Administrator

Administrator

 ወረርሽኙን ለማስቆም 70 በመቶ የአለም ህዝብ መከተብ ይኖርበታል የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ለ7 ተከታታይ ሳምንታት መቀነስ አሳይቷል

            በመላው አለም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከክትባቱ በበለጠ ፍጥነት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፣ ያም ሆኖ ግን በአለማቀፍ ደረጃ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፉት 7 ተከታታይ ሳምንታት መቀነስ  ማሳየቱ እንደ መልካም ዜና ሊወሰድ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በአለማችን ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር ለረጅም ጊዜ በተከታታይነት የቀነሰው ባለፉት 7 ሳምንታት ነበር ያሉት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ይህ መልካም ዜና ቢሆንም የሟቾች ቁጥር ግን በተጠቂዎች ቁጥር መጠን ሊቀንስ አለመቻሉንና ቫይረሱ በተለይም አፍሪካን በመሳሰሉ እዚህ ግባ የማይባል የክትባትና የህክምና አቅርቦት የሌለባቸው የአለማችን ክፍሎች በፍጥነት በመሰራጨትና በርካቶችን በመግደል ላይ እንደሚገኝ በሳምንቱ መጀመሪያ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት፣ በጽኑ ከታመሙ የቫይረሱ ተጠቂዎች ብዛት ያላቸው ሰዎች ለሞት የሚዳረጉባት ቀዳሚዋ የአለማችን ክፍል አፍሪካ መሆኗን ማረጋገጡንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የቡድን ሰባት አገራት ከሰሞኑ ባካሄዱት ስብሰባ፣ መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ላላቸው አገራት 870 ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለመለገስ መስማማታቸውን ያደነቁት ዳይሬክተሩ፤ ወረርሽኙን ለማስቆም እስከ መጪው አመት ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ ቢያንስ 70 በመቶውን መከተብ እንደሚገባና ለዚህም 11 ቢሊዮን ክትባቶች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል፡፡
በእንግሊዝ ሳምንቱን አመታዊ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት የቡድን 7 አገራት፣ ለደሃ ሀገራት ለመስጠት ቃል የገቡት 1 ቢሊዮን የሚጠጋ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለአገራቱ በቀጥታ ወይም በአለም የጤና ድርጅት የክትባት ጥምረት ኮቫክስ በኩል እንዲደርስ ይደረጋል መባሉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜናም፣ በአሜሪካ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ማክሰኞ ከ600 ሺህ ማለፉን የዘገበው የአሜሪካ ድምጽ፣ የተጠቂዎች ቁጥር በአንጻሩ ከ33.5 ሚሊዮን ማለፉ መነገሩን ገልጧል፡፡


