Administrator

Administrator

Saturday, 29 June 2013 11:08

አዘኔታ!

ምሽቱ ገፍቷል፤ ለኮሌጁ ዘበኞች ደግሞ በጣም ገፍቷል፤ አንድ ተማሪ የግቢውን በር ማንኳኳት የሚፈቀድለት እስከ ምሽቱ 4፡30 ድረስ ነው፤ አሁን 4፡40 ሆኗል፤ በጣም መሽቷል፤ በዚህ ሰዓት ደፍሮም የሚያንኳኳ ተማሪ የለም፤ ዘበኞቹም አዝነው አይከፍቱም፡፡ አሁን ወደ ግቢው ለመግባት ሁለት አማራጮች ናቸው ያሉት፡፡ አንድ፣ በአጥር መዝለል ሌላም፣ዘበኞቹን በጥቂት ብሮች መደለል፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው አደጋ አላቸው፡፡ በአጥር ሲዘል የተገኘ ተማሪ ቢያንስ ለአንድ ሴሚስተር ከኮሌጁ ይታገዳል። ዘበኞቹ ደግሞ እንደ ጉስቁልናቸው አይደሉም፤ በብር አይታለሉም፤ በዚህ ላይ ሁለት እና ሶስት ስለሚሆኑ እርስ በርስ ይጠባበቃሉ፤ብቻ ደረቆች ናቸው፤ በሰላም ጊዜ እንኳ ተማሪዎችን የሻይ ግብዣ አይቀበሉም፡፡ ሌላኛው የተሻለ እና ብቸኛ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ቤርጎ ማደር ነው፡፡ ክፋቱ ግን እርሱ ሁሉንም መፈፀም አይችልም፡፡

“አምላኬ! ምን አይነት ጣጣ ውስጥ ነው የከተትከኝ!” አባቱ ደግሞ ደውለው ነበር፡፡ አደራቸውን ለማደስ፡፡ እሺ ታዲያ አሁን የት ሄዶ ነው? ይህን ያህል ከቶም አምሽቶ አያውቅም፡፡ 4፡53 እንደ አለመታደል ሆኖ ጊዜውም የፈተና ወቅት ነው፡፡ ደብተርና መፅሃፎቼን ለአመል ያህል ልግለጣቸው እንጂ አንዲት ዐረፍተ ነገር እንኳ መረዳት አልቻልኩም፡፡ የስሜት ህዋሳቶቼ በሙሉ ውጭ ነው ያሉት፡፡ ጆሮዎቼ የበሩን መንኳኳት ይጠብቃሉ፡፡ ሲራመድ ዱቄት ላይ ይሄድ ይመስል ኮቴው ባይሰማም መተላለፊያው ላይ ኮቴ ባዳመጥኩ ቁጥር አይኖቼን በር ላይ እሰካለሁ፡፡ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት፣ ከዚያ ድምጹ እየራቀ ይሄዳል፡፡ ጸጥታ፡፡ ነፋስ፡፡ ኃይለኛ ነፋስ፡፡ በመኝታ ክፍላችን ውስጥም ከባድ ጸጥታ ሆኗል። ቀና ብዬ ሌሎች ሶስት የመኝታ ክፍል ጓደኞቼን ቃኘኋቸው፡፡ ሁሉም አንገታቸውን ወረቀት ላይ ደፍተዋል፡፡ ጭንቅላታቸውን መጽሐፍት ውስጥ ደብቀዋል፡፡

እስቲፋኖስ በመሰላቸት ደጋግሞ ፀጉርን ያካል፤ ይፎክታል፤ የዘወትር ልምዱ ነው፡፡ አትክልቲ ጉንጮቹን እጆቹ መዳፎች ውስጥ ቀብሮ ደብተሩ ላይ አድፍጧል፡፡ መኩሪያ አንዳች ነገር ይጫጭራል፣ ሲያጠና እጁ አያርፍም፤ ካልጻፈ አይገባውም ወይም የገባው አይመስለውም፡፡ ክፍላችንንም ቃኘሁት፡፡ ያልተጠረገ ቤት፣ ያልተነጠፈ አልጋ፣ የተዘበራረቁ መጻህፍት፣ ያልተከደነ ደብተር፣ በአልጋው ስር የወደቁ ካልሲዎች፣ ያለቁ እስኪርቢቶዎች… ዐይኔን ወደ ጓደኞቼ መለስኩት። ያልተበጠረ ፀጉር፣ የደፈረሱ አይኖች፣ የጎበጠ ትከሻ፣ መረጋጋት የማይታይበት ፊት… ጥናቴን ትቼ አይኔን ሳንከራትት ጭንቀቴ ገብቷቸው ሶስቱም ካቀረቀሩበት ቀና ቀና እያሉ በቦዙ ዓይኖቻቸው ሲያፈጡብኝ የባሰ ጨነቀኝ፡፡ ሰዓቴን አየሁ፡፡ 5፡10፡፡ ማድረግ የምችለው ነገር ስላልነበር ወጥቼ ቀጥታ ወደ ግቢው በር አመራሁ፡፡ የእስጢፋኖስ የመሰላቸት እና የንጭንጭ ድምጽ ተከተለኝ፡፡ ነፋሻ ምሽት ነው፡፡

እንደምትሀት ይወረወራል ነፋሱ፡፡ ባሕር ዛፎቹን ገንድሶ ሊጥል የፈለገ ይመስላል፡፡ ያ ባይቻለውም ጎንበስ ቀና እያደረጋቸው ነው፡፡ ዛፎቹ መቅኔያቸው እንደተንጠፈጠፈ የሽማግሌ ጉልበቶች እየተንቋቁ አጎንብሰው ይመለሳሉ፡፡ ወደ ግቢው በር እየቀረብኩ በመጣሁ ቁጥር የሰዎች አጀብ ቢጤ ታየኝ፡፡ እርምጃዬን አፈጠንኩ፡፡ ረጃጅም ቅልጥሞቼን አወናጨፍኳቸው፡፡ የክርስቶስ ያለህ! ይህ ተዓምረኛ ልጅ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆኖ ዘበኞቹ መኻል ቆሟል፤ ቀጫጫ ሰውነቱ በብርድ ይንዘፈዘፋል፤ ረዥም ሉጫ ጸጉሩ ተንጨባሯል፤ ጥቋቁር አይኖቹ ወዲያ ወዲህ ይንከባለላሉ፤ ግትር አፍንጫውን ቅዝቃዜ አርጥቦታል፡፡ ተንደርድሬ መሀላቸው ገባሁ፡፡ አዟዙሬ አየሁት፡፡ ደህና ነው። ቆዳው ብቻ በብርዱ ሳቢያ ተጉረብርቦ ፎጣ መስሏል። የምለውን አጣሁ፡፡ ምላሴ እንኳን በእንዲህ አይነት ቀውጢ ሰዓት ይቅርና በደህናው ጊዜም አይታዘዝልኝም፡፡ በጥያቄ ዐይን አየሁት። ወተት ጥርሶቹ ስስ ከንፈሮቹን ሸርተት አድርጎ አሳየኝ። አሁን የሆነውን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብኝም። ድሮውንም ሳየሁ ጠርጥሬያለሁ፤ እስከ አሁንም መሳቀቄ ራሱ ከንቱ ነበር፡፡ ቶማስን እንኳንስ የመቀሌ ኮሌጅ ማህበረሰብ፣ የመቀሌ ህዝብ ሳያውቀው አይቀርም፡፡

