Administrator

Administrator

   ጀርመናዊው ኡዌ (ባንተን) ሸፈር፤ ድምፃዊ፤ ጊታር ተጫዋችና የሩት ሮክ ሬጌ ሙዚቃ አርቲስት ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ማይክ የጨበጠው በ19 ዓመቱ ሲሆን “ባንተን” የሚለውን ቅፅል ስም ያወጡለት የሙያ ባልደረቦቹ የጃማይካ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ በስነግጥም የተካነ የሙዚቃ አጫዋች ወይም ዲጄ መሆኑን በማድነቅ ነው ቅፅል ስሙን የሰጡት፡፡ ኡዌ "FREE YOUR MIND" በሚል ስያሜ አዲስ  አልበሙን  ከወር በፊት ለዓለም ገበያ አቅርቧል፡፡ ሙዚቃዎቹ የተሰሩት ሶስቱን አህጉራት አፍሪካ፤ አሜሪካና አውሮፓን በማካለል ሲሆን በተለይ ኮስታሪካ፤ ኢትዮጵያ፤ ጀርመን፤ ጃማይካና ደቡብ አፍሪካ ላይ ቀረፃዎች ተከናውነዋል፡፡ ከሰላሳ በላይ ሙዚቀኞችና ከስምንት የተለያዩ አገራት ተሳትፈውበታል፡፡ በጀርመንና በአውሮፓ ስሙ የናኘው የሬጌ አሳታሚ ጋንጃማን የአልበሙን ሚክሲንግና ማስተሪንግ የሰራው ሲሆን በዲጂታል የሙዚቃ አውታሮችና በሲዲ አሳትሞ ለዓለም ገበያ ያቀረበው ደግሞ ራስታ ያርድ ሬከርድስ ነው፡፡
‹‹ፍሪ ዩር ማይንድ›› ለኡዌ አራተኛ የሙዚቃ አልበሙ ሲሆን የመጨረሻ አልበሙን “ሜንታል ዋር” ካሳተመ ከ9 ዓመታት በኋላ ለገበያ የቀረበ ነው፡፡ ዘፈኖቹ በእንግሊዘኛ፤ በጀርመንኛ፤ በፓቶዋ እና በአማርኛ ዜማዎች መቀንቀናቸው አልበሙን ልዩ ያደርገዋል፡፡ አብረውት የሰሩት ድምፃውያን የበርሊኑ ጋንጃማን፤ የኢትዮጵያው ራስ ጃኒ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው አፍሪካ ሴሌ ናቸው፡፡
አርቲስቱ በመላው አውሮፓ በተለይ ጀርመን ውስጥ በሬጌ ሙዚቃ ስሙ የገነነ ሲሆን በካሬቢያን ቅኝት የተሟሹት ዜማዎቹ፤ ጥልቅ እሳቤ ያላቸው ስንኞቹና ምርጥ የሙዚቃ ቅንብሮቹ ተወዳጅነትን አትርፈውለታል፡፡ በአዲስ አልበሙ “ፍሪ ዩር ማይንድ” ላይ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት (Ark of the covenant) በሚል ርእስ ሁለት ሙዚቃዎችን በሬጌ እና ደብ  ስልቶች፣ ከታዋቂው የኢትዮጵያ ሬጌ ሙዚቀኛ ራስ ዮሃንስ (ራስ ጃኒ) ጋር በመጣመር ሰርቷቸዋል፡፡ ኡዌ ባንተን ከሚኖርበት የጀርመን ከተማ ቢሌፌልድ ከግሩም ሠይፉ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-


                  ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን መጎብኘትህ በቅርቡ ላሳተምከው አዲስ አልበም አስተዋጽኦ አድርጓል?
አዎም አይደለምም፡፡ አዎ፤ ምክንያቱም ለእኔ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ መምጣቴ ነበር፡፡ ጉብኝቱ ለእኔ በጣም ትልቅ ትርጉም ያለውና የመጀመርያውን ተሞክሮ ያገኘሁበት ነበር፡፡ ጉዞው የረዥም ጊዜ ምኞቴና እቅዴ ስለነበር ጉዞውን እንዳሳካ  የባረከኝን ልዑል እግዚአብሔርን  አመሰግነዋለሁ፡፡  እምነቴን ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል።
አይደለም ስል ደግሞ ዋናው ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ ያለኝን አመለካከትና ትርጉም ጉብኝቱ አልቀየረውም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት ሁሉንም ነገር ለብዙ ዓመታት ስማረውና ሳጠናው ነው የኖርኩት። የሆነ ሆኖ፣ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የራስታ ማህበረሰቦችን በአካል ለመገናኘት መቻሌን እንደ በረከት እቆጥረዋለሁ፡፡ ከሁሉም  ጋር በግንባር መወያየትና መማማር መቻሌ ፍፁም አስደሳች ነበር፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣ የኢትዮጵያ ጉብኝቴ በእምነት እንድጠነክር አድርጎኛል፡፡ እናም የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ በቅርቡ እንደገና እንደምመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት የሰራኸው ሙዚቃና የፃፍካቸው ግጥሞች እጅግ አስደማሚ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ሀሳቡ ከየት ነው የመነጨው? ለዓለምስ ምንድነው ፋይዳው?
