Administrator

Administrator

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አህያና አንድ ለማዳ ውሻ በአንድ ጌታ ቤት ይኖሩ ነበረ፡፡
አህያው ከጋጣ ውስጥ ብዙ አጃና ገብስ እንዲሁም ሳር ተደርጎለት እስኪጠግብ እየበላ ይተኛል፡፡ ትንሹ ቡችላ ውሻ ደግሞ ሳሎን ውስጥ ለእሱ በተዘጋጀለት ሶፋ ላይ ይቀመጣል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በጌታው ጭን ላይ ቂብ ይላል፡፡ ጌትዬው ምግብ የሚበላ ከሆነ ለውሻው ይቀነስና ይሰጠዋል፡፡ ወደ ውጪ ለራት የወጣ እንደሆነም በከረጢት ለውሻው ያመጣለታል፡፡ ውሻውም ጭራውን እየቆላ ይሮጥና ገና ከደጅ ይቀበለዋል፡፡
አህያው በጣም ብዙ ሥራ አለበት፡፡ ወፍጮ ቤት የሚፈጭ እህል ተሸክሞ ይሄዳል፡፡ ከተፈጨ በኋላም ተሸክሞ ይመለሳል፡፡ ወደ እርሻ ቦታም እየሄደ.፣ የተከመረ እህል በኩንታል እየተሞላ ይጫንበትና ወደ ቤት ይመጣል፡፡ ለአህያው፤ ሸክም የዕድሜ ልክ ሥራው ነው፡፡
አህያው በለማዳ ውሻው ምቾትና የቅንጦት ኑሮ በጣም ቅናት ገባውና፤
“እስከ መቼ ድረስ ነው፤ እኔ እዚህ ጋጣ ውስጥ ተቀርቅሬ የምኖረው? እስከ መቼሽ ነው እኔ እንደዚህ ውሻ ሳልንደላቀቅና ኑሮ ሳይደላኝ፣ አንድም ቀን ሳሎን ሳልገባ የምቀመጠው?” ሲል አሰበ፡፡
በመጨረሻም አንድ ቀን ተነስቶ፣ ጋጣውን ሰባብሮ ወጥቶ ወደ ጌታው ቤት አመራ፡፡ ጌትዬው እራት ሊበላ እንደተቀመጠ፣ አህያ ሆዬ ሳሎን ገባ፡፡ እንደ ውሻው ጭራውን እየቆላ፣ እንደ ውሻ “ው ው ው!” እያለ ይጮህ ጀመር፡፡ ይጎማለልና በማላገጥ መልክ ውሻው የሚያደርገውን በመኮረጅ፣ ለጌታው እንደ ቲያትር ያሳይ ገባ፡፡ ጠረጴዛውን በእርግጫ አለው፡፡ የጠረጴዛ ልብሱንም ገፈፈው፡፡ በዚህ ብቻ ባለመርካቱ፣ እንደ ውሻው ጌታው ጭን ላይ ለመቀመጥ ሁሉ ሞከረ፡፡ “የጌታዬ ጭን፤
ለውሻ ተፈቅዶ፣ እኔ ለምን እከለከላለሁ?” እያለ ጮኸ!
ይሄኔ አሽከሮቹ ጌታቸው አደጋ ላይ መሆኑን በመገንዘብ፣ በዱላ፣ በፍልጥና በጅራፍ ቀጥቅጠው ቀጥቅጠው፣ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው፣ አቁስለው፤ ወደ ጋጣው እየነዱ አስገቡት፡፡
አያ አህያ ቆሳስሎ፤ ተሰባብሮ፣ ጋጣው ውስጥ ተኝቶ እያቃሰተ፤
“አዬ! ምነው አርፌ ብቀመጥ? ምነው በተፈጥሮ የተሰጠኝን ማንነቴን አክብሩ ብኖር? በገዛ እጄ፣ ያለ ተፈጥሮዬ፣ ውሻን አክል፣ ውሻን እሆን ብዬ፣ ራሴ ላይ መዘዝ አመጣሁ!” አለ
*          *         *
ያልሆንነውን እንሁን ብለን የሌሎችን ህይወት ለመቀዳጀት መሞከር ቀቢፀ - ተስፋ ነው! ተፈጥሮአችን የማይፈቅደውን ነገር ለመሆን መዳከር ክፉ አባዜ ነው፡፡ በክህሎት የሌላውን ተፈጥሮ “ውስጤ ነው” ማለት ከንቱ ድካም ነው፡፡ ክህሎት ወይም ብቃት የራስን ትጋት የሚጠይቅ ቢሆንም ሰብዕናን፣ ሥነ ምግባርንና ተፈጥሮአዊ ማንነትን ማማከሉን መገንዘብ ያባት ነው፡፡ ማንም የማንንም ቦታ ለመተካት በቅንዓት፣ በምቀኝነትና “በምን - ይጎለኛል?” ሊያደርገው አይችልም፡፡
በሀገራችን ግን፤ ቅንዓትን ከመልካም አስተዳደር፣ ዕድልን ከጥሮ - ግሮ ማግኘት፣ እያምታታን ዘራፍ ማለት እየተለመደ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ ሌላውን ቦታ ከመመኘት ይልቅ ኃላፊነትን መወጣት ነው ዋናው ጉዳይ! በውስጥና በውጪ ኦዲተር የሚመጣብንን ሪፖርት በተግባር ምን ይሁን? ምን እርምጃ እንውሰድ ማለት ተገቢ ነገር ነው! ችግሮቻችን ብዙ ናቸው፡፡ የማስተር ፕላን ጣጣ፡፡ ያላግባብ መሬት መያዝ፡፡ በተሰጠን ቦታ ላይ ግንባታ አለማካሄድ፣ ለባለስልጣናት የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም “እኔ ታክስ ከፋይ ነኝ” (I am a tax - payer) ከሚለው ህዝባዊ አስተያየት ጋር አለማዋሃድ፡፡ ፍትሕ ተዛባ፣ ህጋዊነት ጠፋ … የሚልና ጩኸት የሚሰማ ጆሮ መጥፋት፡፡ የዲሞክራሲ በወገናዊነት እንደ አሸቦ ተሸብቦ መቅረት፡፡ የመልካም አስተዳደር ሽባ ሆኖ በከዘራ መሄድ፡፡ ምኑ ቅጡ፡፡ ዛሬ ደግሞ የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ማገርሸት! የጎረቤት አገርን እብሪት ለመግታት በማቴሪያል፣ በሰው ኃይል፣ በፋይናንስ የምናወጣው ወጪ ጎጂነት የትየለሌ ነው፡፡ ሲሆን ሰላምን የማስፈን የሞራል ዋጋ በከፈልን ደግ ነበር፡፡ “ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት መስጠት” ካልንም፣ ትንኮሳው ከባላንጣችን መምጣቱን አመላካች ነውና ሁሉን በወጉ መያዝ ይጠበቅብናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው!
አንድ አዛውንት ከዓመታት በፊት፣ በመጀመሪያው ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት፤ የትግራይ ሰው ሆነው በኤርትራዊ ድምፃዊ ዘፈን ሲደንሱ ታዩ፡፡
“እንዴት ጦርነቱ ሊጀመር አንድ ሃሙስ ሲቀረው፣ በኤርትራዊ ዘፋኝ እስክስታ ይወርዳሉ?” ቢባሉ፤
“አይምሰላችሁ፡፡ እዚህ ድንበር ላይ የጀርመን ግንብ እንኳ ቢገነባ፣ የሙዚቃ ካሴት መቀባበያ ትንሽ መስኮት ትኖራለች” አሉ ይባላል፡፡
የሁለቱ ህዝቦች ባህላዊ ትሥሥር ምንጊዜም ይኖራል ማለታቸው ነው፡፡ ይህን ዕውነታ ማንም አይክደውም፡፡ የጎረቤት አገር አምባገነን መሪ ምንም አቋም ይውሰድ ምንም፣ “ወረራ ውስጤ ነው፡፡ ማስወረርም ውስጤ ነው!” ቢልም እንኳን፤ የሁለቱ አገር ህዝቦችን ትሥሥር መናቁ ነውና፣ አስተሳሰቡ በማናቸውም መንገድ መሻር አለበት፡፡ ስለሆነም፤ “ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፡፡ እሷኑ ለማጥፋት ይተሻሻል” የሚለው ተረት የእሱ ይሆናል!

Saturday, 18 June 2016 12:47

የዘላለም ጥግ

ስለ ጦርነት
• ሁለቱ እጅግ ኃያል ጦረኞች፡- ትዕግስትና ጊዜ
ናቸው፡፡
ሊዮ ቶልስቶይ
• ከአንድ ጠላት ጋር በተደጋጋሚ መዋጋት
የለብህም፤ አለበለዚያ የውጊያ ጥበብህን
በሙሉ ታስተምረዋለህ፡፡
ናፖሊዮን ቦናፓርቴ
• በጦርነት የሚገደሉት በህይወት ያሉት ብቻ
አይደሉም፡፡
አይሳክ አሲሞቭ
• ጦርነት የውድመት ሳይንስ ነው፡፡
ጆን አቦት
• ሽማግሌዎቹ ጦርነት ያውጃሉ፡፡ የሚዋጉትና
የሚሞቱት ግን ወጣቶቹ ናቸው፡፡
ኸርበርት ሁቨር
• ጦርነትን የሚጀምሩት ወታደሮች አይደሉም፤
ፖለቲከኞች ናቸው፡፡
ዊሊያም ዌስትሞርላንድ
• ጦርነትን ካላጠፋን፣ ጦርነት ያጠፋናል፡፡
ኤች.ጂ.ዌልስ
• ጦርነት ሌቦችን ይፈጥራል፤ ሰላም
ትሰቅላቸዋለች፡፡
ጆርጅ ኸርበት
• ጦርነት ለሰው ልጅ ሽንፈት ነው፡፡
ዳግማዊ ፓፕጆን ፖል
• ጦርነትን መከላከያው እርግጠኛ መንገድ
አለመፍራት ነው፡፡
ጆን ራንዶልፍ
• ግን መቼ ነው መሪዎቻችን የሚማሩት -
መልሱ ጦርነት አይደለም፡፡
ሔለን ቶማስ
• ከሌሎች ጋር በጦርነት ውስጥ ያሉ ሰዎች
ከራሳቸው ጋር ሰላም አይደሉም፡፡
ዊሊያም ሃዝሊታ

