Administrator

Administrator

የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፃሚዎች በተለያዩ አዕምሮአዊ የጤና ችግሮች የተጠቁ ናቸው (የስነ ልቦና ባለሙያ)
ህጉ በአስገድዶ ደፋሪዎች ላይ ያስቀመጠው ቅጣት ለወንጀሉ ተመጣጣኝ አይደለም (የህግ ባለሙያ)

አየር ጤና አካባቢ ከሚገኘው ት/ቤቷ ወጥታ ወደ ቤቷ ለመሄድ በተሳፈረችበት ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ በነበሩ አምስት ወንዶች ታፍና ተወስዳ በደረሰባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ህይወቷ ያለፈው የአስራ አምስት ዓመቷ ታዳጊ ሃና ላላንጎ ጉዳይ ከተማችንን ሲንጣት ሰንብቷል፡፡ ታዳጊዋ ታፍና ከተወሰደችበት መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የቡድን አስገድዶ መድፈር ጥቃታ ተፈፅሞባት፣ ጦር ኃይሎች ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን አካባቢ ተጥላ መገኘቷ መገቡ ይታወሳል፡፡
የህክምና እርዳታ አግኝታ ህይወቷ እንዲተርፍ የተደረገው ሙከራም የተፈፀመባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እጅግ ከባድ በመሆኑና በስለት በመወጋቷ ሳቢያ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይሄ ክፉ ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ድርጊቱም በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በታዳጊዋ ላይ ይህንን አሰቃቂ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ወጣቶችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው፣ ጉዳያቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎታ በዝግ እየታየ ይገኛል፡፡
የሟቿን ታዳጊ ጉዳይ መነሻ በማድረግ ለአስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚያነሳሱ አፈንጋጭ የወሲብ ባህሪያትን ምንነትና የሚያስከትሏቸውን የጤና ቀውሶች እንዲሁም ለወንጀሉ የተቀመጠውን ቅጣት አስመልክቶ ከባለሙያዎች ያገኘነውን ማብራሪያና መረጃ የአዲስ አድማስ
ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡


አስገድዶ መድፈር ከስነ ልቦና
ቀውስ አንፃር
መደበኛ ከሆኑትና ከተለመዱት ወሲባዊ ድርጊቶች በተለየ መንገድ ወሲብን የመከወን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች፣ ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርይ የተጋለጡ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ከእነዚህም መካከል አስገድዶ መድፈር፣ የቡድን ተራክቦ፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ሌሎች ወሲብን ሲፈፅሙ በማየት መርካት፣ ግለ ወሲብና በሰዎች  ስቃይ እርካታን ማግኘት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአስገድዶ መድፈርና በቡድን የሚደረጉ ተራክቦዎች በአብዛኛው የሚፈፀሙት በአልኮልና በተለያዩ የአደንዛዥ እፆች ራስን ስቶ አዕምሮ በአግባቡ እንዳያስብ በማድረግ ነው ይላሉ - ባለሙያዎች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርያት አመላካች የሆኑ ድርጊቶች በአገራችን እየተለመዱ መምጣታቸውን የጠቆሙት የሥነ ልቦና ባለሙያው ዶክተር አንተነህ ተስፋው፤ በተለይ ዕድሜያቸው ከ16-25 ዓመት በሚሆናቸው ወጣቶች ላይ ድርጊቱ በስፋት እየታየ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል፡
ከቴክኖሎጂው እድገትና ወሲባዊ ፊልሞች እንደ አሸን ከመፍላታቸው ጋር ተያይዞ አስገድዶ መድፈር፣ የቡድን ወሲብና ግብረሰዶማዊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ መምጣታቸውንም ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርያት አንዱ የሆነው አስገድዶ መድፈር የአዕምሮአዊ ጤና ቀውስ ውጤት ነው፡፡ ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርያት አጋላጭ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋንኞቹ፡-
ከአስተዳደግ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ስነልቦናዊ ችግሮች
አዕምሮ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች
የሆርሞኖችና ኬሚካሎች መዛባት
የኒውሮኖች ጉዳት ናቸው፡፡
ከአስተዳደግ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የስነ ልቦና ችግሮች
ችግሩ በአብዛኛው ከአስተዳደጋችን ጋር ተያይዞ የሚከሰት ነው፡፡ ለራስ የሚሰጥ አነስተኛ ግምትና በልጅነት ዕድሜ ለወሲባዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆን ለአፈንጋጭ የወሲብ ባህርይ ሊዳርግ ይችላል፡፡
አዕምሮ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች
በአዕምሮአችን ላይ በበሽታም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች አካላዊ ጉዳቶች ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጉዳቶች ደግሞ የአዕምሮአችንን የወሲብ ክፍል ሊጎዱትና በዚያም ሳቢያ በወሲባዊ ባህርያችን ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ለአፈንጋጭ የወሲብ ባህርይ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡
የሆርሞኖችና የአዕምሮ ኬሚካሎች መጠን መዛባት
አንድሮጅንና ኤስትሮጅን የተባሉት በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙት ሆርሞኖች ወሲባዊ ፍላጐትና ስሜታችንን ለመቆጣጠር የማረዱን ናቸው፡፡ የእነዚህ ሆርሞኖች መዛባት በወሲባዊ ባህርያችን ላይ የሚያስከትሉት ተፅእኖ ቀላል አይደለም፡፡
 የኒውሮኖች ጉዳት
የአዕምሮ ሴሎች እርስ በርስ እንዲተሳሰሩና መልእክት እንዲለዋወጡ የሚያደርጉ የአዕምሮአችን መረቦች በተለያየ ምክንያት ጉዳት በሚደርስባቸው ጊዜ አፈንጋጭ ለሆነ ወሲባዊ ባህርይ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ ለአፈንጋጭ ወሲባዊ ባህርይ ልንጋለጥ የምንችለው በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ሲሆን ችግሩ በወቅቱ ታውቆ የባለሙያ እገዛ ካላገኘ በጊዜ ብዛት አፈንጋጭ የወሲብ ባህርይው ሙሉ በሙሉ የግለሰቡን አዕምሮ በመግዛት በራስ መተማመን የሌለውና ወሲባዊ እሳቤውን ለመቆጣጠር የማይችል ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የችግሩ ተጠቂ የሆነ ሰው ለራሱ ያለው ግምት እጅግ አነስተኛ ስለሚሆን ራሱን ከማህበረሰቡ ያገላል፡፡ ራሱን ለማጥፋትም ይፈልጋል፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት የችግሩ ተጠቂዎች የስነልቡና ባለሙያዎች ጋር ወይንም የስነ አዕምሮ ሐኪሞች ዘንድ በመሄድ ለችግራቸው መፍትሄ መሻት ይኖርባቸዋል፡፡
የአስገድዶ መድፈር ድርጊት የተፈፀመባት (የተፈፀመበት) ሰው ብቻ ሳይሆን የፈፀመው ግለሰብም ጭምር የህክምና እርዳታ ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ መመቻቸት ይኖርበታል ያሉት የስነልቡና ባለሙያው ዶክተር አንተነህ፤ ይህ አሰራር በሌሎች አገራት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አስገድዶ መድፈርና ህጋዊ ተጠያቂነቱ
በ15 ዓመቷ ታዳጊ ወጣት ላይ የተፈፀመው የቡድን አስገድዶ መድፈር ወንጀል ያስቆጣቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የድርጊቱ ፈፃሚዎች በአፋጣኝ ተይዘው ለድርጊታቸው ተመጣጣኝ የሆነና ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል (መቀጣጫ የሚሆን) ፍርድ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ሰንብተዋል፡፡ የወንጀሉ ፈፃሚዎች በሞት እንዲቀጡ አሊያም የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲወሰንባቸው የጠየቁም በርካቶች ናቸው፡፡ ለመሆኑ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ለዚህ መሰሉ ድርጊት የሚሰጠው የቅጣት ውሳኔ እምን ድረስ ነው? የህግ ባለሙያው አቶ ዳዊት ታዬ ለዚህ ማብራሪያ አላቸው፡፡
የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ፤ የአስገድዶ መድፈርን ወንጀል እስከ አስር አመት ሊደርስ በሚችል ቅጣት የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጐ አስቀምጦታል፡፡
ድርጊቱ የተፈፀመው አስራ አምስት ዓመት ባልሞላት ሴት ልጅ ላይና በብዙ ሰዎች ተባባሪነት ከሆነ ቅጣቱ እስከ አስራ አምስት አመት ሊደርስ እንደሚችል ይገልፃል፡፡ ድርጊቱ ሞትን የሚያስከትል ሲሆን ደግሞ ቅጣቱ ከፍ ሊል ይችላል፡፡ ሆኖም በአስገድዶ መድፈር ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ የቅጣት ህጐች ደፋሪዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያላቸው ናቸው ብሎ ለመናገር እንደማያስችሉ አቶ ዳዊት ይናገራሉ፡፡
“ህጉ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀመ ሰው ወንጀሉን የፈፀመባትን ሴት ያገባ እንደሆነ ክሱ ቀሪ ሊሆን እንደሚችል ያስቀምጣል፤ ይህም የድርጊቱ ፈፃሚዎች ጋብቻ በመፈፀም ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስለሚያስቡ ድርጊቱን ከመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም፤ ምክንያቱም ወንጀሉን በጋብቻው ካስቀሩ በኋላ ጋብቻውን ደግሞ በቀላሉ ሊተውት ይችላሉና” ሲሉ አስረድተዋል አቶ ዳዊት፡፡
ተጎጂውን ለአካል ጉዳት፣ ለስነ ልቦና ቀውስና ባስ ሲልም ለህልፈት የሚዳርገውን ይህን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከልና ከነአካቴውም ለማጥፋት የሁሉንም የጋራ ህብረትና ጥረት ይጠይቃል፡፡
 ጉዳዩ ጊዜ የሚሰጥና ለነገ በይደር የሚተው አይደለም፡፡ ግለሰቦች፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ማህበረሰብ፣ ፖሊስ (መንግስት)፣ መምህራንና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንዲሁም የፆታ እኩልነት ተሟጋቾች ዛሬውኑ አገራዊ እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ነገ በሃና ላይ ከተፈፀመው ጥቃት የከፋ በሌሎች ላይ ላለመፈፀሙ ምንም ማረጋገጫ እንደሌለን መዘንጋት የለብንም እሳቱን ለማጥፋት ከመረባረብ ቃጠሎ እንዳይነሳ መከላከል የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