ዘበኞቹ በዚህ መኻል አዝነው ከህግ ውጭ እንዲገባ ፈቀዱለት፡፡ ይህን ጊዜ በእፎይታ ተነፈስኩ፡፡ እንዲያውም ትህትናቸዉ ለጉድ ነበር፤ ይግረምህ ብለው ነው መሰለኝ አንደኛው ዘብ እራሳቸውን ለብርድ አጋልጠው ጋቢያቸውን ከላያቸው ገፈው አለበሱት፡፡ ፊታቸው ላይ ያየሁት ርህራሄ ልቤን ዘልቆ ተሰማኝ፡፡ “የት ነበርክ?!” አልኩት፡፡ ፈገግታ - የእሱ ምላሽ፡፡ ቶማስ፣ “የት ነበርክ?!” ደግሜ ጠየቅሁት፡፡ ንጻታቸው የሚያስፈራ ጥርሶቹን በሰፊው ገለጻቸው፡፡ “የት ነ-በ-ር-ክ?!” አሁንም ፈገግታ፡፡ ትከሻውን ይዤ እንደ ጆንያ አራገፍኩት፡፡ “ለምጠይቅህ ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ የት ነበርክ?! ደግሞስ ልብሶችህስ?! ትከሻውን አማታብኝ፡፡ ይዤው መንገድ ጀመርን፡፡ ትዕግስቴ ተሟጦ ቢያልቅም ምን እንደምለው ግራ ገብቶኛል፡፡ የመጨረሻ ልናገር የምችለው ክፉ ነገር ቢኖር፡- “ከእንግዲህ ስለ አንተ አያገባኝም፡፡ ገደል ግባ!” ይሆናል፡፡ በቃ፡፡ “ጃኬቱን ዛሬም አውልቀህ ሰጠህ አይደል?!” ከግድ-የለሽነት በተቀላቀለ አዎንታ ትከሻውን ነቀነቀ። በወዲያኛው ሳምንት የተገዛ ጃኬት ነበር፡፡

እሱንም አውልቆ በሰጠው ጃኬት ምትክ ነበር የገዛነው። ምናልባት የዋጋው ውድነት አሸንፎት አይሰጥ እንደሁ ብዬ ለአንድ ጃኬት 500 ብር ስንከፍል ቅር አላለኝም ነበር፡፡ ይኸው ጉድ ሰራኝ፡፡ ያለ ወትሮዬ የማደርገውን መቆጣጠር ተሳነኝ፡፡ በድጋሚ ይዤ ወዘወዝኩት፡፡ “ለምስኪኑ አባትህ እንኳን አታዝንላቸውም?! እኔንስ ያለ ዕዳዬ ለምን ታሰቃየኛለህ?! ለምን ነብሴን ታስጨንቃለህ?! ለሰው ማዘን፣ የተቸገረን መርዳት፣ መጥፎ አይደለም፡፡ ግን እንዲህ ቅጥ ሲያጣ ደግሞ በምንም መልኩ ቢሆን ጥሩ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዴት ያን ያህል ብር አውጥተን የገዛነውን ጃኬት አውልቀህ ትሰጣለህ?! ለዚያውም በዚህ ብርድ …” አቋረጠኝ፡፡ “ምንተስኖት፣ ሰውየውን ብታያቸው እንዲህ አትልም ነበር፡፡ በዚህ ብርድ በብጣሽ ሸሚዝ ግንብ ስር ኩርምት ብለው ሳያቸው ልተባበራቸው ይገባኝ ነበር፤ ተባበርኳቸው፡፡ እስከ አሁን የቆየሁትም ሳጫውታቸው ነው፡፡ አየህ እናቴ “የተቸገሩ ሰዎች ከምንም በላይ ሰው ይናፍቃቸዋል” ትል ነበር፤ እና ከአንዱ የኔ-ቢጤ ጋር ማውራት ከጀመረች ቀኑ ይመሽ፣ ምሽቱ ይነጋ ነበር…” ጆሮዎቼ በሁለት እጆቼ ደፈንኳቸው፡፡ ሁሌም የሚነግረኝ ይህንኑ ነው፡- እናቴ፣ እናቴ፣ እናቴ … ኪሱ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በሙሉ አራግፎ “የኔ-ቢጤ” ለሚላቸው ያከፋፍላል፡፡

“ለምን?” ስል፡- “አየህ እናቴ ድሆችን መርዳት ያለብን ከተረፈን ላይ ቆንጥረን ሳይሆን ከሚያስፈልገን ጭምር ላይ መሆን አለበት፤ ትለኝ ነበር” ነው መልሱ፡፡ የራሱን ትቶ የሌሎች ተማሪዎችን አሳይመንት ይሰራል፡፡ “ተው” ስል እየፈገገ፡- “አየህ እናቴ ከራሷ በፊት ሌሎችን ታስቀድም ነበር” ይላል፡፡ እንዲህ እንደዛሬ ጃኬቱን አውልቆ የሰጠ ጊዜም፡- “ለምን?” ብዬ ስሞግተው፡- “እናቴ ሁለት ነጠላ ካላት አንዱን ለታረዘ ታለብስ ነበር’ ነው ያለኝ፡፡ ምን ዓይነት ልክፍት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ለተቸገሩ የሚቸረው ንብረቱን፣ ገንዘቡን እና ጊዜውን ብቻ አይደለም፤ እንባውንም ጭምር ነው፡፡ ሳንቲም አጥቶ ኪሱ ሲራቆት (ያው ሰጥቶ ሲጨርስ) እንባው ይጎርፋል፡፡ ደውሎ አባቱ ላይ ይጮህባቸዋል፤ እንደመታደል ሆኖ ደህና ኑሮ አላቸው አባቱ፤ እናም ገንዘብ ይልኩለታል፡፡ ለአራት ወራት መከርኩት፤ ተቆጣሁት፤ አብሬው ላይ ታች አልኩ፤ አሁን ግን ሰለቸኝ፤ መረረኝ፡፡ እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባሁበት ቀን ብላሽ ቀን ነው። አባቱ ናቸው እዚህ ጣጣ ውስጥ የነከሩኝ፡፡ እናም ደግሞ የኮሌጁ ዲን፡፡

ብቻ መጀመሪያ አደራውን ስቀበል ይህን ያህል እቸገራለሁ ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር፡፡ … ከአምስት ወራት በፊት፣ እዚህ ኮሌጅ በገባሁ ማግስት አንድ አባት ልጃቸውን አስከትለው ወደ ዶርማችን መጡ፡፡ የኮሌጁ የተማሪዎች ዲን አብሮአቸው አለ፡፡ ካሉት አምስት አልጋዎች አራቱ በእኔ፣ በእስጢፋኖስ፣ በመኩሪያ እና በአትክልቲ ተይዘው አንድ አልጋ ብቻ ነው ያልተያዘው፡፡ እንግዳው ሰውዬ እና ዲኑ ጎርደድ እያሉ ክፍሉን ቃኙት፡፡ እንደ አጋጣሚ አራታችንም የዚያ መኝታ ክፍል ተጋሪዎች እዚያው ነበርን፡፡ ዲኑ ሲቀሩ አባትና ልጅ በየተራ ተዋወቁን፡፡ ልጅ ቶማስ፣ አባት ሙሉ ወርቅ ይባላሉ፡፡ ቶማስ በቅጽበት ተዋሀደን፡፡ አራታችን መኻል ሆኖ ሲያወራን ለረዥም ጊዜ የምንተዋወቅ እንመስል ነበር፡፡ ሁኔታው ገርሞኛል፡፡ የመጣንበትን ቦታ፣ የተማርንበትን ትምህርት ቤት፣ ሌላው ቀርቶ ውጤታችንን በየተራ አስለፈለፈን፡፡ እርሱም እንደ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ ነው፤ መኩሪያ የሲዳሞ፣ እስጢፋኖስ የጅማ፣ አትክልቲ ደግሞ የዚሁ የመቀሌ ልጅ ነው፡፡ ቀልቤ ቶማስ የጫረው ጨዋታ ላይ እንደሆነ፣ ድንገት ቀና ስል የቶማስ አባት እና ዲኑ ባይናቸው መልዕክት ሲለዋወጡ አየኋቸው፡፡ አፈጠጡብኝ።

