Administrator

Administrator

• አዳዲስ ክልሎች የሌላ ብሔር ተወላጆችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል
   • ሲዳማ ክልል የበርካቶችን ህይወት ከቀጠፈ ግጭት በኋላ፣ 10ኛው ክልል ሆኖ ተዋቅሯል፡፡
   • በቅርቡ ምዕራብ ኦሞ፣ቤንች ሸካ፣ ከፋ ዳውሮና ሸካ ተጣምረው 11ኛውን ክልል መስርተዋል
   • የክልልነት ጥያቄ ካነሱ የደቡብ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ወላይታ ዞን ውጥረት እንደነገሰ ቀጥሏል
   • የጉራጌ ዞን በክላስተር  እንዲደራጅ ከመንግስት የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል
   • የጋሞ ህዝብ ከዓመታት በፊት  ያቀረበው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ፣ ወደ ቀጣይ እርምጃ ይገባል ተብሏል
   • በጂንካ ከክልል እንሁን ጥያቄ ጋር ተያይዞ አያሌ ዜጎች ለጥቃት ተዳርገዋል
       
     ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተዋቀረው ፌደራላዊ ስርዓትና ይህንም ተከትሎ ተግባራዊ በሆነው የአገሪቱ ህግ መንግስት ለብሔሮች በሚሰጠው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሳቢያ፣ ብሔርን መሰረት አድርገው የሚዋቀሩ ክልሎች ጉዳይ አሁንም ለውጥረት፣ ግጭትና ሞት ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡
 በሲዳማ ክልል ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ያለምንም ፈቃድ ክልሉ የመሆን ጥያቄያችንን ተግባራዊ እናደርጋለን ባሉ የክልል ተወላጆችና በመንግስት መካከል ተፈጥሮ በነበረው ውጥረትና ይህን ተከትሎ በተቀሰቀሰ የብሔር ግጭት ሳቢያ የበርካቶች ህይወት አልፏል፡፡
 በዛው ዓመት የሲዳማን የክልል እንሁን ጥያቄ ተከትሎ፣ በአዋሳ ከተማ ውስጥ በተቀቀሰ ግጭት በርካቶች ለሞት አደጋ ሲዳርጉ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስትና የግለሰቦች ንብረትና ሃብት ወድሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ተበትነዋል፡፡ የማታ ማታም ክልሉ በህዝበ ውሳኔ 10ኛው ክልል ሊሆን በቅቷል፡፡
ቀጣይ ባለተራ በደቡብ ህዝቦች ክልል ውስጥ ተዋቅሮ የኖረው የምዕራብ ኦሞ ቤንች ሸካ፣ የከፋ፣ የዳውሮና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ህዝቦች ሆኑ። በአካባቢው ለወራት ከዘለቀ ውዝግብና ውጥረት በኋላም መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ አስራ አንደኛ ክልል ሆኖ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ድምፅ ሰጥተው የራሳቸውን ክልል በመስራት የደቡብ ምእራብ ክልል አራት ከተሞችን የክልሉ መቀመጫ በማድረግ ተዋቅሯል፡፡
የደቡብ ክልል ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄው፤ በዚህ ብቻ አላበቃም-ቀጥሏል፡፡ ክልል የመመስረት ጥያቄን አጥብቀው ከሚያነሱ የደቡብ ክልል አካባቢዎች መካከል የወላይታ ዞን አንዱ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር ሳቢያ በዞኑ አሁንም ውጥረቱ እንደነገሰ ነው፡፡
የጋሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫም ከዓመታት በፊት ለዞኑ ምክር ቤት ያቀረበው የክልል እንሁን ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅሬታውን አቅርቦ ምላሽ ባላገኘበትና የህዝቡ ጥያቄ ፍላጎት በተጨፈለቀበት ሁኔታ ክልሉን በሁለት ክልሎች ከፍሎ ለማዋቀር እየተደረገ ያለውን ሩጫ አጥብቄ እቃወማለሁ ብሏል፡፡
ከ3 ዓመታት በፊት የራሱን ክልል ለማቋቋም ለደቡብ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ባለማግኘቱ ቅሬታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማቅረብ መልስ እየተጠባበቀ ባለበት ሁኔታ የህዝብን ፍላጎት ያላገናዘበና ህገ መንግስታዊ መብቱን የሚጨፈልቅ ተግባር ለመፈጸም የሚደረገውን ጥረት አጥብቀን እንቃወማለን ብሏል ፓርቲው፡፡
የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንብር አቶ ዳሮት ኮምባ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የጠየቁት ህገመንግስታዊ  ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነና ህዝብ ያልተስማማበትን ውሳኔ  በጫና  እንዲቀበል የሚገደድ ከሆነ፣ ወደ ቀጣይ ህጋዊ እርምጃዎቻችን መሄዳችን አይቀሬ ነው ብለዋል። ህዝብ ሳይመክርበት በአቋራጭ የሚደረጉ አካሄዶችን እንቃወማለን ሲሉም አክለዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የተካተተው የጉራጌ ህዝብ እራሱን በቻለ ክልል ለማዋቀር ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን ለጥያቄው ምላሽ ባለማግኘቱሰሞኑን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ ሰንብቷል፡፡
