Saturday, 14 May 2016 12:29

ሰው የውበት እንስሳ ነው

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

“-- በነገራችን ላይ፤ ሰውን ከእንስሳት የሚለየው ማሰብ መቻሉ አይመስለኝም፡፡ ይልቅስ፤
ሰውን ከእንስሳ የሚለየው መሳቅ መቻሉ ነው፡፡--”

ማቲው አርኖልድ መሰለኝ፡፡ ‹‹አግዚአብሔር ዓለሙን ሰርቶ ሲጨርስ፤ ከሰራበት መሣሪያ አንድ ረስቶ ሄደ፡፡ ያም መሣሪያ ሜታፈር (ተለዋጭ ዘይቤ) ነው፡፡ ይህ መሣሪያ ከሰው እጅ ገባ፡፡ ከገጣሚው እጅ ገባ፡፡ ሰውም ከያኒ ‹‹ፈጣሪ›› ሆነ››  ይላል፡፡ ከያኒው፤ የህሊና ሽቱ፣ የጥበብ መዳፍ፣ የውበት ዋሽንት ነው፡፡ የከያኒው ጥረት፤ ከአፈር የተሸሸገን ወርቅ እንደ ማውጣት ነው፡፡
ወርቁን አውጥቶ የስሜትና የእውነት ጌጥ ሰርቶ ነፍሳችንን ያስጌጣታል፡፡ እርሱ ሲመጣ፤ በጥበብ አበባና ቅጠል ላይ እንደ ንብ ያስደንሰናል። በውበት የማለዳ ጤዛ ፊታችንን እንታጠባለን፡፡ ከብርሃን ድር የተሰራ የደስታ ሸማ እንደርባለን፡፡ እንደ ሽመላ እንዘምራለን፡፡ እንፍነከነካለን፡፡
በተራ የሰርክ ህይወት ነፋስ የረገፈውን የስሜት ቅጠል ያለመልመዋል፡፡ በወንዝ ዳር የተተከለች የወይራ ዛፍ አድርጎ ያለመልመናል፡፡ ለአፍታም ቢሆን በተራ ህይወት ላይ ያነግሰናል፡፡ የህይወትን አስደሳችነት ይጨምርልናል፡፡ አፍኖ ከሚይዝ የዘወትር ሃሳባችን በማላቀቅ፣ ለቅፅበት ታህል ነፋሻ አየር ለመሳብ ብቅ የምንልበት ልዩ መስኮት ይሰጠናል፡፡ እንደ ፈርዖን ሰራዊት ያለ እረፍት ከሚያሳድድ የኑሮ ጣጣ ለአፍታ ያሳርፈናል። በኑሮ በርሃ ጣመን የመታንን በጎቹን፤ እንደ ሙሴ ባህርን ሰንጥቆ ውሃ አፍልቆ ያጠጣናል። ለሰከንድ ዕድሜም ቢሆን ህይወትን ያጣፍጥልናል፡፡ ከዚህ የላቀ ምን ጥበብ አለ፡፡ እኛ ተራ ሟች ፍጡራን ከዚህ የበለጠ ምን እንሻለን፡፡
በኑሮ በረሃ የደከሙ የህይወት መንገደኞችን ያሳርፋል፡፡ ለተወሰነች ሰዓት ልጅ ያደርገናል። ዓለቱን በበትር መትቶ፤ የውበት ውሃ አፍልቆ ያጠጣናል፡፡ ለአፍታ ‹‹ከወዛደርነት›› ያወጣናል። ተስፋና መሻታችንን በአስተኔ ይሞላልናል፡፡ ይህ መሻት ኃይል ነው፡፡ እየሳበ ከኑባሬ ያደርሰናል። ከህይወት አበባ ቀስሞ፤ ምናቡን የማር ቀፎ አድርጎ፤ የውበት ማር ይቆርጣል፡፡ ከያኒው የውበት መነኩሴ ነው፡፡ ዓይኑም የንስር ነው፡፡
አሁን ፈጣን ማህበረሰባዊ ለውጥ ውስጥ ነን። በሁለንተናችን ፈጣን ለውጥ ላይ ነን። ለውጡ በህፃናቱ ዜማ፣ በወጣቶቹ ቀልድ፣ በአዛውንቱ ተረት፣ በሰዓሊው ሸራ ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ የማህበረሰባችን የአሁንና የወደፊት መልክ በኪነ ጥበብ ሞራ ላይ ታትሟል፡፡ ማን ሊያነብ ይችላል?
