Administrator

Administrator

  • ከ2 ዓመት በላይ ወጣቷ የት እንደገባች አልታወቀም
  • ኤጀንሲው የተጣለበት የፈቃድ እገዳ ተግባራዊ አልሆነም

    ከሁለት ዓመት በፊት አል-ኢስማኤል በተባለ የውጪ አገር የግል ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ በኩል በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኮንትራት ውሏ ፀድቆ ወደ ሳውዲ አረቢያ የተላከችው ወጣት ደብዛ መጥፋት እያወዛገበ ነው፡፡ ወጣቷ ላለፉት 27 ወራት የት እንደገባች የሚያመለክት አንዳችም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ ሀያት አሊ መሐመድ በሚል ስም የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ ሳውዲ የተጓዘችው ወጣቷ፤
ከአገር ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦችዋ ጋር አንዳችም ግንኙነት  ባለማድረግዋ ቤተሰቦችዋ የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ሊያውቁ እንዳልቻሉ ይገልፃሉ። ወደ ሳውዲ የላካት ኤጀንሲ ሀያት አሊ ያለችበትን ሁኔታና የት እንደምትገኝ እንዲያሳውቃቸው ቤተሰቦቿ ኤጀንሲውን ቢጠይቁም ኤጀንሲው ምላሽ ባለመስጠቱ ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ኤጀንሲው ወጣቷ ያለችበትን ሁኔታ በአፋጣኝ ተከታትሎ እንዲያሳውቅ ያሳስባል፡፡ ኤጀንሲውም ሳውዲ ድረስ ሄዶ ወጣቷን ለማግኘት ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሀያት አሊ መሐመድ የተባለችው ወጣት በምን ሁኔታና የት እንደምትገኝ ተጣርቶ ምላሽ እንዲሰጠው ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቆንስላዎች ጉዳይ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጥያቄ ያቀርባል፡፡
የቆንስላ ጉዳይ ክትትል ቢሮው በበኩሉ፤ ወጣቷ የምትገኝበት ሁኔታ ተጣርቶ እንዲገለፅለት ሪያድ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ከኤምባሲው ምላሽ ሊገኝ ባለመቻሉ የሃያት ቤተሰቦች እጅግ በከፋ ሃዘንና ሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ  የወጣቷ እህት የኔነሽ አያሌው ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ የወጣቷ ደብዛ መጥፋት በእጅጉ ያሳሰባቸው ቤተሰቦች፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በተደጋጋሚ የአፋልጉን ጥሪ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የጠቆመችው የኔነሽ፤ ኤጀንሲው ተግባሩን በአግባቡ ባለመውጣቱ የሥራ ፈቃዱ እንዲታገድ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም ትዕዛዝ ቢተላለፍበትም ኤጀንሲው አሁንም በስራ ላይ እንደሚገኝ ገልፃለች፡፡ ‹መንግስት ህገ ወጥ ስደትን እቃወማለሁ፤ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደሚፈልጉበት አገር ለስራ መሄድ ይችላሉ› ባለው መሰረት፣ ዕድሉን ተጠቅማ በህጋዊ መንገድ የሄደችው እህቴ፤ ያለችበት ሳይታወቅ ሁለት ዓመት ከሶስት ወራት ማለፉ እጅግ የሚያሳዝንና ስጋት የሚፈጥር ነው ያለችው የኔነሽ፤
“የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተረባርበው እህቴ ያለችበትን ሁኔታ እንዲያሳውቁንና ከስጋት እንዲያወጡን እማፀናለሁ” ብላለች፡፡ ስለጉዳዩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ከመንግስት የቀረበበትን ውንጀላ ተቃውሟል

