Administrator

Administrator

Thursday, 26 August 2021 00:00

የአፍጋኒስታን ነገር

በስተመጨረሻም፤ “ተማሪዎቹ” ከ20 አመታት በኋላ በድል ዝማሬ ታጅበው ወደ ቀደመ ርስታቸው፣ ወደ ተነቀሉባት መናገሻቸው ወደ ካቡል ተመለሱ። በአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታንና ኢራን በብዛት ከሚነገረው ፓሽቶ የተሰኘ ቋንቋ የወሰዱትንና “ተማሪዎቹ” የሚል ትርጉም ያለውን “ታሊባን” የተሰኘ ቃል መጠሪያቸው ያደረጉት ታጣቂዎች፤ ከሁለት አስርት አመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ዳግም በአፍጋኒስታን ምድር ከፍ ብለው ታዩ፡፡
እ.ኤ.አ በ2001 ወርሃ መስከረም መጀመሪያ በአሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት ለፈጸመው የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ከለላ ሰጥቷል በሚል በጥቅምት ወር ላይ በአሜሪካ መራሹ ጦር ክፉኛ መደብደብ የጀመረውና በሁለተኛ ወሩ ፍርስርሱ ወጥቶ ወደ ተራራ የሸሸው የአፍጋኒስታኑ የታሊባን አስተዳደር፤ ለሁለት አስርት አመታት በየተራራው ስር አድፍጦ በተወንጫፊ መሳሪያዎች ሲያደባያት ወደነበረችው ካቡል ሰተት ብሎ ገባ፡፡
ከሳምንታት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ ጦራቸው በአፍጋኒስታን የነበረውን የ20 አመታት ቆይታ አጠናቅቆ እንደሚወጣ በይፋ ሲያስታውቁ፣ አለም በመገረምም በመደነቅም ነበር የሰማቻቸው። ባይደን በተናገሩት መሰረት የአሜሪካ ጦርና የሌሎች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል አገራት ጦር አፍጋኒስታንን መልቀቅ በጀመሩበት ቅጽበት ነበር፣ የታሊባን ወታደሮች የአፍጋኒስታንን ቁልፍ ከተሞች መቆጣጠርና ወደፊት መግፋት የጀመሩት፡፡
አሜሪካ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ አድርጋ ያቋቋመችው የአፍጋኒስታን መንግስት ጦር፣ የታሊባንን ጥቃት መቆጣጠር የሚችልበት አቅም አላገኘም፡፡
ባለፈው ዕሁድ ማለዳ…
ታሊባን በድል እየገሰገሰ መዲናዋን ካቡል ተቆጣጠረ፤ ፕሬዚዳንት አሽረፍ ጋኒ፣ ቤተ መንግሥታቸውን ለታሊባን ታጣቂዎች ትተው፣ ወደ ጎረቤት አገር ታጃኪስታን  ጥለው ተሰደዱ፡፡
ታሊባን እሁድ ዕለት ካቡልን መቆጣጠሩን ተከትሎ፣ ቀጥሎ የሚሆነው ነገር ያሳሰባቸውና የታሊባን ቀጣይ እርምጃ ለነፍሳቸው ያሰጋቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታውያን፣አገር ጥለው ለመሰደድ፣ ወደ አውሮፕላን ማረፊያዎች መጉረፍ ያዙ፡፡
ታሊባን ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ የበቀል እርምጃዎችን ይወስዳል፤ የአክራሪነት አመለካከት የሚያንጸባርቁ ፈታኝ ህጎችን በመተግበር አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል የሚለው ስጋት፣ ብዙዎች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እንዳነሳሳቸው ነው የሚነገረው፡፡  
ከታሊባን መስራቾች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ሙላህ ባራዳርን ጨምሮ ለአመታት በኳታር በስደት የኖሩ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ወደ አፍጋኒስታን መመለስ መጀመራቸውን ተከትሎ፣ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አካታች እስላማዊ መንግስት ለመመስረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በአገሪቱ መረጋጋትን ለመፍጠር ሲል ከአውሮፓውያን መንግስታት ጋር ይሰሩ ነበር ያላቸውን ጨምሮ ለሁሉም የቀድሞ መንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ባለስልጣናት ሙሉ ምህረትና ይቅርታ ማድረጉን በይፋ ያስታወቀው ታሊባን፤ በማንም ላይ የበቀል እርምጃ እንደማይወስድ በመግለጽ፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሴቶች በሸሪአ ህግ መሰረት መብታቸው ተከብሮላቸው እንደሚኖሩ ቃል የገባው ታሊባን፤ መገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲሰሩ እንደሚፈቅድም ተናግሯል፡፡ ታሊባን በአፋጣኝ ህጋዊ መንግስት ለመመስረት ከቀድሞው የአፍጋኒስታን መንግስት አመራሮችና ፖለቲከኞች ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ቢያስታውቅም፣ በአብዛኛው ዜጋ ልብ ውስጥ ግን መጪው ጊዜ የጭቆና እና የእርስ በእርስ ብጥብጥ ይሆናል የሚል ስጋት መፈጠሩን ዘገባዎች ያትታሉ፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ ቀጣዩ ሁኔታ ያሰጋቸው ከ60 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውንና የኤምባሲ ሰራተኞቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት ርብርብ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ አሜሪካ እስካለፈው ማክሰኞ ድረስ 3 ሺህ 200 ያህል ዜጎቿን ለማውጣት መቻሏን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ አፍጋኒስታውያን ስደተኞችን ለመቀበል በራቸውን ክፍት እንደሚያደርጉ የሚያስታውቁ አገራትም እየተበራከቱ ሲሆን፣ እንግሊዝ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች ለመቀበል ማቀዷን አስታውቃለች፡፡ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ ከአሜሪካ በቀረበላት ጥያቄ መሰረት 2 ሺህ ያህል አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን ለመቀበል መስማማቷን ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ ማስታወቃቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ለመሰደድ የተዘጋጁ አፍጋኒስታናውያን ቁጥር በእጅጉ በተበራከተበትና እነ ጀርመንን የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸውን በጦር አውሮፕላኖች ጭምር ለማስወጣት ርብርብ በማደረግ ላይ በሚገኙበት በዚህ አደገኛ ወቅት፣ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች በአገሪቱ አየር ክልል የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸው ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው እየተነገረ ነው፡፡
የአፍጋኒስታን የአየር ክልል ላለመጠቀም የበረራ አቅጣጫቸውን እየቀየሩ በፓኪስታንና ኢራን የአየር ክልሎች በረራ ማድረግ ከጀመሩ አየር መንገዶች መካከል ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ብርቲሽ ኤርላይንስ እና ቨርጂን አትላንቲክ እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ታሊባን አገሪቱን ተቆጣጥሮ መንግስት ለመመስረት ደፋ ቀና እያለ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ እንግሊዝን ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት ለቡድኑ ፈጥነው እውቅና መስጠት እንደማይፈልጉ በይፋ እያስታወቁ ነው፡፡
አሜሪካ ከ20 አመታት በፊት ታሊባንን ከስልጣን ለማውረድ ወደ አፍጋኒስታን ጦሯን ካዘመተችበት ጥቅምት ወር 2001 አንስቶ በነበሩት 20 ያህል አመታት፣ ከ3 ሺህ 500 በላይ የጥምር ጦር ወታደሮች በጦርነቱ መሞታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል። ከእነዚህ ወታደሮች መካከል 2 ሺህ 300 ያህሉ የአሜሪካ ወታደሮች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከ20 ሺህ 660 በላይ የሚሆኑ አሜሪካውያን ወታደሮች ደግሞ ቁስለኛ መሆናቸውን ያብራራል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከአፍጋኒስታን ብሄራዊ ጦርና የፖሊስ ሃይል ከ69 ሺህ በላይ ወታደሮች እንዲሁም ከ47 ሺህ በላይ ንጹሃን ዜጎች በጦርነቱ ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ታሊባንን ጨምሮ ከአማጽያን ቡድኖች ደግሞ 84 ሺህ ያህል ታጣቂዎች መገደላቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
