Administrator
የጋዜጠኛ እስክንድርና የእነ አንዷለም አራጌ ይግባኝ እልባት አላገኘም
የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ ተጨማሪ ጊዜ ጠየቁ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶችና ሽብር ለመፈፀም ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ሰርታችኋል በሚል ተከሰው የተፈረደባቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበሩት የእነ አንዷለም አራጌ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ በረቡዕ እለቱ ቀጠሮ እልባት ሳያገኝ ተላለፈ፡፡ በእለቱ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎት አዳራሽ ውስጥ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ችሎቱን ለመከታተል ቦታውን ሞልተው የዳኞችንና የታሳሪዎችን መምጣት እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ቢጠባበቁም ግን አልተሳካም፡፡
በመጨረሻ የእነ አንዷለም ጠበቆችና አቃቤ ሕጉ ወደ ጽ/ቤት ተጠርተው ሲሄዱ ነው፤ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ የተወሰኑ ጋዜጠኞችና የታሳሪ ቤተሰቦች ተከትለዋቸው የሄዱት፡፡ የመሀል ዳኛው አቶ ዳኜ መላኩ፣ ለታሳሪ ጠበቆችና ለአቃቤ ህግ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ በዚሁ መዝገብ 30 ያህል ሰዎች ይግባኝ የጠየቁ መሆናቸውን፣ መዝገቡም ለ10 ቀን ዘግይቶ እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል፡፡ “መዝገቡ ሰፊ ነው፤ ጉዳዩን ረጋ ብለንና ሰፊ ጊዜ ወስደን ልንመረምረው ይገባል” በማለት የተናገሩት የመሃል ዳኛው፤ ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጡ ገልፀዋል፡፡ ዳኛው ከዚህም በተጨማሪ፣ ማረሚያ ቤቱ ለምን እስረኞቹን ወደ ፍ/ቤት አላቀረበም በሚል ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ የቀጠሮ ትዕዛዝ አልደረሰንም የሚል ምላሽ አግኝተዋል፡፡
ዳኛው ግን፣ “በእኛና በማረሚያ ቤቱ ፀሐፊዎች መካከል መካካድ ተጀምሯል ማለት ነው እኛ ቀጠሮውን በወቅቱ ለማረሚያ ቤቱ ፀሐፊዎች ሰጥተናል” ብለዋል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ በእለቱም በጠቅላይ ፍ/ቤት የተገኙት ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመውሰድ እንደሆነ ለዳኛው አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የወጣቶችን ሀሳብ በማናወጥ፣ ለአመፅ በማነሳሳትና የመንግሥትን ስም ማጥፋት በሚል ክስ የቀረበበትን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በመወከል ጠበቃው ለከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረቡት ጥያቄ፤ ምስክሮችን ለማደራጀት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው፣ ለሚያዚያ 15 ቀን 2005 ዓ.ም መከላከያ ምስክሮች እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ሦስት ግለሰቦች ራሳቸውን ያጠፉበት መፀዳጃ ቤት እንዲፈርስ ተጠየቀ
ራሳቸውን ለማጥፋት ከሞከሩት ስድስት ግለሰቦች ሦስቱ ተርፈዋል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 25፣ በተለምዶ እሬሳ ማዞሪያ እየተባለ በሚጠራው ሠፈር ውስጥ ለበርካታ አመታት በህዝብ መፀዳጃ ቤትነት ሲያገለግል የቆየ ክፍል ውስጥ ሰሞኑን አንድ ረዳት ሳጅን ራሱን ሰቅሎ እንደተገኘ ምንጮች ገለፁ፡፡ ንብረትነቱ የቀበሌ በሆነው መፀዳጃ ቤት ውስጥ ስድስት ግለሰቦች ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው ሦስቱ ሲሞቱ ሦስቱ ተርፈዋል፡፡ ወላጅ እናቱን በሞት ካጣ በኋላ በመንፈስ ጭንቀት ይሰቃይ የነበረው የ14 ዓመቱ ታዳጊ በ1999 ዓ.ም በዚህ መፀዳጃ ክፍል ውስጥ ራሱን እንዳጠፋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ነዋሪዎች በወቅቱ መፀዳጃው ቤት እንዲፈርስ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡
ሆኖም መፀዳጃ ክፍሉ ሳይፈርስ የታዳጊው አጎት እራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው ሠዎች ደርሠው አትርፈዋቸዋል፡፡ አንዲት ሴትም እራሷን ለማጥፋት ሞክራ በሠዎች እርዳታ ተርፋለች፡፡ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ እንዲሁ በዚሁ መፀዳጃ ቤት ውስጥ እራሱን ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡ እነዚህ ግለሠቦች በሌሎች መፀዳጃ ቤቶች ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው አግዳሚ እንጨቶቹ የበሠበሱ በመሆናቸው ሳይሳካላቸው እየቀረ ወደዚህ መፀዳጃ ክፍል እንደሚመጡ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረው የ18 ዓመት ወጣት በዚሁ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ራሱን አጥፍቶ እንደተገኘ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
በሁኔታው የተማረሩ ነዋሪዎች መፀዳጃ ክፍሉን ለማፍረስ ሙከራ አድርገው የነበረ ቢሆንም ተጠቃሚው በርካታ በመሆኑና ሌላ አማራጭ ስለሌለ ሳይፈርስ ቀርቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ አንድ ረዳት ሳጅን በተመሳሳይ ሁኔታ ራሱን ሰቅሎ ተገኝቷል፡፡ ወጣቱ በ2000 ዓ.ም ፖሊስ ለመሆን ስልጠና በመውሰድ ላይ ሳለ ባጋጠመው የአዕምሮ ህመም ምክንያት ሥልጠናውን አቋርጦ ወደ ቤተሠቦቹ ተመልሶ ነበር፡፡ አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ በተደረገለት ህክምና ካገገመ በኋላ ለተጨማሪ ህክምና በፖሊስ ሆስፒታል ሳለ ከሆስፒታሉ ህንፃ ላይ እራሱን ቢፈጠፍጥም ህይወቱ ተርፏል፡፡ ተመልሶ ወደ ማሠልጠኛው ገብቶም ስልጠናውን ጨርሶ ወደ ስራ የተሠማራው ወጣቱ፤ ለሦስት አመታት በሙያው ሲሠራ የቆየ ሲሆን ባለፈው ሳምንት እናቱ ቤት ምሳውን ከበላ በኋላ እናቱ ወደ ለቅሶ ቤት ሲሄዱለት ወደ መፀዳጃ ቤቱ በመሄድ ህይወቱን አጥፍቷል፡፡ በክስተቱ የተበሳጨ አንድ የአካባቢው ወጣት የመፀዳጃ ቤቱን በር በንዴት የገነጠለው ሲሆን ነዋሪዎች ለሚመለከተው ክፍል ችግሩን በመጠቆም መፍትሄ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ገልፀዋል፡፡
