Administrator

Administrator

የተሽከርካሪዎችን አቅምና ብቃት የሚለካ ቴክኖሎጂ ፈጥሯል

ኢትዮጵያዊው የምህንድስና ባለሙያ ናሆም በየነ ያቋቋመው ‘ኔቪቲ’ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ በየአመቱ በአሜሪካ በሚካሄደው ‘ኢቭሪዴይ ሄልዝ አዋርድስ ኦፍ ኢኖቬሽን’ የተባለ ሽልማት የመጨረሻው ዙር እጩ ተሸላሚ ሆነ፡፡
ኔቪቲ ኩባንያ ያመረተው ‘ናቪሴክሽን ሲስተም’ የተባለ የወጣቱ ኢትዮጵያዊ ፈጠራ፤ ‘ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ’ በተባለው ዘርፍ ለሽልማት ከተመረጡት የመጨረሻዎቹ እጩዎች አንዱ መሆኑ የተገለጸው፣ ላስቬጋስ ውስጥ በተካሄደው የዘንድሮው ዲጂታል ሄልዝ አመታዊ ጉባኤ ላይ እንደሆነ ታዲያስ መጽሄት ከኒዮርክ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያዊው ናሆም ለሽልማቱ ያሳጨውን ፈጠራ የሰራው፣ በፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በመከታተል ላይ በነበረበት ወቅት በ “ሪሃብሊቴሽን ሳይንስ” ዘርፍ ካከናወነው የዶክትሬት ድግሪ የመመረቂያ ጥናቱ በመነሳት እንደሆነ ተገልጿል፡፡የአሽከርካሪዎችን አቅምና ብቃት ለመለካት የሚያስችሉ መረጃዎችን በተደራጀ ሁኔታ ለመሰብሰብና በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚችል የተቀናጀ ቴክኖሎጂ እንደሆነ የተነገረለት ‘ናቪሴክሽን ሲስተም’ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያገኘ ሲሆን፤ በአሽከርካሪዎች ደህንነት ላይ ለውጥ የሚፈጥር አዲስ ግኝት እንደሆነ እየተነገረለት ይገኛል፡፡
“የኩባንያዬ ግብ ቤተሰቦች መቼ ማሽከርከር መጀመርም ሆነ ማቆም እንደሚገባቸው የሚያሳይ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ አሁን አሁን ማሽከርከር የጤና ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱም በአለም ላይ ከሚከሰቱ የመኪና አደጋዎችና ግጭቶች 93 በመቶ የሚሆኑት ከአሽከርካሪዎች ስህተት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡” ብሏል፤ ናሆም፡፡
በአሜሪካ በአሽከርካሪዎች ደህንነት ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ስርአቱን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ማገዝ እንደሚገባ ማመላከታቸውን የጠቆመው ናሆም፤ ኩባንያው በቀጣይም በተለይ በእድሜያቸው ለጋ ለሆኑና ላረጁ ሰዎች የመንጃ ፈቃድ በሚሰጥበትና በሚታደስበት ጊዜ አግባብነቱን የሚያረጋግጡ መሰል የተሻሻሉ የመኪና ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ስራውን በስፋት እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡
ናሆም የመጀመሪያ ዲግሪውን ከቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በባዮ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተቀብሏል፡፡ ከፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲም በ “ሪሃብሊቴሽን ሳይንስ” ዶክትሬቱን አግኝቷል፡፡ በ2012 “ኔቪቲ” የተባለ ኩባንያውን በማቋቋም ወደስራ ከመግባቱ በፊትም፣ በናሳ ጆንሰን የጠፈር ምርምር ማዕከል በኤሌክትሮኒክስና የኮምፒውተር መሳሪያዎች ዲዛይንና ፈጠራ መስክ ሲሰራ እንደቆየ ታውቋል።


13 ሺ ሠራተኞች ያስተዳድራል
ዘመናዊ ሆስፒታል፣ ት/ቤት፣ ስታዲየም፣ ፍ/ቤት ሠርቷል
ተባይን በአርተፊሻል ተባይ ያጠፋል
ባለቤቱ ለሕዳሴው ግድብ 25 ሚ.ብር ሰጥተዋል
ለአየር መንገድ በሳምንት 12 ሚ.ብር ይከፍላል

በኬንያ ትልቅ የአበባ እርሻ ነበራቸው። እንደቀድሞው አይሁን እንጂ አሁንም አለ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የጋበዟቸው በወቅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚ/ር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩ ናቸው፡፡ ግብዣውን ከመቀበላቸው በፊት ግን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንዳለ አስጠኑ፡፡ ፍጹም ምቹ ባይሆንም መሥራት የሚያስችል ሆኖ አገኙት፡፡ ከዚያ በ1997 ዓ.ም በምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን፣ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ፣ በዝዋይ ከተማ በ500 ሄክታር መሬት ላይ በኢትዮጵያ ትልቁን የአበባ እርሻ በ80 ሚ.ዩሮ መሠረቱ - ሆላንዳዊው ሚ/ር ገረት ባርንሆርንና (Berrit Barnoorn) ልጃቸው ሚ/ር ፒተር ባርንሁርን፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው አበባ 65 በመቶው የዚህ እርሻ ምርት ነው፡፡ 13 ሺህ ሠራተኞች ያሉት ድርጅቱ፤40 የአበባ ዓይነት ያመርታል፡፡ ምርቱን በሙሉ የሚያቀርበው ለውጭ ገበያ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 95 በመቶውን የሚያቀርበው የአበባ ዋጋ ቢወደድም ሆነ ቢረክስ፣ በተወሰነ ዋጋ ለማቅረብ ለተስማማቸው ሱፐርማርኬቶችና ሱቆች ነው፡፡ 5 በመቶውን ብቻ ነው በጨረታ የሚሸጠው፤ ሼር ኢትዮጵያ፡፡

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር (አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ) አምራች ላኪዎች ማህበር፣ የአባሎቹን እርሻ እንድንጐበኝ በጋበዝን መሠረት፣ ጥቂቶቹን የአበባ እርሻዎች አይተናል፡፡ ለዛሬ ግን ሼር ኢትዮጵያ የአባባቢን ደህንነት ለመጠበቅና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት እናያለን፡፡ ሼር ኢትዮጵያ ምርቱን ወደ አውሮፓ ለሚያጓጉዝለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሳምንቱ 12 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍል፣ የእርሻው ባለቤት ሚ/ር ገረት ባርንሆርን (በግላቸው) ለታላቁ ህዳሴ ግድብ 25 ሚሊዮን ብር መለገሳቸውንና ድርጅቱ ከቀድሞው ጠ/ሚ የኘላቲንየም ዋንጫ መሸለሙን የድርጅቱ ሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አቶ ከማል ሁሴን ገልጸዋል፡፡ አሁን በጉብኝቱ ወቅት የታዘብኩትንና አቶ ከማል የነገሩንን ላጫውታችሁ፡፡ ሼር ካሉት 96 ግሪን ሀውሶች (የአበባ ማብቀያ ዳሶች) ወደ አንዱ ስንገባ፣ አቶ ከማል “ድሮ ቢሆን የኬሚካሉ ሽታ አያስገባችሁም ነበር፤ አሁን ግን ይኸው እንደምታዩት ምንም የለም” አሉ፡፡ የምን ኬሚካል? በማለት ጠየቅን፡፡ “አበባውን የሚያጠቁትን ተባዮች ለመከላከል ኬሚካል እንጠቀም ነበር፡፡

