Administrator

Administrator

አክሰስ ሪል እስቴትን ለማስቀጠል ያቀረቡት ጥናት አዋጪ ነው ተብሏል

ከሁለት አመታት በፊት በአክሰስ ሪል እስቴት ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ አገር ጥለው የተሰደዱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ ከመንግስት አካላት ጋር በተደረገ ድርድር ወደ አገራቸው ገብተው የጀመሯቸውን ስራዎች ለማስቀጠልና ከተለያዩ አካላት ለቀረቡባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በመስማማት ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
አክሰስ ሪል እስቴት አክስዮን ማህበር ክፍያ የተቀበለባቸውን ቤቶች በወቅቱ ሰርቶ ማጠናቀቅና ለቤት ገዢዎች ማስረከብ ባለመቻሉ ከቤት ገዢዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ከቀረቡባቸው ክሶች ለመሸሽ አገር ጥለው የወጡት የአክሰስ ሪል እስቴት፣ የአክሰስ ካፒታልና የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል መንግስት በሰጣቸው ያለመከሰስ ዋስትና ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎችና ባለአክስዮኖች በጋራ ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነት በኩባንያው ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ውጤት አልባ መሆኑን ተከትሎ፣ መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ባመለከቱት መሰረት የሚመለከታቸው የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴትን ችግር ለመፍታት ያስችላል በሚል አቶ ኤርሚያስ አዘጋጅተው የላኩትን የአክሲዮን ማህበሩ ወቅታዊ ሁኔታና የቀጣይ አቅጣጫ አመላካች ሰነድና የማገገሚያ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ዝርዝር ሃሳብ ሲመረምር የቆየው ኮሚቴው፤ የግለሰቡን ሃሳብ አዋጭነት በመገንዘብ ያወጡትን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
አቶ ኤርሚያስ ችግሩን መፍታትና ዕቅዱን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት፣ ከተመሰረቱባቸውና ሊመሰረቱባቸው ከሚችሉ ክሶች ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ ሲችሉ እንደሆነ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታ ያጤነው ኮሚቴው፤ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ያለመከሰስ ዋስትና ተሰጥቷቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውንም ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ኮሚቴው ከወራት በፊት በሰጠው መግለጫ፤ አክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ካሉበት እዳዎች ይልቅ ሃብቱ እንደሚበልጥ ጠቅሶ፤ ተገቢው የተቀናጀ ስራ ከተሰራ ኩባንያው ማገገምና የጀመራቸውን ስራዎች ማጠናቀቅ እንደሚችል መገለፁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

       የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅ/ሲኖዶስ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያንን አዋርደዋል፤ አባቶችን ዘልፈዋል›› ያላቸው አለቆች ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ በፓትርያርኩ ትእዛዝ መታገዱ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ሰንበት ት/ቤቶች ተቃውሞ ገጠመው፡፡
የአ/አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ባለፈው ሳምንት እሑድ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አዳራሽ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባካሔደው የግማሽ ቀን ውይይት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው ‹‹አማሳኝ አለቆች›› ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ባለመፈጸሙ ቤተ ክርስቲያኒቱ በከፋ ኹኔታ እየታወከችና እየተመዘበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
ፓትርያርኩ ውሳኔ እንዲቆዩ ማዘዛቸውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውሳኔውን ለማስፈጸም ባለመቻሉ፣ ‹‹አማሳኝ አለቆች›› በሚል የተገለጹ የአድባራት ኃላፊዎች እንቅስቃሴያቸውን ለሚቃወሙ አገልጋዮች ስም እያወጡ፣ በገንዘብ ኃይል ከሥራቸው እንዲፈናቀሉና ያለፈቃዳቸው እንዲዘዋወሩ፤ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የድርሻቸውን እንዳይወጡ ከመዋቅር ውጭ ባደራጇቸው አካላት እየከፋፈሉና በፖሊቲከኛነት እየወነጀሉ ከአገልግሎት በማገድ ለእስርና እንግልት እየዳረጉ እንደኾነ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
“የአማሳኝ አለቆች” ቡድኑ ‹‹ፓትርያርኩ በእጃችን ናቸው፤ የምንፈልገውን እናስፈጽማለን›› በሚል ዕድገትና ሹመት ለማሰጠት ወደኋላ እንደማይልና ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ በዋናነት ‹‹ሊያሠሩን አልቻሉም›› ያላቸውን የወቅቱን የሀገረ ስብከቱን ረዳት ሊቀ ጳጳስ የመወንጀል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፤ ከመጪው የግንቦት ቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ በፊት ከሓላፊነታቸው የሚነሡበትን ተቃውሞ የማጠናከር ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡  ቅ/ሲኖዶሱ በ‹‹አማሳኝ አለቆች›› ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አለመፈጸሙ፣ ‹‹እነ እገሌ ምን ኾኑ? እኛስ ምን እንኾናለን?›› በሚል እየተዘበተበትና ‹‹በእግሩ የመጣ በመኪና ይሔዳል›› በሚልም ለከፋ ሙስና በር እንደከፈተ ተናግረዋል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ የታቀደው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ በ‹‹አማሳኝ አለቆችና ቲፎዞዎቻቸው የውኃ ሽታ›› መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፤ ያለተጠያቂነት የሚፈጽሙት ቤተ ክርስቲያኒቱን የመለያየትና የመመዝበር ድርጊት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን የአገልግሎት ተነሣሽነት እየጎዳ ከመኾኑም በላይ ‹‹የቅ/ሲኖዶሱ ልዕልና ጠፍቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ በግለሰቦቹ እጅ ላይ ያለች አስመስሏታል›› ብለዋል፡፡ ‹‹ወዳልተፈለገ ነገርስ አያመራም ወይ?›› ሲሉም ውይይቱን ለሚመሩት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የአንድነቱ ሊቀ መንበር ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡
‹‹በሃይማኖት ሕጸጽ የሚጠረጠሩ ሰባክያን ተመድበውብናል›› ያሉ የመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስና የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች በበኩላቸው፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት በዝማሬና በስብከተ ወንጌል የመሳተፍ መብታቸው አስተምህሮዋን በሚፃረሩ የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎችና ሕገ ወጥ ሰባክያን ስምሪት መታወኩን በምሬት ገልጸዋል፡፡ በሰሚት መድኃኔዓለም በግለሰቦች ፍላጎት የባለጸጋ ልጆች ብቻ ተሰብስበው የሚማሩበት ሁኔታ መፈጠሩን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ‹‹የሀብታምና የድኃ›› ብሎ የመክፈል አዝማሚያ መስተዋሉን አስረድተዋል፡፡ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር ይህ ዐይነቱ አካሔድ እንዲታገድ በጠየቀው መሠረት በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተሰጠው መመሪያ በደብሩ አስተዳደር ተቀባይነት ባለማግኘቱ የአመራር አባላቱ እስከመታሰር መድረሳቸው በእንባ ተገልጧል፡፡
በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ትምህርትና ቃለ ምዕዳን የሰጡት በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ጉበኞች ፈጽሞ እንደማይተኙ ጠቁመው እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴም መረጃው እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ እንቅስቃሴአቸው የተደራጀና በከፍተኛ ገንዘብ የተደገፈ እንደኾነ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸው፣ ‹‹ጥቅማቸው እንዳይዘጋ በሰው ሕይወትም ከመምጣት ወደኋላ አይሉም›› ብለዋል፡፡ ይኹንና ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፓትርያርኩ አንሥቶ ሙስናን ለመዋጋት ወደ ኋላ እንደማትል አረጋግጠዋል፡፡
‹‹መሾምና መሻር የእናንተ ድርሻ ባይኾንም ስለ ቤተ ክርስቲያን ግን አይመለከታችኹም አይባልም፤ እንዲያውም የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የአስተዳደሩ ሐሳብ መጋቢዎች ናቸው፤›› ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፤ ወጣቱ በትጋትና በብልሃት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አጥር ኾኖ ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ከየአጥቢያው በተነሡት ችግሮች ዙሪያም የሚገባውን ያኽል አልሠራም ካሉት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ ኹሉም ራሱን እንዲፈትሽና የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ ውይይቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው አቡነ ቀሌምንጦስ አስታውቀው፤ ‹‹አማሳኞች›› የወጣቱን ጥያቄ ከመንገድ በማውጣት ከግንቦቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ ትንኮሳ ከመፍጠር ስለማይመለሱ እንደ ዜጋም እንደ ሃይማኖተኛም በትዕግሥትና በሰላማዊ መንገድ መዋቅርን ጠብቆ በመንቀሳቀስ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
ቁጥራቸው ከ780 በላይ የኾኑ የሰባቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሰንበት ት/ቤት ክፍሎች ሓላፊዎችና የ160 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አመራሮች በተገኙበት በዚኹ የውይይት መርሐ ግብር÷ ሰንበት ተማሪው በሃይማኖት ሕጸጽ በሚጠረጠሩና አፍራሽ ተልእኮ ባላቸው ሰባክያን ዙሪያ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋቋመው አጣሪ አካል እንዲያቀርብ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በተያያዘ ዜና÷ የውይይት መርሐ ግብሩን እንደ ስጋት ከሚመለከቱ አካላት እንደኾነ የተጠረጠረ ዛቻና ማስፈራሪያ በሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤት አንድነት አመራሮች ላይ እየተፈጸመ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡ በዕለቱ ውይይቱን ሲመሩ በነበሩት የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሊቀ መንበር ቀሲስ ኄኖክ ዐሥራት ዛቻና ማስፈራሪያው ከደረሰባቸው አመራሮች አንዱ እንደሆኑ የጠቆሙት ምንጮች፤ ‹‹መንግሥት ከኛ ጋር ነው፤ አንተን ለማጥፋት ጥቂት ገንዘብ ይበቃናል›› የሚሉ ግለሰቦች ሳያቋርጡ በስልክ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዳደረሱባቸው ገልጸዋል፡፡