“አሜሪካ ፆታዊ ጥቃቶችን አጥብቃ ትቃወማለች”
አገራቸው በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን አጥብቃ እንደምትቃወምና የሴቶችን አቅም በመገንባትና በማሳደግ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በህብረት እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ኤም ሃስላክ ገለፁ፡፡ ከህዳር 16 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በዘለቀው የነጭ ሪባን ቀን፤ በኤምባሲው በተዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ከተሳተፉት የአሜሪካ አምባሳደር ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ የአፍታ ቆይታ አድርጋለች፡፡

አምባሳደር በመሆን ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣትዎ በፊት ስለ ኢትዮጵያ ያውቁ ነበር?
በ1980ዎቹ በኢትዮጵያ በተከሰተው ረሃብና የድህነት ችግር ላይ ከአሜሪካ መንግስት ጋር እሰራ ነበር፡፡ በ2010 አለም አቀፍ የድህነት መዋጋትና የምግብ ዋስትና (አሁን Future Initative እየተባለ የሚጠራውን) ድርጅት ወክዬ ወደ ኢትዮጵያ መጥቻለሁ፡፡
አሁን ሲመጡ ምን ለውጥ አዩ?
ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ አገሪቱ እያደገች በመሄድ ላይ መሆኗንም ለማየት ችያለሁ፡፡
ፆታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ሰሞኑን በተዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከተደራራቢ የሥራ ኃላፊነትዎ አንፃር ይህን እንዴት ተወጡት?
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን አገሬ አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ ለዚህም ነው በፀረ ፆታዊ ጥቃትና ሴቶችን በማብቃት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው፡፡ ይህ የነጭ ሪባን ቀን ደግሞ ለፆታዊ ጥቃቶች ያለንን ተቃውሞ የምናሰማበት ስለሆነ ነው በኤምባሲው በተዘጋጁ ፕሮግራሞች ላይ ሁሉ ተሳታፊ የሆንኩት፡፡ በግሌ ደግሞ ከመሃከለኛው ህዝብ ጋር መሆን ደስታን ይሰጠኛል፡፡ ለሰዎች ድጋፍና ተስፋን ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት እወዳለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ቦታዎች ላይ መገኘትም የሚሰጠኝ ደስታ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
በቅርቡ በቡድን በተደረገባት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ህይወቷ ያለፈው ታዳጊ ወጣት ሃና ላላንጐ ጉዳይ በአገሪቱ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ጉዳዩ በማህበረሰቡ ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ቢሆንም አንዳንድ ወገኖች መንግሥት ስለ ጉዳዩ ብዙም ያለው ነገር የለም በማለት ይተቻሉ፡፡ በእናንተ አገር እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲያጋጥም የመንግስት ሚና ምንድነው?
የሃና ጉዳይ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ወይንም የሚከሰት ብቻ አይደለም፡፡ በመላው ዓለም የሚከሰትና የተከሰተም ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ለማስቀረት ዋንኛው መፍትሄ ህብረተሰቡን ማስተማር ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ ለጉዳዩ ያገባኛል ማለት መቻል አለበት፡፡ ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ባል ሚስቱን ሲደበድብ ወይም ጐረምሳው ወጣቷን ሲመታ አይቶ በዝምታ ማለፍ አግባብ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው እንዲህ አይነት ፆታዊ ጥቃቶች ሲፈፀሙ ሲያይ ለማስቆም ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ሴቶች በራሳቸው ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆም የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግም ጥረት እናደርጋለን፡፡ በፆታዊ ጥቃቶች ላይ መንግስታችሁ ጥብቅ አቋም እንዳለው አውቃለሁ፡፡ የአስራ ስድስት ቀናቱን የነጭ ሪባን ቀን በማስተባበር እየሰራ የነበረው የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ እናም መንግሥታችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ ነው፡፡
የሁለት ሴት ልጆች እናት ነዎት፡፡ አንደኛዋ ልጅዎ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሰማርታለች፡፡ የት ነው የምትሰራው? ለጋዜጠኝነት ሙያ ያለዎት ስሜትስ ምን ይመስላል?
ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ አንዷ ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ለሁለት ሳምንታት ቆይታ ሄዳለች፡፡ ለጋዜጠኝነት ፍቅር አላት፡፡ ከኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም ዲግሪዋን ወስዳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ለቢቢሲ ትራቭል እንዲሁም፣ ለኒውዮርክ ታይምስና ለሌሎች መፅሄቶች ትሰራለች፡፡ ለሙያው ጥሩ ስሜት አለኝ፡፡   

