Administrator

Administrator

‘ዘ ናይንቲ ናይን ሲሪየስ’ የተሰኘው የአይዳ ሙሉነህ ስራ

የታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት ፎቶግራፈር አይዳ ሙሉነህ እና የኢትዮ-አሜሪካዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ የስነ-ጥበብ ስራዎች፣ በፍራንክፈርት የሞደርን አርት ሙዚየም (MMK) ውስጥ  በተከፈተ አለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በመታየት ላይ እንደሚገኙ ታዲያስ ከኒውዮርክ ዘገበ፡፡
ታዋቂ አፍሪካውያን ዘመናዊ አርቲስቶች ስራዎቻቸውን ያቀረቡበትና ጣሊያናዊው የ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን  ገጣሚ ዳንቴ በጻፈው ‘ዘ ዲቫይን ኮሜዲ’ የተሰኘ የግጥም ስራ የተሰየመው ‘ሄቨን፣ ሄል፣ ፑርጋቶሪ ሪቪዚትድ ባይ ኮንቴምፖራሪ አፍሪካን አርቲስትስ’ የተባለው አለም አቀፍ የስነ-ጥበብ ኤግዚቢሽን፣ እስከ መጪው ሃምሌ አጋማሽ ድረስ ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
በታዋቂው የስነ-ጥበብ አጋፋሪ ሲሞን ጃሚ እና በሞደርን አርት ሙዚየም ትብብር በተዘጋጀው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ የቀረቡት ስራዎች፣ በቀጣይም በተለያዩ የአለም አገራት በሚገኙ አራት ቦታዎች ለእይታ እንደሚበቁ ተነግሯል፡፡
ከዚህ ቀደሞቹ  ከአፍሪካ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ኤግዚቢሽኖች በተለየ የአፍሪካ ስነ-ጥበብ፣ የድህረ ቅኝ-ግዛት ጉዳዮችን ማንጸባረቅ ብቻ ሳይሆን ውበትን አጉልቶ በማሳየት ጭምር ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል በሚል እምነት የዘንድሮውን ኤግዚቢሽን እንዳዘጋጀ፣ ሞደርን አርት ሙዚየም አመልክቷል፡፡
‘ዘ ናይንቲ ናይን ሲሪየስ’  የተሰኘውን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎቿን በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ለእይታ ያበቃችው አይዳ ሙሉነህ፣ ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በፊልም፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን፣ ስራዎቿን በተለያዩ ታላላቅ ኤግዚቢሽኖች ላይ ከማቅረብ ባለፈ፣ በርካታ አለማቀፍ ሽልማቶችን ለማግኘት የቻለች የፎቶግራፍ ባለሙያ ናት፡፡  
በአሁኑ ወቅት፣ ‘ደስታ ፎር አፍሪካ’ (DFA Creative Consulting plc.) የተባለና ትኩረቱን የፈጠራ ሥራዎች ላይ በማድረግ፤ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚሆኑ የፈጠራ ሃሳቦችን የማማከር፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ፎቶግራፎችን የማንሳትና ባህላዊ ዝግጅቶችን የማቀድ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ኩባንያ በማቋቋም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡
የታላላቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ታሪክ በሚተርከውና በቅርቡ ለህትመት እንደሚበቃ በሚጠበቀው ‘ተምሳሌት’ የተሰኘ መጽሃፍ ውስጥ የተካተቱት በርካታ ፎቶግራፎችም በአይዳ የተነሱ ናቸው፡፡
ነዋሪነቷ በኒውዮርክ የሆነው ኢትዮ-አሜሪካዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱም፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የስነጥበብ ትምህርቷን የተከታተለች በአለማቀፍ ደረጃ የምትጠቀስ ሰዓሊ ናት፡፡ የተለያዩ አለማቀፍ ሽልማቶችን የተቀበለች ሲሆን  የስዕል ስራዎቿም በከፍተኛ ዋጋ ተሸጠውላታል፡፡ ከእነዚህም መካከል፣ የዛሬ አራት ዓመት በታዋቂው አጫራች ድርጅት ሱዝቤይ አማካይነት፣ 1 ሚሊዮን 22 ሺህ  ዶላር (20 ሚሊዮን ብር ገደማ) የተሸጠላት ርዕስ አልባ ስዕሏ  ይጠቀሳል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን÷ በየመድረኩ ከሚሰማው የአክራሪነት ፍረጃና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ የገጠሙትን የስም ማጥፋትና የማኅበሩን አገልግሎት የማሰናከል ወቅታዊ ተግዳሮቶች፣ ተቀራርቦ በግልጽ በመመካከርና በጸሎት መፍትሔ ለማስገኘት ሲያደርግ የቆየውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡
የማኅበሩ የሥራ አመራር ጉባኤ ከመጋቢት 27 - 28 ቀን 2006 ዓ.ም በአቡነ ጎርጎሬዎስ ት/ቤት አዳራሽ ባካሔደውና ከ46 የሀገር ውስጥና የውጭ ማእከላት የተውጣጡ 160 ያህል አመራሮች በተሳተፉበት የመንፈቅ ዓመት መደበኛ ስብሰባ በወቅታዊ ኹኔታዎች ላይ ባደረገው ግምገማ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ህልውናና በማኅበሩ አገልግሎት ቀጣይነት ላይ ተጋርጧል ያላቸውን ወቅታዊ ተግዳሮቶች በዝርዝር በማንሣት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተጠቁሟል፡፡
የሥራ አመራር ጉባኤው ለማኅበሩ አስፈጻሚ አካል ባስቀመጠው የመፍትሔ አቅጣጫ፣ ማኅበሩ በቅ/ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደርያ ደንብ መሠረት ትውልዳዊ ተልእኮውን ለአባቶች በመታዘዝና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመወሰን የመፈጸም አሠራሩና ፍላጎቱ እንደጸና መኾኑንና ለወቅታዊ ተግዳሮቶቹ በግልጽ ተቀራርቦ ከመመካከርና ከጸሎት ውጭ በሌላ መንገድ የሚመጣ መፍትሔ ይኖራል ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡
የሥራ አመራር ጉባኤው በተዛባ አመለካከትና በሐሰተኛ ክሥ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶችና የመንግሥት አካላትን ግራ በማጋባትና በማሳሳት የማኅበሩን አገልግሎት ማስተጓጎል ዋነኛ አጀንዳ አድርገዋል ባላቸው ግለሰባዊና ቡድናዊ ቅስቀሳዎች ላይ በትኩረት መወያቱ ተነግሯል፡፡
መንግሥት ከሚያካሒደው የፀረ አክራሪነት ትግልና ከቤተ ክርስቲያኒቷ የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ አፈጻጸም ጋራ በማያያዝ የሚሰነዘሩበትን የስም ማጥፋት ዘመቻዎችና መሠረተ ቢስ ክሦች ከአባቶች፣ ከአስተዳደር ሓላፊዎች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች፣ ከመንፈሳውያን ማኅበራትና ከመላው ምእመናን ጋራ ተቀራርቦ በመረዳዳትና በጸሎት ፍትሐ እግዚአብሔርን በመጠየቅ የመፍታት የወትሮ ጥረቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን አቅጣጫ ማስቀመጡንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የማኅበሩ ዓላማና ፍላጎት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚነሣና ጥቅሙም ለቤተ ክርስቲያኒቱ በመኾኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱና ከሀገሪቱ ህልውና የሚቀድም የተለየ የማኅበር (ቡድናዊ) ዓላማና ጥቅም እንደሌለም የሥራ አመራር ጉባኤው ያወጣው ውሳኔ ያመለክታል፡፡
አባላቱንና ተቋማዊ አሠራሩን በተመለከተ በማስረጃ ተደግፈው የሚቀርቡለትን ችግሮች ከመተዳደርያ ደንቡና ከውስጣዊ አሠራሩ አኳያ ያለማመንታት ለማረም ምንጊዜም ዝግጁ እንደኾነ የመከረው የሥራ አመራር ጉባኤው፥ ቤተ ክርስቲያናቸውን ከመከባከብ ባሻገር ለሀገራቸው ልማታዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚበቃ አቅምና ሥነ ምግባር እንዳላቸው የሚያምንባቸውን ከ30ሺሕ መደበኛና ከግማሽ ሚልዮን በላይ ደጋፊ አባላት ያቀፈውን ይህን መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር በማበረታታት የድርሻውን እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ፣ በተለያዩ ክሦችና ውንጀላዎች ለማሸማቀቅ ያለዕረፍት የሚደረገው ሐሰተኛ ቅስቀሳና የክሥ ዘመቻ አግባብነት እንደሌለው ውጤትም እንደማያመጣ አስታውቋል፡፡    