አሁን ግን ኬሚካል የምንጠቀመው ለፈንገስ ብቻ ነው፡፡ አበባ የሚያጠቁ ጀርሞችን ለማጥፋት የምንጠቀመው የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እውቅና በሰጠው Integrated pest management control system Imps በተባለ ዘመናዊ ሰው ሠራሽ ዘዴ (አርቴፊሻል ጀርም) ነው፡፡ “ቅደም እዚያ ጋ ያያችኋት ልጅ እስካውት ትባላለች፡፡ የእሷ ሥራ፣ የአበቦቹን ቅጠሎች በሚያጐላ መነፅር (ማይክሮስኮፕ) እያየች ጀርም መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ ጀርም ካየች እዚያ ቦታ ላይ ነጭ ወረቀት ታስቀምጣለች፡፡ ‘እዚህ ቦታ አበባ የሚጠቃ ጀርም አለ’ ማለቷ ነው፡፡ ጀርሞችን ለማጥፋት የተመደቡ ሰዎች ደግሞ፣ አርቴፊሻል ጀርም ፈጣሪውን ዱቄት ነገር ያደርጉበታል፡፡ አርቴፊሻል ጀርሙ ይፈጠርና አበባ አጥቂዎቹን ጀርሞች እያሳደደ ከእነዕንቁላላቸውና ዕጫቸው ይበላቸዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች አርቴፊሻል ጀርሙስ በአባባቢ ላይ ጉዳት አይፈጥርም ወይ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን ምንም ጉዳት አይፈጥርም፡፡ ምክንያቱም እውነተኛው ጀርም ከሌለ አርቲፊሻሉ የሚበላው ነገር ስለሌለው ይሞታል” በማለት አስረድተዋል፡፡ በተንጣለለው የሼር ኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ ብቻውን አይደለም ያለው፡፡ ከሼር ውጭ የራሳቸው አስተደደር ያላቸው ዝዋይ ሮዝ፣ ኤክው፣ አርበርና ኘራም የተባሉ አበባ አምራች ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ራሳቸውን የቻሉ ድርጅቶች ቢሆኑም በሼር ስር ናቸው፡፡ ሼር 13 ሺ ሠራተኞች አሉት ሲባል የአራቱን ድርጅቶች ሠራተኞች ጨምሮ ነው፡፡ አፍሪ ፍሎራ / Afri flora / የሚለው ስም ከሼር ኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ስላየን ምንድን ነው? ብለን ጠየቅን፡፡ የሼር ኢትዮጵያን የአበባ ምርት በመላው ዓለም የሚሸጥና የድርጅቱ የንግድ ምልክት መሆኑን አቶ ከማል ነገሩን፡፡

ይህ ብቻ አይደለም። አፍሪ ፍሎራ ከሼር ውጭ የሆነ የራሱ አስተዳደር ያለው፣ ለድሃው ሠራተኛ የቆመ፣ ሚዛናዊ የአበባ ሽያጭ ተካሂዶ ሠራተኛውም ከሽያጩ እንዲጠቀም የሚያደርግ ፌር ትሬድ (Fair Trade) አራማጅ የግል ድርጅት ነው፡፡ ሼር የዚህ ድርጅት አባል ስለሆነ፣ ሠራተኞቹም ከፌር ትሬድ ከሚገኘው ሽያጭ ገቢ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ እንዴት መሰላችሁ፣ የአንድ አበባ ዋጋ አንድ ዩሮ ቢሆን በፌር ትሬድ ዓላማ መሠረት አፍሪ ፍሎራ በሁለት ዩሮ ይሸጥና አንዷን ዩሮ ለሠራተኛው ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሠራተኛው የሽያጩን ግማሽ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ገንዘቡ በጥሬው መጥቶ ለሠራተኛው በጥሬው አይከፋፈልም፡፡ የሠራተኛውን ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ሙያዊ ክህሎቱን ለማዳበርና ለማሻሻል …. በአጠቃላይ ሠራተኛውን ለሚጠቅም ነገር ይውላል፡፡ በዚህ መልኩ ከፌር ትሬድ የሚመጣውን ገንዘብ ሼር ኢትዮጵያ የሚያስተዳድረው ብቻውን ሳይሆን ከሠራተኛው ከተመረጠ ኮሚቴ ጋር ነው፡፡ ሼር ኢትዮጵያ ለሠራተኞቹና ለህብረተሰቡ ካደረገው ነገር አንዱ ሁሉም ሠራተኞች በነጻ፣ የዝዋይ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ በአነስተኛ ክፍያ የሚታከሙበት ሆስፒታል መገንባቱ ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተሠራው ዘመናዊ ሆስፒታል፤ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት የተገጠመለት ስለሆነ በሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ዘመናዊነት አዲስ አበባ ከሚገኘው ኮሪያ ሆስፒታል ቀጥሎ ይመደባል ተብሏል፡፡ “ከኬንያ የመጣ ሶፍትዌር የተገጠመለት ሲሆን ከካርድ ክፍል እስከ ምርመራ፣ ላቦራቶሪ፣ ፋርማሲ፣ አልጋ ክፍሎች…. ድረስ በኔትዎርክ ስለተያያዙ በሆስፒታሉ የወረቀት ሥራ የለም፣ በሽተኛው ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ የተሰጠውን ቁጥር እያሳየ አስፈላጊውን አገልግሎት ያገኛል” ይላሉ ኦፊሰሩ፡፡ እንደማንኛውም ሆስፒታል፣ ተኝተውና በተመላላሽ ለሚታከሙ ሕሙማን ሁሉን አቀፍ የመከላከልና የማከም አገልግሎት እንደሚሰጡ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ደምሳቸው ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በ100 ኪ.ሜ ዙሪያ ሆስፒታል ያለው አዳማና ሻሸመኔ ነው፡፡

የመውለጃ ቀኗ የደረሰ ሴት ሆስፒታል ወደሚገኝበት ስትወሰድ አጣዳፊ ምጥ ይዟት፣ ጨቅላውም ሆነ የእናቲቱ ጤና ችግር ላይ እንዳይወድቅ ሆስፒታሉ አማራጭ ሆኗል ብለዋል ዶ/ር ደምሳቸው፡፡ 140 አልጋ፣ ሁለት ስፔሻሊስት ሐኪም (የጽንስና የማህጸን እንዲሁም የቀዶ ሕክምና)፣ 6 ጠቅላላ ሐኪም፣ 4 የጤና መኮንን፣ 3ዐ ነርሶች፣ 7 አዋላጆች በአጠቃላይ 147 ሠራተኞች እንዳሏቸው የጠቀሱት ሚዲካል ዳይሬክተሩ፤ በቀን ከ300 በላይ ለሆኑ ተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎት እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ እንደማንኛውም ሆስፒታል መንግሥት በሚከተለው የጤና ፖሊሲ መሠረት የሕጻናት ክትባት፣ ለነፍሰ ጡሮች የጽንስና የማኅፀን ክትትል፣ የወባ፣ የቲቢ፣ የኤች አይቪ ኤድስ…. ሕክምና በነጻ ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ በማንኛውም በሽታ፣ ሠራተኛውን በነጻ፣ የአካባቢውን ማህበረተሰብ በአነስተኛ ክፍያ ያክማል፡፡ በሆስፒታሉ አጐቷን አስተኝታ ስታስታምም ያገኘናት ራሄል ባህሩም፤ ለካርድ 15 ብር፣ በቀን ደግሞ ለአልጋ 45 ብር እንደሚከፍሉ ገልጻ፣ ከግል ሐኪም ቤቶች ጋር ሲነጻጸር ተመጣጣኝ መሆኑን ገልጻለች፡፡ “ሆስፒታሉ የግል ቢሆንም የአካባቢውን ነዋሪ እንደ መንግሥት ሆስፒታል አነስተኛ ዋጋ ነው የምናስከፍለው፡፡ ለምሣሌ ለካርድ 15 ብር፣ ተኝቶ ለሚታከም በሽተኛ ቁርስ ምሣ ራት በልቶ፣ የሐኪምና የነርስ ክትትል ተደርጐለት በቀን 45 ብር ነው የምናስከፍለው፡፡ ክፍያው ከሌላ የሕክምና ተቋም ጋር ሲነጻጸር ነጻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለድርጅቱ ሠራተኞች ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ ሁሉም ሕክምና በነጻ ነው፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ኬንያ ልከን እናሳክማለን” ብለዋል ዶ/ር ደምሳቸው፡፡ ሌላው ሼር ኢትዮጵያ ለማህበረሰቡ እየሰጠ ያለው አገልግሎት በትምህርት ዘርፍ ነው፡፡

