Administrator

Administrator

አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ ይሆናልን?
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው ሲደፍሩ ምክንያታቸው ምንድነው?
ከላይ ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ባለሙያዎች የሚሰጡት ምላሽ፡-
አስገድዶ መድፈር የፍቅር መግለጫ አይደለም፡፡ ሰዎች በሚፋቀሩበት ጊዜ አንዱ ለአንዱ ከማሰብ ውጪ አካልንና ስነልቡናን የሚጎዳ ነገር በፍጹም አይፈጽሙም፡፡
ወንዶች ሴቶችን ወይንም ሴቶች ወንዶችን አስገድደው የሚደፍሩበት ምክንያት ኃይልን ለማሳየት፣ በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም ተገዶ መደፈር እና ተመሳሳይ ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑም እንደ ብቀላ በመሳሰለው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በአዳማ ከተማ በአንድ ወንድ ልጅ ላይ የደረሰ ተገዶ መደፈርን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ የሰጡትን ሐሳብም እናስነብባችሁዋለን፡፡
የልጁ ምስክርነት የሚከተለው ነው፡፡
“...ሰውየው አብሮኝ ለነበረው ሰው እንዲህ አለው፡፡ ...ያንን ጥቁር ልጅ ሌሊት አስር ሰአት ላይ ስራ ስለአለኝ ለዛ ጉዳይ ስለምፈልገው ጥራልኝ... አለው፡፡ እኔም ላነጋግረው ስወጣ አስቀድሞ እጄን ነበር የያዘኝ፡፡ ጊዜው እኮ መሽቶአል ስለው ...ግድየለም... ዋጋ እንነጋገራለን...በለሊትም ሰው ከምንቀሰቅስ ከእኔ ጋር ብታድር ይሻልሀል አለኝ፡፡ እኔም ግድ የለም ዋጋ ንገረኝና እመለሳለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እቤቱ አስገብቶ በቃ...ልብስህን አውልቅ...ተኛ...የሚል ትእዛዝ ነው የሰጠኝ፡፡ በቃ... ስለፈራሁኝ ብቻ ልብሴን አውልቄ ተኛሁ...”
በአዳማ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ቢሮአቸው የሚገኘው የስነልቡና ባለሙያው አቶ መኮንን በለጠ የልጁን ሁኔታ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
“...የዚህ ልጅ ታሪክ... እድሜው 18 አመት ሲሆን ተወልዶ ያደገው ባሌ ሮቤ አካባቢ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ወላጅ አባት በበሽታ ምክንያት በመሞቱ ምክንያት እናትየው ካገባችው ሰው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ጋር መግባባት ስላቃተው ...ማለትም ከእንጀራ አባቱ ለተወለዱ ልጆች የሚደረገው እንክብካቤ እና ቤተሰቡ ለእርሱ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ ልዩነት ስለነበረው በበጎ ፍቃድ አሳዳጊዎች ምክንያት ወደ አዳማ መጥቶአል፡፡ ይህ ልጅ ወደ አዳማ ከመጣ ገና አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆኖአል፡፡ አስገድዶ የደፈረው ሰው የልጁን ታሪክ በማጥናት እና በማባበል ...እኔ ሆቴል አለኝ... ስራ አስገባሀለሁ... በማለት ሊያግባባው ሞክሮአል፡፡ ከዚያም ባገኘው እለት አስገድዶ ሲደፍረው ልጁ የነበረውን ጉልበት ተጠቅሞ በላዩ ላይ የተቀዳደደ ልብሱን በእጁ ይዞ ... አምልጦ ...ማመን በሚያቅት ሁኔታ ነበር ወደነበረበት የሄደው...”
