Administrator

Administrator

    ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ወደ ማላዊ አስገብቷል በሚል ተከስሶ ጉዳዩ በፍ/ቤቱ እየታየ የነበረውን ባሻ አድነው የተባለ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ከፍርድ እንዲያመልጥ አድርገዋል የተባሉት የማላዊ የአገር ውስጥ ጉዳዮችና የደህንነት ሚኒስትር ፖል ቺቢንጉና የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዋና ሃላፊ ሁድሰን ማንካዋላ መታሰራቸውን ኒያሳ ታይምስ የተሰኘው ድረገፅ ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያዊው ስደተኛ የክስ ሂደት ሳይጠናቀቅና ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ተከሳሹን በሙስና ወደ አገሩ እንዲያመልጥ በማድረግ ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል የተከሰሱትን ሁለት ባለስልጣናት ጉዳይ የሙዙዙ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እያጣራ ሲሆን ባለስልጣናቱ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የእስራት ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ዘገባው አመልክቷል፡፡ ከሁለቱ ባለስልጣናት ጋር ተባብረዋል የተባሉ ሶስት የመንግስት ኃላፊዎችም ክስ እንደተመሰረተባቸው ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው ግንቦት ከሌሎች ሁለት የማሊ ዜጎች ጋር በመተባበር ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ማሊያዊ እንዲገቡ አድርጓል በሚል የተከሰሰውን ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ባሻ አድነው ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍ/ቤቱ፤ ባለፈው ማክሰኞ የእስር ትዕዛዝ ያስተላለፈበት ሲሆን ግለሰቡ ግን ባለስልጣናቱ ተሳትፈውበታል ተብሎ በተጠረጠረ ሙስና ከአገር እንዲወጣ መደረጉ ተረጋግጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ክስ የመሰረተው በሚኒስትሩ፣ በሁለት የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች፣ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ውስጥ ባዋለው የፖሊስ መኮንንና ወደ ፍርድ ቤት ሲያመላልሰው በነበረው የስደተኞች ጉዳይ ሃላፊ ላይ ሲሆን ተጠርጣሪዎች የፊታችን ሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ታዝዟል፡፡
ባለስልጣናቱ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ስልጣን ከያዙ ወዲህ በሙስና የተያዙ የመጀመሪያዎቹ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ ጉዳዩ አዲሱ አስተዳደር እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እንዴት እንደሚያስተናግድ የሚፈተንበት ይሆናል ብሏል፡፡
የኡጋንዳ ፖሊስ ካባላጋላ በተባለች ከተማ ዙሪያ ባደረገው ለሁለት ቀናት የዘለቀ አሰሳ፤ ሁለት ኢትዮጵያውያንንና አንድ ኡጋንዳዊን በሽብርተኝነት ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኒው ቪዥን የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘገበ፡፡
አበበ መኮንንና አስፋው ወንድወሰን የተባሉትን ኢትዮጵያውያንና ጁማ ሲምዋንጋ የተባለውን ኡጋንዳዊ ከአስር ቀናት በፊት በሽብርተኝነት ጠርጥሮ ማሰሩን የገለጸው ዘገባው፤ ግለሰቦቹ ከተያዙ በኋላ ጉራንጉር ውስጥ በተከራዩት መኖሪያ ቤታቸው ፍተሻ መደረጉን አስረድቷል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ከየት አግኝቶ በቁጥጥር ውስጥ እንዳዋላቸው የገለጸው ነገር የለም፡፡

     ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለ200 ሺ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎች ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት ሊጀምር እንደሆነ ተገለፀ፡፡
ኦል አፍሪካ ዶት ኮም እንደዘገበው፤ የኩባንያው የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ በስራ ፈጠራ ዘርፍ የሚካሄደውን ልማት ለማሳደግ ከልማት ፕሮግራሙ ጋር በተፈራረመው የትብብር ስምምነት፣ የተመድ የልማት ፕሮግራም በአገሪቱ ድጋፍ ለሚያደርግላቸው 200 ሺ ስራ ፈጣሪዎች ስልጠናና ክትትልን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እገዛዎችን ያደርጋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት፤ የኩባንያው በጎ ፈቃደኛ ስራ አስፈጻሚዎች ለኢትዮጵያውያኑ ስራ ፈጣሪዎች በስትራቴጂና በማርኬቲንግ ላይ

ያተኮረ ሙያዊ ስልጠናና ድጋፍ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ምርጥ ስራ ፈጣሪዎችን የመደገፍ፣ ለ “ፎርአፍሪካ ኢንሺየቲቭ” የፈጠራ ሽልማት እንዲታጩ የማገዝና የኩባንያውን አጋዥ ሶፍትዌር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ስራ ያከናውናሉ ተብሏል።
ባለሙያዎቹ ከዚህ በተጨማሪም ስራ ፈጣሪዎቹ ለወደፊት በማይክሮሶፍት የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ማዕከል በኩል ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንዲለዋወጡና አለማቀፍ እውቅና እንዲያገኙ እገዛ እንደሚያደርጉ ዘገባው አስረድቷል፡፡
አዲሱ የትብብር ስምምነት፣ ማይክሮሶፍት ኩባንያ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማፋጠንና የአገር በቀል ስራ ፈጣሪዎችን አቅም በመገንባት አህጉሪቱ በአለማቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት የማጎልበት ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው “ፎርአፍሪካ ኢኒሺየቲቭ” የተሰኘ ፕሮግራም አካል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

    የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ የብራዚል ጉዞ  በ20ኛው ዓለም ዋንጫ  ተሳትፎ  ባይሳካም፤ ለሁለት ሳምንት ዝግጅት መሄዳቸው አልቀረም፡፡
በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ጥረት በብራዚል በካምፕ በአይነቱ የተለየ ዝግጅት የሚያደርጉት ዋልያዎቹ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ  ተሳታፊነት ብራዚልን በመርገጥ አስደናቂ ብቃት ያሳየችውን አልጄርያ ከመግጠማቸው በፊት ጥሩ ብቃት ላይ እንደሚደርሱ እየተነገረ  ነው፡፡ ከብራዚል ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርገው ብሄራዊ ቡድኑ  በቆይታው የሚያገኘው ጥቅም ያመዝናል። አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቋሚ ተሰላፊ ቡድናቸውን ለመለየት ያሰቡ ይመስላል፡፡ ባሬቶ በሃላፊነቱ በቆዩባቸው ጊዜያት ቋሚ አምበል አለመሾማቸው ሙሉ ቋሚ ተሰላፊዎች አለመለየታቸውን ያመለክታል፡፡ ፍቅሩ ተፈራ፤ አበባው ቡጣቆ እና ፍፁም ገብረማርያም አምበሎች እንደሚሆኑ እየተገመተ ነው፡፡ አዳነ ግርማ፤ ሳላዲን ሰኢድና መስኡድ መሃመድም ለሃላፊነቱ ብቁ መሆናቸውም ይገለፃል፡፡ 19 አባላትን ያካተተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  የመጀመርያው ልዑክ ረቡዕ ወደ ብራዚል ተጉዟል፡፡ ቀሪዎቹ ዛሬ ይበራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በብራዚል በሚኖረው የ14 ቀናት ቆይታ 33 አባላት ያሉት ልዑክ ይኖረዋል። በብራዚሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት ከሰሜን ብራዚል ከመጣው ሬምዋ ከተባለ ክለብ ይጫወታል፡፡ የዛሬ ሳምንት ደግሞ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ጨዋታ አስተናግዶ በነበረው የማኔ ጋሪንቻ ስታድዬም ሁለተኛውን ጨዋታ ያደርጋል፡፡  ከ2 ሳምንት በኋላ  ደግሞ ሬዮ ግሬምዬ ከተባለ ክለብ ጋር ሶስተኛውን የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ሦስቱም የብራዚል ክለቦች በአገሪቱ የክለብ ውድድር በ4ኛ ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ጨዋታዎቹ አቋምን ከመፈተሽ ባሻገር ተጫዋቾቹን ለማስተዋወቅ ጥሩ እድል እንደሚፈጥር አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ተናግረዋል፡፡
በ2015 እኤአ ላይ ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚካሄድ  የምድብ ማጣርያ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር  ከመጫወቱ በፊት ቢያንስ ስምንት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሊያደርግ ይችላል፡፡ ዋልያዎቹ ባለፈው ሰሞን  በሉዋንዳ ላፓላንካ ኔግራስ ከተባለው የአንጎላ ብሄራዊ ቡድን ጋር በመጀመርያ የወዳጅነት ጨዋታቸው ተገናኝተው 1ለ0 ተሸንፈዋል፡፡
በሉዋንዳ 11 ዲ ኔቨምብሮ ስታድዬም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንጎላ ያሸነፈችው ፍሬዲ የተባለ ተጨዋች በ16ኛው ደቂቃ ላይ ባገባት ብቸኛ ግብ። የአንጎላው ፕሬዝዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ የክብር እንግዳ ነበሩ፡፡
ከብራዚል መልስም  በነሀሴ ወር ሁለት የደርሶ መልስ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ፈርኦኖቹ ከተባለው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለማድረግ ቀጠሮ መያዙም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 2 የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታው ጳጉሜ 2 ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከአልጄርያ  ይገናኛል፡፡ አልጄርያና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ እና ዋና ውድድሮች 6 ጊዜ ተገናኝተዋል። እኩል አንዴ ተሸናንፈው በ4 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በምድብ 2 ከአልጄርያ፤ ከማሊ እና ከኢትዮጵያ ጋር ማጣርያ የምትገባው አራተኛ ቡድን ማላዊ ሆናለች፡፡ ማላዊ ምድቡን የተቀላቀለችው በሁለተኛ ዙር ቅድመ ማጣርያ ቤኒን ጥላ በማለፍ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙንሶኜ በሞሮኮው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመካከለኛው እና የምስራቅ ዞን አንድ ተወካይ መኖሩ አይቀርም ብለዋል። ከዞኑ አራት ቡድኖች በምድብ ማጣርያው የሚካፈሉ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሱዳን በቀጥታ ወደ ምድብ ሲገቡ በቅድመ ማጣርያ ያለፉት ደግሞ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በማጣርያ  በሜዳዋ በምታደርጋቸው ጨዋታዎች ባለፈው ሁለት ዓመት ያሳየችው ብቃት ለጥንካሬዋ ምክንያት እንደሚሆን ኒኮላስ ሙንሶኜ ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የመካከከለኛው እና ምሰራቅአፍሪካ ሻምፒዮና አዘጋጅ እንደሆነች ይታወቃል።