    በአቶ ሐይሉ ገ/ሕይወትና በሼል ኢትዮጵያ ወይም ኦይል ሊቢያ መካከል ስለነበረው ሁኔታ አቶ አብዱልመሊክ ሁሴን በተባሉ ሰው ወይም ስም የተፃፈውን አቤቱታ ተመልክተነዋል፡፡ የአቶ አብዱልመሊክ ሁሴን አቤቱታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ “በግልፅ ደብዳቤ” የተፃፈ ሲሆን ዋናው ዓላማው አቶ ሐይሉ ገ/ሕይወት በሼል ኢትዮጵያ ወይም ኦይል ሊቢያ “የተነጠቁትን ቦታ” ማስመለስ ነው፡፡ አቶ አብዱልመሊክ፤የአቶ ሐይሉ የሕግ አማካሪ ወይም ጠበቃ ወይም ጋዜጠኛ ይሁኑ በግልፅ ባናውቅም ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ቢሆኑ እንኳን ማንሳት የሚገባቸውን ቁልፍ ጥያቄ ሳያነሱ አገር ምድሩን ወንጅለዋል፡፡ ለነገሩ ቁልፉ ጥያቄ ከተነሳ አቤቱታው አያስፈልግም ወይም እዚያው መልስ ያገኛል፡፡ ስለዚህ አማራጭ ሆኖ ያገኙት ዙሪያውን መወንጀል ነውና ይህንኑ አድርገዋል፡፡
ለመሆኑ አቶ ሐይሉ ተወሰደባቸው የተባለው ቦታ የተጠቃሚነት መብት ቀድሞ የነበረው ማነው? ሼል ኢትዮጵያ ለዓመታት ሲገለገልበት በነበረው ቦታ ላይ የሼልን መሠረተ - ልማት ተጠቅመው ነዳጅ ማከፋፈል ጠይቀውና ተፈቅዶላቸው የመጡ ሰው ናቸው፡፡ በአጭር አገላለፅ አቶ ሐይሉ የነዳጅ ወኪል ለመሆን ጠይቀው በተፈቀደላቸው መሠረት ነው ከሼልም ከቦታውም ጋር ግንኙነት የፈጠሩት፡፡ ከዚያ ቀድሞ ለዓመታት ሼል ኢትዮጵያ በቦታው ላይ ማደያ ገንብቶ ሲሰራ ነበር፡፡ አሁንም ሼል ኢትዮጵያን የገዛው ኦይል ሊቢያ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን ጥሬ ሀቅ ደብቀው ነው አቶ አብዱልመሊክ ያለ ይሉኝታና ያለ ሀፍረት የስንቱን ስም ያጠፉትና የወነጀሉት፡፡ የሕግ ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎች ተጨማሪ ሀቆችን ለግልፅነት እናንሳ፡፡
የዚህ የማደያ ቦታ ባለቤት አቶ አሰፋ መንገሻ ይባላሉ፡፡ በንጉሱ ዘመን መሬት የግል ሃብት የነበረበት ጊዜ ስለሆነ ሼል ኢትዮጵያ ከአቶ አሰፋ መንገሻ ባዶ መሬት በመከራየትና ማደያ በመገንባት ስራውን ማካሄድ ጀመረ፡፡ በመካከል ደርግ ወደ ስልጣን መጣ፡፡ እናም የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ያደረገውን አዋጅ ቁጥር 47/1967 አወጀ፡፡ መሬቱንም ወረሰ፡፡
የነዳጅ ማደያ ስራን ያለ ቦታ ማከናወን ስለማይቻል፣ ይህንኑ በመረዳት ነዳጅ ማደያዎችን ብቻ የተመለከተው መመሪያ በደርግ መንግስት አማካይነት ወጣ፡፡ በዚሁ መሠረት ሼል ኢትዮጵያ በቦታው ላይ የመስራት ህጋዊ መብት እንደማንኛውም የውጭ ኩባንያ አገኘ፡፡ እናም ስራውን ቀጠለ፡፡ አቶ ሐይሉ ወደ ሼል የመጡት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ደምበኛ በማደያው ነዳጅ የማከፋፈሉን ስራ ከሼል ጠይቀው፣ በ1971 ዓ.ም ከተፈቀደላቸው በኋላ የሽያጭ ወኪልነት ውላቸው እየታደሰ ንግድ ፈቃድ አውጥተው በወኪልነት ሲሰሩ፣ማደያውን በህገ ወጥ መንገድ የተቆጣጠሩ መስሏቸው፣ በገዛ ፍቃዳቸውን ውሉን በ2001 ዓ.ም እስኪያቋርጡ ድረስ ሰርተዋል፡፡ በእነዚህ አመታት እንደ ሌሎቹ ማናቸውም የቆዩ ወኪሎች ኩባንያውን ወክለው ከሦስተኛ ወገን ጋር ግንኙነት ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ አቶ ሐይሉ የቦታው ሕጋዊ ባለቤት ነኝ በማለት ስውር ደባ የጀመሩት፡፡ ዝርዝሩን እዚህ መግለፅ የማንፈልገውን የተለያየ መንገድ በመሄድ፣የቦታው ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሁሉም ግን ሕገወጥ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አቶ ሐይሉ ከወረዳ አስፈፃሚዎችና ፈፃሚዎች ጋር በመመሳጠር፣ ኩባንያው ሳያውቅ ውዝፍ ግብር በፍርድ ቤት ተገደው እንዲከፍሉ የተደረገበትን ድራማ ሌላ ጊዜ በስፋት ማቅረብ የምንችል መሆኑን ለአንባብያን እንገልፃለን፡፡
ሊቢያ ኦይል ኢትዮጵያ ሊሚትድ፤ ይህ ድርጊት ህገወጥ እንደሆነና ከድርጊታቸውም ተቆጥበው ከኩባንያው ጋር እንደ ከዚህ በፊቱ በሰላም እንዲሰሩ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም፣ ይባስ በለው ኩባንያው መሳሪያዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካላነሳ፣ተጠያቂ እንደማይሆኑ ማስጠንቀቂያ ላኩ፡፡ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ኩባንያው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ የተገደደው፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ከአቶ አሰፋ መንገሻ በደርግ ከተወረሰ በኋላ ቦታው የመንግስት ነው፡፡ ሼል ኢትዮጵያ ድሮም የእሱ አልነበረም፡፡ ቀጥሎም የእሱ አልነበረም፡፡ መሬት፣ የመንግስት ነውና፡፡ የመገልገል መብቱ ግን ያኔም የተረጋገጠ ነው፡፡ አሁንም በእጁ ያለ ነው፡፡ አቶ ሐይሉ በውክልና ከተጠጉ በኋላ ስር ለስር በሰሩት ስራ አጽመ-ርስታቸው ሊያደርጉት አሰቡ፡፡ አልተሳካም፣ ሊሳካም አይችልም፡፡ ሕግና ስርዓት ያለበት ሀገር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች (በሁሉም ደረጃ የሚገኙት) የአቶ ሐይሉን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የኦይል ሊቢያን የተገልጋይነት ባለመብትነት በፍርዳቸው አረጋግጠዋል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎትም ውሳኔዎቹ የሕግ ስህተት እንደሌለባቸው አረጋግጧል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አቶ አብዱልመሊክ፤ጥቂት ማጣራት ሳያደርጉ ሌላ ሕገወጥ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ አቶ አብዱመሊክ፤ ለስግብግብና ሕገወጥ ፍላጐት መሟላት ሲሉና ምንም ሳያፍሩ በኢትዮጵያ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ሁሉ በወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የሚል የክስ ማዳበሪያ ይዘወ ቀርበዋል፡፡ ሀገሪቱ እጆቿን ዘርግታ የጋበዘቻቸውን የውጭ ኢንቨስተሮች፤ ሽፍታና ወራሪ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሁሉ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ፣ስራ አላሰራ ብለዋል ለማለትም በቁ፡፡ በሚያሳፍር ሁኔታ የሊቢያ ሕዝብ ተባብሮ ያስወገዳቸውን አምባገነኑን መሀመድ ጋዳፊን ዋቢ በማድረግ ኦይል ሊቢያን በጋዳፊ ስም እስከ መወንጀልም ደርሰዋል፡፡ የሚገርመው ነገር አቶ አብዱልመሊክ ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነትም አንስተዋል፡፡
መርምሮ ደባቂ ነው ወይስ መርምሮ አጋላጭ ነው? እንዴትስ ነው አንድ መርማሪ ጋዜጠኛ ኦይል ሊቢያ፣ የሊቢያ ኩባንያ ስለሆነና ሊቢያን ያስተዳድሩ የነበሩት ጋዳፊ ስለነበሩ፣ ሼልን መግዛቱ አግባብ አይደለም ብሎ የሚነሳው? እውነቱን ለመናገር ለጋዳፊ የሚቀርበው የትኛው አስተሳሰብና ተግባር ነው?
አቶ አብዱልመሊክ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነትም አንስተዋል፡፡ ትክክለኛው ኪራይ ሰብሳቢነት የተፈፀመበትን ጉዳይ ደብቀው፣ ሌሎችን ለመወንጀል ሲጣጣሩ፣ የኪራይ ሰብሳቢዎች የዘመኑ ፋሽን መሆኑን በሚገባ አረጋግጠውልናል፡፡ የማይመለከታቸውን፣ የእርሳቸው ያልሆነውን ቦታ በአቋራጭ ለመንጠቅና ለመክበር ከተደረገው የአቶ ሐይሉ እንቅስቃሴ በላይ ምን ኪራይ ሰብሳቢነት አለ? ከአባት ያልወረሱትን፣ ከሌላ ሰው ያልገዙትን፣ በስጦታ ያላገኙትን የመንግስት ቦታ፤ሼልን ተጠግተው በውክልነት ሲገለገሉ፣ የከፈሉትን ግብር ብቻ መነሻ አድርገው ቦታውን ጠቅልዬ ልውሰድ የሚሉትን ሰው አቤቱታና ክስ፣ በየደረጃው ውድቅ ያደረጉት የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ሁሉ፣ በአቶ አብዱልመሊክ ኪራይ ሰብሳቢ ተብለዋል፡፡
ስለዚህ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ፀሐፊው፤ ሼል ኩባንያ በአስተዳደር በኩል መሄድ ሲያቅተው ፍርድ ቤትን አቋራጭ መንገድ አድርጐ የፈለገውን ማስፈፀም እንደቻለ ማቅረቡ የፍርድ ቤቶችን ክብር፣ ህልውና፣ ሥራ እጅጉን ይነካል፡፡ ፍርድ ቤቶች በማንም የሚመሩ፣ የማንንም ጉዳይ አስፈፃሚ ናቸው ማለቱ ነው? ስለሆነም ፍትህ በኢትዮጵያ የለም እያለ ነው? ደግሞስ የወረዳና የክፍለ ከተማ አስፈፃሚዎች ውሣኔ፣ የመጨረሻ ውሳኔ ይሁን እያለ ነው?
ጋዜጣውስ ምን እያደረገ ነው? ያስተናገደው ፅሁፍ ነፃ አስተያየት ነው? የመርማሪ ጋዜጠኛ ሪፖርት ነው? የጠበቃ አቤቱታ ነው? ምንድነው? ሦስተኛ ወገንን በቀጥታ የሚወነጅል ሀሰተኛ መረጃ ሲቀርብ ማጣራት የለበትም? ፍሬ ጉዳዩ፣ ሂደቱ፣ ውሳኔው በማይታወቅ መደምደሚያ፡-
የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ሀገር እያጠፉ፣ የዜጐችን መሬት እየቀሙ ነው፤
ፍርድ ቤቶች በማያገባቸው ጉዳይ እየገቡ፣ የዜጐችን ባለመብትነትና መንግስትን ስራ እያወኩ ነው
ሼል ኢትዮጵያ አለማቀፍ አጭበርባሪ ነው፣
ኦይል ሊቢያ ከጋዳፊ ሀገር ስለመጣ፣ሼልን እንዲገዛ ሊፈቀድለት አይገባም ነበር----
የመሳሰሉ አሳፋሪና ሕገወጥ ማጠቃለያዎች፣እንዴት ጉዳይ ሆነው በጋዜጣው ላይ ወጡ? ኦይል ሊቢያ ሕግና ስርዓት ባለበት ሀገር እየሰራ ይገኛል፡፡ ሕግና ስርአትንም አክብሮ ይሰራል፡፡ መብቱንም እንደዚሁ በሕግና ስርአት ያስከብራል፡፡

