Administrator

Administrator

         ገዳሙ ጨርሶ ሳይጠፋ ጉዳያቸው በሲኖዶሱ እንዲታይ መናንያኑ ጠይቀዋል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ አንድነት ገዳም ተፈትቶ፣ መናንያኑና መነኰሳቱ መበተናቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡ ጥንታዊውን ገዳም ለመፈታት፣ ማኅበረ መነኰሳቱንም ለመበተን ያበቃቸው በአካባቢ ተወላጅነት የገዳሙን መሬት በተለያዩ ጊዜያት ተቆጣጥረው ለግላቸው ይጠቀሙ ከነበሩ ግለሰቦች ጋር ተፈጥሮ የቆየውና በተለያዩ ምክንያቶች እየተካረረ የመጣው አለመግባባት መኾኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ በኅዳር ወር 2006 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ገዳሙን ለቀው የወጡት በቁጥር ከ50 - 80 የሚገመቱ መነኰሳት፣ መነኰሳዪያትና መናንያን ከተለያዩ አህጉረ ስብከትና ክልሎች የተሰባሰቡ ሲኾኑ በሀገረ ስብከቱ ውሳኔ ከአስተዳዳሪነት የተነሡትን አበምኔቱን መ/ር አባ ተክለ ብርሃን ሰሎሞንን ጨምሮ ከፊሎቹ በአሁኑ ወቅት በደነባ በኣታ ለማርያም ገዳም ተጠልለው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የወረዳው መንግሥታዊ አስተዳደር፣ ከእነዋሪና ደነባ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ገዳማውያኑንና ግለሰቦቹን በተለያየ ጊዜ በማገናኘት ለአለመግባባቱ የመፍትሔ ሐሳብ ሲሰጡና ውሳኔ ሲያሳልፉ እንደቆዩ ያስታወሱት መነኰሳቱ፤ ‹‹ተሰዳጅና መጤ›› ከሚል በቀር ግለሰቦቹ የሚያቀርቡባቸው ክሦች መሠረተ ቢስ እንደኾኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ የገዳሙን ሥርዐተ ማኅበር በመጣስ የመሬት ይዞታውን፣ ቅርሱንና የልማት ቦታውን ለመከፋፈል የሚሹ ግለሰቦች በሥነ ምግባር ጉድለት ርምጃ ከተወሰደባቸው የስም መናንያን ጋራ በማበር ያቀረቡትን አቤቱታ ብቻ በመቀበል በፓትርያርክ የሚሾሙት አበምኔት በሀ/ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ከሓላፊነት መነሣታቸውን ያስረዱት ማኅበረ መነኰሳቱ፣ አንዳንድ የሀ/ስብከቱን ሓላፊዎች በስም በመጥቀስ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የገዳሙን መሬት ይዘው ከገዳማውያኑ ጋራ ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩትን የአካባቢውን አርሶ አደሮች ትክ መሬት እንዲያገኙና ለንብረታቸውም ካሳ እንዲሰጣቸው በማድረግና ጣልቃ ገብነትን በመከላከል የገዳሙን ይዞታና ሥርዐተ ማኅበሩን ያስከበሩትን፤ በግብርናና በሽመና ሥራዎች፣ በሙዓለ ሕፃናት፣ በኪራይ ቤቶች ግንባታ የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት ልመናን ያስቀሩትን አበምኔት አላግባብ ከሓላፊነት ማንሣት÷ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ኤፍሬም ስለ አበምኔቱ የአስተዳደርና ትምህርት ብቃት እንዲሁም ልማታዊነት ሲሰጡ የቆዩትን ምስክርነት የሚያስተባብልና የገዳሙን መተዳደርያ ደንብ የሚጥስ ከመኾኑም በላይ በሀ/ስብከቱ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር አስከፊ መገለጫ ነው ብለዋል ማኅበረ መነኰሳቱ፡፡

