Administrator
“ላይት ኢን ሻዶው” ፎቶ ኤግዚብሽን ሐሙስ ይከፈታል
የአዲስ አድማስ ፎቶ ጋዜጠኛ የሆነው አንተነህ አክሊሉ ያነሳቸው ከ30 በላይ ፎቶግራፎች የተካተቱበት “ላይት ኢን ሻዶው” የፎቶግራፍ አውደርእይ ካዛንቺስ በሚገኘው ኦዳ ታወር የፊታችን ሐሙስ ከምሽቱ 12 ሰዓት እንደሚከፈት አዘጋጁ አስታወቀ በኦዳታወር ሶስተኛ ፎቅ በቅርቡ በተከፈተው ኮክ ቺክን ባር እና ሬስቶራንት የሚከፈተው አውደርእይ “ጥበብ፣ ከተማና ገጠር” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን ባለፉት ሰባት ዓመታት ፎቶግራፈሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውሮ ያነሳቸው ምርጥ ፎቶግራፎች ይካተቱበታል፡፡ የፎቶግራፍ ኤግዚብሽኑ እስከ ነሐሴ 20 ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
ለግእዝ ትንሣኤ ያለመ ኪነጥበባዊ ዝግጅት ነገ ይቀርባል
የግእዝ ቋንቋ እንዲያንሰራራ ያለመ ኪነጥበባዊ ዝግጅት ነገ ማምሻውን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በኮሌጁ የምግብ አዳራሽ የሚቀርቡትን ድራማ፣የጥንታዊ ፅሁፎች ንባብ ፣ቅኔ፣ የግዕዝ ግሰሳ (ትንተና) ፣ጭውውትና ዜናን በግእዝ የኮሌጁ የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በህብረት እንደሚያዘጋጁት የጠቀሰው የአዘጋጆቹ መግለጫ፤ ለግእዝ ቋንቋ እና ለኢትዮጵያ የቀድሞ ስልጣኔ አክብሮት ያላቸው ወገኖች ሁሉ በነፃ ዝግጅቱን መከታተል እንደሚችሉ አብስሯል፡፡ የኮሌጁ የግእዝ ክፍለ ትምሕርት ኃላፊ መምህር ዘርአዳዊት አድሓና ስለጉዳዩ ማብራሪያ ጠይቀናቸው፤ ኮሌጁ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ቋንቋውን በዲፕሎማ ደረጃ እያስተማረ መሆኑን ገልፀው “በየዓመቱ ደብረ ታቦር ሲከበር ክርስቶስ ለተማሪዎች ምስጢር መግለጡን አስታውሰን ከአብነት ትምህርት ቤቶችን በወረስነው ትውፊት ከበዓለ ደብረታቦር ጋር እናከብረዋለን” ብለዋል፡፡
የአገር ሰምና ወርቅ
ልለምንህ ጣና - ልማጠንህ ዓባይ - አዋሽ እሺ በለኝ
አገሬ ተድራ - አገር ጠርቻለሁ - የአገር ድግስ አለኝ፤
አገሩን የዳረ - አገር ህዝብ የጠራ
ለአገር የጠመቀ - ለአገር የደገሰ፣
መሬቱ እንጀራው ነው - ሀይቁም ወይንጠጁ
መች ይጨንቀውና - ደረሰ አልደረሰ፤
ይኸው አገር መጣ!
ይኸው አገር ወጣ!
አገር ድግስ በይ - አገር ላይ የወጣ - አገር ሊያይ የመጣ
ብትታየው ጊዜ - አገር ሙሽራዬ - ከአገር ሁሉ በልጣ
አገር ልቡ ቆመ - አገር ማድነቂያ አጣ - አገር አቅም አጣ፡፡
ይኸው ይቺውልህ፤
በአገር ፍቅር ቬሎ - በአገር ሰረገላ
አገር ስትመዘን - በሰው ተመስላ
ይህን ታህላለች
ይህን ትመስላለች
በል ሀቅ እንፈልቅቅ - ከሯጭ ህብረ - ቀለም
በአትሌት ሰምና ወርቅ - በ‹‹ሀገር›› ቀልድ የለም!!
