Administrator

Administrator

Saturday, 23 October 2021 14:20

የፖለቲካ ጥግ

 • ከባዱ በሽታ ሙስና ሲሆን ክትባቱ ደግሞ ግልፅነት ነው።
  ቦኖ
• ህግን የሚፈጥረው ጥበብ ሳይሆን ሥልጣን ነው።
  ቶማስ ሆብስ
• በግሌ ሙስናን መቅረፍ ትልቅ ችግር ነው ብዬ አላስብም።
  ኢምራን ክሃን
• በመንግስት ውስጥ ሙስናን መቃወም ታላቁ የአርበኝነት ግዴታ ነው።
  ጂ.ኢድዋርድ ግሪፊን
• ሙስናን የሚዋጉ ወገኖች ራሳቸው ንፁህ መሆን አለባቸው።
  ቭላድሚር ፑቲን
• እንዳለመታደል ሆኖ፣ ሙስና በመንግስት ኤጀንሲዎችና በህዝባዊ ተቋማት ውስጥ በስፋት ይሰራጫል።
  ጆርጅ ፓፓንድሮ
• ሙስናን መዋጋት የመልካም አስተዳደር ጉዳይ አይደለም። ራስን መከላከል ነው። አርበኝነነት ነው።
  ጆ ባይደን
• ሙስና የተፈጥሮ አደጋ አይደለም።
  ዴቪድ ኑስባም
• ሙስና የጥቂት አገሮች ችግር ብቻ አይደለም፤ ዓለማቀፋዊ ችግር ነው።
  ንጉዬን ታን ዱንግ
• ችሮታ ብቻ ሳይሆን ሙስናም ጭምር ከቤት ይጀምራል።
  ኬ ሃሪ ኩማር
• ሙስና ለዋሺንግተን እንግዳ አይደለም፤ ታዋቂ ቤተኛ ነው።
  ዋልተር ጉድማን
• የወጣቱ ሃላፊነት ሙስናን መገዳደር ነው።
  ኩርት ኮቤይን


Saturday, 23 October 2021 14:17

የስኬት ጥግ

• ሃብት ምንድን ነው? የጅሎች ህልም ነው፡፡
  አብርሀም ካሃን
• ብዙ ሃብት ብዙ ጠላትን ይፈጥራል፡፡
  የስዋሂሊ አባባል
• ብልህ ሰው ገንዘቡን በጭንቅላቱ እንጂ በልቡ ውስጥ ማስቀመጥ የለበትም፡፡
  ያልታወቀ ደራሲ
• ድሃ ሆነህ ከተወለድክ ጥፋቱ ያንተ አይደለም፤ድሃ ሆነህ ከሞትክ ግን ጥፋቱ ያንተ ነው፡፡
  ቢል ጌትስ
• ተኝተህ ገንዘብ የምትሰራበትን መንገድ ካልፈጠርክ፣ እስክትሞት ድረስ ትለፋለህ፡፡
  ዋረን በፌ
• ሀብት የሰው የማሰብ ችሎታ ውጤት ነው፡፡
  አየን ራንድ
• ሃብት መፍጠር ስህተት አይደለም፤ ገንዘብን ማፍቀር እንጂ፡፡
  ማርጋሬት ታቸር
• ሃብት እንደ ዛፍ ሁሉ ከቅንጣት ዘር ይበቅላል፡፡
  ጆርጅ ኤስ. ክላሶን
• ድህነት የሚመጣው ከሀብት መቀነስ አይደለም፤ ከፍላጎት መጨመር እንጂ፡፡
  ፕሌቶ
• ሃብት በእግዚአብሔር አይን ትልቅ ሃጢያት ሲሆን፤ ድህነት በሰው አይን ትልቅ ሃጢያት ነው፡፡
  ሊዮ ቶልስቶይ
• ደስታ ገንዘብ ሊገዛው የማይችል እውነተኛ ሀብት ነው፡፡
  አሎን ካሊናኦ ዲዋይ
• በልፅጎ ከመሞት ይልቅ በልጽጎ መኖር የተሻለ ነው፡፡
  ሳሙኤል ጆንሰን

