Administrator

Administrator

ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-
ጠብመንጃን መጠቀም ማቆም እንችላለን? እባክህ ማንም ሰው ጠብመንጃ የምትችለውን ሁሉ እያደረግህ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በጣን ነው የማመሰግንህ፡፡
ታጃህ - የ10 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-
ጠብመንጃን በተመለከተ አንዳንድ የህግ ለውጦች መደረግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ ነፃ አገር ናት፤ ቢሆንም ግን በጠብመንጃ ላይ ገደብ መደረግ አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ እባክህን ሰዎች ከባድ መሳሪያ እንዲይዙ አትፍቀድላቸው፡፡ መሳሪያ ለመያዝ በቂ ምክንያት ሊኖር ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ባለፈው ጊዜ ት/ቤት ውስጥ በተከሰተው ግድያ በጣም አዝኛለሁ፡፡
ጆሲ - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡-
እኔ የምኖረው ቺካጐ ውስጥ ነው፡፡ 9 ዓመቴ ነው፡፡ ያንተም ሴት ልጅ 9 ዓመቷ ይመስለኛል፡፡ አዲሱ ቤትህን እንደወደድከው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን በጣም ዝነኛ ሆነሃል፡፡ አዲሱ ቤትህ ፒዛ ልትጋብዘኝ ትችላለህ? ኦባማ፤ ይመችህ!
ብሪያን - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ካርተር፡-
እባክህን ሰዎች ዓሳ ነባሪዎችን እንዳይገድሉ አስቁማቸው፡፡ በየወሩ ብዙ ዓሳ ነባሪዎች እንደሚገደሉ አውቃለሁ፡፡ ለእነሱ ጥበቃ የሚያደርግ ህግ ብታወጣም ጥሩ ይመስለኛል፡፡
ቦቢ - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ካርተር፡-
በጣም ግሩም ሰው ትመስለኛለህ፡፡ ኦሃዮን ከገባችበት የኢነርጂ (ሃይል) ቀውስ በማውጣት አሜሪካን መለወጥ ያስፈልጋል ያልከው ነገር ትክክል ይመስለኛል፡፡ ገና 13 ዓመቴ ቢሆንም እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነትህ በጣም እወድሃለሁ፡፡
ብሪያን - የ13 ዓመት ህፃን

Monday, 20 October 2014 08:40

እንቆቅልሽ

  • ከአንድ ፓውንድ ላባና ከአንድ ፓውንድ ሸክላ የትኛው የበለጠ ይመዝናል?
    • በግድግዳ ውስጥ መመልከት እንድንችል ያደረገን የፈጠራ ውጤት ምንድን ነው?
    • በጨለማ ክፍል ውስጥ ነኝ ብለህ አስብ፡፡ እንዴት ከጨለማ ክፍሉ ትወጣለህ?
    • ቆዳዬን ስትገፉኝ እኔ ሳላለቅስ እናንተ ታለቅሳላችሁ፡፡
    • ስትመግቡኝ እኖራለሁ፤ ውሃ ስታጠጡኝ ግን እሞታለሁ፡፡

 