      በአሸባሪው ቡድን IsIs ታጣቂዎች አሰቃቂ ግድያ የተገፀመባቸው ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ለመዘከርና ሽብርተኝነትን ለማውገዝ ባለፈው ረቡዕ መንግስት በጠራው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ ተቃዋሚ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር የፈጠሩት ግጭት የዓለም አቀፍ ሚዲጠያዎችን ትኩረት ስቧል፡፡በእለቱ በአልጀዚራ በተላለፈ ዘገባ፤ ህዝቡ በከፍተኛ ጩኸትና ቁጣ መንግስትን የሚተቹ መፈክሮችን እያሰማ ባለበት፣ በፀጥታ ሀይሎች የተወሰደው እርምጃ ታይቷል፡፡ ሰልፈኞች ሲደበደቡ የሚያሳዩ የተለያዩ ምስሎችም ተሰራጭቷል፡፡ የኢትዮጵያውያኑን በISIS ታጣቂዎች የመገደል አሰቃቂ ትዕይንት በተደጋጋሚ በምስል አስደግፎ ሲያቀርብ የነበረው ዩሮ ኒውስ፤ ረቡዕ እለት ምሽት ጀምሮ ሰልፉ ሲጀመር የነበረውን ሁኔታና በሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ ፖሊስ ከሰልፈኛው ጋር የተጋጨበትን ትዕይንት አሳይቷል፡፡ በዚህ አጭር የቪዲዮ ትዕይንት፤ መሬት ላይ የወደቁ ወጣት ሴቶች በፖሊስ ሲደበደቡ እንዲሁም አንድን ወጣት በርካታ ፖሊሶች መሬት ላይ በወደቀበት ሲደበድቡ ተስውሏል፡፡ ለረቡዕ እለቱ ሰላማዊ ሰልፍ ትኩረት ሰጥቶ የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ ሰልፈኛው ያሰማውን ተቃውሞና
በመጨረሻም ፖሊስ የሃይል እርምጃ ሲወስድ የሚያሳይ ዘገባ አስተላልፏል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰልፉ ከተከናወነ ከሰአታት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የታሰበው ሰልፍ በስኬት መጠናቀቁን ጠቁመው አንዳንድ ህገ ወጦች በሰልፉ ላይ ረብሻ ማስነሳታቸውንና ከዚህ ጀርባም የሰማያዊ ፓርቲ እጅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ረብሻውን ተከትሎ በ7 የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተናገሩት ነገር የለም፡፡ በእለቱ ሪፖርተራችን በመስቀል አደባባይ ተገኝቶ እንደተመለከተው፤ በተለይ በቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት አካባቢ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች በከፍተኛ ጩኸት መንግስትን የሚያወግዙ መፈክሮች እያሰሙ
ሲቃወሙ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሽብርተኝነትን የሚያወግዘውን ንግግር እያደረጉ ሳለም ከፍተኛ ጩኸትና ተቃውሞ የተስተጋባ ሲሆን አንዳንዶችም ከፖሊስ ጋር ግጭት ፈጥረዋል፡፡ በመንግስት የተጠራውን ሰልፍ ተከትሎ፣ አብዛኞቹ የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ የነበሩ ሲሆን በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች የታክሲ እጥረት ተፈጥሮ እንደነበርም ታውቋል፡፡  ፖሊስ ሰልፉን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን በርካቶች በግርግርና በትርምስ መሃል ወድቀው ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የቀይ መስቀል አምቡላንሶችም ተጎጂዎችን ወደ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲያመላልሱ የነበረ ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ከሰዓት በኋላ እየታከሙ

ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡ ፖሊስ በረብሻው መሃል ያገኛቸውን በርካታ ግለሰቦች በየቦታው በቡድን በቡድን ከሰበሰበ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲያመላልስ እንደነበር የአይን እማኞች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ተቃውሞውን አደራጅቷል ሲል የወነጀለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ረቡዕ ዕለት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ መንግስት የጠራውን ሰልፍ በመደገፍ አባላቱና ደጋፊዎቹ በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ማስተላለፉንና ጥሪውን ተከትሎ እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ላይ የሄዱ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ገና ወደ መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት እየታደኑ መታሰራቸውን አስታውቋል፡፡ ፓርቲው “መንግስታዊ ሽብር የህዝብን ቁጣ ያባብሳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም” በሚል ባወጣው መግለጫው፤ “መንግስት በዜጎች ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ በእጅጉ የሚያሳዝንና በጥብቅ ሊወገዝ የሚገባው ነው” ብሏል፡፡ መንግስት፤ ረብሻውን ያነሳሳው ሰማያዊ ፓርቲ ነው ማለቱን አጥብቆ የተቃወመው ፓርቲው፤ “የመንግስትን ቸልተኝነት በተቃወሙ ሰዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሳያንስ፣ ጉዳዩን ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አዛምዶ ተቃውሟቸውን ማጠልሸት በፍፁም ተቀባይነት የሌለው አፀያፊ ተግባር ነው፤ መንግስት ነኝ ከሚል አካል በፍፁም የማይጠበቅ ስህተት ነው” ብሏል፡፡ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች  የተገኙት እንደማንኛውም ዜጋ በሰልፉ ለመሳተፍ እንደሆነም ፓርቲው አስታውቋል፡፡ በእለቱም 8 ያህል የአመራር አባላቱ ከሰልፉ በፊት እና በኋላ ተደብድበው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቆ፤ በየፖሊስ ጣቢያውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡ሁለት የፓርቲው እጩ የምርጫ ተወዳዳሪዎችም ፖሊስ ጣቢያ ለታሰሩት የፓርቲው አመራሮች እራት ለማድረስና ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡     


