Administrator

Administrator

እየጮሁ ማውራትና መጨቃጨቅ ተከልክሏል
በሞባይል ወደ ውጭ አገራት መደወል አይፈቀድም
የሞባይል ባለቤት መሆን የሚችሉት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ብቻ ናቸው

የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በሚገኝባት ደቡብ ኮሪያ፣ በተጠቃሚዎች ላይ የሚታየውን የስነ-ምግባር ጉድለት ለመቅረፍ ሲባል አዲስ የአጠቃቀም መመሪያ መውጣቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ዮንሃፕ የተባለውን የደቡብ ኮሪያ የዜና ተቋም ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአገሪቱ የሞባይል ተጠቃሚዎች ላይ ከሚታዩ የስነ-ምግባር ጉድለቶች መካከል፣ ሰው በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ጮክ ብሎ ማውራትና መጨቃጨቅ ይገኙባቸዋል፡፡አዲሱ የአገሪቱ የሞባይል አጠቃቀም የስነ-ምግባር መመሪያ እንደሚለው፣ ተጠቃሚዎች ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው በትህትና መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡በሞባይል ስልክ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጭቅጭቆችን ለማስወገድ ሲባልም፣ የተደወለላቸው ሰዎች ጥሪያቸውን ሲመልሱ፣ ለደዋያቸው ማንነታቸውን ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
 የደዋያቸውን ማንነት እንዳወቁ መግለጽም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ደዋዩ ራሱን ለማስተዋወቅ ጊዜ እንዳይፈጅ ያግዘዋል ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ በሆነችው ደቡብ ኮሪያ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ2 ቢሊዮን በላይ እንደደረሰ የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ አለማቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ ክልክል ነው፡፡
የሞባይል ስልክ ባለቤት መሆን የሚችሉትም፣ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡

አብዛኞቹ የአገሪቱ ባለስልጣናት ፖሊሲ ሲያወጡ ጠንቋይ ያማክራሉ
የታይላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራዩዝ ቻኖቻ፣ ወደ ጠንቋዮች ጎራ ብሎ የመጪውን ጊዜ ዕጣ ፋንታ በተመለከተ የሚሰጡትን ትንቢትና ምክር መስማት ክፋት የለውም፤ ጥንቆላም ራሱን የቻለ ጥበብ ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
“ጠንቋዮች የሚነግሩኝን ትንቢት ልብ ብዬ እሰማለሁ፡፡ ምክራቸውንም እቀበላለሁ፡፡ እንዲያውም በቅርቡ በአገሪቱ ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጋር ግጭት ውስጥ ልገባ እንደምችል አስጠንቅቀውኛል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መገናኛ ብዙሃን መሪያችን ጠንቋይ ቤት ይሄዳሉ ሲሉ ያሰራጩት ዘገባም ትክክለኛ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ቻኖቻ በመገናኛ ብዙሃን ስለጠንቋይ አማኝነቴ የሰማችሁት ትክክል ነው ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠላቶቻቸው ካሰሩባቸው ድግምትና አስማት ለመንጻት ሲሉ፣ ከእግር እስከ ራሳቸው ጠበል መጠመቃቸውን በወሩ መጀመሪያ ላይ በይፋ መናገራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአገሪቱን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታክሲን ሺንዋትራን ጨምሮ በርካታ ደንበኞችን ወዳፈራው ኢት የተባለ የማይናማር ታዋቂ ጠንቋይ በመሄድ ምክር ይሰማሉ መባሉን ያስተባበሉት ቻኖቻ፣ ይሄም ሆኖ ግን ወደ ጠንቋዩ የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው አልደበቁም፡፡
ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች አብዛኞቹ፣ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ሲያስቡ ወደ ጠንቋዮች ሄደው፣ “ይበጃል፣ አይበጅም?” ብለው የማማከር ልማድ እንዳላቸው የጠቆመው ሮይተርስ፣  ታይላንድ ወደዘመናዊነት እየተሸጋገረች ያለች አገር ብትሆንም፣ ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ጥንቆላና መሰል የባዕድ አምልኮ አሁንም ድረስ በስፋት እንደሚከናወንባት አመልክቷል፡፡

