Administrator

Administrator

Saturday, 13 November 2021 14:36

ፍቱን መድሃኒት

ለዚህች ሀገር ችግር - መፍትሔ ጥቆማ
አንድ ሀሳብ ነበረኝ - ይሄ ሕዝብ ቢሰማ!
ህላዌ ነታችን
ልቃቂት ፈትላችን
ቁጢቱ ሲመዘዝ - ድውሩ ፈትላችን
"ወፌ ቆመች" ብለን ......
ድኸን በመጣነው - ረጅም መንገዳችን
በነፋስ አውታር ላይ
በእሳት ሰረገላ
ሽምጥ ሲመለስን - ድንገት ተገናኘን -
ከሸክላነት ገላ!
ያኔ
ከፈጣሪ ሃሳብ - ከአፈር ተፈጥረናል
መላእክት ታዞልን - ከአውሬ
ተጫውተናል
ርቃን ገላ ሆነን በጸጋው ሞቀናል
ፍጥረቱን ስንገዛ .........
ባይገባን ነው እንጂ - ለካ በክብራችን -
ከብሔር ድመናል!
አወይ የዚያን ጊዜ
ምስጢሩ ከፍ ሲል - የእግዜር ዘር ይዘናል
ዝቅ ሲል ነገሩ - የጥንቱ ጭቃችን - አፈር
ይቀርበናል!
እንደ ታላቅ ዥረት - ፈስሰን ላናበቃ
ከእድሜ በላይ ሆነን - ስንተኛ ስንነቃ
ስንበላ ስንጠጣ - በማይጎድፍ ጸጋ
ከቶ መች ነበረን?
የሚበርደን ክረምት - የሚሞቀን በጋ ?!
ደግ ታሪክ ሆኖ - ይህ ሁሉ ካለፈ
እኔ ምክር አለኝ ............
ለዚህ ዘመን ችግር - ሃቅ እውነት የጻፈ!
ትውልድ ያስታረቀ - በደልን ያራቀ
የእሳት እንባን ጠርጎ - ፊትን ያደረቀ
ምቹ ቅዱስ አልጋ - በልብ የጸደቀ
ሰው ሆኖ መኖር ነው ................
ፍቱን መድሃኒቱ - ከጥንት የታወቀ !
ጥበቃ
ኢትዮጵያን እናፍርስ - ብለው ሲማማሉ
ክብርዋን ለማዋረድ - ስምዋን ሲታገሉ
ህልማቸው ጉም ሆኖ - ተነነ በአፍታ
ዛሬም እሳት ሆኖ ………………
ቅጥርዋን ይጠብቃል - የሰማዩ ጌታ!
     (ነፃነት አምሳሉ)


Saturday, 13 November 2021 14:35

የፖለቲካ ጥግ

• አገርን ከጠላት ለመከላከል የሚያስፈልገው ሠራዊት ነው፤ ስልጣኔ ከጥፋት ለመከላከል የሚያስፈልገው ግን ትምህርት ነው፡፡
  ጆናታን ሳክስ
• ህዝብ፤ አገሩን ከባዕድ ወራሪዎች የመከላከል መብት አለው፤ አገሩን ሊያወድሙበት ከመጡ ወራሪዎችም የመከላከል መብት አለው፡፡
  ኖርማን ፊንክልስቲን
• አገራችንን ከሽብርተኝነት አደጋ ለመከላከል ቁርጠኛ ነኝ፡፡
  ጂም ሪዩን
• -አሜሪካ የህዝቧን ደህንነት ለመጠበቅ የፈቃድ ወረቀት ፈፅሞ አትሻም።
  ጆርጅ ደብሊው. ቡሽ
• የእኔ ጀግኖች፤ ዓለማችንን ከአደጋ ለመጠበቅና የተሻለች የመኖሪያ ሥፍራ ለማድረግ በየቀኑ ህይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሰዎች ናቸው -ፖሊሶች፣ የእሳት አደጋ ተከላካዮችና የጦር ሰራዊት አባላት።
  ሲድኒ ሼልደን
• ወርቅ በእሳት ይፈተናል፤ ጀግኖች ደግሞ በመከራ።
  ሴኔካ
• ጀግና የሌሎችን ጥንካሬ ይቀበላል።
  ቬሮኒካ ሩት
• ጀግና ተዋጊ መቼ ማፈግፈግ እንዳለበት ያውቃል።
  ማዮሪን ጆይስ ኮኖሊ
• ያለ ፍርሀት ድፍረት ሊኖር አይችልም።
  ክርስቶፈር ፓኦሊኒ
• ነፃነት ማለት ሃላፊነት ነው። ለዚያ ነው አብዛኛው ሰው የሚፈራው።
  ጆርጅ በርናንድ ሾው

