Saturday, 25 November 2023 20:17

“ሲበቃ በቃ ነው…”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… መቼም ያቺ “..ድሮ ቀረ” የሚሏት ነገር በሰበብ አስባብ ብቅ ማለቷ ባይቀርም …አለ አይደል… አንዳንዴ ‘ፍሬሽ’ ነገር አይጠፋም፡፡
 የምር’ኮ… አንዳንዴ የሆነ ነገር ትሰሙና…በቃ “ጆሮዬ ነው!” ትላላችሁ፡፡
አንዳንዴ ”ሲበቃ በቃ ነው“ እንዴት አንጀት ያርሳል መሰላችሁ፡፡ ግን ደግሞ ድፍረት ይጠይቃል፤ወኔ፡፡ በተለይማ ‘ራስ’ ላይ “ሲበቃ በቃ ነው” ማለት… አለ አይደል… “ሊታረቀን ይሆን እንዴ?” ያሰኛችኋል፡፡ አሀ… የምር’ኮ እንዲህ ሲባል ምን ትዝ ይላችኋል መሰላችሁ..”ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል…” የሚሉት ነገር፡፡
እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቃ ‘ቤስት ፍሬንድ’ ምናምን የሚባል ነገር ቀረ ማለት ነው? የምር … ከግብፅ አውሮፕላንና መድፍ ይልቅ… የሚያሰጋው ይሄ! በቅርብ የምናውቀው ወዳጃችን… ‘ሲያበላው ሲያጠጣው’ በነበረ የልብ ጓደኛው፣ ሀምሳ ምናምን ሺህ ብር ሲጭበረበር … ተስፋ ያላስቆረጠ ምን ያስቆርጥ!
አሀ… ጭራሽ እኮ አሁን አሁንማ ‘የልብ ጓደኝነት’ የሚባለው ቀረላችሁና… አለ አይደል… ‘ፍሬንድሺፕ’ የሆነ ኢንቬስትመንት ነገር ሆነላችሁ፡፡ ዘንድሮ… የጓደኝነት መስፈርት ‘ባህርይ’ ሳይሆን… የባንክ ደብተር ሆኖላችኋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ… ለስድሳ አምስት ሳንቲም አረቄም… ለስድስት ብር ‘ወርቅ ውሃም’ መፈነጋገል! ይህንን ነበር “ሲበቃ በቃ ነው!” ማለት፡፡
“እኔን ካንተ በፊት…” “ካንቺ ያስቀድመኝ…” ምናምን እንኳን በእውን ሊታይ ቀርቶ… በልብ ወለድም ቢፃፍ “አቤት ውሸት!” የሚያሰኝ እየሆነ ነው፡፡
ስሙኝማ.. እዚህ አገር እኮ… በቃ፣ አንዳንዱ ‘እንደልቡ’ እንዲሆን ‘ልዩ ፍቃድ’ የተሰጠው ይመስላችኋል፡፡ አንዳንዱ ባለሥልጣን የአዳራሽ ውስጥ የቦርድ ስብሰባም ይሁን… የዛፍ ስር የቤተ ዘመድ ጉባኤ… ለመፎከር ‘ፍቃድ የተሰጠው’ ይመስላል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት አንድ ወዳጄ… የሆነ ‘እንጎቻ ቦስ’ [ቂ…ቂ…] “ሁልሽም የመዋቅር ጊዜ ታገኛታለሽ…” ብሎ ሲፎክርባቸው ውሎ… ምን አለፋችሁ… እንደተንጨረጨረ ነው የዋለው፡፡
አሀ… ከፈለገ ‘የቀረው ይቀራል’ እንጂ ገና ለገና… ‘አብዮት ማስነሳት ቀርቷል’ ተብሎ መሰደብ አለብን! [አንተ ወዳጄ… እንዴት ነው፣ የማኦን ጥቅስ ‘ቀዩዋን መጽሐፍ ልስጥህ እንዴ!] እናላችሁ… በዚህ ለ’እነ እንትናም ባልሆነ ዘመን…ለምን ይፎከርብናል!
የምር ግን… እዚህ አገር ምን ግርም ይለኛል መሰላችሁ… ይሄ ‘ሹም ሽረት’ የሚሉት ነገር፡፡ ከሆነ ቦታ “እፎይ ተነሳልኝ…” ያላችሁት ‘ቦስ’ ዞሮ ሌላ ቦታ ‘ገጭ’! እና… በ‘ቀሺምነት’ ከአንድ ቦታ ተነስቶ… ሌላ ላይ ቁጭ… እንዴት ነው ነገሩ! ‘ሥልጣን’ አካባቢም “የሰፈር ልጅ ተደጋገፍ” ምናምን የሚባል ነገር አለ እንዴ! ሂሱን ጠጥቶ ጠጥቶ ከሆነ ቦታ የተነሳ ‘ቱባ…’ በአስራ አምስተኛው ቀን የሆነ አዳራሽ ውስጥ “አገራችን በተያያዘችው የግንባታ ጥረት…” ምናምን ሲል… በቃ፣ ተስፋ ነው የምትቆርጡት! ልጄ… እንኳን አዲስ ሊገነባ የተሰነጠቀውን መለሰኛ ሲሚንቶ የሚያቀርብ ጠፍቷል፡፡
እናላችሁ… ይልቅ “ሲበቃ በቃ ነው” ማለት እንዲህ ዓይነቱን ነው፡፡ “ከሌለህ፣ የለህም፣” እንደሚለው… እዛ ‘ላይም’ “ካልቻልክ አልቻልክም” መባል አለበት፡፡ አሀ…‘የላቦራቶሪ አይጥነት’ ሰለቸና! ‘አንገታችን የሚደርሰው’ ነገር በዛብን’ኮ!