በአደረባት ድንገተኛ ሕመም ሕይወቷ ያለፈው  ደራሲና ጋዜጠኛ እቱ ገረመው የቀብር ሥነ ሥርዓት የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም በትውልድ ሀገሯ አርባ ምንጭ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በርካታ ወዳጅ ዘመዶቿና የከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
የአንዲት ሴት ልጅ እናት የነበረችው ጋዜጠኛ እቱ ገረመው፥ በአዲስ አድማስ፣ በኔሽንና በኢትዮ- ቻናል ጋዜጦች፣ በእፎይታና በቢዝነስ ታይምስ መጽሔቶች፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በዛሚ ሬዲዮ ላይ በጋዜጠኝነት ሞያዋ ሠርታለች፡፡
ጋዜጠኛዋ ባለፉት ሦስት ዓመታት “ማሺሪያ” (በወላይትኛ ሴትዮዋ ማለት ነው) የተሰኘና በሴቶች ላይ ትኩረት አድርጐ የሚታተም መጽሔት ስታዘጋጅ የቆየች ሲሆን፤ በዚህ መጽሔት በአርባ ምንጭና በአካባቢው የሚታዩ የሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጥ፣ የክልሉ ሴቶችን ጭቆና በመታገልና መብታቸው እንዲከበር የበኩሏን ጥረት አበርክታለች፡፡ ጋዜጠኛዋ እቱ  “የጭን መነባንብ” የተሰኘ ልብወለድ መጽሐፍም ለኅትመት አብቅታለች፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፥ በእቱ ገረመው ድንገተኛ ህልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለፅን፤ ለልጇ፣ ለቤተሰቦቿና ለወዳጅ ዘመዶችዋ መጽናናትን እንዲሰጣቸው እንመኛለን፡፡

አንድ ስዕል 300 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል
የኳታሩ ሚ/ር ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የመንግስት በጀት ለስዕል ግዢ አውጥተዋል

