Administrator

Administrator

ሠማያዊ ፓርቲ የአይኤስን የሽብር ድርጊት ለማውገዝ መንግስት የጠራውን ሠልፍ አውኳል በሚል በመንግስት እየተወነጀለ ሲሆን ፓርቲው በበኩሉ፤ በተፈጠረው ረብሻ እጄ የለበትም፤ መንግስት ያለ አግባብ የስም ማጥፋትና ውንጀላ ዘመቻ ከፍቶብኛል ሲል አማሯል፡፡ መንግስትና የመንግስት ሚዲያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት በፓርቲው ላይ የሚሠነዝሩትን ውንጀላ ካላቆሙም ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ሊወስደው እንደሚችል አስታውቋል፡፡ መንግስት ግን ሠማያዊ ፓርቲ ሁከቱን ስለመፍጠሩ በቂ ማስረጃ አለኝ ብሏል፡፡ በሌላ በኩል፤ ሠማያዊ ፓርቲ ሠሞኑን በቅስቀሳ ፖስተር አለጣጠፍ ጉዳይ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ ደርሶታል፡፡ በእነዚህ አወዛጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡


ሠማያዊ ፓርቲ መንግስትንና የመንግስት ሚዲያዎችን እከሣለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው?
መንግስት የፓርቲው ተግባር ያልሆነን ጉዳይ አንስቶ “በረቡዕ እለቱ ሠላማዊ ሠልፍ ላይ ሁከት የፈጠረው ሠማያዊ ፓርቲ ነው” በሚል በሃሰት መወንጀሉና በፍርድ ቤት ሣይረጋገጥ ጥፋተኛ አድርጐ በመፈረጁ፤ ፌደራል ፖሊስ “7 የሰማያዊ አመራሮችን አስሬያለሁ” ያለውም ሃሰት ነው፤ የታሠሩት 6 ናቸው፤ እነሱም ከሠልፉ በፊት ነበር የታሠሩት፤ አንደኛው የዚያኑ ቀን ነው የተፈቱት፡፡
ኢቢሲንም እንከሣለን ብላችኋል፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?
የውሸት ዘገባ በማሠራጨቱ ነው፡፡ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” እያለ በምርመራ ያልተያዘን ጉዳይ አንስቶ ሠማያዊ ነው ሁከቱን ያቀነባበረው የሚሉ መሠረት የሌላቸው ስም አጥፊ ዘገባዎችን ሲሰራ ከርሟል፡፡ እነዚህ ሃሰተኛና የአንድ ወገን ዘገባዎች ደግሞ በምርጫው እንቅስቃሴ ላይ እክል እየፈጠረብን ነው፡፡ ይህ የጣቢያው ድርጊት የማይቆም ከሆነ ወደ ክስ መሄዳችን አይቀርም፡፡
“ፓርቲው የህብረተሰቡን መሪር ሃዘን ተጠቅሞ የራሱን አጀንዳ ለማስፈፀም ሲተጋ ነበር” ነው የተባለውና ከተጐጂ ቤተሰቦችና ከህብረተሰቡ የገጠማችሁ  ተቃውሞ አለ…
ኧረ ምንም አይነት ተቃውሞ አላጋጠመንም፡፡ እኛ እንደ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ከንቲባ ድሪባ ኩማ ሀዘንተኞችን አጽናንተናል ብለን ለሚዲያ ፍጆታ ባናውለውም፣ አመራሮቻችን ሃዘንተኞቹን  በየቤታቸው በመገኘት አጽናንተዋል፡፡
እንደውም በአጋጣሚ ከሠማያዊ ፓርቲ የመጣን አልመሠላቸውም ነበርና ሠማያዊ ፓርቲዎች እንዴት ነው ያላፅናኑን የሚል ሃሜት እዚያው ቁጭ ብለን ስንሰማ ነበር፡፡ እናም የሟቾቹ ቤተሰቦች በጥሩ መንፈስ ነበር የተቀበሉን፡፡ አሁንም ፈጣሪ መጽናናቱን ይስጣቸው እንላለን፡፡
በሠልፉ ላይ የፓርቲው አመራሮችም ሆኑ አባላትና ደጋፊዎች የነበራቸው ተሣትፎ በምን መልኩ ነበር?
መንግስት ሠልፉን ቢጠራም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አይኤስ የፈፀመውን አሠቃቂ ግድያ ለማውገዝ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን እንዲገኙ በዋዜማው ጥሪ አስተላልፈናል፡፡ ሠልፉን በሚገባ ደግፈን ነው የወጣነው፡፡
በሠልፉ ላይ መንግስትን ነው ወይስ አይኤስን ነው ለመቃወም የወጣችሁት? አጀንዳችሁ ምን ነበር?
በመግለጫችን ላይ ግልጽ አድርገነው ነበር፡፡ አይኤስ በወገኖቻችን ላይ የፈፀመውን አሠቃቂ ግድያ እንቃወም የሚል ነው፡፡ ሃዘናችሁን ለመግለጽና ድርጊቱን ለማውገዝ አደባባይ ውጡ ነው ያልነው፡፡ ከዚያ በተረፈ መንግስትን መቃወም የተጀመረው ረቡዕ ብቻ አይደለም፤ በዚህ ጉዳይ ቀደም ብሎ ተቃውሞ ሲገጥመው ነበር፡፡
ማክሰኞ እለት ሰው ራሱ ወጥቶ ነበር የተቃወመው፡፡ ማክሰኞ በራሱ የወጣው ህዝብ እኮ ነው ረቡዕ እለት በድጋሚ ተቃውሞውን ያሰማው፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ተቃውሞ የተፈጠረው ማንም ስላደራጀው ሣይሆን መንግስት ከዚያ በፊት ይሠጣቸው በነበሩ መግለጫዎች የተነሳ ነው፡፡
“ኢትዮጵያዊነታቸውን እናጣራ፣ ህገወጥ ስደተኞች ናቸው” የሚሉት መግለጫዎች ሰው ያስቆጣል፡፡ የሰውን የቁጣ ስሜት የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አጀንዳ አድርጐ መግለጽ ተገቢ አይደለም
መንግስት ተቃውሞውን ሠማያዊ ፓርቲ ስለማቀነባበሩ ማስረጃ አለኝ እያለ ነው …
ይሄ አዲስ አይደለም፡፡ በኢህአዴግ ቤት የተለመደ ነው፡፡ የውሸት ማስረጃ ማቀነባበር የተለመደ ነው፡፡ የታሠሩት አምስት አባሎቻችን ሌሊት እንደሚመረመሩና በምርመራው ወቅትም ፓርቲውን እንዲለቁ ግፊት እንደሚደረግባቸው ሰምተናል፡፡ ለምሣሌ አመራራችን ወይንሸት ሞላ የተያዘችው ገና ሰልፉ ሣይጀመር ነው፡፡ እሷ ላይ ታዲያ ምን አደረገች ተብሎ ነው ማስረጃ የሚቀርብባት፡፡ በእለቱ ምን ያደረገችው ነገር አለ? ማስረጃ ብለው የሚያቀርቡት የውሸት ነገር በኢህአዴግ ቤት በሽበሽ ነው፡፡ የኛን ነገር ግን የሚፈርደው ታሪክ ብቻ ነው፡፡
በዚህ ሰሞን ደግሞ በክልክል ቦታዎች ላይ የቅስቀሳ ፖስተር ፓርቲው ለጥፏል በሚል ከምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ ደርሶታል፤ በእናንተ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው መረጃ ምንድነው?
ይሄ  ፓርቲው በጣም የተቸገረበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለምርጫ ቦርድም ረቡዕ እለት ከኛ ቁጥጥር ውጪ እንደሆነ በመግለጽ ደብዳቤ ፅፈናል፤ በግለሰብ ደረጃ ሣይሆን በተቀነባበረ ደረጃ ይሄን ነገር የሚያደርግ አካል እንዳለም ተረድተናል፡፡
ስለዚህ ይሄን ምርጫ ቦርድ ተገንዝቦ ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ክትትል እንዲያደርግልን ጠይቀናል፤ ነገር ግን ለደብዳቤው ትኩረት ሣይሰጡ መልሰው እኛኑ ነው እየከሰሱ ያሉት፡፡ በእኛ በኩል የተሠሩ ስህተቶችን እየፈለግን እያረምንም ነው፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ፣ በፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች አካባቢ ሣይታወቅ የተሠሩ ስህተቶች ሲያጋጥሙንም ፈጥነን እንዲነሣ እያደረግን ነው፡፡
ፖስተሮቻችን እየተቀደዱ ከመጣላቸውም በላይ በአንዳንድ ቦታዎች የተቀደዱት ከመሬት ተነስተው የተከለከሉ ቦታዎች ላይ ሆን ተብለው ተለጥፈው ተመልክተናል፡፡ እኛ በጭራሽ ያልተንቀሳቀስንባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለምሳሌ በመስጊድ ላይ ተለጥፎ አይተናል፡፡ በአካባቢው ግን የኛ የቅስቀሳ ቡድኖች ድርሽም አላሉም ነበር፡፡
እነዚህን ችግሮች እንግዲህ ለቦርዱ አመልክተናል፡፡ ቦርዱ እርምጃ የማይወስድ ከሆነ ህብረተሰቡ እንዲከታተልልን ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በእናንተ በኩል የደረሳችሁበት ምንድነው?
ሆን ብለው የፓርቲውን ስብዕና ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ ተረድተናል፡፡ ለዚህም ነው ለቦርዱ ከአቅማችን በላይ ሆኗል ብለን ደብዳቤ የፃፍነው፡፡ ቦርዱ ከኛ ጐን በመቆም ለህዝቡም ይሄን ነገር እንዲያሳውቅልን እንፈልጋለን፡፡
እስካሁን ያለው የቅስቀሳ ሂደታችሁ ምን ይመስላል?
በአራቱም የሃገሪቱ ጫፎች የቅስቀሳ ቡድን አሠማርተናል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች ተግዳሮት እየገጠመን ነው፡፡ ለምሣሌ በአዋሣ አትቀሰቅሱም በሚል ከፖሊስ ተቃውሞ ገጥሞን ነበር፤ ነገር ግን አባሎቻችን ጉዳዩን አለዝበው በማየታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ቅስቀሳ ማድረግ ተችሏል፡፡ ግን የምርጫ ኮሚቴ አባላችን ሳምሶን ግዛው “በሞባይል ፖሊስ ፎቶ አንስተሃል” በሚል ፍ/ቤት ቀርቦ የ7 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆበታል፡፡ እንግዲህ ፎቶ ማንሣትም ወንጀል ሆኖ፣ ዋስትናም አስከልክሎ ለእስር ዳርጓል ማለት ነው፡፡
ሌላው ምስራቅ ጐጃም እና ምዕራብ ጐጃም ላይ አስተባባሪዎቻችን ሣሙኤል አወቀ እና አዲሱ ጌታነህ ተደብድበውብናል፡፡ ለከፍተኛ ጉዳትም ተዳርገው ህክምና እየተከታተሉ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ የምርጫ ቅስቀሳ ፖስተሮች መቀደድ አንዱ ያስመረረን ጉዳይ ነው፡