አሜሪካ አፍጋኒስታንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ ከጦርነት ጋር በቀጥታ በተያያዙ የተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 241 ሺህ እንደሚደርስ ብራውን ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ባወጣው የጥናት ውጤት ማመልከቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ባለፉት 20 ያህል አመታት ከ2.7 ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን ጦርነቱን በመሸሽ አገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ፓኪስታን መሰደዳቸውን የዘገበው አልጀዚራ በበኩሉ፤ በአፍጋኒስታን በዚህ አመት የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 18.4 ሚሊዮን መድረሱንም አስነብቧል፡፡
አሜሪካ ባለፉት 20 ያህል አመታት በአፍጋኒስታን በየዕለቱ 300 ሚሊዮን ዶላር ያህል ለጦርነት ወጪ ታደርግ እንደነበር ያስታወሰው ፎርብስ መጽሄት፣ በጦርነቱ ያወጣችው ወጪ በድምሩ ከ2.26 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚደርስም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡ ከዚህ ወጪ መካከልም 85 ቢሊዮን ዶላር ያህሉን ያፈሰሰችው በሳምንታት ውስጥ ብትንትኑ ለወጣው የአፍጋኒስታን ጦር ስልጠና መሆኑንም ዘገባው ያስረዳል፡፡


 አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ በሚል ስያሜ በሚታወቀው የቀድሞው የቡርኪናፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራ ግድያ ክስ የተመሰረተባቸውና በስደት ላይ የሚገኙት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ ጉዳይ ከ35 አመት በኋላ በፍርድ ቤት ሊታይ መወሰኑን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1987 በፈተጸመ ጥቃት ቶማስ ሳንካራን በመግደል ወንጀል የተከሰሱትንና ድርጊቱን እንዳልፈጸሙት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡትን የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬን ጨምሮ  ክስ የተመሰረተባቸው 13 ሰዎች ጉዳይ በመጪው ጥቅምት ወር መጀመሪያ በጦር ፍርድ ቤት መታየት እንደሚጀምር የአገሪቱ አቃቤ ህግ ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከሚታየው ሌሎች ተከሳሾች መካከል የኮምፓዎሬ የቀኝ እጅ እንደነበሩ የሚነገርላቸው የቀድሞው የአገሪቱ ደህንነት ሃላፊ ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬ እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ለህግ ሳይቀርብ ከመቆየቱ ጋር በተያያዘ ክስ ቢመሰረትባቸውም ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ተጠርጣሪዎች እንዳሉም አስታውሷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1983 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ቶማስ ሳንካራ፣ ከአራት አመታት በኋላ በኮምፓዎሬ ሴራ በ37 አመት ዕድሜው መገደሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኮምፓዎሬ በበኩላቸው ለ27 አመታት በስልጣን ላይ ቆይተው በ2014 በተቀሰቀሰ ህዝባዊ አብዮት ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ወደ ኮትዲቯር ተሰድደው እስካሁን በዚያው በስደት ላይ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡


3 የኮሮና መድሃኒቶች በምርምር ሂደት ላይ ይገኛሉ

            የተለያዩ አይነት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በቅናሽ ዋጋ እናቀርባለን እያሉ መንግስታትን ጭምር የሚያጭበረብሩ ቡድኖች መበራከታቸውን አለማቀፉ የፖሊስ ጥምረት ኢንተርፖል ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስጠንቀቁን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
መሰል አጭበርባሪዎች 40 በሚደርሱ የተለያዩ የአለማችን አገራት ላይ የኮሮና ክትባት ሽያጭ ጥቃቶችን ማድረሳቸውን የስታወቀው ኢንተርፖል፣ ቡድኖቹ በተደራጀ እና በተጠና ሁኔታ ስለሚንቀሳቀሱ መንግስታት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቡድኖቹ ከክትባት አምራች ኩባንያዎች ጋር ህጋዊ የስራ ግንኙነትና ውክልና ያላቸው በማስመሰል በሃሰተኛ የኤሜይልና የስልክ መልዕክቶች አገራትን ለግዢ እንደሚያግባቡ የጠቆመው ዘገባው፣ ፈቃድ ያላገኙ ወይም በገበያ ላይ የሌሉ ክትባቶችን ጭምር ለመሸጥ እንደሚስማሙና ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያደርሱ መነገሩንም ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ የአለም የጤና ድርጅት ሶስት አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ መድሃኒቶች በምርምር ሙከራ ላይ እንደሚገኙ ከሰሞኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ አርቴሱኔት፣ ኢሜቲኒብና ኢንፊሊክሲማብ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው መድሃኒቶቹ በቀጣይ በ52 የተለያዩ የአለማችን አገራት የኮሮና ተጠቂዎች ላይ እንደሚሞከሩና ውጤታማ ሆነው ከተገኙ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ፈቃድ እንደሚያገኙም አመልክቷል፡፡


 ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ብቻ በአፍሪካ አህጉር 30 ሺህ የሚጠጉ ህጻናት በካንሰር ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን የአለም የቴና ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎች የሚደረጉ ህክምናዎችን በማስተጓጎል ከፍተኛ ጥፋት ማስከተሉን ያስታወሰው ድርጅቱ፣ በአፍሪካ ከሚገኙት አገራት በ46 በመቶው የህጻናት ካንሰር ምርመራ መስተጓጎሉን አመልክቷል፡፡
በአፍሪካ የካንሰር ህክምና የሚያገኙ ህጻናት 30 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውንና በህጻናነት ካንሰር የመሞት ዕድል በአፍሪካ 80 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፣ በከፍተኛ ገቢ አገራት ግን 20 በመቶ ብቻ መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡

 በመላው አለም በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝና ባለፉት 30 አመታት ብቻ በአለማችን ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ራሳቸውን እንዳጠፉ አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡
ኢንጁሪ ፕሪቬንሽን በተባለው ጆርናል ላይ የወጣወን ጥናት ጠቅሶ አንድ ዘገባ እንዳለው፣ በመላው አለም በየአመቱ በአማካይ 800 ሺህ ያህል ሰዎች ራሳቸውን እያጠፉ ቢሆንም ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ግን በእጅጉ አናሳ ነው፡፡
እ.ኤ.አ እስከ 2019 ድረስ በመላው አለም ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች ቁጥር 759 ሺህ እንደሚጠጋ የጠቆመው ዘገባው፣ ግማሽ ያህሉ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሁሉም የአለማችን አካባቢዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ያሳየው ከ70 አመት በላይ በሚገኘው የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  ትዝ ይላችኋል፤ በዚያን ሰሞን እንኳን ዶከተር ዐቢይ በቴሌቪዥን ቀርቦ “የሕዳሴው ግድብ ፍፁም ሆኖ መጠናቀቅ አለበት” እያለ በቴሌቪዥን ሲያወራ። ካልረሳችሁት እሱን ተከትለው ሌሎችም ኢትዮጵያውያን፣ “ግድቡ የእኔ ነው፤ ግድቡ የእኛ ነው” እያሉ በቴሌቪዥን ቀርበው ሀሳባቸውን ሲያንፀባርቁ  ነበር። አሁን ትዝ አላችሁ?!