    መልስ
ሁለቱም እኩል ናቸው
መስኮት
ማሰቡን በማቆም
ሽንኩርት
እሳት


Monday, 20 October 2014 08:38

ማራኪ አንቀፅ

    ማታ ከራት በኋላ መኝታ ክፍሌ ውስጥ ብቻዬን ነበርኩ፡፡ በሩ ተንኳኳና ከፈትኩት፡፡ ጋናዊቷ ሄለንና ሲዳናዊቷ አህላም ቆመዋል፡፡ ተዘግቶ ከነበረው በር በስተጀርባ እንደ እኔ ለሥልጠና የመጡ ሴቶች ቆመው አያለሁ የሚል ደቃቅ ግምት እንኳን ስላልነበረኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ እኔ ዩኒቨርሲቲ ስማር ሴቶች ወደ ወንዶች፤ ወንዶችም ወደ ሴቶች መኝታ ክፍል ድርሽ እንዲሉ አይፈቀድም ነበር፡፡ ግር ቢለኝም ቀድሜ፣ “ታዲያስ! እንዴት ናችሁ?” ያልኳቸው እኔ ነበርኩ፡፡ ፊቴ ግን፣ “ምነው በሰላም ነው ወደ ወንዶች ዶርም የመጣችሁት?” የሚል ጥያቄ ከአንደበቴ በላይ ጮኸ እንደጠየቃቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡
ምናልባት በቃል ካቀረብኩት ሰላምታ ይልቅ ፊቴ ላይ የተንፀባረቀው ጥያቄ በጉልህ ተሰምቷት ይሆናል፤ ጋናዊቷ ሄለን ለሰላምታዬ ምላሽ ሳትሰጥ፣ “አህላም አብረኸን ወደ ባሩ እንድንሄድ ትፈልጋለች፡፡” አለችኝ ፈገግ ብላ፡፡ ከእንግሊዝኛዋ ከምዕራብ አፍሪካ ከመጡ ሰልጣኞች ጋር ጭራሽ የማይነፃፀር ጥርት ብሎ የሚሰማ ነው፡፡ ዩጋንዳ የገባሁት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር፡፡ እዚህ በምዕራብ ዩጋንዳ፣ ኪባሌ ደን ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ወደሚገኘው የማካራሬ ዩኒቨርሲቲ የመስክ ሥልጠና ጣቢያ ከሌሎች ሃያ ስድስት ሠልጣኞች ጋር የደረስነው ትላንት ነው፡፡
“አህላም ራሷ አትናገርም እንዴ ሄለን የምታወራላት?” ብዬ እያሰብኩ ዞር ብዬ በትዝብት ሳያት፣ ሱዳናዊቷ አህላም፣ “አዎ፣ ከእኛ ጋር እንድትመጣ ፈልገን ነበር፡፡” ብላ ቀይ ፊቷን በውብ ፈገግታ አደመቀችው፡፡ ፊቷ ላይ የዋህነትና ግልጽነት ይነበባል፡፡ ረጅምና ደርባባ ናት፡፡
መኝታ ክፍሌ ተንኳክቶ በሴቶች ስጋበዝ ከኩራት ይልቅ የተሰማኝ መደነቅ ነበር፡፡ የእኛ አገር ሴቶች መቼም እንዲህ አያደርጉም፡፡ ሱዳኖች እንዲህ ያደርጋሉ ማለት ነው? … አልመሰለኝም፡፡ አህላም የተለየች መሆን አለባት፡፡ ወይም ከእኔ ጋር ማምሸት እንደምትፈልግ ስትነግራት ሄለን አደፋፍራት ይሆናል ወደ መኝታ ክፍሌ የመጡት፡፡ … ለነገሩ ከሌሎች አፍሪካውያን ይልቅ እኔ ከሷ ጋር የሚቀራረብ መልክ አለኝ፡፡ ገና ካሁኑ ዘመዶቿን ናፈቀች ማለት ነው? ብዬ እያሰብኩ፣ ሰለቀኑ ውሏቸው እየጠየቅኳቸው ወደ ባሩ ስንወርድ አህላም ቁጥብ ለመሆን ሞከረች፡፡ እንግሊዝኛዋ ጥሩ ፍሰት የለውም እንጂ ለመግባቢያ በቂ ነው፡፡ ባሩ በረንዳ ላይ ተቀምጠን ለስላሳ ጠጣን፤ ዳማ ተጫወትን፡፡ አህላም ወሬ ለመፍጠር አልሞከረችም፡፡ ጭምት ሆነችብኝ፡፡ አንደበቷን ገና በእንግሊዝኛ ስላላፍታታችም የፈለገችውን እንደልብ ለማውራት ይቸግራታል፡፡ ከሷ ይልቅ በጣም ጥሩ እንግሊዝኛ ከምታወራው ከሄለን ጋር ብዙ ሳናወራ አልቀረንም፡፡ ከሷ ጋር ብዙ ባንጫወትም አህላም አጠገቧ በመቀመጤ ደስተኛ ነበረች፡፡
(ከደራሲ ኢዮብ ጌታሁን “አለላ መልኮች” የተሰኘ ልብወለድ የተቀነጨበ)

