Administrator
አራተኛው ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ
ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለአራተኛ ጊዜ በትናንትናው ዕለት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል። የ15 ኪሎሜትር የሩጫ ውድድርን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ስፖርታዊ ፍልሚያዎች ተደርገዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒሰቴር የስፖርት ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በውድድሩ ላይ ተገኝተዋል። መነሻውን ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ባደረገው ውድድር ብርቱ ፍልሚያ እንደታየበት ለማወቅ ተችሏል።
ሚኒስትር ደኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት "እንደኬሮድ መሰል የሩጫ ውድድሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። በዚህ ውድድር ያሸነፋችሁ እና የተወዳደራችሁ አትሌቶች ጠንክራችሁ ቀጥሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ምስጢሩ ሕብረ ብሔራዊ አትሌቶችን ማግኘቱ ነው። በሁሉም አቅጣጫ እንደእነዚህ ዓይነት ውድድሮች መካሄድ ይኖርባቸዋል።" በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም ለኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር አዘጋጆች ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
የኬሮድ የስፖርት እና የልማት ማሕበር ቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ተሰማ አብሽሮ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች እና ተወዳዳሪ አትሌቶች በውድድሩ በማሳተፋቸው ምስጋናውን ገልፆ፤ "ኬሮድ ሩጫ በቡታጅራ፣ ወራቤ እና ሆሳዕና በተለያዩ ክልሎች ላይ ውድድሩን ለማዘጋጀት ዕቅድ አለው። የኬሮድ ዓላማ ሰላምን መስበክ ነው። ሕብረተሰቡ ሊደግፈን ይገባል።" ሲል ተናግሯል። የፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለሆኑ አትሌቶች መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
በአንድ ኪሎሜትር የዊልቸር ውድድር በሴቶች፤ አንደኛ አብነት ጌትነት የወርቅ ሜዳልያ እና 5 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ እምነት ከበደ የብር እና 3 ሺህ ብር፣ ሶስተኛ ሰዓዳ አብደላ የነሐስ ሜዳልያ እና 2 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል። በወንዶች ውድድር ደግሞ፣ አንደኛ አቡበክር ጀማል የወርቅ ሜዳልያ እና 5 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ ዳዊት ዮሴፍ የብር ሜዳልያ እና የ3 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ዳንኤል ዲባባ የነሐስ ሜዳልያ እና የ2 ሺህ ብር ሽልማት ተሸላሚዎች መሆናቸው ታውቀዋል።
በ15 ኪሎሜትር የሴቶች ሩጫ ውድድር አንደኛ መብርሂት ግደይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወርቅ ሜዳልያ እና የ100 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ መቅደስ ሽመልስ በግል የብር ሜዳልያ እና የ50 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ኑኖ ሻንቆ ከኦሮሚያ ፖሊስ የነሐስ ሜዳልያ እና የ25 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ለመሆን በቅተዋል። በወንዶች ደግሞ፣ አንደኛ ጨምዴሳ ደበላ በግል የወርቅ ሜዳልያ እና የ100 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ ዘነበ አየለ ከዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብ የብር ሜዳልያ እና 50 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ጂግሳ ታደሰ በግል የነሐስ ሜዳልያ እና 25 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
እንዲሁም አሸናፊ አትሌቶች ለወከሏቸው የስፖርት ክለቦች የዋንጫ ሽልማት ከውድድሩ የክብር ዕንግዶች እጅ ተቀብለዋል።
"ለኢትዮጵያ ሰላም እሮጣለሁ" በሚለው የዘንድሮው የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በተጨማሪነት የሕዝባዊ ሩጫ ውድድር እንደተካሄደና ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ተሳታፊዎች ሜዳልያ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።
18091 ፕሮጀክቶች - በዓመት!
• አዲስ አበባ ፈካ፣ ጸዳ፣ ነቃ ነቃ ያለችበት ዓመት ነው 2016።
• ከተማዋ ቀንና ሌሊት በሥራ የተጠመደችበት ዓመትም ነው
በጥበብ ካልተጉ 18091 ሺ ፕሮጀክቶችን መሥራትና አሳምረው ለውጤት ማድረስ፣ ጀምረው መጨረስ አይችሉም።
ዓመቱን ሙሉ በብርቱ ተምረው ከሠሩ ነው የፈተና ውጤት የሚያምረው፤ የወደፊት ተስፋ የሚፈካው፤ መንፈስ የሚነቃቃው። እንቁጣጣሹም ከተማውም የሚደምቀው።
የሌሎች አድናቂና የዳር ተመልካች ሆነን የምንቀርበት ምክንያት የለም የሚል የእልህ ስሜት ውስጣችን ሲያነሣሣ፣ በዚህም ሌት ተቀን ስንሠራ፣ በሙያ ፍቅርና በብርቱ መንፈስ ስንጥር ነው፣ ኑሮም አገርም በበጎ የሚቀየረው።
ደግሞም መልካም የሥራ ውጤት ሲያዩ የብዙዎች መንፈስ እየተነቃቃ ስሜታቸውንም እንደሚገልጹና ለሥራ እንደሚነሣሡ፣ የፒያሣ-አራት ኪሎ የኮሪደር ልማት የተመረቀ ጊዜ አይተናል። ይሄው በጎ መንፈስ በሌሎቹ የኮሪደር ልማት የምረቃ አጋጣሚዎችም ተመሳሳይ በጎ መንፈስ እየተደጋገመ ሲደምቅ ተመልክተናል።
ከተረጂነትና ከውርደት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ የሚመጥን አዲስ ተጨማሪ ታሪክ የማይፈጠርበት ምክንያት የለም። ወደ ዕድገትና ወደ ብልጽግና በመገሥገሥም አዲስ አበባ የሥራ መዲና፣ ኢትዮጵያ የስኬት ምሳሌ ተብለው እንዲጠቀሱ ማድረግም ይቻላል። እንደሚቻል ብቻ ሳይሆን፣ እውን እንደሚሆን ከንቲባዋ ሲገልጹ… ሌላ ምሥጢር የለውም፤ ሠርተን አገራችንን እንለውጣለን በማለት እንደተናገሩ እናስታውሳለን።
ዘንድሮ የተሠሩና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችም የዚህ ግሥጋሤ ጅምርና ምስክር ናቸው ማለት ይቻላል።
አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በአካልና በግላጭ ደምቀው የሚታዩ ሥራዎች ናቸው። ከቅርብም ከሩቅም በርካታ ሺህ የከማዋ ነዋሪዎች ከየአካባቢያቸው እየመጡ የዐድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምን ጎብኝተዋል። በኮሪደር ልማት የተስፋፉና የተሻሻሉ መንገዶችን፣ አምረው የተሠሩ የእግረኛና የብስክሌት መስመሮችን፣ በዛፎችና በመብራቶች ደምቀው የተዋቡ አካባቢዎችን እየተዘዋወሩ አይተዋል። ዘና ለማለት ልጆቻቸውን ይዘው ጎራ ማለት ሲያዘወትሩም ታዝባችሁ ይሆናል። “የከተማዋን የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሪፖርት በአካል እንደመመልከት” ልትቆጥሩት ትችላላችሁ።
በእርግጥ ሁሉንም ፕሮጀክት ሁሉንም የሥራ ውጤት እየዞርን የመጎብኘትና የመመልከት ዕድል ይኖረናል ማለት አይደለም። ግን ችግር የለውም። ከንቲባ አዳነች አቤቤና የቢሮ ኀላፊዎች ሰሞኑን ለከተማዋ ምክር ቤት ያቀረቡትን ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት ዐጠር ዐጠር አድርገን መቃኘት እንችላለን።
ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል
ከግንባታው ግዙፍነትና ፍጥነት ጋር፣ በውበቱና በታሪካዊነቱ የተደነቅንበትና የኮራንበት የዓድዋ ድል መታሠቢያ ሙዚየም፣ የዓመቱ ማሳያ ዓርማ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅና ሲመረቅ ታስታውሳላችሁ። ድንቅ ነው።
በማግሥቱ ውስጣችንን ዙሪያችንን ስንመለከት ግን… በደስታና በምስጋና ንግግሮች ፋንታ፣ እልፍ ጥያቄዎች እየተደራረቡ ይመጣሉ። “ታዲያ ሌሎች እልፍ ፕሮጀክቶችስ ለምን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ አይቻልም?” የሚሉ ሐሳቦች በሚሊዮኖች አእምሮ ውስጥ ይፈጠራሉ።
ታሪካዊው ሕንጻ ተገንብቶ በእውን ሲመረቅ በማየታችን የደስታና የእርካታ መንፈስ ባይርቀንም እንኳ… በቦታው የእልህ ስሜቶች እየተወለዱ፣ “ሌት ተቀን በመትጋት፣ ተጨማሪ ታሪክ መሥራት”… እያሉ ይወተውቱናል።
ከዚያ ወዲህ ብዙ ሥራዎች ሲፋጠኑና ሲጠናቀቁ ብናይ ታዲያ ምን ይገርማል?
የዐድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ብዙ ልምድ አግኝተንበታል በማለት በዓመታዊ ሪፖርት የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፕሮጀክት ክትትልና አመራር ልምድ አግኝተንበታል። የኮሪደር ልማት በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ጠቅሞናል ብለዋል።
የኮሪደር ልማትም በተራው፣ የከተማዋን የኢኮኖሚና የሥራ ከማፋጠን፣ ለኑሮ ጽዱና የተዋበ አካባቢ ከመፍጠር በተጨማሪ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ እንደመጣ ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
ግንባታዎችን በጥራት የመምራት “ዲሲፕሊንና” በፍጥነት ለውጤት የማብቃት ተጨማሪ ልምድ አግኝተናል።
የሥራ ባህል ለማሳደግ ችለናል ብለዋል - ከንቲባዋ።
በሕዝባችን ዘንድ የልማት ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ልማቱ ወደ አካባቢያቸው እንዲመጣ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል።
በእርግጥም ደግሞ የኮሪደር ልማት በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚቀጥል ከንቲባዋ ሲገልጹ፣ ጥናት የተካሄደባቸውና ለሥራ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በሌላ አነጋገር፣ 2016 ዓ.ም. እልፍ የፕሮጀክቶች ስኬት የተመዘገበበት ዓመት ሆኗል። ይህም በሪፖርት እየተዘረዘረ ቀርቧል። ነገር ግን፣ በዚህ ብቻ ረክቶ መቀመጥ የለም። እንዲያውም ለሚቀጥለው ዓመት አስበልጦ ለመሥራት መነሻና መንደርደሪያ ብርታት እንደሚሆን ከንቲባዋ ጠቁመዋል። “የአዲስ አበባ ልማት ሁሉንም ማኅበረሰብ ያቀፈና ማንንም ወደኋላ ያልተወ ነው” ብለዋል።
እንግዲህ የመጪውን ዓመት ለመገመት የዘንድሮውን ማየት ነው።
በመንግሥትና በበጎ አድራጎት ሥራ ከ18091 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበት ዓመት
በፍጥነት እየተጠናቀቁ ለአገልግሎት ከበቁት ግንባታዎች መካከል አንዳንዶቹ “ሜጋ ፕሮጀክቶች” ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው።
የዓደዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም
ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል
ቃሊቲ - ቱሉዲምቱ - ቂሊንጦ መንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች
3 ግዙፍ የገበያ ማዕከላት
የጉለሌ የተቀናጀ ልማት
የፒያሣ አራት ኪሎ፣ የሜክሲኮ ሳር ቤት የመሳሰሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች
እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶችን ለማየት ሌሎችንም አለፍ አለፍ እያልን ለመጥቀስ እንሞክር።
’’ለነገዋ ’’10 ሺ ሴቶችን እየተቀበለ ሥልጠና የሚሰጥ ማዕከል
የተሻለ ይገባታል
የሴቶች ተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ተገንብቶ ሥልጠናዎችን መስጠት ጀምሯል። ዕምቅ ዐቅማቸውን እንዲጠቀሙ፣ ሕይወታቸውን እንዲመሩ፣ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ችግር ሳይበግራቸው እንዲያንሰራሩ፣ ከራሳቸውም አልፈው ለሌላ እንዲተርፉ ነው የሥልጠናዎቹ ፋይዳ።
የማዕከሉ ትልቅነት ከዩኒቨርስቲ አይተናነስም። በአንድ ጊዜ 10ሺ ሴቶችን ተቀብሎ ሥልጠና የመስጠት ዐቅም አለው። ግን ከዚያም በላይ ነው። ጠለላና ከለላ ይሆናል። ማደሪያ ክፍሎች ተሟልተውለታል። ለልብስና ለምግብ አይቸገሩም። የሴቶች ህልምና ራዕይ፣ መተማመኛና አለኝታ፣ ሥንቅና ተስፋ ነው ማለት ይቻላል።
“ቀዳማይ ልጅነት
(የሕፃናት ማቆያ እንክብካቤና ትምህርት)
አዲስ አበባ ህጻናት የሚያድጉባት ምቹ ከተማ
“የቀዳማይ ልጅነት” በሚል ስያሜ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች፣ ዋና ዓላማቸው የሕፃናትን የአእምሮና የአካል ዕድገት ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ግን፣ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ቤተሰቦችና ወላጆች ትልቅ ድጋፍ ይሆንላቸዋል። ልጆችን ለጎረቤቶች አደራ እየሰጡ፣ ከአክስትና ከአያት ጋር እንዲውል እየወሰዱ፣ ወደ መደበኛ ሥራ መሄድ በዛሬ ዘመን አይቻልም። ብዙ እናቶች ልጆችን ማሳደግ ማለት፣ በመደበኛ ሥራ ጋር መለያየትና ቤት ውስጥ መዋል ማለት ይሆንባቸዋል።
“የቀዳማይ ልጅነት” በሚል ስያሜ እየተስፋፉ ያሉ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎቶች፣ ለልጆች ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለሴቶች ትልቅ ትርጉም አላቸው። ሕፃናት በተለይ እናቶች በየተሰማሩበት የሙያና የሥራ መስክ ላይ የዕድገት ጉዟቸው እንዳይስተጓጎል ጥሩ ዕድል ያገኙበታል።
አዲስ አበባ “ሕፃናትን ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ” ትሆናለች ብለን እየሠራን ነው። ከ320ሺ ገደማ ሕፃናት “የቀዳማይ ልጅነት ትምህርትና እንክብካቤ” እንዲያገኙ ክትትልና ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል - ከንቲባዋ።
ለዚህም ነው ከ3680 በላይ የመዋዕለ ሕፃናት መምህራን ሠልጥነው ወደ ሥራ የተሰማሩት።
5200 የሕፃናትንና የእናቶችን ጤንነት እንዲሁም የልጆችን ዕድገት ቤት ለቤት እየተከታተሉ ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎችም ተመርቀው ሥራ ጀምረዋል።
10800 ነብሰ ጡር እናቶች እና ሕፃናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ አግኝተዋል።
ዋናው ጤና - የትልልቅ ሆስፒታሎች ግንባታ!
ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በጤና ተቋማት አገልግሎት እንደተስተናገዱና አገልግሎት እንዳገኙ ዓመታዊው ሪፖርት ይገልጻል። ብዙዎቹ ተመላላሽ ታካሚዎች ናቸው። በየጊዜው እየተስተናገዱ ሕክምናቸውን ይከታተላሉ፤ የጤና አገልግሎት ያገኛሉ። ለተመላላሽ ታካሚዎች የተሰጡ የአገልግሎት መስተንግዶዎች በአጠቃላይ ከ13 ሚሊየን ይበልጣሉ።
ከ190 ሺህ በላይ እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል የጤና አገልግሎች እንዳገኙና በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች እንደጨመረ ገልጸው፣ በዚህም ምክንያቶ የእናቶች ሞት እንደቀነሰ ተናግረዋል።
የጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት በመስፋፋቱ፣ ከመቶ ሺህ ወሊዶች ውስጥ በእናቶች ላይ የሚያጋጥመው የሞት አደጋ ከ34 በታች ሆኗል። ለታዳጊ አገራት በዓለም ጤና ድርጅት የወጣውን መስፈርትና በአገራዊ ራዕይ የተዘጋጀውን ግብ ለማሳካት ተችሏል። ግን በዚህ አያበቃም። የእናቶች ጤንነትና ደህንነት ይበልጥ እየተሻሻለ እንደሚሄድ አያጠራጥርም።
የሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እየተስፋፋ ቁጥራቸውም እየጨመረ ነው። የዘውዲቱ መታሰቢያና የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም የራስ ደስታ ዳምጠውና የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች ነባር ዐቅማቸውና አገልግሎታቸው እንዲስፋፋ፣ ተጨማሪ ሕንጻዎች እየተሠሩ ነው፤ የሙያ መሣሪያዎች እየተሟሉ ነው። የሕንጻዎቹ ግንባታ ከ50 በመቶ አልፏል።
ሦስት አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች በአዲሱ ዓመት አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተዘጋጁ ነው።
ሁለት ትልልቅ ሆስፒታሎችም እየተገነቡ ግማሽ ላይ ደርሰዋል። በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት ለመስጠት ይበቃሉ ብለዋል የጤና ቢሮ ኀላፊ ዶ/ር ዮሐንስ።
በኮልፌ ቀራኒዮ የተጀመረው የዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ 68% እንደደረሰ የገለጹት የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሆስፒታሉ 520 በላይ ክፍሎችና 423 አልጋዎች እንደሚኖሩት ተናግረዋል።
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ሆስፒታልም ከትልልቆቹ መካከል የሚመደብ ነው። ግንባታ ወደ ስድሳ በመቶ ደርሷል። 520 ክፍሎችና 370 አልጋዎች ይኖሩታል ብለዋል - ከንቲባዋ።
ትውልድን መገንባት - የተማሪዎች ውጤት ዘንድሮ ተሻሽሏል።
የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ዘንድሮ ከ626 ሺህ በላይ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ከ232 ሺህ በላይ ማድረስ ችለናል ብለዋል - ከንቲባዋ።
“የመዋዕለ ሕፃናት” ትምህርት ሲታከልበት፣ የተማሪዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን 175 ሺህ በላይ ሆኗል።
ከበጎ አድራጎት የገንዘብ፣ የዐይነትና የሙያ ድጋፎችን ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት 6.4 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል። ይህም ተማሪዎችን ለማገዝ ጠቅሟል። በተማሪዎች ምገባ 780 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ ችለዋል። የተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ የትምህርት ቁሳቁስና የመምህራን የሥራ ልብስ ተሟልቶ እንደቀረበም ተገልጿል። ደብተር፣ ስክርቢቶ፣ የትምህርት ቤት ልብስ ለልጆች ማሟላት የስንትና ስንት ቤተሰብ ራስ ምታት እንደነበረ ማን ሊረሳው ይችላል? ወላጆች ይመሰክራሉ።
በእርግጥ መጻሕፍት አቅርቦትም ወጪው ቀላል እንዳልሆነ የከተማዋ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ተናግረዋል። እንደ አዲስ የተዘጋጁትን የመማሪያ መጻሕፍት ለሁሉም ተማሪዎች ለማዳረስ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር በጀት ይጠይቃል። ቢሆንም ለሁሉም ተማሪዎች ማዳረስ ተችሏል። የትምህርት ጥራት ከመማሪያ መጻሕፍት ውጭ አይታሰብምና። ደግሞስ ከንቲባዋ፣ “ትልቁ ሥራችን የትውልድ ግንባታችን ነው” ብለው የለ!