ታዲያ በዚያን ጊዜ አንዲት እንጨት ተጠግርራ የተሸከመችና ከእንጨቱ ብዛት የተነሳ ከወገቧ በላይ ያጋደለች የምትመስል ሴት አላያችሁም? ያችን ሴት እያሳየ በሚመስል ሁኔታ ዶ/ር ዐቢይ ታዲያ “አባይ የሚገነባው የእነዚህን የእንጨት ተሸካሚዎች ድካም ለመቅረፍ ነው” በሚል መልክ እጁን እንጨት ወደ ተሸከመችው ጎባጣ ሴት እየጠቆመ፣ ደጋግሞ ያችን ሴት ለህዝብ ያሳያት ነበር። እናም ያቺ ሴት ታዲያ፣ የእናቴ ጓደኛ ነች። አጓንዴ ትባላለች።
ታዲያ እናቴና አጓንዴ አንጨት ለመልቀም እንጦጦ ሲወጡ አይለያዩም። አጓንዴ ከሽሮ ሜዳ ዶርዜ ሰፈር ትነሳለች። እናቴ ደግሞ ከቀጨኔ ወጣ፣ ከጨፌ ዝቅ ብሎ ከሚገኘው  ከጉራጌው  አርጋው ቤት አካባቢ ትነሳና፣ ከባዱን የእንጦጦን ዳገት መውጣት ከመጀመራቸው በፊት ቁስቋም  ማርያም ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገናኛሉ። ከዚያም የቁስቋሟ ማርያም እንድታበረታቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ሰው እየሰማቸው በጋራ ሆነው ይፀልያሉ። ከዚያም የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ት/ቤትን አልፈው፣ ሽቅብ የእንጦጦን ዳገት ይያያዙታል።
ዳገቱን ሲወጡ ከላያቸው ላይ ለጠፍ የሚያደርጓት ትንሽ ብጫቂና እድፋም ነጠላ ለብሰው፣ ወገባቸውን እንደዚሁ በረጅም አዳፋ ነጠላ ጠምጥመውና በብብታቸው አካባቢ እንጨት የሚያስሩበትን ገመድና እንጨት ለመተፍተፍ የምትረዳ አነስተኛ መጥረቢያ ሸጎጥ አድርገው ነው።
እንዲህም  ሆኖ ወደ እንጦጦ ሲወጡ፣ ዝናብም  ሆነ ፀሐይ፣ ብርድም ኖረ ነፋስ፣ ግድ አይሰጣቸውም፡፡ ዳገቱን የሚወጡት እየሳቁ፣ እየዘፈኑ፣ ማርያምን እያመሰገኑ፣ ለማንም በሚገርም ሁኔታ የደስተኝነት ስሜት ተላብሰው ነው። በተጨማሪም በመንገድ ሲሔዱ ያዩትን ሰው ሁሉ ሰላም ሳይሉ አያልፉም። ለነገሩ በመንገድ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰላም ማለት ለአጓንዴ ጭምር ያስተማረቻት እናቴ ነች።
አንድ ቀን እናቴን፤ “ያገኘሽውን በሙሉ የፍቅር እስከ መቃብሩን በዛብህን ይመስል ሰላም ማለት አይሰለችሽም እንዴ? “ብዬ ጠየቅኳት። “በዛብህ ደግሞ ማን ነው? እኔ የማውቀው ሠላምተኛ  የእናቴ  (ያያትህ) ጎረቤት የሆኑትን አቶ አርጋው ጨንገሬን ብቻ ነው “አለች። ቀጠለችናም፤ “ስለ አቶ አርጋው ሰላምተኝነት ብትሰማ ምን ልትል ነው፣ እኔን በዚች የሰናፍጭ ቅንጣት በምታክል ሰላምታ ሰጭነቴ የምታደንቀኝ!” አለችኝ።
 እናቴ ስትነግረኝ፤ “(ጎረቤቷ አቶ አርጋው) ድሮ ታክሲ እንዳሁኑ ባልበዛበት ጊዜ ጧት ተነስተው በእግራቸው መርካቶ እስኪደርሱ ድረስ፣ ባርኔጣቸውን አንስተው ያገኙትን ሁሉ (ትግሬ ሆነ አማራ፣ ጉራጌ ሆነ ኦሮሞ፣ ነጭ ሆነ ጥቁር፣ ቀጭን ሆነ ወፍራም፣ ደርግ ሆነ መኢሶን) ምንም ሳይመርጡ ሰላምታ ሲሰጡ ይቆዩና፣ ባርኔጣቸውን መልሰው በራሳቸው ላይ የሚያጠልቁት እግቢያቸው ሲደርሱ ነው” አለችኝ።
 እናም  እናቴ እየተደነቀች በምትነግረኝ በአቶ አርጋው አስደናቂ ምግባር ተመስጬ፣ እስከ አሁን ድረስ ያገኘሁትን ሁሉ ሰላም ማለት ያስደስተኛል፣ደግሞም ሰላምታ መስጠትን እመቤቴ ማርያምም ትወደዋለች” አለችኝ።
ታዲያ የእነዚህን እንጨት ለቃሚ እናቶች ውጪያዊ ጉስቁልና አይቶ፣ በአንጻሩ እየሳቁና ተደስተው፣ ላዩት ሁሉ ሰላምታ እየሰጡ፣ በምስጋናና በተስፋ ሲኖሩ የተመለከታቸው ሁሉ ግራ ይጋባል። እኔም እንደ ውጪው ሰው፣ የእናቴ ሁኔታ ድንገት በአዕምሮዬ ውስጥ ሲታወሰኝ በእጅጉ ግራ እጋባለሁ።
ድሃ ሆነው፣ እንጨት ለቅሞ ለመሸከም ቀን በቀን ተራራ እየወጡና እየወረዱ፣ እንዴት ሁሉ ነገር እንደተሟላለት ሀብታም ሲፍለቀለቁ ይውላሉ” እላለሁ።
እንደገና ደግሞ ምን አለ፣ በዚህ ትዕግስታቸው፣ በዚህ ሰላምታ አሰጣጣቸው፣ በዚህ ማመስገን አወዳደዳቸው፣ ከዚህ የእንጨት ሸክም ስራ አንስቶ እኔ ያለሁበት መስሪያ ቤት፣ የሽያጭ ክፍል ሠራተኛ የሆኑትን እነ አልማዝ በለጠን ወዲያ አሽቀንጥሮ በእነሱ ምትክ የሽያጭ ሠራተኛ ቢያደርጋቸው እላለሁ።
ደግሞም ቀጠል አደርግና፣ አሁን እነ አልማዝ እንግሊዝኛ ከመናገር ውጪ ሌላ ምግባር የሌላቸው ሽያጭ ሠራተኛ ይባላሉ! አንድ ደንበኛ እንኳን በቅንነት ሲያናግሩ ተሰምተው የማያውቁ ወስላቶች! ፀረ ሙስና ከዚህ በለቃቀማቸው!” እላለሁ።
ይህንን ብሶት ሳሰማ የሚሰማኝ ያ የቢሮ ጎደኛዬ (ደርጋጎ)፤  ወደ ጆሮዬ ጠጋ ይልና “ፀረ ሙስና ምን ጥፍር አለው፣ጥፍሩ እኮ ለስላሳ ነው” ይለኛል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ እናቴና አጓንዴ ፣እንጦጦ እንጨት ያለበት ደን ውስጥ የሚገቡት በቀጨኔ በኩል አድርገው፣ ጥድ የሚባለውን ተራራማ ስፍራ አቋርጠው ነው። እናቴ እኔን የወለደችው ፣አጓንዴም ታምሬን የወለደችው በጥድ ብቻቸውን ሲጓዙ በወንዶች ተደፍረው ነው። ሁለቱም ባንድ ቀን ተደፈሩ፤ በተመሳሳይ ቀን ማርገዛቸውን አሳውቀው ወንድሞቻቸው ጋር በመኖር ከንጨት ለቀማ ቀሩ፤ በተመሳሳይ ቀን ልጆች ወለዱ፤ ልዩነቱ እናቴ እኔን (ወንድ) ወለደች። አጓንዴ ደግሞ ታምሬን (ሴት) ወለደች።
ታዲያ ሁለቱም እንጨት ቆራጭ የሆኑት የእናቴና የአጓንዴ ወንድሞች በጧት ተነስተው፣ የእንጨት መቁረጫ ስል መጥረቢያቸውን ይይዙና፣ "በድጋሚ እንዳትደፈሩ ሸኝተናችሁ፣ ጥድን አሳልፈናችሁ እንመለስ" ሲሏቸው የሚሰጡት መልስ የሚገርም ነው።
"እንኳን ተደፈርን ምን ሆንን?  ልጆች አገኘን፣ በእጃችን ፍቅርና ተስፋ ገባ” ይላሉ።
ምን አይነት አገላለጽ ነው!? እኔማ ይህ አነጋገራቸው ስጋት ያሳድርብኛል። እንዲህ ሲሉ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ወይም አምነስቲ የተባለው ድርጅት ሰራተኞች ይሰሟቸውና፣ በደፋሪው ምትክ እነሱን እስር ቤት እንዳያስገቧቸው እላለሁ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ከባድ እንጨት ተሸክመው፣ ከእንጨቱ ክብደት የተነሳ አጎንብሰው፣ በሁለቱም እጆቻቸው ዱላ ተመርኩዘው፣ እንደ አህያ በአራት እግር በሚመስል ሁኔታ ሲጓዙ፣ ሰው አይቶ “አሁንስ አህያ መሰላችሁ”  ይላቸዋል። ታዲያ ለዚህ አባባል እነሱ ግድም አይሰጣቸው። "ኤዲያ! እንምሰላ! በማን እድላችን! አህያ እኮ ጠንካራ ነች፤ እንደዚሁም የእግዚአብሔር ፍጥረት ነች፤ እንዳህያ ጠንካራ ብንሆንማ ለልጆቻችን እንደ ሐብታም ልጆች ሚሪንዳ እየሰጠን፣ ሁለት ሁለት ፓስቲና ሳንቡሳ ገዝተን እያበላን እናሞላቅቃቸው ነበር” ሲሉ የሰሟቸው ሰዎች ነግረውኛል። በእነሱ ቤት ሚሪንዳ ፓስቲና ሳንቡሳ ትልቅ መጠጥና መብል መሆኑ ነው።