ከዕለታት አንድ ቀን አያ ጅቦ አራት ልጆቹን፤ ማለትም - መዝሩጥን፣ ማንሾሊላን፣ ድብልብልን እና ጣፊጦን ይዞ በለሊት መንገድ ይሄዳል፡፡ እየተጓዙ ሳለ ድንገት አንዲት ከቤቷ የወጣች አህያ ያገኛሉ፡፡ ይሄኔ አባት ጅብ፤
 “ልጆቼ ሆይ! እንግዲህ እኔ በጣም አርጅቻለሁና ይቺን አህያ እኔ ነኝ የምበላት! እናንተ ራቅ ራቅ ብላችሁ ትጠብቁኛላችሁ” አለ፡፡
ይሄኔ መዝሩጥ፤ “አባዬ ኧረ አንድ ብልት እንኳን አጋራን?” ይለዋል፡፡
 “አይሆንም! ምንም አላቀምስህም” ይላል ጅቦ፡፡
 ይሄኔ ማንሾላ ይነሳና፤ “ለእኔስ አባቴ?” ይላል፡፡
 አያ ጅቦም፤ “እንካ ጆሮዋን ብላው” ይለዋል፡፡
ቀጥሎ ድብልብል ይመጣና፤ “ለእኔስ አባቴ?” ይለዋል፡፡
“አንተ ሽሆና ይደርስሃል” ይላል አያ ጅቦ፡፡
ቀጠለና ጣፊጦ ጠየቀ፡- “አባዬ የእኔንስ ነገር ምን አሰብክ?” አለ፡፡
 “አንተ ቆዳዋን ካገኘህ ያጠግብሃል” አለ፡፡
ልጆቹ አባታቸው አህያዋን ዘርጥጦ ጥሎ ሲበላ ዘወር አሉ፡፡ አያ ጅቦ ዋና ዋናውን የአህያዋን ብልት እንደበላ፤ ድንገት የአህያዋ ጌታ ሲሮጥ መጣ፡፡ አያ ጅቦ ፈርጥጦ መውጫ የሌለው የጫካ ጥግ ውስጥ ገብቶ ይሰረነቅና እየጮኸ ልጆቹን ይጠራል፡፡ ልጆቹ ቀርበው ወደ ጫካው ይጠጉና፤ “አባታችን ምነው ትጮሃለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
አያ ጅቦም፤ “አድነን ልጄ መዝሩጥ?” ይላል፡፡
 መዝሩጥም፤ “አባቴ ምን ሰጥተኸኛል እንደበላህ እሩጥ!”
#ልጄ ማንሾለላ!” ይላል አያ ጅቦ፡፡
 “ምን ሰጥተኸኛል ካንድ ጆሮ ሌላ!?” ይለዋል ማንሾለላ፡፡
“አድነኝ ልጄ ድብልብል?”
 “አይ አባት! ሸሆና ለማን ውለታ ይሆናል?!”
 ቀጥሎ አያ ጅቦ ጣፊጦን ጠየቀ፤ “አድነኝ ልጄ ጣፊጦ?!”
“ማን የጎረሰውን ማን አላምጦ?” አለ ጣፊጦ፡፡
መላወሻም አጋዥም ያጣው አያ ጅቦ፤ እዚያው ተወጋና ሞተ፡፡
 * * *
 ዛሬ እኔ ነኝ ዋናው ጅብ ማለት አይሠራም! ቀድመው ያላሰቡበት ግለኝነትና ሆዳምነት ምን ላይ እንደሚጥለን አለማሰብ፣ የማታ ማታ ያላጋዥ ያለመጠጊያ ያስቀራል፡፡ ከካፒታሊዝም ምርኮኛነታችን ጀምሮ ስግብግብነት፣ በዝባዥነት፣ ዘረፋና ግፍ ይበረክታል፡፡ ያላየነው የገንዘብ ትርፍ ማህበራዊ መልካችንን ያዥጎረጉረዋል፡፡ እንኳን ሊያተርፈን ራሳችንን ያጎልብናል፡፡ “አድነኝ ልጄ እገሌ?” ቢባል ምላሽ አይኖረውም፡፡ ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ መግባባትና መስማማት ያለብን ሰዓት ነው፡ ፡ ስለ ምርጫ መግባባታችን፣ ስለ ሃይማኖት መግባባታችን፣ ስለ አንድነት መግባባታችን፣ ስለ ድንበር ጉዳይ መግባባታችን፤ ስለ ውሃ ፖለቲካ መግባባታችን፣ ስለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች መግባባታችን፤ ስለ ዓለም ዲፕሎማሲ መግባባታችን… ስለ ሃያላኑ ፉክክር መግባባታችን፣ ብርቱ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ የሳሱ ድንበሮችና መንግስት አልባ አገራት ወደ አሰቃቂ እልቂት ሊያመሩ እንደሚችሉ፤ ሶማሊያም፣ የመንም፣ ሊቢያም፣ ኢራቅም ሶሪያም  ለመነሻ አስረጅነት የቆሙ ተጨባጭ ምሳሌዎቻችን ናቸው! ነገ በየአገሩ ይሄው ሁኔታ ላለመከሰቱ ምንም አስተማማኝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህልውና የለም፡፡ በትናንሽ የፖለቲካ አታካራ ተሞልተን፣ ትናንሽ ሙሾ በማውረድ ጊዜያችንን ከምናባክን፣ ትልቁን የዓለም አቀፍም አገር አቀፍም ስዕል (The Bigger Picture) የምናይበትን ዐይናችንን እንክፈት፡፡
 ምዕራባውያን፤ ባህል፣ ሃይማኖትና ጥናታዊ ታሪክ ያላቸውን አገሮች ኢራቅ፣ ኢራን፣ ሶርያ፣ የመን፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና … አሁን ደግሞ የእኛው አገር ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩት ያለ ነገር አይደለም፡፡ ግሎባላይዜሽንን ይነቅፋሉ የሚለው አጀንዳ የዋዛ አይደለም፡፡ ባህል የሌላቸው ባለ ባህሎቹን እየገደሉ ነው፡፡ የቅርቦቹ ሶማሊያና ሊቢያ በመንግሥት-አልባ ሁኔታ ውስጥ መሆን፣ በማንም ይሁን በማን ለመጠቃታቸው ሰፊ በር ከፍቷል፡፡ ወደ ሊቢያ በጣሊያን አዛዥነት ስለዘመተው ያለዕዳው ዘማች የኤርትራ ወጣት (ደራሲው አበሻ ይለዋል) እንዲህ የሚል ሀሳብ ይገኝበታል፡፡ ስለ ሊቢያ በረሀ ነው፡- “የመሸበር ስሜት፣ ሐዘን፣ ተስፋ ቢስነት እና ፀፀት ፊታቸው ላይ ይነበባል፡፡ የበረሀው ስዕል አሰቃቂ ነው፡፡ አንዲት ዛፍ አትታይም፡፡ አንዲትም የሳር አገዳ የለችም፡፡ የውሃ ነገርማ ባይነሳ ይሻለዋል፡፡ ወደየትም አቅጣጫ መንቀሳቀስ አይታሰብም፡፡ ግራ፣ ቀኝ፣ ወደ ፊት፣ ወደ ኋላ፣ ወደ የትም መሄድ አይቻልም፤ ምክንያቱም የትም ይሁን የት ህይወት በአሸዋ ተከባ ነው የምትገኘው፡፡ በየትም ቢዞሩ ጠጠር ኮረት ድንጋይ፣ እና የአቧራ ክምር! ያ በረሀ እንደ ባህር ሰፊ፣ ግን በጥላቻ የተሞላ! ባህሩ ውስጥ ቢያንስ ዓሣ ማየትና የማዕበል ድምፅ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ እዚህ ሊቢያ በረሃ ግን አንዲትም ወፍ አትዘምርም፡፡ አትበርምም፡፡ ያ ክፍቱ ደመና አልባ ሰማይ የጋለ ምድጃ ነው፡፡ በዚያ ጠራራ ንደድ ውስጥ ያለ ሰው፣ ያ መሬት፣ የህይወት ይሁን የሞት መለየት ይሳነዋል፡፡ ይሄን መሬት ከአረንጓዴው፣ ከንፋሳማው እና ከለሙ የኢትዮጵያ ምድር ጋር ማነፃፀር ከንቱ ድካም ነው! የሲዖልና የገነት ነው ልዩነቱ!?”
ስለ አበሻ የጦርነት ብቃት የሚገርም ትንተናም አለው - በሊቢያ በረሐ፡- አበሻ፣ ጣሊያንና አረብ የውጊያ መንፈሳቸው ምን ይመስላል? “ለአበሻ፣ ጦርነት ውጤቱ ምንም ዋጋ ያስከፍል ወደፊት መግፋት ነው፡፡ (ግፋ በለው እንደማለት) ለጣሊያኖች፤ አዛዥህ እንዳለህ ተዋጋ ነው፡፡ ጠላት ግንባር ለግንባር ቢፋጠጥህም ካልታዘዝክ አትተኩስም፡ ፡ ካልታዘዝክ ብትታረድም ፀጥ በል ነው! ለዐረቦች ወደ ጠላትህ ፈጥነህ ሩጥ፡፡ ሁኔታው የሚያዋጣ ከመሰለህ ነብስህን ለማዳን ፈርጥጥ ነው፡፡ የየተዋጊውን ባህሪ ለእኔ ብሎ መስማት የእኛ ፈንታ ነው፡፡ ጊዜው አስጊ ነው፡፡ ጎረቤቶቻችንን በቅጡ እናስተውል፡፡ ሩቅ የሚመስሉንን ዕጣ ፈንታ ስናይ፣ “ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት!” እንበል፡፡ “ጎረቤትክን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ!” ማለት የአባት ነው!!