ከገዳማቸው የተፈናቀሉት ማኅበረ መነኰሳቱ ሥርዐተ ማኅበራቸውን ጠብቀው በገዳሙ የጀመሩትን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎት ለመቀጠል እንዲችሉ፤ የገዳሙ ቅርሶች፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲጠበቁ፣ በገዳሙ ያለጧሪ የቀሩት ድኩማን አረጋውያን ደኅንነትም እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የደብረ ብሥራት ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር በኾኑት አቡነ ዜና ማርቆስ የተመሠረተ የዐሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገዳም መኾኑን የገዳሙ ታሪክ ይገልጻል። ገዳምነቱን ሳይለቅ እስከ 8000 መናንያንን እያስተዳደረ በሥርዐተ ማኅበር በቆየው ገዳም፣ ሰበካ ጉባኤ በማቋቋም ወደ ደብርነት እንዲቀየርና በቃለ ዐዋዲ እንዲመራ ለማድረግ ተሞክሮ እንደነበር የገለጹት የዜናው ምንጮች÷ ሲኖዶሱ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገዳማት አስተዳደር መምሪያና የቅርስ ጥበቃ የሚመለከታቸው አካላት ኹሉ ከጻድቁ የእጅና የመጾር መስቀሎች ጀምሮ በርካታ ቅርሶች የሚገኙበትን የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሥርዐተ ምንኵስናና የትምህርት ማዕከል ጨርሶ ሳይጠፋ መታደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

በቅርቡ የተቋቋመው “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” ከትናንት በስቲያ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ የማህበሩን የመተዳደሪያ ደንብ ያፀደቀ ሲሆን አመራሮቹንና የስራ አስፈጻሚ አካላትንም መርጧል፡፡ ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ሊቀመንበር፣ ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጐስ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም ጋዜጠኛ ነብዩ ሃይሉ ዋና ፀሃፊ በመሆን የተመረጡ ሲሆን ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አፈ-ጉባኤ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ምክትል አፈ-ጉባኤ እንዲሁም ጋዜጠኛ ብሩክ ከበደ የአፈ-ጉባኤ ፀሃፊ ሆነው እንደተመረጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ የተመረጡት አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ማህበሩ ሙያተኛውን ብቻ ማዕከል አድርጐ በመንቀሳቀስ የአባላቱን መብት እንደሚያስከብር፣የአባላቱን ሙያዊ ክህሎት በተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚያዳብርና ሃሣብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተሟላ መልኩ ለማስከበር በትጋት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ አዲሱን የጋዜጠኞች ማህበር ማቋቋም ያስፈለገው በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የጋዜጠኞች ማህበራት የሙያተኛውን መብት በቅጡ ማስከበር ባለመቻላቸው ነው መባሉ ይታወሳል፡፡

አንድ ኪሎ ጤፍ በአውሮፓ ከ200 ብር በላይ ይቸበቸባል
የአሜሪካ አውሮፓና፣ እስራኤል ገበሬዎች ጤፍ እያመረቱ ነው
ከጤፍ ተፈላጊነት የኢትዮጵያ ገበሬዎች መጠቀም አለባቸው ተባለ “ጤፍ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሱስ ነው” ትላለች - የ”ዘ ጋርዲያን” ዘጋቢዋ ኤሊሳ ጆብሰን፤ ባለፈው ሳምንት ለንባብ ባበቃችው ዘገባ ላይ፡፡ በአገሪቱ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ጤፍ እንደሚያመርቱና ከአገሪቱ የእርሻ መሬት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነውም በጤፍ እንደሚሸፈን ትገልጻለች፡፡ በአገሪቱ ለምግብነት ከሚውሉ የሰብል አይነቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝና እንጀራም ብሄራዊ ምግብ እስከመሆን መድረሱን በዘገባዋ ጠቁማለች፡፡ ጤፍ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋል አልፎ በእንጀራ መልክ ባህር ተሻግሮ በተለይ በምዕራባውያን አገራት በሚገኙ ዲያስፖራዎች መበላት ከጀመረ አስርት አመታት እንዳለፈው የምታስታውሰው ዘጋቢዋ፤ አሁን አሁን ደግሞ የጤፍ ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ትናገራለች፡፡

