Saturday, 05 March 2016 11:01

የመቻቻል ጀግኖች

Written by  በተሾመ ብርሃኑ ከማል
Rate this item
(0 votes)

   የመቻቻል ጥያቄ ሲነሳ ሰዎች ራሳቸውን ትክክል በማድረግ፣ «እኛ ምን አጠፋን? ምንስ አደረግን? እነሱ ናቸው እንጅ!» ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ያለምንም ጥርጥር ሁሉም ለራሱ ትክክል ነው፡፡ ይህንን ሐቅ በተለያየ ምሳሌ እንመልከተው፡፡
ትክክልነት ከሃይማኖት አንጻር
በፀሐይ ለሚያመልክ ፀሐይን ማምለክ ለእሱ ትክክል ነው፡፡ አንድን አምላክ ሁለትም ሦስትም ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ የፍጥረት ዓይነት የራሱ የሆነ አምላክ እንዳለው የሚያምንም በራሱ አመለካከት ትክክል ነው። የሁሉም ነገር ፈጣሪ አንድና አንድ ብቻ ነው የሚልም በራሱ መንገድ ትክክል ነው፡፡ አንድና አንድ የሚባል ነገር የለም፤ አንድ ብቻ ነው የሚልም በራሱ መንገድ ትክክል ነው፡፡ ሁሉም በራሱ ግንዛቤ በራሱ ስሌት፣ በራሱ ማረጋገጫ፣ በራሱ ትንተና፣ በራሱ ምዘና፣ በራሱ አመለካከት፣ የራሱ የሆነ ትክክል አለው፡፡ ዋናውን ትክክል ማለትም የሁሉንም የሚያውቀው ራሱ ፈጣሪ ብቻ ነው። ስለዚህ ሁሉንም ለራሱ ለፈጣሪ ትተን በተለይም የእርሱ ልዩ ጠበቆች አለመሆናችንን አምነን፣ ወይም እርሱን በመተካት «ይህ ትክክል ነው፤ያ ግን ትክክል አይደለም» ከሚል እቡይ አመለካከት ተላቀን፣ በመቻቻል ስሜት ተሞልተን ሌላው የሚያምነውን፣ የሚያስበውን፣ የሚያመልከውን፣ ወዘተ ለመረዳት ጥረት ካላደረግን በስተቀር ምንጊዜም «እኛ ትክክል፣ እነርሱ ግን ስህተት ናቸው» ከማለት አንድንም፡፡ ለመረዳት ጥረት ስናደርግ ግን አንድ ባንሆንም የሚያመሳስሉን ነገሮች በርካታ መሆናቸውን እንገነዘባለን። በዚህም ለመቀራረብና ለመረዳዳት እንችላለን፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ጠላቶች አንሆንም፡፡
ጠባብነት
በእርግጥም አንድ ሰው ጠባብ የጎሳ፣ የብሔር ብሔረሰብ፣ የሕዝብ፣ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የቀለም ------ አመለካከት ሲኖረው በጠባብ ዓለሙ ውስጥ በብቸኝነት እንደሚኖር አያጠያይቅም። የዚህ ሰው ዓለምም እንደ አመለካከቱ ጠባብ ብቻ ሳይሆን ሰዎችም እንደ እርሱ በጠበበች ዓለም የሚኖሩ ይመስለዋል፡፡ በአንድነት ላይ የተመሠረተ ብዝኀነት በተቃራኒው የመተጋገስና የመቻቻል መሠረት ሲሆን፣ ብዝኀነትን ማስወገድ የማይችል መሆኑን ሲገነዘብ፣ ራሱንም ሌሎችንም መጥላት ይጀምራል፡፡ በተቃራኒውም በአካባቢው ከእሱ ጋር ተመሳስሎና ተቻችሎ የሚኖር መሆኑን ሲረዳ፣ ያኔ አዲስና አብሮ ለመኖር የሚያበቃ ሀቅ ይኖረዋል፡፡