  1. የተወዳዳሪዎች ብዛት
በኦሮሚያ ክልል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በአብዛኞቹ ቦታዎች፣ አይወዳደሩም፡፡
ገዢው ፓርቲ፣ በኦሮሚያ 60% ገደማና ከዚያ በላይ፣ ያለተወዳዳሪ ነው የቀረበው፡፡
2.  የብርቱ ፉክክር አካባቢዎች
አዲስ አበባ፣ ለከተማ ምክር ቤትና ለፓርላማ፣ ሶስት ፓርቲዎች በብርቱ የሚፎካከሩበት ሆኗል፡፡ ብልፅግና፣ ኢዜማና ባልደራስ፡፡
የአማራ እና የደቡብ ክልሎች፣ በተለይ ከተሞችና ዙሪያቸው፣ የበርካታ ፓርቲዎች፣ ዋና የፉክክር አካባቢዎች ናቸው፡
3. የምርጫው መንፈስ
የአምስት ዓመት የአመፅ፣ የለውጥና የነውጥ ክስተቶችን ተከትሎ የሚካሄደው ምርጫ፣ ደብዘዝና ረጋ ያለ ስሜት ተላብሷል፡፡
በተጠበቀው ብዛት፣ መራጭ፣ በጊዜ አልተመዘገበም፡፡ ግማሽ ያህል ሳይመዘገብ፤ የጊዜ ገደቡ በመድረሱ ነው፣ የተራዘመው፡፡
የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የሰላም መደፍረስ፣ የፀጥታ ችግር፣ ግጭትና ጥቃት፣ የምርጫውን መንፈስ አደብዝዘውታል፡፡
በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመረጋጋት አዝማሚያ መያዛቸው፣ ገዢው ፓርቲም የበርካታ ሚሊዮን አባላት መዋቅሩን በሙሉ ሃይል አለማዝመቱ፣ የምርጫ ትኩሳትን የሚያበርድ ሆኗል፡፡
የምርጫውንና የውጤቱን አዝማሚያ በቅጡ ለመለካት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የሙያና የብስለት አቅም ገና አልተፈጠረም፡፡
የምርጫ መረጃዎችን ማደራጀትና የጥናት ዳሰሳዎች፣ ማካሄድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ፣ ገና በወጉ አልተጀመሩም፡፡ ሰፊ ጥናትና ጥልቅ ትንተና ይቅርና፣ በጥሬው የዜጎች አስተያየትን ወይም የመራጮችን ዝንባሌ፣ የማጠያየቅ ልማድም የለም፡፡
የብዙ መራጮችን ትኩረት የሚስብ፣ ብዙ ዜጎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ምን ምን እንደሆነ፣ ከፓርቲዎችና ከፖለቲከኞች አቋም ጋር በማዛመድ የምርጫውን አዝማሚያ የሚጠቁም፣ የተጨበጠ መረጃና የተሟላ ትንታኔ ማቅረብ፣ ከኢትዮጵያ አቅም በላይ ነው፡፡
    እንዲያም ሆኖ፣ የተወዳዳሪዎች ብዛት፣ የፓርቲዎች አቅም፣ የመራጮች ምዝገባ፣ ጠቅላላ የምርጫው መንፈስና የአገሪቱ ሁኔታ፣ የማመዛዘኛ መስፈርቶች ናቸው፡፡    የተወዳዳሪዎች ቁጥር ማነስ፣ ለገዢው ፓርቲ አመቺ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዳት ነው፡፡ የተወዳዳሪዎች ብዛት ደግሞ፣ የገዢውን ፓርቲ ፈተና፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አቅም ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን፣ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርሳቸውም ተፎካካሪ ስለሆኑ፣ የመራጮችን ድምጽ የሚከፋፍልና የሚበትን፣ በዚህም የገዢውን ፓርቲ ፈተና የሚያቀል ሊሆን ይችላል፡፡ በኦሮሚያ ክልል፡
ለ171 የፓርላማ ወንበር የተመዘገበው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ 268 ተወዳዳሪዎች ይፎካከራሉ፡፡
በ104 የፓርላማ ወንበሮች ላይ፣ ብልፅግና ፓርቲ ብቻ ነው ተወዳዳሪ ያስመዘገበው፡፡
በአማራ ክልልም፡
ለ128 የፓርላማ ወንበሮች፣ በአጠቃላይ ከ740 በላይ ተወዳዳሪዎች ይፎካከራሉ፡፡ ለእያንዳንዱ ወንበር፣ በአብዛኛው 5 እና ከዚያ በላይ ተወዳዳሪዎች አሉ፡፡ ብዙ ፓርቲዎች የተረባረቡበት የአዲስ አበባ ብርቱ ፍክክር!
በአዲስ አበባ፣ ለእያንዳንዳንዱ የፓርላማ ወንበር፣ 7 ወይም ከዚያ በላይ ፓርቲዎች ይፎካከራሉ፡፡
በአዲስ አባባ፣ ለ23 የፓርላማ ወንበር በሚፎካከሩ ፓርቲዎች የቀረቡ እጩዎች፣


