Saturday, 29 November 2014 10:37

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በግንቦቱ ምርጫ ስለመወዳደራቸው እርግጠኛ አይደሉም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)
  • በሂደቱ ተሣታፊ እንሆናለን ብለዋል
  • የመወዳደሪያ ምልክት እየወሰዱ ነው

      ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ስለመወዳደራቸው እርግጠኛ ባይሆኑም  በሂደቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ እየገለፁ ነው፡፡
“ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ብሔራዊ ምርጫዎች ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች ያልተፈቱ ቢሆንም በ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ ሂደት ውስጥ እንሳተፋለን” ሲሉ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የመወዳደሪያ ምልክታቸውን ለምርጫ ቦርድ በማቅረብም ላይ ናቸው፡፡
አባላቱ ለምርጫው መወዳደሪያ ምልክት እንዲጠቁሙት በጽ/ቤቱ በር ላይ ማስታወቂያ የለጠፈው የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ ሠላማዊ ሠልፍና ህዝባዊ ስብሰባ ማድረግን ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ችግሮች ባለበት ስለምርጫ ጉዳይ ማውራት አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀው ፓርቲያቸው በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ ሂደት አካል ለመሆን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምርጫው ማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ እንሣተፋለን” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ይህ ማለት በሂደት በምርጫው አንወጣም ማለት አይደለም፤ እስከመጨረሻው በሂደቱ ተጉዘን የማያስኬድ መስሎ ከታየን ከምርጫው ራሳችንን ልናገልል እንችላለን ብለዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፤ በቀጣዩ ምርጫ ሊያሳትፋቸው የሚችለውን የመወዳደሪያ ምልክት ከቦርዱ እንደሚወስዱ አስታውቀው፤ በምርጫው ፍትሃዊነትና አሣታፊነት ላይ ከመንግስት እና ከምርጫ ቦርድ ጋር መምከር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

“አሁን ባለው ሁኔታ የቀጣዩን ምርጫ ባህሪ ከወዲሁ መገምገም አይቻልም” ያሉት አቶ ማሙሸት፤ ምርጫውን ማሸነፍ ይቻላል አይቻልም የሚለውም ከሂደቱ ተነስተን የምናየው ይሆናል ብለዋል፣ ፓርቲያቸው በምርጫው ሂደት እስከ መጨረሻው ሊሳተፍ እንደሚችል በመጠቆም፡፡ የመድረክ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው በምርጫው በሚደረጉ ዝግጅቶች ተሣታፊ እንደሚሆን እንጂ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ እንዳልወሰነ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር መረራ፤ ህብረተሰቡን ለምርጫው የማዘጋጀት፣ ምልክት መምረጥ የመሳሰሉትን ፓርቲያቸው እንደሚከውንና ምርጫው ከቅርጫነት ያለፈ ትርጉም ያለው እንዲሆን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይቶችንና ድርድሮችን ማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል፡፡
 መድረክ በምርጫው ሂደት ተሣታፊ ሆነ ማለት ይወዳደራል ማለት እንዳልሆነ የጠቆሙት ዶ/ር መረራ መወዳደሩን የምንወስነው በመጨረሻው ሰአት ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው የመላ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ሊቀመንበር አቶ መሳፍንት ሽፈራው በበኩላቸው፤ የፓርቲያቸው ብሔራዊ ምክር ቤት ወደምርጫው በመግባት ጉዳይ ገና ውሣኔ ያላሳለፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ሌላው የጋራ ምክር ቤቱ አባል የኢትዮጵያውያን ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ በመርህ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ተሣታፊ እንደሚሆንና በምርጫውም ተወዳዳሪ ሆኖ እንደሚቀርብ ፕሬዚዳንቱ ለአዲስ አድማስ አረጋግጠዋል፡፡ ፓርቲያቸው በሠላማዊ ትግል በምርጫ አሸንፎ ሃገር መምራት ይቻላል የሚል ፖሊሲ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ተሻለ ሰብሮ፤ በ2007 ምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረቡ ምርጫው ምቹ ነው ከሚል ድምዳሜ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡
 አሁንም ከፍተኛ ለምርጫ እንቅፋት ናቸው ተብለው በፓርቲዎች የተጠቆሙ ችግሮች ውይይት አልተካሄደባቸውም፣ ቀና ምላሽም አልተሰጣቸውም ብለዋል፡፡
 በቦርዱ የሚሠጡ ስልጠናዎች እንዲሁ ስልጠና ተሰጥቷል የሚል ሪፖርት ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር በስልጠናው የሚነሱ ችግሮች መፍትሔ አልባ ናቸው ሲሉ አቶ ተሻለ አማረዋል፡፡ እንደመርህ ወደምርጫው ውድድር መግባትን እንቀጥላለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ ፤ በወቅቱ የሚፈጠሩ ክስተቶች ፓርቲው በምርጫው ተወዳዳሪ ሆኖ የመዝለቁን ጉዳይ ይወስናሉ ብለዋል፡፡
“ዋናው ጉዳይ ምርጫውን እንዴት ተአማኒ ማድረግ ይቻላል” የሚለው ነው መነሳት ያለበት” የሚሉት አቶ ተሻለ ሠብሮ፤ “በርካታ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ተአማኒ ይሆናል ብሎ ከወዲሁ መናገር አይቻልም” ብለዋል፡፡ “የህሊና እስረኞች ይፈቱ” በሚል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እያካሄደ ያለው አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በምርጫው ፓርቲው ይሳተፍ ዘንድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ቀደም ብሎ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ወደ ምርጫው ተሣታፊነት መግባቱ በምርጫው መሳተፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን እንደማሳይ ጠቁሞ የምርጫ ምህዳሩ በሚሰፋበት ሁኔታ ላይ አበክሮ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
ምርጫ ቦርድ  ከህዳር 15 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን እየወሰዱ መሆኑን ጠቁሞ እስከ ረቡዕ ዕለት ብቻ 15 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን መውሰዳቸውን የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡    

Read 1434 times