«መቻቻል፣ መቻቻል፣ መቻቻል» ሲባል የምንከፍለው መስዋዕትነት የለም ማለት አይደለም። መስማት የማንፈልገውን ሐሳብ፣ አመለካከት፣ ትርጉም፣ ፍልስፍና፣ ከእምነታችን ፍጹም የሚቃረን ነገር እንሰማለን፡፡ ሰምተንም ችለን ዝም እንላለን ወይም እንተወዋለን፡፡ ይህ አንዱ መስዋዕትነት ነው፡፡ ማየት የማንፈልገውን እንቅስቃሴና ድርጊት እናያለን። ለምሳሌ አንድ ሙስሊም ወይም ክርስቲያን ሰዎች በአደባባይ ሲያጓሩ ቢያይ፣ ነገሩ ከአምልኮተ ሰይጣን ጋር የተያያዘ ከሆነ ከሃይማኖታቸው ጋር የሚቃረን ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን አይተን እንዳላየን እናልፈዋለን። ይህ ሁለተኛው መስዋእትነት ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚያጨፋጭፍ የጦርነት እሳት ተጭሮብን፣ ወገናችን ቆስሎብን፣ ንብረታችን ወድሞብን አቅም ቢኖረንም እንኳን የከፋ ችግር እንዳይከተል አስቀድመን በማሰብ ዝም እንላለን፡፡ ከተጎዳንም እርቅ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሦስተኛው ዓይነት መቻቻል ነው፡፡ ድንበራችን ተደፍሮብን፣ በድንበራችን መደፈር ምክንያት እኛም ተደፍረን «በሉ ወደ ድንበራችሁ ተመለሱ ብለን እንመክራለን» ይህም አራተኛው ዓይነት መቻቻል ነው። «በራሳችን ውኃ አትጠጡም፣ እኛ ካልፈቀድንላችሁ አትጠቀሙበትም፤» እየተባልን በሰላም አብረን ለመኖር ስንል እንለማመጣለን። ይህም አምስተኛው ዓይነት መቻቻል ነው፡፡
 የተለያዩ ሃይማኖት፣ እምነት፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ፣ ወዘተ ባለበት ኅብረተሰብ ውስጥ ለመቻቻል ሲባል የሚከፈል የመስዋዕትነት ዓይነቱ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ መከፈሉ ግን ዋጋ አለው፡፡ በመቻቻል ሰላም ይሰፍናል፡፡ አብሮ መኖር ይፈጠራል። የሰው ሕይወት፣ ንብረት፣ የሥራ ጊዜ፣ ወዘተ የበለጠ እንዳይጠፋ ያደርጋል፡፡ በእርግጥም «የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ ያውሬ መሄጃ ይሆናል እንጂ፤» የሚል መፈክር አንግበን በመጓዝ በሺሕ ዓመታት ለሚቆጠር ጊዜ ጦርነት በማካሄዳችን አለመጠቀማችንን ከተረዳን፣ «ያንተም ቤት ለምቶ የኛም እንዲለማ፣ እብሪቱን ትተን በል እንስማማ?» በሚል ተክተን በመቻቻል ለመሥራት ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል፡፡
ያለ ምንም ጥርጥር ይህችን አገር ወደተሻለ የታሪክ አድማስ ልናሸጋግራት የምንችለው መቻቻልን በመካከላችን ስናሰፍን ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ስለመቻቻል በዓለም የታወቁ የመቻቻል ጀግኖች (ሊቃውንት) ምን ብለዋል? ነገሩ በጣም ሰፊ ቢሆንም በጥቂቱ እንመልከተው፡፡
የመቻቻል ጀግኖች
በዚች ጦርነትና የእርስ በእርስ እልቂት በሞላባት ዓለማችን ውስጥ ስለ አብሮ መኖር የሚታገሉ ጀግኖችም አሉ፡፡ ሁሉንም ጀግኖች መዘርዘር ባንችልም ዓለም ያደነቃቸውን ብቻ ለአብነት እንቃኝ፡፡ ዓለም በግንባር ቀደምነት ከሚጠራቸው የመቻቻል ጀግኖች መካከል ደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ አንዱ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ ጁላይ 18 ቀን 1918 የተወለዱት ኔልሰን ማንዴላ፤ የመረረ ጥላቻን፣ የቀለምና የዘር ልዩነትን፣ ኢ-ፍትሐዊ አስተዳደርን ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