ከእነዚህ እንቅስቃሴዎቹ መካከልም  ባለፈው ሰኞ ነሀሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ያካሄደው የስራ ማቆም አድማ ተጠቃሽ ነው፡፡ ማን እንደጠራው በትክክል አልታወቀም በተባለው በዚሁ የስራ ማቆም አድማ፣ ከዳቦ ቤቶችና ከህክምና ተቋማት ውጭ በወልቂጤ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቋማት ዝግ ሆነው ውለዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የመንግስት አካላት በዞኑ ውስጥ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪውን ለማወያየት ጥሪ ቢያደርጉም፣ ነዋሪዎቹ ለመሰብሰብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የጉራጌ ዞንን በክላስተር ለማደራጀት በመንግስት ተይዞ የነበረው አቅጣጫ ህዝቡን የሚከፋፍልና ማንንቱን የሚያሳጣ ተግባር ነው በሚል ከዞኑ ነዋሪ ህዝብ ተቃውሞ ገጥሞታል። በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ከትናት በስቲያ ተሰብስቦ የነበረው የጉራጌ ዞን ምክር ቤትም ዞኑ ከአጎራባች ዞኖች ጋር በአንድ ክልል ስር እንዲደራጅ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ አድርጎታል- ከ97ቱ የምክር ቤት አባላት 52 የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውመውታል፡፡
የጉራጌ ዞን ከከምባታ ጠምባሮ፣ሀድያ ሀላባ፣ስልጤና ጉራጌ ዞኖች እንዲሁም ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በአንድ ክልል ስር እንዲደራጁ የሚጠይቀውና  የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ርዕስቱ ይርዳው በተገኙበት፣ በዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ መሀማድ ጀማል የቀረበውን ሃሳብ የዞን ምክር ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። በሁለት ተከፍለው እንደ አዲስ ይደራጃሉ ከተባሉ አስራ አንድ ዞኖችና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ውሳኔውን ባለመቀበል ውድቅ ያደረገው የጉራጌ ዞን ም/ቤት ብቻ ሲሆን ሌሎቹ ሁሉም የዞን ምክር ቤቶችና አፈጉባኤዎችና የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ይህንኑ የፀደቁ ውሳኔዎቻቸውን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ለፌደሬሽን ምክር ቤት አስገብተዋል፡፡
ከሁለቱ አዲስ ክልሎች መካከል አንደኛውን ለመመስረት በምክር ቤቶቻቸው  ውሳኔ ያሳላፉት ዞኖች የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ጋሞ ጎፋ የደቡብ ኦሞና የኮንሶ ዞኖች ናቸው! የአማሮ፣ ባስኬቶ ቡርጂ፣ ደራሼና አሌ ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶችም ይህንኑ በጋራ የመደራጀት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
ሁለተኛውን ክልል በጋራ ለመመስረት የሚያስችላቸውን ውሳኔ ያሳለፉትና በምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁት ደግሞ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ሀላባ፣ ከምባታ ጠምባሮ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ሲሆኑ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የክላስተር አደረጃጀቱን ባለመቀበል ብቸኛው የዞን ምክር ቤት ሆኗል፡፡
ይህ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔም በአካባቢው ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት  ሆኗል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የዞኑ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት፣ በአካባቢው ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር በሚሞክሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡ የጉራጌ ዞን የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪው  ሌተና ኮሎኔል ፈጠነ ፍስሃ ህብረተሰቡ ደስታውን በሰላማዊ መንገድ መግለፅ አለበት ብለዋል፡፡
ይህንኑ በደቡብ ክልል እየበረታ የመጣውን የክልልነት ጠያቄ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሠጡን የፖለቲካ ሳይንስ ምዑሩ ዶክተር ዮሴፍ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ አገሪቱ አሁን ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂው ስርአቱ ነው፡፡ የፌደራሊዝም ስርአቱ በብሔር ማነንት ላይ ያተኮረ መሆኑ የችግሮች ሁሉ መሰረት ነው ያሉት ምዑሩ ብሔር ላይ ያተኮረ ክልል ሲዋቀር “ባለቤት”ና “መጤ” የሚሉ ስሜቶችን በመፍጠር አስከ አሁን ያላየነውን ችግርና መፈናቀል  ሊያስከትል ይችላል ብለዋል፡፡
“ይህ የእኛ ክልል ነው፤ ከዚህ ለቃችሁ ውጡ” በሚል ምክንያት፣ በአገሪቱ የሚታየው ውጥንቅጥ የተፈጠረው በዚሁ በብሔር አደረጃት ሳቢያ ነው፡፡ እናም አዳዲስ የሚቋቋሙት ክልሎቸም በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች እንዲገለሉና ለአደጋ እንዲጋለጡ በማድረግ፣ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላሉ ብለዋል ዶ/ር ዮሴፍ፡፡
አሁን በተጀመረው የመልሶ ማዋቀር ሂደት የጉራጌ ዞን ምክር ፣አዲስ ክልል የሚመሰርቱ ከሆነ፣  የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ክልል ህልውና ያከትማል፡፡