Saturday, 13 November 2021 14:34

የዘላለም ጥግ

 • የዕውቀት ብቸኛው ምንጭ ተሞክሮ ነው፡፡
  አልበርት አንስታይን
• የትኛውም ታላቅ ነገር ድንገት አይፈጠርም፡፡
  ኢፕክቴተስ
• ደስታን የሚያመጣልን ጉዞው እንጂ መዳረሻው አይደለም፡፡
  ዳን ሚልማን
• ራስህን ማወቅ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡
  አርስቶትል
• ከአንተ ከማይሻል ሰው ጋር ፈጽሞ ወዳጅነት አትፍጠር፡፡
  ኮንፋሺየስ
• ፍልስፍና የእውቀት ሳይንስ ነው፡፡
  አርስቶትል
• ሰው የሁሉም ነገሮች መለኪያ ነው፡፡
  ፕሮታጎረስ
• ያለ ሳቅ የሚያልፍ ቀን የባከነ ቀን ነው፡፡
  ኒኮላስ ቻምፎርት
• ህይወት የሚፈታ ችግር ሳይሆን የሚኖሩት እውነታ ነው፡፡
  ሶሬን ኪርክጋርድ
• ሰዎችን ከጠላህ በእነሱ ተሸንፈሀል ማለት ነው፡፡
  ኮንፋሺየስ
• ለፍቅር መድሀኒት የለውም፤ የበለጠ ማፍቀር እንጂ፡፡
  ሄነሪ ዴቪድ
• ዓለምን ሳይሆን እራስህን አሸንፍ።
  ሬኔ ዬስካርተስ
• የሌሎች ባህሪ የውስጥህን ሰላም እንዲረብሸው አትፍቀድ፡፡
  ዳላይ ላማ

Saturday, 13 November 2021 14:08

የጥበብ ጥግ

 • መፃሕፍትን ውደድ እንዴት ያለ በረከት ነው!
  ኤሊዛቤት ቮን አርኒም
• መፃሕፍትን ከማንበብ ይልቅ መፃፍ ነበረብኝ፡፡
  አላን ላይትማን
• እንደ መፅሐፍ ያለ ታማኝ ወዳጅ የለም፡፡
  ኸርነስት ሄማንግ ዌይ
• አንድ ጊዜ ማንበብ ከተማርክ፣ ለዘላለም ነፃ ትወጣለህ፡፡
  ፍሬድክስ ዳግላስ
• ጥሩ መፅሐፍ ማንበብ የመጓዝ ያህል ነው፡፡
  ኢማ ጉሊትፍርድ
• በመፃሕፍት ካልተከበብኩ በስተቀር እንቅልፍ አይወስደኝም፡፡
  ጆርግ ሊዊስ ቦርግስ
• ማለፊያ መፅሐፍ መጨረሻ የለውም፡፡
  አርዲ ከሚንግ
• ያለ መፃሕፍት መኖር አልችልም፡፡
  ቶማስ ጃፈርሰን
• ምርጥ ወዳጄ የምለው ያላነበብኩትን መፅሐፍ የሚሰጠኝን ነው፡፡
  አብርሃም ሊንከን
• ደግመን ስናነብ ሌላ አዲስ መፅሐፍ እናገኛለን፡፡
  ማሶን ኩሌይ
• መፃሕፍት የነፍስ መስታወት ናቸው፡፡
  ቨርጂንያ ውልፍ
• መፃሕፍት የሌሉበት ክፍል፣ ነፍስ አልባ አካል ማለት ነው፡፡
  ማርከስ ቱሊየርስ ሲሰሮ
• መፅሐፍ ስታነብ ፈፅሞ ብቻህን አይደለህም፡፡
  ሱሳን ዊግስ
• የተማርኩትን ሁሉ የተማርኩት ከመፃሕፍት ነው፡፡
  አብርሃም ሊንከን
• አሮጌ ኮት ለብሰህ አዲስ መፅሐፍ ግዛ።
  ኦስቲን ፌልፕስ
• መፃሕፍት የአዕምሮ ልጆች ናቸው፡፡
   ጆናታን ስዊፍት