ዘንድሮ የተማሪዎች ውጤት መሻሻሉ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ከሳምንት በፊት በይፋ የተገለጸውን የ8ኛ ክፍል የፈተና ውጤት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በፈተናው 50 ነጥብና ከዚያ በላይ ውጤት ያገኙ ተማሪዎች ብዙ ናቸው።
በቀን የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች 82.4 በመቶ ያህሉ፣ በቀን የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ 96 በመቶ ያህሉ ከ50 ነጥብ በላይ ውጤት በማግኘት አልፈዋል ብለዋል፤ሃላፊው።
ከ290 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል አግኝተዋል
የጤናውም፣ የትምህርቱም፣ የኮሪደር ልማቱም… ሁሉም ፕሮጀክቶችና ጥረቶች፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ “ነዋሪዎች ሠርተው ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያግዙ ናቸው” ማለት ይቻላል።
የኢንቨስትመንትና የንግድ ፈቃድ አመዘጋገብን በዘመናዊ አሠራር በማሻሻል ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ ገበያን ማረጋጋት፣ የማምረቻና የገበያ ማዕከላትን መገንባትና ማዘጋጀት… እነዚህና ተመሳሳይ ጥረቶች በሙሉ፣ የነዋሪዎች የመተዳደሪያ ሥራ እንዲሳካና አዳዲስ የሥራ ዕድሎች በብዛት እንዲፈጠሩ የሚጠቅሙ ናቸው።
በእርግጥ ደግሞ፣ ዘንድሮ ለ330 ሺህ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ከማከናወን በተጨማሪ፣ ለ78 ሺህ ያህል አዲስ ንግድ ፍቃድ እንደተሰጠ የከተማዋ የንግድ ቢሮ ኀላፊ ገልጸዋል።
1919 የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ታድሰዋል። 2619 አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችም ተሰጥተዋል።
ከ7500 በላይ ኢንተርፕራይዞች የ2.5 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዳገኙ ያወሱት ከንቲባ አዳነች፣ ቀድሞ ከተሰጠው ብድር 2.6 ቢሊዮን ብር ማስመለስ እንደተቻለ ጠቅሰዋል። 466 አምራች ኢንዱስትሪዎችም የመሳሪያ ሊዝ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በትልልቅ ኢንቨስትመንቶችና በፕሮጀክቶች፣ በአነስተኛና በመካከለኛ ተቋማት አማካኝነት በአጠቃላይ ከ290 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዳገኙም ተጠቅሷል። 50 መቶ ያህሉም ሴቶች ናቸው ተብሏል።
“ከእናንተ መካከል ያልሰደብኩት ሰው ካለ፤ እሱን ይቅርታ እጠይቀዋለሁ”
በሩቅ ምስራቅ የሚተረክ አንድ አፈ - ታሪክ አለ፡፡ አንዳንዶች ከቪክቶር ሁጎ መጽሐፍ ባለታሪኩ ከዣን ቫልዣ ጋር ያዛምዱታል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንድ በጣም ሀብታምና ዝነኛ ሌባ ነበር፡፡ ከማን ይስረቅ ከማን ምንም አይጨንቀውም፡፡ እሱ መስረቁን እንጂ የተሰረቀባቸው ህዝቦች ምን ያህል እንደሚከፉም ለአንዲት አፍታ አስቦበት አያውቅም፡፡ ብዙ ሰዎች መስረቁን እንዲተው ጠይቀውታል፡፡ የተሻለ ኑሮ እንዲኖርም ሙከራ አድርገዋል፡፡ ያስፈራሩትም ነበሩ፡፡ ግን አልሰማ ብሏል፡፡
አንድ ማታ አንድ ቤት ሰብሮ ይገባል፡፡ የማን ቤት ይሁን የማን አላወቀም፡፡ ሆኖም ከውጪ ሲያዩት ውድ ዕቃና ንብረት ያለው ይመስላል፡፡ ሌባው በመስኮት ዘሎ ሲገባ ከዚያ ቤት ሊሰረቅ የሚችል በጣም ጥቂት ንብረት ብቻ ነው ያለው፡፡
“በከንቱ ዕውቀቴን፣ ጊዜዬንና ጉልበቴን አባከንኩኝ” አለ ለራሱ፤ “ከዚህ የሚወሰድ ነገር አለመኖሩን ቅንጣት ጥርጣሬ ኖሮኝ ቢሆን፣ በጭራሽ አልሞክረውም ነበር፡፡” ሆኖም ይሄን ሁሉ ለፍቶ፣ ስንት ዕውቀትና ጥበብ ያፈሰሰበትን ነገር ትቶ ባዶ እጁን ወደ ቤቱ ለመሄድ አልፈለገም፡፡ መሬት ላይ ብዙ የታሰረ ልብስ አየ፡፡ ስለሆነም ያንን ለመዝረፍ ወሰነ፡፡
ልብሱን በመሰብሰብ ላይ እያለ አንድ ድምፅ ሰማ፡፡ ዘወር ሲልም ከጀርባው አንድ ሽማግሌ ሰው ቆመው አየ፡፡ የተሸከመውን ልብስ መሬት ላይ ዘርግፎ ጥሎ መሮጥ ጀመረ፡፡
ሽማግሌውም፤
“አንድ ጊዜ ቆይ፣ እባክህ አንዴ ቆይ፡፡ አትሂድ፡፡ እኔ አግዝሃለሁ፡፡ ብቻህን ይሄን ሁሉ ተሸክሞ ለመሄድ ይከብድሃል፡፡ እንካፈልና እንሸከመው፡፡ ግማሽ እኔ እይዛለሁ፡፡ ግማሹን አንተ ያዝ”
ሌባው፣ ሽማግሌው ሰውዬ ሌባ ሌባ መሆናቸውን ገመተ፡፡ ግማሽ ግማሽ መሸከም ያለባቸው ለምን እንደሆነ ግን ሊገባው አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ የገቡት እሳቸው ናቸውና ብዙውን እጅ እኔ ልውሰድ ማለት ነበረባቸው፡፡
“እሺ ሊያግዙኝ ይችላሉ” አለ ሌባው፡፡ “እርስዎ ግን ግማሹን አይወስዱም፡፡ ትንሽ ነገር ልሰጥዎት እችላለሁ - ድካምዎትን አይቼ፡፡”
“እሺ ይሁን ግዴለም እንዳልክ” አሉ ሽማግሌው፤ የየድርሻቸውን ተሸከሙና ከቤት ወጥተው መንገድ ጀመሩ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሌባው የሽማግሌው መንቀራፈፍ አሰለቸው፡፡ “ቶሎ ቶሎ ተራመዱ እንጂ” አላቸው በሹክሹክታ፡፡ “ካልፈጠኑ’ኮ መያዛችን ነው፡፡ ከመንጋቱ በፊት መደበቂያዬ ቦታ መድረስ ይኖርብናል፡፡ ፍጠኑ!”
ሽማግሌው በተቻላቸው ፍጥነት ሁሉ ተውተረተሩ፡፡ ግን የተሸከሙት በጣም ከብዷቸዋል፡፡ ሌባው፤ አሁንም አሁንም ፍጠኑ እያለ ያዋክባቸዋል፡፡ “እንዲህ ቀርፋፋ መሆንዎትን ባውቅ ኖሮ መጀመሪያውኑ እንድትሸከሙልኝ አልፈቅድም ነበር! ወይኔ ሰውዬው!” እያለ ቁጭቱን ገለፀ፡፡
በመጨረሻ ሌባው መሸሸጊያ ቤት ደረሱ፡፡
“አሁን እንግዲህ እነዚያን ሁለት ጥቅሎች ያንሱ፡፡ ስላገዙኝ እነሱን ውሰዱ፡፡ ከዛሬ በኋላ ሁለተኛ አይንዎትን ለማየት አልፈልግም” አላቸው፡፡
ሽማግሌው ተሸክመውት የነበረውን ሁለት ጥቅል መሬት ላይ ድንገት ወረወሩት፡፡ ከዚያም ወንበሩ ላይ ዘፍ ብለው ተቀመጡና፤
“እኔ ምንም ልብስ አልፈልግም፡፡ እኔ እንዲያው ልረዳህ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ አየህ ሰብረኸው የገባኸው ቤት የእኔ የራሴ ቤት ነው፡፡ የወሰድከው ልብስም በሙሉ የእኔ ነው፡፡ ’ይሄንን ለመስረቅ የተገደድከው እንዴት ቢቸግርህ ነው‘ ብዬ አሰብኩ፡፡ ስለዚህም በተጨማሪ ምን ልረዳህ እንደምችል አመዛዝኜ በሸክም ልረዳህ ወሰንኩ፡፡
አሁን እንግዲህ የት እንደምኖር አሳምረህ አውቀሃል፡፡ ሌላም ነገር ባስፈለገህ ሰዓት በተጨማሪ መጥተህ መውሰድ ትችላለህ፡፡ ቤቴ ቤትህ ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር መውሰድ ትችላለህ፡፡ የእኔ ንብረት የአንተም ንብረት ነው፡፡”
ሌባው ጆሮውን ማመን አቃተው፡፡ በመጀመሪያ እንደቀልድም መሰለው፡፡ የምር መሆኑን ሲያውቅ ግን “በዐይኔ በብረቱ የሆነውን ነገር ሁሉ ባላይ ኖሮ በጭራሽ አላምንም ነበር፡፡ የገዛ ንብረትዎ ሲሰረቅ ማሳሰር ሲችሉ ፈቅደው ዝም አሉኝ፣ ይባስ ብለው በሸክም እረዱኝ፡፡ በዛ ላይ እንደልቤ እየፈነጨሁ ስሰድብዎ ታግሰው ሲያበቁ፣ በመጨረሻ ደግሞ ሀብቴ ሁሉ ሀብትህ ነው ብለው ሰጡኝ፡፡ ለእኔ ከዚህ በላይ ቅጣት የለም!! ከዚህ በላይም በህይወቴ የተማርኩት ነገር የለም!!” አለ፡፡
***
ሌባም፣ ሀብታምም ከሆነ ሰው ይሰውረን ማለት ደግ ነው፡፡ እንደ ሽማግሌው ሆደ - ሰፊ ህዝብ ሲኖር፣ የሚማር ሌባ አይገኝም፡፡ አንዱ ሲሳካ አንዱ ይጎድላል፡፡ ይቅርታ የሚያደርግ ሲገኝ፣ ይቅርታ የሚደረግለት ሰው አይገኝም፡፡ ይቅርታ ጠያቂ ሲገኝ፣ ተጠያቂው አይገኝም፡፡ ሁለቱ ሰምሮ እንዲገኝ ጥረት የሚያደርጉ ሁነኛ አዛውንቶች ካልተገኙ አገር የቂም፣ የበቀል፣ የእልህ፣ የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣ የሁሉን ለእኔ፣ የልስረቅ አግዙኝ….አገር ትሆናለች፡፡ ሲነገር፣ ሲመከር፣ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የማይሰማ መጨረሻው አያምርም፡፡ ስለሆነም አገርም ለውጥ እርሟ ይሆናል፡፡
ሰውም “የሚስቴ ውሽማ መታኝ፣ ያሳደግሁት ውሻ ነከሰኝ፡፡ ቁጭ ብዬ አደርኩ ገርሞኝ” ሲል ይኖራል፡፡ አንድ ጊዜ የጀርመን ፕሬዚዳንት በሆሎኮስት በአይሁዶች ላይ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ ለእስራኤል ፓርላማ ሲናገሩ፡-