ደግሞም ሰው አህያ ሲባል “አንተ ነህ አህያ ብሎ” ለፀብ ይጋበዛል እንጂ እንዴት በማን እድላችን ብሎ፣ ባህያ ጥንካሬ ተመስጦ፣ ‘እንኳን ‘ብሎ መልስ ይሰጣል። አይ እናቴ! አይ አጓንዴ! የሚገርሙ ናቸው።
እንጨት ለቅመው ከእንጦጦ ሲመለሱ አንዱ ከፊት ሌላው ከኋላ ሆነው፣ ፊትና ኋላ መሆንን እየተለዋወጡ፣ አንዱ ሌላውን እየመራ፣ ማርያም ወንዝ እሸቴ አስፋው ጠጅ ቤት በታች፣ እንጨት የሚሸጡበት ቦታ ድረስ ይጓዛሉ።
አብዛኛውን ጊዜ የሚሸከሙት እንጨት ወደ ጎን ሲታይ፣ ረጅም ስፍራ ስለሚይዝ ባስፋልት ላይ ሲሔዱ የመኪና መንገዱን አብዛኛውን ስፍራ ይሸፍኑታል። ከዚህ የተነሳ እነሱ ባሉበት አካባቢ ከታች በኩል ሆነ ከላይ በኩል የሚያልፍ እግረኛ፣ ባለ አህያም ሆነ ባለ መኪና እንደ ልቡ መንቀሳቀስ ይቸገራል።
አንዳንድ ጊዜማ እነሱ በስፋት ሲሔዱ መንገድ ይዘጋጋና፣ በመንገዱ ላይ ትልቅ የመኪና አደጋ እንዳጋጠመ አይነት መንገዱ ጭንቅንቅ ብሎ ክላክስ በክላክስ ይሆናል።
ሌላ ጊዜ ደግሞ የገበያ ቀን በሚባሉ ቀኖች፣ ባህያ ዕቃ ተሸክመው ወደ ከተማ የሚሔዱ አህዮች ስለሚበዙ የእናቴና የአጓንዴ እንጨት አስፋልቱን ይይዘውና፣ አህዮቹ መተላለፊያ ያጣሉ፡፡ ይህን ጊዜ ታዲያ “ጎዲን ጎዱን “የሚለው የአህያ ባለቤቶች ማስጠንቀቅያ ይበረክታል።
አንድ ቀን ከላይ ከሱልልታ የሚመጡ ባለ አህዮች እንደተለመደው፣ “ጎዲን ጎዲን” በማለቴ እናቴንና አጓንዴን በጣም ግራ አጋቧቸው፤ “ምን ጎዲን ጎዲን ትላላችሁ፤ አታዩም እንዴ? እኛም እኮ አህዮች ነን፣ ባለ አህያ ሆናችሁ፣ ለአህዮች አታስቡም እንዴ?; አለቻቸው እናቴ።
አጓንዴ ደግሞ በተራዋ “እኛም እኮ እንቸኩላለን፣ ማርያም ወንዝ እኮ ቡና ሱሳቸውን ለማስታገስ፣ ቆሎ ቆልተው የልጆቻቸውን ርሐብ ለማስታገስ፣ እንጎቻ አንጉተው ለሚወዱት ባላቸው ለማብላት፣ በማርያም ወንዝ እንጨት ገበያ ተሰብስበው የሚጠብቁን ብዙ ደንበኞች አሉን። እነዚህ ደንበኞች እኮ እንደ ሌሎች ሰዎች የኮረንቲ ምጣድና ምድጃ የላቸውም” ስትል ንዴቷን ገለፀች።
ይህን ጊዜ “ጎዲን ጎዲን” የሚሉት ባለአህዮች፣ የእናቴንና የጓደኛዋን ሁኔታ የተመለከቱት ሁለት ኦሮሞ ሴቶች በጣም ስላዘኑ፣ ያህዮቻቸውን ጭነት አሸጋሽገው እናቴና አጓንዴ የተሸከሙትን ባህዮቻቸው ጭነው፣ እንጨት የሚሸጡበት ማርያም ወንዝ ድረስ አድርሰውላቸዋል። ሌላ ጊዜም ተመሳሳይ የመንገድ መጨናነቅ ተፈጥሮ፣ የተፈጠረውን የትራፊክ ችግር ለመፍታት አንድ የሚኒ ባስ ሹፌር ጭነታቸውን በታክሲው ጭኖ እዚያው መሸጪያ ቦታቸው ድረስ አድርሷቸዋል።
ከዚህ የተነሳ እናቴም ሆነች አጓንዴ እነዚህን ሁለት ኦሮሞ ሴቶችና ባለሚኒባሱን ጨምሮ፣ የቁስቋም ማርያም ማህበር ሲደግሱ ሳይጠሯቸው ቀርተው አያውቁም። ባለአህዮቹም ሆነ ባለሚኒባሱ እቤታቸው ድግስ ካለ፣ በተመሳሳይ፣ እናቴና አጓንዴን ጠርተው ይጋብዟቸዋል።
በዚህ የተነሳ እናቴ ልትድረኝ የምትፈልገው፣ ሱሉልታ ድግስ ተጠርታ ሔዳ ያየቻትን፣ ከእነዚያ ቅንና ደግ ከሆኑ ኦሮሞዎች ውስጥ ያንዱ ልጅ የሆነችውን በቀሉን ነው። አይገምም! እንግዲህ እነዚህ ባንድ ቀን ተደፍረው ባንድ ቀን ያረገዙ፣ በተመሳሳይ ቀን የወለዱ፣ ተደፍረው ልጅ መውለዳቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚመለከቱ፣ እንጦጦ ሲወጡ ተለያይተው የማያውቁ፣ ከእንጦጦ እንጨት ተሸክመው ሲመለሱም ፊትና ኋላ ሆነው ዳገቱን ከመውረድ ውጪ ተራርቀው የማያውቁ ጓደኛሞች፤ ሰሞኑን ግን አጓንዴ ከእነ ጥግርር እንጨቷ፣ በቴሌቪዥን ከዶ/ር ዐቢይ ኋላ ሆና ብቻዋን ታየች።
ለነገሩ "ብቻዬን ሆኜ ፍቶግራፍ አታንሱኝ፣ ጓደኛዬን እምሬን ጠብቋት፣ ከኋላዬ እየመጣች ነው፣" አያለች ነው አሉ፣ ፎቶግራፍ አንሺዎቹ ቸኩለው፣ አጓንዴን ለብቻዋ አንስተው በቴሌቪዥን እንድትታይ ያደረጓት። በዚህ የተነሳ አጓንዴ ብዙ ጊዜ ትፀፀታለች፤ “እንዴት ተለያይተን የማናውቀውን ሰዎች፣ ካንቺ ከጓደኛዬ ለይተው፣ ከዶ/ር ዐቢይ ፊት ለፊት እንድታይ ያደርጉኛል፤ የኦሮሞ ባለ አህያ ሴቶችና ባለሚኒባሶች ይህንን ጉድ በቴሌቪዥን ሲያዩ ምን ይላሉ!?” ትላለች።
አሁንማ እንኳን ለአባይ ግድብ፣ እንኳን ለእንጦጦና ሸገር ፓርክ፣ እንኳን ለደን ልማት ፕሮግራም ---ወዘተ አጓንዴና እናቴ ስራ አግኝተዋል። የሸገር ፓርክ ሠራተኛ ሆነዋል። ከደን ነቀላ ወደ ደን ተከላ ስራ ተዛውረዋል። ቢሆንም ግን እነዛ የእነሱን ጉልበት ጠብቀው
የእለት እንጎቻቸውን አንጉተው የሚበሉ፣ የዕለት ቡናቸውን አፍልተው ፉት የሚሉ የእንጨት ደንበኞቻቸው ጉዳይ አሳስቧቸው ነበር። ሰሞኑን ደግሞ የህዳሴው ግድብ ድምፁ ሳይሰማ ሞልቶ ተገኘ ተባለ። እናም "እኛ ከእንጨት ሸክም እንደወጣን ሁሉ፣ ደንበኞቻችንም ከጭስ አፈና ሊወጡ ነው" እያሉ ነው። እንዳፋቸው ያድርግላቸው፡፡ የሸቀጦችና የአገልግቶች ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመናሩ በተለይ የከተማ ነዋሪዎች እጅግ ለከፋ የኑሮ ውድነት ተጋልጠዋል።
ለመሆኑ  የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንስኤው ምንድን ነው? መፍትሄውስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  ከኢኮኖሚው ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሼ ሰሙ  ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

            በአጭር ጊዜ ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት መባባስን ያስከተለው  ምንድን ነው?