ውድ እግዚአብሔር፡-
ወንድሜ ቶሎ ቶሎ ሽንቱን ይሸናል፡፡ እኔ ግን አይመጣብኝም፡፡ ለእኔ ብዙ ያልሰጠኸኝ አልቆብህ ነው?
ናቲ- የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ኤሊዬ ሞታብኛለች፡፡ ጓሮአችንም ቀብረናታል፡፡ አሁን ካንተ ጋር ናት እንዴ ?
ከሆነች ሰላጣ በጣም ትወዳለች እሺ፡፡
ዴቭ- የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ትልቅ ስሆን ቅርጫት ኳስ መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ በደንብ መጫወት እንድችል ቆዳዬን ጥቁር አድርግልኝ፡፡ ቁመቴንም በጣም አርዝምልኝ፡፡
አሌክስ- የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ወዳንተ ስፀልይ ደስ ይልሃል አይደል? እኔም ደስ ይለኛል፡፡
ጄሪ- የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
የሰንበት ት/ቤት አስተማሪዬ አንተ ሁልጊዜ እንደምትወደኝ ነግራኛለች፡፡ እውነቷን ነው? ትላንት ሳራ ላይ ያንን ነገር ካደረኩም በኋላ ትወደኛለህ? አውቀኸዋል አይደል?! በጣም አዝናለሁ፤ አሁንም ብትወደኝ ግን ደስ ይለኛል፡፡
ቤቲ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አያቴ ልትሞትብኝ ነው፡፡ አንተ እንደምትፈልጋት ነግራኛለች፤ እኔ ግን እዚህ አብራኝ እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ሌላ የፈለግኸውን ሰው መውሰድ ትችላለህ፡፡
ለእኔ ያለችኝ እሷ ብቻ ናት፡፡ እባክህን ከህመሟ ድና አብራኝ እንድትሆን አድርጋት፡፡
ጆኒ- የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ለምንድነው እባብና ሸረሪቶችን የፈጠርከው? በጣም እኮ ነው የምፈራቸው፡፡
ጄሪ- የ6 ዓመት ህፃን

         በአዲስ አበባ በየዓመቱ የሚካሄደው የአውሮፓ ፊልም ፌስቲቫል ትላንት ዕለት ምሽት በ12 ሰዓት በጣልያን የባህል ማዕከል The Great Beautiful በተሰኘው የጣልያን ፊልም ተከፈተ፡፡
ለ15 ቀናት በሚዘልቀው የፊልም ፌስቲቫል ላይ የ15 አውሮፓ አገራት ፊልሞች ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን የጣልያን ባህል ማዕከልን ጨምሮ በገተ ኢንስቲቲዩትና በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ፊልሞቹ እንደሚታዩ ታውቋል፡፡
ሁሉም ፊልሞች በነፃ ለተመልካች የሚቀርቡ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወይም በእንግሊዝኛ ትርጉም (subtitles) እንደተዘጋጁም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም The Selfish Giant በተሰኘው የእንግሊዝ ፊልም እንደሚጠናቀቅም ታውቋል፡፡

Monday, 06 October 2014 08:41

“መረቅ” ነገ ይመረቃል

በደራሲ አዳም ረታ የተጻፈው “መረቅ” የረጅም ልቦለድ መጽሃፍ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የደራሲው አድናቂዎችና የጥበብ ቤተሰቦች በተገኙበት ነገ ጧት በሃገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡
ለረጅም አመታት በውጭ አገራት የኖረው ደራሲ አዳም በሚገኝበት በሚከናወነው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ፣ የተለያዩ ስነ-ጽሁፋዊ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ስለደራሲው ስራዎችም ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
ለደራሲው ስምንተኛ ስራው የሆነውና 600 ገጾች ያሉት “መረቅ”፣ በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም  120 ብር ነው፡፡