ለዚያም ነው ጥሩዬ
አገር በልቧ አዝላ - በአገር ተውባ
በአገራት ሙሽሮች - በአገራት ተከባ
በአገር አደባባይ - አገር ስታገባ
አገር ወዲያ ጥላ - ወደ አገር ስትገባ
አገር ምድሩ ያለው - ጉሮዬ ወሸባ!!
ነው እንጅ ነውና!!
‹‹ጥሩ›› አገር ብትሆን ነው - አገርን ያከለች - አገር የተሰጠች
ከአገር ተፎካክራ - አገር ያስከተለች - አገር የበለጠች!!
ይኸው ነው ቀለሙ - ይኸው ነው እውነቱ
እሷ ስታሸንፍ - እኛ ሁላችንም - የጨፈርንበቱ!!
ስማ ጋዜጠኛ፤
ይኸውልህ እውነት - የሀቅ ህብረ - ቀለም
በጥሩነሽ አገር - ስለ አገር ቀልድ የለም፡፡
ካላመንክ ጠይቃት - ከአንደበቷ ስማ
እንዲህ ትልሃለች - አገር አስቀድማ...
‹‹ለሌላ አገር አትሌት - እንኳን ሜዳሊያ - መጨረስም ድል ነው
ለኔ አገር ህዝብ ግን - ብር ሽንፈት ሲሆን - ነሀስም ውራ ነው፤
በቃ በኔ ሀገር - ድል ነው እሚባለው
ወርቁን ከነክብሩ - ያስገኘህ ጊዜ ነው!!››
ይህ ነው ሰምና ወርቅ - በጥሩነሽ አገር - የአገር ህብረ - ቀለም
ወርቅ ለለመደ - ነሀስ ግድ አይሰጥም - ብርም ድል አይደለም፡፡
ነሐሴ 5 - 2005 ዓ.ም
(ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የሞስኮ ድል)
ሃናኔና ሃሊቴ የአምስት ሣንቲም ቅቤ ተካፍለው ሲቀቡ ውለው ወደማታ በአምስት ሣንቲም ጐመን ይጣላሉ
(የሚከተለውን ተረት - መሰል ታሪክ ከዚህ ቀደም ትንሽ ለየት ባለ መልኩ ተርከነዋል፡፡ የሚሰማ ጠፍቶ ታሪክ ሲደገም በማየታችን ደግመን አቅርበነዋል፡፡)
አንድ ፀሐፊ እንዳለው “እኔን ቅር የሚለኝ ታሪክ መደገሙ ሳይሆን፤ በበለጠ አስከፊ መልኩ መደገሙ ነው” ይላል፡፡
ዕውነት ሆነው ከመቆየት ብዛት ተረት የሚሆኑ ታሪኮች አሉ፡፡
ባለፈው ሥርዓት፣ ከዕለታት አንድ ቀን የነበሩ፤ ሁለት የትግል ጓዶች ነበሩ አሉ፡፡ ከጊዜ ብዛት ተቃዋሚ ድርጅታቸውን ትተው ወደመንግሥት ለመግባት ተወያዩ፡፡
አንደኛው - “እረ ይሄ ድርጅታችን የሚመች አልመሰለኝም፡፡ አደጋው እየበዛ መጣ”
ሁለተኛው - “ዕውነትክን ነው፡፡ እኔም ከዛሬ ነገ ሁሉም ነገር ቅር እያለኝ መሆኑን፤ ልነግርህ
ሳስብ ነበር፡፡”
አንደኛው - “ታዲያ ከዚህ ወጥተን ለምን ወደመንግሥት አንገባም?”