ለዚህ አንድ ምክንያት ብቻ አይደለም ያለው፤ መነሻ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው። አንደኛ ከባለፈው ጊዜያት የቀጠሉ ችግሮች አሉ። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት፣ የምርትና አቅርቦት መቀዛቀዝን፣ የኤክስፖርት መዳከምን፣ የስራ እድል መጥፋትን፣ የንብረት መውደምን…  አስከትሏል።
እነዚህ መፈጠራቸው ሳያንስ ደግሞ ኮሮና የበለጠ የስራ እድል መዳከምንና የምርታማነት  አለመኖርን አስከትሏል። ይህም ኢኮኖሚውን አዳክሞታል። ይህ በእርግጥ ዓለማቀፍ ሁኔታ ነው። ተፈጥሮ ያመጣው ችግር ነው። በሌላ በኩል፤ የበረሃ አንበጣ መንጋ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ውስጥ 23 በመቶውን አውድሟል። ጦርነቱ ያመጣው ምስቅልቅል አለ። ጦርነቱ በራሱ አዲስ ፍላጎት ፈጥሯል። ለጦርነቱ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች በገፍ አስፈልጎታል። መሳሪያ ስንቅና ትጥቅ ማቅረብ ብቻውን በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖው የበረታ ነው። ሌላው የገበያ ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር ነው። በጦርነቱ ከመንግስት በተቃራኒ የቆመው ሃይል፣ ኢኮኖሚው ላይ አሻጥር በመስራት ተንቀሳቅሷል፤ ሆን ብሎ ዶላር በመግዛት፣ እቃ በመደበቅ፣ ሃብት በመሰወር።  የገበያው ሰንሰለት ቀደም ብሎ በጥቂት ግለሰቦች የተያዘ የገበያ አቅርቦቱን ሆን ብሎ በማዛባት፣ አቅም በማሳጣት የተፈጸመም ተፅዕኖ አለ።
ከሁሉም በጣም ከባዱ ደግሞ መንግስት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ   የሚያስፈልገው ገንዘብ በህትመት ከብሔራዊ ባንክ የወጣ መሆኑ ነው። ያ ማለት የአቅርቦት ኢኮኖሚው ሳያድግ፣ የፍላጎት ኢኮኖሚው ነው ያደገው። በገበያ ዝውውሩ ብዙ ገንዘብ እንዲገባ ተደርጓል። በአንፃሩ አቅርቦት የለም። ስለዚህ ብዙ ገንዘብ፣ ያለችው ጥቂት ምርት አሳዳጅ ሆኗል። እነዚህ ተደማምረው ኢኮኖሚው ላይ ከባድ ተፅዕኖ ፈጥረዋል።
የመጨረሻው ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ላይ የተደረገው ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ ጉዳይ ነው። ብር ከዶላር አኳያ 28 በመቶ የሚደርስ ግሽበት እንዲያሳይ ተደርጓል። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች አንድን ኢኮኖሚ ወደ ወድቀት ነው የሚወስዱት። እንደውም የኛ ማህበረሰብ የፍላጎትና የአቅርቦት ጉዳይ በጣም በድህነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ኢኮኖሚው ሊቋቋመው ቻለ እንጂ ሌሎች ሃገሮች ላይ ቢሆን፣ እንደ ሃገር ከፍተኛ ምስቅልቅል ነበር የሚፈጠረው። እነዚህ ነገሮች ተደምረው ነው እንዲህ ችግሩ የተባባሰው።
የዶላር ምንዛሬ በጥቁር ገበያ  በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ በኢኮኖሚው ለይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ሊያብራሩልን ይችላሉ?
በእርግጥ የጥቁር ገበያ ምንዛሬ በቀጥተኛ አካሄዶች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እስካሁን ድረስ ያህል ከባድ የሚባል አልነበረም። ከዚህ በፊት የነበረው የጥቁር ገበያ በአመዛኙ ከባንክ የተፈቀደላቸው ዶላር ሲያንሳቸው፣ ጉዞ ሲያደርጉ በኪሳቸው የሚይዙት ዶላር ሲያስፈልጋቸውና በአብዛኛው የኮንትሮባንድ ንግዱ ነበር ተጠቃሚው። በዚህ ምክንያት ዋናውን የኢትዮጵያ የዶላር ኢኮኖሚ አልነበረም ይጎዳ የነበረው። አሁን ግን በሂደት ዋነኛው የዶላር ኢኮኖሚ መስመሩ የጥቁር ገበያው ሆነ። ዋነኛው መስመር መሆኑ ደግሞ የዶላር ፍላጎቱን አናረው፤ መንግስትም ለአቅርቦት ኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ዶላር ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊ ምክንያቱ ፍላጎት ማደጉ ነው።  ይህ ሁኔታ ፍላጎትን በመጨመሩ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች  ፍላጎት ጨምሯል። ይህም የዶላር ፍላጎት መጨመር እንዲኖር አድርጓል። ያ በመሆኑ ባለችው ትንሽ ዶላር ላይ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ ዋጋው መጨመሩ አይቀርም። ይሄ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ውጤት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ መንግስት ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ጋር በነበረው ግንኙነት፤ የኢትዮጵያ ብር አሁን ባለው ገበያ ተገቢው ዋጋ ላይ አይደለም፤ከዚህ በታች ዝቅ ማለት አለበት የሚል መግባባት ላይ ተደርሷል።  ስለዚህም መንግስት በሂደት ቀስ በቀስ ብር ከዶላር ያለውን ምጣኔ  መቀነስ ነው የጀመረው። ይሄ ሲሆን የቅናሹ መቆሚያ ገደቡ ስለማይታወቅ፣ ሰዎች በራሳቸው ግምት እየተነሱ በየጊዜው የዶላር ፍላጎትን ተከትለው ዶላር ላይ ዋጋ መጨመር ጀመሩ ማለት ነው። አንዳንዱ በአንድ በኩል፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም አለ። በሌላ በኩል፤ መንግስት በጣም ዝግ ያለ የጭማሪ ሂደት ውስጥ በመግባቱ፣ የዶላር ገበያው በግምት ላይ ተመስርቶ፣ በግለሰቦች ፍላጎት ዋጋው እንዲወሰን ተደርጓል።
ሌላው ለዶላር ፍላጎት መጨመር መንስኤው አሻጥር ነው። በርካታ ሰዎች ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ፣ በብዙ ቦታዎች ንብረት  እየሸጡ፣ ሃብታቸውን ወደ ዶላር በመለወጥ፣ ዶላሩን አከማችተው በመያዛቸው፣ የዶላር ዝውውሩ እንዲቀንስ አድርገውታል። እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ናቸው ዶላር በጥቁር ገበያ ዋጋው እንዲንር ያደረጉት።
አሁን ለተፈጠረው የኑሮ ውድነትና የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ጦርነቱ በራሱ ምን ያህል ነው ድርሻው?
የጦርነት ኢኮኖሚ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ጦርነቱ ምን ያህል የወጪ ፍላጎት እንዳለውም አይታወቅም። ያ ማለት ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ለጦርነቱ የሚወጣው ወጪ መጠን ይበዛል፤ ቀለብ፣ የመሳሪያ አቅርቦት በተለይ ተተኳሾች፣ ነዳጅ ወዘተ ምን ያህል ያስወጣል የሚለው አይታወቅም። በዚህ የተነሳ ጦርነቱ የሚያስከትለውን ኪሳራ፣  አስቀድሞ በትክክል መገመት ያስቸግራል። ለእኔ ከጦርነቱ በላይ ባለፉት ሶስት አመት የተከሰተው አለመረጋጋት በተለይም የሰዎች መፈናቀልና መገደል፣ ማህበራዊ ህይወት መናጋት ወዘተ ነው።….ብዙ ችግር ያስከተለው፡፡
አሁን ላይ ላለው ችግር የበለጠውን አስተዋፅኦ እያደረገ ያለው ጦርነቱ፣ ገና መጀመሩ ስለሆነ  የጎላ ተፅዕኖ ልናይ የምንችለው፣ ምናልባት በቀጣይ በጀት ዓመት ነው። አሁን መንግስት ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በህትመት ያቀርባል። ግልፅ መሆን ያለበት መንግስት በቀላሉ  ለዚህ ጦርነት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በሁለት መንገድ እንደሚያገኝ ነው። አንደኛው በእቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ፣ ለእነሱ የተመደበውን ወደ ጦርነቱ ማዞር ነው። ሁለተኛው መንገድ ተጨማሪ ገንዘብ ማተም ነው። እነዚህ ሁለቱም መንገዶች ለአንድ ኢኮኖሚ በጣም ጠንቅ ናቸው። ኢኮኖሚው ወይም አቅርቦቱ ከሚሸከመው በላይ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ሲገባ፣ የሸቀጦች ዋጋ ከሚገባው በላይ እንዲንር ምክንያት ይሆናል። ፕሮጀክቶች ሲታጠፉ ደግሞ በተያዘላቸው ጊዜ ባለመፈጸማቸው፣ ለስራ የተዘጋጀ ሃይል ወደ ስራ እንዳይገባ በማድረግ፣ የስራ እድልን ይቀንሳሉ፤ የስራ አጥነት ቁጥሩን ይጨምራል። በሌላ በኩል፤ አቅርቦትን ያዳክማሉ። በተያዘላቸው ጊዜ አልቀው ቢሆን ምርታቸውን ወደ ገበያ አውጥተው ገበያውን በማረጋጋት አስተዋፅ ይኖራቸው ነበር። ነገር ግን አሁን እኛ እየተጋፈጥን ያለነው ያለፉት ሶስት ዓመታት አለመረጋጋቶች ውጤትን ነው። የጦርነቱ ውጤት ገና ለወደፊት ነው በደንብ ጎልቶ የሚታየው። ከአሁን በኋላ በደንብ ግልፅ እየሆነ ይመጣል።
የሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነቱ ጊዜያዊ ነው ወይስ ዘላቂነት ይኖረዋል?
