Administrator

Administrator

59.8 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል

 በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት የትምህርት ዘርፉ ዕድገት ከዜሮ በታች እንደሆነ የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 9ኛ መደበኛ ጉባዔ ከየካቲት 4 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፤ በጉባዔው የመጀመሪያ ቀን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለምክር ቤቱ አባላት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል። በዚሁ ሪፖርት ላይ ትኩረት ያደረጉበት ጉዳይ የትምህርት ዘርፍ ነበር።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአማራ ክልል የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አመልክተዋል። በተለይም ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ የዘርፉ የዕድገት ምጣኔ ከዜሮ በታች እንደሆነ አስረድተዋል።
የዕድገቱ ማሽቆልቆል ዋነኛው ምክንያት በክልሉ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አንስቶ በተከታታይ የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አረጋ ከበደ፤ “በዚሁ ችግር ምክንያት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አልቻሉም” ብለዋል። አክለውም፤ “ይህ ሁኔታ የትውልድ ቅብብሎሽን የሚገታ ታላቅ ስብራት ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
“የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የትምህርት ዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ አብራርተዋል፡፡ በዚህም 4 ሺህ 965 የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት ታቅዶ፣ 2 ሺህ 210 ክፍሎች እንደተገነቡ ጠቁመው፤ ከዕቅዱ 44 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ 8 ሺህ 882 ክፍሎች ጥገና እንደተደረገላቸው፣ ከእነዚህም ውስጥ 5 ሺህ 136 የመማሪያ፣ 3 ሺህ 746 የአስተዳደር አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። 38 ሺህ 442 ለመማር ማስተማር ስራ የሚያገለግሉ ጠረጴዛዎችን ለማቅረብ ታቅዶ፣ 19 ሺህ 445 ጠረጴዛዎች ማቅረብ ስለመቻሉ፣ ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 51 በመቶ ለማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
ከመጽሐፍት ሕትመት ጋር በተያያዘ በክልሉ በጀት 4 ሚሊዮን 22 ሺህ 473 መጽሐፍት መታተማቸውንና 3 ሚሊዮን 17 ሺህ 249 ያህሉ መሰራጨታቸውን ጠቁመዋል። በዚህም ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲመዘን፣ 75 በመቶ ያህል መሳካቱን ነው ያስረዱት።
በሌላ በኩል፣ በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን መጽሐፍት ታትመው፣ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ያህሉ መሰራጨታቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር ሲመዘን 61 በመቶ ተሳክቷል ብለዋል። ይሁን እንጂ በወቅታዊው የጸጥታ ችግር ሳቢያ የመጽሐፍት ስርጭቱ ፈተና እንደገጠመው አስታውቀዋል።
“በስርጭት ወቅት የገጠሙ ችግሮችን በመቋቋም የመማሪያ መጽሐፍትን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ማስራጨት ተችሏል” ያሉት አቶ አረጋ ከበደ፤ የታተሙ መጽሐፍት ለስርጭት በሚጓጓዙበት ወቅት የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸው እንዳሉ አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ተግባር የፈጸመው የትኛው ወገን እንደሆነ አልገለጹም፡፡