“ማመቅ” ወይስ “ማሟሟት”?!
ሙሼ ሰሙ
 
የማሳቹሴት ገዢና 5ኛው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤልብሪጅ ጄሪ፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩዎች እንዲያሸንፉ በሚያመቻች መልኩ ዲስትሪክቶቻቸውን በአዲስ መልክ እንዲካለሉ የሚፈቅድ ቢል ማጽደቃቸውን ተከትሎ፣ “ጄሪ ማንደሪንግ” የሚባል ቃል ተፈጠረ።
“ጄሪ” ከኤልብሪጅ ጄሪ ስም የተወሰደ ሲሆን “ማንደር” ደግሞ “ሳላማንደር” ከተባለው የድራገን ዝርያ በመዋስ የተፈጠረ ድቅል ቃል ነው። “ሳላማንደር” የሚለው ቃል መነሻው አንዱ አዲስ “ክልል” የአፈ ታሪኩን ድራገን “ሳላማንደር” በመምሰሉ ነበር። ዛሬ ላይ ቃሉ ከመለመዱ የተነሳ ምርጫን ለማጭበርበር አዳዲስ አከላለልን የሚፈጥሩ መንግስታት መጠርያ ሆኗል።
የሳላማንደር “መንግስታት” በሳላማንደሪንግ ድምጽን ለማፈን ሁለት ስትራቴጂ እንደሚጠቀሙ ይወሳል።
1ኛ) መፈልቀቅ/ማሟሟት (Cracking) ይባላል። የተቃዋሚ ፓርቲ መራጮችን በሰፊ አከላለል ውስጥ በመበተን ወይም ወረዳን ወደ ክፍለ ከተማ በማሳደግ የተቃዋሚን ድምጽ በማሟሟት (Dilute) ድምጻቸውን ማሳሳት ነው።
2ኛ) ማመቅ (Packing) ይባላል። የተቃዋሚ ፓርቲ መራጮችን ድምጽ በአንድ አካባቢና ዝቅተኛ መስተዳድር፣ ቀበሌ ወይም ወረዳ እንዲታጨቅ በማድረግ ድምጻቸውን ማፈን ነው።
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በ1997 ላይ አንዳንድ የአዲስ አበባ ወረዳዎችን በማጣመርና ሌሎችን በመክፈል ጄሪ ማንደሪንግ ሰርቷል። ለምሳሌ ወረዳ 17 ላይ 4 ገበሬ ማህበር በመደበል፣ ከወረዳ 15 ላይ ግማሹን ከወረዳ 18 ጋር በመቀላቀል፣ ቃሊቲና አቃቂን በማዋሃድ ወዘተ...
6ኛው የአዲስ አበባ ምርጫ እጩ አቀራረብ፣ ከወረዳ ወደ ክፍለ ከተማ መስፋፊያዎችን ከነባሮቹ ጋር ማጣመሩና 6 እጩ ከማቅረብ በክፍለ ከተማ ደረጃ 14 እጩ ወደ ማቅረብ መሸጋሸጉ የትኛውን “ጄሪ ምንደራ” ሊመስል ይችላል?! “ማመቅ” ወይስ “ማሟሟት”?! ከውጤቱ የምናየው ይሆናል?!!


ጣሊያናዊው አርቲስት ሳልቫቶሬ ጋራኡ ከአየርና ከመንፈስ አዋህጄ ሰራሁት ያለውና ‹እኔ ነኝ› የሚል ስያሜ የሰጠው በአይን የማይታይ ምናባዊ ሃውልት 18 ሺህ ዶላር መሸጡን ዘ ኒውዮርክ ፖስት ባወጣው አስገራሚ ዜና አስነብቧል፡፡
ግዝፍ ነስቶ የቆመ ሳይሆን ከዚህ በፊት ከተለመደው በተለየ መልኩ ምናባዊ የሆነውን አነጋጋሪ ሃውልት በተመለከተ አርቲስቱ በሰጠው ማብራሪ፤ ‹ልታዩት ባትችሉም፤ ሃውልቱ ግን አለ› ሲል መናገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ሃውልቱ ጣሊያን ውስጥ በሚገኝ አንድ አደባባይ በተከለለ 5 ጫማ በ5 ጫማ ስፋት ያለው ቦታ ላይ እንደሚገኝ መናገሩንም ገልጧል፡፡
አርትራይት በተባለው የጣሊያን የስነጥበብ ስራዎች አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለጨረታ የቀረበው ይህ አነጋጋሪ ሃውልት፣ ከከፍተኛ ፉክክር በኋላ በ18 ሺህ 300 ዶላር መሸጡን የጠቆመው ዘገባው፣ አሸናፊው ግለሰብ በአይን የማይታየው ምናባዊ ሃውልት ባለቤት መሆኑን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው መነገሩንም ገልጧል፡፡
ጣሊያናዊው አርቲስት በዚህ አመት ብቻ የማይታይ ሃውልት ሲሰራ ይህ ሶስተኛ ጊዜው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር በሚላን ከተማ መሰል ምናባዊ ሃውልት አቆምኩ በማለት ህዝቡን አደናግሮ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
‹ባዶ ቦታ አጥሮ፣ የምን ሃውልት እያሉ ማደናገር ነው› በማለት ለተቹት ሰዎች፤ ‹ሃውልቱን ለማየት የሚችለው፣ ምናበ ሰፊ የሆነ ሰው ብቻ ነው› ሲል አስገራሚ ምላሹን የሰጠው ጣሊያናዊው አርቲስት፣ ባለፈው ሳምንትም ከኒውዮርኩ የአክሲዮን ገበያ አቅራቢያ አንድ ነጭ ክብ ቦታ ከልሎ ‹አፍሮዳይት ፒያንጄ› የተሰኘ ሃውልቴን ጎብኙልኝ ሲል ብዙዎችን ማደናገሩን አውስቷል፡፡በመላው አለም ከ5 እስከ 11 አመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ህጻናት መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ወይም 160 ሚሊዮን ያህል ህጻናት ለእድሜያቸው በማይመጥን ስራ የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰባቸው እንደሚገኙ ከሰሞኑ የወጣ አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እና በተመድ የሰራተኞች ድርጅት ከሰሞኑ ባወጡት ሪፖርት እንዳሉት፣ እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2022 መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 9 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የጉልበት ብዝበዛ ሰለቦች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ህጻናት በስፋት ለጉልበት ብዝበዛ ከሚዳረጉባቸው የስራ ዘርፎች መካከል የግብርናው ዘርፍ ቀዳሚነቱን እንደሚይዝ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከአጠቃላዩ የጉልበት ብዝበዛ ሰለቦች 70 በመቶው ወይም 112 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናት በዘርፉ ተሰማርተው ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውንና 20 በመቶው በአገልግሎት፣ 10 በመቶው ደግሞ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደተሰማሩም ገልጧል፡፡
ህጻናት በብዛት ለከባድ የጉልበት ስራ ከተዳረጉባቸው የአለማችን አካባቢዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ እድሜያቸው ከ5 እስከ 17 አመት ከሚሆናቸው የአገራቱ ህጻናት መካከል ሩብ ያህሉ የድርጊቱ ሰለቦች መሆናቸውንም አክሎ አስረድቷል፡፡
የጉልበት ብዝበዛ ሰለቦች የሆኑ ህጻናት ቁጥር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ጭማሪ ያሳየው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 መሆኑን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ለዚህም በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚገኝበትና ተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ለአደጋው ተጋላጭ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