አሁን ኢኮኖሚያችን ላይ የምናያቸው ችግሮች አንደኛው፣ ታቅደው ታስበው የሚፈጸሙ ሰው ሰራሽ ችግሮች ናቸው። ለምሳሌ በዶላር መወደድ ምክንያት የጤፍ ዋጋ የሚንርበት ምክንያት አይገባኝም። የ300 እና 400 ብር የዋጋ ጭማሪ ማምጣቱ፣ የስግብግብነትና የተፈጠረውን እድል ከሚገባው በላይ የመጠቀም ባህሪ መኖሩ እንዲሁም፣ ተቆርቋሪነት ያለመኖሩ ውጤት ነው። እነዚህ ሰዎች አውቀው አቅደው የሚፈጥሯቸውን ችግሮች መፍታት ይቻላል።- ስርዓትና ህግ በማበጀት፣ አቅርቦቱን በማሻሻል። የሸማቾችና የአምራቾች ህብረት ስራ ማህበራትን እንደገና እንዲያንሰራሩ በማድረግ ብዙ ነገሮችን ማሻሻል ይቻላል።
በሌላ በኩል ማምረት የሁለትና ሶስት ወር ስራ አይደለም። በቂ ዝግጅት፣ በቂ ጥናትና አቀራረብ ይፈልጋል። ጠንካራ ስራዎች መሰራት አለባቸው።  ኤክስፖርት ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የሚያማልል ፖሊሲ መቅረፅ፣ የታክስ ሁኔታዎችን ማሻሻል፣ የተቀላጠፈ የአገልግሎት መዘርጋት፣ የሙስና ሰንሰለቱን መበጣጠስ ያስፈልጋል፤ የጉምሩክ ስርአትን ማሻሻል ያስፈልጋል። እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ደግሞ ጊዜን ይጠይቃሉ።
የሃገር ውስጥ ምርትን መጨመር፣ ኤክስፖርትን ማሳደግና ማስፋፋት ያስፈልጋል፤ እነዚህም  የረጅም ጊዜ  ሥራን ይጠይቃሉ፡፡ ሰው ሰራሽ አሻጥሮች የፈጠሩትን  ችግር ግን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ሰዎችን በማረም፣ ሃቀኞችን በማበረታታትና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ የሸማቾች ማህበራትን በማጠናከር መቅረፍ ይቻላል። በሌላ በኩል፤ መንግስት የገንዘብ ህትመቱን መቀነስ አለበት።
አሁን ባለው ሁኔታ ያለ እቅድ ኢኮኖሚው ከሚሸከመው በላይ በገበያ ያለው ገንዘብ፣ ከ20 እስከ 25 በመቶ የጭማሪ ደረጃ  አሳይቷል። ይሄን ገንዘብ በአፋጣኝ ከገበያው  ሰብስቦ ግሽበትን  ጋብ ማድረግ ያስፈልጋል። አንዳንዴ አቅርቦትን ባላሳደገ ኢኮኖሚ፣ ፍላጎትን ብቻ ተከትሎ መሄድ መልካም አይሆንም።
ብሔራዊ ባንክ ንብረትን አስይዞ መበደርን መከልከሉ በኢኮኖሚው ላይ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
እንደውም የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ዘግቷል ማለት እንችላለን። በትክክለኛው ሰዓት ቢወሰን ኖሮ ብዙ ችግር መቅረፍ ይቻል ነበር። አሁን ቢዘገይም ውሳኔው ትክክል ነው። ባንኮች የገንዘብ ስርጭታቸውን እንዲቀንስ መደረጉ፣ በተለይ ብድር በተሰጠ ቁጥር ወደ ገበያው የሚገባውን የገንዘብ መጠን መቀነስ ያስችላል። ስለዚህ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
እስቲየኑሮ ውድነቱን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የውሳኔ እርምጃዎች ይንገሩን?
የመንግስት ሰራተኛውን ደመወዝ በማሻሻል የሚቀረፍ ችግር አይኖርም። ዋናው አቅርቦትን ማሳደግ ነው። አሁን በየሰው ኪስ የሚገባው ገንዘብ መጠን ጨምሯል። ነገር ግን አቅርቦት ባለመኖሩ በየሰው ኪስ የገባው ገንዘብ ጥቂት ምርትን ነው የሚያሳድደው። ስለዚህ መንግስት ደሞዝ ከመጨመር ይልቅ አቅርቦት ማሳደግ ላይ ቢሰራ ነው የተሻለ የሚሆነው።
ሌላው የአገልግሎት ዋጋዎች ላይ ቅናሽ ማድረግ ነው። የመብራ፣ ስልክ፣ ውሃ፣ ታክስ የመሳሰሉት ላይ ቅናሽ ማድረግ ያስፈልጋል። ታክስ ሲባል የገቢ ታክስ ማለት ሳይሆን አቅርቦት ላይ የሚጣሉ እንደ ኤክሳይስ ታክስ፣ ሱር ታክስ የመሳሰሉትን ነው። እነዚህ ላይ ቅናሽ ቢደረግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል። ለምሳሌ የመብራት ወጪ ለምግብ ከሚወጣው የሚተናነስ አይደለም። እዚህ ላይ ቅናሽ ማድረግ ያስፈልጋል። በዋናነት ግን በሁሉም ዘርፍ አቅርቦትን ማሳደግ ነው ወሳኙ። በእህል ምርቶች ላይ የሚጣሉ ታክሶችን ማሻሻል ተገቢ ነው። የዳቦ  አምራቾችን በተለይ በስፋት የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ማበረታታት ጠቃሚ ነው። መንግስት ትልቁ ስራው ዜጎች እንዳይራቡ ማድረግ ነው፤ የዜጎችን በልቶ ጠጥቶ የማደርን ፍላጎት  ማረጋገጥት የችሮታ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታው ነው። ይህን ካልተወጣ መንግስት ዋነኛ ሃላፊነቱን ዘንግቷል ማለት ነው።

 በትግራይ  የተፈጠረው ጦርነት ያስከተላቸው ሰብአዊ ቀውሶች የተራዘመ ጊዜ ችግር ሆነው ሊቆዩ እንደሚችሉ ያስገነዘበው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጦርነቱ በአማራና አፋር ክልልም በመቶ ሺዎችን አፈናቅሎ ለእርዳታ ጠባቂነት ዳርጓል ብሏል።
በትግራይ ክልል ካሉ አጠቃላይ 5.2 ሚሊዮን ያህል ተረጅዎች ውስጥ 4 መቶ ሺህ ያህሉ  ለእርዛት መዳረጋቸውን ያመለከተው የተቋሙ ሪፖርት፤ 75 በመቶ ለሚሆኑ አጠቃላይ ተረጂዎች የህውኃት ታጣቂ ሃይል በፈጠረው ጦርነት ምክንያት መተላለፊያ ኮሪደር ባለመገኘቱ  እርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ ጠቁሟል።
በአሁን ወቅት የምግብ አቅርቦት ወደ ትግራይ እየገባ ያለው በአፋር በኩል በአባኦላ መሸጋገሪያ ብቻ መሆኑንና በዚያም በኩል ቢሆን መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ በነበረበት ወቅት ህውኃት ጦርነቱን በመቀጠሉ መተላለፊያውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብሏል- የተቋሙ ሪፖርት።
በአሁን ወቅት ወደ ትግራይ በቂ እርዳታ እየገባ ካለመሆኑም ባሻገር በቀጠለው ጦርነት ምክንያት አርሶ አደሮች የእርሻ ተግባራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉና  ሪፖርቱ አመልክቶ ይህም ችግሩን እንዲራዘም ያደርገዋል ብሏል።
በበርካቶቹ የትግራይ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የእርሻ ጊዜውን መጠቀም ሳይችሉ መቅረታቸውንና አጠቃላይ ሊመረት ከሚገባው የሰብል ምርት ከ25 እስከ 50 በመቶ ያህሉ ብቻ መከናወኑን ሪፖርቱ አመልክቷል።
በዚህም ትግራይ ያለው ችግር እስከ ጥቅምት 2015 ሊቆይ እንደሚችል ከወዲሁ የተገመተ ሲሆን በዚህም ዜጎች በእጅጉ ተጎጂ እንደሚሆኑ ተመልክቷል።
በትግራይ አሁንም ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ የምግብና የጤና አቅርቦት እጥረት የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ እየፈተነ ከአመት በላይ እንደሚዘልቅ ሪፖርቱ ያመለክታል።
የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የየብስና አየር ትራንስፖርት ግንኙነት መቋረጡም የክልል ነዋሪዎች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጦ እንዲቆይ ከማድረጉም ባሻገር፣ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለሰው ልጅ አስፈላጊና መሰረታዊ ከሆኑ መካከል አንዱ የመረጃ ልውውጥ ግንኙነት እንደመሆኑ የትግራይ ህዝብ ከመረጃ ርቆ በአፈና ውስጥ እንዲቆይ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በተዛመተው ጦርነት ከሁለቱም ክልሎች ከ8 መቶ ሺህ ያላነሱ ዜጎች መፈናቀላቸውን፣ የክረምት የእርሻ ተግባር መስተጓጎሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ይህም ሃገሪቱን በተራዘመ ሁኔታ ለሚፈትን የሰብአዊ ቀውስ እንደሚያጋልጣት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ሪፖርት አመልክቷል።

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ እመት ጦጣ እሰው ማሳ ገብታ፣ እሸት ስትቦጠቡጥ፣ የማሳው ባለቤት ይደርስባትና ይይዛታል። ከዚያም እግቢው ውስጥ ካለው ትልቅ ግንድ ላይ ጥፍር አድርጎ ያስራትና ወደ ቤቱ ይገባል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አያ ዝንጀሮ እየተጎማለለ ሊጠይቃት ይመጣል።
አያ ዝንጀሮ፡
“እመት ጦጢት እንዴት አረፈድሽ?”
