ጋዜጣን በፀፀት
የጋዜጣ አንባቢና የውሃ-ሙላት አንድ ነው፡፡ ጋዜጠኛና ለውሃ-ሙላት የዘፈነው አዝማሪም እንደዚያው ተመሳሳይ፡፡ ኧረ እንደውም ተተካኪ ናቸው፡፡ ለጋዜጣ መፃፍ ለውሃ ሙላት እንደመዝፈን ነው፡፡ የሰማው ሲሄድ ያልሰማው ይመጣል፡፡ ቆሞ የሚያዳምጥ ጋዜጣ አንባቢና የውሃ ሙላት የለም፡፡ እየሄደ አዳምጦህ፣ እያዳመጠህ ይሄዳል…
የ11 ዓመት እስር በመጽሐፍ
በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ምክንያት ለ11 ዓመታት በእስር ከቆዩት ኢትዮጵያዊያን አንዷ የነበረችው ከበደች ተክለአብ፤ በ1983 ዓ.ም አሳትማ ለአንባቢያን ያቀረበችው መጽሐፍ “የት ነው” የሚል ርዕስ የተሰጠው የግጥም መድበል ሲሆን በሥነ ግጥምም ቢሆን ርዕሰ ጉዳዩን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ላይ በማድረግ በአገራችን ፈር ቀዳጅ መፅሀፍ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ሳንታና ከጋዳፊ መመሳሰሉ ችግር ፈጥሮበታል
እውቁ ጊታሪስት ካርሎስ ሳንታና ከሟቹ ሞአመር ጋዳፊ ጋር መመሳሰሉ ችግር ፈጥሮበት እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ፡፡ ጋዳፊ ከመሞታቸው በፊት በተለያዩ የሶሽያል ሚዲያ መድረኮች “ሳንታና ጋዳፊ ነው ይገደል” እና “ሳንታና ሞቷል” የሚሉ ሰዎች በዝተው እንደነበር ዘገባው አትቷል፡፡
በትውልዱ ሜክሲኳዊ የሆነው ካርሎስ ሳንታና በላቲን፤ብሉዝ፤ ጃዝና ሮክ የሙዚቃ ስልቶች ከ1960 ጀምሮ በዓለም ዙርያ ሲደነቅ የኖረ ሙዚቀኛ ነው፡፡
ከ13 ዓመት በፊት በሮክ ኤንድ ሮል የዝነኞች መዝገብ የሰፈረው ካርሎስ ሳንታና፤ በ1999 እ.ኤ.አ “ሱፐር ናቹራል” በሚል የሰራው አልበሙ በመላው ዓለም ከ25 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች ተቸብችቦለታል፡፡ የ64 ዓመቱ ካርሎስ ሳንታና በ44 ዓመት የስራ ዘመኑ 10 የግራሚ ሽልማቶችና 3 የላቲኒ የግራሚ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡
የኮልድ ፕሌይ ‹ማይሎ ዛይሎቶ› ገበያ ተሟሟቀ
ሰሞኑን ለገበያ የበቃው የኮልድ ፕሌይ አዲስ አልበም ‹ማይሎ ዛይሎቶ› ገበያው እየቀናው እንደሆነ ቢልቦርድ ገለፀ፡፡ በዘመናዊ የሮክ ሙዚቃው የሚታወቀው የኮልድ ፕሌይ ባንድ የመጨረሻ አልበሙን ከ3 ዓመታት በፊት ያሳተመ ሲሆን ሰሞኑን ለገበያ ያበቃው ‹ማይሎ ዛይሎቶ› የባንዱ 5ኛ አልበም ነው ፡፡‹ ማይሎ ዛይሎቶ› በሚል የወጣው የአልበሙ ስያሜ ዋይት ሮዝ በሚል በ1970ዎቹ ተደርጎ ከነበረው ፀረ ናዚ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በየቦታው ይፃፉ ከነበሩ መልዕክቶች መወሰዱን የገለፀው የ34 ዓመቱ የባንዱ መሪ ክሪስ ማርቲን ነው፡፡ የኮልድ ፕሌይ አዲስ አልበም ‹ማይሎ ዛይሎቶ› በአማዞን ድረገፅ ዋጋው ተቀንሶ በ3.99 ዶላር ሲሸጥ ገበያው ተሟሙቋል፡፡ አልበሙ ባለፈው ሰኞ ለገበያ በበቃበት የመጀመሪያው ቀን 90ሺ ቅጂ መሸጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዊል ፋረል የክብር ሽልማት ተቀበለ ኤዲ መርፊ ትወና እንደ ሰለቸው ተናገረ
ዊል ፋረል በማርክ ትዌይን የተሰየመ የኮሜዲ አዋርድ እንደተሸለመ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡ የክብር ሽልማቱ በፊልም እና ሌሎች ኪነ ጥበባዊ ስራዎቻቸው የአሜሪካን ማህበረሰብ በጥሩ መንገድ ቀርፀዋል ተብለው ለተመረጡ የኮሜዲ ተዋናዮች የሚዘጋጅ ነው፡፡ ኮሜድያኑ ዊል ፋረል ልዩ የክብር ሽልማቱን ባለፈው እሁድ በጆንኤፍ ኬኔዲ ማዕከል በተደረገ ስነስርዓት ላይ ተቀብሏል፡፡ ከ1998 እ.ኤ.አ ጀምሮ ይህን የክብር ሽልማት ካገኙት ታዋቂ የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች መካከል ቲና ፌይ፤ ሪቻርድ ፕሬየር፤ ቦብ ኒው ሃርት፤ ሎረኔ ሚካኤልስና ስቲቭ ማርቲን ይገኙበታል፡፡ የሃብት መጠኑ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር የሚገመተው የ44 ዓመቱ ዊል ፋሬል፤ በአንድ ፊልም 20 ሚሊዮን ዶላር ከሚከፈላቸው ጥቂት ተዋናዮች አንዱ ነው፡፡
“ፓናሮማ አክቲቪቲ 3” በሆረር ፊልሞች የገቢ ሪኮርድ ያዘ