የቃል ኪዳኑ ታቦት ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ካነበብኩበት ጊዜ አንስቶ በአእምሮዬና በተመስጦዬ ውስጥ የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት “ክብረ ነገስት” የተሰኘውን መፅሐፍ የጀርመንኛ ትርጉም ማንበቤም ሌላው ምክንያት ነው። በክብረ ነገስት ላይ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደመጣ ያነበብኩት ታሪክ ሁሌም ያስደንቀኛል፡፡ ምንም እንኳን ለኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ታሪክና ባህል ማዕከላዊ ሚና ቢጫወትም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ለአብዛኛው የአለም ክፍል ምስጢር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን አሁን የምንኖረው በአንድ ወቅት ተሰውሮ የነበረው ነገር ሁሉ ወደ ብርሃን በሚወጣበት ዘመን ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዓለም ዙሪያ ያለውን ግንኙነት የሚያፋጥንባቸውን መንገዶች ፈጥሯል። ይህ ለበጎም ለክፉም ዓላማዎች ሊውል ይችላል፡፡ እውቀትና ጥሩ መልእክቶች በፍጥነት እንደሚሰራጩበት ሁሉ ለፖለቲካ ግጭት አደገኛ መቀስቀሻም ሊሆን ይችላል። በዚህ ውጥንቅጥ መሃል የእግዚአብሔር መልእክትና የሰው ልጅ መዳን ወደ አራቱ የዓለም ማዕዘናት መዳረሱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰዎች ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሲያውቁና በክብረ ነገስት ወደ ኢትዮጵያ የደረሰበትን ታሪክ ሲረዱ፣ አሥርቱን የእግዚአብሔር ትእዛዛት እውነተኛ ባህሪ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል፡፡
በዘፈኖችህ ውስጥ ኢትዮጵያን ደጋግመህ ጠቅሰሃል፡፡ በዓለም የሬጌ ሙዚቃ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት ሚና እንዴት ይገለጻል?
በራስ ታፋሪያኖች እምነት፣ በሬጌ ሙዚቃ ልዩ መልእክት፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ጉልህ ሚና ትጫወታለች፡፡ መነሻው በጃማይካ፣ በካሪቢያንና በአሜሪካ ውስጥ ቢሆንም፤  በትራንስ አትላንቲክ የባሪያ ንግድ ወቅት  ወደ ምዕራቡ ዓለም የተጋዙት አፍሪካውያን ያመጡት ውጤት ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ እንደ ነቢይ የሚቆጠረው ማርከስ ጋርቬይ ወደ አፍሪካ እንድንመለከትና  በተከበረው አፍሪካዊ ማንነት ላይም አፅንዖት ሰጥቶ አስተምሯል፡፡ ኢትዮጵያ በፋሺስት ወራሪዎች ጥቃት ሲሰነዘርባት በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ብዙ አፍሪካውያን ኢትዮጵያን ዳግም ነፃ ለማውጣት በተደረገው ትግል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ይደግፉ ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ተወዳጁ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባደረጉት ጥረት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት መስራቾች አንዷ ሆናለች፡፡ ይህ ሁሉ ባለፉት ዓመታት በሰው ልጆች ለፍትህና ለእኩልነት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ትግል ጠንካራ ተምሳሌትና ምልክት ሆኗል፡፡ እና አሁን በዓለም ዙሪያ በሬጌ ሙዚቃ ተወዳጅነት ሳቢያ ብዙ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክም ግንዛቤ እያገኙ መጥተዋል፡፡
ከራስ ጃኒ (ራስ ዮሐንስ) ጋር እንዴት አብራችሁ ልትሰሩ ቻላችሁ?