Sunday, 24 October 2021 00:00

ለኢትዮጵያ ሙዚቃ

ከመንዙማ፣ ከአሚናዎች፣ ከጉባኤ ቃና የተፈለቀቁ ሙዚቃዎች
(በጣም የምወዳት ባለቅኔ ድምጻዊት/
ሸማ ነጠላውን ለብሰው
አይበርዳቸው አይሞቃቸው
ሐገሩ ወይናደጋ ነው
አቤት ደም ግባት – ቁንጅና
አፈጣጠር ውብ እናት
ሐገሬ እምዬ ኢትዮጵያ
ቀጭን ፈታይ እመቤት
እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ላይ ካደረሱት ድምፃዊያን መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ ታዋቂው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲ ኤን ኤን፤ በተደጋጋሚ ጂጂን እና የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርቧል፡፡ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም በአዘፋፈን ስልቷ፤ በድምጿ፤ በሙዚቃ ቅንብሯና በአጠቃላይ ታሪኳን በተመለከተ ሰፊ ሽፋን ሲሰጧት ቆይተዋል፡፡ ይህች ስመ ገናናዋ ድምፃዊት ጂጂ ከ14 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሐገሯ መጥታ በህዝቧ ፊት የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው ባለፉት 20 ዓመታት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም የሙዚቃ፤ የሥነ ግጥም እና የሥነ ፅሁፍ ሃያሲያን ስራዎቿን ተንትነውላታል። በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ ላይ በቀረበ ጥናት፤ ጂጂ ከኢትዮጵያ ድምፃዊያን የሚለያት ሙዚቃዎቿ እጅግ የጠለቀ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን  በውስጣቸው አምቀው የያዙ በመሆናቸው እንደሆነ የተገለፀበትም አጋጣሚ አለ፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው ሐገሯን በሙዚቃዎቿ ውስጥ የምትገልፅባቸው መንገዶችም እየተነሱ ተተንትነዋል፡፡ ለጂጂ ሀገር ማለት ቤተሰቧ፣ ኑሮዋ፣ ትዝታዋ፣ መልክዐ ምድሯ፣ ወንዞችዋ፣ ተራሮችዋ፣ ህዝቧ… ሲሆኑ የአቀራረብ ዘይቤዋ ጆሮ ግቡና እጅግ ማራኪ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ደግሞ አባይ ወንዝ ላይ የተፃፉ አያሌ የኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ተሰብስበው ሚዛን ላይ ተቀምጠው ነበር። በርካታ ገጣሚያንና ድምጻዊያንን አባይን በየራሳቸው እይታ ሲገልፁት፤ ሲያንቆለጳጵሱት፤ ሲሞግቱት፤ ሲወቅሱት፤ ሲቆጩበት… እንደነበር በጥናት ተዳሷል። በመጨረሻም በግጥም፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኃህን፤ በሙዚቃ  ጂጂን የሚያክል የጥበብ ሥራ ግን አልተገኘም ተብሏል፡፡ ፀጋዬ የስነ ግጥም ጣሪያ ሲሆን፤ ጂጂ ደግሞ የሙዚቃው ቁንጮ ተብላለች፡፡ ከፀጋዬ የሚከተለው ቀርቦ ነበር፡-
ዓባይ የጥቁር ዘር ብስራት፣
የኢትዮጵያ የደም ኩሽ እናት፤
የዓለም ስልጣኔ ምስማክ፣
ከጣና በር እስከ ካርናክ፤
ዓባይ የአቴንስ የጡቶች ግት፣
የዓለም የስልጣኔ እምብርት፤
ጥቁር ዓባይ የጥቁር ዘር ምንጭ፣
የካም ስልጣኔ ምንጭ፤
ዓባይ-ዓባይ ዓባይ-ጊዮን፣
ከምንጯ የጥበብ ሳሎን፣
ግሪክ ፋርስና ባቢሎን፣
ጭረው በቀዱት ሰሞን፡፡
ዓባይ የአማልእክት አንቀልባ፣
የቤተ-ጥበባት አምባ፤
ከእሳት ወይ አበባ
ይህ የሎሬት ፀጋዬ ግጥም በኢትዮጵያ ሥነ ግጥም ውስጥ ደረጃው አንደኛ ነው ተብሏል፡፡ ፀጋዬ ራሱ በባለቅኔነቱ ግዙፍ ሰብዕና ቢሰጠውም፣ ይህ አባይ የሚለው ግጥሙ ደግሞ በተለያዩ የሥነ ግጥም መለኪያዎች  ልዕለ ጥበብ (Masterpiece) ነው ተብሏል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው የጂጂ ዓባይ በሙዚቃው ዘርፍ ከፀጋዬ ገ/መድህን ዓባይ ጋር በእኩል ደረጃ ተደንቋል፡፡
የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና፡፡
ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት፡፡
ግርማ ሞገስ
የአገር ፀጋ የአገር ልብስ
ግርማ ሞገስ፡፡
ዓባይ…
የበሐረው ሲሳይ
እያለች ከትውስታ በማይጠፋ የሙዚቃ ስልት የምታንቆረቁር ድምፃዊት እንደሆነች ተነግሮላታል፡፡ እነዚሁ ሁለት የኪነ-ጥበብ ሰዎች ዓባይ ላይ ባቀረቧቸው ስራዎቻቸው የዓባይን መልክ፤ ቁመና፤ ታሪክና ማንነት ገልፀዋል፡፡ ዓባይ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው ከመገለፁም በላይ በተለይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተያይዞ መጥቶ ጣና ሐይቅ ውስጥ ገብቶ ግዙፍነቱ ይጨምራል። ጣና ላይ ደግሞ 37 ያህል ደሴቶች አሉ፡፡ በነዚህ ደሴቶች ከ21 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገዳማት አሉ፡፡ እጅግ አስገራሚ የኢትዮጵያ ቅርሶችም በነዚህ ገዳማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ዓባይ ላይ ይፀለያል፤ ይቀደሳል፤ ይዘመራል፤ በብህትውና ይኖራል፤ ይታመንበታል፡፡  አባይ የኢትዮጵዊያን መንፈስ ነው፡፡ እምነት ነው፡፡ ሀብት ነው፡፡ ይህን አንደምታ ይዘው ነው እነ ጂጂ ዓባይ ላይ ፍፁም ተወዳጅ የሆኑ ስራዎችን ያቀረቡት፡፡
በተመሳሳይ ፀጋዬ ዓድዋ ላይ የፃፈው ሥነ-ግጥሙ ሌላው ተጠቃሽ ስራው ነው፡፡ እጅጋየሁ ሽባባውም ዓድዋ ላይ ያቀነቀነችው ዘፈን እንደ ፀጋዬ ዓይነት እጅግ ጥልቅ ስሜትን የሚያስተጋባ ሥራ እንደሆነ ተመስክሮላታል፡፡ ፀጋዬ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ጋር ፍቅር ጋር የወደቀ ገጣሚ ነው በሚል፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን-ግጥሞቹ ተዘርዝረዋል፡፡ እጅጋየሁ ሽባባውም እንዲሁ ኢትዮጵያዊነትን በስፋት”  የምታስተጋባ ድምፃዊት እንደሆነች በልዩ ልዩ መድረኮችና ጥናቶች ተገልጿል፡፡ በቅርቡም   ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ፤ የሥነ-ግጥም አድናቂ መሆኗንና ጠቁማ እነ ፀጋዬ ገ/መድህንን በስራዎቻቸው እጅግ እንደምትወዳቸው ተናግራለች፡፡  በተለይ በወለዬዎች መንዙማ እና በአሚናዎች የድምፅ ቅላፄ ላይ ተመስርታ ወደ ዘመናዊ ሙዚቃ አምጥታቸዋለች ይባላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጂጂ ራሷም ትስማማለች፡፡ ገና ከህፃንነቷ ጀምሮ የአሚናዎች የአገጣጠምና የዜማ ስልት እጅግ እጅግ እንደሚገርማትና እንደምትወደው አውስታለች፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት እነ ጂጂ ቤት ለመጣች አሚና ልብሶቿን አውጥታ እንደሰጠቻት የልጅነት ታሪኳን ታወሳለች ጂጂ፡፡  ከመንዙማ እና ከአሚናዎች የሙዚቃ ስልት ተፈልቅቀው የወጡት ስራዎቿ ለህዝብ ጆሮ ቅርብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በዚህ ስልት ከተጫወተቻቸው ዘፈኖች መካከል ደግሞ “ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታ” እያለች የምትዘፍነው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ- ፅሁፍ መምህር የሆኑት አቶ ወንደሰን አዳነ በጂጂ ሥራዎች ላይ ባቀረቡት ጥናት፤ ለዚህ ሙዚቃ ውበትና የሥነ-ግጥም ብቃቱ እጅግ የተዋጣለት መሆኑን ገልጸዋል። በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ እጅጋየሁ ሽባባው የመጀመሪያዋን አልበም ለቀቀችው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ፅሁፍና የፎክሎር መምህር የሆኑት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በአጋጣሚ የጂጂን ካሴት ማታ ሰምተውት ነበር፡፡ ጠዋት ሊያስተምሩ ወደ ተማሪዎቻቸው ዘንድ መጡ፡፡ እንዲህም አሉ፡- “ዛሬ እንቅልፍ ሳይወስደኝ ነው ያደርኩት” አሉ። ተማሪዎቻቸውም “ምነው? ምን ሆንክ?” አሏቸው፡፡ እርሳቸውም “ፍቅር እየራበኝ” እያለች የምትዘፍን ልጅ እጅግ እየደነቀችኝ ደጋግሜ ስሰማት ነው ያደርኩት” አሉ። ልጅቷን ግን ያወቃት የለም፡፡ እሳቸውም ስሟ እጅጋየሁ ነው፤ከናንተ ውስጥ ሲሉ ጠየቁ፡፡ የሚያውቃት  ግን ጠፋ፡፡ እርሳቸውም ሲናገሩ “በኢትዮጵያ ውስጥ ከ26 ዓመት በኋላ በሙዚቃ ስልቷ ነፍሴን የገዛችው ይህች ድምፃዊት ናት፡፡ በእኔ ግምት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ታደርሰዋለች ብዬ የምተማመነው በዚህች ልጅ ነው፡፡   ተስፋ መስጠቱን እንጂ እምነት መዋረድን እንደሚጨምር ብዙ ሰው አይገነዘብም። ውርደትን ቀምሶ ማሳለፍ ግን
ውሎ ሲያድር የትዝታ ጠባሳ ትቶ ያልፋል።
እምነት ስንል ሁለት መልክ አለው። በሰው የሚታመን አለ፤ በፈጣሪው የሚታመን አለ። ሁለቱም ይፈተናሉ።
አንደኛው ይወድቃል፣ ሌላኛው ይፀናል። ይኸኛው ራሱን ለማስወደድ ወድቆ ይነሳል፤ ያልሆነውን ለመሆን
ይጣጣራል። ጥረቱ ሁሌ ያዘልቃል ማለት ግን አይደለም። ለምሳሌ፣ ታፍሶ እስር ቤት ቢታጎር ምን ማድረግ
ይችላል? የሚበላበት፣ የሚፀዳዳበት፣ የሚያወራበትና የሚጋደምበት ሰዓት ሲገደብለት። ከማማ ላይ ቁልቁል  እንደ ወፍ ሊለቅመው ሲያነጣጥርበት። በ “ደምክን ካፈር እንዳልደባልቅ” ዐይን ሲጎመዠው። ቀን ቀን እንደ እህል
ከተሰጣበት ሜዳ ላይ ተንጋልሎ ቅማል ሲቀምል። ነፋስ የበተነውን ኤሎሄ! ኤሎሄውን መላእክት ለቅመው
ሲመዘግቡለት። ሌት እንደ አጣና ደርድሮ ሲያጋድመው፤ እግር አናቱ ላይ ሲተሻሽበት። በአንድ ጀምበር ሽበት
ሲወርረው። ወንድ ልጅ ባንጀቱ ደም ሲያረግዝ። ልቦና ከሰጠው ያኔ፣ ችላ ያላቸውን ጒዳዮች ከልብ ጉያ እያወጣ
ይበረብራቸዋል። ያከበዳቸው ቀልለው፣ ያቀለላቸው ከብደው ያገኛቸዋል።
በተወሰነ ሥፍራና በጠበበች ሰዓት ውስጥ መገናኘት ያለ ውዴታ ማቀራረቡ አይቀርም። መቀራረብ መተያየትና
መጠናናትን፣ መጠናናትም እያደር መተዋወቅና መገላለጥን ይወልዳል። (ስንቴ አብረው በልተዋል፤ ስንቴ ጎን ለጎን
ተቀምጠው አንሾካሹከዋል። የወዳጁ ግራ ጆሮ ላይ ማርያም እንደ ሳመችው የታየው ግን ገና ዛሬ ነው!)
መገላለጥ የድብብቆሽ ኑሮ ጠር ነው። አብሮነትና ወዳጅነት ለስጋት ፍቱን መድኃኒት ነው። ሰው ሆድና ጀርባውን
ከተገላለጠ እርቃኑን ቀረ፣ ራሱን ለነቀፌታ አመቻቸ። ሌላው ሊያጠፋው ወይ ሊያለማው የሚችልበት ሁኔታ
ተፈጠረ። የማይበጅ ኢትዮጵያዊነት ተሸረሸረ ማለት ነው!
አብሮ መኖር ትልቅ አደራ፣ ትልቅ አደጋ የሆነው ለዚህ ነው። … ወይ ተማምኖ እየተጋገዙ መኖር ነው፤ አለዚያ ያለእረፍት መገዛገዝ፣ ያለእፍረት መነዛነዝ ነው። እምነት የሚመዘነውና የግል የሚሆነው፣ በእሳት ተፈትኖ ካለፈ ነው። የምቹ ዘመን እምነት እንዳልተገራ ወይፈን ለቁም ነገር አይውልም። ዘመን ያመጣውን፤ ዘመን ይሸኘዋል እንዲል በነፍስ ለመገናኘትና በቋንቋ ለመግባባት አንድ ሰሞን አይበቃውም። አስቀድሞ የዲሪቶው ሽፍንፍን መገፈፍ አለበት። ይኸ እውነት ሕዝብና ግለሰብን አይለይም። መተማመን እርቃን መቅረት ነው። መከራም የሚላከው ይህን የማስመሰል ካብ ለመናድ ነው። ካብ ለካብ ሳይተያይ፣ ገሃዱን ሳይሸፋፍን የተገኘ ወዳጅ እንግዲህ እንዴት ውድ ነው? ፍቅሩ እንዴት ድንቅ ነው? ትዝታው እንዴት የማያረጅ ነው?
ቢያንስ ለአንድ ሌላ ሰው የልቡን አሳብ መግለጥ ያላወቀ፣ መከራ ያልሞከረውን ምሥኪን በሉት። ከሚመሳስሉት
ክልል ወጣ ብሎ ማየት ያልተቻለውን ዕውር በሉት። መከራ ያልመከረውን ጅል በሉት፤ ወደ ትፋቱ ዳግም፤ ታጥቦ ጭቃ በሉት። ሁሉን እንደ ተጠራጠረ፣ የራሱ እስረኛ ሆኖ ይኖራል። ኑሮው የተሟላ ይመስላል፤ ሕይወትን ግን አያጣጥማትም። ነፍሱን አላካፈለምና፤ የበዛ ሕይወት አይቀበልም። ተዘግቶ እንደ ኖረ ደጅ፣ ብርሃን
እንደማይገባው፣ ለጨለማ ትርፎች መከማቻ እንጂ ለምንም አይበጅ! ይኸ ለግለሰብም ለሕዝብም እውነት ነው።
የእህል ዘር ተቋጥሮ ቢቀመጥ ተቋጥሮ ይቀራል። ተቋጥሮ ይረሣል። ሊያበዛው የሚችለውን የሕይወት ኃይል
በውስጡ ነክሶ ይዞታልና ብቻውን ይሞታል … የተዘጋው ደጅ ሲከፈት ብቻ ጨለማው ሥፍራ ይለቃል።
የተቋጠረው ሲበተን መትረፍረፍ ይጀምራል። ይህን ደጅ የሚከፍትና የተቆለፈውን መዳፍ የሚዘረጋጋ ቅድም
እንዳልነው በአብዛኛው መከራ ነው።
መከራ ባቆራኛቸው ዘንድ ከቀን ቀን የሚከሰተውን ማስተዋል ይጠቅማል። የመጀመሪያው ቀን ላይ ከልማድ
መታገድ፣ የራሴ የሚባል መታጣት ያስቆጣል እንበል። አለዚያም ምግቡ ረሃቡና ጥሙ፣ የሰው ጠረኑ …
መተፋፈጉ ሙቀቱ፣ ማንኮራፋቱ … የመኝታ አለመመቸቱ፣ ኲርፊያው፣ ሌት የጀርባ አጥንት ሲላቀቅ
ድምፃድምፁ፣ ዐመል ያሳጣል እንበል። ውሎ ሲያድር ግን ይህም ይለመዳል። ይባስ ይዋሃዳል። ጊዜ ሲርቅ፣
ሁኔታዎች ሲለዋወጡ፣ በናፍቆት ይታሰባል። ይህ እርቃን የመውጫ አቦሉ ነው።
አሁን ግን መሽቷል፤ ይነጋ ይሆናል … ተስፋ የተደረገበቱ ይዘገያል፤ በልብ ውዝዋዜ “እስከ መቸ ይሆን?”
ይላል። መላ መምታት፣ በጭፍን በሠቀቀን መኖር፣ መፍረክረክ ይጀምራል። ከመሠረቱ ፈርሶ እንደገና አምሮ
ሊገነባ … ይኸኔ የሰው ዋጋ ይታወቃል፤ ቀልሎ መገኘት ወይም ለቁም ነገር መብቃት። መደጋገፍ … ተስፋ
መሠጣጣት፣ በመከራ እየቀለዱ ቀን መግፋት። ይህ የመደማመጥ፣ የመግባባትና የመተሣሠር ሁለተኛ ነው።
ሦስተኛም አለው፦ “ትዝ ይልሃል? … የማያልፍ የለም አለፈ እኮ!” ይላል …
በእንዲህ የተገኘ ወዳጅ እንዴት ውብ ነው? እንዴት የማይረሣ፣ እንዴት የሚመረጥ ነው?
(በምትኩ አዲሱ፤ መስቀል ተ ሠላጢን፣ መለስተኛ ንዛዜ፣ መስቀልኛ ነገር።  ገጽ 131—134)

