Administrator

Administrator

         ውህደት ለመፈፀም ተደጋጋሚ ድርድሮችን ሲያካሂዱና ስምምነት ሲፈፀሙ የቆዩት አንድነት ፓርቲ እና መኢአድ፣ የውህደት ጅምራቸው ካለመሳካቱም በተጨማሪ በየፊናቸው ለሁለት ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ነው የከረሙት፡፡ በመጨረሻም የምርጫ ቦርድ፣ ከመኢአድ ፓርቲ በአቶ አበባው መሃሪ ለሚመራ ቡድን፣ ከአንድነት ፓርቲ ደግሞ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ ለሚመራው ቡድን እውቅና ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ እውቅና ያልተሰጠው በአቶ በላይ የሚመራው የአንድነት ቡድን ብዙም ሳይቆይ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተቀላቅሏል፡፡

እገዳው ለ15 አመታት ተግባራዊ ሆኖ ቆይቷል
    የአሜሪካ ፌዴራል አቪየሽን ባለስልጣን የአገሪቱ አውሮፕላኖች በተወሰኑ የኢትዮጵያ የድንበር ካባቢዎች የአየር ክልል ውስጥ እንዳይበሩ የጣለችውንና ለ15 አመታት ተግባራዊ ሆኖ የቆየውን እገዳ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡ባለስልጣኑ የበረራ እገዳውን የጣለው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት እንደነበር
አስታውሶ፣ እገዳው በተጣለባቸው አካባቢዎች የደህንነትና የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንና የአደጋ ስጋት የሌለበት መሆኑን በጥናት በማረጋገጡ እገዳውን ማንሳቱን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው መረጃ አስታውቋል፡፡በወቅቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተከሰተውን የድንበር ግጭት በድርድር ለመፍታት የተጀመረው ጥረት መስተጓጎሉን ተከትሎ፣ በአካባቢው የነበረው አጠቃላይ ሁኔታ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው በሚል የበረራ እገዳው እ.ኤ.አ በ2000 ግንቦት ወር መጣሉን የጠቀሰው የባለስልጣኑ መረጃ፣ እገዳው መነሳቱ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መጽደቁን ተከትሎ፣ የአሜሪካ አውሮፕላኖች በየትኛውም የኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

  • ሰሞኑን 35 ስደተኞች የያዘ ጀልባ የመን ሳይደርስ ሰጥሟል
  • በዓመት 200 ገደማ ኢትዮጵያውያን በበረሃ እና በባህር ጉዞ ላይ ሞተዋል
  • “በህጋዊ ምዝገባ የስራ ጉዞ መታገዱ ህገወጥ ስደትን አባብሷል”