እኚህም ታላቅ ሰው ከድል በኋላ ሕዝብን የበደሉ ሰዎችን ሁሉ ይቅር በማለት በአገራቸው የተቻቻለ ኅብረተሰብ ይኖር ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ታግለዋል፡፡ እኚህ የኖቤል ሽልማት ባለቤት፤ «የሰው ልጅ ታላቅ ክብር ከመውደቁ ላይ ሳይሆን በወደቀ ቁጥር ለመነሳት ከመቻሉ ላይ ነው» በማለት ተቻችሎ ለመኖር ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት ቢኖርም ተስፋ ሳይቆርጡ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ያስታውሱናል። እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ አገራቸውን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ያወጡት ማሐንዳስ ካራማቻድ ጋንዲ (1869-1948) በሕይወታቸው ከፍተኛ ፈተና ያሳለፉ የመቻቻል ጀግና ሲሆኑ፣ እሳቸውም «የተለወጠች ዓለምን ለመመልከት የምትሻ ከሆነ ራስህ ተለወጥ» ይላሉ፡፡
 ሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች በአንዱ ወይም በሌላው መልኩ የሚለያዩ ቢሆኑም፣ በአንድነት በዚህ ዓለም ላይ ከሀቅ በስተቀር ሌላ እንደሌለ ያውጃሉ» ቻይናዊው የቡድሃ ሃይማኖት አባት ዳላይ ላማ 14ኛ (ላሞ ዞንደሩብ በ1935 ተወለዱ) በሕይወት ዘመናቸው ስለ ሰላም፣ ስለ መቻቻል፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አብሮ መኖር በሰበኩ ከፍተኛ  መንገላታት፣ ስቃይና ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ እኚህ የቡድሃ እምነት አባት፣ የግል ሕይወታቸው ከአንድ ለነፍሱ ካደረ መነኩሴ ሕይወት የተለየ ባይሆንም፣ ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲበለጽጉ ረድተዋል፡፡
«በሚቻለው ሁሉ ሩሁሩሆች ሁኑ፣ ያም ምንጊዜም ይቻላል፤» በሚል አባባላቸው የሚጠቀሱት እኚህ አባት፤ «ደስታ ተዘጋጅቶ የሚገኝ ሳይሆን ከራስህ ድርጊት የሚገኝ ነው፤» በማለት ሰዎች ተቻችለው ለመኖር ተግተው መሥራት እንዳለባቸው አበክረው ያስገነዝባሉ። በእኚህ ታላቅ ሰው አባባል መቻቻልን ተግባራዊ ስናደርግ ጠላታችን ብለን የፈረጅነው አስተማሪያችን ሆኖ ልናገኘው እንችላለን፡፡
ዕውቁ ሊባኖሳዊ ደራሲ ኸሊል ጂብራን (1883-1931) ብዙ መጻሕፍት በመጻፍ የታወቀና ለዓረብ ሥነ ጽሑፍ በዘመናዊ መንገድ መዳበር አስተዋጽኦ ያደረገ ነው፡፡ «አንተ ወንድሜ ነህ፤ እኔም እወድሃለሁ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቤተ መቅደስ ውስጥ ተንበርክከህ ስታመልክ አፈቅርሃለሁ፡፡ አንተም ወንድሜ በመስጊድ ውስጥ ፀሎት የምታደርሰው እንደዚያው፡፡ የገናናው ፈጣሪያችን የፍቅር ጣቶች የተዘረጉት ለሁሉም ስለሆነ፣ ለሁሉም ምሉዕነት መንፈስ እየሰጡ ስለሆነና ሁላችንንም ለመቀበል በጉጉት የሚጠብቅ ስለሆነ እኔና አንተ ሁላችንም የአንድ ሃይማኖት ልጆች ነን፤›› ማለቱ ይታወቃል፡፡