 የኒውዚላንዷ ከተማ ኦክላንድ በዘንድሮው የኢኮኖሚስት መጽሄት ለኑሮ ምቹ ምርጥ የአለማችን ከተሞች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ ከተማዋ ለዚህ ክብር ከበቃችባቸው ጉዳዮች መካከልም በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ትምህርት ቤቶች፣ ቲያትር ቤቶች፣ ሬስቶራንቶችና ሌሎች የባህል ማዕከላትና መስዕቦች እንዳይዘጉ ለማድረግ የተከተለችው ስኬታማ አካሄድ በጉልህ እንደሚጠቀስ ተነግሯል፡፡
በ2021 የአለማችን ለኑሮ ምቹ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ በሁለተኛነት የተቀመጠችው የጃፓኗ ከተማ ኦሳካ ስትሆን፣ የአውስትራሊያዋ አዴላዴ፣ የኒውዚላንዷ ዌሊንግተን፣ የጃፓኗ ቶክዮ፣ የአውስትራሊያዋ ፐርዝ፣ የስዊዘርላንድ ከተሞች ዙሪክና ጄኔቫ፣ እንዲሁም የአውስትራሊያዎቹ ከተሞች ሜልቦርንና ብሪስባኔ እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የኢኮኖሚስት መጽሄት የምርመራ ክፍል የአለማችንን ከተሞች ሰላምና መረጋጋት፣ የጤና አገልግሎት፣ ባህልና አካባቢ ጥበቃ፣ እንዲሁም ትምህርትና መሰረተ ልማት በተሰኙ ስድስት ዋና ዋና ምድቦች ከ30 በላይ በሚሆኑ የመለኪያ መስፈርቶች እየገመገመ በየአመቱ በሚያወጣው በዚህ ሪፖርት፣ ዘንድሮ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የከተሞች ደረጃ ሰፊ ልዩነት ማሳየቱ ተነግሯል፡፡ ከእነዚህም መካከል ላለፉት አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረችውና ዘንድሮ ወደ 12ኛ ደረጃ ዝቅ ያለችው የኦስትሪያዋ ከተማ ቪየና ትገኝበታለች፡፡

  የአፍሪካ አየር መንገዶች ከኮሮና ቫይረስ ቀውስ ጋር በተያያዘ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በድምሩ የ10.21 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠማቸው የአፍሪካ የአየር መንገዶች ማህበር ከሰሞኑ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ የአየር መንገዶች በ2020 የፈረንጆች አመት ያጓጓዟቸው መንገደኞች ቁጥር በ2019 ከነበረበት በ63.7 በመቶ ቅናሽ በማሳየት 34.7 ሚሊዮን መድረሱን የማህበሩ ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን በአመቱ ከአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል በአገር ውስጥ፣ በአህጉራዊና በአለማቀፍ በረራዎች በድምሩ በርካታ ቁጥር ያላቸውን መንገደኞች በማጓጓዝ ቀዳሚነቱን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን፣ ኢጅፕትኤር፣ ሮያል ኤር ሞሮኮ፣ ሳፋሪና ኬንያን ኤርዌይስ ይከተላሉ፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በበርካታ የአለማችን አገራት የጉዞ ክልከላዎችን በማድረጋቸውና የጉዞና እንቅስቃሴ ገደቦች በመጣላቸው ሳቢያ፣ የአለማችን ስድስቱ ግዙፍ አየር መንገዶች በአመቱ በድምሩ 110 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ እንዳጋጠማቸውም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 አሜሪካውያን ቢሊየነሮች ለአመታት ምንም ግብር አለመክፈላቸው ተጋለጠ

            የአለማችን አጠቃላይ የተጣራ ሃብት 431 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ወይም ወደ ግማሽ ኳድሪሊዮን ዶላር መጠጋቱን ፎርብስ መጽሄት ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ቦስተን ኮንሰልቲንግ ግሩፕ የተባለ ተቋም ያወጣውን አለማቀፍ የሃብት ሁኔታ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከአለማችን 431 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት ውስጥ ከሩብ በላይ የሚሆነው ወይም 126 ትሪሊዮን የሚገመተው ሃብት የተያዘው ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ባፈሩ ባለ ከፍተኛ ሃብት ሚሊየነሮች ነው፡፡
የአለማችን አጠቃላይ የተጣራ ሃብት በመጪዎቹ አራት አመታት ከ500 ትሪሊዮን ዶላር ወይም ከግማሽ ኳድሪሊዮን ያልፋል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በአለማችን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት ያፈሩ ባለ እጅግ ከፍተኛ ሃብት ሚሊየነሮች ቁጥር 60 ሺህ መድረሱንና እነዚህ ባለጸጎች በድምሩ 22 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት መያዛቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የቢዝነስ ዘገባ ደግሞ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ኤለን መስክና ዋረን ቡፌትን ጨምሮ በርካታ ስመጥር የአለማችን ቢሊየነሮች፣ ለረጅም አመታት ምንም አይነት የገቢ ግብር አለመክፈላቸውን የሚያረጋግጥ አንድ መረጃ ከሰሞኑ ይፋ መደረጉን ሲኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ፕሮፐብሊካ የተባለው ድረገጽ ከሰሞኑ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ እ.ኤ.አ በ2007 እና በ2011 አምስት ሳንቲም ግብር ለመንግስት ያልከፈሉ ሲሆን፣ የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ቢሊየነሩ ኤለን መስክ በበኩላቸው በ2018 ምንም አይነት ግብር አልከፈሉም፡፡
የአሜሪካ 25 ታላላቅ ባለሃብቶች እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2018 በነበሩት አመታት አጠቃላይ ሃብታቸው በ401 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ ቢያሳይም ባለሃብቶቹ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በገቢ ግብር መልክ የከፈሉት ግን 13.6 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር መረጃው አጋልጧል፡፡


