Administrator

Administrator

በዚህ ወር ብቻ ከ218 ሺህ በላይ ስደተኞች ባህር አቋርጠው አውሮፓ ገብተዋል

   ራሱን በህጋዊ መንግስትነት የሰየመው ናሽናል ሳሊቬሽን ገቨርንመንት ኦፍ ሊቢያስ ጄኔራል ናሽናል ኮንግረስ ቃል አቀባይ ጀማል ዙቢያ የአውሮፓ ህብረት በመንግስትነት እውቅና የማይሰጠው ከሆነ፣ ኮንግረሱ የአውሮፓ አገራትን በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ተጨማሪ ስደተኞች እንደሚያጥለቀልቅ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ቃል አቀባዩ ለዘ ቴሌግራፍ እንዳሉት፣ ባለፈው አመት የአገሪቱን መዲና የተቆጣጠረው ኮንግረሱ ከህብረቱ የመንግስትነት እውቅና ከተነፈገው፣ በራሱ ወጪ ጀልባዎችን ተከራይቶ አፍሪካውያን ስደተኞችን በሜዲትራኒያን ባህር በኩል በማጓጓዝ አውሮፓን የባሰ በስደተኞች ከማጥለቅለቅ አይመለስም፡፡
ሊቢያ በግዛቷ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ የሚሄዱ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን ለማስቀረት በየአመቱ በአስር ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ታደርጋለች ያሉት ቃል አቀባዩ፣ የአውሮፓ ህብረት በመንግስትነት እውቅና የማይሰጠን ከሆነ ስደተኞችን እየጫንን አውሮፓን እናጥለቀልቃታለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ኮንግረሱ አለማቀፍ እውቅና የተሰጠውን የሊቢያ ተወካዮች ምክር ቤት ታማኝ ሃይሎች በጦርነት አሸንፎ መዲናዋን ቢቆጣጠርም፣ የአውሮፓ ህብረት ግን ለኮንግረሱ የመንግስትነት እውቅና ሳይሰጥ መቆየቱን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ተመድ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ በዚህ ወር ብቻ ከ218 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ገብተዋል ማለቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

   ባለፉት 20 አመታት በድረገጽ አማካይነት የተለያዩ ዲጂታል መጽሃፍትን ለሽያጭ በማቅረብ የሚታወቀው አማዞን፤የታተሙ መጽሃፍትን የሚሸጥበትን የመጀመሪያውን መደብር በሲያትል መክፈቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
አማዞን ቡክስ የተሰኘው ይህ የመጽሃፍት መሸጫ መደብር የኩባንያውን የድረገጽ ሽያጭ መረጃዎች መሰረት አድርጎ የተመረጡ 6 ሺህ መጽሃፍትን ለሽያጭ ማቅረቡን የጠቆመው ዘገባው፣ የመጽሃፍቶቹ የመሸጫ ዋጋም ከድረገጽ የሽያጭ ዋጋ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
በአዲሱ መደብራችን የምንሸጣቸው መጽሃፍት የድረገጽ ሽያጭ ደንበኞቻችንን ፍላጎት፣ የቀረቡልንን የግዢ ጥያቄዎች፣ የመጽሃፍቱን ተወዳጅነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መሰረት አድርገን የመረጥናቸው ናቸው ብለዋል፤ የአማዞን ኩባንያ ምክትል ፕሬዚደንት ጄኔፈር ካስት፡፡
አማዞን አዲሱ የመጽሃፍት መደብር የሚያስመዘግበውን ሽያጭ ገምግሞ፣ በቀጣይም በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የታተሙ መጽሃፍትን መሸጫ መደብሮችን የመክፈት ዕቅድ እንዳለውም ተነግሯል፡፡
lone wolf attacks

- ባለፈው ወር በሙስና ተከስሰው፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ነው
- የመዲናዋ ከንቲባና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩም ስልጣን ለቀዋል

   በሩማኒያ መዲና ቡቻሬስት ውስጥ በሚገኝ አንድ የምሽት ክለብ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ32 በላይ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸው የቀሰቀሰው ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠ/ ሚኒስትር ቪክቶር ፖንታ በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣን እንደለቀቁ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ከ20 ሺህ በላይ ሩማንያውያን ባሳለፍነው ማክሰኞ በከተማዋ ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ መንግስት ሙሰኛ ነው፤ የደህንነት ክትትል አሰራሩም ደካማ ነው በማለት ተቃውሟቸውን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፖንታም በነጋታው ስልጣን መልቀቃቸውን በይፋ እንዳስታወቁ ጠቁሟል፡፡
ለ3 አመት ከመንፈቅ በስልጣን ላይ የቆዩት ጠ/ ሚኒስትር ቪክቶር ፖንታ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው፣ ጉዳያቸው በአገሪቱ ፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ዘገባው ጠቁሞ፣ በስልጣን ላይ እያሉ በታክስ ማጭበርበር፣ በሙስና እና ከህገወጥ ገንዘብ ጋር በተያያዘ በክስ የተመሰረተባቸው የመጀመሪያው የአገሪቱ ጠ/ ሚኒስትር እንደሆኑም ገልጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡባቸውን ክሶች በሙሉ ክደው መከራከራቸውንና ክስ የመሰረቱባቸውን አቃቤ ህጎች ፍጹም ሙያዊነት የጎደላቸው ሲሉ መተቸታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባስተላለፉት መልእክት ከስልጣን መልቀቃቸው ጎዳና ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ያሰሙትን ዜጎች ያስደስታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ አገሪቱን ከብጥብጥ ለማዳንና ተተኪ መንግስት ማቋቋም የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ስብሰባ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

   የአልቃይዳው መሪ አይማን አል ዛዋሪ፣ በመላው አለም የሚገኙ ጂሃዲስቶች በምዕራባውያን አገራት በተለይ ደግሞ በአሜሪካ ላይ ሌሎች ተጨማሪ የተናጠል የሽብር ጥቃቶችንት እንዲፈጽሙ ጥሪ ማቅረባቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
አል ዛዋሪ በሳምንቱ መጀመሪያ በቪዲዮ ባስተላለፉትና በተለያዩ ድረገጾች በተሰራጨው የድምጽ መልዕክት፣ የቡድኑ አባላትና ደጋፊዎች በአሜሪካ ግዛት ውስጥ እንዲሁም ከአሜሪካ ጥቅም ጋር በሚተሳሰሩ በመላው አለም የሚገኙ ተቋማት ላይ በተናጠል ጥቃት እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
16 ደቂቃ በሚፈጀው የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ ፍልስጤማውያን ባለፈው ወር በእስራኤላውያን ላይ ያደረሱትን ጥቃት ያወደሱት የአልቃይዳው መሪ፣ አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ በመቀጠሏ ጂሃዲስቶች ዋነኛ የጥቃት ኢላማ ሊያደርጓት እንደሚገባ ገልጸው፣ “የእስራኤል ደጋፊ የሆኑ ሁሉ፣ በሞትና በኢኮኖሚ ድቀት ዋጋቸውን ማግኘት አለባቸው” ብለዋል፡፡  
የአልቃይዳው መሪ አይማን አል ዛዋሪ፣ ሶስት ሰዎች የሞቱበትንና 264 ያህልም የቆሰሉበትን የቦስተኑን ጥቃት ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከዚህ ቀደም የተፈጸሙና በርካታ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረጉ በተናጠል የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን በዋቢነት በመጥቀስ፣ መሰል ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ለጂሃዲስቶች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሁለት ዓመት 250 ህሙማንን ለማሳከም አቅዷል