ሁለተኛው - “ይሻለናል”
ተስማሙና ባንድ በሚያውቁት ሰው በኩል ወደ መንግሥት የፖለቲካ መዋቅር ገቡ፡፡ ጠርናፊያቸው አንድ የሚያውቁት ሻምበል ሆነ፡፡
የፖለቲካ ርዕዮተዓለምና አቋም ላይ ተወያዩ፡፡ ተዋወቁ፡፡ ተማማሉ፡፡ የትግሉ አካል ሆኑ፡፡ ንቃታቸው አስተማማኝ ነው፡፡ ቀድሞ በነበሩበት ድርጅት ውስጥ በቂ ንባብ አድርገዋል፡፡
እየነቁ እየተደራጁ ቀጠሉ፡፡ በመካከል ከሁለቱ አንደኛው ወደ ኪዩባ የመሄድ ዕድል ያጋጥመዋል፡፡
ኪውባ ሄዶ፣ ንቃቱን አዳብሮ፣ ትምህርት አበልጽጐ ወደሀገሩ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል፡፡
ተንሰፍስፎ ያንን የትግል ጓዱን ይፈልገዋል፡፡ ተገናኙ፡፡
“እንዴት ነህ?” አለ ከኩባ የመጣው፡፡
“በጣም ደህና ነኝ፡፡ አንተስ?” አለ አዲሳባ የቆየው፡፡
“ኪውባ በጣም ድንቅ ነበር፡፡ ብዙ ጓዶች አፍርቻለሁ፡፡ የዳበረ ዕውቀት ይዤ መጥቻለሁ ብዬ አምናለሁ” አለው በነቃ ኩራት፡፡
“መልካም፤ በሚገባ ታወራኛለህ!”
“ለመሆኑ ሻምበልስ? ጤናውን እንዴት ነው?”
“ዉ! ሻምበልኮ ታሰረ” አለው እዚህ የቆየው፤ በሀዘንና እንጉርጉሮ ቃና አቀርቅሮ፡፡
ይሄኔ ከኩባ የመጣው በጣም ግራ ገባው፡፡ “እንኲን ታሰረ!” እንዳይል በሳል የማይል ጓዱ ነው፡፡ “ለምን ይታሰራል?” እንዳይል፤ የራሱንም ዕጣ - ፈንታ አያቅም፡፡ ስለዚህ ሲቸግረው፤
“አቤት የአብዮታችን ፍጥነት?!” አለ፤ ጭንቅላቱን በሁለቱ እጆቹ መካከል ቀብሮ፡፡
ጊዜ አለፈና እንደተባለው ሁለቱም ዕጣ - ፈንታቸው እሥር ቤት የሚከትታቸው ሆነና እሥር ቤት ተገናኙ፡፡ ለንፋስ ወጥተው የግል ጨዋታ ሲጨዋወቱ፤
አንደኛው - “እህስ ጓድ፤ አሁንስ የአብዮታችን ፍጥነት ምን ይመስልሃል?”
