Saturday, 04 June 2016 12:17

“በአገሬ ላይ ቅር ተሰኝቻለሁ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

ትውልድና እድገታቸው ባሌ አዳባ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በትውልድ ቀያቸው ተከታትለዋል፡፡ ከ9-10ኛ ክፍል ለመማር በ17
ዓመታቸው ወደ ጐባ ከተማ አቀኑና ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ይናገራሉ - የዛሬዋ እንግዳችን ወ/ሮ መድሃኒት መኩሪያ፡፡ የአዲስ
አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እንዴት ከአደባ ወደ አዲስ አበባ ከዚያም ወደ ውጭ አገር እንደሄዱና ከ13 ዓመት በፊት ስለከፈቱትና በግፍ ተቀማሁ ስላሉት ት/ቤት
እንዲሁም በአጠቃላይ ህይወታቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

    ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ እንዴትና ለምን ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ቻሉ?
12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቅኩ ዩኒቨርስቲ የመግባት ፍላጐትና ዓላማ ነበረኝ፡፡ ሆኖም ውጤቱ ለዩኒቨርስቲ የሚያበቃ ስላልነበረ የተለያዩ አጫጭር የሙያ ኮርሶችን ለመውሰድ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ኮርሶችን ከወሰድኩ በኋላ ከኢትዮጵያ ወጣሁ፡፡
በምን ምክንያት ነበር ከኢትዮጵያ የወጡት? ወዴትስ ነበር የሄዱት?
ወደ ውጭ የሄድኩት የስዊዘርላንድ ዜጋ አግብቼ ነው፤ በጋብቻ ማለቴ ነው፡፡ መጀመሪያ የሄድኩትም የባለቤቴ አገር ስዊዘርላንድ ነው፡፡ የሚሰራው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ስለሆነ እንደነ ዛምቢያ፣ ኬኒያና በሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች ኖረናል፡፡ ብዙ ዓመታትን በተለያዩ አገራት እየተዘዋወርን ስንሰራ ከቆየን በኋላ፣ በ1994 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጣን፡፡
ከመጣችሁ ወደ 14 ዓመት ሊሆናችሁ ነው፡፡ ምን እየሰራችሁ ነበር የቆያችሁት?
ባለቤቴ ያው በሙያው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡ እኔ ደግሞ በተወለድኩበት ቀዬ ያሉ ህፃናትን መርዳት እፈልግ ስለነበር፣ የህፃናት ት/ቤት ከፍቼ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ አዳባ ወስጥ በአንድ ጊዜ ሶስት ቦታ ከፍቼአለሁ፡፡ ከት/ቤት በተጨማሪ ዝዋይ ውስጥ “Rainbow Generation” የተባለ ሴቶችን የማብቃት ስራ የሚሰራ የስልጠና ድርጅት ከፍቼ፣ ሴቶችን ኢምፓወር ማድረግ ጀመርኩኝ፡፡ ሬይንቦው ሁለት ስራዎች አሉት፤ አንዱ እንደነገርኩሽ ሴቶችን አሰልጥኖ ስራ ማስቀጠር ሲሆን ሁለተኛው ህፃናትን ማስተማር ነው፡፡ ሴቶች የሆስፒታሊቲ ስልጠና ይወስዱና ይቀጠራሉ፡፡ ይሄ ውጤታማ ስራ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡
እስቲ ስለ ህጻናት ት/ቤቶቹ አጀማመር ይንገሩኝ?
ት/ቤቶቹን ልክፍት የቻልኩት በአካባቢው ወላጆች ጥያቄ ነው፡፡ የትውልድ አካባቢዬ እንደመሆኑ ወደ ቦታው ስሄድ የአማርኛ ት/ቤት ባለመኖሩ፣ “ልጆቻችንን አማርኛ ለማስተማር ሩቅ ቦታ እየላክን ተንገላቱብን፤የተለያየ ችግር እያጋጠማቸው በመሆኑ እባክሽ እዚሁ ቀያቸው ላይ ት/ቤት ክፈችልን” ብለው ወላጆች ተደጋጋሚ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እነሱ አማርኛ ት/ቤት ክፈቺ ነው ያሉኝ፡፡
 እኔ ደግሞ ት/ቤት መክፈት ካለብኝ ለአማርኛ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ት/ቤት ነው መክፈት ያለብኝ በሚል፣ ከከተማው አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥቼ ከኬጂ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ከፈትኩኝ፡፡
ኦሮምኛ ኬጂ፣ ኦሮምኛ ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል፣ አማርኛ ኬጂ እና ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ቀጠልኩኝ፡፡ መጀመሪያ በወር 15 ብር ነበር የምናስከፍለው፡፡ ሶስት ልጅ ያለው ሰው ከሆነ፣ አንዱን በነፃ እናስተምር ነበር፡፡ በኋላ ሁኔታቸውን ሳይ ያንን 15 ብር ለመክፈልም ሲቸገሩ አስተዋልኩ፡፡ ያን ጊዜ በነፃ ማስተማር ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ ደግሞ እስከ 8ኛ ክፍል እንዳስተምር ተፈቀደልኝ፡፡ ከ42 በላይ መምህራን ነበሩኝ፡፡
 የት/ቤቶቹን ወጪ እንዴት ነው የምትሸፍኑት?