       በህጋዊ ምዝገባ ወደ አረብ አገራት የሚደረግ ጉዞ ከታገደ ወዲህ፣ በየመን በኩል እየተሰደዱ ለአደጋ የሚጋለጡ ኢትዮጵያዊያን መበራከታቸውንና ባለፉት ስድስት ወራት 47ሺ ያህል ስደተኞች የመን እንደገቡ RMMS ሰሞኑን ገለፁ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን እና ሌሎች አለማቀፍ ድርጅቶች በጋራ ያቋቋሙት ይሄው ተቋም እንደሚለው፣ ዘንድሮ የስደተኞቹ ቁጥር ከአምናው በእጥፍ ይበልጣል፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ 250 ስደተኞች የመን ለመግባት ሲሞክሩ፣ በባህርና በበረሃ ጉዞ ላይ መሞታቸውን ተቋሙ ጠቅሶ ከስደተኞቹ መካከል ሰማኒያ በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ሰሞኑን በባህር ጉዞ ላይ በተፈጠረ አደጋ አንድ ጀልባ መስመጡን የዘገበው ኤኤፍፒ፤ ጀልባዋ 35 ስደተኞችን አሳፍራ ነበር ብሏል፡፡ ከጉዞ አደጋ በተጨማሪ ስደተኞቹ የመን ከገቡ በኋላም ግማሽ ያህሉ በወሮበላ ቡድኖች እንደሚታገዱ የገለፀው RMMS፤ ከእገታ ለመለቀቅ ከቤተሰብ ገንዘብ እንዲያስልኩ ይገደዳሉ ብሏል፡፡ ለስደት የሚገፋፉ ዋና ዋና ምክንያቶችን ለማወቅ በሺ በሚቆጠሩ ስደተኞችና በትውልድ አካባቢዎቻቸው ላይ ጥናት ያካሄደው ይሄው ተቋም፤ በኢትዮጵያ ዋናዎቹ መንስኤዎች የኑሮ ችግር እንዲሁም ህይወትን የሚያሻሽል ነገር ፍለጋ ናቸው ብሏል፡፡ የፖለቲካ ችግርም የተወሰነ ጫና እንደሚፈጥር ተቋሙ ጠቅሶ፣ የደላሎች ድርሻ ግን ብዙዎች እንደሚያስቡት አይደለም፤ ከመቶ ስደተኞች መካከል በደላላ ግፊት ለስደት የሚነሳሱት ከሁለት ወይም ከሦስት አይበልጡም ብሏል፡፡
ብዙ ወጣቶች ወደ ስደት የሚያቀኑት አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ባለማወቃቸው ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ተቋሙ ሲያስረዳ፤ በአመት ውስጥ ወደ የመን ከገቡት ኢትዮጵያዊያን መካከል ሩብ ያህሉ ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተባረሩና ካሁን በፊት ስደትን የሞከሩ ናቸው ብሏል፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ የስደተኞቹ ቁጥር የተባባሰበት ሌላው ምክንያት፣ በህጋዊ ምዝገባ ወደ ሳዑዲ አረቢያና ወደ ኩዌት ሲደረግ የነበረው የስራ ጉዞ በመንግስት መታገዱ ነው ብሏል - የተቋሙ ጥናት፡፡ በሌላ በኩል ሶማሊያ ውስጥ ከድህነት በተጨማሪ የሰላም እጦት ወጣቶችን ለስደት እንደሚገፋፋ ተቋሙ ገልፆ፤ በኤርትራ ደግሞ ከኑሮ ችግር ሌላ ዋነኛው ግፊት የመንግስት ከፍተኛ የፖለቲካ አፈና ነው ብሏል፡፡ በሊቢያና በግብጽ በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት ከሚሞክሩ ስደተኞች መካከል ከሶሪያዊያን በመቀጠል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ኤርትራዊያን መሆናቸውን የጠቀሰው ይሄው ተቋም፤ ባለፉት አራት ወራት 15ሺ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ እንደተሰደዱ ገልጿል፡፡ ስደት የተባባሰው በድህነትና በአፈና ምክንያት አይደለም በማለት የኤርትራ መንግስት ሲያስተባብል፤ ወጣቶች እንዲሰደዱ በማድረግ አገሪቱን ኦና ለማድረግ አለማቀፍ ሴራ እየተካሄደብኝ ነው ብሏል፡፡

 

ውህደት ለመፈፀም ተደጋጋሚ ድርድሮችን ሲያካሂዱና ስምምነት ሲፈፀሙ የቆዩት አንድነት ፓርቲ እና መኢአድ፣ የውህደት ጅምራቸው ካለመሳካቱም በተጨማሪ በየፊናቸው ለሁለት ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ነው የከረሙት፡፡ በመጨረሻም የምርጫ ቦርድ፣ ከመኢአድ ፓርቲ በአቶ አበባው መሃሪ ለሚመራ ቡድን፣ ከአንድነት ፓርቲ ደግሞ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ ለሚመራው ቡድን እውቅና ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ እውቅና ያልተሰጠው በአቶ በላይ የሚመራው የአንድነት ቡድን ብዙም ሳይቆይ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተቀላቅሏል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች ቀደም ሲል አንድነት ፓርቲ ውስጥ እንደነበሩና በክፍፍል ምክንያት ወጥተው ፓርቲ እንዳቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ በፓርቲዎች ክፍፍል እና በወቅታዊ የፖለቲካ ውዝግቦች ዙሪያ ለጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ የሰጡትን አስተያየት አቅርበናል፡፡