“ዛሬ የእሥራኤል ህዝብ እያየኝ በዚያን ዘመን ስለተገደሉ፣ አሁን የትም ሄጄ ይቅርታ ልጠይቃቸው ለማልችላቸው ሰዎች፣ በሀፍረት እጅ እነሳለሁ” ብለው ነበር፡፡ በማናቸውም ወቅት ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ የሆነ መሪና የፖለቲካ ሀላፊ፣ እንዲሁም ይቅርታ ለማድረግ ዝግጁ የሆነ ተበዳይ መኖር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የሰላም ቁልፍ ይሄው ነውና፡፡ ለይቅርታ አንዱ ቁልፍ ነገር፣ ሌላውም ሰው እንደኔ ሊያስብ ይችላል የሚል ከቡድን ስሜት የራቀና የጠራ አስተሳሰብ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ስለተማሪ ንቅናቄ በፃፈው አንድ መጣጥፍ፤ “ለነሱ ቡድን የገበረውን የሚነዳ ከብት ይሆናልና ይነዱታል፡፡ የሚጠሉት ቢኖር የሚያስብ ሰው ነው…” ብሎ ነበር፡፡ ይሄ አባዜ ዛሬም አልለቀቀንም፡፡ ግትር የቡድን ስሜት ለሀገር እንዳልበጀ አለ፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ዘውድ - ጫኝ፣ አስጫኝና አድራጊ ፈጣሪ ይዞ ሲጓዝ የኖረ እንጂ ከልብ ለህዝቡ ያሰበ አልነበረም፡፡ የራስን ዕምነት የሁሉ ዕምነት አድርጎ መውሰድ ሌላው አደጋ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ግትር እምነት እንደ ዕፅ ዐይነ - ሥጋንና ዓይነ - ህሊናን ይጋርዳልና ዛሬም በብርቱ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ይቅርታ የመጠያየቅ ባህል ልበ - ብሩህነትንና ልበ - ንጹነትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ባህል ለአገርና ለህዝብ መንገድ ቀዳጅ መሆኑን አምኖ ዕብሪት ትቶ፣ ክፋትን አስወግዶ፣ የመጣው ይምጣን ትቶ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ወደድንም ጠላንም በቁርጠኝነት መደረግ ያለበት ሁነኛ ነገር ነው፡፡ ሁሉን በመናቅ፣ ሁሉን ዝቅ አድርጎ፣ ሁሉን በማንጓጠጥ፣ ሁሉን አወቀ አላወቀ ምን ለውጥ ያመጣ፣ በማለት የበላይነትንና የውስጠ - ምኞት እርካታን ብቻ ለማሳካት መደገግ ከቶም የትም የሚያደርስ አይደለም፡፡ ካልሆነ ለታዋቂው የጀርመን የሙዚቃ ቀማሪ እንደተሰጠው አባባል፤ “ከመካከላችሁ ያልሰደብኩት ሰው ካለ፣ እሱን ይቅርታ እጠይቀዋለሁ” ብሏል የተባለውን ዓይነት የዕቡይ ፌዝ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ የብዙ ዕድሜ ምልክት አይደለም!
“የትጥቅ ተፋላሚዎች በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ የሚያስችል አቅም አለን” - የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን
የትጥቅ ትግል ተፋላሚዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል አቅም እንዳለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው ከሌሎች ኮሚሽነሮች ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለተፋላሚዎቹ አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ መንግስትንና ሌሎች አካላትን ኮሚሽኑ እየጠየቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በመጪው ሳምንት በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪና በድሬዳዋ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እንደሚጀምር የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ስራውን ለማስተባበር የኮሚሽኑ ሞያተኞችና ኮሚሽነሮች ወደ አካባቢዎቹ ስምሪት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ስራውን ለመጀመር ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተገናኘ፣ ቀሪ ስራዎች እስከሚጠናቀቁ እየተጠባበቀ መሆኑም ተጠቁሟል።
አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ በአብዛኛዎቹ ክልሎች እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በአፋር ክልል ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ከባድ ሙቀት ያለበት በመሆኑ፣ በክልሉ የሚከናወነው አጀንዳ ማሰባሰብ ጥቅምት ወር ግድም እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ተፋላሚዎች በአገራዊ ምክክር ሂደቱ የመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሳተፉ የማድረግ አቅም እንዳለው ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
“ይህ የምክክር ሂደት ክርክር አይደለም፤ ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበት ሂደት ነው” ያሉት መስፍን (ፕ/ር)፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ካሉበት ሆነው ለኮሚሽኑ አጀንዳ መላክ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
መግለጫውን የሰጡት ሌላው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐመድ ድሪር፣ ለስራ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች በሂደቱ ላይ ያለመሳካት ጥርጣሬ አለመነሳቱን አውስተው፣ “በሕዝቡ ዘንድ የመሸማቀቅና ጥያቄ ያለማቅረብ ሁኔታ እስካሁን አልታየም” ብለዋል። ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም፣ “ምክክር አሁን በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር የሚያያዝ አይደለም፤ ሂደቱ ለአገሪቱ ያስፈልጋታል፤ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግስት ኮሚሽን አይደለም።” ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም፣ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የመንግስት ሃሳብ ነው። ነገር ግን የእኛን አካሄድ ይዘውረዋል ማለት አይደለም” በማለት አስረድተዋል።
“የአማራና የትግራይ ክልሎች ቀርተው ምክክር ተካሄደ ቢባል ቀልድ ነው” ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፣ “መንግስትን እንደባለድርሻ አካል ነው የምንቆጥረው” ብለዋል።
“በትግራይ የተለየ ዕንቅፋት አልገጠመንም። ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር የተያያዙ የሚቀሩ የቴክኒክ ስራዎች ስላሉ ነው። ስራዎቹ ሲጠናቀቁ፣ ሂደቱ ይጀምራል” ሲሉ ያብራሩት ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “የግድ ሁሉም አንድ ላይ እስኪሆኑ መጠበቅ ላያስፈልግ ይችላል” ብለዋል።
በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ከቆዩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር ኮሚሽኑ ምን እየሰራ እንደሆነ ከአዲስ አድማስ የተጠየቁት ለኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ ተናግረዋል። “ከሃይማኖት ተቋማቱ ጋር ውይይት ተደርጎ ችግሩ ተፈትቷል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ስራ ከገባ፣ ሁለት ዓመታትን ማስቆጠሩ የሚታወቅ ነው።
ዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር ተካሄደ
አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር ያዘጋጀው የዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር ዛሬ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል። በዚህ መርሃ ግብር የገነነ ስራዎች እና ሕይወት በዝርዝር መዘከሩ ተነግሯል።
መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ቤዛው ሹምዬ ማሕበሩ ባለፉት አስር ዓመታት ስላደረጋቸው ዕንቅስቃሴ አትተዋል። አክለውም "ያለፉትን በመዘከር፣ የሰሩትን በማክበር ተተኪዎችን እንፍጠር!" በሚል መሪ ቃል ስለተዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር በዝርዝር አብራርተዋል።
የገነነ መኩሪያ የሕይወት ታሪክ በንባብ የቀረበ ሲሆን፣ በሕይወት ዘመኑ ያበረከታቸው የተለያዩ ስራዎች በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ተዘክረዋል። ከገነነ መኩሪያ "ኢሕአፓ እና ስፖርት" መጽሐፍ የተቀነጨበ ስራ ለዕድምተኞች በትረካ ቀርቧል።
