Administrator
ወሬ ሲበዛ ጭቃ ከግድግዳ ተፍረክርኮ ይወድቃል፡፡ ሙቀጫም ለጭፈራ ይነሳል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ከብዙ ዓመታት በፊት ሰዎች እንደ ዛሬ ሳይሰለጥኑ በፊት፤ በአንዲት ትንሽ ከተማ አንድ እንደ ተዓምር የሚቆጠር ነገር ተፈጸመ፡፡ አንድ ቀንድ ያለው ጉጉት በአቅራቢያው ከሚገኘው ጫካ መጥቶ ከአንድ ሰው ግቢ ከሚገኝ የእህልና የከብት መኖ፣ እንዲሁም ጥራጥሬ መጋዘን ውስጥ ይገባል፡፡ ሲነጋ እንዳይወጣ፤ ሌሎች ዶሮዎች ያዩኝና ልዩ ዓይነት ወፍ መሆኔን ሲረዱ ይጮሃሉ፡፡ ስለዚህ ዝም ብዬ ልቀመጥ ብሎ ወሰነ፡፡
ጠዋት የግቢው አሽከር ለከብቶች መኖ ሊወስድ ሲመጣ ጉጉቱን ጣራው አግዳሚ ላይ ሆኖ አየውና ደንግጦ “ጭራቅ! ጭራቅ!” እያለ እየጮኸ ወደ ጌትየው ሄዶ ተናገረ፡፡ የቤቱ ጌታም “አይ አንተ! አንተንኮ እንደ እጄ መዳፍ ነው የማውቅህ፡፡ በሰፊ ሜዳ ቁራና ጥንብ - አንሣ የማባረር ልብ አለህ! አንዲት ጫጩት አንድ ጠባብ ቦታ ሞታ ብታይ ግን ወደዚያ ለመቅረብ ትልቅ ዱላ ፍለጋ ትሄዳለህ፡፡ ይሄን ጭራቅ ያልከውን እኔ ራሴ ሄጄ አየዋለሁ፡፡ ውሸት ቢሆን ወዮልህ!”
ጌትዬው ወደ መጋዘን ገብቶ ሲያይ በድንጋጤ ተስፈንጥሮ ወጣ፡፡ ሮጦ ወደ ጎረቤቶቹ ሄዶ “ጎበዝ ማለቃችን ነው፡፡ አንድ አደገኛ ፍጡር ግቢዬ ገብቷል! ወጥቶ ወደ ከተማ ከገባ ህዝብ ማለቁ ነው፡፡ እንረዳዳና እዚሁ እርምጃ እንውሰድበት!” አለ፡፡
ወሬው ወዲያው ከመንደር መንደር በረረ፡፡ ከመንገድ መንገድ ሮጠ፡፡ ሰዉ ከፊሉ ገጀራ፣ ከፊሉ ቆንጨራ፣ ከፊሉ ጦር፣ አካፋም፣ ማጭድም እያየዘ ወደግቢው ይመጣ ጀመር፡፡ ሰራዊት እንጂ አንድ ቀንዳም - ጉጉት ሊገድል የመጣ አይመስልም፡፡ በመጨረሻ ጭራሽ የከተማው ከንቲባ በሌሎች ሹማምንት ታጅበው መጡ፡፡ በተማው ለጥንቃቄ በየገበያው ምሽግ አሰርተዋል፡፡ አንድ የጎበዝ አለቃ ወደጉጉቱ ሄዶ ነበር፡፡ ድምፁን ሲሰማ በርግጎ ተመለሰ፡፡ ሌሎች ሁለት ሰዎች ሞከሩ፡፡
ጉጉቱ ዓይኑን እያጉረጠረጠ በፍርሃት የሚያወጣው ድምፅ መብረቅ የመታቸው ያህል አስደግንጧቸው ዘለው ወጡ፡፡ በመጨረሻ አንድ መንዲስ የሚያህል ሰው፣ ያገሩ ጦረኛ ነው የሚባል ጀግና፣ ከጉጉቱ ሊተናነቅ ወስኖ መጣ፡፡ ከዛም በፉከራ ቃና “አንድን ጭራቅ “ጉድ! ጉድ!” በማለትና ዐይን ዐይኑን በማየት ልታባርሩት አትችሉም፡፡ ሁልሺም ቡከን ነሽ፡፡ ይሄን ጭራቅ ቀንዱን ይዤ ከጣራው ማውረድ አለብኝ! አለ፡፡ ሁለቱም የመጋዘኑ በር ብርግድ ብሎ ተከፈተ፡፡ አሁን ጉጉቱ ከጣራው አግዳሚ እንጨት ላይ ተቀምጦ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ጀግናው መሰላል አምጡልኝ አለ፡፡ መጣለት፡፡ ሰው ከፊሉ “ደፋር!” “አምበሳ!” አለው፡፡ ከፊሉ ይፀልይለት ጀመር፡፡
ጀግናው ወደ ጉጉቱ እየቀረበ ሄደ፡፡ ጉጉቱ ሁኔታውን በመጠራጠር የህዝቡን ጩኸት በመስማትና ምንም መውጫ እንደሌለው በማሰብ፤ ክንፎቹን አርገበገበ፡፡ ኩምቢውን ከፈተ፡፡ መንቆሩን ለጦርነት ያዘጋጀ መሰለ፡፡ ኩ-ፍ-ኩ-ኩ-ህ!” እያለ በፍጥነት መጮህ ጀመረ፡፡ ሰው “በለው!” “ያዘው” “አሳየው!” እያለ ከሥር ይጮህ ጀመር፡፡
“አይ ያገሬ ሰው! እኔ ያለሁበት ቦታ ቆመሽ ቢሆን አዳሜ ትንፍሽ አትይም ነበር!”
ጥቂት እርከን ለመውጣት ሞከረና ጀግናው፤ መርበትበት፣ መራድ ጀመረ፡፡ ቀስ እያለ በደረጃው ወረደ፡፡ ሰውም “አውሬው በትንፋሹ መርዞት ነው እንጂ የእኛ ጀግና እንዲህ ያለ ሰው አልነበረም፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ያለ አውሬ ፊት ቆመን ህይወታችንን ማጥፋት አለብን እንዴ?” እያለ መንሾካሾክ ጀመረ፡፡ “ከተማችንን እንዳያጠፋ ምንድንነው የምናደርገው ማለት ቀጠለ?” በመጨረሻ ከንቲባው መፍትሄ አመጡ፡፡
“ከመዘጋጃ ቤቱ ወጪ ተደርጎ ለመጋዘኑ ባለቤት የገንዘብ ካሳ እንስጥ፡፡ ለእህሉም. ለጭዱም፣ ለነዶውም መግዣ ይካካስለትና መጋዘኑ ከነአደገኛው አውሬ ይቃጠል! አሁን ለኢኮኖሚ የምናስብበት ጊዜ አይደለም!” ብራቮ ተባለ! ተጨበጨበ!