በፈረንሳዊው ሰዓሊ ፖል ጎጊን እ.ኤ.አ በ1892 የተሳለውና “ናፊያ ፋ ልፖኢፖ” የሚል ርዕስ ያለው ስዕል በአለማችን የስዕል ስራዎች ሽያጭ ታሪክ ክብረ ወሰን ባሰመዘገበ መልኩ በ300 ሚሊዮን ዶላር መሸጡን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የሁለት ልጃገረዶችን ምስል የሚያሳየው ይህ ስዕል፣ ሩዶልፍ ስቴችሊን በተባሉት ስዊዘርላንዳዊ የስነጥበብ ስራዎች ሰብሳቢ ግለሰብ ባለቤትነት ኩንስት በተባለ ሙዚየም ውስጥ ለረጅም አመታት እንደቆየና ሰሞኑን በኳታር ለሚገኝ አንድ ሙዚየም እንደተሸጠ ዘገባው ጠቅሷል፡፡
በስቴችሊንና በኩንስት ሙዚየም መካከል በቅርቡ አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ፣ ግለሰቡ ስዕሉን ለኳታሩ ሙዚየም ለመሸጥ መወሰናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኳታር ከዚህ ቀደምም በስዕል ሽያጭ ታሪክ ከፍተኛው ገንዘብ የተከፈለበትንና በሰዓሊ ፖል ሴዛኔ የተሳለውን የስዕል ስራ በ158 ሚሊዮን ፓውንድ መግዛቷን አክሎ ገልጧል፡፡
ኳታር ለስነጥበብ ስራዎች ግዢ ከፍተኛ ገንዘብ እንደምታወጣና፣ ባለፈው አመት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የቀድሞው የኳታር የባህል ሚኒስትር ሼክ ሳኡድ ቢን ሞሃመድ አል ጣኒ፣ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ወጪ በማድረግ ለስነጥበብ ስራዎች ግዢ ማዋላቸውንም አስታውሷል፡፡


“ምርጫውን ያራዘሙት ሽንፈት ስላሰጋቸው ነው” ተቃዋሚዎች
*የአሜሪካና እንግሊዝ መንግስታት ምርጫው መራዘሙን ተቃውመዋል


በዛሬው ዕለት ይከናወናል ተብሎ ቀን የተቆረጠለትን የናይጀሪያ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ለስድስት ሳምንታት አራዝመዋል በሚል በአለማቀፍ ደረጃ ትችት እየተሰነዘረባቸው ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ ምርጫውን አላራዘምኩም ሲሉ አስተባበሉ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ፕሬዚዳንቱ ምርጫውን ለማራዘም በተላለፈው ውሳኔ ውስጥ እጃቸው እንደሌለበትና ውሳኔውን ያስተላለፉት አካላት በጉዳዩ ዙሪያ እንዳላማከሯቸው አስታውቀዋል፡፡
የአገሪቱ የምርጫ አስፈጻሚ ባለስልጣናት፣ ቦኮ ሃራም የተባለው ጽንፈኛ ቡድን ምርጫውን የሚያስተጓጉል ድርጊት ሊፈጽም ይችላል በሚል ከጸጥታ ሃይሎች የተገለጸላቸውን ስጋት መነሻ በማድረግ ምርጫው ለስድስት ሳምንታት እንዲራዘም መወሰናቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
የናይጀሪያ ምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ አታሂሩ ጃጋ፣ ምርጫው ሊራዘም የቻለው መራጮችን ከቦኮ ሃራም ከሚሰነዘሩ የሽብር ጥቃቶ መከላከል የሚችል በቂ የጸጥታ ሃይል ባለመኖሩ ነው ቢሉም፣ በምርጫው ለመወዳደር የተዘጋጁ የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ምርጫውን ያራዘሙት እንዳይሸነፉና ስልጣናቸውን እንዳይነጠቁ በመስጋት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን እና ፓርቲያቸው ፒዩፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ከቀድሞው የአገሪቱ የጦር መሪ ሙሃማዱ ቡሃሪ እና ኦል ፕሮግሬሲቭስ ኮንግረስ ከተሰኘው ተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዘገባው፤ቡሃሪ በስልጣን ላይ ያለው የጆናታን መንግስት የቦኮ ሃራምን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመግታት አቅምም ሆነ ፈቃደኝነት ይጎድለዋል ሲሉ መተቸታቸውንና እሳቸው ስልጣን ላይ ከወጡ ቦኮ ሃራምን በወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠፉ ቃል መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ምርጫው መራዘሙን ማስታወቁን ተከትሎ፣ ውሳኔው በአለማቀፍ ደረጃ እየተተቸ እንደሚገኝ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፤የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በአገሪቱ ያሉ የጸጥታ ስጋቶች ምርጫን ለማራዘም በቂ ምክንያት ሊሆኑ አይችሉም ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ጸሃፊ ፊሊፕ ሃሞንድ በበኩላቸው፤ ናይጀሪያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት የምንደግፍ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር ናይጀሪያውያን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ለማገድ ምክንያት ሊሆን አይገባም በማለት ምርጫው መራዘሙን ተችተዋል፡፡