 ሱዳን በ245.1 በመቶ የዋጋ ግሽበት ትመራለች አፍሪካን
             
       ከአፍሪካ ሃገራት በወቅታዊ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ በ3ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ሱዳን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች፡፡ የአለም ባንክ ከሰሞኑ  ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው፡ በፖለቲካ ሁከትና  አለመረጋጋት ውስጥ  የምትናጠው ሱዳን፣ በ245.1 በመቶ የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት አፍሪካን ትመራለች፡፡
በየጊዜው የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ቀውስ የማንጣት ዚምባብዌ ደግሞ፣ በ86.7 በመቶ  የዋጋ ግሽበት በሦስተኛ ደረጃ ላይተቀምጣለች። ኢትዮጵያ በ34.5 በመቶ የዋጋ ግሽበት በሦስተኛ ደረጃ ላይ  ስትገኝ፡፡  አንጎላ 23.9 በመቶ፣ ሴራሊዮን 17.3 በመቶ፣ ጋና 16.፣3 በመቶ፣ናይጀሪያ 16.1 በመቶ፣ደቡብ ሱደን 16 በመቶ፣ዘምቢያ 15.7 መቶ በማስመዝገብ እስከ 10ኛ  ያለውን ደረጃ ይዘዋል በቅድመ ተከተላው መሰረት፡፡
ከአፍሪካ ሃገራት በጣም ዝቅተኛ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ያስመዘገቡ  አስር ሃራት ደግሞ ደቡብ ሱዳን፣ቤኒን፣ሲሸልሲ፣ ካሜሮን፣ ኤርትራ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ረፐብሊክ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን ስዋዚላንድ እና ቻድ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ግሽበት የተመዘገበው በምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች እንዲሁም በግንባታ የግብአቶች ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገቡ ሃገራት የህዝባቸውን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል  ላይ መትጋት እንደለባቸው የዓለም ባንክ ሪፖርት አሳስቧል፡፡

 በአዲስ አበባ የሚስተዋሉ የአስተዳደር መደበላለቅ ችግሮችን በባለሙያዎች እያስጠና መሆኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ የአዲስ አበባ  ከተማ  አስተዳደርና  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወሰን ለማካለል የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን መረዳቱን ጠቁሞ፣ ማካለል ያለበቂ የህዝብ ተሳትፎ መፈጸም እንደሌለበት አሳስቧል።
“ህዝብ የአስተዳደር ውሳኔን የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት እንደ ዜጋ በሂደቱ ላይ የመሳተፍና  የማወቅ መብቱ በአግባቡ ሲከበርለት ብቻ ነው” ያለው የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ “በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መሃከል ያሉ የወሰን ችግሮችን ለመፍታት የአስተዳደር ወሰን ማካለሉ ጠቃሚ መሆኑ ባይካድም፣ ውሳኔዎቹን ማስተግበር የሚቻለው፣ ዜጎችን አሳትፎ፣ የሂደቱ ባለቤት በማድረግ እንጂ፣ በሃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ሊታወቅ ይገባል” ብሏል።
“በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መሃከል ስላለው የወሰን ማካለል ጉዳይም ሆነ በየቦታው የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች በቀጣይ በሚካሄደው ሃገራዊ የምክክር መድረክ ይፈታል” የሚል እሳቤ እንዳለው የጠቆመው ፓርቲው፤ መንግስት በአንጻሩ ሃገሪቱ ያለችበትን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ ያላደረጉ እንደ ክላስተርና የአስተዳደር ማካለል አይነት  ውሳኔዎች መስተዋላቸው ተገቢ አይደለም ሲል ነቅፏል።
እንዲህ አይነት የህዝብ ተሳትፎን ያላማከለ፣ በቁንጽል እሳቤዎች ላይ የተንጠለጠለና ጊዜውን ያልጠበቀ አካሄድ ከፍተኛ ስህተት በመሆኑም፣  በፍጥነት ሊታረምና ሊስተካከል እንደሚገባም አስስቧል-።
“በየአካባቢው የሚኖረው ህዝብ፤ የመንግስትን ውሳኔዎች የመቀበል ግዴታ የሚኖርበት፣ እንደ ዜጋ በሂደቱ ላይ የመሳተፍና የማወቅ መብቱ ሲከበርለት ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል- ፓርቲው።
በአዲስ አበባ እየተስተዋሉ ያሉ የአስተዳደር መደበላለቅ ችግሮችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን ሰብስቦ በጥናት የሚለይ ቡድን በማሰማራት ቀደም ብሎ ስራዎችን እንደጀመረ የጠቆመው ኢዜማ፤ ጥናቱ ሲጠናቀቅም ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በአገራችን የተመረተና የኮቪድ 19 በሽታን በቤት ውስጥ ለመመርመር የሚያስችል መሳሪያ ገበያ ላይ የዋለ ሲሆን መሳሪያው የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እውቅናና ፍቃድ የተሰጠው መሆኑም ተገልጿል፡፡
ጥሬ ዕቃዎችን ከአሜሪካ በማስመጣት ምርቱን በአገራችን እያመረተ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያዎች በማቅረብ ላይ የሚገኘው “Access bio inc” ትናንት ምርቶቹን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኮቪድ 19 በሽታን በቤት ውስጥ ለመመርመር ያስችላል የተባለውና “care start የሚል ስያሜ የተሰጠው መሳሪያው በ10 ደቂቃ ውስጥ ውጤቱን ለማወቅ የሚያስችል ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ፋርማሲዎች ለገበያ ቀርቧል ተብሏል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን ያመለከቱት የ“አክሰስ ባዮ ኢንክ” የስራ ኃላፊዎች፤ በአገራችንም በበሽታው ተይዘውና ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑን አስታውቀዋል። ህብረተሰቡ በበሽታው መያዝ አለመያዙን ለማወቅ በቀላሉ በፋርማሲዎች በሚያገኛቸው “care start” የመመርመሪያ መሳሪያዎች እራሱን በመመርመር ማረጋገጥ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
አክስስ ባዩ ኩባያው ከዚህ ቀድም የወባ መመርመሪያን መሳሪያዎች ወደ ህንድና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን ያስታወሱት የድርጁቱ የስራ ኃላፊዎች፤ አሁን ደግሞ ይህንኑ ቤት ለቤት የኮቪድ 19 በሽታን ለመመርመር የሚያስችል መሳሪያ እያመረተ ወደ ውጭ አገር በመላክ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን፣ በዛሬው ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀመረ።