ሁለተኛው - “አይ ወዳጄ!! አሁንማ አንደኛውን ጄት ሆኖልሃል! ሁላችንንም ጠራርጐን
ገብቷል!” አለ፡፡
* * *
ከሁሉ ነገር በፊት ከመከዳዳት ይሰውረን፡፡ ስለሰው ትተን ስለአብዮታችን ፍጥነት የማናወራበት ጊዜ ይስጠን፡፡ ሁላችንንም ጠራርጐን ገባ የማንባባልበት፤ “ውሃ ሲወስድ አሳስቆን” የማንዘባበትበት ቀና ዘመን ያምጣልን፡፡
የሮጠ ሁሉ እንደማያሸንፍ የሰሞኑ አትሌቲክስ ያስተምረናል፡፡ ድል፤ ሰዓት ጠብቆ ሊቀያየር እንደሚችልም የሰሞኑ አትሌቲክስ ያስተምረናል፡፡ አንዳንዱ ገና ከጅምሩ ሊያቋርጥ እንደሚችል የሰሞኑ አትሌቲክስ ይነግረናል፡፡ ብዙውን የሩጫ ክፍል ሄዶ ሄዶ ማብቂያው ግድም መሸነፍ ሊኖር እንደሚችልም የሰሞኑ አትሌቲክስ አሳይቶናል፡፡ ቢደክሙም፣ ቢዝሉም፣ ውጣ - ውረዱ ከባድ ቢሆንም፤ ሳይታክቱ፤ በጽንዓት ሮጦ እድሉ አምባ ለመድረስ እንደሚቻልም የሰሞኑ አትሌቲክስ ያለጥርጥር አመልክቶናል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ራስን በማዘጋጀት፣ በልበ - ሙሉነትና በብልህነት ጊዜና ቦታን ማወቅ ያለውን ፈትልና ቀስም የሆነ፤ ግንኙነትና ትስስር በአጽንኦት እንድናስተውል ታላቅ ተመክሮን አጐናጽፎናል፡፡ ሩጫ ትንፋሽ እንደሚጠይቅ፤ ትግልም ትንፋሽ ይጠይቃል፡፡ ሩጫ ጉልበት እንደሚፈልግ ትግልም ጉልበት ይፈልጋል፡፡ ሳይዘጋጁ የገቡበት ሩጫ ተሸናፊ እንሚያደርግ፣ ሳይዘጋጁ የገቡበት ትግልም ከተሸናፊነት ጐራ ያስፈርጃል፡፡ ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል፤ ይሏል፡፡ ተዘጋጅቶ የሩጫው ሰንበር ላይ ወጥቶም መቼ ማፈትለክ እንዳለብን ካላወቅን፤ የተሻለ ብልጠት ያለው እንደሚቀድመን ሁሉ፤ በትግል ሠፈርም ተዘጋጅቶ ገብቶ ጊዜን ባለማወቅ ሳቢያ፤ ብልጡ ይቀድመናል፡፡ ከሩጫው ሜዳ የተፎካካሪን ብስለትና ጥንካሬ አንዳንዴም ተንኮል ከቁጥር መጣፍ ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንዱ ተንከባክቦ የያዘው ጥንካሬ አለው፡፡
ተጋትሮም ተስፈንጥሮም ኬላውን ሰብሮ፣ በጥንካሬው ይዘልቃል፡፡ አንዳንዱ በልምድ ያዳበረው ብስለት አለው፡፡ ስለዚህም የተፎካካሪውን አቅምና በብልህነት የሚጠቀምበትን የጊዜ ሰሌዳ፣ ይመዝናል፡፡ አንዳንዱ የሌሎችን የመሮጫ ረድፍ በመዝጋት፣ ሲመች ጭራሹን በመገፋተር በብልጠትና በተንኮል ይሮጣል፡፡ የባሰበት እስኪነቃበት ዕፅ ይጠቀማል፡፡ እነዚህ የሩጫ ስልቶች የፖለቲካ ስልቶቻችን ተመሳሳይ ገጽታዎች ናቸው፡፡ ሩጫችን ለድል ያበቃን ዘንድ ግብዓቶቹን ሁሉ በአግባቡ ማጤን ዋና ነገር ነው፡፡ “ፈጣን ነው ባቡሩ” እንደምንል ሁሉ፤ “ያልተመለሰው ባቡርን”፤ አልፈን ተርፈንም፤
“እልም አለ ባቡሩ
ወጣት ይዞ በሙሉ” ማለታችንን አንርሳ፡፡
“አወይ መሶሎኒ፤ አወይ መሶሎኒ
ተሰባብሮ ቀረ፣ እንደጃፓን ስኒ” የሚለውም አንድ ሰሞን መዝሙር ነበር፡፡
ይድነቃቸው ተሰማ አንድ ጊዜ ስለሱዳን የእግር ኳስ ቡድን መሻሻል ተጠይቀው፤ “ሱዳን ዘግታ ስትለማመድ ቆይታ፣ ራሷን አጠናክራ፣ ወደፊት መጣች፡፡ እኛ እንደዱሯችን ነው የቆየነው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር “ቆመን ጠበቅናቸው፤ ጥለውን አለፉ!” ብለዋል፡፡ ራስን ማጠናከር ዋና ነገር ነው፡፡