“ፓናሮማ አክቲቪቲ 3”የተባለው ሆረር ፊልም ባለፈው ሳምንት በሰሜን አሜሪካና በመላው ዓለም ለእይታ የበቃ ሲሆን ከበጀቱ 16 እጥፍ የሚልቅ ከፍተኛ ገቢ አስገባ፡፡ ፊልሙ በመጀመርያ ሳምንት ገቢው በሰሜን አሜሪካ ብቻ 80 ሚሊዮን ዶላር በመድረሱ በሆረር ፊልሞች ታሪክ አዲስ የገቢ ሪኮርድ ማስመዝገብ መቻሉን ቦክስ ኦፊስ ሞጆ አመልክቷል፡፡ በፓራማውንት ፒክቸርስ በ3 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው ‹ፓናሮማ አክቲቪቲ 3” በሳይንሳዊ ልቦለድ ላይ ያተኮረ አስፈሪ ፊልም ነው፡፡ ከ18 ዓመት በፊት የተሰራው “ፓናሮማ አክቲቪቲ” ክፍል 1 እና ሁለተኛው ክፍል 3 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶባቸው በመላው ዓለም 371 ሚሊዮን ዶላር አስገብተዋል፡፡
የጋዳፊ ቤተሰብና ሊቢያ ለሆሊውድም አልተመቹም ነበር
በጋዳፊ የሥልጣን ዘመን ቤተሰባቸው ሊቢያ ለሆሊውድ ሳይመቹ መቆየታቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አመለከቱ፡፡ ዘገባዎቹ በሆሊውድ ፊልሞች ታሪክ በሊቢያ የገጠሙ ውጣ ውረዶችን በማስታወስና የጋዳፊ ቤተሰብ በሆሊውድ የነበራቸው ኢንቨስትመንት እጅግም ያልተሳካ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በ1977 እ.ኤ.አ “ዘ ሜሰጅ” በሚል ርዕስ በነብዩ መሃመድ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያተኩርና በአንቶኒ ኪዊን ሊተወን የነበረ ፊልም በበጀት እጥረት ሳይሰራ ቀርቷል፡፡
“ባለትዳሮቹ” ትያትር ሰኞ ይመረቃል
የአርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ድርሰት እና ዝግጅት የሆነው “ባለትዳሮቹ” አዲስ ትያትር ሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ አርቲስት ስናፍቅሽ ተስፋዬ በረዳት አዘጋጅነት በሠራችበት ትያትር ራሷ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ወለላ አሰፋ፣ ተስፉ ብርሃኔ፣ ዮናስ ጌታቸው፣ አዲስዓለም መግራ እና ለምለም አሰፋ በተዋናይነት ተሳትፈዋል፡፡ ከታምሩ ብርሃኑ የቅርብ ጊዜ ሥራዎች መካከል “አስከሬኑ” ፊልም እንዲሁም ከሌሎች ፀሐፍት ጋር “ሰው ለሰው” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ይጠቀሳሉ፡፡
ታዳጊዎች የደራሲ ሐዲስን ልደት በትዕይንተ ጥበባት ያከብራሉ
በአዲስ አበባ የሚገኙ ታዳጊዎች እና ሕፃናት የክቡር ዶክተር ሐዲስ አለማየሁን ልደት በትዕይንት ጥበባት ያከብራሉ፡፡ ዛሬ ጠዋት በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ትልቁ አዳራሽ በሚቀርበው ዝግጅት የአንጋፋው ደራሲ እና ዲፕሎማት ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ 102ኛ ዓመት ልደት መታሰቢያ ይከበራል፡፡ዛጎል ቤተመፃሕፍት ባዘጋጀው ዝግጅት “ተረት ተረት የመሠረት” ከሚለው የደራሲው መፅሐፍ ድራማዊ ትረካ፣ የልጆች ግጥም፣ ሥእል፣ ዳንስ፣ ሙዚቃና መሠል ዝግጅት ይኖራል፡፡ የክብር ዶክተር ሃዲስ አለማየሁ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና የወ/ሮ ክበበፀሃይ (ባለቤታቸው) ሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት ሠራተኞች የክብር እንግዳ በሚሆኑበት ዝግጅት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ፤ ሐዲስ አለማየሁ በደራሲነትና በዲፕሎማትነት ስላደረጉት አስተዋፅኦ ገለፃ ያደርጋሉ፡፡ በዝግጅቱ ከአዲስ አበባ ከተውጣጡ ታዳጊ ወጣቶች ሌላ ገጣሚ ሜሮን ጌትነት፣ ድምፃዊት ሙኒት መስፍን፣ እና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
“ፒያሳ፣ ማህሙድጋ ጠብቂኝ” ነገ ለውይይት ይቀርባል
በቅርቡ ለንባብ የበቃው የደራሲ መሃመድ ሰልማን “ፒያሳ ማህሙድጋ ጠብቂኝ” የተሰኘ መፅሐፍ በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት በሚዩዚክ ሜይደይ ኢትዮጵያ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡ አምስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዘክር አዳራሽ የሚካሄደውን ውይይት ደራሲና ኃያሲ መስፍን ሃብተማርያም ይመሩታል፡፡