         ቁልፍ መረጃዎችን እያወጣ በዓለማቀፍ ደረጃ ክፉኛ ሲያሳጣት የከረመውን ኤድዋርድ ስኖውደን የተባለ ግለሰብ አሳድዳ ለመያዝና ለመፋረድ ደፋ ቀና ማለቷን የቀጠለችው አሜሪካ፣ አሁን ደግሞ ከእሱ የባሰ የብሄራዊ ደህንነት መረጃዎቼን እየዘረፈ በማውጣት ጉድ የሚሰራኝ ሌላ ሚስጥር መንታፊ ግለሰብ መጥቶብኛል ስትል ባለፈው ረቡዕ በይፋ መናገሯን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ስኖውደን የሚያወጣቸውን መረጃዎች እያተመ ለንባብ በማብቃት የሚታወቀው ዘ ኢንተርሴፕት የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ፣ ባለፈው ማክሰኞም ከዚህ ማንነቱ ያልተገለጸ ግለሰብ ያገኘውን የአገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት መረጃ ለንባብ ማብቃቱን ተከትሎ ነው የአሜሪካ መንግስት አሁንም ሌላ አዲስ መረጃ ዘራፊ እንደመጣበት ያመነው፡፡
ዘ ኢንተርሴፕት ለንባብ ያበቃው ጽሁፍ፣ በኦባማ የስልጣን ዘመን አሜሪካ በሽብርተኝነት ጠርጥራ የምትመዘግባቸው ግለሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱንና  የግለሰቦችን መረጃ በሚስጥር እያፈላለገች የመያዝና የመሰለል ስራዋን የበለጠ አጠናክራ መግፋቷን የሚያትት ነው ተብሏል፡፡
ጋዜጣው ግለሰቡ ያወጣቸው መረጃዎች አገሪቱ በሽብርተኝነት ጠርጥራ ከመዘገበቻቸው ዜጎች ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያረጋግጡ ናቸው ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን ጋዜጣው ወጡ የተባሉትን የሚስጥር መረጃዎች በአግባቡ ካለመረዳት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረሱን  መናገራቸውን  አስረድቷል፡፡
ማንነቱ ባልተገለጸው ግለሰብ አማካይነት ወጡ ያላቸውን መረጃዎች ጠቅሶ ጋዜጣው እንዳስነበበው፣ አሜሪካ እስከ 2013 ነሃሴ ወር ድረስ 5ሺህ ያህል ዜጎቿን በከፍተኛ፣ 18 ሺህ ያህሉን ደግሞ በመለስተኛ ደረጃ በሽብርተኝነት ጠርጥራ የመዘገበች ሲሆን፣ 1ሺህ 200 የራሷን ዜጎች ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ 16 ሺህ የተለያዩ አገራት ዜጎችንም ‘በአየር መንገዶችና በድንበር አካባቢዎች ጥብቅ ፍተሻ ሊደረግባቸው የሚገቡ’ በማለት ስማቸውን መዝግባ ይዛለች፡፡
ግለሰቡ ያወጣቸው እነዚህ አዳዲስ መረጃዎች፣ ስኖውደን መረጃ በማውጣቱ ሰበብ ለእስር እንዳይዳረግ በመስጋት ከአሜሪካ አምልጦ ወደ ሩስያ ከኮበለለ በኋላ በነበረው ጊዜ በአገሪቱ ብሄራዊ የጸረ ሽብርተኝነት ማዕከል  የተዘጋጁ እንደነበሩ መረጋገጡን ጠቁሞ፣ ይህም መረጃዎቹን ያወጣው ሌላ ግለሰብ መሆኑን  የሚያሳይ ነው መባሉን ገልጿል፡፡ የአገሪቱ ባለስልጣናት የአዲሱን መረጃ መንታፊ ማንነት ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ግለሰቡ ምናልባትም በሚመለከታቸው የአገሪቱ የደህንነት መረጃ ተቋማት ውስጥ የሚሰራ ሊሆን እንደሚችል መገመቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ግለሰቡ ምን ያህል የሚስጥር መረጃዎችን እንዳወጣም ሆነ መረጃዎቹ አፈትልከው መውጣታቸው በአገሪቱ መንግስት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ የአገሪቱ መንግስት ያለው ነገር ባይኖርም፣ መረጃዎቹ ‘ሚስጥራዊና ለውጭ አገራት መንግስታት ተላልፈው የማይሰጡ መረጃዎች’ በሚል  መለያ በአገሪቱ የደህንነት መረጃ ተመዝግበው እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ጠቁሟል፡፡
አዲሱ መንታፊ ያወጣቸው መረጃዎች ስኖውደን ከዚህ በፊት ካወጣቸው የደህንነት መረጃዎች ጋር ሲነጻጸሩ በሚስጥራዊነታቸው አነስተኛ እንደሆኑ ዘገባው ጠቁሞ፣ ስኖውደን ካወጣቸው 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአገሪቱ የደህንነት መረጃዎች አብዛኞቹ ‘ጥብቅ ሚስጥሮች’ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡

የቻይናው የሞባይል ቀፎ አምራች የግል ኩባንያ ዚያኦሚ፣ የእነጋላክሲና አይፎን ዘመን አክትሟል፣ ከአሁን በኋላ ከማንም በላይ ከፍ ብዬ የምታየው የአገሬ ‘የስማርት ፎኖች’ ንጉስ እኔ ነኝ እያለ ነው፡፡
በአገረ ቻይና የስማርት ፎን ገበያ ዋነኛ ተፎካካሪው የነበረውን የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ በዘንድሮው ሁለተኛ ሩብ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሽያጭ ያስከነዳውና ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣው ዚያኦሚ፣ ይህ ስኬቱ በአገሩ ምድር የስማርት ፎን ገበያ መሪነቱን እንዳስጨበጠው ሲኤንኤን ሰሞኑን ከሆንግ ኮንግ ዘግቧል፡፡
ከአራት አመታት በፊት የተመሰረተው የቻይናው ስማርት ፎን አምራች ዚያኦሚ፣ በአገሪቱ ገበያ ያለውን ድርሻ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት በማሳደግና ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው የገበያ ድርሻ 240 በመቶ ጭማሪ በማድረግ በአሁኑ ወቅት 14 በመቶ ማድረሱ የተነገረ ሲሆን፣ በሩብ አመቱ ለገበያ ያቀረባቸው ስማርት ፎኖች ቁጥርም 15 ሚሊዮን መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ዚያኦሚ በተጠቀሰው ጊዜ 97 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ለቻይና ገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ የካፒታል አቅሙም ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡  
ሳምሰንግን ጨምሮ ዋነኛ ተፎካካሪዎች የነበሩት ሁዋዌ፣ ሌኖቮና ዩሎንግ በሩብ አመቱ በአማካይ 10 በመቶ የገበያ ድርሻ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ዚያኦሚ በቻይና ቀዳሚውን የገበያ ድርሻ ቢይዝም ከአገር ውጭ እምብዛም እንደማይታወቅ አስታውሷል፡፡
ኩባንያው በአገር ውስጥ እያስመዘገበ ያለውን ስኬት በማስፋፋት በአለም አቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ተወዳዳሪና መሪ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ  ሲሆን፣ ይህን እቅዱን ለማሳካት በሚችልበት መንገድ ዙሪያ ባለፈው አመት ከጎግል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር የጋራ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተዘግቧል፡፡
ዚያኦሚ ወደ አለማቀፉ የስማርት ፎን ገበያ ዘልቆ ለመግባትና ንግስናውን ድንበር ለማሻገር የጀመረውን ጉዞ፣ ምርቶቹን ወደ ሩስያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ፣ ታይላንድና ቱርክ በመላክ ለመጀመር እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡
የኩባንያው ስማርት ፎኖች በአሁኑ የቻይና ገበያ በ130 ዶላር እየተሸጡ ሲሆን፣ ዋጋቸው ከአፕል ምርቶች ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሶስተኛ ያነሰ እንደሆነ ተነግሯል፡፡


