Administrator

Administrator

 ጊዜ ባርና ሬስቶራንት ዛሬ ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ ልዩ የሙዚቃ ድግስ ማስናዳቱን ገለፀ። በዚህ የሚዚቃ ድግስ ድምፃዊ ታረቀኝ ሙሉ (በባይተዋር ጎጆ)፣ አዲስ ጉልሜሳ (የማህሙድ)፣ አብነት ደምሴ (የማሪቱ) እና ዋሲሁን ረታ (የሙሉቀን) ድምፃዊያኑ ከማህሌት ባንድ ጋር በመጣመር በቀጥታ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ዳዊት ፍሬው ሀይሉ ሳክስፎን እንደሚጫዎትም የጊዜ ባርና ሬስቶራንት ሃላፊዎች ገልፀዋል።
በዚህ ልዩ ምሽት ከወዳጅ ዘመድ ጋር ቦሌ ማተሚያ ቤት በሚገኘው ጊዜ ጀርባ ባርና ሬስቶራንት መጥተው በመታደም አስደሳች ጊዜ  እንዲያሳልፉ ግብዣ የቀረበ ሲሆን የሙዚቃ ድግሱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድና ቀድመው የመጡ ብቻ እንደሚስተናገዱ ለማወቅ ተችሏል። በጢስ አባይ የኢኮኖሚ ልማት፣ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅት አዘጋጅነት የተሰናዳው የመጀመሪያው ዙር ሀገር አቀፍ የቢዝነስ ማሻሻያ ገበያ ትስስር መፍጠሪያ ዎርክ ሾፕ ባሳለፍነው ሳምንት በጊዮን ሆቴል ተካሄደ፡፡ አማካሪ ድርጅቱ፤ በዎርክሾቱ በሆቴልና ማኒፋክቸሪንግ ዘርፎች መነሻነት የተጠናው ቅድመ ዎርክ ሾፕ፣የኢትዮጵያ ገበያ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ አስቸኳይ ፖሊሲ ሊወጣለት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በአማካሪ ድርጅቱ የኦኮኖሚ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪና የወርክሾፑ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መንገሻ አበበ ሞሴነህ፤ የአሰራር ምልከታ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም 50 ሆቴሎችን፣50 ኢንዱስትሪዎችንና 50 ተጠቃሚዎችን በአላማ ተኮር የናሙና ዘዴ ያጠኑትን የማርኬቲንግ ጥናት በወርክሾፑ ያቀረቡ ሲሆን በምርት እጥረት፣በምርት ጥራት መጓደል፣ ኢኮኖሚያዊ ባልሆነ የምርት ዋጋ ጭማሪና መሰል ችግሮች ሳቢያ ፈተና ውስጥ የገባውን የኢትዮጵያ ገበያ፣ የህዝብ ብሶት ተከትሎ ከሚመጣ የኢንስፔክሽን እና የሬጉሌሽን የቁጥጥር ሥራ ይልቅ የሀገሪቱን የንግድና ኢንቨስትመንት አቅም መሰረት ያደረገ፣ በአመራረትና በግብይት ሂደት የምርት ጥራትን ያመለከተ፣የምርት ስርጭት ፍትሀዊነት፣ከባቢያዊና የፍጆታ ፍላጎትን፣ ፍትሃዊ የመሸጫ ዋጋ ደረጃንና የማርኬቲንግ ማበረታቻ ሥርዓትን የሚያመለክት የማርኬቲንግ ፖሊሲ አለመኖሩ ገበያው ቅጥ እንዲያጣ ማድረጉን በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡
በተቀያያሪ የገበያ ፍሰት ውስጥ በመሆናችን ነው ከምርትና አገልግሎት የምናገኘው እርካታም በየጊዜው እየተቀያየረና በኑሮ ውድነት እየተለበለብን ሲሉ የጥናቱ አካል የሆኑ ተጠቃሚ የማህበረሰብ ክፍሎች መናገራቸውም በጥናት ግኝቱ ተካቷል፡፡


  ባለቤትነቱ የቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቱር ኤንድ ትራቭል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሆነውና 300 ሚ.ብር እንደወጣበት የተነገረለት “ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል” የተሰኘ ባለ  ኮከብ ሆቴል፣ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡
በተለምዶ አትላስ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው ሆቴሉ በ500 ካ.ሜ ላይ ያረፈ ሲሆን 40 ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች፣ ለትልልቅና ለመለስተኛ ስብሰባ የሚሆኑ አዳራሾች፣ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ ባርና ሬስቶራንቶች እንዳሉት የተናገሩት የሆቴሉ ሀላፊዎች፤ ለ100 ሰዎች የስራ ዕድል መክፈቱንም ጠቁመዋል፡፡
ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቱር ኤንድ ትራቭል፤ በአስጎብኚነትና በጉዞ ወኪልነት፣ በአስመጪነትና በላኪነት፣በትራንስፖርት ዘርፍ፣ህንፃ በማከራየትና በመሸጥ እንዲሁም በፋብሪካ አገልግሎት ተሰማርቶ የሚገኝ አገር በቀል ድርጅት መሆኑም ታውቋል ኩባንያው በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች 10 ሪዞርቶችን የመገንባት እቀድ እንዳለውም የሆቴሉ ባለቤት ገልፀዋል፡፡ በሰበታ ከተማ ቀበሌ 04 የሚገኘው “ቱሉ መገርሳ ኢንተርናሽናል ሆቴል” ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት እንደሚመረቅ ወጣቱ ባለሃብት አቶ ጅሩ መገርሳ ገለፁ፡፡ በቅርቡ ከሌላ ባለ ሃብት በ150 ሚ.ብር የተገዛውና ለእድሳቱ 100 ሚ.ብር የተመደበለት ሆቴሉ ከ5 ሺህ ካ.ሜ በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን 54 አልጋዎች እስከ 2000 የሚደርስ ሰው የሚይዙ  የስብሰባና የሰርግ አዳራሾች፣ ስቲምና፣ሳውና ባዝ፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖች፣ የመዋኛ ገንዳ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሆቴል ሊያሟላ የሚገገባውን  ያሟላ ነው ተብሏል፡፡ አሁን በሙሉ አቅሙ ስራ ሳይጀምር 182 ሰራተኞችን ቀጥሮ  የሚያሰራው ይሄ ሆቴል፤ እድሳቱ ሲጠናቀቅና በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር፣ የሰራተኞቹን ብዛት ወደ 265 እንደሚያሳድግ ባለሃብቱ፣ የሆቴሉ ማናጀርና የባለሃብቱ አማካሪዎች ምረቃውን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ሆቴሉ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ስጋ ቤትና አዳራሽ ፣የልጆች መጫወቻ፣ ድራፍት ቤት፣የኦሮሞ የባህል ምግብ አዳራሽ እየተሟሉለት ነው ተብሏል፡፡ በቀጣይም አራት ደረጃውን የጠበቁ ሬስቶራንቶች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ በምረቃው ሳምንት ከ15-20 ሺህ ሰው ይታደማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት የሆቴሉ ሃላፊዎች፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለዘጠኝ ቀናት መራዘሙን በያንዳንዱ ቀናት ከ1500-2000 ሰዎች ብቻ እንደሚያስተናግድ ተገልጿል፡፡