 “ሞት በኩላሊት ይብቃ” የተሰኘ በጐ አድራጎት ማህበር፣ ገንዘብ በማሰባሰብ በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩና ረዳት የሌላቸውን ህሙማን ለመርዳት ማቀዱን አስታወቀ፡፡
በኩላሊት ህመምተኞች፣ በባለሙያዎችና በበጐ ፈቃደኛ መስራች አባላት የተቋቋመው ማህበሩ፤ሥራ የጀመረ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት 250 ያህል ህመምተኞችን ለማሳከም እንዳቀደ ተጠቁሟል፡፡
በነገው ዕለት መነሻውን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣መድረሻውን ኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት ሀውልት ያደረገ፣ በኩላሊት ህመም መንስኤና መፍትሔ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ   የእግር ጉዞ እንደሚደረግም ማህበሩ ሰሞኑን በካፒታል ሆቴል በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የማህበሩ መስራች አቶ ኢዮብ ተወልደ መድህን እንደገለፁት፤የፊታችን አርብ ለኩላሊት ህሙማን መርጃ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

Saturday, 07 November 2015 09:55

የዘላለም ጥግ

(ስለ ችሮታ)
• የድሆችን ህይወት ካላሻሻልክ ችሮታ አደረግህ
አይባልም፡፡
ማኖጅ ብሃርጋቫ
• ዓለም የምትፈልገው ችሮታ ሳይሆን ፍትህ
ነው።
ሜሪ ዎልስቶንክራፍት
• ፍትህ የበለጠ የሰፈነበት ህብረተሰብ ብዙ ችሮታ
አይፈልግም፡፡
ራልፍ ናዴር
• ችሮታ፤ የእምነትና የተስፋ ውጪያዊ መገለጫ
ሊሆን ይችላል፡፡
ጆሴፍ ቢ ዊርዝሊን
• እውነተኛ ችሮታ፤ ምንም ማካካሺያ ሳያስቡ
ሌሎችን የመጥቀም ጥልቅ ፍላጐት ነው፡፡
ኢማኑኤል ስዊዲንቦርግ
• የሰዎች ባህርይ (ሰብዕና) በችሮታ የተነሳ ሊበላሽ
ይችላል፡፡
ቴዎዶር ሄርዚ
• ችሮታ እጅግ በርካታ ሃጢያቶችን ይፈጥራል፡፡
ኦስካር ዋይልድ
• ችሮታ ከቤት መጀመር አለበት፤ እዚያው
መቅረት ግን የለበትም፡፡
ፊሊፕስ ብሩክስ
• ችሮታ፤ ከልብ በፈቃደኝነት የሚሰጥ ነገር ነው፡፡
ሩሽ ሊምባው
• ስሞሽ (Kiss) ችሮታ አይደለም፡፡ ንግድንና
ችሮታን ፈጽሞ አትደባልቁ፡፡
ጆኒ ሳይሞንስ
• ግሩም ሙዚቃ፤ ታላቅ አገልግሎትና ችሮታ
የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ፡፡
ማይክል ሌዩኒግ
• በችሮታ ሥራ ከተሳተፍኩ በቅጡ የሥራው
አካል ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡ ስሜ በበራሪ
ወረቀታችሁ ላይ እንዲሰፍር ብቻ አልሻም፡፡
ናንሲ ሎፔዝ
• በአሁኑ ወቅት በዓመት 30 ገደማ የችሮታ
ጨረታዎችን እያከናወንኩ ነው፡፡
ጄፍሬይ አርቼር
• ፕሬስን ለችሮታ ሥራዬ ካልሆነ በቀር ለሌላ
ለምንም ነገር ፈጽሞ ተጠቅሜበት አላውቅም፡፡
ሒዘር ሚልስ

የኢህአዴግ መልዕክቶች፡
• አሁንም ኃያል ነኝ። ከውሳኔዬ ውልፍት የለም (ሚኒስትሮችም ጭምር)።
• መሪውን የጨበጡት፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደሆኑ ተመልከቱ።
• በሺ የሚቆጠሩ የበታች ባለስልጣናት፣ በዘመቻ ተጠራርገው ይባረራሉ።