Monday, 20 October 2014 08:24

የፀሃፍት ጥግ

* ውሸት ፍጥነት አለው፤ እውነት ደግሞ ፅናት፡፡
ኤዴጋር ጄ.  ሞህን
* እጅግ አደገኛ ውሸት የሚሆኑት በጥቂቱ   የተዛቡ እውነቶች ናቸው፡፡
ጆርጅ ክሪስቶፍ ሊችተንበርግ
* ግማሽ እውነት ማለት ሙሉ ውሸት ነው፡፡
የአይሁዳውያን አባባል
* ለአንተ ብሎ የዋሸ፣ በአንተ ላይም መዋሸቱ    አይቀርም፡፡
የቦስኒያዎች አባባል
* ማንንም ስለማልፈራ ጨርሶ አልዋሽም፡፡
  የምትዋሸው የምትፈራ ሲሆን ብቻ ነው ፡፡
ጆን ጎቲ
* ሁሌም ጨካኝ ሳይሆኑ ሃቀኛ የመሆኛ     
   መንገድ  አለ፡፡
አርተር ዶብሪን
* እንደማንኛውም ውድ እቃዎች ሁሉ    
   እውነትም ብዙ ጊዜ ይጭበረበራል፡፡
ጄምስ ካርዲናል ጊቦንስ
* እውነትን ማበላሸት ከፈለግህ ለጥጠው፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
* ውሸት ስትናገር የአንድን ሰው እውነት   
 የመስማት መብት እየሰረቅህ ነው፡፡
ካሊድ ሆስኒ
* ብዋሽ ግዴለኝም፤ ትክክል አለመሆን ግን  ያስጠላኛል፡፡
ሳሙኤል በትለር
* ሃቀኝነት የጥበብ መፅሐፍ የመጀመርያው  
   ምዕራፍ ነው፡፡
ቶማስ ጄፈርሰን
* ውሸት ከመናገር የበለጠ የሚከፋው ቀሪ     ህይወትን ለውሸት ታማኝ ሆኖ መኖር ነው፡፡
ሮበርት ብራውልት

