Saturday, 18 June 2016 12:53

የወግ ዕቃው ድብ አንበሳ

Written by  ደገፍ ግደይ
Rate this item
(0 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
ሰፈር
ድንኳኖች ተተከሉ፡ ዘላቂ መሰል ሰፈር ተደራጀ። ሠራተኛ ከተተ፡- ባለሙያ ኃምሳ፡ ሥራ ቤቶች፡ ዕንጨት  ለቃሚና ውኃ ቀጂው በጥቅል መቶ ሴትና ኃምሳ ወንድ፡ ንጉሡ የተወላቸው ጠባቂ ኃምሳ የታጠቀ ወታደር  ነበሩ። ግንዲላዉን ካንድ ትልቅ ዲማ ጥላ ሥር ኣኖሩት፤ ጊዜና ጉልበት ፈጂው ሥራ፡ ግንዲላዉን ተጠንቅቆ ጠርቦና ቀጥቅጦ ነጋሪት ማበጀት፡ ተወጠነ። የንፉቅቅ ነው፤ እልኽ ያስጨርሳል፤ ቢኾንም፡ ሠራተኛ ሳያሠልስ ተጋተረው። ከኹለት ዓመት ተመንፈቅ በላይ ፈልፍለው የግንዲላውን ልብ  አወጡት፤ በስተውስጡ በደንብ የተላገ ልሙጥና የወጥ ዕንጨት ገላው ውፍረቱ ኹለት ጣት፡ የአፉ ጐን ስምንት ጫማ፡ የድፍኑ ቂጥ አምስት፡ ቁመቱ ደሞ ዓሥራ ኣራት ጫማ ውስጠ ክፍት ግንድ (የወጥ ዕንጨት ቀፎ) ኾኖ ተሰናዳ። ቀጥሎም ፊትና ዃላው በቆዳ ይለጐማል።
ዓዳኝ ተሰማራ!
የላምና የበሬ ቆዳ ምን ቢሰፋ፡ ምን ቢወጠር የነጋሪቱን አፍ እንዳይሸፍን ከጥዋቱ ተገንዝበውታል።  ስለዚኽም፤ ንጉሡ ኣለ የሚባለዉን የዝሆን ኮርማ ገድለው ቆዳዉን፡ ጭን ዓጥንቱን፡ የፊትና ዃላ ቅልጥሙን እናም ጥርሱን ያመጡለት ዘንድ  ስመ ጥር ዓዳኞቹን አሰማራ። ቆዳው ከንቱ እንዳይቀር ዓስበው እንዲጨምቱም ዓደራ ተባሉ፤ ዓናቱን መፈጥረቅ፡ ጦሩን ከታች ከኾድ ወደ ላይ መሰንቀር ነው።  ቆዳው ተበላሽቶ ለጉዳዩ ስለማይውል፡ ከጐን ወይም ከጫንቃው  ልቡ ላይ ማነጣጠር ኣይኾንም።  ዓዳኝ ዅላ እንሰሳዉን በጐኑ ወግቶ ሥሥ አከላቱን (ሳንባዉን ወይም ልቡን) ይሻልና፡ ልማዱ ላኹኑ ሙያ ስለማይበጅ ማስጠንቀቂያ አከል ዓደራው ጠበቀ። እንግዲኽ፡ ዓደኑ የተፈጸመው ጥንት ባሩድ ባገሩ ሳይታወቅ ነው፤ በዘመነ ጦርና ጐራዴ፡ በፋስና ካራው ዘመን። ያኔ ዝሆኑን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ዓይኑን የሚሸነቍር ወይም ዓናቱን የሚፈጠርቅ ጀግና ዓዳኝ ማስፈለጉ ግድ ነበር።