በተጨማሪም፣ ለቀድሞ የእግርኳስ ተጨዋቾች ተካ ገለታ፣ ግርማ አበበ፣ እና ጌቱ መልካ፤ ለቀድሞ ቦክሰኛ ደረጀ ደሱ እና ለድምጻውያኑ ጎሳዬ ተስፋዬ እና አብዱ ኪያር፣ ለሁለገቡ የኪነ ጥበብ ሰው ዳዊት አፈወርቅ፣ ለተዋናይ ተሰማ ገለቱ፣ ለኬሮግራፈር ዳንኤል ደሳለኝ፣ ለጋዜጠኛ እንግዱ ወልዴ እና ለሕግ ባለሞያዋ ሰናይት ፍስሐ (ፕ/ር) ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እና የገነነ መኩሪያ ባለቤት ወይዘሮ አስቴር አየለ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ታድመዋል።
አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር የተመሰረተበትን አስረኛ ዓመት በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተከብሯል።
33ኛው XXXIII ኦሎምፒያድ በፓሪስ
ከ15 ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች ያገኛል
ኢትዮጵያ 3 ወርቅ፣ 5 ብርና ነሀስ- Nielsen
ኢትዮጵያ የወርቅ፣ 5 ብርና 5 ነሐስ- Athletics weakly
ባለፉት 32 ኦሎምፒያኖች ከኢትዮጵያ 282 ኦሎምፒያኖች (208 ወንድና 74 ሴት) ተሳትፈዋል 58 ሜዳልያዎች (23 የወርቅ፣ 12 የብርና 23 የነሐስ) ተገኝተዋል
ወጭ 9.5 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ 5.3 ቢሊዮን ዩሮ
በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ሁለት ሳምንታት ቀርተዋል፡፡ በ32 አይነት ስፖርቶች 329 የኦሎምፒክ ውድድሮች ይደረጋሉ። ከ10,672 ኦሎምፒያኖች 206 አገራትን በመወከል ይሳተፋሉ።
ፈረንሳይ ለኦሎምፒክ መስተንግዶ በአጠቃላይ ያወጣችው በጀት ከ9.5 ቢሊዮን ዩሮ አልፏል። ከበጀቱ 96 በመቶው በግሉ ሱክተር ተሸንፏል።
ዓለምዓቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ አጋር ኩባንያዎች የኦሎምፒክ የት/ቤትና የፈቃድ ቢሮ ናቸው። ግሪክ በ2004 አቴንስ ላይ 9.1 ቢሊዮን ዩሮ ፤ ጃፓን በ2022 ቶኪዮ ላይ 12.9 ቢሊዮን ዩሮ እንዲሁም እንግሊዝ በ2012 እ.ኤ አ ለንደን ላይ 15 ቢሊዮን ዩሮ ለኦሎምፒክ መስተንግዷቸው አውጥተዋል፡፡
የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴው 4.3 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ሲያደርግ ዓለምአቀፍ ኦሎምፒክ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ (750 ሚሊዮን ዩሮ ከቲቪ መብት፤ 470 ሚሊዮን ዩሮ ከዋና አጋሮች) መድቧል። CDES የተባለ ተቋም ባዘጋጀው የኢኮኖሚ ትንታኔ ፈረንሳይ ከኦሎምፒኩ ቢያንስ እስከ 5.3 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ እንደምታገኝ ይጠበቃል፡፡ ከመስተንግዶው ጋር በተለያየ መንገድ የሰሩ ከ80 በላይ ኩባንያዎችም እስከ 3 ቢሊየን ዩሮ ገቢ እንደሚኖራቸው ገምቷል።
ከ15 ሚሊዮን በላይ የኦሎምፒክ ታዳሚዎች በፓሪስ እንደሚገኙ የተጠበቀ ሲሆን ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ ናቸው ተብሏል።
አዘጋጅ ኮሚቴው ከ10 ሚሊዮን ትኬቶች መሸጣቸውንም አረጋግጧል።
የNielsen Gracenote ትንበያ
ኦሎምፒኩ 1 ወር ሲቀረው በዓም 55 አገራት የሚንቀሳቀሰው Neilsen የተባለ የሚዲያ ተቋም የሜዳሊያ ትንቢያውን Gracenole virtual medal table በሚል ይፋ አድርጓል። የሜዳልያ ሰንጠረዡን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ግምት ያገኙት አገራት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ግሬት ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ናቸው፡፡
ባለፉት 8 ኦሎምፒያዶች በመሪነት የጨረሰችው አሜሪካ በድምሩ 123 ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ አንደኛ እንደምትሆን ሲተነበይ፤ ቻይና በ87 ፣ ግሬት ብሪቴን በ62 ፣ ፈረንሳይ በ56 እንዲሁም አውስትሪሊያ በ48 ሜዳልያዎች እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ እንደሚያገኙ ተገምቷል፡፡
በኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ብዛት ደግሞ አሜሪካ በ37 መሪነቱን እንደምትይዝ ሲጠቆም፣ ቻይና በ36 ፤ ፈረንሳይ በ29፣ ሆላንድ በ17 ግሌት ብሪቴን በ14 የወርቅ ሜዳልያዎች ተከታታይ ደረጃዎችን እንደሚያገኙ ተገምቷል፡፡
ኢትዮጵያ 3 ወርቅ፣ 5 ብርና 5 የነሐስ
Nielsen Gracenote
በNeillsen ትንበያ መሰረት ኢትዮጵያ ፓሪስ ላይ 3 የወርቅ ሜዳሊያዎችን እንደምታገኝ፤ ከአፍሪካ ትልቁን ውጤት እንደምታስመዘግብና ከዓለም 16ኛ ደረጃ እንደሚኖራት ነው የተገመተው፡፡
በግሬስኖት ትንቢያ መሰረት ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፣ 5 የብርና 5 የነሐስ በድምሩ 13 ሜዳልያዎች እንደምታገኝ ሲተነበይ የቅርብ ተቀናቃኟ ኬንያ ደግሞ 3 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 9ሜዳሊያዎችን እንደምትሰበስብ ተጠብቋል ፡፡
በተያያዘ Total Olympics ድረገፅ በስለው ትንታኔ መሰረት ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ጠንካራ ተፎካካሪ ትሆናለች። ከ2020-2024 ከማድረጓ በፊት በዓለም ሻምፒዮና እና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች 6 የወርቅ፣ 8 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎችን መሠብሰቧን አመልክቷል።
ኢትዮጵያ 1 ወርቅ፣ 5 ብር፣ 5 ነሀስ
Athletics weekly
ታዋቂው የአትሌትክስ መፅሔት AW (Athletics weekly) ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ግምት የሰጠ መስላል። ከ5 ወራት በፊት በአትሌቲክስ ስፖርቶች ላይ አተኩሮ ባሰራጨው የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ትንበያና ትንታኔ ኢትዮጵያ -- 1 የወርቅ፣ 5 የብርና 5 የነሐስ ሜዳያዎችን እንደምትሰበስብ ገምቷል። በተጨማሪ በ4ኛ ደረጃ 5 የኦሎምፒክ ዲፕሎማዎችም ለማስመዝገብ እንደምትችል አመልክቷል።
በኦሎምፒኩ ላይ ኢትዮጵያ በመካከለኛ እና በረጅም ርቀት ወድድሮች ዋና ተፎካካሪ እንደምትሆን የመፅሄቱ ትንታኔ ቢገልፅም የወርቅ ሜዳልያ የምትወስደው በሴቶች ማራቶን ብቻ መሆኑን ነው የጠቀሰው። በፓሪስ 2024 ብቸኛው የወርቅ ሜዳሊያ ግምት የተሰጣት በሴቶች ማራቶን የዓለም ሪከርድ ባለቤቷ ትግስት አሰፋ ናት። 5 የብር ሜዳልያዎችን በሴቶች1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሐይሉ ፣ በ5ሺ ሜትር ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ጉዳፍ ጸጋይ፤ በ10ሺ ሜትር ሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ እና በሴቶች ማራቶን አማኔ በሬሶ ያገኛሉ ብሏል በሀተታው፡፡ አምስቱን የነሐስ ሜዳሊያዎች ደግሞ በ1500 ሺ ሴቶች ብርቄ ሃይሎም፤ በ10ሺሜትር ለተሰንበት ግደይና ሰለሞን ባረጋ፣ በ5ሺ ሜትር ወንዶች በሪሁ አረጋዊና በወንዶች ማራቶን ሲሳይ ለማ እንደሚያገኟቸው ገምቷል።
በአትሌቲክስ ዊክሊ ትንታኔ መሠረት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሜዳሊያ አደን ከባድ ተፎካካሪ ሆነው የሚጠቀሱት በሴቶች የኬንያዋ ፌዝ ኪፕዮገን ፤የሆላንዷ ሲፋን ሀሰን በወንዶች ደግሞ የኡጋንዳና የኬንያ አትሌቶች እንዲሁም የኖርዌዮ አትሌት ኢንግሪብስተን ናቸው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ለወርቅ ሜዳሊያ 50 ሺ ዶላር
ሲንጋፖር 737 ሺ ዶላር ጣሊያን
201 ሺ ዶላር አሜሪካ 37 ሺ ዶላር
በፓሪስ 2024 ላይ በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዎች የሚሰጥ በዓለም አትሌቲክስ ማህበር 2.4 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል ፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር በአትሌቲክስ ውድድሮች የወርቅ ሜዳልያ የሚያገኙት አትሌቶች 50 ሺ ዶላር እንደሚሸለሙ አስታውቋል