ዐይኔን ሰበርሁ፡፡ ተሰናብተውን ሊወጡ በር ጋ ከደረሱ በኋላ ከጓደኞቼ ነጥለው ጠሩኝ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ሄድኩ፡፡ አቶ ሙሉ ወርቅ ባንድ እጃቸው እኔን፣ በሌላ እጃቸው ቶማስን ይዘው መንገድ ጀመሩ፡፡ ዲኑ ከጎኔ ሆኖ ተከተለን፡፡ ወደ እርሱ ቢሮ ነበር የሄድነው፡፡ ቶማስን የፊተኛው ክፍል ውስጥ አቁመው እኔን ይዘውኝ ወደ ዋናው ቢሮ ዘለቁ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን አንዳችም አልተናገርኩም። ቀጣዩ ነገር ምን እንደሚሆን በጉጉት ሳይሆን በአግራሞት እየጠበቅሁ ነበር፡፡ ሁለቱ ጎን ለጎን፣ እኔ ከፊት ለፊታቸው ተቀመጥን፡፡ አቶ ሙሉወርቅ “ልጄ…” አሉኝ ንግግራቸውን ሲጀምሩ፡፡ ልክ እንደ ልጃቸው ቶማስ ብስል ቀይ ይሁኑ እንጂ የሱን ያህል ዐይን አይስቡም፡፡ ቀጭን ናቸው፤ ጆሮአቸው ትልልቅ፣ ጥርሶቻቸውና ዐይኖቻቸው ትንንሽ፣ አፍንጫቸው ደግሞ አጠር አጠር ብሎ ወደ ግንባራቸው ሰቀል ያለ ነው፤ ጸጉራቸው ሉጫ ነው፤ ጥቁር ሉጫ፡፡

ጅምር ንግግራቸውን አቋርጠው ኪሳቸውን መዳበስ ጀመሩ፡፡ ከኪስ ቦርሳቸው ጉርድ ፎቶ አውጥተው አቀበሉኝ፤ ያለችበትን የዕድሜ ክልል መገመት የሚያስቸግር ሴት ምስል አለበት፤ በምንም በምንም ቶማስን የምትመስል ሴት ፎቶ፤ ጸጉር፣ ግንባር፣ ዓይን፣ አገጭ፣ አፍንጫ … ሁሉ ነገራቸው ይመሳሰላል ሳይሆን አንድ ነው፤ እህቱ ወይ እናቱ መሆን አለባት፡፡ “ልጄ” ቀጠሉ የቶማስ አባት፡፡ “ልጄ እርሷ የምታያት ሴት የቶማስ እናት ናት፤ አምና ነው በድንገተኛ ሕመም ያረፈችው፡፡ ቶማስ፣ የኔም የሷም ብቸኛ ልጃችን ነው፤ እና ለእርሱ የነበራት ፍቅር ፍፁም ልዩ ነበር፡፡ እኔን ከነመኖሬም አያስታውሱኝም፡፡ ሁለቱ አብረው ይበላሉ፤ አብረው ይጠጣሉ፤ በአንድነት ይጫወታሉ፤ አንድ ላይ ይተኛሉ … አሁን እንግዲህ አስራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው፡፡ እስከ አስራ ስምንተኛው ዓመት ማብቂያው ድረስ … ማለትም በሞት እስክትለየው ድረስ ግን ጡቷን ይጠባ ነበር፤ ደረቅ ጡቷን ይመጠምጥ ነበር። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ለመኻላ እንኳን አንድም ቀን ተለያይተው ተኝተው አያውቁም፤ እና ይህን ሁሉ ያነሳሁት ለምንድነው? …እ… ዲኑ እንደነገሩኝ በኮሌጁ ውስጥ አንድ አልጋ ለሁለት መጋራት አይፈቀድም፡፡ የኔ ልጅ ደግሞ በዚህ በኩል ከፍተኛ ችግር አለበት። በምንም ዓይነት ብቻውን መተኛት አይችልም።

እና አብሮት የሚተኛ ሰው ከተገኘ ያን ማድረግ እንደሚችል ተነግሮኛል፡፡ ማለት፣ ፍቃደኛ ከሆነ ከአንድ ሌላ ሰው ጋር አልጋ እንዲጋራ ተፈቅዶለታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እናንተ መኝታ ክፍል ውስጥ ተመድቧል …” ንግግራቸውን ገታ አድርገው አዩኝ፡፡ ስሜቴን ለማንበብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዲኑ ዓይኖችም እንዲሁ ላዬ ላይ ይተራመሳሉ፡፡ አንገቴን ደፋሁ፡፡ አካሄዳቸው ገብቶኛል፡፡ ቀጠሉ፡- “…እ…ምን ነበር ያልኩት? …እ…አዎ እናም ደግሞ ያች እናቱ፣ ፍጹም ደግ ነበረች፤ ካፏ ነጥቃ ታጎርሳለች፤ ተጠምታ ታጠጣለች፤ ተርባ ታበላለች፤ እሷ መሬት ወርዳ እንግዳን አልጋ ላይ ታስተኛለች፡፡ የብቻ ነበር የሷስ ደግነት፡፡ እንደኔ ልፋት ቢሆን ይሄኔ ስንት ጥሪት ባየቆየን ነበር፡፡ እርሷ ግን ያመጣሁትን ሁሉ አንዳንዴ ለቤት እንኳ እስኪቸግረን ድረስ ታከፋፍለው ነበር፡፡ ቶማስ ታዲያ ከርሷ ብሶ ቁጭ አለ፡፡ ምኑም አይቀረው፡፡ ልብሱ፣ ጫማው፣ ለኪሱ የሚሰጠው ገንዘብ፣ ሁሉንም እናቱ ታደርግ እንደነበረው ተቸግሮ ላያቸው ያከፋፍላል … ታዲያ አሁን እኔ ብዙ ነገር ያስፈልጋልና ከአዲስ አበባ ገንዘብ ብልክለት አንዳችም አይጠቀምበትም፡፡ ይረጨዋል፡፡ ለዚህም ከጎኑ ሆኖ የሚረዳው ሰው ያስፈልገዋል፡፡