የከባድ ሚዛን ቦክሰኞቹ ኢትዮጵያዊው ሳሚ ረታ እና ግብጻዊው አህመድ ሰኢድ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን የማጠናከር አላማ ይዞ በሚዘጋጀውና በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄደው የቦክስ ግጥሚያ አገራቸውን ወክለው እንደሚፋለሙ ተገለፀ፡፡
ኢትዮጵያዊው የከባድ ሚዛን ቦክሰኛ ሳሚ ረታ ባለፈው ሳምንት ለአናዶሉ ኤጀንሲ እንደተናገረው፣ ሁለቱ ቦክሰኞች ሰላማዊውን ፍልሚያ ለማካሄድ ተፈራርመው ቀን የቆረጡ ሲሆን  የአለም አቀፉ የቦክስ ፌዴሬሽንም ለውድድሩ እውቅና ሰጥቷል፡፡ ውድድሩን ያዘጋጀው ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነው ‘አፍሪካ ስፖርትስ ፕሮሞሽን’ የተባለ ድርጅት ሲሆን  የውድድሩ አላማም በሁለቱ አገራት መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን ማጠናከር ነው፡፡ ውድድሩ፣ ‘አፍሪካውያን አንድ ህዝቦች ናቸው’ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ ይሆናል ተብሏል፡፡ “ግጥሚያው የሁለቱን አገራት አንድነት የምናሳይበትንና ‘አለመተማመን ገደል ግባ!’ ብለን በጋራ የምናውጅበትን ዕድል ይፈጥራል” ብሏል ሳሚ ረታ፡፡ የአለም አቀፉ የቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ኦኔስሞ ኤ ንጎዊ በበኩላቸው፣ የውድድሩ መሰረታዊ አላማ በአፍሪካ አህጉር ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ “በአፍሪካውያን  መካከል ህብረት መፍጠር” የሚለውን ይህን ታላቅ ሃሳብ ይዞ ለተነሳው ለሳሚ ረታ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት ውሳኔ ማሳለፏ አስደስቶኛል፡፡ አባይ ለሁሉም የሚበቃ የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ ሁሉም አገራት በሰላማዊ ሁኔታ አብረው መኖር የሚችሉበትን እንዲሁም የፈጣሪን ስጦታ በትብብር መንፈስ የሚጋሩበትን መንገድ እንዲፈልጉ እንመክራለን” ብለዋል ንጎዊ፡፡
የቦክስ ግጥሚያው በናሽናል ኤርዌይስ ስፖንሰርነት በዲኤስ ቲቪ ሱፐር ስፖርት ቻናል በቀጥታ እንደሚሰራጭ የገለጸው ሳሚ፣ ግብጻዊው ተፋላሚው አህመድ ሰኢድም፣ በውድድሩ ለመሳተፍ በሙሉ ፈቃደኝነት ተስማምቶ ፊርማውን እንደማኖሩ፣ ቀኑን አክብሮ እንደሚመጣና እንደሚፋለሙም በእርግጠኛነት ተናግሯል፡፡
የውድድሩ ስፖንሰር የናሽናል ኤርዌይስ ባለቤት አቶ አበራ ለሚ በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው የውድድሩን ሃሳብ ታላቅነት በመረዳትና በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የሚጫወተውን ሚና በማጤን፣ ግጥሚያውን ስፖንሰር ማድረጉን ለአናዶሉ ኤጀንሲ ተናግረዋል፡፡
የ32 አመቱ የከባድ ሚዛን ቦክሰኛ ሳሚ ረታ፣ ከዚህ በፊት ካደረጋቸው 21 የቦክስ ግጥሚያዎች፣ በ18ቱ ማሸነፉን ለኤጀንሲው ገልጿል፡፡