የኢትዮጵያ ጤፍ በአለም ገበያ ቀጣዩ ተፈላጊ ሰብል ለመሆን እንደሚችል በመግለጽ፣ ነገ ከነገ ወዲያ ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ለአለም የምታበረክተው ሁለተኛው ስጦታ ጤፍ መሆኑ እንደማይቀር ትናገራለች፡፡ በውስጡ ካልሺየም፣ አይረን፣ ፕሮቲንና ሌሎች ንጥረነገሮችን የያዘውና ለጤና ተስማሚ የሆነው ጤፍ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ነው ዘ ጋርዲያን ከሰሞኑ ያስነበበው ዘገባ የሚያስረዳው፡፡ “ጤፍ በውስጡ የያዘውን ንጥረ ነገር ባወቅሁ ጊዜ እጅግ ነበር የተገረምኩት፡፡ በህይወት ዘመኔ ሁሉ ስመገበው የኖርኩት ጤፍ፤ እንዲህ ያለ ጠቃሚ ነገር መሆኑን አላውቅም ነበር፤ የሚገርም ነገር ነው!” ያለችው ነዋሪነቷ በለንደን የሆነው ኢትዮጵዊቷ ሶፊ ከበደ ናት፡፡ ሶፊ በጤፍ ተገርማ አላበቃችም፡፡

የግርምት ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጭም መሆን እንደሚችል ገብቷታል፡፡ ለዚህ ነው ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ ለንደን የሆነ ‘ጦቢያ ጤፍ’ የተሰኘ የንግድ ኩባንያ ከባለቤቷ ጋር በማቋቋም፣ ጤፍን ከአምራች አገሮች እየገዛች ወደእንግሊዝ በማስመጣት መሸጥ የጀመረችው፡፡ የዘጋርዲያን ዘገባው እንደሚለው፣ ዛሬ “ፕላኔት ኦርጋኒክን” የመሳሰሉ የለንደን ታላላቅ መደብሮች ጤፍ አሽገው በመቸብቸብ ላይ ናቸው፡፡ በእነዚህ መደብሮች አንድ ኪሎ የጦቢያ ጤፍ ዱቄት 7 ፓውንድ (ከ200 ብር በላይ) ይሸጣል፡፡ በመደብሮቹ በጤፍ ዱቄት የተሰራና የተለያዩ ማጣፈጫዎች የታከሉበት ዳቦም ለገበያ ይቀርባል፡፡ ጤፍ አሁን የአገር ቤትና የአገር ልጅ ምግብ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ምዕራባውያን አገራት ዜጎችም በጤፍ አምሮት መለከፍ ይዘዋል፡፡ ፍላጎቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ “ማማ ፍሬሽ” የተባለው የንግድ ኩባንያ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ለአመታት እንጀራ ሲያቀርብ መቆየቱንና በአሁኑ ወቅትም ወደ ፊLላንድ፣ ጀርመን፣ ስዊድንና አሜሪካ እየላከ እንደሚገኝ ዘገባው ያሳያል፡፡ ወደ አሜሪካ የሚልከውን ምርት በ2014 በእጥፍ የማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ ያለው ኩባንያው፤ በቅርቡም የጤፍ ፒዛ፣ ዳቦና ብስኩት እያመረተ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር ዘገባው ያስረዳል፡፡

ዘጋቢዋ እንደምትለው፤ “ጥያቄው ኢትዮጵያ እና አርሶ አደሮቿ ከዚህ አለማቀፍ ገበያ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለው ነው፡፡ ለመሰል የተወሰኑ አገራት ምርት ብቻ የሆኑ በንጥረነገር ለበለጸጉ የምግብ እህል ሰብሎች እያደገ የመጣው አለማቀፍ ፍላጎት፣ በድህነት የሚማቅቁ የአምራች አገራትን ማህበረሰቦች ጎጂ ሲሆኑ ይታያሉ ትላለች ዘጋቢዋ፡፡ ይህን እውነታ ለማስረዳት የቦሊቪያና የፔሩን ተሞክሮ በአብነት የምትጠቅሰው ዘጋቢዋ፣ በእነዚህ አገራት የሚመረተው “ኪየኑአ” የተሰኘ የሰብል አይነት በብዛት ወደ ውጭ አገራት መላኩ፣ በአገሪቱ የምግብ እጥረት ማስከተሉን እንዲሁም ሰብሉን አምርቶ በብዛት በመሸጥ የምዕራባውያኑን ፍላጎት ለማሟላት በሚል በአርሶአደሮች ዘንድ የመሬት ሽሚያና ግጭት መፈጠሩን ትገልጻለች፡፡ “በኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ለጤፍ ያላቸው ፍላጎት እያደገ ነው፡፡ በአገሪቱ የጤፍ ዋጋ ባለፉት አስርት አመታት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም ድሃ ዜጎች ጤፍ መግዛት የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ አምራቾችም ምርታቸውን ወደ ከተማ እያወጡ በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡” ያለችው ዘጋቢዋ፤ የመንግስትን መረጃ ጠቅሳ እንደጻፈችው፣ በከተማ የሚኖሩ ዜጎች በአመት በአማካይ 61 ኪሎግራም ጤፍ እንደሚመገቡ ይገመታል፡፡