Saturday, 13 November 2021 14:03

የወቅቱ ጥቅስ


"ይቅር-ባይነት የደግነት ሁሉ የበላይ ነው!!

ከእኔ ይቅር ማለት ታላቅ ፀጋንመጎናጸፍ ነው፡"
በኢንቨስትመንት ዘርፍ በተቀዳጁት የላቀ ስኬት የሚታወቁት አሜሪካዊ ቢሊየነርና ችሮታ አድራጊ ዋረን በፌ፤ እንደማንኛውም ሰው ብዙ ችግሮችና ውጣ ውረዶች ተጋፍጠዋል ሳያሰልሱ ተግተው በፅናት በመስራት ግን የስኬት ማማ ላይ ሊወጡ ችለዋል፡፡
የዓለማችን ቁጥር 1 ባለጸጋ ሊሆኑም በቅተዋል፡፡ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ለችሮታ አድራጊዎች በመለገስም ስማቸው ይነሳል፡፡
 በፌ ገና በ11 ዓመት ዕድሜው ላይ ነበር የመጀመሪያውን አክስዮን የገዛው፡፡ ኮካ ኮላና አይስክሬም የሰጠ ይድከም ነው፡፡ በእርግጥ የኮካ ኮላ ትልቅ የአክስዮን ድርሻ አለው፡፡ የትዊተር አካውንት ቢኖረውም ተጠቅሞበት አያውቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ105.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያለው ሲሆን ይህም የዓለማችን 10ኛ ባለፀጋ ያደርገዋል፡፡
የቢሊኒየሩን አስር አስገራሚ እውነታዎች እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡ የልጅነት ዘመኑን “አንተ” እያልን እንዘልቅና ወደ ጉልምስና ዕድሜው ላይ “አንቱ” እያልን እንደምንተርክ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን፡፡ እነሆ የቢሊኒየሩ አስገራሚ እውነታዎች፡፡
በፌ የመጀመሪያ አክስዮኑን የገዛው በ11 ዓመት ዕድሜው ነበር
አብዛኞቹ የዕድሜ እኩዮቹ ቤዝ ቦል በሚጫወቱበትና የኮሚክ መፃህፍት በሚያነቡበት ወቅት ነበር፤በፌ አክስዮን  የገዛው፡፡ እ.ኤ.አ በ1942 ዓ.ም በ11 ዓመት ዕድሜው ላይ
የ“Cities Service Preferred (አሁን CITGO በሚል ይታወቃል) አክስዮንን ስድስት ድርሻዎች ገዛ- እያንዳንዳቸውን በ38 ዶላር፡፡
 በ16 ዓመቱ 53 ሺ ዶላር አግኝቷል
በፌ ከልጅነቱ ጀምሮ ዘዴኛ ብቻ ሳይሆን እጅግ ጠንካራ ሰራተኛም ነበር፡፡ አባቱ የኮንግረስ አባል ሆነው ሲመረጡ፣ ቤተሰቡ መኖሪያውን ከኦማሃ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ አዛወረ፡፡ በዚያን ጊዜ  ታዳጊው በፌ “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጣን በየጠዋቱ ለደንበኞች እያደረሰ፣በወር 175 ዶላር ገደማ ያገኝ ነበር፡፡ (በወቅቱ አብዛኞቹ መምህራን ከሚያገኙት ደሞዝ በላይ ማለት ነው፡፡)
በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች ሥራዎችንም ጎን ለጎን ይሰራ ነር፡፡ ለምሳሌ፡- ያገለገሉ የጎልፍ ኳሶችን መሸጥና ሌሎችም፡፡ 16 ዓመት ሲሞላው ታዲያ ከገዛቸው የተለያዩ አክስዮኖችና ኢንቨስትመንቶች 53 ሺ ዶላር አገኘ፡፡