የምርጫ ሰሞን የፓርቲዎች ክፍፍል
በየምርጫው የፓርቲዎች ግጭትና ክፍፍል የተለመደ ቢሆንም የዘንድሮው ይለያል፡፡ በመንግስት አቋም ተወስዶበት የተሰራ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በራሱ ስራና ብቃት መመረጥ እንደማይችል አውቋል፡፡ ስለዚህ ህዝቡን አማራጭ ማሳጣት ይፈልጋል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ስህተቶችን በማጉላት እንዲሁም ሬዲዮ ፋናን፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንንና ምርጫ ቦርድን  በመጠቀም፣  “የተቃውሞው ጎራ እርባና ቢስ ነው፤ ብትወደኝም ባትወደኝም ከእኔ ጋር ትኖራለህ” በሚል ህዝቡ ላይ ጫና ለማሳደር የመጫን ስራ ሆን ብሎ እየሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድነት ላይ የወሰደውን ውሳኔና የሰጠውን መግለጫ ማየት ይቻል፡፡ “የእነ ትዕግስቱ ቡድን ለእኛ ስለሚታዘዝና በእኛ ሃሳብ ስለሚስማማ እንጂ የራሱ ድክመት አለበት” በማለት አንድነትን ለእነሱ አፅድቆላቸዋል፡፡ ሌላው በእኛ በሰማያዊ ፓርቲ ላይ ቦርዱ
የጀመረው ዘመቻ ነው፡፡ ይቅርታ እንድንጠይቅ ደብዳቤ ፅፎብን ነበር፡፡ እንደ ጥፋት ያቀረባቸው
ነገሮች ግን እዚህ ግባ የማይባሉና ጥፋት ያልሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ትብብር ለምን ሰራችሁ፣ ያልተመቸንን ስብሰባ ትተን መውጣት መብራታችን ሆኖ ሳለ እንዴት ረግጣችሁ ትወጣላችሁ በሚል ነው የመጨረሻ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ  የፃፈልን፡፡ ሬዲዮ ፋናንና ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ብንመለከት፣ እንደሌሎቹ ፓርቲዎች እኛ ላይ ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ጠሩኝ፡፡ አክብሬ ሄድኩኝ፤ እዚያው ሬዲዮ ፋና ስቱዲዮ ውስጥ ለሁለት ሰዓት ከተቀረፅኩኝ በኋላ መጨረሻ ላይ ፊልሙ ተበላሽቷል አይተላለፍም አሉኝ፡፡ እኛ የቀረፅነው ስላለ እንስጣችሁ አልናቸው፤ አልፈለጉም፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመሳሳይ ጥያቄ ይዞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታንን ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል አነጋገራቸው፤ ግን በቴሌቪዥን አልተሰራጨም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ለእነሱ ፕሮፓጋንዳ የሚመች መልስ ስላልሰጠን ነው፡፡ ይህን ሁሉ ስመለከተው መንግስት ሆን ብሎ ፓርቲዎችን ጥላሸት ለመቀባት ለህዝብ ለማሳየት እየተደረገ ያለ ጥረት መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡“አንድነት” ለሁለት ስለመሰንጠቁእኔ በበኩሌ አንድነት ለሁለት ተሰነጠቀ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም ቅር ተሰኘን የሚሉ ጥቂት ሰዎች ሄደው ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ አቀረቡ፡፡ ከስራ አስፈፃሚው እስከ ታች ያለው የፓርቲው መዋቅር ግን በእነ አቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራ ነው፡፡ የፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት አፈጉባኤ፣
ምክትል አፈጉባኤ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ኃላፊ…  ከእኛ ጋር ቀላቀሉት ናቸው፡፡ ሌላው አንድነት የት አለ? ከእኛ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፓርቲው ትልቁን የኃላፊነት ቦታ የያዙት ስለሆኑ እኔ አንድነት ተሰነጠቀ አልልም፤ ከኛ ጋር ተዋሃደ እንጂ አልተሰነጠቀም፡፡ በአሁኑ ሰዓት እዚህ እየመጡ እየተመዘገቡ ነው በክልልም ለምርጫው እጩ እስከማቅረብ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ከእኛ ጋር የተቀላቀሉትን ብዛት በቁጥር ለመግለፅ እቸገራለሁ፡፡ በአጠቃላይ በአቶ በላይ ፈቃዱ ሲመሩ የነበሩት እውነተኛዎቹ የአንድነት አባላት ከነመዋቅራቸው ወደ እኛ መጥተዋል፡፡ “አንድነት ሰማያዊ ሴራ ፈረሰ” ስለመባሉበብዕር ስም ተፅፎ የወጣው፤ ዘገባ ሃሰት ነው፡፡ ምክንያቱም በእስር ላይ ያሉትን እነ ሃብታሙ አያሌውን ሁልጊዜ እናገኛቸዋለን፡፡ እንደውም ወደፊት አብረን ስለምንሰራበት ሁኔታ በየጊዜው እንወያያለን፡፡ ከሃብታሙም ሆነ ከየሺዋስ ጋር ጓደኛሞች ነን፡፡ የአንድነት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ በመግባታቸው ኢህአዴግ በደረሰበት ድንጋጤ ሆን ብሎ የሚያስወራው ነው፡፡ እዚያ ዘገባ ላይ ከተፃፈው አንድ ምሳሌ ልንገርሽ፡፡ በበላይ ፍቃዱ የሚመራው ቡድን በዶ/ር ያዕቆብ ሸምጋይነት ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ጋር በተናጠል ሲደራደር ቆይቷል ተብሎ ተፅፏል፡፡ ይሄ አይን ያወጣ ውሸት ነው፡፡ እኔና በላይ ፍቃዱ ከጓደኝነታችን የተነሳ ለመገናኘት ሽማግሌ
