅ ድረስ ቀርቅቤ የጫንኩት አምባገነንነትንና ባርነትን ነው፡፡ እንግዲህ ሳልነግርህ እንደሚገባህ ጨቋኝ ገዢዎችና አምባገነን አለቆች ተሻምተው ነው የሚገዙኝ፡፡ አምባገነንነት ህዝቡን የሚጠረንፉበት ስርዓት ሲሆን ባርነትን ደግሞ በነፃ እንደ እጀ ሙቅ ያጠልቁለታል፡፡ › እያለ አብራራ፡፡ ››
ሰውየው አውርተውኝ ሲጨርሱ ‹‹ይህንን ሁሉ የሚያከፋፍል ገበሬ ይኖራልንዴ?›› ስል እንደቀልድ ጣል አረኩባቸው
እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ ‹‹የሚገዛ ካለ የሚያከፋፍል አይጠፋም፡፡ በርግጥም እነዚህን ነገሮች ገበሬ መስሎ የሚያከፋፍለው ራሱ ሰይጣን መሆኑን ያወኩት በስመዓብ ብዬ ፀሎቴን ጀምሬ ስጨርስ ነበር፡፡›› እያሉ በሳቅ ተንፈቀፈቁ፡፡
ወይ ግሩም፡፡ አድማጭ ካለ አስተማሪው በየትም አለ አይደል የሚባለው፡፡
‹‹… የቻይኖችን ብልሃት ደግሞ ልንገርህ …..››
እንዲህ እንዲህ እያለ ሲያወራኝ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወስዶኝ ኖሮ፣ አውሮፕላኑ  መሬት ሲዳብስ ራሱ ፈፅሞ አልሰማሁትም ነበር፡፡ ሁሉም እቃውን እያነሳ ወደ መውጫው ሲያቀና ነበር የተቀሰቀስኩት፡፡ የአየር መንገዳችን አርማ ያለበት ቅጠልያ የክር ፎጣ ከፊቴ ላይ ጣል አድርገውልኝ ኖሯል፡፡ እንደልማዴ አፌን ከፍቼ እንደከሰል ባቡር እያጓራሁ አንኮራፍቼ ይሆን?
በድካም እየተንጠራራሁ ስነሳ ወደ መውጫው መንገድ ጉዞውን ጀምሮ የነበረው ሚስተር ካዙኪ በሙሉ ፈገግታ ተሞልቶ ወደ እኔ መጣና እንዲህ አለኝ፤
‹‹….ለካ ስምህ የማውቀው የመሰለኝ በርግጥም ስለማውቀው ኖሯል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትራችሁ ስም አይደለም’ንዴ?!›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
በፈገግታ ተሞልቼ በአዎንታ ራሴን ሽቅብና ቁልቁል ስነቀንቅ አንገቴ ላይ ህመም ተሰማኝ፡፡
‹‹እኔ ደግሞ ነፍሳቸውን ይማርና ሽንዞ አቢን ያሥታወስክ መስሎኝ ነበር፡፡›› አልኩት፤እንደቀልድ፡፡ ቀድሞውኑ ምን እንዳሰበ ገምቼ ነበር፡፡ ‹‹ ለነገሩስ ሁለቱም ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው … ፡፡››
የአንገቴን ህመም እያባበልኩ በዚያውም የሽማግሌውን ትራስ ከአንገቴ ዙሪያ አቅፎኝ አገኘሁትና በምስጋና ስመልስለት፤ ውሰደው እባክህ በሚል እጁን አወናጨፈ፡፡
‹‹ለመልስ ጉዞ ይሁንህ፡፡ ትመለስ የለም?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
በፈገግታ አንገቴን ወደ ጎን ዘንበል፣ ከንፈሬን ወደ ጎን ሸርመም፣ ግንባሬን ሸብሸብ…. አድርጌ በምልክት መለስኩለት፡፡ የገባው አልመሰለኝም። በመቀጠል በድካም የዛለ ሰውነቴን በኮሪደሩ መሃል እንደ ሃምሳ እግር መጎተት ጀመርኩ፡፡ አፍንጫዬን ጥቅጥቅ አድርጎ አፍኖኝ አገኘሁት፡፡ የአፍ ጠረን በጣም ነው የሚረብሸኝ፡፡
ከኋላዬ በርቀት፤ ‹‹… ኮ .. ል .. ን … ›› የሚል የሽማግሌው ድምፅ ተሰማኝ፡፡
መልካም ዕድል እንደማለት በጃፓንኛ። ሁለቱንም እጆቼን ወደላይ በማድረግ ተሰናበትኩት፡፡ ኢቹጎ ኢቺ!

 

 

 የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Read 681 times