  ፍቅር የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡ የምትኖሩት ፍቅርን ትማሩ ዘንድ ነው። የምታፈቅሩትም መኖርን ትችሉ ዘንድ! ለሰው ልጅም ከዚህ ውጪ ሌላ ትምህርት አያሻውም፡፡
ማፍቀር ማለትስ ምንድነው፣ አፍቃሪ ተፈቃሪውን ለዘለዓለሙ ወደ ራሱ ስቦ ሁለቱ አንድ እንዲሆኑ እንጂ?
ደግሞስ … ማንን ወይም ምንን ይሆን ማፍቀር የሚገባ? እውን ከሕይወት ዛፍ ቅጠሎች አንዷን መርጦ ልብ ያጋተውን መላውን ፍቅር ማዝነብ ይገባ ይሆን?
ግና፣ ቅጠሉን ያፈራው ቅርንጫፍ፣ ቅርንጫፉን የያዘው ግንድ፣ ግንዱን ያቀፈው ቅርፊትስ…? ቅርፊት፣ ግንዱን፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ቅርንጫፎቹን የመገቡት ስሮችስ? ስሮቹንስ ያቀፈው አፈር? አፈሩንስ ያለማው ፀሐይ? ውቅያኖስ … አየሩስ?
ዛፍ ላይ ያለች ትንሽ ቅጠል፣ ለፍቅራችሁ ከተገባች፤ መላ ዛፉን ምን ያህል እጥፍ ትወዱት!? ከአጠቃላዩ ነጥሎ አንዱን ክፋይ የሚወድ ፍቅር፣ ራሱን ለሐዘን አጭቷል ቀድሞ ነገር!
እናንተ ግን፣ “ከአንድ ዛፍ ቅርንጫፍ እንኳ፣ እልፍ አእላፍ ቅጠሎች አሉ…
አንዳንዱ ጤነኛ፣ አንዳንዱ ታማሚ፤ ገሚሱ ቆንጆ ሌላው አስቀያሚ፡፡
ከፊሉ ግዙፍ ከፊሉ ድውይ፣ አማርጦ መውደድ አይገባም ወይ?”
ስትሉ ሰማሁ…
እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣
ከታማሚው መጠውለግ ነው የጤነኛው ትኩስነት የሚመነጭ፡፡ እናም እንዲህ እላችኋለሁ፣ አስቀያሚነት የውበት መኳያዋ፣ ቀለም እና ብሩሿ ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑ፣ ድውዩ ቁመቱን ለለግላጋው ባይሰጥ ለግላጋው መለሎ የሚሆን ይመስላችኋል?
እናንተ የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡ ራሳችሁን ላለመከፋፈል ተጠንቀቁ፡፡ ፍሬን በፍሬ ላይ፣ ቅጠልን በቅጠል ላይ፣ ቅርንጫፍን በቅርንጫፍ ላይ አታስነሱ፤ ግንዱንም በሥሮች ላይ፣ ዛፉንም ከእናት አፈሩ አታጣሉ፣ አታናክሱ፡፡ ይህ ደግሞ … በእርግጥም … አንዱን ከሌላው አስበልጣችሁ ወይም ከተቀረው ሁሉ ለይታችሁ ስትወዱ የምታደርጉት ነው፡፡
አዎን … እናንተ ሁላችሁም … የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡ ሥራችሁም የትም ነው። ቅርንጫፍና ቅጠሎቻችሁም በሁሉም ሥፍራ፣ ፍሬዎቻችሁም በሁሉም አፍ ውስጥ! በዚያ ዛፍ ላይ ያሉት የትኞቹም ፍሬዎች፣ የትኞቹም ቅርንጫፍ እና ቅጠሎች፣ የትኞቹም ሥሮች፤ የእናንተው ፍሬ፣ የእናንተው ቅጠልና ቅርንጫፍ፣ የእናንተው ሥሮች ናቸው፡፡
ዛፉ፣ ጣፋጭና ባለማራኪ መዓዛ ፍሬ ቢቸር፣ ሁሌ ጠንካራና ፍፁም አረንጓዴ ሆኖ ቢታይ … ሥሮቹን ወደ መገባችሁበት የሕይወት ወለላ እዩ…
ፍቅር የሕይወት ወለላ ነው፡፡ ጥላቻ ደግሞ የሞት መግል፡፡ ፍቅር ግን ልክ እንደ ደም፣ ሳይታጎልና ሳይገደብ በሕይወት ሥሮች ውስጥ ሊፈስስ ይገባዋል፡፡ የደም ፍሰት ሲገደብ በሽታ እና ወረርሽኝ ይሆናል፡፡ ጥላቻስ ምንድነው? ለጠይውም ለተጠይውም፣ ለመጋቢውም ለተመጋቢውም ገዳይ መርዝ የሆነ የታፍነ፣ የተገደበ ፍቅር እንጂ…
በሕይወት ዛፋችሁ ላይ ያለች ቢጫ ቅጠል፣ ሌላም ሳትሆን ፍቅር-ያስጣሏት ቅጠል ነች፡፡ ቢጫዋን ቅጠል አትውቀሷት። ደርቆ የተንጨፈረረው ቅርንጫፍም ሌላም ሳይሆን ፍቅር የተራበ ቅርንጫፍ ነው። የደረቀውን ቅርንጫፍ አትውቀሱት፡፡ የበሰበሰው ፍሬም ቢሆን ሌላም ሳይሆን ጥላቻ የመረዘው ፍሬ ነው፡፡ የበሰበሰውን ፍሬ አትኮንኑት፡፡
ይልቁንም የሕይወትን ወለላ፣ ለጥቂቶች ብቻ ችሮ ለብዙዎች የሚነፍገውን፣ በዚህም ራሱን ጭምር የነፈገውን፣ ዕውርና ንፉግ ልባችሁን ውቀሱ፡፡ የፍቅር መጸነሻው፣ የመውደድ አብራኩ ራሥን ማፍቀር ነው፡፡
የራስ ፍቅር ቢኖር እንጂ ፍቅር የሚባል ጨርሶ የለም፤ የሚቻልም አይደለም። ከሁሉን አቃፊው እኔነት በቀር የቱም እኔነት እውን አይደለም፡፡ ስለዚህም፣ እግዚአብሔር መላ ፍቅር ነው፤ ምክንያቱም ራሱን ይወዳልና፡፡
ፍቅር ካሳመመህ … መውደድ ስቃይ ከሆነብህ … እውነት እልሃለሁ … እስካሁን ድረስ እውነተኛው ማንነትህ፣ የፍቅር ወርቃማ ቁልፍ ገና እጅህ አልገባም ማለት ነው፡፡ አላፊ ጠፊ እኔነትን ስላፈቀርክ፣ ፍቅርህም እንዲሁ አላፊ ጠፊ ነው፡፡
 የወንድ ሴትን ማፍቀር ፍቅር አይደለም። ይልቁንም የሩቅ ተምሳሌቱ ነው፡፡ ወላጅ ለልጁ ያለው ፍቅርም፣ ሌላም ሳይሆን የፍቅር ቤተ መቅደስ ደጀ ሰላሙ ነው፡፡ የትኛውም ወንድ የሁሏም ሴት አፍቃሪ፣ የትኛዋም ሴት የሁሉም ወንድ አፍቃሪ እስክትሆን ድረስ፤ የትኛውም ልጅ የሁሉም ወላጅ ልጅ፣ የትኛውም ወላጅ የሁሉም ልጅ ወላጅ እስኪሆን ድረስ … ወንዶችና ሴቶች … ሥጋና አጥንት ከሥጋና አጥንት ጋር ስለመተቃቀፍ ይለፍፉ እንጂ … ፈፅሞ በተቀደሰው የፍቅር ሥም ሰይመው አያርክሱት፡፡ ይህ የፍቅርን ሥም ማጠልሸት ነውና፡፡ አንድ እንኳ ጠላት ካለህ ምንም ጓደኛ እንደሌለህ እወቀው። ጠላትነት ያሸመቀ ልብ ለወዳጅ ማደሪያ ይሆናል እንዴ ?
በልቦቻችሁ የጥላቻ ዘር እስካለ ድረስ የፍቅርን ሐሴት አታውቋትም፡፡ የሕይወት ወለላን ለሁሉም መግባችሁ ለአንዲት ቅንጣት ነፍሳት ብትነፍጉ፣ ያቺ የተነፈገችዋ ሕይወታችሁን ታመርረዋለች፡፡ የቱንም ነገር ሆነ ማንንም ስትወዱ፣ እንደ እውነቱ ከሆነ የምትወዱት ራሳችሁን ነው፡፡ ስትጠሉም እንዲሁ ነው … የቱንም ነገር ሆነ ማንንም ስትጠሉ እንደ እውነቱ የምትጠሉት ራሳችሁን ነው፡፡ የምትወዱትና የምትጠሉት ልክ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ላይነጣጠሉ ተጣምረዋልና፡፡ ለራሳችሁ ታማኝ ብትሆኑ ኖሮ፣ የምትወዱትንና የሚወድዳችሁን ከመውደዳችሁ በፊት የምትጠሉትንና የሚጠላችሁን ትወድዱ ነበር፡፡
ፍቅር መልካም ምግባር አይደለም፡፡ ፍቅር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ከዳቦና ከውኃ፣ ከዓየርና ከብርሃን የበለጠ ፍቅር ያሻችኋል፡፡ ማንም በማፍቀሩ አይኩራራ፣ ይልቁንም ነጻ ሆናችሁ እንዲሁ በዘፈቀደ አየሩን ወደ ውስጥ እንደምትስቡትና እንደምታስወጡት ሁሉ ፍቅርንም እንዲሁ በነጻነት ልብም ሳትሉ ተንፍሱት፡፡ ፍቅር፣ ማንም እንዲያወድሰው አይሻም፡፡ ይልቁንም ለፍቅር የተገባ ልብ ሲያገኝ ያን ልብ ያወድስ ይቀድሰዋል እንጂ። ከፍቅርህ ወሮታ አትጠብቅ፡፡ ፍቅር በራሱ ለፍቅር በቂ ሽልማቱ ነው፤ ልክ ጥላቻ ለጥላቻ በቂ ቅጣቱ እንደሆነው ሁሉ፡፡ ከፍቅር ጋር ሒሳብ አትተሳሰቡ፡፡ ፍቅር ሒሳብ የሚያወራርደው ከራሱ ጋር ብቻ ነውና፣ ተጠያቂነቱም ለማንም ሳይሆን ለራሱ ብቻ!
ፍቅር አያበድርም፣ አያውስምም። ፍቅር አይገዛም፣ አይሸጥምም፡፡ ሲሰጥ ግን ሁለመናውን ይሰጣል፡፡ ሲወስድም ሁለመናውን ይወስዳል፡፡ መቀበሉ በራሱ መስጠት ነው፡፡ መስጠቱም በራሱ መቀበል! እናም፣ ለዛሬም፣ ለነገም ለከነገወዲያም እንዲሁ ነው፡፡
ራሱን ሳይሰስት ለባሕሩ የሚለግስ የትኛውም ወንዝ፣ ዘወትር በባህሩ ደግሞ እንደሚሞላ ሁሉ እናንተም እንዲሁ ፍቅር መልሶ ይሞላችሁ ዘንድ ራሳችሁን አንጠፍጥፋችሁ ለፍቅር ስጡ፡፡
አዎን … የባሕሩን ሥጦታ ከባሕሩ የሚነፍግ ኩሬ መጨረሻው መበስበስም አይደል !? በፍቅር … ትንሽ ወይም ትልቅ የሚሉት ነገር የለም፡፡ ፍቅርን መለካት፣ መመተር … ለፍቅር ደረጃ ማውጣት ስትሞክር፣ ፍቅር መራር ትዝታዎቹን አስታቅፎህ እብስ ይላል...
በፍቅር ዘንድ … ትናንት ወይም ዛሬ፣ ዛሬ ወይም ነገ… እዚህ ወይም እዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ወቅቶች የፍቅር ወቅቶች ናቸው፡፡ የትኛውም ቦታ ቢሆን ለፍቅር ማረፊያነት የተገባ! ፍቅርን … ወሰንም ሆነ ዳር ድንበር፣ ካቴናም ሆነ የተዘጋ በር አይገድበውም፡፡ የትኛውም መሰናክል ጉዞውን ያሰናከለው ፍቅርም በተቀደሰው የፍቅር ሥም ለመጠራት ባልተገባው፡፡
ዘወትር፣ ፍቅር ዕውር ነው ብላችሁ ስታወሩ እሰማለሁ፡፡ አዎን፣ አፍቃሪ በተፈቃሪው ላይ አንዳችም እንከን አያይም ማለታችሁ ነው፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ … ይሄ ዓይነት አለማየት የማየት ከፍታ ጫፍ ነው፡፡
በምንም ነገር ላይ እንከን አታዩ ዘንድ ምነው ሁሌ በታወራችሁ፡፡----
(ከ“መጽሐፈ ሚርዳድ” በሚካኤል ኔይሚ - ትርጉም - ግሩም ተበጀ)

   ሰሞኑን በታላቋ አገር አሜሪካ፤ ፊላዴልፊያ ግዛት  ውስጥ  ተፈጸመ የተባለው  ጉዳይ ብዙዎችን ጉድ አሰኝቷል። እንኳን በገሃዱ ዓለም ቀርቶ በሆሊውድ ፊልሞችም ይቅርና በፊልምም ሆነ በልብወለድ ቢቀርብ የሚታመን አይደለም። ግን ድርጊቱ በእውን ተከስቷል- በአሜሪካ ምድር። ያውም በጠራራ ፀሃይ። ያውም በአደባባይ፤ ሰዎች በተሰበሰቡበት። አዎ ምድር ለምድር በሚምዘገዘግ ባቡር ውስጥ  ነገር ይጀምራታል-ይተነኩሳታል። ምድር ከፖሊስ እስከ ጋዜጠኛም ጉድ አሰኝቷል።
ድርጊቱ የተከሰተው ባለፈው ረቡዕ ነው። በፊላዴልፍያ ግዛት የምድር ለምድር የመንገደኞች ባቡር  ውስጥ 10  መንገደኞች ተሳፍረዋል።
ፌርማታ የተሳፈረው የ35 ዓመቱ ፊትሶን ንጎ የተባለ የጎዳና ተዳዳሪ ጎልማሳ ብቻዋን ተቀመጠች አንዲት ተሳፋሪ አጠገብ ሆዶ ይቀመጣል። ብዙም ሳይቆይ ከዚህች  ከማያውቃት ተሳፋሪ ጋር ትግል ይጀምራል። ደጋግማ  እየገፈተረች ራሷን ለመከላከል ብትሞክርም  በመጨረሻም ግን አልቻለችም ተሸነፈች።
ያ ሁሉ ተሳፋሪ ባለበት አስገድዶ ይደፍራታል። አሳፋሪውና አሳዛኙ ነገር አንድም ሰው ጣልቃ ገብቶ ከጥቃቱ ሊያድናትና ሊታደጋት አለመቻሉ ነው። ሌላው ቀርቶ ለፖሊስ እንኳን ለመደወል የሞከረ አልነበረም። ሁሉም ግን በሞባይል ካሜራ ጥቃቱን እየቀረፀ ነበር።
አንደኛው ፌርማታ ላይ ፖሊስ ደርሶ ጥቃት ፈፃሚውን በቁጥጥር ስር እስኪያውለው ድረስ ለ6 ደቂቃ ያህል ተሳፋሪዎቹ ድርጊቱን ሲቀርፁ እንደነበር ባቡሩ ውስጥ የተገጠመው የቅኝት ቪዲዮ ካሜራ ያረጋግጣል።
ተሳፋሪው ሴትየዋን ከጥቃቱ ለማዳን ግን መረዳቱ ቢቀር እንኳን ይሄን አሰቃቂ ጥቃት በፊልም  እየቀረጸ ከ5 ደቂቃ በላይ የማየት ብርታት እንዴት ኖረው  ፍላጎት አለማሳየቱ ከፍተኛ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ አያጠራጥርም።
“ባቡሩ ውስጥ ከነበረው ብዙ ተሳፋሪ አንጻር፣ ቢያንስ አንዳቸው ጣልቃ ገብተው አንድ የሆነ ነገር ማድረግ ነበረባቸው” ያለው አንድ የአካባቢው ፖሊስ፤ “እንዲህ ያለ ድርጊት ሲፈጸም ነው ዝም ብሎ ያያል፤ ህብረተሰባችን የደረሰበት ቀውስ ይናገራል፤ በጣም የሚረብሽ ነገር ነው” ብለዋል።
በነገራችን ላይ ፖሊስ በሴትየዋ ላይ ስለተፈፀመው ጥቃት  በሰጠው መግለጫ፤ “አስፈሪ የወንጀል ድርጊት ነው ብሎታል።
ማንም ሰው እንዲህ ያለ ድርጊት ሲገጥመው ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርግም አስበዋል። “ድርጊቱን ሲመለከቱ የነበሩ ሰዎች አሉ። አንዱ ተሳፋሪ እንኳን 911 ቢደውል ኖሮ፣ ጥቃቱን በፍጥነት ማስቆም ይቻል ነበር” ነው ያሉት ፖሊሱ። ጥቃት ፈጻሚው አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በ3 የወንጀል ድርጊቶች በፍ/ቤት ክስ እንደተመሰረተበት ታውቋል።
የጥቃቱ ተጎጂ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል መወሰዷን የጠቆመው ፖሊስ፤ በርካታ መረጃዎች መስጠቷን በመጥቀስም “በጣም ጠኝካራ ሴት ናት” ሲል ብርታቷን አድንቋል።