ግብጽ ከሁለት አመታት በፊት በሚናያ ግዛት በሚገኝ የፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ባለፈው ሰኔ ወር የሞት ፍርድ ከጣለችባቸው 183 የሙስሊም ብራዘር ሁድ አባላት መካከል፣ የሰላሳ ስድስቱን የሞት ቅጣት ማንሳቷንና የፍርድ ሂደቱ እንደገና እንዲታይ ባለፈው ረዕቡ መወሰኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ ፍርድ ቤቱ ሞሃመድ ባዲ የተባሉትን መንፈሳዊ መሪ ጨምሮ በ36 ተከሳሾች ላይ ጥሎት የነበረውን የሞት ቅጣት ለማንሳትና ፍርዱ እንደገና እንዲታይ የወሰነበትን ምክንያት በግልጽ አለማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ ተቋማት በ183 የሙስሊም ብራዘር ሁድ ደጋፊዎች ላይ ፍርድ ቤቱ የጣለውን የሞት ቅጣት በአጽንኦት ሲተቹት እንደነበርም አስታውሷል፡፡
የሞት ፍርዱ ከተጣለባቸው 183 ግብጻውያን መካከል 147 የሚሆኑት የፍርድ ሂደታቸው በሌሉበት ሲታይ መቆየቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የጥናት ጽሁፎችን አደባባይ ለማውጣት ትኩረት ተሰጥቷል

 የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ከተቋቋመ ከ30 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በነሐሴ ወር 1982 ዓ.ም ለንባብ የበቃችው “ብሌን” የሥነፅሁፍ መፅሔት ፤ ከ15 ዓመት የህትመት መቋረጥ በኋላ ሰሞኑን ታትማ ዳግም ለአንባብያን ቀረበች፡፡
የደራስያን ማህበር 50ኛ ዓመት ክብረበዓልን ምክንያት በማድረግ በሰኔ 2003 ዓ.ም የ“ብሌን” መፅሔት ልዩ ዕትም (ቁ.7) ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ መደበኛው የመፅሄቷ ዕትም ለዓመታት ሳይታተም ቀርቷል፡፡ ከማህበሩ የ30 ዓመት ጉዞ በኋላ መጽሄቷ ብቅ ስትል ለኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ ዕድገት እንደ አንድ ብስራት ቆጥረን ነበር ያሉት የአሁኗ የ“ብሌን” ዕትም አርታኢዎች፤ መፅሔቷ “ቅፅ 1፣ ቁጥር 1” መባሏ ቢያንስ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ዕትም በየዓመቱ ይታተማል የሚል ተስፋን የሚያመላክት ቢሆንም በማህበሩ የ24 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከ7 የበለጠ የ“ብሌን” እትም ሊታተም አልቻለም ብለዋል፡፡
ለመፅሄቷ መቋረጥ ተጠያቂው ሁላችንም ነን በማለትም አርታኢዎቹ ኋላፊነቱን ለሁሉም አከፋፍለዋል፡፡ “… በመጀመሪያ ደረጃ የኢደማን አመራር ይዘው የነበሩትን ሁሉ የሚመለከት ቢሆንም የችግሩ አድማስ ግን ሁላችንንም የሚያካትትና ሁላችንንም በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሚያስጠይቅ ነው፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ መፅሄቷ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ የጠንካራ ተሳታፊዎች እጦት፣ የህትመት በጀትና የደጋፊ ወገን እጥረት መፅሄቷ ወቅቷን ጠብቃ እንዳትወጣ ዋነኛ ተግዳሮቶቿ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ የመፅሔቷ ዕትም ትኩረት የተደረገው በምርምር አምባው ተወስነው የነበሩ የጥናት ውጤቶችን ወደ “ብሌን” መድረክ በማምጣት አደባባይ ማውጣት ላይ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ሶስቱ (የስንቅነሽ አጣለ፣ የቴዎድሮስ ገብሬና የአራጌ ይመር) ተመርጠው እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡
“የዚህ ዓይነቱ ሙከራ ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ብሌን በምርምርና በፈጠራ፣ በሂስና በንድፈ ሃሳብ መካከል ድልድይ ሆና እንድታገለግል ምኞታችን ነው” ብለዋል፤ አርታኢዎቹ፡፡
በ108 ገፆች የተቀነበበችው “ብሌን” መፅሄት፤ ከጥናትና ምርምር ፅሁፎች በተጨማሪ አጭር ልቦለድና ግጥሞችን ያካተተች ሲሆን በ50 ብር ለገበያ ቀርባለች፡፡ መፅሄቷ በዓመት ሁለት ጊዜ እየታተመች ለአንባቢያን እንደምትደርስም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 14 February 2015 15:22