     የቲያትር ትምህርቷን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመከታተል ከትውልድ አገሯ ባሌ፣ አጋርፋ አካባቢ የመጣችውን ለምለም ኃይለሚካኤል (ሚሚ)፣ በጥልቅ የሙዚቃ ፍቅሯ የተነሳ በ“ኢትዮጵያን አይድል” ለመወዳደር የትውልድ ቀዬዋን ጅማን ለቅቃ አዲስ አበባ የገባችው ጠሪፍ ካሣሁን (ሜላት) እንዲሁም እዚሁ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ራሔል ጌቱ (ለምለም)፣ እየሩሳሌም ቀለመወርቅ (ሣራ) እና ዘቢባ ግርማ (እሙዬን) ያገኘኋቸው እንደ ብርቅ ከሚታዩበት የአማራ ክልል ደብረታቦር ከተማ ውስጥ ነበር፡፡
“የኛ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው ፕሮጀክት፤ በኢመርጅ ሊደርስ ኮንሰልታንሲ ትሬይኒንግ፣ በማንጐ ፕሮዳክሽንና በዴሎይት ኮንሰልቲንግ በተቋቋመው ኮንሰርቲየም የሚተዳደር ሲሆን በእንግሊዝ መንግስት የልማት ድርጅት (ዲኤፍአይዲ) እና በናይክ ፋውንዴሽን ትብብር በገርል ሀብ ኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እነዚህ አምስት ወጣት ሴቶች የተወኑበትን አዲስ ፊልም ሰሞኑን በጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የደብረታቦር ከተማ አስመርቋል፡፡ ከአዲስ አበባ በ666 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች በ11 ሰዓት ላይ ለሚከናወነው የፊልም ምረቃ ፕሮግራም ገና በስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሥፍራውን አጨናንቀውት ነበር፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ ሣምንታዊውን የ “የኛ” የሬዲዮ ድራማና የአምስቱን ወጣቶች ሙዚቃ አጥብቀው የሚከታተሉና በእጅጉ የሚወዱ እንደሆኑ ሁኔታቸው ይመሰክራል፡፡ እስካሁን በሬዲዮ ድራማቸው የሚያውቋቸውና የሚያደንቋቸው ገፀባህሪያት፡- ሚሚ፣ እሙዬ፣ ለምለም፣ ሣራና ሜላት ፊልም ሲሰሩ ደሞ ለማየት እጅግ የጓጉ ይመስላሉ፡፡ ህፃን አዋቂው በሁለት ትላልቅ የፊልም ማሳያ ስክሪኖች ለእይታ የሚበቃውን ፊልም ለማየት አሰፍስፏል፡፡ የሁለትና የሶስት ሰዓታት የእግር ጉዞ አድርገው ከሥፍራው የደረሱ ወጣቶችም ነበሩ፣ እነዚህ አምስት ወጣቶች በአካባቢው ያተረፉትን እውቅናና በህብረተሰቡ ላይ የፈጠሩትን ስሜት ማወቅ እምብዛም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ይህም ፕሮጀክቱ የተቀረፀበትን ዓላማ ተግባራዊ እያደረገ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ በሥፍራው እየተዘዋወርኩ ያነጋገርኳቸው ወጣቶች፣ ታዳጊዎችና አዋቂዎች ስለየኛ፣ ስለድራማዎቹና ዘፈኖቻቸው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ትኩረት አድርጐ በሚንቀሳቀስባቸው የሴቶች ጥቃት፣ ያለዕድሜ ጋብቻና አስገድዶ መድፈር በስፋት በሚታይባቸው የአማራው ክልል አካባቢዎች ሴቶች ልጆችን ወደኋላ ከሚያስቀሩ አስተሳሰቦችና ተግባራት አላቆ ማህበራዊ ለውጥን ለማምጣት የተቀረፀ ሲሆን የሬዲዮ ፕሮግራሙ በአካባቢው እጅግ ተደማጭ መሆኑን ለማወቅ ችያለሁ፡፡
በአምስቱ ወጣት ሴቶች የተሠራው ፊልም ምረቃ ሲጠናቀቅ ወጣቶቹን ለማየት፣ ከተቻለም በእጅ ለመንካት የአካባቢው ወጣቶችና ህፃናት ያሳዩት የነበረው ሁኔታ እጅግ ስሜት የሚነካ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆኑ ወጣት ሴቶችም አምስቱ ወጣቶች ያረፉበት ሆቴል ድረስ በመሄድ ለወጣቶቹ ስሜታቸውን የገለፁበት ሁኔታ አስገራሚ ነው፡፡
ሰሞኑን በሊቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የሚሰማው  በእነዚህ አምስት ወጣቶች የተሰራው የስደት ዘፈን የፊልሙ አካል ሲሆን የተመልካቹን ስሜት  በእጅጉ የነካ ነበር፡፡
እሩቅ ማዶ እሩቅ አገር ሄዳለች
እታበባ ውብ አለሜ የት አለች
በእኔ እድሜ ነበር የተላከችው
ከማታውቀው አገር የተሸኘችው
እንኳን ጠረኗ ጠፍቶ ትንፋሿ ነው
የእሷ እጣ ታሰበ ለእኔ ለታናሿ፡፡
የሚል ስንኝ ያለው ዘፈኑ፤ የስደትን አስከፊነትና መራራነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ከፈልም ምረቃው በኋላ ከ5ቱ ወጣቶች ጋር በጅማሬያቸው፣ በህልሞቻቸው፣ በተስፋዎቻቸውና በገጠመኞቻቸው ዙሪያ ጥቂት አውግተን ነበር፡፡
    