በገጠር የሚኖሩት ደግሞ 20 ኪሎግራም፡፡ የአገሪቱ መንግስት አመታዊ የጤፍ ምርቱን በ2015 በእጥፍ የማሳደግ እቅድ አለው፡፡ ይህም የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ አቅርቦቱን ለማሳደግ ያስችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት፣ የንግድና ገበያ ዳይሬክተር ዴቪድ ሃላም እንደሚሉት፣ አገር በቀል የሰብል ምርቶችን ለአዳዲስ አለማቀፍ ገበያዎች በማቅረብ ጥሩ ገቢ ማግኘት መቻሉ እንዳለ ሆኖ፣ መንግስታት አነስተኛ ሰብል አምራቾች ከእነዚህ ገበያዎች የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባዮ ዳይቨርሲቲ ተቋም የቀድሞ ሃላፊ የነበሩት የግብርና ተመራማሪው አቶ ረጋሳ ፈይሳ በበኩላቸው፣ ጤፍን በከፍተኛ መጠን እያመረቱ ለውጭ ገበያ የማቅረቡ አካሄድ በአግባቡ ካልታቀደና ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደጋ አለው ማለታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ አካሄድ፣ አርሶ አደሮች ለሌሎች ምርቶች ትኩረት እንዳይሰጡ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በብዛት አምርቶ ለገበያ የማቅረቡ አካሄድ አነስተኛ ገበሬዎችን ተጠቃሚ በማያደርግ መልኩ ለጥቂት አትራፊዎች ሲሳይ ሊሆን ይችላል፡፡ በአለማቀፍ ገበያ ላይ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ጤፍ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ የአሜሪካ ገበሬዎች ጤፍ ማምረት መጀመራቸውን የገለጸው ዘገባው፤ የአውሮፓ፣ የእስራኤልና የአውስትራሊያ ገበሬዎችም በሙከራ ደረጃ ጤፍ ወደማምረት መግባታቸውን ጠቁሟል፡፡

የ “ጦቢያ ጤፍ” ኩባንያ ባለቤት የሆነችው ሶፊ ከበደ፤ በለንደን ለገበያ የምታቀርበውን ጤፍ፣ ከአገር ቤት ሳይሆን ከደቡባዊ አውሮፓ አገራት ገበሬዎች እንደምትገዛ ገልጻለች፡፡ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች የሚያመርቱትን ማኛ ጤፍ ለእንግሊዝ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላትና የአገሯ ገበሬዎች ምርታቸውን ለአለማቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን የማይችሉበት መንገድ እንደሌለም ለ “ዘጋርዲያን” ተናግራለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 የኢትዮጵያ መንግስት ጤፍን በእንጀራ መልኩ ካልሆነ በቀር በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚከለክል ህግ ማውጣቱን የወሳው ዘገባው፤ ይሄም ሆኖ ግን እገዳው ዘላቂ እንደማይሆን ገልጿል፡፡ ምክንያቱም የመንግስት ስትራቴጂ ያስቀመጠው ግብ ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ የሚውል በቂ የጤፍ ምርት ማምረት ነውና፡፡

ከአስራ አራት ቀን በፊት “አድዋ ይከበር ይዘከር ለዘላለም” በሚል መሪ ቃል ከአዲስ አበባ ጣይቱ ሆቴል የእግር ጉዞ የጀመሩት የጉዞ አድዋ አባላት፤ የካቲት 23 ታሪካዊቷ አድዋ አምባ እንደሚደርሱ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ወደ አድዋ የሚያደርጉትን ታሪካዊ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በዶ/ር አኧዘ ጣዕመ፣ ሙሉ የጤንነት ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን “ዘ አዘር ፌስ ኦፍ ኢትዮጵያ” ሙሉ ወጪያቸውን እንዲሁም አዲካ ለቀረጻ የሚያገለግላቸውን መኪና እንዳበረከተላቸው ከተጓዦቹ አንዱ የሆነው አርቲስት መሃመድ ካሣ ገልጿል፡፡