ጋሽ ስብሃት - የዛሬ 29 ዓመት

ታዬ፡-     አንዳንዶቹ የበዓሉ ግርማ ገጸ ባሕርያት ጋብቻን በሚመለከት … በተለይ በኪነት ዓለም ውስጥ ስሜት ያላቸውና የሚሳተፉቱ … ጋብቻን በጥርጣሬ ዓይን ነው የሚያዩት።  ለምን? ጋብቻን ከኪነት ስራቸው ጋር እንደሚፎካከር፣ እና እንደልቡ ለመሆን እንደማይችል ደራሲው… ለምን? ላገባት ሴት ጊዜውን መስጠት አለበትና ያ ደግሞ የፈጠራ ጊዜውን እንደሚሻማ አድርገው የሚናገሩ፣ የሚሰማቸው ገጸ ባህሪያት አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ስሜት አንተ የለህም?
ስብሐት፡- እኔ እንደሱ አይሰማኝም፡፡ ግን ይገባኛል የነሱ ስሜት፤ በደንብ ይገባኛል … ምክንያቱም እውነት ነው፡፡ ሚስት የኪነትን ጊዜ፣ ሀሳብ፣ “ኢነርጂ”፣ ሁሉን ትሻማለች ሳይሆን ትጋራለች ብንል ነው ጥሩ፡፡
ታዬ፡-     ለምን?
ስብሐት፡- ሽምያ መነጣጠቅ ነው፡፡ መጋራት ግን የሷ ተራ ሲሆን ለሷ ጊዜህን ትሰጣለህ፡፡ የኪነት ተራ ሲሆን ለኪነት ጊዜህን ትሰጣለህ፡፡ እሷም ከተዋደድን ይሄ ይገባታል፡፡
ታዬ፡-     ስለዚህ የፈጠራ ስራውን ጋብቻ ሊያስተጓጉልበት አይችልማ?
ስብሐት፡- የፍቅር ጋብቻ ከሆነ አይችልም ነው የምለው፡፡ እንዲያውም ሴትዬዋ ብዙ ልታግዘው ትችላለች፤ ብዙ ልታበረታታው ትችላለች፡፤ ጉልበት ልትሆነው ትችላለች … ድክመት ሳይሆን፡፡
ታዬ፡-     ከበዓሉ ጋር ስለ ሥነ ጽሑፍ በምትወያዩበት ጊዜ ብዙ ልዩነት የታየበት ነጥብ አለ እስካሁን ድረስ? ለምሳሌ በዚህ ነገር ላይ እኔ አልስማማም የተባባላችሁበት አለ… ስለ ሥነ ጽሑፍ ባላችሁ አመላከከት?
ስብሀት፡- አዎ፡፡
ታዬ፡-     ምን ምንን በሚመስል ነገር?
ስብሐት፡- ቅድም ያልኩህ ነው … መነሻው ጥያቄ ሌላ ሆኖ ነው እንጂ፡፡ እሱ መጻፍ ስለምትችል ሳንሱር እንዲያልፍ እያሰብክ መጻፍ አለብህ … እና ማሳተም አለብህ፤ ልትነበብ ካልሆነ ለምን ትለፋለህ ያለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ለሳንሱር ብዬ ከጻፍኩማ ምኑን ጻፍኩት? ለራሴ … እና በደንብ የሚሰማኝን ለመጻፍ፣ ለማውጣት ካልሆነ ምኑን ጻፍኩት ነው እንግዲህ ልዩነታችን፡፡
ታዬ፡-     ስለዚህ አንተ በምትደርስበት ጊዜ መጀመሪያ የምታተኩረው አድማጭህ ላይ ሳይሆን ራስህ …?
ስብሐት፡- አድማጩ ላይ ነው! አንባቢዬ ላይ ነው! ግን አንባቢዬ ሳንሱር አይደለም፤ ሰው ነው፡፡ እንጂ እንዲያውም አንባቢዬ ላይ ነው በጣም የማተኩረው፡፡ ተግባባን?
ታዬ፡-     አዎን፤ ገባኝ፡፡ ባንተ አስተያየት ደራሲው በሚጽፍበት ጊዜ ይሄ ሳንሱር ያልፋል፤ ይሄ ሳንሱር አያልፍም የሚለው ነጥብ አጻጻፉን ሊወስነው፣ ወይ ሊለውጠው አይገባም ነው?