   በኢቢሲ የተመለከትነው የከፍተኛ ባለስልጣናት ስብሰባ፣ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። ካሁን በፊት፣ ብዙ ስብሰባዎችን አይተናል፤ ብዙ ንግግሮችን ሰምተናል። የአሁኑ፣ እንዴት የብዙዎችን ትኩረት ሊስብ ቻለ? ኢህአዴግ፣ ‘የህዝብ የልብ ትርታ’ን ማዳመጥ ስለጀመረ ይሆን?
‘የሕዝብ የልብ ትርታ’ን ማዳመጥ ብቻውን፣ አሪፍ ነው ማለቴ አይደለም። የሕዝብን ስሜት ተከትሎ፣ የታክሲ ስምሪት ቁጥጥር መጀመሩ ወይም የሸቀጦች ዋጋ ተመን ለማወጅ መሞከሩ፤ ምን ትርፍ አስገኘ? የትራንስፖርት እጥረትን ከማባባስና ገበያን ከማቃወስ ያለፈ ውጤት አላመጣም። ዜጎችን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሁነኛ መፍትሄ የማበጀት ብልህነትም ያስፈልጋል።
ለነገሩ፣ ኢህአዴግ፣ ብዙ ጊዜ፣ ዜጎችን አያዳምጥም። በሁለት በሦስት ዓመት ጉባኤ ሲያካሂድ፤ ወይም በየመንፈቁ፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሲሰበሰብ፣ በርካታ እቅዶችን ያወጣል፤ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል። በቃ፤ ከዚያ በኋላ፣ ከላይ እስከ ታች፣ ውልፍት ማለት የለም። ከዚያ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች... (ችግሮችና አቤቱታዎች) ብዙም ሰሚ አያገኙም። በሰሞኑ ስብሰባ ላይ፣ ‘ዜጎች፣ ሰሚ አጥተዋል’ እያሉ የኢህአዴግ መሪዎች ሲናገሩ አልነበር!
በእርግጥ፣ አንዳንዶቹ ችግሮች፣ ያን ያህልም ቁምነገር የሌላቸው ጊዜያዊ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ። በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ አቤቱታዎችና የተጋነኑ ጩኸቶችም ይኖራሉ። ነገር ግን፣ ለተጨባጭ ችግሮችና አቤቱታዎችም ቢሆኑ፣ ኢህአዴግ ፊት አይሰጥ።
ከራሱ እቅድና ውሳኔ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች ሲመጡ፣ “እውነት ናቸው ወይስ አይደሉም? ቁምነገር ይዘዋል ወይስ አልያዙም?” ብሎ ለመመርመርና ለመመዘን፣ ፈቃደኛ አይሆንም። እንዲያውም፣ ‘አፍራሽ’ እና ‘አደናቃፊ’ ብሎ ሊፈርጃቸው ይችላል። ጭራሽ፣ የዜጎችን አቤቱታ መስማት (‘የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ’)... እንደ ድክመትና እንደ ጥፋት የሚቆጠርበት ጊዜ አለ። “አድርባይነት” በማለት ይሰይመዋል።
“አብዮታዊ ፓርቲ ነኝ” የሚለው ኢህአዴግ፤ ለውጥ ለማምጣት እታገላለሁ እንጂ፤... ከህዝብ የስሜት ነፋስ ጋር አብሮ ለመንጎድ፤ መስሎ ተመሳስሎ ለማደር፣ በዚህም ተወዳጅነትንና ዝናን ለማትረፍ የምሯሯጥ፣ “አድርባይ”ፓርቲ አይደለሁም” ይላል።    
እና፣ ‘አድርባይ’ ላለመባል፣ ምን ማድረግ ይሻላል? ዜጎችን አለማዳመጥ? ችግሮችን ላለማየት አይንን መጨፈን? አቤቱታዎችን ላለመስማት ጆሮን መድፈን? “ዜጎችን የሚያዳምጥ የመንግስት አካልና ባለስልጣን ጠፍቷል” ተብሎ የለ? (በባለስልጣናቱ ስብሰባ ላይ ማለቴ ነው)።
ተመልካችና ሰሚ ሲጠፋ፤ ተጨባጭ ችግሮች ያለ መፍትሄ እየተባባሱ፣ እውነተኛ አቤቱታዎች ወደ እሮሮ ይቀየራሉ። ያኔ፣ ችግሮች ሲባባሱ ነው፣ እሮሮዎች የሚደመጡት።
ነገር ግን፣ ኢህአዴግ፤ የህዝብን ጩኸት በማዳመጥ ብቻ አይመለስም። ጩኸቱን ይወርሰዋል። “ፍትህ ጠፋ” እያለ ዋና የእሮሮ ባለቤት ይሆናል። “ሙስና አገርን ገደለ”፣ “አገር መቀመቅ ወረደች”፣ “ኢህአዴግ በሰበሰ”... እነዚህ ሁሉ፣ ካሁን በፊት ከኢህአዴግ የሰማናቸው ምሬቶች ናቸው። ሰሞኑን እንደሰማነውም፣ “መሪዎች የሚሰሩትን አያውቁም”፤ “አላግባብ የጥቅም መረብ ዘርግተው አገሪቱን ተብትበዋታል”፤ “ከማውራት ውጭ ለውጥ አላመጣንም”፤ “ለግብር ይውጣ ህዝቡን እየጠራን፣ በአሰልቺ ስብሰባ እንዲርቀን አድርገናል”፤ “ህዝቡ ሰሚ አጥቶ በኢህአዴግ ተስፋ ቆርጧል”...
እንዲህ የኢህአዴግ መሪዎች፣ ኢህአዴግ ላይ የትችትና የወቀሳ ናዳ ሲያወርዱ፤ አገሬው ምን ይበል? የሚጨመር ትችት ከየት ይመጣል?
“አላግባብ የመሞዳሞድና የሙስና መረቦች በዘመቻ መበጣጠስ አለብን”፣ “ጠራርገን በማባረር፣ ህዝቡ ተስፋ እንዲያገኝና በኢህአዴግ ላይ እምነት እንዲያድርበት ዘመቻ ማካሄድ ይኖርብናል”፤...  
ኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ወይም በስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ፣ እንዲህ አይነት ውሳኔ ከተላለፈና የዘመቻ እቅድ ከወጣ በኋላስ? ከዚያ በኋላማ... ወደ ቀድሞው “ሴቲንግ” ይመለሳል። በቃ፣ ሌላ ጉዳይ መስማት አይፈልግም።
“ኧረ፣ የኢህአዴግ መሪዎች በኢህአዴግ ላይ ያዘነቡት ውርጅብኝ ተጋኗል” ብሎ አስተያየት የሚሰጥ ሰው ቢመጣ እንኳ፣ ሰሚ አያገኝም። ምናልባትም፣ ‘አፍራሽ’፣ ‘ፅንፈኛ’፣ ‘አደናቃፊ’ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል። ጠራርጎ የማባረር ዘመቻው ላይ፣ ... እንደማንኛውም ፈጣን ዘመቻ፣ ንፁሁን ከነውረኛው፣ ቀናውን ከአጥፊው ጋር መጠረጉ የማይቀር ነው። ነገር ግን፣ ዘመቻውን በመደገፍ የሚያጨበጭብ እንጂ፣ ቅሬታ የሚያቀርብ ሰው ቦታ አይኖረውም።
በእርግጥ፣ ነውረኛውና አጥፊው፣ እሪታውን መልቀቁ አይቀርም። ግን፣ ንፁሁና ቀናው ሰራተኛም፣ አላግባብ ተባረርኩ ብሎ አቤቱታ ቢያቀርብ፣ ማንም አይሰማውም። የክልል የቢሮ ሃላፊ ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ ይቅርና፣ ሚኒስትሮችና አንጋፋ የኢህአዴግ መሪዎችም፣ ዘመቻውን ለመተቸት ቢሞክሩ፣ ለውጥ አያመጡም። እንዲያውም፣ መረር ያለ ምላሽ ይመጣባቸዋል። ይህም ብቻ አይደለም። በቪዲዮ ተቀርፆ በቲቪ ይሰራጫል፤... ሰሞኑን በኢቲቪ እንዳየነው አይነት ማለት ነው። አለምክንያት አይመስለኝም። መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ዘመቻው ላይ ቅሬታ ለመሰንዘር ለሚሞክሩ ሰዎች፣ ማስጠንቀቂ ነው።
ከስልጣን የሚባረር የቢሮ ሃላፊ ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ ይቅርና፣ ሚኒስትሮችና አንጋፋ መሪዎችንም ቢሆን እንደማልምር ተመልከቱ። በቃ፤ ውሳኔ ከተላለፈና እቅድ ከወጣ በኋላ፤ ወዲህ ወዲያ ውልፍት ማለት የለም - ከታች እስከ ላይ፣ አንድ አይነት ቃል ነው የሚነገረው።  እናም፣ አንደኛው ሚኒስትር ወይም ሌላኛው አንጋፋ መሪ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባድ ተግሳፅ ሲሰነዝሩ በቲቪ ስንመለከት፤ ኢህአዴግ ለበታች ባለስልጣናት፣ ለካድሬዎችና ለአባላት እንዲሁም ለሌላውም ዜጋ፣ ማስጠንቀቂያ እያስተላለፈ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ተግሳፅ የደረሰባቸው ሚኒስትሮችና መሪዎች፣ ተግሳፁን እንዴት ያስተናግዱታል? በአብዛኛው፣ በፀጋ ከመቀበል እንደ መስዋዕትነት ከመቁጠር ውጭ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም - “ለፓርቲዬ የምከፍለው መስዋዕትነት ነው” ሊሉም ይችላሉ። እንዲያውም፣ በኢህአዴግ መሪዎች ዘንድ በጣም የተለመደ አባባል አለ። “ፓርቲው... በሚኒስትርነት አልያም በጥበቃ ሰራተኝነት እንድሰራ ቢመድበኝ፤ ያለ ማንገራገር እሰራለሁ” ... በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምተን የለ? ለፓርቲያቸው የሚያበረክቱት መስዋዕትነት ነው።
