Saturday, 27 April 2013 10:30

የሠማያዊ ፓርቲ አመራሮች በቤኒሻንጉል ታስረው ተፈቱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

“ወደ ወረዳው በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለናል” - የፓርቲው አመራሮች

በቅርቡ ከቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለው የነበሩና እንዲመለሱ የተደረጉ የአማራ ክልል ተወላጆች ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከት ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ የተጓዙ የሰማያዊ ፓርቲ ሶስት አመራሮች ለአምስት ሰዓት ታስረው እንደተለቀቁ ተናገሩ፡፡ የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ እሳቸውን ጨምሮ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ የፓርቲው የህግ ጉዳይ ሀላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ እና በደብረ ማርቆስ የፓርቲው የዞን አስተባባሪ አቶ በቃሉ አዳነ በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ለአምስት ሰዓታት ታስረው የተለቀቁት ወደ ወረዳው በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ነው፡፡

የፓርቲው አመራሮች በባታ፣ ዱጢና ባሩዳ ቀበሌዎች በመዘዋወር ከመፈናቀል የተመለሱትን አርሶ አደሮች ያነጋገሩበትና የቀረፁበትን ቪዲዮ የወረዳው ባለስልጣናት ተነጥቀው ሙሉ ለሙሉ እንደደመሰሱባቸው አቶ ይልቃል ገልፀዋል፡፡ “ወደ ዞኑና ወረዳው የሄድነው ህገ-መንግስታዊ የመዘዋወር ነፃነታችንን ተጠቅመን ቢሆንም ምናልባት በጥርጣሬ የሚመለከተን ካለ በሚል ከመታወቂያችን በተጨማሪ የፓርቲያችንን የድጋፍ ደብዳቤ ይዘን ነበር” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ከወረዳው ወደ ቀበሌ ስንገባ ካድሬዎችና የወረዳ ባለስልጣናት ከሰሙ መረጃ እንዳይደበቅ በሚል ለጊዜው ደብዳቤውን አለማሳየታቸውን፣ ያም ቢሆን የትም ቦታ በነፃነት የመዘዋወር መብት ስላላቸው ምንም ዓይነት እንግልት ሊደርስባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው አመራሮች በምን ሁኔታና እንዴት እንደታሰሩ ተጠይቀው አቶ ይልቃል ሲመልሱ፤ እሳቸውና ባልደረቦቻቸው በየቀበሌው ተዘዋውረው የአካባቢውን ህዝብ፣ ተፈናቃዮችንና ወጣቶችን አልፎ አልፎ ከማነጋገር ውጭ ሰውን አለመሰብሰባቸውን ገልፀው፤ ሥራቸውን አከናውነው ከወረዳው ሊወጡ ሲሉ እንደተያዙ ተናግረዋል፡፡

“የተያዝንበት ሁኔታ እንደ ህጋዊ ዜጋ ሳይሆን የአሸባሪ ያህል ነው” ያሉት አቶ ይልቃል፤ ከወረዳው በመውጣት ላይ እያሉ በፖሊስ፣ በደህንነት፣ በአስተዳዳሪና በትራፊክ ፖሊስ ተከበው መኪናቸው እንድትቆምና ንብረት እንዲያስረክቡ ከተደረጉ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን አብራርተዋል፡፡ “በሞባይል ከያዝናቸው ተጨማሪ ጥቃቅን ማስረጃዎች በስተቀር በቪዲዮ ካሜራ የያዝነው ምስል ሙሉ በሙሉ በወረዳው ባለስልጣናት ተደምስሶብናል” ብለዋል - ሊ/መንበሩ፡፡ በቀበሌዎቹ በተዘዋወሩባቸው ጊዜያት የተፈናቃዮቹ ሁኔታ ምን እንደሚመስል የጠየቅናቸው አቶ ይልቃል፤ ተፈናቅለው የተመለሱት አማርኛ ተናጋሪ አርሶ አደሮች በሚዲያ ከሚወራው የበለጠ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአማራ ክልል የመጡ አርሶ አደሮች በአስቸኳይ ንብረታቸውን አስረክበው ቀበሌውን ለቀው እንዲወጡ የሚል የ58 አርሶ አደሮች ስም ዝርዝር እስካሁን ተለጥፎ ማየታቸውን የነገሩን አቶ ይልቃል፤ በግርግሩ ዘጠኝ ሺህ ብር የምትሸጥ ላማቸውን በ1ሺህ ብር፣ በኪሎ አራት ብር ከሃምሣ የሚሸጥ በቆሎ በአንድ ብር ከሃምሳ ሸጠው የሄዱ ተፈናቃዮች ከተመለሱ በኋላ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን እንደታዘቡ አቶ ይልቃል ገልፀዋል፡፡ ከእስር የተፈቱበትን ሁኔታ የጠየቅናቸው አቶ ይልቃል ሲመልሱ፤ “እኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረን የወረዳው ባለስልጣናት ከዞንና ክልል ጋር ሲደዋወሉና ስብሰባ ሲሰበሰቡ ቆይተው ከአምስት ሰዓታት በኋላ “በአስቸኳይ ወረዳውን ለቃችሁ ውጡ” በሚል ማስጠንቀቂያ እያጣደፉ አስወጥተውናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “የሚገርመው ሲላቁን ይቅርታ አድርጐላችኋል ብለውናል፤ እኛ ግን ያጠፋነው ነገር ስለሌለ ይቅርታ አልጠየቅንም” ብለዋል አቶ ይልቃል ጌትነት፡፡

Read 2110 times