ከራስ ጃኒ (ራስ ዮሐንስ) ጋር የተገናኘነው በአዲስ አበባው ጥሩ ጓደኛዬ ራስ ሳም አማካኝነት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን በጎበኘሁበት ወቅት ከራስ ሳም ጋር የተዋወቅሁ ሲሆን፤ ከዛም በኋላ ወደ አውሮፓ በዛው ክረምት ላይ መጥቶ የሙዚቃ ስራዎቼን ባቀረብኩበት የሬጌ ጃም ፌስቲቫል ላይ  ተገናኝተን ብዙ ተጫውተናል፡፡
 በወቅቱ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ስለሰራሁት ዘፈኔ ለራስ ሳም ስነግረው፣ ኢትዮጵያዊ አርቲስት በአማርኛ ቋንቋ የዘፈኑን ታሪክ እንዲጫወት ማሰቤን ገለፅኩለት፡፡ ይሄን ጊዜ ከራስ ዮሐንስ ጋር እንድሰራው የጠቆመኝ ራስ ሳም ነው፡፡ ራስ ዮሐንስ ዘፈኑንና ሀሳቡን ስለወደደው ወዲያውኑ ስቱዲዮ ገብቶ ቀረፃውን በማከናወን የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ራስ ጃኒ እና ባለቤቱ ኢየሩሳሌም ሀብቴ እጅግ በጣም ግሩምና አፍቃሪ ሰዎች ናቸው፡፡ የሙዚቃውን ቀረፃ እውን ለማድረግ እንዲሁም ለሙዚቃ ቪዲዮው ስራ ቅን ትብብር አድርገዋል፡፡ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
በመጨረሻ  የምታስተላልፈው መልእክት…
በአንድ ወቅት በታሪክ ውስጥ ተደብቆ የነበረው ነገር ከእንግዲህ እንቆቅልሽ አይደለም፡፡ የዓለም ህዝቦች ለመዳን  ወደ ኢትዮጵያ ይመለከታሉ፡፡ ጠላቶቿ ብዙ ናቸው፣ ግን ልክ ቁራጭ ሻማ በብርሃኗ ጨለማውን እንደምታበራው ኢትዮጵያም እምነቷን ጠብቃ መቀጠል አለባት፡፡ ማንም ሰው ጊዜውን ማቆም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ በክፉም ላይ መልካም ድል እንደሚያደርግ እናምናለን። አንድነት ጥንካሬ ነው፡፡ ጸሎታችን ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዛሬም ለዝንተ ዓለምም እንወዳታለን።            እንግሊዛዊው ቢሊየነር ሪቻርድ ብራንሰን ቨርጂን ጋላክቲክ በተባለችዋ የራሳቸው የጠፈር መንኮራኩር ባለፈው እሁድ ማለዳ ያደረጉትን ጉዞ በስኬት አጠናቅቀው በመመለስ በራሳቸው መንኩራኩር ጠፈር ደርሰው የተመለሱ የመጀመሪያው ሰው ሆነው በታሪክ መመዝገባቸው ተነግሯል፡፡
የ71 አመቱ ሰር ሪቻርድ ብራንሰን ከሶስት የጉዞ አጋሮቻቸውና ከሁለት የበረራ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ባለፈው እሁድ ከአሜሪካ ኒው ሜክሲኮ ወደ ጠፈር ባደረጉት ዩኒቲ 22 የሚል ስያሜ ያለው ጉዞ፤ መንኮራኩሯ ከምድር ከ85 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በመምጠቅ ጉዞዋን በስኬት አጠናቅቃ መመለሷን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ቢሊየነሩ አንድ ሰዓት ያህል የፈጀውን ጉዞ በስኬት አጠናቅቀው ምድርን እንደረገጡ በሰጡት መግለጫ፣ ጉዞው አንዳች ልዩ ደስታና ሃሴት የሚፈጥርና እንደ ተዓምር የሚቆጠር መሆኑን መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ብራንሰን በቴክኖሎጂና በጠፈር ጉዞ እየተፎካከሯቸው የሚገኙትን አሜሪካዊያን ቢሊየነሮች የስፔስ ኤክስ ኩባንያ ባለቤት ኤለን መስክና የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ቀድመው ወደ ጠፈር በመጓዝ ታሪክ መስራታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ቤዞስ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ህዋ ሊጓዙ ቀን መቁረጣቸውንም አስታውሷል፡፡
ጉዞው አጭር ቢመስልም ትርጉሙ ትልቅ መሆኑንና ኩባንያው በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያደርገው ያሰበው የጠፈር ቱሪዝም ጉዞ ስኬታማ እንደሚሆን ለማረጋገጥ ታስቦ የተደረገ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ከ17 አመታት በፊት የተቋቋመው ቨርጂን ጋላክቲክ በቅርቡ ሊያካሂደው ላሰበው የጠፈር ሽርሽር ተመዝግበው ተራ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱንና አንድ መንገደኛ እስከ ሩብ ሚሊዮን ዶላር ያህል ለጉዞው እንደሚከፍልም ዘገባው አስታውሷል፡፡


     በ2020 በየደቂቃው ረሃብ 11 ሰዎችን፣ ኮሮና 7 ሰዎችን ገድሏል

           ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በአለም ዙሪያ የሚገኙ 811 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ 10 በመቶ የሚሆነው የረሃብ ሰለባ መሆኑን እንዲሁም 2.37 ቢሊዮን ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሰለባ መሆናቸውን ተመድ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የአለም የምግብ ፕሮግራምና የጤና ድርጅትን ጨምሮ አምስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት በጋራ ባወጡት በዚህ ሪፖርት፤ በመላው አለም የረሃብ ሰለቦች የሆኑ ሰዎች ቁጥር ባለፈው አመት ከነበረበት በ161 ሚሊዮን በመጨመር 811 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹ ሲሆን ከአለማችን ህጻናት መካከል 22 በመቶ የሚሆኑት ወይም 149 ሚሊዮን ህጻናት የመቀንጨር ችግር ሰለቦች መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በአፍሪካ የረሃብ አደጋ ሰለቦች ቁጥር ባለፈው አመት በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአመቱ በአህጉሪቱ 282 ሚሊዮን ሰዎች የረሃብ አደጋ ሰለቦች መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ፣ የምግብ እህሎች ምርት መቀነስ፣ የእርስ በእርስ ግጭቶችና የኢኮኖሚ ቀውሶች ለምግብ እጥረት ችግሩ መባበሳስ በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለጋሽ አገራት ለድሃ አገራት የሚሰጡትን የምግብ ድጋፍ መቀነሳቸውም ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡
ኦክስፋም ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በበኩሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ሪፖርት፣ በአመቱ በኮሮና ሳቢያ ከሞቱት ይልቅ በረሃብ ሰበብ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር እንደሚበልጥ የገለጸ ሲሆን፣ ኮሮና በየደቂቃው 7 ሰዎችን ሲገድል ረሃብ ግን 11 ሰዎችን መግደሉን አመልክቷል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ በሚያጋጥሟቸው አደጋዎችና ጥቃቶች ለሞት የሚዳረጉ ስደተኞች ቁጥር ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ መጨመሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከጥር እስከ ሰኔ በነበሩት ወራት ከ1 ሺህ 146 በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ለሞት መዳረጋቸውን ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ባህሩን አቋርጠው የተጓዙ ስደተኞች ቁጥርም በ56 በመቶ ያህል ጭማሬ አሳይቷል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ከሞቱባቸው የሜዲትራኒያን ባህር የጉዞ መስመሮች መካከል ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የሚወስደው በቀዳሚነት ይጠቀሳል ያለው የድርጅቱ ሪፖርት፣ በዚህ መስመር በድምሩ 741 ስደተኞች ለሞት መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡
ባለፈው አመት ከኮቪድ ወረርሽኝ የጉዞ ክልከላዎች ጋር በተያያዘ ወደ አውሮፓ አገራት የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ2015 የፈረንጆች አመት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በአመቱ 1 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አገራት ስደተኞች በባህር ጉዞ ወደ አውሮፓ መግባት መቻላቸውንና አብዛኞቹም የሶርያ ስደተኞች መሆናቸውን ገልጧል፡፡

የጋና ፓርላማ ባለፈው ሳምንት ለአገሪቱ ቀዳማዊት እመቤቶች የወሰነው የደመወዝ ጭማሪ የአገሪቱን ዜጎች ማስቆጣቱንና ትችት ማስከተሉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ቀዳማዊት እመቤት ርብቃ አኩፎ አዶ ባለቤታቸው ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለአራት አመታት ያህል በአበል መልክ የተከፈላቸውን 151 ሺህ 618 ዶላር ሙሉ ለሙሉ እንደሚመልሱ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የጋናው ፕሬዚዳንት አኩፎ አዶ መንበረ ስልጣኑን ሲቆናጠጡ አብረዋቸው ወደ ቤተመንግስት የገቡት ርብቃ፣ ፓርላማው ለእሳቸውና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ባለቤት የደመወዝ ጭማሬ ማድረጉ አግባብ አይደለም የሚሉ ወቀሳዎች መበራከታቸውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ አበል ክፈሉኝ ብዬ አይደለም ሲከፍሉኝ የኖሩት፣ የወሰድኩትን ገንዘብ አንድም ሳላስቀር ለሚመለከተው የመንግስት አካል እመልሳለሁ ማለታቸውን ነው ዘገባው ያስነበበው፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ አበሉን እንደሚመልሱ ከመናገራቸው ባለፈ ፓርላማው በቅርቡ ያጸደቀላቸውን አዲስ ደመወዝ እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ፓርላማው ለእሳቸውም ሆነ ለአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ባለቤት የወሰነላቸው ወርሃዊ ደመወዝ 3 ሺህ 500 ዶላር እንደሚደርስና ይህም ከአገሪቱ ሚኒስትሮች ደመወዝ ጋር እኩል መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፤ ናይጀሪያ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች በኋላ በነበሩት 61 አመታት በሙስና ሰበብ በድምሩ 582 ቢሊዮን ዶላር ያህል ማጣቷን ዋይአይኤጂኤ የተባለ አንድ የአገሪቱ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ከአለማችን 179 አገራት በሙስና መስፋፋት 30ኛ ደረጃን በያዘችው ናይጀሪያ ከፈረንጆች አመት 2011 እስከ 2015 ተጨማሪ 1.3 ትሪሊዮን የመንግስት ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ መደረጉን በጥናት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

    የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸው ባለፈው ሃሙስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው የቀሰቀሱት ተቃውሞ ወደ ከፋ ብጥብጥ፣ ሁከት፣ ግድያና ዝርፊያ አምርቷል፤ እስከ ረቡዕ ድረስም 72 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡
ከ1990ዎቹ ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተ የከፋ ነውጥ እንደሆነ የተነገረለትና ዙማ ከተወለዱበት ካዙል ናታል ግዛት የተነሳው ነውጥ ወደተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶችና ከተሞች መስፋፋቱን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲርል ራማፎሳ አገሪቱን ከከፋ ጥፋት ለመታደግ ከ2 ሺህ 500 በላይ የጸጥታ ሃይሎችን ቢያሰማሩም ከነውጠኞች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑንና ሁከትና ብጥብጡ ዝርፊያና ግድያው ግን ለቀናት ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ፣ ሰኞ ዕለት ብቻ 200 ያህል የገበያ ማዕከላት መዘረፋቸውንና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ አገራት ስደተኞች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ደቡብ አፍሪካውያን በተለይ ረቡዕ ዕለት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአገሬውና የተለያዩ አገራት ዜጎች መጋዘኖችን፣ መደብሮችን፣ የመንግስትና የህዝብ ተቋማትን መዝረፋቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት በእሳት መጋየታቸውን፣ ሆስፒታሎችና የኮሮና ቫይረስ ክትባት የሚሰጥባቸው ማዕከላት መዘጋታቸውን፣ ጎዳናዎችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን አመልክቷል፡፡