Monday, 20 October 2014 08:21

ዋሽንግተን - በአዲስ አበባ

        ለትምህርት ወደ አሜሪካ የሄዱት በወጣትነታቸው ነው - በ20 እና በ21 ዓመታቸው፡፡ ከአገር የወጡበትን ዓላማ ለማሳካት ኮሌጅ ገብተው ሴቷ ስለ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር)፣ ወንዱ ደግሞ ስለ ቴክኒክ ሙያ ተምረዋል፡፡
በአሜሪካ መኖር የሚቻለው እየሰሩ ነው፡፡ ያለበለዚያ ዶላር የሚመነዝር ቅልጥጥ ያለ የከበርቴ ልጅ መሆን የግድ ነው፡፡ ወጣቶቹ እንደዚያ ስላልሆኑ፣ ተግተው መሥራት ነበረባቸው፡፡ በዋሺንግተን ዲሲና ሜሪላንድም “አዲስ አበባ” የተባለ ምግብ ቤት ከፍተው የኢትዮጵያን ባህልና ምግብ በማስተዋወቅ ከ30 ዓመት በላይ እየሰሩ ኖረዋል፡፡
ዕድሜአቸውን በሙሉ በውጭ አገር መኖር አልፈለጉም፡፡ ወደ አገራቸው ተመልሰው በቋጠሯት ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ፣ ለወገኖቻቸው የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ወሰኑ፡፡
ወ/ሮ ወርቅነሽ ጌታቸውና አቶ አስፋው አምዴ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ አቶ አስፋው፣ በቀድሞው ልዑል መኮንን በአሁኑ አዲስ ከተማ መሰናዶ ት/ቤት የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አሜሪካ የሄዱት እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም ነው፡፡
ወ/ሮ ወርቅነሽ ደግሞ 1ኛ ደረጃን በአርበኞች ት/ቤት፣ 2ኛ ደረጃን በቀድሞው እቴጌ መነን፣ በአሁኑ የካቲት 12 መሰናዶ ት/ቤት ጨርሰው ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን የተጓዙት ከአምስት ዓመት በኋላ ነበር፡፡
በዚያው ዓመት ነበር ሁለቱ ጥንዶች የተዋወቁት፡፡ ከዚያም እንደ ድርጅትም እንደ ማህበረሰብም ሆነው ከዚህ የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያን በመቀበል፣ አገሪቷንም ለአሜሪካ በማስተዋወቅ በአምባሳደርነት ሲያገለግል የቆየውንና ታዋቂውን “አዲስ አበባ ምግብ ቤት” እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ መክፈታቸውን ይናገራሉ፡፡
እዚያም የኢትዮጵያን ምግብና ባህል በማስተዋወቅ ለ21 ዓመት ሰሩ፡፡ ምግብ ቤቱ የበለጠ ታዋቂ እየሆነ፣ የሚያስተናግደው አበሻም ሆነ ፈረንጅ እየጨመረ ሲሄድ፣ መኪና ማቆሚያ ቦታ ጠበበ፡፡
 በ2005 ዓ.ም ሜሪላንድ ወደተባለችው ከተማ ተዛውረው፣ እዚያም ታዋቂውን አዲስ አበባ ምግብ ቤት መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሜሪላንድ 8 ዓመት ከሰሩ በኋላ ነው ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አዲስ አበባ የመጡት፡፡ጥንዶቹ ከ10 ዓመት በፊት ቦታ ገዝተው የሆቴል ግንባታ ጀመሩ፡፡
70 የመኝታ ክፍሎች ያሉትና አትላስ አካባቢ የሚገኘው ዋሺንግተን ሆቴል ሥራ የጀመረው በቅርቡ ቢሆንም በሚሰጠው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ወ/ሮ ወርቅነሽ ይናገራሉ፡፡
ለስብሰባ፣ ለመዝናናትም ሆነ ለሥራ… ከውጭ ለሚመጡ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶችና የቢዝነስ ሰዎች ያዘጋጀነው 5ኛና 6ኛ ፎቅ ያሉት ቪአይፒ ክፍሎች እኛን ከሌሎች ሆቴሎች ይለዩናል ያሉት ወ/ሮ ወርቅነሽ፤ በሁለቱ ፎቆች ያሉት ክፍሎች ለአንድ መሪ ቤተሰብ፣ ባለሥልጣናትና አጃቢዎች ወይም ለአንድ አገር ዲፕሎማትና አብረውት ለሚመጡ የሥራ ኃላፊዎች ወይም ለአንድ አገር የቢዝነስ አባላት ቡድን … የሚከራዩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ቪአይፒ ክፍሉ የራሱ ሳሎን፣ የራሱ ምግብ ማብሰያ (ኪችን) ለቤተሰብና አብረው ላሉ እንግዶች የሚሆኑ 5 መኝታ ክፍሎች፣ ጃኩዚ፣ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ ዋና መኝታ ቤት፣ የራሱ ባርና መዝናኛ ቴራስ፣ ልዩ የደህንነት ጥበቃ… ያሉት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አሁን ያልተጠናቀቁ ነገሮች ስላሉ ሁሉም ነገር ሲያልቅ ሆቴሉ በጠቅላላ 180 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ያሉት አቶ አስፋው፤ ዋሺንግተን በነበረው አዲስ አበባ የባህል ምግብ ቤት የተሰየመው የምግብ አዳራሽ ሁሉንም ዓይነት ባህላዊ ምግቦች ያዘጋጃል ብለዋል፡፡
 ኮሎምቢያ በማለት የበሰየሙት ዘመናዊ ሬስቶራንት ከ40 በላይ የውጭ አገር ምግቦች እንደሚያዘጋጅ፣ ሁለት ባር እንዲሁም በመቅደላ የተሰየመ ትልቅ አዳራሽ፣ ጆርጅታውን ጂምና ስፓ፣ አዲስ አበባን 360 ዲግሪ እያዩ የሚዝናኑበትና በ18 ዲስትሪክት የተሰየመ ቴራስ ሬስቶራንትና ባር፣ … እንዳሉት ገልጸው፤ ሆቴሉንና የተለያዩ አገልግሎት መስጪያዎችን በውጭ አገር ስሞች የሰየሟቸው ለብዙ ዓመታት የሚያውቋቸውን የአሜሪካ አካባቢዎች ለማስታወስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡የሆቴሉ ምግብ በእንግዶች የተወደደ ንፁህ፣ ጣፋጭና ጥራቱን የጠበቀ ቢሆንም ዋጋው ተመጣጣኝ በመሆኑ ኪስ አይጐዳም፣ አንድ ምግብ በ150 ብር መመገብ ይቻላል፣ ከዚያም በታች አለ ብለዋል፡፡
የመኝታ ክፍሎቹ ዋጋ ሲንግል ቤድ 95 ዶላር፣ ደብል ቤድ 120 ዶላር፣ ሱት ክፍሎች 160 ዶላር፣ ልዩ የሆነው ቪአይፒ 950 ዶላር እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ስብሰባ ሲኖርና አስጐብኚ ድርጅቶች በርከት ያሉ እንግዶች ሲያመጡ የዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ሆቴሉን ሲሰሩ ነገሩ ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ የጠቀሱት አቶ አስፋው፤ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሰጠው ዕድል ቋሚ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዳስገቡ ገልፀው፣ ከባንክ ብድር ማግኘት፣ የጉምሩክ ቢሮክራሲ፣ ባለሙያ የሆነ የኮንስትራክሽን ሠራተኛ እጥረት… ዋና ዋናዎቹ ችግሮች እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ ሆቴሉ ለ130 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠረም ለማወቅ ተችሏል፡፡      