ዕከማ ዕፅ
ዓዳኝ ከጫካው  እንዳለ የነጋሪቱ ዋናው ሥራ- የስኬት የክሽፈቱ ባይኾን ነው?- ተከናወነ ። ይኸውም ከተቆረጠ ሦስት ዓመት የሞላው ያኹኑ ውስጠ ክፍት ግንድ፣ ድፍን ስድስት ወር መዓዛቸው በተለያዩ የጪስ ዕንጨቶች ታጠነ፤ ሙላዉን ሞቀ። በዚኽ መንገድ የቀረው የግንዱ ወረዘትና ልምላሜ ፈጽሞ ይደርቅና ድንቅ የኾነ ዕድሜ ቀጥል ባሕሪ ይላበሳል። እየታጠነ ሳለም በያይነቱ ሙጫ፣ ዘይት፣ ማጠንከሪያ ፈሳሽ በኾዱም በጀርባዉም እየመላለሱ ያጠጡት ነበር። ከኒኹ ፈሳሾች ኣንዱ የሬት፣ የልባንጃ፣ የቍልቋል ደም ድብልቅ ነው። ታምሶ የተወቀጠ የጎመን ዘር፣ ተልባና ኑግ ደጋግመው  እየነሰነሱና የጋለውን ዓዲስ ምጣድ እያሹ ውልውል ብሎ እስኪያብረቀርቅ ድረስ እንደሟሟሸት ነገር። ይኸኔ ነው ጥንቃቄ፣ ሙያ፣ ልብ ብሎ መከታተል የሚያስፈልገው፤ የዕንጨቱን ባሕሪ፣ ልቡን ማግኘትም ማወቅም። ቅባት አንሶት እያለ በጥድፊያም ኾነ ከልክ በላይ ቢታጠን ግንዱ ቶሎ ይደርቅና ወዲያው  ይሠነጠቃል። ያ ዅሉ ልፋት… ከንቱ! ቅባቱ እንደተለደፈበት ጪስ ሳይጠግብ፣ የሚገባውን እሳት ሳያገኝ ከቀረም፣ ርጥበቱ ስለማይወጣለት፣ ቆይቶ ቆይቶ መጐሸም ሲጀምር ይነቃል። እንግድያስ፣ ይቺ ሳት ነበረች የኹለቱ ከያንያን ሙያና ጥበብ የፈተነችው። ይችን ፈተና  ከተወጧት፡ እፎይ ማለት ይቻላል፤ ነጋሪቱ ተበጅቶ ያለቀ ያኽል ነው። ከንግዲኽ እስከ ፍጻሜው ኣልጋ ባልጋ ባይኾንም፣ የቀረው ሥራ ቀለል ያለ፣ እማያደናግር፣ ተረጋግቶ ማዝገም ነው።
ዓዶ ወሸባ!
ዓዳኞቹ ከሰነበቱበት በረኻ የተሻው ግዳይ ይዘው ገቡ፡-ኻያ ሰው የወሳንሳ የተሸከመው አንዳች የሚያኽል ቆዳ፡ አራት አራት ሰው የተሸከማቸው ጠርብ የሚያካክሉ የዝሆን ጥርሶች፣ ኹለት ግዙፍ የጭን ዓጥንቶች፣ ስምንት አነስ ያሉ የፊትና ዃላ ቅልጥሞች። ዓዳኞቹ ቆዳዉን ሲገፉ እክል እንዳይገጥም ከመሥጋታቸው የተነሣ በሦስት ቀን ጨረስን አሉ።  ከሌላ ግዳይ የተነቀሉ ኹለት ኹለት ሰው የሚሸከማቸው ኹለት ጥርሶችም ተጨመሩ። ጥቂት ዓዳኞች በግብግቡ አንዱ እግሩን፣ ሌላው እጁን የተሰበሩ ኹለት ቁስለኞችን ተሸክመው ነበር።