የመራጮች ምዝገባ ትዝብት ግኝት መግለጫ


           በቅርቡ የሚከናወነው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በ2010 ዓ.ም የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ስር እንዲሰድ እንዲሁም በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ እርምጃ ነው። የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ፣ ከአባል ድርጅቶቹ የተውጣጡ ታዛቢዎች መልምሎ በማሰልጠንና የምርጫ ሂደቱ አካታች፣ ግልፅ እንዲሁም ተዓማኒነት ያለው መሆኑን እንዲታዘቡ በማድረግ ለመጪው ምርጫ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። የምርጫ ትዝብት ዓላማ በምርጫ ሂደት ለዜጎች፣ ለዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ለሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ለተለያዩ የመንግስት አካላት ከፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ የሆነን መረጃ የማሰባሰብና የማቅረብ ሲሆን ይህን መረጃ መሰረት በማድረግ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የምርጫውን አካታችነት፣ ግልጽነትና ተዓማኒነት እንዲገመግም ያስችላል።
ህብረቱ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም (በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም) ድረስ የመራጮች ምዝገባን ባከናወነባቸው ሥፍራዎች ታዛቢዎችን አሰማርቶ ሂደቱን ሲታዘብ ቆይቷል። የመራጮች ምዝገባን ለመታዘብ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 144 ታዛቢዎችን ከአባል ድርጅቶቹ በመመልመል የምዝገባ ሂደቱ ላይ የጐላ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ አሳሳቢ ኩነቶችን ጨምሮ ህብረቱ ባዘጋጃቸው የመራጮች ምዝገባ ሂደትን የሚገመግሙ ልዩ ልዩ መጠይቆች ላይ በመመርኮዝ፣ ከመራጮች ምዝገባ ሂደት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እንዴት እንደሚሰበስቡ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ሆኖም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተወሰኑ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ በተያዘለት ጊዜ አለመጀመሩ ወይም በጭራሽ አለመከናወኑ፤ እንዲሁም ቦርዱ ለታዛቢዎች የሚሰጠው የእውቅና ፈቃድ (ባጅ) በመዘግየቱ ሳቢያ ህብረቱ ካሰለጠናቸው ታዛቢዎቹ መካከል ማሰማራት የቻለው 117ቱን ብቻ ነው። የህብረቱ ታዛቢዎች መታዘብ በቻሉባቸው ሥፍራዎች ሁሉ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎችን በተመረጡ ቀናት ውስጥ ከመራጮች ምዝገባ መክፈቻ ሰዓት አንስቶ እስከ መዝጊያ ሰዓት ድረስ ታዝበዋል። በዚህ መግለጫ ላይ የቀረቡት መረጃዎች የህብረቱ ታዛቢዎች ከሚያዝያ 2 ቀን እስከ  ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው በጎበኟቸው 1,190 የምርጫ ምዝገባ ጣቢያዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
የህብረቱ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ትዝብት ግኝቶች
ህብረቱ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከባድ የቤት ሥራ እንደነበር እንደሚገነዘብ አስቀድሞ ሊገልፅ ይወዳል። የመራጮች ምዝገባ ምንም እንኳን ዘግይቶ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ቢጀመርም፣ በፀጥታ ችግሮች እንዲሁም ከምርጫ አስፈፃሚዎች በቀረቡ የተለያዩ ቅሬታዎች ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች በጭራሽ አልተካሄደም ነበር። ነገር ግን የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች ከተከፈቱና ምዝገባው ከተጀመረ በኋላ የህብረቱ ታዛቢዎች በታዘቧቸው 1,192 ጣቢያዎች የተሰበሰበው መረጃ ምዝገባው ቦርዱ ያወጣቸውን ህግጋት ከሞላ ጐደል የተከተለ እንደነበር ያሳያል።