      በአሜሪካ በመጪው ወር ለሚካሄደው የግዛትና የኮንግረስ ምርጫ የሚወዳደሩ ጥቁር ፖለቲከኞች ቁጥር ክብረ ወሰን ማስመዝገቡንና የፖለቲካ ተንታኞችም፣ ባራክ ኦባማ በምርጫ አሸንፈው በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት መሆናቸው በጥቁር አማሪካውያኑ ላይ ለታየው የፖለቲካ ተሳትፎ እድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በሁለቱ ምርጫዎች የሚሳተፉ ጥቁር ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከ100 በላይ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ 83 ያህል ጥቁር የሪፐብሊካንና የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ለአሜሪካ ምክር ቤት እንደሚወዳደሩና ይህም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ አስታውቋል፡፡25 ያህል አፍሪካ አሜሪካውያን በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች ለሴናተርነት፣ ለገዢነት ወይም ለሌተናንት ገዢነት ስፍራዎች እንደሚወዳደሩና፣ ይህም በአገሪቱ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛ እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡ከዚህ ቀደም ለአሜሪካ ምክር ቤት አባልነት በርካታ ጥቁሮች የተወዳደሩበት እንደሆነ የተመዘገበው፣ እ.ኤ.አ በ2012 የተካሄደውና ፕሬዚዳንት ኦባማ ለሁለተኛ ዙር አሸንፈው በስልጣን መቀጠላቸውን ያረጋገጡበት ምርጫ ሲሆን  በዚህ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ጥቁሮች 72 እንደነበሩ ዘገባው አስታውሷል፡፡ በግዛቶች ምርጫ በርካታ ጥቁሮች የተወዳደሩበት አመት እ.ኤ.አ 2002 እንደነበረ ጠቁሞ፣ በወቅቱ የተወዳዳሪዎች ቁጥር 17 እንደነበርም አስረድቷል፡፡ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካን አሜሪካን ፖለቲክስ ኤንድ ሶሳይቲ ማዕከል ዳይሬክተር  ፕሮፌሰር ፍሬዴሪክ ሲ ሃሪስ፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ጥቁሮች በምርጫ ድምጽ እንዲሰጡና  ጥቁር ፖለቲከኞችም ከዚህ ቀደም በጥቁሮች ተይዘው በማያውቁ የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች ላይ ለመቀመጥ እንዲወዳደሩ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