  - የ140 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ለሁለት ይካፈላሉ
         - የፍቺው መንስኤ አልታወቀም

               ቢሊየነሮቹ ቢል ጌትስና ሜሊንዳ ጌትስ ባለፈው ሳምንት ፍቺ (ሜይ 3) ለመፈፀም መወሰናቸውን ይፋ ሲያደርጉ ብዙዎች ተደናግጠዋል። ለ27 ዓመታት የዘለቀው ትዳራቸው  ሰላማዊና የተረጋጋ እንደነበር ይነገራል። በቢዝነስ ስራቸውና በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴያቸው  ስኬትና ዕውቅና ተቀዳጁት ጥንዶቹ ሦስት ልጆችንም አፍርተው ለቁም ነገር አብቅተዋል- አሁን የኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው። ጥንዶቹ የ45 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያፈሩ ሲሆን በስማቸው የሚንቀሳቀስ የ50 ቢሊዮን ዶላር ፋውንዴሽን መስርተዋል- የዛሬ 20 ዓመት። ይሄ ሁሉ ግን ትዳራቸውን ከፍቺ አልዳነም። ፍቺውን ተከትሎም የ140 ቢ.ዶላር ሃብት ክፍፍል እንደሚፈጸም ታውቋል። ፍቺው “የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንን” የወደፊት ዕጣ ፈንታን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገባው ተነግሯል።
ቢል ጌትስና ሚሊንዳ ጌትስ የተዋወቁት እዚያው ማይክሮሶፍት ውስጥ ነው። የማይክሮሶፍት መስራቹ ቢል ጌትስ፤ ያኔ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበረ ሲሆን ሚሊንዳ ደግሞ የመልቲ ሚዲያ ምርቶች ማርኬቲንግ ማናጀር ነበረች። እ.ኤ.አ በ1987 የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት ጥንዶቹ፤ በ1994 ዓ.ም በሃዋይ ደሴት ላይ ጋብቻውን ፈፅመዋል። በሲያትል የዋሽንግቶን ሃይቅ ዳርቻ ላይ የተንጣለለ ቪላ ውስጥ የሚኖሩት። በእርግጥ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ሌሎች መኖሪያ ቪላዎች እንዳላቸውም ይታወቃል።
እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተመሰረተው “ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን”፤  በአፍሪካና ሌሎች ታዳጊ አገራት የማህበረሰብ ጤና፣ የአየር ንብረት ለውጥና በትምህርት ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። ባለፉት 20 ዓመታት ባደረገው እንቅስቃሴም የብዙዎችን ህይወት በመለወጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በዓለም ግዙፉ የግል የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመሆን በቅቷል።
ሜሊንዳ ጌትስ “ፓይቮታል ቬንቸርስ” የተሰኘ የኢንቨስትመንት ተቋም በ2015 በግሏ የመሰረተች ሲሆን ተቋሙ በአሜሪካ የሚገኙት ሴቶችና ቤተሰቦችን ለመደገፍ እንዲሁም ማህበራዊ ግስጋሴን ለማምጣት አልሞ የሚሰራ ነው ተብሏል።
ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ጥንዶቹ ፍቺ ለመፈጸም መወሰናቸውን ባለፈው ሜይ 3 ይፋ ሲያደርጉ፤ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር መግለጫ፤ “በቀጣዩ የህይወታችን ምእራፍ ጥንዶች ሆነን አብረን መቀጠል እንችላለን ብለን አናምንም” ብለዋል። ሜሊንዳ ጌትስ በበኩሏ፤ “ይሄ ትዳር ሊጠገን በማይችል ሁኔታ ፈርሷል” ብላች- በፍቺ ማመልከቻዋ ላይ።
“ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል” እንደዘገበው፤ የቢሊየነሮቹ ትዳር ድንገት አይደለም ለፍቺ የበቃው። ሚሊንዳ ጌትስ  ከ2019 ጀምሮ ፍቺ ለመፈጸም የተለያዩ ጠበቃዎችን ስታማክር ቆይታለች። ለዚህ ውሳኔዋ ያበቃት ደግሞ ቢል ጌትስ፣ በወሲብ ንግድ ተከሶ ከተፈረደበት ጄፍሪ ኢፒስቲን ጋር ግንኙነት እንዳለው ከተገለፀ በኋላ ነው ብሏል- ጋዜጣው።  ኒውዮርክ ታይምስ በኦክቶበር 2019 ባቀረበው ዘገባ፤ ቢል ጌትስ ከ2011 ጀምሮ ከኢፕስቲን ጋር ለበርካታ ጊዜያት መገናኘቱን ጠቁሟል። ቢል ጌትስ በበኩሉ፤ ከኢፕስቲን ጋር ምንም ዓይነት የቢዝነስም ሆነ የወዳጅነት  ግንኙነት እንደሌለው አስተባብሏል- በወቅቱ።
ጥንዶቹ ፍቺያቸውን ይፋ ባደረጉበት ዕለት፣ ቢል ጌትስ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የአክስዮን ድርሻ ለባለቤቱ ማዛወሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሃብት ክፍፍሉ አካል ይመስላል።
ቢሊየነሮቹ ጥንዶች የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ባሉት ጊዜያት  በሥራ ተጠምደው ነው የከረሙት። ፋውንዴሽኑ ኮቪድ -19ን ለመከላከል የሚደረገውን ዓለማቀፍ ጥረት ለመደገፍ 1.75 ቢሊዮን ዶላር የለገሰ ሲሆን በኮቪድ-19 ክትባቶች ጥናትና ምርምር ላ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተዘግቧል።