በዚህም በኩል ዲኑ ሊተባበሩኝ ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ገንዘቡን በሳቸው ስም እልካለሁ …እ… ለትምህርት የሚያስፈልጉ መገልገያ መሳሪያዎች ሆኑ ሌሎች አላቂ የየዕለት መገልገያ ቁሳቁሶች የሚያጋዛው ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ እንደ አንተ ተማሪ የሆነ፣ ለተማሪ የሚያስፈልጉትን እቃዎች የሚያውቅ ሰው መሆን አለበት፤ እና በእነዚሀ ሁለት ጉዳዮች ላይ ብትተባበረኝ …እ” ብለው ድንገት ሳግ አፈናቸው፡፡ እንባቸውም ተከተለ፡፡ ነገሮች ግራ አጋቡኝ፡፡ መናገር አልቻልኩም፡፡ ፀጥታ፡፡ የለቅሶ ድምጽ፡፡ ፀጥታ፡፡ የመናገር ተራ ዲኑ ወሰዱ፡፡ የችግሩን ሁኔታ በገባቸው አቅጣጫ ነገሩኝ፡፡ ብተባበራቸው በትምህርቴም ሆነ በሌላ ልጎዳ እንደማልችል ሊያሳምኑኝ ሞከሩ፡፡ ካልፈለግሁ እና የማልችል ከመሰለኝ ግን አለመተባበር ሙሉ መብቴ እንደሆነ አስረዱኝ፡፡ ዝምታ ሰፈነ፡፡ በዚህ ቅጽበት አስቤ ፍቃደኛ ብሆን የሚከተለውን መዘዝ ወይም ፈቃደኛ ባልሆን የሚሰማኝን ፀፀት ማመዛዘን አልቻልኩም።

ፊት ካለው ክፍል የዲኑ ፀሐፊ ታይፕ ስትቀጠቅጥ ይሰማል፡፡ “ላግዝሽ? ታይፕ መምታት እችላለሁ፡፡” የቶማስ ድምጽ፡፡ ማሰብ አላስፈለገኝም፡፡ “እሺ፤ ልተባበራችሁ ዝግጁ ነኝ፡፡” አልኩ፡፡ አቶ ሙሉወርቅ ተንደርድረው በመምጣት አቀፉኝ፡፡ “እንግዲህ እኔም አንተን ቶማስን በማይበት ዐይኔ ነው የማይህ፤ ቃል ኪዳን ፈፀምን ማለት ነው፡፡” አሉኝ፡፡ እኚህ መከረኛ አባት ታዲያ ዛሬም ደውለው ነበር፡፡ ከአሳቤ ስመለስ ጐንበስ ብዬ አየሁት ቶማስን፡፡ አሻቅቦ ያየኛል፡፡ “እሺ አባትህም በሰቀቀን እንዲሞቱ ትሻለህ?!” የሞት ነገር ሲነሳ ስሜቱ በጣም እንደሚነካ አውቃለሁ፡፡ ያለሁበት ሁኔታ ግን ስሜቱን እንድጠብቅለት የሚያደርግ አልነበረም፡፡ የተደበላለቀ ስሜት ሰፍኖብኛል፡፡ ሐዘን፡፡ መታከት፡፡ ንዴት፡፡ ተስፋ መቁረጥ፡፡ ወደ ዶርም ስናመራ መንገድ ላይ እነ እስጢፋኖስን አገኘናቸው፡፡ እኛን ፍለጋ መውጣታቸው ነበር። ቶማስ በወፍራም አዲስ ጃኬት ፈንታ አዳፋ ጋቢ ለብሶ ሲያዩት ምን እንደተከሰተ ለመገመት ጊዜ አልወሰደባቸውም። ሁላቸውም ቃል እንኳን ሳይናገሩ ተያይዘን ወደ ዶርም ገባን፡፡ ብርድ ልብሳችንን ከአልጋችን ላይ አንስቼ አለበስኩት። መቼስ የኔ የምለው ነገር የለኝም፤ ሁሉ ነገር የኛ ሆኗል፤ ጊዜዬ እንኳን የኔ አይደለም፡፡

መኩሪያ እና አታክልቲ ቀኑን ሙሉ ከመጽሐፍ ጋር ሲታገሉ ስለዋሉ በተቀመጡት ማንቀላፋት ጀመሩ፡፡ እስጢፋኖስም ወፍራም ጉንጮቹ ተንጠልጥለዋል። ዐይኖቹ ደክመዋል፡፡ እየተነጫነጨ ራሱን ያካል፡፡ መኩሪያና አታክሊቲ ገፍቶ የመጣ እንቅልፋቸውን መቋቋም ስላልቻሉ ተኙ፡፡ ቶማስ፣ እስጢፋኖስ እና እኔ ብቻ ቀረን፡፡ ብዙም ሳይቆይ እስጢፋኖስ ማላዘን ጀመረ። እስካሁን ባለው ህይወቴ ውስጥ ካጋጠሙኝ ሰዎች ከቶማስ እኩል የሚገርመኝ ሰው ቢኖር እስጢፋኖስ ነው፤ ምንም ነገር አያስደስተውም፤ ሁሌ ይነጫነጫል፡፡ በትምህርቱ ከማንም አያንስም፤ በኑሮውም ብዙ አይጐድለውም፤ ቤተሰቦቹ ከጅማ በየወሩ በቂ ብር ይልኩለታል፤ ግን ሁሌ እንዳላዘነ፣ እንደተነጫነጨ ነው የሚኖረው፡፡ ሲለው የኮሌጁ ምግብ አልተስማማኝም፤ የአገሩ አየር ፀባይ ጥሩ አይደለም፣ እከሌ የሚባል መምህራችን ደካማ ነው፣ ሴቶች አፍጠው ያዩኛል፣ የቤተሰብ ደብዳቤ ዘገየብኝ፣ እያለ እዬዬ ይላል፡፡ ሁሉም ነገር ሞትን ያስመኘዋል፡፡ “ሕይወት ዋጋ ቢስ ናት፣ ከመኖር አስር ጊዜ መሞት ይሻላል፡፡” የሚለው የዘወትር መነባንቡ ነው፡፡

በእርሱ የተነሳ ዶርማችን ውስጥ ሰላም ጠፍቷል። እርሱ መነጫነጭ ሲጀምር ቶማስ እያባበለው ያለቅሳል፡፡ እስጢፋኖስ ግን አይጽናናም፡፡ ቶማስ ሊረዳቸው ያልቻለ ሰዎች ቢኖሩ እስጢፋኖስ ዋነኛው ይሆናል፡፡ አሁንም መነጫነጭ ሲጀምር ቶማስ ማባበሉን ያዘ፡፡ “እስጢፍ ለምን አትረጋጋም? ሁሌ ለምን እንዲህ ትሆናለህ?!” “በዚህች ዓለም ውስጥ ምን መረጋጋት አለ? ይታይህ ቀን ከሌት ማጥናት ነው፤ ለአስራ ስንት ዓመት ፍዳ ማየት፤ መሰቃየት፤ ከዚህ ሁሉ ታድያ ሞቶ መገላገል አይሻልም?!” ጠረጴዛውን በቡጢ ደለቀው፤ እና የሚወደውን የመጽሐፈ መክበብ ጥቅሶች አዥጐደጐዳቸው፤ መጽሐፈ መክበብን በቀን ቢያንስ አንዴ ሳያነብ አይውልም፤ ሙሉ መጽሐፉን በቃሉ ሸምድዷል፡፡ “….ከፀሐይም በታች የተሰራው ሥራ ሁሉ ከብዶኛልና ህይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ንፋስንም እንደመከተል ነው…ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ ሃሳብ የሰው ጥቅም ምንድነው? ዘመኑ ሁሉ ሀዘንና ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው…አሁንም ቢሆን ከኛ ይልቅ የሞቱት ከነሱም ደግሞ ገና ያልተፈጠሩት ይሻላሉ…ፈተና፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መባዘን፣…ከንቱ ነው፤ ሁሉ ነገር…” ቀባጠረ የራሱንም እያከለ፡፡ በቃ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ነገር ነው የሚያስመርረው፤ ሞት የሚያስመኘው፡፡ ቶማስ ብዙም አልገፋም፡፡ የእስጢፋኖስ ጭንቀት አስጨነቀው፡፡ ሊያለቃቅስ ጀመረ፡፡ እስጢፋኖስ ደግሞ ካለ ነገሩ ለሰው ግድ የለውም፡፡ ቶማስ ሰውን መርዳት ሲያቅተው ምን ያህል እንደሚጨነቅ፣ ምን ያህል መንፈሱ እንደሚረበሽ አውቃለሁ፡፡ ደግነቱ እስጢፋኖስ ወዲያውኑ ተነስቶ ተኛ፡፡ እኔም አካሌ ዝሎ ስለነበር ጋደም አልኩ፡፡