አያዩት ግፍ የለ፤
አይሰሙት ጉድ የለ!
ካራ በዕርግብ አንገት፣ ለዕርድ እየሳለ
“ሠይጣን ሰለጠነ”፣ በደም ተኳኳለ!!!
ሌላነት(Otherness) የሚሉት አዲስ ሾተል አለው
ፀረ-ሰው ለመሆን፣ ማልዶ የሞረደው፡፡
“ዕወቁኝ” ነው የሚል፣ ይህ የገዳይ ቢላ
ሌላም ቋንቋ የለው፣ ወትሮም ለሰው- በላ፡፡
(ይሄን በላዔ-ሰብ፣ ማነው ስሙ? አትበሉ
ስሙን መጥራት ለሱ፣ ነውና እኩይ ድሉ፡፡
ይሄን በላዔ - ሰብ፣ ምን ዓለመ? አትበሉ፡፡
ከጀርባው ያለው ኃይል፣ ያው ደሞ እንዳመሉ
እኔ ነኝ ይለናል፣ ሲሞላለት ውሉ!)
*       *     *
አወይ ያገሬ ልጅ!
ወገኔማ ምን ያርግ፣ አደለም በውዱ
ግድ ሆኖበት እንጂ ነጥፎበት ማዕዱ
ቀን ቢወጣ ብሎ፣ ካገር መሰደዱ፡
ነው እንጂ እንዳቅሙ፣ ጎጆ እስከሚሠራ
የጎሸ ቀን በስሎ፣ ጠሎ እስከሚጠራ
መቼ ጥሞ ያቃል፣ የስደት እንጀራ?!
ወዮ የእናቴ ልጅ! ያ ሁሉ መከራ
ጉሮሮውን ሲያስብ አንገቱን ለካራ!!
*      *     *
ያንድ ቀን አይደለም፣ የጨካኝ ጉድ ጓዙ
ቀበቶን ማጥበቅ ነው፣ የቆራጥ ሰው ደርዙ!
የዚህን ሁሉ ግፍ
የመከራ ምዕራፍ
ገፆቹን ለማጠፍ፤
ራስ በራስ ቆመን፣ ጨክነን በዕርጋታ
ችግሩን ከሥሩ፣ የነቀልን ለታ
ሞት እዬዬ ይላል፣ ሆኖ በ‘ኛ ቦታ!!
ከመቀደም መማር፣ ትልቅ ዋጋ እንዳለው
መቼም ቀን ወደፊት፣ አለመቀደም ነው!!
(በስደት ላይ ሳሉ ልጆቻቸው በአረመኔዎች ለተጨፈጨፉባቸው
ወላጆችና በሐዘን ላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ)
                                          (ሚያዚያ 13 ቀን 2007)