እንግዲህ የሁለቱ ታዋቂ የዓላማችን ቢሊየነሮች ፍቺ አይቀሬ ከሆነ ዘንዳ ቀሪው በከፍተኛ የህግ ባለሙያዎች የታገዘ የሃብት ክፍፍል ይሆናል። ጥንዶቹ ሃብታቸውን እኩል የሚካፈሉ ከሆነም ሚሊንዳ ጌትስ በዓለማችን ሁለተኛዋ የሴት ቢሊየነር እንደምትሆን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በክፍፍሉ የ70 ቢ.ዶላር ገደማ ሃብት ይደርሳታል። በዚህ መሃል የሚነሳው ጥያቄ ታዲያ የቢልና ሜሊንዳ ሶስት ልጆችስ ምን ያህል ገንዘብ በውርስ ያገኛሉ የሚለው ነው።
በነገራችን ላይ ሶስቱም ልጆቻቸው ነፍስ ያወቁ የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው። እነሱም የ25 ዓመቷ ጄኒፈር ካታሪን ጌትስ፣ የ21 ዓመቱ ሮሪ ጆን ጌትስ እና የ19 ዓመቷ ፎቢ አዴሌ ጌትስ በመባል ይታወቃሉ።
በአሁኑ ወቅት የዓላማችን አራተኛው ቢሊየነር እንደሆነ የሚታወቀው ቢል ጌትስ በተደጋጋሚ በሰጠው መግለጫ፤ አብላጫውን የሃብቱን ድርሻ የሚሰጡት ለቤተሰቡ ፋውንዴሽን መሆኑን አስታውቋል። ልጆቻቸው  ከሃብቱ የሚደርሳቸው 10 ቢሊዮን ዶላር ብቻ  ነው ተብሏል።
እ.ኤ.አ በ2017 ቢል ጌትስ ለልጆቹ ለምን ከፍተኛ ገንዘብ በውርስ እንደማይሰጥ አስረድቷል። “ለልጆች ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብቱን ማውረስ ውለታ አይደለም። የራሳቸውን የህይወት መንገድ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ያበላሻል።” በማለት።
የቢሊየነሮቹ የሃብት ዝርዝር
-  ዋሺንግተን ሃይቅ ደርቻ የሚገኝ የተንጣለለ
   የመኖሪያ ቪላ-65 ሚ.ዶላር
- በፍሎሪዳ፤ ዌሊንግተን የሚገኝ መኖሪያ ቤት-
   55 ሚ.ዶላር
- በካሊፎርኒያ፤ ኢንዲያን ዌልስ የሚገኝ መኖሪያ
   ቤት-1 ሚ.ዶላር
- በማዕከላዊ አሜሪካ ቤሊዜ የሚገኝ የግል
  ደሴት- 25 ሚ.ዶላር
- ቅንጡ የስፖርት መኪናዎች ስብስብ
   - 650 ሺ   ዶላር
- የስነ-ጥበብ ስብስብ (የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ
   ስራዎችን ጨምሮ)- 130 ሚ.ዶላር
- ካስኬድ ኢንቨስትመንት (ኩባንያ) -29.9
   ቢ.ዶላር
- ዲሬ ኤንድ ካምፓኒ (አክስዮን)- 11.9 ቢ.ዶላር
- የካናዳ ብሔራዊ የባቡር መስመር (አክስዮን)-
   11 ቢ.ዶላር
- ዲያጎ (አክስዮን)- 1.6 ቢ.ዶላር
- ማይክሮሶፍት (አክስዮን) - 26.1 ቢ.ዶላር
የዓለማችን ሁለቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ቢሊየነሮች ፍቺ  የዓለማቀፍ ሚዲያዎች ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ነው የሰነበተው። በተለይ ደግሞ ጥንዶቹ ፍቺውን ይፋ ከማድረግ ባለፈ ምክንያታቸውን ለመግለፅ አለመፍቀዳቸው ሁሉም የየራሱን ግምትና መላ ምት እንዲሰጥ አስገድዶታል። የጥንዶቹ ትዳር ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ መዝለቁና የሁለቱም ባለትዳሮች ዕድሜ ከ50 ዓመት ያለፈ መሆኑ ለብዙዎች ፍቺውን እንቆቅልሽ አድርጎባቸዋል። የማይክሮሶፍት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ኩባንያውን የመራው ቢልጌትስ፤ በ2009 ዓ.ም ከዋና ሥራ አስፈፃሚነቱ የለቀቀ ሲሆን ዓምና ደግሞ ከቦርድ ሊቀ መንበርነቱ በፈቃዱ አስረክቧል። ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ በአሁኑ ሰዓት ፋውንዴሽንን በሊቀ መንበርነት እያስተዳደሩት ይገኛሉ። የጡረታ ዘመን ሥራቸው ያደረጉትም ይመስላል።
ጥንዶቹ በአሁኑ ሰዓት ይህ የቤተሰቡ ፋውንዴሽን ከፍቺው በኋላ ይቀጥላል ወይ የሚለው ጉዳይ ለብዙዎች ጥርጣሬ  የፈጠረ ቢሆንም ጥንዶቹ ግን ፋውንዴሽኑን በተመለከተ ምንም የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር ነው የገለፁት። ግን ግን ጥንዶቹን ለፍቺ ያበቃቸው ምክንያት ምን ይሆን?  በመሃላቸው ገብቶ ሰይጣን ቢገባ ነው? (የፈረንጅ ትዳር ውስጥ ሰይጣን አይገባም እንዴ?!)


 "--በርካታ አርአያ የሆኑኝ ሰዎች ቢኖሩም፣ ከሁሉም የላቀችው አርዓያዬ ግን እናቴ ናት። ዛሬም ድረስ የምመራባቸውን የሕይወት መርሆዎች የቀሰምኩት ከሷ ነው። ከዋና ዋናዎቹ መካከልም፤ ሁሉንም ሰው እኩል ማክበር የሚለው መርህ ትልቁ ነው።--"
        ባለፈው ሰኞ ለሊት በኮሮና ሳቢያ ህይወታቸውን ባጡት  ወ/ሮ ዘሚ የኑስ የተሰማንን ሀዘን እየገለፅን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መፅናናትን እንመኛለን፡፡
      ዝግጅት ክፍሉ

             የተወለድኩት ጥር 9 ቀን 1951 ዓ.ም አዲስ አበባ ነው። አባቴ ትጉህ ሠራተኛ ነበር። ልጅነቱን በእረኝነት ያሳለፈው አባቴ፤ እውቅ የወንዶች ሙሉ ልብስ ሰፊ ነበር። ገጠር የተወለደችው እናቴ፤ የ9 ዓመት ልጅ ሳለች ነው የተዳረችው። ሁለቱም ወላጆቼ የትምህርት ቤትን ደጃፍ አልረገጡም። ነገር ግን እጅግ አስተዋዮች ነበሩ።
በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ለወጣቶች አስጊ የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመፍራት፣ በ17 ዓመቴ ወደ ጣልያን ተሰደድኩ። በጣልያን ትምህርት እየተማርኩ ጎን ለጎንም፣ በአገሪቱ ማዕከላዊ የስደተኞች ፅሕፈት ቤት ውስጥ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ። ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በጥምረት በሚንቀሳቀሰው ፅሕፈት ቤት ውስጥ ሥሰራ፣ በጣልያን በኩል ወደ ሌሎች አገራት የሚሻገሩ ብዙ ሺ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችን አስተናግጃለሁ።
በ1973 ዓ.ም ለአጭር ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ  በመጣሁ ጊዜ፣ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ “ፀረ-አብዮተኞች ከአገር እንዲኮበልሉ እረድተሻል" በሚል በመወንጀል፣ ጥቁር መዝገብ ውስጥ አሰፈረኝ። እንደመታደል ሆኖ ግን ለሁለተኛ ጊዜ  በማምለጥ፣ አሜሪካ ገባሁኝ፡፡ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስም ለ14 ዓመታት ያህል በስደት ኖርኩኝ።