የሞተበት ሲላጭ፤ ያልሞተበት ቅቤ ይቀባል (የጉራጌ ተረት)
ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ከአንድ ውጊያ ድል በኋላ፤ እስቲ ያሳለፍነውን ጦርነት እንዴት እንዳሸነፍ እንመርምር ይባባላሉ፡፡ ነብር - “የእኔ መኖር ነው ዋናው፡፡ የእኔ ፍጥነት ጠላቶቻቸውን አደነጋግሩዋቸዋል” አለ፡፡ ዝሆን - “የእኔ ግዙፍነት ጠላቶቻችንን ብርክ አሲዞዋቸው እንደነበር ሁላችሁም ምስክር ናችሁ” አለ፡፡ ዝንጀሮ - “እኔ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በየዛፉ ላይ እየተንጠላጠልኩ ‘ወዮላችሁ! የአያ አንበሶ ጦር ዶጋመድ ሊያደርጋችሁ እየመጣ ነው’ ስላቸው ጫካውን እየለቀቁ ሲፈረጥጡ አይታችኋል፡፡
‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ የሚባለው ዕውነት መሆኑን ታዝባችኋል፤” አለ፡፡ አጋዘን - “እኔ በስንቅ፣ በትጥቅና በንብረት ጥበቃ ማገልገሌን መቼም አትክዱም፡፡ ዞሮ ዞሮ ዋናው ሁላችንም የአያ አንበሶ ምልምሎች መሆናችን ነው፡፡ ያ መቼም አሌ አይባልም፡፡ ሁላችንንም የረዳን የሳቸው አቅምና ዝና ነው፡፡ ድሉም የእሳቸው ውጤት ነው” አለና ተቀመጠ፡፡ ሁሉም በተራ በተራ ዘራፍ እያሉ ራሳቸውን እያደነቁ ተቀመጡ፡፡
በመጨረሻ ጦጢት ተነስታ፤ “እኔ ግን በመጠኑ ቅር ብሎኛል” አለች “ለምን? ምክንያትሽን አስረጂና?” ተባለች፡፡ ጦጢትም እንዴት ስሜቷን ተቆጣጥራ እንደምትናገር በማስላት፤ ድምፁዋን አጠራችና፤ “ጌቶቼ! ወንድሞቼ! እህቶቼ! ጠላቶቻችንን በወኔ መደምሰሳችን እርግጥ ነው እጅግ አስደሳች ነገር ነው፡፡ ዕድሜ ለጀግናው መሪያችን፤ በማያወላውል ሁኔታ ድል መትተናቸዋል!! የሚቀጥለውንም ውጊያ እንደምናሸንፍ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ሆኖም ከእኛ ጋር ሊሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ከጠላት ጋር ደርበን ማጥፋት ያለወገን ያስቀረናል፤ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እና እንደምታውቁት በሌሎች ደኖች ደግሞ እኛን ለማጥቃት ጊዜ የሚጠብቁ በርካቶች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ዓለም ተገለባባጭ ነው፡፡ አሮጌው ይሄድና አዲሱ ይተካል፡፡ እኛ ሄደን ተተኪው ይመጣል፡፡
ስለዚህ እንዳለፈው ጊዜ ስለጦርነቱ እንኳ የሚያወራ አንድ አውሬ ሳናስቀር ሁሉንም መደምሰሱ፣ ነገ ይህን ጫካ ለቅቀን ስንሄድ ወሬ ነጋሪ እንኳ እንዳይቀር ያደርጋል፡፡ ከጠላትም ለዓይነት አንዳንድ ብናስተርፍ ይሻላል፡፡ ደሞም እንደኛ ሊያስብ የሚችለውን ብንለይና አብረን ብንጓዝ ጥሩ ነው”፡፡ ሁሉም “ጦጢት ውነቷን ነው” አሉ፡፡ *** ሁሉንም ጠራርጌ አጥፍቼ እኔ ብቻ ልቅር ማለት ጐጂ እንደሆነ እናስተውል፡፡ ሁሉን እንደመስሳለን፤ ሁሉን ድባቅ እንመታለን ያሉ ከሂትለር እስከ ፒኖቼ Apre moi le deluge (እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል) ካለው የፈረንሳዩ ሉዊ፤ ከቦልሼቪክ ደበኞች፣ በሴራ ተተኪ ነን እስካሉት እስከ “ጋንግ ኦፍ ፎር” በየዘመኑ ገነው ሲጠፉ አይተናል፡፡ ማንም ፊቴ አይቆምም የሚለው የሞንጐሊያዊው ጄንጂስ ካን ታሪክ መልካም ምሳሌ ይሆነናል፡፡ ሞንጐሊያውያን ቻይናን በወረሩ ሰዓት፤ ጄንጂስ ካን የተባለው መሪያቸው አሸንፎ ቻይና ሲገባ፣ ይቺ አገር ለምንም አትሆንም ብሎ ከማሰብ ተነስቶ “ለፈረሴ እንኳን ለግጦሽ መሬት የሌላት አገር ናት ቻይና፡፡
ድምጥማጧን ማጥፋት አለብኝ” አለ፡፡ “ለምን ታጠፋታለህ?” ሲባል፤ “እነዚህን ቻይናውያን ከምድረ - ገጽ አጥፍቼ መሬታቸው ላይ ለፈረሴ የግጦሽ ሣር ባበቅል ይሻላል” አለ፡፡ ይሄኔ አንድ ቹ ሴይ የሚባል ብልህ ሰው፤ እንደምንም ተጣጥሮ የጄንጂስ ካን አማካሪ ሆኖ ነበርና፤ “ቻይናን ከምታጠፋት እያንዳንዱ ቻይናዊ ቀረጥ እንዲከፍል ብታደርግ ብዙ ገንዘብ ልታገኝ ትችላለህ” አለው፡፡ ጄንጂስ ካን በምክሩ ተስማማ፡፡ ቀጥሎ ግን አንዲት ካይ ፌንግ የምትባል ከተማ ወርሮ ሊያወድም ፈለገ፡፡ አማካሪው ቹ ሴይ፤ “ጄንጂስ ካን ሆይ! የቻይና ጠበብት ሁሉ መሀንዲሶቹ፣ ሐኪሞቹ፣ ባለ እጆቹ … ሌሎች ከተሞቻቸው ሲወረሩ የመጡት ወደዚች ከተማ ነው፡፡ ከተማይቱን ከማጥፋት ለምን በባለሙያዎቹ አትጠቀምባቸውም” ሲል መከረው፡፡ ጄንጂስ ካን ምክሩን ተቀበለ፡፡ መንገዶች ተሠሩ፡፡ ህንፃዎች ተገነቡ፡፡ ሆስፒታሎች ተቋቋሙ፡፡ “ሰዎችን የሚነዳቸው የግል ፍላጐት ነው፡፡ ይህንን ፍላጐት ለማሳካት የሚያረጉትን ጥረት በማየትና በዘዴ በማግባባት አገር ልታድን ትችላለህ” ይላል ቹ ሴይ፡፡ ችግሩ የሚመጣው ምክር የማይሰሙ መሪዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ሰው ቀረጥ እንዲከፍል አድርግ ሲባል በአንድ ጀንበር ሱሪ ባንገት አውልቅ ልበል ያለ እንደሆን ነው፡፡ የግል ፍላጐታቸው የአገር ካዝና የሚያራቁት ከሆነ፣ ሙስናው ካጠጠና የዚህ መሸፈኛ ደግሞ “እኔ ብቻ ነኝ” የሚያስችል ሥልጣን ከሆነ አገር አለቀች፡፡
ከዚህ ቀደም ለዚች አገር ህልውና ሲባል መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ዛሬም ነገም ይከፈላል፡፡ መስዋዕትነቱ የተከፈለው ተወዶ፣ ለውጥ በማምጣት ታምኖ፣ ከልብ ታግሎ ነበር፡፡ የተቀደሰ መስዋዕትነት የሚባለውም ያ ነው፡፡ አግባብ ነው፡፡ አግባብ የማይሆነው ተገዶ፣ ሳያስቡና ሳያልሙ፣ ምናልባትም ለምን እንደሆነ ሳያውቁ መስዋዕትነት መክፈል የሆነ እንደሆነ ነው፡፡ ህዝብ ማናቸውም ነገር ለምን እንደሚከናወን የማወቅ፣ መረጃ የማግኘት መብት አለው፡፡ ያ ካልተከበረለት በገዛ አገሩ ባይተዋር፣ በገዛ ቤቱ እንግዳ ይሆናል፡፡
“ሁሉም ነገር ለጽድቅ ነው - ዝም በል” ሲባል አሜን ካለ፤ የአቦ - ሰጡኝ መስዋዕትነት ከፈለ ማለት ነው፡፡ ለልጁ፣ ለትውልዱ የሚያስተላልፈው የመረጃ ቅርስ ሳይኖረው፣ በሕግ አምላክ የሚልበት ልሣን ሳይኖረው፣ አንዲት የሰለጠነች አገር እየተመኘ ካለፈ፤ ለአገርም ለታሪክም ደግ አይሆንም፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ስለሌለውም “ይሄ አይሆንም” ብሎ ሽንጡን ገትሮ፣ ታግሎ የሚያታግለው የለምና፣ ውሎ አድሮ፤ ሁሉንም እየተካሄደ ያለውን ነገር “ይሁን ግዴለም ለበጐ ነው!” የሚልና “ለምን ይሆናል?” ብሎ የማይጠይቅ ህዝብ ይፈጠራል፡፡ ይሄ አደጋ ነው! አንዱ ከአገር ጋር ሲያለቅስና አገር እንዴት ላድን ሲል፤ ሌለው አገር የሚገድል ከሆነ፤ ገጣሚው “..ዘመንና ዘመን እየተባረረ ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ” እንዳለው ሊሆን ነው፡፡ የመተካካት ዘመን የራሱ አባዜ አለው፤ ሁሉም እኩል ካልተሳሰበ ግን “የሞተበት ሲላጭ፣ ያልሞተበት ቅቤ ይቀባል” የሚለው የጉራጌ ተረት ዓይነት ይሆናል፡፡ ከዚያ ይሰውረን፡፡