አያስፈልገንም፤ ሁልጊዜም ቢሆን እየተገናኘን በአገራችን ወቅታዊ በጎና መጥፎ ጉዳዮች ላይ ሌት
ተቀን የምንነጋገር የምንከራከር ነን፡፡ እኔና ዶ/ር ያዕቆብ አንድ ላይ ሆነን ሻይ ጠጥተን እንደማናውቅ ላረጋግጥልሽ እወዳለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ የሚመራብን ወሬ  የኢህአዴግን ድንጋጤ የሚያሳይ ነው፡፡
እንደ ክፍፍሉ ውህደቱ መፍጠኑአሁን ጥቃቅንና አነስተኛ የፕሮግራም ልዩነቶችን እያነሳን ጊዜ የምናባክንበት ወቅት ላይ አይደለንም፡፡ በመሰረቱ አንድነትና ሰማያዊ በአብዛኛው ፕሮግራሞቻቸው ላይ ልዩነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ዋና ዋናዎቹ ላይ ከተስማማን በጥቂትና ጥቃቅን የፕሮግራም ልዩነቶች ላይ በሂደት በውይይትና በክርክር የምንስማማባቸው ይሆናሉ፡፡ አብረን ለመስራት የሚከለክሉን ስላልሆኑ ይሄ
አያስጨንቀንም፤ በአሁኑ ሰዓት እንደ ቁምነገር የምናነሳው አይደለም፡፡ የአንድነት አባላት በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ የሚኖራቸው የአመራር ቦታቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ወደኛ የመጡት የአንድነት ሰዎች በትልልቅ የአመራር ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ በፓርቲው ስልጣንና ሹመት ውስጥ ብቻ ሳይሆን አሁን አዲስ አበባ ላይ በምናቀርባቸው እጩዎች ላይ ጥሩ ጥሩ ተፎካካሪዎችን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የመመረጥ መብታቸው እስከ ከፍተኛ አመራር ድረስ ክፍት ስለሆነ መብታቸው ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ ተነጋግረንበታል፡፡ አሁን ከተቀላቀሉን ውስጥ ብዙዎቹ ጥሩ ጥሩ የአመራር ብቃት ያላቸው ስለሆኑ ለፓርቲያችን ያስፈልጉናል፡፡ በፓርቲው ወሳኝ ወሳኝ ቦታ ላይ ገብተው የመስራት መብት አላቸው፡፡ በቀሪው አንድ ሳምንት ውስጥ በእጩነት እንዲገቡም እናደርጋለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሌም “ፓርቲዎች ትከፋፈላላችሁ፤ አትግባቡም” እንባለለን፡፡ ይሄ ቁጭት በውስጣችን እያለና ገዢው ፓርቲ ሆን ብሎ “ተጣልተዋል፤ ተከፋፍለዋል” የሚለውን ስራዬ ብሎ በተቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እያናፈሰ ባለበት አስቸጋሪ ሰዓት ፓርቲያችንን የሚያግዝና የሚያጎለብተን ኃይል ሲመጣ እንዴት አንደሰትም፡፡ ከዛ በተረፈ በሁለቱም ፓርቲዎች በኩል ያለን ሰዎች የምንተዋወቅና የምንግባባ ስለነበርን እንደ አዲስ አንተያይም፤ አብረን ለመስራት ሁሉንም ነገር ያቀልልናል፡፡ለምርጫ ስላቀረቧቸው እጩዎች ብዛት እስካሁን ፓርቲያችን በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ 400 የሚጠጉ እጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ አሁን ደግሞ እጩ የማስመዝገቡ ሂደት ለአንድ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ በዚህ በቀረን አንድ ሳምንት አዲስ ከተቀላቀሉን ሰዎች ውስጥ የምናስመዘግባቸው ይኖራሉ፡፡ በአጠቃላይ የእጩዎቻችን ቁጥር ወደ 500 ከፍ ሳይል እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ ልናስመዘግብ ያቀድነው የእጩዎች ብዛት 300 ነበር፡፡ በምርጫ ዘመቻ የፓርቲዎች ስህተትና ትኩረትምርጫው እየቀረበ እንደመሆኑ መጠን በውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በትናንሽ ጉዳዮችና በእርስ በርስ ፉክክር ላይ ከማተኮር ይልቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትልቁን የአገራቸውን ምስል እንዲያዩ እመክራለሁ፡፡ ልዩነትም ቅራኔም ቢኖር መቻቻልና ቅራኔን በጥበብ
በመያዝ ለውጤት ወደሚያበቃ ትግል ተጠናክረን መግባት አለብን፡፡ ዛሬ የምንሰራው ስህተት ልብ ሰብርና ህዝቡን ተስፋ የሚያሳጣ እንዳይሆን በመጠንቀቅ በጥበብ መጓዝና ለምንታገልለት ህዝብ የተስፋ ብርሃን መፈንጠቅ ይኖርብናል፡፡ ፓርቲዎች የገዢውን ፓርቲ ከፋፋይ ሴራ በማወቅ፣ ከፍተኛ
ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