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ በታደሙበት ዝግጅት ነው፣  ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው።

በታሪክ ውስጥ ማለፍና ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚባሉ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል፣ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ግን ዕድልም ድልም ነው፡፡ ይሄ ትውልድ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ባለ ዕድልም ባለ ድልም ነው፤ ብለዋል ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ዩኒት 9 የሚባለው ሁለተኛው ተርባይን፣ የተሳካ ተከላና ሙከራ ከተደረገ በኋላ ኃይል የማመንጨት ስራው እውን ሆኗል ተብሏል።

በዛሬው ዕለት ሥራ የጀመረው ሁለተኛው ዩኒት፣ 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የእንኳን ደስ ያለን ንግግራቸውን የቋጩት የተሟላ ስኬትና እርካታ በመመኘት ነው፡-
እነሆ አሁን የሕዳሴ ግድብ ከንድፍ አልፎ፣ ግንባታው ተገባድዶ፣ ግዙፍ ውኃ በጉያው ይዞ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው፤ ከዘፈን-እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢትዮጵያን በብርሃኑ ሊያደምቃት፣ ኃይል ሆኖ ሊያበረታት ከጫፍ ደርሷል። በፈጣሪ ርዳታና በኢትዮጵያዊ ወኔ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቀን የልባችን እንደሚሞላ አልጠራጠርም።  እንኳን ደስ ያለን!!