መጋዘኑ በአራቱም አቅጣጫ እሳት ተለቀቀበት፡፡ ምስኪኑ ወፍ በነበልባል ተለብልቦ አሰቃቂ ሞት ሞተ!
* * *
ነገሩ “አይ መሬት ያለ ሰው!” ያልነውን ያስታውሰናል፡፡ ነገርን በቅጡ አለማየት አሳቻ ፍፃሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ ስለሆነም ወፍ አይተን ጭራቅ አየን እንላለን፡፡ አገሬው መንገኛ ከሆነ እንግዲህ ይህንኑ ጭራቅ ጭራና ቀንድ ጨምሮለት ያልሆነ ስዕል ፈጥሮ መዐት ይፈጥራል፡፡ የሰማህ ላልሰማህ የተባለ ይመስል እንደአዋጅ - ቃል ወሬ ይለፍፋል፡፡ ከዚያ ያገሩ ሹማምንት ያገባናል በሚል በተሳሳተው ነገር ላይ መመሪያ ይጨምሩበታል፡፡ መፍትሄ የማይፈጥር፣ ችግር ብቻ የሚያወራ ህዝብ ያልታደለ ነው፡፡ ኑሮ እንጉርጉሮ እንዳይሆን ማሰብ ያሻል! በወሬ የሚኖር ሰው፣ ነገር ያባብሳል እንጂ አንድ የመፍትሔ ጠጠር አይጥልም፡፡ ጎበዙን በለው! በለው! ለማለት የተፈጠሩ ይመስል፤ “በቅሎ ግዙ ግዙ አንድ አምሌ ላያግዙ!” ይሆናል ግርግሩ፡፡ ራሳችን በፈጠርነው የተሳሳተ ምስል “አስፈሪ! አደገኛ! …” እያልን፤ እሱኑም ፈርተን፤ ሌላውንም አስፈርተን፣ እሳት እንለኩሳለን! ይሄው ነው የአገራችን ፖለቲካ ነገረ - ሥራ!
“ጥፋታችንን አናምን፣ ሀጢያታችንን አንቀበል
ሁሌ ዝግጁና ፈጣን፣ በሌላው ላይ ለመቸከል
ደባ ነው መንገዳችን ሰርክ
ለእምዬ የአብዬን እከክ፣ በጥበብ ቅብ ለመላከክ!”
እንዳለው ገጣሚው፣ ራሳችን የሰራነውን ጥፋት በፈረደበት የበታች ወይም ቀን የጣለው ላይ መላከክ ነው ስራችን፡፡ ጥንት በአንድ አገር ዕምነት. ፍየል የዋህ ናት ትባል ነበር፤ አሉ፡፡
በሥርየት ቀን ቄስ ፍየሏ ጭንቅላት ለይ እጁን አድርጎ፣ የህዝቡን ሀጢያት ይናዘዛል፡፡ ጥፋት ሁሉ ወደ የዋህ ፍየል ይሄዳል፡፡ ይተላለፋል፡፡ ከዚያ ፍየሏ ወደ በረሀ ትነዳለች፡፡ እዛው ትቀራለች፡፡ የሰዉን ኃጢያት ሁሉ ይዛለት ጠፋች ማለት ነው፡፡ እንግዲህ Scapegoat የሚለው የፈረንጆች ቃል ከዚህ ነው የመጣው” ሊባል ይችላል፡፡ በሌላ ላይ ማሳበብ፣ በሌሎች ላይ መጫን ነው የአበሻ ኑሮ ዘዴ፡፡ ማዖ የባህል አብዮቱ ከሽፎ ክፉኛ ሲወድቅበት ምንም ይቅርታ አልጠየቀም፡፡ ይልቁንም በከፍተኛው የፓርቲ አመራር አባል ላይ ላከከ፡፡ የግል ፀሐፊውንም እንኳ ከወንጀሉ ነፃ አላደረጋትም፡፡ የእኛን ጨምሮ በየትም አገር በዘመቻም፣ በፕሬስም፣ በማፍረስም፣ በመገንባትም አንዳንድ የዋህ ፍየል አይጠፋም፡፡ ያውም እንደ ሰበብ ተደርጎ ሲቆጠር የማያጉረመርም ፍየል! ሌላ ምሣሌ:- ጥንት ጃንሆይ ለፀሐፊ ትዕዛዙ በቃል መመሪያ ይሰጡ ነበር አሉ፡፡ ያ መመሪያ ወደ ሥራ ተመንዝሮ ውጤቱ ሰናይ ከሆነ ምስጋናው ለጃንሆይ ይሆናል፡፡ ያልተሳካ ከሆነ ግን እርግማኑ ከፀሐፊ ትዕዛዝ ራስ አይወርድም፡፡ ዓለም የሥርዓተ- መላከክ (escapegoatism) ዓለም ነው፡፡
በተግባርና በወሬ መካከል ያለው ገደል - አከል ርቀት ሳይገደብ ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ወሬ - ናፈቅ ትውልድ አገር ይሸረሽራል! “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚለው የአበው አነጋገር ቧልት አይደለም፡፡ “ወሬ ሲበዛ ጥበብ ዋዛ” እንደማለት ነው፡፡ ወሬ ሲበዛ ያልተሰራው ተሰራ፣ ያላሸነፈው አሸነፈ፣ ያልቀናው ቀና ማለትን ይወልዳል፡፡ ከጊዜ ብዛት ሰው ያምናል፡፡ ከዚያ ውሸት ሁሉ ዕውነት ይመስላል፡፡ “ወሬ ሲበዛ ጭቃ ከግድግዳ ተፍረክርኮ ይወድቃል፡፡ ሙቀጫም ለጭፈራ ይነሳል” የሚለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው!