   -  ያልተደራጀና ወጥነት የሌለው የድጋፍ አሰጣጥ ትርምስ ፈጥሯል
    - ዓለማቀፍ ተቋማት ለተፈናቃዮች ትኩረት እንዲሰጡ ሁሉም ድምጹን ያሰማ

           ከሰሞኑ ባገረሸው ጦርነት ሳቢያ የደቡብ ወሎ አካባቢ በተፈናቃዮች እየተጨናነቀ ነው፡፡ የጠላት ጦር ወደ አካባቢው ሊገባ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ማረበቡን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ምን ይመስላል? ተፈናቃዮች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? የዓለማቀፍ ሰብአዊ ድጋፍ ተቋማትስ? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአካባቢው የሰብአዊ ድጋፎችን በማድረግ ተግባር ላይ የተሰማራው የ”ወሎ ህብረት የልማትና በጎ አድራጎት ማህበር” አመራር አቶ ያሲን መሐመድ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል። እነሆ፡-

               እስካሁን በአካባቢው ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ምን ይመስላል?
የሰብአዊ ድጋፍ ሁኔታ ደረጃውን የጠበቀ የተደራጀና ወጥነት ያለው አይደለም። በአለማቀፍ ደረጃ በሚታወቁ የድጋፍ ስታንዳርዶች አይደለም የሚሰራው፤ ዝም ብሎ በጨበጣ፣ ግለሰቦች  በሚያመጡት ሃብት ላይ የተንጠለጠለ፣ ማዕከል  የሌለው  አይነት ነው። የተወሰኑ የማዘዣ ማዕከላት አሉ፤ ነገር ግን እርዳታውን እናስተባብራለን የሚሉ አካላት ፖለቲካው ላይ ተሳታፊ ስለሆኑ፣ ጦርነቱንም መምራት ይሻሉ። አጠቃላይ ፖለቲካውን መቆጣጠር ይፈልጋሉ። ከዚያው ጎን ለጎን እርዳታውንም እነሱ ብቻ ማስተባበር ይሻሉ፡፡ ስለዚህ የእርዳታ አሰጣጡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ አንዳንድ ወገኖች በአንድ እግራቸው ፖለቲካው ላይ በሌላ እግራቸው ሰብአዊ ድጋፉ ላይ መቆማቸው፣ በተለይ የሰብአዊ ድጋፍ በሚመለከታቸው የሰብአዊ ድጋፍ ተቋማት ትኩረት እንዳያገኝና ማህበረሰቡ ተገቢውን ድጋፍ እንዳያገኝ እያደረገው ነው። እኔ ለምሳሌ  ወደ 40 የሚጠጉ የቤተሰብ አባሎቼ ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ የኔ ዘመዶች እንኳ ተነስቼ ባስረዳ፣ 75 በመቶ የሚሆኑት እስካሁን አንድም ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም። በአንጻሩ ሌሎች የሚቀርበውን ድጋፍ ከሚገባቸው በላይ ደጋግመው የሚወስዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ ሁሉ የድጋፍ አሰጣጡን በትርምስ የተሞላና ወጥነት የሌለው አድርገውታል። ይሄም የድጋፍ አሰጣጡን ለተበላሸ አሠራር የተጋለጠ ያደርገዋል። አብዛኛዎቹ እርዳታ ወሳጆች ደግሞ ወጣቶች መሆናቸውን ስናይ፣ አቅመ ደካሞች በአግባቡ የማያገኙበት ዕድል እንደሚፈጠር መገመት አያዳግትም። ይሄን ሁሉ የፈጠረው ወጥነት ያለው የድጋፍ አሰጣጥ ስርዓት አለመዘርጋቱ ነው። የእያንዳንዱ ተፈናቃይ ትክክለኛ መረጃ ተመዝግቦ አለመያዙም በዚህ እርዳታ አሰጣጥ ላይ ችግር እንደፈጠረም  መረዳት ተችሏል። በዚያ ላይ የተረጂው ቁጥር በትክክል ሳይመዘገብ፣ ምን ያህል ተጠባባቂ ክምችት እንዳለ ሳይታወቅ፤ እጅግ በጣም በተምታታ ሁኔታ ነው ድጋፍ ሲሰጥ የቆየው- በተለይ ከሁለት ወራት ወዲህ።
ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ነገሩ መልኩን እየለወጠ መጥቶ ጦርነቱ ከወሎ ምድር ይወጣል ሲባል፣ ጭራሽ እየገፋ በመሄዱ ነጻ የነበሩ መሬቶች በጠላት ቁጥጥር ስር እየሆኑ መጡ። ይሄን ተከትሎም ተፈናቅለው በየቦታው የነበሩ ሰዎች ጠላት ሲጠጋ፣ እነሱም ከተፈናቀሉበት ቦታ በድጋሚ ወደ ኮምቦልቻ፣ ሃርቡ የመሳሰሉ ከተሞች  እየተፈናቀሉ ነው ያለው። በየትምህርት ቤቶቹ ያለው የተፈናቃይ ሁኔታ ደግሞ በእውነቱ ልብ የሚሰብርና እጅግ አሳዛኝ ነው። የሚገርመው ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም የመንግስት አካል ብቅ ብሎ አለማየቱና ተፈናቃዮችን ለማጽናናት አለመሞከሩ ነው።
በሌላ በኩል፤ ህዝቡ ተፈናቅሎ ወደ ትላልቅ ከተሞች ሲጎርፍ፣ የጠላት ሰላይ ከህዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ቢመጣ እንኳን የሚጣራበት መንገድ አለመኖሩ ያሳስባል። እኛ እንደውም እነዚህን ተፈናቃዮች ለአንድ ቀን የሚሆን ብስኩት ያቀመስናቸው ከመከላከያ ለምነን ነው። በተረፈ ህብረተሰቡ ነው ባለው አቅም እርስ በርሱ እየተረዳዳ ያለው።
የዓለማቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች በአካባቢው የሉም?
አሉ፤ ነገር ግን የተቀናጀ ስራ እየሰሩ አይደሉም። የመንግስት ድጋፍ አድራጊዎችም አሉ፤ ግን እንዳልኩት ድጋፉ የተቀናጀና መሰረታዊ የእርዳታ አሰጣጥ መስፈርቶችን  ያሟላ አለመሆኑ ነው ችግር የተፈጠረው። በየእርዳታ ማዕከሉ ሰዎች በጠዋት ይሰለፋሉ። ነገር  ግን ማታ ባዶ እጃቸውን ይበተናሉ። ይህ ነው እየሆነ ያለው። በነገራችን ላይ ሰዎች ሊረዱት የሚገባው ጠላት ከወረራቸው አካባቢዎች ወደ ደሴና ሌሎች ከተሞች የገቡ ተፈናቃዮች፣ በየሰው ቤት ተጠልለው ነው ያሉት፤ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አይደለም ያሉት።  በደሴ ከተማ እያንዳንዱ ሰው በየቤቱ  ቢያንስ እስከ 15 የሚደርሱ ተፈናቃዮችን አስጠልሎ ከቤተሰቡ እየቀነሰ እየመገበ ነው። አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝተኛ የከተማው ህዝብ ምን ያህል የወገኖቹን ስቃይ እንደተሸከመ መረዳት አያዳግትም። ይሄን ማህበረሰቡ ውስጥ የገባውንና በየቤተሰቡ የተጠለለውን ተፈናቃይ፣ መንግስትም ሆነ ረድኤት ድርጅቶች አያስቡትም። ድጋፋቸውም ሪፖርታቸውም እኒህን ተፈናቃዮች ታሳቢ ያደረገ አይደለም። በየቦታው ተከራይተው የሚኖሩም ተፈናቃዮች አሉ። እነዚህ እንግዲህ የራሳቸው ገቢ የሌላቸው፣ በሰው ድጋፍ የሚኖሩ፣ የእርዳታ ማግኛ መንገዱን ያላገኙ ዜጎች ናቸው። መንግስት ይህን ሁኔታ ተረድቶ በጊዜ ማስተካከያ ካላደረገ፣ በቀጣይ ሊከሰት የሚችለው ሰብአዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ነው የሚሆነው፡፡ በአካባቢው ያሉ የመንግስት አካላትም ሆኑ የረድኤት ተቋማት፣ ችግሩን አሳንሰው በመመልከት፣ ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑ የከፋ ችግር እንዳይፈጥር ስጋት አለን።
በጦርነቱ ያጋጠመውን ሰብአዊ ቀውስ በተመለከተ ጥናት ስታካሂዱ ነበር፤  ምን ላይ ደረሰ?
አሁን ያሰባሰብናቸውን መረጃዎች በመተንተን ላይ ነው ያለነው። መረጃዎችን ወደ ሪፖርት ለውጠን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን። ጥናታችን በጣም ሰፊ ነው። በቀጣይ ሪፖርቱ ለሁሉም እንዲደርስ እንጥራለን።
“ወሎ ህብረት” በአሁኑ ወቅት ምን አይነት ድጋፎችን እያደረገ ነው? ተፈናቃዮችስ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
በዚህ ቀውስ የሚያሳዝነው ነገር፣ ሴቶችና እናቶች ሶስትና አራት ህጻናት ይዘው ላለፉት 3 ወራት ጫካ ውስጥ ነው ተሸሽገው  የቆዩት።  በተለይ በሶዶማ፣ በድሬ ሮቃ ጦርነት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጫካ ውስጥ ነው ተደብቀው የኖሩት። በጠቅላላው አካላቸው በእጅጉ የተጎዳ፣ ለመንቀሳቀስ እንኳ አቅም ያነሳቸው ተፈናቃዮች ናቸው። እውነት ለመናገር እነዚህን ወገኖች እየደገፈ ያለው የአካባቢው ማህበረሰብና በግላቸው እርዳታ ያሰባሰቡ ሰዎች ናቸው። አለማቀፍ ተቋማት ለአካባቢው የሰጡት ትኩረት በጣም አናሳ ነው። የእኛ ተቋም “ወሎ ህብረት” ቀደም ሲል ሲሰራ የነበረውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አሁን ሊሰራ አይችልም። ምክንያቱም እኛ  ከበጎ አድራጎት ስራዎች ጎን ለጎን  የወሎ ማህበረሰብን አደጋ ውስጥ የጣለ ሁሉ ወራሪ ነው ብለን ነው የምናምነው። ስለዚህ በዚህ አቋም በአካባቢው በነጻነት እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት መንቀሳቀስ አንችልም።  እኛ ስናደርገው የነበረው የድጋፍ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎብናል ማለት ነው። የኛ ተቋም በነጻ ህክምና መስጠትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ያደርግ ነበር። ይሄን ሁሉ አሁን ላይ ማከናወን አልቻልንም፤  ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ማለት ነው።
በአካባቢው ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? የጦርነቱ ስጋትስ ምን ያህል ነው?
አንደኛ፤ አሁን ጦርነቱ ገፍቶ ደቡብ ወሎ በአመዛኙ ከተያዘ፣ ብዙ ነገር ተበላሸ ፈረሰ ማለት ነው። በነገራችን ላይ  አለማቀፉ ተቋማት ወሎ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በሚገባ ያውቁታል። ግን ለምን ዝምታ  እንደመረጡ አይታወቅም። በነገራችን ላይ የጦርነቱ ስጋት ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ነው። ነገርዬው አፋጣኝ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል፡፡ አለማቀፍ ተቋማትም ነገሩን በቸልታ እንዳይመለከቱ፣ ሁሉም ድምፁን ሊያሰማ ይገባል።
ህወኃት ከሰሞኑ እንደ አዲስ የቀሰቀሰው ጦርነት በነዋሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሯል ማለት ይቻላል?
እንግዲህ  አሁን በከተሞች አቅራቢያ የከባድ መሳሪያ ድምጾች በየሰአቱ እየተሰማ ነው፡፡ ደሴ አካባቢ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ይሰማል። (ቃለ ምልልሱ የተደረገው ረቡዕ ነው) በዚህ ሁኔታ ውስጥ ህፃናትና ሴቶች ይረበሻሉ። በተለይ ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ በደሴ አካባቢ ይሰማ የነበረው የከባድ መሳሪያ ድምጽ በጣም  ነበር የሚረብሸው። የጠላትን ወረራ በተመለከተ ግን ብዙ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። እንዴት ጠላት በዚያ መጠን እስኪጠጋ ድረስ ዝም ተባለ? ሳይጠጋ መከላከል ወይም መመከት የሚቻልበት መንገድም አልነበረም?  አሁን የጠላት ሃይል ወደ ከተሞች የመጠጋት ሁኔታ እያሳየ ነው፡፡ ይሄ ማህበረሰቡ ላይ ስጋት ቢደቅን የሚገርም አይሆንም። ባዶ እጁን ያለ ህዝብ ነው። ህፃነትና ሴቶች ቢሸበሩ የሚደንቅ አይደለም። መንግስት ለዚህ በቂ ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑ ደግሞ በእጅጉ አጠያያቂ ነው።