ከያኒው ንቁ ነው፡፡ ማህበረሰባችንን በዓይን - በሰበከቱ ቃኝቶ ይተረጉምልናል፡፡ ‹‹ሳለ - አይሰጥ›› ሆኖ የተቀመጠውን እውነት እያወጣ ያጎርሰናል፡፡ እውነትን እንድንዘክር ያደርገናል፡፡ ዛሬን - ከመጪው አስተያይተን እንደ ማህበረሰብ መድረሻችንን እንድንወስንም ያግዘናል፡፡ የኪነ ጥበብ ስራዎቻችንን ገምግመን፤ የነገ አቅጣጫችንን ከሩቅ ማየት እንችላለን። በእውነት፤ ኪነ ጥበብ ማህደረ - ህብረተሰብ ነች። ሰውም ሥነ ውበታዊ እንስሳ ነው፡፡
እስኪ በዙሪያችሁ ያለውን ቁሳቁስ ተመልከቱ፡፡ ውበትና አገልግሎት እንደ ነፍስና ሥጋ ተጣምረው የፈጠሩት ዓለም ነው፡፡ ሰው ኢኮኖሚስቶች እንደሚያስቡት፣ ኢኮኖሚያዊ እንስሳ አይደለም፡፡ እንዲያውም ስነ ውበታዊ እንስሳ  ነው፡፡
በነገራችን ላይ፤ ሰውን ከእንስሳት የሚለየው ማሰብ መቻሉ አይመስለኝም። ይልቅስ፤ ሰውን ከእንስሳ የሚለየው መሳቅ መቻሉ ነው፡፡ እንስሳት በትንሹም ቢሆን ያስባሉ። ግን አይስቁም፡፡ ጨርሶ ምናባዊ አይደሉም፡፡ ውበትን ማደን የሚችለው፤ አርኖልድ ከፈጣሪ እጅ ስትወድቅ ያያትን መሣሪያ (ሜታፈርን) የያዘው ከያኒው ነው፡፡ ምናባዊነት፤ ሰውን ከዛሬው የስልጣኔ ዕድገት ደረጃ አድርሶታል፡፡ ስለዚህ ሰውን ሰው ያደረገው ሥነ ውበት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ብዙዎች በሚያስቡት መጠን፤ ሰው በትርፍና ኪሳራ ስሌት የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚያዊ ፍጡር አይደለም፡፡ ሰው እንዲያ ያለ ፍጡር ቢሆን ኖሮ፤ አዲስ ነገርን ለማየትና የሆድ ድንበርን ተሻግሮ ሄዶ፣ ውበትና እውነትን ለማደን መከራውን ባልበላ ነበር፡፡ የምድራችን ስልጣኔ የተገኘው ለአንዲት ስንኝ ቃል ነፍሱን ሊሸጥ ዝግጁ እንደሚሆን ገጣሚ፤ ትርፍን የማያሰላ ነፍስ በያዙ ሰዎች ሥራ ነው።
በምናብ ሳይጎለብቱ በአእምሮ ፈጣሪ መሆን አይቻልም፡፡ ሌሎች በምናብ የፈጠሩትን ነገር፤ ነጋዴው ሸቀጥ ያደርገዋል፡፡  ምናቡ ሞቶ በአእምሮ ክህነት የሚቀናጣ ሰው ግማሽ እንስሳ ነው፡፡ በአቶሚክ ፊዚክስ የተራቀቀው ምሁር ለአንዲት ውብ ስንኝ ልቡን ወለል አድርጎ መክፈት ከነሳነው ግማሽ እንስሳ ነው። ‹‹ግጥምን የማያውቅ እግዜርን አያውቅም›› ብሎ ነበር ያ ዳንቴ፡፡ እውነቱን ነው፡፡
እንደኔ አስተያየት፤ ሰውን ሰው ያሰኘው ውበት ነው፡፡ ኪነ ጥበብ ነው፡፡ ዙሪያችሁን ተመልከቱ፡፡ የሰው ልጅ ለግልጋሎት ከሰራው ነገር ይልቅ ለውበት የሰራው ይበልጣል፡፡ ለግልጋሎት ከሚያወጣው ወጪ፤ ለውበት የሚከፍለው ገንዘብ ይበልጣል፡፡ ይህን ስታዩ ሰው የውበት ባሪያ መሆኑን ታረጋግጣላችሁ፡፡
መኪና ውስጥ ስትገቡ የሚሸተው ‹‹ፍሬሽነር››፣ በኬክ ቤት በረንዳ የምታዩት ቁሳቁስ፤ በመስተዋት ተቀምጦ የምትመለከቱት  ጣፋጭ ኬክ ላይ ያሉት ቀለሞች፣ መጠቅለያው፣ የሴቶቹ ጌጣ ጌጥ፣ የወንዶች ሳሎን ሁሉ የሰውን ሥነ ውበታዊ እንስሳነት የሚመሰክሩ ናቸው። በተረት ተረት ተኮትኩተን አድገን፤ በሙሾ ምድሪቱን እስክንሰናበት ድረስ የውበትና የጥበብ ግዞተኞች ነን፡፡
ስለዚህ ስለ ኪነጥበብ መነጋገርና መወያየት ይኖርብናል፡፡ ወዳጄ እዝራ አብደላ ይህን እየሰራ ይመስለኛል፡፡



Read 4670 times