      ለፕሮጀክቱ እንዴት ታጫችሁ?
ለፕሮጀክቱ የታጨነው የተሰጠውን ፈተና ተወዳድረንና አልፈን ነው፡፡ አምስታችን ከመመረጣችን በፊት ለውድድር የቀረብነው 69 የምንሆን ልጆች ነበርን፡፡ ውድድሩ በ3 ዙሮች የተሰጠ ሲሆን ይህንን ሁሉ አልፈን ነው የተመረጥነው፡፡
ወደ ሥራው ስትገቡ እንዲህ አይነት ዓላማ ያለው ሥራ እንደሆነ ታውቁ ነበር?
ሥራው ሲጀመር እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም መሆኑን አናውቅም ነበር፡፡ አንድ ተከታታይ የሆነ የሬዲዮ ድራማ እንደሚሰራ ነበር የምናውቀው፡፡ ሥራው የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነና ሙዚቃ ያለው ድራማ ያለው እንደሆነ የተነገረን ወደ ሥራው ከገባን በኋላ ነው፡፡ ከዛ ሥራውን በሚገባ ተገንዝበን እኛም እራሳችን የፕሮጀክቱ አባል ሆንን፡፡
የ“ኛን” ከተቀላቀልን በኋላ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ከምንሰራው ነገር ጋር በደንብ እንድንተዋወቅና እንድንዋደድ የተደረግንበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህም የምንሰራውን ሥራ በሚገባ እንድናውቀው፣ እርስ በርሳችንም በደንብ እንድንተዋወቅ ረድቶናል፡፡ የስድስት ወራት የልምምድ ጊዜያችን ሲጠናቀቅ ሁላችንም ቀደም ሲል ከነበረን አስተሳሰብ በእጅጉ ተለወጥን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የትወና፣ የሙዚቃና የድምፅ ስልጠናዎች በብቁ ባለሙያዎች ይሰጠን ነበር፡፡ በድራማው ላይ ወክለን የምንተውናቸውን ገፀ ባህሪያት በድንብ እንድናውቃቸውና እንድንለምዳቸው ለማድረግ ከገፀባህርይው ጋር ተመሳሳይነት ካላቸው ሰዎች ጋር እንድንውል ተደርገናል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ የቀየረንና ሥራው በድንብ ስሜት ሰጥቶን እንድንሰራው አድርጐናል፡፡
ስለሴቶች ጥቃትና ችግር የነበረን ግንዛቤ እንደአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ነበር፡፡ ስለጉዳዩ በየሚዲያው የሚነገረው አሰልቺ በሆነ መልኩ ስለነበር፣ ጆሮ ሰጥተን ለማዳመጥና ግንዛቤ ለመጨበጥ አልቻልንም ነበር፡፡ ነገር ግን “የኛ” ይህንን ቀየር አድርጎ ሳቢና አዝናኝ በሆነ መልኩ፣ የሰዎችን አስተሳሰብ ሊለወጥ የሚችል ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ሥራ በመግባቱና እኛም የዚህ ፕሮጀክት አባል በመሆናችን እጅግ ደስተኞች ነን፡፡
የፕሮግራሙን ዓላማ ምን ያህል ተረድተነዋል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ሴት ልጆችን ወደ ኋላ የሚያስቀሩ አስተሳሰብና ተግባራት በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች እነዚህን ተግባራት ለማስቀረት የሚችልና ሴቶችን በማስተማር ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ዓላማን ይዞ የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑን እናውቃለን፡፡ ማህበረሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት፣ ሴት ልጆችን ማበረታታት መደገፍና ማስተማር እንደሚገባው የማስተማርን ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ሴት ልጆች የሚገጥማቸውን እንቅፋት ስናስወግድና እነሱን ስናበረታታ የምንለውጠው የእነሱን ህይወት ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡንም ጭምር ነው የሚል ዓላማ ያለው መሆኑን እናውቃለን፡፡
ይህንን ዓላማ ለማሳካት ጥረታችሁ ምን ያህል ነው? የእናንተስ አመለካከት ምን ያህል ተለውጧል?
ወደ ሥራው ከመግባታችን በፊት ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያገኘነው ልምድና ትምህርት እኛን ሙሉ በሙሉ የቀየረንና ስራው ወደ ውስጣችን ገብቶ እንዲዋሃደን ያደረገ ነበር፡፡ የስልጠናና የልምምድ ጊዜው ሲጠናቀቅ ሁላችንም በደንብ ነው የነቃነው፡፡ ጉዳቱ በቅድሚያ ለእኛ ሊሰማን ይገባል፡፡ እኛ በደንብ ሲሰማን ነው መልዕክቱን በሚገባ ለማድረስ የምንችለው፡፡ በዚያ የስድስት ወር ጊዜ ከምንሰራቸው ገፀ ባህርያት ጋር እንድንዋሃድ መደረጉ ለዚህ በጣም ጠቅሞናል፡፡ እያንዳንዱን ነገር አውቀነው ውስጣችን ተዋህዶ ነው የምንሰራው፡፡ እያንዳንዷ ከአፋችን የምትወጣው ቃል ምን ስሜት ይዛ አንደምትወጣ መገመቱ ከባድ ነው፡፡ አንድ ሥራ ስንሰራ ስንት ሚሊዮን ሴቶችን መቀየር እንደሚችል እያሰብን ነው የምንሰራው፡፡ የተሸከምነው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነም ይገባናል፡፡
በግላችሁ ከዚህ ፕሮጀክት አገኘነው የምትሉት ዕድልና በህይወታችሁ ላይ ያመጣው ለውጥ  ምንድነው?
ፕሮጀክቱ በግል ለእያንዳንዳችን ትልቅ እድል ነው፡፡ መንገድ ጠራጊያችን ነው፡፡ አስተሳሰብና አመለካከታችንን በሚገርም ሁኔታ ለመለወጥ እንድንችል ያደረገንም ነው፡፡ “የኛ” ከትልቅ ግንድ የተነሳና በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት ዛፍ ነው፡፡ ሰፊ ቤተሰብ ያለው፣ ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ሥራውን በመከባበርና በፍቅር የሚሰራበት ቤት ነው፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት አባላት ጋር አብሮ መስራት በራሱ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ሲቀጥል ደግሞ በህይወታችን ህልም የሆኑብንና እንኳንስ አብረናቸው ልንሰራ ቀርቶ ለማየት እንጓጓላቸው ከነበሩ ታላላቅ ሙያተኞች ጋር ለመስራት መቻል የማይታመን እድል ነው፡፡ እንደ አይዳ አሸናፊ፣ ሰሎሜ ታደሰ፣ አስቴር አወቀ፣ አብርሃም ወልዴ፣ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ ዓለማየሁ ታደሰና ኃይሌ ሩትን ከመሳሰሉ ታላለቅ ሙያተኞች ጋር ለመስራት መታደል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች‘ኮ ህልሞቻችን ነበሩ፡፡ በተረፈ የሙዚቃና ትወና ችሎታችንን በማዳበር፣ ከሰዎች ጋር እንዴት ተግባብቶ መስራት እንደሚቻል ስለተማርንበት ቀላል የማይባል ጠቀሜታን ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የራሳችን አስተሳሰብ እንዲቀየርና ስሜቱ እንዲሰማን በማድረጉ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ በቃላት ሊገለፅ የማይችልና ከአዕምሮ በላይ የሆነ ዕድል ነው ያገኘነው፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ሊያቆመን ይችላል፡፡ ምንም አያቆመንም፡፡ ችግሩ የት ጋ እንዳለ፣ መንስኤና ምክንያቱ ምን እንደሆነና ችግሩን እንዴት መፍታት እንደምንችል እናውቃለ፡፡ እንዲህ ሙሉ እንድንሆን ያደረገን ደግሞ ይህ ፕሮጀክት ነው፡፡
እስከዛሬ በስፋት የምትታወቁት በሬዲዮ ድራማና በዘፈናችሁ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፊልም ሰርታችሁ አስመረቃችሁ፡፡ እንዴት ነው አዲሱ ሥራ አይከብድም?
ምንም አይከብድም፡፡ ፊልሙ ላይ የመጡት ያው የሬዲዮኖቹ ገፀባህሪያት ናቸው፡፡ ለእኛ አዲስ አይደሉም፡፡ ከሬዲዮ ድራማው ውስጥ ተቆርጦ የወጣ ታሪክ ነው ፊልም ሆኖ የተሰራው፡፡ እናም ብዙም አዲስ ነገር ሆኖ አላስቸገረንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሥራውን የሰራነው ከበቂ በላይ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ታላላቅ ባለሙያዎች ጋር በመሆኑ፣ ለእኛ ነገሮች እንዲቀሉና ሥራውን በአግባቡ እንድንሰራው አድርጎናል፡፡ ምንም የተቸገርንበት ነገር የለም፡፡
በሲኒማው ውስጥ የሚታየው ዘፈን ሰሞኑን በአገራችን ከተፈጠረው አስከፊ ሁኔታ ጋር ተገጣጥሟል፡፡ ይህ ለእናንተ ምን ስሜት ሰጣችሁ? ብዙ ሰዎች ዘፈኑ በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ላይ በተፈፀመው አስከፊና ዘግናኝ ድርጊት መነሻነት እንደተሰራ ያስባሉ፡፡ እንዴት ነበር ሙዚቃውን የሰራችሁት?
ሙዚቃው የተሰራው በድራማው (በየኛ ድራማ) 4ኛ ሲዝን ላይ እሙዬ የተባለችው ገፀ-ባህርይ ኑሮ ከአቅሟ በላይ ሆኖባት፣ የቤተሰቧን ህይወት ለመለወጥ ወደ አረብ አገር ስደት የምትሄድበት ታሪክ አለ፡፡ በእሱ ምክንያት ነው ሙዚቃውን የሰራነው፡፡
ግን ፊልሙ ውስጥ እንዲካተት ተስማማንበትና አስገባነው፡፡ ለፊልሙ የተሰራው ሌላ ሙዚቃ ነበር፤ እኛ ግን ይህንን መረጥነውና እነሱም ተስማምተውበት ነው የገባው፡፡ ዘፈኑ በእያንዳንዳችን ቤት ውስጥ ያለ ኑሯችን ነው፡፡ ሲከፋሽ ብድግ አድርገሽ የምትሰሚው አይነት ነው፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ዘፈኑን ስንዘፍነው የምር “ፊል” እናደርግ ነበር፡፡ ሙዚቃው ሀዘንን ብቻ አይደለም የሚናገረው፤ ተስፋን፣ ራዕይን ሁሉ የሚያወራ ነው፡፡ ዘፈኑ አሁን ከተፈጠረው ነገር ጋር ሲገጣጠም ወይም ታሪኩ ውስጥ ገብቶ ስክት ሲል እንደ አዲስ ነው ያለቀስነው፡፡ ግጥምጥሙ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ አገራችን አሁን የገጠማት ሀዘን ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ግጥምጥሙ በደስታ ቢሆንና ዘፈናችን ተደማጭነትን ቢያገኝ ደስ ይለን ነበር፡፡
በዚህ ሥራ ላይ ከተሰማራችሁ በኋላ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጓዝና ከፕሮግራሙ (ድራማችሁ) ተከታታዮች ጋር የመገኘትና ዕድሉን አግኝታችኋል፡፡ በየሥፍራው ስትዘዋወሩና ከአድማጮቻችሁ ስትገናኙ የገጠማችሁ ለየት ያለ ነገር ነበር? ስሜታቸውስ ምን ይመስላል?
በአማራ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች ተዘዋውረናል፡፡ በዚህ ቦታ ያገኘነውን የህዝብ አስተያየትን ለመናገር ቃላት ያጥረናል፡፡ ህብረተሰቡ ሲወድሽ የእውነቱን ነው የሚወድሽ፡፡ የጆሮ ጌጥ፣ ሻሽ፣ የእጅ አምባር እየገዙ ስጦታ ይሰጡናል፡፡ እንጅባራ ውስጥ የእኛን ዘፈን ግማሹን በአገውኛ ቀይረውና ሚክስ አድርገው መድረክ ላይ ሲያቀርቡት ማመን ነው ያቃተን፡፡ የአምስትና የሰባት ሰዓት የእግር መንገድ እየተጓዙ ያለንበት ድረስ ይመጡም ነበሩ፡፡ እስቲ ልንካሽ፣ እስቲ ልንካሽ እስቲ ልቀፍሽ… ሲሉ ስሜት ይነካሉ፡፡ ፍቅራቸው ከምር ነው፡፡ “አንቺን መስማት ከጀመርኩ በኋላ ተስፋ ማድረግ ጀምሬ ህይወቴ ተቀየረ” ሲሉን በጣም ደስ ይለናል፡፡ “መንገድ ላይ ነው አይደል የምታድሪው?” ብሎ ሻርፕ ገዝቶ የሰጠን አድማጭም አለ፡፡ በደብረማርቆስ፣ በአንኮበር፣ በቡሬ ያጋጠመን የተመልካች አቀባበልና ስሜት በቃላት ሊገለፅ የሚችል አይደለም፡፡
ክፍያችሁ ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምን ያህል ነው?
 ስለክፍያ የተጋነኑ ነገሮች ሊወሩ ይችላሉ፡፡ ግን እውነታው እንደማንኛውም ጥሩ ተከፋይ ኢትዮጵያዊ አርቲስት፣ በጥሩ የወር ደመወዝ ተቀጥረን መስራታችን ነው፡፡ እኛ የየኛ” ብራንዶች ነን፡፡ ከዚህ የተለየ ሥራ መስራትም አንችልም፡፡ የተመረጥነው ትልቅ ዓላማ ላለው ሥራ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ውጭ ያለው ሥራ እንዳያጓጓን የሚያደርግ ጥሩ ክፍያ እየተከፈለን እንሰራለን፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ምን የመስራት ዕቅድ አላችሁ?
ለማህበረሰቡ ሊጠቅሙ የሚችሉ ነገሮችን መስራት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ ማገዝ፣ ሴቶችን ማስተማርና መደገፍ እንደሚገባና ይህም ዓለማችንን በመቀየር ረገድ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ እናስተምራለን፡፡ አንድ እናት ሳትማር ፕሮፌሰርና ዶክተር ሊሆኑ የሚችሉ ልጆችን ማፍራት ከቻለች፣ ብትማርማ ምን ልትፈጥር እንደምትችል እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም አያቆመንም፡፡ አብረናቸው ከሰራናቸው ሰዎች የተማርነው የስራ ዲሲፒሊን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በደንብ ቀርፆናል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስንሰራ ቆይተን፣ ወጥተን የማይረባ ነገር ለመስራት አንችልም፡፡ ስለዚህም የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ አሁን ካለንበት አስተሳሰብና አመለካከት አይለውጠንም፡፡ የህብረተሰባችን አመለካከት ተለውጦ፣ ሴት ልጆች ተምረው የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችሉበትን ጊዜ ለማየት እጅግ እንናፍቃለን፡፡