Saturday, 06 August 2022 14:44

ማራኪ አንቀፅ

   ማጠቃለያ


          የእኔ ዓላማ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘመነ ቅስና የነበሩትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣
ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ቀውሶችን ጠባይ፣ ምንጭ፣ ተገብሮት (Effect)፣ ክትያና ምላሽ፥ ለእኛ በሚኾን መልኩ መመርመር ነው፡፡ የወሰዷቸው
ኹለተኛ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ (ፍልቪያኖስ) እና የጊዜው ባሕታውያን እነዚህን ቀውሶች ለመፍታት ርምጃዎች፥ ለታሪካዊና ወቅታዊ ሕመሞቻችን ድኅነት ሊኾኑ በሚችሉበት ኹኔታ ማጤን ነው፡፡ ሦስተኛ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለአንጾኪያ እና ለአንጾኪያ ቤተክርስቲያን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲ’ኮ’ ሃይማኖታዊ ስንጥቆችና ሽንቁሮች መፍትሄ እንዲኾን የአደረጉትን ዕሴታዊና ክሂሎታዊ ብቁነቶቹን፥ የሀገራችን የሃይማኖትና የፖለቲካ ልሂቃን ሊማሩበት በሚችሉት አኳኋን ማመላከት ነው፡፡ እነዚህን ሦስት ዓላማዎች በተናጥል ወይም በትስስር ከማሳካት አንጻርበዚህ መጽሐፍ፤ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን አስተዳደግ፣ የሊቅነት አበቃቀል፣ ታሪካዊ መቼት፣ አእምሯዊ ሥሪት፣ ሥነ ልቡናዊ ውቅርንና ማኅበረ ፖለቲካዊ እሳቤዎቹን በጥንቃቄ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ የእርሱን ዘመነ ቅስና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓትና መዋቅር ባሕርይን በመጠኑ ለመተንተን ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ እርሱ የተነሣበት ጊዜ የሽግግር ዘመን እንደመኾኑ፥ የቀውስ ዘመን መሻገሪያ ትምህርቶቹንና ተግሣጾቹን፣ አሕዛባዊ የባህል ዕሴትን በክርስቲያናዊ የባህል ዕሴት የመተካት ውጥኖቹን፣ አዲስ ማኅበራዊ ሥርዓት የማዋለድ ተጋድሎውን ለማስገንዘብ ጥሬያለሁ፡፡  የቤተ ክርስቲያን እና የቤተ መንግሥት ጋብቻና ፍቺ፥ በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የሚያሳድሯቸውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖችን ገለጥለጥ አድርጌ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ አኹን ሀገራችን እና ቤተ ክርስቲያናችን የሚገኙበት ኅሊናዊ እና ነባራዊ ኹኔታ፥ አንጾኪያ እና የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ አንድ ሺሕ ስድስ መቶ ዓመታት በፊት ከነበሩበት ኹኔታ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከዚህ መጽሐፍ በኹለት ወገን የምንማራቸው ቁም ነገሮች አሉ፡፡ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ እና እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረስብ፡፡ እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ታሪካዊ እና መስክ ወለድ ችግሮችን በጊዜ እና ጊዜ ወስዶ አለመፍታት፥ ለማኅበረሰባዊ ቅራኔ፣ ለሕዝባዊ ዐመፅ፣ ለማኅበራዊ ዕሴቶች መሰባበር፣ ለብሔራዊ ጥርጣሬና ክፍፍል፣ ለእርስ በእርስ እልቂት፣ ለታሪካዊ ቁርሾና ቁርቁስ እንደሚዳርግ ተምረናል፡፡ በብሔረ ሀገር እና በብሔረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ መልክዐ ምድራዊ መስፋትና መጥበብ፣ መገፋፋትና መዋዋጥ፣ ፍጥጫና ጦርነት ክሡታዊ ኹነቶች መኾናቸውን፤ የሀገር ግንባታ ሥራ ትውልዳዊ ቅብብሎሸና የትላንትና የዛሬ ጥረት ድምር ውጤት እንደኾነም ለመገንዘብ የቻልን ይመስለኛል፡፡ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ልሂቃን አለመስከን ወይም የእርስ በእርስ ፍጥጫ ሀገርን ለብተና፤ ማኅበረሰብን ለሰብአዊና ቁሳዊ ጉስቁልና እንደሚያጋልጥ ኹሉ፥ የእነዚህ አካላት ስክነት ለሀገር እና ለማኅበረሰብ ፍቱን መድኃኒት እንደሚኾንም ተምረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚከሠት ቅጽበታዊና ሂደታዊ የማኅበራዊ ዕሴቶች መናጋት፣ የባህልና የዕሴት ተቃርኖ፣ በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች መካከል ያሉ ማኅበራዊ ግንኙነቶች መዛባት፣ የምጣኔ ሀብት ክፍፍል ኢ-ፍታሐዊነትና የአልተመጣጠነ የሀብት ሥርጭት ይዘዋቸው የሚመጧቸው ሀገራዊ ቀውስ ምንነቶችን በሚገባ ተረድተናል ብዬ እገምታለሁ፡፡


Saturday, 06 August 2022 14:36

የግጥም ጥግ

If I can stop one heart from breaking
By Emily Dickinson
If I can stop one heart from breaking,
I shall not live in vain;
If I can ease one life the aching,
Or cool one pain,  
Or help one fainting robin
Unto his nest again,
I shall not live in vain.
ከንቱ አይደለም መፈጠሬ
ትርጉም፡- በሽሽግ ወርቁ
አንድን ቅስም ከቅጭት ካዳንኩ
      ከንቱ አይደለም መፈጠሬ
ያንድን ህይወት ቁስል ካከምኩ
ወይ አንድ ስቃይ ካቃለልኩ
ወይ አንድዋን የወደቀች ወፍ
ጎጆዋ መልሼ ባተርፍ
     ትርጉም ያገኛል መኖሬ
      ከንቱ አይደለም መፈጠሬ፡፡

  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ሳቢያ  ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው  “ንባብ ለህይወት” የመጻህፍትና የምርምር ተቋማት  አውደ ርዕይ፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተ ሲሆን ለአምስት  ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል፡፡
በዚህ 5ኛው “ንባብ ለህይወት”  አውደ ርዕይ ላይ ደራሲያን፣ የመጻህፍት አሳታሚዎችና አከፋፋዮች እንዲሁም የምርምር  ተቋማት እየተሳተፉ ሲሆን አዳዲስ መጻሕፍት በ20 በመቶ  ቅናሽ እየተሸጡ ነው ተብሏል፡፡
የ’ንባብ ለኢትዮጵያ’ ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ከበደ፤ በአውደ-ርዕዩ  በመቶዎች የሚቆጠሩ  ደራሲያን፤ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ሥራዎቻቸውን ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በአውደ ርዕዩ ከ50 በላይ አዳዲስ መጻሕፍት እንደሚመረቁና የመጻሕፍት ውይይት እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አውደ-ርዕዩን፤ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት፣ ከ’ንባብ ለህይወት’ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።