ኮፍያው
ነገሩ የተጀመረው በኮፍያ ነው - ለምሳ ቤት መጥቶ ሲወጣ፣ በሩ አካባቢ ባገኘው ኮፍያ - ጥልፍልፍ የቴኒስ መጫወቻ (የራኬት) ምስል በላዩ ላይ ያለበት ኮፍያ፡፡ ኮፍያውን አንስቶ መኪናው ውስጥ ከተተውና ወጣ፡፡ ወደ ቢሮው ከገባ በኋላ የኮፍያውን ነገር ሊረሳው አልቻለም፡፡ “የማን ኮፍያ ነው?” የሚል ጥያቄ በአእምሮው ውስጥ አንቃጨለ፡፡ “አንድ ወንድ ጥሎት የሄደው ነው” … የሚል ምላሽ ከአእምሮው ስርቻ መልሶ አስተጋባ፡፡ ሀሳቡን ለማባረር ራሱን በሥራ ለመጥመድ ሞከረና አቃተው፡፡ ሥራ መሥራት ሲያቅተው ወደ ሚስቱ ደወለ፡፡ ሚስቱ፣ ቤት ነው የምትውለው፡፡ ከተጋቡ ገና አራት ወራቸው ነው፡፡ ስሟ ሶፊ ቢሆንም “ምጥን!” ይላታል፤ ሲያቆላምጣት - በዚህ አጠራሩ እሷ ባትስማማም፡፡ ምጥን ያለች ናት፤ አይኗ የተመጠነ፣ እጆቿ የተመጠኑ ውበቷ የተመጠነ፡፡ ትርፍ የሚባል ነገር የላትም፡፡ ጥርሷ ያምራል ግን ትንሽ አፍንጫዋ … የሚሏት አይነት አይደለችም፡፡ ሁሉ ነገሯ ያምራል፡፡
ስልኩን አነሳች፡፡ ትንሽ አወሩ፡፡ “ዛሬ፣ ቤት ማን መጥቶ ነበር?” አላት ባለቤቷ አበራ - እንደዘበት፡፡ ለአፍታ ዝም አለች፡፡ “ዛሬ … ዛሬ … ማንም አልመጣም … እኔ ምልህ …” ብላ ወደ ሌላ ወሬ አመራች፡፡ “ኮፍያው የማን ነው?” ሊላት ፈለገ፤ ግን ቃላቱ ከአንደበቱ ሊወጡለት አልቻሉም፡፡ እየዋሸችኝ ነው? ለምን ትዋሸኛለች? ሰውነቱን አንዳች ነገር ሲወረው ተሰማው፡፡ ትንሽ አውርተው ስልኩ ተዘጋ፡፡ ቢሮው ውስጥ እንዳለ ፈዞ ቆመ፡፡ እሱና እሷ ብቻ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ አንድ ኮፍያ እንዴት ሊገኝ ይችላል? ኮፍያ መቼም እግር የለው፣ የሰው ግቢ ውስጥ ዘሎ የሚገባው! የአንድ ሰው … የአንድ ወንድ ጭንቅላት ላይ ሆኖ መግባት አለበት ወደ ግቢው፡፡ ያንን ኮፍያ ያደረገው ጭንቅላት የማነው? የብዙ ሰዎች ምክር በአእምሮው መጣ፡፡ ለምን አታገባም? በልጅነትህ እናትህ አንተን እና አባትህ ጥላችሁ ስለሔደች ነው? እናትህ ምን አይነት ጨካኝ ብትሆን ነው በገዛ ጓደኛው አባትህን ከድታው የሄደችው? አባትህ ግን ምን አይነት ሞኝ ቢሆን ነው? እድሜ ዘመኑን ሲሰማው የነበረ ንግግር፣ ምክር እና ጥያቄ፡፡
በመጨረሻ ሶፊን ሲያገኝ የሴት ጥላቻው እንደጉም በኖ፣ ትዳር መያዙን የሰሙ ሁሉ ማመን አልቻሉም ነበር፡፡ “ምን አስነክታው ነው?!” ብለው ነበር ያዳነቁት፡፡ ከሶፊ ጋር በትዳር ሲኖሩ ለጥርጣሬ የሚያበቃ አንዳችም ድርጊት አይቶባት አያውቅም፡፡ ሁሌም ግን እንደሰለላት ነው፡፡ … ሁሌም አይኖቹ ለጥርጣሬ የሚሆን ነገር ለማግኘት በንቃት ይቃብዛሉ፡፡ ሶፊ ላይ ግን ምንም ነገር አግኝቶ አያውቅም - ኮፍያውን ግቢው ውስጥ ወድቆ እስኪያገኝ ድረስ፡፡ ኮፍያውን ካገኘ በኋላ ነው ስጋት እንደደራሽ ያዋከበው - የፈራው ደርሶ በነፍሰ ስጋው እየተጫወተች እንዳይሆን ሰጋ፡፡ ምን ነበር አባቱ የሚለው? “አጥንት ቢሰበር ወጌሻ ይጠግነዋል፡፡ የተሰበረን ልብ ግን ከሞት በቀር የሚያድነው የለም! በተለይ በሴት የተሰበረ ልብ …” ነበር የሚለው፡፡ ልቡ በሴት እንዳይሰበር ስንት አመት ነበር የተጠነቀቀው? እናቱ ከውሽማዋ ጋር ስትሔድ የአባቱ ብቻ ሳይሆን የእሱም ልብ ነበር የታመመው፡፡ ስቃዩን ያውቀዋል! እና ሶፊ … ከቢሮው ተስፈንጥሮ ወጣና ሲበር ወደ መኪናው ሔዶ ኮፍያውን አወጣው፡፡ የማን ኮፍያ ነው!? ወደ አፍንጫው አስጠጋው፡፡ የወዝ ሽታ አፍንጫውን ሰነፈጠው፡፡ አሽቀንጥሮ ከጋቢናው ወንበር ላይ ጣለው፡፡
“ጎረምሳ ይሆናል፣ ወይ ደግሞ መላጣ! መላጣ ነው በዚህ የሙቀት ወር ኮፍያ የሚያደርገው - መላጣውን ለመሸፈን፡፡ ለዚህ ነው የኮፍያው አስቀያሚ የወዝ ሽታ ያልጠፋው፡፡ ከኔ ግን በምን አባቱ በልጦባት ነው?”… የኮፍያውን ባለቤት አሰበው፡፡ መላጣ … ምናልባትም ቴኒስ ተጫዋች፡፡ “ወይኔ!” ብሎ የመኪናውን ኮፈን በቡጢ ነረተው፡፡ “ቀደም ብዬ ለምሳ ቤት በመሔዴ ደርሼባቸው ያ መላጣ ተደናግጦ ይሆናል ኮፍያውን ጥሎ የፈረጠጠው፡፡ ይኼ መላጣ!” አለ በንዴት፡፡ “ግን ለምን መላጣ መረጠች? ስንት ባለጎፈሬ ሞልቶላት! ምናልባትም እኮ መላጣነቱን ይሆናል የወደደችው!” በሆዱ ወፈ ሰማይ ጥያቄ ፈለፈለ፡፡ ለሶስት ቀን እያደባ፣ ሰአት እየቀያየረ ባለኮፍያውን በአሳቻ ሰአት ሊያጠምደው ሞከረ፤ አልቻለም! ሌሊት እየተነሳ ከቤቱ ጓሮ ዞሮ አካባቢውን መረመረ፡፡ መላጣው ሰውዬ አጥር እየዘለለ ሊሆን ይችላል የሚገባው፡፡ የአጥር ጥግ ሁሉ አሰሰ - አንድም ዱካ የለም፡፡ “መላጣ ሰው እንዴት እንደምጠላ!” … ሰው መሰላችሁ!?” ይል ጀመር ለጓደኞቹ፡፡ ጓደኞቹ የጋራ አለቃቸውን በሾርኒ እያማው ስለሚመስላቸው ይስቃሉ፡፡
አለቃቸው መላጣ ነው፡፡ “ከአስር መላጣ አንድ ሾጣጣ!” አለ አንድ ቀን አፉ እንዳመጣለት፡፡ መላጣና ሾጣጣ ምን እንደሚያገናኛቸው ጓደኞቹ አልጠየቁትም - ዝም ብለው ሳቁ የጋራ አለቃቸውን እያሰቡ፡፡ በነጋታው አለቃው ጉዳዩን ሰምቶ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጠው፡፡ መላጦችን የሚጠላበት አንድ ተጨማሪ ምክንያት አገኘ፡፡ ከሶስት ቀን በኋላ ሚስቱ በእንቅልፍ ልቧ ስትዘባርቅ ሊሰማት ወስኖ ለተከታታይ ሁለት ቀናት አጠገቧ ተገትሮ አደረ፡፡ በሁለተኛው ቀን አጠገቧ እንደቆመ ነቃች፡፡ “ምነው!” አለችው በእጁ የያዘውን አውራ ጣቷን እያየች፡፡ ደንግጦ ለቀቃት፡፡
“አውራ ጣቱን የተያዘ ሰው፣ ሲያዝ ቀን የሰራው ይዘከዝካል” ብለው ሰዎች እንደመከሩት አልነገራትም፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በአምስተኛው ቀን፡ ከአምስት ቀን በኋላ ለምሳ መጥቶ ማዕድ ቀርቦ እየበሉ ሳለ ጥያቄ አነሳላት፡፡ “ስለ መላጣ ሰው ምን አስተያየት አለሽ?” አላት እንደዘበት፡፡ ጥያቄው ግራ ያጋባት ይመስል አይኗን እያስለመለመች አየችው፡፡ “ስለመላጣ ነው ስለሰላጣ?” … ጠየቀችው ለምሳ የቀረበውን ሰላጣ እያየች፡፡ “ስለ መ.ላ.ጣ?... ማለቴ እኔ አሁን መላጣ ሰዎችን እጠላለሁ…” አላት ሳቀች፡፡ “እኔ ደሞ መላጣ ሰው እወዳለሁ! አባቴ እኮ መላጣ ነበር፡፡ አንተም ቶሎ ብትመለጥ ደስ ይለኛል፡፡ የመላጣው ሰውዬ ባለቤት ብባል ደስ ይለኛል … ኸኸኸኸኸኸኸኸኸኸኸ” አስረዝማ ሳቀች ሶፊ፡፡ “እና አባትሽን እንዲያስታውስልሽ ነው መላጣ የጠበስሽው?” በሆዱ አጎረምርሞ ዝም አለ፡፡ ያ መላጣ እዚሁ ሰፈር ውስጥ ይሆናል እኮ የሚኖረው! ጎረቤቶቹን አሰባቸው፡፡