ወደተጎጂው ስንመለስ የሰውየውን አባባል እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
“...እኔ እኮ ወድጄህ ነው፡፡ አፈቅርሀለሁ፡፡ ገና ሳይህ ነው ልቤ የተሸበረው... ወዘተ ሲለኝ ...እኔ እኮ ሴት አይደለሁም፡፡ ለምን ታፈቅረኛለህ... ብዬ ገፍትሬው ነው ያመለጥኩት፡፡”
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...አስገድዶ መድፈር ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው ወንድ ሴት ልጅ ላይ በሚያደርሰው ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት እንደሚስተዋለው ግን ወንድ ወንድን እንዲሁም ሴት ወንድን የሚደፍሩበት አጋጣሚ አለ፡፡”
ወንድ ለወንድ አስገድዶ መድፈር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መኮንን ቤተሰብ ይህ ነገር ሲፈጸም ቅድሚያ የሚሰጡት ሁኔታውን ለማድበስበስ እና ለመካድ እንጂ ልጆቹ የስነልቡና ድጋፍ ወይንም ፍትህ፣ ሕክምና እንዲያገኙ አይደለም፡፡ ይህ ብዙዎች የሚያደርጉት ሙከራ ሲሆን አንዳንድ ወላጆች፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ግን በፍጥነት እርምጃ የሚወስዱ መሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡  
ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ እንደሚሉት፡-
“...ብዙ ጊዜ ሬፕ (አስገድዶ መድፈር) የሚያደርጉ ሰዎች ከተመሳሳይ ጾታም ይሁን ከተቃራኒ ጾታ ባጠቃላይም ከሰዎች ጋር ጥሩ አይነት ግንኙነት መፍጠር የማይችሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ምክንያትም ከአስተዳደግ ወይንም ከተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ከሰዎች ጋር     ጥሩ የሆነ መግባባትና ግንኙነት መፍጠር የሚያቅታቸው ከሆነ እንደዚህ ያለውን (አስገድዶ መድፈር) የመሳሰለውን ወንጀል እንዲፈጽሙ ያነሳሳቸዋል፡፡”
ተገዶ መደፈር የደረሰበት ልጅ እንደገለጸው፡-
“...ድርጊቱን ፈጻሚው ሰው በህግ እንዲጠየቅ በሚደረግበት ጊዜ... እኔ እነዚህን ሰዎች ከየት እንደመጡ አላውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ድርጊትም አልፈጸምኩም፡፡ ልጁንም አልጠራሁትም ...እንዲያውም አላገኘሁትም በማለት ነበር የካደው..” ብሎአል፡፡
አቶ መኮንን እንደሚገልጹትም፡-
“...ልጁ የደረሰበት ጉዳት ከፍ ያለ ስለነበር በጊዜው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ቦታ በሚያገኝበት በዚህ ስፍራ ሲመጣ ባለሙያዎች በህግ አንጻርም ሆነ በህክምናው እንዲሁም በስነልቡናው ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኝ ጥረት አድርገዋል፡፡ አስገድዶ ደፋሪው ምንም እንኩዋን ለመካድ ቢሞክርም በወቅቱ ልጁ እራቁቱን ...የተቀዳደደውን ልብሱን በእጁ ይዞ መምጣቱ እና ሌሎች የተለያዩ መረጃዎች በመኖራቸው     እውነቱን ለማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡”
አቶ መኮንን የህግ ባለሙያዎችን እና የህብረተሰቡን ትብብር በሚመለከትም፡-
“...ፖሊሶች ለሙያቸው ስነምግባር ተገዢ መሆን እንዳለባቸው ቢያምኑም በጣም የሚያሳዝነው ግን ...አንዳንድ ፖሊሶች ለወንጀለኛው የማገዝ ነገር ይታይባቸው ነበር፡፡ ተጎጂው ባለበት ሌላም ታዛቢ በሚገኝበት ካለምንም ፍርሀት ...እኔ ዋስ ሆኜ አስወጣዋለሁ... ምንም ችግር የለም ሲሉ የተስተዋሉ ነበሩ፡፡ አስገድዶ ደፋሪው በዚህ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የሚታማ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሕግ ሳይቀርብ የቆየ መሆኑን እያወቁ እንደዚህ ያለ ንግግር በተናገሩ ላይ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቢያዝኑም በሌላ በኩል ደግሞ  ለሙያቸው ተገዢ የሆኑ ጠንካራ የፖሊስ አባላት አቃቤ ሕጎች እና ዳኞች በመኖራቸው ጉዳዩን በጥንካሬ ይዘው ከዳር በማድረሳቸው ጥፋተኛው በስምንት አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አስችለውታል፡፡ ምንም እንኩዋን ጉዳት የሚያደርሱ ባይታጡም ለትክክለኛው ስራቸው የቆሙትን በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እወዳለሁ...” ብለዋል፡፡