በርካታ እናቶች በተለይም አዲስ ወላድ እናቶች የአመጋገብ ስርአታቸው ጡት በማጥባት ግዜ ስለሚኖረው ተፅእኖ ሰፊ እውቀት የላቸውም፡፡ ከወሊድ በኋላ ቀድሞ የምንመገበውን የምግብ አይነት ሙሉ በሙሉ መቀየር አስፈላጊ ባይሆንም የሚከተሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡-
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
የእናት ጡት ወተትን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የእናቲቱ አመጋገብ የተስተካከለ ባይሆን እንኳን ህፃኑ ምንም አይነት ተጨማሪ ምግብ ሳያስፈልገው ማግኘት ያለበትን ንጥረ ነገር ከእናት ጡት ወተት ብቻ የሚያገኝ መሆኑ ነው፡፡
ነገር ግን የእናቲቱ አመጋገብ የተስተካከለ ባልሆነበት ሁኔታም ህፃኑ የሚያስፈልገውን ንጥረ ነገር ያገኛል ማለት እናቲቱ እንዲሁም በህፃኑ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ የእናቲቱ አመጋገብ ያልተስተካከለ ከሆነና ሰውነቷ ማግኘት ያለበትን ንጥረ ነገር በተገቢው መጠን ማግኘት ካልቻለ የምታመነጨው ወተት በብዛትም ሆነ በጥራት ሊቀንስ ይችላል፡፡     
በተመሳሳይ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ምግብ በተገቢው ሰአት ማግኘት ከልቻለ አስቀድሞ ያጠራቀመውን ምግብ መጠቀም ይጀምራል ይህም በሰውነታችን የሚኖረው የምግብ ክምችት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በዚህ ምክንያት የእናቲቱ ጉልበት ስለሚዳከም ለልጇ የሚያስፈልገውን እንክብከቤ ላታደርግ ትችላለች፡፡
ብዙ የሚያጠቡ እናቶች ከሌሎች በተለየ መልኩ ቶሎ ቶሎ የእራብ ስሜት ሊኖረቸው ይችላል ይህም እናቲቱ ከምትመገበው ምግብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወተት ለማመጨት በስራ ላይ የሚውል በመሆኑ ነው፡፡
ልክ እንደ እርግዝና ግዜ ሁሉ ምግብን በሰአቱ በመመገብ እና በመካከሉ ፈሳሽ ወይም ሌሎች ተጨማሪ ምግቦችን በመውሰድ ይህን የእርሀብ ስሜት ለማጥፋት እንዲሁም ጥሩ የሰውነት ጥንከሬ እንዲኖር ለማድረግ ይረዳል፡፡
በሰውነት ውስጥ ያለውን ካሎሪ መጠን መቆጣጠር    
አንዲት የምታጠባ እናት በሰውነቷ ሊኖራት የሚገባው የካሎሪ መጠን ምንያህል ነው? ለሚለው ጥያቄ አንድ መልስ ማግኘት አይችልም፡፡ ነገር ግን ብዙውን ግዜ የሚያጠቡ እናቶች በሰውነታቸው ሊኖር የሚገባው የካሎሪ መጠን ከማያጠቡ እናቶች በ500 ኪሎ ካሎሪ መብለጥት እንዳለበት ይመከራል፡፡ ይህም አንዲት የሚታጠባ እናት በሰውነቷ ሊኖር የሚገባውን የካሎሪ መጠን ከ2000-2500/ ያደርሰዋል ማለት ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አንዲት እናት ከላይ በተጠቀሰው ቁጥር ከመመራት ይልቅ በእለት ተእለት እንቅስቃሴዋ የሚኖራትን የእርሀብ ስሜት ብትከተል ሰውቷ የሚያስፈልገውን ያህል ምግብ ማግኘቱን በቀላሉ መቆጣጠር ትችላለች፡፡
የሰውነት ክብደት፣ የምታደርገው አካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የስልቀጣ ስርአት የሚከናወንበት ፍጥነት እንዲሁም እናቲቱ የምታጠባበት የግዜ ልዩነት ሰውነት የሚያስፈልገውን የካሎሪ መጠን ከሚወስኑ ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የሰውነት ክብደትን ቀስ በቀስ መቀነስ  
አንዳንድ እናቶች ከወሊድ በኋላ የሚኖርን የሰውነት ክብደት በአጭር ግዜ ውስጥ መቀነስ ሲችሉ አንዳንዶች ላይ ግን ይህ ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር የሰውነት ክብደት እረዘም ላለ ግዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህም በእናቲቱ የሰውነት ሁኔታ፣ የምግብ ምርጫ፣ በምታደርገው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሁም የስልቀጣ ስርአቱ እንደሚከናወንበት ፍጥነት ይወሰናል፡፡
የሚከተሉት ነጥቦች አንዲት የምታጠባ እናት ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖራት ለማድረግ ይረዳሉ፡-
የሰውነት ክብደትሽን ቀስ በቀስ መቀነስ (ወደ ቀደመው የሰውነት አቋምሽ  ለመመለስ ቢያንስ ከአመት ያላነሰ ግዜ መውሰድ)
ከወሊድ በኋላ በሚኖሩት ሁለት ወራት ውስጥ ክብደት ለመቀነስ በሚል ቀደም ሲል ከምትመገቢው መጠን አለመቀነስ  
ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ከፍተኛ የካሎሪ መጠን ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ምግቦች የሚመነጨውን ወተት መጠን እንዲቀንስ የማድረግ ባህሪ አላቸው፡፡
በአጠቃላይ ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ክብደት ለመቀነስ በሚል የምግብ መጠን መቀነስ ወይም አመጋገብ ላይ ለውጥ ማድረግ አይመከርም፡፡ ነገርግን የሰውነት ክብደት ከመጠን ያለፈ ከሆነ በቅድሚያ ሀኪም ማማከር ያስፈልጋል
በሰውነትሽ ያለው ፈሳሽ በቂ መሆኑን ማረጋገጥ (አንዳንድ ምግቦች በሰውነታችን ያለው ፈሳሽ መጠን እንዲቀንስ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡)