Saturday, 13 December 2014 10:51

የግጥም ጥግ

መቼ ነው ያለሁት?
ዛሬ ነግቶ መሽቶ ቀኑን አልፈውና፣
ሌላው ቀን ሲተካ ሲሆን ትናንትና፣
ይኸው እኖራለሁ አለሁ እኮ ዛሬ፣
ደግሞም ለዓመታት  ተስፋ አለኝ መኖሬ፣
    እያልሁ አስብና፣
    ሞቴን እረሳና፣
    እቅዴን አውጥቼ፣
    ምኞቴን አስፍቼ፣
ደጉን ተመኝቼ፣
ክፉውን ዘንግቼ፣
ሞትን ተሸክሜ ግን እየረሳሁት፣
ጎንበስ ቀና እያልሁ ይኸውና አለሁት፡፡
ምንም ባላውቀውም ቀኑን መሻገሬ፣
የነገን እንጃ እንጂ አለሁ ግን ለዛሬ፡፡
ሞት ትዝ ቢልም፣ ከራርሞ ከራርሞ …
    ከስንት ቀን አንዴ፣
መች ተስፋ ቆርጬ፣ ሰብዓዊ ፍጡር…
        ሰው አይደለሁ እንዴ!
ሃሳብ አይገባኝም፣ ባስብስ ምን ልሆን …
           ከቶ የማይቀረውን፣
ስለዚህ ማሰብስ፣ ዛሬን እንጂ ኑሮን …
    ፋታ የማይሰጠውን፡፡
ግን ታዲያ! …
    ማለፌን ሳስታውስ እንደገና ደግሞ፣
    ከውጥኔ በፊት ሞት ሲመጣ ቀድሞ፣
        ድንገት ፀጥ እልና፣
        ክልትው እለውና፣
        ሁሉም ይቀርና፣
        ጣጣዬ  ያከትምና፣
        ክርችም ብሎ ቁልፉ፣
        ይዘጋል ምዕራፉ፡፡
ቀነ - ሞታችንን እኔም ሆንኩ ሌላው …
          ጨርሰን አናውቀው፣
ስለዚህ ነው ሰዎች፣ “መቼ ነው ያለሁት?”
    ብዬ የምጠይቀው፡፡
                  * * *
አምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
ህዳር 2007 ዓ.ም

የ25 ዓመቷ አሜሪካዊት ጄድ ሲልቪስተር፤ በእርግዝና ወቅት በተፈጠረባት አምሮት መላቀቅ ዳገት ለሆነባት ክፉ ልማድ እንደተጋለጠች ትናገራለች፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ነፍሰጡር ሳለች የጀመረችው የመፀዳጃ ቤት ወረቀት (ሶፍት) የመብላት ልማድ ከወለደችም በኋላ ሊላቀቃት አልቻለም፡፡ ዛሬ ያ አምሮት ወደ ሱስ ያደገ ይመስላል፡፡ በየቀኑ አንድ ጥቅል ሶፍት ታነክታለች፡፡
“ባረገዝኩ በሁለተኛ ወሬ ነው ሶፍት የመብላት አምሮት (ፍላጐት) ያደረብኝ፡፡ ለምን እንደሆነ ግን አሁንም ድረስ አላውቀውም፡፡
 ከጣእሙ ይልቅ ደስ የሚለኝ ሻካራነቱ ነው፡፡ ደረቅነቱን እወደዋለሁ” ያለችው ጄድ፤ “ቤተሰቦቼ ለጤናዬ ጥሩ አለመሆኑን ይነግሩኛል፤ ነገር ግን ለመተው አልቻልኩም” ብላለች፡፡
ልጇን ከተገላገለች አንድ ዓመት ከሦስት ወር ያለፋት ቢሆንም መፀዳጃ ቤት ገብታ በተቀመጠች ቁጥር ሶፍት እየቀረደደች መብላቷን ገፍታበታለች፡፡ በየቀኑም አንድ ሙሉ ጥቅል ሶፍት እንደ ምግብ አኝካና አጣጥማ እንደምትውጥ ተናግራለች፡፡ ነፍሰጡር ሳለች መፀዳጃ ቤት ገብታ ጥቅል ሶፍት ስታይ “ይሄንን መብላት አለብኝ” እያለች ትጐመዥና ትመኝ እንደነበር ያስታወሰችው ጄድ፤ ዛሬ ግን አንዳንዴ ወደ መታጠቢያ ከመሄድ ሁሉ ራሷን እንደምታቅብ ገልፃለች፡፡ “ምክንያቱም ከሄድኩኝ መብላቴ አይቀርም፡፡ ሽንት ቤት በሄድኩ ቁጥር ወደ 8 ገደማ የሶፍት ቁራጮች እበላለሁ አንዳንዴም ሶፍቱን ለመብላት ስል ብቻ መፀዳጃ ቤት ለመሄድ እገደዳለሁ” ትላለች፡፡
ለመብላት የምትመርጠውን የሶፍት አይነት ስትናገር ደግሞ፤ ከውዶቹ ይልቅ በየሱፐርማርኬቱ የሚገኙት ተራና ርካሽ ሶፍቶች ምርጫዋ እንደሆኑ ገልፃለች፡፡
“የተለያዩ የሶፍት ምርቶች የተለያየ ጣእም አላቸው፤ በመፀዳጃ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅል ለምበላው፣ አንድ ጥቅል ደግሞ ለተለመደው አገልግሎት አስቀምጣለሁ” ብላለች ጄድ ሲልቪስተር፡፡ የመጨረሻ ወንድ ልጇን ከተገላገለች ጊዜ ጀምሮ (16 ወራት ገደማ ማለት ነው) ሶፍት መብላቷን ለመተው ብዙ ታግላለች፤ ሆኖም አልተሳካላትም፡፡ ልጅ ከወለድኩ በኋላ አምሮቱ የሚተወኝ መስሎኝ ነበር ያለችው ጄድ፤ ነገር ግን ሶፍት መብላቴን ላቆም አልቻልኩም ትላለች - ተስፋ በቆረጠ ቅላፄ፡፡
“ሶፍት መብላቴ ለሰውነቴ መልካም ሊሆን እንደማይችል አውቃለሁ፤ እስካሁን ግን ምንም የጤና ችግር ወይም ህመም አላስከተለብኝም” ያለችው ሚስ ሲልቪስተር፤ ሶፍት ስትበላ ልጆቿ እንዳያዩዋት ለመደበቅ እንደምትሞክር ገልፃ ድንገት ካዩዋት ግን እንደሚቆጧት ተናግራለች፡፡ ጄድ ሲልቪስተር የአምስት ልጆች እናት ናት፡፡ የአገራችን ሰው “አያድርስ ነው” የሚለው ለካ ወዶ አይደለም!!