በአማራ ክልል 10 ሺህ 983 የቅድመ አንደኛ፣ መካከለኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ አውስተው፣ ከእነዚህ ውስጥ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸውን እያከናወኑ ያሉት 7 ሺህ 44 ትምህርት ቤቶች ወይም 67 ነጥብ 7 በመቶው ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል። መደበኛ ስራቸውን ያቋረጡ ትምህርት ቤቶች ብዛት 3 ሺህ 466 እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
“ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ቢታቀድም፣ 2 ሚሊዮን 786 ሺህ 483 (ወይም 40 ነጥብ 2 በመቶ) ብቻ ናቸው እየተማሩ የሚገኙት ያሉት አቶ አረጋ፤ 59 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይህም ከወቅታዊው የጸጥታ ችግር የተያያዘ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ቢናገሩም፣ ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ማብራሪያ ግን በአማራ ክልል “እየተሰራ ነው” ያሉት የሰላም ማስፈን ስራ ስኬታማ መሆኑንና ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር በአብዛኛው የአማራ ክልል ሰላም ማስፈን መቻሉን ነው የጠቆሙት፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ይሳቅ ወልዳይ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ለእስር እንደተዳረጉ ተጠቆመ። ፓርቲው ከመንግሥት የሚደርስበት ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መምጣቱንም ገልጿል።
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ይሳቅ የታሰሩት ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በፓትሮል መኪና በመጡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሲሆን፣ መኖሪያ ቤታቸው እንደተፈተሸም የኢህአፓ ተቀዳሚ ሊቀ መንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ጠዋት ላይ መኖሪያ ቤታቸው ከተፈተሸ በኋላ፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከቀኑ 6:30 ወዳልታወቀ ቦታ “ወስደዋቸዋል” ብለዋል።
እስካሁን አቶ ይስሃቅ የተወሰዱበትን ቦታ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ የገለፁት ሊቀመንበሩ፤ ፓርቲው የታሰሩትን ቦታ እያጣራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአቶ ይሳቅ የእስር መነሻ የፖለቲካ አመለካከታቸው መሆኑንና ከዚህ በፊት ለእስር ተዳርገው እንደነበር በማውሳትም፣ ይሁንና ከተወሰኑ ሰዓታት እስር በኋላ እንደተፈቱ ተናግረዋል። ከእስር ባሻገር፣ ከመንግስት የጸጥታ አካላት የተለያዩ የግድያ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እንደሚደርሳቸውና ይህንንም ሁኔታ ለፓርቲው ጽሕፈት ቤት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
“መንግስት ኢሕአፓ ላይ በጣም ትኩረት እያደረገ ነው። በኦሮሚያ ክልል ብዙ አባሎቻችን ታስረዋል። በሐረር ክልል አንድ የፓርቲያችን አመራር ታስሮ ተፈትቷል።” ያሉት መጋቢ ብሉይ፣ “ኢሕአፓን ከፖለቲካ ዕንቅስቃሴው ለማስቆምና የሕዝብ ድምጽ እንዳይሆን ለማድረግ ነው እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጸሙት።” በማለት አስረድተዋል።
“አሁንም በሰላማዊ ትግል ላይ ጽኑ ዕምነት አለን” የሚሉት መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ “ሕገ መንግስቱ የሚፈቅድልን ከመቶ በላይ የሰላማዊ ትግል ዓይነቶች አሉ” በማለት ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ፓርቲያቸው ቢሞክርም፣ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የእመቃ ዕርምጃ እንደተወሰደና እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች ለወራት ታስረው መቆየታቸውን አብራርተዋል።
ተቀዳሚ ሊቀ መንበሩ፤ “ኢሕአፓን ባሳደዱት ቁጥር እየጠነከረ የሚመጣ ድርጅት ነው። ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግርዋል።