በዚህ ወቅት የሚኖር ከፍተኛ የሆነ የካሎሪ መጠን መቀነስ በሚመነጨው ወተት ብዛትም ሆነ ጥራት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ስለሚኖር በተቻለ መጠን አመጋገብ ላይ ገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ጤናማ እና የተስተካከለ አመጋገብን መከተል
የምታጠባ እናት የምትመገበውን ምግብ አይነት በማብዛት እንዲሁም በማመጣጠን ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲኖራት ማድረግ ትችላለች፡፡ ፕሮቲን፣ ቅባት እንዲሁም ሀይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን አመጣጥኖ መመገብም እረዥም ሰአታትን ካለምግብ መቆየት እና ሰውነት የሚፈልገውን ንጥረ ነገር ማግኘት ይቻላል፡፡
የምትመገበው ምግብ ሁሉንም የምግብ አይነቶች ያካተተ ማድረግ ሰውነቷ እንዲሁም የምታጠባው ህፃን የሚያስፈልገውን ቫይታሚን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን እንዲያገኝ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የምትመገበው ምግብ በውስጡ በሚይዘው ንጥረነገርም ሆነ በአይነቱ የተለያየ መሆን ይኖርበታል፡፡
ቅባት ያላቸው ምግቦችን መመገብ
የቅባት መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች የህፃኑ የአተነፋፈስ ስርአት ላይ የሚያስከትሉት ችግር እንዳለ ሆኖ እናቲቱም በልብ ህመም ወይም ሌሎች በሰውነታችን ያለው የኮሌስትሮል መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ የጤና እክሎች ሊያጋልጣት ይችላል፡፡ ስለዚህ አንዲት የምታጠባ እናት አነስተኛ የቅባት መጠን ያላቸውን ምግቦች በመመገብ ሰውነቷ ወተት ለማመንጨት የሚያስፈልጉትን ንጥረነገሮች ማሟላት ትችላለች፡፡ እንደ የወይራ ዘይት፣ አሳ፣ አቮካዶ፣ ኦቾሎኒ የመሳሰሉት ለዚህ ተጠቃሽ የሚሆኑ የምግብ አይቶች ናቸው፡፡
የጡት ወተት እንዳይመረዝ ጥንቃቄ ማድረግ
ማንኛዋም ጡት የምታጠባ እናት የጡት ጫፍ አካባቢ የፀዳ መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም የምትመገበው ምግብ ወተቱን በሌሎች አላስፈላጊ ኬሚካሎች እንዳይበከል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባታል፡፡
የሚከተሉት ነጥቦች የጡት ወተት በሌሎች አላስፈላጊ ኬሚካሎች እንዳይበከል ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳሉ፡-
የተለያዩ የምግብ አይነቶችን መመገብ (የምታጠባ እናት አንድን የምግብ አይነት አዘውትራ የምትመገብ ከሆነና ያ ምግብ በውስጡ አላስፈላጊ ኬሚካሎችን የያዘ ከሆነ የጡት ወተት የመበከል እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡)
የትኞቹ ምግቦች ለጡት ወተት መበከል ምክንያት እንደሆኑ መለየት
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምግቦችን በሚገባ አጥቦ መመገብ
አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች ምግቦችን በትኩስነታቸው መመገብ
የመጠጥ ውሀን አፍልቶ መጠቀም ወይም የተጣራ ውሀን መጠጣት  
የአልኮል መጠጦችን መቀነስ
የምታጠባ እናት የምትወስደውን የአልኮል መጠን መቀነስ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እናቲቱ የምትወስደው አልኮል በቀጥታ ወደ ጡት ስለሚሄድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በህፃኑ ጤንነት ላይ የሚያስከትለው ተፅኖ ይኖራል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እናቲቱ የአልኮል መጠጥ ከወሰደች በኋላ ባሉት አራት ሰአታት ውስጥ የምታጠባ ከሆነ ወደ ህፃኑ የሚደርሰው ወተት በውስጡ አልኮል የያዘ ነው፡፡ ይህም ህፃኑ ነጭናጫ እና እንቅልፍ አልባ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል፡፡
አልኮሉ ከሰውነቷ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ሁለት ወይም ሶስት ሰአታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ እንደወሰደችው የአልኮል መጠን እና አይነት ይለያያል ስለዚህ አንዲት እናት አልኮል ከመውሰዷ በፊት ለቀጣዩ ሁለት ወይም ሶስት ሰአታት ማጥባት አይኖርባትም፡፡      
ብዙ ውሀ መጠጣት እና የአነቃቂ ንጥረነገሮችን ፍጆታ መቀነስ
ጡት የምታጠባ እናት በቀን ወደ አስራስድስት ብርጭቆ ፈሳሽ ያስፈልጋታል፡፡ ይህም ከምትመገበው ምግብ የምታገኘውን ፈሳሽ የሚጨምር ሲሆን በተለያየ ግዜ የሚኖራትን የውሀ ጥም ተከትሎ መጠጣት የሰውነቷን የውሀ ፍላጎት ለማርካት አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ሽንት ንፁህ እና ፈዛዛ ቢጫ ቀለም ካለው በሰውነቷ በቂ የውሀ ክምችት መኖሩን አመላካች በመሆኑ በሰውነቷ ያለው ፈሳሽ  በቂ መሆኑን በዚህ መከታተል ትችላለች፡፡
በተቃራኒው የህክምና ባለሙያዎች ጡት የምታጠባ እናት በቀን ውስጥ የምትወስደው የአነቃቂ መጠጥ እና ምግቦች ፍጆታ ከ300/ሚሊግራም መብለጥ እንደሌለበት ይመክራሉ፡፡ ይህም እንደ ቸኮሌት፣ ሻይ፣ ቡና እንዲሁም አንዳንድ የለስላሳ መጠጦችን ይጨምራል፡፡ 