Saturday, 02 May 2015 10:39

የፖለቲካ ጥግ

ምርጫ
በአፍሪካና በአውሮፓ
*አል ባሺር ተቃዋሚዎች በሌሉበት በዝረራ አሸነፉ
*የ71 ዓመት ባለጸጋ፤የ26 አመት ሥልጣን

    እምብዛም የማይገርማችሁን አንድ ወሬ ልንገራችሁ፡፡ ለ26 ዓመታት ሱዳንን የገዙት የ71 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ኡመር ሃሰን አልበሽር፤ሰሞኑን በሱዳን በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 94 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል ተባለ፡፡ ምርጫ የተባለው ወጉ እንዳይቀር ነው እንጂ አልበሽር ለብቻቸው ነው የተወዳደሩት፡፡ ዋና ዋና የአገሪቱ ተቃዋሚዎች ቀደም ብለው ነው ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉት፡፡  ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አልነበረም የሚሉት ተቃዋሚዎቹ፤ ሲቪል ማህበራትና ሚዲያው በመንግስት ታፍነው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በነገራችን ላይ አልበሽር በ1989 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ይኸው ለ26 ዓመታት ሱዳንን ሲገዙ ቆይተዋል፡፡ አልበሽር በዓለም አቀፉ የጦር ፍ/ቤት የዘር ማጥፋት እንዲፈጸም በማዘዝ ተከሰው በተገኙበት እንዲያዙ ውሳኔ ተላልፎባቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ዕድሜ ለአፍሪካ ህብረት! ያለመከሰስ ሬዚዳንታዊ መብት አላቸው በሚል የፍርድ ቤቱን አንቀበልም ብሏል፡፡ የሱዳንን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን የታዘበው ሲሆን አውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ፣እንግሊዝ፣ኖርዌይ ምርጫውን ተችተውታል፡፡ ከወዳጆቿ ጋር በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር በፖለቲካዊ ጉዳዮች “ጾመኛ” የሆነችው የቻይና ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ ለአልበሽር የእንኳን ደስ አልዎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡አሁንም ከምርጫ አልወጣንም፡፡ ቦታው ግን አውሮፓ ነው፡፡ ጊዜው ደግሞ የዛሬ 12 ዓመት፡፡ የኖርዌይ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ጄንስ ስቶልትንበርግ፤ራሳቸውን ለምርጫ ውድድር እያዘጋጁ ነበር- ለሦስተኛ ጊዜ አገራቸውን በጠ/ሚኒስትርነት ለመምራት፡፡ ከአገሪቱ ንጉስ ጋር መደበኛውን የአርብ ስብሰባ ከተሰበሰቡ በኋላ አንድ ለየት ያለ ነገር ልሞክር ብለው አሰቡ - ስቶልትንበርግ፡፡ (ማንም ሞክሮት የማያውቅ!) ምርጫ እየደረሰ ስለነበር ጠ/ሚኒስትሩ የድምጽ ሰጪውን ትክክለኛ የልብ ትርታ ለማወቅ ነበር የፈለጉት፡፡ ይሄን የት እንደሚያገኙት ደግሞ ያውቃሉ፡፡ ታክሲ ውስጥ! እናሳ? “እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቴ የሰዎችን አስተያየት መስማት ይጠቅመኛል፤ ሰዎች የልባቸውን የሚናገሩበት ቦታ ቢኖር ደግሞ ታክሲ ውስጥ ነው” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፤ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልልስ፡፡ ም ኖርዌይን ሁለት ጊዜ በጠ/ሚኒስትርነት ያገለገሉት ስቶልትንበርግ፤ የኦስሎ ታክሲ ነጂዎችን ዩኒፎርም ለበሱና የፀሃይ መነፅራቸውን ሰክተው ታክሲ መሾፈር ጀመሩ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ለአንድ ተሲያት በኋላ የከተማዋን ነዋሪዎች እያሳፈሩ አገልግሎት ሰጡ - እግረመንገዳቸውንም አስተያየት እያደመጡ፡፡ ከታክሲ ተሳፋሪዎቹ መካከል አንደኛዋ፤ “በዚህ በኩል በጣም ነው ስቶልትንበርግን የምትመስለው” ብላቸዋለች ጠ/ሚኒስትሩን ሹፌር፡፡ ሌላኛዋ ተሳፋሪ ደግሞ ደብዳቤ ልትልክላቸው ትፈልግ እንደነበር ጠቁማ እሳቸውን ታክሲ ውስጥ በማግኘቷ ዕድለኛነቷን ገልፃለች፡፡
ተሳፋሪዎች ከሹፌሩ ጋር የሚያደርጉት ጭውውት በአብዛኛው ወደ ፖለቲካ ያደላ ነበር፡፡ ሚ/ር ስቶልትንበርግ ከአንድ ተሳፋሪ ጋር በትምህርት ጉዳይ ላይ አውርተዋል፡፡ “ዋናው ነጥብ ጎበዝ ተማሪዎች የሚያልሙት ነገር መኖሩን ማረጋገጥና ለሚፍጨረጨሩት ደግሞ  ተጨማሪ እገዛ ማድረግ ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ለተሳፋሪው ነግረውታል፡፡ ሰውየው በኦስሎ ታዋቂ ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ኋላ መመልከቻ መስተዋት በማየት ብቻ ያወቋቸው ተሳፋሪዎች ነበሩ፡፡ ሰዎች እስካላወቋቸው ድረስ ግን ማንነታቸውን አይገልጹም ነበር፡፡ እናም… የመራጩን ህዝባቸውን እውነተኛ ስሜት … ሃሳብ … እይታ የቻሉትን ያህል ተገነዘቡ፡፡ በእርግጥ ጠ/ሚኒስትሩ በምርጫው አላሸነፉም፡፡ ቁምነገሩ ግን እሱ አይደለም፡፡ ለሚመሩት ህዝብ ያላቸው   አመለካከት ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች የመራጩን ህዝብ እውነተኛ ስሜት ለመረዳት --- ለማወቅ የሚጨነቁ ይመስላችኋል? (አረ ሲያልፍም አይነካቸው!) እነሱም ግን ምርጫ ሲደርስ አንድ ለየት ያለ ነገር ያደርጋሉ፡፡ (ታክሲ ባይነዱም!) ህገ
መንግስት በመደለዝ የስልጣን ዕድሜያቸውን ያራዝማሉ፡፡ (ሰው እንደየተሰጥኦው ነው!) የአፍሪካ መሪዎች ከማንም በላይ ሥልጣንን ቢወዷትም በቀጥታ ከህዝብ አይደለም የሚወስዷት፡፡ ሲመቻቸው ይነጥቃሉ፡፡ ያጭበረብራሉ፡፡ ራሳቸው ያወጡትን ህግና ህገመንግስት እስከመደለዝ ሁሉ ይደርሳሉ፡፡ የታክሲ ሹፌር ሆኖ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ?--- የሚለውን ግን እርሱት!በነገራችን ላይ በቡሩንዲ ከወር በኋላ በሰኔ አጋማሽ ላይ ሊካሄድ በታሰበው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ሊቀሰቀስ ይችላል ብለው ያሰቡትን ብጥብጥ በመስጋት፣ 17 ሺ ቡሩንዲያውያን ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ወደ ጎረቤት አገራት (ሩዋንዳና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) እንደተሰደዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቁሟል፡፡ (በአፍሪካ ምርጫ ያሰድዳል!) የፈሩት አልቀረም፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፒሬ ንኩሪኒዛ ፤ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለሶስተኛ ዙር ሊወዳደሩ
መዘጋጀታቸውን ተከትሎ ባለፈው እሁድ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን ፖሊስ ሰልፉ ህገወጥ ነው (ህገወጥ እኮ ፕሬዚዳንቱ ናቸው!) በሚል ከሰልፈኛ ጋር በፈጠረው ግጭት፣ ሁለት የተቃዋሚ ሰልፈኞችን የገደለ ሲሆን አራት እንደቆሰሉ የቡሩንዲ ቀይ መስቀል ማህበር ቃል አቀባይ አሌክሲስ ማኒራኪዛ ለሮይተርስ ተናግረዋል፡
በነገራችን ላይ የአፍሪካ መሪዎችና ምዕራባውያን ረብሻና ጠብ ይፈጠራል በሚል የቡሩንዲው ሬዚዳንት በምርጫው እንዳይወዳደሩ አሳስበዋቸው ነበር (“ሚስትህ ወለደች ወይ ቢሉት ማንን ወንድ ብላ” አለ አበሻ!) አሜሪካና አውሮፓም የሳቸውን ወደ ምርጫ መግባት ተከትሎ ብጥብጥ ቢነሳ እርምጃ እንደሚወስዱ ጠቁመዋል (የሰማቸው የለም እንጂ!) አያችሁልኝ አይደል … የአፍሪካን ነገር! አንድ አምባገነን በስልጣን እንዲቀጥል ሺዎች የሚገደሉባት ከንቱ  አህጉር ናት፡፡ እኔ የምለው …. ይሄ አፍሪካ ህብረት የሚባል ድርጅት ውስጡ ሰው የለም እንዴ?! (የቻይና ህንፃ ብቻ እኮ ነው የሚመስለው!)  