• ፕሬዚዳንት ትራምፕና ፑቲን በሳኡዲ ተገናኝተው ሊወያዩ ነው

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ጦርነቱ ቆሞ በአፋጣኝ ድርድር እንዲጀመር ሁለቱም አገራት መስማማታቸውን አስታወቁ፡፡

ትራምፕ ከሰሞኑ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት የ1 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የስልክ ንግግር፤ ለሦስት አመት ገደማ የዘለቀውን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም፣ በአፋጣኝ ድርድር እንዲጀመር መስማማታቸውን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ዓላማ በቅርቡ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በሳኡዲ አረቢያ ተገናኝተው እንደሚወያዩ የገለጹት ዶናልድ ትራምፕ፤ በመቀጠልም አንዳቸው የሌላኛቸውን ሀገር ለመጎብኘት ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም የሚያስፈልጉ ቅድም ሁኔታዎችን ባይጠቅሱም፤ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፔቴ ሄግዘ፤ የዩክሬን የኔቶ አባልነት ጉዳይ የማይሳካ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት አሸንፈው ዋይት ሃውስ ከገቡ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነትን እንደሚያስቆሙ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡

በሌላ ዜና፤ በሩሲያ ለሦስት ዓመታት ታስሮ የቆየው አሜሪካዊ መምህር ማርክ ፎጌል ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከእስር ተለቆ ለአገሩ አሜሪካ በቅቷል፡፡ ለታጋቹ አሜሪካዊ መምህር ከእስር መፈታት ትራምፕ ከሩሲያው መሪ ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ወሳኝ ነበር ተብሏል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ተፈራዳሪ ዊትኮፍ በዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ፤ "ማርክ ፎጌልን ማስፈታት ወሳኝ ነበር፤ በዚህ ረገድ ሩሲያውያን በጣም፣ በጣም ተባባሪ ነበሩ" ብለዋል፡፡

የፎጌል መለቀቅ የፕሬዚዳንት ትራምፕና ፑቲን ግንኙነት ወደፊት እየጠነከረ የሚሄድ መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት ዋትኮፍ፤ "መልካም ግንኙነት ነበራቸው ብዬ አስባለሁ፤ ይህም መቀጠል አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማርክ ፎጌልን በዋይት ሀውስ ተቀብለው ያነጋገሩ ሲሆን፤ ፎጌል ከሩሲያ እስር ነጻ ያወጡትን ፕሬዚዳንት ትራምፕና ተደራዳሪዎቹን አመስግኗል፡፡

ፎጌል ለጀርባ ህመሙ በህክምና የታዘዘ ማሪዋና ይዞ በመገኘቱ ምክንያት ነበር በሩሲያ ከ2021 ጀምሮ ለእስር የበቃው፡፡ ማርክ ፎጌልን ከእስር በመልቀቋ ሩሲያን እንደሚያደንቁ የተናገሩት ትራምፕ፤ የተደረገውን ድርድር "በጣም ፍትሃዊ" ሲሉ ገልጸውታል፤የስምምነቱን ዝርዝር ባይናገሩም፡፡

አትሌት ፅጌ ድጉማ በፈረንሳይ ሊቪ የዓለም አትሌቲክ የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ ሆነች

በፈረንሳይ ሊቪ የዓለም አትሌቲክ የቤት ውስጥ ውድድር በሴቶች 800 ሜትር አትሌት ፅጌ ድጉማ አሸናፊ ሆናለች፡፡

አትሌቷ 1:59.02 በመግባት ውድደሩን ማሸነፏን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በአብርሃም ገነት የተጻፈው “ሳላዛት” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ፤ ሰሞኑን ገበያ ላይ እንደዋለ ደራሲው ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡

በ500 ብር ለሽያጭ የቀረበው ልብወለድ መጽሐፉ፤ በጃፋርና በሀሁ መጽሐፍ መደብሮች ማግኘት እንደሚቻል ታውቋል፡፡

አብርሃም ገነት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚጽፋቸው ተወዳጅ አጫጭር ልብወለዶቹና ወጎቹም ይታወቃል፡፡

“ሳላዛት” በረዥም ልብወለድ ዘርፍ፣ ለጸሃፊው የበኩር ሥራው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

****
"አለማችን ፕላኔታዊ ውሕደት ያስፈልጋታል"

”--ዓለምን በአንድ ፌደሬሽን ማሰባሰብ ግቡ ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት ለማምጣት ቢሆንም ውጤቱ ግን ከዚህ ያለፈ ነው። ዓለምን በአንድ ፕላኔታዊ ፌደሬሽን ማሰባሰብ ያስፈለገው ጦርነትን ለማስቀረት፣ ሰላምና ፍትሕን ለማስፈን፣ የምድር አየር ንብረት ለሰው ልጅና ለሌሎችም ፍጡራን ተስማሚ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግና ስልጣኔን በተለይም የህዋ ስልጣኔን ለማቀላጠፍ ነው። ስለ ህዋ ስልጣኔ በቀጣዩ ሁለንታዊ መድረክ ስለምናወሳ አሁን በዝርዝር አንሄድበትም። አስተዳደርን በተመለከተ ይህ ፌደሬሽን፣ ዓለምን ጠቅልሎ ይዞ የሚገዛ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። አሁን በፌደሬሽኑ ስር ያሉ ሀገራትን እውነታ በተግባር ማየት ትችላላችሁ። የፌደሬሽኑ ስልጣን እንደ መከላከያ፣ የህዋ ምርምር፣ አየር ንብረትና የውጭ ግንኙነት ባሉ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ነው። እነዚህ ጉዳዮች በቁጥር ውስን ቢሆኑም የምድርንና የሰው ልጅን ዕጣ የሚወስኑ ታላላቅ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ስኬት ማምጣት የሚቻለው በሀገራት ደረጃ በተበጣጠሰ ሁኔታ ሳይሆን እንደ ፕላኔት በአንድ ማዕከል መሥራት ሲቻል ነው። ከዚህ ውጭ ሀገራቱ ራሳቸውን ነው የሚያስተዳድሩት። ዓለም በሙሉ በፌደሬሽኑ ስትካተት ደግሞ የፌደሬሽኑ የውጭ ግንኙነት ስልጣን ፕላኔቷን ወደ መወከል ይሸጋገራል።”