ስብሐት፡- ልክ! እኔ ስጽፍ ይሄ ለአንባቢዬ ግልጽ አይሆንም፤ ይሄ ግልጽ ይሆናል … ስለዚህ እንደዚህ እያልኩ ነው፡፡ አንባቢ ነው ሀሳቤ ውስጥ ያለው፤ ሳንሱር የለም፡፡
ታዬ፡-     ስለ አንባቢ ካነሳን አልቀረ ምን ዓይነት አንባቢዎች ናቸው በአእምሮህ ውስጥ የሚጉላሉት… በምትደርስበት ጊዜ አንድን የሆነ ድርሰት፣ ልቦለድ? ለምሳሌ ወይ በመደብ፣ ወይ በትምህርት፣ ወይ በጾታ እንደዚህ ታስባቸዋለህ አድማጮችህን? … በዚህ ዓይነት አታያቸውም?
ስብሐት፡- እኔ የማስበው አንባቢዬ ከኔ እኩል ሊያስብ ይችላል፤ ከኔ እኩል ሊሰማው ይችላል፡፡ ስለዚህ እኔ ቃላቱን፣ አባባሉን አጥቼበት ካልሆነ በስተቀር አንባቢዬ አይስተኝም፡፡ ምክንያቱም እኔ ውስጥ ያለ ሁሉ አንባቢዬ ውስጥም አለ፡፡ ያው የሰው ነገር ስለሆነ የምጽፈው … ስለ ምኞት፣. ስለ ኩም ማለት፣ ስለ መውደድ፣ ስለ መጥላት፣ ስለ ተስፋ፣ እንደዚህ፣ እንደዚህ ስለሆነ ምንም ለአንባቢ የማይገባ ነገር አይኖርም፡፡ በቃ እኩያ ነን እኔና አንባቢዬ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ምናልባት እኔ ላስተምር አይደለም የምጽፈው፤ ተረት ልነግር ነው እንጂ፡፡
ታዬ፡-     በዚህስ ነጥብ ላይ አትለያዩም? ለምሳሌ እሱ የስነ ጽሑፍ ሚና ህብረተሰብን ማስተማር …
ስብሐት፡- ነው ይላል እሱ፡፡
ታዬ፡-     ይላል? በዚህ ነጥብ ላይ ግን አትስማሙም?
ስብሐት፡- አንስማማም፡፡
ታዬ፡-     ለማስታረቅም አልሞከራችሁም? ያው እንደተለያየ ነው ያለው ሀሳባችሁ?
ስብሐት፡ አዎ! እርቅ ምን ያደርጋል? በዚህ በኩል እኮ ሲለያዩ ነው ጥሩ፡፡ እሱም የራሱን መንገድ ይይዛል፤ እኔም የራሴን፡፡ ሁለታችንም በየበኩላችን አስተዋጽዖ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
ታዬ፡- እንደዚያም ሆኖ ግን፣ ይህም የሀሳብ ልዩነት ኖሮ ትግባባላችሁ?
ስብሐት፡- በጣም!
(ከላይ የቀረበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትርፍ ጊዜ የሥነፅሁፍ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የሥነፅሁፍ መፅሔት “ብሌን” ዋና አዘጋጅ ታዬ አሰፋ፤ የዛሬ 29 ዓመት የለንደን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ስለአማርኛ ልቦለዶች የትረካ ስልት ለሚያደርጉት ጥናት ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ሲሆን ሰሞኑን ከወጣው “ብሌን” መፅሔት የቀነጨበ ነው።)
ቅጽ 8፣ ቁ.፤  (ታህሣሥ 2007)

