Sunday, 05 May 2024 00:00

የትንሣኤ (ፋሲካ) በዓል አከባበር በየአገሩ

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(0 votes)

በረሃብ ምክንያት ወደ ግብጽ ወንድማቸው ዮሴፍ ዘንድ ከአባታቸው ጋር ተሰደው የነበሩት የያዕቆብ ልጆች ተባዝተው ከ435 ዓመት በኋላ ወደ ሃገራቸው የተመለሱበት፣ የግብጽ ታላላቆች የተመቱበትንና ከግብጽ የወጡበትን ቀን ፋሲካ ብለው በየዓመቱ በግ በማረድና ያልቦካ ቂጣ በመብላት ያከብራሉ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው።
ይህ የአይሁዶች ፋሲካ ነው። በዓሉ የቂጣ በዓል ወይም በዓለ ናእት ተብሎ እንደሚከበርም ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ “በዓላት” በተሰኘ መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።
ይህንኑ በዓል ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ካከበረ በኋላ በዕለተ ዓርብ ተሰቅሎ በእለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ መነሳቱም ይታወቃል። ይህንኑ ይዘው ነው ክርስትያኖች ትንሣኤን የሚያከብሩት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት፤ ትንሣኤ ምንጊዜም ከአይሁድ ፋሲካ በኋላ የሚከበር ነው። በዓሉ ከእሑድ ውጭ በሌላ ቀን አይከበርም። የአይሁድ ፋሲካ በየዓመቱ ሲከበር ግን ሰኞም፣ ማክሰኞም… በሁሉም እለት ሊውል ይችላል።