• ልብ አንጠልጣይ ታሪክንና ትልልቅ ሃሳቦችን ያስታረቀች ደራሲ
• ለዘመናችን ቀውሶች ሁነኛ መፍትሔዎችን አቅርባለች

“እስቲ በአንድ ሺ ኮፒ አትመን እንሞክረው” ተብሎ የተጀመረው የሃሪ ፖተር ታሪክ፣ በህትመትና በሽያጭ ብዛት... አቻ ያልተገኘለት ዝነኛ ታሪክ ሆኗል፡፡ ግማሽ ቢሊዮን ኮፒ ሊደርስ ምን ቀረው! “ለማንኛውም፣ የቀን ስራ ብታፈላልጊ ይሻላል” የተባለችው ደራሲ፤ በአለም የመጀመሪያዋ ቢሊዬነር ደራሲ ሆናለች - ጄኬ ሮውሊን።
በድርሰቶቿ ውስጥም፣ የ“ተዓምረኛ ሰዎችን” ታሪክ ነው የምታስነብበን። እምቅ የተፈጥሮ አቅማቸውን ካዳበሩ፣ ትንግርተኛ ብቃት ሊቀዳጁ የሚችሉ፣ የአስር ዓመት ልጆች... ናቸው ዋናዎቹ ባለታሪኮች። በምናብ በማሰብ ብቻ አገር ምድሩን የሚያንቀጠቅጡ ፣ ጥቂት ቃላትን በማነብነብ አዳራሹን በጣፋጭ ምግብ የሚሞሉ፣ ስንዝር የምታክል ብትር በማወዛወዝ ብቻ መብረቅ የሚያወርዱና እንደ ንስር የሚበርሩ፣ ብርጭቆ እግር አውጥቶ እንዲራመድ ነፍስ የሚዘሩ፣  ቅጠል ስራስር፣ ጨውና ምናምን አዋህደው በአንድ ጠብታ በሽታን የሚፈውሱ ወይም አገርን የሚያቃጥሉ... እንዲህ አይነት ብቃት፣ በእርግጥም ትንግርት ነው፡፡ ግን ምሳሌያዊ ትርጉሙንም ስንመለከትስ?
አለምን የሚቀይሩ ትልልቆቹ የለውጥ ማዕበሎች፣ ከጥቂት ሰዎች ምናብ ውስጥ የተፈለፈሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ወይም ከጥቂት ብሩህ አእምሮዎች የፈለቁ ትክክለኛ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በመፃሕፍት ውስጥ የሰፈሩ፣ በንግግር የሚደመጡ ቃላት፣…እውቀትን ወይም ጭፍንነትን በማስፋፋት አለምን የሚያስደንቅ አዲስ ታሪክ ይፈጥራሉ - ለክፉም በደግም፡፡
መቶ ሺ ኩንታል ጭነት፣ ውቅያኖሶችንና በረሃዎችን አቋርጦ የሚጓዘው… በመርከብና በባቡር ሹፌሮች ጥቂት የእጅ እንቅስቃሴ አማካኝነት ነው፡፡ ጣታችንን ሞባይል ላይ በማንሸራተት ስንት ተዓምር መስራት እንችል የለ? እንዲያውም፣ ስንለምዳቸው፣ ተራ ነገር ይመስሉናል እንጂ፣ የሰው ልጅ፣ አጀብ የሚያሰኙ ብቃቶች አሉት፡፡ እነዚህን ብቃቶች ነው በሀሪ ፖተር ታሪኮች ውስጥ በምሳሌያዊ አገላለጽ የምናገኛቸው፡፡
ግን፣ በዋዛ አይደለም፣ እንዲህ አይነት ብቃት ላይ የሚደረሰው። አእምሮን ተጠቅሞ መማር፣ ማጥናት፣ መመርመርና ማወቅ ያስፈልጋል። ሳይታክቱ መሞከር፣ መለማመድ፣ መስራት....
ግን፣ ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። በእርግጥ፣ ከአላዋቂነትና ከጭፍንነት ይልቅ፣ አስተዋይነትንና ለመቀዳጀት መትጋት፣ አዋቂነትን... ከስንፍናና ከገልቱነት ይልቅ... ችሎታንና ሙያን ለማዳበር መጣጣር፣ አንድ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን፣ በእውቀቱና በችሎታው አማካኝነት፣ ዋጋ ያለው ጠቃሚ ነገር ለመስራትና ስኬት ላይ ለመድረስ የማይጣጣር ከሆነ፣ ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ጭራሽ፣ ለመጥፎ አላማም ሊያውለው ይችላል - ሰዎችን ለማታለል፣  የስራ ውጤታቸውን ለመዝረፍ፣ ህይወታቸውን ለማጥፋት ወዘተ፡፡ በስኬት መንገድ መጓዝ፣  አልያም ስኬትን በሰበብ አስባቡ እያጣጣሉ በከንቱ መንዘላዘል፣ ወይም በዝርፊያ ጉራንጉር ውስጥ መደናበር... የእያንዳንዱ ሰው ምርጫ ነው።
ግን፣ እያንዳንዱ ምርጫ... ከእለት እለት ሲደጋገም፣ የየራሱ ውጤትና መዘዝ አለው፡፡ በዚህም የእያንዳንዱ ሰው ‘ማንነት’ ይቀረፃል፣ ይሸረሸራል ወይም ይጣመማል። እንደየምርጫው፣ ከቀን ወደ ቀን፣… እየጠነከረ፣ እየተልፈሰፈሰ ወይም እየደደረ የሚሄድ የተለያየ ‘ሰብእና’ ይፈጠራል።
በአንድ በኩል፤ በራሱ ብቃትና ማንነት የሚተማመን፣ መልካምና ቀና ሰብእና ይኖራል፡፡ ይሄ ሰዎችን በተግባራቸውና በባሕርያቸው የሚመዝን ፍትህን የሚወድ ስብዕና ነው - ጥሩ ሰዎችን የሚያደንቅ የፍቅር ሰብዕና
በሌላ በኩል፤ በአቅመ ቢስነት  የሚንከላወሱ፣ የሰው ፊት እያየ ወዲህና ወዲያ የሚወዛወዝ ደካማና አስመሳይ ሰብእና ይኖራል፡፡ ይሄ፣ ሰዎችን የሚመዝንበት አንዳች ሚዛን የለውም፡፡ ከመንጋው አቧራ ጋር፣ ከአውራው ጩኸት ጋር፣ ከሰፈሩ ሆይሆይታ ጋር አብሮ የሚነፍስ ገለባ ነው። ጭፍን ቲፎዞ ስለሆነ፤ በዘር ሲያቧድኑት ይቧደናል፤ በሃይማኖት ሲያቧድኑትም እንደዚሁ። ይሄ አስቀያሚ ርካሽ ሰብዕና ነው።
ሌላ ደግሞ አለ - በጥላቻና በምቀኝነት ስሜት የሚንቀሳቀስ፣ ሰዎችን በማሰቃየትና በመግዛት እርካታ ለማግኘት የሚመኝ ጠማማ እኩይ ሰብእና። በአጥፊ የጭካኔ ተግባሩ፣ በእኩይ የምቀኝነት ባሕሪው...ምክንያት ውግዘት አይደርስበትም? ሊደርስበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ማምለጫና ማመካኛ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ ደግሞም መንገድ አያጣም። እያንዳንዱ ሰው፣ እንደየ ተግባሩና እንደየ ባሕሪው እንዳይመዘን ማድረግ ነው - ዘዴው፡፡ ማለትም፣... ሰዎችን በዘር ማቧደን፣ በሃይማኖት ማቧደን፣ በሃብት ልዩነት ማቧደን ...!
የእኩልነት ማመካኛ ዘዴዎችን…እናውቃቸዋለን?
ሰዎችን በጅምላ ማቧደን ከቻለ፣ በቃ፣ የቱንም ያህል ጥፋት ቢፈፅም፣ የቱንም ያህል እኩይ ቢሆን፣ “ወገናችን” ብለው በጭፍን የሚቀበሉት ሰዎችን አዘጋጀ ማለት ነው። ቀን ከሌት አሉቧልታ የሚያናፍስ፣ ፕሮፖጋንዳ የሚነዛ፣ ዝባዝንኬ የሚያወራ ውሸታም ቢሆንም እንኳ፤ አጨብጫቢ እንደማያጣ ያውቃል፡፡ ንብረት ቢዘርፍ ወይም ቢያቃጥል፣ ሰውን ቢያሰቃይ ወይም ቢገድል... አያስጨንቀውም። ማመካኛ አዘጋጅቷል - “ለአገር አስቤ፣ ለብሔረሰብ ተቆርቁሬ፣ ለሕዝብ ወግኜ፣ ለሃይማኖት ብዬ ያደረግኩት ነው” ይላል። እንደ ወንጀለኛ ሳይሆን፣ እንደ ጀግና እንዲታይ ይጠብቃል።
የሚቃወመው ሰው ከመጣ፣ መፍትሄው ቀላል ነው፤ “የውጭ ሃይሎች ተላላኪ፣ የአገር ጠላት፣ የባዕዳን ቅጥረኛ፣ ባንዳ፣ ሰርጎ ገብ፣ ከሃዲ....” ተብሎ እንዲፈረጅ ማድረግ ይቻላል። የማይደግፉትን ሰዎች እንዲህ እያንበረከክ፣ ከነጥፋቱና ከነእኩይነቱ፣ እንዳሻው ይፈነጫል።
በእርግጥ፣ በፅናት ከተጋፈጥነው፣ እርቃኑ ተጋልጦ፣ በሽንፈት ሊፈጠፈጥ ይችላል። ነገር ግን፣ እኩይነት አንዴ ስለተከሰከሰ፣ እስከ ዘላለሙ ተሸነፈ ማለት አይደለም። ለጊዜው ይሸነፋል እንጂ፣ ጨርሶ አይሞትም። የሃሪ ፖተር ዋና ጠላት የሆነው ቮልድሞት የተሰኘው የፅልመት ጌታ፣ እንዲህ አይነት እኩይ ገፀ ባህርይ ነው። ምንም ቢሸነፍ፣ ጠፍቶ የማይጠፋ እኩይነት!