እንቅልፍ ሊወስደኝ አካባቢ ቶማስ ነቅነቅ አድርጐ ቀሰቀሰኝና ጠጋ ብሎ በጆሮዬ “እስጢፎን የምረዳበትን ዘዴ ሳስብ ነበር፤ አሁን አገኘሁ፡፡” አለኝ፡፡ አየት አድርጌው ፊቴን አዙሬ ተኛሁ፡፡ ጠጋ ብሎ አቀፈኝ፡፡ ጠዋት አንድ ሰዓት ግድም ዶርማችን ውስጥ ትርምስ ሰምቼ ነቃሁ። ቶማስ አጠገቤ የለም፡፡ አትክልቲና መኩሪያ ዶርማችንን ያምሱታል፡፡ ዘልዬ ተነሳሁ፡፡ ምን እንደሆኑ ብጠይቅ የሚመልስልኝ ጠፋ፡፡ ኋላ መኩሪያ በጣቱ ወደ እስጢፋኖስ አልጋ ጠቆመኝ፡፡ ተንደርድሬ ሄድኩ፡፡ እስጢፋኖስ ዓይኖቹ ተገለባብጠው አልጋው ላይ ተዘርሯል፡፡ “ምን?!” ብዬ ጮህኩ፡፡ ለጥንቃቄው ደንታ አልነበረኝም፡፡ አቅፌ ነቀነቅሁት፡፡ ዝም፡፡ ሰውነቱን ዳበስኩት፤ ይቀዘቅዛል፡፡ ደረቱ ላይ እጄን ጫንኩ፤ ምንም፡፡ ሰውነቴ መንዘፍዘፍ ያዘ፡፡ ቀድሞ የነቃ ሌላውን የመቀስቀስ ልማድ ስለአለ ከእንቅልፉ ሊቀሰቅሱት ሲሉ ነበር እንዲያ ሆኖ ያገኙት፤ ሞቶ። አትክልቲ ፊቱ ገርጥቶ ባለበት ሐውልት መስሎ ተገትሯል፡፡ ከንፈሮቹ ደርቀዋል፡፡ መኩሪያም ምንም አይናገርም፡፡ ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አፉን በሰፊው ከፍቶ ቆሟል፡፡

“ሰዎች እርዳታ እንጥራ እንጂ፡፡ ተንቀሳቀሱ።” እያልኩ በባዶ እግሬ ወጥቼ ሮጥኩ፡፡ ወዴት እንደምሄድ ግን አላውቅም፤ኋላ ነው መንገድ ቀይሬ ወደ ዲኑ ቢሮ ያመራሁት፡፡ እዚያ ስደርስ ቶማስ በር ላይ ቆሞ አገኘሁት፡፡ እርሱም እንደኔው ሁኔታውን ሊነግር እንደመጣ ገባኝ፡፡ “ዲኑ አልገቡም?” አልኩት፡፡ ጥያቄዬን ችላ ብሎ “አየህ ምንተስኖት እስጢፋኖስ በጣም ነበር የሚያሳዝነኝ፤ ልረዳው ባለመቻሌ ዘወትር እንደተጨነቅሁ ነበር፡፡ የተቸገረ ጓደኛን መርዳት አለመቻል በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ አስቤ እንደደረስኩበት ደግሞ ከዚህ የተሻለ እስጢፋኖስን የምንረዳበት መንገድ የለም፤ እና…” አላስጨረስኩትም፡፡ እጄ ቡጢ ሆኖ ሲወናጨፍ ይታወቀኛል፡፡ አጓርቶ ወደ ኋላ ተዘረረ፡፡ ደነዘዝኩኝ፡፡ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁኝ፡፡ እንደምንም ከወደቀበት ተነሳ፡፡ “አንተምኮ ታሳዝነኝ ነበር፡፡” አለኝ ፈገግ እንደማለት ብሎ፡፡ ሲናገር ጥርሶቹ በምላሱ እየተገፉ ወደቁ፤ ባዶ ድድ፡፡ ጭንቅላቴን ይዤ መጮህ ጀመርኩ፡፡ እንባዬ ጅረት ሆኖ ፈሰሰ፡፡ በዚህ መሃል አእምሮዬ ውስጥ አንድ ነገር ፈነዳ፡፡ “ለእናቱም ያዝንላቸው ነበር ማለት ነው?” ከዚህ በኋላ ማሰብ አልቻልኩም፡፡ ጨለማ ሆነ፡፡ ፀጥታ ሆነ፡፡ (ውድ አንባቢያን- ከዚህ በላይ የቀረበው ታሪክ በድጋሚ የወጣ ነው)

ከሁለት ሳምንት በፊት 36ኛ ዓመት ልደቱን ያከበረው እና “ጄይዙስ” የተባለ አዲስ አልበሙን ከሰሞኑ ለገበያ ያቀረበው ካናዬ ዌስት፤ የዘመኑ ስቲቭ ጆብስ እኔ ነኝ ሲል ተናገረ፡፡ በሌላ በኩል ካናዬ ዌስት እና ፍቅረኛው ኪም ካርዴሽያን ከሳምንት በፊት የመጀመርያ ሴት ልጃቸውን የወለዱ ሲሆን ኖርዝ ኖሪ ዌስት የሚል ስምም አውጥተውላታል፡፡ ሁለቱ ዝነኞች ለሴት ልጃቸው ያወጡት ስም ለብራንድ አይመችም ተብሎ ቢተችም ከተወለደች ወር ያልሞላትን ህፃን የመጀመርያ ፎቶ ለማግኘት የመገናኛ ብዙሃን እሽቅድድም ላይ እንደሆኑ የጠቀሱት ዘገባዎች፤ የህፃኗ ፎቶ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ሰሞኑን ሁለት ሚዲያዎች የኖርዝ ኖሪ ዌስት የመጀመርያ ፎቶን አግኝተናል በማለት ህትመታቸውን ቢያሰራጩም ፎቶው ሃሰተኛ እንደሆነ መታወቁን ቲኤምዜድ ዘግቧል፡፡

“ፒፕል ማጋዚን” የብራድ ፒት እና አንጀሊና ጆሊ ሁለት መንታ ልጆችን የመጀመርያ ፎቶ በ14 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶ ማተሙን ያስታወሰው ዘገባው፤ ቤተሰቡ ይህን ገንዘብ ለበጎ አድራጎት እንደለገሱ እና ካናዬ እና ፍቅረኛውም ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጽሙ ይገመታል ብሏል፡፡ የመጀመርያ ሴት ልጁን ባገኘ በማግስቱ “ቀጣዩ ስቲቭ ጆብስ እኔ ነኝ” ሲል የተናገረው ካናዬ ዌስት፤ “በኢንተርኔት፤ በሙዚቃ፤ በፋሽንና በባህል የምፈጥረው ተፅእኖ እንደ ስቲቭ ጆብስ አብዮተኛ ያደርገኛል” ብሏል፡፡