ደራሲ ከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሳሌ” በሚል መጽሐፋቸው ስለ አውራ ዶሮ፣ ድመትና የአይጥ ግልገል ሲተርኩ የሚከተለውን ይሉናል፡-
  ከሰፈሯ ውጪ የትም ሔዳ የማታውቅ አንዲት የአይጥ ግልግል ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን  እናቷ ሳታውቅባት ለዙረት ወጣች። ስትመለስም ለእናቷ ይህን ነገረቻት፡-  “አንድ ያየሁት እንስሳ የዋህ ነው፤ አይኖቹ ያምራሉ፤ ረጅም የከንፈር ፂም አለው፤ ገላው ለስላሳ ነው፤ ድምጹ ደርባባና-የተዋበ ስለሆነ- ላጫውተው ጠጋ አልኩኝ፡፡ ሌላኛውና ቀዥቃዣው ፍጡር ግን የቀይ ስጋ ቁንጮ ራሱ ላይ ያለው ነው፤ ሲራመድ ጎብላላ ነው - ያስፈራል፤ በዚያ አሸባሪ ድምፁ ጮኸ፤ ከጉያውም ሁለቱን እጆቹን አወጣና ዘረጋ፤ አንድ ጊዜ እንደ ቁርበት  አራግፎ  ሲያጓራብኝ ምን ይዋጠኝ፤ የት ልግባ፡፡ ያንን መልከ መልካሙን ግን በወጉ እንኳን ሳልተዋወቀው ቀረሁ፤ ስለዚህ ፈጥኜ ወደ ቤቴ መጣሁ እልሻለሁ፡፡” አለቻት፡፡
እዛ ምን ወሰደሽ አንቺ ክልብልብ
አይጦች ስትባሉ የላችሁም ቀልብ
አይጥ ሞቷን ስትሻ ስታበዛ ሩጫ
ሄዳ ታሸታለች የድመት አፍንጫ
ሲባል የነበረው እስከነ ተረቱ
ባንቺ ሳይ ደረሰ በክልፍልፊቱ፡፡
ያ መልከመልካም ፊቱ የሚታይ
ድመት የሚባለው አውሬ አይደለም ወይ
መልኩ ቅልስልስ ነው ያ ክፉ አታላይ
ዋ የሰራው ስራ እሱ በኛ ላይ
ባታውቂው ነው እንጂ ጥንቱንም ሲፈጠር
አጥፊያችን እሱ ነው የትውልዳችን ጠር
እልቅስ ቀብራራው የደነገጥሽለት
 እኛን የሚጎዳ ክፋትም የለበት
ስሙም አውራ ዶሮ
እንደውም አንዳንዴ ሰው ሊበላ ሲያርደው
ለእኛም አንዳንድ ጊዜ ያገለግለናል
አጥንትና ስጋው ሲጣል ይተርፈናል፡፡
 ብላ እናቲቱ እየዘረዘረች ሁሉን አስረድታ
ለልጇ መከረች፡፡
---------
ሰው ጠባዩ ታውቆ ፊት ሳይመረመር
መልኩን አይቶ ብቻ ይረባል አይረባም
 ክፉ ነው  ደግ ነው ማለት አይገባም፡፡
***
የአውራ ዶሮ የድመትና አይጥ ግልገል ታሪክ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት ስናነበው ስንተርከውና ስንጽፈው፤ ሲወርድ ሲዋረድ  የመጣ ተረት ነው። ትምህርትነቱ ግን ምንጊዜም ለማህበረሰባችን ጠቃሚ ስለሆነ ይኸው ስንጠቅሰው እንኖራለን። ፋይዳው የሚመነጨው ዛሬም መልከ መልካም ጢማም --- የሚያምሩ፣ ገላቸው ልስልስ፣ ብዙ ጅራታም ሰዎች ስላሉ ነው። የልባቸውን ሳናውቅ በአንደበታቸው  እየተማረክን  እንታዘዛለን፡፡ የከረባታቸው ማማር ይገዛናል። ተክለ ሰውነታቸው ያማልለናል። አንዳንዴም የአብዮታዊ እንቅስቃሴ ፍልሚያ ብዙ ነገሮችን እንድናስተውል ጊዜ ስለማይሰጠን ካለፈ በኋላ ለቁጭትና ለፀፀት  ይዳርገናል፡፡
በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለቁጭትና ፀፀት ምንግዜም ሰፊ ቦታ አላቸው። ችግሩ የቁጭቶቹና ፀፀቶቹ አይነትና መጠን በጣም በርካታ በመሆኑ ለመያዝ ለመጨበጥ  አለመቻሉ ነው። አይያዝ አይጨበጤነታቸው የሚመጣው ደግሞ አንዱን ፈር ሳናሲዝ  ሌላው ወዲያው ወዲያው ስለሚከታተልብን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው ዝግጁ የሆነ አእምሮ ያስፈልጋል። አለበለዚያ እንደ 1966 አብዮት - ቤት ለቃቂው እቃውን ሳያወጣ፣ ገቢው እቃውን አምጥቶ ሳያስገባ  ፍጥጫ ይከፈታል፡፡
 በተደጋጋሚ በሀገራችን  ያጋጠመን  ነገር፣ በቶሎ የመፎከር - በቶሎ ለሬዲዮ ዲስኩር የመጣደፍ   አባዜ ነው፡፡ ለህዝባችን የምንሰጠውን መረጃ ብንሳሳት -- ስነ አዕምሯዊ መዛባት ሊያስከትል እንደሚችል አለማሰብ እጅግ  ጎጂ ነው፡፡  “ሳያስቡት የጀመሩት ቀረርቶ  ለመመለስ ያስቸግራል” ለሚለው ተረት ያጋልጠናል፡፡  እንጠንቀቅ!!