በነገራችን ላይ በኦሎምፒክ መድረክ የሜዳልያ ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች የተለያዩ አገራት የገንዘብ ሽልማቶችን በቦነስ መልክ በማቅረብ ይሰራሉ።
ታዋቂው ፎርብስ መፅሄት በሰራው ዘገባ ከ4 ዓመት በፊት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለወርቅ ሜዳሊያ ሲንጋፑር 737ሺ ዶላር በመሥጠት ግንባር ቀደም ስትሆን ጣሊያን 201ሺ ዶላር በመስጠት ተጠቅሰዋል።
አሜሪካ ለወርቅ 37,500 ዶላር፣ ለብር 22,500 ዶላር እዲሁም ለነሐስ 15ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት እንደምታዘጋጅ የፎርብስ ትንታኔ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ ያስታወቁት ነገር የለም፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው በሚገኘው አትሌቶችና አሰልጣኞች በኦሎምፒክ የሚመዘገብ ውጤት ላይ በሚሰጥ የገንዘብ ሽልማት እኩል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡ እንሰጣለን ኢትዮጵያ ባለፉት 32 ኦሎምፒያዶች
ባለፉት 129 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት 32 ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያ በ14 የተሳተፈች ሲሆን 33ኛው ኦሎምፒያድ ለ15ኛ ጌዜ የምትካፈልበት ይሆናል። በኦሎምፒክ መድረክ ሁሉንም ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ሲሆን በከፍተኛ የውጤት ታሪካቸው ከሚጠቀሱ 8 አገራት አንዷ ናት። አፍሪካን በመወከል ደግሞ ከኬንያ ቀጥሎ ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች፡፡
በፓሪስ ፈረንሳይ ከሚስተናግደው 33ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው 14 ኦሎምፒያዶች 282 ኦሎምፒያኖች (208 ወንድ እና 74 ሴት) ተሳትፈዋል፡፡ ከእነሱም መካከል 36 ኦሎምፒያኖች ከ1 እስከ 3 ባሉ ደረጃዎች ስኬታማ በመሆን 58 ሜዳልያዎችን (23 የወርቅ፤ 12 የብርና 23 የነሐስ) ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል፡፡ ከሜዳልያዎቹ ስብስብ 23 የወርቅ ሜዳልያዎችን ለኢትዮጵያ ያጎናፀፉት 14 ናቸው፡፡ በተረፈ 11 የብር ሜዳልያዎች በ12 እንዲሁም 23 የነሐስ ሜዳልያዎች በ20 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ተገኝተዋል፡፡
በቦክስ ስፖርት በ8 ኦሎምፒያዶች 28 ኦሎምፒያኖች (28 ወንድ )፤ በብስክሌት በ9 ኦሎምፒያዶች 31 ኦሎምፒያኖች (30 ወንድ 1 ሴት)፤ በውሃ ዋና በ3 ኦሎምፒያዶች 5 ኦሎምፒያኖች (3 ወንድ 2 ሴት) እንዲሁም በቴኳንዶ በ1 ኦሎምፒያድ (1 ወንድ) ተሳትፈዋል።
*****************
የኢትዮጵያ ቡድን
ፓሪስ 2024 ላይ በአትሌቲክስ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች፤ የዓለም ሪከርድ ባለቤቶች፤ አንጋፋና ወጣት ኦሎምፒያኖች የተሰባሰቡበት ነው። የቡድኑ ሙሉ ዝርዝር ከዚህ በታች የቀረበው ነው።
800 ሜትር ሴቶች
ፅጌ ድጉማ፣ ሐብታም ዓለሙ፣ ወርቅነሽ መለሰ፤ ንግስት ጌታቸው (ተጠባባቂ)
1500 ሜትር በወንዶች -
አብዲሳ ፈይሳ፣ ሳሙኤል ተፈራ፣ ኤርሚያስ ግርማ፣ ታደሰ ለሚ (ተጠባባቂ)
1500 ሜትር ሴቶች
ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ብርቄ ሃየሎም፣ ድርቤ ወልተጂ፤ ሂሩት መሸሻ (ተጠባባቂ)
5ሺህ ሜትር ወንዶች
ሀጎስ ገ/ህይወት፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ አዲሱ ይሁኔ፤ ሰለሞን ባረጋ (ተጠባባቂ)
5ሺህ ሜትር ሴቶች
ጉዳፍ ፀጋዬ፣ መዲና ኢሳ፣ እጅጋየሁ ታዬ፤ ፍሬወይኒ ኃይሉ (ተጠባባቂ)
10 ሺህ ሜትር ወንዶች
ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ በሪሁ አረጋዊ፣ ሰለሞን በረጋ፤ ቢኒያም መሀሪ (ተጠባባቂ)
10 ሺህ ሜትር ሴቶች
ጉዳፍ ፀጋዬ፣ ፎቴን ተስፋዬ፣ ፅጌ ገ/ሰላማ፣ አይናዲስ መብራቱ (ተጠባባቂ)
3ሺህ ሜትር መሠናክል ወንዶች
ለሜቻ ግርማ፣ ሳሙኤል ተፈራ፣ ጌትነት ዋለ፤ አብርሃም ስሜ (ተጠባባቂ)
3ሺህ ሜትር መሠናክል ሴቶች
ሲምቦ ዓለማየሁ፣ ሎሚ ሙለታ፤
በማራቶን ሴቶች
ትዕግስት አሰፋ፣ አማኔ በሪሶ፣ መገርቱ ዓለሙ፤ ጎይቶቶም ገ/ስላሴ (ተጠባባቂ)
በማራቶን ወንዶች
ቀነኒሳ በቀለ ፣ ሲሳይ ለማ፣ ዴሬሳ ገለታ፤ ታምራት ቶላ (ተጠባባቂ)
በ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ወንዶች
ምስጋና ዋቁማ
አረንጓዴ አሻራ - ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያቀፈ
ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ሲተክሉ ነው ያገኘናቸው - የስሪላንካ አምባሳደር ቴሻንታ ኩማራሲሪ። ፍላጎታቸው ግን ችግኝ ለመትከል ብቻ አይደለም። “አረንጓዴ አሻራ እንዴት እየሄደ ነው? ምን ዐይነት ትምህርትና ልምድ እናገኝበታለን?” በማለት በቅርበት እንደሚከታተሉት ነግረውናል። አረንጓዴ አሻራ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲኖረው አድርጋችኋል፤ በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ እንደሚቀስሙ አምናለሁ ብለዋል - አምባሳደሩ።
አረንጓዴ አሻራ የሁላችንም ሥራ የሁላችንም አሻራ ነው በሚል የባለቤትነት መንፈስ ያነጋገረን ደግሞ አሸናፊ ወርቁ (አሸበል) ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ነው የመጣነው፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ እየተከልን ነው ብሎናል። ሐሳባቸው ግን ከዚህም በላይ ነው። ዓመቱን ሙሉ የሚንከባከቡትና የሚያለሙት ቦታ እንዲኖር ይፈልጋሉ። እናም፣ ከመንግሥት የምንፈልገው “እዚህ ጋር ትከሉ ብሎ ቦታ እንዲሰጠን ብቻ ነው” ይላል - አሸበል።
አረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ ሽታ እንደሌለውና ሊኖረው እንደማይገባ የገለጹልን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለስ ምን ይላሉ? አረንጓዴ አሻራ ከፖለቲካ በላይ እንደሆነ ሲገልጹ፣ ትውልድን የማኖር አገርን የማጽናት ጉዳይ ነው ብለዋል ጠቅላይ ጸሐፊው። አረንጓዴ ዕፅዋት የፈጣሪ ጸጋ ነው፤ ሀብትም ውበትም ነው። ሰዎች ጥበብ ጎድሏቸው አረንጓዴ ጸጋ አጥተዋል። እናም… ይህን ለመመለስና ትውልድን ለማዳን የሃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ ላይ አርአያነታቸውን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል - ጠቅላይ ጸሐፊው።
አረንጓዴ አሻራ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያቅፋል። አረንጓዴ አሻራ ምግብም ውበትም ነው። ይሄ፣ የከንቲባ አዳነች አቤቤ አገላለጽ ነው። የከተማችን ነዋሪዎች የፆታ፣ የእድሜ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ሀገር በቀል ዛፎችን፣ የውበት ዕፅዋትን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች በጋራ እየተከሉ እንደሆነ ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ታሪክ… ለዓለምም ለአገርም ነው። “አካባቢ ተራቆተ” እየተባለ በዓለም ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ተወርቷል። ዓለማቀፍ ስብሰባዎች በብዛት ተካሂደዋል። እልፍ የስምምነት ሰነዶች ተፈርመዋል። ነገር ግን፣ በጎ ለውጥ ሲያመጡ እንዳልታየ ጠ.ሚ. ዐብይ አህመድ ሲገልጹ፣ “በስብሰባ አይቀየርም፤ በሱፍ ለባሾች አይቀየርም” ብለዋል። ችግኝ የሚተክሉ እጆች ናቸው የችግር መፍትሔ የሚሆኑት። “ይህን ተግባር በመፈጸም ለዓለም ማስተማር ከኢትዮጵያ ይጠበቃል” ብለዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አረንጓዴ አሻራ፣ እንደ ስሙ ልምላሜ ነው - አብቦ የሚያፈራ። ባለፉት አምስት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል። አረንጓዴ አሻራ ፍሬያማ ነው። ግን ለዛሬ ብቻ አይደለም። ለትውልድ ይተርፋል። ለኑሮ ብቻ ሳይሆን ለታሪክም ነው። ከነስሙ “አሻራ” ተብሎ የለ!