በህመምም፣ በአቅም ማነስም፣ “አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” ጥፋት ያጠፉም፣ በበላይ ተንኮልና ጥላቻም፣ በፓርቲ ምሥረታም፣ በመተካካትም ሰበብ ሰዎችን ስናገልል ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዕጣ - ፈንታ ስዕል አኳያ ማየት ብልህነት ነው፡፡ በተዘበራረቁና በተወሳሰቡ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ቂም መያዝ፣ መከፋፈል፣ አንድነትን ማናጋት፣ ወይም መሰነጣጠቅና “የትልቁ አሣ ትንሹን አሣ መዋጥ አባዜ” ማስተናገድ ክፉ ልማድ ነው፡፡ ይህ ልማድ እንዳይደገም “ሃናኔና ሃሪቴ የአምስት ሣንቲም ቅቤ ተካፍለው ሲቀቡ ውለው፣ ወደማታ በአምስት ሣንቲም ጐመን ይጣላሉ” የሚለውን የወላይታ ተረት ማስተዋል ደግ ነው፡፡
የ”ሚስ ዩኒቨርስ” ውድድር በመስከረም ይካሄዳል
ዓላማውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ላይ ያደረገው “ሚስ ዩኒቨርስ” የቁንጅና ውድድር፤ በመጪው መስከረም ወር ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ አዘጋጁ “ክሬቲቭ ኮሙኒኬሽን ኤንድ ኤቨንትስ” አስታወቀ፡፡ የውድድሩ ምዝገባና ፈተና ነሐሴ 11 እና 12 በፓኖራማ ሆቴል የሚካሄድ ሲሆን መስከረም 10 በራዲሰን ሆቴል በሚካሄደው የ“ሚስ ዩኒቨርስ” የቁንጅና ውድድር፤ አሸናፊዋ ከምታገኘው ሽልማት በተጨማሪ ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ማስተማርና መቀስቀስ ይጠበቅባታል፡፡
“ጣምራ ጦር” ከ30 ዓመት በኋላ ተመልሶ መጣ
በታተመበት ዘመን ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው “ጣምራ ጦር” ታሪካዊ ልቦለድ መጽሃፍ፤ ከ30 ዓመት በኋላ ዳግም ታትሞ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ የደራሲ ገበየሁ አየለ የበኩር ሥራ የሆነው ልቦለዱ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1975 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲታተም 30ሺህ ቅጂዎች እንደተሸጠለትና ለሦስት ጊዜ እንደታተመ የገለፀው ደራሲ ገበየሁ አየለ፤ አሁን የታተመው በአንባቢያን ጥያቄ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ታትሞ ሲወጣ በአንጋፋው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ በሬዲዮ የተተረከው ልቦለዱ፤ የሶማሊያው ጄነራል ሲያድባሬ በኢትዮጵያ ላይ በፈፀመው ወረራ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ከማተሚያ ቤት የወጣው ባለ 222 ገፁ “ጣምራ ጦር”፤ በ41 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን በተሰራጨ በሦስት ቀናት ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንደተሸጠ ደራሲው ገልጿል፡፡
የአዳም “ሕማማትና በገና” ውይይት ይካሄድበታል
የደራሲ አዳም ረታ ረዥም ልቦለድ “ሕማማትና በገና” ነገ ውይይት እንደሚካሄድበት ሚዩዚክ ሜይዴይ አስታወቀ፡፡ ውይይቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት አዳራሽ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለሦስት ሰዓታት ይዘልቃል፡፡ የመነሻ ሃሳብ በማቅረብ ውይይቱን ከሚዩዚክ ሜይዴይ ባለሙያዎች ጋር የሚመሩት የሥነጽሑፍ ባለሙያው አቶ ቴዎድሮስ አጥላው ናቸው፡፡