ከነ አያ አንበሶ በታች ያሉት የዱር አራዊት ሁሉ ተሰብስበው ትልቅ ግብዣ ተደረገና ዳንሱ፣ ጭፈራው፣ ዳንኪራው ቀለጠ! ደራ! ከደናሾቹ መካከል ጥንቸል ተነስታ፤
“ዝም ብለን ከምንደንስ እንወዳደርና ምርጥ ዳንሰኛው ይለይ!” አለችና ሃሳብ አቀረበች፡፡ በሃሳቡዋ ሁሉም ተስማሙና ጭፈራው ቀጠለ፡፡ ሁሉም በተራ በተራ ወደ መድረክ እየወጣ ችሎታውን አሳየ፡፡
በመጨረሻ ዳኞች ተሰይመው ውጤት ተነገረ፡፡ በውጤቱ መሰረት አንደኛ - ዝንጀሮ፣ ሁለተኛ ቀበሮ፣ ሶስተኛ - ጦጣ ሆኑ፡፡
ዝንጀሮ መመረጡን በማስመልከት መድረክ ላይ ወጥቶ ተጨማሪ ዳንስ በማሳየት ታዳሚዎቹን አራዊት አዝናና፡፡ ንግግርም አደረገ፡፡ አራዊቱ በጣም በመደሰት ንጉሣችን ይሁን ብለው ወሰኑ፡፡
በዝንጀሮ ንጉሥ መሆን ቀበሮና ጦጣ ቅናት እርር ድብን አደረጋቸው፡፡ ስለዚህ መዶለት ጀመሩ፡፡
ጦጣ፤ “አያ ቀበሮ መቼም ከዳኝነት ስተት ነው እንጂ ዝንጀሮ ከእኛ በልጦ አይመስለኝም። አንተስ ምን ይመስልሃል?”
ቀበሮም፤ “እኔም እንዳንቺው ነው የማስበው፡፡ የዘመድ ሥራ ነው የተሰራው፡፡ ግን አንዴ ሆኗል ምን ይደረጋል?”
ጦጣ፤ “አንዴ ሆኗል ብለንማ መተው የለብንም”
ቀበሮ፤ “ምን እናደርጋለን ታዲያ?”
ጦጣ፤ “እኔ ወጥመድ ላዘጋጅ፡፡ አንተ እንደ ምንም ብለህ ወጥመዱ  ጋ አምጣልኝ” አለችው።
“ወጥመድ ላይ ሥጋ አድርጌ እጠብቃችኋለሁ፡፡ አንተ ዝንጀሮን ትጋብዘዋለህ” ቀበሮ በሃሳቡ ተስማምቶ ዝንጀሮን ሊያመጣው ሄደ፡፡
ዝንጀሮ በአዲስ የሹመት ስሜት እንደሰከረ፤ እየተጐማለለ ይመጣል፡፡ “ይህን የመሰለ ሙዳ ሥጋ አስቀምጬልሃለሁ” አለው ወደ ሥጋው እያሳየው፡፡
ዝንጀሮም፤ “አንተስ? ለምን አልበላኸውም?” ይሄን የመሰለ ሙዳ እንዴት ዝም አልከው?” አለው፡፡
ቀበሮ፤ “ውድ ዝንጀሮ ሆይ! ለንግሥናህ ክብር ይሆን ዘንድ ብዬ ያዘጋጀሁት ነውና ስጦታዬን ተቀበለኝ?” አለው እጅ በመንሳት፡፡
ዝንጀሮ “ስጦታህን ተቀብያለሁ፤” ብሎ ወደ ወጥመዱ ዘው አለ፡፡ እዚያው ታስሮ ተቀረቀረ! ተናደደ! በምሬትና በቁጭት በደም ፍላት ተናገረ፤
“ለዚህ አደጋ ልትዳርገኝ ነው ለካ ያመጣኸኝ? አንት ሰይጣን! ለንዲህ ያለ ወጥመድ ነበር ለካ ስታባብለኝ የነበረው? አረመኔ!” አለው፡፡
ቀበሮም፤ እየሳቀ፤ “ጌታዬ ዝንጀሮ ሆይ! የአራዊት ንጉሥ ነኝ እያልክ፤ ግን እቺን ቀላል አደጋ እንኳን ማለፍ አልቻልክም! ይሄ የመጀመሪያ ትምህርት ይሁንህ" ብሎ ጥሎት ሄደ፡፡
*   *   *
“ሹመት ያዳብር” የሚለውን ምርቃት የሀገራችን ህዝብ ጠንቅቆ ያቃል፡፡ በልቡ ግን “አደራዬን ተቀበል” የሚል ጠንካራ ማስጠንቀቂያና ጠንካራ መልዕክት ልኮ ማስገንዘቡ ነው። ካልሆነ አደራ በላ ትሆናለህ!
አደራ! ሲባል፤ የመብራት የውሃዬን ነገር አደራ ማለቱ ነው፡፡
አደራ! ሲባል፤ የትምህርትን ነገር ጠንቅቀህ ምራ ማለት ነው፡፡ ውስጡን በደምብ መርምር ማለት ነው፡፡ አደራ ሲባል፤ የኢንዱስትሪውን ሂደት፤ የትራንስፖርቱን (የባቡሩን፣ የመኪናውን፣ የአየሩንና የእግሩን ጉዞ) ነገር በቅጡ በቅጡ ያዙት ማለት ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃውንና የሳይንስና ቴክኖሎጂው ጉዳይ ዕውነተኛ አሠራር፣ ብስለትና ከዓለም ጋር የሚሄድ እንዲሆን ማድረግ ዋና ነገር ነው ማለት ነው፡፡
አደራ! ሲባል በተለይ የገቢዎችን ነገር፣ እከሌ ከእከሌ ሳትሉ ኢ-ወገናዊ በሆነ ዐይን በማየት፤ የታረመ፣ የተቀጣ፣ ከስህተቱ የተማረ አካሄድ እንድትሄዱ ማለት ነው፡፡
አደራ! ሲባል የኑሮ ውድነቱን፣ የዋጋ ማሻቀቡን ጉዳይ አንዳች መላ አበጁለት ማለት ነው፡፡
አደራ ሲባል! በዚህ በደቀቀ ኢኮኖሚ ላይ የህዝብ ሃብት ያለ አግባብ አታባክኑ፤ እያንዳንዱን ሳንቲም ለቁም ነገር አውሉት ማለት ነው፡፡
አደራ! ሲባል፤ የሥራ ዕድል የሚፈጥረውን የግል ዘርፉን የሚያበረታታ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አሰራር አትዘርጉ ማለት ነው፡፡ አደራ! ሲባል፤ ጠ/ሚኒስትሩ ዓምናም ዘንድሮም (ሰሞኑን) እንዳደረጉት፣ ለምስጉን ግብር ከፋይ ባለሃብቶች፣ ሽልማትና ዕውቅና በመስጠት፣ ሃቀኝነትንና ታማኝነትን አበረታቱ ማለት ነው፡፡  
አደራ! ሲባል ከሁሉም በላይ ጸጥታንና ደህንነትን አረጋግጡ፤ማንም የትም ሰርቶ መኖርን ህገ መንግስታዊ መብት አድርጉለት ማለትም ነው፡፡   
አደራ ሲባል በአጭሩና በጥብቁ ቋንቋ “አደራ - በላ አትሁኑ” ማለት ነው፡፡
በተለምዶ እኛ አገር “ባለፈው ሥርዓት” የሚል ፈሊጥ አለ፡፡ “ያለፈው ሹም ጥፋተኛ ነበር፣ ደካማ ነበር፤ እኔ ግን አንደኛ ነኝ…” ዓይነት አንድምታ ያለው ነው፤ ያለፈው ሹም የበደላችሁን እኔ እክሳለሁ! እንደማለትም አለበት፡፡ ይህን እንጠንቀቅ፡፡
የተሻሪም የተሿሚም ሂደት ተያያዥ ሥርዓት ነውና ሰንሰለቱ ተመጋጋቢ ነው፡፡ እንጂ የወረደው ጠፊ፣ የተሾመው ነዋሪ ነው ማለት አይደለም፡፡ በቅንነት፣ በሰብዓዊነት፣ በለሀገር አሳቢነት ካላየነው፤ ሁሉም ነገር ከመወነጃጀል አይወጣም፡፡ በተሰበሰበ ቀልብ፣ በሙያ ክህሎትና በዲሞክራሲያዊ አረማመድ ነው ፍሬያማ ለመሆን የሚቻለው፡፡ ያንን ካልተከተልን ንጉሥ ነኝ እያልክ ይቺን ቀላል አደጋ እንኳን ለማለፍ አቃተህ” እንባባላለን፡፡
ጐባጣውን የምናቃናው፣ ጐዶሎውን የምንሞላውና የምናስተካክለው፤ መዋቅር የምናጠናክረው፣ እዚህ ጋ ተሳስተናል እንተራረም የምንባባለው፤ ለሀገር ይበጃል፣ ብለን ነው። የሾምነውና ያስቀምጥነው ሰው ተስተካክሎ የተበጀውን ሥርዓት ለግል ጥቅሙ ካዋለ፤ አደራውን ከበላ፣ አድሎኛ ከሆነ፣ በመጨረሻም ያለውን ሁኔታ ከመጠበቅ አልፎ በማሻሻል፤ ለውጥ ካላመጣ፣ የወላይትኛው ተረት እንደሚለው፤ “ፈርጅ ያለው ነጠላ አሰርቼ፤ መልክ የሌለው ሰው ይለብሳል” ሆነ ማለት ነውና ከወዲሁ እንጠንቀቅ፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”ን እንዋጋ!
“ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፡፡ መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው” የሚለውንም አንዘንጋ፡፡

  • የአማራ ክልል ነባራዊ ሁኔታ ፈተናዎች ተስፋዎች (በጦርነት- መፈናቀል- መስዋዕትነት)
        • ወደ 4ሚ. የሚጠጋ ህዝብ ነው እርዳታ የሚጠብቀው
        • በእርዳታና በመድሃኒት እጦት ሰዎች እየሞቱ ነው

        አሁን አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ የህልውና ዘመቻ ተከትሎ በተለይ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ የዋግ ህምራና የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ችግር መፈናቀልና ሰብአዊ ቀውስ እየደረሰ ይገኛል። የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የአማራ ክልል መንግስት ጉዳዩን እንዴት ያየዋል? ጦርነቱ እንዴት ነው የሚቋጨው፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉና በተወረሩ አካባቢዎች ያሉት ወገኖች ጉዳይ እንዴት ይታያል? የእርዳታ አሰጣጡስ ጉዳይ ምን ይመስላል በሚሉና በተያያዥ ጉዳች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ባህርዳር ተጉዛ የክልሉን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህን በጽ/ቤታቸው እንደሚከተለው አነጋግራቸዋለች። እነሆ፡-