( ከ”ሳላዛት“ የተቀነጨበ)
***

መጽሐፉ፤ በአዲስ አበባ በጃፋር እና ሀሁ መጽሐፍ መደብሮች፣ እንዲሁም በባሕርዳር አዳነ መፅሐፍ መደብርና በሌሎች የክፍለ ሀገር ከተሞች መፅሐፍ መደብሮችም ይገኛል፡፡
በቀጥታ መግዛት ለምትፈልጉ ባሕር ዳር፡- 0910625217 አዲስ አበባ፡- 091 396 0314 ወይም 091 128 0984 ደዉሎ ማግኘት ይቻላል፡፡

” በቴሌ ብር አንድ ትሪሊዮን ብር ዝውውር ተፈጽሟል“

ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት አመት ስድስት ወራት ውስጥ 61 .9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ፣ የተቋሙን የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀምን አስመልክቶ፣ ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫም፣ በበጀት አመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት፣ በቴሌ ብር አማካኝነት አንድ ትሪሊዮን ብር ዝውውር መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡ ወጪ ቆጣቢ የዲጂታል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ 3.5 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት 202 በሚሆኑ አካባቢዎች አዳዲስ የገመድ አልባ አገልግሎቶችን ማስፋት መቻሉን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤በስምንት ከተሞች ላይ የ5ኛ ትውልድ (5ጂ ኔትወርክ) አንዲሁም 67 ከተሞችን የ4ኛ ትውልድ (4ጂ ኔትወርክ) ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎችን ዳግም ወደ አገልግሎት ለማስገባት በተሰራው ስራ 216 አካባቢዎች ሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አብራርተዋል።

ተቋሙ እኒህን ጨምሮ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራትም ባለፉት 6 ወራት 61.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ያስታወቁት ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ43 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በዛሬው ዕለት መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች፡፡

ስብሰባው፤"የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ከስብሰባው አጀንዳዎች መካከል የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ ይገኝበታል።

በዚህም ኢትዮጵያ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና የተመረጠች ሲሆን፤ ለሦስት ዓመታትም የምክር ቤቱ አባል ሆና ታገለግላለች።

በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ዘመናት በቁርጠኝነት የሰራችው ኢትዮጵያ፤ የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ ብሔራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿንና ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ አንጻር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያስገኝላታል ተብሏል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፤ 15 አባል አገራት አሉት።

ለ29ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ተቋም ጠቅላላ ጉባኤ ለቅድመ ስብሰባ አዲስ አበባ የመጡ የቀዳማዊ እመቤቶች አማካሪዎች የአድዋ ድል መታሰቢያንና የብሔራዊ ቤተመንግስትን ጎብኝተዋል።

Wednesday, 12 February 2025 19:37

የነብይ ገፅ

ንክሻ


የነብይ ገፅ

ነቢይ መኮንን!