    “ቴአትረ ቦለቲካ” የሚል መፅሃፍ ሊያወጡ ነው
በመጪው ግንቦት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ካለፈው ምርጫ የተለየ ውጤት ቨመጣል ብለው እንደማይጠብቁ የተናገሩት የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በምርጫውም እንደማይወዳደሩ አስታወቁ፡፡ በ “ቴአትረ ቦፖለቲካ ፣ አሉባልታና የአገራችን ፖለቲካ ገመና” በሚል ርዕስ የፃፉት አዲስ መፅሀፍ በቅርቡ በገበያ ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል፡፡
“የኢህአዴግን አካሄድና የተቃዋሚው ጎራ ያለበትን ሁኔታ ሳየው በግንቦቱ ምርጫ ካለፈው የተለየ ነገር ይመጣል ብዬ አላስብም” ያሉት አቶ ልደቱ፤ ኢህአዴግ ምርጫውን ሙሉ በሙሉ በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ እንደቀጠለ ነው፣ ተቃዋሚው ጎራም ካለፉት ስህተቶቹና ድክመቶቹ ተምሮ ራሱን ለማሻሻል ያደረገው ብዙ ነገር የለም ሲሉ ምክንያታቸውን ገልፀዋል፡፡ “ድፍረት አይሁንብኝ እንጂ ተቃዋሚው ጎራ በፓርላማ ያለችውን አንድ መቀመጫ አስጠብቆ ይቀጥላል ወይ የሚለው በራሱ ለኔ ጥያቄ ነው” ሲሉም ጥርጣሬያቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በተቃዋሚ ፓርቲ ዙሪያ የተደረጉ የትብብር ሙከራዎች ትግሉን የጎዱ እንጂ የጠቀሙ አይደሉም ሲሉ የሚሞግቱት አቶ ልደቱ፤ ፓርቲዎች በእንተባበር ጥያቄዎች ባይዳከሙ ኖሮ በአሁኑ ወቅት ሁለት ወይም ሶስት ጠንካራ ፓርቲዎች ይኖሩን ነበር ብለዋል፡፡