ለነገሩ፣ አይገርምም። ቢያንስ በሃሳብ ደረጃ፣ መስዋዕትነትን እንደ ቅዱስ ምግባር የማይቆጥር ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ነው። መስዋዕትነት፣ የአምልኮ ያህል በሚከበርበት አገርና ባህል ውስጥ ነው ያለነው። ለማንኛውም፣... ለአዲሱ ዘመቻ እስከጠቀመና፣ የፓርቲውን መልእክት ለማስተላለፍ እስካገለገለ ድረስ፣... በቲቪ የሚተላለፍ ስብሰባ ላይ፣ አንዱ ከፍተኛ ባለስልጣንና መሪ፣ ከባድ ተግሳፅ ቢሰነዘርበት... የመስዋዕት ተረኛ ሆኗል ማለት ነው። ያኔ፣ ከላይ እስከ ታች፣ የፓርቲ መሪና ሚኒስትር፣ የክልል ባለስልጣንና ካድሬ፣ የቀበሌ አስተዳዳሪና ተራ አባል ሁሉ፣ “መስመሩን ይይዛል፤ ሰልፉን ያሳምራል”። ይሄም አይገርምም።
“ሰልፍን ማሳመር”፣ በአገራችን ጎልቶ የሚታይ ጥንታዊ ባህል ነው። ቅንጣት የሚያፈነግጥ ሃሳብ፣ እንዳይኖር እንፈልጋለን። ለምሳሌ፣ በሃይማኖት ዙሪያ፣ “ከተለመደው ነባር ሃሳብ” ውጭ፣ ምንም አዲስ ነገር ከመጣ፣ ብዙዎችን ያስቆጣል። አንዱ ሌላውን ለማጥፋት፣ ዘመቻ ይከፈታል።
በፖለቲካም ተመሳሳይ ነው። “እኔ የምደግፈው ፓርቲ ላይ፣ አንዳች ትችት ትንፍሽ እንዳትል። አንተ የምትደግፈው ፓርቲ ላይ፣ የእውነትም ይሁን የሃሰት ውንጀላ ሳዥጎደጉድበትም፣ አፍህን ያዝ”... የሚል ስሜት የገነነበት ባህል አለብን። ሁሉንም፣ በመስመር ማሰለፍ ያምረናል። ሌላውም እንዲሁ፣ በራሱ መስመር ውስጥ ካላስገባሁ ሞቼ እገኛለሁ ይላል። እናም፣ ከመጠፋፋት ውጭ ሌላ መፍትሄ አይታየንም።
በእርግጥም፣ ለጭፍን እምነት ሳይሆን ለሳይንስ፣ ለጭፍን ስሜት ሳይሆን ለእውነታ፣ ለጭፍን ጉልበትና ለቡድን ሳይሆን፣ ለማስረጃና ለአእምሮ ዋጋ የሚሰጥ ስልጡን ባህል ብናዳብር ኖሮ፤ ችግር አይኖርም ነበር። ነፃነትንና ለእውነታ በፅናት የመቆም ስነምግባርን፤ መከራከርንና መከባበርን ያዋሃደ መፍትሄ እናገኝ ነበር። ያንን ስልጡን ባህል እስካላዳበርን ድረስ ግን፤ ብዙም አማራጭ አይኖረንም።
በየፊናው አዛዥ ናዛዥ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችና ቡድኖች፣ ገናና ለመሆን ሲሻኮቱና ሲጋጩ፣ አገሬው በስርዓት አልበኝነት ይታመሳል። ወይም ደግሞ፣ ከፋም ለማም፣ አንዱ ሰው፣ አንዱ ቡድን፣ አንዱ ውሳኔና እቅድ፣ ሌሎችን ሁሉ አንበርክኮ ገናና ይሆንና፣ ከላይ እስከ ታች፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ “ስርዓት” ይሰፍናል። “የፓርቲ መመሪያ ከላይ ወደ ታች የማውረድ አሰራር”፣ “የማዕከላዊነት አሰራር” ብለው ይጠሩታል። ከማዕከል፣ አንዳች ውሳኔና እቅድ ሲወጣ፣ በዙሪያው የተዘረጋ ቅርንጫፍ በሙሉ፣ አቅጣጫውን ያስተካክላል።
ታዲያ፣ “መስመር የሚያስይዝ የማዕከላዊነት አሰራር”፣ ለውሳኔና ለእቅድ ብቻ አይደለም። መሪነትንም ይጨምራል። ጭፍን እምነትና ስሜት በበዛበት የኋላቀርነት ባህል ውስጥ፣... ያው፣... በርካታ ፊታውራሪዎችና አበጋዞች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች፣ በየፊናቸው ገናና ለመሆን ሲሻኮቱና ሲጋጩ፣ አገር ይቀወጣል። ጥንታዊው የጎሳ አስተዳደር፣ ከእንዲህ አይነት መቋጫ የሌለው የግጭት ስርዓት አልበኝነት ያልተላቀቀ አስተዳደር ነው።
ኢትዮጵያ፣ ለሺ ዓመታት፣ በየጣልቃው ወደ ስርዓት አልበኝነት ብትንሸራተትም፣ በተወሰነ ደረጃ አገራዊ ስርዓት እስከመመስረት የደረሰ፣ ትልቅ የስልጣኔ ታሪክ የተሰራባት አገርም ናት። እናም፣ አብዛኛው ሰው፣ በርካታ አበጋዞችና ቡድኖች የሚሻኮቱበት ስርዓት አልበኝነትን አይፈልግም። እና ምን ይሻላል?
ሁለት አማራጮች አሉ። በአንድ በኩል፣ የትኛውም አበጋዝና ቡድን፣ አዛዥ ናዛዥ የማይሆንበት፣ ገናና እንዲሆንም የማይፈቀድበት፣ የእያንዳንዱ ሰው የሃሳብ ነፃነትና የምርት ባለቤትነት መብት የሚከበርበት፤ እያንዳንዱ የመንግስት ባለስልጣን በሕግ የተገደበ ሃላፊነትን ብቻ የሚያገኝበት ስልጡን ስርዓት መፍጠር ይቻላል - የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የነፃነት ስርዓት ልንለው እንችላለን።
ለምሳሌ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን፣ እንዲሁም የሌሎች ሚኒስትሮች ሃላፊነት፣ ምን እንደሆነ ለማወቅ፣ የግድ የሚስጥር ተካፋይ የውስጥ አዋቂ መሆን አያስፈልግም። የሕገመንግስት አንቀፆችን ማንበብና መገንዘብ በቂ ይሆናል። ከዚያ ውጭ ውልፍት ማለት፣ አይቻልማ - የህግ የበላይነት በሰፈነበት ስልጡን ስርዓት። ይሄ አንዱ አማራጭ ነው። ነገር ግን፣ ለአእምሮና ለሳይንስ ክብር የሚሰጥ ስልጡን ባህል ካልዳበረ፣ የሕግ የበላይነት ስርዓትን መፍጠር አይቻልም።
ሌላኛው አማራጭ? ብዙ አበጋዞችና ቡድኖች፣ በየፊናቸው ገናና ለመሆን እየተጋጩ አገር በስርዓት አልበኝነት ጨለማ ከምትታመስ፣... አንዱ መሪ፣ ገናና ሆኖ ቢወጣ ይሻላል። ግን፣ ወደ ግጭት የሚያመራ ሽኩቻ እንደጠፋና አንድ መሪ ገናና ሆኖ እንደወጣ፣ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? ውስጥ ለውስጥ እየተሻኮቱ ሊሆን ይችላል። “ሕገመንግስት ላይኮ፣ የእያንዳንዳቸው የሥልጣን ልክ በዝርዝር ተፅፏል” ብንል ዋጋ የለውም። በሕገመንግስት አንቀፆች ላይ መተማመን የሚቻለው፣ ስልጡን ባህልና የሕግ የበላይነት ሲስፋፋ ነው።
ካልተስፋፋስ? ያው፣ ስርዓት አልበኝነትን በመጥላት ብቻ፤... አንድ መሪ፣ ከሌሎች ሁሉ ጎልቶ እንዲወጣ እንጠብቃለን። አለበለዚያ፣ ነገሮች ሁሉ ‘አይጥሙንም’። እናም፣ ገናናነትን የሚጠቁም አጋጣሚንና ንግግርን የማየት ፍላጎት ያድርብናል። አለበለዚያ፣ በመሪነት የተቀመጠውን ሰው፣ እንደ ደካማ እንቆጥረዋለን። ለዚህም ይመስለኛል፤ ባለፉት አመታት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አብዛኛውን ጊዜ፣ ከአነጋገራቸው ቁጥብ እና ሰከን ያሉ በመሆናቸው፣ በብዙዎች ዘንድ እንደ ደካማ የተቆጠሩት። የሚናገሩትን ሃሳብ በማገናዘብና በመመዘን፣ ጥንካሬንና ድክመትን ከመለካት ይልቅ፣ ቁጥብነትን እንደድክመት የሚቆጥር ባህል ውስጥ መሆናችን ያሳዝናል።
ከሦስት የስልጣን ዓመታት በኋላ፣ ሰሞኑን፣ ቆጣ እና ረገጥ ያለ ንግግራቸውን በቲቪ ስንመለከትስ? ወዲያውኑ ነው፣  የጠንካራ መሪ ዝና ያገኙት። በቲቪ የተሰራጨው ስብሰባ፣ የጠ/ሚ ኃይለማሪያምን ስልጣን በጉልህ የሚያሳይ መልእክት የያዘ ነው የምለውም በዚህ ምክንያት ነው።    

      አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 20 ባወጣው እትሙ፤ ‹‹ህልምና ኑሮ ሲምታታ እንዲህ ነው - ከእውነት ዓለም ጋር የተላተመው የጤና ኢንሹራንስ!›› በሚል ርዕስ ዮሐንስ ሰ. የተባሉ ጸሃፊ አንድ ጽሁፍ ለንባብ አቅርበው ነበር፡፡ ጸሃፊው የጤና ኢንሹራንስ ጉዳይ አብከንክኗቸው፣ ተግባራዊነቱ ላይ ጽልመትና ጥላቻ የጋረደበት ትችታቸውን ቢሰነዝሩም ጉዳዩን እንደ ጉዳይ ማንሳታቸው በራሱ ሊያስመሰግናቸው ይገባልና በቅድምያ ላነሱት ርዕሰ ጉዳይ ልባዊ ምስጋናችንን በኤጀንሲው ስም ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡
እኛ እንደምንገምተው፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ነገሮችን በመረጃ አስደግፎ ለአንባቢ እውቀት የሚያስጨብጥ ጋዜጣ ነው፡፡ ሆኖም ዮሐንስ ሰ. (መረጃ ለማግኘት መሯሯጡ ዳገት ሆኖባቸው ነው መሰል) በወፍ በረር ስለ ጤና ኢንሹራንስ በሰሙት ወሬ ተደግፈው የጻፉት ጽሁፍ ትክክል ባለመሆኑ ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተገደናል፡፡
በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ ጽሁፍ፣ ጸሃፊውንም ሆነ አንባቢውን ማምታታቱ አይቀርም። ዮሐንስ ሰ. ስለ ጤና ኢንሹራንስ ለመጻፍ ሲነሱ በቂ መረጃ ይዘው ስላልነበረ የጽሁፋቸውን ርዕስ ‹‹ህልምና ኑሮ ሲምታታ እንዲህ ነው!!›› ብለው ለመጀመር ተገደዋል፡፡ ሃቁን  ለመናገር ከእውነት ዓለም ጋር የተላተመው የጤና ኢንሹራንስ ሳይሆን መረጃን በበቂ ሁኔታ ባለማሰባሰብ ከገሃዱ ጋር የተላተሙት ራሳቸው ለመሆናቸው ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ የሚመስል የፈጠራ ስራቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
ጸሃፊው በመግቢያቸው ‹‹የቤተሰብዎን ጤንነት (ጥርስ ከማስተከል በቀር…) ሁሉም አይነት ምርመራ፣ህክምናና መድሃኒት ያገኛሉ - ነጻ ወይም ደግሞ 25 ብር ባልበለጠ የወር መዋጮ፡፡ ይህን ይመስላል መንግስት የጀመረው አስደናቂ የጤና ኢንሹራንስ›› በሚል የጤና ኢንሹራንሱ ምናባዊ የህልም ዓለም እንደሆነ ስላቅ አዘል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ጸሃፊው በምናባዊ ዓለም ውስጥ ሆነው በመጻፋቸው መንግስት ሃገሪቱ ውስጥ ለመተግበር ያቀደው የጤና መድህን ሁለት አይነት መሆኑን እንኳን ከሚያውቁ ሰዎች ለመጠየቅ ዕድል አልነበራቸውም። ዮሐንስ ሰ. ያልተገነዘቡት በማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓትና በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መካከል ያለውን ልዩነት ነው። የማህበራዊ የጤና መድህን ማለት በመደበኛው ክፍለ-ኢኮኖሚ ለተሰማሩ (ደመወዝ ተከፋይ የሆኑ ሠራተኞች) 3%  ከደሞዛቸው  መዋጮ በማድረግ፣አሰሪያቸውም ተመሳሳይ ፐርሰንት እያዋጣላቸው ዜጎች ያልተጠበቀ ድንገተኛ ህመም ሲገጥማቸው ከኪስ የሚወጣ የገንዘብ ክፍያ ሳይኖር የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና መድህን ሥርዓት ነው፡፡ ይኸኛውን የመድህን ስርዓት መንግስት ገና በሃገሪቱ ተግባራዊ አላደረገውም።  በመጪው ጥር ወር ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ እዚህ ጋ ጸሃፊው ባልተጀመረ ነገር አስተያየት መስጠታቸው ትዝብት ላይ ሳይጥላቸው አልቀረም።
ሁለተኛው የጤና መድህን ስርዓት ደግሞ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የሚባለውና መደበኛ ከሆነው ክፍለ-ኢኮኖሚ ውጭ በተለይም በግብርና ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያገለግልና ቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ ዓመቱን ሙሉ ያልተጠበቀ ህመም ሲከሰት የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ነው፡፡ ይሄም ቢሆን በአባላት መዋጮ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን እስከ 25 % በሚደርስ የመንግስት ድጎማ የተደገፈ ነው፡፡ ይህ የመድህን ስርዓትም ቢሆን ገና በሙከራ ደረጃ ላይ ያለና በሚታዩ ድክመቶች ዕርማት እየተወሰደ የማስፋፍያ ስራ የሚሰራበት ነው፡፡
እዚህ ጋ ጸሃፊውን ዮሃንስ ሰ.ን ለመጠየቅ የምንፈልገው ለመተቸት የፈለጉት ገና ያልተጀመረውን የማህበራዊ የጤና መድህንን ነው ወይንስ በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓትን?...
በጽልመት ከታጀበው ጽሁፋቸው ለመረዳት እንደሞከርነው ጸሃፊው ‹‹የህልም ዓለም!›› በማለት ለመንቀፍ የሞከሩት የመድህን ስርዓት፤ ገና በሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኘውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓትን ይመስለናል፡፡ በእርግጥ የጸሃፊው ትኩረት በዚህ መድህን ስርዓት ላይ ከሆነ ሥለ መድህን ሥርዓቱ ምንም አይነት ግንዛቤ የላቸውምና ስለ ሂደቱ ጥቂት ማውጋቱ ለአንባቢ ትክክለኛውን መረጃ ከማቀበል ባሻገር ጸሃፊው ለሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደግሙ አጋዥ እርምጃ ይሆናል፡፡
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ኢትዮጵያ ውስጥ የሙከራ ትግበራውን የጀመረው ከዛሬ አራት አመት በፊት በአማራ፣በትግራይ፣ በኦሮምያና በደቡብ  ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልላዊ መንግስታት  በሰኔ ወር 2003 ዓ.ም ነበር - በ 13 ወረዳዎች ፡፡  በእነኚህ ወረዳዎች የተጀመረው የሙከራ ትግበራ፤ ጠንካራና ደካማ ጎን እየታየ በተደረገ የማስፋፍያ ሥራ በአሁን ሰአት ይህ የሙከራ ትግበራ ወደ 198  ወረዳዎች አድጓል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ሂደቱ ከችግር የጸዳ ነበር ብለን ወገባችንን ይዘን አንሞግትም፡፡ የተወሰኑ ችግሮች እንደነበሩ መንግስትም ሆነ ሥራው የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት በትክክል ይረዳሉ፡፡ ግን ደግሞ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም መልክዐ - ምድራዊ ችግሮች ባሉባት ሀገር አዲስ የሆነን ነገር  መሞከር ቀርቶ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚታገዘው የናሳ ስፔስ ሺፕም ከስህተት የጸዳ ሊሆን እንደማይችል ለሁላችንም ግልጽ ይመስለናል፡፡
የሙከራ ትግበራው ያመጣውን ውጤት ከመዘርዘራችን በፊት የጤና መድህን ሥርዓትን በሃገራችን ለመተግበር ለምን አስፈለገ? የሚለውን መመለሱ ተገቢ ይመስለናል፡፡ ጸሃፊ ዮሃንስ ሰ. እንዳሉት ‹‹የህልም ዓለም ›› ለመፍጠር መንግስት በከንቱ ጊዜውንና ገንዘቡን ለማባከን ወይንስ የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት የሃገሪቱን የጤና ስርዓት ሌሎች ሃገሮች ወደሚከተሉት አቅጣጫ ለመምራት?