የምርጫ ጣቢያዎች አወቃቀርና ተደራሽነት
የምርጫ ምዝገባ ጣቢያዎች ሊከፈቱ የሚገባው መራጮች በቀላሉ ተጉዘው ሊያገኟቸው በሚችሏቸው ሥፍራዎች እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የዜጎችን የመምረጥ መብት ከማረጋገጥ አንፃር ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ህብረቱ በታዛቢዎቹ አማካኝነት የሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው 96 በመቶ የሚሆኑት የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች (ማለትም ከ1,192 ጣቢያዎች ውስጥ 1,147) መራጮች በቀላሉ ተጉዘው ሊያገኟቸው በሚችሉበት ርቀት ላይ የተከፈቱ ነበሩ። ህብረቱ ከታዘባቸው 1,192 የምዝገባ ጣቢያዎች መካከል በአማካይ 9 በመቶ ያህሉ ለመጓዝ ለሴቶች ይበልጥ አስቸጋሪ ሲሆን ይህ ቁጥር በገጠር በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች 12 በመቶ እንዲሁም በከተማ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች 6 በመቶ ያህል ነው። በተጨማሪም ታዛቢዎች ከጎበኟቸው ጣቢያዎች 12 በመቶ ያህሉ ለአካል ጉዳተኞች ወይም ለመንቀሳቀስ እርዳታ ለሚያሻቸው ዜጎች (አዛውንቶች፣ ጨቅላ ህፃናትን የያዙ እናቶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ወዘተ..) ያለረዳት ገብተው መስተናገድ የማይችሉባቸው ነበሩ።
በአብዛኛው የመራጮች ምዝገባ የምርጫ ህጉ በሚፈቅዳቸው ቦታዎች የተከናወነ ሲሆን፤ የህብረቱ ታዛቢዎች በ45 ቦታዎች የምርጫ ቦርድ በህግ በከለከላቸው ቦታዎች ማለትም በፖሊስ ጣቢያ፣ በግል መኖርያ ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ፅ/ቤት በሚገኝበት ህንፃ፣ በጦር ካምፕ ውስጥ ምዝገባ እንደተካሄደ ሪፖርት አድርገዋል። ምንም እንኳን የምርጫ ቦርዱ ምዝገባ የሚካሄድባቸው ሥፍራዎች ዜጎች ከዝናብና ፀሀይ የሚከላከል ጥላ ባለበት ሥፍራ መሆን እንዳለበት ቢደነግግም፣ ህብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች 57 በመቶ ያህሉ የምዝገባ ጣቢያዎች ምንም አይነት ከዝናብ ወይም ከፀሀይ ዜጎችን የሚከላከል ጥላ አልነበራቸውም።
በምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ አፈፃጸም መመሪያ ቁጥር 06/2013 መሠረት፤ አንድ የምርጫ ጣቢያ ቢያንስ ሶስት የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊኖሩት እንደሚገባ ተደንግጓል። ይህን በተከተለ መልኩ ህብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች በ71 በመቶ ያህሉ ቢያንስ ሶስት አስፈፃሚዎች መኖራቸው አበረታች ምልከታ ነው። በተጨማሪ ታዛቢዎች በጎበኟቸው አብዛኞቹ ጣቢያዎች የምርጫ ምዝገባ ቁሳቁሶች በአብዛኛው ተሟልተው ነበር። ነገር ግን በ40 የምርጫ ጣቢያዎች በጣት ላይ የሚቀባ ቀለም እንዳልነበረ ታዛቢዎች ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን ይህ በድምጽ መስጫ ዕለት ሊፈጠር የሚችልን በተደጋጋሚ የመምረጥ ስጋት ለማስቀረት ከሚኖረው ሚና አንፃር ሊታሰብበት እንደሚገባ ህብረቱ ያምናል። በተጨማሪም የህብረቱ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው ጣቢያዎች ውስጥ በ16ቱ ምዝገባ ጣቢያዎች መዝገብ (Polling Station Journal) እንዳልነበረ ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን በ12 ጣቢያዎች ደግሞ የምስክርነት ቅፅ (Testimony Form) እንዳልነበር ሪፖርት ተደርጓል።
አካታችነት  
የአንድን የምርጫ ሂደት ፍትሀዊነትና ተዓማኒነት ለመመዘን በምርጫ ሂደቱ ውስጥ የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው መለኪያ ነው። የህብረቱ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው 1,192 የምዝገባ ጣቢያዎች በ928ቱ ማለትም 77 በመቶ ከነበሩት የምርጫ አስፈፃሚዎች ቢያንስ አንዷ ሴት የነበረች ሲሆን፣ አብዛኞቹ የምርጫ አስፈፃሚዎችም በወጣትነት የእድሜ ክልል የሚገኙ ነበሩ። ምንም እንኳን ይህ የሚበረታታ ቢሆንም፣ 23 በመቶ ያህሉ የምዝገባ ጣቢያዎች ሁሉም የጣቢያው ሠራተኞች ወንዶች ነበሩ። የአካል ጉዳተኞች በምርጫ አስፈጻሚነት የተሳተፉበት በ5 በመቶ ጣቢያዎች ብቻ ነበር። ይህም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነጥብ እንደሆነ ህብረቱ ያምናል።
ደህንነት
ህብረቱ ካሰማራቸው ታዛቢዎች መካከል የመራጮች ምዝገባ በተደረገባቸው የመራጮች  ምዝገባ ጣቢያዎች ወይም አቅራቢያ የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ሪፖርት ያደረጉት በጣም ጥቂቶች (3 በመቶ ያህሉ) ቢሆኑም፣ በአገሪቱ ውስጥ የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ በከፊል ወይም በጭራሽ አለመካሄዱ ለቁጥሩ ዝቅተኛ መሆን አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኙት የመተከል እና ካማሺ ዞኖች እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አንዳንድ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ለዚህ እንደማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በተጨማሪም የምርጫ ቦርድ ባወጣው መመሪያ መሠረት የመራጮች ምዝገባ በሚከናወንበት እያንዳንዱ ሥፍራ ቢያንስ አንድ የፀጥታ አካል ሊገኝ እንደሚገባው ቢደነግግም፣ የህብረቱ ታዛቢዎች ከታዘቧቸው የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች መካከል 61 በመቶ ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ አካላት እንዳልተገኙ የተሰበሰበው መረጃ ያሳያል። በሌላ በኩል የፀጥታ ሀይሎች በተገኙባቸው ቦታዎች በአብዛኛው ሳይጋበዙ ወደ ምርጫ ጣቢያው አለመግባታቸው አበረታች ነው። ነገር ግን በ31 አጋጣሚዎች  የፀጥታ ሀይሎች ያለምርጫ አስፈፃሚዎች ፈቃድ ወደ ጣቢያዎች መግባታቸውን ታዛቢዎች  ሪፖርት አድርገዋል።
የመራጮች ምዝገባ ህግጋትንና ሥነ ሥርዓቶችን ማክበር
ምዝገባ በተካሄደባቸውና የህብረቱ ታዛቢዎች በተመለከቷቸው የምርጫ ጣቢያዎች በአብዛኛው የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ ቦርድን የመራጮች ምዝገባ የአሰራር ህጎች የተከተሉ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ታዛቢዎች ከተመለከቷቸው የምዝገባ ጣቢያዎች ቢያንስ በ96 በመቶ ያህሉ በታዛቢዎች፣ ፓርቲ ተወካዮች ወይም ጋዜጠኞች ላይ ምንም አይነት ገደብ ያልተጣለ ሲሆን ይህም አበረታች ምልክት ነው። በመራጭነት ከተመዘገቡ ዜጐች መካከል የ99 በመቶ ያህሉ ተመዝጋቢዎች መረጃ በመራጮች መዝገብ ላይ በአግባቡ የሰፈረ ሲሆን የመራጭነት ካርድ መቀበላቸውንም ታዛቢዎች አረጋግጠዋል። ይህም ምልከታ መልካም እንደሆነ ህብረቱ ቢያምንም፣ አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። ለምሳሌ ያህል ታዛቢዎቻችን በተመለከቷቸው ጣቢያዎች ቢያንስ 3 በመቶ ያህሉ ማንነታቸውንና አድራሻቸውን አረጋግጠው እንዲመዘገቡ ያልተፈቀደላቸው ሲሆን ህብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች 8 በመቶ ያህል በሚሆኑት ከመዝጊያ ሰዓት በፊት በሰልፍ ላይ የነበሩ ዜጎች ሳይመዘገቡ ጣቢያዎቹ መዘጋታቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ አግኝቶታል። በተጨማሪም ምንም እንኳን የህብረቱ ታዛቢዎች ከ90 በመቶ በላይ በሚሆኑት ጣቢያዎች ከጠዋት እስከ ማታ እንዲታዘቡ ቢፈቀድላቸውም፣ በ6 በመቶ ያህሉ ግን በህግ በተፈቀደው መሰረት የመራጮች መዝገብ ላይ የሰፈሩ መረጃዎችን ማየት አልተፈቀደላቸውም።