መላጣ ከመካከላቸው አለ እንዴ? ከቤታቸው ፊት ለፊት ያሉትን ሰውዬ አሰባቸው፡፡ እሳተ ጎመራ እንደቦደሰው ተራራ፣ መሀል አናታቸው ላይ ብቻ ነው ጸጉር የሌለው፡፡ እሳቸው ደሞ ኮፍያ አያደርጉም! ሌሎቹ ጎረቤቶቹ ደሞ አርቴፊሻል ፀጉር ካልተጠቀሙ በስተቀር ከመከም ጎፈሬ ናቸው፡፡ ቴኒስ የሚጫወት ከመካከላቸው አሰበ፤ ማንም ሊመጣለት አልቻለም፡፡ ጎረቤቶቹ ከሜዳ ቴኒስ ይልቅ ለፈረስ ጉግስ የቀረቡ ናቸው፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በስድስተኛው ቀን፡ ፀጉር ቤት ሔዶ “አንድ ዘመድ ሞቶብኛል!” ብሎ ፀጉሩን ተላጨ፡፡ መላጣ ሆኖ የዛን ቀን ወደቤት ቢገባም ሚስቱ ሶፊ ግን የተለየ ስሜት አልሰጣትም፡፡ “እሷ የምትወደው የተፈጥሮውን ራሰ በራ ይሆናል!” ብሎ ተናዶ ራቱን ሳይበላ ተኛ፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በሰባተኛው ቀን፡ ጓደኛውን ማትያስን ደውሎ ጠራው፡፡ ከሶፊ ጋር ሲጋቡ አንደኛ ሚዜው ነበር፡፡ ራሰ በራ ባይሆንም በቅርቡ ራሰ በረሀ የመሆን እድል አለው ሲል አሰበ፡፡ ራሰ በራ በሆነ ሰው ብቻ ሳይሆን በእጩ ራሰ-በራዎች መቅናት ጀምሯል፡፡ “ማቲያስ እንቢ የማትለኝ አንድ ነገር እንድታደርግልኝ እፈልጋለሁ!” ብሎ እግሩ ስር ወደቀ፡፡ ማቲያስን በግድ እሺ ካሰኘ በኋላ ከእግሩ ስር ተነሳ፡፡ “ሚስቴን ላምናት አልቻልኩም፡፡ በኔ ላይ የደረበችብኝ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍንጭ አግኝቻለሁ፡፡ ሰውዬው መላጣ ይመስለኛል…” ብሎ ስለኮፍያው ነገረው፡፡ “እና አንተ ሌላ ፍላጐት እንዳለው ሰው ሆነህ ቅረባት፡፡ ማለቴ… በቃ ልታወጣት እንደምትፈልግ…” አለው ማትያስን በመለማመጥ፡፡
ማትያስ በንዴት ጥሎት ሄደ! ኮፍያውን ባገኘ በስምንተኛው ቀን፡ ማትያስን አፈላልጐ አገኘው፡፡ እንባ አውጥቶ ለመነው፡፡ “የአባቴን ቁስል እያወክ!” በግድ…በግድ አሳመነው፡፡ እቅድ ነደፉ፡፡ እሱ ለመስክ ሥራ እወጣለሁ ብሎ ሊሄድ፤ ማትያስ ደሞ የእሱን መውጣት ተከትሎ እሷን ሊፈታተን፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በሃያኛው ቀን፡ ማትያስ “ዝም ብለህ ነው! ሚስትህ ንፁህ ናት! ይኸው ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ እቤታችሁ እያመሸሁ ተፈታተንኳት፡፡ እሷ ግን እንዴት ክብሯን የምትጠብቅ መሰለችህ?” አበራ፤ “አይምሰልህ ሴቶችን አንተ ስለማታውቃቸው ነው፡፡ ውጪ ራት ጋብዛት፡፡ ለኔ እንዳትነግረኝ አደራ ብለህ ንገራት!” ኮፍያውን ባገኘ በሃያ ስድስተኛው ቀን፡ ሶፊ ስልክ ደውላ “አቤ…ቆየህ እኮ በጣም… ዛሬ ጓደኛህ ማትያስ ራት እንብላ አለኝ፡፡
እኔ ግን ደስ አላለኝም፡፡ አበራ ልቡ እየመታ “ሶፊ ደሞ ምን ማለትሽ ነው? ማትያስ ማለት እኔ ማለት ነው እያልኩሽ፡፡ እራት በልታችሁ መመለስ ነው፡፡ ምን ችግር አለው?…” ነዘነዛት፡፡ ተስማማች፡፡ ኮፍያውን ባገኘ በሃያ ሰባተኛው ቀን፡ ማትያስ፣ “አበራ ሚስትህ በጣም ታማኝ ናት! አንተ በሰጠኸኝ ገንዘብ እራት ጋብዣት እስከ ስምንት ሰአት ድረስ አብረን አመሸን፡፡ ግን… እኔንጃ በህይወቷ ሙሉ እንዳንተ የምትወደው ሰው እንደሌለ አረጋግጫሁ!” አበራ ንድድ አለው፡፡ በቃ የሴቶችን ልብ ማግኘት ከባድ ነው ማለት ነው? አባቱም እናቱን ታማኝ ናት ብሎ በደመደመበት ሰአት ነበር ጥላው የጠፋችው፡፡ አእምሮው የእናቱን ድርጊት እንደፊልም ማጠንጠን ጀመረ፡፡ ሶፊማ በፍፁም ልታታልለኝ አትችልም! “እና ካሁን በኋላ ተልእኮዬን ጨርሻለሁ?” አለ ማትያስ፡፡
“አንድ የመጨረሻ እድል ማቲ…” ለመነው ኮፍያውን ባገኘ በሃያ ስምንተኛው ቀን፡ ማትያስ ሶፊ ቤት ሲጫወት አመሸ - የሰአቱ መንጐድ እንዳልተገነዘበ መስሎ፡፡ እኩለ ሌሊት ተጠጋ፡፡ በቤቱ ወስጥ እሱና ሶፊ ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ በጣም መምሸቱን ሲያረጋግጥ “በጣም ስለመሸ እዚሁ ባድር…” የሚል ሰበብ አቀረበ፡፡ ኮፍያውን ባገኘ ሃያ ዘጠነኛው ቀን፡ አበራ ራሱ ለማትያስ ደወለ፡፡ “እሺ?” አለ አበራ “ምን እሺ አለ?” ማትያስ ቀዝቀዝ አለ፡፡ የሆነ ነገር ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ አበራ ልቡ መታ፡፡ በአንድ በኩል ሚስቱ ስታታልለው ስለያዛት ደስታ፣ በሌላ በኩል ክህደቷ እንደወላፈን ገረፈው፡፡ “እኔ እኮ ነግሬሃለሁ! ሴቶች ከሀዲ ናቸው! ያ መላጣን ማውጣቷ ሳያንስ አንተንም! የማላውቃቸውን ስንት ወንዶች… ስንት ወንዶች…” የአበራ ድምፅ በለቅሶ ሻከረ፡፡ “ባክህ ዝም በል! ምንም የሆነ ነገር የለም! ትላንትና ማታ ሚስትህ ባለጌ ብሆንባትም አክብራ ሶፋ ላይ አስተኝታ፣ መኝታ ቤቷን ቆልፋ ነው የተኛችው!” ማትያስ ስልኩን ጆሮው ላይ ዘጋው፡፡ አበራ እልህ በልቡ ተንተከተከ፡፡
ከማትያስ ጋር እንደተመሳጠሩ ወይ ጠርጥራ በነፍሰ ስጋው እየተጫወተች ነው እንጂ… አእምሮው ውስጥ ያሉ ድምፆች አስተጋቡ - “የሴቶችን ልብ ማመን አትችልም! ልባቸውን ወንድ ያኘዋል ማለት ዘበት!” ሲፈራ ሲቸር ማቲያስ ጋር ደወለ፡፡ ያሳለፈውን ህይወት እየተረከ ማትያስ እንዳያዝንለት አደረገ፡፡ ማትያስ በጣም ተጨነቀ፡፡ “እሺ አሁን ምን አድርግ ነው የምትለኝ?” “ሚስቴን ማመን እፈልጋለሁ! ያን ለማድረግ የመጨረሻ! የመጨረሻ! አንድ ነገር ብቻ ተባበረኝ! ከዛ በኋላ አላስቸግርህም ማትያስ አማራጭ አልነበረውም “የተቆለፈ ልብ በአልኮል ይከፈታል! ያኔ የተደበቀ ማንነት ይወጣል!” አለ አበራ ኮፍያውን ባገኘ በሰላሳኛው ቀን፡ ማትያስ ሁለት ሰአት ላይ ወደ ሶፊ መጣ፡፡ ራት በልተው ሲጨርሱ ይዞ የመጣውን ሻምፓኝ ከፈተ፡፡
ሶፊ አልጠጣም አሻፈረኝ አለች፡፡ ማትያስ ለአበራ ደውሎ ነገረው፡፡ አበራ ለሶፊ መልሶ ደወለ “ሶፊዬ ማትያስ ማለት እኔ ማለት ነው፡፡ እሱ እኮ ብቸኝነት እንዳይሰማሽ ነው፡፡ ለኔ ስትይ እሺ በይው…” ለመናት፡፡ ሶፊ አንደኛውን የሻምፓኝ ብርጭቆ ተቀብላ ተጐነጨች… ደገመች… ኮፍያውን ባገኘ ሰላሳ አንደኛው ቀን ጠዋት፡ አበራ ጠዋት ወደ ቤቱ መጣ፡፡ በሩን ከፍቶ ሊገባ ሲል የግቢውን ቆሻሻ የሚደፋው ልጅ ከበሩ መግቢያ ላይ አገኘው፡፡ እድሜው ከዘጠኝ አመት አይበልጥም፡፡ “ጋሼ፤ ቆሻሻ አለ?” “የለም!” ብሎት አልፎት ሊገባ ሲል፣ ልጁ እየተቅለሰለሰ ጠጋ አለው፡፡” “ጋሼ ይቅርታ! ባለፈው ቆሻሻ ልወስድ ስገባ ያቺን ኬፕ… ማለቴ ኮፍያ ግቢ ውስጥ ረስቻት ወጣሁ፡፡