ከእለታት አንድ ቀን አንዲት ቀበጥ ልጅ ከእናቷና ከሴት አያቷ ጋር አብራ ትኖር ነበር፡፡ ከቀበጥነቷም በላይ የሥራ ዳተኝነቷ አስቸጋሪ ነበር፡፡
እናትና አያት ይወያያሉ፡-
አያት - እንደው የዚችን ልጅ ነገር ምን ብናደርግ ይሻላል?
እናት - እረ እኔም ከዛሬ ነገ እጠይቅሻለሁ እያልኩ ስፈራ ስቸርኮ ነው የቆየሁት፡፡ የአያት አንጀት ሆኖብሽ ስለምታቆላብሻት እንዳትቀየሚ ብዬ ታገስኩ፡፡
አያት - እረ የምን ቅያሜ ነው እሱ?
እናት - እንግዲያው ለምን ቁጭ አድርገን ነገረ-ስራዋ ሁሉ እንዳልጣመንና ከእንግዲህ ቤቷን ቤቴ ብላ በስነ ሥርዓት እንድትኖር እናስጠንቅቃት፡፡
አያት - አዎ፤ መቼም የሙት ልጅ ናትና አባቷ ከሞተ ወዲህ ሀዘኗም ብስጭቷም በዝቶቦታል ብለን ብዙ ታገስናት፡፡ አሁን ግን በዛ!
እናት - መብዛት ብቻ! ተንዛዛች እንጂ! ምግብ በልታ ውልቅ! ጠዋት የወጣች አገሩን ስታካልል ውላ መምጣት! እራቷን በልታ ክልትው!
አያት  አዲስ ሀሳብ አመጡ:-
“ቆይ እስቲ ዛሬ መቼም አዕምሮ አላት፡፡ ታስብበትና ወደ ቀልቧ ትመለስ ይሆናል”
እናት - ምን አድርገሽ ቀልብ እንዲኖራት ታደርጊያታለሽ?
ምን እናድርግ ትያለሽ?
አያት - ወደ አልጋዋ እንጠጋና ወለሉን እኔ ልጥረግ እኔ ልጥረግ እያልን እንጣላ፡፡ ለመጥረግ እንታገል፡፡ ስትነቃ ተዉት እኔ እጠርጋለሁ በማለት ይሉኝታ ይይዛትና ትነሳለች፡፡
እናት - በጣም ድንቅ ሃሳብ! በይ ነይ እንሂድ፡፡
እናትና አያት እንደተባባሉት፤ አንድ መጥረጊያ ለሁለት ይዘው፤
አያት - ተይ ዛሬ እኔ ነኝ የምጠርገው?
እናት - ምን ሲደረግ!? አንቺ አርፈሽ ቁጭ በይ!
አያት - አብደሻል ስንት ዘመን አንቺ ልትጠርጊ ነበርኮ?
እናት - አይሆንም አልኩ አይሆንም!
ትግሉ ቀጠለና ልጅቱ ነቃች፡፡
ከአልጋዋ ቀና አለችና፤
“ለምን ትረብሹኛላችሁ? ቤቱን ለመጥረግ ይሄን ያህል ትግል ምን ያስፈልጋል? አንዳችሁ ዛሬ ጥረጉ፤ አንዳችሁ ደግሞ ነገ ጥረጉ” ብላ ተመልሳ ተኛች፡፡
***
የሥራ ሥነምግባር መሰረቱ ግብረገብነት ነው፡፡ ለእናት ለአባት መታዘዝ ነው! ጥቃቅኖቹን ትዕዛዛት በማክበር ማደግ የእድገትን ቁልፍ መጨበጥ ነው፡፡
“አጓጉል ትውልድ
ያባቱን መቃብር ይንድ”
የሚባለው በዋዛ አይደለም፡፡ በጥንቱ ዘመን “ያልተቀጣ” “አሳዳጊ የበደለው!” የሚል ስድብና እርግማን ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ በምርቃትም ደረጃ “ትምህርትህን ይግለጥልህ!” ማለት የምርቃት ሁሉ ምርቃት ነው፡፡ ከወላጅ ማክበር ወደ መምህር ማክበር፤ ከዚያም ወደ አለቃ ማክበር ማደግ፤ ለአንድ ወጣት ትውልድ ትልቅ እሴት ነው፡፡ እነዚህ እሴቶች የሀገር ባህል አይናቄ መሰረቶች ናቸው፡፡ የግብረገብነት ባህል ሲያዩት ወይም ሲያወሩት ቀላል፤ ሲመረምሩት ግን ጥልቅ ነገር ነው፡፡ የትምህርት ባህል፣ የሥራ ባህል፣ የአስተዳደር ባህል፣ የፖለቲካ ባህል፣ የኮሙኒኬሽን ባህል፣ የውይይት ባህል፣ የመቻቻል ባህል… የሁሉ ነገር መሰረት ናቸው፡፡
ዴቪድ ቦህም የተባለ ፀሀፊ፡-
“…በውይይት ሂደት መንቃት በተካፋዮቹ በተሳታፊዎቹ መካከል የሚፈጠር የትርጉም መረዳዳት ፍሰት ነው፡፡ በመጀመሪያ ተሳታፊው ሁሉ የየግሉን አቋም/ጐራ ይይዝና ይሄን ብለቅ ሞቼ እገኛለሁ ይላል፡፡ እያደር ግን ከየግል ደረቅ አቋም ይልቅ የወዳጅነት ስሜት የበለጠ እንደሚሆን እየታየ ይመጣል፡፡ ምንም አይነት የወዳጅነት ቀረቤታ ሳይኖር መግባባት ብቻ ድንቅ ባህሪ ይሆናል…” ይለናል፡፡
አንዳችም ልዩና መሰረታዊ ዓላማ ከጀርባው ሳይኖር ወዳጅነትን መፍጠር መባረክ ነው፡፡ ለሀገር ለወገን የሚበጅ እፁብ ነገር ነው፡፡ ስብዕና፣ ዕውቀት፣ ምጥቀተ-ህሊና፣ የጋራ-ቤትን ማፍቀር፤ መሰረታዊ መነሻዎችና ማደጊያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ከመሰረት ከንጣፉ እኒህን ጉዳዮች ማወቅና መገንዘብ መቻሉ ደርዝ ያለው ነገር ነው፡፡ መተሳሰብ፤ መወያየት፣ ማንበብና መናበብ፣ በሥርዓት መኖር፤ የጋራ ምጥቀተ-ህሊና (Consciousness) ያስፈልገዋል - የሀገራዊነት መሰረቱ ይሄው ነውና!
ወጣቱን ሳይዙ ጉዞ ምን ተይዞ ጉዞ ነው፡፡ ወጣቱ ሲባል ደግሞ ለትምህርት ዝግጁ የሆነው፣ ለመንቃት የሚተጋው ራሱን ምንጊዜም ለመለወጥ የሚታትረው፣ አርቆ ማስተዋል ጐዳና ላይ ያለው ነው፡፡ በእርግጥ አገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ካለብን ከቤተሰብ አስተዳደግ፣ ከትምህርት ቤት መታነፅ፣ ለአካለ - ሥራ መብቃት ጋር የተሳሰረ ወጣት ይዘን መሄድ ይኖርብናል፡፡
የዕውር የድንብር አለመሄድ ትልቁ ጥበብ ነው፡፡ ወጣቱ ህይወትን የሚቃኝበት ኮምፓስ ያሻዋል፡፡ ሌሎችን የሚማርክበት ማግኔት ያለው እንዲሆንም እንጠብቃለን፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን መረጃ - የለሽ ትውልድ እንዳይፈጠር ሁሉም ዜጋ አስተዋፅዖ ሊያደርግ ይገባል፡፡
የጥበብ ዐይኑ የተከፈተ ወጣት የበለፀገ ዕይታ ይኖረዋል፡፡ በኪነጥበብ እንዲጠነክር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በቅጡ ማወቅ የአንድ ህብረተሰብ የዕድገት ምልክት ነው፡፡ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለዕለት - እንጀራ መፈለጊያ የሚበቃ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ምሉዕነት ያለው የዕውቀት ቀንዲል ለመጨበጥ እንዲነሳሳ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡
እጓለ ገብረ ዮሐንስ የተባሉ የአገራችን ደራሲ ስለአቴናውያን ሲፅፉ፤ “እሊህ አቴናውያን የነበራቸው አዲስ ነገር ለመስማትና ለመናገር መጓጓት ንጹሕ ሰብዓዊ ስሜት ነው፡፡ ወደፊት ለመራመድ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በማናቸውም የአውሮፓ ሥልጣኔ ክፍሎች ዘንድ የነሱን ማህተም ያልተሸከመ ነገር አይገኝም፡፡ ጫፉን ለመጥቀስ ያህል በሳይንስ ረገድ እነ ዲሞክሪቶስ እስከ አቶምፊዚክስ ድረስ የደረሱ ነበሩ፡፡ በፖለቲካ ድርጅት ረገድ እስከ ዲሞክራሲ የደረሱ ነበሩ፡፡ ለዚህ ሁሉ የሥልጣኔ ሀብታት መገኛ ለመሆን የቻሉት በንጹህ ሰብዓዊ ጠባይ እየተመሩ አዲሱን ነገር በመመኘት ስለዚያም በመናገርና በመስማት ነው” ይሉናል፡፡ አዲስ ነገር ለማየት የሚጓጓ ትውልድ ያስፈልገናል፡፡ ይህ ማለት ግን መነሻውን፣ ታሪኩን፣ ባህሉን፣ የዕውቀት ውርሱን በመመርመር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ “ማናቸውም የህሊና ተግባር በህገ - ምክንያት የተመሠረተ (Causalities) መሆን አለበት” ይሉናል የጠቀስናቸው ፀሐፊ፡፡
ብርሃናማ ነገ እንዲኖር ዛሬ ብርሃናማ ትውልድ የሚወራረሰው የጽሑፍም ሆነ የአፈ - ንግርት ቅርስ እንዲያፈራ፤ ምሁራን በተለይም ፀሐፍት የወጣቱን ዐይን ሊከፍቱለት ይገባል -በዚህ ረገድ የራሳቸውን መክፈልት ሊከፍሉ ይገባል፡፡ እንዲያው በደፈናው ትውልድን መራገም ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ሃዋርያና ደቀመዝሙር መሆን አለባቸውና፡፡ ተቀምጠን ከምናላዝን ተንቀሳቅሰን ለነገ ለውጥ እናምጣ ነው ጉዳዩ! “የተቀመጠች ወፍ ሆዷን ስትዳብስ የበረረች ወፍ አፏን ትዳብሳለች” ማለት ይሄው ነው፡፡  