ሃርቫርድ ቢዝነስ ስኩል ለመግባት ፈልጎ ሳይቀበሉት ቀረ
በፌ ከብራኔስካ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ ሃርቫርድ ቢዝነስ ስኩል ለመግባት አመልክቶ ነበር፡፡ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱን በሚወስነው አጭር ቃለ መጠየቅ ወቅት ታዲያ ቁርጡ ተነገረው፡፡ የት/ቤቱ ኃላፊ፤ “እርሳው፣ሃርቫርድ አትገባም” ብለው አሰናበቱት፡፡
ቢሊዬነሩ ከ1958 አንስቶ መኖሪያ ቤታቸውን አለወጡም
ስለ ቢሊኒየር ስናስብ ብዙ ጊዜ ወደ አዕምሮአችን የሚመጣው የተንጣለሉ ቅንጡ ቪላዎችና ወድ አውቶሞቢሎች ናቸው፡፡ ይህ ግን ለዋረን በፌ አይሰራም፡፡ እ.ኤ.አ ከ1958 አንስቶ በ31 ሺ 500 ዶላር በገዙት የኦማሃ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነው የሚኖሩት…ባለ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት ተራ ቤት ውስጥ!
በፌ በ2013 በቀን 37 ሚሊዮን ዶላር ያስገቡ ነበር
እ.ኤ.አ በ2013 መጨረሻ ላይ የሃብታቸው መጠን የተጣራ 59 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በዚያው ዓመት በቀን በአማካይ 37 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኙ ነበር፡፡
94 በመቶ ገደማ ሃብታቸውን ያገኙት 60 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ነው
ስኬት በማናቸውም ዕድሜ ላይ ይመጣል፡፡ በፌ ከ60 ዓመታቸው በፊት በእጅጉ ስኬታማ ነበሩ …በ52 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ የሀብታቸው መጠን 372 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር …99 በመቶ ሃብታቸውን ያገኙት 50 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ነው፡፡ በ89 ዓመታቸው ላይ የሀብታቸው መጠን 81.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በትዊተራቸው ላይ ፅፈው አያውቁም
ዋረን በፌ ከ1.25 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር ገጽ (e warren Buffett) ቢኖራቸውም፣ ስምንት ጽሁፎች ብቻ ናቸው የተለጠፉት፡፡ አንዱም ታዲያ በእሳቸው የተጻፈ አይደለም፡፡
“የትዊተር መልዕክት ስለመፍጠር ያጫወተችኝ አንድ ወዳጄ ነበረች፡፡ እርሷ ናት እነዚያን ጽሁፎች የለጠፈችው። እኔ ግን ትዊተር ላይ ምንም ነገር ጽፌ አላውቅም።” ሲሉ ለCNBC አጋርተዋል። ቢሊኒየሩ፣ የማንም ትዊተር ተከታይ አይደሉም፡፡ ኢሜይል ልከውም አያውቁም፡፡
የቀናቸውን 80  በመቶ የሚያሳልፉት በማንበብ ነው