በጆሃንስበርግ፣ ሱዌቶና ደርባንን በመሳሰሉ አካባቢዎች ዘራፊዎች ተደራጅተውና መሳሪያ ታጥቀው በመሰማራታቸው የጸጥታ ሃይሎች ድርጊቱን ለማስቆም የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ እስከ ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ ፖሊስ በመላ አገሪቱ ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን እንዳስታወቀም አመልክቷል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ነውጠኞች የገንዘብ መክፈያ ማሽኖችን በመስበር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መዝረፋቸውንና ሆቴልና ሬስቶራንቶችን ጨምሮ በርካታ የንግድ ተቋማት መዘረፍና መቃጠላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአመጽና ብጥብጡ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ተጎጂ መሆናቸውንና በዚህም ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች ከስራቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ መነገሩንም አስረድቷል፡፡ ቴኪዊኒ በተባለ ግዛት ብቻ 1.09 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱንም ለአብነት አንስቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ዜጎችን ለሞት የዳረገውንና የንብረት ውድመት ያስከተለውን ብጥብጥ፣ ጋጠወጥነትና ዘገባ ያወገዙ ሲሆን፣ ወንጀለኞች በአፋጣኝ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ ህዝቡ ወደመረጋጋት እንዲመለስና ህግ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።
ተደራራቢ የሙስና ክሶች ተመስርተውባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የ79 አመቱ ጃኮብ ዙማ የተመሰረቱባቸውን ክሶች በተመለከተ ችሎት ቀርበው ምላሻቸውን እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ጥሪ ቢደረግላቸውም፣ በተደጋጋሚ በእምቢተኝነት ፍርድ ቤት ሳይገኙ በመቅረታቸው የአገሪቱ ከፍተኛ የህገ መንግሥት ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት የ15 ወራት እስር ቅጣት እንደጣለባቸውና እስራቸው እንዲዘገይ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ ለእስር እንደተዳረጉ የሚታወስ ነው፡፡              ዴልታ በመባል የሚታወቀውና በፍጥነት በመዛመትም ሆነ በገዳይነቱ ከሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች እንደሚልቅ የተነገረለት አደገኛው የኮሮና ዝርያ በአለም ዙሪያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ እንደሚገኝና የከፉ ወረርሽኞችን ሊያስከትል እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በጥቅምት ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በህንድ የተገኘው ዴልታ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ ወደ ሌሎች የአለማችን አገራት በፍጥነት በመሰራጨት እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ወደ 104 አገራት መግባቱን የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ሰኞ ከጄኔቫ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
እስካለፈው ሳምንት በነበሩት አራት ተከታታይ ሳምንታት በአለማቀፍ ደረጃ የኮሮኖ ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመር ማሳየቱን ያስታወሱት የድርጅቱ ዳይሬክተር፣ ለአስር ሳምንታት ቅናሽ ሲያሳይ የዘለቀው የሟቾች ቁጥርም ባለፈው ሳምንት ጭማሬ ማሳየቱን በመግለጽ ለዚህም ዴልታ የተባለው ዝርያ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡
ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ሲጂቲኤን እንደዘገበው፤ ዝርያው በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋባቸው ካሉት አገራት አንዷ በሆነችው አሜሪካ ለወራት ቅናሽ ሲያሳይ የቆየው የቫይረሱ ስርጭት ባለፉት ሳምንታት ጭማሬ ማሳየት የጀመረ ሲሆን በየቀኑ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች አማካይ ቁጥር ከአንድ ወር በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በተለይ በሰሜናዊ አካባቢዋ በሶስተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ መፈተን በጀመረችው አፍሪካ አጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ረቡዕ ከ6 ሚሊዮን ማለፉን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፣ የሟቾች ቁጥርም ወደ 154 ሺህ መጠጋቱንና በአህጉሩ ከ37 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች መሰጠታቸውንም አመልክቷል፡፡
በኡጋንዳ ባለፈው ሳምንት ብቻ የኮሮና የእንቅስቃሴ ገደብ ህጎችን ጥሰዋል የተባሉ ከ2 ሺህ 180 በላይ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

              (ወዳጅህን ከጎረቤትህ ታገኛለህ ጠላትህን እናትህ ትወልድልሃለች!)