“ሀ በሉ” ነገ በሐዋሳ ይመረቃል
በኮሜዲያን ታሪኩ ሰማንያ እና ቢኒያም ዳና የተፃፈው “ሀ በሉ” ፊልም ነገ በሀዋሳ ከተማ ባህል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ የ100 ደቂቃ ርዝመት ያለው አስቂኝ ፊልሙ፤ በአይዶል ውድድር ለመሳተፍ ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ በመጡ ሁለት ወጣቶች ላይ ያጠነጥናል፡፡
በፊልሙ ላይ ደራሲዎቹን ጨምሮ ካሙዙ ካሳ ማሚላ፣ ኪችሌ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡ በደቡብ ክልል የአማርኛ ለዛ የተሰራው ይሄ ፊልም፤ አዋሳን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ እንደሚታይ ማወቅ ተችሏል፡፡ ፊልሙ ሙሉ በሙሉ በሐዋሳ የተሰራ ሲሆን ፕሮዱዩሰሩ ቀደም ሲል “ቴክ ኢት ኢዚ” የተሰኘውን ፊልም ፕሮዱዩስ ያደረገው ሻና ፊልም ፕሮዳክሽን እንደሆነ ታውቋል፡፡
“የዓለም ታላላቅ ታሪኮች ለሕጻናት” ለንባብ በቃ
በአዲስ አድማስ “እንጨዋወት” አምዱ የሚታወቀው ደራሲና ወግ ፀሃፊ ኤፍሬም እንዳለ ያዘጋጀው “የዓለም ታላላቅ ታሪኮች ለሕጻናት” መፅሃፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሃፉ የሮቢን ሁድ፣ ሮቢንሰን ክሩሶ፣ “ሪፕ ቫን ዊንክል እና ሌሎች ታላላቅ ሰዎችን ታሪኮች ይዟል፡፡ 86 ገፆች ያሉት የሕጻናት መጽሐፍ፤ በጃፋር መጻሕፍት መደብር በ20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ኤፍሬም እንዳለ በቅርቡ ያሳተመውን የስኬት መፅሃፍ ጨምሮ የተለያዩ የወግና የትርጉም ሥራዎችን ለንባብ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃዎችና ፈዋሽነታቸው
ማንኛውም ጤናማ ሰው ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን በፍልውሃ መታጠብ ይገባዋል
እርጅና የተጫጫናቸው ክፍሎች፣ የወላለቁ የቧንቧ መክፈቻና መዝጊያዎች፣ የተላላጡ ግድግዳዎች፣ ያረጁ ፎጣዎች፣ የተንሻፈፉ ነጠላ ጫማዎች፣ እድሜ የተጫናቸው ሠራተኞችና ተራ ጠባቂ ደንበኞች በብዛት የሚገኙበት ሥፍራ ነው-ፍልውሃ፡፡ ከህመማቸው ለመፈወስና፣ የሻወር አገልግሎት ለማግኘት ከፍቅረኞቻቸው፣ ከባለቤቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመታጠብ በርካቶች ወደ ፍልውሃ ይሄዳሉ፡፡ ድርጅቱ የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም ሥፍራው ሁልጊዜም በደንበኞች እንደተጨናነቀ ነው፡፡