ባለፈው መኪና ውስጥ አይቻት ልጠይቅዎት ስል ሄዱ፡፡ በኋላ ፊልድ ሄደዋል አሉኝ…” አበራ አናቱን በዱላ የተመታ ያህል ደነገጠ፡፡ “ያንተ ነው?” አለ ልጁ ላይ እያፈጠጠ፡፡ ልጁ በድንጋጤ እንደተዋጠ ጭንቅላቱን ላይ ታች ወዘወዘ፡፡ “እና መላጣ ምናምን ስል የበረው በራሴ ፈጥሬ ነው?” አለ አበራ ሳይታወቀው እየጮኸ “ምናሉኝ ጋሼ?” ልጁ ግራ ተጋብቶ ጠየቀው፡፡ ልጁን ችላ ብሎ ወደ ግቢው ሲገባ ማትያስ አይኑ እንደቀላ ወደ በሩ ሲመጣ አየው፡፡ ቆሞ ጠበቀው፡፡ “ያው ደስ ይበልህ! ያሰብከው ሁሉ ሆነልህ! በመጠጥ አደንዝዘህ የምትፈልገውን ፈፅመናል!...” ማትያስ በንዴት ባሩድ የተቃጠሉ ቃላቶቹን እንደጥይት ተኮሳቸው፡፡ “ከሌላ ወንድ ጋር እስክታያት መቼም ቢሆን አርፈህ እንደማትቀመጥ እርግጠኛ ነበርኩ! ሚስት ያገባነው ለበቀል ነበር!” ብሎት ሄደ፡፡
ሚስቱን እጅ ከፍንጅ በመያዙ እርካታን ጠብቆ ነበር፡፡ እርካታ የለም! ፈፅሞ እርካታ ውስጡ የለም! ንፁህነቷ እየጐላ የእሱ መሰሪነት እየገዘፈ መጣበት፡፡ ቤት ሲገባ የሶፊ ሻንጣ ለጉዞ ተዘጋጅቶ ተቀምጧል፡፡ አንገቷን ደፍታ ከሶፋው ላይ ተቀምጣለች፡፡ ቀጭን እንባ በፊቷ ላይ ይወርዳል፡፡ በቆመበት ቁልቁል አያት! መግቢያ ቀዳዳ አጥታ ስትሽቆጠቆጥ በእርካታ ተሞልቶ እንደሚያስተውላት ነበር ያሰበው፡፡ መሳሳቱ ወለል ብሎ ታየው! እንደ አልማዝ የጠነከረ ታማኝነቷን እሳት ሆኖ ማቅለጥ ቢያቅተው፤ በውሃ ሸርሽሮ በድን አካሏ ቃል ኪዳን እንዲሰብር ማድረጉ መልሶ አንገበገበው…
ዋልያዎቹ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ዜብራዎቹን ይገጥማሉ
በ2014 እኤአ ላይ በብራዚል ለሚካሄደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቦትስዋና ሊገናኙ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው መደበኛ ልምምዱን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሲጀምር የግብ አዳኝ ሰላዲን ሰይድ ተቀላቅሎታል፡፡የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ በአፍሪካ ዞን በ10 ምድቦች በሁለት ዙር ግጥሚያዎች 40 ግጥሚያዎች ተደርገው 83 ጎሎች ከመረብ ያረፉ ሲሆን በ3 ግቦቹ የማጣርያው ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የሚመራው ኢትዮጵያዊው ሳላዲን ሰኢድ ነው፡፡ ሳላዲን ሰኢድ በዓለም ዋንጫው የምድብ መማጣርያ ሁለት ጎሎችን በመካከለኛው አፍሪካ ላይ 1 ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ላይ እንዳገባ ይታወሳል፡፡
ዋልያዎቹ እና መሪነታቸው በምድብ ማጣርያው መልካም አጀማመር ያሳየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያስፈልገውን ትኩረት ተነፍጎ ከያዘው ወርቃማ እድል እንዳይሰናከል መታሰብ ይኖርበታል፡፡ ዋልያዎቹ ዝግጅታቸውን ከ3 ሳምንታት ቀደም ብሎ ለመስራት ታቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም ለብሄራዊ ቡድኑ ከተመረጡ ተጨዋቾች ብዙዎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስና የደደቢት ተጨዋቾች በመሆናቸውና ሁለቱ ክለቦች በአህጉራዊ የክለብ ውድድሮች በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት ሙሉ ቡድኑን ለመሰብሰብ ባለመቻሉ የዝግጅት ጊዜው እንዲያጥር አስገድዷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫው በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ 1 መሪነቱን እንደያዘ ነው፡፡ ነገ ቦትስዋናን በሜዳው የሚያስተናግደው ደግሞ መሪነቱን ለማስጠበቅ ነው፡፡
ሌሎቹ የምድብ አንድ ተፋላሚዎች ደቡብ አፍሪካ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ በሶስተኛው ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታቸው ኬፕታውን ላይ ይገናኛሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካ፤ ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ የሚገኙበትን ምድብ 1 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁለት ጨዋታዎች በሰበሰበው አራት ነጥብና ሁለት የግብ ክፍያ እየመራ ነው፡፡ መካከለኛው አፍሪካ በ3 ነጥብ ሁለተኛ ፤ ደቡብ አፍሪካ በሁለት ነጥብ ሶስተኛ እንዲሁም ቦትስዋና በ1 ነጥብ የመጨረሻ ደረጃውን በቅደም ተከተል ይዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያው እዚህ አዲስ አበባ ላይ ከቦትስዋና አቻው ጋር ነገ የሚገናኝበት ግጥሚያ 3ኛው የምድብ ጨዋታ ነው፡፡ አራተኛው የምድቡን ጨዋታ ከዚህ ጨዋታ 10 ሳምንታት በኋላ ከሜዳው ውጭ በጋብሮኒ ቦትስዋናን መልሶ የሚገጥምበት ነው፡፡
በሳምንቱ ደግሞ በምድቡ አምስተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ለማድረግ ደቡብ አፍሪካን በሜዳው ያስተናግዳል፡፡ ከ6 ወራት በኋላ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር በሚያደርገው ስድስተኛው የምድብ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያው ሂደት የሚያበቃ ይሆናል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ አሁን በያዘው የመሪነት እድል እንዲጠቀም በሰፊ የዝግጅት እቅድ ፤ በተሟላ የፋይናንስ አቅም፤ በተጨዋቾቹ አጠቃላይ ደህንነት እና ጤና ላይ በሚደረግ ጥብቅ ክትትል እና ለውጤት በሚሰጡ የማበረታቻ ሽልማቶች መደገፍ ይኖርበታል፡፡ በየጊዜው በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ አቋሙን የሚፈትሽባቸው የወዳጅነት ጨዋታዎችንም በግድ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ስለ ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ተሳትፎ በቀረበ አሃዛዊ ዘገባ ብሄራዊ ቡድኑ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ሳይገጥመው፤ በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ሲወጣ በተጋጣሚዎቹ ላይ ስምንት ጎሎች አግብቶ የተቆጠረበት አንድ ብቻ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከስምንቱ ጎሎች አምስቱ በቅድመ ማጣርያው በሶማሊያ ላይ እንዲሁም በምድብ ማጣርያው ሁለቱ ጎሎች በመካከለኛው አፍሪካ ላይ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ዋልያዎቹ በሜዳቸው ሲጫወቱ ያገቧቸው ሲሆን ከሜዳ ውጭ በማጣርያው ለኢትዮጵያ የተመዘገበችው ጎል