ኤሌክትሪክ በየሰዓቱ ይጠፋል “የእጃችንን አገኘን” -10 ቢ.ብር ሲባክን ዝም ብለናል
15 ቢ. ብር የፈጁትን የነፋስ ተርባይኖች፤ በ5 ቢ.ብር የውሃ ግድብ መተካት ይቻላል
ከ10 ቢ. ብር በላይ ሃብት በከንቱ ባከነ፤ እንደ ዘበት በነፋስ ተወሰደ ማለት ነው
በረሃብተኛ ድሃ አገር፣ ይሄ ሁሉ ብክነት እብደት ነው? ወንጀል ነው? ወይስ ምን?
ግን፤ ወይ ነገሬ አላልነውም፤ ወይ አብረን አጨብጭበናል፤ ወይ በዝምታ ፈቅደናል
የግድብ ግንባታን የሚቃወሙ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ መጫወቻቸው አድርገውናል
ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችን፤ “የድህነት ጠበቃ” ብለዋቸው ነበር
አገር አመት የነፋስ ተርባይኖች አቅም (ሺሜዋ) በአመት ያመነጩት ሃይል (ሺ ጊዋሃ) የተርባይኖቹ ብቃት
ጀርመን 2005 31 50 18%
ፈረንሳይ 2005 7.6 15 22%
ፖላንድ 2005 2.5 5.6 25%
ብሪታኒያ 2005 8.7 19 25%
ስፔን 2005 23 49 24%
ጣሊያን 2005 8 13.6 19%
አሜሪካ 2001 4 6.7 19%
በውሃ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ጣቢያዎች ብቃትስ? ከ40 – 50%
መንግስት ባለፈው ወር የተፈራረመውን ውል ጨምሮ፣ በነፋስ ተርባይን ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ሶስት ጣቢያዎችን ለማቋቋም 770 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ሃብት አፍስሷል። ቀላል ገንዘብ አይደለም። ከ15.4 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። የሶስቱ ጣቢያዎች ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ተደማምሮ ስንት እንደሆነ ደግሞ ተመልከቱ - 325 ሜጋዋት ብቻ ነው። በቃ፡፡ እና …ለዚህ ነው ያ ሁሉ ገንዘብ እየፈሰሰ ያለው? በገንዘብ መጫወት ይሉሃል፣ ይሄ ነው።
ለንፅፅር ያህል የህዳሴ ግድብ፤ ከነፋስ ተርባይኖቹ ጋር የሚመጣጠን የማመንጨት “አቅም” ለመፍጠር ምን ያህል ገንዘብ እንደሚፈጅበት ማስላት እንችላለን። ከግልገል ጊቤ ጣቢያዎች ጋር፣ አልያም ከተከዜ ወይም ከጣና በለስ ግድቦች ጋርም ማነፃፀር ይቻላል። የግድቦቹ አማካይ የግንባታ ወጪ፣ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአንድ ሜጋዋት 1.2 ሚሊዮን ዶላር አይደርስም። በዚህ ሂሳብ፣ ባለ 325 ሜጋዋት ማመንጫ ግድብ ለመገንባት፣ ቢበዛ ቢበዛ በአማካይ 390 ሚሊዮን ዶላር ቢፈጅ ነው (ማለትም፣ ከስምንት ቢሊዮን ብር በታች)። ለነፋስ ተርባይ ሲሆን ግን፣ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ!
ታዲያ፤ በአነስተኛ ወጪ፣ ከውሃ ሃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ግድቦችንና ጣቢያዎችን መገንባት እየተቻለ፣ ያ ሁሉ ገንዘብ ለምን በነፋስ ተርባይን ይባክናል? እንዴ! ከሰባት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ልዩነትኮ፣ በጣም በጣም ብዙ ነው። በየእለቱና በየሰዓቱ መብራት እየተቋረጠ ስራ የሚስተጓጎለው፣ ፋብሪካዎች የሚከስሩት፣ ጨለማ ውስጥ የምናድረው፤ የኤሌክትሪክ ማሰራጫና ማከፋፈያ ተቋማት በማርጀታቸውና በማነሳቸው ነው ተብሎ የለ! በከንቱ የሚባክነውን ገንዘብ፣ ለዚህ ለዚህ ማዋል ይቻል ነበር።
“መቼም፣ የበርካታ ቢሊዮን ብር ሃብት በከንቱ እንዲባክን አይደረግም፤ አንዳች አሳማኝ ምክንያት መኖር አለበት” የሚል ሃሳብ ይመጣላችሁ ይሆናል። ‘ሃሳብ’ ሳይሆን፣ ‘ምኞት’ ብትሉት ይሻላል - ለዚያውም የማይጨበጥ ምኞት። አንዳችም አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርብላችሁ አታገኙም። በነፋስ ተርባይን አማካኝት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት፣ በጣም ከፍተኛ ወጪ እንደሚፈጅ...፣ በይፋ የሚታወቅ፣ በቁጥር የተሰላ፣ ማንም ጤናማ ሰው ሊክደው የማይችል ሃቅ ነው።
አስገራሚው ነገር፣ የነፋስ ተርባይኖች ችግር፣ ብዙ ገንዘብ መፍጀታቸው ብቻ አይደለም። ለካ አንዳንዴ የአገራችን ሰዎች “የባሰ አታምጣ” የሚሉት ወደው አይደለም! በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ነው። በብዙ ወጪ የተተከሉት የነፋስ ተርባይኖች፣ የታቀደላቸውን ያህል ውጤታማ አይደሉም። ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቃታቸው አነስተኛ ነው። የአቅማቸውን 30 በመቶ ያህል እንኳ ብቃት የላቸውም። በውሃ ግድብ አማካኝነት ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ጣቢያዎች ግን፣ የአቅማቸውን 48 በመቶ በሚደርስ የላቀ ብቃት ኤሌክትሪክ እንደሚያመነጩ የኢትዮጵያ የበርካታ አመታት መረጃ ያሳያል። ይህን ለማረጋገጥና የአምና መረጃዎችን ለማየት፤ ብሔራዊ ባንክ በየሶስት ወሩ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች ተመልከቱ። አልያም ከአስር አመታት በፊት የነበረውን መረጃ፣ ከኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሪፖርቶች ታገኛላችሁ።
በአጭሩ፣ የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችን እና የውሃ ግድብ ጣቢያዎችን ስናነፃፅር፣ የነፋስ ተርባይኖች ኪሳራና ብክነት እጥፍ ድርብ መሆኑን በማያጠራጥር መንገድ መገንዘብ እንችላለን። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች፣ የግንባታ ወጪ በግማሽ ያህል ቅናሽ ነው። ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቃታቸው ደግሞ ከነፋስ ተርባይኖች በ70 በመቶ ያህል ይልቃል።
እንዲያውም፣ ወደ ፊት የነፋስ ተርባይኖቹ ብቃት ይባስ እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም። ለምን በሉ። አንደኛ ነገር፣ የነፋስ ተርባይኖች እድሜ በጨመረ ቁጥር፣ ብቃታቸው እየወረደ ይሄዳል። ሁለተኛ ነገር፣ ለነፋስ ተርባይኖች እጅግ በጣም ተስማሚ የሆኑ ነፋስ የሚበዛባቸውና የሚዘወትርባቸው ቦታዎች ናቸው አሁን ጥቅም ላይ የዋሉት። ወደ ፊት ተመሳሳይ ቦታ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። እናም የነፋስ ተርባይኖች ብቃት ከ25 በመቶ በታች መውረድ አይቀርለትም።