     ባለፈው ሳምንት የኖቤል የሰላም ሽልማት የተቀበለችው ፓኪስታናዊቷ የህጻናት መብቶች ተሟጋች ማላላ ዮሱፋዚ፣ የናይጀሪያ መንግስትና አለማቀፉ ማህበረሰብ ቦኮ ሃራም በተባለው አሸባሪ ቡድን የታፈኑትን 219 የአገሪቱ ልጃገረዶች በአፋጣኝ ለማስለቀቅ በስፋት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረቧን ቢቢሲ ዘገበ፡፡የመብት ተሟጋቾች ከስድስት ወራት በፊት በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱትና አሁንም ድረስ በአሸባሪዎች ቁጥጥር ስር የሚገኙት የአገሪቱ ልጃገረዶች ነጻ እንዲወጡ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ያቀረበችው ማላላ፣ ልጃገረዶቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀልና ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ትምህርት ማግኘት ይገባቸዋል ብላለች፡፡“የአገሪቱ መንግስት እና አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ አፋጣኝና ሰላማዊ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያደርጉትን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድጉ እጠይቃለሁ” ብላለች ማላላ፡፡ማላላ ባለፈው ሃምሌ ወር ወደ ናይጀሪያ በማምራት በጉዳዩ ዙሪያ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ጋር መወያየቷን የጠቆመው ዘገባው፣ ልጃገረዶቹ ባለፈው ሚያዝያ በሰሜን ምስራቃዊ ናይጀሪያዋ ቺቦክ ከተማ ወደሚገኘው የአዳሪ ትምህርት ቤታቸው በመጓዝ ላይ ሳሉ  በቦኮ ሃራም ታጣቂዎች መጠለፋቸውን አስታውሷል፡፡
የናይጀሪያ መንግስት ልጃገረዶቹን ለማስለቀቅ በቂ ጥረት አላደረገም የሚል ትችት እንደሚሰነዘርበት የጠቀሰው ቢቢሲ፤ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአገሪቱ ሚኒስትሮች ግን ትችቱን እንዳጣጣሉት አመልክቷል፡፡በቅርቡ “ልጃገረዶቻችንን መልሱልን” የሚል ዘመቻ ያዘጋጁ የናይጀሪያ የመብት ተሟጋቾች፣ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ አቡጃ  ወደሚገኘው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቤት ማምራታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ፖሊሶች ወደ ስፍራው እንዳይደርሱ እንደከለከሏቸው አክሎ ገልጧል፡፡

      በምዕራብ አፍሪካ አገራት የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እስከ ነገ ከ9ሺህ በላይ ይደርሳል  ተብሎ እንደሚጠበቅ የአለም የጤና ድርጅትን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ባለፈው መጋቢት ወር በጊኒ የተከሰተውና በምዕራብ አፍሪካ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኢቦላ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ 8ሺህ 914 ሰዎችን እንዳጠቃና ከነዚህ ውስጥም 4ሺህ 447 ያህሉ ለህልፈት እንደተዳረጉ የጠቆመው ዘገባው፣  ቁጥሩ ዛሬና ነገ ከ9ሺህ በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ረዳት ዳይሬክተር ብሩስ አይልዋርድ እንዳሉት፣ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በተከሰተባቸው አንዳንድ አካባቢዎች አዳዲስ ሰዎችን የማጥቃቱ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ቢኖሩም፣ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተስፋፋ በመሆኑ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ድርጅቱ እንደተነበየው፤ የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ በየሳምንቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ አስር ሺህ ሊደርስ ይችላል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ኢቦላ በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት በቫይረሱ የተጠቁና የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ ይፋ እየተደረጉ ያሉ መረጃዎች፣ የተዛቡና ከትክክለኛው ቁጥር ያነሱ ናቸው ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ችግሩን ለመቅረፍ ተገቢው ጥረት እንዳይደረግ የሚያዘናጋ ነው ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው ባለፈው ረቡዕ በኢቦላ ዙሪያ ለመምከር በዋይት ሃውስ በጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ፣ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የጤና ባለሙያዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ የቫይረሱን ስርጭት መግታት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑንና የአገሪቱ መንግስትም ኢቦላ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው መግለጻቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሲዲሲና ከሚመለከታቸው የአገሪቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ብሄራዊ ግብረሃይል አቋቁመው በአፋጣኝ ወደ ስራ መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ኢቦላን ለመዋጋት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የተለያዩ የዓለም አገራት መሪዎችን እንደሚያግባቡ መናገራቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ቢቢሲ ከአፍሪካ ውጭ ያለውን የኢቦላ ክስተት በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ የዘንድሮው ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በአሜሪካ 8፣ በጀርመን 3፣ በስፔን 3፣ በኖርዌይ 1፣ በፈረንሳይ 1 እና በእንግሊዝ 1 በድምሩ 17 ሰዎች በኢቦላ የተያዙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም አንድ አሜሪካዊ፣ አንድ ጀርመናዊና ሁለት ስፔናውያን ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ ከሶስቱ ሰዎች በስተቀር ሁሉም በቫይረሱ የተያዙት ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት በሄዱበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የታዋቂው የማህበረሰብ ድረገጽ የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙክበርግ የኢቦላን ወረርሽኝ ለመግታት የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ የሚውል የ25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ብሉምበርግ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ዙክበርግና ባለቤቱ ፕሪስኪላ ቻን ገንዘቡን ለአሜሪካው ሲዲሲ ፋውንዴሽን ያስረከቡ ሲሆን፣ የህክምና ማዕከላትን ለማቋቋምና አፍሪካውያን ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የመሳሰሉ ስራዎች እንደሚውል ተነግሯል፡፡
“ኢቦላ የበለጠ ከመስፋፋቱና አለማቀፍ የጤና ቀውስ ከመሆኑ በፊት በአፋጣኝ በቁጥጥር ውስጥ ልናውለው ይገባል” ብሏል ዙክበርግ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት፡፡