“ቴአትረ ቦለቲካ፡ አሉባልታና የአገራችን ፖለቲካ ገመና” የተሰኘ ሶስተኛ መፅሃፋቸው በቅርቡ እንደሚወጣ የጠቆሙት አቶ ልደቱ፤ መፅሃፉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሉባልታዎች ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ተናግረዋል፡፡ አሉባልታ የተቃውሞ ጎራውን ትግል ክፉኛ እንደጎዳውም ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል፡፡

ልጅ ወልዶ የመሳም ፍላጎት አንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሊያገኛቸው ከሚጓጓላቸው ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ልጅ የማግኘት ጉጉት በተለያዩ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሊስተጓጎል አልፎም መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡   
የአለም የጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2010ዓ/ም ባወጣው ጥናት መሰረት በአለማችን ላይ ቁጥራቸው 48.5 ሚሊዮን የሚገመት ጥንዶች የዚህ የማሀንነት ችግር ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ የተደረገው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1990-2010/ አመተ ምህረት በ190/ የተለያዩ ሀገሮች ነው፡፡ በጥናቱም በ1990/ ዓ/ም 42.2/ ሚሊዮን የነበረው የመሀንነት ችግር ያለባቸው ጥንዶች ቁጥር በ2010/ ዓ/ም 48.5/ ሚሊዮን መድረሱን ጠቁሟል፡፡
በዛሬው ፅሁፋችን በተፈጥሮ ከሚከሰተው መሀንነት ውጪ ከአኗኗር እንዲሁም ከመድሀኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሀንነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች በሚመለከት የባለሙያ ማብራሪያ አካተን ያጠናቀርነውን ፅሁፍ እንዲህ ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡
ለዛሬ ያነጋገርናቸው ባለሙያ ዶክተር አበበ ሀይለማሪያም ይባላሉ፡፡ ዶክተር አበበ በዘውዲቱ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ሀኪም ናቸው ለመሆኑ በህክምናው ሳይንስ መሀንነት እንዴት ይገለፃል? በቅድሚያ ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡
“...ሁለት ጥንዶች ምንም አይነት የእርግዝና መከላከያ ሳይወስዱ በተገቢው መጠን የግብረስጋ ግንኙነት እያደረጉ ቢያንስ ለአንድ አመት መውለድ ካልቻሉ መሀንነት ይኖራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን መከላከያ ሳይወስዱ መውለድ አለመቻላቸው የመሀንነት ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል እንጂ መሀንነት ነው ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ መሀንነት መሆኑን ለማረጋገጥ የተለያዩ ምርመራዎች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡”
የወር አበባ ኡደት መዛባት፣ ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረ የአባላዘር በሽታ በማህጸን ቱቦ ወይንም በህክምናው fallopian tube ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ትቶት የሚያልፈው ቋሚ የሆነ ጠባሳ  መሀንነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ ዶክተር አበበ፡-
“በሴቶች በኩል መሀንነትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የእድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንቁላል የሚያመነጩት እጢዎች እድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር ቀደም ሲል ያመነጩ የነበረውን ያህል እንቁላል ላያመነጩ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ እድሜ ትልቁና ዋነኛው ምክንያት ነው ማለት እንችላለን፡፡ የወር አበባ ኡደት ሲዛባም የሴቷ እንቁላል ላይመነጭ ይችላል ወይም ደግሞ እንዳስፈላጊነቱ ጊዜውን ጠብቆ ላይመጣ ይችላል፡፡ ከዛ ውጪ ከተለያዩ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም የአባላዘር በሽታዎች የተነሳ የማህፀን ቱቦ መዘጋት ሊኖር ይችላል ይህም የሴቷን እንቁላልና የወንዱ የዘር ፍሬ በተገቢው መንገድ እንዳይገናኙ ሊያደርግ ስለሚችል ለመሀንነት አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተፈጥሮ ለመራባት የሚያስፈልጉ አካላት ላይኖሩ ይችላሉ እሱም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ሌሎች እንደ ቲቢ ያሉ በሽታዎችም ማህፅን አካባቢ ከሚፈጥሩት ችግር የተነሳ ፅንስ እንዳይፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡”
በዝርዝ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪም የተለያዩ መድሀኒቶች ከመውሰድ ለምሳሌ ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘ ለረዥም ጊዜ መውሰዱ መድሀኒቶች በሴቷ በኩል መሀንነትን ሊያመጡ እንደሚችሉ ዶክተር አበበ ይገልፃሉ፡፡
“...ለመሀንነት የሚያጋልጡ የተለያዩ መድሀኒቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የደም ግፊት መድሀኒቶች ለመሀንነት የሚያጋልጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ማለት ሁሉም የደም ግፊት መድሀኒቶች ለመሀንነት ያጋልጣሉ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ መድሀኒቶች በውስጣቸው የያዙት ንጥረነገር ለመሀንነት የሚኖረውን ተጋላጭነት የሚጨምሩበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ ለአእምሮ ህመም ለረዥም ጊዜ የሚወሰዱ መድሀኒቶችም በተመሳሳይ ለዚህ ችግር ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው እንደዚህ አይነት መድኒቶች በሀኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ ስለሆኑ ይህን አይነቱን ችግር እንደሚያስከትል ከታወቀ ባለሙያው ሌሎች መድሀኒቶችን ሊያዝ ይችላል፡፡
በተለምዶ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ወይም መርፌ ለዚህ ይዳርጋል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ነገርግን በህክምናው ሳይንስ የዚህ አይነት አመኔታ የለም፡፡ ማለትም ይህን በሚመለከት በተደረጉት የተለያዩ ጥናቶች የዚህ አይነት መድሀኒቶች መሀንነትን እንደማያመጡ ተረጋግጧል፡፡”