እንዴት ብትሉ፤ ..አዎ፣ አንድ እኩይ ተግባር ሊከሽፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ..እነዚያ የእኩይነት ምንጮች፣... እነዚያ የጭፍንነት፣ የጥፋትና የክፋት አስተሳሰቦች ሁሌም ይኖራሉ። ለጊዜው ተቀባይነታቸው ሊከስም ይችላል፡፡ የጠፋም ይመስላሉ፡፡ ግን አይጠፉም። በአንድ ሰው ጭንቅላት ውስጥ ተጣብቀው፣ የጭንቅላቱ ጓሮ ውስጥ ስር ሰደደው ቀስ በቀስ ነፍስ ለመዝራት ሲፍጨረጨሩ ልናገኛቸው እንችላለን፡፡ (እንዲህ አይነት ሃሳቦችን ተዓማኒ በሆነ መንገድ ወደ መሳጭ ታሪክ መቀየር ከባድ ነው፡፡ ጄኬ ሮውራን ግን በሚገርም ጥበብ ምርጥ ድርሰት ሰርታበታለች፡፡
የሃሪ ፖተር የመጀመሪያ የሞት ሽረት ትግል ከዚህ ጋር ይመሳሰላል - Harry Potter and the Philosopher’s Stone)።
የእኩይነት አስተሳሰብ፣ ለጊዜው ባይሳካለት እንኳ፣ ከአንዴም ሁለቴ ቢሸነፍም እንኳ፣ አይሞትም። እዚህኛው ወይም እዚያኛው መፅሃፍ ውስጥ አድፍጦ ይቀመጣል፡፡ ይሄ አይገርምም፡፡ በጭፍን የማመን አክራሪነትን፣ ሳያመርቱ ንብረት የመውረስ ሶሻሊዝምን፣ የጅምላ ጥላቻ ዘረኝነትን የሚሰብኩ መፃህፍት፣ ሁሌም ይኖራሉ። በእነዚህ መፃህፍት የሚመረዙ፣ የሚማረኩና የሚሰክሩ ሰዎችም ያጋጥማሉ። እናም፣ እኩይነት እንደገና ነፍስ ዘርቶ፣ ለመንገስ ጊዜ አይፈጅበትም።
መፃህፍት ውስጥ የተሰገሰጉ እኩይ አስተሳሰቦች፣ ፊት ለፊት ተጋፍጠን በትክክለኛ አስተሳሰብ አፍረጥርጠን ካላመከንናቸው፣ ብዙም ሳይቆይ፣ አገር ምድሩን የሚያናውጥ፣ በጭፍን ሁላችንንም የሚሰለቅጥ ግዙፍ አውሬ ይሆኑብናል፡፡ ይሄ በሃሪ ፖተር ሁለተኛው ታሪክ ውስጥ፣ ዋና ማጠንጠኛ ሃሳብ ነው (Harry Potter and the Chamber of Secrets የተሰኘው ሁለተኛው የሃሪ ፖተር ታሪክን ይመልከቱ።)
እኩይነት ድብቅ ሴራ ወይስ የአደባባይ ድግስ?
እኩይነት፣.. ከአንድ ሰው ጭንቅላት ላይ ተጣብቆ ወይም አንድ መፅሃፍ ውስጥ መሽጎ... ቀስ በቀስ ነፍስ ዘርቶ ሊነግስብን ይችላል ሲባል፣… “በቀላሉ የማይታይ ስውር ሴራ” ይመስላል። ግን ስውር ሴራ አይደለም። ይልቅስ፣ እኩይነት፣ በግላጭ የሚዘጋጅ ድግስ ነው።
ባለፉት መቶ አመታት፣ ዛሬም ድረስ ብዙ ቀውስንና እልቂትን እያስከተሉ የሚገኙ አመፆችን፣ ግጭቶችንና አምባገነን አገዛዞችን ተመልከቱ። ሁለተኛውን የአለም ጦርነት የለኮሱ ሦስቱ መንግስታት (የጀርመን፣ የጣሊያንና የጃፓን መንግስታት)፣ በየአገሮቻቸው የገነኑት፣ በስውር ሴራ አይደለም። “ከራስህ በፊት አገርህን አስቀድም፣ ከራስህ በፊት ብሄርህን አስቀድም” በሚል የአደባባይ መፈክር ነው፣ በአምባገነንነት ለመግዛት የቻሉት።
ብዙ ስቃይ የፈፀሙት። ከዚያም፣ ሌሎች አገራት ላይ በመዝመት፣ ከ60 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለእልቂት ዳርገዋል። በዩጎዝላቪያና በሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ድረስ በበርካታ አገራት፣ “ከራስህ በፊት ብሔር፣ ብሔረሰብን አስቀድም... በብሔረሰብ፣ በጎሳ ተቧደን”... በሚል መፈክር ብዙ እልቂት ደርሷል።
ይህም ብቻ አይደለም። “ከራስህ በፊት፣ ሌሎች ሰዎችን አስቀድም... ከራስህ በፊት፣ ሰፊውን ህዝብ አስቀድም” የሚሉ ኮሙኒስቶችና ሶሻሊስቶች፣ አለምን በደም አጥበዋል። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ጨርሰዋል።
“ከራስህ በፊት፣ የሃይማኖት ሰባኪውን አስቀድም፤... ከራስህ በፊት፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን አስቀድም” የሚሉ አክራሪዎችም እንዲሁ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ብዙ ጥፋት አድርሰዋል።
የግል አእምሮን በማጣጣል ጭፍን እምነትን እያወደሱ የሚሰብኩን የግል ንብረትን በማጣጣል፣ መስዋዕት መሆንን እያደነቁ የሚደሰኩሩብን.... የግል ማንነትን በማጣጣል በጅምላ ፍረጃ መቧደንን እያራገቡ ዘረኝነት የሚለፍፉብንኮ በአደባባይ ነው። እነዚህ የእኩይነት አስተሳሰቦች፣ ስውር ሴራዎች አይደሉም - በአደባባይ የተሰበኩ፣ የተደሰኮሩ፣ የተለፈፉ አስተሳሰቦች ናቸው - በግላጭ የቀረቡ ድግሶች።
ቅዱስ የሆኑት፣ የግል አእምሮ፣ የግል ንብረትና የግል ማንነት ደግሞ፤ እንደ መጥፎ ነገር ተቆጥረው ተንቋሽሸዋል - በአደባባይ። እኩይነት በእንዲህ አይነት “መፈንቅለ ሃሳብ” አማካኝነት እንደገና ነፍስ ዘርቶ ይነግስብናል -  ትክክለኛው እንደ ስህተት፣ ጠቃሚው እንደ ጎጂ፣ ቅዱሱ እንደ እኩይ ተቆጥሮ እንዲወገዝ፣ እንዲወነጀል፣ እንዲፈረድበት በማድረግ! ... (Harry Potter and the Prisoner of Azkaban በተሰኘው ሦስተኛው የሃሪ ፖተር ታሪክ ውስጥ፣ ይህንን ቁም ነገር አጉልቶ የሚያሳይ ተመሳሳይ ማጠንጠኛ ጭብጥ እናገኛለን)።
ምን ይሄ ብቻ!
የመደናበርና የድንዛዜ ዥዋዥዌ
“ኧረ እንንቃ፡፡ እኩይነት ነፍስ ዘርቶ እየመጣብን ነው!” ብለው እነ ሃሪ ፖተር፣ አዳሜን ለማስጠንቀቅ ሲሞክሩ፣ ብዙም ሰሚ  አያገኙም፡፡ አዎ፣ አብዛኛው ሰው፣ እኩይነት እንዳይነግስ ይፈራል፡፡ ግን በጥንቃቄ አስቦ፣ እኩነትን ለመመከት አይጣጣርም፡፡
ከዚያ ይልቅ ፍርሃትን እያግለበለበ፣ (እንደ ዶናልድ ትራም፣ ጭፍን ስሜትንና ዘረኝነት እየቆሰቆሰ) በአዳሜ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ስልጣን ለመያዝ የሚፍጨረጨር የሚደናበር ይበራከታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ፣ “የውሾን ስም ያነሳ…” እንደሚባለው፤ “እኩይነት ነፍስ እየዘራ ነው፤ ቮልድሞት እየመጣብን ነው” ብሎ በግልጽ አደጋው እንዲገለጽ የማይፈልጉ የድንዛዜ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡
ቮልድሞት የሚለውን ስም የሚተነፍስ ሰው መኖር የለበት ይላሉ፡፡ “አጅሬው”፣ “ስም አይጠሬ”፣ “ያ የምናውቀው”…በማለት ያድበሰብሱታል (እንደ ሂላሪ እና እንደ ኦባማ ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት አክራሪነት አደገኛ መሆኑን በግልጽ ለመናገር አይፈልጉም አይደል?)
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? የጄ.ኬ ሮውሊን ድርሰቶች፣ እጅግ መሳጭና ልብ አንጠልጣይ የመሆናቸው ያህል፣ በዚያው ልክ ከላይ በጠቀስኳቸው አይነት... በርካታ ጥልቅ ሃሳቦችና ጭብጦችም የበለፀጉ ድርሰቶች ናቸው።