የነፋስ ተርባይኖች ብቃት 30 በመቶ እንኳ መድረስ ያልቻለው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። በሁሉም የአውሮፓ አገራትና በአሜሪካ ጭምር፣ ላለፉት በርካታ አመታት በተጨባጭ የተመዘገበ መረጃ ነው። የነፋስ ተርባይን አፍቃሪ ተቋማት ራሳቸው የሚያቀርቡትን መረጃ ብቻ ልጥቀስላችሁ። የነፋስ ተርባይኖችን ለማስፋፋት መንግስታት ተጨማሪ ድጎማ መስጠት ይኖርባቸዋል እያለ ዘመቻ የሚያካሂደው የጀርመን ተቋም HSH NORDBANK፤ ባለፈው መስከረም ወር Sector Study WIND ENERGY በሚል ርዕስ ካቀረበው አመታዊ ሪፖርት የተወሰዱ ጥቂት መረጃዎችን እነሆ።
ከአመት በፊት በ2005 ዓ.ም፤ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ ባለ 31ሺ ሜጋዋት የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች፣ 50ሺ ጊዋሃ ሃይል አመንጭተዋል ይላል ሪፖርቱ። ይህም ማለት የተርባይኖቹ ብቃት 18% ገደማ እንደሆነ ያረጋግጣል። የአሜሪካም ተመሳሳይ ነው። በ2001 ወደ አራት ሺህ ሜጋዋት የሚጠጋ አቅም ያላቸው የነፋስ ተርባይኖች በ19% የብቃት ደረጃ 7ሺ ጊዋሃ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳመነጩ፣ የአሜሪካ የኢነርጂ መስሪያ ቤት ገልጿል - እየተገባደደ ባለው የፈረንጆች አመት ባወጣው ሪፖርት።
የብሪታኒያ ትንሽ ይሻላል። የ8.7ሺ ሜጋዋት አቅም ያላቸው የነፋስ ተርባይኖች፣ በአመት ውስጥ ያመነጩት የሃይል መጠን 19 ሺ ጊዋሃ ነው። (ማለትም ተርባይኖቹ የሚሰሩት በ25% ብቃት ነው)። ምን አለፋችሁ? በየትኛውም የአውሮፓ አገር፣ በየትኛውም ጊዜ፣ የነፋስ ተርባይኖች ብቃት 30% ደርሶ እንደማያውቅ፤ HSH NORDBANK ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል። ከተርባይኖቹ እድሜ ጋርም፣ ብቃታቸው ወደ ሃያ በመቶ ይወርዳል።
ነፋስ ተርባይኖች ብቃት፣ በአንዳንዶቹ አገራት ከ20 በመቶ ሊበልጥ የቻለው አንዳች ተአምረኛ ዘዴ ስለፈጠሩ አይደለም። በመሬት ላይ ሳይሆን በባህር ላይ የተተከሉ ተርባይኖችን ስለሚጠቀሙ ነው ልዩነት የተፈጠረው። ምድር ላይ ከሚተከሉት ተርባይኖች ይልቅ የባህር ላይ ተርባይኖች፤ በጥቂቱም ቢሆን የላቀ ብቃት አላቸው። እንዲያም ሆኖ፤ ብዙም ለውጥ የለውም። አንደኛ፣ የባህር ላይ ተርባይኖች ያን ያህልም የሚያስመካ ልዩነት አያመጡም። ሁለተኛ ነገር፤ ባህር ለሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት፤ ትርጉም የለውም። ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ነጋ ጠባ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችና አጨብጫቢዎች ከሚለፍፉት ስብከት በተቃራኒ፤ የነፋስ ተርባይኖች ብቃት ውሎ አድሮ በተጨባጭ 20% ገደማ እንደሚሆን ለመግለፅ ፈልጌ ነው።
በውሃ ግድብ አማካኝነት የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ጣቢያዎች ግን፣ ከብዙ አመታት አገልግሎት በኋላም በአማካይ 48 በመቶ ገደማ መሆኑን ደግሞ አትርሱ። ለዚህ ማረጋገጫ፣ ከኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽንና ከብሄራዊ ባንክ የ2006 ዓ.ም ሪፖርቶች በተጨማሪ፣ ሌላ መረጃ ትፈልጉ ይሆናል። Study on the Energy Sector in Ethiopia በሚል በጃፓን ኤምባሲ የተዘጋጀውን የጥናት ሰነድ መቃኘት ትችላላችሁ፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በነበረው መረጃ መሰረት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ግድቦች በድምር “ባለ 670 ሜጋዋት” እንደነበሩ በማስታወስ፤ በአማካይ በአመት 2.84 ጊዋሃ ሃይል ያመነጩ እንደነበር ጥናቱ ይገልፃል። (የግድቦቹ ብቃት ከ48% በላይ ነበር ማለት ነው።) የአምና መረጃዎችን ብንመለከትም፣ ተመሳሳይ ውጤት እናገኛለን።
የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችና የውሃ ግድብ ጣቢያዎች፤ ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቃታቸው እንዲያ የሚራራቀው ያለምክንያት አይደለም። የመኪና ሞተርን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ልዩነቱን ለማሳየት ልሞክር። ሞተሩ የአቅሙን ያህል ለመስራት ነዳጅ ያስፈልገው የለ? የነፋስ ተርባይኖች፣ መንቀሳቀሻ ነዳጃቸው “ነፋስ” ነው። ለውሃ ግድብ ጣቢያዎች ደግሞ፤ ነዳጃቸው ውሃ ነው። እንዲህ የየራሳቸው “ነዳጅ” ቢኖራቸውም፤ የነዳጅ አጠቃቀማቸው ግን ይለያል። የነፋስ ተርባይኖች ነዳጃቸውን (ነፋስን) መቆጣጠርና ማጠራቀም አይችሉም። የነዳጅ መቆጣጠሪያና ማርሽ እንደ ሌለው መኪና ቁጠሩት - ለአቀበቱም ለቁልቁለቱም፣ ሲቆምም ሲጓዝም ነዳጁን ይጠቀማል። ነዳጅ ሲቋረጥበት፣ ከማጠራቀሚያ አውጥቶ መጠቀም አይችልም። ነዳጅ ሲያልቅበት በጀሪካን እስኪመጣለት ድረስ መኪናውን አቁሞ እንደሚጠባበቅ ሾፌር ማለት ነው። የውሃ ግድቦች ግን፤ የነዳጃቸው (የውሃ) መጠንን እየተቆጣጠሩ መልቀቅ፤ ብዙ የኤሌክትሪክ ሃይል በማያስፈልግበት ወቅትም ውሃውን ይዘው ማቆየትና ማጠራቀም ይችላሉ። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች፤ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት ብቃታቸው ከፍተኛ የሚሆነው በዚህ ዋና ምክንያት ነው።እዚህ ላይ፤ አንድ ቀላል ጥያቄ ቢነሳ አይገርምም። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች ብቃት በእጥፍ የሚበልጥ ከሆነ፤ ወጪያቸው ደግሞ በግማሽ ያህል ቅናሽ ከሆነ ለምንድነው የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችን ለመገንባት ሃብት የሚባክነው? ወጪያቸው እጥፍ ነው፤ ብቃታቸው ደግሞ በግማሽ የወረደ መሆኑ እየታወቀ!