   ከዕለታት አንድ ቀን አያ ጅቦ አራት ልጆቹን፤ ማለትም - መዝሩጥን፣ ማንሾሊላን፣ ድብልብልን እና ጣፊጦን ይዞ በለሊት መንገድ ይሄዳል፡፡ እየተጓዙ ሳለ ድንገት አንዲት ከቤቷ የወጣች አህያ ያገኛሉ፡፡
ይሄኔ አባት ጅብ፤
“ልጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ በጣም አርጅቻለሁና ይቺን አህያ እኔ ነኝ የምበላት! እናንተ ራቅ ራቅ ብላችሁ ትጠብቁኛላችሁ” አለ፡፡
ይሄኔ መዝሩጥ፤
“አባዬ ኧረ አንድ ብልት እንኳን አጋራን?” ይለዋል፡፡
“አይሆንም! ምንም አላቀምስህም” ይላል ጅቦ፡፡
ይሄኔ ማንሾላ ይነሳና፤
“ለእኔስ አባቴ?” ይላል፡፡ አያ ጅቦም፤ “እንካ ጆሮዋን ብላው” ይለዋል፡፡
ቀጥሎ ድብልብል ይመጣና፤
“ለእኔስ አባቴ?” ይለዋል፡፡
“አንተ ሽሆና ይደርስሃል” ይላል አያ ጅቦ፡፡
ቀጠለና ጣፊጦ ጠየቀ፡-
“አባዬ የእኔንስ ነገር ምን አሰብክ?” አለ፡፡
“አንተ ቆዳዋን ካገኘህ ያጠግብሃል” አለ፡፡
ልጆቹ አባታቸው አህያዋን ዘርጥጦ ጥሎ ሲበላ ዘወር አሉ፡፡
አያ ጅቦ ዋና ዋናውን የአህያዋን ብልት እንደበላ፤ ድንገት የአህያዋ ጌታ ሲሮጥ መጣ፡፡
አያ ጅቦ ፈርጥጦ መውጫ የሌለው የጫካ ጥግ ውስጥ ገብቶ ይሰረነቅና እየጮኸ ልጆቹን ይጠራል፡፡ ልጆቹ ቀርበው ወደጫካው ይጠጉና፤
“አባታችን ምነው ትጮሃለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
አያ ጅቦም፤
“አድነን ልጄ መዝሩጥ?” ይላል፡-
መዝሩጥም፤
“አባቴ ምን ሰጥተኸኛል እንደበላህ እሩጥ!” ይለዋል፡፡
“አድነኝ ልጄ ማንሾለላ!” ይላል አያ ጅቦ፡፡
“ምን ሰጥተኸኛል ካንድ ጆሮ ሌላ!?” ይለዋል ማንሾለላ፡፡
“አድነኝ ልጄ ድብልብል?”
“አይ አባት! ሸሆና ለማን ውለታ ይሆናል?!”
ቀጥሎ አያ ጅቦ ጣፊጦን ጠየቀ፤
“አድነኝ ልጄ ጣፊጦ?!”
“ማን የጎረሰውን ማን አላምጦ?” አለ ጣፊጦ፡፡
መላወሻም አጋዥም ያጣው አያ ጅቦ፤ እዚያው ተወጋና ሞተ፡፡
*           *          *
ዛሬ  እኔ ነኝ ዋናው ጅብ ማለት አይሠራም! ቀድመው ያላሰቡበት ግለኝነትና ሆዳምነት ምን ላይ እንደሚጥለን አለማሰብ የማታ ማታ ያላጋዥ ያለመጠጊያ ያስቀራል፡፡ ከካፒታሊዝም ምርኮኛነታችን ጀምሮ ስግብግብነት፣ በዝባዥነት፣ ዘረፋና ግፍ ይበረክታል፡፡ ያላየነው የገንዘብ ትርፍ ማህበራዊ መልካችንን ያዥጎረጉረዋል፡፡ እንኳን ሊያተርፈን ራሳችንን ያጎልብናል፡፡ “አድነኝ ልጄ እገሌ?” ቢባል ምላሽ አይኖረውም፡፡ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ መግባባትና መስማማት ያለብን ሰዓት ነው፡፡ የሃይማኖት መግባባታችን፣ ስለአንድነት መግባባታችን፣ ስለድንበር ጉዳይ መግባባታችን፤ ስለዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች መግባባታችን፤ ከሁሉም በላይ ስለአይኤስአይኤስ መግባባታችን… ብርቱ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ የሳሱ ድንበሮችና መንግስት አልባ አገራት ወደ አሰቃቂ እልቂት ሊያመሩ እንደሚችሉ፤ ሶማሊያም፣ የመንም፣ ሊቢያም፣ ኢራቅም ለመነሻ አስረጅነት የቆሙ ተጨባጭ ምሳሌዎቻችን ናቸው! ነገ በየአገሩ ይሄው ሁኔታ ላለመከሰቱ ምንም አስተማማኝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህልውና የለም፡፡ በትናንሽ የፖለቲካ አታካራ ተሞልተን፣ ትናንሽ ሙሾ በማውረድ ጊዜያችንን ከምናባክን፣ ትልቁን የዓለም አቀፍም አገር አቀፍም ስዕል (The Bigger Picture) የምናይበትን ዐይናችንን እንክፈት፡፡ ምዕራባውያን፤ ባህል፣ ሃይማኖት እና ጥናታዊ ታሪክ ያላቸውን አገሮች ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሶርያ፣ የመን፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና … አሁን ደግሞ የእኛው አገር ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩት ያለነገር አይደለም፡፡ ግሎባላይዜሽንን ይነቅፋሉ የሚለው አጀንዳ የዋዛ አይደለም፡፡ ባህል የሌላቸው ባለባህሎቹን እየገደሉ ነው፡፡ የቅርቦቹ ሶማሊያና ሊቢያ በመንግሥት-አልባ ሁኔታ ውስጥ መሆን፣ በማንም ይሁን በማን ለመጠቃታቸው ሰፊ በር ከፍቷል፡፡
ወደ ሊቢያ በጣሊያን አዛዥነት ስለዘመተው ያለዕዳው ዘማች የኤርትራ ወጣት (ደራሲው አበሻ ይለዋል) እንዲህ የሚል ሀሳብ ይገኝበታል፡፡ ስለሊቢያ በረሀ ነው፡-
“የመሸበር ስሜት፣ ሐዘን፣ ተስፋ ቢስነት እና ፀፀት ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ የበረሀው ስዕል አሰቃቂ ነው፡፡ አንዲት ዛፍ አትታይም፡፡ አንዲትም የሳር አገዳ የለችም፡፡ የውሃ ነገርማ ባይነሳ ይሻለዋል፡፡ ወደየትም አቅጣጫ መንቀሳቀስ አይታሰብም፡፡ ግራ፣ ቀኝ፣ ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ፣ ወደየትም መሄድ አይቻልም ምክንያቱም የትም ይሁን የት ህይወት በአሸዋ ተከባ ነው የምትገኘው፡፡ በየትም ቢዞሩ ጠጠር ኮረት ድንጋይ፣ እና የአቧራ ክምር!
ያ በረሀ እንደባህር ሰፊ፣ ግን በጥላቻ የተሞላ!  ባህሩ ውስጥ ቢያንስ ዓሣ ማየትና የማዕበል ድምፅ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ እዚህ ሊቢያ በረሃ ግን አንዲትም ወፍ አትዘምርም፡፡ አትበርምም፡፡ ያ ክፍቱ ደመና አልባ ሰማይ የጋለ ምድጃ ነው፡፡ በዚያ ጠራራ ንደድ ውስጥ ያለ ሰው፣ ያ መሬት፣ የህይወት ይሁን የሞት መለየት ይሳነዋል፡፡ ይሄን መሬት ከአረንጓዴው፣ ከንፋሳማው እና ከለሙ የኢትዮጵያ ምድር ጋር ማነፃፀር ከንቱ ድካም ነው! የሲዖልና የገነት ነው ልዩነቱ!?”
ስለአበሻ የጦርነት ብቃት የሚገርም ትንተናም አለው - በሊቢያ በረሐ፡- አበሻ፣ ጣሊያንና አረብ የውጊያ መንፈሳቸው ምን ይመስላል?
“ለአበሻ፣ ጦርነት ውጤቱ ምንም ዋጋ ያስከፍል ወደፊት መግፋት ነው፡፡ (ግፋ በለው እንደማለት) ለጣሊያኖች፤ አዛዥህ እንዳለህ ተዋጋ ነው፡፡ ጠላት ግንባር ለግንባር ቢፋጠጥህም ካልታዘዝክ አትተኩስም፡፡ ካልታዘዝክ ብትታረድም ፀጥ በል ነው!
ለዐረቦች ወደ ጠላትህ ፈጥነህ ሩጥ፡፡ ሁኔታው የሚያዋጣ ከመሰለህ ነብስህን ለማዳን ፈርጥጥ ነው፡፡ የየተዋጊውን ባህሪ ለእኔ ብሎ መስማት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ጊዜው አስጊ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችንን በቅጡ እናስተውል፡፡ ሩቅ የሚመስሉንን ዕጣ ፈንታ ስናይ፣ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት!” እንበል፡፡ “ጎረቤትክን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” ማለት የአባት ነው!! 

Saturday, 02 May 2015 10:32

ጣት መቀሰር እስከመቼ?!

(ቆም ብሎ ማሰቡ ለራስም ለሀገርም ይጠቅማል!)