በበርካታ ፊልሞችና የሪያሊቲ የቲቪ ፕሮግራሞች ላይ በትወና የተሳተፈችው ታዋቂዋ ኔዘርላንዳዊት ተዋናይት ላውራ ፓንቲኮሮቮ ፕላን ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ እያከናወናችው የሚገኙ ሥራዎችን ጐበኘች፡፡
“Because I’m a girl” በሚል መሪ ቃል በፕላን ኢንተርናሽናል የሚሰሩትንና የሴቶችን አቋመ በማጐልበትና ህይወታቸውን በመቀየር ላይ ትኩረት ያደጉትንና በደቡብ ክልል የተሰሩትን ሥራዎች የጐበኘችው ተዋናይቷ ባየችው ነገር እጅግ መደነቋንና ሴቶች በእውቀትና በልምድ የዳበር ሰብእና እነዲኖራቸው የሚደረገው ጥረት ሊቀጥልና ሊበረታታ የሚባው እንደሆነ ተናግግራለች፡፡
ተዋናይቷ ከትናንት በስቲያ በጁፒተር ሆቴል በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገረችው ሴቶች በእውቀት ታንፀው ሲያድጉ አቅም ያላቸው በቀላሉ የማይወድቁ በመሆኑ በዚህ ሴቶችን በማብቃቱ ተግባር ላይ የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ እንዳስደሰታት ገልፃለች፡፡
ኔዘርላንዳዊቷ ተዋሃይት ከተሳተፈችባቸው ፊልሞች መካከል X-factory, Stars dancing on ice, my dirty greasy, nasty fiancé, and I’m a star get me out of here የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡ ተዋናይ ላውራ ለአራት ቀናት በኢተዮጵያ ያደረገችውን ቆይታ አጠናቃ ከትናንት በስቲያ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡

   የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንሲስ ኦላንዴ፤ በኢቦላ የተጠቁ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራትን የጐበኙ ሲሆን ባለፈው አርብ እለት ጉብኝታቸውን የጀመሩት ከጊኒ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ 1200 ዜጐቿን በቫይረሱ ለተነጠቀችው ጊኒ፤ ቀደም ሲል በሀገራቸው መንግስት ስም 100 ሚሊዮን ዩሮ እንደለገሱና ገንዘቡም በአገሪቱ የኢቦላ ህክምና ማዕከላትን ለማቋቋም እንደዋለ ተዘግቧል፡፡ በአሁኑ ጉብኝታቸው 200 አልጋዎችንና የተንቀሳቃሽ ህክምና ማዕከል ድጋፍ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በጊኒ የተለያዩ የህክምና ጣቢያዎችን ተዘዋውረው የጐበኙ ሲሆን ከጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ጋር በሽታውን በተመለከተ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡ በኢቦላ የተጠቁ የአፍሪካ ሀገራትን በመጐብኘት የመጀመሪያው የአውሮፓ መሪ ናቸው የተባሉት ፕሬዚዳንት ኦላንዴ፤ ከጊኒው ጉብኝታቸው በኋላ በኢቦላ ወደተጠቃችው ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሀገር ወደ ሴኔጋል ተጉዘው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ስብሰባ ላይ እንደተሳተፉ ተዘግቧል፡፡
በተመሳሳይም ከስብሰባው ጐን ለጐን በጊኒ እንዳደረጉት ሁሉ በኢቦላ ጉዳይ ከሴኔጋል የጤና ሚኒስትሮችና የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር መክረዋል ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦላንዴ በሶስት ቀናት ቆይታቸው ከጊኒና ሴኔጋል በተጨማሪ ሴራሊዮንና ላይቤሪያን እንደጎበኙ ታውቋል፡፡  

“የፀሐይ ብርሃንን ጭምር ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል እንቀይራለን”

ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም ለንባብ በበቃው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዕትም ላይ፤የነፋስ ተርባይን የኤሌክትሪክ ሃይልን በተመለከተ ያወጣችሁት ዘገባ ስህተት ነው፡፡ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር የነፋስ ኃይልን ብቻ ሳይሆን የፀሐይ ብርሃንንም ወደ ኤሌክትሪክ ኢነርጂ እንቀይራለን፡፡
 በእርግጥ ከውሃና ከንፋስ ኃይል ውዱ የንፋስ ኃይል ነው፡፡ ነገር ግን ከነፋስ ሃይል ማመንጨት የጀመርነው የሃገራችንን ኢኮኖሚ ጭምር ለማልማት የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ስለሄድን ነው፡፡ በውሃ ሃብታችን እስከ 50 ሺ ሜጋ ዋት  ማልማት የምንችል ሲሆን በንፋስ ኃይላችን ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ማመንጨት እንችላለን፡፡
 ይሄን ሃብት ደረጃ በደረጃ በመጠቀማችን እንኳንስ ዜጐች፣የኛን እድገት የማይፈልጉትም ጭምር አዎንታዊ ምላሽ ላይ ተጋንኖ እንደቀረበው እየሰጡ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አገሪቱ የንፋስ ኃይል በመጠቀሟ በጋዜጣው ላይ እንደ ከሰረች ተደርጎ የቀረበው የተጋነነ ነው፡፡ እንደውም “ውዱን ሃብት ጭምር ለማልማት የቻለች፣ እያደገች ያለች ኢትዮጵያ” ብላችሁ ነው መዘገብ ያለባችሁ፡፡
በኃይል በኩል ገና ሊለማ የሚችል ብዙ ሃብት አለን፡፡ በአሁን ሰዓት 2268 ሜጋ ዋት ብቻ ነው ያለን፡፡ ከዚህ ውስጥ 171 ሜጋ ዋት የምናመርተው ከንፋስ ሲሆን በቀጣይ ሊለማ የሚችል ከውሃ እስከ 50 ሺ ሜጋ ዋት፣ ከነፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት እንዲሁም ከምድር እንፋሎት ከ10 ሺ ሜጋ ዋት በላይ እምቅ ሃብት አለን፡፡
ነገር ግን ቀደም ባሉት ዓመታት በአብዛኛው በውሃ ላይ አተኩረን የቆየነው፣ ውሃ በርካሽ የገንዘብ አቅም መልማት ስለሚችል ነው፡፡ አሁን ግን  የሃገራችን  ኢኮኖሚ በማደጉ በውሃ ላይ ጥገኛ ከምንሆን ከንፋስም ጭምር ኃይል እያመነጨን ለሃገራችን ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል እናቀርባለን፡፡ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ የመጣውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማርካት ከንፋስ ሃይል ማመንጨት የግድ ነው፡፡ ሃገሪቱ ይሄን ሃይል የመፍጠር አቅም ስላጐለበተች ነው ወደዚያ የተገባው፡፡ በመቀጠል  ደግሞ ከፀሐይ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት በዝግጅት ላይ ነን፡፡
አቶ ምስክር ነጋሽ፤
የውጭ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ
f