ከራሳችን ባለቤቴ ሰርቶ ከሚያገኘው ነው፡፡ ለመምህራን ደሞዝና በአጠቃላይ ለት/ቤቱ ወጪ ምንም አይነት ድጋፍ ከማንም አናገኝም፡፡ ይህንን ሶስት አራት ጊዜ ተጠይቀን መልሰናል፡፡ ባለስልጣናቱም ይህንን በደንብ ያውቃሉ፡፡ በየወሩ ለመምህራን ደሞዝና ለተለያየ ወጪ ከ30ሺህ ብር በላይ ይወጣል፡፡ መምህራኑ በተደጋጋሚ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ የወላጅ ኮሚቴዎች ተሰባስበው ወላጆች በአንድ ልጅ 35 ብር እንዲከፍሉ ተደረገ፡፡ እንደገና ጥያቄው ተነሳ፡፡ እኔም ጨመርኩ፤ ወላጆች እንደገና በልጅ 15 ብር ጨመሩ፡፡ በዚህ ትንሽ እንደተጓዝን፣ ወላጆች አቃታቸውና ጭማሪው እኔ ላይ ወደቀ፡፡ መቼስ የህሊና እርካታ ፈልገሽ፣ ገንዘብም ወድደሽ አይሆም፡፡ እናም ሁሉንም ጥያቄ ተቀብዬ ቀጠልኩኝ፡፡ እንደገና የደሞዝ ጭማሪው ተጠየቀና፣ ወላጆች ያንን 50 ብር መክፈል ጀመሩ፡፡ እንዲህ እያልን ነው ለ13 ዓመታት በጥሩ ሁኔታ የቀጠልነው፡፡
ከወራት በፊት በእርስዎና በከተማው ባለስልጣናት መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረና ት/ቤቱን እንደተነጠቁ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ ይንገሩኝ?
ከአዳባ ስምንት ኪሎ .ሜትር ርቀት ሄረሮ ከተማ ላይ ነበር አንዱ ት/ቤት፡፡ እሱን ዘጋሁት፡፡ አንዱ ደግሞ ስቴት ፋርም ላይ ነበር፤እስከ ቅርብ ጊዜ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ያው የአዳባውን ሲቀሙን አብሮ ለመንግስት ተመለሰ ማለት ነው፡፡
 በምን ምክንያት ነው ት/ቤቶቹን የተቀሙት?
የአካባቢው ባለስልጣናት የተለያየ ምክንያት ያቀርባሉ፤አንዱም አሳማኝ አይደለም እንጂ፡፡ ባለፈው ነሐሴ ለዚህ ዓመት ትምህርት ልናዘጋጀው ስንሞክር ባለስልጣናቱ ለካ ለሌላ ግለሰብ ሰጥተውት ነበር፡፡ እኔ በተዋረድ ችግሩ እንዲፈታና ስራዬን እንድቀጥል ብጠይቅም የሚሰማኝ ሳጣ፣ እዚህ አዲስ አበባ መጣሁና ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አመለከትኩኝ፡፡ ተወካዮች ወደ ቦታው ተላኩ፡፡ ያው ቦታው የመንግስት ነው፤ግን እኛ ከስድስት በላይ የመማሪያ ክፍሎችን ሰርተን አስፋፍተነው ነበር፡፡ እቅዴ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ለማስቀጠል ነበር፡፡
መሬትም ጠይቀን አልሰጡንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ተወካዮቹ ጉዳዩን ካጠኑ በኋላ ለሌላ ግለሰብ መሰጠቱን ሲያውቁ ከግለሰብ ተወስዶ ለግለሰብ አይሰጥም፤ ከተመለሰ ለመንግስት ነው መሆን ያለበት፤ ለአንቺ ምን እናድርግልሽ አሉኝ፡፡ አይ እኔ ከዚህ በኋላ መቀጠል አልፈልግም፤ወገኖቼን ልርዳ፤ ለተወለድኩበት አካባቢ የአቅሜን ላድርግ ባልኩኝ እንዴት እንዲህ እሆናለሁ አልኩና ከፋኝ፤በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ አንዳንድ የምፈልጋቸው ቁሳቁሶች ት/ቤቱ ውስጥ ይቀሩኛል፡፡ እነሱን ለመውሰድ ተነጋግረን አልሰጡኝም፤አመለክታለሁ፡፡
ት/ቤቱ በመወሰዱ በእርስዎም ሆነ በተማሪዎች ላይ ደረሰ የሚሉት ጉዳት አለ?