           በትግራይ ወርዒ በሚባል በረሃ ውስጥ ሁለት ወንድማማቾች ሽፍቶች ነበሩ፡፡ ክፉ ደግ አይተው አብረው ያደጉ ናቸው፡፡ ብዙ ባልንጀሮችና ተከታዮች አፍርተዋል፡፡ ታላቅም  ታናሽም በተከታዮቻቸው መካከል የየራሳቸው ቡድን መስርተዋል፡፡ የየቡድኑን የጎበዝ አለቃም ሾመዋል፡፡ በየጊዜው ከግብረ-አበር ተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ዘረፋ ያካሂዱ ነበር። አንድ ቀን እስከነ ተከታዮቻቸው ከደጋ ተምቤን ቆላ ወርደው፣ አሳቻ ቦታ መርጠው፣ እንደ ልማዳቸው አድፍጠው ሲጠባበቁ አያሌ ሸቀጥና የዐረብ ንብረት በግመል ጭኖ የመጣ የነጋዴ ቅፍለት (Caravan) ያጋጥማቸውና ሙልጭ አድርገው ይዘርፉታል፡፡
 ከዚያም የተዘረፈው ይከፋፈል ይባላል፡፡ ታላቅዬው እስከነ አሽከሮቹ “ይሄ ንብረት በሙሉ ለእኔ ቡድን ይሰጥና በሚቀጥለው የምንዘርፈው ደግሞ ለአንተ ቡድን ይሁን”  የሚል አዲስ የብልጠት ሀሳብ አመጣ፡፡ ትንሽዬውም በጣም ተናደደና “በምንም ዓይነት የእኩል መሆን አለበት” ብሎ አሻፈረኝ፣ ሞቼ - እገኛለሁ አለ፡፡
ታላቅ ታናሽን ካልገደለ እንደማያርፍ በማመን ዘወር ብሎ መሳሪያውን ያቀባብላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ያስተዋለ የታናሽዬው የጎበዝ አለቃ የሆነ፣ ባዳ ሰው ለታናሽዬው በጩኸት እንዲጠነቀቅ ምልክት ይሰጠዋል፡፡
ተኩስ ሲጀመር ያ የጎበዝ አለቃ ቀድሞውንም ተዘጋጅቶ ነበርና ታላቅዬውን ቀንድቦ ይጥለዋል፡፡  የታላቅዬው ወገኖች ይሸነፋሉ፡፡
ታናሽዬውም፤ ያን የጎበዝ አለቃ ጠርቶ፡-
“ካብ ጎረቤት ትረኽቦ ፈታዊኻ
ፀላኢንከ ትወልደልካ ኣዴኻ”
(“ወዳጅህን ከጎረቤትህ ታገኛለህ
ጠላትህን እናትህ ትወልድልሃለች”)
አለና  “በል ንብረቱን በሙሉ ሳታዳላ አከፋፍል” ብሎ አዘዘው፡፡
*   *   *
ዕድሜያቸው፣ አስተዳደጋቸው፣ የተማሩበት የትምህርት ሥርዓት፣  የታገሉበት ርዕዮተ- ዓለም፣ የኖሩበት የትግል ታክቲክና ብልጠት፣ የሚመኙት የረዥም ጊዜ ስትራቴጂና ግብ እጅግ ተቀራራቢ የሆኑ ወንድማማቾች፣ ሥጋ- ዘመዶች፣ ወንድም  አከል ጓደኛሞች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና መንግስታት እጅግ የተለየና ተዓምራዊ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር አዋላጅ ቢመጣ አማላጅ፣ አዋዳጅ ቢመጣ አጣማጅ፣ አወቅሁሽ ናቅሁሽ መባባላቸው፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚል የዕኩይ- ፉክክር ማድረጋቸው የማይቀር ነው፡፡ የአንድ እናት ልጆች ናቸውና፡፡ የአንድ አስተሳሰብ ጥንስሶች ናቸውና፡፡  ስለሆነም ለመራራቅ መተዛዘብ፣  ለመነካካት መቀራረብ ይቀናቸዋል፡፡ ቀላሉን ያወሳስባሉ፡፡ ውስብስቡን ያናንቃሉ፡፡ “ምን አለ?” ሳይሆን፣ “ማን አለ?” እና “የማን ሰው ነው?” ይሆናል የጨዋታው ህግ፡፡ በየትኛውም አጀንዳ ላይ አንዱ እሚለውን ለማፍረስ ሌላው ሳይተኛ ያድራል፡፡
ከየጎራቸው ውጪ ያለው ህዝብ ቢመክራቸው በጄ አይሉም፡፡ ማተቤን ማተብህ አድርግ፣ ለእኔ ዕምነት አደግድግ፣ ማለትን እንደ አሠርቱ ትዕዛዛት ሊያስጠኑት ይጣጣራሉ እንጂ ሁሉን መርምረህ የሚበጅህን አንተ ዕወቅ አይሉትም፡፡ በልዩነቶቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በአንድነቶቻቸው ላይም ይጣላሉ፡፡ መጣላትን እንደ ዓላማ የያዙ እስኪመስለን ድረስ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ- የሚሉም ያጋጥማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅት እንጂ አገር የላቸውም፡፡ ከቶውንም “ተመሳሳዮች  ይገፋፋሉ፣ ተቃራኒዎች ይሳሳባሉ” የሚለውም የሳይንስ ህግ አይገዛቸውም፡፡ በምንም ስለ ምንም ጉዳይ አይደማመጡምና። ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ አንድ ተንኮል ተግተው፣ አንድ ምሥጢር ተጋርተው አድገው እኒህ ወንድማማቾች እንደምን ሊፋቀሩ ይቻላቸዋል? ለህዝቡ፣ ለጋራ-ቤታችን፣ ለአገሩ፣ ለአህጉሩ፣ ለሉሉ ስንል ተሳስበን እንደር፣ ደግ ደጉ ይታየን ቢባሉ ልሣን ለልሣን ማን ተግባብቶ?
“ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት”
እንዲል መፅሐፈ-ተውኔት ይጠፋፋሉ፡፡ በቋንቋ መጠፋፋት ወደ አለመግባባት፣ ወደ አለመቻቻልና ወደ መቂያቂያም ከዚያ አንድያውን ወደ መፈጃጀት ያመራቸዋል፡፡ ይሄ ለሀገር አይበጅም፡፡ ሁሉን ከልብ ካላረጉት ከጊዜያዊ ታክቲክነት አያልፍም፡፡
“መርሃ ግብር አውጣ፣ ልዩነት አውጣጣ፣ አማራጭ አምጣ፣ የአማራጭ አማራጭ አዋጣ፣ እንደምንም አናት ውጣ..” ነው ነገሩ፡፡ ብቻ ይኸንንም አታሳጣ! ከማለት በቀር መቼም ምርጫም አማራጭም የለም፡፡
ተመራጩ፣ አስመራጩ፣ አማራጩ፣ ታዛቢውና ሀሳዊ- ተመልካቹ በሙሉ፣ በአንድ ልብ እንዲያስቡ፣ ህዝቡን ትተው በንብረቱ የማይጣሉና ራሳቸውን ሳይሆን የአገሪቱን ህልውና ማዕከል የሚያደርጉ ተሟጋቾች ለማግኘት ማለም ይገባናል፡፡ አለበለዚያ ከስንት ዘመን በፊት እንደተባለው ዛሬም “ጠላታችንን እናታችን እንደምትወልድልን” ከማየትና ከመታዘብ ሌላ መላም ላይኖረን ነው፡፡ ለማንኛውም፤
እናት ብዙ ልጆች አሏት
ያም “እናቴ” ያም “እናቴ” ብሎ ሚላት፡፡
ያም በፍቅር እንዳያንቃት
ያም በቅናት እንዳይነክሳት
ያ ከሥሯ እንዳይነቅላት
ያም ባፍጢሟ እንዳይተክላት
ሰብሰብ ብለህ ሰብስባት!!
ብሎ አደራን ማጥበቁ ሳይሻል አይቀርም፡፡

  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከትግራይ ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርና ጥቃት በአፋጣኝ ሊቆም እንደሚገባ ያሳሰበ ሲሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤  በትግራይ ተወላጆች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ላይ የሚደረግ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር እንዲቆም ጠይቋል።
ኢሰመኮ፤ በሲቪል ሰዎች ላይ እንግልትና እስር፣ ጥቃት እንዲሁም  የንግድ ቤት መዘጋት መከሰቱንና ሕይወት መጥፋቱን የጠቀሰው ኢሰመኮ፤በእስረኞችና በምርኮኞች ላይ የሚደርስ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀምን የሚያመላክቱ መረጃዎች እጅግ እንደሚያሳስበው አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸውን  መረጃ ደርሶኛል ብሏል።
አምነስቲ ኢንተርናሽል በበኩሉ፤#የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የትግራይ ተወላጆችን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መልኩ አስሯል; ሲል መግለጫ አውጥቷል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ታስረው እንደሚገኙ የጠቆመው አምነስቲ፤ መንግሥት ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርን እንዲያቆምና አሁንም ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩትን በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቅ ጠይቋል።
የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ፤ “ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው ማንነቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ለእስር አልተዳረገም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

  በትግራይ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ  እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት፣ ብሎም በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከሰቱንና ሕይወት መጥፋቱን፣ እንዲሁም በታሳሪዎችና በምርኮኞች ላይ የሚደርስ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን   ለውትድርና መጠቀም የሚያመላክቱ መረጃዎች እጅግ የሚያሳስበው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ ሦስት የትግራይ ተወላጆች ላይ በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸውን  ለኮሚሽኑ የደረሱት ጥቆማዎች ያመለክታሉ።
ይህ  ጥቃት የደረሰው ከእለቱ አንድ ቀን አስቀድሞ ፍየል ውሃ በሚባል ቦታ የሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች በወሰዱት የጥቃት እርምጃ የፎገራ ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑ የሚሊሽያ ቡድን አባላትና የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መገደላቸው  ከተነገረ በኋላ ነው። ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋዱን ጉመራ ወንዝ ተብሎ ከሚጠራና  ከተገደሉት የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ትውልድ ቦታ የኃላፊውን እሬሳ ለመቀበል  የመጡ ነዋሪዎች  ጥቃቱን እንዳደረሱ ይነገራል።
የፎገራ ወረዳና የአካባቢው የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊዎች በወሰዱት አፋጣኝ እርምጃ ሁኔታው የተረጋጋና ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም፣ የተከሰተው ሁኔታ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንዳይዛመት የሚያሰጋ ነው ብሏል ኢሰመኮ።  በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይና የሕወሃት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች ተቃዋሚ ናቸው በሚል በሲቪል ሰዎች ላይ እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች የሚያሳስቡ መሆናቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል። በተጨማሪም፤ በአላማጣና አካባቢው በድጋሚ ያገረሸውን ግጭትና በመኾኒ እየተወሰዱ ስለመሆናቸውን የሚነገሩ የበቀል ጥቃቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰዎች መፈናቀል እያደረሰ ነው ብሏል።
ቴሌኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራውን አዳጋች ያደረገው ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን የተደራሽነት ሁኔታ በተመለከተ የሚያደርገውን ክትትል የሚቀጥልና በቆቦ፣ በወልዲያና በማርሳ ተጠልለው የሚገኙ ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚጎበኝ መሆኑን አስታውቋል፡፡   
ኢሰመኮ የግጭቱ መባባስና የግጭቱ ተጽእኖ በአፋርና በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎችን ጨምሮ ወደ ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጭምር መስፋፋቱ እጅግ እንደሚያሳስበው ነው የጠቆመው።
እንዲሁም ኮሚሽኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚደርሱትንና በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሱ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋትና የእንግልት መረጃዎችንም እየተከታተለ ይገኛል።  የሚድያ ሰራተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌሎች  ቦታዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ለኮሚሽኑ ጥቆማዎች ደርሰውታል።
ከሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ  ተባብሶ የታየው  ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ክስተትና እስር ሁኔታ ተገቢውን ትኩረትና መፍትሔ ከአለማግኘቱ በተጨማሪ፤ በስፋት የሚደመጡ የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች ሁኔታው ሊያባብሱና  ብሎም በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ትስስር ሊያላሉ የሚችሉ ናቸው። ስለሆነም፣ በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልል መስተዳድሮች በነዚህ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ሕግ ፊት ሊያቀርቡ ይገባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “በተለይም ይህን በመሰለ ፈታኝና የውጥረት ወቅት መንግስት ለሲቪል ሰዎችና ተጋላጭ ለሆነው ማኅበረሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የማድረግ ተጨማሪ ኃላፊነት የሚጣልበት ጊዜ ነው። መሰረታዊ የሆኑ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና የሰብአዊ መብቶች መርሆች በግጭት ወቅት ጭምር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያዙና ሲቪል ሰዎችና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ላይ ከፍ ያለ ግዴታ የሚጥሉ ናቸው።  ስለሆነም ኮሚሽናችን በእስር ላይ ያሉ  ሰዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ የሚያደርገውን የክትትል ስራ የሚቀጥል ሲሆን፣ በግጭቱ ለሚሳተፉ ወገኖች በሙሉ እንዲሁም የሚድያ ተቋማትን ጨምሮ ለሀገራዊና ለዓለም አቀፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሙሉ ማንኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር፣ መግለጫዎችና ተግባራት እንዲቆጠቡ ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል” ብለዋል። 
በሌላ በኩል ኢሰመኮ፤  ሰኔ 23፣ 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙትን በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ አበበ ባዩ፣ መልካም ፍሬ ይማም፣ ፍቅርተ የኑስ፣ ዊንታና በርሄ እና ምህረት ገብረክርስቶስን ጨምሮ 21 የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን ጠቁሟል፡፡
ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል ሦስቱንና አንድ ሌላ ታሳሪን ጨምሮ አራት እስረኞች ማክሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ መለቀቃቸውንና ቀሪዎቹ ታሳሪዎች በወንጀል ስለተጠረጠሩ ለምርመራ ስራ በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ መሰጠቱን ፖሊስ ለኮሚሽኑ  የገለጸ ቢሆንም፣ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማየቱና ታሳሪዎቹን ለመጎብኘት አለመቻሉ፤ እንዲሁም ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ሳይገናኙ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸው ኢሰመኮን  እጅግ የሚያሳስበው ነው ብሏል።
ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑና በእስር ያሉ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብት ፈጽሞ ሊከለከሉ የማይገቡና ተጠርጣሪዎች በሕይወት መኖራቸውንና አካላዊ ደኅንነታቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሰረታዊ የሕግ ጥበቃዎች መሆናቸውን በመግለጫው አስታውሷል፤ኢሰመኮ፡፡
ስለሆነም የፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አሁንም በእስር ያሉ የአውሎ ሚድያና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞችና ሰራተኞች በሙሉ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው እንዲገናኙ እንዲያደርጉ፣ የታሳሪዎቹን የእስር ሁኔታ ሕጋዊነት እንዲያስረዱና፣ ከፍርድ ቤት የተሰጠ የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በስተቀር ታሳሪዎቹ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ኮሚሽኑ  አሳስቧል፡፡
 ሕግን ያልተከተለ ማንኛውም አይነት እስር በሕግና ፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚኖርን እምነት የሚሸረሽር በመሆኑ፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር ሙሉ በሙሉ መቆም ያለበት ተግባር ነው ያሉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹን ለመጎብኘትና የአያያዛቸውን ሁኔታ ለማወቅ የሚያደርገውን ጥረት ይቀጥላል” ብለዋል።


Page 1 of 535