የጉዞው ዓላማ የአድዋ ጀግኖችን መዘከርና እነሱ የተጓዙበትን አስቸጋሪ መንገድ ማስታወስ ሲሆን አባላቱ የጉዞ መስመራቸውን ያደረጉትም አጼ ሚኒልክ ጦራቸውን ከአዲስ አበባ ይዘው በወጡበት መንገድ ነው ብሏል - አርቲስት መሃመድ፡፡ በዛሬው እለት ከአዲስ አበባ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ በምትርቀው ሀይቅ ከተማ የሚደርሱ ሲሆን የጉዞው ፍጻሜ የአድዋ በዓል ዕለት የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ይሆናል፡፡ የጉዞው አባላት መሃመድ ካሳን ጨምሮ 5 ሲሆኑ የኢትዮፒካ ሊንክ ሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ብርሃኔ ንጉሴ እንዲሁም ኤርሚያስ አለሙ፣ ሙሉጌታ መገርሣ (አማሩ) እና አለም ዘውዱ ካሣሁን ይገኙበታል፡፡በጉዟቸው የጤና እክል እንዳላጋጠማቸው የገለጹት የጉዞው አባላት፤ በዶ/ር አኧዞ የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በቶም ፊልም ኘሮዳክሽን የቀረበው “ፅኑ ቃል” ፊልም የካቲት 2 ቀን 2006 ዓ.ም በሁሉም የግል ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም

የካቲት 3 በሸራተን አዲስ እና በመንግስት ሲኒማ ቤቶች ለእይታ ይቀርባል፡፡
የ1 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን ይህን ፊልም ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ

የፈጀ ሲሆን ዳንኤል በየነ ዳይሬክት አድርጐት፣ ቶማስ ጌታቸው በደራሲነትና ኘሮዱዩሰርነት ተሣትፎበታል፡፡
የሮማንስ ሰስፔንስ ዘውግ ባለው በዚህ ፊልም ላይ መሪ ተዋናዮቹን እነ ግሩም ኤርሚያስ፣ ማህደር አሰፋና ኤልያስ

ወሰንየለህን ጨምሮ ከ450 በላይ ባለሙያዎች ተሣትፈውበታል፡፡
ቶም ፊልም ኘሮዳክሽን ከአሁን ቀደም “ስርየት” እና “ፔንዱለም” የተባሉ ፊልሞችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡

የግጥም፣ የወግና የአጭር ልቦለድ ስብስቦች የተካተቱበት  ‹‹ታሽጓል››  መጽሐፍ፣ ባለፈው ሳምንት አርብ በጎንደር ከተማ ‹‹ሲኒማ አዳራሽ›› የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ገዛኸኝ ፀጋው፣ በክብር እንግድነት በተገኙበት በይፋ መመረቁን በስፍራው የነበረው ሪፖርተራችን ዘግቧል፡፡  
 የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የጎንደር ቅርንጫፍ ሰብሳቢ በሆኑት በአቶ ግርማይ ከበደ የተደረሰው ‹‹ታሽጓል›› መጽሐፍ፣ 123 ገጾች ሲኖሩት፣ በ30 ብር ለገበያ መቅረቡ ታውቋል፡፡


በሮማን ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሄር የተጻፈው “ሪፍሌክሽንስ” የተሰኘ የእንግሊዝኛ ግጥሞችና የፎቶግራፎች ስብስብ መጽሃፍ ባለፈው አርብ በኢትዮጵያ ሆቴል ተመርቆ ለንባብ በቃ፡፡ ነዋሪነቷ በለንደን የሆነው ሮማን፤“የውስጣዊ ስሜቴ ነጸብራቆች ስብስብ ነው” ብላለች- መፅሃፉን።  በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ 60 ግጥሞችና በመምህር ቶማስ ለማ የተነሱ 26 ፎቶግራፎችን ያካተተው “ሪፍሌክሽንስ”፤ በተለያዩ የመፃህፍት መደብሮችና አዟሪዎች እጅ የሚገኝ ሲሆን በ40 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ገጣሚዋ በቀጣይ የታዋቂ ኢትዮጵያውያን ገጣሚዎችን የተመረጡ ግጥሞች ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎም በውጥ አገር ውጭ ተነባቢ ለማድረግና የአገሪቱን ስነጽሁፍ ለተቀረው አለም የማስተዋወቅ ዕቅድ እንዳላት በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተናግራለች፡፡