ጦጢትም፤ “ደህና አርፍጃለሁ። አንተስ  ደህና ነህ?”
አያ ዝንጀሮ፤ “በጣም ደህና ነኝ። ወደ ሰፈርሽ ብቅ ብዬ ለዐይኔ ሳጣሽ፣ የት ሄዳ ይሆን እያልኩ ስጨነቅ ነበር “
ጦጢትም፤ “ቆየሁ´ኮ! ብታይ ጌታዬ፣ ሰብሉ ውስጥ ከያዘኝ ጀምሮ ብዙ አሰረኝ።”
“ምን አጠፋሽ ብሎ ነው?”
“ምን እባክህ እኔ ለራሴ ሆድ የለኝ። የአገር ምግብ አምጥቶ፣ ይሄን የመሰለ ምግብ እኔ ቤት እያለልሽ ምን ልሁን ብለሽ ማሳዬ ውስጥ ገባሽ ብሎ ነው!”
“አንቺ ለምን እምቢ አልሽ?”
“ይገርምሃል! በጣም ጥግብ ብያለሁ። ከዚህ በኋላ ማር አልልስም!”አለች።
አያ ዝንጀሮም፤ “ወይኔ! እኔ ባገኘሁት ጥርግ አድርጌ ነበር የምበላው” አለ።
ጦጢትም፤ “እኔ በጣም ስለመረረኝ ማን ይተካኛል?” እያልኩ ስጨነቅ ነበር።”
ዝንጀሮ ተስገብግቦ፤
“እንዴ! እኔ ልተካሽ ታዲያ?”
“አርገኸው ነው አያ ዝንጀሮ!”
“መልካም፤ በይ ልፍታሽና አንቺ እሰሪኝ።”
“እሺ የእኔ ቆንጆ!” ብላ ተፈታች።
ከዚያም ዝንጀሮን ከግንዱ ጋር ጥፍር አድርጋ አሰረችውና፤
“በል የሚበላ ነገር ልፈልግ”፣ ብላው ሄደች።
ቆየት ብሎ የሰብሉ ባለቤት መጣ።
ከዚያም በጦጣዋ ቦታ ዝንጀሮን ታስሮ አገኘውና፤
“ምን ልታደርግ እዚህ ተገኘህ!?” አለው።
“ጦጢትን ተክቼ አንተ የምታቀርበውን ምግብ እየጠብኩኝ ነው።”
ባለ ሰብሉም ወደ ቤት ገብቶ ጉማሬ አለንጋውን ይዞ መጥቶ፣ የውስጥ ቆዳው ውጪ እስኪታይ ሙልጭ አድርጎ ገረፈና ለቀቀው።
ዝንጆሮም፤
“አይለመደኝም!” ብሎ ምሎ ተገዝቶ ተለቀቀ።
*   *   *
ብልጦች እንዳያሞኙንና መጫወቻ እንዳያደርጉን እንጠንቀቅ።
ከሁሉ በፊት፤
“ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” የሚለውን ተረት አንዘንጋ።
አያ ዝንጀሮ፤ “ጦጢት ለምን ታሰረች” የሚለውን ጥያቄ ባለመጠየቁ፤ በጦሷ ገብቶ፤ ያስጠይቀኛል ሳይል ቀለጠ። እንደተስገበገበ የአለንጋ ዋጋውን ቀመሰ።
የሌሎችን ንብረት፣ የሌሎችን ፈንታ መውሰድ ቀርቶ መመኘትም ትክክል አይደለም። ያልለፋንበትን፣ ያልደከምንበትን ገንዘብ አንፈልግ፣ ንብረትም ላግኝ አንበል። ይሄ ልማድ እያደረ ያልተመቸን ጊዜ ወደ መስረቅ ወደ መመዝበር ይሄዳል። አለመታመን የረባ የኃላፊነት ቦታ ላይ አለመሾምን ያመጣል። በላብ ዋጋ አለመክበር የሚከሰተው፣ በአግባቡ የመበልፀግን ጉዳይ፣ ሂሳብ ውስጥ ካለማስገባት ነው።  ውርደት ከሌብነት የሚመጣ  አባዜ ነው። ሁሉንም ነገር ስናደርግ ጥንቃቄንና አለመጣደፍን ሥራዬ ብሎ ማጤን ይገባል። ጥንቃቄ ወደ ፍርሃት እንዳያደርሰንም ከመሰረቱ ብልህነትንና ዘዴ ማወቅን እንደሚጠይቅ ልብ እንበል። አለመጣደፍ ዋና ጉዳይ ነው ስንል፤
“ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ”
…የሚለውን የትናንት ግጥም ሳንረሳ ነው። ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም ዋና ነገር ነው። ናፖሊዮን ቦናፓርት እንዳለው፤
“የተወሰደብንን ቦታ ማስመለስ እንችላለን።
ያጣነውን/ያጠፋነውን ጊዜ ግን ማስመለስ አይቻለንም።”
አንድም ደግሞ እያጎ እንዳለው (በሼክስፒር ልሳን)፤
“አንዴ የሆነን ነገር ለምን ሆነ ማለት
ለማለት ብቻ ማለት…”
አንዴ ሆኗልና ወይ ለማረም፣ ወይ ከናካቴው ስለ ነገሩ እርግፍ አድርጎ ለመርሳት ዝግጁ መሆን  መለኛነት ነው። ይህ እሳቤ አዲስ ዘዴ ወደ መቀየስ ሊወስደን ስለሚችል፣ ለህይወታችን ሂደት ዓይተኛ ግብዓት ይሆነናል። ከዕድል ሁሉ መልካም ችግርን በትክክል የመፍታት ፀጋን መጎናፀፍ ነው። ወደተነሳንበት ሀሳብ ተመልሰን በለሆሳስ ስናስቀምጠው፤ ለኔ ብቻ ማለትን፣  ሁሉን ልብላው ማለትን፣ መስገብገብን እናስወግድ ዘንድ የህይወት ተመክሮ ይመራናል። አለበለዚያ ብዝበዛ፣ ምዝበራ፣ ዘረፋ ደረጃ የሚያደርሰን የራስ ወዳድነት አባዜ ነው!
“ሆዱን ያየ ሆዱን ተወጋ” ከላይ ያነሳናቸውን መዘራዝሮች ሁሉ የሚያካትትልን ለዚህ ነው!!