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ምክንያቶች በሴቶች በኩል መሀንነትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ይሁኑ እንጂ ለመሀንነት ሴቷም ሆነች ወንዱ ተመጣጣኝ የሆነ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል ዶክተር አበበ፡፡
“...በአብዛኛው ከወንዱም ከሴቷም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ወንዱ ከ30-50% ወይም በአማካኝ 40% የወንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይ የተቀረው 40% በሴቷ በኩል የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ከሁለቱም ምክንያት ሊሆን የሚችልበት 10% ይሄ ነው ተብሎ የማይገለፅ ደግሞ 10% ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ መሀንነት ምክንያቱ በአንድ ወገን ነው ብሎ መደምደም አይቻለም፡፡”
ቀደም ሲል ባለሙያውም እንደ ገለፁት ምንም እንኳን ወንዱ እንዲሁም ሴቷ ለመሀንነት ያላቸው አስተዋፅኦ በመቶኛ ደረጃ ይለያይ እንጂ መሀንነት በሴቶች ብቻ ሳይወሰን በሁለቱም ፆታዎች ላይ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ መሀንነት በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት ችግር አድርጎ የማሰብ የቆየ ልማድ አለ፡፡ ይህም የህክምናው ሳይንስ ከሚለው ፈፅሞ የራቀ ነው እንደ ማብራሪያው፡፡
“...በተለይ እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች መሀንነት የሴቷ ችግር ብቻ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ይህ የሆነበት የተለያዩ ባህላዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ አመለካከቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላውና ለዚህ አይነቱ አመለካከት መንስኤ የሚሆነው ደግሞ ችግር ሲኖር ሁለቱም ጥንዶች በጋራ ሆነው ህክምናቸውን ለመከታተል የሚኖራቸው ተነሳሽነት ነው፡፡ በአብዛኛው ይህ የመሀንነት ችግር ሲከሰት ሴቶች ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋም ይመጣሉ፡፡ አብዛኞቹ ወንዶች ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆኑም ስለዚህም ሴቷ እንደ ምክንያትነት ትጠቀሳለች፡፡ ነገር ግን መሀንነት በተመጣጣኝ ሁኔታ በወንዱም ሆነ በሴቷ ላይ ሊከሰት የሚችል ችግር ነው፡፡”
መሀንነት በተፈጥሮ እና በአንዳንድ የጤና ችግሮች የሚከሰት ቢሆንም ከአኗኗር እንዲሁም ከመድሀኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ መሀንነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች አሉ፡፡
“...ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ተፈጥሯዊና እንደ አባላዘር ያሉ በሽታዎች ለመሀንነት ሚዳርጉ ዋነኛ ምክንያቶች ይሁኑ እንጂ ከዛ ውጪ ሌሎች ከአመጋገባችን ወይም እለትተለት የምናደርገው እንቅስቃሴ ለመሀንነት የሚኖረንን ተጋላጭነት ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አመጋገብን ብንመለከት አንዳንድ ሴቶች የሰውነታቸው ክብደት በጣም ዝቅተኛ ይሆንና ሰውነታቸው የሚፈለገውን ንጥረ ነገሮች በተገቢው መንገድ ላያገኝ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የወር አበባ መዛባትን አንዳንዴም ጭርሱንም እንዲቀር ሊያደርገው ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ልጅ ለመውለድ የሚኖረውን ሁኔታ ሊያዘገይ ወይም መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡”
የሴቷ የሰውነት ክብደት ጤናማ የሚባለው ምን ያህል እንደሆነና የክብደት መቀነስ የሚለው ቀደም ሲል ከተጠቀሰው የወር አበባ መዛባትን ከማስከተሉ ባለፈ መሀንነትን ሊያስከትል የሚችልባቸውን መንገዶች ዶ/ር አበበ እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡   
“..አንዲት ሴት በአማካኝ ሊኖራት የሚገባው የሰውነት ክብደት ሀምሳ ኪሎ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ክብደቷ ከዛ በታች ከሆነ ይህ የክብደት ማነስ ለወር አበባ መዘግየት ብቻም ሳይሆን ከአእምሮ የሚመነጩ የተለያዩ ኬሚካሎች በተገቢው መጠን እንዳይመነጩ ሊያደር ይችላል፡፡ ይህም የሴቷ እንቁላል ከዘር ማፍሪያ እጢ ፅንሱ እስከ ሚፈጠርበት የማህፀን ክፍል የሚኖረው መንገድ ላይ ተፅእኖ ሊፈጥር ስለሚችል በዚህ ሁኔታ መውለድ ሊዘገይ ወይም መሀንነት ሊከሰት ይችላል፡፡”   
መሀንነትን በሚመለከት በህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ለዘመናት የመሀንነት መንስኤ ናቸው ተብለው በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል መሀንነትን በዘር የሚመጣ ችግር አድርጎ ማሰብ አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች ከቤተሰብ አባላት መካከል አንዳቸው ይህ የመሀንነት ችግር ሲገጥማቸው “ኧረ እኛ በዘራችን መሀንነት የለም...” ሲሉ የሚደመጡት፡
“..ሁሉም የመሀንነት ችግር በዘር የሚመጣ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም በተወሰነ ደረጃ ከዘር ጋር የሚያያዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ቀደም ሲል ጠቅሼዋለሁ ለመሀንነት ሚያጋልጡ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የተለያዩ genetic disorder ወይንም በዘር የሚወረስ የተፈጥሮ መዛባት የምንላቸው ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡
ይህ ማለት አንዳንድ ጊዜ  በተፈጥሮ ለመራባት የሚያስፈልጉት ህዋሶች (Gene) በሰውነታችን ውስጥ ላይገኙ ይችላሉ ወይም ደግሞ ባላስፈላጊ ሁኔታ ተባዝተው ሊገኙ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ የዚህ አይነት ምክንያቶች ለመሀንነት የሚዳርጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ነገር ግን ከቤተሰብ አባላት ውስጥ የመሀንነት ችግር ተከስቶ ስለማያውቅ ወይም ይህ አይነቱ ችግር ያለበት ሰው የለም ማለት ፈፅሞ መሀንነት ሊያስከትል አይችልም ማለት አይደለም...” እንደ ዶ/ር አበበ ኃ/ማርያም የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት፡፡