ትዳር መመስረት የፈለጉ ወንዶች ለመንግሰት ፕሮፖዛል ማቅረብ አለባቸው
የአገሪቱ ወንዶች ከ4 አገራት ሴቶች ጋር መጋባት አይችሉም

ሳኡዲ አረቢያ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር ትዳር መመስረት ለሚፈልጉ ዜጎቿ ጥብቅ የሆነ የትዳር መመሪያ ማውጣቷንና የአገሪቱ ወንዶች ከአራት አገራት ሴቶች ጋር እንዳይጋቡ መከልከሏን ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የሳኡዲ መንግስት ያወጣውን የትዳር መመሪያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር ትዳር መመስረት የሚፈልጉ ዜጎች፣ የትዳር ፕሮፖዛልና የሚኖሩበት ከተማ ከንቲባ ፊርማ ያረፈበት የነዋሪነት መታወቂያ ለአገሪቱ ፖሊስ ማቅረብና ማስገምገም ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመካ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት አሳፍ አልቁሪሽ እንዳሉት፣ መንግስት ትዳር ፈላጊዎች የሚያቀርቡለትን ፕሮፖዛል ገምግሞ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ አዲሱ መመሪያ እንደሚለው፤ ትዳር ፈላጊው ዕድሜው ከ25 ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ትዳር የነበረውና የተፋታ ከሆነ ደግሞ፣ ከሌሎች አገራት ሴቶች ጋር አዲስ ትዳር መመስረት የሚችለው፣ ፍቺው ከተፈጸመ ከከ6 ወራት ጊዜ በኋላ ነው፡፡
“ዘ መካ” የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ሰሞኑን በጉዳዩ ዙሪያ ያወጣውን ዘገባ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደገለጸው፣ ትዳር ፈላጊው የቀድሞ ትዳሩን በህጋዊ ፍቺ ያላፈረሰ ከሆነ፣ አዲስ ትዳር መመስረት የሚችለው በመንግስት ከሚተዳደር ሆስፒታል የቀድሞ ሚስቱ በጸና መታመሟን ወይም መሃን መሆኗን የሚያረጋግጥ አልያም የቀድሞ ሚስቱ አዲስ ትዳር ቢመሰርት እንደማትቃወም የሚገልጽ ማስረጃ ሲያቀርብ ነው፡፡ አዲሱ የሳኡዲ አረቢያ መንግሰት ለአገሪቱ ትዳር ፈላጊ ወንዶች ያወጣው የጋብቻ መመሪያ፣ ወንዶቹ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ተቀጥረው ከሚሰሩ የፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቻድ እና በርማ ሴቶች ጋር በፍጹም ትዳር መመስረት እንደማይችሉ ጥብቅ እገዳ የሚጥል መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡
ሳኡዲ አረቢያ በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቀሰው ዘገባው፣ ዘጠኝ ሚሊዮን ከሚደርሱት ከእነዚህ የውጭ አገራት ሰራተኞች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ወይም 500 ሺህ ያህሉ የትዳር እገዳ ከተጣለባቸው አራቱ አገራት የመጡ ሴቶች መሆናቸውን ጨምሮ ገልጧል፡፡

የሩስያ ዜግነት ያላቸው አባላትን የያዘ አለማቀፍ የድረገጽ ሌቦች ቡድን የአሜሪካን ግዙፍ ኩባንያዎች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ ድርጅቶችን፣ የንግድ ኩባንያዎችንና የግለሰቦችን የድረገጽ መረጃዎችና ፓስ ዎርዶችን (የሚስጥር ቁልፎች) መዝረፉን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ሆልድ ሴኪዩሪቲ የተባለውን ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ቡድኑ ከ420 ሺህ በላይ በሚሆኑ የኩባንያና የግለሰብ ድረገጾች ላይ የፈጸመው ይህ የስርቆት ተግባር፣ በዘርፉ በአለም ዙሪያ የተፈጸመ ትልቁ የመረጃ ዘረፋ ነው፡፡ ዘራፊዎቹ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢሜይል አድራሻዎችን የሚስጥር ቁልፍ በርብረው እንዳገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ መሰል ተግባር ከተፈጸመባቸው መካከልም በዓለማችን ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች እንደሚገኙበት የሆልድ ሴኪዩሪቲን መስራች አሌክስ ሆልደን መናገራቸውን አስረድቷል፡፡
አስር ያህል አባላትን የያዘው ይህ የዘራፊዎች ቡድን ተቀማጭነቱን ያደረገው፣ ከካዛኪስታንና ከሞንጎሊያ ጋር በሚዋሰነው የሩስያ ደቡብ ማዕከላዊ አካባቢ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አባላቱ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
የቡድኑ አባላት የራሳቸውን የኮምፒውተር ፕሮግራም በመፍጠርና የድረገጾችን መረጃ በመስረቅ በሚያገኙዋቸው የሚስጥር ቁልፎች አማካይነት የኩባንያዎችንና የግለሰቦችን የመረጃ ልውውጥና ሚስጥር በእጃቸው እንደሚያስገቡ ተገልጿል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ፣ቡድኑ የዝርፊያ ስራውን በረቀቀ መንገድ ማከናወን ከጀመረ ጥቂት አመታት እንደሆነው ገልጾ፣ የሚስጥር ቁልፎችን በመዝረፍ የሚያገኛቸውን የኩባንያዎችና የግለሰቦች ሚስጥሮች መደራደሪያ በማድረግ የገንዘብ ምንጭ አድርጎ እንደሚጠቀም ተነግሯል፡፡