በፕርሽያ የህክምና ሙያና ጥናት ረዥምና የዳበረ ታሪካ ያለው ነው፡፡ የጥንት ኢራናውያን መድሀኒቶች ከሜሴፖታሚያ፤ ከግብጽ፤ ከቻይናና፤ ከግሪክ የህክምና ባህሎች የተወጣጣ ሲሆን ይሄ ከአራት ሺ አመታት በላይ ሲዳብር የነበረ እውቀትና የህክምና ሙያ ነው  በ13ኛው ክፍለ ዘመን ለአውሮፓ  የህክምና ሙያ መሰረት የሆነው።
ጁንዲሻፑር ዩኒቨርስቲን (3ኛው ክ/ዘመን ኤዲ) የመሳሰሉ የኢራን የትምህርት ማዕከሎች፣ ከተለያዩ ሥልጣኔዎች የወጡ ታላላቅ ሳይንቲስቶች መፈልፈያ ነበሩ፡፡
የኢራን የህክምና ባለሙያዎች፣በታላቁ የእስልምና ሥልጣኔ ወቅት፣ በህክምና ሳይንስ ለተመዘገበው ዕድገት ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በመካከለኛውና ቅርብ ምስራቅ የመድሃኒት ቅመማና ሥርጭትን ጨምሮ የህክምና ሳይንስ ወደ ጥንት የሜሶፖታሚያ ዘመን የሚዘልቅ ረዥም ታሪክ አለው ፡፡
 ኢራን ማናቸውንም ዓይነት የጤና ክብካቤ አገልግሎቶች በማቅረብ ከሚጠቀሱ የዓለማችን ምርጥ አገራት አንዷ ናት፡፡ ግሩም የጤና መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች አሏት፤ ዓለማቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ፡፡ በላቀ ደረጃ የተማሩና የሠለጠኑ የህክምና ባለሙያዎች አፍርታለች፡፡ ከምዕራባውያንና ምስራቅ አገራት አንጻር የህክምና አገልግሎት ክፍያ በእጅጉ ተመጣጣኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው የላቀ ጥራት ያለው የጤና ክብካቤ አገልግሎት ወይም የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚፈለጉ ህመምተኞችና ቱሪስቶች የትኩረት ማዕከል የሆነችው፡፡
የህክምና ቱሪዝም በኢራን
የህክምና ቱሪዝም ወይም የህክምና ጉዞ (ሜድ ቱር)፤ የኢራን የህክምና ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ከተጫወቱ ዘርፎች አንዱ ሲሆን  እያንዳንዱን የሰው ልጅ ህይወት ትናንሽ ክፍል ያካትታል፡፡ ይህን ዕድገት በተጨባጭ ለማየት ወደ ኢራን ተጓዙ፡፡ በርግጥ የህክምና ጉዞ (med tour) ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እያንዳንዱን የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ ነው፡፡
የህክምና ቱሪዝም ባለው ዕምቅ አቅምና ተነፃፃሪ ብልጫ የተነሳ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል፡፡ የህክምና ቱሪዝም፤ ከነዳጅ ኢንዱስትሪው (oil industry) እና አውቶሞቢል ኢንዱስትሪው በመቀጠል በዓለም 3ኛው ትልቁ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በአገሪቱ  የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ትርጉም ያለው አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን በቅርቡ ያለ ጥርጥር የዓለማችን ቁጥር 1 ትልቁ ኢንዱስትሪ ይሆናል፡፡
ኢራንን እንደ ህክምና ቱሪዝም መዳረሻነት ለመምረጥም ሆነ ወደ ኢራን ለመጓዥ ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ አስደማሚ ችሎታ ካላቸው የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች እስከ ግሩም የደንበኛ አገልግሎት እንዲሁም ከዝቅተኛ የህክምና ክፍያ እስከ የኢራን ከተሞች ውብ መስብህ ድረስ የሚዘልቅ፡፡
በአነስተኛ ወጪ ህክምና ለማግኘት ወደ ኢራን ተጓዙ፡፡ ዝቅተኛ የህክምና ክፍያ፣ ከኢራን የህክምና ቱሪዝም ጥቅሞች አንዱ ነው፡፡
የኢራን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ሰፊ ነው፡፡ በርካታ የህክምና ቱር ኩባንያዎች አሉ፡፡ አሊያም እንደ ታላቁ ዛንጃኒስ ያሉ ሆቴሎች አሉ፡፡ አንዱ የዛንጃን ሆቴል ለምሳሌ በህክምና ቱር ረገድ ሊረዳችሁ ዝግጁ ነው፡፡
ኢራን በህክምና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው በእጅጉ አድርጋለች፡፡ የጤና ቱሪዝም በይፋ የተጀመረው እ.ኤ.አ ከ2003 አንስቶ ቢሆንም፤ ዘርፉ በዓይን ቀዶ ህክምና፣ በካንሰር፣ በውስጥ አካላት ቅድመ ተከላ፣በዓይን ህመም ፈውስ በፊትም ይታወቃል፡፡ በተዋጣላቸው የህክምና ባለሙያዎች፣ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ታገኛላችሁ፡፡ ከዚያም በምቹና አስደሳች ከባቢ ውስጥ በፍጥነት ጤናችሁን ትቀዳጃላችሁ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኩዌት፣ ኳታርና ኢራቅን ጨምሮ ከአረብ አገራት በርካታ ዜጎች ለህክምና ወደ ኢራን ይመጣሉ፡፡ በብቃት በተደራጁና ጥራታቸውን በጠበቁ ሆስፒታሎች ውስጥ ይታከማሉ፡፡ ከአውሮፓ አገራት ይልቅ ኢራንን ይመርጣሉ፡፡ አንድም የህክምና ዋጋ ከአውሮፓ በእጅጉ ዝቅተኛ በመሆኑ፤ አንድም ደግሞ ለቅርበቱ፡፡
የዛሬዋ ኢራንና  አቅሞቿ
ከአብዮቱ ድል  በፊት ኢራን  በጤናውና ህክምናው ዘርፍ  ጥገኛ ከሆኑ አገራት አንዷ ነበረች፡፡ ከእስላማዊ አብዮቱ ድል በኋላና አሁን ደግሞ (ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ) በዓለም ከሚገኙ ዋነኛ የህክምና ማዕከላት አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡
ኢራን በአሁኑ ወቅት  ከሚያስፈልጓት መድሃኒቶች ውስጥ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነውን በአገር ውስጥ እያመረተች ሲሆን ከ14 በላይ recombination መድሃኒቶችም ታመርታለች፤አብዛኛውም ካንሰርን ለመሳሰሉ በሽታዋች ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ ኢራን በደም መተካት ህክምና (blood transfusion medicine) ዘርፍ በእሰያ ካሉ 5 ቀዳሚ አገራት አንዷ ናት፡፡ በተጨማሪም በዓለም ሁለተኛዋ የፕላዝማ ቴራፒ ፕሮጀክት ተግባሪ ናት፡፡
የኢራን የጤና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ በውበትና ትሪትመንት ዘርፍ የተሟላ የህክምና አገልግሎቶችን  ይሸፍናል፡፡ የፊት እንዲሁም የእጅና እግር ውበት፣የጥርስ ማስተካከያ፣የመካንነት፣ የውፍረት ቅነሳ ቀዶ ጥገና፣የጀርባ ህመም፣የልብ ህመም፣የዓይን ቀዶ ጥገና፣የተለያዩ ካንሰሮች ሴል (ቲሹ) ምርመራና ህክምና፣ እንዲሁም የውስጥ አካል ቅድመ ተከላ፣የነርቭ ቀዶ ጥገና እና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች በኢራን ይሰጣሉ፡፡
የፕላስቲክ ቀዶ ህክምናዎች በኢራን
ኢራን በዓመት ውስጥ በሚከናወኑ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምናዎች ብዛት በዓለም  ቀዳሚዋ ናት፡፡ በኢራን በዘመናዊ የህክምና ተቋማት ውስጥ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና በሚያደርጉ ግለሰቦች ዘንድ ከተቀዳጀችው እምነት ባሻገር፣ በፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ዋጋ አንጻር በኢራንና ሌሎች አገራት መካከል ያለው ከፍተኛ ልዩነት ህመምተኞች ኢራንን ተመራጭ  እንዲያደርጓት አበረታቷቸዋል፡፡
የህክምና አገልግሎት በኢራን ለምን?
ኢራን  የዓለም ጎብኚዎችን በሚያማልሉት ባህላዊ፣ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ትንግርቶቿ ትታወቃለች፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት ደግሞ የህክምና ቱሪዝም በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ወደ አገሪቱ እንዲጓዙ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡
ኢራን በዓለም ቀዳሚ ከሆኑት የጤና ቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ናት፡፡ ከመላው ዓለም የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደዚህች አገር የሚጓዙ ህመምተኞች  በከፍተኛ መጠን እየጨመሩ መጥተዋል፡፡
መንግስት የጤና ቱሪዝሙን በንቃት እያስተዋወቀ ነው፡፡ ኢራን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመላው ዓለም ለሚመጡ ጎብኚዎች አስተማማኝ የህክምና መዳረሻ ሆናለች፡፡
የህክምና ማዕከላትና ሆስፒታሎች የጤና ቱሪዝም ያለውን አቅም ተገንዝበዋል፤ እናም ግሩም የማረፊያ ስፍራ፣የላቀ ህክምና፣ ተመጣጣኝ ዋጋና ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶች የሚያቀርቡ ተቋማት ለጎብኚዎች (ተጓዦች) ግሩም አማራጭ ሆነዋል፡፡
በኢትዮጵያና በኢራን መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበትን 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢራን የባህል ማዕከል የታዳጊዎች የስዕል ውድድር አዘጋጅቷል፡፡
የውድድሩ ጭብጥ ፡- የኢትዮ - ኢራን ወዳጅነት
ዕድሜ ፡- ከ 11 እስከ 16 ዓመት
የማስረከቢያ ቀነ-ገደብ፡-   ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ እስከ  መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም  ድረስ
የኢራን ባህል ማዕከል ለውድድሩ አሸናፊዎች  ሽልማት ይሰጣል፡፡
የውድድር ጭብጡን ወይም ደንቦችን በተመለከተ ጥያቄ ካለዎት በኢሜይል አድራሻችን፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይጻፉልን፡፡
ለበለጠ ዝርዝር መረጃ የፌስቡክ ገፃችንን ይጎብኙ፡፡
https://www.facebook.com/IranianculturalcenterInaddisababa

Page 7 of 546