የአንዲት ሴተኛ አዳሪ ኢትዮጵያዊትን የዕለት ማስታወሻ የሚተርከውና በአርታኢ ፍፁም ብርሃኔ የተዘጋጀው “ሮዛ ቁጥር ሁለት” መፅሃፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡
ነዋሪነቱ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ የሆነው የመፅሃፉ አርታኢ የባለታሪኳን ዳያሪዎች አሰባስቦ ለህትመት ለማብቃት አንድ ዓመት እንደወሰደበት ግልጿል፡፡ በዚህ መፅሃፍ የመጀመሪያው ክፍል ከአንድ ዓመት በፊት የታተመ ሲሆን ከ45ሺ በላይ ሰዎች እንዳነበቡትና መፅሃፉን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡  

በአቢሲኒያ ኢንተርቴይንመንት እየተዘጋጀ በኤፍኤም 96.3 ላይ ሲሰራጭ የቆየው የቀጥታ የስልክ መስመር የድምፅ ውድድር ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡
ለመጨረሻ ውድድር የቀረቡ አምስት ተወዳዳሪዎች በቀጥታ ከስቱዲዮ የሚያካሂዱትን የድምፅ ውድድር ለመዳኘት ታዋቂ የሙዚቃ አቀናባሪዎችና ድምፃውያን በስፍራው ይገኛሉ፡፡ በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡት ተወዳዳሪዎች የግጥም፣ የዜማና የሙዚቃ ቅንብር ሙሉ ወጪያቸው ተችሎ ነጠላ ዜማ እንዲሰሩ እንደሚደረግ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ አቶ አባተ ማንደፍሮ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
አቢሲኒያ ኢንተርቴይንመንት እስከ አሁን ድረስ በአምስት ዙሮች ባደረገው የቀጥታ ስልክ መስመር የድምጽ ውድድር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ350 በላይ ጀማሪ ድምጻውያን እንደተካፈሉ አቶ አባተ ተናግሯል፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረበት 4ኛ ዓመት በዚሁ ዕለት እንደሚከበርም ገልጿል፡፡

በድምፃዊ ዳንኤል ዘውዱ የተሰራው “የዝና” የተሰኘና ነባር ዘፈኖች የተካተቱበት የሙዚቃ አልበም በገበያ ላይ ዋለ፡፡
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የተስፋዬ ወርቅነህን ተወዳጅ ዜማዎች ሪሚክስ በማድረግና በድጋሚ በመስራት በገበያ ላይ ያዋለው ድምፃዊ ዳንኤል ዘውዱ ለዘፈኖቹ ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተገቢውን ክፍያ መፈፀሙንና የቅጂ መብቱን ጠብቆ መስራቱን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
የዘፈኖቹ ግጥሞች የተወሰነ ማሻሻያዎች እንደተደረጉባቸውና በታዋቂ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መሰራታቸውንም ድምፃዊው ተናግሯል፡፡  

ላለፉት ሃምሳ አመታት ተስለው የተጠራቀሙ የሰዓሊ ወርቁ ጐሹ የስዕል ስራዎች ለዕይታየ ማቀርቡበት “ላይት” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ የፊታችን አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ሙዚየም አርት ጋለሪ ይከፈታል፡፡
በዚህ አውደ ርዕይ እጅግ በርካታ የስዕል ስራዎች የሚቀርቡ ሲሆን የተለያዩ ጉዳዮችን እንደሚዳስሱም ተገልጿል፡፡
አውደ ርዕዩ እስከ ፌቡራሪ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ለጐብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም አዘጋጁ ጐሹ አርት ጋለሪ ከላከው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