  • የጠ/ሚኒስትሩ መጥፋት የፈጠረው ውዥንብርና “የሽግግር መንግስት” ጥድፊያ
     • በዘንድሮ በጀት ዓመት ከኤክስፖርት ከ10 ቢ. ዶላር በላይ ተገኝቷል
      • በቀጣዩ ዓመት በሌብነት ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል


                 የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ድምጽ ለአንድ ወር ገደማ መጥፋቱ ውዥንብር ፈጥሮ ሰንብቷል- በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው። በእርግጥ በአሜሪካ ኦሪጋን ድል የተቀዳጀው የአትሌቲክስ ቡድናችን ወደ አገር ቤት መምጣትን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው የደስታና የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል- ብዙም ግን ውዥንብሩን አላጠፋውም።
“ጠ/ሚኒስትሩ ጤና ቢሆኑ ኖሮ በራሳቸው ቤተ-መንግስት ውስጥ በተዘጋጀው የአትሌቲክስ ቡድኑ የአቀባበልና የሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ ይገኙ ነበር።” የሚል መላምት መቀንቀን ጀመረ።
ከሁሉም የሚገርመው ግን የጠ/ሚኒስትሩ ድምጽ ጠፋ ብለው በአገሪቱ የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠርና አገሪቱ በመሪ እጦት ወደ ቀውስ እንዳትገባ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም በአደባባይ ሃሳብ ያቀረቡ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መከሰታቸው ነው።
ይህንን ለአንድ ወር ገደማ የዘለቀውን ውዥንብር ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ደምስሰውታል- ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እመርታ ከታየበት መረጃ ጋር በመከሰት። ከሰሞኑ በ2014 ማክሮ ኢኮኖሚ ግምገማና በ2015 የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ አቅጣጫ ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በ2014 የበጀት ዓመት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡን ጠ/ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የ6 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡም ተጠቁሟል።
“በማክሮ ኢንዲኬተርስ- በሁሉም- ከኢንፍሌሽን በስተቀር ያገኘነው እመርታ በእጅጉ ይበል የሚያሰኝ- የሚያኩራራ- ይበልጥ እንድንተጋ የሚያነሳሳ ነገር ነው።” ብለዋል- ጠ/ሚኒስትሩ ስለተመዘገበው ዕድገት ሲገለጹ።
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በፓርላማ በተገኙበት ወቅት ከነበሩበት መንፈሳዊና አካላዊ ገጽታ በእጅጉ ተሽለውና በሃይልና በአዎንታዊ ስሜት ተሞልተው ነው የተስተዋሉት በሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ውይይት ወቅት። በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት መደሰታቸውም በገጽታቸው ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር።
“ዘንድሮ በኤክስፖርት ከ10.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው ያገኘነው፤ ከሸቀጦችና አገልግሎት ዘርፉ።  ከዳያስፖራ ከሚላከው (ረሚታንስ) እና የውጭ ቁጥተኛ ኢንቨስትመንት ሲጨመር ገቢው ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋል። ለኢትዮጵያ ይህ ትልቅ አይደለም።
ኢትዮጵያ ከዚህ አምስት ስድስት እጥፍ ማደግ አለባት- ነገር ግን ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር በጣም ትልቅ እመርታ ነው፤ የማይጠበቅ እመርታ ነው።” ሲሉ በተገኘው ውጤት የተሰማቸውን እርካታ በቃላት ጭምር ገልጸውታል።
የላቀ ውጤት የተመዘገበው ደግሞ በኤክስፖርት መሆኑ ዘርፉ አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሰረት ለመገንባት ሚናው ቀላል እንዳልሆነ ነው የተጠቆመው።
