Sunday, 06 November 2016 00:00

ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ባለቤቱ እጅ ገብቷል

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

‹‹ሠይጣን የሚያድረው፤ ከዝርዝር ነገሮች ነው››

  ይኸው አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፈጠረው የሰላም ጥላ አረፍ ብዬ ማሰላሰል ይዤአለሁ። ያ ‹‹ፖለቲካዊ ጠሮ›› (Political Hurricane) ብዙ ካንገላታን በኋላ አሁን ደብ ብሏል፡፡ ነጠላ እንደሚቋጭ ሰው፤ አዕምሮዬ ሁለት ነገሮችን መቋጨትና ማሰላሰል ይዟል፡፡ በሁለት ሐሳቦች ቅኝት ያንጎራጉራል፡፡ አንዱ የደስታ፤ ሌላው የመጓደል ቅኝት ነው፡፡ እኒህን ሁለት የህሊና ቅኝቶች ድምጽ እንዲያገኙ ለማድረግ እጽፋለሁ። በደስታ የማውጠነጥነው ነገር፤ የዴሞክራሲ ስርዓቱ ከእውነተኛ ባለቤቷ እጅ መግባቷን በመመልከት የተፈጠረ ደስታ ነው፡፡ በመጓደል ስሜት የሚጎተጉተኝ ነገር፤ በሁከቱ ወቅት በታየው በማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት ሳቢያ የተፈጠረው ቁስል እንዲሽር ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሳለ፣ ለዚህ ጉዳይ የተለየ ትኩረት አለመሰጠቱ ነው፡፡
መንግስት የችግሩ ምንጮች የአመራር ጉድለት ወይም የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ያወሳል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ነገሮችንም እንደ ምክንያት ያነሳል፡፡ ለችግሩ ምክንያት ሆነው የታዩትን ነገሮችም ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህ ረገድ ሊነሳ የሚችለው የጋለ ወቅታዊነት ያገኘው የካቢኔ ሹም ሽሩ ነው፡፡ በዚህ የመንግስት ውሳኔ ብዙዎች መደሰታቸውን የሚያመለክቱ አስተያየቶችን እየሰማሁ ነው፡፡ መልካም ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ለውጡ የፖሊሲ ካልሆነ፤ ለውጥ አያመጣም›› ሲሉ ይሰማል፡፡ እኔ ይህ ‹‹መሐይም›› አስተያየት ይመስለኛል፡፡ አሁን ከኢህአዴግ የፖሊሲ ለውጥ አልጠብቅም፡፡ ኢህአዴግን ኢህአዴግ የሚያሰኙ ፖሊሲዎችን ከቀየረ ኢህአዴግ መሆኑ ይቀራል፡፡ የፖሊሲ ለውጥ በሚቀጥለው ምርጫ፤ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ሊሳካ የሚችል እንጂ ከኢህአዴግ የሚጠበቅ እርምጃ አይመስለኝም፡፡ ‹‹ጽድቁ ቀርቶ፤ በወጉ በኮነኝ›› ለማለት የሚጋብዝ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግንም፤ ‹‹ከስቼ ቢያዩኝ ጅማት ለመኑኝ›› ሊያሰኘው ይችላል፡፡