በነፋስ ተርባይኖች ምትክ 325 ሜጋዋት የሚያመነጭ ግድብ ቢገነባ ኖሮ፣ ወጪው በ7.6 ቢሊዮን ብር ያነሰ ይሆን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፣ የግድብ ሃይል ማመንጫ ብቃት 48% ገደማ ስለሆነ፤ በየአመቱ 1300 ጊዋሃ ሃይል ማመንጨት በቻለ ነበር። የነፋስ ተርባይኖች ግን፤ ወጪያቸው በእጥፍ ቢበልጥም፤ በየአመቱ የሚመነጩት ሃይል 800 ጊዋሃ ገደማ ብቻ ነው።ልዩነቱ እጥፍ ድርብ ነው። የነፋስና የግድብ ማመንጫ ጣቢያዎቹ “ባለ 325 ሜጋዋት” የሚል ስያሜ ቢለጠፍባቸውም፤ ወጪያቸውና ብቃታቸው በጣም ይራራቃል። የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች፤ ወጪያቸው ከፍተኛ፣ ብቃታቸው ደግሞ ዝቅተኛ ነው። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች ደግሞ ወጪያቸው ዝቅተኛ፣ ብቃታቸው ግን ከፍተኛ። እንዳያችሁት፣ “ባለ 325 ሜጋዋት” የተሰኙት የነፋስ ተርባይኖች በአመት 800 ሜዋሃ ገደማ ብቻ ነው ማመንጨት የሚችሉት። የዚህን ያህል የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨትማ፤ ባለ 190 ሜጋዋት የግድብ ማመንጫ ጣቢያ መገንባት በቂ ነው - ለዚያውም ወጪው 230 ሚሊዮን ዶላር አይሞላም - ከ5 ቢሊዮን ብር በታች መሆኑ ነው። እንግዲህ አስቡት፤ ይህችኑ የሃይል መጠን ለማመንጨት ነው ከ15 ቢሊዮን ዶላር በሚበልጥ ወጪ ለነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች እየፈሰሰ ያለው። በሌላ አነጋገር፤ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በከንቱ እንዲባክን ተደርጓል። እብደት፣ ወንጀል ወይስ ምን? የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ በዚህ ብክነት ላይ የተሳተፉና የተባበሩ ሃላፊዎች ውሎ አድኖ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ እስከዚያው ግን መብራት በየሰዓቱ እየተቋረጠብን እንቀጥላለን፡፡ ለነገሩ፤ አስር ቢሊዮን ብር በከንቱ ለነፋስ ሲበተን እያየን ዝምታን የመረጥን ሰዎችስ፤ መብራት ሲቋረጥብን ቢውል ቢያድር ይገርማል፡፡ የእጃችንን ነው ያገኘነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢቦላ ስጋት በወር 8 ሚ. ዶላር እያጣ ነው
በ 6 ወራት 8 አዳዲስ አውሮፕላኖችን አስገባለሁ ብሏል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ በፈጠረው ስጋት ምክንያት የመንገደኞች ቁጥር በመቀነሱ፣ በወር ከ8 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ እያጣ እንደሆነ ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
የአየር መንገዱን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያምን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ኢቦላ ለአየር መንገዱ ከየትኛውም አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ በበለጠ በእንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ተግዳሮት ሆኖበታል፡፡
ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የአየር መንገዱ ዋነኛ ማዕከል፣ በኢቦላ ቫይረስ ከተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የረጅም ሰዓታት በረራ የሚወስድ ርቀት ላይ ቢገኝም፣ በሽታው በአየር መንገዱ ተጓዦች ቁጥር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ አልቀረም ያሉት አቶ ተወልደ፤ ሁኔታው በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚቀየርና የመንገደኞች ቁጥርም ወደነበረበት እንደሚመለስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡በአገራቱ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ፣ በመላ አህጉሪቱ ከሚደረጉ በረራዎች በአብዛኞቹ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩንና በሽታው ለአፍሪካ አየር መንገዶች ዋነኛው ስጋት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢቦላ ወደ አፍሪካ አገራት በሚጓዙ መንገደኞች ላይ ስጋት መፍጠሩን የጠቀሰው ዘገባው፤ በተለይም በእስያውያን መንገደኞች ዘንድ ያለውን ፍላጎት እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ በዘርፉ የሚታዩ የገበያ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ አየር መንገዱ የቀየሳቸውን የረጅም ጊዜ የዕድገት ዕቅዶች መተግበሩን እንደሚቀጥል ገልጸው፣ እስከ መጪው 2015 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት፣ 3 ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ጨምሮ 8 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ገዝቶ በስራ ላይ እንደሚያሰማራ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለት ቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት የሚውል የ41.4 ሚሊዮን ዶላር ብድር አይኤንጂ ካፒታል ከተባለ አሜሪካ የፋይናንስ ተቋም ማግኘቱን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የገንዘብ ብድሩ መገኘቱና አውሮፕላኖቹ መገዛታቸው፣ በአፍሪካ ትልቁ የጭነት አየር መንገድ ሆኖ የመዝለቅ ዕቅድ ለያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቅምንና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተገልጿል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢቦላ ሰበብ እየተገለሉ ነው
የዋሽንግተን የጤና ዳይሬክተር ጆክሴል ጋርሺያ
የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የጤና ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ጆክሴል ጋርሺያ በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን በኢቦላ ምክንያት እየተገለሉ እንደሆኑ ዘ ዋሽንግተን ታይምስ ዘገበ፡፡