“ኤክስፖርት ላይ ያልተሳካለት ኢኮኖሚ በብዙ ምክንያት ማደግ አይችልም። ምንም እንኳን የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ብዙ ቢሆኑም፤ ዋናው ግን የኛ ቡድን የራሱን ስራና ውጤት መገምገም ያለበት በኤክስፖርት ምን አመጣሁ ብሎ ነው፤ እሱ ሲስተካከል ብዙዎቹን የምናያቸውን አመላካቾች (ኢንዲኬተርስ) የማስተካከል አቅም አለው።” ሲሉ አብራርተዋል-ጠ/ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ዕድገትና ብልጽግና ትገሰግስ ዘንድ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኘው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝቧ ዕምቅ አቅም መሆኑን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ሁለት ችግሮች እንደሚስተዋሉ አልሸሸጉም።
“አንደኛው፤ በከፍተኛ ደረጃ እርዳታ የሚጠብቅና የልመና ባህሪ የተለማመደ ትውልድ እየፈጠርን መሆኑ ነው፤ ይህ ለብልጽግና ጠር ነው” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ “ሰርቶና ደክሞ ለውጥ የሚያመጣ ሃይል ነው መፈጠር ያለበት እንጂ ቁጭ ብሎ በሰበብ አስባቡ ችግር እየተናገረ መረዳት የሚያስብ ኃይል አደገኛ ነው።” ብለዋል።
ሁለተኛው የሚያስፈራውና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ደግሞ፤ ጦረኛ ህብረተሰብ (Warrior Society) እየተፈጠረ እንዳይመጣ ነው ይላሉ።
“እንደ ትውልድ-እንደ ህዝብ ውጊያን በጣም የሚያፈቅር ስለ ውጊያ የሚያወራ ስለ ውጊያ የሚያስብ ህጻናት ሆነው ዱላን እንደ ክላሽ የሚሰሩ ዓይነት ትውልድ ከፈጠርን ኪሳራ ነው፤ የውጊያ ትውልድ ልማት አያመጣም። መማር- መፍጠር- መስራት የሚል ትውልድ ነው አገር የሚያቀናው እንጂ ጦረኛ ትውልድ አይደለም።” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ አመራር ሆነው፣ ፓርቲ ሆነው፣ ክልል እየመሩ ህብረተሰቡን በሙሉ- ህጻን ሽማግሌውን- ለውጊያ የሚያሰለጥኑ- የሚያዘጋጁ- የሚያስታጥቁ አካላትን በተመለከተ የዛሬው ሳይሆን የነገው ነው የሚያሳስበኝ ይላሉ-ጠ/ሚኒስትሩ።
“ህብረተሰቡን በሙሉ ጦረኛ ካደረግህ ልማት አይመጣም፤ ለማኝና ጦረኛ ትውልድ አገር ሊያቀና አይችልም፤ ይሄ ብዙ ልንሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው።” ሲሉ ምክርም ማሳሰቢያም ሰጥተዋል፤ ዶ/ር ዐቢይ።
ሌላው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ሌብነት መሆኑን ጠቁመዋል። “ሌብነት፤ ጌጥ-ልምምድ- ምንም ነውር የሌለበት ጉዳይ እየሆነ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ማንም ሰው ምንም ሳይሰጋ እንደፈለገ የሚሰርቅበትና ገንዘብ የሚሰበስብበት ሁኔታ ጥፋት እንዳያስከትል ጥንቃቄ ያስፈልጋል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
“በአንድ በኩል እናለማለን፤ በአንድ በኩል ይፈርሳል፤ በግብርና ያመጣነው እመርታ በጣም ትልቅ ነው፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ቢሮክራት ለመታወቂያና መንጃ ፈቃድ ብር የሚቀበል ከሆነ ዋጋ የለውም። ህዝብ የምናስመርር ከሆነ ዋጋ የለውም። ኢንፍሌሽንን (ግሽበትን) ብናስተካክል ሌብነት ካለ ዋጋ የለውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ጠንከር ማለት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።” ብለዋል።
በዚህ ብቻ ግን አላበቁም። በመጪው ዓመት አንድ ጠንካራ ስራ የሚያስፈልገን በዚህ ጉዳይ ላይ ነው፤ ሌብነት ልምምድ  ሆኖ መቀጠል የለበትም ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ከማክሮ ኢኮኖሚ ገምጋሚ ቡድኑ ጋር የተሰበሰቡበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “ዘንድሮ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እመርታ አምጥተናል። ይህን በጋራ ማክበር ስለሚያስፈልግ ነው። ሁለተኛው ለቀጣዩ ዓመት ከዘንድሮውም ትንሽ የተለጠጠ ዕቅድ አቅደናል።   ይህንን ለማሳካት ደግሞ የዘንድሮውን ማክበርና  ለሚቀጥለው መዘጋጀት ስለሚፈልግ  በጋራ እንድንዘጋጅ ነው።” ብለዋል። ቡድኑንም ለተመዘገበው የኢኮኖሚ እመርታ በማመስገን፤ ለቀጣዩ ሥራ እንዲተጉ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ከጠ/ሚኒስትሩ መጥፋትና ከተፈጠረው ውዥንብር ጋር በተገናኘ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ ተቆርቋሪ ዜጎች፤ ጠ/ሚኒስትሩ ለረዥም ጊዜ ድምጻቸውን ማጥፋታቸው ውዥንብር ለሚነዙ ወገኖች ዕድል ስለሚከፍት፣ በየጊዜው የሚገኙበትን ሁኔታ ለህዝባቸው በማሳወቅ፣ ሀገርና ህዝብን ከአላስፈላጊ ሽብርና ውዥንብር ቢያድኑ መልካም ነው ብለዋል።Page 6 of 620