እኔ የፖሊሲ ለውጡን ትቼ፤ በካቢኔ ለውጡ ዙሪያ ሐሳብ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ የተደረገው የካቢኔ ለውጥ አስደሳች የሆነውን ያህል፤ አሳሳቢ ነገሮችም ያሉት ነው፡፡ ሆኖም ነገሩን በሚዛን ስናየው፤ ለውጥ ባለማድረግ ከሚገኘው ጥቅም የበለጠ ለውጥ በማድረግ የሚገኘው ጥቅም የሚበልጥ መስሎ ይታያኛል፡፡ የህዝብ እምነት በከፋ ደረጃ ለተሸረሸረበት መንግስት ውሳኔው ህይወት የሚዘራ እንጂ የሚጎዳ አይሆንም፡፡ እንዲሁም ለውጡ ከላይ መጀመሩ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ እርምጃ ነባሩንና ትችት ያስነሳ የነበረውን (በታችኛው መዋቅር ላይ ያተኮረ ሹም ሽር) አካሄድ የቀየረ እርምጃ በመሆኑ የሚደገፍ ነው፡፡ ሆኖም በበኩሌ ከተጠቀሱት በጎ ነገሮች በላቀ ግምት የማከብረው አንድ ጉዳይ አለ። ይህም ጉዳይ ከመነሻዬ ‹‹የዴሞክራሲ ስርዓቱ ከእውነተኛ ባለቤቷ እጅ መግባቷ›› በሚል የጠቀስኩት ጉዳይ ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ረገድ የማነሳውን ነገር ለማቅረብ አንድ ምሣሌ እጠቀማለሁ፡፡ ይህ ምሣሌ ወደ ቻይና ይወስደኛል፡፡ ቻይና ሄጄ የማነሳው የአንድ ቻይናዊ ፈላስፋ ታሪክን ነው፡፡ ባለታሪካችን ‹‹ሳንዙ›› ይባላል። ሳንዙ፤ ክርስቶስ ከመወለዱ ከ500 ዓመታት በፊት በምድረ ቻይና የተመላለሰ ፈላስፋነው፡፡ የጦርነት ባለሙያ ነው፡፡ ሳንዙ በዓለም ህዝብ ዘንድ የሚታወቀው ‹‹የጦርነት ጥበብ›› (The Art of War) በተሰኘ መጽሐፉ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው፤ ወደ ጎን 25 የሚደርሱ የቻይና ፊደላትን መያዝ በሚችሉና ማስመሪያ በመሳሰሉ ቀጫጭን የሸንበቆ ቁርጥራጮች ላይ ነው፡፡ ሳንዙ፤በጥንታዊት ቻይና ‹‹ሁ›› የተባለች ግዛት የተወለደ ሲሆን፤ የሐገሩ ንጉሥ ‹‹ሐሉ›› ይሰኛል፡፡
ንጉስ ‹‹ሐሉ››ክፉ ጎረቤት ነበረው፡፡ ‹‹ው›› በተባለች ግዛት የነገሠው፤ የንጉሥ ‹‹ሐሉ››ክፉ ጎረቤት ክፉ አሰቦ ዝግጅት ጀመረ፡፡ ወታደራዊ አቋሙን ማጠናከር ያዘ፡፡ ታዲያ ይህን ሁኔታ የተመለከተው ንጉሥ ‹‹ሐሉ›› ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት አሰበ፡፡ ስለዚህ የጦር ባለሙያ ያልነውን ‹‹ሳንዙ››ን ጠርቶ ምክር ጠየቀው፡፡ ‹‹ሳንዙ›› የጦር መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ነጋዴዎችና  ሌሎች ሰዎች ጭምር መመሪያ አድርገው የሚጠቀሙበትን ዘመን ተሻጋሪ ጥበብ ያስተማረ ፈላስፋ ነው፡፡ በዚህ የጦር ባለሙያ እምነት ‹‹የተደራጀና ብቃት ያለው ሠራዊት እንጂ የጀሌ መብዛት ፋይዳ የለውም፡፡››
ስለዚህ በርካታ ሠራዊት ካለው እና ለወረራ ዝግጅት ሲያደርግ ከነበረው የ‹‹ው›› ንጉሥ የሚሰነዘርን ጥቃት በብቃት ለመመከት፤ ብቃት ያለው እንጂ ብዛት ያለው ሠራዊት አያስፈልግም የሚል እምነት የነበረው ‹‹ሳንዙ››፤ ‹‹ማንኛውንም ሰው ምርጥ ወታደር ማድረግ ይቻላል›› ብሎ ያስብ ነበር፡፡ ስለዚህ ንጉሡ፤ ‹‹አንተ ማንኛውንም ሰው ብቁ ወታደር ማድረግ ይቻላል ትለኛለህ፡፡ እንዲያው ለመሆኑ፤ እነዚህን የቅልጣን ኑሮ የለመዱ፤ በዶሮ ላባ ሊደማ የሚችል የላመ ሰውነት ያላቸውን ሞልቃቃ የጭን ገረዶች ብቁ ወታደር ልታደርጋቸው ትችላለህን?›› ሲል ‹‹ሳንዙ›› ጠየቀው፡፡