           በክልሉ የአዲስ መንግስት ምስረታው እንዴት ነበር? የመንግስት ባለስልጣናት ሹመትስ ምን ይመስላል? ህዝቡስ  በአዲሱ መንግስት ስሜቱ ምን ይመስላል?
እንግዲህ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተካሂዷል። ይህ ምርጫ ከሌሎች ጊዜያት ምርጫዎች በብዙ ምክንያት ለየት ብሎ የተካሄደ ነው። የመጀመሪያው ለየት የሚልበት ወቅቱን ጠብቆ የተካሄደ  አልነበረም። በኮረና ወረርሽኝና በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በተለይም ኮሮና ቫይረስ ባደረሰው ከፍተኛ ጫና ምርጫውን በወቅቱ ማስኬድ አልተቻለም። አንዱ ይሄ ነው። ሁለተኛ ይህ ምርጫ ከሌሎቹ አምስት ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ ህዝቡ የተሳተፈበት፣ እውነተኛ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የተካሄደበትን ሂደት ያሳየ ነው። ምንም እንኳ በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር፣ ምርጫው ዘግይቶ ቢካሄድም ያሸነፈው ፓርቲ ከፌደራል እስከ ክልል የመንግስት ምስረታ ተካሂዷል። የመንግስት ምስረታ ማካሄድ ብቻ አይደለም፤ አጠቃላይ የመንግስት ምስረታና አደረጃጀቱን መልሶ የማጠናከር ስራው አሁን ላይ በክልላችን ከዞን እስከ ወረዳዎች ደርሶ እየተሰራ ነው።
ይህን ስንመለከት እንደ አማራ ክልል፣ በአዲስ መንግስት ምስረታ፣ በተለይም የአመራር የሃላፊነት ቦታ አሰጣጥን በተመለከተ ከ75 በመቶ በላይ አዳዲስ አመራሮች የመጡበት መንግስት ምስረታ ነው የተካሄደው። የአዳዲስ አመራሮች መምጣት ብቻ ሳይሆን ከቀድሞው ባልተለመደ ሁኔታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሸንፈው መንግስት ባይመሰርቱም እንኳን የዴሞክራሲ ስርጭቱን የበለጠ ለማስፋት፣ በተለይ የማቻቻል ባህላችንን ለማሳየትና አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለመክፈት፣ በተለይም ከብሄራዊ መግባባትና ከሀገር ግንባታ አኳያ፣ የተለየ ገጽታ ስላለው፣ በካቢኔ ደረጃ የተሾሙበት ለየት ያለ ስልት የፈጠረ ነው። በሌላ በኩል፤ ምሁራን የመጡበት፣ በስነ- ምግባራቸው ላቅ ያለ ደረጃ ያላቸው፣ የመስራት ፍላጎታቸው ከፍተኛ የሆነ ጭምር ሰዎችን ለመቀላቀል ተሞክሯል።
ሌላው ከተዋፅኦ አኳያ ብንመለከት ከሁሉም አካባቢዎች የመመልመል ስራ ተሰርቷል። ይህ እንግዲህ የተሳካ አካሄድ ነው ብለን እናምናለን። ከመቼውም ጊዜ በላይ ህዝቡ ተስፋ የሚያደርግባቸው መሪዎች የመጡበት ጊዜም ነው። ክልሉ አንደምታውቂው ብዙ ውስብስብ ችግር ያሉበት ነው ። ጠላቶቹም ብዙ ናቸው። አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ አኳያ፣  የተደረገው የአመራር ስምሪትና የመንግስት ምስረታው ችሮችን ሁሉ ይፈታል የሚል ተስፋ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ነው። እንዴት ካልሽኝ? ከመንግስት ምስረታው በኋላ የህዝብ አስተያየት እስከ ታች ድረስ ሰብስበን ነበር። ከመጣው የህዝብ አስተያየት መካከል  ማለትም ከተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ከ90 በመቶ በላይ ምስጢር ተጠብቆ ሳይዝረከረክ ስነ-ስርዓቱን ጠብቆ የተካሄደ ምርጫ ነው የሚል ነው። የሌላ ሶስተኛ ወገን ተፅዕኖ ሳይኖር፣ በአውጫጭኝና በጎጥ ሳይመደብ፣ ራሽናል በሆነ መንገድ የተካሄደ ስለመሆኑ ህዝቡ በአስተያየቱ  ተገልጿል። በአጠቃላይ የመንግስት ምስረታው፣ በምስረታው የተመረጡ አመራሮችና በአጠቃላይ ሂደቱ ህዝብ ተስፋ እንዳደረበት የሚያሳይ ነው።
ሌላው ከመንግስተ ምስረታው ቀጥሎ የተዋቀረው የካቢኔ አባል አጠቃላይ የስራ ድርሻችን ምንድን ነው? በሚል የመግቢያ ኮርስ ውይይት ተደርጓል። አሁንም በክልሉ ተቀዳሚው ሥራ፤ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ ሲሆን የክልሉ ህዝብ ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ የማሳየትና የደህንነት ጉዳይ ቀዳሚ ነው ብሎ ስራውን ጀምሯል። ቀጥሎ ደግሞ የአማራ ህዝብ ጥያቄ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮችን በዝርዝር ለመፍታት የሚያስችሉ እቅዶች ላይ ኦሬንቴሽን ተሰጥቶ አዲሱ መንግስት ወደ ስራ የገባበት ሁኔታ አለ።
ትህነግ ጦርነት ከከፈተ እነሆ አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት። በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል የተባለው ጦርነት እየተስፋፋ ይገኛል። አሁን በምንነጋገርበት ወቅት  እንኳን እንደነ ወልዲያ ላሊበላና ሌሎች ከተሞች ተይዘው ይገኛሉ።  በርካታ የአማራ ህዝብ ለሞትና ለመፈናቀል ተዳርጓል። ይህንን ጦርነት በአጭሩ ለማጠናቀቅ ምን መደረግ ነው ያለበት? የዚህ ጦርነት ገፈት ቀማሽ የሆነው የአማራ ህዝብ፣ በአሁኑ ሰዓት ጦርነቱን ከመመከት፣ ሰራዊቱን ከመደገፍና ከመታገል አኳያ ያለው ስሜት ምን ይመስላል? ምክንያቱም በመንግስት በኩል መዘናጋትና ክፍተቶች አሉ የሚል ቅሬታ ይሰማል…
መልካም! እንዳልሽው የህልውና አደጋን በተመለከተ ስናነሳ፣ ክልላችን ላይ አሸባሪው የህወሃት ሀይል ሁለት ጊዜ ወረራ ፈጽሟል። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የነበረው ወረራ አለ። በድጋሚ ከአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ሌላ ወረራ ተፈጽሞብናል። ስለዚህ የመጀመሪያው የህግ ማስከበር ዘመቻ ነበር። ሁለተኛው ህልውና ላይ የተጋረጠ ወረራ ስለሆነ የህልውና ዘመቻ ተደርጓል። እንዳልሽው አጠቃላይ ወረራው ከ11 ወራት በላይ የዘለቀ ነው።
በታሪክ አጋጣሚ ደግሞ ክልላችን አጎራባች በመሆኑ ዋጋ እየከፈለ ነው ያለው። በአጠቃላይ የአሸባሪውን የህወሃት እንቅስቃሴ በተመለከተ በወረራ ብቻ የሚቆም አይደለም።
የወረራው መንፈስና ዓላማ፣ አጠቃላይ አገርን የማፍረስ፣ ከተቻለም ዳግም አገርን እየመራ እንዳለፉት 30 ዓመታት መበዝበዝ ነው። ይሄ ነው አጠቃላይ እንቅስቃሴውና የፕሮጀክቱ ዓላማ።
ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት የሚሳካ አይደለም። እንዳይሳካም አስፈላጊው ነገር ሁሉ እየተደረገ ነው ያለው። የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጡ ልዩ ሀይሎች፣ ሚሊሻዎችና ወጣቶች በከፍተኛ ደረጃ ተደራጀተው ህልውናቸውን ለማስከበር ትግል ላይ ናቸው።  በደንብ እየተዋጋን አይደለም፤ ክፍተት አለ ላልሺው፣ ይሄ ሀሰት ነው። በዚህ ጉዳይ ኦፕሬሽኑን እየመራ ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነው።  ጦርነት ሳይንስ ነው።  ይህንን የሳይንሱ ባለቤቶቹ የሚተነትኑት ነው። መቼ ያበቃል? ለምን አላለቀም? የሚሉና መሰል ጥቄዎች በዚያው ይመለሳሉ። እርግጥ የኦፕሬሽኑን ሥራ ፖለቲከኛው በበላይነት ይመራዋል። ይሄ ምንም ጥያቄ  የለውም። ነገር ግን እነዚህ አይነት ነገሮች ከደህንነት ጉዳይ አኳያ ቴክኒክ የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ በዝርዝር መነጋገር አንችልም። አጠቃላይ ዝግጅቱን በተመለከተ ግን ከእኛ የሚጠበቀውን በሙሉ እያደረግን ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ እስካሁን  ከሰራቻቸው በተለየ ሁኔታ የመከላከያና የልዩ ሀይሉን ለማጠናከር ከፍተኛ የሰው ሀይል የማደራጀት ስራ ተሰርቷል። ይሄ አንድ ትልቅ ለውጥ  የሚታይበት ነው።  ህዝቡ ከአንድ ቤት ሁለትና ከዚያ በላይ ልጆቹን ጭምር “ለህልውናህ ዝመት” ብሎ መርቆ የሚልክበትን ሁኔታ እያየን ነው። ልጆቹን ከመላክ ባሻገር በስንቅ ዝግጅት፣ ገንዘብ በማዋጣትና በሌሎች ድጋፎችም ጭምር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ደሃ የሚባለውን የህብረተሰብ ክፍል ጨምሮ  እስከ ትልልቅ ባለሀብቶች ድረስ ያሉት ለዚህ የህልውና ዘመቻ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ ነው ያሉት። በውጪ ያሉ ዲያስፖራዎች፣ ምሁራን፣  የመንግስት ሰራተኞች… ሳይቀሩ አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ጫና ሳይገድባቸው፣ ህልውናቸውን በማስቀደም ደሞዛቸውን እስከ መስጠት ነው ትግል እያደረጉ ያሉት። እንደሚታወቀው ጦርነት አውዳሚ ነው። በሁለቱም በኩል ጦርነት ጎጂ ነው። በዚያ ላይ የጠላት ባህሪ የተለየና እጅግ አስቀያሚ ነው። ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በኢኮኖሚ ሰብአዊ ቀውስ እንዲደርስ ለማድረግ፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዲደቅ  የሚያገኘውን ሁሉ የሚያጠፋ ሃይል ነው።
ሰብአዊ ሀብትን ከማጥፋት፣ ሰውን ከመረሸን ባሻገር… መቼም አይታችሁት ይሆናል እንስሳትን እስከ መግደልና እስከ ማውደም የዘለቀ አረመኔነት ነው ያለው። ይህን የሚያደርገው ሆን  ብሎ በክልሉ ላይ የኢኮኖሚ ጫና በማድረስ ህዝቡ እንዲጎሳቆል ለማድረግ ነው። ሆስፒታሎችን ይዘርፋል፣ ት/ቤቶችን ያፈርሳል፣ ሌሎች ተቋማትንም ይዘርፋል፣ መሰረተ ልማቶችንም ያወድማል። የሚጭነውን ይጭናል፤ የቀረውን ያቃጥላል። ለምሳሌ ሆስፒታል ውስጥ ገብቶ የሚጭነውን ይጭንና የማይጫን ማሽነሪና ሌላ ካለ ያቃጥላል። ይህ ሆን ተብሎ ነው- ህዝብን ለመጉዳት ወራሪና አሸባሪ ሀይሉ የሚያደርሰውን ጉዳት ህዝቡ ተገንዝቧል። ይህንን ሀይል ለመዋጋትና  ከስሩ ለማጥፋት የአማራ ህዝብ በሙሉ ዝግጁ ነው። የአማራ ህዝብ ብቻ አይደለም፤ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችም በዚህ ጉዳይ ያሳዩት ምላሽ በጣም ከፍተኛ ነው። በአጋጣሚ ጦርነቱ የሚካሄድበት አማራ ክልል ሆኖ ጫናውን ሌሎችም ክልሎች ስለሚገነዘቡ፣ እገዛ ሲያደርጉ ትመለከታላችሁ።
ይሄ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው። አሸባሪው ህውሃት የጋራ ጠላታችን መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ስለተገነዘና ይህን ጠላት ካላስቆምነው ነገም ለሌሎቹ አደጋ ስለሚሆን፣ ከስሩ ለማጥፋት እየተሰራ ነው። በነገራችን ላይ አሸባሪው ህውሃት ማለት ባለፉት 30 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ውስጥ በተለይም ባለፉት  ሶስት ዓመታት በሁሉም ክልሎች ለተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች መነሻና ዋናው አቀንቃኝ እሱ ነው።  ሰሞኑን  ኦሮሚያ ላይ ለተፈጠረው ግጭትም ሆነ ሌላ ጊዜ በሌላ ቦታ ለሚፈጠርም ለእያንዳንዱ ግጭት እጁ አለበት።
ከሀዲው ህወሃት ብቻውንም አይደለም፤ ከውጪ ጠላቶቻችን ጋር አብሮ ነው የሚሰራው። በዚህ ደረጃ ጨካኝ የሆነውን ጠላታችንን ህውሃትን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቱ በሚገባ አውቆታል፤ ተገንዝቦታልም። ስለዚህ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው፤ አንድ የሚነሳ ሃቅ ግን አለ። ጦርነቱ እየተራዘመ በሄደባቸው አካባቢዎች በተለይም ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በተለይም ደግሞ የዋግ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ የሰሜን ወሎ አስተዳደርና የደቡብ ወሎ ደግሞ ውስን ቀበሌዎች፣ ሰሜን ጎንደርም የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ወረራ ከመፈጸሙም በላይ ጦርነት እየተካሄደ ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው።
እርስዎ እንዳሉት ጦርነት ሳይንስ ነው። ሚሊተሪ ሳይንስም የሳይንሶች የበላይ ነው ይባላል። ይሄ ያግባባናል። አሁን ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ግራ እያጋባ ያለው የህወሃት ጡንቻ እንዴት ፈረጠመ? የሚለው ነው። በህግ ማስከበሩ ዘመቻ በሶስት ሳምንት ተበታትኖ ዋሻ የገባው ህወሃት፤ አሁን ከክልሉ አልፎ የአማራና አካባቢዎችን እስከ መውረር የደረሰው  በምን አቅም ነው ይላሉ?
እውነት ለመናገር መጀመሪያ አካባቢ፣  እዚህ ወረራ ይፈጸማል የሚል እምነት አልነበረንም። እኛ ትኩረታችን ልማት ላይ እንጂ የጦርነት ዝግጅት አልነበረንም። ሲጀመር ደግሞ ያ ሁሉ  ከተካሄደ በኋላ የትግራይ ህዝብ ነጻነት እንዲያገኝ፣ ወደ ልማት እንዲገባ በሚል በመንግስት በኩል አቋም ተወስዶ፣ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት ሲፈጸም፣ ምናልባትም ተጸጽቶ የትግራይን ህዝብ ነፃ ያደርጋል፤ የትግራይን ህዝብ ይተዋል የሚል እምነት ነበረን እንጂ ከዚህ በላይ  የትግራይን ህዝብም ሆነ ሌላውን ለመበደል ይንቀሳቀሳል የሚል ግምት አልተወሰደም ነበር። በዚህ መልኩ ያንን እድል ተጠቅሞ ሀይል አደራጅቶ ወረራ ፈጽሟል። ከውጪ ሃይልም ጋር ተቀናጅቶ ነው ሀገር እየወጋና እያፈረሰ ያለው። በሌላ በኩል የትግራይን ህዝብ  አስገድዶ የሰው ማዕበል (HUman wave) ነው የለቀቀው።
አሁን ላይ የህወሃት በደል ለትግራይ ህዝብም እየገባው  እንደሆነ እገምታለሁ። በጣም ብዙ ሀይል ነው ያለቀበት። ብዙ ህፃናት ናቸው የረገፉት። ብዙ ወጣቶችን ነው እያስጨረሰ ያለው። ይህንን የሚያደርገው በውሸት ፕሮፓጋንዳና አስገድዶ በመያዝ ስልጣን ላይ የሚወጣ በማስመሰል ነው። በውሸት ትርክትና ቅጥፈት የትግራይን ወጣት እየማገደ እዚህ ደርሷል። በኢትዮጵያ መከላከያም በኩል ህወሃት ሂውማን ዌቭ ሲለቅ እንዴት ህዝብ እመታለሁ በሚል ችግር ውስጥ የገባበትና ርህራሄ ለማሳየት የሞከረበት ጊዜም ነበር።
በነገራችን ላይ ወራሪ ሲመጣ ማህበረሰቡ ደጀን ሆኖ ካልጠበቀ ችግር ይመጣል። ማህበረሰቡ ይሄ ነገር አለ ብሎ ነቅቶ መጠበቅ አለበት። እንጂማ ወታደርማ ድሮም አለን እኮ። ወታደር የለም ማለት አይደለም። ዝግጅት ሲባል ማህበረሰቡን እዚህ ቦታ ይሄ አለ ብለሽ፣ በስነ-ልቦና ማዘጋጀትና ማንቃት ማለት ነው። ይህ ሲሆንና ማህበረሰቡ ደጀን ሲሆን ነው ውጤት የሚመዘገበው። ዞሮ ዞሮ በሀይል ደረጃ የወገን ጦር በቂ ሀይልና አቅም አለው። በቂ ሃይልና  ዝግጅት ካለ ለምንድነው ጦርነቱ በፍጥነት የማይቋጨው ለምትይኝ፣ አሁንም ኦፕሬሽኑን የሚመሩት አካላት ናቸው ሳይንሱን መተንተን የሚችሉት ብዬ ነው የምመልስልሽ። አንዳንዴ ለሚዲያም ግልፅ የማይደረግበት አግባብ ሊኖር ይችላል፤ የሚለውም ግንዛቤም መወሰድ አለበት።
ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ሸኔ የተባለው አሸባሪ ታጣቂ ሀይል፣ ዘር ተኮር ጥቃት በማድረግ ንፁሃንን እየጨፈጨፈ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው የአማራ ህዝብ በየአቅጣጫው አደጋ ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝም እንደዚሁ ተመሳሳይ ችግር አለ። በሰሜን ሸዋ ማጀቴ በሚባል አካባቢም ሰሞኑን የ15 አርሶ አደሮች ምርት በተከመረበት በእሳት ቃተሎ ወድሟል፡፡ አንድ የክልል መንግስት ባለበት ያውም በተደጋጋሚ ይህ ሁሉ ጥቃት ሲደርስ፣ የአማራ ክልል መንግስት ከነዚህ ክልል አመራሮች ጋር ተመካክሮ ችግሩን የሚፈታበት አግባብ የለም? ለዚህ ሁሉ ጥፋት ማንስ ነው ተጠያቂው? በጉዳዩ ላይ ከእነ አቶ ሽመልስ አብዲሳስ ጋር ትነጋገራላችሁ?