Monday, 06 October 2014 08:33

የፍቅር ጥግ

አንድ ወጣትና አንዲት ኮረዳ በሞተር ሳይክል ይጋልባሉ፡፡ ሞተሩ 100 ሜትር በሰዓት ይከንፋል፡፡
ኮረዳዋ፡- ቀስ በል በናትህ፤ በጣም ያስፈራል!
ወጣቱ፡- አይዞሽ፤ ደስ ይላል እኮ!
ኮረዳዋ፡- ምንም ደስ አይልም፤ በናትህ በጣም ነው የሚያስፈራው!
ወጣቱ፡- እንግዲያውስ እወድሃለሁ በይኝ፡፡
ኮረዳዋ፡- እሺ እወድሃለሁ፤ ግን ቀስ በል!
ወጣቱ፡- በይ ሄልሜቴን ውሰጂና ጭንቅላትሽ ላይ አጥልቂው፤ እኔን አስጨንቆኛል፡፡
በነጋታው በወጣ ጋዜጣ ላይ፡- አንድ ሞተር ሳይክል ፍሬን በጥሶ ከአንድ ህንፃ ጋር በመጋጨቱ ሞተሩ ላይ ከነበሩት ሁለት ሰዎች አንደኛው ህይወቱ ወዲያው አልፏል፡፡ የሆነው እንዲህ ነው፡- ጥንዶቹ ግማሽ መንገድ እንደከነፉ፣ ፍሬኑ እምቢ ማለቱን ወጣቱ ተገንዝቧል፡፡ ነገር ግን ፍቅረኛው ይሄን እንድታውቅ አልፈለገም፡፡
ይልቁንም ለመጨረሻ ጊዜ እወድሃለሁ የሚለውን ጣፋጭ ዜማዋን ማዳመጥ ስለፈለገ እንድትልለት ጠየቃት፡፡ ከዚያም ሄልሜቱን (ከአደጋ መከላከያውን) ከራሱ ላይ ወስዳ እንድታጠልቀው አደረጋት፡፡
ወጣቱ ሄልሜቱን ባለማድረጉ ለሞት እንደሚዳረግ ያውቅ ነበር፡፡ እሱን ያሳሰበው ግን የፍቅረኛው ህይወት ነው፡፡ ስለዚህም እሱ ሞቶ፤ እሷን አተረፋት፡፡  

Monday, 06 October 2014 08:32

የፀሐፍት ጥግ

ስለፖለቲካ

ፖለቲካ በጣም ብርቱ ጉዳይ ስለሆነ ለፖለቲከኞች የሚተው አይደለም ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ፡፡
ቻርልስ ደጎል
በእኛ ዘመን ከፖለቲካ መራቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ጉዳዮች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ጆርጅ አርዌል
ፖለቲካ ፍልስፍናን በተካበት ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡
ጆሲ ማርያዲ ኢካዲ ኪውይሮዝ
ፖለቲከኛ፤ ጌታ ለመሆን አገልጋይ መስሎ ይቀርባል፡፡
ቻርልስ ደጎል
እውነት በአብላጫ ድምፅ አይወሰንም፡፡
ዶግ ግዊን
ለችግሮቻቸው የቀድሞውን አስተዳደር ያልወቀሱ ብቸኛ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሺንግተን ናቸው፡፡
ያልታወቀ ፀሐፊ
ወግ አጥባቂ ማለት ምንም ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ መሰራት የለበትም ብሎ የሚያምን ሰው ነው፡፡
አልፍሬድ ኢ.ዊጋም
የከተማዋን መክፈቻ ቁልፎች ለፖለቲከኛ ከመስጠት ይልቅ መቆለፊያዎቹን መቀየር ሳይሻል አይቀርም፡፡
ዶውግ ላርሰን
እጅግ በጣም ጥቂት ሴት ፖለቲከኞች ያሉበት ምክንያት ሁለት ፊት ላይ ሜክአፕ መቀባት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
ማዩሪን መርፊ
የቤተሰብ ሐረግህን ለማስጠናት ለምን ገንዘብ ትከፍላለህ፤ ፖለቲካ ውስጥ ግባና ተቀናቃኞችህ ያጠኑልሃል፡፡
ያልታወቀ ፀሃፊ
አንድ አሜሪካዊ ለዲሞክራሲ ለመዋጋት ውቅያኖስ ይሻገራል፤ ለብሄራዊ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ግን ጎዳና አይሻገርም፡፡
ቢል ቫውግሃን
ድምፅ መስጠት (ምርጫው) አይደለም ዲሞክራሲ የሚባለው፤ የድምፅ ቆጠራው ነው፡፡
ቶም ስቶፓርድ

            መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በማዕከሉ ባዘጋጀው የመስቀል በአል አከባበር ስነስርአት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገች፡፡ በእለቱ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ከማዕከሉ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ በመስቀል አከባበር ስነስርአት ላይ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የመንግስት አካላት የተገኙ ሲሆን ዝግጅቱን በንግግር የጀመሩት የመቄዶንያ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ብርሀኔ ጸጋዬ እና የድርጅቱ መስራችን ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም በለጠ ማዕከሉ በአራት ማዕከላት 650 በላይ ለሚሆኑ ተረጂ ወገኖች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልፀው ከመንግስት የጠየቀውን 30.000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደተሰጠው፣ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ የተረጂውን ቁጥር ወደ 10,000 /አስር ሺህ/ ለማሳደግ ዝግጅት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ማዕከሉም የጎበኙትና 100.000 ብር የለገሱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ፓትሪያርክ ብፁህ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብጹሃን ጳጳስ፣ ይህንን እርዳታ እንዲያደርጉ የረዳቸውን እግዚአብሔርን አመስግነው ማዕከሉ እያከናወነ ያለው ተግባር እግዚአብሔር የሚወደው መሆኑን የገለፁ ሲሆን እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ወደፊት በማስተባበርም ሆነ በገንዘብ እግዚአብሔር በሰጠን፣ አቅማችን በፈቀደ እንቀጥልበታለን ብለዋል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ልዩ ረዳት አቶ አሰፋ መብራቴ፤ ይህ ተቋም ከሌሎች የተለየ እውቅናና ክብር እንድንሰጠው ያደረጉ ተግባሮችን እየሰራ ያለ ማዕከል ነው፡፡ ከማዕከሉ ጋር አብረን ለመስራት ፈቃደኛ መሆናችንን ማረጋገጥ እንወዳለን ያሉ ሲሆን፤ የወረዳ 9 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ በፈቃዱ በበኩላቸው፤ የሀገር ባለውለታ ለሆኑት አረጋውያን እየተደረገ ያለውን ድጋፍና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እናደንቀዋለን፤ ከዚህም ባሻገር እንደ አስተዳደር ልንተጋገዝ የሚገባ ጉዳይ ሲገኝ ተጋግዘን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ
ምዝገባው የሚካሄደው የስራ አጡን ቁጥር ለማወቅ ነው ተብሏል