   “ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፤ በሀገሪቱ ውስጥ ስራ አጥነት ተንሰራፍቶአል፤ መብራት፣ ውሃና ኔትወርክ የለም፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በትራንስፖርት ችግር እየተንገላቱ ነው፤ በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፤ የግሉ ፕሬስ በነጻነት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ ለመጥፋት ተቃርቦአል፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚፈለገው መልኩ በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፤ በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ መልኩ እየተሰደዱ ነው፡፡…” ሌሎችም ለቁጥር የሚታክቱ ምሬቶችና አቤቱታዎች ከየአቅጣጫው በየጊዜው ይሰማሉ፡፡ በዚችው በእኛዋ ሀገር፡፡
ከእነዚህ አቤቱታዎች አንዳንዶቹ መንግስትም ጭምር የሚቀበላቸው (የሚያምናቸው) ቢሆኑም እስካሁንም ድረስ ችግሮቹ መቀረፍ አልቻሉም፡፡ ለምን?! ምክንያቱ የሚመስለኝ የችግሮቹ መንስኤዎች ላይ አትኩሮ ችግሮቹን ለመቅረፍ ከመስራት ይልቅ ሰበብ መስጠት ወይም ጥፋቱን ተሸካሚ ፈልጎ በማሸከም ላይ ስለሚታትር ይመስለኛል፡፡ ሐጢአቱን ለሌሎች አሸክሞ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ፡፡
እስቲ ጥቂት ወደ ኋላ መለስ እንበልና ከላይ ለተነሱትና ለሌሎች አንዳንድ ችግሮች መንግስት ተጠያቂ ያደረገው እነማንን እንደሆነ እናስታውስ፡፡… በአጭሩ ለየትኛውም ችግር ራሱን ተጠያቂ አላደረገም ማለት ይቀላል፡፡ በተደጋጋሚ ችግሮቹን ከጉዳዮቹ ጋር እጅግ በጣም ጥቂት ንክኪ ያላቸው አካላት ላይ ጭኖ ራሱን “ነጻ አድርጎአል፡፡” አሁንም እየሆነ ያለው እንደዛ ይመስለኛል፡፡ ጊዜ ያለወጠው አዙሪት!
ዛሬም እንደ ቀድሞው መንግስትና ሚዲያዎቹ በደቡብ አፍሪካ፣ በሊቢያ በረሀና በሜዴትራንያን ባህር ዳርቻ ስደተኛ ወገኖቻችን በግፍ መገደላቸውን ተከትሎ ለችግሩና ለጥፋቱ ብቸኛ ተጠያቂ “ህገ ወጥ ደላሎች” (ቃሉ ራሱ የተጣራ ፍቺን ይሻል) ናቸው እያሉን ነው፡፡ ዘይገርም ነው! መቼ ይሆን ጣታችንን ሌሎች ላይ ብቻ መቀሰር የምናቆው?! መቼስ ነው ማድበስበሱን ትተን ከእውነታው ጋር መጋፈጥ የምንችለው?! ያሰኛል፡፡
ከምንጊዜውም በበለጠ መልኩ በአሁኑ ወቅት በርካታ ወገኖቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ በሚዳርግ መንገድ ከሀገራቸው ተሰደዋል፤ እየተሰደዱም ነው፡፡ በመንገዳቸውም ሆነ ተሰደው በሚኖሩባቸው ሀገሮችም ህይታቸውን እስከሚያጡ ድረስ በርካታ እንግልቶች እየደረሱባቸው ነው፡፡ ይሄ ሀቅ ነው፡፡ የአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የሠርክ ወሬ የሆነና እኛም የምንስማማበት ሀቅ፡፡ ታዲያ ጉዳዩ አቅጣጫውን መሳት የጀመረውና አለመተማመኑ የጎላው ዜጎቻችን የሚሰደዱበትን ምክንያት መጠየቅ ሲጀመር ነው፡፡ ያኔ ጉዳዩ ከመፍትሔው መነጠል ጀመረ፡፡ የሚመለከተውም ለዜጎቹ ኃላፊነት እንደሚሰማው አካል የችግሩን ምክንያቶች አምኖና ተቀብሎ በመጋፈጥ ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ ከመሞከር ይልቅ ችግሩ የሚሳበብበትን አካል መፈለግ ያዘ፡፡ የዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ እከሌ ነው ለማለት፡፡ ያስገርማል፤ ያሳዝናልም!
እርግጥ ነው፡፡ ለአንድ ክስተት መፈጠር በርካታ ምክንቶች ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ምክንያቶች ምን ያህል ድርሻ አላቸው? የምክንያቶቹ መነሻስ (ሰበብ) ምንድን ነው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ እውነታውን እስከፈለግን ድረስ ይህ ወደ እርግጡ ድምዳሜ የሚያደርሰን ጤናማ መንገድ ይመስለኛል፡፡…
እርግጥ ነው ሰዎች ከሀገራቸው እንዲሰደዱ “ህገ ወጥ ደላሎች” የሚያደርጉት የራሱ አስተዋጽኦ አለ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሌሎች ጭፍጫፊ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መልካም፡፡… ቀጥለን ግን መጠየቅ ያለብን እነዚህ ምክንያቶች ለችግሩ የሚያዋጡት ድርሻ ምን ያህል ነው? የሚለውን ነው፡፡ መልሱ ብዙም ጥናትን የሚፈልግ አይደለም፡፡ ብዙም ሳንደክም ልንመልሰው እንችላለን፡፡ በመንግስት እየተጠቀሱ ያሉት ምክንያቶች በምንም መልኩ ለዜጎች መሰደድ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀሱ ቀርቶ ስሌት ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ ድርሻቸው ጥቂት ነውና፡፡
እውነቱን እንናገር ከተባለ፣ ወገኖቻችን እንዲሰደዱ ግፊት የሆኗቸው ሌሎች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገቡ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህን ምክንያቶች ለማወቅ የሚፈልግ አካል ካለ ተጓዦቹንና ከስደት ተመላሾቹን ቀረብ ብሎ ይጠይቃቸው፡፡ ሀገራቸውንና ወገኖቻቸውን ተለይተውና ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱባቸውን ምክንያቶች ይነግሩታል፡፡…  ምክንያታቸው የኢኮኖሚ ችግር ነው፡፡ የእንጀራ ጥያቄ! ደግሞም ይህንን ማወቅ ውስብስብና የበዛ ምርምርን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሽሽቱንና ማድበስበሱን ስለፈለግነው እንጂ ለማንም ያልተደበቀ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡
አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን ጉዳዩን ለመመርመር እንሞክር፡፡ እስቲ በመንግስትና በሚዲያ ተቋማቱ “ፍረጃ” ተስማምተን፣ ለጥፋቱ ተጠያቂዎች “ህገ ወጥ ደላሎች ናቸው” ብለን እንነሳ፡፡ የምንደርስበት ውጤት (ብዙም ስሌት ውስጥ ሊገቡ የማይገቡ ሌሎች ጭፍጫፊ ሰበቦች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ) አሁንም የችግሩ ዋና ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንዴት?
ሲጀመር ዜጎች የ“ህገ ወጥ ደላሎቹ”ን ስብከት ሰምተውና አምነው ከሆነ የሚሰደዱት፣ ደላሎቹ ጋር የወሰዳቸውም ሆነ ደላሎቹን እንዲያምኑ ያደረጋቸው ያለባቸው የኢኮኖሚ  ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ችግር ከሌለባቸውና የዳቦ ጥያቄያቸውን መመለስ የሚችሉ ከሆነማ ለምን ከደላሎቹ ጋር ይገናኛሉ? ለምንስ ደላሎቹ የሚሏቸውን ያምናሉ? መቼስ “መረጃው ስለሌላቸው ነው” የሚል የዋህ እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡
ሀገር አቋርጠው ሲጓዙም ሆነ ደርሰው በሚኖሩባቸው ሀገሮች ህይወትን እስከማጣት የሚደርስ እንግልት ሊያገኛቸው እንደሚችል እኮ “ህገ ወጥ” ደላሎቹ “ታገኛላችሁ” ብለው ከሚሰብኳቸው በበለጠ መንግስትም ሆነ በርካታ መገናኛ ብዙሀን ያለማቋረጥ ነግረዋቸዋል፤ እየነገሩአቸውም ነው፡፡ ግን ከመሄድ አላመነቱም፡፡ ለምን? ማመን ስለማንፈለግ እንጂ መልሱ አሻሚ አይደለም፡፡ ይህንን የሚያጠነክር ሌላም ነጥብ እዚህ ጋ ማንሳት እንችላለን፡፡ በተሰደዱበት ሀገር ሲደርስባቸው ከነበረው እንግልት፣ ከሞት መንጋጋ አምልጠው… የመጡት ወገኖቻችንም ውለው ሳያድሩ አሁንም ተመልሰው ከሞት ወዳመለጡባቸው ሀገሮች እየሄዱ ነው፡፡ መቼም እጅግ የዋህ ካልሆንን በቀር “እነሱም በደላሎቹ ተታለው ነው” አንልም፡፡ አይተውታልና፡፡ ይኸው ነው፤ ማመን ቢገደንም ቅሉ በዚህም አልን በዚያ ዜጎቻችን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ከሚሰደዱባቸው ምክንያቶች ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የኢኮኖሚ ችግር፣ የእንጀራ ጥያቄ… ነው፡፡ ይህንን ማመን ግን ተጠያቂ ስለሚያደርገን ሳይሆን አይቀርም፤ ሐጢአቱን ሁሉ ለደላሎች ሰጥተን ለመንጻት የምንሞክረው፡፡
ደግሞም እኮ (ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ በቀር) በደሉን የሚሸከም አካል ፈልገን እሱ ላይ ጣት መቀሰር በምንም ስሌት መፍትሔ አይደለም፡፡ መፍትሔው ስህተትንና ድክመትን አምኖ መቀበልና ችግሩን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው፡፡ በዚህም የችግሮቹ ምክንያቶች ላይ በማተኮር መስራት ነው ለሀገርም ለራስም የሚጠቅመው፡፡ ችግሩን ሌሎች ላይ ስላንከባለልንና ጣታችንን ስለቀሰርን ወይም ጉዳዩ ሌላ አቅጣጫና ትርጉም እንዲይዝ ስለደከምን “ነጻ” የምንሆን ይመስለናል እንጂ አንሆንም፡፡ ይህንንም በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ እያየነውም ነው፡፡
የትናንት ቀመር ለትናንት እንጂ ለዛሬ አይሰምርም፡፡ ይህ ዘመን ሌላ ነው፡፡ የህዝቡ አስተሳሰብም ሆነ እውቀት የቀድሞው አይደለም፡፡ ተለውጦአል፤ አድጓልም”፡፡ ያልነውንና የሰጠነውን ብቻ የሚያምንበትና የሚቀበልበት ዘመን አልፎአል፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ምናልባትም ከምንነግረው በላይ ያውቃል፡፡ ስለ ሁሉም መረጃ አለው፡፡ ለቴክኖሎጂው ምስጋና ይግባውና ትውልዱ መረጃን በእጁና በኪሱ ይዞ ነው የሚዞረው፡፡ ለዚህም ነው በአዎንታም ይሁን በአሉታ ለየክስተቱ ምላሽ ሲሰጥ የሚስተዋለው፡፡ ይህንን ማወቅና መገንዘብ፣ ተገንዝቦም ራስን ከትውልድና ከሁኔታዎች ጋር ማዘመን ከአንድ መንግስት የሚጠበቅ ብልህነት ነው፡፡ ቆም ብሎ ማሰቡ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግስት… ይጠቅማል፡፡
በተለይ አሁን ከምንጊዜውም በላይ ሀገራችንና ዜጎቿ በየአቅጣጫው እየተፈተኑ ያሉበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሀገሩንና ህዝቦቿን እወዳለሁ የሚል ዜጋም ሆነ መንግስት ዛሬ ትናንት እንዳልሆነ ሊያስተውል፣ ቆም ብሎም ሊያስብ ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ለሁሉም ይጠቅማልና፡፡… በተለይ መንግስት ከተለመደው አዙሪት መውጣት፣ ኃላፊነት መውሰድና ከችግሮች ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ ይኖርበታል፡፡ እስከፈለገ ድረስ ይህንን ማድረግ አያቅትም፡፡ ሥራን መስራት፣ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ሁሌም ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግና ጣትን መቀሰር ራስን ለትዝብት ከመዳረግ ባለፈ አንዳች ትርፍ የለውም፡፡ ደጃፍን እንጂ ወንዝ አያሻግርም፡፡  
አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር እውነቱን አምኖና ተጋፍጦ ዘላቂ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ጣት የምንቀስርበትን መፈለግ ለጊዜው የሚበጅ ቢመስለንም የነገ እጥፍ ኪሳራ ነው፡፡ ደግሞም እኮ ድክመትን መቀበል ጀግንነት እንጂ ሽንፈትና ክስረት አይደለም፡፡ አያስከፋምም፡፡ የሚያስከፋውስ ችግሮችን ሌሎች ላይ መጣል፣ ለማድበስበስ መሞከርና ችግሩን ላልተገባ የፖለቲካ ትርፍ ለማዋል መድከም ነው፡፡
ደግሞም እንደ መንግስት በዚህ ሂደት ውስጥ የምናደርጋት እያንዳንዷ ክንውን፣ የዛሬ አንድምታዋንና ነገ የምታፈራውን ፍሬ መገመት ይገባል፡፡ እስከ ዛሬ የዘራነው ምን እንዳፈራልን እያየን ነው፡፡ ዛሬ የምንዘራውም ነገ ልጆቻችንን ሊያጠፋ እንደሚችል እንገንዘብ፡፡ ፊታችን ስለቆመው ዛሬ ብቻ ሳይሆን ስለነገም ቆም ብለን እናስብ፡፡ ደግሞም የምር ከፈለግን አያቅተንም፡፡ በፍጹም!
መልካም ሰንበት!