-1
ትናንት ማታ ግር የሚያሰኝ ነገር አጋጠመኝ ። ሌሊቱን ሁሉ ግር ብሎኝ አደረ።
እግዚአብሔር ይይላትና … ፣ ያቺ ልጅ አካላቴን አተኩሳው አደረች። እንዲችው ስገላበጥ። እሷና እኔ በጥቂት ወይም ምንም አልባሳት እየተረዳን የምንተውንባቸው የተለያዩ ተውኔቶች ስደርስ። በሀሳብ ልምምድ ስናደርግ .......
-2
ትናንት ማታ ቢሮ ሥራ አምሽተናል። ደክሞኝ ነበር። ወደ ቤት ለመግባት መገናኛ የሚወስደኝን ሚኒባስ ታክሲ ከስቴድዮም ያዝኩ። ታክሲው ቢሞላም እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጋ ጥቂት ተሳፋሪዎች እንድንታቀፍ በወያላው መታዘዛችን አልቀረም። ለእኔ እና ከጐኔ ለነበረችው ልጅ የደረሱን ሴትዮ እጅግ ወፍራምና ረዥም በመሆናቸው በልከኛ ሰው እንዲቀየሩልን፤ ይኸ ካልተቻለም እሳቸው ተቀምጠው እኛን ይታቀፉን ዘንድ አመለከትኩ። ለፈገግታ ያሰብኩት ነገር ባይሆንም ተሳፋሪው መሳቁ አልቀረም።
መገናኛ ጫፍ ስደርስ ጣመኔን ለማስታገስ እና አንድ ነጭ ማኪያቶ እየጠጣሁ ከእግሬ ላይ ለአፍታ ልወርድለት በማሰብ እዚያው አካባቢ ካለ ሻይ ቤት ጐራ አልኩ። ቤቱ ሙሉ ነበር። ይንጫጫል። ዙሪያውን የተገጠሙት መስታወቶች ምስሉን እየተቀባበሉ የቤቱን ስፋትና የሕዝቡን ቁጥር አባዝተውታል።
-3
ልታስተናግደኝ የመጣችውን ልጅ አተኩሬ  ዐየኋት።
በሻይ ቤቱ የሥፍራ መታጣት ምክንያት አሁን ግልፅ ሆኖልኛል። ማንም ጐረምሳ (እስከ ጐልማሳ ሊዘልቅ ይችላል) ይኸች ውብ ቀንበጥ ልጅ ከማራኪ ፈገግታዋ ጋር የምታቀርብለትን ቡና አየደጋገመ ከመጨለጥ ሌላ እምብዛም አማራጭ አልተተወለትም።
“ነጭ ማኪያቶ” አልኳት እሷን በማየት እንደ ባለጌ የላሉ ዐይንና ከንፈሮቼን ቀይ ፊቷ ላይ አንጠልጥዬ።
እመኑኝ፤ ለእኔ ብቻ የተሰናዳ ፈገግታ መግባኝ ስታበቃ ወደ ትዕዛዝ ሄደች። ዛሬም ቢሆን ሳይንስ ያልደረሰባቸው ብዙ ምሥጢሮች እና ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌም ያከል፣ የረዥም ቆንጆ ልጅ የሚያምር ፈገግታ በዚያች ቅዕበት፤ በየት በኩል ገብቶ፣ ምን ልዩ ቅመም ጨምሮ የኔን ደም እንዲያ አጣፈጠው? ምን እቶን አንድዶ እንዲያ አፈላው?
- 4 -
አደንቃት ጀመር። ደሞም ይገባታል።
ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ኧረ የምን ሃያ … ፣ ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊትም ይቺን የመሰለች ለጋ ቆንጆ በጠኔ ጥንፍር ትላታለች እንጂ በሰደፍ ቢያስፈራሯት እንኳ ኬክ ቤት ሙባሽር አትሆንም ነበር። አውሮፓና አሜሪካ በስደት ላይ ካልሆነች በቀር።
ይኸው አሁን ይቺ ለልዕልትነት የታጨች የምትመስል ልጅ፣ ሽርጧን በአጭር ታጥቃ ስታበቃ ለእኔ ነጭ ማኪያቶ ለማቅረብ ሽር ጉድ ስትል ትታያለች።