‹‹ሳንዙ›› ለንጉሡ ጥያቄ የሰጠው መልስ፤ ‹‹ያለ አንዳች ጥርጥር ብቁ ወታደር ላደርጋቸው እችላለሁ›› የሚል ነበር፡፡ እናም የንጉሡን የጭንገረዶች ማሰልጠን ጀመረ፡፡ የጭን ገረዶቹን ሰብስቦ ራስን የመከላከል ወታደራዊ ጥበብ ለማስተማር ሲሞክር፤ እኒያ ከቅምጥል ህይወት በቀር ሌላ የማያውቁ ሴቶች ተቸገሩ፡፡ ‹‹ሳንዙ››ም ግራ ተጋባ። ሆድ የሚያንቀጠቅጠው ከበሮ ቢደለቅ ቢነረትም ሴቶቹ ‹‹ሳንዙ›› የሚያሳያቸውን አካላዊ እንቅስቃሴ ተከትለው መንቀሳቀሱን ትተው ማሽካካት ያዙ፡፡ አስቸገሩ፡፡
‹‹ሳንዙ››ከሚጠቅሳቸው መርሆዎች፤ ‹‹ትዕዛዝን ግልጽ ባለማድረግ የሚፈጸም ስህተት የጄነራል፤ ትዕዛዙ ግልጽ ሆኖ ሳለ የሚፈጸም ጥፋት የሠራዊት ነው›› የሚለው አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ሳንዙ›› ለጭን ገረዶቹ የሰጣቸው ትዕዛዝ ግልጽ መሆኑን አረጋግጦ፤ የጀመረው ሥራ ቧልት ወይም ጨዋታ አለመሆኑን ለማስረዳት ጥረት ቢያደርግም ሴቶቹ እየቧለቱና እየተሸኮረመሙ አስቸገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የጭን ገረዶቹ ‹‹ጠርናፊ›› የሆኑት ሴቶች፤ ከሰልፉ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲወጡ አዘዘ፡፡ እርሱም ከሁለቱ ሴቶች መሐል ገብቶ፤ ሰልፍ አሳምሮ ከቆመ በኋላ ሰይፉን ከሰገባው መዝዞ ግራ ቀኝ በመሰንዘር፣ የሴቶቹን አንገት እየቀላ ከሰልፈኞቹ ፊት ጣለው፡፡ ያሳዝናል። ግን ከዚያች ቅጽበት ወዲያ ሴቶቹ ወታደር ሆኑ፡፡ እናም የሚሰጣቸውን ተልዕኮ እና ግዳጅ ለመፈጸም የሚያስችል ብቃት አገኙ፡፡
ይህ ታሪክ የተጠቀሰው ምሣሌ ሆኖ እንዲያገለግል ነው፡፡ እናም በምሣሌው፤ ‹‹ሳንዙ›› ህዝብ ነው፡፡ የሳንዙ ትዕዛዝ፤ የህዝብ ትዕዛት ነው፡፡ የሳንዙ ቁጣ፤ የህዝብ ቁጣ ነው፡፡ የህዝብ ቁጣ በሩቅ የሚያስፈራ የተባ ሰይፍ ነው፡፡ ‹‹ግርማው›› ብቻ ያስፈራል፡፡ ባለፈው እና በያዝነው ዓመት መጀመሪያ በሐገራችን ያየነው ‹‹ፖለቲካዊ ጠሮ›› (Political Hurricane)፤ አስፈሪ የህዝብ ቁጣ ከሰይፍ የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ ቁጣ በገዢው ፓርቲ አመራሮች ዘንድ የሚታዩትን ችግሮች ለማስተካከል አስገዳጅ ሁኔታ የፈጠረ ነበር፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ፈጽሞ ቸል ሊባል የማይችል ህዝባዊ ግፊት ፈጠረ፡፡ ፓርቲው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ አደረገ፡፡ ታዛዡ አዛዥ የሆነበት ሁኔታ እንዲቀየር አደረገ፡፡
እንዲህ መሆኑ ለበጎ ነው፡፡ አሁን የተፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከገዢው ፓርቲ መልካም ፈቃድ የመነጨ ከሚሆን፤ እንዳሁኑ በህዝብ ግፊት የተቀሰቀሰ መሆኑ ለዴሞክራሲ ስርዓቱ መጠናከር አወንታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡ ይህ ሂደት እንደኛ ላለ የዴሞክራሲ ስርዓት ጀማሪ ለሆነ ህዝብ የሚሰጠው ትልቅ ትምህርት አለ፡፡ በርግጥ የመንግስት ባህርይ፣ አሰራር እና አደረጃጀት በህዝብ ፈቃድ የሚወሰን መሆኑን ለማየት ቻልን፡፡ ህዝቡ የተሰጠውን ነገር እየተቀበለ የሚኖር ግዑዝ ፍጡር ሳይሆን፤ በነጻ ምርጫው ሥልጣን የሰጣቸው መሪዎቹ እርሱ የሚፈልገውን ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው እንዲያውቁ አደረገ፡፡ መሪዎች የህዝብን ፈቃድ ለመፈጸም የማያቅማሙ አመራሮች እንዲሆኑ አደረገ፡፡ ይህ ሂደት ለዴሞክራሲ ስርዓታችን እሴት የሚጨምር ይመስለኛል፡፡