እናላችሁ… መዓት ነገር “ሲበቃ በቃ ነው” የሚል እየጠፋ… ከአንገታችንም እያለፈብን ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ... ይሄ  የ‘መፈክር’ ነገር ልባችንን እንዳቆሰለው! የምር! በቃ በጨርቅ መፈክር ካልተደረደረ “የምናምን ቀን” ማክበር አይቻልም ማለት ነው!
ኮሚኩ ነገር ደግሞ ምን መሰላችሁ…‘እውነት’ የሚሆን መፈክር የለም፡፡ አሀ…ልክ ነዋ! ይኸው ዓለም የወዛደር አልሆነች… ኢምፔርያሊዝም አልወደመ… ተፈጥሮ በቁጥጥር ሥር አልዋለች! አሀ… ለጨርቁም ይታዘንለታ! እኛ ይኸው… የአሜሪካን ገበያ ሰብረን እንገባለን እያልን… ጨርቁን ሁሉ ‘ላንለብሰው’ ሰቅለን ጨረስነው!
 እናላችሁ…. ጨርቅና ቀለም የሚጨርስ የመፈክር ጋጋታ “ሲበቃ በቃ ነው፣” ካላልን… ነገርዬው ሁሉ…. አለ አይደል… “ሆድ ሲያውቅ፣ ዶሮ ማታ፣” ይሆናል፡፡ የምር መፈክርን “ሲበቃ በቃ ነው፣” የተባለ እለት… ብቻዬንም ቢሆን ‘የተለመደው ቦታ’ ሰልፍ እወጣለሁ - መፈክር ይዤ! ቂ…ቂ…
እንደውም… ሀሳብ አለን፡፡ በዘንድሮ የዚህ አገር ፖለቲካ ‘ማን ምን እንደሚፈልግ’ ግራ ስለገባን… ሁሉ ነገር ‘አንገታችን ላይ የደረሰ ዜጎችን’ የሚወክል “ሲበቃ በቃ ነው፣” የሚባል ፓርቲ ይቋቋምልን፡፡ [እኔ የምለው… መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ.. ‘ምልመላ’ ቀረ እንዴ! አሀ… አሁን ትንሽ “እፎይ” እንደማለት ብለናላ! አንድ ሰሞን’ኮ ቢራ እንኳን ስንጎነጭ… “ይሄን ቢራ’ኮ ውስኪ ማድረግ ይቻላል…” ዓይነት ‘ምልመላ፣’ መከራችንን አብልቶን ነበር፡፡ እና… ‘እንዲመዘገብልን’ የምንፈልገው… እኛ ‘ሲመለመል’ ደስ የሚለን ሰው ሳይሆን… የባህር ዛፍ ቅጠል ነው፡፡ ቂ….ቂ…!
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን ሳልነግራችሁ ብቀር ያቃዠኛል ብዬ ነው፡፡ የቮልስን ነገር ሰማችሁልኝ! ቮልስ ሆዬ የቸርችል ጎዳናን ዳገት “እኔስ ከእግረኛ ምን ተለየሁ፣” እያለች እያቃሰተች ትወጣለች፡፡ ሊሞዚን ሆዬ ደግሞ በሆዷ፤ “ጠቁሞ እዚህ አገር ያመጣኝ የእጁን አይጣ…” እያለች ቮልስን አልፋት ሽው ማለት፡፡ እናላችሁ… የ’አበሻ ልብ አውቃ’ የሆነችው ቮልስ ምን አለች መሰላችሁ… “ሊሞ፣ ተይ እንዲህ አያድርግሽ.. መልክ እኮ አላፊ ጠፊ ነው” አለችላችኋ! አሀ…’ከማን ዋለችና!
እናችሁ… ዘንድሮ መዓት ነገር የተበላሸው… አለ አይደል…”ሲበቃ በቃ ነው” የሚል እየጠፋ ነው፡፡ “ከእንግዲህማ እንዲህ መቀጠል አትችልም!” የሚል ነገር በተደጋጋሚ መስማት እየናፈቀን ነው፡፡ ነገርዬው ሁሉ፣ “አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ስድስት ወደ ኋላ…” የሆነው፣ መዓት ነገር ከዓመት ዓመት ያው ‘ውሃ ቢወቅጡት ቦጭ’ የሆነው… እንትና ያበላሸውን፣ እንትና ‘የሚያብሰው’.. “ሲበቃ በቃ ነው፣” የሚል ጠፍቶ ነው፡፡
‘ሲበቃ በቃ ነው’ ለጽሁፍም ይሰራል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1523 times