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ደጋፊዎቻቸው ገንዘብ አዋጥተው በስማቸው በመሰረቱት ቤተ መቅደስ ውስጥ ባቆሙላቸው ጣኦት አማካይነት እየተመለኩ እንደሆነ የዘገበው ሮይተርስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የደጋፊዎቻቸው ድርጊት እንዳስደነገጣቸውና አፈንጋጭ እንደሆነ መናገራቸውን አስታወቀ፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች፣ ራጅኮት በተባለችው የህንድ ምዕራባዊ ከተማ በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጭ ብለው የሚያሳይ ጣኦት አቁመው እያመለኩ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
“ነገሩ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ግለሰቦቹ የሰሩት ስራ ለዘመናት ከዘለቀው ታላቁ የህንድ ባህል ጋርም የሚጋጭ ነው፡፡ ባህላችን እንዲህ አይነት ቤተ መቅደሶችን እንድንሰራ አላስተማረንም” በማለት ድርጊቱን አውግዘውታል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የተከፉት የተወሰኑ የቤተ መቅደሱ ፕሮጀክት አስፈጻሚ አባላት በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጣኦት በአንድ የሂንዱ ፈጣሪ ሃውልት ለመተካት አቅደዋል፡፡
“ጠቅላይ ሚኒስትራችንን እንወዳቸዋለን፤ እናመልካቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እሳቸው እስከዛሬ ከነበሩት መሪዎቻችን ሁሉ የተለዩ ትልቅ ሰው ናቸው!” ብለዋል፤ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የዋለውን መሬት በነጻ ያበረከቱት ፓሬሽ ራዋል የተባሉ ህንዳዊ ባለጠጋ፡፡

Saturday, 14 February 2015 15:01

የኔ ወፍ

ቀኑ የኔን ሃሳብ
ውስጤን ከገለፀ
አንቺነትሽ በኔ
ገብቶ እንደሰረፀ
ሃሳቤን ልንገርሽ
የልቤን ስጦታ
አበባ ያንስሻል
‹ወይን› አይሰጠኝ ደስታ
ተመልከቺ ፍቅሩን
ያንቺን ልዩ ቦታ
ወስደሽ ከጣቴ ላይ
የደሜን ጠብታ፡፡

ትዝታ
ድምፅሽ ሲቀያየር
ሆነሽ አጠገቤ
ፍስስ የሚልብኝ
ቆራጥ ያልኩት ልቤ
ያልሆንኩትን ሆኖ
እኔነ ጠፍቶ
እያሰብኩኝ አንቺን
መናፈቄ በዝቶ
ሲቀያየርብኝ
መውደድና መጥላት
መከልከል መለገስ
መጨከን መራራት
ሲለዋወጥብኝ
ፈሪነት ደግነት
ታዝቤዋለሁኝ
ሲሰማኝ ውብ ደስታ
ትርጉሙ ፍቅርሽ ነው
ሰናይ ነው ትዝታ፡፡
(ከእስክንድር ለማ ክብረት
“የኔ ወፍ” የግጥም መድበል የተወሰደ፤
የካቲት 2007 ዓ.ም)