የሰሞኑ አሳዛኝ ክስተት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርግ ይችላል፤ ነገር ግን በሃገሪቱ ተመዘገበ በተባለው ተአምራዊ ኢኮኖሚ ላይ ግን ጥርጣሬን ያጭራል?”    ረዳት ፕሮፌሰር ሃሰን ሁሴን

በአንድ ሳምንት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተደራራቢ የሞት መርዶን አስተናግደዋል፡፡ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም በሊቢያ የሚንቀሳቀሰው የእስላማዊ መንግስት አቀንቃኙ አይኤስ፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን መግደሉን አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በአይኤስ እጅ የወደቁት ደግሞ የተሻለ ህይወት ፍለጋ በሊቢያ አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ባደረጉት ጥረት መሃል ነው፡፡
ይህ አስከፊ አጋጣሚ የተፈጠረውም በዚያው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ በስደት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ባለበትና 3 ኢትዮጵያውያን የመገደላቸው መርዶ በተነገረበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ ለኢትዮጵያውያን መራር ያደርገዋል፡፡
በሌላ በኩል አልጀዚራም ሆነ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ በየመን እንዲሁ በተመሳሳይ ስደት ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጦርነት መሃል ለሰቆቃ ተዳርገዋል፡፡ በዚያው አስከፊ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው ሮቤ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ወላጆች፣ ሚያዚያ 11 ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ከ900 በላይ ስደተኞች ጭና ስትገጓዝ የነበረችው ጀልባ መስጠሟን ሰምተው መሪር ሃዘንን አስተናግደዋል፡፡
በአንድ ሳምንት ውስጥ የተፈጠሩት እነዚህ ሁሉ አሳዛኝ ክስተቶች፣ለጊዜው ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረጉ ቢመስልም በዚያው ልክ ኢትዮጵያውያኑን ከአስፈሪ ሞት ጋር ለመጋፈጥ ለምን ስደትን የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደርጋሉ የሚለው በሁሉም ህሊና ውስጥ የሚመላለስ ጥያቄ ሆኗል፡፡
ቀውሱ የተፈጠረው የኤስያ ነብሮች የተባሉ ሃገራት በ1970ዎቹ ያስመዘገቡት አይነት ተአምራዊ ኢኮኖሚ ሃገሪቱ አስመዝግለች በሚባልበትና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ መሆኑ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊነትን እየተላበሰች ነው በተባለባት ሀገር መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ በተደጋጋሚም ሃገሪቱ ከአፍሪካ ሃገሮች ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ነው ከተባለ ለምንድነው በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቿና ሴት ልጆቿ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሃገራቸውን ጥለው የሚሰደዱት? መቼስ ነው ይሄ ፍልሰት የሚያበቃው?
እንደሚታወቀው አስደንጋጩ ዜና ከተሰማ በኋላ የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ “ክስተቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ላሰቡ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ነው” ብለዋል፤ ግን የሃገሪቱ ወጣቶች እንደ ማስጠንቀቂያ አላዩትም፡፡ በአገራቸው የተሻለ ህይወት የመኖር ህልም ያላቸው አይመስልም፡፡ በሃገሪቱ ከፍተኛ ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መበራከት፣የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እድል----ከፖለቲካ ጋር መያያዙና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የፓርቲ አባልነት መስፈርት ማስፈለጉ፣ ከፍልሰቱ ጀርባ እንዳለ በርካታ እማኞች ይገልጻሉ፡፡
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው አለማቀፉ የእድገት ማዕከል፤ በ2012 እ.ኤ.አ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በከተማ የሥራ አጥነቱ በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣
ማስማ በገጠርም ወጣቱ መሬት አልባ መሆኑን ጠቃሚ የስራ እድሎ እንደሌሉት ጠቁሟል፡፡ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፤በሃገሪቱ በሚታይ ደረጃ የትምህርት አቅርቦት ቢጨምርም ተምሮ ለሚወጣው ዜጋ በተማረበት የሙያ መስክ በቂ የስራ እድል አለመኖሩን አስቀምጧል፡፡
በአይኤስ ከተገደሉት መካከልም በዲግሪ የተመረቁ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ከ100ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ባስወጣችበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱም የአይኤስ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እንዲሁ በሃገሪቱ ካሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በጥሩ ደመወዝ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ወጣትም አለበት፡፡
ይሄ ሁሉ የሚያመለክተን ብዙ የሚወራለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ የሃገሪቱን ወጣትና የህዝብ ቁጥር ምጣኔን ለማስተናገድ አለመብቃቱን ነው፡፡ የሀገሪቱን ወጣቶች ለስደት የሚዳርገው የኢኮኖሚ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ወጣቶች አማራጭ የመረጃ ምንጭ መከልከላቸውና የነፃነት ስሜት እንዳይሰማቸው መደረጉ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በየአገሩ የሚገኝ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂ ነው፡፡ በየመን 75ሺህ ያህል የተመዘገቡ ስደተኞች መኖራቸውን የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን በኬንያ ከ20 ሺህ በላይ፣ በግብፅና በሶማሊያ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በስደተኝነት ተመዝግበዋል፡፡
አገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች በግንቦት ወር ምርጫ ይደረጋል፡፡ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄድ ምርጫ ቢሆንም ላለፉት 10 ዓመታት ገዥው ፓርቲ፣ የፀረ ሽብር ህግና የሲቪል ማህበራት ህግ በማውጣት እንዲሁም ተቃዋሚዎችን በተለያዩ መንገዶች በማዳከም፣የምርጫ መወዳደሪያ ሜዳውን መዝጋቱም በገሃድ የሚታይ ሆኗል፡፡
ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በማፈን ደግሞ አገሪቱ ከአለም በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰርም ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃንን በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ ጥቂት ተቃዋሚዎች በቀጣዩ ምርጫ ፓርላማ ሊገቡ ይችሉ ይሆናል፤ ወጣቶች ግን አሁንም የፖለቲካ ተሳትፏቸው የተገደበ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግሮች ባሻገር ኢትዮጵያ በአካባቢው ከሚገኙት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ አንፃር የተረጋጋች ሃገር ነች ማለት ይቻላል፡፡ የአገሪቱ መንግስት በሽብርተኝነት ላይ ጦርነት አውጃለሁ ማለቱ ደግሞ የአሜሪካን ቀልብ ገዝቷል፡፡ ይሄም አሜሪካን የመሳሰሉ ለጋሽ ሃገራት ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ግፊት ከማድረግ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል፡፡ በሃገሪቱ ያለው የጎሳና የሃይማኖት ግጭት፣ የፖለቲካ ነፃነት እጦት በሃያላኑ ሃገራት እምብዛም ትኩረት የተሰጠው አይመስልም፡፡ ዜጎቿን በስደት እያጣች ያለችው ሃገር፣ ይበልጥ በአካባቢው በሽብርተኝነትና ደህንነት ላይ ብቻ አተኩራ የምትቀጥል ከሆነ፣የዜጎች ፍልሰትና የማህበራዊ አለመረጋጋቱም በዚያው መጠን ይቀጥላል፡፡ ከዚያ ይልቅ የቅርብ ጊዜውን አሳዛኝ ክስተት መነሻ በማድረግ መንግስት የመፍትሄ ሃሳቦችን መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም የታለፈባቸውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ቁጭ ብሎ በመመርመር፣ሁነኛ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ካልተቀመጡ አሁንም ስደቱ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም አሳዛኝና አስደንጋጭ መርዶዎችን መስማታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ረዳት ፕ/ር ሀሰን ሁሴን፤ በአሜሪካ ሚኒሶታ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡
 ፅሁፉ ሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም በአልጀዚራ ድረ-ገፅ ላይ ታትሞ ለዓለም የተሰራጨ ነው፡፡  
*ከላይ በቀረበው ጽሁፍ ውስጥ የተካተቱት ሃሳቦች በሙሉ የጸሃፊው ብቻ ነው፡፡