ሌላው አነጋጋሪው ነገር ሽምግልና ነው፡፡
ተገዶ የተደፈረው ልጅ እንደገለጸው “...የእኔ ወገኖች በሽምግልና ሲጠየቁ አይሆንም... አንቀበልም በማለት አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ ጥፋት ተደግሞ በሌላ ሰው ሊደርስ እንደማይገባ ማስተማሪያ እና ደፋሪው ሰው በህግ መጠየቁ ለተደፋሪውም የሞራል ካሳ ስለሆነ... የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም ገንዘብ እንክፈል... ሌላም ካሳ እንስጥ ሲባል... መልሳቸው አንቀበልም የሚል ስለነበር ወደህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ሆኖአል፡፡” አቶ መኮንን በዚህ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“...ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው፡፡ መድሀኒት የሚሆነው ግን ተገቢውንና በጎውን ነገር ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ግን ሰው ለሰው መድሀኒት መሆኑ ቀርቶ መርዝ ይሆናል፡፡ ሽምግልና በሰው ልጆች ዘንድ የታወቀ በጎ ባህርይ ቢሆንም አንዳድ ጊዜ የሚውልበት ቦታ ግን ጎጂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች ተገደው ሲደፈሩ አስገድዶ ደፋሪው በህግ እንዳይጠየቅ ገንዘብ እንክፈል... የሞራል ካሳ እንስጥ የሚባለው ነገር ምክንያቱ ከጥቅም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ለማንኛውም... ይህ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የስነልቡና፣ የሞራል፣ የአካል ደህንነታቸው የሚጠበቀው ጉዳት አድራሹ በሚከፍለው ገንዘብ ሳይሆን በህግ ተገቢውን ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡     እንደ አቶ መኮንን አባባል ሰው ሶስት ድህነቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡  
ሰው መንፈሳዊ ድህነትን ማሸነፍ ይገባዋል፡፡ ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ፈሪሀ እግዚአብሄር ሊያድርበት ይገባል፡፡ ልጆች ተገደው መደፈር ሲደርስባቸው ለጥፋት አድራሹ ወገንተኛ ሆኖ መቆምና ስለልጆቹ የወደፊት ሕይወት አለማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
ሰው ማህበራዊ ድህነትንም ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሰው ለገንዘብና ለጥቅም ሳይሆን  ለእውነት ተገዢ መሆን አለበት፡፡
ሰው በሶስተኛ ደረጃ ማሸነፍ ያለበት ድህነት የአእምሮ ድህነትን ነው፡፡ ሁሉም ሰው የተቻለውን ያህል እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሕይወት እራስዋ ትምህርት ቤት እንደመሆንዋ ማንኛውም ሰው እውቀት እንዲኖረው እራሱን ካዘጋጀ እውቀት ይኖረዋል፡፡
ስለዚህ ... እነዚህ ሶስቱ መበደር የማንችልባቸው ድህነቶች ሲሆኑ ተበድረን ልናሸንፍ የምንችለውን የኢኮኖሚ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ፍላጎት ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር ወይንም ወንጀልን ለመደበቅ ሙከራ ማድረግ ያስጠይቃል ...ሰው... ሽምግልናን ከአግባብ ውጪ ለመተግበር መሞከር የለበትም፡፡