        በአዲስ አበባ  ቤት ለቤት የሚካሄደው የስራ አጦች ምዝገባ አላማ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለማወቅ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከ350 ሺ በላይ ተመዝጋቢዎች ይጠበቃሉ ተብሏል፡፡ ወደ 9 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ተይዞለት ከመስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፤ በዋናነት በከተማዋ ምን ያህል ስራ አጥ አለ የሚለውን ለማወቅና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ፣ የስራ እድሎችን ለማመቻቸት የታቀደ ፕሮጀክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የሙያ ደህንነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ ስዩም ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ እንዲህ መሰሉ ምዝገባ ከዚህ ቀደምም በየጊዜው በከተማዋ እንደሚካሄድ አስታውሰው፣ የአለማቀፍ ሰራተኞች ድርጅት (ILO) ለአገራት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥነት ሁኔታ በተጠናከረ መረጃ የማደራጀት፣ የመተንተንና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተንተርሶ መፍትሄ የመስጠት አካል ነው ብለዋል፡፡ የስራ አጥነትን ሁኔታ አጥንቶ የስራ እድሎችን ማመቻቸት የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮው አንዱ ኃላፊነት እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ምዝገባው ከወር በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደታቀደ ጠቁመዋል፡፡ ቤት ለቤት እየተካሄደ ያለው የስራ አጥነት ምዝገባ፣ ተመዝጋቢዎች በምን አይነት የስራ መስክ ላይ ቢሰማሩ ይመርጣሉ የሚለውን ያካተተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳ፤ ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ የተሰበሰበው መረጃ ተተንትኖ፣ ተመዝጋቢዎች በሚፈልጉት የስራ መስክ ስልጠና ወስደው የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
ቢሮው ስራና ሰራተኛን በነፃ የማገናኘት ኃላፊነቱን ለመወጣትም ራሱ ስራ አጦችንና ስራን ከማገናኘት ባለፈ ፍቃድ የተሰጣቸው ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች ስራ አጦችን ስራ በማስያዝ ተግባር እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ምዝገባው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ለየት የሚያደርገው ጥናትን መሰረት አድርጎ የተለያዩ ማመላከቻዎችን መጠቀሙ እንደሆነ የገለፁት አቶ ካሣ፤ በከተማዋ ያሉ ስራ አጦች በየትኛው የስራ መስክ ነው የበለጠ መሰማራት የሚፈልጉት የሚለውን ለይቶ ለማወቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ መረጃውን በመጠቀምም የተለያዩ የመንግስት እና የግል የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና መስካቸውን እንዲፈትሹ አጋዥ ይሆናል ሲሉ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡
በምዝገባው ወቅት እድሜና የትምህርት ደረጃ የመሳሰሉትን ጨምሮ በትክክልም በአዲስ አበባ ነዋሪ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይሰበሰባሉ ተብሏል፡፡ በአለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት መስፈርት መሰረት እድሜያቸው ከ14-18 ዓመት ያሉት በወጣት ስራ ፈላጊነት ይመዘገባሉ ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ የእድሜ ክልል ላሉ በአቅማቸው ሊሰሩት የሚችሉት ስራ ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም እድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ በዚህ የምዝገባ ሂደት አይካተቱም ብለዋል - ኃላፊው፡፡ በየዓመቱ በርካታ የከተማዋ ስራ አጦች የስራ እድል እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ካሣ፤ በ2006 ዓ.ም ከ230 ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ በዚህ የስራ አጦች ምዝገባ ፕሮጀክትም ከ350 ሺህ ያላነሱ ሰዎች ይመዘገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ምዝገባው የቤት ሰራተኞችን ጨምሮ ማንኛውም ተቀጥሮ የሚሰራና ገቢ የሚያገኝ ግለሰብን አይመለከትም ተብሏል፡፡
ስራ አጦችን ለመመዝገብ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ እንደተገባ የተናገሩት ኃላፊው፤ 734 ሰራተኞች በኮንትራት ተቀጥረው በከፍተኛ አማካሪነት፣ በሱፐርቫይዘርነት፣ በአስተባባሪነት እና በመረጃ አሰባሰቢነት እየተሳተፉ ነው ብለዋል፡፡ መረጃ ሰብሳቢዎችም በዲግሪ የተመረቁ እንደሆኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም የክልል ከተሞች በ2007 ዓ.ም በሃገሪቱ ምን ያህል ስራ አጦች አሉ የሚለውን በዘመናዊ መንገድ ለይቶ ለማወቅ ተመሳሳይ ምዝገባ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ቀደም በሃገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ስራ አጦች እንዳሉ አመላካች የሆነ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መረጃ እንዳልነበረ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡  

በገጣሚ እርቅይሁን በላይነህ የተፃፈው “እርቃንሽን ቅሪ” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ በመፅሃፉ ጀርባ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት፤ በመድበሉ የተካተቱት ግጥሞች ጠንካራ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት መምህር የሆኑት ጋዜጠኛ አስተዋይ መለስ በበኩላቸው፤ “ታሪክን የሚያወሱ ጥሩ ግጥሞች ናቸው” ሲሉ አድንቀዋል፡፡ በ132 ገፆች 77 ግጥሞችን ያካተተው መፅሀፉ፤ በ25 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
ገጣሚው ከዚህ ቀደም “ያልተጠቡ ጡቶችን” የተሰኘ የአጫጭር ልብወለድ መድበልና  “የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢማም አህመድ እስከ አጼ ቴዎድሮስ” የሚል የታሪክ መፅሃፍ ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል፡፡