ከመኝታቸው ከነቁበት ቅጽበት አንስቶ ጋዜጣ ላይ እንዳቀረቀሩ ነው፡፡ እንዲያውም የቀኑን 80 በመቶ ያህል የሚያሳልፉት በንባብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በፌ ለስኬታቸው ቁልፍ ምን እንደሆነ ሲጠየቁ ፣ወደ መጻህፍት ክምር እየጠቆሙ፤”በየቀኑ እንደዚህ 500 ገጾችን አንብብ፡፡ ዕውቀት የሚሰራው እንዲያ ነው። እንደሚባዛ ወለድ ይበራከታል፡፡” ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
በፌ 20 ሙሉ ልብስ ቢኖራቸውም፤ ለአንዱም እንኳ አልከፈሉበትም
ዋረን በፌ 20 የሚጠጉ ሙሉ ልብሶች አሏቸው፤በአንድ ዲዛይነር የተሰሩ ….በማዳም ሊ፡፡
በአንድ ወቅት በፌ ወደ ቻይና በተጓዙበት ወቅት፣ ሆቴላቸው እንደደረሱ ፣”ሁለት ወንዶች ወደ ክፍሉ ዘለው ይገባሉ….ወዲያው ዙሪያዬን እየተሽከረከሩ በሜትር መለካት ጀመሩ፤ ከዚያም የሙሉ ልብስ ናሙናዎች የያዘ መጽሀፍ አሳዩኝና አንዱን ምረጥ አሉኝ፤ ማዳም  ሊ አንድ ሙሉ ልብስ ልታበረክትል ትሻለች” እንዳሏቸው ለCNBC ተናግረዋል፡፡
ዲዛይነሯን ሳያገኟት፣አንድ ሙሉ ልብስ መርጠው ወሰዱ፤ ሌላም ደገሙ፡፡ በመጨረሻም ከምስጢረኛዋ ዲዛይነር ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ፣ ሙያዊ ግንኑነት ያዳበሩ ሲሆን፣እሷም ለበፌ ሙሉ ልብሶች መላኳን ቀጠለች፡፡ 20ዎቹም የበፌ ሙሉ ልብሶች የዲዛይነሯ ስጦታዎች ናቸው፡፡
ዳግም በሊ ዋረን በፌ ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ትካፈል የነበረ ሲሆን እንደ ቢል ጌት ላሉ ሌሎች ስኬታማ የቢዝነስ  ሥራ አስፈጻሚዎችም ሙሉ ልብስ ሰርታ ማልበስ ጀመረች፡፡
የበርክሻየር ሃታዌይ አክስዮናቸውን 85 በመቶ ለችሮታ አድራጊ ድርጅቶች ለመለገስ ቃል ገብተዋል
በፌ ስኬታማ ኢንቨስተርና የተዋጣለቻው የቢዝነስ አስፈፃሚ ከመሆንም ባሻገር የታወቁ በጎ አድራጊም ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም 85  ፐርሰንት የበርክሻየር ሃታዌይ አክስዮናቸውን ለአምስት ፋውንዴሽኖች ቀስ በቀስ ለመለገስ ማቀዳቸውን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ቃላቸውንም አክብረው አድርገውታል፡፡ በጁላይ 2019 ዓ.ም ከ3.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የበርክሻየር ሃታዌይ  አክስዮን፣ለአምስት ፋውንዴሽኖች የለገሱ ሲሆን ከእነዚያም ውስጥ አንዱ ቢል ጌትስና ባለቤታቸው የመሰረቱት “ቢል ኤንድ ጌትስ ፋውንዴሸን” ነው፡፡ ዋረን በፌ ከ2006 አንስቶ 34.5 ቢሊዮን ዶላር ለችሮታ አድራጊ ድርጅቶች ለግሰዋል። ቢሊዮነሩ ገንዘብ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ገንዘብ መለገስም ያውቁበታል፡፡