የምድብ ማጣርያው ሲጀመር ከደቡብ አፍሪካ ጋር አንድ እኩል አቻ በተለያዩ ጊዜ ነው፡፡ በ2014 ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ኢትዮጵያ ለሚኖራት ውጤታማነት ሁለቱ ቁልፍ ተጨዋቾች ሳላዲን ሰኢድ እና ኡመድ ኡክሪ እንደሆኑም የፊፋ ዘገባ ገልጿል፡፡ በዓለም ዋንጫው ማጣርያ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ በተደረጉት አራቱ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 24 ተጨዋቾች አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ በሁሉም አራት ግጥሚያዎች በቋሚ ተሰላፊነት 360 ደቂቃዎች ተሰልፈው ለመጫወት የበቁት አበባው ቡጣቆ እና የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ ብቻ ናቸው፡፡ አሉላ ግርማ 246 ደቂቃዎች፤ ስዩም ተስፋዬ 235 ደቂቃዎች ብርሃኑ ቦጋለ 188 ደቂቃዎች እንዲሁም መሱድ መሃመድ 154 ደቂቃዎችን እያንዳንዳቸው በሶስት ጨዋታዎች ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡
በምድብ 1 ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረጉ የመጀመርያዎቹ ሁለት ዙር ግጥሚያዎች ከፍተኛ ተመልካች ያገኘው ጨዋታ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ መካከለኛው አፍሪካን 2ለ0 ያሸነፈችበት ጨዋታ ሲሆን ግጥሚያውን በአዲስ አበባ ስታድዬም ከ20ሺ በላይ ተመልካች ታድሞታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ በሩስተንበርግ በሚገኘው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም አንድ እኩል አቻ የተለያዩበትን ጨዋታ 13611 ተመልካች ነበረው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያው በሚቀሩት 3 ጨዋታዎች ላይ ከፍተኛውን የነጥብ ውጤት ካስመዘገበ ወደ መጨረሻው የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ከሚደርሱት አስር ቡድኖች አንዱ ይሆናል፡፡ ካፍ በየምድባቸው መሪ ሆነው ለሚጨርሱት 10 ቡድኖች በሚያወጣው በደርሶ መልስ ግጥሚያዎች የሚገናኙት ቡድኖች ተለይተው ጥለው የሚያልፉት በ20ኛው የብራዚል ዋንጫ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፉ 5 ቡድኖች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ የዜብራዎቹ ተስፋ ዜብራዎቹ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ በቂ ዝግጅት አለማድረጉን ዋና አሰልጣኙ ስታንሊ ትሾስሳኔ ያማርራሉ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በዋና ከተማዋ ጋብሮኒ ከማላዊ ጋር የወዳጅነት አድርጓ 1ለ0 ያሸነፈው ቡድኑ ሰፋ ያለ ዝግጅት ባይኖረውም ከኢትዮጵያ በሚደረገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ወደ ብራዚል ለሚደረግ ጉዞ ወሳኝ እንደሆነ በማመን መስራቱን ሜሜጊ የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ ገልጿል፡፡
ባለፈው ሰሞን አሰልጣኙ ለብሄራዊ ቡድኑ በአገር ውስጥ ክለቦች የሚገኙ ተጨዋቾችን ጠርተው የካምፕ ዝግጅታቸውን ሲቲያሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሰልጣኙ አንዳንድ ክለቦች ተጨዋቾችን ለመልቀቅ በማመንታታቸው አሰልጣኙ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ብሄራዊ ቡድን ለማጠናከር ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነውን የ21 ዓመቱ ቦቢ ሽልንዴ ቡድናቸው ለማካተት ፍላጎት አሳይተው ተጨዋቹ የእንግሊዝ ፓስፖርት በመያዙ ያሰቡት ሁሉ እውን ሳይሆን መቅረቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የእንግሊዙ ኤፍሲ ዊምብልደን ክለብ ተጨዋች የሆነውን ቦቢ በቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ለመቀላቀል የተፈለገው በቡድኑ የፕሮፌሽናል ተጨዋች ልምድ ባለመኖሩ እንደሆነም ይገለፃል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ከባድ ግምት መሰጠቱን የገለፀው አንድ የአገሬው ጋዜጣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በካፍ ሻምፒዮስ ሊግ የማሊውን ዲጆሊባ 2ለ0 ካሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የተውጣጡ በርካታ ተጨዋቾች መያዙ ስጋት እንደሆነም አውስቷል፡፡ የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን አሉኝ የሚላቸውን ምርጥ ተጨዋቾች በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ለኢትዮጵያ ጨዋታ ማድረስ አልቻለም፡፡ ዋና አሰልጣኙ በተጨዋቾች ስብስባቸው በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ብዙም የተሳትፎ ልምድ የሌላቸውን ማብዛታቸው ደግሞ ተጨማሪ ጭንቀትን አምጥቶባቸዋል፡፡
ቦትስዋና በማጣርያ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በመጀመርያው ከሜዳዋ ውጭ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ 2ለ0 ተሸንፋ በሁለተኛው በሜዳዋ ከደቡብ አፍሪካ ጋር አንድ እኩል አቻ በመለያየት አንድ ነጥብ ይዛ በምድቡ የመጨረሻ እርከን ላይ ትገኛለች፡፡ የባፋና ባፋና አስጨናቂ ፈተና ደቡብ አፍሪካ ለዓለም ዋንጫ ከሚደረግ የምድብ ማጣርያ መጥፎ አጀማመሯ አገግማ ምድቡን በመሪነት በመጨረስ በጥሎ ማለፍ ወደ የሚደረገው የመጨረሻ የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር መቻሏን የምትወስነው በመጭው ሰኔ ወር ከሜዳዋ ውጭ ከኢትዮጵያ እና ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር በምታደርጋቸው ግጥሚያዎች እንደሆነ ይገለፃል፡፡ የባፋና አሰልጣኝ ጎርደን ሌጀሰንድ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሩብ ፍፃሜ የደረሱበት ስብስባቸውን አጠናክረው ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ቡድን ጋር ለመገናኘት ወስነዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ እና የመካከለኛው አፍሪካ ጨዋታ በኬፕ ታውን የሚደረግ ሲሆን ከተማው ለባፋና ባፋና ውጤታማነት አያመችም የሚል ወሬ በዝቷል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በኬፕታውን ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ ሶስት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በዛምቢያ 3ለ1፤ በአሜሪካ 1ለ0 እንዲሁም በኖርዌይ 1ለ0 እንደተሸነፉ ያስታወሰው ኪኮፍ የተባለ መፅሄት በጉዳት ሳቢያ እስከ 3 ወሳኝ ተጨዋቾች ለግጥሚያው ካለመድረሳቸው ጋር ተዳምሮ ውጤቱን እንዳያበላሸው ያሰጋል ብሏል፡፡