“ተጨባጩንና እውነተኛውን ነገር በጠበቃዬ በኩል ለፍ/ቤት አቅርቤያለሁ”

በተለይ “ገመና” በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የዶ/ር ምስክርን ገፀ-ባህሪ ተላብሶ በመጫወት እውቅናን ያተረፈው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ የ600 ሺህ ብር ክስ የተመሠረተበት ሲሆን አርቲስቱ ለተከሰሰበት ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጥ ፍ/ቤቱ ለትላንትና ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡
ክሱ መመስረቱን ያልካደው አርቲስት ዳንኤል፤ ሆኖም “ክሱ መሰረተ ቢስና ከእውነት የራቀ መሆኑን በመግለፅ ተጨባጩን እውነታ አስፍሬ በጠበቆቼ በኩል ለፍ/ቤት ምላሽ ሰጥቻለሁ” ብሏል - ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ በመሆኑ ከዚህ በላይ ለመናገር እንደማይፈልግ በመግለፅ፡፡
አርቲስት ዳንኤልና ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ፤ “ፋየር ፕሩቭ” የተሰኘ የእንግሊዝኛ ፊልም ወደ አማርኛ በመመለስ አብረው ለመስራት ውል ተፈራርመው የነበረ ሲሆን “አርቲስቱ በገባው ውል መሰረት ስራውንም አልሰራም ብሬንም አልመለሰም” በማለት ወ/ሮ ቤተልሄም የ662 ሺህ 120 ብር ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ፍትሀ ብሔር ቢፒአር ችሎት መመስረታቸው  ታውቋል፡፡
አርቲስት ዳንኤል “ፋየር ፕሩቭ” የተሰኘ የእንግሊዝኛ ፊልም ወደ አማርኛ በመመለስ ስምንት ያህል ትዕይንቶችን ከቀረፀ በኋላ አቋርጦ “የሴም ወርቅ” የተሰኘ ሌላ ፊልም መስራት የጀመረ ሲሆን በዚህ ወቅት ነበር ወ/ሮ ቤተልሔም እሱ የጀመረውን ፊልም “አብረን  እንስራ” የሚል ጥያቄ ያቀረቡለት- አርቲስቱ በቅርቡ ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው፡፡
አርቲስቱ የጀመረውን “ፋየር ፕሩቭ” የተሰኘ ፊልም ከወ/ሮ ቤተልሔም ጋር አብረው ለመስራት ተስማምተው ከተዋዋሉ በኋላ ወደ ሥራው የገቡ ቢሆንም በኋላ ላይ “ወ/ሮዋ የስነ ምግባር ጉድለት ስላለባቸው አብሬያቸው መስራት አልቻልኩም” በሚል ዳንኤል ስራውን ያቆመ ሲሆን ወ/ሮ ቤተልሄም በበኩላቸው፤አርቲስቱ በውሉ መሰረት ፊልሙን በጊዜ ሰርቶ ባለማስረከቡ ብሩን እንዲመልስ መጠየቃቸውንና እሱም ብር አልወሰድኩም በማለቱ ግጭቱ እንደተካረረ መዘገቡ  ይታወሳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮፒካሊንክ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች ከወ/ሮ ቤተልሄም ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣“የስም ማጥፋት ዘመቻ አካሂደውብኛል” ያለው አርቲስቱ፤በግለሰቧና በአዘጋጆቹ ላይ ክስ መመስረቱን ታህሳስ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ተናግሯል፡፡
ወ/ሮ ቤተልሔም የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም በአርቲስት ዳንኤል ላይ የ662ሺህ 120 ብር ክስ መመስረታቸውን የጠቆሙት ምንጮቻችን፤ ከሳሿ የቼክ ቁጥሮችን በማስረጃነት አያይዘው ለፍ/ቤቱ እንዳቀረቡ ገልፀዋል፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፤ ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ ወደ ክስ ለመሄድ የተገደዱት ለፊልሙ መስሪያ ብለው ለአርቲስቱ የሰጡትን ገንዘብ እንዲመልስ ሲጠይቁት “ብር አልወሰድኩም” በማለቱ ነው፡፡ ፍ/ቤቱ አርቲስት ዳንኤል ለቀረበበት ክስ በትላንትናው እለት ምላሽ እንዲሰጥ  ትዕዛዝ አስተላልፎ የነበረ ሲሆን አርቲስቱም ምላሹን በጠበቆቹ በኩል ለፍ/ቤት ማስገባቱን ገልጿል። ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

ከግብጽና ከአልጀሪያ ቀጥላ በአፍሪካ 3ኛ ናት

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ  አገራት ጠንካራ ወታደራዊ ሃይል በመገንባት የመጀመሪያውን ስፍራ እንደምትይዝ በ“ግሎባል ፋየር ፓወር” የተሰራ ጥናት አመለከተ፡፡
 “ግሎባል ፋየር ፓወር” 40 ያህል የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም የአገራትን ወታደራዊ አቅም ለመፈተሽ  የሰራው አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 182 ሺህ ያህል በስራ ላይ የሚገኙ ወታደሮች ያሏት ሲሆን  ከ24 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎቿም በውትድርና መስክ ለመሰማራት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡
ከ560 በላይ ታንኮችና ከ780 በላይ የወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ያሏት ኢትዮጵያ፣ በአህጉሩ ጠንካራ ከሚባሉ አየር ሃይሎች የአንዱ ባለቤት መሆኗን የሚጠቅሰው ጥናቱ፣ አየር ሃይሉ ከ81 በላይ የጦር አውሮፕላኖችና 8 ተዋጊ ሂሊኮፕተሮች እንዳሉትም ገልጿል፡፡
አገሪቱ ለመከላከያ የምትመድበው አመታዊ በጀት 340 ሚሊዮን  ዶላር መድረሱን የጠቆመው ጥናቱ፣ ኢትዮጵያ ከግብጽና ከአልጀሪያ ቀጥላ በአፍሪካ አህጉር ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ያላት ሶስተኛዋ አገር ናት ብሏል፡፡

የማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን ማሰልጠኛ ተቋም የቀድሞ ተማሪዎች የፎቶግራፍ ስራዎች አውደ ርዕይ የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ በ10፡30 በብሔራዊ ትያትር አርት ጋላሪ ይከፈታል፡፡ በአውደ ርዕዩ በአስራ ሶስት የፎቶግራፍ ባለሞያዎች የተነሱ ፎቶግራፎች የሚቀርቡ ሲሆን አውደ ርዕዩ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ ድረስ ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ የማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን ማሰልጠኛ ተቋም ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዜብ ከበደ ገልፀዋል፡፡

Monday, 07 April 2014 16:00

33ኛው “ግጥም በጃዝ”

ረቡዕ ይካሄዳል
33ኛው የ“ግጥም በጃዝ” ምሽት የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ ግጥሞች፣ ወጎችና ዲስኩር በሚቀርብበት ዝግጅት፤ አርቲስት ግሩም ዘነበ፣ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ፣ ምንተስኖት ማሞ፣ በረከት በላይነህ እና ሚሊቲ ኪሮስ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ የመግቢያው ዋጋ በነፍስወከፍ 50 ብር ነው።

በፊልም ባለሙያዋ መቅደስ በቀለ (ማክዳ) ደራሲነትና ዳይሬክተርነት ተሰርቶ በኤራሶል ፊልም ፕሮዳክሽን የሚቀርበው “ሊነጋ ሲል” የተሰኘ አዲስ ፊልም በቅርቡ ለእይታ ሊበቃ ነው፡፡ የፊልሙ ዘውድ ፍቅር ድራማ ሲሆን በ “ባለታክሲው” ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የተወነው ሚኪያስ መሐመድ፣ ታዋቂዋ ተዋናይት ማህደር አሰፋ፣ ቃል ኪዳን አበራ፣ ቢንያም በቀለና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያኖች ተውነውበታል፡፡ ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 11 ወራት የፈጀ ሲሆን በሚያዝያ ወር በግል ሲኒማ ቤቶችና በብሔራዊ ትያትር እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችና የዩቶፒያ ክለብ አባላት፤ በቢዝነስና በስራ ፈጠራ መስክ ለስኬት በማነሳሳት የሚታወቁ ሰዎችን በመጋበዝ አነቃቂ ፕሮግራም አዘጋጁ፡፡ ለአርብ መጋቢት 28 ልዩ ዝግጅት የተመረጠው ቦታ የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተጨማሪ የ“ባለራዕይ ቶክሾው” ባለቤት ዶ/ር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል እና ዶ/ር ወረታው በዛብህ እንዲሁም የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በእንግድነት ተጋብዘዋል፡፡ ውጤታማው የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው እንዲሁም ታዋቂ አርቲስቶች ግሩም ኤርሚያስ እና ሰለሞን ቦጋለ እንደተጋበዙም አዘጋጆቹ ገልፀው፤ ተማሪዎችን ለቢዝነስና ለስራ ፈጠራ በማነሳሳት መልካም ስነ-ምግባርን የሚያላብስ ዝግጅት ነው ብለዋል፡፡

በአንተነህ ግርማ ተፅፎ በኪሩቤል አስፋው ዳይሬክት የተደረገው ‹‹ፍቅር ሲመነዘር›› ፊልም ነገ በ11ሰዓት በሀርመኒ ሆቴል በቀይ ምንጣፍ ሥነ ሥርዓት ይመረቃል፡፡ የ1ሰዓት ከ42 ደቂቃ ርዝመት ያለው ‹‹ፍቅር ሲመነዘር››፤ ሮማንስ ኮሚዲ ፊልም ሲሆን፤ በነገው ዕለት በኤድናሞልና በሀርመኒ ሆቴል እንደሚመረቅ ካም ግሎባል ፒክቸርስ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ‹‹አማላዩ››፣ ‹‹ስውሩ ሰይፍ››፣ ‹‹በራሪ ልቦች››፣ ‹‹ሼፉ››፣ ‹‹ወደ ገደለው›› እና ‹‹አማረኝ›› የተባሉ ፊልሞችን ሰርቶ ለእይታ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