በመዋለ ህፃናት የጀመረው ሼር ኢትዮጵያ ት/ቤት ዘንድሮ 9ኛ ክፍል ከፍቷል፡፡ አቶ ግርማ ቢሆን የሼር ኢትዮጵያ ት/ቤት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ት/ቤቱ በዚህ ዓመት ግማሹ የሠራተኛው ልጆች፣ ቀሪው ግማሽ ደግሞ ከዝዋይ ከተማና ከአካባቢው ማህበረሰብ አቅም እንደሌላቸው አስመስክረው የተቀበሏቸውን 4,200 ተማሪዎች በነፃ እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመንግስትም ሆነ በግል ት/ቤቶች የማይታዩ አሠራሮች እዚህ ይገኛሉ፡፡ ት/ቤቱ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ቢሆንም ትምህርት የሚሰጠው በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋ ነው፡፡ አቶ ግርማ፤ ወላጅ ልጁን አምጥቶ ሲያስመዘግብ ይማርልኝ ብሎ ባስመዘገበው አፍ መፍቻ ቋንቋ በኦሮምኛ ወይም በአማርኛ እናስተምራለን፡፡ በመዋለ ህፃናት በሁለቱም ቋንቋ የሚማሩ 1500 ያህል ህጻናት ሲኖሩ በ24 ክፍሎች ተደልድለው ይማራሉ፡፡ በሁለቱም ቋንቋ አሁን በ1 ኛ 2ኛ፣3ኛ፣4ኛ አራት አራት ክፍሎች እናስተምራለን፡፡ ከ8ኛ በላይ ግን የምናስተምረው በእንግሊዝኛ ነው፡፡ አሁን 89 መምህራን ሲኖሩን አብዛኞቹ በዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ ላቦራቶሪው ጥቃቅን ነገሮችን አጉልቶ በሚያሣይ ዘመናዊ አጉይ መነፅሮች (ማይክሮስኮፕ) እና ለመማር በሚረዱ ቁሣቁሶች ተሟልቷል፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ላቦራቶሪ በበርካታ ኮምፒዩተሮችና ባለሙያዎች የተደራጀ ስለሆነ፣ ህፃናት ከሁለተኛ ክፍል ነው የኮምፒዩተር ትምህርት የሚጀምሩት፡፡

የ5ኛ ክፍል ተማሪ ፎቶሾፕ ስትሠራ አይተናል፡፡ ቤተ መጻህፍቱ በትምህርት ሚኒስቴር ካሪኩለም መሠረት በአዳዲስ መጻህፍት ተሞልቷል፡፡ በት/ቤቱ የደረስነው በምሳ ሰዓት አካባቢ ስለነበር፣ መዋለ ህፃናት የሚማሩ ህፃናት ተሰልፈው ምሣ ወደ ሚበሉበት አዳራሽ ሲገቡ ተመለከትን። ህፃናቱ የድሃ ልጆች ስለሆኑ ቁርስና ምሣ በነፃ እንደሚበሉ፣ ዩኒፎርም፣ መጻሕፍት፣ ደብተርና እስክሪብቶ በነፃ እንደሚሰጣቸው ተነገረን፡፡ የሼር ኢትዮጵያ ባለቤት ሚ/ር ገረት ባርንሁርን “በአገሬ እየተራበ የሚማር ሰው አይቼ አላውቅም” ብለዋል፡፡ “በመማር ማስተማር ሂደት አንዳችም ችግር የለብንም፤ በወር አንድ ጊዜ ከእርሻው ባለቤት ጋር ተቀምጠን እንወያያለን፡፡ የሆነ ችግር ቢያጋጥመን እዚያው እናቀርብና ፈጣን ምላሽ ይሰጡናል፡፡ በቅርቡ እንኳ ለ9ኛ ክፍሎች ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣቸውን አዳዲስ መጻህፍት 93 ሺህ ብር አውጥተው ገዝተውልናል” ብለዋል አቶ ግርማ፡፡ የልጆቹስ ውጤት እንዴት ነው? አልናቸው አቶ ግርማን፡፡ “የልጆቹ ውጤት በጣም ጥሩ ነው። በቅርቡ በምስራቅ ሸዋ ዞን 13 ወረዳ ት/ቤቶች መካከል በተደረገ ውድድር 1ኛ የወጣው የእኛ ተማሪ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎቻችን 100 ፐርሰንት ነው ያለÕት። በ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም 100 ፐርሰንት ለማሣለፍ ብቻ ሳይሆን ውጤታቸውም በጣም ከፍ እንዲል እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡ ሚ/ር ባርንሁርን፤ “ሼር ኢትዮጵያ በመላው ዓለም በጣም ተወዳጅና ስመጥር እንደሆነው ሁሉ ሼር ኢትዮጵያ ትምህርት ቤትም ታዋቂ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙ ከ10 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማደጉን አይቻለሁ፡፡ በዚህም ‘ትምህርት ለሁሉም’ የሚለውን የተባበሩት መንግስታት የሚሌኒየም ልማት ግብ እያሟላን ነው ብለዋል፡፡ሼር ኢትዮጵያ በተመሣሣይ ስም ተመዝግቦ በብሔራዊ ሊግ የሚጫወት የእግር ኳስ ቡድን አለው፡፡ ድርጅቱ ለዚህ ክለብ በዝዋይ ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ ስታዲየም ሠርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሼር ኢትዮጵያ ለአዳሚቱሉ ወረዳ ዘመናዊና ለፍርድ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ የፍ/ቤት ቁሣቁሶች የተገጠመለት እንዲሁም ብሮድባንድ ኢንተርኔት ያለው ደረጃውን የጠበቀ ፍ/ቤት ሠርቶ አስረክቧል፡፡ የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅም ሠራተኞቹን በማስተባበር ዛፍ እየተከለ ነው፡፡ የዛፍ ተከላ ፕሮግራሙ የተጀመረው አምና ቢሆንም ከ26 ሺህ በላይ ችግኞች በዝዋይ ከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠሩም አካባቢ ተተክለው፣ ድርጅቱ የችግኞቹን እድገት የሚከታተሉ ሠራተኞች መመደቡን አቶ ከማል አስረድተዋል፡፡ ከአበባው እርሻ የሚፈሰው ውሃ ወደ ሐይቁ ገብቶ እንዳያበላሽ ከሆላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር፣ ውሃ የሚጠራቀምበት ጉድጓድ ቆፍሮ፣ ውሃው ተጣርቶ በሪሳይክሊንግ ተመልሶ አበባውን እንዲያጠጣ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንበሳ የኢትዮጵያዊነታችን ትልቅ መገለጫ ነው
በሽያጭ የኦሮምኛ ዘፈኖችን የሚወዳደራቸው የለም

ዝነኛው ድምጻዊ ታደለ ሮባ በቅርቡ “ምስጋና” የተሰኘ አዲስ አልበም አውጥቷል፡፡ ከሙያ ባልደረባው ብርሃኑ ተዘራ ጋር
4 አልበሞችን ቢያወጣም ሙሉ አልበም ለብቻው ሲያወጣ ግን የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አበባየሁ ገበያው በሙያውና በህይወቱ ዙርያ አነጋግራዋለች፡፡

በቀበሌ ኪነት በኩል ነው ወደ ሙዚቃ የገባኸው ወይስ በሌላ?
አዎ፤ የ12 ቀበሌ የታዳጊ ኪነት ቡድን ውስጥ እጫወት ነበር፡፡ አሊ ቢራ የሰፈራችን ልጅ ነው፡፡ ያኔ ትንሽ ስለነበርኩ

በደንብ አላስታውስም እንጂ የጊታሯን አምፕሊፋየር የሰጠን እሱ ነበር፡፡  እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የአሊ ቢራ ዘፈኖች

“እንጀራዬ” ሆኑ፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የእሱ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡
ተወልደህ ያደግህበት ሰባተኛ የአርቲስቶች መፍለቂያ ነው፡፡ ከሰፈሩ ብዙ አርቲስቶች የወጡበትምክንያት ምን

ይመስልሃል? ከውሃው ይሆን እንዴ?
አዎ…እነጐሳዬ፣ አለማየሁ ሂርጳ፣ አብዱ ኪያር፣ ቴዲ አፍሮ፣ አብነት አጐናፍር፣ ወንድሙ ጅራ፣ መውደድ ክብሩ… የእዛ