ትንሣኤ ግን እንደዛ አይደለም። ምንጊዜም ከእሑድ ውጪ አይከበርም። ይህ እንዲሆን በቀመር ያስተካከሉት የእስክንድርያ 12ኛ ሊቀ ጳጳስ አባ ድሜጥሮስ ናቸው።
ይህንኑ አስመልክቶ አለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደዮሐንስ “ባሕረ ሐሳብ” በተባለ መጽሐፋቸው፤ “ድሜጥሮስ ጌታችን ባረገ በመቶ ሰማንያ ዘመን በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስነት ተሾመ። በተሾመ በ27 ዘመን መንፈስ ቅዱስ ባሕረ ሐሳብ የተባለ የቁጥር መጽሐፍን ገለጠለት” ብለዋል። በታሪክ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሳው እሑድ መጋቢት 29 ቀን ነው።
ትንሣኤ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው አባ ድሜጥሮስ መጋቢት 29ን ሳይሆን እሑድን እንዳይለቅ አድርገውታል። ስቅለትም ዓርብን አይለቅም። ዘንድሮ በ2016 ዓ.ም. መጋቢት 29 ቀን እንደ ጥንተ ትንሣኤ ቢውልም፣ በአባ ድሜጥሮስ ቀመር ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ትንሣኤን የምታከብረው ሚያዝያ 27 ቀን ነው።
ምዕራባውያን የካቶሊክና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስትያናት ከዚህ ቀን ቀደም ብለው በዓሉን አክብረውታል። ያም ሆኖ በኦርቶዶክስና በተቀረው ክርስትያን መካከል የጾሙ ቀን ብዛትና አከባበር እንዲሁም መከበርያ ጊዜ በዓሉን በሚያከብሩ 95 የዓለማችን ሀገራት መካከል ልዩነት አለ።
ከጾሙ ቀናት ስንነሳ ምእራባውያን 40 ቀን፣ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ 48 ቀን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን 55 ቀን ነው የሚጾሙት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊረዝም የቻለው ከፊት ጾመ ሕርቃልን፣ ከኋላ ሕማማት በማስከተሉ ነው።
የትንሳኤ በዓል አከባበር
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን፣ የትንሣኤ አከባበር ማኅሌት በመቆምና በቅዳሴ ነው። ምእመናንም ቅዳሴውን ከሌሊቱ 6 ሰዓት ጀምሮ ካስቀደሱ በኋላ የትንሣኤ በዓል የኩዳዴ ጾም ፍቺም በመሆኑ ጾም ይፈታል።
እንደየአቅማቸው ዶሮ ወጥ እና በግ አርዶ በመብላት፣ ድፎ ዳቦ እና የተጠመቀ ጠላ አዘጋጅቶ፣ ቡና አፍልቶ በመጠራራት ይከበራል።
በሌሎች ሀገራትስ?
በዓሉን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያከብሩትን 95 ሀገራት እዚህ መዘርዘር አይቻልም። አልፎ አልፎ በአንዳንድ ሀገራት እንዴት እንደሚከበር በአጭሩ ለማየት እንሞክር።
ሰሜን ምእራብ አውሮፓ
በዋዜማው ወይም በበዓሉ እለት ችቦ ያበራሉ። ይህም የይሁዳ መብራት በመባል ይታወቃል። ይህ ሃይማኖታዊ ይዘት ቢኖረውም ከሃይማኖታዊ ይዘት ውጪ የበጋን ማብቃትና የጸደይን መግባት የሚቀበሉበትም ነው። በብሪታንያ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበትን ቀን ለማስታወስ በጸሎተ ሐሙስ የጸሎተ ሐሙስ ገንዘብ ይሰጣሉ።
በጎረቤት ፈረንሳይ ደግሞ የክርስቶስን ስቅለት አስመልክቶ ከእለተ ስቅለት ዓርብ እስከ ትንሣኤ እሑድ አንዳችም የቤተ ክርስትያን ደውል አይደወልም። በእለተ ትንሣኤ የፈረንሳይ ልጆች ደውሎች “ከሮም መልስ ሲበርሩ” ያያሉ። ፈልገው በማግኘት እንዲያጣጥሙ በአዋቂዎች የተዘጋጀላቸው የቸኮሌት እንቁላልም ይደበቅላቸዋል።
ጣልያኖች እለተ ትንሣኤን ከሞላ ጎደል የሚያከብሩት የበከል (የግልገል) ጥብስ፣ የዘውድ ቅርጽ ያለው ዳቦ፣ በቀለማት የተጌጠ ከረሜላ ያለው እንቁላል በመብላት ነው።
በእስራኤል
በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ያሉ ክርስትያኖች ስቅለትን የሚያከብሩት ኢየሱስ ክርስቶስ በፍኖተ መስቀሉ ተጉዞበታል፤ እግሮቹ ረግጠውታል ተብሎ በሚታሰብበት ጎዳና ላይ አብዛኞቹ የየራሳቸውን መስቀል በመሸከም እየተጓዙ ነው። እኒሁ ክርስትያኖችና የሃይማኖት ተጓዦች በእለተ ትንሣኤ ማለዳ በጌቴ ሰማኒ በማስቀደስ በዓሉን ያከብራሉ።
የፊሊፒንስ ካቶሊካውያን ክርስትያኖች
በፊሊፒንስ ካቶሊካውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት የሚያከብሩት ጀርባቸውን ስለት ባለው ነገር እና በቀርከሃ በትር በመግረፍ ነው።
ሜክሲኮ
ሜክሲኮ ስቅለትንና ትንሣኤን ማክበር የምትጀምረው በዓለ ሆሳእና አልቆ ሰሙነ ሕማማት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው። ይህም የሚሆነው ከቤተ ክርስትያን ውጪ የሚገዙትን የዘንባባ ጉንጉን በራቸው ላይ በመስቀል ነው።
ኬንያ
 እንደ ሜክሲኮው ሁሉ በኬንያ ስቅለትና ትንሣኤ መከበር የሚጀምሩት ከሆሳዕና እሑድ ጀምሮ ነው። በእለተ ሆሳዕና ልጆች የኢየሱስ ክርስቶስን በድል ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ለማክበር የዘንባባ ዝንጣፊ ወደ ቤተ ክርስትያን በማምጣት ይዘምራሉ። የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ትምህርት ቤቶችና ታላላቅ የንግድ ተቋማትም በኬንያ ዝግ ሆነው ይሰነብታሉ።
ሴቶች ውሃ የሚነከሩባት ሀንጋሪ
በምስራቅ አውሮፓዊቷ ሀገር ሀንጋሪ፣ ትንሣኤ በፎክሎር ጸደይ እና ማኮረት (የዘር እንቁላል ዝግጁ ከሚሆንበት) ከሚከበሩበት በዓል ጋር ተጣምሮ ይከበራል። ቡዳ እና ፔስት የተባሉ አካባቢዎችን አጣምራ መዲናዋን ቡዳፔስት ያለችው ሀገረ ሀንጋሪ፣ በበዓሉ ወንዶች ሴቶችን በጫወታ መልክ ኩሬ ውሃ ውስጥ በመንከር በዓሉን ሲያከብሩ ሴቶቹ ደግሞ ጌጠኛ እንቁላሎችና አስቂኝ ግጥም ወንዶቹን በመጋበዝ ያከብራሉ።
ትንሣኤ እና የትንባሆ ዛፍ
በፓፓዋ ኒው ጊኒ በሀገሪቱ ባለው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የትንሣኤ ቸኮሌት እንቁላሎች ስለሚቀልጡ በቤተ ክርስትያንና በአካባቢዋ ያሉ ዛፎች እንደ ትንባሆ እና ሲጋራ መስቀያ ያገለግላሉ። ይህም በዕለተ ትንሣኤ እሑድ የቤተ ክርስትያን አገልግሎት ከተፈጸመ በኋላ ለምዕመናን የሚታደል ነው።
ትንሣኤ በሩስያ እና ፕሬዚዳንቱ
 ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሩስያ መሪ ሆነው የዘለቁት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በዓላትን ከምዕመናን ጋር በማክበርም ይታወቃሉ።
መሪው ለጥምቀት ልብሳቸውን አውልቀው ጥምቀተ ባሕር ሲጠመቁ ታይተዋል። በእለተ ትንሣኤም ቤተ ክርስትያን በመሔድ በፊት ጊዜ ከቀድሞ ባለቤታቸው ሉድሚላ ጋር ከዚያን ወዲህም ለብቻቸው ቤተ ክርስትያን በመሔድ ሲያስቀድሱ ታይተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ሁሉ፣ ሩስያውያን ኦርቶዶክሶች ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተነሳ በማለት ሰላምታ ይለዋወጣሉ።፡ ለሰባት ሳምንታት ለጾሙት ሩስያውያን አይብ፣ የተቀቀለ እንቁላል እና የበዓሉ ልዩ ዳቦ ምርጥ የትንሣኤ ምግባቸው ነው።
መልካም የትንሣኤ በዓል!!
*** ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።


Read 949 times