“የኢሳያስን መንግስት ማስወገድ ያስፈልጋል”
የቀድሞ የአየር ሃይል አዛዥ ሜ.ጀ አበበ

የኢትዮጵያ መንግስት
• በከባድ ውጊያ፣ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሻለሁ
• ትንኮሳ እንዳይፈጽም ትምህርት ሰጥተነዋል
• ካለረፈ ግን፣ በተመጣጣኝ እርምጃ እንቀጣዋለን
የኤርትራ መንግስት
• ሁለት መቶ ወታደሮችን ገድያለሁ፤ አቁስያለሁ
• የአሜሪካ መንግስት ፣ እጁ አለበት፤ ጥቃት አነሳስቶብኛል
• የኢትዮጵያ ጦር ወደ ድንበር በብዛት ተሰማርቶብኛል

የኢትዮጵያ መንግስት በፆረና ግንባር ከባድ ውጊያ ተካሂዶ እንደነበር ገልፆ፣ ትንኮሳ በፈፀመው የኤርትራ ጦር ላይ ከፍተኛ የህይወት ኪሳራ አድርሻለሁ፤ እርምጃውም ለሻዕቢያ መንግስት አስተማሪ ነው ብሏል፡፡ የኤርትራ መንግስት በበኩሉ ባልታወቀ ምክንያት የኢትዮጵያ ጦር በብዛት ወደ ድንበር እንደተሰማራና የአሜሪካ እጅ እንዳለበት የተናገረ ሲሆን፤ 200 ወታደሮችን ገድያለሁ ብሏል፡፡
በኤርትራ መንግስት ላይ አስተማሪ እርምጃ መስደናል ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፤ “ሌላ ትንኮሳ ያደርጋል ብለን አንጠብቅም፤፡፡  በድንበር አካባቢ ሌላ ግጭት የሚፈጠር ከሆነ ግን፣ የግጭቱ ብቸኛ ተጠያቂ የሚሆነው የኤርትራ መንግስት ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት፣ ትንኮሳዎችን ለማስታገስና ለመቅጣት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የኢያሳያስን መንግስት የማውረድ ኃላፊነት ግን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአለማቀፉ ህብረተሰብም የሚመለከት ቢሆንም፣ በዋናነት የኤርትራ ህዝብ ጉዳይ ነው ብለዋል -  ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
“ተመጣጣኝ እርምጃ” የሚባለው ሃሳብ እንደማያዛልቅ የተናገሩት የቀድሞ የአየር ኃይል አዛሽ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በበኩላቸው፤ ተመጣጣኝ እርምጃ ማለት እነሱ 200 ከገደሉ፣ እኛ 1000 በመግደል እንቀጣቸዋለን በሚል ስሌት እንደመመራት ስለሆነ አያዋጣም ብለዋል፡፡ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ሙሉ ለሙሉ መወገድ አለበት ያሉት ሜ/ጀ አበበ፣ ተመጣጣኝ እርምጃ የሚባለው ሃሳብ ትርፉ እልቂት ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአሜሪካ መንግስት፣ የድንበር ግጭቱ እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከግጭት እንዲታቀቡ መክረዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት በኢንፎርሜሽን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ ባልታወቀ ምክንያት ጥቃት እንደተፈፀመበት ጠቅሶ፣ ከ200 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ገድያለሁ፣ 300 አቁስያለሁ ብሏል፡፡
ሃላፊነት በጎደለው ድርጊት ደም መፋሰስ እንዲከሰት የተደረገበት ምክንያት አናውቅም ያለው ይሄው መግለጫ፤ የአሜሪካ መንግስትንና አለም አቀፍ ተቋማትን ኮንኗል፡፡
ከጥቃቱ በፊትና በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግስትን እየደገፉ ነው በማለት፡፡ እነዚህ አካላት እውነታውን በመካድ ወራሪውንና ተወራሪውን እኩል ለማውገዝ ሞክረዋል ሲልም ገልጧል፡፡
በድንበር አካባቢ የኢትዮጵያ ጦር በብዛት ተሰማርቶብኛል፤ በዚህ ውስጥም የአሜሪካ መንግስት እጅ አለበት ብሏል - ትናንት የወጣው መግለጫ፡፡  
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው የድንበር ግጭት እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፣ ሁለቱም አገራት ከግጭት እንዲርቁ መክረዋል፡፡ ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶችና መግለጫዎች እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን፣ ባለፈው ረቡዕ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁለቱም አገራት ችግሩን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ አገራቱ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ከ15 ዓመታት በፊት እ.ኤአ. በ2000 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

“ቃና” 8 ስቱዲዮዎች ገንብቷል

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው “የቃና ቴሌቪዥን” ሥርጭትን ተከትሎ ሲኒማ ቤቶችና ቲያትር ቤቶች በተመልካች ድርቅ መመታታቸውን የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት የፊልምና ቲያትር ተመልካቾች ከግማሽ በላይ መቀነሳቸው ባለሙያዎቹን እንዳስደነገጣቸው ገልፀዋል፡፡
የቲያትር አዘጋጆችና ባለቤቶች እንደተናገሩት፤ በሣምንቱ የእረፍት ቀናት ከሚታዩ ቲያትሮች በስተቀር በስራ ቀናት ምሽት ላይ የሚቀርቡ ቲያትሮች ተመልካች አጥተዋል፡፡
በማዘጋጃ ቤት “እንግዳ” እንዲሁም በብሔራዊ ቲያትር “የፍቅር ማዕበል” የተሰኙ ቲያትሮችን የሚያሳየው አርቲስት ማንያዘዋል እንደሻው፤ ባለፉት ሶስት ወራት የቲያትር ተመልካቾች ከ30 በመቶ በላይ መቀነሳቸውን ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል በማዘጋጀ ቤት እየታየ ያለውን ቲያትር እስከ 300 ሰዎች ይመለከቱት እንደነበረ የጠቆመው አርቲስቱ፤ በአሁን ወቅት የተመልካቹ ቁጥር በመቶ እንደቀነሰ ተናግሯል፡፡ “ቃና” ቴሌቪዥን ከመጣ ወዲህ የተመልካቹ ቁጥሩ መቀነሱ የጣቢያው ተፅዕኖ የፈጠረው ነው ብሎ እንደሚያምን የገለፀው ማንያዘዋል፤ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ቲያትር ቤቶች ባዶአቸውን ሊቀሩ ይችላሉ ብሏል፡፡
ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ ሌላ የቲያትር ባለሙያ በበኩሉ፤ የተመልካች ቁጥሩ መቀነሱ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ እየጐዳው በመምጣቱ፣ በቲያትር ስራ የመቀጠል እምብዛም ፍላጐት የለኝም ብሏል፡፡ የቲያትር ባለቤቶችም ለከፍተኛ ኪሣራ እየተዳረጉ እንደሆነ ወዳጆቹ  እንደነገሩት ጠቁሟል፡፡
የ“ታምሩ ሲኒማ ቤት” ባለቤት አርቲስት ታምሩ ብርሃኑም፤ ባለፉት ሶስት ወራት የተመልካች ቁጥር በግማሽ መቀነሱን ይናገራል፡፡ ችግሩ የተፈጠረው “ቃና” ቴሌቪዥን ከመጣ በኋላ በመሆኑ ጣቢያው የፈጠረው ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል አርቲስቱ ግምቱን ተናግሯል፡፡ “እንደ ቢዝነስ ሊጐዳኝ ቢችልም እንደ ሙያተኛ በቃና ደስተኛ ነኝ” ይላል፡፡ የተመልካች ቁጥር በትክክል የቀነሰበትን ምክንያት ለማወቅ ግን ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ነው፤ አርቲስት ታምሩ፡፡
የሴባስቶፖል ሲኒማ ባለቤትና የፊልም ባለሙያው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተመልካች ቁጥር መቀነሱን ባይክድም የ “ቃና” ተፅዕኖ ነው በሚለው ግን አይስማማም፡፡ “ከዚያ ይልቅ በየቦታው በርካታ የግል ሲኒማ ቤቶች መከፈታቸው ተመልካቹ እንዲበታተን አድርጐታል” ብሎ እንደሚያምን ቴዎድሮስ ገልጿል፡፡
የቫይን ሲኒማ ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ገዛኸኝ (ብሩስ) በበኩላቸው፤ የተመልካች ቁጥሩ ከሚገመተው በላይ መቀነሱን ይናገራሉ፡፡ “ለምን ተመልካች አይመጣም?” የሚል መጠነኛ ጥናት ለመስራት መሞከራቸውን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ አብዛኛው ተመልካች የማይመጣው ጥሩ ፊልሞች ስለማይቀርቡ እንደሆነ አረጋግጫለሁ ይላል፡፡ በ “ቃና” ቴሌቪዥን ምክንያት ከሲኒማ ቤት የቀሩም አሉ - ጥቂት ናቸው እንጂ፤ ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡
የፊልም ዳይሬክተሩ ቢኒያም ወርቁ በሰጠው አስተያየት፤ ለተመልካች ቁጥር መቀነስ ዋነኛው ምክንያት “ቃና” ቴሌቪዥን ነው ብሎ እንደሚያምን የተገለፀ ሲሆን፤ ትክክለኛውን ምክንያት ለማወቅ ግን በማህበራቸው በኩል ጥናት ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል “ቃና” ቴሌቪዥን ተርጉሞ ከሚያቀርባቸው ፊልሞች በተጨማሪ ራሱ ለሚሰራቸው አገር በቀል ፊልሞችና አዳዲስ ፕሮግራሞች 8 ስቱዲዮዎች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን የጣቢያው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃይሉ ተ/ሃይማኖት ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ስርጭት በጀመረ በ3 ወር ጊዜ ውስጥም የጣቢያውን ፌስ ቡክ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች እየተከታተሉት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡    