ስለ ኢቦላ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በተለይ በታክሲ ሾፌርነት በመስራት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችን እያገለሉ እንደሚገኙ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አሽከርካሪዎቹ አፍሪካውያን እንደሆኑ ሲያረጋግጡ ቫይረሱን ያስተላልፉብናል በሚል ስጋት ከመኪና እንደሚወርዱ ተናግረዋል፡፡
የመገኛኛ ብዙሃን ሰራተኛ የሆነ አንድ ግለሰብ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወደ አሜሪካ ሲገቡ ለምን የኢቦላ ምርመራ አይደረግላቸውም የሚል ጥያቄ እንዳቀረበላቸው ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ከሁለቱ አገራት ዜጎች ጋር የእጅ ሰላምታ የማይለዋወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዳይሬክተሩ፤ የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎችም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴቸው በኢቦላ ሰበብ መገለል እንደሚደርስባቸው አስታውቀዋል፡፡
በዋሽንግተን ከሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡
“ግልፅና ድብቅ ከብርድልብስ ስር” የሥዕል አውደ ርዕይ ተከፈተ
ጋለሪያ ቶሞካ በትላንትናው እለት “ግልፅና ድብቅ ከብርድልብስ ስር” በሚል ርዕስ ለሁለት ወራት የሚቆይ የስዕል አውደ ርዕይ ከፍቷል፡፡ ለአውደ ርዕይ የቀረቡት የሰዓሊ ዘላለም ግዛው የስዕል ስራዎች ሲሆኑ ብዛታቸው 30 ነው፡፡ ሥዕሎቹ በማህበራዊ ህይወት ላይ የሚያተኩሩ እንደሆኑና በብርድልብስ የተሸፈኑ ግለሰባዊ የውስጥና የውጭ ችግሮችን አጉልተው እንደሚያሳዩ ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
ሰዓሊ ዘላለም ግዛው፤ በ1990 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “አለ ፈለገ ሰላም የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት” ዲፕሎማ እንዲሁም በ2003 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘ ሲሆን ከ20 ጊዜ በላይ በአገር ውስጥ አንድ ጊዜ ደግሞ በአየርላንድ ከሌሎች ሰዓሊዎች ጋር ስራዎቹን ለእይታ አብቅቷል፡፡ በግሉ አውደ ርዕይ ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“ለራስ ማን እንደራስ” መፅሃፍ ይመረቃል
በዶ/ር ወሮታው በዛብህ የተዘጋጀውና ከ70 የሚበልጡ ሥራ ፈጣሪዎችን ታሪክ የሚያስቃኘው “ለራስ ማን እንደራስ” የተሰኘ መጽሀፍ ሰሞኑን ለንባብ የበቃ ሲሆን የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአምባ ሆቴል ይመረቃል፡፡ መፅሀፉ በራስ ፈጠራ እንዴት መለወጥ እንደሚቻልና በመፅሀፉ የተካተቱ ከ70 በላይ ሰዎች እንዴት እንደተለወጡ የተርካል ተብሏል፡፡ በምረቃው ዕለት የጂኒየስ ማሰልጠኛ ተቋም ሰልጣኞች ምረቃ፣ የስኬታማ ሰዎች ልምድና ሌሎች ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል፡፡ መፅሀፉ በ60 ብር ለገበያ የቀረበ ሲሆን የመፅሀፉ አዘጋጅ በሥራ ፈጠራና ብልፅግና ዙሪያ በርካታ መፃህፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል፡፡
“ቁምታም ጾም” በገበያ ላይ ዋለ
በወጣቱ ገጣሚ አያሌው እውነቴ የተጻፈውና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ65 በላይ ግጥሞችን የያዘው “ቁምታም ጾም” የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሃፍ፣ ከትናንት ጀምሮ በገበያ ላይ መዋሉን ገጣሚው ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
92 ገጾች ያሉት “ቁምታም ጾም” የግጥም ስብስብ መጽሃፍ፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና በአዟሪዎች በ42.50 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ለውጭ አገራት የመሸጫ ዋጋው 9 የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡
መጽሃፉ በቅርቡ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር እና በደብረ ማርቆስ በሚካሄዱ የስነ-ጥበብ ዝግጅቶች በይፋ እንደሚመረቅ የገለጸው ገጣሚው፣ በቀጣይም ለህትመት የተዘጋጁ ሌሎች የግጥምና የወግ ስብስብ ስራዎችን ለአንባብያን እንደሚያበቃ ገልጧል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጽሁፍ ተማሪ በነበረበት ወቅት፣ በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል የተለያዩ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ገጣሚው፣ ከ17 አመታት በፊትም ለህትመት የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “የበረከቱ አስኳል” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡
“የደመና መንገድ” የአጭር ልብወለድ መድበል ለንባብ በቃ
በይታገስ ጌትነት ገበየሁ የተፃፉ አጭር ልቦለዶችን የያዘ “የደመና መንገድ” የተሰኘ መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ አጫጭር ልብወለዶቹ በተለያዩ ማህበራዊ፣ አገራዊና የፍቅር ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናሉ ተብሏል፡፡ በ124 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ በ35 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “ጥቁር ነጥብ” እና “ደጅ ያደረ ልብ” የተሰኙ መፅሀፍትን ለንባብ አብቅቷል፡፡
የፀሃፍት ጥግ
እችላለሁም አልችልምም ብለህ ብታስብ አልተሳሳትክም፡፡
ሔነሪ ፎርድ
ወንድ ሆኜ ብወለድ ኖሮ አውሮፓን አስገብራት ነበር፡፡
ሜሪ ባሽኪርትሴፍ
(ሩሲያዊ ሰዓሊ፤ ስለ ጥበብ ሥራዋ የተናገረችው)
ሥራ በቅጡ እንዲከወን ከፈለግህ፣ ባተሌ ሰው ምረጥ፤ ሌሎቹ ጊዜ የላቸውም፡፡
ኢልበርት ሁባርድ
ዕድል የምታግዘው ለዝግጁ አዕምሮ ብቻ ነው፡፡
ሉዊስ ፓስተር
ከራሴ ግራ መጋባት ውጭ ለማንም ሰው የማበረክተው ነገር አልነበረኝም፡፡
ጃክ ኬሮአክ
ኤክስፐርት ማለት ማሰብ ያቆመ ሰው ነው፡፡ ለምን ያስባል? ኤክስፐርት ነዋ!