አካባቢ ልጆች ናቸው፡፡ በተወዛዋዥነትም ብዙ አሉ - ከዚያ ሰፈር የወጡ። እንደሚመስለኝ የመርካቶ ጐረቤት በሆኑ

ሰፈሮች ያደጉ ልጆች ድፍረት አላቸው፡፡ ድፍረትም ታለንትም፡፡ የቦሌ ልጅ ሆነው ከግቢ የማይወጡ፣ ታለንቱ

ቢናራቸውም ላይጠቀሙበት ይችላሉ። ደግሞ የእኛ ሰፈር አርቲስቶች ብቻ ሳይሆኑ ትላልቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾችም

የወጡበት ነው። የቡናና የጊዮርጊስ ተጫዋቾች የማን መሰሉሽ? ዛሬ ግን ሰፈራችን ሜዳ የለም፤  ኳስ ሜዳው ፎቅ

ተሰርቶበታል፤ አስራ ሰባት ሜዳም ትምህርት ቤት ሆኗል፡፡ ለእዚህ እኮ ነው የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የክፍለ ሀገር

ልጆች ብቻ የሆኑት፡፡ የሜዳው ነገር ሊታሰብበት ይገባል፡፡  
እስቲ ስለ “ላፎንቴ”… አመሰራረት ንገረኝ…
ነፍሱን ይማርና የላፎንቴን አንደኛው አባል የነበረው ፀጋቸው የሚባል ጓደኛችንና አለማየሁ ኢርጳ አሮሠ ሆቴል ይሠሩ

ነበር፡፡ “ጐበዝ ልጅ አለ” ብለው  ለአሮሠ ሆቴል ባለቤት ለአቶ ሮባ ነገሩትናእኔም እዛ መጫወት ጀመርኩ፡፡ አሮሠ ሳለሁ

የማልጫወተው ዘፈን አልነበረም፡፡ ኪሱዋሂሊ፣ ጉራጊኛ፣ ሱዳንኛ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ሁሉ እሠራ

ነበር፡፡ ከተፋ ስትሰሪ  ይሄ የሚጠበቅ ነው፡፡ እዛ እየሠራን ሳለ “ያየህራድ አላምረው ሮያል ፓላስ” የሚባል ቤት

ተከፈተ። እዚያ ቤት ከተማው ውስጥ አሉ የተባሉ ዘፋኞች ይሰሩ ነበር፡፡ እኛም ለጥቂት ወራት እዛ ከሰራን በኋላ እኔ፣

አበበ ተካ፣ ብርሃኑ ተዘራና ፀጋቸው ሆነን “ላፎንቴን” በሚል ስራ ጀመርን፡፡ አበበ ወዲያው ወጣ፡፡
አንድ ጊዜ የኦሮምኛ ዘፋኞች ተሰባስባችሁ ማህበር ለማቋቋም ስትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ምን ደረሰ? ዓላማውስ ምን ነበር?
አዎ አንድ ማህበር በኦሮምኛ ዘፋኞች ተቋቁሞ ነበር፡፡ ስብስባው ጨፌ ላይ ነበር የተደረገው። እንቅስቃሴው አሁን ምን

ደረጃ ላይ እንደደረሰ አላውቅም፡፡ የኮፒ ራይት ጥሰትን ለማስቀረት ጠበቅ ብሎና በደንብ ታስቦበት ቢሰራ ጥሩ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ በሽያጭ በኩል የኦሮምኛ ዘፈኖችን የሚወዳደራቸው የለም፡፡ እኛ የማናውቃቸው ዘፋኞች አሉ - ሃረር፣

አርሲ፣ ባሌ… የእነሱ አልበም እስከ 100 ሺ ቅጂዎች ይሸጣል፡፡ የእኛ እኮ እንደነሱ አይሸጥም፡፡ የእነሱ እንደገና “በርን”

ባይደረግ …. ሶስት መቶ ሺና ከዛም በላይ ይሸጥ ነበር፡፡  
በሙዚቃ ሥራ ምን ያህል አድጌያለሁ ትላለህ?
የትምህርት መጨረሻ የለውም፡፡ ግን በሙዚቃ ሥራ በስያለሁ፡፡ በፊት እየዘፈንኩኝ ሳላውቀው፤ ከቅኝት (ሪትም) ሁሉ

እወጣ ነበር፡፡ አሁን በደንብ በስየበታለሁ፤ ግን ገና ይቀረኛል፡፡ በሙዚቃ መሳሪያ በኩል ጊታርና ኪቦርድ ለራሴ መጫወት

እችላለሁ። መማሩና መብሰሉ ነገም የሚቀጥል ሂደት ነው፡፡
የአዲሱ አልበምህ ሽፋን ላይ በአንበሶች ተከበህ ትታያለህ፡፡ አንበሶች ትወዳለህ ወይስ ሌላ ትርጉም አለው?
ከልጅነቴ ጀምሮ አንበሳ እወዳለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ (በአባቶቻችን ዘመን) በአንበሶች ታጅበን ነበር

የምንዋጋው፡፡ ከትውልድ እስከ ትውልድ ብዙ ነገሮቻችን የአንበሳ ነበረ፡፡ አንበሳ አውቶብስ፣ የአየር መንገድና የቴሌ

አርማ …ብቻ የተለያዩ ነገሮቻችን የአንበሳ አርማ ነበራቸው፡፡ አንበሳ የኢትዮጵያዊነታችን ትልቅ መገለጫ ነው ብዬ

አምናለሁ፡፡ ከአንቺና ከእኔ ጀምሮ አንበሶች ነን…አንቺ አሁን የሴት አንበሳ ነሽ፡፡
እርግጠኛ ነህ?
አዎ! የሴት አንበሳ ነሽ…/ሳቅ/ እኔ ደግሞ በእምነቴ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ፡፡ ግን ኮኮቤ ሊዮ ነው - ባላምንበትም፡፡

ሊዮ ደግሞ ምልክቱ አንበሳ ነው። በዚህ የአንበሳ ፍቅሬ ነው በአንበሶች ታጅቤ የምታይኝ፡፡ እንደ ንጉስ ለመሆን ወይንም

ፖለቲከኛ ሆኜ አይደለም፡፡ ከህፃንነቴ ጀምሮ አንበሳ እወዳለሁ። አንድ ሰው የሚፈልገው ነገር ማድረግ አለበት የሚል

እምነት ስላለኝ የምፈልገውን አድርጌያለሁ፡፡ በአልበሙ ላይ የሚታዩት ሁለቱ የእውነት አንበሶች ሲሆኑ እኔ ደግሞ የሰው

አንበሳ ነኝ፡፡
በምትሰራቸው ነጠላ ዜማም ይሁን ሙሉ አልበም ላይ አዳዲስ ወጣቶችን በፊቸሪንግ ታስገባለህ? ወጣቶቹን ለማገዝ

አስበህ ነው?
እንደ አቅሜ ሙዚቃ የማዳመጥ ችሎታ አለኝ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ የማሰራቸው ልጆች ችሎታውና ተሰጥኦው

ቢኖራቸውም ምቹ ዕድልና መድረክ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ እኛ ደግሞ በህዝብ ውስጥ አለን..እናም አዳዲስ ልጆች ከእኛ ጋር

በመሆን ከህዝብ ጋር መተዋወቅ  አለባቸው ብዬ አምናለሁ። በዚህ እነሱም እኛም እንጠቀማለን፡፡ ችሎታቸውን

ስለምናደንቅ ነው የምናሰራቸው፡፡ በፊት ከላፎንቴን ጋር ፊቸሪንግ የሰሩ ልጆች በሙሉ አሁን ትላልቅ ቦታ ደርሰዋል፡፡

ሁሉም ራሳቸውን ችለው ቆመዋል፡፡
ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው እየመጣህ ነው አይደል?
አዎ፡፡ ወደ ፊልም ገብቻለሁ፤ በቅርቡ የሚወጣ ፊልም አለኝ፡፡ እግዚአብሄር ካስተካከለው የተመልካችን አስተያየት አይቼ

ወደፊት የምቀጥልበት ይሆናል፡፡
የአልበም ስራ በሌለ ጊዜ ምንድነው የምትሰራው? ናይት ክለብ…
እኔ ብዙ ጊዜ እዚህ አልሰራም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ነው፡፡ አሁን ግን አልበሜን ከሰራሁ በኋላ ማናጀሬና ማርኬቲንጉ