- 720 ሲም ካርዶችን መጠቀም የሚችል መሳሪያ ተይዟል
- በዘጠኝ ወራት ብቻ 165 የሳይበር ጥቃቶች ደርሰዋል
       በአራት የአገሪቱ ከተሞች በተፈፀሙ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች መንግስት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት ተገለፀ፡፡ በጅግጅጋ፣ በአዲስ አበባ፣ በሃረርና ድሬደዋ 400 የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎች የተያዙ ሲሆን አንዳንዶቹ 8፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ 720 ሲም ካርዶችን የሚጠቀሙ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወልደ አረጋዊ ከትናንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ የአገልግሎት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ሲሆን መንግስትንም ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጐታል፡፡  ባለፉት ዘጠኝ ወራት በጅግጅጋ፣ አዲስ አበባ፣ ሐረርና ድሬደዋ ከተሞች  በተካሄደ አሰሳ፣ 400 የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎች የተያዙ ሲሆን መሳሪያዎቹ ከ8 እስከ 720 ሲም ካርዶችን የመጠቀም አቅም ያላቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡  46  ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በመንግስት ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ማድረሳቸውን አስታውቋል፡፡
ለወንጀሉ መባባስ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የቴክኖሎጂ መወሳሰብ፣ የባለድርሻ አካላት ንቃተ ህሊና ማነስ፣ የሲም ካርድ፣ የቮቸር ካርድና የኢቪዶ አገልግሎት ሽያጭ ከጥብቅ ቁጥጥር ጋር አለመተሳሰር ይገኙበታል፡፡
በአገሪቱ የሚፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶችን የመለየት፣ የመመከትና ምላሽ የመስጠት ተልዕኮ የተሰጠው “ኢትዮ ሶርት” የተባለ ማዕከል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የገለፀው የኤጀንሲው ሪፖርቱ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 165 የሳይበር ጥቃቶች መድረሳቸውንና ማዕከሉ ጥቃቶቹን ማክሸፉን ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሳይበር በአገራችን ከዋና ዋና ወንጀል መፈፀሚያ ስልቶች አንዱ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቅሶ፤ ይሄንን ለመከላከል የሚያስችል የሳይበር ወንጀል ህግ መፅደቁን አመልክቷል፡፡ የአገሪቱን የኤሌክትሮኒክስ ንግድና የኤሌክትሮኒክስ አስተዳደር አገልግሎቶች ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያግዝ የዲጂታል ፊርማ ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ከመንግስት ባንኮችና ከተወሰኑ ተቋማት በስተቀር አብዛኛዎቹ የመንግስት ተቋማት የሳይበር ደህንነት ጉዳይን የተቋማቸው የስትራቴጂክና ኦፕሬሽናል አመራር አካል አድርገው እንደማይወስዱት ያመለከተው ሪፖርቱ፤  ለቁጥጥር አመቺ ያልሆኑ ሥርዓቶችን ስለሚዘረጉ በአገራዊ ደህንነት ላይ ስጋት እየፈጠሩ ነው ብሏል፡፡  

- በኢትዮጵያ የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ረጅሙ ልብወለድ ነው

   በአንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ የተጻፈውና ዘጠነኛ ስራው የሆነው “የስንብት ቀለማት” የተሰኘ የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ በቅርቡ ለንባብ እንደሚበቃ ደራሲው ለአዲስ አድማስ  መግለጫ አስታወቀ፡፡
ደራሲ አዳም ረታ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሲያስተዋውቀው የነበረውን ‘ሕጽናዊነት’ የተባለ ልዩ የአጻጸፍ ስልት በስፋትና በጥልቀት ያሳየበት “የስንብት ቀለማት”፣ በቅርጹም ሆነ በይዘቱ የተለየ እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን ደራሲው ከዚህ ቀደም ባሳተማቸው መጽሃፍት ውስጥ የሚጠቀማቸው ምስሎች፣ ቻርቶች፣ ግራፊክ ዲዛይኖችና ሰንጠረዦች በአዲሱ መጽሀፍም መካተታቸውንና ባለ ሙሉቀለም የግርጌ ስታወሻዎችና ሌሎች አዳዲስ ይዘቶች እንዳሉት ታውቋል፡፡
በመጨረሻ ገፆቹ የአንጋፋውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነጽሁፍ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ ዳሰሳ “ድሕረ ቃል” በሚል ርዕስ ያካተተው መፅሀፉ ፤ በ960 ገጾች በኢትዮጵያ የሥነ ፅሁፍ ታሪክ ረዥሙ ልብወለድ ለመሆን በቅቷል፡፡  8 አቢይ ምዕራፎችና 46 ንኡስ ምዕራፎች ያሉት ልብ ወለዱ፤ ዋጋው 350 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