ህዝቡ በመሪዎች ችሮታ በተሰጠው በጎ ነገር የሚጠቀም እና በመሪዎቹ ንፍገት የሚበደል ህዝብ ሳይሆን፤ የሚገባውን ነገር ማንም በችሮታ መልክ ሊሰጠው ወይም በንፉግነት ሊከለክለው የማይችል ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን በግልጽ አረጋገጠ። ይህ ለሐገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት እሴት የሚጨምር ክንውን ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ህዝቡ መብቱን ለማስከበር የሚያደርገው ጥረት በህግ የተባረከ፤ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች የታነጸ እንዲሆን ማድረግ የሚበጀው መሆኑን ለመረዳት ልዩ ዕድል የፈጠረለትም ይመስለኛል፡፡ ከህግ የወጣ ነገር ለህገ ወጦች ፍላጎት ሲሳይ ሊያደርገው፤ መብቱንና ነጻነቱን ለመሸርሽር የሚያመች ሁኔታን ሊጎትትበት እንደሚችል ለመገንዘብ የሚያስችል ተግባራዊ ትምህርት መቅሰም አስችሎታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ወደ ሁለተኛው ሐሳብ አልፋለሁ፡፡
የተዘነጋ ጉዳይ
ፖለቲካዊ ምህዳሩን በአስፈሪ አውሎ ነፋስ ሲያተራምሰው የነበረው ‹‹ሃሪኬን››፤ አልፎ ምድረ-ፖለቲካው ደብ ያለ ይመስላል፡፡ በርግጥ የገጠመን ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡ አንድን ሐገር እንደ ሐገር የሚያቆሙ ህብረተሰባዊ መዋቅሮቻችን ሁሉ በአስደንጋጭ ሁኔታ ተርገድግደው ነበር፡፡ በበኩሌ፤ ሐገሬ በዚህ መጠን ስትቸገር በዓይን ያየሁበት ሌላ የታሪክ አጋጣሚ የለም ለማለት የሚያስደፍረኝ ነው፡፡ አስፈሪ የጎራ መደበላለቅ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የጎራ መደበላለቁ አሁን ጨርሶ ጠርቷል ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኃይል ሁሉም ባለበት እንዲረጋ ሆኗል፡፡
ታዲያ በተፈጠረው ሁከት ጥቃት የደረሰበት ዘመናትን ያስቆጠረው የህዝባችን የአብሮ መኖር ባህል ጭምር ነው፡፡ በዚህ ነባር የህዝቡ ባህል ላይ የደረሰው ጥቃት ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ እና ከባድ የሐዘን ስሜት አሳድሮ ያለፈ ነበር፡፡ በአብሮ መኖር የሰለጠነ አስተሳሰብ ወይም ባህላዊ ደመ-ነፍስ ያዳበረው ህዝባችን በከባድ ሁኔታ ተፈትኗል፡፡ ይህ የህዝባችን ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ፣ በስሜት እሣትና በሐኬተኛ ፖለቲከኞች ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በበኩሌ፤ ሐገር ሊሞት ሲል ምን ዓይነት የበሽታ ምልክቶች እንደሚታይበት ለመረዳት አስችሎኛል፡፡ የመረጃ ዘመን ቴክኖሎጂ በረከትና መርገም በውል ታይቶኛል፡፡ የመረጃ ዘመን ቴክኖሎጂ ለሐገር ሽረት የሚጠቅመውን ያህል፤ የሐገርን ሞት ለመጎተት ወይም ለማፋጠን ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል አሳይቶኛል፡፡