የመራጮች ምዝገባና የኮቪድ-19 ወረርሺኝ
6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሄደው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ እየተስፋፋ በሚገኝበት ወቅት ላይ እንደመሆኑ ህብረቱ በመራጮች ምዝገባ ወቅት አተኩሮ ከታዘባቸው ጉዳዮች መካከል ቫይረሱን ለመከላከል የተደረጉ ጥረቶችና አፈፃፀማቸው አንዱ ነው። የሚከተሉት በመራጮች ምዝገባ ወቅት ህብረቱ ኮቪድ-19ን በተመለከተ ከሰበሰባቸው ግኝቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች (face masks) እና የእጅ ማጽጃዎች (sanitizers) አቅርቦት በአብዛኞቹ የምዝገባ ጣቢያዎች መሟላቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ 52 በመቶ ያህል በሚሆኑ የመራጮች የምዝገባ ጣቢያዎች የእጅ መታጠቢያ ቦታዎች አልነበሯቸውም፤
- 60 በመቶ የሚሆኑ ህብረቱ የታዘባቸው የምዝገባ አስፈፃሚዎች የእጅ ጓንቶች (Gloves) አልነበሯቸውም፤
- ህብረቱ ከጎበኛቸው ጣቢያዎች መካከል 13 በመቶ በሚሆኑት ጣቢያዎች የምርጫ አስፈፃሚዎች የፊት ጭምብሎችን ያላደረጉ ሲሆን፤ 28 በመቶ የሚሆኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች በአንፃሩ በምዝገባ ወቅት የፊት ጭምብሎችን ያደረጉ ነበሩ፡፡
- ህብረቱ ከጎበኛቸው ጣቢያዎች 23 በመቶ በሚሆኑት የምዝገባ ቦታዎች ዜጎች የፊት ጭምብሎችን ያላደረጉ ሲሆኑ 48 በመቶ በሚሆኑት ጣቢያዎች መራጮች የፊት ጭምብሎችን ያደረጉት በከፊል ብቻ መሆኑ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
- ከላይ እንደሚታየው በምዝገባው ወቅት ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ የተለያዩ የጥንቃቄ ክፍተቶች ያሉ ሲሆን 89 በመቶ ያህል በሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች የኮቪድ-19 ባለሙያዎች አለመገኘታቸው ለሚታዩት ክፍተቶች ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበረው ታይቷል።
ምክረ ሀሳቦች
ከላይ በተጠቀሱት ቅድመ-ግኝቶች ላይ በመመስረት፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ፤ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድሞ ከላይ የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለማስተካከል ይረዳ ዘንድ የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች አስቀምጧል፡-
- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን የሚያካሂደው በዝናባማው የአገሪቱ ወቅት እንደመሆኑ፤ በምርጫ ቀን በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ድምፃቸውን ለመስጠት ለሚመጡ ዜጎች ከፀሀይና ከዝናብ የሚከላከል ጥላ መዘጋጀቱን ሊያረጋግጥ ይገባል።
- ቦርዱ በምርጫ ቀን ለሂደቱ የሚያስፈልጉ እንደ ጣት ቀለም የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በሁሉም ጣቢያዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ አለበት።
- ከምርጫ ጣቢያዎች የመዝጊያ ሰዓት ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በምርጫ ቀን ከመዝጊያ ሰዓት በፊት በጣቢያው ተገኝተው ለተሰለፉ ዜጎች የመምረጥ ዕድል አለመነፈጉን ሊያረጋግጥ ይገባል። ቦርዱ አስፈፃሚዎችን በሚያሰለጥንበት ወቅት አስፈፃሚዎች በዚህ ረገድ በቂ ግንዛቤ መያዛቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚመለከታቸው የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አሰተዳደሮች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመወያየትና በመተባበር በምርጫ ቀን በሁሉም ጣቢያዎች በህግ በተደነገገው መሰረት የፀጥታ አስከባሪ አካላት እንደሚገኙ ሊያረጋግጥ ይገባል። በተጨማሪም የፀጥታ ሀይሎች በምርጫ ጣቢያዎች በሚገኙበት ወቅት ከቦርዱ የሚሰጣቸውን መመርያዎች በማክበር ሊሰሩ እንደሚገባ ህብረቱ ሊያስታውስ ይወዳል።
- የዜጎችን ጤና ከማስጠበቅ አንፃር ቦርዱ በድምፅ መስጫ ዕለት በሁሉም ጣቢያዎች የኮቪድ ባለሙያዎች እንዲገኙ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል። በተጨማሪም ህብረቱ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በመራጮች ትምህርት ላይ የተሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ በቫይረሱ ዙርያ ለዜጎች በቂ ግንዛቤ ሊሰጡ ይገባል ብሎ ያምናል።
መደምደምያ
ህብረቱ፤ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ውጫዊ ተግዳሮቶች መሀል የመራጮች ምዝገባን በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች ማካሄድ መቻሉን ያደንቃል። ከ45,000 በላይ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከመክፈት አንስቶ ወደ 135,000 የሚጠጉ አስፈፃሚዎችን አሰልጥኖ እስከማሰማራት ድረስ ቦርዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰራው ስራ በመልካም ጐኑ የሚጠቀስ ነው። ምንም እንኳን የመራጮች ምዝገባን የማደራጀትና የማካሄድ ተግባርን ውስብስብነት ህብረቱ ቢረዳም፣ በምዝገባ ሂደቱ ወቅት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን የመምረጥ መብት ሊያጣብቡ የሚችሉ ችግሮች መከሰታቸውን መካድ ግን አይቻልም። ከእነዚህ ችግሮች መካከል በአንዳንድ ስፍራዎች የነበረው የምዝገባ ጅማሮ መዘግየት ወይም በጭራሽ አለመካሄድ አንዱ ሲሆን የምዝገባ ቀናት በተራዘመባቸውም ሆነ ምዝገባ ዘግይቶ በተጀመረባቸው ስፍራዎች ስለ ምዝገባው በቂ መረጃ አለመሰጠቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ህብረቱ ከላይ የጠቀሳቸው ግኝቶች እንዲሁም ያስቀመጣቸው የመፍትሄ ሀሳቦች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትኩረት እንደሚታዩ ተስፋ እያደረገ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን በተቆረጠለት ምርጫ ላይ ሁሉም የተመዘገቡ ዜጎች መምረጥ እንዲችሉ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያሳስባል።
(የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ (CECOE)፤ ከ175 በላይ በምርጫ ዙርያ የተለያዩ ስራዎችን የሚሰሩ አገር በቀል የሲቪል ማህበራት ስብስብ ነው።)

Page 7 of 536