ፍራንክ ሊሎይድ ራይት
የምጠጣበት ብርጭቆ ትልቅ አይደለም፤ ግን ቢያንስ የራሴ ነው፡፡
አልፍሬድ ደ ሙሴ
ሰዎች ስለ ሥነጥበብ እኔ የማውቀውን ያህል ብቻ እንኳን ቢያውቁ፣ ሥዕሎቼን ፈጽሞ አይገዙኝም ነበር፡፡
ኤድዊን ሄንሪ ላንድሲር
ተሰጥኦ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ነው፡፡ ስለኤሌክትሪክ ነገረ - ሥራ አይገባንም፤ ግን እንጠቀምበታለን፡፡
ማያ አንጄሉ
ለንግድ ሥራ ተሰጥኦ አለኝ፡፡ ይሄን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልትማረው አትችልም፡፡
አላን ሹገር
“...ሶስት...መበደር ... የማንችልባቸው ድህነቶች...”
አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ ይሆናልን?
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው ሲደፍሩ ምክንያታቸው ምንድነው?
ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ባለሙያዎች የሚሰጡት ምላሽ፡-
አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ አይደለም፡፡ ሰዎች በሚፋቀሩበት ጊዜ አንዱ ለአንዱ ከማሰብ ውጪ አካልንና ስነልቡናን የሚጎዳ ነገር በፍጹም አይፈጽሙም፡፡
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው የሚደፍሩበት ምክንያት ኃይልን ለማሳየት፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ተገዶ መደፈር እና ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑም እንደ ብቀላ በመሳሰለው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በአዳማ ከተማ በአንድ ወንድ ልጅ ላይ የደረሰ ተገዶ መደፈርን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ የሰጡትን ሐሳብም እናስነብባችሁዋለን፡፡
የልጁ ምስክርነት የሚከተለው ነው፡፡
“...ሰውየው አብሮኝ ለነበረው ሰው እንዲህ አለው፡፡ ...ያንን ጥቁር ልጅ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ስራ ስለአለኝ ለዛ ጉዳይ ስለምፈልገው ጥራልኝ... አለው፡፡ እኔም ላነጋግረው ስወጣ አስቀድሞ እጄን ነበር የያዘኝ፡፡ ጊዜው እኮ መሽቶአል ስለው ...ግድየለም... ዋጋ እንነጋገራለን...በለሊትም ሰው ከምንቀሰቅስ ከእኔ ጋር ብታድር ይሻልሀል አለኝ፡፡ እኔም ግድ የለም ዋጋ ንገረኝና እመለሳለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እቤቱ አስገብቶ በቃ...ልብስህን አውልቅ...ተኛ...የሚል ትእዛዝ ነው የሰጠኝ፡፡ በቃ... ስለፈራሁኝ ብቻ ልብሴን አውልቄ ተኛሁ...”
በአዳማ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ቢሮአቸው የሚገኘው የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ የልጁን ሁኔታ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
“...የዚህ ልጅ ታሪክ... እድሜው 18 አመት ሲሆን ተወልዶ ያደገው ባሌ ሮቤ አካባቢ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ወላጅ አባት በበሽታ ምክንያት በመሞቱ ምክንያት እናትየው ካገባችው ሰው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ጋር መግባባት ስላቃተው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ለተወለዱ ልጆች የሚደረገው እንክብካቤ እና ቤተሰቡ ለእርሱ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበረው በበጎ ፍቃድ አሳዳጊዎች ምክንያት ወደ አዳማ መጥቶአል፡፡ ይህ ልጅ ወደ አዳማ ከመጣ ገና አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖአል፡፡ አስገድዶ የደፈረው ሰው የልጁን ታሪክ በማጥናት እና በማባበል ...እኔ ሆቴል አለኝ... ስራ አስገባሀለሁ... በማለት ሊያግባባው ሞክሮአል፡፡ ከዚያም ባገኘው እለት አስገድዶ ሲደፍረው ልጁ የነበረውን ጉልበት ተጠቅሞ በላዩ ላይ የተቀዳደደ ልብሱን በእጁ ይዞ ... አምልጦ ...ማመን በሚያቅት ሁኔታ ነበር ወደነበረበት የሄደው...”