ለዘመናት የተራቆተውን የአገር ገጽታ የሚቀይር፣ ኢትዮጵያን የሚያለመልም፣ ዘመን ተሻጋሪ ትልቅ የጥበብ ሥራ ስለሆነም፣ “ታሪካዊ” የሚል ማዕረግ አይበዛበትም።
እንደማንኛውም ትልቅ ቁምነገር፣ እንደማንኛውም ታሪካዊ ሥራ፣ አረንጓዴ አሻራ “አቃፊ” ባህርይ አለው።
የአረንጓዴ አሻራ ትርጉም፣ የተራቆተውን አገር የልምላሜ ግርማ ማጎናጸፍ ብቻ አይደለም። አዎ፣ አረንጓዴ አልብሶ ያስውባል። ሲታይ ያምራል። ነገር ግን፣ ጣዕምም ምቾትም ጭምር አለው። እንዴት ቢሉ…
ከውጭ አገር፣ ፍራፍሬ፣ የእንጨት ቁሳቁስና የሥጋ ምግቦችን እንደ ብርቅ ነገር ማስመጣት ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። የመራቆት ዕዳ እዚህ ድረስ ነው። የእንጨት ቁሳቁስ ለኢትዮጵያ ብርቅ መሆን ነበረበት? ፍራፍሬስ? ማርና ወተትስ? ብርቅ መሆን አልነበረበትም።
ኢትዮጵያ የፍራፍሬ አገር መሆን ነበረባት። መሆንም አለባት። ንቦች የሚቀስሙት አበባ፣ ላሞች የሚጥግቡበት ሳርና ሰብል፣ ለእንስሳት ሁሉ ተስማሚ መኖ እንደ ልብ የምታበቅል ለምለም አገር መሆን አለባት። በሙያተኞች ታሪክ የምትጠቀስ ኢትዮጵያን የመሰለች የጥበብ አገር፣ የእንጨት ቁሳቁስን ብርቅ ሊሆንባት፣ ተቸግራ ከውጭ አገራት ልታስመጣ አይገባም ነበር። ይሄ የዝቅታ ታሪክ መቀየር አለበት - በአረንጓዴ አሻራ።
ይህም ብቻ አይደለም። ተራራውና ሸለቆው ዛፎች ሲበቅሉበትና አረንጓዴ ሲለብስ፣ ለም አፈር እየተሸረሸረ ተቦረቦረ የኢትዮጵያ መሬት አይራቆትም። በደለል ብዛት ሐይቆችና ግድቦች ውኃ አይሸሻቸውም።
አረንጓዴ አሻራ፣ አገርን ልምላሜ ከማልበስ ባሻገር፣ የማርና የወተት ጉዳይም ነው። የፍራፍሬና የሥጋ፣ የእንጨት ሙያንና የኤሌክትሪክ ብርሃንን ሁሉ ያቅፋል - አረንጓዴ አሻራ።
“ሀብትም ውበትም ነው” የተባለው አለምክንያት አይደለም። ሲያዩት ያምራል። መዓዛው ይማርካል። ግን ደግሞ የኑሮ ጣዕምም ነው። ሲቀምሱት ሲገምጡት ይጣፍጣል። ሲመገቡት ያጠግባል። “ለምግብነትም ለውበትም” በማለት ይገልጹታል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በአገር ደረጃ እንደታየው በአዲስ አበባም የተተከሉ ችግኞችም ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ 41 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ዓምና 17.5 ሚሊዮን ችግኞች።
ዘንድሮ ደግሞ 20 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከት የዓመቱ አረንጓዴ አሻራ ባለፈው ቅዳሜ “ሀ” ተብሎ ተጀምሯል።
ገሚሶቹ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው። ገሚሶቹ አገር በቀል የደን ዛፎች ናቸው። ገሚሶቹ ደግሞ የውበት ዕፅዋት። አረንጓዴ አሻራ ሁሉንም ያቀፈ አገራዊ ፕሮጀክት ነው - የሀብትና የውበት ፕሮጀክት። ለኑሮም ለመንፈስም ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። በልዩነቶች የታጠረ አይደለም። ሁሉንም የሚያቅፍ እንጂ።
የእገሌ ፓርቲ ችግኝ… የእከሌ ፓርቲ ችግኝ የሚል ልዩነት የለም። ችግኞች የፖርቲ አርማ ለብሰው አይጸድቁም። የዚህኛውም የዚያኛውም ችግኞች በአረንጓዴ ልምላሜያቸው አገርን ያሳምራሉ። አብበው ያፈራሉ።
በጾታ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት ልዩነቶች የተገደበ አይደለም። አንተ፣ እሷ፣ እኔ … ሁላችንም የምንተክላቸው ችግኞች በሙሉ፣ “አረንጓዴ አሻራ” ናቸው።
ያለ ልዩነት ሁሉን የሚያሰባስቡና የሚያቀራርቡ፣ እንደ አረንጓዴ አሻራ የመሳሰሉ “አቃፊ” ቁምነገሮችና ሥራዎች እንዲበዙልን አትመኙም? ካሰብንበትና ከተጋንበት ደግሞ፣ ምኞት ብቻ ሆኖ አይቀርም። አይከብደንም። ከአረንጓዴ አሻራ ጥሩ ልምድ አግኝተንበታልና።
የአረንጓዴ አሻራ የበረከት ምሥጢር ብዙ ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በዓለም ዙሪያ “የአካባቢ መራቆጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የዓለም ሙቀት”… እየተባለ በብዙ ስብሰባዎች ብዙ ተወርቷል። እልፍ መግለጫዎች ከግራ ቀኝ እየተቀባበሉ ይስተጋባሉ። የተፈረሙ የስምምነት ውሎችና ሰነዶችም ለቁጥር ያስቸግራሉ።
ኢትዮጵያ የዓለማችን አካል፣ ለዚያውም ከትልልቅ አገሮች መካከል አንዷ ናትና፣ ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያን ይመለከታል። ጉዳይዋ ነው። ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች ኩሩ ታሪካዊ አገርም ናት። ከአገራት ጋር የምትተባበር፣ ትምህርት የምትለዋወጥ ብትሆንም፣ በየአህጉሩና በየአገሩ የሚስተጋቡ አጀንዳዎችን በደረቁ ሊያጎርሷት ሊግቷት ቢሞክሩ፣ እሺ አትልም። በደመነፍስ “ኮፒ” እያደረገች፣ በጭፍን አትከተልም። ተነጂ አትሆንም።
ፍሬና ገለባውን ለይታ፣ የሚሆነውንና የሚበጃትን ለክታ፣ የራሷን መንገድ እየቀየሰች ትጓዛለች። ለአገርና ለሕዝብ፣ ለኑሮና ለታሪክ ትርጉም ባለው መንገድ እያገናዘበች የራሷን ቁምነገር ልብ ትላለች። የራሷን አጀንዳ ትቀርጻለች።
በርካታ አገራት “የአካባቢ መራቆትን እንከላከላለን” በማለት ኢኮኖሚያቸውን ሲያቃውሱ አይተናል። ኢትዮጵያ ግን፣ ኢኮኖሚን የማሳደግና ኑሮን የማሻሻል ራዕይን ጭምር የሚያቅፍ አረንጓዴ አሻራዋን ለዓለም እያሳየች ነው። እንዲህ ዐይነት “ዐቃፊ” የጥበብ ትጋትም ነው፤ ለሌሎች ጥሩ ትምህርትና ልምድ የሚወጣው።
የባለቤትነት መንፈስ መፍጠርስ?
ቀሲስ ታጋይ እንደሚሉት፣ የሃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መልካም አርአያነትን የማሳየት ኀላፊነት አለብን ብለው በጋራ ወስነዋል። በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ችግኞችን በብዛት ለመትከልና ለማልማት ቃል ገብተው፣ በተግባር እያሳዩ እንደሆነም ተነግሯል።
የስሪላንካው አምባሳደር በበኩላቸው፣ አረንጓዴ አሻራ በትልልቅ ቁጥሮች ተዘርዝረው የሚቀርቡ ብዙ ስኬቶችን የማስመዝገቡ ያህል፣ በቁጥር የማይገለጹ ስኬቶችንም አስገኝቷል ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ ውስጥ ብዙ ወጣቶችና ታዳጊ ልጆች ሲሳተፉ አይቻለሁ። ይህም የአዲሱን ትውልድ መንፈስ የሚያነሳሳና የሚያነቃቃ ነው ብለዋል - አምባሳደሩ። አረንጓዴ አሻራን በባለቤትነት ይዞ የሚያሳድግ ትውልድ ተፈጥሯል ማለት ነው።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ባልደረቦቹ ጋር በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባሻገር፣ በባለቤትነት መንፈስ የሚያለሙት ፓርክ ላይም ችግኞችን እየተከልን እንንከባከባለን ሲል ነግሮናል። በባለቤትነት መንፈስ እየሠሩ ያስመዘገቡት ውጤት ታይቶም እንደሽልማት ሌላ የሚለማ ቦታ በአዲስ አበባ መስተዳደር እንደተፈቀደላቸው አሼበል ይገልጻል። በእርግጥ ቦታውን ገና አልተረከቡም። እናም ከመንግሥት የምትፈልጉት ድጋፍ ምን እንደሆነ ስንጠይቀው፣ “እዚህ ችግኝ ትከሉ ብሎ ቦታ እንዲሰጠን ብቻ ነው የምንፈልገው” በማለት መልሶልናል።
አረንጓዴ አሻራ የዚህን ያህል ነው ኢትዮጵያውያንን በሰፊው ማቀፍ የቻለው። ኢትዮጵያውያንም አረንጓዴ አሻራን የራሳቸው አድርገው አቅፈውታል።
አንጋፋው ገጣሚ፣ ተርጓሚና ፀሃፊ ተውኔት ነቢይ መኮንን የፊታችን ሰኞ ይከበራል- ይዘከራል!!
ዓለምን ያልጠገበ መናኝ ልጃገረዶችን ይሰናበታል!
አንዲት ምስኪን አሮጊት በአንድ መንደር ትኖር ነበር፡፡ አንድ ቀን ብዙ ባቄላ አግኝታ ልትቀቅል አሰበች፡፡ ምድጃዋ ላይ እሳት አያይዛ ቶሎ እንዲቀጣጠል የሰምበሌጥ ማገዶ ትጨምር ጀመር፡፡ ባቄላውን ማሰሮ ውስጥ እየከተተች ሳለች፣ አንድ ባቄላ ተፈናጥሮ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ አጠገቡ አንድ ሰንበሌጥ አለ፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ አንድ ከሰል እንደዚሁ ከምድጃው ተፈናጥሮ ተንከባሎ ባቄላውንና ሰንበሌጡ አጠገብ አረፈ፡፡
ሰንበሌጡ፤ “ውድ ጓደኞቼ ከወዴት መጣችሁ?” አለና ጠየቀ- ከሰሉንና ባቄላውን፡፡
ከሰሉ፤ “እኔ ዕድለኛ በመሆኔ ከእሳቱ ተፈናጥሬ ወጣሁ፡፡ በጣም ብዙ ጥረት አድርጌ ነው የወጣሁት፡፡ ዕጣ ፈንታዬ ሞት ነበር፡፡ ይሄኔ አመድ ሆኜ ነበር” አለ፡፡
ባቄላው በተራው፤
“እኔም ቆዳዬ ሳይገሸለጥ ወጥቼ አመለጥኩ፡፡ ሆኖም አሮጊቷ እንሥራዋ ውስጥ ከትታኝ ቢሆን ኖሮ ይሄን እኔም እንደጓደኞቼ ተቀቅዬ ነበር” አለ።
ሰንበሌጡም፤
“እኔስ ከእናንተ የተለየ ሌላ ዕጣ- ፈንታ ይጠብቀኝ ነበር መስሏችኋል?” አለ፡፡ “አሮጊቷ የእኔን ወንድሞችና ጓደኞቼን በሙሉ እሳት ውስጥ ማግዳቸዋለች፡፡ ስልሳውን በአንድ ጊዜ እንደ ጨፈቃ አስራ ለሞት ዳረገቻቸው፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ከእጇ አፈትልኬ እኔ ወደቅሁኝ፡፡”
ከሰል - “እሺ ታዲያ አሁን ምን እናድርግ ትላላችሁ?”