ሰሞኑን  በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ በተካሄደው የእስያ ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ በስብሰባ ማዕከሉ ውስጥ ማስቲካ ሲያኝኩ መታየታቸው ቻይናውያንን ክፉኛ እንዳስቆጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ኦባማ ቤጂንግ ከደረሱበት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ፣ በወጡ በገቡ ቁጥር ማስቲካ ሲያኝኩ እንደነበር የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ይፋ መደረጋቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ የኦባማ ድርጊት የቻይናን ታዋቂ ምሁራን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን እንዳስቆጣ ጠቁሟል፡፡ኦባማ በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይ ማስቲካ ማኘካቸውን ቻይናውያን በንቀት እንደተረጎሙትና ሲና ዌቦ የተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽም፣ ኦባማን በሚተቹ አስተያየቶች መጥለቅለቁን ዘገባው ገልጧል፡፡“ገና ከመኪናቸው ሲወርዱ ጀምሮ፣ እንደ ስራ ፈት ማስቲካ እያኘኩ ነበር” ብለዋል በቢጂንግ ሲንጉሃ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ይን ሆንግ፣ ድርጊቱን በማውገዝ በጻፉት ጽሁፍ፡፡
ማስቲካ ማኘክ በአንዳንድ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት፣ እንደ ነውር እንደሚቆጠር የጠቆመው ዘገባው፣ ሲንጋፖር ማስቲካ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ የሚከለክል ህግ እንዳወጣችና በጃፓንም በስራ ላይ ማስቲካ ማኘክ ክልክል እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ቦኮ ሃራም በአንድ ቀን ብቻ 209 ትምህርት ቤቶችን አቃጥሏል
ፕሬዚዳንቱ ዳግም ከተመረጥኩ ቦኮ ሃራምንና ሙስናን አጠፋለሁ ብለዋል

          ባለፈው ሰኞና ረቡዕ  ዮቤ በተባለ የናይጀሪያ ግዛት በምትገኘው ፖቲስኩም ከተማና  ኮንታጎራ በተባለች ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤትና ኮሌጅ ላይ በአጥፍቶ ጠፊዎች በተፈጸሙ የቦንብ ፍንዳታዎች  የሞቱትን ከ52 በላይ ተማሪዎች ጨምሮ፣ በአገሪቱ ባለፉት 18 ወራት ከ255 በላይ ተማሪዎች በአሸባሪዎች እንደተገደሉ ተዘገበ፡፡የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ዜጎችን ለህልፈት በመዳረግ ላይ የሚገኘውን ቦኮ ሃራም የተባለ ቡድንና ሙስናን ከአገሪቱ ለማጥፋት በሚል ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡
የምዕራባውያን ትምህርት መቆም አለበት የሚል አቋም ይዞ የሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሃራም የተባለ የአሸባሪዎች ቡድን፣ በተለይ ካለፈው አመት ግንቦት ወር ጀምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሽብር ጥቃት መፈጸሙን አጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞና ረቡዕ የተከሰቱት ጥቃቶችም በዚሁ አሸባሪ ቡድን እንደተፈጸሙ ይገመታል ብሏል፡፡
ባለፈው ሚያዝያ ወር በቺቦክ ከተማ ወደሚገኘው ትምህርት ቤታቸው በማምራት ላይ የነበሩ 276 ናይጀሪያውያን ልጃገረዶችን የጠለፈው አሸባሪ ቡድኑ፤ በተማሪዎች ላይ ግድያ መፈጸም ከጀመረ መቆየቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ቦኮ ሃራም ከሳምንታት በፊት ካንኮ በተባለች ከተማ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በከፈተው ተኩስ፣ 13 ያህል ተማሪዎችን መግደሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ሌሎች 15 ተማሪዎችን እንደገደለም  አክሎ ገልጧል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር በዮቢ ግዛት በሚገኝ የመንግስት ኮሌጅ ላይ ባደረሰው ጥቃት 59 ተማሪዎች መሞታቸውን፤ በመስከረም ወር ላይ በግብርና