ሳላዲን ሰኢድ
ዝነኛው የእግር ኳስ ተጫዋች ሳላዲን ሰኢድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 9 ጐሎችን አግብቷል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ እስካሁን አራት ጎሎችን ያገባው የ24 ዓመቱ ሳላዲን፤ደቡብ አፍሪካ ላይ አንድ፤ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ላይ 3 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ሳላዲን በ300ሺ ዩሮ (ከ6ሚ ብር በላይ) የዝውውር ሂሳብ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠ የእግር ኳስ ተጫዋች ነው፡፡
መሠረት ደፋር
በዘንድሮ የሞስኮ የአለም አትሌቲክስ በ5ሺ ሜትር ለአገሯ ወርቅ ያስገኘችው ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር፤ ባለፈው ነሐሴ ወር በተካሄደው የ2013 የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ5ሺ ሜትር ከአገሯ ልጅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ጋር ተፎካክራ በማሸነፍ፣ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 50ሺ ዶላር (1ሚ ብር ገደማ) ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ
በዘንድሮው የሞስኮ የአለም አትሌቲክስ በ10ሺ ሜትር ውድድር አሸናፊ በመሆን ወርቅ ያጠለቀችው ጥሩነሽ ዲባባ፤ በዳይመንድ ሊግ ውድድር በአትሌት መሰረት ደፋር ተቀድማ ሁለተኛ በመውጣት የ5ሺ ዶላር (95ሺብር ገደማ) ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ብዙም ሳትቆይ በቲልበርግ፣ ሆላንድ በተካሄደው 10ኪ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ ተወዳድራም በአንደኝነት በማሸነፍ የወርቅ ባለድል በመሆን ዓመቱን በስኬት ቋጭታለች፡፡
መሃመድ አማን
በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ በ800 ሜትር የወንዶች ውድድር አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለመው መሃመድ አማን፤ በነሐሴ ወር በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ድል በመቀዳጀት የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 50ሺ ዶላር (1ሚ ብር ገደማ) በማግኘት ተደራራቢ ስኬት አግኝቷል፡፡
የኔው አላምረው
በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ የ5ሺ ሜትር ውድድር የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው የ23 ዓመቱ የኔው አላምረው፤ በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ በመሆን የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 50ሺ ዶላር (1ሚ ብር ገደማ) በመሸለም የዓመቱ የስኬት ፈርጥ ለመሆን በቅቷል፡፡