በራፐርነቱ የሚታወቀው ካናዬ ዌስት፤ 100 ሚሊዮን ዶላር ሃብት ሲኖረው፤ በቴሌቭዥን ሪያሊቲ ሾው እና በፋሽን ኢንዱስትሪው አውራነቷን ያስመሰከረችው ፍቅረኛው ኪም ካርዴሽያን 40 ሚሊዮን ዶላር ሃብት አስመዝግባለች፡፡ ካናዬ ዌስት ከ7ኛ አልበሙ “ጄይዙስ” በፊት አስቀድሞ ባሳተማቸው ስድስት አልበሞች በመላው ዓለም 15 ሚሊዮን ቅጂዎች የተሸጡለት ሲሆን 14 የግራሚ ሽልማቶችን ጨምሮ ከ47 በላይ የተለያዩ ሽልማቶች በማግኘት ከፍተኛውን ስኬት የተቀዳጀ ራፐር ነው፡፡

“ማን ኦፍ ስቲል” በተባለው ፊልም ላይ የሱፐር ማንን ገፀባህርይ በብቃት በመተወን ሄነሪ ካቪል እንደተዋጣለት “ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር” ገለፀ፡፡ እንግሊዛዊው ተዋናይ ሄነሪ ካቪል ሱፐርማንን ለመምሰል ሲል 40 ፓውንድ ኪሎ ቀንሷል ያለው ዘገባው፤ ይህን ለማሳካትም ለ11 ወራት በሳምንት 12 ሰዓታትን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረጉን አትቷል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ለእይታ የበቃው ፊልሙ፤ በመላው ዓለም ያስገባው ገቢ 400 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

የሱፐር ማን ፊልሞች ተወዳጅነት በአሜሪካ ብቻ ተወስኖ ቢቆይም “ማን ኦፍ ስቲል” ከአሜሪካ ባሻገር በመላው ዓለም ተወዳጅነት በማግኘት የመጀመርያው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ዋርነር ብሮስ ለፊልሙ በጀት 225 ሚሊዮን ዶላር ያወጣ ሲሆን፤ የሱፐር ማን ገፀባህርይ በካርቱን ኮሚክ መፅሃፍ፤ በቲቪ ተከታታይ ፊልሞች እና እስካሁን በተሰሩ ፊልሞቹ ላለፉት 70 አመታት ዝናና ስኬትን ተቀዳጅቶ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ “ማን ኦፍ ስቲል” መታየት ከጀመረ በኋላ ከሱፐር ማን ጋር የተያያዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች መሟሟቃቸውን የዘገበው “ብሉምበርግ ኒውስ” በበኩሉ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሱፐር ማን ቲሸርቶች እና አሻንጉሊቶች እንደተቸበቸቡ ገልጿል፡፡

ቁምነገር የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ማዕከል በተለያዩ የጋዜጠኝነት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ትናንት ማታ አስመረቀ፡፡ ለአራተኛ ዙር የተመረቁት 31 ተማሪዎች በመሰረታዊ ጋዜጠኝነት፣ ዜናና ፊቸር አፃፃፍ እና በቃለምልልስ ቴክኒክ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምረቃው የተካሄደው ራስ ሆቴል ጀርባ በሚገኘው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አዳራሽ ነው፡፡

በአንጋፋው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ በ“የሺ ሀረጊቱ” የተሰኘ ዘፈን መነሻነት የተፃፈው ልቦለድ መፅሐፍ ታትሞ ለንባብ ቀረበ፡፡ በዚህ ሳምንት እየተሰራጨ ያለውን መፅሐፍ የደረሰው ደጀኔ ተሰማ ነው፡፡ 235 ገፆች ያለውን መፅሐፍ ያተመው እታፍዘር ማተሚያ ቤት ሲሆን አከፋፋዩ ሊትማን ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው፡፡ መፅሐፉ በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ በሌላም በኩል በጋዜጠኛ አቤል አለማየሁ እና ኤልያስ ገብሩ የተዘጋጀው “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡

ጋዜጠኞቹ 255 ገፆች ባለው መፅሐፋቸው ከ12 ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሐይማኖት ልሂቃን እና ፖለቲከኞች ጋር የተደረጉ ሙግቶችና ውይይቶች አካተዋል፡፡ በመፅሐፉ ያለፈው መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩትና ዘንድሮ ህይወታቸው ያለፈው ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ የመጨረሻ ቃል፣ የሃይማኖት መቻቻል፣ ሕገመንግስት፣ የብርቱካን ሚደቅሳ ፖለቲካ የሚሉና ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ መፅሐፉ በሀገር ውስጥ በ49.60 ብር በውጭ ሀገራት በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘዉ ታዋቂዉ የፊልም ኩባንያ ከ”አባይ ሙቪስ” እና በርካታ ሀገርኛ ሲኒማ በመስራት ላይ የሚገኘዉ እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ የተሰማራዉ ኦክቴት ኮምፒዉተር ቴክኖሎጂ በመተባበር በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀዉን እና የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተመሰረተበትን የ30ኛ ዓመት አከባበር ሥነ-ስርዓት ከሰኔ 23 2005 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 2005ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሜሪላንድ ዉስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያን በሚገኙበትን ይከበራል፡፡በዚህም ዝግጅት ላይ ታዋቂ የሀገርችን አርቲስቶች የሙዚቃ እና የተለያዩ ባህላዊ እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ዝግጅቶችን ያቀርባሉ፡፡ በዝግጅቱም ላይ በርካታ ታዋቂ ስፖርተኞች፣ ጋዜጠኞች የፊልም ባለሙያዎች በዝግጅቱ ላይ ይታደማሉ፡፡ ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ብሉ ኦሽንና ናይት ክለብ በመሪ ሲኤምሲ አካባቢ ተከፈተ፡፡ ክለብ ቪ አይ ፒ ሰርቪስ ያለው መስተንግዶ ጋር የሚሰጥ ከ 70 በላይ ለሰራተኞች እድል እንደፈጠረ በተመጣጣኝ አገልግሎት የተለያዩ ባህላዊና የውጪ አገር ምግቦች ያቀርባል በተለይ አርብና ቅዳሜ በዲጄ ሳሚ ይቀርባል፡፡ ብሉ ኦሽን ናይት ክለብ በዘመናዊ የመብራት እና የድምጽ ቴክኖሎጂ የተዋቀረ በውስጥና የውጭ መስተንግዶ በመስጠት ከሌሎች ናይት ክለቦች በተለይ መልኩ አገልግሎት እንደሚሰጥ ሰኔ 15ቀን 2005 ዓ.ም በተመረቀበት ጊዜ ተገልጿል፡፡

በፋሲል አስማማው ተፅፎ በደረጀ ደመቀ የተዘጋጀው “ጀንኖ” የተሰኘ አዲስ ፊልም ዛሬ በሐዋሳ ከተማ እና በሌሎች ክልል ከተሞች ይመረቃል። በጵንኤል ፕሮሞሽንና ማስታወቂያ ድርጅት ፕሮዱዩሰርነትና በታምሩ ብርሃኑ ፕሮዳክሽን የተሠራው ፊልሙ፣ የሮማንቲክ ኮሜዲ ዘውግ ሲኖረው አልጋነሽ ታሪኩ፤እንቁስላሴ ወርቅ አገኘሁ፣ዘነቡ ገሠሠ፣ ደረጀ ደመቀና ተመስገን ታንቱን ጨምሮ ከ60 በላይ ተዋናዮች ተካፍለውበታል፡፡ ፊልሙ በሐዋሳው የሲዳማ ባህል አዳራሽ በሚመረቅበት በዛሬው ዕለት በዲላ፣ በሻሸመኔ እና በነገሌ ቦረና እንደሚመረቅ የፊልሙ ደራሲ ፋሲል አስማማው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ በቅርቡም በአዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ይመረቃል፡፡