198 ሜትር ይረዝማል፣ 46 ወለሎች ይኖሩታል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት በእርዝማኔው ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረለትን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በአዲስ አበባ ከተማ ለማስገንባት ከቻይናው የኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲኤስሲኢሲ) ጋር ስምምነት መፈጸሙን ዥንዋ ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ በተከናወነው የፊርማ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ 198 ሜትር ርዝመትና 46 ወለሎች የሚኖረው የወደፊቱ የባንኩ ዋና ጽ/ቤት፣ በእርዝማኔው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ጥራቱም ከአፍሪካ ምርጥ ህንጻዎች አንዱ እንደሚሆን እናምናለን ብለዋል፡፡
ህንጻውን የሚገነባው የቻይናው የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲኤስሲኢሲ የኢትዮጵያ ቅርንቻፍ ጄኔራል ማናጀር ሶንግ ሱዶንግ በበኩላቸው፣ ኩባንያው በቻይና መሰል ግዙፍ የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በስኬታማ ሁኔታ ሲያከናውን እንደቆየ አስታውሰው፣ ህንጻው ለቻይና እና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም አዲስ ገጽታን የሚያላብስ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ኩባንያውና ባንኩ በቀጣይ በጋራ ተረባርበው ፕሮጀክቱን ስኬታማ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጡም ገልጸዋል፡፡

   ታዋቂዎቹ ድምፃዊያን ነዋይ ደበበ እና ጎሳዬ ተስፋዬ በሊቢያ አሰቃቂ ግድያ ለተፈፀመባቸው   ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት መታሰቢያ የሚሆኑ ዜማዎችን እንደሰሩ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
ኢትዮጵያውያን ለገጠማቸው ብሄራዊ ሃዘን ከማንም በላይ የጥበብ ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ያለው ነዋይ፤ ህዝቡ አንደበታችን ብሎ የጥበብ ሰዎችን ስለሚወክል እኔም  የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ ሙዚቃውን ሰርቻለሁ ብሏል፡፡ “በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው ግፍ መቆም አለበት ብለን ዛሬ ካልወሰንን ነገ የባሰ እንዳይመጣ ያሰጋኛል” ያለው ድምፃዊ፤ ሙዚቃውን ህዝቡን ለማፅናናትና መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሰራው ተናግሯል፡፡
“ሁሉም ያልፋል እስኪያልፍ ግን ያለፋል” በሚል ስያሜ የሰራሁት ሙዚቃ እንደ መዝሙር ሊታይ የሚችልና ዜማዊ ማስተማሪያ የሚሆን ነው ያለው ድምፃዊው፤ ግጥምና ዜማውን ራሱ እንደሰራው ገልፆ ሙዚቃውን ያቀናበረለት ወደፊት በሚያወጣው አልበሙ ከአምስት በላይ ዘፈኖችን የሰራለት ታምራት አማረ በቀና እንደሆነ ገልጿል፡፡ ሙዚቃው ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች መሰማት እንደጀመረ ጠቁሞ፤ ለሙዚቃው ክሊፕ ለመስራት በሳምሶን ስቱዲዮ በኩል እየተንቀሳቀስን ነው ብሏል፡፡  
እንዲህ ያለ መሪር ሀዘን ሲያጋጥም ቅስም ይሰብራል ያለው ጐሳዬ በበኩሉ፤ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው ግፍ ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ ተሰምቶኝ የማያውቅ ጥልቅ ሀዘን ፈጥሮብኛል ብሏል፡፡ ሀዘኑን የሰማሁት አዳዲስ ስራዎችን እያዘጋጀሁ ባለሁበት ሰዓት ነው ያለው ጎሳዬ፤ እንደ ድምፃዊነቴ ሀዘኔን የምገልፀው በጉሮሮዬ በመሆኑ “አኬልዳማ” የሚል የመታሰቢያ ሙዚቃ ሰርቻለሁ ብሏል፡፡ አገሪቱን በገጠማት ሀዘን ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ደም ያላቸው የዓለም ህዝቦች ሁሉ ክፉኛ ማዘናቸው ልቤን ነክቶታል ያለው ወጣቱ ድምፃዊ፤ በሙያው ያለውን ለማበርከት ማቀንቀኑን ተናግሯል፡፡
የመታሰቢያ ሙዚቃውን ግጥም፣ ዜማና ቅንብር የሰራው መኮንን ለማ (ዶክተሬ) እንደሆነ የገለፀው ጎሳዬ፤ ጌታቸው ኃይለማርያም አብሮት እንደተጫወተ፣ አሌክስ ባሪያው ደግሞ ካጀቡት ድምፃዊያን አንዱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
 የጎሳዬ “አኬልዳማ” ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች እየተሰማ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በድሬደዋ የጎርፍ አደጋ ባጋጠመበት ወቅት የመታሰቢያ ሙዚቃ ሰርቼ ነበር ሲል ያስታወሰው ጎሳዬ፤ ማህበራዊ ሃላፊነቴን ለመወጣት ምንጊዜም ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ ብሏል፡፡       

    የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ ጀምሮ ያቋረጠውን 8400 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ሎተሪ (SMS) ከነገ አንስቶ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
ሎተሪው በየቀኑ የሚበረከቱ የሳምሰንግ ሞባይሎች፣ በየሳምንቱ የሚበረከቱ ቶሺባ ላፕቶፖችና 21 ፍላት ስክሪን ቲቪዎች ሲኖሩት፣ በየ15 ቀኑ የሚወጡ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ ሞተር ሳይክሎችና ፍሪጆች እንዳሉት ማህበሩ አስታውቋል፡፡ በሎተሪው መሃልና መጨረሻ ላይ የሚወጡ መኪኖችም እንደተዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከሎተሪው ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በቀጥታ ማህበሩ ለጀመረው የኢ.ሴ ማዕከል ማሰሪያ የሚውል ሲሆን ማዕከሉ ለስብሰባዎችና ስልጠናዎች የሚያገለግሉ አዳራሾች፣ የቢሮ ክፍሎች፣ የሚከራዩ አዳራሾች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ከኪራይ የሚገኘው ገቢ ለጥቃት ሰለባዎችና በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሴቶች ድጋፍ ማድረግያ እንዲሁም ማህበሩ በገንዘብ ራሱን እንዲችል ያግዛል ተብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ የተጀመረው የማህበሩ 8400 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ሎተሪ ከ15 ቀናት በኋላ የተቋረጠው የ8100 የህዳሴ ግድብ SMS ሎተሪ በመጀመሩና ሁለቱን መልዕክቶች በአንዴ ማስተላለፍ ስለማይቻል ነበር ያለው ማህበሩ፤ ከነገ አንስቶ የሚጀመረው የ8400 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ሎተሪ ለ3 ወራት ይቀጥላል ብሏል፡፡

 የግድያ ቪድዮዎቹ አለማቀፍ ስነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው
      አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን እያሰራጫቸው የሚገኙና በተለያዩ አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች፣ ቡድኑ በአለማቀፍ ደረጃ የከፈተው የስነልቦና ጦርነት አካል ናቸው መባሉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የጀርመን የአገር ውስጥ የስለላ ተቋም ሃላፊ ሃንስ ጆርጅ ማሰን እንዳሉት፣ አገራት እነዚህ አሰቃቂ የግድያ ቪዲዮዎች በወጣት ዜጎቻቸው ላይ የሚያሳድሩትን የስነልቦና ተጽዕኖ ለመቅረፍ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል፡፡
የቪዲዮ ምስሎቹ የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ፕሮፓጋንዳ በወጣቱ ትውልድ ልቦና ውስጥ የሚያሰርጹ ናቸው ያሉት ጆርጅ ማሰን፤ ምስሎቹ ለእይታ ሲበቁ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ አሰቃቂነት የሚያሳዩ መልዕክቶችን አብሮ ማቅረብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ በቅርቡ በጀርመን ለሚገኙ ደጋፊዎቹ ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት፣ ባለፈው ጥር ወር በፈረንሳይ የተፈጸመውን ዓይነት ጥቃት እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርቧል ያለው ዘገባው፣ የጀርመን የደህንነት ባለስልጣናትም መልዕክቱን ያስተላለፈው ትውልደ ጀርመናዊው አለማቀፍ አሸባሪ ዴኒስ ኩስፐርት መሆኑን ማረጋገጣቸውን አስታውሷል፡፡
ሲኤንኤን በበኩሉ፤አይሲስ እያሰራጫቸው ያሉት የግድያ ቪዲዮዎች በአለማቀፍ ደረጃ ፍርሃትን እያነገሰ እንደሚገኝና የቡድኑ ቪዲዮዎች ሌሎችም ለመሰል ጥፋቶች እንዲነሳሱ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ዘግቧል፡፡
በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና መምህር ፕሮፌሰር አሪ ክሩግላንስኪ እንዳሉት፤ የአይሲስ የአሰቃቂ ግድያ ቪዲዮዎች፣ ግለሰቦች በግጭት ወቅት  ተመሳሳይ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ስነልቦናዊ ጫና የመፍጠር ሃይል አላቸው፡፡
የጀሃዲስቶች አሰቃቂ ግድያዎች በቪዲዮ ምስሎች በስፋት መሰራጨታቸው፣ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም የማያስቡትን አንገት ቀልቶ መግደል የሚል የጭካኔ ሃሳብ ትኩረት ሰጥተው ማሰብ እንዲጀምሩ በማድረግ ረገድ በአለማቀፍ ደረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