አንዳንድ ነገሮችን እያጠኑ ነው፡፡ ባለፈው ጎንደር ሄጄ፤ ከስፖንሰሬ ከዳሸን ቢራ ጋር አንዳንድ ነገሮችን አስተካክለናል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ደሴና ኮምቦልቻ ሄጄ ነበር፤ አንድ የአፋር ባለሃብት ሆቴል ከፍተው ለምርቃቱ  እንድገኝ ስለፈለጉ ነው፡፡

ቀጥለን ደሞ ወደ ደቡብና ምስራቁ ክፍል እንሄዳለን፡፡
ከአዲስ አልበም በኋላ ኮንሰርት የተለመደ ነው፡፡ ጥያቄ አልቀረበልህም?
ከአሁኑ ለንደን ፕሮግራም እንድይዝላቸው ጠይቀውኛል፡፡ ግን አልሄድም፤ ምክንያቱም አልበሙ በደንብ መሰማትና

መደመጥ አለበት። ሰው ከእኔ ጋር እንዲዘፍን እንጂ እኔ ብቻዬን እንድዘፍን አልፈልግም፡፡ የለንደን ያልኩሽ  ከፋሲካ

በኋላ ስለሆነ ለእኔ ጥሩ ጊዜ ነው፡፡
እስከ አሁን ስንት አልበም ሰራህ?
ከብርሃኑ ተዘራ ጋር አራት አልበሞች ሰርተናል….‹‹ተው አምላኬ››፣ ‹‹እንዲች እንዲች››፣ ‹‹እጅ አንሰጥም›› እና ‹‹ባቡሬ››፡፡

ከዛ በኋላ የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ሰርቼአለሁ፡፡ ለብቻዬ አልበም ሳወጣ ይህ አዲሱ ‹‹ምስጋና›› የመጀመሪያዬ ነው፡፡  
አርቲስቶች ችግር ሲደርስባቸው ቀድመህ ትደርሳለህ ይባላል?…
የተወሰንን አርቲስቶች በክፉም በደጉም የምንገናኝ ነን፡፡ አርቲስቶች ችግር ሲደርስባቸው የሰው እጅ ከሚያዩ፣ ለዚሁ

ዓላማ የሚሆን አንድ ነገር መከፈት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ እድር የለንም፡፡
አሁን እያሰብን ነው፡፡ ለቅሶ ላይ ወይም የሆነ ቦታ ስንገናኝ ለምን አንመሰርትም እንባባላለን። በጓደኞች መካከል ችግር

ሲፈጠር ለመፍታት እንጥራለን፡፡ እኔ ብቻዬን ምስጋናውን (ክሬይቱን) መውሰድ አልፈልግም፡፡ በተረፈ ሜሪ ጆይ ውስጥ

ሁለት የማሳድጋቸው ልጆች አሉኝ፡፡ መናገር የማልፈልጋቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎችም አሉ፡፡ በአጠቃለይ ግን ጥሩ ነው፡፡
የሞባይል ስልክህን መጥሪያ (ሪንግቶን)እንደሰማሁብ  ከአዲሱ አልበምህ ሳይሆን አይቀርም …ተሳሳትኩ?
14ኛው ዘፈን ነው - ‹‹እስዋን ተዋት›› የሚለው። የግጥሙ መነሻ ሃሳብ የማሚላ ነው፡፡ ሙሉውን ግጥም የሰራው ሳሚ

ሎሬት ነው፡፡ በጣም ጎበዝ የሰፈሬ ልጅ ነው፤ ሳሚ፡፡ ዘፈኑ ቀዝቀዝ ብሎ መልዕክቱም ደስ ይላል፡፡
“እስዋን ተዋት” ነው የሚለው፡፡ አንዳንዴ ጓደኞችሽ  ያንቺ ባህሪ ያልሆነውን ነገር ያወራሉ አይደል…”ተዋት በቃ! ተዋት

አትሟት.እኔ እስዋነቷ ነው የምፈልገው… በቃ እንደዚህ አትበሏት..ተዋት” ..ነው የሚለው፡፡ ልጅቷ ሳቅ፣ ጨዋታና ጭፈራ

ትወዳለች፤ ሌላ ምንም ጥፋት የለባትም፡፡ ግን አለ አይደል ሁልጊዜ ነጌቲቩን የሚያወሩ አሉ፡፡ እነሱን ነው … “ተዋት”

የሚለው፡፡

ባለፋት አምስት ዓመታት ሦስት የግጥም መጻሕፍትን አሳትሟል - “እውነትን ስቀሏት” በ2001 ዓ.ም፣ “ከፀሐይ በታች”

በ2004 ዓ.ም እና  “ጽሞና እና ጩኸት” በያዝነው ዓመት፡፡  ሦስተኛው መጽሐፉ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በጣይቱ

ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ በተመረቀበት ወቅት በመድበሉ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት፣ መምህርና ሐያሲ አስቻለው ከበደ

በማጠቃለያቸው ላይ፤ ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል)፤ ተስፋ የሚጣልበት ገጣሚ ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ግጥሞቻቸውን በመጽሐፍ ሰንደው የሚያቀርቡ ገጣሚያን በአብዛኛው “የእኔ ነው” የሚሉትን አሻራ ለመተው ሲታትሩ

ይታያሉ በአንድ ርዕስ ስር ተዘጋጅተው የተለያዩ ክፍሎች የተሰጣቸውን ግጥሞችን በማቅረብ፣ ግጥሞቹን ርዕስ አልባ

በማድረግ፣ ስንኞቹን በተለያየ ቅርጽ በመሰደር እንዲሁም አዲስ ይዘት፣ ቅርጽና ሃሣብ በማስተዋወቅ። ሎሬት ፀጋዬ

ገብረመድህን በ1966 ዓ.ም ባሳተመው “እሳት ወይ አበባ” የግጥም መጽሐፉ መግቢያ “…. አንዳንድ መምህራን የዚህን

ድንጋጌ ዘይቤ (ስታይል) ስም ስላላገኙለትና እኔም ስላልሰየምኩለት “የፀጋዬ ቤት” ይሉታል” ብሏል፤ ለየት ስላለ

የአገጣጠም ስታይሉ ሲገልጽ፡፡
ገጣሚያኑ በቅርጽና ይዘት ላይ አዳዲስ ነገሮችን “ለመፍጠር” የሚነሽጣቸውና የሚያተጋቸው ገጣሚነት የሚሰጣቸው

“ነጻነት” (Poetic Licesence እንዲሉ) እንደሆነ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ “ጽሞና እና ጩኸት”

በተሰኘው ሦስተኛው የሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) የግጥም መድበል፤ “በግጥም እንስከር” የሚለው  ግጥሙ ሲያበቃ በግርጌ  

ማስታወሻው ላይ ግጥሙ ቤት የማይመታ እንደሆነ ጠቁሞ ማብራሪያ ያቀርባል፡-
“ቤት ሰበር ግጥሞች አንዱ የግጥም ዘርፍ እንዲሆኑና ይህ አዲስ የግጥም መልክ በወጣት ገጣሚዎች ይበልጥ እንዲዳብር

በመመኘት፣ እንደ መነሻ በገጽ 45፣51፣56 እና 64 ያሉ ቤት ሰበር ግጥሞችን አቀርቤያለሁ፡፡ ቤት ሰበር ግጥሞች ቤት

አይምቱ እንጂ ዜማ ያላቸው፣ ምጣኔያቸውን የጠበቁና ቤት ከመምታት ውጪ የተቀሩትን የግጥም ባሕሪያት ሁሉ

የሚያሟሉ ናቸው፡፡ በከፊል ቤት የሚመታ ግን በከፊል ቤት የሚሰብር ግጥም ደግሞ ከፊል ሰበር ግጥም ልንለው

እንችላለን፡፡ ቤት አለመምታት (ቤት መስበር) አንዱ የግጥም ባህሪ ሆኖ ቢተዋወቅስ?”
ለግጥም ማስተማሪያነት የሚያገለግሉ ወይም ስለ ግጥምና ቅኔ ምንነት በማጣቀሻነት ሊቀርቡ የሚችሉ መጻሕፍትን