Saturday, 29 June 2013 10:38

የፍቅር ሽልማት

ፍቅር ሽልማት የለውም
አንተ ግን ሽልማት አለህ!
እንደ ትንቢት - ተናጋሪ፣ የነገን ዕውቀት አበጀህ!
የእናት ያባት ዕውቀት ማለት፤
የልጅ ሽልማት ውብ ኩራት!!
የራስህ ትምርት ትጋት
የራስህ ትምርት ንጋት
የዛሬህን ጐዶሎ፣በነገ ጥበብህ መሙላት
ይሄ ብቻ ነው ዓለምህ፣ የራስህ ፍቅር ጉልላት!!
(ነ.መ፤ ኢዮብና አሥቴር ለፍቅር የትምህርት ድል)
ሰኔ 21 2005 ዓ.ም

ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት በሣሉ ብዕረኛ ተፈሪ መኮንን “ግጥም ሞቷል” ሲል በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መርዶ በማርዳት ቁጣዬ የበረታ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከፀሐፊው ጋር የስልክ ሙግት መግጠሜም አልቀረም፡፡ ውሎ ሲያድር ግን የጥበቡን ሰማይ ሳይ ከዋክብት እየነጠፉ፣ ውበት እየጨለመ ሲመጣ ልቤ ደረቴን በስጋት መደብደብ ጀምራ ነበር፡፡ ያ ሥጋትም ስለግጥም ይበልጥ ማሰብ፣ ከዚያም አለፍ ሲል እያነበቡ ሃሳብ ወደማቅረብ የገፋኝ ይመስለኛል እንደተፈራው፡፡ የግጥሙ ሰፈር ልክ የሌላቸው ገለባዎች መፈንጫም መሆኑ አልቀረም፡፡ ነፍስ የሌላቸው ገለባዎች እንደፈርጥ የሚንቦገቦጉትን የብዕር ውበቶች እንዳያንቁ ብዙዎቻችን ሠግተናል። አዝነን አንገታችንንም ደፍተናል፡፡ ግና አሁን አሁን ሰማዩን ሳየው ተስፋ ያረገዘ፣ ውበት ያነገተ ይመስላል፤ ብዙ ገላባዎች ቢኖሩም ፍሬ ያላቸው ወጣት ገጣሚያን መጋረጃውን ገልጠው ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡

ወጣትነት ሙሉነት የሚጠበቅበት ዕድሜ አይደለም፡፡ ወደ ሙሉነት የመድረሻ ጉዞ ፍንጭ እንጂ፡፡ የቀደሙትና ብርቱ የሚባሉት ገጣሚያንም መንገድ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ አሁን የዘመናችን ወጣት ገጣሚያን መንገድ ጥሩ ተስፋ እየሰጠ ነው፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ለጥበቡ ውበት፣ መሥመር እያበጁ፣ ሕይወት እያፈሩ መምጣታቸው አይቀሬ ነውና ልብ የሚሞላ ጉጉት ፈጥሯል፡፡ እውነት ለመናገር የቀደመው ዘመን አፍርቷል ከምንላቸው ገጣሚያን የማያንሱ ገጣሚያን ቁጥርም እየፈጠርን ይመስለኛል፡፡ አሁን የሚያስፈልገን የንባብ ባህል ይበልጥ እንዲጨምር በማድረግ እምቡጦቹ አብበውና አፍርተው፣ ጐደሎዎቻችንን እንዲሞሉ ማስቻል ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ የታተሙ የግጥም መጻሕፍትን ሳይ የተሰማኝ ስሜት ያ ነው፡፡ ተስፋ ያንለጠለጠለ በሣቅ የታጀበ፡፡ ዛሬ ያየነው ተስፋ ነገ በውበት የደመቁ ዓመታት እንደሚወልዱልን አያጠራጥርም፡፡

ቀደም ሲል በዮሐንስ ሞላ መጽሐፍ ላይ የደመቀ ተስፋ እንዳየሁ ሁሉ የወሎው ገጣሚ መንግስቱ ዘገየም ደስ በሚል ልብና ኃይል ተገልጦ አይቼዋለሁ፡፡ ጋዜጠኛ በረከት በላይነህም “የመንፈስ ከፍታ” በሚለው ጥራዙ የፋርስ ግጥሞችን መርጦ በመተርጐምና የራሱን ግጥሞች በማቅረብ የጥበብ ሆዳችንን ረሃብ ለማስታገስ የሚችል አበርክቶት አኑረዋል፡፡ ደስ ይላል፡፡ የበረከት ግጥሞችን በጥልቀት የመገምገምና የመተንተኑን ሥራ ላቆየውና ለጊዜው ቀልቤን የኮረኮሩትን ግጥሞች ልዳስስ መርጫለሁ፡፡ “የፈሪዎቹ ጥግ” ስሜቴን ከዳሳሱት፣ ሃሳቤን ከነጠቁት ግጥሞቹ አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል:- በማያውቀው ስንዝር ዕድሜው እንዳይለካ፤ ባልቀመሰው እርሾ ነገው እንዳይቦካ፤ ይፈራል የሰው ልጅ፤ ይሰጋል የሰው ልጅ አይጨብጥ አይነካ፡፡ አይገርምም! መሸጥ አያሰጋው፣ መግዛት እየፈራ፣ “አለመወሰኑን” ትርፍ ብሎ ጠራ፡፡ እኔ የምለው! ቀኝ ግራ ኋላ፣ ፊት - እስካልተከለለ፤ በጥግ - የለሽ ነገር መሃል መስፈር አለ? ይህ ምስኪን ወገኔ! ላበጀው ጥያቄ እስካልተፈተሸ፤ ቅዠት አቅፎ ያድራል - ሕልሙን እየሸሸ፡፡ ገጣሚው በረከት ተናግሮታል ብዬ የማደምቀው ሃሳብ፣ ሰው ነገር የሚያይበት ተጨባጭ ራዕይ፣ የሚጓዝበትን መንገድ የሚያስተውልበት አይን አጥቶ፣ በሰከረ ዓይን የሚዋዥቅ ሆኗል የሚለውን ይመስላል፡፡ ሁሉ አማረሽ በመሆኑ ወደፊት ፈቅ የሚልበትን ምርጫ እንደ ጨርቅ አውልቆ ጥሏል።