በንጉሡ ዘመን ተሰርተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ክፍሎች፤ እርጅና ተጫጭኗቸውና እድሣት ናፍቋቸው ዛሬም ድረስ ደንበኞቻቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ሥፍራው ለአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታም ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከእንጦጦ ቤተመንግስታቸው ተነስተው ወደእዚህ ሥፍራ ለመውረዳቸው ምክንያታቸው በአካባቢው የተፈጥሮ ፍልውሃ መገኘት ነበር፡፡ እቴጌይቱ በፍልውሃ አካባቢ ውበት ተማርከው ጊዜያዊ ማረፊያቸው ካደረጉት በኋላ፣ በሥፍራው በሚገኘው የተፈጥሮ ፍልውሃ መታጠብ የየዕለት ተግባራቸው ሆነ፡፡ አካባቢውን ወደዱት፡፡ በፍልውሃው ፍቅር ወደቁ፡፡ ይህ ደግሞ ባላቸውን (አፄ ሚኒሊክን) አሣምነው የአገሪቱን መናገሻ ከተማ እስፍራው ላይ ለመቆርቆፍ እንዲችሉ ማድረጉን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፍልውሃዎችን በብዛት ከታደሉት አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የምሥራቅ አፍሪካው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ የአገሪቱን አብዛኛውን ክፍሎች አቋርጦ የሚያልፍ በመሆኑ ነው፡፡ የአዲስ አበባው ፍልውሃ፣ የሶደሬው አባድር፣ ወንዶገነት፣ ወሊሶና አምቦ ኢትዮጵያ ሆቴል የተፈጥሮ ፍልውሃ ከሚገኝባቸው የአገራችን አካባቢዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎችም ከቱሪዝም መስህብነታቸው እና ከገቢ ማስገኛ ምንጭነታቸው በተጨማሪ ለፈውስ አገልግሎት እየዋሉ ነው፡፡ በፍልውሃው አማካኝነት በርካቶች ከያዛቸው ደዌ እንደሚፈወሱ እንሰማለን፡፡ የጥንት አባቶቻችን ለዘመናት ያለ ሳይንሳዊ ዕውቀት ሲጠቀሙበት የኖሩት ይኸው የተፈጥሮ ፍልውሃ፤ አሁን ዘመናዊና ሣይንሣዊ በሆነ መንገድ ጥናትና ምርምር እየተደረገበት ይገኛል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃን በማጥናት ሥራ ላይ ተጠምደው የሚውሉ ተመራማዎች አሁን አዲዲስ የጥናትና የምርምር ውጤቶችን ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከ37°C (ከሰላሣ ሰባት ድግሪ ሴንትግሬድ) እስከ 39°C ድረስ ሙቀት ያለው የተፈጥሮ ፍልውሃ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ማንኛውም ጤናማ ሰው ቢያንስ በሣምንት አንድ ቀን በዚህ የሙቀት መጠን ውስጥ ባለ የፍልውሃ መታጠብ ወይም መዘፍዘፍ ይኖርበታል፡፡ ይህም በምግብ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ንጥረ ማዕድናትንና የተለያዩ ለሰውነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ማግኒዚየም፣ ሶዲየምና ካልሲየም የተባሉ ማዕድናትን ለማግኘት ያስችለናል፡፡ እነዚህ ማዕድናት ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ እንደሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃዎች እንደሚገኙበት ሥፍራ በማዕድን ይዞታቸው መጠንና በአሲዳምነታቸው እንደሚለያዩ የጠቆመው ይኸው ጥናት፤ በውሃው ውስጥ የሚገኙት ማዕድናት የሚሰጡትም የፈውስ አገልግሎት እንደየሁኔታው ሊለያይ እንደሚችል አረጋግጧል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃን ፈዋሽነት በሚያጠናው ባላኒዮሎጂ (Balaneyology) በተሰኘው የጥናትና ምርምር ዘርፍ የተሰማሩ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ባደረጉት