አራቱ ደሞ የስመ ጥሩው ዓዳኝ የነጋን ሬሳ በቃሬዛ ተሸክሟል። ዛፍ ተከለሎ  ፍንክች ሳይል ጠበቀና፡ ዝኆኑ ቀረብ ሲልለት፣ አነጣጥሮ የወረወረው ጦር  በዝሆኑ ቀኝ ዓይን ገብቶ በግራው ወጣ አሉ። ነጋ ግን አፍታም አልቆየ፤ የግዳዩ ዝሆን ግዙፍ እግር ደፍጥጦ ገደለው። ከኹለቱ የዘመቻው ፊት አውራሪዎች አንዱ ነጋ ነበር። ጠቅላላው የነጋሪት ሥራው ጥረት እንዲኽ ሞትን ያኽል ጉዳት ገጥሞታል፤ ብቸኛው ተጐጂም  ነጋ ነበር። ለሥራው ሕይወቱን ሠዋ።
እንደ-- መላ--
ተንግዲኽ ተራው የደበናንሣ ነው፤ ከመለጐሙ በፊት ቆዳዉን ፍቆ፣ አልፍቶ ማዘጋጀት። ቆዳው፣ ከግዳዩ እንደተገፈፈ  ጨው ላመል ነሳንሰው ጠቅልለዉት ኖሮ፣ ከፀሓይ ሲዘረጋ ጥንቡ አላስቀምጥ ኣለ፤ ዙሪያ ገባዉን ተናኘ። ቁርበቱን ለማዘጋጀት ስድስት ወር ፈጀ። ቆዳዉን ወጥረው ከቸከሉት በዃላ የነጭልፊት ሲሳይ እንዳይኾን፣ ቆሞ መጠበቅም ነበረባቸው፤ አሊያማ፡ የሲላ መንቈር አንዴ  ጠቅ ኣርጎ ሥራዉን ብን፡ እነሱን ብናኝ ዘጋኝ አርጓቸው ቁጭ ነው።  የበሬ ሽንት፣ ሞራና በያይነቱ ሥብ፣ ጨውም በገባበት ብጥብጥ ቆዳው ይታጀላል፤ እስኪደርቅም ብዙ ሳምንት ፀሓይ ላይ ይሰጣል። ከዛም ሽታው ለቆ፣ በትክክል ለሰልሶ ነጋሪት ሠሪዎቹ ጠቢባን የልባቸው እስኪደርስ በያይነቱ ቅባትም፡ ዓዞ ከልም (ኰምጣጤም) በተደባለቀበት ፈሳሽ ይዘፈዘፋል። የኩምቢውና የእግሩ ቈዳም ተተልትሎ፡ ተወጥሮ፡ ታጅሎ፡ ደርቆ፡ ለፍቶ ጠፍር ይበጃል፤ ነጋሪቱ  ሲለጐም ቆዳዉን  ደኅና አርገው እየወጠሩ ገላው በዚኹ ይጠፈራል።
ቆዳው ነጋሪቱን ሲያለብስ ኣንዳችም ጋ እንዳይጨማደድ ደክመውበታል። ሥራዉን ለማጠናቀቅ ድምፁን መሞከር፣ ንዝረቱን፣ ማስተጋባቱን መፈተሽ ነው። ጥሩ ነጋሪት መንዘር፣ ማስተጋባት ኣለበት። የገላው(የንጨት ቀፎው) ውፍረት፣ የቆዳው አሰነዳድ፣ ሲዘረጋም የውጥረቱ ልከኛነት ማለፊያ ኹነው ሲያበቁ ነው መልካም ድምፅ የሚያስተጋባው።  በሙከራው ጊዜ አንዳንድ መነካካት ኣልቀረም፤ የድምፁ ጥራትና ዓይነት ነጋሪት ሠሪዉን እስኪያረካው ተብሎ  ገላዉን(የንጨት ቀፎዉን)  እስከ መላግም ተደርሷል።