    “ሬድ ቡል”ን የመሳሰሉ ሃይል ሰጪ መጠጦች በተለይ ከአልኮል መጠጥ ጋር ተደባልቀው ሲጠጡ የጤና ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት ተመራማሪዎች አስጠነቀቁ፡፡
በአውሮፓ የተደረገ ጥናት እንዳረጋገጠው፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ18-29 ዓመት የሚደርሱ ወጣቶች፣ እንደ “ሬድ ቡል” ያሉ ሃይል ሰጪ መጠጦችን (Energy drinks) ከአልኮል መጠጥ ጋር እየደባለቁ ይጠጣሉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚለው፤ ዋነኛው የስጋት ምንጭ በመጠጦቹ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የካፌይን መጠን ሲሆን ይሄም ፈጣን ወይም ያልተመጣጠነ የልብ ምት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ማስመለስ፣ ከፍተኛ የሰውነት መንቀጥቀጥና ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ የልብ በሽታ… የመሳሰሉ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ካፌይን በህፃናት ላይ በጥናት የተረጋገጠ አሉታዊ ተፅአኖ እንዳለው ተመራማሪዎቹ በጥናት ሪፖርታቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡
“የሃይል ሰጪ መጠጦች ተወዳጅነት መጨመር ያደረሰው ሙሉ ተፅእኖ ገና በቁጥር አልተቀመጠም፤ ነገር ግን ወጣቶችን ዒላማ ያደረገው የሃይል ሰጪ መጠጦች ጠንካራ የገበያ ስልት በምርቶቹ ላይ ከሚደረግ ውስንና ተለዋዋጭ ቁጥጥር ጋር ሲዳመር እነዚህ መጠጦች ለህብረተሰቡ ጉልህ የጤና ስጋት የሚሆኑበትን ድባብ ፈጥሯል” ብለዋል - ተመራማሪዎቹ፡፡
ዩሮሞኒተር ባሰፈረው መረጃ መሰረት፣ የሃይል ሰጪ መጠጦች ዓለም አቀፋዊ ሽያጭ እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም ከነበረው 2.4 ቢሊዮን ፓውንድ በ2013 ዓ.ም ወደ 17.3 ቢሊዮን ፓውንድ አሻቅቧል፡፡ “ሬድ ቡል” የተባለው ሃይል ሰጪ መጠጥ በእንግሊዝ በከፍተኛ ሽያጫቸው ከሚታወቁ ለስላሳ መጠጦች በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
አንዳንድ የቡና ዘሮች ተመሳሳይ የካፌይን መጠን ያላቸው ቢሆንም ሃይል ሰጪ መጠጦች ቀዝቃዛውን የሚጠጡ በመሆናቸው በከፍተኛ ፍጥነት የሚወሰዱ ናቸው ብሏል - ጥናቱ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የጥናት ቅኝት እንደሚለው፤ እስካሁን የሚታወቁት ሃይል ሰጪ መጠጦች ካላቸው የካፌይን መጠን በእጅጉ የላቀ ካፌይን የያዙ አዳዲስ ምርቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ሃይል ሰጪ መጠጦች ከካፌይን በተጨማሪ ጉዋራና፣ ታውሪንና ቢ ቪታሚንስ የተባሉ ንጥረነገሮችን እንደያዙ የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፤ ስለምንነታቸውና ከካፌይን ጋር ስላላቸው መስተጋብር ለማወቅ ተጨማሪ ምርምር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ፖሊሲን አይወክልም በተባለ የጥናት ፅሁፍ ላይ እንደተጠቆመው፣ ሃይል ሰጪ መጠጦችን ከአልኮል መጠጥ ጋር ደባልቆ በመጠጣት ጉዳት እንደሚደርስ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ የአውሮፓ የምግብ ደህንነት ባለስልጣን ጥናት፤ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ18-29 የሚደርሱ ወጣቶች ሃይል ሰጪ መጠጦችን ከአልኮል ጋር ደባልቀው እንደሚጠጡ አረጋግጧል፡፡
አጥኚዎቹ እንደሚሉት፤ አልኮል ብቻውን ከመጠጣት የበለጠ ይሄኛው በጣም አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም የስካሩ መጠን ባይቀንስም ሰዎች መስከራቸውን ለማወቅ እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡
ሃይል ሰጪ መጠጦች በአብዛኛው የስፖርት ብቃትን እንደሚጨምሩ እየተነገረ ቢተዋወቁም ከአካል እንቅስቃሴ ጋር ሲጣመሩ ለአደጋ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ ጥናቱ አክሎ ገልጿል፡፡
በእነዚህ መጠጦች ውስጥ መካተት ያለበት የካፌይን መጠን ምን ያህል እንደሆነ ተመራማሪዎቹ በቁጥር ባይገልፁም በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በእንግሊዝ የምግብ ጥራት መመዘኛ አጀንሲ፣ ከታህሳስ ወር ጀምሮ ከፍተኛ የካፌይን መጠን የያዙ ሃይል ሰጪ መጠጦች፣ ይሄንኑ በምርቶቻቸው ላይ እንዲጠቁሙና “ለህፃናት ወይም ለነፍሰጡር ወይም ጡት ለሚያጠቡ ሴቶች አይመከርም” የሚል ማስጠንቀቂያ እንዲያሰፍሩ ያስገድዳል ተብሏል፡፡ በግንቦር ወር ደግሞ ሉቱዋኒያ እንዲህ ያሉ መጠጦች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት እንዳይሸጥ የሚያግድ ህግ በማውጣት የመጀመሪያዋ የአውሮፓ አገር ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Monday, 20 October 2014 08:04