 ቶም ሃንከስ ለ12 ደቂቃ የጠፈር ጉዞ 28ሚ. ዶላር አልከፍልም ብሎ መቅረቱን ተናገረ

                ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም በ2021 የፈረንጆች አመት ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ዝነኞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው ፎርብስ መጽሔት፣ በህይወት ሳለ ከ43 በላይ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃው የህጻናት መጽሐፍት ደራሲው ሮድል ዳል፣ በ513 ሚሊዮን ዶላር የ1ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ደራሲው ለህትመት ካበቃቸው መጽሐፍት መካከል አብዛኞቹ በፊልም መልክ ተሰርተው በስፋት በመታየት ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ፎርብስ፣ ኔትፍሊክስን ጨምሮ ፊልሞቹ በተለያዩ መንገዶች በስፋት መታየታቸው ከፍተኛ ገቢ እንዳስገኘለትም አመልክቷል፡፡
ከ5 አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለየው ታዋቂው ድምጻዊ ፕሪንስ በ120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ላለፉት 8 ተከታታይ አመታት በህይወት ከሌሉ ዝነኞች መካከል ከፍተኛውን ገቢ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃን ይዞ የዘለቀው የአለማችን የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን፣ ዘንድሮ 75 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በማግኘቱ ወደ 3ኛነት ዝቅ ብሏል፡፡
የተከታታይ ፊልሞች ፕሮዲዩሰሩ ቻርለስ ሹልዝ በ40 ሚሊዮን ዶላር፣ የህጻናት መጽሐፍትና ፊልሞች ደራሲው ዶክተር ሲዩስ በ35 ሚሊዮን ዶላር የአራተኛና የአምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውንም ፎርብስ አስታውቋል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ዝነኞች መካከልም የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ እና ኤልቪስ ፕሪስሊ ይገኙበታል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ቶም ሃንከስ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ባለፈው ወር ወደ ጠፈር ባደረጉት ታሪካዊ ጉዞ አብሯቸው እንዲጓዝ ጥያቄ አቅርበውለት እንደነበርና እሱ ግን ክፍያው እጅግ ሲበዛ ውድ ነው በማለትና ግብዣውን ባለመቀበል ከጉዞው መቅረቱን ከሰሞኑ በይፋ መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
12 ደቂቃዎችን በፈጀውና የ28 ሚሊዮን ዶላር ትኬት በተቆረጠበት የጠፈር ጉዞ ላይ እንዲሳተፍ ከጉዞው አዘጋጅ ኩባንያ ብሉ ኦሪጅን ባለቤት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ጄፍ ቤዞስ ግብዣ ቀርቦለት እንደነበር ያስታወሰው ቶም ሃንከስ፣ ምንም ሃብት ቢኖረኝ ለ12 ደቂቃ በረራ 28 ሚሊዮን ዶላር አልከፍልም፤ በጣም ውድ ነው በማለት ሃሳቡን እንዳልተቀበለው ነው የተናገረው፡፡
የ65 አመቱ የኦስካር ተሸላሚ ቶም ሃንከስ፣ ለ12 ደቂቃ ጠፈር ደርሼ ለመምጣት 28 ሚሊዮን ዶላር ምን አስወጣኝ፤ እዚሁ ሆኜ በምናብ ደርሼ መምጣት እችል የለ እንዴ ብሏል፡፡ እያንዳንዳችን ባለንበት ሆነን ወደ ጠፈር የመጓዝን ስሜት ልንፈጥረውና ወንበራችን ላይ ሆነን ጠፈር ላይ የወጣን ያህል እንዲሰማን ማድረግ እንችላለን ማለቱም ተነግሯል፡፡