“ጐሽ እሙዬ አበጀሽ” አልኳት በሆዴ ዐይኔን ከረዥም አንገቷ ላይ ሳልነቅል። ግዴለም ጐበዝ በዚህች ቅድስት ሀገራችን ልጆች ዘንድ የሥራ ክቡርነት ...
-5-
ማኪያቶዬ መጣ።
አወይ! የሲኒውን ማስቀመጫ የያዙት ጣቶች! የምሽቱ ሳይንስ ያልደረስበት ሁለተኛው ምሥጢር የዚህች ልጅ ረዣዥም ጣቶች ያለአጥንት አበቃቀል ነው። ቀና ብዬ ሳያት (አሁንም እመኑኝ) ያን ለእኔ ብቻ የተሰናዳ ፈገግታ ደግማ መገበችኝ።
በምሽቱ እጅግ ያስደነገጠኝ ነገር ግን ወዲያው ተከተለ። ልጅቷ ዐይኗን በዐይኔ ጠብቃ ከቆለፈች በኋላ የውብ ከንፈሮቿን ዙሪያ ዳር ድንበር በምላሷ አረጠበች። ይኽ እንደተጠናቀቀም የማርጠብ ሥራ የተከናወነላቸው የታች ከንፈሮቿ በነጫጭ ትክክል ጥርሶቿ እየነካከሰች ታየኝ ጀመር።
-6-
የመረበሼን ጕዳይ አታንሱት! በርግጥ ጐረምሳ ነኝ ። ጥሩም ለብሻለሁ። ሰውነቴም በኘሮግራም በማደርገው የአካል እንቅስቃሴ የዳበረ ነው። ሆኖም ግን ምንም ያህል የደረት  ስፖርት/push up/ ብሠራና ብረት ባነሳ ደረቴ ከመደደሩ በፊት ተፈጥሮ ከለገሰችኝ ሜትር ከኀምሳ ሳንቲም ቁመት አንዲት ጋት ስንኳ መጨመር አልቻልኩም። አፍንጫዬም ትንሽ ስፋቱን የማስቀንስበት መንገድ ቢገኝ የሚጠላ ዓይነት  አይደለም።
“ቀዮ!” ብሎ ሊያቆላምጠኝ የሚችል ጤነኛ ሰው የለም … ዘመናዊ ወጣት ሴት የኔ ቢጤዎች ካልሆኑ በቀር። በትምህርታቸው ጐበዝ የሆኑ መጠነኛ መልክ የታደሉና አዘውትረው የቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት የሚከታተሉ ወይም በመንፈሳዊ ማኅበር የታቀፉ ዓይነት ኮረዳዎች ካልሆኑ በቀር ... ቆነጃጅት ሁለቴ ዞረው የሚያዩት ዓይነት ቁመናና ውበት አልታደልኩም፤ እንግዲህ መቼም … ፣ ሀቅ እንነጋገር ከተባለ።
በእርግጠኝነት ደግሞ ያቺን የመሰለች ቆንጆ ላይ በቅፅበት የፍቅር ረሀብ ፈጥሮ ሲያበቃ ከንፈር የሚያሳኝከ ዓይነት ሸበላ በጭራሽ እንዳልሆንኩ ምዬ መመስከር እችላለሁ።
-7
እንገደና ከሩቅ ዐይን ለ0ይን ተገጣጠምን። አልተሳሳትኩም። አሁንም ከንፈሯን እጅግ ክፋት በሚያሳስብ አኳኋን እየበላች ዐይኗን አፈዘዘችብኝ። ሰው ነኝና ከአዳም ተፈጥሬያለሁና … ልሳሳት ጀምሬያለሁ። የመታጠቂያዬ ክልል ሙቀት አስጊ በሆነ አኳኋን ሲጨምር ይታወቀኛል።
ከልኳ በሁለት ደረጃ ጠብቦ በተሰፋው መለዮ ልብስ ውስጥ የተከተተውን ጥብቅ ቀጥ ያለ ቁመና እንደ ኬሚስትሪ አጠናሁት። ከቶ ፍላጐቷን ልረዳው አልቻልኩም።
“የከተማው ስመ ጥር ኢንቬስተር የወቅቱ አስተናባሪ ነው” የሐሰት ወሬ ነግረዋት ይሆን?
እንጃ!
-8
ገና ልጠራት እጄን ማንቀሳቀስ ስጀምር ካለችበት እየተሳበች መጣች። አሁንም በብልግና አኳኋን ያን የቀድሞ ረብሻዋን ጀመረች።
“ሒሣብ ስንት ነው?” አልኳት።
-9