በረጅም ዘመን ሂደት የተገመደውና ለብዙዎች እንደ ትንግርት የሚታየው የህዝባችን ጥብቅ ማህበራዊ ትስስርና የአብሮ-ተከባብሮ መኖር ባህል፤ ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደተጋረጡበት ለመረዳት የሚያግዝ ክስተት አድርገን ለማየት እንችላለን፡፡ ከሦስት ወይም ከአራት ዓመታት በፊት በመዲናችን በተካሄደ አንድ ጉባዔ ተሳታፊና ንግግር አቅራቢ የሆኑ አንድ የውጭ ሐገር ሰው (ምናልባት ሙስሊም - አረባዊ) በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ድንቅ የአብሮ መኖር እና የመቻቻል ባህል አጽንታችሁ ቆያታችኋል፡፡ ዛሬ ይህን አኩሪ ቅርሳችሁን ይዛችሁ መቀጠል መቻል - አለመቻላችሁ ከሚፈተንበት ዘመን ደርሳችኋል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሐይማኖት ልዩነት ችግር ሳይፈጥርባችሁ በአንድነት ለመኖር መቻላችሁ ያስደንቃል፡፡ ይህም በብዙ ቦታ ሊገኝ የማይችል ልዩ ቅርሳችሁ ነው፡፡ ሆኖም 21ኛው ክፍለ ዘመን ያመጣውን ፈተና ተቋቁሞ ለማለፍና ዓለም የሚደነቅበትን አኩሪ የአብሮ መኖር እሴት በመጠበቅ መጓዝ መቻላችሁ የሚታየው በወደፊቱ አካሄዳችሁ ይሆናል›› (ቀጥተኛ ጥቅስ አይደለም) በማለት ተናግረው ነበር፡፡ እኚህ ሰው በሐይማኖትና በማንነት ሰበብ የሚፈጠሩ ግጭቶች ከመንገድ እንዳያወጡንና ነባር ቅርሳችንን እንደ እሣት መድምደው እንዳያጠፉት በማያንቀላፋ ትኩረት መጠበቅ እንዳለብን አስታውሰውናል፡፡
ከዚህ አንጻር ባለፈው እና በያዝነው ዓመት መግቢያ አካባቢ በታየው ‹‹ፖለቲካዊ ሃሪኬን›› ሳቢያ የተፈጠሩ የመጠራጠር ስሜቶችን ማከም ያስፈልገናል፡፡ ይህን የመቃቃርና የመጎዳት ስሜት በጥናት ላይ ተመስርተን፤ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ባረጋገጠ አግባብ ቁስሉ እንዲሽር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ችግሩን ከሚገባው በላይ አጋንኜ ለማየት አልፈልግም፡፡ የህዝብን አብሮ የመኖር ባህል የሚጎዱት ችግሮች የተፈጠሩት በጥቂቶች መሆኑን አምናለሁ፡፡ ድርጊቱ የህዝብን ስሜት አያንጸባርቅም፡፡ ለዚህም ነው ችግሩ ድንገት ቦግ ብሎ ወዲያው ሊከስም የቻለው፡፡ ይሁንና ችግሩ በጊዜው በብዙዎች ዘንድ የመጠራጠር፣ የድንጋጤ፣ ግራ የመጋባትና የጭንቀት ስሜት መፍጠር የቻለ፤ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ (ለሥራ ሆነ ለትምህርት) ለመሄድ የማመንታት ሐሳብ ያሳደረ ችግር ሆኖ አልፏል፡፡
በመሆኑም፤ አሁን የችግሩ ፖለቲካዊ አደጋ የታገሰ መሆኑ ቢታይም፤ፈጥሮት የነበረው ስሜት መልሶ ቢረጋጋም፤ በቀላል ችግር ሊያገረሽ የሚችል ህመም የመሆን ዕድል ያለው ይመስለኛል፡፡ ‹‹እባብ ያየ በልጥ በረየ›› እንዲሉ፤ ወደፊት ልጥ በታየ ቁጥር የመበርገግ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል በመገመት፤ የችግሩ ሰንኮፍ ከሥሩ ተነቅሎ እንዲወድቅ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የችግሩን ትክክለኛ ምንጭና የድርጊቱ ዋና ተዋናዮች በደንብ ተለይተው፤ ወደፊት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠር ዝግጁ ሆኖ ለመገኘት የሚያግዝ የህሊና ልምድ ለመቀመር ያስፈልጋል። የተፈጠረው የሥነ ልቦና ቁስል እንዲሽር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ችግሩን በፖለቲካዊ ግምገማ ብቻ ተወስኖ መፍትሔ በመስጠት ሊቃለል የሚችል አይደለም፡፡
በሁከቱ የተቃጠሉ የግለሰብ ቤትና ንብረቶችን እንዲሁም መንግስታዊ ተቋማትን በህብረተሰቡ ተሳትፎ መልሶ ለመገንባት ጥረት እንደሚደረግ ሁሉ፤ የታቃጠሉ የአብሮ መኖር ስሜታዊ እና መንፈሳዊ ጓዞችም በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ መልሰው ሊገነቡ ይገባል፡፡ እንዲያውም የተቋማት መልሶ ግንባታው መነሻ መደረግ ያለበት የመንፈሳዊና ስሜታዊ ንብረቶችን መልሶ በመገንባት ሊሆን ይገባል፡፡  የቀውሱ ሙሉ አንድምታዎች መታየት፤ የአፈጣጠር ሂደቱ መመርመር፤ ችግሮቹን እነማን ለጥፋት ዓላማ ተጠቀሙባቸው የሚለውን በውል መንቀስ፤ የተከተላቸው ጎዳናዎች ሁሉ መለየት፤ በአጠቃላይ የችግሩ መጋቢ የቀውስ ወንዞችና ተፋሰሳቸው ጭምር በዝርዝር መጠናት ይኖርበታል፡፡ ችግሩን በደምሳሳው ማስቀመጥ ሳይሆን በዝርዝር ጥናት አብጠርጥሮ ማወቅ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በዚህ መንገድ ችግሩን ከተረዳነው፤ ወደፊት ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥሙን፤ ምን በምን አግባብ መከላከል እንደምንችል አውቀን፤ ሳንደነባበር ፈጣን ምላሽ መስጠት እንችላለን፡፡ ምናልባትም፤ ችግሩ እንዳይፈጠር ማድረግ እንችላለን፡፡ ከተፈጠሩም እግር አውጥተው ለመራመድ ከሚችሉበት ደረጃ ሳይደርሱ በእንጭጩ ለመቅጨት እንችላለን። ‹‹ሠይጣን›› የሚያድረው በዝርዝሮች ውስጥ ነው። ስለዚህ ሠይጣኑን ለማባረር ዝርዝሩ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
በተረፈ፤ በኢህአዴግ ወይም በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም በህግ ምሁራን የማይጠቀስ አንድ ህገ መንግስታዊ አንቀጽ በመጥቀስ ማጠቃለል እፈልጋለሁ። የህገ መንግስቱ አንቀጽ 88፣ ንዑስ አንቀጽ 2 እንዲህ ይላል፤‹‹መንግስት የብሔሮችን፣ የብሔረሰቦችን፣ የህዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ መርህ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነት፣ አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት፡፡›› መንግስት ይህን ግዴታውን በደንብ መወጣት አለበት። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም አፈፃጸም፤ ከአዋጁ ስንወጣ ንጹህ ሆኖ ለመውጣት የሚያግዝ መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በታላቅ ጥንቃቄ መሥራት ይገባል፡፡



Read 1411 times