      የ2016 ዳይመንድ ሊግ ከትናንት በስቲያ በ8ኛዋ ከተማ ስዊድን ስቶክሆልም ተካሂዷል። 11 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቶች፤ 59 የዓለም ሻምፒዮኖች እንዲሁም 7 የዓመቱን ፈጣን ሰዓት እና ምርጥ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች ተሳትፈውበታል፡፡ በዳይመንድ  ሊጉ በሁለቱም ፆታዎች ከ4 በላይ የውድድር መደቦችን  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡ በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር ፣ በ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች እና በ3000 ሜትር ወንዶች እንዲሁም በ5000 ሜትር  ጠንካራ ተፎካካሪም ናቸው፡፡  
ባለፈው ሐሙስ ስቶክሆልም ላይ  በ800 ሜትር ወንዶች ቤጂንግ አስተናግዳ በነበረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ1 እስከ 5 የወጡ አትሌቶች ተሳትፈዋል፡፡ በተለይ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ዴቪድ ሩድሻ እና የዓለም ሻምፒዮኑ መሐመድ አማን ከ3 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መገናኘታቸው ትኩረት የሳበ ነበር፡፡
በ5ሺ ሜትር ወንዶች በ3ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሆነው የሆነው ዮሚፍ ቀጀልቻ፤ በ2011 በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ የወርቅ ሜዳልያ የወሰደው ኢብራሂም ጄይላንና በውድድር ዘመኑ በ5ሺ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ሙክታር ኢድሪስ ፈታኝ ውድድር አድርገዋል፡፡  ኢማና መርጋ እና የኔው አላምረውም ከተፎካካሪዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሶፍያ አሰፋ፤ በ1500 ዳዊት ስዩም፤ ጉድፍ ፀጋይ እና በሱ ሳዶ ተሳትፈዋል፡፡
የ2016  ዳይመንድ ሊግ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ይገኛል፡፡ በስዊድን ስቶክሆልም ጨምሮ በስምንት ከተሞች  ተካሂዷል፡፡  በኳታሯ ከተማ ዶሃ የተጀመረ ሲሆን ከዚያም በቻይና ሻንጋይ፤ በሞሮኮ ራባት፤ በጣሊያን ሮም፤ በእንግሊዝ በርሚንግሃም እና በኖርዌይ ኦስሎ ከተሞችም ተከናውኗል፡፡ ከ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ በፊት 10 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች በ10 ከተሞች ይደረጋል፡፡ ከሪዮ ኦሎምፒክ በፊት ቀጣዮቹ የዳይመንድ ሊግ አዘጋጅ ከተሞች የፈረንሳይ ከተማ ሞናኮ እና የእንግሊዟ ከተማ ለንደን  ናቸው፡፡ ከሪዮ ኦሎምፒክ በኋላ በስዊዘርላንድ ሎዛን፤ በፈረንሳይ ፓሪስ መደበኛዎቹ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በስዊዘርላንድ ዙሪክ እና በቤልጄይም ብራስልስ ከተሞች ሁለቱ የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድሮች ያስተናግዳሉ፡፡
የ2016 ዳይመንድ ሊግ  በሪዮ ኦሎምፒክ ዓመት መካሄዱ ለየት ያደርገዋል፡፡ በኦሎምፒክ በመካከለኛና በረጅም ርቀት የአትሌቲከስ ውድድሮችና የሜዳ ላይ ስፖርቶች የሚያሰልፏቸውን ምርጥ ኦሎምፒያኖች ለመለየት የሚያግዝ  ነው፡፡ ዘንድሮ በተለይ በ5ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች የኢትዮጵያ አትሌቶች በዳይመንድ ሊጉ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም በሪዮ ኦሎምፒክ ለሚኖር የሜዳልያዎች ስኬት ከፍተኛ ተስፋ ሊፈጥር ይችላል፡፡
በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍ የሚዘጋጀው ዳይመንድ ሊግ  ዘንድሮ በ7ኛ የውድድር ዘመኑ ላይ ይገኛል። አስቀድሞ ይካሄድ የነበረውን ጎልደን ሊግን በተሻለ ደረጃ የተካ ዓመታዊ የአትሌቲክስ መድረክ ሆኖ በስኬት የቀጠለው ዳይመንድ ሊግ በየዓመቱ በ32 የውድድር መደቦች (16 የወንድ 16 የሴት) የሚካሄደ ሲሆን በርካታ ምርጥ አትሌቶች የሚሳተፉበትና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበትም ሆኗል፡፡ በ4 አህጉራት ፤  በ11 የተለያዩ አገራትና 15 ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች የብሔራዊ፣ የዓለምና፣ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆኑ ብዛት ያላቸው አትሌቶችን ማሳተፉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በከፍተኛ የውድድር ደረጃው ሪከርዶች እና የውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓቶች የሚመዘገቡበት መድረክም ነው፡፡በሻምፒዮንሺፕ ደረጃ ባይሆንም በርካታ ምርጥ አትሌቶችን በከፍተኛ የፉክክር ደረጃ የሚያሳትፍ የአትሌቲክስ ታላቅ መድረክ እየሆነ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያውያን
በ7ኛው ዳይመንድ ሊግ ላይ
ዳይመንድ ሊጉ በ8ኛዋ ከተማ ስቶክሆልም ከቀጠለ በኋላ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች  በሁለት ተከታታይ ውድድሮች ተከታትለው በመግባት ፍፁም የበላይነት በማሳየት ላይ ናቸው፡፡  ከሳምንታት በፊት አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት፣ ሙክታር እድሪስ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት ተከታትለው ገብተዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ደግሞ በስዊድን ስቶክሆልም ኢብራሂም ጄይላን፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ እንዲሁም ሙክታር ኢድርስ ሆነው ከ1 እስከ 3 ደረጃ አግኝተዋል። በ5ሺ ሜትር ወንዶች ሙክታር ኢድሪስ በ4 ውድድሮች 30 ነጥብ አስመዝግቦ 1ኛ ሲሆን፤ ሃጎስ ገብረህይወት በ2 ውድድሮች 12 ነጥብ አስመዝግቦ 2ኛ፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ3 ውድድሮች 11 ነጥብ አስመዝግቦ 3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ኢብራሂም ጄይላን በስዊድን ስቶክሆልም ካሸነፈ በኋላ በ10  ነጥብ 4ኛደረጃ ሲይዝ ይገረም ደመላሽና አባዲ አምባዬ በእኩል 3 ነጥብ ዘጠነኛ፤ እንዲሁም ደጀን ገብረመስቀል በ1 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ደግሞ በሞሮኮ ራባት እና በጣሊያን ሮም ያሸነፈችው አልማዝ አያና ለዓለም ሪከርድ እጅግ የቀረበ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የበላይነቷን እያሳየች ነው፡፡ አምና በ6ኛው ዳይመንድ ሊግ በ5ሺ ሜትር ያሸነፈችው ገንዘቤ ዲባባ ስትሆን ዘንድሮ ግን አልማዝ አያናን የሚቀናቀን ያለ አይመስልም። በ3 ውድድሮች በማሸነፍ በ30 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ የኬንያዎቹ ሜርሲ ቼሮኖ በ18 እንዲሁም ቪቪያን ቼሮይት በ13 ነጥብ ይከተላሉ፡፡ ሌሎቹ አትሌቶች ሰንበሬ ተፈሪ በ7 ነጥብ 6ኛ፤ ገለቴ ቡርቃ በ4 ነጥብ 7ኛ፤ ሃፍታምነሽ ተስፋዬ በ3 ነጥብ 9ኛ፤ እቴነሽ ዲሮ እና አባቤል የሱፍ በእኩል 2 ነጥብ 9ኛ እንዲሁም አለሚቱ ሃሮዬ በ1 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሶፊያ አሰፋ በ3 ውድድሮች 12 ነጥብ አስመዝግባ በ3ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በሴቶች 3ሺ መሰናክል ላይ ሶፊያ አሰፋ በዳይመንድ ሊግ በ35 ውድድሮች በመሳተፍ በዳይመንድ ሊጉ የተሳትፎ ልምድ አራተኛ ደረጃ ያላት ሲሆን፤ በ22 ደውድድሮች ከ1 እስከ 3 ባሉ ደረጃ በመጨረስ ውጤቷ በ10ኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው፡፡ እቴነሽ ዲሮ በበኩሏ በ1 ውድድር 4 ነጥብ አስመዝግባ 4ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በ800 ሜትር ወንዶች መሃመድ አማን በ4 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲሆን  በ1500 ሜትር ወንዶች አማን ወቴ በ3 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡በ800 ሜትር ሴቶች ሃብታም አለሙ በ3 ውድድሮች 8 ነጥብ አስመዝግባ 5ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፤ በ1500 ሴቶች ዳዊት ስዩምና ጉድፍ ፀጋይ በ2 ውድድሮች 10 ነጥብ በማስመዝገብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲሆኑ በ6 ነጥብ በሱ ሳዶ 8ኛ ነች፡፡
ስለ ዳይመንድ ሊጉ
ባለፉት ስድስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናር ኤስያ፤ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምስራቅ እና አሜሪካን ያካለለው ውድድሩ ዘንድሮ ደግሞ  በአፍሪካ መካሄድ ጀምሯል፡፡ በአሜሪካዋ ኒውዮርክ የሚዘጋጀውን ግራንድ ፕሪ በመተካት በአፍሪካ የዳይመንድ ሊግ አዘጋጅ ሆና የተመረጠችው የሞሮኮዋ ከተማ ራባት ስትሆን ውድድሩን በመሀመድ አምስተኛ ስታድዬም በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በቅታለች፡፡ በሌላ በኩል ተግባራዊ የሆነ የዳይመንድ ሊግ አዲስ አሰራር የነጥብ አሰጣጡ ነው፡፡ ባለፉት 6 የውድድር ዘመናት ከ1 እሰከ 3 ለሚወጡ አትሌቶች ብቻ  ነጥብ ይሰጥ በር፡፡ ዘነድሮ ከ1 እሰከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች ነጥቦች ይሰጣሉ፡፡  በዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመን አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከሚያገኙት የገንዘብ ሽልማት እና የዳይመንድ ዋንጫ በተጨማሪ በቀጣይ የውድድር ዘመን በቀጥታ ተሳታፊ በመሆናቸው ከፍተኛውን ነጥብ ለማስመዝገብ ፉክክሩ ከባድ ነው፡፡ በዳይመንድ ሊግ በየውድድር አይነቱ በሚሰጥ ነጥብ መሰረት ዳይመንድ ሬስ ተብሎ ደረጃ ይሰጣል፡፡  በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከፍተኛውን ነጥብ ያስመዘገቡ አትሌቶች በአልማዝ ማእድን የተሰራ ልዩ ዋንጫ እና 40ሺ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ፡፡ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫው ተቀማጭነቱ በዙሪክ የሆነው፤ ከ18ኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ በመስራት ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው ቤዬር የተባለ ተቋም ይሰራዋል። በዳይመንድ ሬስ ፉክክር ለመግባት አትሌቶች ውድድሮቹ ከሚደረጉባቸው 14 ከተሞች በ7ቱ የግድ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡
በዳይመንድ ሊጉ አዲስ የነጥብ አሰጣጥ መሰረት በአንደኝነት የሚያሸንፍ አትሌት በመደበኛ ውድድሮች 10 ነጥብ በፍፃሜ 30 ነጥብ፤ 2ኛ ደረጃ የሚያገኝ በመደበኛ 6 ነጥብ በፍፃሜ 12 ነጥብ ፤ 3ኛ ደረጃ የሚያገኝ አትሌት በመደበኛ 4 ነጥብ በፍፃሜ 8 ነጥብ፤ 4ኛ ደረጃ የሚያገኝ አትሌት በመደበኛ 3 ነጥብ በፍፃሜ 6 ነጥብ፤ 5ኛ ደረጃ የሚያገኝ አትሌት በመደበኛ 2 ነጥብ በፍፃሜ 4 ነጥብ እንዲሁም 6ኛ ደረጃ የሚያገኝ በመደበኛ 1 ነጥብ በፍፃሜ 2 ነጥብ ይሰጣቸዋል፡፡ በዳይመንድ ሊጉ ማጠቃለያ አትሌቶች በየውድድር መደቡ በእኩል ነጥብ የሚጨርሱ ከሆነ ባሸነፉት የውድድር ብዛት፤ ይህም አቻ የሚያደርጋቸው ከሆነ በተሻለ ሰዓት እና ውጤት መሰረት አሸናፊዎቹ የሚለዩ ይሆናል፡፡
በዳይመንድ ሊጉ በእያንዳንዱ ከተማ በሚደረግ ውድድር  እሰከ 8ኛ ደረጃ ላገኙ አትሌቶች የሚበረከተው የሽልማት ገንዘብ ዝርዝር እንደሚከተለው ሲሆን ለ1ኛ 10ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 6ሺ ዶላር፤ ለ3ኛ 4ሺ ዶላር፤ ለ4ኛ 3ሺ ዶላር፤ ለአምስተኛ 2500 ዶላር፤ ለስድስተኛ 2ሺ ዶላር፤ ለ7ኛ 1500 ዶላር እንዲሁም ለ8ኛ 1000 ዶላር ይሆናል፡፡
የምንግዜም ውጤት ደረጃ
ባለፉት 6 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት 48 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች ያስመዘገበችው አሜሪካ አንደኛ ደረጃ ሲኖራት፤ ኬንያ በ30 ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ጃማይካ በ14 የዳይመንድ ሊግ ድሎች ሶስተኛ ደረጃ ስትይዝ፤ ኢትዮጵያ በ2012 እኤአ ላይ አበባ አረጋዊ በ1500 ሜትር ዜግነቷን ሳትቀይር ያስመዘገበችውን ድል ጨምሮ በ10 የዳይመንድ ሊግ ድሎች አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ 10 የዳይመንድ ሊግ ድሎች በአምስት አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር መሃመድ አማን በ2012 እና በ2013 እኤአ አሸንፏል። በ5ሺ ሜትር ወንዶች ካላፉት አምስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመኖች አራቱን ሁለት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል፡፡ በ2010 እና 2011 እኤአ ኢማና መርጋ እንዲሁም በ2013 እኤአ የኔው አላምረው ናቸው፡፡ አበባ አረጋዊ ዜግነቷን ሳትለውጥ በፊት በ1500 ሜትር በ2012 እኤአ ላይ አሸናፊ ነበረች፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር መሰረት ደፋር በ2013 እኤአ ያሸነፈች ሲሆን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ 2014 እኤአ ላይ ህይወት አያሌው ድል አድርጋለች፡፡ በ2015 ደግሞ ዳይመንድ ሊጉን በ5ሺ ሜትር ለማሸነፍ የበቃችው ገንዘቤ ዲባባ ነበረች፡፡
ባለፉት ስድስት የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖችን የሚከተሉት ናቸው፡፡
በ3ሺ ሜትር የኔው አላምረው በኳታር ዶሃ በ2011 እኤአ ላይ በ7፡27.26
በ5ሺ ሜትር ደጀን ገብረመስቀል በፈረንሳይ ፓሪስ በ2012 እኤአ 12፡46.81
በሴቶች 1500 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ በፈረንሳይ ሞናኮ በ2015 እኤአ ላይ 3፡50.07
በሴቶች 5ሺ ሜትር አልማዝ አያና በሮም ጣሊያን 14፡12.59

ሦስት አህዮች በጠፍ ጨረቃ ሣር ሊግጡ ወደ ሜዳ ተሰማርተዋል፡፡ ጅቦች ደግሞ ርቧቸው ሲዞሩ አምሽተው፣ በመጨረሻ አህዮቹ ሣር ወደሚግጡበት አካባቢ ይመጣሉ፡፡
“በዚህ ሌሊት፣ በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት እንዲህ ፍንድቅድቅ ያሉት ማንን ተማምነው ነው? ከመብላታችን በፊት እንጠይቃቸው” አሉና ጅቦቹ አህዮቹን ተራ በተራ ለፍርድ እንዲቀርቡ አደረጉ፡፡
የጅብ መሀል ዳኛ የመጀመሪያዋን አህያ አስቀርቦ፤
“ወ/ሮ አህያ፣ በጠፍ ጨረቃ፣ በእኛ ግዛት መጥተሽ ሣር የምትግጪው ማንን ተማምነሽ ነው?” ሲል ጠየቃት፡፡
ወ/ሮ አህያም፤
“አምላኬን ተማምኜ ነው፡፡ ማንም ጥቃት ቢያደርስብኝ አምላክ ይበቀልልኛል ብዬ ነው” ስትል መለሰች፡፡
ሁለተኛዋን አህያ አስጠሩና ዳኛው ጅብ፤
“አንቺስ በጠፍ ጨረቃ በእኛ ግዛት ሣር የምትግጪው ማንን ተማምነሽ ነው” ሲሉ ጠየቋት።
ሁለተኛዋ ተከሳሽ አህያም፤
“እኔ ጌታዬን ተማምኜ ነው የወጣሁት፡፡ ማንም ጥቃት ቢያደርስብኝ፤ ጌታዬ ተከታትሎ ይበቀልልኛል” አለች፡፡
ሦስተኛዋ ተከሳሽ አህያ ቀረበች፡፡
“ማንን ተማምነሽ ነው በእኛ ሰዓት፣ በእኛ ግዛት ሣር የምትግጪው?” ሲሉ ጠየቋት፡፡
አህይትም፤ “እናንተን ተማምኜ፣ እናንተን አምኜ ነው ከቤቴ የወጣሁት” ስትል መለሰች፡፡
ሶስቱ ጅቦች ዳኞች,ኧ ሶስቱን ተከሳሽ አህዮች ወደ ጥግ እንዲቆሙ አድርገው ይመካከሩ ጀመር፡፡
“የመጀመሪያዋን አህያ ብንበላት፤ እንዳለችው አምላክ ሊበቀለን ይችላል፡፡ ለእኛ ለይቶ ባይልከውም ነጐድጓድ ሊያወርድብን፣ መብረቅ ሊልክብን፣ ድርቅ ሊያመጣብን ይችላል”
“ሁለተኛዋን ብንበላትስ?” አለ ግራ ዳኛው ጅብ፡፡
“የእሷም ጌታዋ ሊበቀለን ይችላል፡፡ አሁንም ፍለጋ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እሷንም ብንተዋት ይሻላል፡፡ ይልቅ እቺን እኛን የተማመነችውን ብንበላት ማናባቱ ይጠይቀናል?” አሉና ሁለቱን አሰናብተው ሶስተኛዋ ላይ ወረዱባት፡፡
*   *   *
በርትቶ ራስን ማዳን ነው እንጂ “እናንተን ተማምኜ” ማለት አብዛኛውን ጊዜ አያዋጣ። ምንጊዜም በራስ መተማመንን የመሰለ ነገር የለም፡፡ በራስ ለመተማመን የራስን ብቃት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የራስን ብቃት ለማረጋገጥ ራስን በመሠረታዊ ዕውቀት መገንባት፣ ሁሌ መትጋት፣ ሁሌ መማር ያሻል፡፡ ትምህርት ከመሠረቱ ካልተስተካከለ የተጣመመ ግንድ ለማቃናት እንደመሞከር ይሆናል፡፡ ዛሬ ትምህርት በእጅጉ ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን፤ “ቁልቁል ማደግ” እንደሚለው ነው፡፡
“በጠቅል ጊዜ ያልተማረ
ማዘኑ አይቀርም እያደረ
ዐይናችን ታሞ ታውረን
ኃይለሥላሴ አዳኑን”
ለማለት እንኳ አቅም የለም፡፡ ለመማር አቅም የሌላት አገር የበለፀገ ትውልድ ለማፍራት አትችልም፡፡ የተልፈሰፈሰና የተቆለመመ ህብረተሰብ ነው የምትፈጥረው፡፡ እንዲያ ያለ ህብረተሰብ ደግሞ ነገው የተጭለመለመ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ “መማር፣ መማር፣ መማር” የሚለው የዱሮ መፈክር፤ የሸረሪት ድርም አድርቶበት ከሆነ ተጠራርጐ ጐላ ብሎ ቢታይ በጐ ነው፡፡
ቻይናዎች፤
“ዕቅድህ ለዓመት ከሆነ ሩዝ ዝራ፡፡
ዕቅድህ ለአምስት ዓመት ከሆነ ባህር ዛፍ ትከል፡፡
ዕቅድህ ለዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር” ይላሉ፡፡
(“If your plan is for a year, plant rice;
If your plan is for five years, plant a eucalyptus tree;
If your plan is for ever educate your child.)  
ይህንን አስተምህሮ ሶስት ወገኖች በቅጡ ሊጨብጡት ይገባል፡- አንደኛ ወላጆች፡፡ ሁለተኛ መምህራን፡፡ ሶስተኛ መንግሥት፡፡ ይህ የሶስትዮሽ ትሥሥር (Network) ብቻ ነው የኋሊት እየተንደረደርን ካለንበት አዝቅት ታኮ ሆኖ ሊያቆመን የሚችለው፡፡ ኩረጃን እንደ ባህል እንዳንይዝ በግሮ የሚከላከልልን ይኼው የሶስትዮሽ አጥር ነው፡፡ ታሪካዊ ምፀቱ ቢያስገርምም እዚህ ተጠቃሽ ቢሆን አግባብ ነው የምንለው ነገር አለ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር “ከሌሎች አገሮች የዕድገት አካሄድ ቢያንስ በአግባቡ መኮረጅ እንቻል”፡፡ ያን ያሉት ለትምህርት ቤት ፈተና ኩረጃ አልነበረም! ያ የበለጠ ለመሥራት፣ የበለጠ ለመትጋት፣ የበለጠ ለመነሳሳት ነበረ። አሁን የሚታየው ግን ሥንፈተ - ትምህርት ነው! ይህ አደጋ ነው፡፡ ትልቅ ሥጋት፣ ትልቅ ጥንቃቄ፣ ትልቅ ቆራጥነት ይጠይቃል፡፡ በገጣሚ መንግሥቱ አገላለጽ፣ “መርፌ ትሠራለህ?” ከሚል ማህበረሰብ ተነስተን “መኮረጅ ትችላለህ?” ወደሚል ትውልድ ማቆልቆላችን አሳዛኝ ነው፡፡ ከቶማስ ኤዲሰን 128 የውድቀት ልምድ ባንማር፣ እንደቅዱስ ያሬድ ስምንቴ ከወደቀችው ትል መማር አቅቶናል፡፡
ጥንካሬያችን በሰው ኃይል ጥራት የተገነባ ይሆን ዘንድ የትምህርትን መሠረታዊ ጉዘት እናጢን፡፡ የመምህራኖቻችንን ሙያዊ ብቃትና ስብዕና እንፈትሽ፡፡ የመንግስትን፤ የትምህርት ላይ ትኩረት፤ ከልብ እንመርምር! “ከእሾህ አጥር የሰው አጥር ይጠነክራል” የሚለው ተረት በቅጡ የሚባን ያኔ ነው!!