መካያው ግን የነጋሪት ሠሪው ስሜት ኣይደለም፤ የነጋሪት መቺዎቹ ቃል፣ በተለይም የኣለቃው ያባ ነጋሪት እንጂ።  ሠሪው  ሺ ጊዜ ነጋሪቱን ይውደድ፣ ጐሻሚው ካልፈቀደው ምን ሊረባ? እናም ዋናው መቺ፤ ‘መርምረው፣ ኣናግረውና ይኾን እንደኹ ኣስታውቀን፡’ ተባለ።
ምርጡ ነጋሪት ኣምስቱን የብቃት ድምፆች ይዞ መገኘት ይኖርበታል። እንደ ገደል ካላስተጋባ፣ እንደ ጉማሬ ካለጉረመረመ፡ እንደ ጅብ ካላሽካካ፣ እንዳንበሳ ካላገሣ፣ አብሶ ኣስግምግሞም ድንገትም ልብ እሚሠነጥቀውን የደመናትን ነጐድጓድ ገንዘብ ካላረገ ነጋሪት ተብዬ ነው። እነዚኽ ኣምስት የድምፅ መለዮዎች ካልኖሩት፣ ነጋሪት መባሉን ይባላል፡ ምርጥ ግን አይደለም፤ ብርቅ ድንቅ አያሰኝም፤  ለታላቁ ንጉሥ ኣይበቃም።
የነጋሪቱ ሠሪዎችና ዋና መቺው አባ ነጋሪት አንድ ኹለት ሳምንት ዓብረው ተቀመጡ፤ ድምፁን ሲመረምሩ፣ ቆዳዉን ሲወጥሩና ሲያረግቡ፤ ዓለፍ ዓለፍ ብለውም ከጐኑ የመረጡዋቸው ቦታዎችን ፋቁ፤ በሆጻ ዓጠቡ። ይኽ ዅሉ ሲደረግ፣ ነጋሪት መቺው ነጋሪቱን ደጋግሞ እንደመታ፡ እንዳዳመጠ፣ የሚፈልጋቸውን በያይነቱ ድምፆች ሊያሰማ እንደጣረ ነበር። የነጋሪት መቺዎቹ ኣለቃ የልቡ ሲሞላለት ራሱን ይነቀንቅና ነገሩ ዕልባት ያገኛል።
ሥዕል
ሠዓሊዎች፤ እስካኹን ከእጃቸው ያልገባውን ነጋሪት፣ ደሞ በተራቸው ተረከቡት፤ ፍጻሜዉን ሊያስውቡት ነው።  የሠዓሊ ጌታው  ሰባት ራሱን  መልከ መልካምና መንፈስ ቃኝ ሥዕሎች በነጋሪቱ ላይ ሣለ። ቀለም እሚበጠብጡ፣ መቃ ብርዕ ቀርጸው፣ ጫፈ ጭራው መሣያ ዕንጨት ዓጥበው እሚያቀርቡ ዓሥራ ኣምስት ረዳቶች ነበሯቸው። ኹለቱ ድንቅ ሠዓሊዎች የነጋሪቱ ኣፍ ላይ ተጠበቡ፡-  የዕድሜ ጸጋ ምሳሌዉን ዲማ ተጠልሎ ንጉሥ በዙፋኑ፣ ከሥሩም ዜጎቹ ያገባላቸው ግብር ላይ ተኰልኩለው ፀሓይ ስትወጣ። ሰላምና ብልጽግናን የሚያውጅ ግሩም ትዕይንት።