ወደተጎጂው ስንመለስ የሰውየውን አባባል እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
“...እኔ እኮ ወድጄህ ነው፡፡ አፈቅርሀለሁ፡፡ ገና ሳይህ ነው ልቤ የተሸበረው... ወዘተ ሲለኝ ...እኔ እኮ ሴት አይደለሁም፡፡ ለምን ታፈቅረኛለህ... ብዬ ገፍትሬው ነው ያመለጥኩት፡፡”
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...አስገድዶ መድፈር ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው ወንድ ሴት ልጅ ላይ በሚያደርሰው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት እንደሚስተዋለው ግን ወንድ ወንድን እንዲሁም ሴት ወንድን የሚደፍሩበት አጋጣሚ አለ፡፡”
ወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መኮንን ቤተሰብ ይህ ነገር ሲፈጸም ቅድሚያ የሚሰጡት ሁኔታውን ለማድበስበስ እና ለመካድ እንጂ ልጆቹ የስነልቡና ድጋፍ ወይንም ፍትህ፣ ሕክምና እንዲያገኙ አይደለም፡፡ ይህ ብዙዎች የሚያደርጉት ሙከራ ሲሆን አንዳንድ ወላጆች፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ግን በፍጥነት እርምጃ የሚወስዱ መሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...ብዙ ጊዜ ሬፕ (አስገድዶ መድፈር) የሚያደርጉ ሰዎች ከተመሳሳይ ጾታም ይሁን ከተቃራኒ ጾታ ባጠቃላይም ከሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መፍጠር የማይችሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ምክንያትም ከአስተዳደግ ወይንም ከተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ጥሩ የሆነ መግባባትና ግንኙነት መፍጠር የሚያቅታቸው ከሆነ እንደዚህ ያለውን (አስገድዶ መድፈር) የመሳሰለውን ወንጀል እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸዋል፡፡”
ተገዶ መደፈር የደረሰበት ልጅ እንደገለጸው፡-
“...ድርጊቱን ፈጻሚው ሰው በህግ እንዲጠየቅ በሚደረግበት ጊዜ... እኔ እነዚህን ሰዎች ከየት እንደመጡ አላውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጊትም አልፈጸምኩም፡፡ ልጁንም አልጠራሁትም ...እንዲያውም አላገኘሁትም በማለት ነበር የካደው..” ብሎአል፡፡
አቶ መኮንን እንደሚገልጹትም፡-
“...ልጁ የደረሰበት ጉዳት ከፍ ያለ ስለነበር በጊዜው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ በሚያገኝበት በዚህ ስፍራ ሲመጣ ባለሙያዎች በህግ አንጻርም ሆነ በህክምናው እንዲሁም በስነልቡናው ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኝ ጥረት አድርገዋል፡፡ አስገድዶ ደፋሪው ምንም እንኩዋን ለመካድ ቢሞክርም በወቅቱ ልጁ እራቁቱን ...የተቀዳደደውን ልብሱን በእጁ ይዞ መምጣቱ እና ሌሎች የተለያዩ መረጃዎች በመኖራቸው እውነቱን ለማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡”
አቶ መኮንን የህግ ባለሙያዎችን እና የህብረተሰቡን ትብብር በሚመለከትም፡-
“...ፖሊሶች ለሙያቸው ስነምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ቢያምኑም በጣም የሚያሳዝነው ግን ...አንዳንድ ፖሊሶች ለወንጀለኛው የማገዝ ነገር ይታይባቸው ነበር፡፡ ተጎጂው ባለበት ሌላም ታዛቢ በሚገኝበት ካለምንም ፍርሀት ...እኔ ዋስ ሆኜ አስወጣዋለሁ... ምንም ችግር የለም ሲሉ የተስተዋሉ ነበሩ፡፡ አስገድዶ ደፋሪው በዚህ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የሚታማ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሕግ ሳይቀርብ የቆየ መሆኑን እያወቁ እንደዚህ ያለ ንግግር በተናገሩ ላይ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቢያዝኑም በሌላ በኩል ደግሞ ለሙያቸው ተገዢ የሆኑ ጠንካራ የፖሊስ አባላት አቃቤ ሕጎች እና ዳኞች በመኖራቸው ጉዳዩን በጥንካሬ ይዘው ከዳር በማድረሳቸው ጥፋተኛው በስምንት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አስችለውታል፡፡ ምንም እንኩዋን ጉዳት የሚያደርሱ ባይታጡም ለትክክለኛው ስራቸው የቆሙትን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እወዳለሁ...” ብለዋል፡፡
ሌላው አነጋጋሪው ነገር ሽምግልና ነው፡፡
ተገዶ የተደፈረው ልጅ እንደገለጸው “...የእኔ ወገኖች በሽምግልና ሲጠየቁ አይሆንም... አንቀበልም በማለት አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥፋት ተደግሞ በሌላ ሰው ሊደርስ እንደማይገባ ማስተማሪያ እና ደፋሪው ሰው በህግ መጠየቁ ለተደፋሪውም የሞራል ካሳ ስለሆነ... የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም ገንዘብ እንክፈል... ሌላም ካሳ እንስጥ ሲባል... መልሳቸው አንቀበልም የሚል ስለነበር ወደህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ሆኖአል፡፡” አቶ መኮንን በዚህ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው፡፡ መድሀኒት የሚሆነው ግን ተገቢውንና በጎውን ነገር ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ግን ሰው ለሰው መድሀኒት መሆኑ ቀርቶ መርዝ ይሆናል፡፡ ሽምግልና በሰው ልጆች ዘንድ የታወቀ በጎ ባህርይ ቢሆንም አንዳድ ጊዜ የሚውልበት ቦታ ግን ጎጂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች ተገደው ሲደፈሩ አስገድዶ ደፋሪው በህግ እንዳይጠየቅ ገንዘብ እንክፈል... የሞራል ካሳ እንስጥ የሚባለው ነገር ምክንያቱ ከጥቅም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለማንኛውም... ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የስነልቡና፣ የሞራል፣ የአካል ደህንነታቸው የሚጠበቀው ጉዳት አድራሹ በሚከፍለው ገንዘብ ሳይሆን በህግ ተገቢውን ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡ እንደ አቶ መኮንን አባባል ሰው ሶስት ድህነቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡
ሰው መንፈሳዊ ድህነትን ማሸነፍ ይገባዋል፡፡ ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ፈሪሀ እግዚአብሄር ሊያድርበት ይገባል፡፡ ልጆች ተገደው መደፈር ሲደርስባቸው ለጥፋት አድራሹ ወገንተኛ ሆኖ መቆምና ስለልጆቹ የወደፊት ሕይወት አለማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
ሰው ማህበራዊ ድህነትንም ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሰው ለገንዘብና ለጥቅም ሳይሆን ለእውነት ተገዢ መሆን አለበት፡፡
ሰው በሶስተኛ ደረጃ ማሸነፍ ያለበት ድህነት የአእምሮ ድህነትን ነው፡፡ ሁሉም ሰው የተቻለውን ያህል እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሕይወት እራስዋ ትምህርት ቤት እንደመሆንዋ ማንኛውም ሰው እውቀት እንዲኖረው እራሱን ካዘጋጀ እውቀት ይኖረዋል፡፡
ስለዚህ ... እነዚህ ሶስቱ መበደር የማንችልባቸው ድህነቶች ሲሆኑ ተበድረን ልናሸንፍ የምንችለውን የኢኮኖሚ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ፍላጎት ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር ወይንም ወንጀልን ለመደበቅ ሙከራ ማድረግ ያስጠይቃል ...ሰው... ሽምግልናን ከአግባብ ውጪ ለመተግበር መሞከር የለበትም፡፡