Tuesday, 21 April 2015 08:19

ድብርት

እንዳለብዎ ይጠርጥሩ
   የተስፋ መቁረጥ ስሜት
እረፍት ማጣት
የመዝናናት ፍላጎት መቀነስ
ከጓደኛ ወይም ከቤተሰብ መራቅ
የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም በተቃራኒው አብዝቶ መመገብ
በቀላሉ የማይታገስ የራስ ምታት ስሜት
የእንቅልፍ ማጣት አሊያም የመደበት ስሜት
የስራ ፍላጎት ማጣት
እኔ ጠቃሚ አይደለሁም ብሎ ማሰብ
የማስታወስ ችግር
ካለብዎ ድብርት እንዳለብዎ ይጠርጥሩና ሃኪምዎን ያማክሩ፡፡ በወቅቱ ያልታወቀና ህክምና ያላገኘ የድብርት በሽታ ለአህምሮ ህመም የሚዳርግዎ ከመሆኑም በላይ ራስን የማጥፋት ስሜት እንዲያድርብዎ በማድረግ ለከፋ አደጋና ጉዳት ሊዳርግዎ ይችላል፡፡   

Tuesday, 21 April 2015 08:14

የፖለቲካ ጥግ

የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች 5ቱ ውድ ጀቶች

የሞሮኮ ንጉስ አውሮፕላን (ቦይንግ 747)
የሞሮኮው ንጉስ በምቾትና በድልዎት መብረር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ። የሚበሩት የላቀ ምቾትና ውበት እንዳለው በሚነገርለት ቦይንግ 747 ሲሆን የተገዛው በ450 ሚ. ዶላር ነው፡፡ አውሮፕላኑ ባለ ሁለት ፎቅ ነው - ዋናውና የላይኛው ፎቅ፡፡ በዋናው ፎቅ ላይ የስብሰባ ክፍሎች፣ የግል ሲኒማ አዳራሽና ሰፊ የመጫወቻ ስፍራ ይገኛል፡፡ በላይኛው ፎቅ ላይ ደግሞ የፑል መጫወቻዎችና 5 የግል መኝታዎች አሉት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ምርጡ የፕሬዚዳንት  ጀት ነው- የሞሮኮው መሪ ቦይንግ 747፡፡
የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ጀት (ቦይንግ 767)
የአወዛጋቢው መሪ የሮበርት ሙጋቤ የግል አውሮፕላን፣ ከአፍሪካ ምርጥ የፕሬዚዳንት ጀቶች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ አያስገርምም፡፡ ምንም እንኳን ዚምባቡዌ በ10ሩ የአፍሪካ ሃብታም አገራት ዝርዝር ውስጥ ባትገኝም  የፕሬዚዳንትዋ የግል ጀት ግን በአፍሪካ ምድር እጅግ ውድ ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ አውሮፕላኑ የዚምባቡዌ ግብር ከፋይ ዜጎችን 400 ሚ. የዚምባቡዌ ዶላር አላየሁም ብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ አገሪቱ 360 ሚ. ዶላር ያህል እንደምንም የከፈለች ሲሆን የ40ሚ. ዶላር እዳ ግን ይቀርባታል። የአውሮፕላኑ ከፍተኛ ፍጥነት 858 ኪ.ሜ በሰዓት ሲሆን ይሄም ከዓለማችን ፈጣን ጀቶች ተርታ ያሰልፈዋል፡፡ ምቾትና ውበት ለመፍጠር ታልሞ የተሰራው ውስጣዊ ክፍሉም ለፕሬዚዳንታዊ ቤተሰቦች ተስማሚ ያደርገዋል ተብሏል፡፡  
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት አውሮፕላን (ቦይንግ 737)
እዩኝ እዩኝ የሚወዱት የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ፣ በቅርቡ ከሥልጣን ከመውረዳቸው በፊት Eagle One ተብሎ በሚጠራ ቅንጡ አውሮፕላን ሲበሩ ነው የኖሩት፡፡ ቦይንግ 737 የናይጄሪያ ግብር ከፋዮችን 390 ሚ. ዶላር ፈጅቷል፡፡ አውሮፕላኑ ፕሬዚዳንቱ በአየር ላይ ሲሆኑ ደህንነታቸውን  የሚያረጋግጡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች  እንደተገጠመለት ኤርባስ አስታውቋል፡፡  
የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አውሮፕላን (A340-500)
የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት A340-500 የተሰኘውን  ባለ አራት ሞተሮች ግዙፍ የግል ጀት ነው የሚጠቀሙት፡፡ እንዲህ ያለው አውሮፕላን ለወትሮው 150 መንገደኞችን የሚያሳፍር ሲሆን ይኼኛው ለፕሬዚዳንቱ ምቾትና ቅንጦት ታልሞ የተሰራ ነው፡፡ የግል መኝታ ክፍል እንዲሁም ሁሉ ነገር የተሟላለት ሻወር አለው፡፡ A-340 አንዴም እንኳን ሳይቆም እስከ 14 ሰዓታት ድረስ በአየር ላይ መብረር ይችላል፡፡
የሊቢያ ፕሬዚዳንት ጀት (A-340)
የሊቢያ ፕሬዚዳንት ኦፊሴላዊ አውሮፕላን በአብዛኛው የሚታወቀው Afrigiyah One በሚል ስሙ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ምቾትና ውበት የጎላበት ሲሆን ድሎት ያላቸው ክፍሎች፣ መኝታ ቤት፣ ሻወሮች፣ ዲቪዲ ማጫወቻዎችና የግል ወጥ ቤት አለው፡፡ ይሄም ትሪፖሊ ላይ ድንገተኛ ችግር ቢፈጠር ፕሬዚዳንቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ ለበርካታ ወራት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል፡፡ አራት ሞተሮች ያሉት ይሄው A-340 ጄት፤ 411 ሚ. ዶላር እንደፈጀ ይገመታል፡፡ ውስጡም የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት በሆኑ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች የተደራጀ ነው  ተብሏል፡፡
(ምንጭ፡ Africa Cradle ድረ ገጽ፤2015)