የጤና አገልግሎትን ማግኘት የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ይህ መብት እንዲከበር ደግሞ ሦስት ነገሮችን በሚዛናዊነት ሳይነጣጠሉ ማስኬድ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ሃብታም ከደሃ ሳይለይ ዜጎች ህመም ሲገጥማቸው አገልግሎት የሚያገኙበት መብት (Equity)፣ ሁለተኛ ዜጎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና አገልግሎት ( Quality Health Services )፤ ሦስተኛ አገልግሎቱን በጥራት መስጠት የሚያስችል የጤና ፋይናንስ ( Health Financing )፡፡ እነኚህ ሦስት ነገሮች የጤና አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት አንድም ሦስትም ነገሮች ናቸው፡፡
እነኚህን ሦስት ነገሮች ማንጸርያ አድርገን የሃገራችንን የጤና አገልግሎት ስንቃኝ፣ መንግስት ለሁሉም ዜጎች ጤናን ለማዳረስ ጠንክሮ የመስራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህን ለመፈጸም የጤና አገልግሎት በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ የጤና ተቋማትን በብዛት ከመገንባት ባሻገር በዘርፉ የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት ላይ ይገኛል፡፡ ሦስተኛዉና ዋናው የጤና አገልግሎቱ የሚመራበት ፋይናንስ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የጤና ፋይናንስ  ስንመለከት፣ 50 በመቶ የሚደጎመው ለጋሽ ሃገራት በሚሰጡን ድጋፍ ነው፡፡ ( አያድርገውና ይህ እርዳታ ድንገት ቀጥ ቢል ምን ያህል ምስቅልቅል እንደሚፈጠር መገመት አይከብድም)፡፡  የጤናው ዘርፍ የፋይናንስ ምንጭ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ከመንግስት ካዝና የሚገኘው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለጤና ዘርፍ ከሚውለው ጠቅላላ ወጪ 16 በመቶ  የሚሆነውን  ብቻ የሚሸፍን ነው፡፡ ቀሪው ደግሞ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት በመስጠት ከሚያገኙት ገቢ የሚገኝ ነው።
በእርዳታ ላይ የተደገፈ የጤና ፋይናንስ ይዞ እስከመቼ? … እስከመቼ በልመና ዜጎቻችን ይታከሙ?.... ለጋሾቻችን ፊት ያዞሩብንና እርዳታቸውን ያቆሙ ቀን ምን ይዋጠን?... መልሱ ቀላል ነው፡፡ ተጨማሪ የጤና ፋይናንስ አቅም መፍጠር!! ይህን ለማድረግ ደግሞ አዲስ የጤና ፋይናንስ ስርዓት ለሃገሪቱ ማስተዋወቅ - የጤና መድህን ስርዓትን፡፡
በዓለም ላይ የጤና መድህን ስርዓት ከእድርና ከዕቁብ ቅርጽ ተላቆ  አሁን ያለውን መልክ ለመያዝ ወደ 700 ዓመታት በፈጀ ሂደት ውስጥ እንዳለፈ ታሪክ ያወሳል፡፡ ዘመናዊው የጤና መድህን አባት ግን  ቻንስለር ኦቶቫን ቢስማርክ የተሰኘው የጀርመን ቻንስለር እንደሆነና  እ.ኤ.አ. በ1883 ዓ.ም ያወጣው ህግ መነሻ መሆኑን ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በቢስማርክ አርቃቂነት የተጀመረው የጤና ኢንሹራንስ፣ የተለያየ ቅርጽ ይዞ አተገባበሩም ከሃገራት፣ሀገራት እየተለያየ ዓለምን አዳረሰ፡፡ ዛሬ በተለያየ መልኩ የጤና ኢንሹራንስን ተግባራዊ ለማድረግ የማይፍጨረጨር ሃገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ የአፍሪካ ሀገሮችን ሁኔታ በምንመለከትበት ጊዜ ብዙዎቹ የምስራቅና የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ እንደወጡ ይከተሉት የነበረውን የጤና አገልግሎትበማሻሻል የጤና አገልግሎትን በፍትሀዊነት ለዜጎቻቸው ለማዳረስ የተለያዩ የጤና መድህን ዓይነቶችን በመንድፍ ተግባራዊ አድርገዋል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ሀገሮች መካከል ሩዋንዳ፤ ሴኔጋል፤ማሊ፤ኡጋንዳ፤ታንዛንያና፤ጋና ይገኙበታል። ሩዋንዳ የጤና መድህን ስልትን በመከተል እ.ኤ.አ እስከ 2007 ድረስ ከ9.5 ሚሊዮን ህዝቧ ውስጥ 5.7 ሚሊዮን የሚሆነውን በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በማካተት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች።
ሃገራችን ኢትዮጵያም  የጤና መድህን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ በሙከራ ደረጃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በሙከራ ደረጃ በአራት ክልሎች በ198 ወረዳዎች በመተግበር ላይ ትገኛለች። ይህም በመሆኑ በሀብታሙና በድሀው እንዲሁም ከፍተኛ የጤንነት ችግር ያለበት የጤንነት ችግር ብዙም በሌለበት መካከል መረዳዳትና፣ መደጋገፍ እንዲፈጠርና  ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት  እንዲሰፍን ምክንያት እየሆነ መምጣቱ  ታይቷል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሙከራ ትግበራው  ዜጎች የጤና አገልግሎት በሚሹበት ወቅት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ክፍያ በመቀነስ አባላትና ቤተሰቦቻቸው ህመም ባጋጠማቸው ወቅት ህክምና እንዲያገኙ የሚያበረታታና የጤና አገልግሎት አጠቃቀምን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው፡፡
ከዚህ ረገድ ካየነው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የሙከራ ትግበራ የተካሄደባቸው ወረዳዎች ካልተካሄደባቸው ጋር ሲነጻጸሩ የማህበረሰቡ የጤና አጠቃቀም ላይ መድህኑ ያመጣውን ለውጥ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ገለልተኛ በሆነ አማካሪ የተሰራውና ባለፈው ግንቦት ወር ለህትመት የበቃው የግምገማ ጥናት እንደሚያስረዳው የጤና መድህኑ በተተገበረባቸው ወረዳዎች የጤና አጠቃቀም ድግግሞሽ0.7 አድጓል፡፡ ይህም በሃገር አቀፍ ካለው አማካይ የጤና አጠቃቀም ( 0.34) አንጻር ሲታይ ትልቅ እድገት ነው፡፡
በአባላት ረገድም ካየነው እስከ ባለፈው ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም በአራቱም ክልሎች 1,344,055 ቤተሰቦች ወይም 6,504,146 ሰዎች አባል ሲሆኑ 2,214,557 ሰዎች ህክምና አግኝተው ወጪያቸው በመድህኑ ተሸፍኗል፡፡
እንግዲህ ይሄን ነው ጸሃፊ ዮሐንስ ሰ. ‹‹ የህልም ዓለም!›› በማለት ሊያጥላሉት የሞከሩት፡፡ አራት ዓመት ሙሉ የሚከሰቱ ድክመቶችን በማረም የጤና መድህኑን የሙከራ ትግበራ ከ 13 ወረዳ ወደ 198 ማድረስ ትግስትና እልህ አስጨራሽ ትግል እንጂ የ‹‹ህልም ዓለም›› የወለደው ቅዠት አለመሆኑን ያገኘነውና ያስመዘገብነው ውጤት ይመሰክራል፡፡
በስተመጨረሻ ዮሐንስ ሰም ሆኑ ሥለ ጤና መድህኑ የተሳሳተ አቋም ያላቸው ሰዎች እንዲገነዘቡልን የምንፈልገው ሃቅ፣ የሚሰጡን አስተያየት እንድንሻሻል ታስቦ ከሆነ ድክመታችንን በማረም የተሻለ የጤና ስርዓት በሃገራችን እንዲሰፍን ሌት ተቀን እንጥራለን፡፡ ህብረተሰቡ በጤና መድህን ሥርዓት ላይ ያለውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ በጋራ ለመስራት እንዲሁም መረጃ ለመለገስ በራችን ምንጊዜም ክፍት ነው፡፡ ይሄ ሳይሆን ቀርቶ በተሳሳተ መረጃ ህዝብን ለማደናገር መሞከርና ሥራን ማደናቀፍ ግን ወንጀል ነውና ተጠያቂ ሊያደርግም ይችላል፡፡
በተረፈ በመጪዎቹ አምስት አመታት ውስጥ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን በመላ ሃገሪቱ ለመተግበር መንግስት እንደሚሰራ ልናረጋግጥልዎ እንወዳለን፡፡ እርስዎም ‹‹ከህልም ዓለም ›› ትችትዎ ወጥተው እውነቱን ለማየትና ሃቁን ለመጻፍ እንደሚበቁ ሙሉ እምነት አለን፡፡
ከኢትዮጵያ የጤና መድህን
ኮሚኒኬሽንና ሞቢላይዜሽን ዳይሬክቶሬት

     ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሀብታም ጌታ አገልጋይ፤ ከቤት ጠፍቶ ወደ ዱር ይሄዳል። እዚያም አንድ ባዶ ዋሻ ያገኝና እዚያው ለመኖር ይወስናል፡፡ ሆኖም ገና አንድም ቀን ሳያድር የዚሁ ዋሻ ባለቤት የሆነው አያ አንበሶ ከች ይላል፡፡ አገልጋዩ ሰው በጣመ ደነገጠ፡፡ “አለቀልኝ!” ብሎ ተስፋ በመቁረጥ ካሁን አሁን ዘሎ ደቆሰኝ እያለ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ ሆኖ አያ አንበሶ ዘሎ ሰውዬው ላይ ሳይወጣ ቀረ፡፡ ሰውዬው ደርቆ ተገርሞ ያስተውለዋል፡፡
ይልቁንም ማጥቃቱን ትቶ ያባበጠ መዳፉን ወደ አየር ከፍ አድርጐ እያቃሰተ አሳየው። ሰውዬው ትኩር ብሎ ሲያይ አንዳች የሚያክል እሾክ ተሰቅስቆበታል፡፡ ስለዚህ ቀስ ብሎ እየሳበ ነቀለለት፡፡ የቆሰለውንም አሠረለት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁስሉ ሙሉ በሙሉ ዳነለት፡፡
አያ አንበሶ ምሥጋናው ወሰን የሌለው ሆነ፡፡ ስለሆነም ሰውዬውን ጓደኛ አደረገው፡፡ ዋሻውም ቤታቸው ሆነ፡፡
ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ ግን ሰውዬው ወደ ዘመዶቹ መሄድ ፈለገ፡፡ አያ አንበሶን ተሰናብቶ ወደናፈቃቸው ወዳጅ ዘመዶቹ ሄደ፡፡ ከሰው ጋር ሲቀላቀል ግን አንዳንድ ሰዎች ከጌታው ጠፍቶ መሄዱን አስታውሰው እጁን በገመድ አስረው ወስደው ለጌታው አስረከቡት፡፡
ጌታውም ለሌሎች መቀመጣጫ ይሆን ዘንድ በአደባባይ የትርዒት ሸንጐ ላይ ለአውሬዎች እንዲጣልና ህዝብ እንዲያየው አዘዘ፡፡ በዚያ የፍልሚያ ቀን አውሬዎች ሰውዬው ላይ ተለቀቁበት፡፡ ከነዚህ አውሬዎች መካከል አንድ ግዙፍ አንበሳ ይታያል፡፡ ያ አገልጋይ ሜዳው ላይ ተጥሎባቸዋል፡፡
ግዙፉ አንበሳ ቀድሞ ወደ ሰውዬው አመራ፡፡ “ደቆሰው በቃ!” ሰባበረው በቃ!” ይላል ህዝቡ፡፡
የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አንበሳው ሰውዬው እግር ሥር አጐንብሶ በፍፁም አክብሮትና ፍቅር ይተሻሸው ገባ! ደስተኝነቱ ፊቱ ይ ያበራል!ይህ አንበሳ የጥንቱ የዋሻ ጓደኛው አያ አንበሶ ነው!
ተመልካቹ ሁሉ፤ “ሰውዬው ምህረት ሊደረግለት ይገባል!” እያለ ጮኸ!
የከተማው ከንቲባ ከአውሬ የዚህ ዓይነት ምሥጋናና ደግነት በማየታቸው ተደስተው፣
“ሁለቱም በነፃ ይለቀቁ” ብለው አወጁ!
*   *   *
ከአንበሳ መዳፍ እሾክ የመንቀል ያህል ደግነት ለመሥራት መጣር ትምህርትነቱ ኃያል ነው፡፡ አንበሳና ሰው የመቀራረብና አብሮ የመኖር ደረጃ ሲደርስ፣ ሰውና ሰውማ ማንም ይሁን ማን ተስማምቶ መኖር ሊያቅተው አይገባም፡፡ መቻቻል በቁም ትርጉሙ ስንወስደው የማይስማሙ ወይም የሚቃረኑ ኃይሎች፣ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ ምንም ያህል ተፃራሪ ቢሆኑ የሀገር ጉዳይን
አማክለው ካዩት፤ የጋራ መድረክ አያጡም፡፡ ባለሙያውና ፖለቲከኛው የጋራ ቦታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ፖለቲከኛውና ፖለቲከኛው (የተለያየ ፓርቲ አባል ቢሆኑም) የጋራ መቻቻያ ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ ከመቀራረብ መደፋፈር መወለድ የለበትም፡፡ ተባብሮ አብሮ መሥራት እንጂ ምሁሩን ማግለል ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ግምት ውስጥ ማስገባት በዓለም ታሪክ የታዩትን ታላላቅ ስህተቶች
ከመፈፀም ያድነናል! ለጠብ አለመቸኮል ተገቢ ነው፡፡ “ወዳጅና ወዳጅ የተጣሉ እንደሆን መታረቅም አይቀር፣ እንደ ጥንቱም አይሆን” የሚለውን ግጥምም አለመዘንጋት ነው!
ገሀድ ዕውነት በአደባባይ ሲወራ ለመስማት አብዛኛው ህዝብ ይናፍቃል፡፡ ብዙ ከመፈንደቅና ያለልክ የሀዘን ማቅ ከመልበስ ይሰውረን!
አንዳንድ ምሁራን የለውጥ እርምጃ (ተሃድሶ) (Reformism) ወደ አብዮት ያመራል ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ “አብዮት እንዳይፈጠር ታኮ ይሆናል” ይላሉ፡፡ እንደየአገሩ ልዩ ባህሪ ግብዓቶቹ ወሳኝነት አላቸው የሚሉት ወገኖች ደግሞ እንደየሁኔታው ሁለቱን አካሄዶች
ያሞግሷቸዋል ወይም ይሽሯቸዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ፀሐፊው ሀንቲንግተን እንደሚለው፤ ከተሀድሶ እርምጃ ጋር የሚያያይዙት የአብዮት ችግሮች አንድም የምሁር መገለል፣ አንድም የገበሬ መከፋት ናቸው፡፡ በሀገራችን የአቀባባይ ከበርቴዎችና የቢሮክራሲ ደላሎች አደጋ ብዙ ሊሸሸግ ቢሞከርም ዛሬ አደባባይ መውጣቱ ዘግይተንም ቢሆን ዐይናችንን መግለጣችንን ይጠቁማል፡፡ እንግዲህ ኔትዎርኮቹን ሁሉ መፈተሽ ነው
ቀሪው ጐዳና! ስብሰባዎቻችን የተሞሉት “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ” በሚለው ስላቅ ከሆነ መንፈሳቸው አስቂኝ ይሆናል፡፡ ሙሰኛው የፀረ ሙስና ተናጋሪ ሲሆን ምፀቱ አስገራሚ ነው፡፡ የትላንቱን ታሪክ ከዛሬው ሁኔታ የሚያላትመው ደስኳሪ ከውይይት ይልቅ ድንፋታን የሙጥኝ ሲል፤ “ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?” ብሎ መሸሞር ግድ ይሆናል፡፡ ሀቅ አይነቀን፡፡ ግልጽነት አይመመን፡፡ ወገናዊነትን፣
ዘረኝነትን፣ ፅንፈኝነትን፣ ትምክህተኝነትን እናስወግድ ካልን ከልብ እናስወግድ!
በዱሮው ዘመን፤ “ጉዟችን ረዥም፣ ትግላችን መራራ” ይባል ነበር፡፡ መንፈሱ ለየቅል ቢሆንም፤ የአሁኑም ዘመን ትግል መራራና ረዥም መሆኑ አልቀረም፡፡ “ለዳገት የጫንከው ሜዳ ላይ እንዳይደክም፣ ማልዶ መነሳት!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ 