ይሄኔ ባቃላው - “ጎበዝ ሞትን የማምለጥ እድል ካገኘን ዘንድ እንደ ልብ ጓደኛሞች ሁሉ ወደ ሌላ አገር ሄደን ወደፊት ሊመጣብን የሚችለውን መዓት ማምለጥ አለብን”
ሁሉም በዚህ ሀሳብ ተስማሙ፡፡ ወደ ሌላ አገር ለመሄድም መንገድ ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንድ ትንሽ ወንዝ አጠገብ ደረሱ፡፡ ከወንዙ ወዲህ ማዶ ወደ ሌላኛው ዳርቻ ለማቋረጥ ምንም ድልድይ የለም፡፡ ይህን ችግር ለማቃለል ዘዴ ሲያወርዱ ሲያወጡ ሳለ፣ ሰንበሌጡ አንድ ደግ ሀሳብ አቀረበ፡፡ እንዲህ አለ፡-
እንዳውም ሰንበሌጡ ከዳርቻ ዳርቻ ተዘረጋ፡፡ ትዕግስት አልባውንና አሁንም በመቀጣጠል ላይ ያለው ከሰል በድፍረት ሰምበሌጡ ላይ ወጥቶ እየጨፈረና ዳንኪራ እየመታ፣ በአዲስ ድልድይ ላይ መጓዝ ጀመረ፡፡ ሆኖም እሰንበሌጡ ድልድይ መካከል ላይ ሲደርስ፤ ውሃው ገርገጭ ገርገጭ እያለ ሲጮህ ሲሰማ ወደፊት ለመጓዝ ድፍረት አጣ፡፡ ፈራ፡፡ በዚህ መካከል የከሰሉ እሳት የሰንበሌጡን አካል ለብልቦ ሁለት ላይ ከፈለው፡፡ ሰንበሌጢ በሁለት ተከፍሎ ወንዙ ውስጥ ገባ፡፡
እሱን ተከትሎ ከሰሉም ሰጠመ፡፡ የውሃውን ገላ ሲነካም ቸሰስ እያለ ጨሰ፡፡ የመጨረሻ እስትንፋሱም በዚያው ቆመች፡፡
ባቄላው ግን በተፈጥሮው ጠንቃቃ ነበረና ዳርቻው ላይ እንደቆመ ነበር፡፡ |የሆነውን ሲያይ ሳቁን ሊገታው አልቻም፡፡ ሳቁን ለቀቀው፡፡ መሬት ላይ እየተንከባለለ ሳቀ፡፡ ሳቀ…. በመጨረሻ ግን በሳቅ ብዛት ፈነዳና መሬት ላይ ተዘረረ፡፡ ትረፍ ሲለው አንድ መንገደኛ ልብስ ሰፊ ወንዙ ዳር አረፍ ብሎ ነበረና በባቄላው የደረሰውን አይቶ አዘነ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ባቄላውን አንስቶ በጥቁር ክር ቆዳውን ሰፋና አዳነው፡፡ ባቄላው አመሰገነው፡፡ ሆኖም ልብስ -ሰፊው በጥቁር ክር ነበረና የሰፋው እስከዛሬ ድረስ ባቄላዎች አናት ላይ ያኔ ሰውዬው ሲሰፋ የተቋጠረው ክር ጠቁሮ ይታይባቸዋል፡፡ እንደ ጥቁር ጠባሳ መሆኑ ነው፡፡
****
እንደሰንበሌጡ ከብዙ ችግር የዳኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ለሌሎች ሲሉ እንደጧፍ የነደዱና የሚነዱ ብዙ ናቸው፡፡ እንደከሰሉ ከነእሳታቸው በሌሎች መስዋዕትነት የሚደፍሩና የቁርጡ ቀን ሲደርስ ግን በስጋት የሚሞቱ አያሌ ናቸው፡፡ የሎሎችን ሥቃይ እያየ የሚስቅ ወዮለት ቢባል እውነት ነው። እንደ ባቄላው መፈንዳት አለ። ደግነቱ ከመከራ ትረፍ ያለው አትራፊ ያዝለታል፡፡ ሆኖም ጠባሳው ዕድሜ ልኩን ይከተለዋል፡፡ የሁሉም ምሳሌ ባገራችን ነበሩ፣ አሉ፣ ካልተማማርን ወደፊትም ይኖራሉ፡፡
ከስንት መዓትና የደም አበላ የወጡ ጓደኛሞች ካልተሳሰቡ ማን ሊተሳሰብ ይችላል? ስንት የጋራ ባላንጣ ያላቸው ያንድ እናት ልጆች ካልተግባቡና ህብረት ካልፈጠሩ፣ ማን ህበረት ሊኖረው ይችላል? ስንት ረዥም መንገድ የሚጠብቃቸው መንገደኞች ካልተጋገዙና አብረው ካልገፉ መንገዱ መቼ ያልቅላቸዋል?
የትላንትና ቂምን ለዛሬ አሳድሮ ለትኩስ በቀል መዘጋጀት የኖረ በሽታችን ነው። የተሳሰሩት ችግሮች አገራችንን አስረው ወደባሰው መቀመቅ እንድትጓዝ ያደርጓታል፡፡
የሀገራችን ታጋዮች የድርጅት አባላት፣ የፓርቲ አመራሮች፣ በየደረጃው በሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ዜጎች የሃገራችንን የጋራ ስዕል ከማየት ይልቅ በዛሬ ሽርፍራፊ ጉዳዮች ላይ በትናንት የባቄላው ጠባሳ ላይ፣ በነገ ሸውራራና እኔ ብቻ ልኑር ባይ ርእይ ላይ እያተኮሩ አቅማቸውን መበታተናቸው ለአገርና ለሀዝብ የሚገድ ተግባር ላይ አለመረባረባቸው ለውድቀት እየዳረገን መሆኑ ብዙ ጊዜ የታየ ሀቅ ነው፡፡ ዛሬም ገና ያልለየለትና መፍትሄ ያላገኘ ችግር ነው፡፡ በስንቶች መስዋዕትነት የተገኘን ፍሬ ማባከን የተለመደ ሆኗል፡፡ የተፈጠረውን እድል በሰዓቱ ከመጠቀም ይልቅ እገሌ ካለበት ሞቼ እገኛለሁ በሚል ነገ ዛሬ ሲሉ፣ እድን ማጣት ዕጣ - ፈንታችን ሆኗል፡፡ በዚህም አገርን ለተደጋጋሚ ችጋር ህዝብን ለጉስቁልና መዳረጉ ይዘወተራል፡፡ “ውቃቢ አምላክ ሲቀርብ እታጠባለሁ ሲሊ እድፍ አንገት ይደርሳል” የሚባለው መሆኑ ነው፡፡
ነፃነትን፣ ዲሞክራሲን፣ ፍትህን አድሎ የሌለው ምርጫን፣ ዛሬም ይሁን ነገ በምኞትና በፀሎት ለማግኘት አይቻልም፡፡ ሁሉም በየደረጃው የሚጠይቀው መስዋዕትነት አለው፡፡ በየደረጃው የሚፈታተነው ወኔ አለው፡፡ ውጣ ውረዱ ብዙ ነው፡፡ በየጉዳዩ ላይ እስከ መጨረሻ መታገል እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ እያንዳንዱን ጉይ እስከ ፍፃሜው ድረስ አውጠንጥኖ ማወቅ ያሻል፡፡ ስለ ነገ የተሻለ ህይወትና የዓላማ ቁርጠኝነት ከማሰብ ይልቅ ስለ ትላንት ቂምና ቁርሾ የኋሊት ማየት ሰንበሌጡ እያለቀ ከሰሉንና ባቄላው እየበዛ መሄዱን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡ ወደፊት ከመጓዝ ወደ ኋላ መጎተትን ያስወድደና “ዓለምን ያልጠገበ መናኝ ልጃገረዶችን ይሰናበታል” እንደማለት ነው፡፡
“አዕጋሪ ፀሀይ” (የፀሐይ እግሮች) የግጥም መፅሐፍ ለንባብ በቃ
በደራሲና ገጣሚ ሚካኤል አስጨናቂ (ኢ/ር) የተሰናዳው የጸሐይ እግሮች የግጥም መፅሐፍ ለንባብ በቃ። መፅሐፉ በፍቅር በማህበራዊ ጉዳይ፣ በፖለቲካና በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ሀሳቦች የተዳሰሱባቸው 75 ግጥሞችን ያካተተ ነው።
በመፅሐፉ ጀርባ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት ደራሲና ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ ገጣሚና ደራሲ ሰለሞን ሳህለ ትዕዛዙ ና ገጣሚና ደራሲ አሌክስ አብርሃም እንደገለፁት፤ ገጣሚና ደራሲ ወጣት ሚካኤል አስጨናቂ (ኢ/ር) ይህ የግጥም መድብል እንኳን ለግጥም አፍቃሪያን ከግጥም ራቅ ላሉ ሁሉ ግጥም ምን ማለት እንደሆነ ማሳያ ስለመሆኑ ብሎም ገጣሚና ደራሲው ሚካኤል የጎልማሳን ሃሳብ የትልቅ ሰው አስተውሎትን በውጥጡ አጣምሮ የያዘ ወጣት ስለመሆኑና በግጥሞቹ የማይደርስበትና የማይዳስሰው ሀሳብ እንደሌለ እንዲሁም ያልተዳሰሰ የስሜታችን ክፍል እንደሌለ መስክረዋል።
የጸሐይ እግሮች የግጥም ስብስብ መፅሐፍ በ108 ገፅ ተቀንብቦ በ250 ብር ለገበያ ቀርቧል። ደራሲና ገጣሚ ሚካኤል አስጨናቂ (ኢ/ር) ከዚህ ቀደም “ተቤራ” እና “ሸግዬ ሸጊቱ” የተሰኙ ሁለት የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መፅሀፎችን ለንባብ ማብቃቱ አይዘነጋም።