ማልኰም ኤክስ የተባለው አሜሪካዊም፤ «ከሰማይ በስተቀር ሌላ ምንም በሌለበት አንድ ሌሊት ሙዝደሊፋ (መካ ውስጥ የሚገኝና በሐጅ ሳምነት ጉዞ የሚደረግበት ሥፍራ) ከሙስሊም ወንድሞቼ ጋር ተኝቼ  ከእንቅልፌ ብንን አልኩ፡፡ በዚያ ጊዜም ከሁሉም አገሮች ሁሉም ዓይነት ቀለም፣ መደብ፣ ደረጃ፣ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውና ለማኞች ያለአንዳንች ልዩነት ሲያንኮራፉ አስተዋልኩ» ሲል መቻቻልን በማይረሳ መንገድ ገልጾታል፡፡
«ብዙ ጊዜ ቡድሒዝም ሃይማኖት ነው ወይስ ፍልስፍና? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ማንኛውንም ብትለው ምንም አይደል፡፡ ቡድሒዝም ምንም በለው ምን አንተ ያልከው ነው የሚሆነው፡፡ ሌላውን ትተን የቡድሃ አስተምህሮት ነው ብንለው ብዙም ፋይዳ ያለው ለውጥ አንፈጥርለትም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሐቅም ቢሆን የቡድሃ፣ የክርስቲያን፣ የሂንዱ፣ ወይም የሙስሊም ብለን ምልክት የምናበጅለት አይደለም። የማንም ሰው ሞኖፖሊ አይደለም፡፡ በራስ ዕይታ ብቻ መተርጎምም በሰው ልጆች አዕምሮ ውስጥ ጎጂ የሆነ ጠባብ አመለካከትን ሊያሰፍንና ነፃ ሆነን ሀቅን እንዳንረዳ መሰናክል ሊሆንብን ይችላል፡፡» ያለው ደግሞ ዋልፖላ ራሑላ የተባለ ታላቅ ሰው ነው፡፡
 ህንዳዊው ንጉሠ ነገሥት አሾካም፤ «ማንም ቢሆን የራሱን ሃይማኖት አክብሮ የሌላውን ሃይማኖት ማኮሰስ የለበትም፡፡ ነገር ግን ለአንዱ ወይም ለሌላው ምክንያት የሌላውን ሃይማኖት ማክበር አለበት። ይህንን በማድረግ የራስን ሃይማኖት ለማሳደግና ሌላውን ሃይማኖት እንዲያገለግል ለማድረግ ይችላል። የራስን ክብር በመሻት ከዚህ ተፃራሪ በሆነ መንገድ መሥራት ማለት ሌላውን ሃይማኖት መጉዳት ማለት ነው፡፡
ባለው አቅም የራሱን ሃይማኖት የሚያከብርና ሌላውን ሃይማኖት የሚያሳንስ ሁሉ የራሱን ሃይማኖት ከፍ ያደረገ ቢመስለውም ሃይማኖቱን እጅግ በከፋ ሁኔታ መጉዳቱን መገንዘብ ይኖርበታል። ስለዚህ መስማማት፣ መግባባትና መቻቻል ጥሩ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ሌሎች የሚሉትን ለማዳመጥ ይብቃ፣ ለማዳመጥም ፈቃዱ ይሁን» በማለት ይገልጻል፡፡
የሰላም ፍላጎት
«ሰላምና ጦርነት»፣ «አና ከሪኒና»፣ «ሪዘረክሽን - ትንሳኤ» በሚሉና በሌሎችም  ሥራዎቹ የሚታወቀው ሩሲያዊው ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሰው ሌቭ ኒኮላየቪች ቶልስቶይ፤ «ሁሉም ሰው ለመለወጥ የሚፈልገው ሁሉንም ሰዎች ነው፤ አንድም ሰው ግን ራሱን ለመለወጥ ጥረት ሲያደርግ አይታይም፤» በማለት ለመቻቻል ከሁሉ አስቀድሞ ራስን መለወጥ እንደሚያስፈልግ በነዚህ እምቅ ቃላት ያስተምረናል፡፡
«ጊዜው ወላጆች ወጣት ልጆቻቸውን ተዋህዶ በመኖር ውበትና ጥንካሬ መኖሩን የሚያስተምሩበት ጊዜ ነው» በማለት የገለጸችው ደግሞ አሜሪካዊቷ ደራሲ፣ ተዋናይትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማያ ነጀሎ ናት። ሄንሪ ዳቪድ ሶሩ (1817- 1862) እጅግ ዝነኛ ከሆኑት ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በደራሲነትም ይታወቃል፡፡ «እኔ በፍጥነት የምጠይቀው መንግሥት እንዳይኖር ሳይሆን የተሻለ መንግሥት እንዲኖር ነው። ይህም መንግሥት የሚገዛ ሳይሆን የሚያስተዳድር እንዲሆን ነው» ሲል የተናገረው ሄንሪ ዳቪድ ሶሩ፤ «ከጠባብ አመለካከት፣ ከትምክህተኛነት፣ ካለመቻቻል፣ ከአድሎአዊነት ለመላቀቅ አሁንም ጊዜው አልረፈደም» በማለት የመቻቻልን አስፈላጊነት አስተምሯል፡፡