ማሰልጠኛ ተቋም 44 ተማሪዎችንና መምህራንን መግደሉን፤ በሃምሌ ወር በማሙዱ ከተማ አዳሪ ትምህርት ቤት ባደረሰው ጥቃት 29 ተማሪዎችና መምህራን መሞታቸውን አስታውሷል፡፡ ቦኮ ሃራም ባለፈው ወር፣ 209 ትምህርት ቤቶችን ማቃጠሉንና በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የንብረት ውድመት መፈጸሙን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ለቦኮ ሃራም ጥቃት ተገቢውን ምላሽ አልሰጡም በሚል በዜጎቻቸው እየተተቹ ያሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን በበኩላቸው፤ ቦኮ ሃራምንና ሙስናን ከአገሪቱ የማጥፋት አላማቸውን ከግብ ለማድረስ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ አገሪቱንና ዜጎቿን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል ያሉት ጆናታን፣ ከተመረጡ ቡድኑ ያገታቸውን ልጃገረዶች እንደሚያስለቅቁና የሽብር ሰንሰለቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚበጣጥሱ ቃል ገብተዋል፡፡

ረጅም አመታት በውጭ አገራት ያሳለፈው ገጣሚ ሃይሉ ገ/ዮሃንስ (ጎሞራው)፤ ባደረበት ህመም በሚኖርባት ስዊድን በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ በተወለደ በ79 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡እ.ኤ.አ በ1935 በአዲስ አበባ የተወለደው ሃይሉ፤ የቤተክህነት ትምህርት እየተከታተለ ያደገ ሲሆን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከተማረ በኋላ፣ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የስነ መለኮት ትምህርት ተከታትሏል፡፡
በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ተቋም ገብቶ የተማረው ገሞራው፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው በግዕዝ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተለያዩ የስነጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ ታዋቂነትን አትርፏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ይካሄድ በነበረ የግጥም ውድድር ላይ ባሸነፈበት “በረከተ መርገም” የተሰኘ ግጥሙም  ይታወቃል፡፡ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት ይካፈል የነበረው ገጣሚው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከዩኒቨርሲቲው ተባርሯል፡፡
በ1957 ዓ.ም የጻፈው “በረከተ መርገም” የተሰኘ ግጥሙ በ1966 ዓ.ም የታተመለት ሲሆን በ1980 ዓ.ም በስዊድን በድጋሚ ታትሞለታል፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ለንባብ ባበቃው “አንድነት” የሚል አነስተኛ መጽሃፍ ሳቢያ ለእስር የተዳረገው ሃይሉ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በቴክኒክና በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች በመምህርነት አገልግሏል፡፡
ወደ ቻይና በማምራትም በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ የቻይናን ስነጽሁፍ ያጠና ሲሆን የቻይንኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላትና የቻይንኛ-እንግሊዝኛ የሃረጋት መጽሃፍ አዘጋጅቷል፡፡ ወደ ኖርዌይ ሄዶ የፖለቲካ ጥገኝነት ካገኘ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ቆይቶ ወደ ስዊድን በመጓዝ ኑሮውን በስቶክሆልም አድርጎ ቆይቷል፡፡