Tuesday, 21 April 2015 08:13

የፍቅር ጥግ (ስለ ትዳር)

ብልጥ ስለነበርኩ፣ እኔ ለራሴ ላደርገው የማልችለውን ነገር የሚያደርግልኝን ሰው አገባሁ፡፡
ሮብ ሎዌ
ፍቅር የያዘው ወንድ እስኪያገባ ድረስ ጎደሎ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አበቃለት፡፡
Zsa Zsa Gabor
ባገቡ ወንዶች የተሰሩ ብዙ ታላላቅ ፈጠራዎችን መጥቀስ የምትችሉ አይመስለኝም፡፡
ኒኮላስ ቴስላ
ከእነአካቴው አግብቼ አላውቅም፤ ሰዎች ችግር ያለብኝ እንዳይመስላቸው ግን ፈትቼ ነው እላቸዋለሁ፡፡
ኡላይኔ ቡስለር
አገባለሁ፤ ሚስት ግን አይኖረኝም፡፡ ጋብቻ የምመሰርተው ከላጤ ህይወት ጋር  ነው፡፡
ቻርልስ ቡኮውስኪ
በማግባቴ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ በቃላት መግለፅ እንኳ አልችልም፡፡
ማይክ ቢርቢግሊያ
ያገባሁት በጣም ፈጥኜና በጣም ወጣት ሳለሁ ነው፡፡
ኒኮል ኪድማን
ውሸት መናገር ለልጅ ጥፋት ነው፤ ለአፍቃሪ ጥበብ ነው፤ ለወንደላጤ ስኬት ነው፤ ላገባ ወንድ ሁለተኛ ተፈጥሮው ነው፡፡
ሔለን ሮውላንድ
ለማግባት የሚሹ ሁሉ ከጋብቻቸው በፊት ለወራት ያህል የምክር አገልግሎት ባለሙያ ጋ መሄድ አለባቸው፡፡ ይሄን ማድረግ ወንዶቹን ከብዙ የገንዘብ ኪሳራ፣ ሴቶቹን ከብዙ የልብ ስብራት ያድናቸዋል፡፡
ጄምስ ብሮሊን
ያገባሁትም የፈታሁትም በ23 ዓመቴ ነው፡፡
ሄለን ፊሸር
እውነተኛ ደስተኞች ያገቡ ሴቶችና ላጤ ወንዶች ብቻ ናቸው፡፡
ኤች.ኤል.ሜንኬን
በየዕለቱ ቆንጆ መሆኔን ከሚነግረኝ ሰው ጋር ትዳር በመመስረቴ ሲበዛ ዕድለኛ ነኝ፡፡
ዴብራ ዊንገር

Tuesday, 21 April 2015 07:55

የሰዓሊያን ጥግ

ብሔራዊ ጋለሪ እሳት ቢነሳ የትኛውን ስዕል ነው የማድነው? በሩ አቅራቢያ ያለውን ነዋ!
ጆርጅ በርናርድ ሾው
የራስን ዓለም መፍጠር ድፍረት ይጠይቃል፡፡
ጆርጂያ ኦ‘ኬፌ
ምንም ነገር ማስመሰል የማይፈልጉ ምንም አይፈጥሩም፡፡
ሳልቫዶር ዳሊ
ሰዓሊ መሆን በህይወት ማመን ነው፡፡
ሔነሪ ሙር
ህልሞችን ወይም ቅዠቶችን ፈፅሞ አልስልም፡፡ የምስለው የራሴን እውነታ ነው።
ፍሪዳ ካህሎ
ቀለም የቀን ሙሉ ልክፍቴ፣ ደስታዬና ስቃዬ ነው፡፡
ክላውድ ሞኔት
ተፈጥሮ ለዓይን የሚታየው ብቻ አይደለም .. የነፍስንም ውስጣዊ ምስሎች ይጨምራል፡፡
ኢድቫርድ ሙንሽ
ስዕል የማይናገር ግጥም ነው፤ ግጥም የሚናገር ስዕል ነው፡፡
ፕሊታርች
ሁሉም ነገር የየራሱ ውበት አለው፤ ሁሉም ሰው ግን አያየውም፡፡
አንዲ ዋርሆል
የእውነታ ዓለም የራሱ ገደብ አለው፤ የምናብ ዓለም ገደብ የለሽ ነው፡፡
ዣን ዣክ ሩሶ
ሰው የሚስለው በአዕምሮው እንጂ በእጁ አይደለም፡፡
ማይክል አንጀሎ
ህይወት፤ ያለማጥፊያ (ላጲስ) የመሳል ጥበብ ነው፡፡
ጆን ደብሊው. ጋርድነር
ስለ ስዕል አልማለሁ፤ ከዚያም ህልሜን እስላለሁ፡፡
ቫን ጎግ
ስዕል የተፈጥሮ የልጅ ልጅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ዝምድና አለው፡፡
ሬምብራንድት
ስዕል የዕለት ማስታወሻ የመመዝገቢያ ሌላ መንገድ ነው፡፡
ፓብሎ ፒካሶ
ስዕል ህይወቴን ሙሉ አድርጎልኛል፡፡
ፍሪዳ ካህሎ