ያዘጋጁ ጥቂት የማይባሉ ደራሲያን አሉ። የዘሪሁን አስፋው “የሥነ ጽሁፍ መሠረታዊያን”፣ የብርሃኑ ገበየሁ “የአማርኛ ሥነ

ግጥም”፣ የአለማየሁ ሞገስ “የአማርኛ ግጥምና ዜማ ማስተማሪያ”፣ የአቤ ጉበኛ “መስኮት”፣ የፍቅረድንግል በየነ “ሰምና

ወርቅ ሰዋሰው”፣ የአስፋው ተፈራ “ፀጋዬ“፣ የታደለ ገድሌ  “ትንቅንቅ” … መጻሕፍት ይጠቀሳሉ፡፡
ገጣሚ ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) “ቤት አለመምታት ወይም ቤት መስበር አንዱ የግጥም ባሕሪ ሆኖ ቢተዋወቅስ?” በሚል  

በአማርኛ ግጥም አጻጻፍ ላይ አዲስ ነገር ለማከል ላሳየው ጉጉነት፣ ደራሲ አቤ ጉበኛ ከ42 ዓመታት በፊት መልስ

ሰጥቶበታል፡፡ ደራሲው “መስኮት” በሚል ርዕስ በ1964 ዓ.ም  ባሳተመው የመጀመሪያ የግጥም መጽሐፉ መግቢያ ላይ፣

ቤት የማይመታ ወይም የሚሰብር አገጣጠም ቀደም ብሎ የሚታወቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡
“ቤት የማይመቱ ሁለት ግጥሞች በዚህ መጽሐፌ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነሱም በእንግሊዝኛ (ብላንክ ቨርስ) በሚባለው

የግጥም ዓይነት የሚታዩ ሲሆን፣ በሀገራችንም ይህ የግጥም ዓይነት እንግዳ አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ቤት የማይመታ

ግጥም በሀገራችን በጣም የታወቀና የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ከውጪ ቋንቋ ከተተረጐሙ መጻሕፍት መካከል እንደ

መዝሙረ ዳዊት፣ መኀልየ ሰለሞን ያሉት ቤት በማይመታ ግጥም የተጻፉ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥ ከተደረሱት አብዛኞቹ

የያሬድ ቅኔዎች ቤት የላቸውም፡፡”
በመጽሐፌ ቤት የማይመቱ ወይም የሚሰብሩ ግጥሞችን ያቀረብኩት አዲስ ነገር ፈጥሬያለሁ ለማለት ሳይሆን የአሠራር

ልማዱ እንዳለ ለማሳየት ነው የሚለው አቤ ጉበኛ፤ አንድ ቃል አንድ ቤት እንድትመታ የሚደረግበት አጭር የግጥም

መንገድ እንኳ አዲስ አለመሆኗን ማወቅ ጠቃሚ ነው ብሎ የሚከተለውን የሆታ ግጥም በማሳያነት አቀርቧል፡-
በወጨፎ፤
ፈጀው ጠልፎ፤
በውጅግራ፤
ተካው ጅግራ፤
በናስ ማሰር፤
ፈጀው ነስር
“ዕውቀት ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍና የሚወራረስ በመሆኑ የፋርሳዊው ገጣሚ የኦማር ኻያምን አገጣጠም በአማርኛ

የግጥም ሥራዎቼ ለመጠቀም ሞክሬያለው፤ በአማርኛ ቋንቋ ግጥም የመጻፊያ መንገዶቻችን በጣም ብዙ ስለሆኑ ከሌላው

መዋስ የሚያስመኘን አይደለም፡፡ በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ያለው የአገጣጠም ስልት ቢጠና

ተጨማሪ ስልቶችም ሊገኙ ይችላሉ” ይላል፡፡
በአማርኛ ቋንቋ የግጥም አጻጻፍ ስልት ውስጥ ቤት የማይመቱ የአገጣጠም ዘዴዎች በብዛት እንዳሉ ሲያብራራ፤ በዝርው

ጽሁፍና ለዚያም ማሳያ ግጥሞችን ያቀረው አቤ ጉበኛ፤ ይህንን ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት “ፈረንጆች ከሚሉት ውጭ

በአገራችን ዕውቀት ያለ ለማይመስላቸው ሰዎች” ምላሽ ለመስጠት መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የሀዘንና የለቅሶ ግጥሞች እንዴት እንደሚጻፉ፣ ገጸ ባህሪ ያለውና የሌለው ግጥም አዘገጃጀት፣ ስለፉከራና ሽለላ አጻጻፍ፣

ስለ በገናና የሆታ ግጥም ምንነት፣ ስለ የእንካ ሰላንታያ ግጥም አገጣጠም፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ የ“ምሕላ”

ግጥሞች ምንነት፣ ስለ አዝናኝና አስደሳች ግጥሞች፣ ስለ ቅኔ አጻጻፍና የምክር ግጥሞች … ማብራሪያና ምሳሌዎችን

ጠቅሷል፡፡ ቤት ለማይመታ ወይም ለሚሰብር ግጥም “የቅን ሰው መዝሙር” የተሰኘ ግጥሙን በማሳያነት አቅርቧል፡፡
እጅግ ይገርመኛል እጅግ ይደንቀኛል፤
ነገሩን ሳስበው ቁሜ ተቀምጨ፡፡
አንዳንድ ግራ ሰዎች ሲጠሉኝ ሳያቸው፤
ምርር አርገው ከልብ ምንም ሳልነካቸው፤
እንዲሁ በዓለም ላይ በመኖሬ ብቻ፤
ምናልባት ምናልባት ይሆን ቆጭቷቸው፤
ዓየርን ፀሐይን በተካፈልኳቸው?
አንድ ቀን ሳላስብ በማንም ላይ ክፉ፤
ለመጉዳት ሃሣብም መንገድም ሳይኖረኝ፤
እንዲህ ያሉ ፀሮች ለማፍራት የቻልሁ፤
በሰው ክፉ አስቤ ክፉ ብፈጽም፤
ዕድል ባሰናክል ባበላሽ ጥቅም፤
ለንብረት ለሕይወት ጠላት ብሆን ኑሮ፤
ኸረ ጠላቶቼ ስንት ሊሆኑ ነበር?
ግን ጠላት ከማፍራት ግን ጠላት ከማብቀል፤
ቅንነት ይበልጣል ከክፋት ይልቅ፤
ይታገላል እንጂ ሊያሳስት ሰውን፤
ይፈታተናል ወይ ሰይጣንን ሰይጣን፣
መልአክና ሰይጣን ጓድ ይሆናሉ ወይ?
እኔ አለሁኝ እንጂ ለማንም ሰው ክፉ፤
ግድ አለኝ ጠማሞች በከንቱ ቢለፉ?
ሰሎሞን ሞገስ(ፋሲል) በ”ጽሞና እና ጩኸት” የግጥም መጽሐፉ፣ ቤት አለመምታት አንዱ የግጥም ባህሪ ሆኖ

ቢተዋወቅስ? በሚል ላቀረበው ጥያቄ ከ42 ዓመታት በፊት አቤ ጉበኛ “መስኮት” በሚል የግጥም መጽሐፉ ከላይ

በቀረበው መልኩ ማብራራቱን ለማስታወስ ያህል ነው፡፡ መምህርና ሐያሲ አስቻለው ከበደ እንደመሰከሩለት፤ ሰሎሞን

ሞገስ (ፋሲል) ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት ገጣሚያን አንዱ እንደሆነ በሦስቱ መጻሕፍቱ ባቀረባቸው ግጥሞች ብቃቱን