ኮንቲኔንታል የተባለው ታዋቂ የአሜሪካ ነዳጅ አምራች ኩባንያ ባለቤት ባለጸጋው ሃርሎድ ሃም፤ ከ26 አመታት በፊት ከባለቤታቸው ሲ አን ሃም ጋር የመሰረቱትን ትዳር በፍቺ በማፍረሳቸው፣ ለቀድሞ ሚስታቸው  የ1 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ መወሰኑን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡በጥንዶቹ መካከል ሊታረቅ የማይችል ቅራኔ  መኖሩ ለፍቺው ምክንያት እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤  ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት በሃርሎድ ሃም ላይ የ1 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ቅጣት እንደጣለባቸው  አመልክቷል፡፡
የባልና ሚስቱ ፍቺ በአለማችን ታሪክ ከፍተኛ የካሳ ክፍያ የሚፈጸምበት እንደሚሆን  የገለጸው ዘገባው፤ የ68 አመቱ ባለጸጋ የ20.2 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያካበቱ ቢሊየነር መሆናቸውን  ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ የካሳውን አንድ ሶስተኛ በመጪው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲከፍሉና፣ ቀሪውን ቢያንስ በየወሩ 7 ሚሊዮን ዶላር እየከፈሉ በሂደት እንዲያጠናቅቁ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ጥንዶቹ በትዳራቸው ሁለት ሴት ልጆችን እንዳፈሩ ዘገባው አስታውሷል፡፡

Saturday, 15 November 2014 10:38

አስገራሚ የቃላት ፍቺዎች

ብልጥ
ድንገት ወንዝ ውስጥ ቢወድቅ፣ በዚያው ገላውን ታጥቦ የሚወጣ ሰው
ፀጥታ
የመጀመሪያው ልጅ ከመወለዱ በፊትና የመጨረሻው ልጅ ትዳር ይዞ፣ከወላጆቹ ቤት ሲወጣ ብቻ  የሚገኝ  
ግብዣ
ለሴቶች - ከሌሎች ተጋባዥ ሴቶች የተሻለ አምሮና  ተውቦ ለመታየት የሚፎካከሩበት
ለወንዶች - ምግብ በጥራትና በገፍ የሚገኝበት መልካም  አጋጣሚ
ሻይ ቡና
ለሴቶች - ሻይ ቡና
ለወንዶች - ቁርጥ፣ ወይን ጠጅና ቢራ
ሃያሲ
እንደ እበት ትል ከሌሎች ቆሻሻ ላይ እንጀራውን የሚያገኝ    

ከ1ሚ. በላይ ህዝብ ተኝቶ መታከም በሚያስፈልገው የአዕምሮ ህመም ይሰቃያል
በአዕምሮ ህሙማን ህክምና ማዕከል ያሉት አልጋዎች ከ700 አይበልጡም


በርካታ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር እንደገጠማቸው የሚጠቁሙ ምልክቶች ቢታይባቸውም ታማሚነታቸውን አምነው ለመቀበልና ለችግራቸው መፍትሄ ለመፈለግ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ አዕምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት ሊዳረግና የተለመደ ተግባሩን መወጣት ሊሳነው ይችላል፡፡ ለአዕምሮ መታወክ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ስነ ልቦናዊ ውጥረቶች፣ ስደት፣ ጦርነት፣ ተገዶ መደፈር፣ አደንዛዥ እፆች፣ የመኪና አደጋ፣ ኢንፌክሽን አምጪ በሽታዎችን አለመቆጣጠር፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪዎችን የሚያማክሩ የስነ ልቦና ባለሙያዎች አለመኖር… ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በአዳማ ከተማ “Media and Mental Illness” በሚል ርዕስ ወርክሾፕ አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ  የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች እንደሚያመለክቱት፤ የአዕምሮ ጤና ችግር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን  ስቃይና ሞት ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡ በወርክሾፑ ላይ ጥናታቸውን ካቀረቡት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአዕምሮ ሀኪምና በዩኒቨርሲቲው የአዕምሮ ህክምና ክፍል መምህር፣ ዶ/ር መስፍን አርአያን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ፤ በአዕምሮ ጤና ችግር ዙርያ አነጋግራቸዋለች፡፡የአዕምሮ ጤና ችግር ስንል ምን ማለታችን ነው?