እንደ አርቆ አስተዋይና እንደ ብልህ ውድ የአሜሪካ ልጅ የሚቆጠሩት ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ (1917-1963) በበኩላቸው፤ «ልባችንና ዕውቀታችንን አስተባብረን ከልብ ብንሠራ፣ የዘረኛነትንና የአለመቻቻል አመለካከትን ለመቀየር ብንችል፣ በሕይወት ዘመናችን ያሉ ሕፃናት የኅብረ ብሔራትን ውበት ሊያደንቁ እንደሚችሉ በሀቅ አምናለሁ፡፡ ይህም ሳይሆን ቀርቶ ልዩነታችንን ልናቆም ካልቻልን ቢያንስ ዓለማችንን ለልዩነት ምቹ ልናደርጋት ይገባል» በማለት ለሰዎች ተቻችሎ መኖር ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
መውላና ጀላሉዲን ሩሚ የታወቁ ፐርሺያዊ ሱፊ ሲሆኑ የእሳቸውም ግጥሞች በመቻቻል ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ «ክርስቲያን፣ ይሁዲ፣ ሙስሊም፣ ዞሮአስተራዊ፣ ድንጋይ፣ ምድር፣ ተራራ፣ ወንዝ፣ ሁሉም የየራሳቸው ልዩ ምሥጢር ሲኖራቸው ትክክል ስለመሆናቸውም ሆነ አለመሆናቸው ማንም ሰው ዳኝነቱን ሊሰጥባቸው አይችልም፤» በሚል አባባላቸው ይታወቃሉ፡፡
ሌሎችም ያልተጠቀሱ በርካታ የመቻቻል ጀግኖች አሉ፡፡ በሀገራችንም ያሉትን የመቻቻል ጀግኖች ግጥማችውን፣ መጣጥፋቸውን፤ የምርምርና የፍልስፍና ሥራዎቻቸቸውን፣ ንግግራቸውን በማየት ጥቅሶቻቸውን ማውጣት ይቻላል፡፡ ለጊዜው ግን ይብቃን፡፡
ሁሉም ሰው ሰላም፣ መቻቻልና አብሮ መኖር ያስፈልገዋል
እናም፣ ለሁሉም ዕድሜና ለሁሉም ሕዝብ እንዲሁም ለእናት አገራችን ሰላም፣ መቻቻልና አብሮ መኖር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁሉም ሰዎች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ፣ ቀን ከሰዎች ጋር ሲገናኙና ሌሊት ለመተኛት ጋደም ሲሉ የሰላም ቀንና ሌት እንዲሆንላቸው ይመኛሉ፡፡ ሰላም የሰፈነበት ቀንና ሌሊት ከሁሉም ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ ነውና። በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖርና መቻቻል ዛሬም ወደ ፊትም አስፈላጊ ናቸው፡፡ በመሆናቸውም በየዘመኑ ይደገማሉ፡፡ ይደጋገማሉ፡፡ በእርግጥም የአገራችን ዕድገት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረው ሰላም ስለሰፈነ በመሆኑ ሁላችንም ለሰላም ብንታገልና ስለ ሰላም ብንዘምር አትራፊዎች እንደምንሆን ያረጋግጥልናል፡፡