መላ ቅጡ በጠፋ ስካር ውስጥ ተዘፍቆ ትክክለኛ አድራሻውን የሚያሳየውን ሕልሙን ወደ ኋላ ዘንግቷል ነው የሚለው፡፡ ሕልም የሌለውና ሕልሙን የሸሸ ሰው መድረሻው የት እንደሚሆን ሊሰብከን አልሞከረም፡፡ የወደደ ሰው ወደ መጽሐፍ ቅዱሱ ዮሴፍ፣ ወዲህ ቀረብ ሲል ደግሞ ወደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ተጠግቶ “ሕልም አለኝ” የምትለውን ሃሳብ መፈልፈል አለበት፡፡ ለዚያም መሰለኝ “ይህ ምስኪን” ብሎ ለሕልም አልባው ሰው ከንፈር የመጠጠለት! “ሸማኔ ሲፎርሽ” ለኔ ከተመቹኝ ግጥሞች አንዱ ነው፡፡ “ታታሪው” ሸማኔ! ከመመሳሰል ውስጥ ውበትን ቀምሮ፤ “ጥበብ” ያለብስናል ካንድ ቀለም ነክሮ፡፡ ለባሾች አይደለን? እንተያያለን፤ እንተያያለን፤ ኤዲያ!! ጥለቱ ጋ ስንደርስ እንለያያለን፡፡ መቼም አይታክተን! እንወርዳለን ቆላ፤ እንወጣለን ደጋ፤ ጥለት አመሳሳይ ሸማኔ ፍለጋ እዚህ ግጥም ውስጥ ዋነኛው ተዋናይ ሸማኔ ነው፡፡ በእማሬያዊ ፍቺው ምናልባት ሸማኔው ብዙ ሲሆን፤ በብዙ ሊተነተን ይቻላል፡፡

በርግጥም ስለግጥም የፃፉ ምሁራን እንደሚሉት ግጥም ራቁቱን የተሰጣ ባይሆን ይመረጣል፡፡ ለአንባቢው አዲስ ቃና፣ ፍልፍል ውበት ቢያበቅል ደስ ይላል፡፡ እንደግጥሙ ሆኖልን ጥለት ውበት በመሆኑ ሸማኔ ፍለጋ ላይ ታች ካልን ይገርማል፡፡ ደስ የማይለው ግን ለማመሳሰል መሆኑ ነው፡፡ ከመመሳሰል መለያየት ሳይሻል አይቀርም፡፡ እንኳን ጥበብ ሰው ራሱ ቢመሳሰል ሕይወት ትሠለቻለች፤ ተስፋ ትርቃለች። ቀለምም አያምርም፡፡ ዜማም ይጠነዛል፡፡ በረከት ያለው የትኛው መመሳሰል እንደሆነ ስላላወቅን የየራሳችንን መጠርጠር እንጂ የየልባችንን መደምደሚያ ቀዳዳ የለንም፡፡ ቢሆንም እንዲህ ወዲያ ወዲህ መባዘንም ጥሩ ነው፡፡ መመርመር ክፋት የለውም፡፡ የበረከት “የመንፈስ ከፍታ” የፋርሶቹን ግጥሞችም ይዟል፡፡ ለዛሬ ላስቃኛችሁ የወደድኩት ግን የራሱን የበረከትን ስለሆነ አልነካውም እንጂ እጅግ ያደነቅሁለት ምርጥ ግጥሞችን አስሶ መተርጐሙ ነው፡፡ አሁን ግን ወደ በረከት “ልዩነት” ተመልሼ በመሄድ ጥቂት እላለሁ፡፡

ብዙዎች አንደበቱ ባይጥም፤ ለጆሮ ባይመች ትምህርት አሰጣጡ “ኤዲያ” የጋን ውስጥ መብራት በማለት አድመው ካዳራሹ ወጡ፡፡ ጥቂቶች የመምህሩ ዕውቀት፤ “የጋን ውስጥ መብራት” መሆኑን ያመኑ፤ አምነው የተግባቡ አዳራሹን ትተው “ወደ ጋኑ” ገቡ፡፡ እዚህ ግጥም ውስጥ አንድ መምህር ጐልቶ ይታያል፤ ማስረዳት የማይችል፤ ለሌሎች ዕውቀቱን ማካፈል ያልታደለ፡፡ ቅላፄው ለጆሮ የማይጥም። በዚህ ምክንያት የክፍሉ ተማሪዎች ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አንዱ ወገን እዚህ ሰውዬ ዘንድ ተቀምጦ ጊዜ ከማቃጠል አዳራሹን ለቅቆ መሄድ ይሻላል በሚል መምህሩን ንቆ ትቶት ወጥቷል፡፡ ሌላኛው ወገን ደግሞ መምህሩ ቀሽም በመሆኑ ተስማምቷል፤ ሃሳቡን ለሌሎች ማካፈል የማይችል የጋን ውስጥ መብራት በሚለው ተግባብቷል፤ ስለዚህም በተመሳሳይ አዳራሹን ትተው ወጥተዋል። ግን የውስጡን እሣትና ብርሃን ፍለጋ ጋኑን መፈልፈል ይዘዋል፡፡ የጋኑን መብራት ያነቀው ምንድነው የሚል ፍለጋ ይመስላል፡፡

ተስፋ የቆረጠና ተስፋውን ያልጣለ ወገን ለየቅል ቆመዋል፡፡ መምህሩ የተደበቀ ሕይወት፣ መንገድ ያጣ ውበት ቋጥሯል። ግን መንገድ የለውም፤ ጋን ውስጥ ገብቶ ከጋን ውስጥ እሣቱን ማውጣት ይቻል ይሆን…ቢሆንም የበረከት ከፊል ገፀ ባህርያት ወደ ጋኑ ገብተዋል። አዳራሹ ውስጥ መምህሩ ሻማ መሆን ካልቻለ መምህሩ ውስጥ ያለውን ሻማ ፍለጋ መዳከር ሊጀምሩ ይሆን? ማን ያውቃል? “ኑሮና ጣዕም” ሌላው የበረከት በረከት ነው፡፡ ሙያዬን ታውቃለህ፤ ማጀቴን ታያለህ፤ “እንጀራሽ እንክርዳድ፣ ገበታሽ ጣዕም - አልባ” ለምን ትለኛለህ በል ዝም ብለህ ብላ ቸርቻሪ መንግስታት፣ ሰነፍ ገበሬዎች፤ በዝባዥ ነጋዴዎች፣ በበዙባት ዓለም፤ ጠንካራ ጥርስ እንጂ ቀማሽ ምላስ የለም ሕይወትን አትመራመር፣ አታጣጥም…ዓለም በስግብግቦች ተሞልታለች፡፡

ቀልብ ያለው የለም፤ የሰው ጆሮ ሣንቲም ሲያቃጭል ከመደንበር ያለፈ ማጣጣም አቅቶታል ስለዚህ አቃቂር ለማውጣት አትሞክር! ይልቅ እዚህ ውበት ስትፈለፍል፤ ቃና ስታጣጥም ከሩጫው እንዳትቀር ዓለም ውበቷን ጥላለች፡፡ ሰውየው ብቻህን አትበድ…!ሁሉም ነገር ተናካሽ ጥርስ እንጂ አጣጣሚ ምላስ አጥፍቷል፡፡ ሰውየው አትጃጃል ባይ ትመስላለች፡፡ ጠቅለል ሲል በረከት፤ በቃላቱ ሃይል አያስደነግጥም፤ በዜማ ሽባነት ግራ አያገባም፡፡ ቀለል አድርጐ ስንኝ መቋጠር ይችላል፡፡ ግጥም ቀዳሚ ተግባሩ ደስታ መፈንጠቅ ነው - የሚለውን የበርካታ ምሁራን ሃሳብ ይዞ የሚቀጥል ይመስላል። ወደፊት ደግሞ የተሻለ ችቦ ከመንገዱ ሲንቦገቦግ ይታየኛል፡፡ ተስፋው ሩቅ፣ ዕድሜው ለጋ ነው….የወጣትነቱ እፍታ ጥሩ ነው፡፡ የፋርስ ግጥሞቹ ምርጫና ስልት ደግሞ ልዩ ነው፡፡