አሳይቷል፡፡ ግጥምና አገጣጠምን ለማሳደግ አዲስ ሃሣብና መንገድ ለመፍጠር ሲያስብ ግን የተመኘው ነገር ቀድሞ

ያልነበረ መሆኑን መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡


የኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን የስፖርት ጋዜጠኛ የሆነው መኳንንት በርሄ ላጋጠመው የደም መርጋት ህመም በደቡብ አፍሪካ ህክምናውን እየጀመረ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ የደም ናሙና የሰጠው የስፖርት ጋዜጠኛው፤ በትናንትናው እለት ደግሞ የዶፕለር ምርመራ አድርጎ በቀኝ እግሩ ላይ የደም ማመላለሻ ቧንቧ‹‹ ቬን›› መዘጋቱ ተረጋግጧል። ከሁለቱ ምርመራዎች ውጤት በኋላ የተዘጋውን የደም ማመላለሻ ቧንቧ የሚከፍትበትን ልዩ ህክምና በአስቸኳይ ማድረግ እንዳለበት በሃኪሞቹ ተነግሮታል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው መኳንንት በርሄ ካጋጠመው የጤና እክል ሙሉ ለሙሉ ለመዳን ለሚያደርገው ከፍተኛ ህክምና ከ350 ሺ ብር በላይ ይጠበቅበታል፡፡ ለስፖርት ጋዜጠኛው ገንዘብ ማሰባሰብ ከተጀመረ አንድ ሳምንት ወዲህ ብዙም ባለመገኘቱ አሁንም ከፍተኛ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡

ጓደኛው ትዕግስት ገመቹ በኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት ሠራተኞች 43ሺ እንደተሰበሰበለት ገልፃ፤ አንዳንድ ድርጅቶች ድጋፍ ለመስጠት ቃል በገቡት መሰረት እየተጠባበቅን ነው ብላ፤ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ገንዘቡ በሙሉ ተሰብስቦለት ህክምናው ቶሎ እንደሚጨርስ ተስፋ አደርጋለሁ ብላለች፡፡ ለህክምና የሚያስፈልገውን ገቢ ለማሰባሰብ የትእግስት ገመቹን አድራሻ ለምን መጠቀም እንዳስፈለገ ያስረዳቸው ጓደኛው ትእግስት ገመቹ፤ መኳንንት በአገር ውስጥ ስለሌለ ገንዘቡን እንዳስፈለገ ለማንቀሳቀስና ለመላክ እንዲቻል በመታሰቡ ነው ብላለች፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ በቆየው የ3ኛው ቻን ቻምፒዮንሺፕ የኢትዮጵያን የምድብ 3 ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት በማስተላለፍ እና የተለያዩ ዘገባዎችን በመስራት ለሙያው ያለውን ፍቅር እና ትጋት አሳይቷል፡፡ ዘገባውን በቀጥታ እየሰራ የነበረው መኳንንት በርሄ ነው ህክምናውን ለማድረግ እዛው ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅድስተ ማርያም ቅርንጫፍ የባንክ ቁጥር….. 1000070999076 ወይንም ተጨማሪ መረጃ ካስፈለገ ደግሞ ጓደኛውን ትዕግስት ገመቹን ማነጋገር ይቻላል፡፡ ስልክ…0910-10-17-93

             የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ባለፈው ሰኞ በቀጥታ የአገሪቱ ቴሌቪዥን የተሰራጨ ንግግር አድርገዋል፡፡ የአልበሽር ንግግር በሶስት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን ለመጀመርያ ጊዜ  የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን ያካተተ ነበር። በቻይና መንግስት ትብብር በተሰራው የብሉ ናይል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከተሳተፉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል አልበሽር ወደ ስልጣን የመጡበትን የ1989ኙን መፈንቅለ- መንግስት በማቀነባበር ወሳኝ ሚና የተጫወቱትና በ2000 ዓ.ም ከገዢው ፓርቲ የ“ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ” ተገንጥለው “ኦፖዚሽን ፖፑላር ኮንግረስ” ፓርቲን ያቋቋሙት ሀሰን አልቱራቢ፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የአልበሽር አማካሪ የነበሩትና ታህሳስ ላይ የ“ለውጥ ፓርቲ”ን የመሰረቱት ጋዚ ሳላሀዲን አትባኒ እና የ“ኡማ ፓርቲ” መሪ  ሳዲቅ አልመሃዲ ይገኙበታል፡፡
አልበሽር በንግግራቸው ላይ ሶስት የለውጥ ፕሮግራሞች ያሏቸውን ነጥቦች ይፋ አድርገዋል። የመጀመሪያው ፕሮግራም ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ተከታታይ ውይይት አሁን በስራ ላይ ባለው የአገሪቱ ህገመንግስት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በመምከር፣ ህገመንግስቱ የገዥው ፓርቲ ሰነድ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር፣ ሁሉንም ሀይሎች ያሳተፈ ህገመንግስት ማርቀቅን ያካትታል።  ሁለተኛው ፕሮግራማቸው በአገሪቱ ውስጥ ፀጥታ እና መረጋጋትን  በማምጣት፤ሱዳንን ከአማፂያን ሽኩቻ ነፃ ማድረግ እንደሆነ የገለፁት አልበሽር፤ለዚህ ደግሞ የአቡጃ፣ የዶሃ፣ የስርት እና ሁሉን አቀፉን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ሶስተኛው ፕሮግራም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዳይንኮታኮት እርምጃ መውሰድን የሚመለከት ሲሆን ለዚህም የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሚደረግ አልበሽር ገልፀዋል፡፡ “ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካወጀች በኋላ ነዳጅ መደጎማችንን እንድናቆም  በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ስንመከር ተግባራዊ አለማድረጋችን ስህተት ነበር፡፡ በአለም ላይ የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ቢመጣም  ህዝባችን ላይ ጫና እንዲፈጠር ስላልፈለግን ተግባራዊ ሳናደርገው ቀርተናል፡፡ አዲሱ የኢኮኖሚ ፓኬጅ ድሆችን አይጎዳም፤ምክንያቱም ድሆች መኪና የላቸውም፡፡ እነሱን በዘካት ቻምበር እና በደሞዝ ጭማሪ እንዳይጎዱ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል፡፡
ሁሉም ሱዳናውያን የተሃድሶው ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረቡት አልበሽር፤ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል - ያለ ሰላም ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሌለ በመጥቀስ፡፡ አልበሽር ይሄን ይበሉ እንጂ የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም ተብሏል፡፡ “በሱዳን ውጤት የሌለው የፖለቲካ ሽኩቻ ማብቃት አለበት” በማለት ብቻ  ነው ጉዳዩን አድበስብሰው ያለፉት፡፡
  የአልበሽር የሰሞኑ ንግግር ከቀደምት ንግግሮች የሚለየው ተቃዋሚዎችን በማካተቱ ሲሆን ይሄም በ25 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከአስራ አራት አመት መለያያትና ተደጋጋሚ እስር በኋላ በአልበሽር ንግግር የታደሙት ሀሰን አልቱራቢ፣“ከንግግሩ የምንጠብቀውን አላገኘንም፤ስለፖለቲካ  እንቅስቃሴም ሆነ ስለሚዲያ ነፃነት ምንም አልተባለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የኡማ ፓርቲ መሪ  ሳዲቅ አልመሀዲ ግን በችኮላ አስተያየት ለመስጠት የፈለጉ አይመስሉም፡፡    “በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ አስተያየት ከመስጠቴ በፊት ጉዳዩን በደንብ ማጤን ይገባኛል” ነው ያሉት፡፡ የአገሪቱን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት የሚመሩት ፋሩቅ አቡ አሊ፣ከአልበሽር ንግግር ቀደም ብለው ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ፤“ፕሬዚዳንቱ በፖሊሲያቸው ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች በተለይ በመስከረሙ ግጭት የሞቱትን ሰዎች አስመልክቶ ይቅርታ ሲጠይቁ መስማት እፈልጋለሁ” ብለዋል። አልበሽር ግን የተባለውን  ይቅርታ ባለፈው ሰኞ ንግግራቸው ላይ  አልጠየቁም፡፡  
እንዲያም ሆኖ ግን የአልበሽር ድንገተኛ የለውጥና የህዳሴ ንግግር እንዲሁም የ“እንወያይ” ጥሪ ብዙዎችን አስገርሟል - ድንገተኛና ያልተጠበቀ በመሆኑ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ ከፍርሃት የመነጨ ነው ይላሉ - የአልበሽርን የለውጥና የህዳሴ ንግግር፡፡
በደቡብ ሱዳን ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በተለይም ከነዳጅ አቅርበት ጋር ተያይዞ በሰሜን ሱዳን ላይ አሉታዊ ጫናውን እንዳያሳርፍ በመፍራት የወሰዱት እርምጃ ነው የሚሉት ተንታኞች፤በሌላ በኩል የሚፈነዳበት ወቅት የማይታወቀው ነገር ግን አይቀሬው ህዝባዊ አመፅ ከመምጣቱ በፊት እድላቸውን ለመሞከር ሲሉ ያደረጉት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በተለያዩ የአረብ አገሮች የተካሄዱና አሁንም ያልበረዱ ህዝባዊ አመፆችን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ -ተንታኞቹ፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ የአልበሽር አዲስ የለውጥ ጥሪ  ከአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋር ያለባቸውን እሰጥ አገባ በአገር ውስጥ  ነፍጥ ከታጠቁ  ወገኖች ጋር በመደራደር ከራሳቸው ከሱዳናውያን የሚመጣውን ግፊት ለመቀነስ ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንዲህ ይበሉ እንጂ አልበሽር ቢያንስ በሰኞው ንግግራቸው መሳሪያ ከታጠቁ  ኃይሎች ጋር ስለሚደረገው ውይይት ምንም የሰጡት ፍንጭ የለም፡፡
የአልበሽር ንግግር ከመደረጉ በፊት የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት የተለያዩ መረጃዎችነ ለሚዲያዎች መስጠታቸውም ሌላው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን  ቀድመው በሰጡት አስተያየት፤ አልበሽር በንግግራቸው ሁሉን አቀፍ የሆነ የለውጥ እቅድ እንደሚያቀርቡና የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት ሁሉንም ወገኖች ያካተተ መፍትሄ እንደሚፈለግ ሲገልፁ፤ ሌላ ባለስልጣን ለሮይተርስ  በሰጡት መግለጫ፤ አልበሽር ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች የአገሪቱን ህገመንግስት እንደገና አርቅቀው መንግስትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀርባሉ ብለው ነበር። ከአልበሽር ንግግር በኋላ የተደበላለቁ እስተያየቶች መደመጣቸውን ተከትሎ የገዢ  ፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና  የፓርቲ ጉዳዮች ሀላፊ ኢብራሂም ጋንዱር በሰጡት መግለጫ “በሽር ለህዝቡ ንግግራቸውን ለማቅረብ ያቀዱት ከፓርቲዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ነበር፤ነገር ግን ብዙ ጥርጣሬዎች እና መላምቶች ቀድመው በመናፈሳቸው ለህዝቡ ንግግር ለማድረግ ተገደዋል” ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ከተሳተፉ በኋላ የንግግራቸውን ቀጣይ ክፍል እንደሚያቀርቡና ሁለተኛው ክፍል ብዙ ጉዳዮችን ዘርዘር ባለ መልኩ እንደሚያካትት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
“የሱዳን ህዳሴ” የሚለው ሰነድም በገዢው ፓርቲ በኩል የቀረበ በመሆኑ የመንግስት ሰነድ አድርጎ መውሰድ እንደማይቻል የገለፁት ኢብራሂም፤ፓርቲያችን ለሱዳን ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎች እያቀረበ ሳይሆን ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎችም የራሳቸውን ሀሳብ እንዲያመጡ እድል እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በሰኞው የአልበሽር ንግግር “ብዙዎች ተስፋ ቆርጠዋል” የሚለውን አስተያየት ኢብራሂም አይቀበሉትም፡፡  “አስተያየቱ ትክክል አይደለም፤ምክንያቱም ከአልበሽር ንግግር በኋላ የተሰራ ፈጣን ቅኝት ህዝቡ  በፕሬዚደንቱ ንግግር መርካቱን ነው የሚያሳየው” ብለዋል፡፡
በአለምአቀፍ ተቋሟት ይፋ የሚደረጉ የጥናት ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፤ሱዳን በሙስና፣ በልማት  እና በፕሬስ ነፃነት ረገድ  ከመጨረሻዎቹ የዓለም አገራት ተርታ ትመደባለች፡፡ ፕሬዚዳንት አልበሽርም  አስራ አንድ አመቱን ካስቆጠረው የዳርፉር ጦርነት ጋር በተያያዘ በሰዎች ግድያና በዘር ማጥፋት ወንጀል በአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት የሚፈለጉ መሪ ናቸው፡፡ ባለፈው መስከረም ወር  ከነዳጅ ዋጋ ጋር ተያይዞ በሱዳን በተፈጠረ አለመረጋጋት፣ ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች በፀጥታ ሀይሎች መገደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቢገልፅም፤የአልበሽር መንግስት ቁጥሩ እጅግ የተጋነነ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡

በሲኒማው ዘርፍ አስተዋጽኦ ለማድረግና ለፊልም ተመልካቹ የፊልሞችን ተደራሽነት ለማስፋት እየሠራ እንደሆነ የገለፀው ባታ ሪል እስቴት፤በ22 ማዞሪያ አካባቢ ባስገነባው “ባታ ኮምኘሌክስ” ህንጻ ላይ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት እንደሚከፍት አስታወቀ፡፡ በመዲናችን የፊልም ማሣያ ሲኒማ ቤት እጥረት እንዳለ ተገንዝቤያለሁ ያለው ድርጅቱ፤ክፍተቱን ለመሙላት በቅርቡ “አቤል ሲኒማ” ን በመክፈት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል።

በሙሉጌታ ቢያዝን የተሰናዳው ባለ “ሚኒስከርቷ” የሥነ ግጥምና አጫጭር ታሪኮች ስብስብ የተሰኘ መድበል ታትሞ ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ በ83 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ ግጥሞችንና ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን በ25 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ደራሲ መስፍን ኃ/ማርያም ይዘከራል “በመፃህፍት የዋጋ ተመንና ዋጋ የመፋቅ ጉዳይ” ላይ ከአከፋፋዮችና አዟሪዎች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በብሄራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፃህፍት አዳራሽ ምክክር እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ገለፀ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመፅሃፍ ዋጋ በህትመቱ ላይ ከተገለፀው ውጪ በተለያዩ መንገዶች እየተፋቀና እየተደለዘ በተጋነነ ዋጋ ለአንባቢያን መቅረቡ እንዳሳሰበው የጠቆመው ማህበሩ፤ድርጊቱ ደራሲውንም አንባቢውንም እየጎዳ ነው ብሏል፡፡ የማህበሩ የፅ/ቤት አስተባባሪና የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ አቶ ደሳለኝ ስዩም ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤በአሁኑ ጊዜ የመፅሃፉ ዋጋ 50 ብር ሆኖ ሳለ 0 በመጨመር 500 ብር እንዲሁም 25 ብር የሚለውን 250 ብር በማድረግ በተጋነነ ዋጋ እየተሸጠ ሲሆን ጉዳዩ በባለድርሻ አካላቱ ትኩረት እንዲያገኝ የዛሬው የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ታዋቂውንና አንጋፋውን የሥነፅሁፍ መምህርና ደራሲ መስፍን ኃ/ማርያም የሚዘክር ዝግጅት በመጪው ማክሰኞ እንደሚካሄድ ማህበሩ አስታወቀ፡፡ “ዝክረ መስፍን ኃ/ማርያም” በሚል የተዘጋጀው ፕሮግራም በብሔራዊ ሙዚየም የሚቀርብ ሲሆን በእለቱ ደራሲው በኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ ውስጥ ያበረከተው አስተዋፅኦ እየታሰበ ይመሰገናል ተብሏል፡፡

የሚውዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ መሥራች የነበረው የአርቲስት ሽመልስ አራርሶን የህይወት ታሪክ የሚዘክረው ፊልም

የፊታችን ሐሙስ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄድ ስነ ስርዓት ይመረቃል፡፡
የአርቲስቱን 7ኛ የሙት ዓመት መታሠቢያ ምክንያት በማድረግ በቁም ነገር ሚዲያ ስቱዲዮ የተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም፤

የአርቲስቱ  የህይወት ጉዞና ሥራዎች ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ስለአርቲስት ሽመልስ አራርሶ

የሙያ ምስክርነትና ልዩ ልዩ ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን በኤክስኘረስ ባንድ ጣዕም ያላቸው ሙዚቃዎችም

ይቀርባሉ ተብሏል።