በጋዜጠኛ ሸዋዬ ገላው ተጽፎ፣ በራሱ በሸዋዬና በደመወዝ ጎሽሜ የተዘጋጀው “ባቢሎን” የተሰኘ ኮሜዲ ፊልም በሳምንቱ መጀመሪያ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ለእይታ በቃ፡፡
የአንድ ሰዓት ከአርባ ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ፊልሙ፤ በብድር ባገኙት ገንዘብ የኤሌክትሪክ ምጣድ በማደስ ራሳቸውን ለመለወጥ የሚተጉ ጓደኛሞች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች የሚያሳይ ሲሆን  ሰርቶ ለመጨረስ አንድ አመት ከመንፈቅ ፈጅቷል፡፡ በፊልሙ ላይ አሰፋ በየነ፣ ሰላም ይሁን አስራት፣ በረከት በላይነህ (አመዶ)፣ ትዕግስት በጋሻው፣ እንግዳ ጌታቸው እና ሌሎች ተዋንያን ተሳትፈውበታል። ጋዜጠኛ ሸዋዬ ገላው በ“ገመና 2” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በደራሲነት ተሳትፏል፡፡

በገጣሚ ሰሎሞን ሞገስ /ፋሲል/ የተጻፈው “ጽሞና እና ጩኸት” የተሰኘ የግጥም መድበል ዛሬ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በጣይቱ ሆቴል የጃዝ አምባ ማዕከል ይመረቃል። የገጣሚው ሶስተኛ ስራ የሆነው መጽሃፉ፤76 ገጾች ያሉት ሲሆን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 59 ግጥሞችን አካቷል፡፡ የመሸጫ ዋጋውም 20 ብር ነው፡፡
ገጣሚው ከዚህ በፊት ‘እውነትን ስቀሏት’ እና ‘ከጸሃይ በታች’ የተሰኙ የግጥም መፃህፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን በተለያዩ የስነጽሁፍ መድረኮች ላይ ግጥሞቹን በማቅረብም ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል በህግ ባለሙያዋ ሂሩት ምህረት የተጻፈው “ማርሲላስ” የተሰኘ የረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ነገ ማለዳ በሐገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡ ለፀሃፊዋ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ልቦለዱ፤270 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በ75 ብር በተለያዩ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡

           ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ከጐንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር ያዘጋጃቸው “ጐንደርን ለአገር ቤት” እና “ጐንደርን ለህፃናት” የተሰኙ የቱሪዝም ዳይሬክተሪዎች ታትመው  ባለፈው ሳምንት ጐንደር ከተማ በሚገኘው ቋራ ሆቴል ተመረቁ፡፡ የምረቃ ስነስርዓቱን የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ ከፍተውታል፡፡
ከዚህ በፊት “ጐንደርን ለአገር ቤት” የተሰኘ የጐንደር ቱሪዝም ማውጫ በእንግሊዝኛ መውጣቱ የሚታወስ ሲሆን የአገር ውስጥ ጐብኚዎችና የጐንደር ከተማ ነዋሪዎች ስለጐንደር ቅርሶች ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ቅርሶቹን እንዲንከባከቡ በማሰብ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ  መቅረቡን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ት ህይወት ሀብታይ ተናግራለች፡፡ ማውጫው በዋናነት የጐንደርን ዋና ዋና መስህቦች ያካተተ ሲሆን በተለይም የአፄ ፋሲለደስ ግንቦችን፣ ደብረ ብርሃን ስላሴን፣ የአፄ ፋሲለደስ መዋኛን እንዲሁም  ጐንደር ያሏትን ፓርኮችና ሙዚየሞች የሚያስቃኝ ነው፡፡
በዚሁ እለት “ጐንደርን ለህፃናት” የተሰኘ መጽሐፍም የተመረቀ ሲሆን ህፃናት የጐንደርን መስህቦች እንዲያውቁና በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ በሚያስችላቸው መንገድ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን በዚህ አመት ብቻ የቱሪዝም ማውጫ ሲያስመርቅ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ቀደም ሲል “የሰሜን ሸዋ የቱሪዝም ዳይሬክተሪ” እና “የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፓርኮች ዳይሬክተሪ”ን አስመርቋል፡፡ ድርጅቱ በየሁለት ወሩ የሚወጣና ቱሪዝም ላይ አተኩሮ የሚሰራ “ቱባ” የተሰኘ መጽሔት እንደሚያዘጋጅም ይታወቃል፡፡