እዛም እያለሁ በመዋቢያ ንጥረ ነገሮችና በአጠቃቀማቸው ዙሪያ ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ፣ በፊልም ማዕከልነቷ በምትታወቀው ሆሊውድና በቤቨርሊ ሂልስ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ቦታዎች፣ በቆዳና ፀጉር እንክብካቤ ላይ በማተኮር በሙያዬ እሰራ ነበር። ስራው በዘርና በባህል፣ በአስተዳደግና በኑሮ ደረጃ እጅጉን ከሚለያዩ ብዙ አይነት ሰዎች ጋር በማገናኘት፣ የሕይወት ትምህርት እንድቀስም እድል ሰጥቶኛል።
ወታደራዊው መንግስት መውደቁን ተከትሎ፣ ለራሴ በገባሁት ቃል መሰረት፣ በ1983 ዓ.ም ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። በስራ አጥነት ተስፋ የቆረጡ ብዙ ወጣቶችን ስመለከት፣ ልቤ በሃዘን ተሰበረ። ይሄኔ ነው ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልዬ በመምጣት፣ ወጣቶችና ህፃናት ላይ በማተኮር፣ ለምወዳት ሀገሬ የድርሻዬን ለማበርከት የወሰንኩት። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ በኋላ፣ የስራ እድል ለመፍጠርና የሙያ ክህሎቴን ለወገኖቼ ለማካፈል በማሰብ፣ በሀገሪቱ ፈቃድ የተሰጠው የመጀመሪያውን የውበት ማሰልጠኛ ት/ቤት ከፈትኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ በኒያና የውበትና ሞዴሊንግ ት/ቤት፣ ከ6 ሺ በላይ ወጣት ሴቶችና ወንዶችን አሰልጥኜ አስመርቄያለሁ።
የውበት ት/ቤቱ፣ የማስተምርበት ብቻ ሳይሆን የምማርበትም ቦታ ነው ማለት እችላለሁ። እንዴት? ቢባል፣ የተለያየ ህይወትን አልፈው ከሚመጡ ብዙ ተማሪዎች ጋር ስለምገናኝ፤ ስለ ወጣቶች ኑሮ፣ ስለ ፍላጎቶቻቸውና ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ጥልቅ እውቀት አግኝቼበታለሁና፡፡ በውበት ሙያ ሰልጥነው ለመስራት የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ ገንዘብ ከፍለው ለመሰልጠን አቅም አልነበራቸውም። ይሄን በማስተዋል መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነጻ የትምህርት እድል አመቻቸሁ። ነፃ የትምህርት እድሉ፤ በአብዛኛው ተገድደው በወሲብ ስራ፣ በቤት ሰራተኝነትና በቀን ስራ ተሰማርተው ለነበሩ ወጣት ሴቶች በእጅጉ ጠቅሟል። ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን፤ ሰብእናቸውን የሚያበለጽግና ተደብቆ የቆየ የግል ዝንባሌያቸውን የሚያዳብር፤ እንዲሁም አኗኗራቸውን የሚቀይርና በራስ የመተማመን መንፈሳቸውን የሚያሳድግ የሕይወት ክህሎት ስልጠና ለመስጠት በትጋት ሰርቻለሁ። ዛሬ አብዛኛዎቹ ወጣቶች በውበት ሳሎኖች ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ሆኑ የተወሰኑት ደግሞ የራሳቸውን የውበት ሳሎኖችና ስፓዎች ከፍተዋል።
በዚህ መሃል ግን፣ ትንሹ ልጄ የኦቲዝም ችግር እንዳለበት በባለሙያ ተነግሮኝ፣ ከባድ ፈተና ውስጥ ገባሁ።። ያልወሰድኩት ት/ቤት የለም። ሁሉም ግን “የተለየ ባህሪ አለው” እያሉ በየተራ አሰናበቱብኝ፡፡ ይሄኔ ነው የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ህፃናት ያሏቸው ወላጆች፣ የሚጋፈጧቸውን ፈተናዎች በቅጡ የተገነዘብኩት። ኦቲዝም እንደ ጤና ችግር ሳይሆን እንደ እርግማን እየተቆጠረ፤ በርካታ ህፃናት “አንዳች ነገር ተጠናውቷቸዋል” በሚል በሰንሰለት ታስረው፣ ጨለማ ውስጥ እንደሚወረወሩ አስተዋልኩ። አንዳንዶቹማ በቤተሰባቸውም ጭምር  ይገለላሉ።
በኢትዮጵያ የኦቲዝም ችግር ያለባቸውን ህፃናት የማስተናገድ አቅም ያለው ት/ቤት ፈልጌ ሳጣ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረብኝ። ልጄን ይዤ ወደ አሜሪካ ብሄድ፣ መሰል ት/ቤቶችን እንደ ልቤ እንደማገኝ አውቃለሁ። ሆኖም በመሄድና እዚህ በመቅረት መሃል ብዙ ዋለልኩኝ። ከሁሉም በፊት ከገባሁበት ከባድ ውዥንብርና ተስፋ መቁረጥ ወጥቼ፣ ከእውነታው ጋር ለመጋፈጥ ቆርጬ መነሳት ነበረብኝ። ከዚያም ወደ አሜሪካ የመሄዱን ነገር እርግፍ አድርጌ ተውኩት። ምንም እንኳን ለልጄ የሚሻለው አሜሪካ ቢሆንም፣ እሱን ይዤ ስሄድ፣ እዚህ ያሉ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ህጻናት፣ የህሊና እረፍት እንደማይሰጡኝ አሰብኩኝ። እናም እዚሁ ሀገሬ ላይ ሆኜ፣ ህብረተሰቡን ስለ ኦቲዝም ማስተማርን፣ የሕይወት ዓላማዬ አድርጌ ተነሳሁ። ልጄንና ተመሳሳይ የጤና እክል ያለባቸውን ህፃናት ለመርዳትና የወላጆችን በተለይም የእናቶችን ሸክም ለመጋራት በቁርጠኝነት ወሰንኩ።
በኢትዮጵያ ስለ ኦቲዝም ግንዛቤ የመፍጠር ጉዞዬን የጀመርኩት፣ ከውበትና ፋሽን ሙያ ጋር በተያያዘ ለጋዜጠኞች በምሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ላይ፣ እግረ መንገዴን ስለ ኦቲዝም በመናገር ነበር። ኦቲዝምን የተመለከቱ መረጃዎችን (ምልክቶቹን፣ ተፈጥሮአዊ ሁኔታውን፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎቹን) ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት ፣ የተለያዩ ሚዲዎችን እጠቀም ነበር። በዚህ መንገድ ጉዳዩ በስፋት እየታወቀ መጣ። ነገር ግን ግንዛቤ መፍጠር ብቻውን በቂ አልነበረም። በ1994 ዓ.ም ጆይ የኦቲዝም ማዕከልን ከፈትኩ። ጆይ የኦቲዝም ማዕከል፣ በኢትዮጵያ የኦቲዝም ችግር ያለባቸውን ህፃናት ተቀብሎ የሚያስተናግድ የመጀመሪያው የኦቲዝም ማዕከል ነው። ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ከተጋፈጥናቸው ትላልቅ ፈተናዎች መካከል፣ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረትና የገንዘብ አቅም ውስንነት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስለ ኦቲዝም ያለኝን እውቀትና ግንዛቤ ለማስፋት ጥረት ማድረግ ነበረብኝ። በምርምርና ከወላጆች የድጋፍ ሰጪ ቡድን ጋር በሚደረግ የተሞክሮ ልውውጥ ብዙ ግንዛቤ አግኝቻለሁ። ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሃገር ባለሙያዎች፣ ኦቲዝም ተኮር መረጃዎችን ለማግኘት ብዙ ተግቻለሁ። በበርካታ ሀገራት በኦቲዝም ዙሪያ የሚሰጡ ወርክ-ሾፖችንና ስልጠናዎችን እያሰስኩ ተሳትፌያለሁ። እነዚህም ስልጠናዎች፣ ስለ ኦቲዝም ያለኝን እውቀትና ግንዛቤ በቅጡ አጎልብተውልኛል። እኔም ያገኘሁትን እውቀት ለማዕከሉ ሰራተኞች በማጋራት፣ አንድ ፕሮግራም ለመቅረጽ በቃን። ፕሮግራሙ የልጆቹን የየግል ፍላጎት በማወቅና በመለየት፣ ለእያንዳንዳቸው ተስማሚ የሆነ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ነው።
በተለይ “አቡጊዳ ፎነቲክስ” በሚል የፈጠርኩት አዲስ የቋንቋ ስርዓተ ትምህርት፣ ውጤታማ በመሆኑ በእጅጉ አስደስቶኛል። በግዕዝ ፊደላት ላይ ተመርኩዞ የተቀረፀው ስርዓተ ትምህርቱ፤ ሀገር በቀል እውቀትና መሳሪያዎችን ከድምፅ ልሳኖች (ፎነቲክስ) ጋር በማቀላቀል የሚያቀርብ ነው። ፕሮግራሙ ተማሪዎች የመንጋጋ ጡንቻዎቻቸውን እንዲያንቀሳቅሱ፣ ድምጾችንና ቃላትን እንዲፈጥሩና እንዲያወጡ እንዲሁም ቃላትን በመገጣጠም ዓረፍተ ነገሮችን መስራት እንዲችሉ የሚያግዛቸው ሲሆን ትኩረታቸውን ለመሰብሰብ፣ አቅማቸውንና የማሰብ ክህሎቶቻቸውን ለማዳበርም ይረዳቸዋል።
ይህንን ፕሮግራም ከጀመርን ወዲህ የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ህፃናት፣ የማንበብና የመፃፍ ክህሎት ላይ አስደናቂ መሻሻል አይተናል። የ”አቡጊዳ ፎነቲክስ” ፕሮግራም መጀመሩን ተከትሎ፣ የልጆቻችን ችሎታ ተሻሽሏል። ለምሳሌ ሳሚያ የተባለችው ታዳጊ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ13 ዓመት እድሜዋ  ልሳኗ ተከፍቶ መናገር ጀምራለች። የኔም ልጅ ጆጆም ቢሆን ፣ ማንበብና ፍላጎቱን በአንደበቱ መግለጽ ጀምሯል። ልጄ እራሱን ችሎ ስልኬ ላይ መደወልና ማነጋገር በመቻሉ፣ የትም ብሆን እንኳን ድምጹን መስማት ችያለሁ። ለስራ ከቤት ስወጣ፣ እንደ ድሮው በሀዘንና በብቸኝነት ስሜት በመስኮት አሻግሮ መመልከቱን ትቷል። አሁን ነገሮች ተቀይረዋል። ልጄ ወደ ት/ቤት ሲሄድም ሆነ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ከአጠገቤ ሲለይ፣ ፊቱ በደስታና በፈገግታ ተሞልቶ እጁን እያወዛወዘ “ባይ! ባይ!” ይለኛል እንጂ፣ እንደ ወትሮው የሃዘንና የመከፋት ስሜት አይታይበትም።
በአሁኑ ጊዜ የኦቲዝም ችግር ያለባቸውን እንቁ የሆኑ 80 ታዳጊዎችን በተቋሙ ውስጥ ተቀብለን እያስተናገድን  ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል በምንሰጣቸው ጠንካራ ፕሮግራሞችና ህክምናዎች ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸውን ስናገር ደስታ ይሰማኛል።
ከጎናችን ሆነው ያገዙንን ሁሉ አመሰግናቸዋለሁ። በተለይ ደግሞ ለግሎባል ፈንድ ፎር ችልድረን፣ ለዴቪድ ልዊስ ፓካርድ ፋውንዴሽን፣ ለፊንላንድ ኤምባሲ፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና ድጋፋቸውን ሳይሰስቱ  በቸርነት ለለገሱን ግለሰቦችና ተቋማት ሁሉ ምስጋናዬ ወደር የለሽ ነው። በእርግጥ የባለቤቴ፣ የቤተሰቤና የጓደኞቼ አስተዋፅኦም እጅግ ከፍተኛ ነውና፣ እነሱም ምስጋና ሲያንሳቸው ነው።
የልህቀት ማዕከል በመክፈት ፕሮግራሙን የማስፋት እቅድ አለኝ። ለህንፃ መስሪያ የሚሆን ቦታ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ተረክበናል። ለግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማሰባበስ ስራም ተጀምሯል። ፕሮጀክቱን እንድናጠናቅቅ ሊያግዙን የሚፈልጉ በርካታ በጎ ፈቃኞች እንደምናገኝ እርግጠኛ ነኝ።
በቅርቡ በፋና ኤፍኤም 98.1 ሬዲዮ፣ ዘወትር እሁድ ከምሽቱ 1፡00-2፡00 የሚተላለፍ “ያገባናል” የተሰኘ ፕሮግራም ጀምሬአለሁ። ይሄም ከበርካታ ሰዎች ጋር ለመገናኘትና ተሞክሮዬን ለማካፈል እንዲሁም ከሌሎች ለመማር ትልቅ እድል ይፈጥርልኛል ብዬ አምናለሁ።
በርካታ አርአያ የሆኑኝ ሰዎች ቢኖሩም፣ ከሁሉም የላቀችው አርዓያዬ ግን እናቴ ናት። ዛሬም ድረስ የምመራባቸውን የሕይወት መርሆዎች የቀሰምኩት ከሷ ነው። ከዋና ዋናዎቹ መካከልም፤ ሁሉንም ሰው እኩል ማክበር የሚለው መርህ ትልቁ ነው። የአንድ ወገን መረጃ በመስማት ብቻ ማንም ላይ አለመፍረድ፤ በማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ውስጥ በጎ ሀሳብ መያዝ፤ እንዲሁም የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች በሙሉ በአሸናፊነት መወጣት እንደምችል ማመን እንዳለብኝ አስተምራኛለች። “አንቺ የምትፈልጊውን ነገር፣ ራስሽ ካልሰራሽው ማን ይሰራዋል?” እያለችም ታበረታታኝ ነበር። ዛሬም ድረስ፣ ማንኛውንም ነገር ከመወሰኔ በፊት እናቴን አስባታለሁ። ሌላ የህይወቴ ኃይል ልጄ ቢላል ነው። ውጥኔን ለብቻዬ እንደጀመርኩትና ወደፊት ብቻዬን ብሆን እንኳን ፈተናዎችን ማሸነፍ እንደምችል ያስታውሰኛል። የኦቲዝም ችግር ካለበት ልጄ ከጆጆ ጋር ፍቅር እየሰጠሁት አብሬ መኖሬ፣ ዓለምን በተለየ መነፅር እንድመለከት አስተምሮኛል።
በግል ህይወትና በስራ ላይ ፈተናዎችን መጋፈጥ የተለመደ ነው ብዬ ስለማምን፣ በየቀኑ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ቀድሜ ራሴን አዘጋጃለሁ። ለውሳኔ አለመጣደፍን ተምሬአለሁ። እንቅፋቶች አላማዬን እንዲያሰናክሉብኝ ወይም ብርታቴን እንዲሸረሽሩብኝ አልፈቅድም። በቀኝ ጣቴ ላይ ያጠለቅኩት ቀለበት ይህን ያስታውሰኛል።