በናትናኤል ፋንቱ የተፃፈው “ከነፍስ እስከ ዩኒቨርስ” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ መፅሀፉ በዋናነት በስነ ፈለክ ምርምር፣ በፕላኔቶች፣ በፀሐይና መሰል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ “ከነፍስ እስከ ዩኒቨርስ” ስለምንኖርባት ዓለም ምን ያህል እናውቃለን፣ ማወቁስ ለምን አስፈለገ? ስለክዋክብት ማወቅስ ምን ይጠቅማል ለሚሉትና ተያያዥ ጥያቄዎች መጠነኛ መልስ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለው መፅሀፉ፤ 156 ገፆች ያሉት ሲሆን በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ የመፅሀፉ አዘጋጅ ናትናኤል ፋንቱ ከዚህ ቀደም “የእኔ ስላሴዎች - ህይወት፣ ፍቅርና ሳቅ”፣ “ስለ አረንጓዴ አይኖች”፣ “ሴቶች ለምንድን ነው ወሬ የማያቆሙት?” እና “የአምላክነት ቅምሻ” የተሰኙ መፃህፍትን ማሳተሙ ይታወሳል፡፡

በቀድው የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ግርማ ተስፋው የተደረሰው “ሰልፍ ሜዳ” የተሰኘ ልብወለድ መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ የልቦለዱ ማጠንጠኛ ከአብዮት በኋላ በሚያጋጥም የህይወት ፈተና ላይ በተዋቀረ በተለይም የሰው ልጆች በአብዮት ማግስት ለሚኖሩት ህይወት ትርጉም ማጣት፣ ብቸኝነት፣ ድብታና የባዶነት አዘቅት ውስጥ መስጠም በመፅሀፉ እንደ ዋንኛ ጭብጥ ተነስቷል፡፡
240 ገፆች ያሉት ልቦለዱ፤ በሊትማን መፃህፍት አከፋፋይነት የቀረበ ሲሆን በ49 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የጠፋችውን ከተማ ሐሰሳ” የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

የጋዜጠኛ ግርማ ወ/ማርያም “የ ‘ኛ ነገር” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ ማህበራዊ ትዝብቶች፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ሌሎች ርዕሶች የተዳሰሱበት የግጥም መፅሀፉ፤ 76 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን በ70 ገፆች የተቀነበበ ነው፡፡ መፅሀፉ ድንገት ከቤቱ እንደወጣ ለቀረውና በጣም ለሚያከብረው ደራሲ በዓሉ ግርማ መታሰቢያነት ይሁንልኝ ብሏል፡፡ መድበሉ በ25 ብር ይሸጣል፡፡ ጋዜጠኛው ከዚህ በፊት “አለቃ ሙስና እና…” በሚል ርዕስ መፅሃፍ አሳትሟል፡፡