በ40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ጥሩነሽ እና ኢማና ይጠበቃሉ
በፖላንዷ ከተማ ባይድጎስዝ ነገ በሚደረገው 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ጠንካራ ቡድን በማሳተፍ ለተቃናቃኝ አገሮች ፈተና እንደምትሆን ተገለፀ፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ከ56 አገራት የተውጣጡ ከ432 በላይ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ለአዋቂ እና ለወጣት በተዘጋጁ አራት የውድድር መደቦች ይሳተፋሉ፡፡ በአዋቂ አትሌቶች ውድድሮች የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ እንደምትሆን የተጠበቀችው ኬንያ ብትሆንም ባለፉት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ለሜዳልያ ፉክክር የበቁት ኤርትራ እና ኡጋንዳም ጠንካራ አትሌቶች ያሳትፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ ከ1980 ወዲህ በተደረጉ የአዋቂ አትሌቶች ውድድሮች በወንዶች 13 የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ኬንያ ስትመራ ኢትዮጵያ 11 በማስመዝገብ ሁለተኛ ነች፡፡
በሴቶች ደግሞ 9 የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ የምትመራ ሲሆን ኬንያ በ4 የወርቅ ሜዳልያዎች ትከተላለች፡፡ ለሻምፒዮናው አይኤኤኤፍ ለሽልማት ያዘጋጀው 280ሺ ዶላር ሲሆን በዋናዎቹ የወንዶች 12 ኪሎ ሜትር እና የሴቶች ስምንት ኪሎሜትር ውድድሮች በግልና በቡድን እስከ ስድስት በሚመዘገበው ደረጃ መሰረት ገንዘቡን ያከፋፍላል፡፡ ለግል አሸናፊዎች ለወርቅ ሜዳልያ 30ሺ ዶላር ለቡድን አሸናፊ ደግሞ 20ሺ ዶላር ተመድቧል፡፡ በ40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ከሁለት አመት በፊት በስፔን ፑንታ ኡምቡራ የገጠመውን የውጤት መቀዛቀዝ እንደሚያሽል ተስፋ ተደርጓል፡፡
በአዋቂ ወንዶች ከተያዙት አትሌቶች ከ2 አመት በፊት በስፔን ፑንታ አምብራ በተካሄደው 39ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ12 ኪሎሜትር የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ያስገኘው የ24 አመቱ ኢማና መርጋ እና በለንደን ኦሎምፒክ በ10ሺ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘውና ከፍተኛ ልምድ ያለው ታሪኩ በቀለ በሜዳልያ ተቀናቃኝነት ትኩረት አግኝተዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በአገር አቋራጭ ሩጫ ለአራት ጊዜያት የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው ጥሩነሽ ዲባባ እና ለሁለት ጊዜያት በታዳጊዎች ውድድር ያሸነፈችው ታናሽ እህቷን ገንዘቤ ዲባባ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኢማና መርጋ የዓለም አገር አቋራጭ የሻምፒዮናነት ክብሩን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን የገለፀው የአይኤኤኤፍ ዘገባ ጥሩነሽ ዲባባ በበኩሏ በአዋቂ ሴቶች የስምንት ኪሎሜትር ውድድር በኢትዮጵያዊ አትሌት ለመጨረሻ ጊዜ ከ5 ዓመት በፊት የተገኘውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር ወደ ኢትዮጵያ ልትመልስ ትችላለች ብሏል፡፡
በባይድጎስዝ 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በአዋቂ ሴቶች ህይወት አያሌው፤ ገነት ያለው ፤መሰለች መልካሙና በላይነሽ ኦልጅራ ተሳታፊ ሲሆኑ በወንዶች ደግሞ ከኢማና መርጋ ሌላ ማራቶኒስቱ እና የዘንድሮው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ አሸናፊ ፈይሳ ሌሊሳ ፤ ሞሰነት ገረመው፤ አበራ ጫኔ፤ ታሪኩ በቀለ እና መካሻው እሸቴ ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ በወጣት አትሌት ውድድሮች ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች አዳዲስ አትሌቶችን በብዛት የምታሳትፍ ይሆናል፡፡ በወጣት ወንዶች የ8 ኪሎሜትር ውድድር የ18 አመቱ ሃጎስ ገብረህይወት የሚጠበቅ ነው፡፡ ባለፈው ወር በቦስተን አሜሪካ በቤት ውስጥ የ3ሺ ሜትር ውድድር አዲስ ሪከርድ ያስመዘገበው ሃጎስ ዘንድሮ በጃንሜዳ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶች ውድድር አሸናፊ ነበር፡፡ ባለፈው አመት በዓለም የታዳጊዎች ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሙክታር ኢድሪስም ለውጤታማነቱ ግምት ያገኘ ሲሆን አትሌቱ ከሁለት ወራት በፊት በጣሊያን የተደረጉ ሶስት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን የአገር አቋራጭ ውድድሮች በማሸነፍ ጥሩ ብቃት መያዙ ተመስክሮለታል፡፡
በወጣት ሴቶች የ6 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ ኢትዮጵያ አዳዲስ አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በስፔን ፑንታ ኡምብራ ተደርጎ በነበረው 39ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በውጤቱ በኬንያ በጣም ተበልጦ ነበር፡፡ በወቅቱ በአትሌቶችና በቡድን ደረጃ ለሽልማት ከቀረቡት 8 የወርቅ ሜዳልያዎች የኬንያ ቡድን 6ቱን ሲወስድ የኢትዮጵያ ቡድን 2 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ብቻ አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ የኬንያ ቡድን በሻምፒዮናው ከቀረቡ 24 ሜዳልያዎች 11 ሲወስድ በኢትዮጵያ የተመዘገበው 5 ሜዳልያዎች ብቻ ነበር፡፡ በሻምፒዮናው ለሽልማት ከቀረበው ገንዘብ የኬንያ ቡድን 127ሺ ዶላር በመረከብ ከፍተኛ የበላይነት ሲያሳይ ለኢትዮጵያ የደረሰው 72ሺ ዶላር ብቻ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ኤኮን ለአፍሪካ አስተዋፅኦዮን እቀጥላለሁ አለ