በኦቲዝምና በሌላ በማንኛውም የጤና እክል የሚቸገሩ ሁሉም ህፃናት፣ በሰው ልጅነታቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ሲያገኙና በህብረተሰቡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በነጻነት ሲሳተፉ ማየት እሻለሁ። በኢትዮጵያ የኦቲዝም ችግር ባለባቸው ልጆች ላይ የሚከሰተውን ስቃይ የሚያባብሱትን አጉል ፍረጃ፣ ማግለልና ባዶ ቤት ውስጥ መቆለፍን ለማስቆም እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት አለብን። የእናቶች እምባ ታብሶ ማየት ምኞቴ ነው። ሌላው ህልሜ ደግሞ፣ ወጣት ልጆቻችንና እህቶቻችን ገላቸውን በመሸጥ ሳይሆን፣ በክህሎታቸው ኑሮአቸውን ሲመሩ ማየት ነው። የቤት ሰራተኞችና የቀን ሰራተኞች፣ በተሰማሩበት የስራ ቦታ ሁሉ ተገቢውን አክብሮት እንዲያገኙ አልማለሁ።
ለወጣት ሴቶች የምለግሰው ምክር እንዲህ የሚል ነው። ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት። የምትሰሩትን እወቁ፤ ለማንኛውም ዓይነት ሱስ ተገዢ አትሁኑ። ማንም እንዲረግጣችሁና እንዲረማመድባችሁ አትፍቀዱ። በውስጣችሁ ምን ያህል እምቅ አቅም እንዳላችሁ ተገንዘቡ፤ እናም ማንንም ለመምሰል ሳይሆን ራሳችሁን ለመሆን ጣሩ። ከምታደንቁት ሰው በምንም አታንሱም፤ አላማችሁን እውን ለማድረግ በትጋት ሰርታችሁ ስኬትን ተቀዳጁ። ከሌሎች ሰዎች ጋር ፈጽሞ አትፎካከሩ። መፎካከር ያለባችሁ ከራሳችሁ ጋር ብቻ ነውና። በሙሉ አቅምና በላቀ ብርታት መስራታችሁን አረጋግጡ፤ ራሳችሁን ውደዱ።  
ምንጭ፡- (“ተምሳሌት፡ ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች” ፤2007)


 በብዛት ከከተቡ አገራት በ80 በመቶው ኮሮና ብሶባቸዋል

           የአለም የጤና ድርጅት “በአለማቀፍ ደረጃ ልዩ ስጋት ፈጥሯል” ብሎ የፈረጀውና ከሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ሁሉ በቀላሉ የመሰራጨት አቅም ያለው በህንድ የተገኘው “B.1.617’’ የተባለ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ወደ 50 የአለማችን አገራት መዛመቱንና ከእነዚህም መካከል ሰባቱ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ይህ የቫይረሱ ዝርያ ከህንድ ውጭ በርካታ ሰዎችን ካጠቃባቸው አገራት መካከል እንግሊዝ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሲሆን፣ ቫይረሱ ብራዚልንና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ወደ 50 ያህል አገራት መዛመቱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ቫይረሱ የተገኘባቸው የአፍሪካ አገራት ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ከሰሞኑ ደግሞ ወደ አልጀሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ናይጀሪያ መግባቱ መረጋገጡንም አክሎ ገልጧል፡፡ ኦል አፍሪካን ኒውስ በበኩሉ፣ በአፍሪካ አህጉር እስካሁን ድረስ ከ14 ሚሊዮን በላይ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መሰጠታቸውን ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም ለበርካታ ዜጎቻው የኮሮና ክትባትን በስፋት ካዳረሱ ቀዳሚዎቹ አገራት መካከል 80 በመቶ ያህሉ ከህዝብ ብዛት አንጽር የቫይረሱ ስርጭት ከወትሮው ብሶ መቀጠሉ ተዘግቧል፡፡
በአለማችን የኮሮና ክትባትን በስፋት ከሰጡት ቀዳሚዎቹ አገራት ሲሼልስ፣ እስራኤል፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ቺሊ እና ባህሬን መካከል ከእስራኤል በቀር ሁሉም የቫይረሱ ስርጭት ከወትሮው በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መረጋገጡንና ይህም በክትባቶቹ ፍቱንነት ላይ ጥያቄ ማስነሳት መጀመሩን ፎርብስ ዘግቧል፡፡


  ሳልቫ ኬር የደቡብ ሱዳንን ፓርላማ በተኑ

          ኡጋንዳን ላለፉት 35 ያህል አመታት ያስተዳደሩትና ባለፈው ጥር ወር በተካሄደ አወዛጋቢና ደም አፋሳሽ ምርጫ ያሸነፉት ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ ባለፈው ረቡዕ ለ6ኛ ዙር የስልጣን ዘመን ቃለ መሃላ መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡
የ76 አመቱ ሙሴቬኒ ለቀጣዮቹ ስድስት አመታት አገሪቱን ለማስተዳደር በመዲናይቱ ካምፓላ በይፋ ቃለ መሃላ በፈጸሙበት በዓለ ሲመት ላይ ከ10 በላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ ሰኞ ዕለት የአገሪቱ ፖሊስ በዓለ ሲመቱን ለማወክ አቅደዋል ያላቸውን ከ40 በላይ ተጠርጣሪዎች ማሰሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሌላ የአፍሪካ ዜና ደግሞ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር በአገሪቱ ከሶስት አመታት በተደረሰው የሰላም ስምምነት የተገቡ ቃሎችን ተፈጻሚ ለማድረግ በሚል ባለፈው ቅዳሜ የአገሪቱን ፓርላማ መበተናቸውን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱን የፓርላማ አባላትንና ከፍተኛ ባለስልጣናት ከገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ለመምረጥ ታስቦ በ2018 የተፈጸመው ስምምነት 25 በመቶ የፓርላማ አባላትን ከተቀናቃኙ የሬክ ማቻር ፓርቲ ለማድረግ ተወስኖ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በዚህ መሰረትም ሳልቫ ኬር ፓርላማውን መበተናቸውንና አዲሱን ፓርላማ ከሰሞኑ ያዋቅራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡


  በማኅበረሰባችን ልማድ መሠረት በዕድሜ ታላቅ የሆኑ ሰዎችን (ወንዶችን) ‘’ጋሼ’’ ወይም “ጋሽዬ” ብሎ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ”ጋሼ” ብሎ ”አንተ” ከተከተለ ደግሞ የበለጠ ቀረቤታ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ተማሪዎቹና የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት አብዛኞቹ “ጋሼ” ወይም “ጋሽዬ” እያሉ ይጠሩታል፡፡ መጠሪያ ስሙ አስፋው የምሩ መሆኑን የማያውቁ ብዙ ናቸው።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ በዛፍ ጥላ ሥር የተጀመረ የማስተማር ተግባር ከ60 ዓመታት በላይ ቀጥሎ፣ ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ  ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች የትምህርት ዕድል ከፍቷል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የዝቅተኛው ማኅበረሰብ ክፍል አባላት (እናቶች፣ሕፃናት፣የጎዳና ተዳዳሪዎች) ደግሞ የተለየ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ለዚህን ያህል ጊዜ ለማስተማርና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ የተቻለው ያለ ምንም ቋሚ በጀት መሆኑ ደግሞ እጅግ በጣም ያስገርማል፡፡
በሦስት የተለያዩ ሥርዓተ መንግሥቶች (የንጉሥ፣ የወታደር እና የዘር ፌደራሊዝም) ውስጥ አንድ ዓይነት ዓላማ ማለትም “መሃይምነትንና ድኅነትን መቀነስ” የሚለውን ሃሳብ ይዞ ለመዝለቅ ብዙ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚያስፈልግ መገመት አያስቸግርም፡
“ነብይ በአገሩ…”
ተረቱ “ነብይ በአገሩ አይከብርም” የሚል ቢሆንም፣ ጋሼን በተመለከተ “አይከብርምን” በአይታወቅም” ብንተካው ለእውነታው ይቀርባል፡፡ አብዛኛው ሰው ስለ ጋሼ ማንነትና ሥራዎቹ አያውቅም፡፡ በእርግጥ ለዚህ ነገር ዋናው ምክንያት ጋሼ ራሱ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ በ1964 ዓ.ም በታተመች የመነን መጽሄት ላይ ከዚህ የሚከተለው ሰፍሯል፡
“አስፋው የምሩ የሚሠራውን ሥራ እወቁልኝ የማይል፤ ስለሚሰጠው አገልግሎት እንዲያመሰግኑት ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ሥራውን መሥራት እንጂ በሠራተኝነቱ ስሙ እንዲነሳ የማይሻ ሰው ነው፡፡”
ይህ ከላይ የቀረበው ሃሳብ ጋሼን በቅርብ የሚያውቁት፤ ሁሉ በአንድ ቃልና በአንድ ልብ የሚመስክሩት እውነታ ነው።
ሌላው ምክንያት ግን የእኛም የማወቅ ፍላጎት ማነስና የማስተዋወቅ ጥረት ውስንነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በኋላ በዝርዝር እንደምናየው ጋሽየ በአገራችን ከፍተኛ ክብርና ዕውቅና ያለውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሸልማት ድርጅት “የ 1962 ዓ.ም የትምህርት ዘርፍ’ ተሽላሚ ነበር። ከእኛ በተሻለ የሚያውቁት የዓለም ሕጻናት ደግሞ “የዓለም ሕጻናት ጀግና” ብለው መርጠዉታል፡፡ ይሀንን ሽልማት ኔልሰን ማንዴላና ታዋቂዋ የህጻናትና የልጃገረዶች መብት ተሟጋች ማላይላ ያገኙት ከጋሽዬ በኋላ ነው።
እንደ አስፋው የምሩ (ጋሽዬ) አይነት ብዙም የማይታውቁ ሰዎች እንዴት ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ተግባር ማከናወን እንደቻሉ አስፋው የምሩን (ጋሽዬን) በተምሳሌትነት አቅርቦ ማየት ይቻላል፡፡ ጋሼ የሕይወቱን ጥሪ የመለሰበትን መንገድ፣ ያጋጠሙትን ውጣ ውረዶችና የተከተላቸውን የሕይወት መርህዎች መቃኘት ብዙ ያተርፋል፡፡
የሕዝብ ፍቅርና ክብር
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ላበረከተው ማህበራዊ አገልግሎት ከሕዝቡ ያገኘው የፍቅር ምላሽ ለእሱ ታላቁ ሽልማቱ ነው፡፡ ሁሉም “ጋሼ” የሚለውን እንደታላቅ የፍቅርና የክብር መገለጫና የማዕረግ ስም ይጠቀሙበታል። ተማሪዎቹ “የዕውቀት አባታችን፣” ወላጅ አልባ ሕፃናት “የመንፈስ አባታችን”፣ ዝቅተኛ የማህበረሰብ አባላት “የድሆች አባት” እያሉ ይጠሩታል፡፡ የጎዳና ልጆች  ‘ጋሼ’ እያሉ የእጃቸውን መዳፍ ደረታቸው ላይ በማሳረፍ፣ በልባቸው ውስጥ እንዳለ ያሳዩታል። ታላቅ የጋሼ ሽልማቶች እነዚህ ናቸው፡፡
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት
የሽልማቱ መጽሄቱ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል፡-
“……እኝህ በአገልግሎት ስሜት የተነሱ ትጉህ ኢትዮጵያ ይህንን ኃላፊነት በፈቃዳቸው ተሸክመው ሥራውን በሚመሩበት ጊዜ፤ ያላንዳች ጥቅም ሰውነታቸውንና ዕውቀታቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መስዋዕት አድርገው መድከማቸውን የማስተማር፣ አገልግሎት ኮሚቴና ባላደራዎችም ተመልክተውታል፡፡
“…….ይህንን የመሰለ አገልግሎት እፈጽማለሁ ብሎ ለሚነሳ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህ ምሳሌ ኃይልና ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን ስለተገነዘበ፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1962 ዓ.ም የማስተማር አገልግሎት ሽልማት የወርቅ ኒሻንና የምስክር ወረቀት፣ ከ፲ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ጋር ለአቶ አስፋው የምሩ እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡
የዓለም ሕፃናት ሽልማት
ይህ ሽልማት በዓለም ላይ ለሕፃናት መብት ታላላቅ ተግባር ላከናወኑ ጀግኖች የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡ ለሽልማቱ የቀሩበት ዕጩዎች የሕይወት ታሪክና የረዷቸው ሕፃናት ታሪክ በፊልም ተቀርጾ ለዓለም ሕፃናት ይቀርብላቸዋል። በዓለም ላይ የሚገኙ ከ40000-50000 የሚቆጠሩ መምህራን ፕሮግራሙን ያስተባብራሉ፡፡
እድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ልጆች በቀጥታ ድምጽ በመስጠት ከቀረቡት 3 ዕጩዎች ሕፃናቱ ልባቸውን የነካውን ሰው ጅግና ብለው ይመርጣሉ፡፡ ምርጫው የሚካሄደው በህፃናቱ ነው፡፡ ሕፃናቱ “ጀግናቸው” አድርገው የመረጡት ሰው የዓመቱ የሕፃናት ጀግና ተበሉ ዓለም አቀፍ እውቅና እና ሽልማት ያገኛል። በዚህ ዓለም አቀፍ ምርጫ የተሳተፉ ልጆች  ከፍተኛው ቁጥር 7.1 ሚሊዮን ነው።
እ.ኤ.አ በ2001 /1993 ዓ.ም/ የዓለም ሕፃናት የመረጡት የእኛውን ጋሼ ነበር። ጋሼ ሽልማቱን በማሸነፍ የዓለም ሎሬት የሚል ማዕረግ ያገኘ ሲሆን  እሱ ግን ማረግና ክብሩን ትቶ “ጋሼ” መባሉን መርጦ የተለመደ ስራውን ቀጠለ።
የሽልማት ሥነስርዓት በስዊድን አገር የሚደረግ ሲሆን ሽልማቱንም የሚሰጡት የስዊድኗ ንግሥት ናቸው፡፡
ማንዴላና ማላይላ
ሽልማቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕፃናትና አስመልክቶ ከሚሰጡ ሽልማቶች በጣም ከፍተኛው ሲሆን ይህንን ሽልማት ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም አግኝተዋል። እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም  ደግሞ  የተማሪዎችና የወጣቶች መብት ታጋይ ማላይላ ተሸልማለች ከጋሼ በኋላ ማለት ነው፡፡ ጋሼም የኖቤል ሽልማት እጩ እንዲሆን የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቷል፡፡

የዓለም አቀፍ ወዳጆች ማኅበር ሽልማት
ጋሼ በጣም ለተቸገሩ ህፃናት መብት እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ላበረከተው አስተዋጽኦ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ ከዚህ የዓለም አቀፍ ድርጅት የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡ ሰርተፍኬቱ ላይ እንዲህ ይላል፡-
አስፋው በ10,000 የሚቆጠሩት ችግረኛ ተማሪዎችን በት/ቤቱ ያስተማረ ሊሆን ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የመማር እድሉን ማግኘት የማይችሉ ልጃገረዶች ናቸው፡፡ አስፋው የተቸገሩ ልጆችን ለመርዳትና ወደ ተሻለ ሕይወት ለማምጣት ያደረገው ጥረት ለረዥም ጊዜና አንዳንዴም በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የተከናወነ ነው፡፡  
“…ዓለም አቀፍ ወዳጆች ማኅበር አስፋው የምሩ ለወላጆች/ሕፃናት መብት ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ  ይህንን የዕውቅና ሽልማት አበርክቶልታል፡፡ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችም የተሰጡት ለሕፃናትና ለእናቶች ያደረገው ማኅበራዊ ድጋፍና ለወጣቶች ላበረከተው የረዥም ጊዜ የትምህርት አገልግሎት ነው፡፡
ስንብት
(ጋሽየ ድምጹን ሳያሰማ ክስልሳ ዓመታት በላይ ለወጣቶች፣ ለእናቶች፣ ለህጽናትና ‘ለጎዳና ልጆች’ ተስፋና ፍቅርን ሲሰጥ እንደኖረ፣ አገርና ሕዝብም ታላቅ ሰው እንዳጡ ሳይታወቃችው፣ ሚያዚያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ላይመለስ ተሰናበተ። ለእኔ አገራችን ካፈራቻችው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነህ። ፈጣሪ ለነፍሰህ ሙሉ እረፍትን ይስጣት። ለኛም ያንተን መንገድ የምነከተልበተን ጥበብና ልቦና ይስጠን!!)ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 እጅግ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ 10 ስፖርተኞች ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ታዋቂው ቦክሰኛ ኮኖር ማክግሪጎር በ180 ሚሊዮን ዶላር በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ፎርብስ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳስታወቀው፣ የባርሴሎናው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በ130 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን፣ የጁቬንቱሱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የዳላስ ካውቦይስ ቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋቹ ዳክ ፕሪስኮት በ107.5 ሚሊዮን ዶላር፣ የሎሳንጀለስ ሌከርሱ ኮከብ ሊቦርን ጄምስ በ96.5 ሚሊዮን ዶላር፣ የፓሪስ ሴንጄርመኑ ተጫዋች ኔይማር በ95 ሚሊዮን ዶላር፣ የጠረጴዛ ቴኒስ ኮከቡ ሮጀር ፌደረር በ90 ሚሊዮን ዶላር፣ የኤፍ ዋኑ ሊዊስ ሃሚልተን በ82 ሚሊዮን ዶላር፣ ቶም ብራዲ በ76 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ኬቪን ዱራንት በ75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኞች መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡ አስሩ ባለከፍተኛ ገቢ ስፖርተኞች ባለፈው አመት በድምሩ 1.05 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን ያስታወቀው ፎርብስ፣ ምንም እንኳን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለማችን ስፖርት ላይ ክፉኛ ጉዳቱን ቢያደርስም በአስሩ ስፖርተኞች በአመቱ ያገኙት አጠቃላይ ገቢ በአንጻሩ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ28 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡

Page 12 of 536