ለብዙ ዓመታት በውስጣችን በነበረ ግጭት ምክንያት ለሥልጣኔ ያበቃን የሥራ ባህላችን፣ ማኅበራዊ እሴታችን፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን ቀስ በቀስ ተሸርሽሮ ለሥልጣኔአችን ባዕድ ሆነናል፡፡ ትናንት የፕሪስተር ጆንን ዕርዳታ ማለትም የገናናውን የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ዕርዳታ ለማግኘት የመጡ አገሮችና እስከ ዋና ከተማቸው ገብተን ያረጋጋናቸው፣ ዛሬ እነሱ ራሳቸው ከፈለጉት ጋር የንግድ ትስስር መሥርተው እኛን ከማን ጋር መነገድ እንዳለብንና እንደሌለብን የሚነግሩን በሌላ ምክያት ሳይሆን ድሆች በመሆናችን ነው፡፡
ፈረንጆቹን ትተን ዓረቦች ወንድሞቻችን እንኳን ፈጣሪ በሰጣቸው ፀጋ የትናንት ዕርዳታችንን፣ አለኝታነታችንን፣ ለችግራቸው ደራሾች መሆናችንን --- የሺሕ ዓመታት ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለው አይተው ስንራብ አልደረሱልንም፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ እስከ 1950ዎቹ መጀመሪያዎች ድረስ በዓረብያ ድርቅ ሲከሰት ለስደት የሚመጡት፣ የእህል ምርት የሚያፍሱት፣ ምጽዋት የሚቀበሉት ከዚች አገር እንደነበር የታወቀ ቢሆንም ይህ ዛሬ ተረስቷል። በመረሳቱም እኛ የሚታዘንልንና የምንናቅ እነሱ ደግሞ የደላቸውና የሚከበሩ ሆነዋል፡፡ ልጆቻችንንም፣ እህቶቻችንንም፣ ወንድሞቻችንንም የሚገዙ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሄ ሊያስቆጨን ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
በመጨረሻም የመቻቻል፣ የመፋቀር፣ አብሮ የመኖርና የአንድነት ምስጢራችንን በሐበሻነታችን ውስጥ መፈለግ እንችል እንደሆን አንድ ተጨማሪ ነገር ልበል፡፡ «ሐበሻ» የሚለው ቃል ጥቁር፣ ጠይም፣ ቀይ፣ የቀይ ዳማና በእነዚህ የቆዳ ቀለሞች ውስጥ የሚገኝ ኅብረ ቀለም ያለ ሕዝብን የሚወክል ሲሆን፣ ይህም በአፍሪካ ቀንድ ድብልቅና ዝንቅ ቀለም የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት አገር ከጥንት ጀምሮ «ሐበሻ» ተብሎ እንደሚጠራ የታወቀ ነው፡፡
ቃሉ ብዙ ጊዜ ሲነገር እንደሚሰማው ተደበላልቆና ተዛንቆ የሚኖር ሕዝብ ማለት ከሆነ ደግሞ ጥንታውያን ሰዎች «ሐበሻ» ያሉን የተለያየ ቀለም፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች መሆናችንን ሳይገነዘቡ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል በቀለሙ፣ በዘሩ፣ በጎሳው፣ በብሔሩ የሚኮራው የኢትዮጵያዊ የጥንቱ የሐበሻነት እርሾ ወይም ቅመሙ በውስጡ ስላለ ነው ወደሚል ግንዛቤ ሊወስደን ይችላል፡፡
ድብልቁና ዝንቁ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚገኝ ሲሆን የተለያየ ቋንቋ ቢናገርም ያው «ሐበሻ» ሆኖ ይገኛል፡፡ አራቱን ዋና ዋና ቋንቋዎችም (ኩሻዊ፣ ሴማዊ፣ ኦሟዊ  ናይሏዊ) ተደበላልቀውና ተዛንቀው የሚኖሩ ናቸው። በዚህ ዓይነት ተደበላልቆ የሚገኘውን ባህላችንንና ማኅበራዊ ሕይወታችንን እንዲሁም ሌላውን የሕይወት ፈርጃችንን ስንመለከተው በእርግጥም «ሐበሾች» ነን፡፡ ስለዚህ መስማማት፣ መግባባትና መቻቻልን  የህይወታችን  መርህ  አድርገን  እንቀበለው።

Read 1813 times