Saturday, 24 June 2023 20:30

የራያና አላማጣ ጉዳይ እያወዛገበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 የራያ አካባቢዎች በጀት ለትግራይ ክልል እንዲይተላለፍ የሚጠይቁ የ145ሺ ሰዎች ፊርማ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቧል
      - የሰሞኑ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ጉብኝት ፕሬዚዳንት ጌታቸው በፅኑ ተቃውመውታል
                
        በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባናል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ላይ አሁንም ውዝግቡ እንደቀጠለ ነው፡፡
የፌደራል መንግስቱ ለሚቀጥለው በጀት ዓመት ለራያና አካባቢዎቹ የሚመድበውን የበጀት ድጎማ ለትግራይ ክልል እንዳያስተላልፍ የሚጠይቁ 145 ሺ ሰዎች ፊርማ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
በወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አሰመላሽ ኮሚቴ አማካኝነት ለፌደሬደሽን ምክር ቤት የቀረበው ጥያቄ፤ የሰሜኑ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ስር የነበሩ አራት መዋቅሮችን የተመለከተ ነው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተጠሪነታቸው ለአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሆኑት ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ራያ ወፍላ እና ዛታ ወረዳዎች እንዲሁም የኮረም ከተማ አራቱ መዋቅሮች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ ጉዳዩ ከሚመከለተው ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን እንደሚመለከተውና ምላሽ እንደሚሰጥበት መግለፁ ተጠቁሟል፡፡በተያያዘ ዜና፤ የአሜሪካ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች በደቡብ ራያ አላማጣ ከተማ ውስጥ ያካሄዱት ጉብኝት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት በአቶ ጌታቸው ረዳና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ፓርቲ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡አቶ ጌታቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ “የአማራ ሃይሎች በህገወጥ መንገድ በሀይል የያዙትን አካባቢ ዲፕሎማቶቹ መጎብኘታቸው፣ የትግራይ ግዛቶች በፅንፈኛ ሃይሎች የሃይል ቁጥጥር ስር መሆናቸውን እንደመቀበል ይቆጠራል” ብለዋል፡፡ “ዲፕሎማቶቹ የአካባቢዎቹ ህገወጥ አስተዳደር ባለስልጣናት ባቀነባበሩት ድራማ ላይ ለምን እንደተሳተፉ ግልጽ አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ድርጊቱ አሜሪካ ለፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ያላትን ቁርጠኝነት የሚፃረርና ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ፓርቲ በበኩሉ፤ የዘር ማጽዳት ተግባር በፈፀሙና አካባቢውን  በጉልበት  በተቆጣጠሩ ሃያሎች ግብዣ በአካባቢው የሚደረግ ማንኛውም ይፋዊ ጉብኝት ተቀባይነት የሌለው አደገኛ ተግባር ነው ብሏል፡፡

Read 2518 times