“ዲሞክራሲያዊ ውይይት ከሌለ አገሪቱ እንደአገር አትቀጥልም”

    ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ “ከጋዜጠኞች የሚሰነዘርብኝን ትችት አልፈራም፤ ነጻ ሚዲያ ለዲሞክራሲ ግንባታው ሂደትና ለልማት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው” ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ትናንት ዘገበ፡፡
“ፍጹም እንዳልሆንን እናውቃለን፤ በመሆኑም ከማንኛውም ጋዜጠኛ የሚቀርብብንን ትችት ለመቀበል ዝግጁ ነን” ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቢቢሲ የአፍሪካ አገልግሎት አዘጋጅ ሜሪ ሃርፐር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
“በዚህች አገር ውስጥ የማህበራዊ ሚዲያውን የመረጃ ፍሰት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው በስፋት የሚጠቀም ንቁና ወጣት የህብረተሰብ ክፍል እንደመኖሩ፣ ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ልውውጥና ውይይት በሌለበት ሁኔታ አገሪቱ እንደ አገር መቀጠል አትችልም፡፡ ከዚህ አንጻር በትክክለኛው ጎዳና ላይ እንገኛለን ብለን እናምናለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፡፡
ባለፈው አመት ታስረው የነበሩት አንዳንድ ጦማርያንና ጋዜጠኞች፣ “እውነተኛ” ጋዜጠኞች” አልነበሩም፤ ታሳሪዎቹ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የታሰሩትም በሙያቸው ሳይሆን መንግስትን ለመናድ ከሚፈልጉ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ማስረጃ በመገኘቱ ነው ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል፡፡
“ጋዜጠኞች በዚህች አገር ውስጥ የሚሰሩትን ስራና የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ ማምታታት እንደሌለብን ግልጽ ሊሆንልን ይገባል”

ሲሉም አክለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፡፡