በጣም እንጂ! ከስር ጀምሬ ለፍቼ ያሳደግኳቸውን ተማሪዎች መጨረሻ፣ የልፋቴን ፍሬ ሳላይ መወሰዱ በጣም አሳዝኖኛል፡፡ ሁለተኛ መምህራን ስራ አልባ ሆነዋል፡፡ ከጥበቃዎቹና ከሁለት መምህራን በስተቀር ቀሪዎቹን 40 መምህራን አልተቀበሏቸውም፡፡ የአገልግሎት ልከፍል ብሞክር እንኳን ዶክሜንታቸውን ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ ሶስተኛ ተማሪዎቹን ጥሩ አድርገን ይዘናቸው ነበር‹፡፡ በትምህርት ጥራት፣ ከዩኒፎርማቸው፣ከትምህርት አቀባበላቸው ጀምሮ ምርጥ ምርጥ ልጆች አድርገናቸው ነበር፡፡ በአካባቢው ከሚገኙ ት/ቤቶች ምርጡ የእኛ ስለመሆኑ ራሳቸው የከተማው ባለስልጣናትም መስከረዋል፡፡
ት/ቤቱ ሲከፈት የጀመሩ በርካታ ተማሪዎች፣አሁን ዩኒቨርስቲ ገብተው እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ መርጋ፣ ሌላ ቦታ እንሰጥሽና ስሪ፤ በርቺ ብለውኝ ነበር፡፡ እኔ ግን አንዴ ሞራሌ ስለተነካ በቃኝ ብያለሁ፡፡ ሬንቦ ጀነሬሽን ት/ቤት ከአሁን በኋላ አይቀጥልም፡፡ ከ850 በላይ ተማሪዎቼን ትቼ ነው የመጣሁት፡፡ ከሁለት ወር በፊት ቢሆን ኖሮ ያናገረሽኝ፣ እንዲህ ተረጋግቼ እንባ ከአይኔ ጠፍቶ አላናግርሽም ነበር፡፡ ሌት ከቀን ነበር የማለቅሰው፡፡ የሚገርምሽ ከኪሴ እያወጣሁ የባለስልጣናቱን ልጆች ሁሉ ነበር በነፃ የማስተምረው፡፡ ልጆቻቸው ያደጉበትን፣ ጥሩ እውቀት የሚያገኙበትን ት/ቤት ለመዝጋት ከጨከኑ፣ እኔ ምን ቀረኝ ብዬ ለመቀጠል እከራከራለሁ፡፡ ባለቤቴ ይህን ግፍ ሲመለከት የሚኖረው አመለካከትና የሚሰማው ስሜት ምን ሊሆን ይችላል? የአገር ገጽታ ግንባታስ የሚጀምረው ከየት ነው?
በት/ቤቱ መወሰድ የወላጆች ስሜት እንዴት ነበር?
እሱን በቃል ለመግለጽ እቸገራለሁ፤ሰልፍ ሁሉ ወጥተው ጮኸው ነበር፡፡ ት/ቤቱ አይወሰድብን፤ይህቺ ሴት ናት ልጆቻችንን ከመንገላታት ሩቅ ሄደው ከመማር ያዳነችልን፣ ት/ቤቱም ተማሪዎቹም በአካባቢው ካሉት በጥራትም በውጤትም የተለየና የበለጠ ነው ብለው ቢጠይቁም ሰሚ አላገኙም፡፡
የርክክብ ስነ - ስርዓቱ ምን ይመስል ነበር?