በመቀመጫው ገጽ ኹለት ሌሎች ሠዓሊዎች ውግያን ሣሉ፡- ድል የተቀዳጀው ንጉሥ በዓውደ ውግያው እንዳለ፣ ድል ኣድራጊው ሰራዊት በንጉሡ ፊት እየፎከረ ግዳይ ሲጥልና ምርኮዉን ሲያስቆጥር፣ ምርኮኛውን ሲነዳ። ዙሪያዉን ደሞ ተጨማሪ ኹለት ሠዓሊዎች ዕውቅ  ምሳሌዎችና ጥለቶች በተሞላ ሥዕል አንቈጠቈጡት፡- በገነት ጽጌያትና ኣትክልት መኻል ቄሱ፣ ገበሬው፣ ነጋዴው፣ ባለጁ፣ በዘለለት ኑሮና ተግባሩ ተሰማርቶ።  ነጋሪቱስ ርግጥም ተሠራ፡፡ ጕዳዩሳ ተቋጨ? በጭራሽ! ሠረገላ እንጂ ያስፈልጋል ለራሱም ለመቺዎቹም።   
ቅልጥም
ሥዕሉ ሲሣል ጐን ለጐን ደሞ ባለሙያዎቹ የጭን ዓጥንቶቹንና ቅልጥሞቹን ተያያዙዋቸው። ዓጥንቱን ቦርብረው፣ መቅኑን (ቅባቱን) ሙልጭ ኣርገው ኣፈሰሱት፤ ከዛም ልዩ ጨውና ዓመድ ሞሉትና በሠም ዓተሙት።  ይኸኔ ግዙፉ ዓጥንት ነጋሪት መምቻ ዱላ ኾነ። እጀታው ጐመድ(ቍርበት) ተሰካለት፤ መለልታው  በማለፊያ ንቅሳት አማረ፤ ዓንጣጩ  ሥርጉድና ስንብር ኣርጎ ለመቺ ኣመቻቸው። ዓሥራ ኹለት ያጥንት ዱላዎች፣ ድንቅ የጅ ጥበብ በረከቶች ኾኑ። አምስት መቺ ዓሥሩን ዱላ ሲመቱበት፡ ኹለት ለምናልባቱ ይቀመጣል።
ሠረገላ
መምጫው ወደ መጨረሻ ቢኾንም፤ የማይቀረው ተግባር በጊዜው ጊዜ ደረሰ፡- ነጋሪቱን የሚያጓጉዝ ባላራት መንኰራኵር ሠረገላ ተሠራ። ስፋቱ ባራቱ የጋሪው ጥግ ኣንዳንድ ሰው ሳይጣበብ ቆሞ የሚያጫውት ነበር። ሰያፍ መወጣጫ አስጠጉና  ነጋሪቱን ተጨንቀው፣ ተጠበው ከጋሪው ላይ ኣወጡት። ነጋሪቱ የጥንት አካሉ ቀፎ ኹኖ፣ በጣም ቀሎ ቢገኝም ኣኹንም ይካበዳል፤ አራት ፈረስና ኣንድ ኻያ ሰው ነው ጐትቶ የጫነው። ወጥቶ ሲያበቃ፣ እንዳይነቃነቅ ባራቱ ጥግ ሥር ወሸሉበት፣ እንዳይንከባለልም በጠፍሩ ከጋሪው ጋራ አሰሩት። ደሞም ደጋን ጥርሶቹን ጫፍ ለጫፍ  አጋጥመው  (አኩስሞች ፅንብል እንዲሉ) ጌጠኛ የክብር ዓጀብ፣ ተድባብም፣ ዓምደ ወርቅም ኣስመሰሏቸው። በዚኽ ጊዜ ሥራው  ተከናውኖ ነጋሪቱ ለምረቃ  መብቃቱና  ማጓጓዝም እንደሚቻል ተነገረ፤ የንጉሡን መላክተኛ የምሥራቹን ኣስይዘው ወደ ግርማዊ ላኩት። እንግዲኽ አኩስም የንጉሡ መዲና፣ በሰዉ ሃሳብ ትንጓለል ገባች፤ የመልስ ጉዞ ዝግጅት ተጀመረ።
ድንኳን ሊነቀል፣ ጎጆ ሊፈርስ ነው። ነገር ግን፣ ሰፈሩን ከቦ መንደር ተቆርቁሯል፤ አንዳንዱም መጤ እዚኽ ሊቀመጥ ቆረጠ።  

Read 1880 times