በመጀመሪያ ደረጃ ቅድም እንዳነሳሁልሽ፣ ከአሁን ቀደምም በተደጋጋሚ ማጀቴና አጣዬ አካባቢ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚፈጠሩ ጥቃቶች ቤኒሻንጉልም ላይ የሚፈጸመውን ጨምሮ መነሻቸው ህውሃት ነው። ይህንን የሚቀበሉ ተላላኪና ባንዳ ሃይሎች አሉ። አንዱ ኦነግ ሸኔ ነው። ኦነግ ሸኔም ብቻ አይደለም። ከመንግስት ሃይሎች ውስጥም እነሱን የሚተባበር ባንዳ አለ። በተለይ ከታችኛው መዋቅር ከዞንም ከወረዳም ከቀበሌም ውስጥ እነዚህ ባንዳዎች አሉ። ይህ በግልጽ ታውቆ ከአንዴም ሁለትና ሶስት ጊዜ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እርምጃ ወስዶበታል። በሰሜን ሸዋም እንደዚሁ ተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ጠላቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ ግጭቶች ግን ተራና ደራሽ ግጭቶች አይደሉም። በረጅሙ ታቅዶ አማራን ለማጎሳቆል፣ ክልሉ ዝቅ እንዲል ቀጥሎም አገር የማፍረስ ስትራቴጂ ነው። እንግዲህ ከዚህ በፊት የውሸት ተረክ አለ። ያንን መነሻ በማድረግ በሰሜን ሸዋም በሌሎቹ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎችም እህል እስከማቃጠል የሚደርሰው ትንኮሳ፣ ብሄርን ከብሄር፣  ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት አገር ለማፍረስ የተሰራ ፕሮጀክት ነው። ይሄ ግን አይቀጥልም፤ አይሳካም። የአማራ ህዝብም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀንደኛ ጠላታቸው ማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቀቃሉ። አሸባሪው ህውሃት ላይ የሚደረገውን ዘመቻ በጭራሽ ችላ ሊሉት አይችሉም። ችላ ሊባል አይገባም። ሁለተኛ እየደረሰ ላለው ጥፋና በደል መንግስት ሃላፊነት መውሰድ አለበት።
የትኛው መንግስት፣ የክልሉ ወይስ የፌደራል መንግስት?
ሁለቱም! የክልሉ መንግስትም ሃላፊነት መውሰድ አለበት  የፌደራል መንግስትም ሃላፊነት በመውሰድ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ይሄ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ከእኛም ክልል አኳያ እየደረሰ ያለውን ነገር ማስቆም አለብን። በኦሮሚያም ሆነ ሌላው ቦታ ላይ የሚደርሰውን የአማራን ህዝብ ጥቃት ማስቆምና ህዝቡን ከአደጋ መጠበቅ አለብን። እንደ መንግስት ማለቴ ነው።
ይህን ብለን ስናበቃ ግን እኛም ዝም ብለን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም። ይሄ መታወቅ አለበት። ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ያለነው። በፊት የነበሩትም ችግሮች የተቀረፉትና እየተቀረፉ የመጡት በመስራታችን ነው። አሁንም፣ የተመሰረተው አዲሱ መንግስት ፣ይህን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ አመራሮች ከፌደራልና ከኦሮሚያ መንግስት ጋር  በጋራ እየተወያዩና በቅርበት እየሰሩ ነው ያሉት። ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም ጋር ቢሆን ከአዲሱ የክልላችን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ይልቃልና ከፌደራል አመራሮች ጋር ተገናኝተው በጥልቀት ተወያይተዋል።
በዚህ መንገድ  እዚያ ችግሩ ያለበት ቦታ ላይ መሰማራት ያለበት ሀይል እንዲሰማራ አድርገዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይም ተደጋጋሚ ውይይት እየተደረገ ነው ያለው። አሁንም ችግሩ በአንድ ጀምበር የሚፈታ አይደለም።  ይህ ጉዳይ በይድረስ ይድረስ ወይም በድንገት የመጣ አይደለም። ታቅዶና ታስቦ የሚፈጸም እስከሆነ ድረስ ፣ ጠላቶቻችንን ለኢትዮጵያና ለአማራ ክልል አደጋ የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ከላደረስንና በተለይም አሸባሪው ህወሃት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ወስደን ስጋት እንዳይሆን ካልታገልነው ይሄ ችግር በተዓምር ሊቆም አይችልም። ነገም ሊከሰት ይችላል። ይሄ ችግር ዳግም እንዳይከሰት እየለፉና እየጣሩ ነው ያሉት። ኦሮሚያ ኦነግ ሸኔ ላይ ብዙ እርምጃ ወስዷል፤ እየወሰደም ነው ያለው።  እርግጥ ነው ጥቃቱ ሆን ተብሎ ዘር ተኮር ሆኖ የሚከሰት ነው። ነገር ግን ደግሞ ሌሎቹም ላይ ጭምር ጥቃት እያደረሰ ይገኛል። አማራ ላይ ብቻ አይደለም ማለቴ ነው። አማራ ግን በስፋት ተጎድቷል። በአጠቃላይ ይሄ የአሸባሪው ህውሃት ከውስጥና ከውጪ ጠላቶቻችን ጋር በማበር አገር የማፍረስ፣ ፕሮጀክት የማስፈጸም እንቅስቃሴ ውጤት መሆኑ ተወስዶ፣ ዋናውን የፕሮጀክቱን ባለቤት በሚገባ መምታትና ማክሰም ዋነኛ ሥራ ተደርጎ መወሰድ አለበት።
ጦርነቱ በግንባርና በነፍጥ ከመካሄዱ ባሻገር ዋነኛው ጦርነት ተብሎ የሚነገርለት የሳይበሩ አለም ጦርነት ነው። በሳይበሩ ጦርነትም በዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴም የእኛ ወገን ደከም ያለ መሆኑ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ነው። ቅድም እንዳልነው አጎራባች በመሆኑ ዋነኛ ተጠቂ የሆነው የአማራ ክልልና ህዝቡ  በሳይበሩ በኩል ምላሽ የሚሰጡ የተማሩ ወጣቶች አሉት ወይ?
የሳይበር ጦርነት አሁን ጊዜው የፈጠረውና ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍ ነው። አሁን ያለንበት  የዲጂታል ዘመን በዚህ ላይ እንድንሰራ ግድ ይለናል። እንደ ሀገርም እንደ ክልልም በዚህ ዘርፍ ላይ ስራችን ክፍተት ያለበት ነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም ብዙ በጎፈቃደኞች መሰማራት ጀምረዋል።
አሸባሪው ህውሃት የተጠቀመበት የሳይበር ሰራዊቱን ቀደም ሲል አገር ሲመራ በነበረበት ጊዜ ጀምሮ አስቦበት አዘጋጅቶ አገር ለማፍረስም እየተጠቀመበት ነው። በአገር ውስጥ በግልም በመንግስትም ሚዲያዎች ውስጥ ጭምር የሱን ጋሻ ጃግሬዎች በመሰግሰግ በውጪ አገር ያሉትንም በማሳለፍ፣ እንደ አንድ መሳሪያ እየተዋጋበት ይገኛል። በተለይ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በማደናገር እየሰሩበት ይገኛሉ። ይህ ስለተነቃበትና ህዝቡም እየገባው በመሆኑ ለሳይበሩ ጦርነት በእኛም በኩል የሳይበር ጦረኛ ማዘጋጀት ስለሚያስፈልግ ሀቅ ላይ የተመሰረተ እውነትነት ያለውን የሳይበር መረጃ የሚያሰራጭና የህውሃትን ውሸት የሚያጋልጥ የሳይበር ሰራዊት  እየተደራጀ ነው ያለው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረ ስራ አለ፡፡ እኛ እንደ ክልል ያንን ሞዴል ተጠቅመን በጎ ፈቃደኞችን ማደራጀትና በዋናነት በመንግስት ኮሙኒኬሽን ስር ተቋማዊ መዋቅር አስይዘን የሚቀጥል ይሆናል፤ ጥሩ ጅምር ላይ ይገኛል። በነገራችን ላይ ጦርነቱን ሁሉም መቀላቀል፣ ካድሬውም ጭምር የሳይበር ተዋጊ መሆን አለበት። ካድሬ ዝም ብሎ እስከዛሬ በተለመደው መንገድ ብቻ መጓዝ የለበትም የመንግስት ሃላፊ በቲውተር ሳይቀር ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ መስጠት አለበት። ካድሬው በሳይበሩ አለም ያሉ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮችን ሁሉ መጠቀም መቻል አለበት። በዚህ ደረጃ ለውጥ አለ። አሁን የትዊተር ዘመቻውን ብትመለከቺ፣ በፌደራል ደረጃም የተቀናጀ ሆኖ ቀጥሏል። በጣም ጥሩ ነው። የሳይበር ጦርነቱ በክልልም በፌደራልም ቀጥሏል። በጣም ጥሩ ነው። እዚህ የሚወድመው መሰረተ ልማት የሀገር ሀብት ነው። እዚህ የሚረሸነው ንፁህ ዜጋ የሌላው ህዝብ ወንድም ነው። ስለዚህ ሁሉም በጋራ ጠላትን የመዋጋት ሃላፊነት ነው ያለበት። ጦርነቱ ያመጣው አንዱና ትልቁ ነገር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያጠናከረ መሆኑ ነውና፣ ሁሉም በጋራ መስራት ለውጤት መብቃት ያለበት ጊዜ ላይ ነን እንጂ ችግሩ የአማራ ክልል ብቻ ሆኖ መታየት የለበትም።
በክልሉ የአማራ ምሁራን መማክርት የሚባል መቋቋሙም ይታወቃል። እነዚህ ምሁራን በዚህ ወቅት ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ከማፍለቅ አኳያ ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ይላሉ?
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታና አሁን በገጠመን የአማራ ክልል አጠቃላይ ጫና አኳያ፣ የአማራ ምሁራን መማክርት አባላት በደንብ የተደራጁ ናቸው። እውነት ለመናገር ብዙ እያገዙንም ነው ያሉት። እነዚህ አባላት በአብዛኛው ሳይንሳዊ በሆነው፣ የእውቀትና ምርምር ጉዳይ ላይ በማማከር በደንብ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ሁኔታዎችን በመተንተን፣ የነገን የአማራ እጣ ፈንታ፣ የነገን የሀገር እጣ ፈንታ፣ ዓለም አቀፍ፣ አገር አቀፍና ክልላዊ ሁኔታውን ነባራዊና ህሊናዊ እውነታውን በመተንተን ለዚህ የሚያስፈልገውን ነገር እያደረጉ፣ ወደ ኦፕሬሽን እንድንገባ በማድረጉ ረገድ በእጅጉ እያገዙን ይገኛሉ። ይህም ብቻ አይደለም።
አጠቃላይ አሁን የምንገኝበትን ሁኔታ የሚመራና በኮማንድ ፖስት በክልሉ ፕሬዚዳንት የሚመራ ቡድን አለ፣ በአይነትም በገንዘብም ሎጂስቲክ የሚያሳስብ አለ፣ ሌሎች ሚዲያና ኮሙኒኬሽን እንዲሁም አጠቃላይ የህዝብ ንቅናቄውን የሚመራ አለ በዚህና በርካታ ጉዳዮች የምሁራኑ መማክርት ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርጉናል። በየዘርፍ በየዘርፋቸው ምሁራዊ አስተያየት ያመጣሉ። ትንታኔ ለሚስፈልገው ነገር ትንተና ይሰራሉ። እኛ  የምናደርገው ትግል ለአጭር ጊዜና  ህወሃትን ለማስወገድ ብቻ አይደለም። መጪው የተጋረጠ አደጋ ምንድነው? የሚለውና የውጪው አሰላለፍ በዚህ  ደረጃ ይህን መልክ የያዘው ለምንድነው? የሚለው  በነዚህ ምሁራን ተተንትኖ ተቀምጧል። ቀጣይ አደጋ የሚሆኑ እነማን ናቸው? በምን መልኩ ነው ወረራስ እተፈጸመ ያለው? ለምን? የሚለውም ጉዳይ በምሁራን እየተተነተነ ለዚህ ሁሉ አጠቃላይ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያለው ለአሸባሪው ህወሃት ብቻ አይደለም።
አሁን ጦርነቱን ተከትሎ ስለተፈናቀሉ ወገኖች እናንሳ። በኮምቦልቻ ፣ በደሴ፣ አሁን አባይ ማዶ ዘንዘልማ በጎንደር እብናት አካባቢ በደባርቅና በመሳሰሉ ቦታዎች በርካታ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። ከነዚህ ተፈናቃዮች ኮምቦልቻ፣ ደሴና ህርዳር የሚገኙትን የማየት አጋጣሚውን አግኝቻለሁ። በተለይ በደሴ ያሉት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለመታዘብ ችያለሁ። ከመንግስት፣ ከበጎ ፈቃደኞች ፣ ከዲያስፖራው ከአማራ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች ከግለሰቦችና ከተለያዩ የልማትና የንግድ ድርጅቶች እርዳታ በአይነትም በገንዘብም ይገባል። እርዳታው በትክክል አልደረሰንም የሚሉ ዱቄት መጥቶ ማብሰያና ማገዶ አጣን የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ችግሮች በርካቶች ናቸው። በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ? እርዳታ አሰጣጡን በምን መልኩ ነው እየመራችሁት ያለው?
ተፈናቃዮቹን በሚመለከት በተለያየ ጊዜና ቦታ በተፈጠሩ ግጭቶች በተለይ የቅርብ ጊዜውን የአሸባሪውን የህውሃን ወረራ ተከትሎ እስካሁን በክልላችን ከ1.7 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ህዝብ ተፈናቃይና ተረጂ ሆኗል። ይህን ስልሽ በየዘመድ ቤት፣ በበጎ ፈቃደኞች ቤት እየተጠጉ ያሉትን ጨምሮ። በክልሉ ከ30 ያላነሱ መጠለያዎች አሉ። በነዚህ መጠለያዎች የሚኖሩት ከ1.7 ሚሊዮን ጥቂት ፐርሰንቱ ብቻ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ወደ 800 ሺህ የሚጠጋው በቅርብ ጊዜ አሸባሪው ህውሃት ወረራ ከፈጸመባቸው አካባቢዎች የተፈናቀለ ህዝብ ነው ማለት ነው። እነዚህ በተጨባጭ በእኛ ማኔጅመንት ስር ያሉ ናቸው ማለት ነው። ነገር ግን ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ያለው ህዝብም ድጋፍ ይፈልጋል። አሁን እንደውም አሳሳቢ ችግር ውስጥ ያለው ሰሜን ወሎ  ያለው ህብረተሰብ ነው። ዋግ ላይ ያለውም ህዝብ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው።
በተለይ ቶሎ የማይድኑና ከሰዎቹ ጋር የሚዘልቁ ህመሞች (ክሮኒክ)ያለባቸው ሰዎች ስኳር፣ ደም ግፊት ኤች አይቪና የመሳሰሉ ህመሞች ያሉባቸው በመድሃኒት እጥረት እየሞቱ ነው። ምክንያቱም አሸባሪው ህወሃት ጤና ጣቢያዎችን ዘርፏል፤ የቀረውን አቃጥሏል። በሌላ በኩል፤ በረሃብ እያለቁ ነው ያሉት። እርዳታ ማቅረብም አልተቻለም።
የውጪ የእርዳታ ድርጅቶች ለትግራይ ህዝብ እያቀረቡ ያሉትን እርዳታ፣ ለእኛ ወገን እያደረሱ አይደሉም፡፡ በቁጥር ደረጃ ወደ 4 ሚ. ህዝብ ነው እርዳታ የሚጠብቀው። በሁለቱ ዞኖች ብቻ ማለቴ ነው፡ በቁጥር በእኛ ወገን ያለው ነው የሚበልጠው። በአጠቃላይ ይህን ያህል ህዝብ ችግር ላይ ወድቋል። በተለይ ደግሞ እኛ ልንደርስላቸው ያልቻልባቸው የተወረሩ አካባቢዎች ላይ ያለው ህዝብ በጣም አሳሳቢ ደረጃ  ላይ ነው ያለው።
በሁለተኛ ደረጃ ተፈናቅሎ በተለያዩ ጊዜዊ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ያለውና በአብዛኛው በዘመድና በበጎ ፈቃደኞች ቤት ተጠልሎ የሚገኘው (በነገራችን ላይ ተፈናቃይ የሌለበት ዞን የለም ክልላችን ውስጥ) የደሴው ከፋ ስለሚል ነው ብዙ ጊዜ ደሴ የሚነሳው እንጂ በሁሉም ዞኖችን ውስጥ  ተፈናቃይ አለ። እነዚህን በተመለከተ እርዳታ ከሚያቀርቡ አንዳንድ አለምአቀፍ ድርጅቶችም ጋር በተመሳሳይ የፌደራል መንግስት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና ከክልላችን የአደጋ ስጋ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ድጋፍ እያቀረብን ነው። ድጋፉን በተመለከተም ቢሆን የድጋፍ አሰጣጡ እንዲሁ በዘልማድ የሚመራም አይደለም። ይህንን የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከልና ኮሚቴ ተቋቁሞ በጽ/ቤት ደረጃ ስራ እየተሰራ ነው። (Emergency Coordionation Center) በዚህ ደረጃ ከሁሉም ከሚመለከታቸው ዘርፎች የተቀናጀ ኮሚቴ ይህን ይሰራሉ፤ ያቀናጃሉ ያስተባብራሉ፡፡ በነገራችን ላይ ይህን በሙሉ ሰዓት ስራነት ነው የሚሰሩት፡፡ ይህ ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠነው የሚያሳይ ነው፡፡ የዳሰሳ ጥናት ይሰራሉ፣የት አካባቢ ምን አይነት ድጋፍ ያስፈልጋል የሚለውን ይለያሉ ማለት ነው፡፡ ምን ያህል ዘይት ፣ምን ያህል አልባሳት፣ ምን ያህል አልሚ ምግብ፣ ለየትኛው መጠለያ እንደሚያስፈልግ ያጠናሉ በዚያ መሰረት ያደርሳሉ፡፡
ፅ/ቤቱ በማን ስር ነው የሚመራው?
ፅ/ቤቱ በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ስር ሆኖ ነገር ግን ብዙ አመራሮች በባለበኔትነት የሚመሩት ነው፡፡ ይሄ በየጊዜው ከፕሬዚዳንቱም ከምክትል ፕሬዚዳንተሩም፣ እኛን ጨምሮ በጥብቅ የምንከታተለው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነው የድጋፍ አሰጣጡ የሚሰራው፡፡ የደሴ አካባቢው እንደዚህ አይነት ፅ/ቤትና ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ ነው፡፡ ከቡድኑ ጋር የፌደራል አካላትም አብረው እየሰሩና እየተከታተሉ ነው። በተቻለ መጠን በወረራ ካሉት ውጪ ያሉትን እስካሁን የእርዳታ አቅርቦት ችግር አለ የሚል ግምገማ የለንም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሂደት በየጊዜው ተፈናቃይ እየጨመረ ስለሚመጣ፣ በአንዳንድ በኩል ያልፈፈናቀለውም አጋጣሚውን ለመጠቀም ስለሚቀላቀል ማኔጅመንት አካባቢ ያልጠሩ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥርጣሬ አለ፡፡ እሱን ለማስተካከል እየሰራን ነው፡፡ ለምሳሌ ዱቄት ተሰጥቶ ማብሰያ ቀርቶ ከሆነ ይሄን ለማስተካከል እየተሰራ ነው። በቅርቡ ይስተካከላል። በየጊዜውም ከፍተኛ አመራሩ በየመጠለያ ጣቢያዎቹ እየሄደ እየጎበኘ፣ ጉድለት አለ የሚባልበትን ቦታ እያስተካከለ ነው ያለው። ለጽ/ቤቱ ብቻ ስራውን ሰጥቶ አመራሩ ቁጭ  አላለም ለማለት ነው።  • በክልሎቹ 1ሺ 436 የጤና ተቋማት ወድመዋል
   • 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል
             
