Saturday, 16 July 2016 12:09

ዜድቲኢ የዘረጋውን የኤሌክትሪክ መስመር ፕሮጀክት አስረክበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     ዜድቲኢ ኢትዮጵያ በመላው አገሪቱ የዘረጋውን የኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር (OPGW) ፕሮጀክት አጠናቅቆ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ በሸራተን አዲስ በተደረገ ስነስርዓት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስረከበ፡፡ በ37 ሚሊዮን ዶላር በመላ አገሪቱ የዘረጋው ይሄው ኦፕቲካል ግራውንድ ፓወር በ17 ተኩል ወራት የተጠናቀቀ ሲሆን 1260 ካ.ሜትር መሸፈኑም በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተዘጋጀው በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ከዜድቲኢ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ሊ ጉዋንግ ዮንግ በተረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ዜድቲኢ ስራውን ከተረከበበት ሰዓት አንስቶ በትጋት በመስራት በታቀደው ሰዓት ማስረከባቸውን ተቁመው ፕሮጀክቱን ያለምንም ችግር ማጠናቀቃቸው ስራውን የበለጠ ስኬታማ አድርጎታል ብለዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ሊ ጉዋንግ ዮንግ በበኩላቸው ዜድቲኢ ባለፉት 16 ዓመታት የኢትዮጵያ የመንግስት አጋር ሆኖ በትልልቅ የቴሌኮም ፕሮጀክቶች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን ገልፀው ይህ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የአገሪቱን የሀይል አቅርቦት አስተማማኝነት እንደሚያሳድገው ተናግረዋል፡፡በዕለቱ የፕሮጀክቱ ስራተኞችና አስተባባሪዎች ባቀረቡት አጭር ዘጋቢ ፊልሞና ፎቶ ኤሌክትሪክ ሳይቋረጥ 132 ኪሎ ቮልትና 230 ኪሎ ቮልት ሀይል እያለፈበት መስመሩን እንዴት እንደዘረጉና ወንዝና ሌሎች መልክአምድሮች ላይ የኤሌክትሪክ መስመሮች ሲበጠሡ ለመቀጠል የገጠማቸውን ፈተና የገለፁ ሲሆን ያም ሆኖ የሰው ህይወት ሳይጠፋና አደጋ ሳያጋጥም መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
የኬብል መስመር ዝርጋታው ከኤሌክትሪክ ሀይል በተጨማሪ ለኔትወርክ፣ ለድምፅ ስርጭትና ለመሰል ተግባራት ኢትዮ ቴሌኮም እንደሚጠቀምበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዋየር ዝርጋታው በምስራቅ ኢትዮጵያ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብና በመላው አዲስ አበባ መካሄዱም ተገልጿል፡፡




Read 1396 times