ከሰጠችኝ መልስ ላይ አንድ ብር ጉርሻ ኒኬሉ ላይ ሳስቀር በመልካም የቋንቋው ዐዋቂ ቅላፄ እና ሆን ተብሎ ጉሮሮ ላይ እንዲሻክር በተደረገ አማላይ ድምፅ ‘Thank you lt is more than enough’ አለችኝ።
-10
ስወጣም ንግሥት ሳባ ከምሽት ጉብኝቱ በኋላ ንጉሥ ሰለሞንን ከመኝታ ክፍሏ በሸኘችበት ቅሬታና ዐተያይ በዐይኗ ሸኘችኝ።
-11
ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ እሷው ነበረች የምናቤ መከፈቻ። ቁርስ እንደ ወትሮው አልተበላልኝም።
ዘወትር ከፍ እንጂ ዝቅ ሲል ታይቶ የማይታወቀውን የምግብ ፍላጐቴን የምትወደው እናቴ፤ “ምን ነክቶሀል? ማታ እንቆቆ ወይም የዱባ ፍሬ አቆይሀለሁ” አለችኝ ያልተነካውን ፍርፍር እያነሳች።
- 12
ቀኑን ሙሉ ሳስባት ዋልኩ። ለሰው የማይነገር ሆነብኝ። መቼም ለምቀርባት የአለቃዬ ፀሐፊ “አንዲት ቆንጆ ልጅ በፍቅሬ ተቸግራለች ብላት” እስከ ምሳ ሰዓት በድፍን መሥሪያ ቤቱ ተዳርሶ በሽርደዳ ልጟዕ ይጨርሱኝ ነበር። ለብቻዬ በሆዴ ይዣት ዋልኩ።
ያቺ ውብ ልጅ እንዴት ከሰው ሁሉ መርጣ አኔን እንደወደደች አያሰብኩ ሆዴ አሁንም አሁንም በሚፍነከነኩ ጥቃቅን ደስተኛ ቢራቢሮዎች እንደተመላ  ሆነ።
ለሥራ ክብርና ፍቅር ያላት የሰውን ውስጣዊ ማንነት እና ትልቅነት በቅፅበት አበጥራ የማወቅ ተሰጥኦ የታደለች ውብ የሐበሻ ወጣት በመሆኗም ጥቂት ጥናት አካሂጄ ለቁም ነገር ላስባት ወሰንኩ።
“እንዴ ‘ከዚህች ልጅ ጋር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ አየተባባሉ ከፍ ያለ ደረጃ ለመድረስ ይቻላል !!” ስል አመንኩ።
ማታ እሄዳለሁ። በቃ ወስኛለሁ! ማታ ሄጀ ሳበቃ ለውዷ ልጅ የፍቅር ጥያቄ ተገቢውን የፍቅር ምላሽ እሰጣለሁ።
- 13
ዛሬም ሥራ አምሽቻለሁ። ተከታታይነት ያለው እና በጥድፊያ መጠናቀቅ ያለበት ዓይነት ሥራ ነው።
እንደወጣሁ ወደ መገናኛ የሚወስደኝን ሚኒባስ ታከሲ ከስቴዲዮም ያዝኩ። ታክሲው ቢሞላም … . እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጋ ጥቂት ተጨማሪ ተሳፋሪዎችን እንድንታቀፍ በወያላው መታዘዛችን አልቀረም። ዛሬ ደግሞ ለእኔ እና ከጎኔ ለተቀመጠው ልጅ የደረሰን ጐረቤት የሆነው ቴዎድሮስ ነበር። “ሃይ ዳዊት ትንሽ ጠጋ በል” አለኝ ቀኝ የጭን አጥንቴን እያደቀቀ።
- 14
መናገኛ ስንደርስ “ .. ቴዲ አንተ ሠፈር ግባ ። እኔ እዚህ ሻይ ቤት ሰዎች ቀጥሬያለሁ።” አልኩት አብሮኝ እንዳይመጣ ከሩቅ እየተከላከልኩ።
“ሀሀሀ …” ዳዊት ሸር የተመላው ሳቅ እየሳቀ “እዚያ ሻይ ቤትማ … እኔም ደረስ እላለሁ። አንዲት ከንፈሯን የምትነክስብኝ ቀይ ቆንጆ ልጅ … ..”
***
(የትሮይ ፈረስ፤ በአሳምነው ባረጋ)

 

Page 6 of 758