ዜሮ ደረጃ ነበር - የርክክብ ስነ-ስርዓቱ፡፡
 እንኳን 13 ዓመት አንድ ቀን እንኳን ድጋፍ ያደረገ ሰው በእንደዚህ ዓይነት መልኩ ይሸኛል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምንም አይነት ክብር አልነበራቸውም፤ ለእኔ፡፡ በእርግጥ እኔ ስሰራ የነበረውና ገንዘብ ያወጣሁት፣ከእነሱ ምስጋና ለመሰብሰብ ወይም ስምና ዝና ፈልጌ አይደለም፡፡
 ለተወለድኩበት አካባቢ የበኩሌን ጠጠር በመጣል፣ የህሊና እርካታና እረፍት ለማግኘት ነው፡፡ ቢሆንም ሰው ነኝና፤እኔን የሸኙበት መንገድ ደስ አይልም፡፡ አገር አለኝ፣ ወገን አለኝ ተብሎ እንዳይታሰብ የሚያደርግ ነው፡፡ እንኳን ለእኔ ለባለቤቴም ከባድ ነው፡፡ ወገቡ እየጐበጠ እየሰራ ባገኘው ገንዘብ ነው ስንረዳ የነበረው፡፡ ምላሹ ይሄ ሲሆን ያሳዝናል፤በጣም ያሳፍራል፡፡
አሁን አዲስ አበባ ምን እየሰሩ ነው?
ቅድም እንደነገርኩሽ “ሬንቦው ቻሪቲ ኦርጋናይዜሽን” ነው ድርጅታችን፡፡ ሬንቦው ት/ቤትም በዚህ ድርጅት ስር ነበር፡፡ ዝዋይ ለሴቶች ስልጠና የምንሰጥበትና ሴቶችን የምናበቃበት ድርጅት አለ፤እሱን እየሰራሁ ነው፤ግን ሳልዘጋው አልቀርም፡፡
ለምን?
በምን ሞራል ልስራ? ሰው ካለችው ትንሽ ነገር ላይ ለወገኑ ማካፈል፣ መልካም ስራ ሰርቶ ህሊናውን ማስደሰት አይችልም፡፡ እንዴ? እንዴት አይነት ነገር ነው? ከኪሴ ብር ባወጣሁና በረዳሁ ት/ቤት ከተቀማሁ፣ ነገስ ምን እንደሚገጥመኝ ምን አውቃለሁና ነው የምቀጥለው፡፡ እኛ እድሜያችን እየገፋ ነው፤ማረፍ መጦሪያችንን መያዝ ሳያምረኝ በለፋሁ፣የእውነቴን ነው የምልሽ አገሬ ላይ ቅር ተሰኝቼአለሁ፡፡ ደግሞ ትምህርት ተተኪ ዜጋ የሚታነፅበት ነው፤ንግድ አይደለም የከተማው መንግስት ይሄንን እድል መጠቀም አልፈለገም፤ዞሮ ዞሮ የተጐዱት ህፃናትና ወላጆቻቸው ናቸው፡፡
ት/ቤቱ ውስጥ ቀሪ ንብረት አለኝ ብለውኝ ነበር፡፡ ለመሆኑ ምንድን ናቸው የቀሩት?  
አስራ አራት ኮምፒዩተር አለን፡፡ ት/ቤቱ ሁሉንም ኮምፒዩተሮች እየተጠቀመባቸው አይደለም፡፡ ስራ ላይ አይደሉም፡፡ ት/ቤት ስንረካከብ እወስዳለሁ ካልኳቸው እቃዎች አንደኛው ኮምፒዩተሮቹ ናቸው፡፡ ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እኮ የአዳባ ከተማን ባለልጣናት ከስሰሽ ካሳ ተቀበይ ብለውኝ ነበር፡፡ እኔ ንብረቴን ይስጡኝ፤ካሳ ከእግዚአብሔር ነው ብዬ ነው የተውኩት፡፡ ሁሉን ያደረግሁት ለህብረተሰቡና ለህፃናት ነው፡፡ ከፊፋ ያመጡልን በርካታ ኦሪጂናል የፊፋ ኳሶች ነበሩን፤ ተሰረቀ አሉ፡፡ እሺ ቀሪውን ኳስና ኮምፒዩተሩን ስጡኝ ብያለሁ፤ይህንን ከተቀበልኩኝ ይበቃል፡፡  
የራስዎ ልጆች አሉዎት?
አራት ልጆች አሉኝ፡፡ የመጨረሻዋ ዩኒቨርስቲ እየተማረች ነው፡፡ ሁለቱ ማስተርሳቸውን እየሰሩ ነው ያሉት፡፡ እዚህ አምስት ስድስት ልጆች ሰብስቤ እያሳደግኩኝ ነው፡፡ እኔም ቲዎሎጂ ተምሬ ዲግሪዬን ይዣለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ እየኖርን ነው፡፡      






Read 6677 times