የፍቅር ጥግ

(ስለውበት)

ውበት  እውነት ነው፤ እውነትም ውበት፡፡
ጆን ኪትስ
ውበትን የምትመለከት ነፍስ አንዳንዴ ብቻዋን ልትጓዝ ትችላለች፡፡
ገተ
ፍቅር በውስጥህ ስለሚበቅል ውበትም እዚያው ይበቅላል፡፡ ፍቅር የነፍስ ውበት ነውና፡፡
ቅዱስ ኦገስቲን
የሴቶች ትህትና በአጠቃላይ ከውበታቸው ጋር ይጨምራል፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
ውበት ያለው ፊት ላይ አይደለም፤ ውበት ልብ ውስጥ ያለ ብርሃን ነው፡፡
ካህሊል ጀብራን
ውብ የሆነ ማንኛውም ነገር የማየት ዕድል አያምልጥህ፤ ውበት የእግዚአብሔር የእጅ ፅሁፍ ነውና፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
ፈገግታዋ የማይከደንና ገፅታዋ ደስታ የማይርቀው ሴት፣ ምንም ብትለብስ ማማሯ አይቀርም፡፡
አኔ ሮይፊ
በዓለም ላይ ያሉ ምርጥና እጅግ ውብ የሆኑ ነገሮች በዓይን መታየትና በእጅ መዳሰስ አይችሉም፤ በልብ ነው መጣጣም ያለባቸው፡፡
ሔለን ከለር
ውበት ዓይንን ብቻ ሲያስደስት፤ ሸጋ ስብዕና ነፍስን ይማርካል፡፡
ቮልቴር
በእርግጠኝነት ለውበት ፍፁም የሆነ መለኪያ የለውም፡፡ ይሄም ነው ፍለጋውን እጅግ አጓጊ የሚያደርገው፡፡
ጆን ኬኔዝ ጋልብሬይዝ
የውበትን ያህል በቀጥታ ወደ ነፍስ የሚጓዝ ምንም ነገር የለም፡፡
ጆሴፍ አዲሶን