            ከቀናት  በኋላ (ጥቅምት 24 ቀን 2014) አንደኛ አመቱን የሚደፍነው የህውሃት ሃይል የቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልል ከተስፋፋ ወዲህ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው፤ 1ሺ 436 የጤና ማዕከላት መውደማቸውን አለማቀፍ የሃኪሞች ቡድን ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባሉት 8 ወራት  ከደረሰው ጉዳት በበለጠ መንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ካወጀ ወዲህ ህወሃት  የፈጸማቸው ጥቃቶችና ሰብአዊ ውድመቶች በእጅጉ የከፋ መሆኑን ሪፖርቱ ያስገነዝባል።
ቀደም ሲል  በጦርነቱ 678 ሺህ 130 ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ባለፉት 3 ወራት ገደማ በህውሃት ወረራ ተጨማሪ 1.2 ሚሊዮን ዜጎቹ በተለይ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በርካታ የጅምላ ግድያዎች መፈጸማቸውን፣ የግለሰቦች ንብረት መውደማቸውንና የጤና ተቋማትና ት/ቤቶች መዘረፋቸውን በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የህወሃት ሃይል በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት እያደረሰ  መሆኑን ያስታወቀው የአለማቀፍ የሃኪሞች ቡድን ሪፖርት፤ በተለይ ከጤና ተቋማት ጋር በተያያዘ 271 የጤና ማዕከላት፣ 1,143 ክሊኒኮች፣ 22 ሆስፒታሎች በድምሩ 1,436 የጤና ተቋማት መዘረፋቸውንና  መውደማቸውን ጠቁመዋል።
በአንጻሩ ቀደም ብሎ  ወደ ትግራይ እርዳታ የማድረሱ ተግባር ያለ ችግር በተለይ የህክምና መሳሪያዎችና አልሚ ምግቦችን ወደ ትግራይ  ያጓጓዡ 211 ተሸከርካሪዎች ሳይመለሱ መቅረታቸውን ያወሳው ሪፖርቱ፤ በዚያም ሳቢያ በአሁን ሰዓት  የህክምናና አልሚ ምግብ እርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎሎን ጠቁሟል። በተጨማሪም ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ 2,500 ሜትሪክ ቶን እርዳታ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተጠባበቀ መሆኑን ሪፖርቱ አስታውቋል።
በአጠቃላይ የህክምናና አልሚ ምግቦች ድጋፍ በመስተጓጎሉ በአፋርና አማራ ክልል ያሉ ተፈናቃዮችን ጨምሮ በትግራይ የሚገኙ 92 ሺህ 835 ህፃናትና ነፍሰ ጡር ሴቶች ለእርዛት መዳረጋቸው ነው  ሪፖርቱ የጠቆመው።
በአሁን ወቅት ህውሃት በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ዋግህምራ፣ ሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎን ጨምሮ በአፋር ክልል ዞን 1 እና ዞን 2 በተባሉ 7 ግንባሮች ጦርነት መክፈቱ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በአጠቃላይ በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልል ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በጦርነቱ ሳቢያ ተፈናቅለው በየአካባቢው በሚገኙ 32 ያህል መጠለያ ካምፖች ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል።

Page 2 of 556

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.