የሴኔጋል ተወላጅ የሆነው የአር ኤንድ ቢ እና የሂፖፕ ምርጥ ዘፋኝ ኤኮን፣ በአፍሪካ የማደርጋቸውን አስተዋፅኦዎችን እቀጥላለሁ ሲል ለሲኤንኤን ተናገረ፡፡ በሙሉ ስሙ አሌያሙኒ ዳማላ ባዲራ ተብሎ የሚጠራው ኤኮን ‹ስታድዬም› በሚል ስያሜ አራተኛ የአልበም ስራውን ለገበያ እንደሚያበቃ ታውቋል፡፡ ከእነ ማይክል ጃክሰን፤ ሌዲ ጋጋ፤ ስኑፕ ዶግ እና ኤሚነም ተጣምሮ በመስራት የሚታወቀው ኤኮን በአዲሱ አልበሙ ከፍተኛ ስኬት ሊያገኝ እንደሚችል ያምናል፡፡
ከአፍሪካ የፈለቀና በዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ስኬት የተቀዳጀ አርቲስት መሆኑን የገለፀው ኤኮን፤ በኪነጥበብ እና በበጎ አድራጎት ስራዎች ለአህጉሪቱ በአርዓያነት የሚታዩ ስራዎችን መስራት የምንጊዜም ፍላጎቴ ነው ብሏል፡፡ ከ10 አመት በፊት የመጀመርያ አልበሙን ለገበያ ያበቃው ኤኮን፤ አስቀድሞ በ3 አልበሞቹ በመላው አለም ከ10 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎችን ሸጧል፡፡ ሙዚቃ የሚያሳትምና የሚያከፋፍል “ኮንቪክት” የተሰኘ ኩባንያ እንዲሁም ልብስና የፋሽን ቢዝነስ እያንቀሳቀሰ የሚገኘው ኤኮን፤ በሴኔጋል ‹ኮንፊደንስ› በተባለ ፋውንዴሽኑ ለትምህርት ቤት እና ለጤና ጣቢያ ግንባታ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ያካሄዳል፡፡
‹ኦዝ ፡ ዘ ግሬት ኤንድ ፓወርፉል› ገበያውን ይመራል
‹‹ኦዝ ፡ ዘ ግሬት ኤንድ ፓወርፉል›› የተሰኘው ፊልም በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2013 ከፍተኛውን ገቢ ለማግኘት የበቃ ፊልም መሆኑን ሎስአንጀለስ ታይምስ አስታወቀ፡፡ በዋልት ዲዝኒ፣ በ215 ሚሊዮን ዶላር የተሰራው ፊልም ከሁለት ሳምንት በኋላ በመላው ዓለም ከ288 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል፡፡ ፊልሙ ለእይታ በበቃባቸው የመጀመርያዎቹ ሶስት ቀናት በዓለም ዙርያ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማስገኘቱ፣ የፊልሙ ቀጣይ ክፍሎችን የመስራት ሃሳቦችን አነሳስቷል፡፡
በጥንቆላ አፈታሪክ ዙርያ የሚጠነጥነው “አድቬንቸር ፋንታሲ” ፊልም፣ ጄምስ ፍራንኮ በመሪ ተዋናይነት ሰርቶበታል፡፡ ሚላ ኩኒስ፤ ራቼል ዊሴዝ እና ሜሸል ዊልያምም ተውነውበታል፡፡ ‹ኦዝ፡ ዘ ግሬት ኤንድ ፓወርፉል›፣ ከ74 አመታት በፊት ‹ዘ ዎንደርፉል ዊዛርድ ኦፍ ኦዝ› በተባለው ዘመን ያልሻረው መፅሃፍ ላይ በመመስረት በ3ዲ የተሰራ ነው፡፡ የፊልሙ ዲያሬክተር በስፓይደርማን ሶስት ፊልሞች ከፍተኛ አድናቆት ያተረፈው ሳሚ ራይሚ ነው፡፡
አዴሌ በአጭር ጊዜ ሁሉንም ሽልማት ወስዳለች
እንግሊዛዊቷ ድምፃዊት አዴሌ በጥቂት አመታት ውስጥ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ሽልማቶችን ሁሉ በመሰብሰብ ስኬታማ እንደሆነች ቢዝነስ ኢንሳይደር ገለፀ፡፡ አዴሌ ከ3 ሳምንታት በፊት በ85ኛው የኦስካር ምሽት ላይ ለጀምስ ቦንድ ፊልም በሰራችው ሙዚቃ በምርጥ ኦርጅናል ዜማ ዘርፍ የኦስካር ሽልማት ወስዳለች፡፡ የ24 አመቷ አዴሌ አዲስ አልበም ለመስራት እንደማትቻኮል ወኪሏ ሰሞኑን ያሳወቀ ሲሆን፣ የመስራት ፍላጎት ቢኖራት እንኳን ዘንድሮ ጋብቻ ለመመስረት ማቀዷ ዝግጅቷን ያስተጓጉለዋል የሚሉ ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡
አዴሌ በትልልቆቹ የኪነጥበቡ ኢንዱስትሪ ሽልማቶች ተሸላሚ የሆነችበት እድሜ በጣም የሚያስገርም ነው ያለው ዘ ቢዝነስ ኢንሳይደር፣ 9 የግራሚ፤ 4 የአሜሪካን ሚውዚክ አዋርድ፤ 12 የቢልቦርድ ሚውዚክ አዋርድ እና 4 የብሪት አዋርድ ሽልማቶችን በመሰብሰብ ወደር የለሽ ሆናለች፡፡ ‹21› የተሰኘው የአዴሌ ሁለተኛ አልበም በ2011 እና 2012 የዓለምን ገበያ ለመምራት የበቃ ሲሆን በአለም ዙርያ 12.5 ሚሊዮን ቅጂ ተሸጧል፡፡ አዴሌ ‹‹19›› በሚል ርእስ የመጀመርያ አልበሟን በመልቀቅ የዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪን የተቀላቀለችው ከ4 ዓመታት በፊት ነበር፡፡
ቻይና ለሆሊውድ ፊልሞች ተመችታለች፤ የቻይና ፊልሞች ግን አልቀናቸውም
የሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች፣ የቻይና መንግስት በሚፈፅምባቸው ሳንሱር ቢማረሩም፣ የአገሪቱ ገበያ ተመችቷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በቻይና የተሰሩ ፊልሞች በዓለም አቀፍ ገበያ እንዳልተሳካላቸው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ለሆሊውድ ፊልሞች፣ ትልቋ ገበያቸው አሁንም አሜሪካ ነች፡፡ በመቀጠልም ጃፓን፡፡ ነገር ግን በቻይና የሆሊውድ ፊልሞች ገበያ በየአመቱ በ30% እያደገ መጥቷል፡፡ እናም በ2012 ቻይና ለሆሊውድ ፊልሞች ሦስተኛ ገበያ ሆናላቸው 2.71 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተውባታል፡፡ በከፍተኛ ወጪ ተሰርተው ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ ፊልሞች (ለምሳሌ ስካይ ፎል እና ዘ ዳርክ ናይት ራይዝስ) በቻይና ገበያ ደርቶላቸዋል፡፡
‹ኩንጉፋ ፓንዳ 3› የተባለውን ፊልም፣ ድሪም ዎርክስ ከቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር እንደሚሰራ የጠቀሰው ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዋልት ዲዝኒ ደግሞ‹አይረን ማን 3› በከፊል በቻይና ምድር መቅረፁን ገልጿል፡፡ በ2002 እኤአ በቻይና የነበረው የሲኒማ ቤቶቸ ብዛት ከ10 አመታት በኋላ በ10 እጥፍ በማደግ 13ሺ ደርሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በቻይንኛ ቋንቋ የተሰሩ የቻይና ፊልሞች፣ በአለም ገበያ ያገኙት ተቀባይነት እጅግ የቀዘቀዘ መሆኑን ያመለከተው የሲኤንኤን ዘገባ ነው፡፡ በቻይና ቋንቋ የተሰሩት ፊልሞች በአገር ውስጥ ያላቸው ገበያ የተሟሟቀ ቢሆንም ከአገር ውጭ ግን ብዙም አልተሳካላቸውም፡፡ “ሎስት ኢን ታይላንድ” የተባለ ፊልም በቻይና እስከ 202 ሚሊዮን ዶላር ቢያስገባም፤ በሰሜን አሜሪካ ያስገባው ከ70ሺ ዶላር አይበልጥም፡፡