መረጃ፤ ፍልውሃ በሁለት የተለያዩ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው (Filtrate hot spring) የተባለውና በመሬት ስንጥቅ አማካይነት ወደ ከርሰ ምድር ውስጥ የገባው የዝናብ ውሃ እጅግ ሞቃታማ በሆነው የመሬት ክፍል ውስጥ ደርሶ፣ በውስጡ ከሚገኙ የከርሰ ምድር ማዕድናት የያዘው ሞቃት ውሃ፣ በመሬት ውስጣዊ ግፊት አማካኝነት ወደ መሬት ገፅ በመውጣት በፍል ውሃነት ይከሰታል፡፡ ሌላው የተፈጥሮ ፍልውሃ (Primary hot spring) የተባለው ሲሆን ይህ ውሃ የሚፈጠረው በተፈጥሮ በከርሰ ምድር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ አማካኝነት በርካታ ማዕድናትና ንጥረ ነገሮች ከውሃው ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ በመሬት ግፊትም ውሃው ወደ ገፀ ምድር ሲወጣ በርከት ያሉ ለጤና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ማዕድናትንና ንጥረ ነገሮችን ይዞ ይወጣል፡፡ በሁለቱ የተለያዩ መንገዶች የሚገኘው ፍልውሃ፤ የተለያዩ የማዕድንና የጋዝ መጠኖች ያሉት ሲሆን የሶዲየም ክሎራይድ ይዘትም አለው፡፡ ከ3-5% የሚደርስ የሶዲየም ክሎራይድ ይዘት ያለው የተፈጥሮ ፍልውሃ፤ ለመገጣጠሚያ ብግነት፣ ለቁርጥማት ለነርቭ በሽታ፣ ለአጥንት መሳሳት፣ ለጡንቻ መተሳሰር እና መሰል የጤና ችግሮች መድሃኒት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
የተፈጥሮ ፍልውሃ ከዚህ በተጨማሪ ለቆዳ በሽታዎች፣ ለመተንፈሻ አካላት ችግሮች እፎይታን ይሰጣል፡፡ የአዕምሮን የማሰብ ችሎታ ከፍ ለማድረግ፣ ድብርት ሲጫጫነን፣ ጤናማ የልብ ምት እንዲኖረን፣ ሰውነታችን ውስጥ የሚፈጠሩ መርዛም ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድና የሆርሞን ስርዓታችንን ለማስተካከል የተፈጥሮ ፍልውሃዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡
ከከርሰ ምድር የሚገኙት የተፈጥሮ ፍልውሃዎች በሚኖራቸው የሙቀት መጠን እንደሚለያዩ መረጃው ጠቁሞ፤ በዚሁ የሙቀት መጠናቸው ልክም በአራት የተለያዩ መደቦች እንደሚከፈሉ ገልጿል፡፡ የሙቀት መጠናቸው ከ25°C በታች የሆኑና ከከርሰ ምድር የሚገኙት ቀዝቃዛ የምንጭ ውሃ (Cold Spring water) ሲባሉ፣ የሙቀት መጠናቸው ከ25-34°C ድረስ ያሉት ደግሞ ለብ ያለ (Tepid Spoizing Spring water) ይባላሉ፡፡ ከ34-42°C ድረስ ያሉት የገፀ ምድር ውሃ ሞቃታማ (Warm Spring water) በሚል መጠሪያ ሲታወቁ ከ42°C በላይ ያሉት ደግሞ ፍልውሃ (hot Spring water) ተብለው ይጠራሉ፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው እነዚህ የተለያየ የሙቀት መጠን ያላቸው የተፈጥሮ ፍልውሃዎች፤ እንደሙቀት መጠናቸውና እንደማዕድን ይዘታቸው የሚሰጡት የፈውስ አገልግሎትም ይለያያል፡፡ የሙቀት መጠናቸው ከፍ ያለ ፍልውሃዎች እንፋሎታቸው ከባድ በመሆኑ የደም ግፊት፣ የልብ ድካም፣ የካንሰር፣ የጉበትና የኩላሊት ህሙማንና ነፍሰጡር ሴቶች ባይጠቀሙ ተመራጭ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