“ኤሌክትሪክ በየሰዓቱ ይጠፋል” በሚል ርዕስ ቅዳሜ ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም በታተመው ጋዜጣችሁ የወጣውን ፅሁፍ ከአነበብኩት በኋላ ይህንን ሃሳብ ለመሰንዘር ወደድኩኝ፡፡
ፅሁፉ ሙሉ በሙሉ ጉዳዩን የፈተሸ ባይሆንም፣ መደምደምያውም ትክክል ነው ብዬ ባላምንም እንደዚህ ዓይነት አብይ ጥያቄ ይዞ በመነሳቱ ግን አድንቄዋለሁ - በሁለት ምክንያት፡፡ በድፍረትና በተቆርቋሪነት የቀረበ በመሆኑ፣ እንዲሁም በተቻለ መጠን በመረጃ በመደገፉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ነገሮች በብዙ የስራ ዘርፎች የማይታዩ ባህሪዮች ናቸውና፡፡
ወደ አስተያየቴ ስገባ፣ በመጀመሪያ በፅሁፉ በተነሱት አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የራሴን ላክልና በመደምደሚያው ያልተስማማሁበትን ምክንያት አቀርባለሁ፡፡ ከዚያም የራሴን ለየት ያሉ መደምደሚያዎች ደግሞ አስከትላለሁ፡፡ በመሰረቱ በፅሁፉ የቀረቡ ንፅፅሮች ትክክል ናቸው፡፡ ያም ብቻ አይደለም፡፡ ንፋስ በየሰከንዱ የሚለዋወጥ ስለሆነ፣ የንፋስ ጄኔሬተሮች የሚያመነጩት ኃይል በጣም ተቀያያሪ ነው፡፡ ይህም በኦፕሬሽን ላይ ጭምር በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ አለው፡፡ ከዚህም ሌላ የንፋስ ጀነሬተሮች በሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ መግነጢሳዊ ስበታቸው ከመረቡ የተለየ ስለሆነ ለሲስተሙ ጥንካሬና (stability) በአደጋ ጊዜ ሲስተሙን ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ አያግዙም፡፡ ያም ሆኖ ግን የንፋስ ኃይል ማልማት ተቀባይነት ያገኘበት ጠንካራና አሳማኝ ምክንያቶች አሉት፡፡
በመጀመርያ የንፋስ ኃይል ለማልማት በጣም ፈጣን መሆኑ ነው፡፡ በተለይም ከውሃ ኃይል ጋር ሲነፃፀር የሚወስደው ጊዜ በጣም አጭር ነው ሊባል ይችላል፡፡ አንድን የንፋስ ኃይል ጣቢያ ለማልማት እንደ ሁኔታው ከ16-19 ወራት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩልም አንድን መካከለኛ ወይም ከፍተኛ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለማልማት ቢያንስ ቢያንስ 6 እና 8 ዓመት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የከፍተኛ ኃይል የማምረቻ ጊዜያቸው ተመጋጋቢ መሆኑ ነው፡፡ የአንዱ ምርት ዝቅ በሚልበት ወቅት የሌላኛው ምርት ከፍ ይላል፡፡ የውሃ ሃብታችን ግንቦት ወር አካባቢ ዝቅተኛ ሲሆን የንፋስ መጠኑ ደግሞ በዚህ ወር አካባቢ ይበረታል፡፡ ስለዚህም ጥሩ የሆነ የኃይል አቅርቦት ቅይጥ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም እስከ አሁን የለሙት የንፋስ ኃይል ጣቢያዎች ከከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ማእከላት በጥሩ ቅርበት መሆናቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚዘረጋው የኃይል ማስተላለፍያ መስመር ወጪ በንፅፅር አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የንፋስ ኃይል ላይ የወጣው ኢንቨስትመንት እንደ ፅሁፉ አቀራረብ ብክነት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ አገራችን በከባቢያዊ ወይም በአረንጓዴ ልማት የበኩሉዋን አስተዋፅኦ ለማድረግ የገባችው ፖለቲካዊ ቃል መረሳት የለበትም፡፡
እንደዚያም ሆኖ ፅሁፉን በበጎ በመረዳት የሚከተሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው - በሚመለከታቸው አካላት፡፡ አንደኛ፣ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው የኃይል ልማት ኢንቨስትመንት “ፖርትፎልዮ” ምን መምሰል አለበት? ይህም ማለት የንፋስ ድርሻ (ከቴክኒካዊም ሆነ ከኢኮኖሚያዊ መመዘኛዎች አንፃር) ስንት በመቶ መሆን አለበት ብሎ መወሰን ነው፡፡
ሁለተኛ፣ አሁን ያለው ጠቅላላ የሲስተሙ ኦፕሬሽን ላይ የንፋስ ኃይል ጣቢያዎች ባህሪይ ምን ይመስላል? በጠቅላላ የሲስተሙ መደላድል (stability) ላይስ ያለው ሁኔታ እንዴት ነው? የሚሉት ናቸው፡፡ ከዚህ ዋናው አርእስት ውጭ ስለ መብራት መቆራረጥ ለማንሳት ያህል ደግሞ ችግሩ በኃይል መቆራረጥ ላይ ብቻ የተወሰነ አድርጎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፡፡
 መቆራረጡ በመብራት ኃይል አጠቃላይ ሲስተም እቃዎች ላይ የማርጀት ሂደት (depreciation) ከሚገባው በላይ እንዲፋጠን እንደሚያደርግ መታወቅ አለበት፤ ተገቢው ገቢ እንዳይሰበሰብ ከማድረጉም በተጨማሪ፡፡ በብዙ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች እንዲሁም ድርጅቶች ተደጋግሞ እንደተገለፀውም፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በተወሰነ መጠን የማቀዝቀዝ ውጤቱ ሳይረሳ፣ እነዚህ ከፍተኛ ችግሮች በዘርፉና በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳይ ለመቅረፍ የኃይል ዘርፋችን የችግር አያያዝ (Crisis/Problem Management) የተዳከመበትና የተዘበራረቀበት ምክንያት ምንድን ነው? ወይም በቀላል አማርኛ ችግሮቹን በተረጋጋ እጅ ለመፍታት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

        ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት እጅግ በጣም ክፉ ሚስት የነበረችው ገበሬ ነበረ፣ ይባላል፡፡ ይህች ሚስቱ ማታ ከእርሻ ተመልሶ፣ ሞተር ቀንበሩን ሰቅሎ ገና እፎይ ሳይል እንዲህ ትለዋለች -
“መጣህ፤ በል ምግቡን አሙቀው”
“እሺ የእኔ እመቤት” ብሎ ፍቅሩን ጭምር ገልፆላት፣ወጡን ምድጃ ላይ ይጥዳል፡፡
“በል ና እግሬን ደህና አርገህ እንድታጥበኝ ውሃ አሙቅ”
“እሺ” ይልና ውሃውን ጥዶ ጣባውን ያቀርባል፡፡ ከዚያም ውሃው ሲሞቅ እግሯን ያጥባል፡፡
“በል እንጀራ ከመሶብ አውጣ፡፡ ወጡን በሳህን አቅርብ” ትለዋለች፡፡
“እሺ የእኔ ቆንጆ” ይላል፡፡ ይበላሉ፡፡
“ጀርባዬን በስብ እሽልኝ” ትለዋለች፡፡
ይሄንንም ያደርጋል፡፡
ጠዋት ቁርስ አቀራርቦ አልጋው ላይ እንዳለች ባፍ ባፏ ያጐርሳታል፡፡ ከዚያ ሞፈር ቀንበሩን አውርዶ፣ በሬዎቹን ጠምዶ ወደ እርሻው ይሄዳል፡፡
ህይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡
አንድ ቀን ባለቤቱ በድንገት ታመመች፡፡ ከላይ ከታች አጣደፋት፤ትኩሳቷ በረታ፡፡ ሌሊቱን አረፈች፡፡
አዝኖ አልቅሶ በሥርዓት አስቀበራት፡፡
ከባለቤቱ ሞት በኋላ ሚስት ሳያገባ ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡ በኋላ አገሬው ሸምግሎት ሌላ ሚስት እንዲያገባ ተደረገ፡፡
ይህቺኛዋ ሚስቱ የቀድሞዋ ሚስቱ ፍፁም ተቃራኒ ሆነች፡፡ ደግ የደግ መጨረሻ፤ ታዛዥ የታዛዥ መጨረሻ!!
“እግርሽን ልጠብሽ?”
“ምን ሲደረግ! እኔ ነኝ እንጂ እማጥብህ!”
“ምግብ ላቅርብ?”  
“ምን ሲደረግ እኔ የት ሄጄ!” ትላለች፡፡
“በይ ጀርባሽን ልሽሽ!”
“ምን ቆርጦህ እኔ ነኝ እንጂ የማሽልህ!”
ፍቅር በፍቅር ይሆናሉ፡፡
ይህ ገበሬ የዚችኛይቱ መልዐክነት በጣም ስሜቱን ነክቶት ጧት ማታ ትገርመዋለች፡፡
ታዲያ አንድ ማታ እሷ ቀድማው ተኝታለች፡፡
ፀሎቱን ሲፀልይ እንዲህ አለ፤
“አምላኬ ሆይ፤ ከዚች እጅግ ደግ ከሆነች ባለቤቴ የበለጠች የምትመጣ ከሆነ ምነው እቺም በሞተች!!”
***
Human wants are unlimited ይላል በኢኮኖሚ ንድፈ - ሀሳብ አኳያ ፋና - ወጊ ከሆኑት ሊቃውንት አንዱ የሆነው  Adam Smith (አዳም ስሚዝ)፡፡ ሰው በቃኝ አያቅም እንደ ማለት ነው - ከላይ እንዳየነው ገበሬ፡፡ የመጨረሻውን ሀብት፣ የመጨረሻውን ፍቅር፣ የመጨረሻውን ረዥም ዕድሜ ቢሰጠው በቃኝ አለማለት የሰው ልጅ ጠቅላይ - ባህሪ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ የሚስገበገቡ፤ በመመዝበር፣ በመስረቅና በመሞሰን የተካኑ ሰዎችን ማሰብ ያስደነግጣል - ይብስም ያሰጋል!
ሮበርት ግሪን የተባለው ድንቅ ፀሐፊ እንዲህ ይለናል፡-
“አንዳች የሀገር ችግር ጠሎ ጠሎ bአንድ ነጠላ ጠንካራ ግለሰብ ምክንያት የመጣ ሊሆን ይችላle፡፡ ያ ግለሰብ ዋና በጥባጭ፣ ዋና ትዕቢተኛ፣ ዋናው መልካሙን ሁሉ መራዥ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያሉትን ሰዎች የመንቀሳቀስ ዕድል ከሰጠሃቸው ብዙዎች ተከታዮችና በእነሱ ተፅዕኖ ሥር የሚወድቁ ሰዎች ተፈጠሩ ማለት ነው፡፡ በእነሱ አማካኝነት የሚባዛውንና የሚራባውን ችግር በጭራሽ ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፡፡ በጭራሽ መደራደር አያስፈልግም፡፡ የማይመለሱ፣ የማይቀለበሱ፣ የማይድኑ ናቸውና፡፡ በማራቅ ወይ በማጥፋት ብቻ ነው ተፅዕኗቸውን ማሟሸሽ ወይም መገላገል የሚቻለው፡፡ የችግሩን ሥረ መሰረት ፈልገህ ምታ፤ ከዚያ አጃቢው መንጋ ይበተናል”
እንዲህ ያሉ ሰዎች መናኸሪያ አንድም ቢሮክራሲው፣ አንድም ደግሞ የስልጣን መንበር ዙሪያ ነው፡፡ አንዱን አውራ በመፍራት አያሌ የተነካኩ ሰዎች እንዳይጠየቁ፣ እንዳይጋለጡ ማድረግ ይዘወተራል፡፡ ተጠያቂዎቹ ሰዎች ብጤዎቻቸውን በንፍቀ - ክበባቸው ስለሚኮለኩሉ የአይነኬነት ምህዋራቸውን ያሰፋሉ፡፡ ማንም እንዳይደርስባቸው አጥር ያጥራሉ፡፡ ይሄን አይነት የተተበተበ የወገናዊነት፣ የእከክልኝ ልከክልህ፣ “እኔ - እያለሁ - ማንም - አይነካህ”፣ “ማ - ባቀናው - አገር - ማን - ይኖራል?” የሚል ባህል ዋና የመሰንበቻ ሙስና ነው፡፡ ከመንጋው በፊት አውራውን ማግኘት ግድ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ የቢሮክራሲ መረብ ከአስተዳደር ብልሹነት እስከ ፖለቲካዊ ዝቅጠት መቀፍቀፊያ ኢንኩቤተር ነው፡፡ በዝምድና መስራት፣ በፖለቲካ መሞዳሞድ፣ ንፁህ መስሎ ባደባባይ መጮህ፣ የአስተሳሰብ ንቅዘት፣ በመፈክር የልብ ባዶነትን መሸፈን ወዘተ … ነቀርሳ - አከል የሀገራችን ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮች በዋሉ ባደሩ ቁጥር ማጎንቆላቸው አይቀሬ ነው፡፡ አልፈው ተርፈው መለመዳቸውና “ይሄ‘ኮ ያለ ነገር ነው!” መባላቸው በተደጋጋሚ የታየ ነገር ነው፡፡ በግለሰብ፣ በቡድን አሊያም በፓርቲ ደረጃ የዕብጠትና የማናለብኝ አባዜ ሌላው ያፈጠጠ ጦር ነው፡፡ ይህን ይዞ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ላይ ነኝ ማለት ቢያንስ ራስን ማሞኘት ነው - “እኔ ባልኩህ መንገድ ብቻ ሂድ - አለዛ …” እያሉ ዲሞክራሲ የለምና!
ሌላው አሳሳቢ ችግር በአንድ ምህዋር ላይ መሽከርከር ነው፡፡ ፎቶ - ካሜራ ዐይን ውስጥ ያለ ሰው እራሱን አያይም ይባላል፡፡ ከምህዋሩ ወጥቶ በአንድ ቅኝት የሚሽከረከረውን ሰው ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለውጥ ለማምጣት የአዘቦቱን ነገር መተውና በተለየ ዐይን ማየት (out of the box እንዲሉ) ያስፈልጋል፡፡ ከቶውንም ዐይናችንን ሳናሽ መፈፀም፣ በተግባር ማሳየት ያለብንን የዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ የፍትሕ መጓደል ጉዳይ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ነገ ዛሬ ማለት የሌለብንን የሙስናና የማጭበርበር ጉዳይ ለአፍታም ቢሆን ሳይዘገይ በግልፅ እርምጃ ወስደን ማሳየት አለብን፡፡ አለበለዚያ “ከሞትና ከህይወት የቱን ትመርጣለህ?” ቢባል፤ ሲያስብ ዘገየ፤ እንደሚባለው ይሆናል!