Monday, 20 April 2015 15:46

የየአገሩ አባባል

 በፀደይ ወቅት እናት መሬት እርጉዝ ናትና በቀስታ ተራመድ፡፡
ሰው ከተፈጥሮ ሲርቅ ልቡ ይደነድናል፡፡
ትንሿ አይጥ እንኳን የራሷ ንዴት አላት፡፡
የመጀመሪያው መምህራችን የራሳችን ልብ ነው፡፡
የሚንጫጩ ወፎች ጎጆ አይሰሩም፡፡
ሞክሮ መውደቅ ስንፍና አይደለም፡፡
ፍየል እንደሚሰጥህ ከገመትክ ግመል ጠይቅ።
በሰው አህያ ጉዞ አትጀምርም፡፡
ዳንስ የማያውቅን ዛፍ ነፋስ ያስተምረዋል፡፡
የማይናገር ሰውና የማይጮህ ውሻን ተጠንቀቅ፡፡
ጦጣ የምትሞት ዕለት ዛፎች ሁሉ ያንሸራትታሉ፡፡
እንቁላል ሻጭ ገበያ ውስጥ ጠብ አያነሳም፡፡
አላርፍ ያለ እግር የእባብ ጉድጓድ ውስጥ ዘው ይላል፡፡
ዝናብ በአንድ ጣራ ላይ ብቻ አይዘንብም፡፡
ጦርነት ዓይን የለውም፡፡
በአንበሳ የሚመራ የበግ ሰራዊት፣ በበግ የሚመራ የአንበሳ ሰራዊትን ማሸነፍ ይችላል።
የልመና ውሃ ጥም አያረካም፡፡

Monday, 20 April 2015 15:37

የፀሐፍት ጥግ (ስለ ሞት)

ሞት ትልቁ የሰው ልጅ በረከት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ሶቅራጠስ
ሞት አንድ ራቅ ያለ የውሃ ዳርቻ ላይ ማረፍ ነው፡፡
ጆን ድራይድን
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ሰው ሲሞት ከመፅሃፍ ውስጥ አንድ ምዕራፍ ተገንጥሎ አይደለም የሚወጣው፤ ወደተሻለ ቋንቋ ነው የሚተረጎመው፡፡
ጆን ዶኔ
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ሞት ሁሌም ስጋን የሚከተል ጥላ ነው፡፡
የእንግሊዛውያን ምሳሌያዊ አባባል
ሞት ልብህን አያስደነግጠውም፤ ሁልጊዜም ለመሄድ ዝግጁ ነውና፡፡
ዣን ደ ላ ፎንቴን
(ፈረንሳዊ ገጣሚ)
ብዙ ሰዎች በ25 ዓመታቸው ቢሞቱም እስከ 75 ዓመታቸው አይቀበሩም፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን
(አሜሪካዊ ፖለቲከኛ፣ ሳይንቲስትና ፈላስፋ)
ሞት ብልህ ሰውን መክፈል የሚገባን ዕዳ መሆኑን እወቁ፡፡
ዩሪፒዴስ
(ግሪካዊ ገጣሚ)
መሞትን አልፈራም፤ ሲከሰት መገኘት ብቻ ነው የማልፈልገው፡፡
ውዲ አለን
(አሜሪካዊ ዳይሬክተር፣ ተዋናይና ኮሜዲያን)
እንደመወለድ ሁሉ መሞትም ተፈጥሮአዊ ነው፡፡
ፍራንሲስ ቤከን
(እንግሊዛዊ ፖለቲከኛና ፈላስፋ)
አንድ ሰው ኮርቶ መኖር ሳይችል ሲቀር ኮርቶ መሞት አለበት፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
(ጀርመናዊ ፈላስፋና ፀሐፊ)
መቼ እንደሚሞት የማያውቅ ሰው፣ እንዴት እንደሚኖር አያውቅም፡፡
ጆን ሩስኪን
(እንግሊዛዊ የጥበብ ሃያሲ)