  አጫጭር ቪዲዮችን ለማጋራት የሚያስችለውና በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማትረፍ ላይ የሚገኘው ቲክቶክ በጥቅምት ወር ብቻ ከ57 ሚሊዮን ጊዜያት በላይ በተጠቃሚዎች ዳውንሎድ መደረጉንና ላለፉት 10 ተከታታይ ወራት በብዛት ዳውንሎድ በመደረግ ቀዳሚው የአለማችን አፕሊኬሽን መሆኑን ቴክ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ቻይና ሰራሹ አፕሊኬሽን ባለፈው አመት 2020 በብዛት በመደረግ ቀዳሚው የአለማችን አፕሊኬሽን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ አፕሊኬሽኑ ባለፈው ወር በብዛት ዳውንሎድ ከተደረገባቸው አገራት መካከል ቻይና እና አሜሪካ እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡
በጥቅምት ወር ብቻ 56 ሚሊዮን ያህል ጊዜ ዳውንሎድ የተደረገው ኢንስታግራም ከቲክቶክ በመቀጠል በወሩ በብዛት የተደረገ ሁለተኛው አፕሊኬሽን መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ፌስቡክ፣ ዋትሳፕና ቴሌግራም እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡


   የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በሚገኙ 193 አገራት ውስጥ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ከ8 ሚሊዮን በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ መፈጠሩንና አብዛኛው ቆሻሻም በውቅያኖሶች ውስጥ እንደተጣለ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በውቅያኖስ ውስጥ ከተጣለው 26 ሺህ ሜትሪክ ቶን ያህል የፕላስቲክ ቆሻሻ መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከሆስፒታሎች የወጣ እንደሆነና ቆሻሻው ለውሃ አካላት ስነምህዳር ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ነው መባሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ የቻይናና የአሜሪካ ተመራማሪዎች በጋራ የሰሩትን ጥናት ዋቢ አድርጎ ዘገባው እንዳለው፣ ኮሮናን ለመከላከል ሲባል ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ቁሳቁሶች እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
በአለም ዙሪያ ከተመረተው የፕላስቲክ ቆሻሻ መካከል 72 በመቶ ያህሉ ከእስያ አገራት የወጣ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ እስከ ሃምሌ ወር ድረስ በአለም ዙሪያ ከኮሮና ጋር በተያያዙ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ሳቢያ እንስሳት ለሞት የተዳረጉባቸውና የተጎዱባቸው 61 ያህል ክስተቶች መመዝገባቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


  በመላው አለም የአካል ጉዳተኛ ህጻናት ቁጥር ከ240 ሚሊዮን ማለፉንና ህጻናቱ የመብቶቻቸው ተጠቃሚዎች እንዳይሆኑ የሚያግዷቸው እንቅፋቶችና ፈተናዎች እየተበራከቱ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ሰሞኑን ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ የህጻናትን አጠቃላይ ደህንነት ሁኔታ ለመገምገም የሚያስችሉ 60 ያህል ነጥቦችን መሰረት በማድረግ በ42 የአለማችን አገራት የሰራውን ጥናት ውጤት ባካተተበት ሪፖርቱ እንዳለው፣ የአካል ጉዳተኛ ህጻናት በአብዛኛው ከሌሎች ህጻናት ጋር ሲነጻጸር ተገቢው ትኩረት አይሰጣቸውም፡፡
አካል ጉዳተኛ ህጻናት በማህበረሰባቸው ውስጥ በበቂ መጠን ተሳትፎ እንዳያደርጉ ጫና እንዳለባቸውና የተመጣጠነ ምግብና የንጹህ ውሃ አቅርቦት በበቂ መጠን እንደማያገኙ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለተለያዩ አካላዊና ልቦናዊ ጥቃቶች እንዲሁም ለጉልበት ብዝበዛ እንደሚዳረጉም አመልክቷል፡፡
የአካል ጉዳተኝነት ችግር ያለባቸው ህጻናት ከሌለባቸው ጋር ሲነጻጸር፣ ከትምህርት ገበታ ውጭ የመሆን፣ አነስተኛ የንባብ ችሎታ የመያዝ፣ ደስተኛ ያለመሆን እድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነም ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡


Page 5 of 566