የአዕምሮ ጤና ችግርን በሶስት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ ቀላል፣ መካከለኛና ከባድ ወይም በፈረንጅኛው ሳይኮሲስ የሚባለው ማለት ነው፡፡ ችግሮቹ እንደየሁኔታው የህክምና እርዳታ ሊደረግላቸው ይችላል፡፡ ቀላል የአዕምሮ ጤና ችግር የምንለው በተለያዩ ምክንያቶች አዕምሮአችን ሲወጣጠርና ሲጨነቅ የሚከሰት ሲሆን ይህ ችግር በከተማም ሆነ በገጠር ይስተዋላል፡፡ በዕለት ተዕለት ህይወታችን በሚገጥሙን ነገሮች ስንጨናነቅ ሊከሰት የሚችል ችግርም ነው፡፡ ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን በሚገባ ስለሚያውቁ ወደ ሀኪም ሔደው የህክምና እርዳታ ለመጠየቅ የሚችሉ ናቸው፡፡
መካከለኛ የአዕምሮ ጤና ችግር የምንለው ደግሞ የስሜት መዋዠቅ ይታይባቸዋል፡፡ አንድ ወቅት ድብርት ውስጥ ይገባሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተቃራኒው ይሆናሉ፡፡ እነዚህ በሁለት አይነት የአዕምሮ ጤና ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች፤ በአንድ አገር እስከ 20 በመቶ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ቁጥራቸው ከ25-40 በመቶ ሊደርስም ይችላል፡፡ ትንሹን እንኳን ወስደን በአገራችን ያለውን ሁኔታ ብናየው፣ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ቢያንስ 18 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ በቀላልና መካከለኛ የአዕምሮ ጤና ችግር የሚጠቃ ነው፡፡ ከባዱና ሳይኮሲስ እየተባለ በሚጠራው የአዕምሮ ጤና ችግር የተጠቁ ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ሆኖ እይታቸው፣ አመለካከትና የአስተሳሰብ ባህርያቸው ሲዛባ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ለሌሎች የማይታይን ነገር ማየት፣ ሌሎች የማይሰሙትን ድምፅ መስማት … አይነት ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የባህርይ ለውጥም ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ኬጂቢ ቦንብ ጠምዶ እየተከታተለኝ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ያን ግዜም ራሳቸውን ለመከላከል በሚወስዱት እርምጃ በሌሎች ሰዎች ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና ችግር ከምንላቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ድብርት ነው፡፡ ድብርት መዳን የሚችል ህመም ሲሆን በአግባቡ ካልታከመ ህይወትን የሚያሳጣ አደገኛ ችግር ነው፡፡ በዚህ ሳይኮሲስ እያልን በምንጠራው አደገኛ የአዕምሮ የጤና ችግር የተጠቁ ሰዎች በሆስፒታል ውስጥ ተገኝተው የቅርብ ክትትልና እርዳታ ማግኘት የሚገባቸው ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገራችን 1.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በከፍተኛ የአእምሮ ጤና ችግር እየተሰቃዩ ነው፡፡ ዛሬውኑ ተኝቶ መታከም፣ ዛሬውኑ መድኀኒትና መርፌ ማግኘት፣ ዛሬውኑ የምክር ህክምና ማግኘት የሚገባቸው ናቸው፡፡
ለአዕምሮ ጤና ችግር ዋንኛ መንስኤዎች ተብለው የሚጠቀሱት ምንድናቸው?
ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ውጥረቶች፣ ተገዶ መደፈርና አደንዛዥ እፆችን መጠቀም ዋንኞቹ ብለን ልንጠራቸው እንችላለን፡፡ እነዚህ ነገሮች የአዕምሮ ጤና ችግር ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተረፈ ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር በገጠማቸው ጊዜ ወደ ህክምና ተቋማት ሄዶ እርዳታ ማግኘት አለመፈለጋቸው በቀላሉ ሊድን የሚችለውን ችግር ውስብስብና አደገኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡
አብዛኛው የአዕምሮ በሽተኛ በየቤቱና በየፀበሉ ታስሮ ነው ያለው፡፡ ጥቂቱ ደግሞ በየመንገዱና በየጎዳናው እየዞረ ነው፡፡ እነዚህ ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው እርዳታ ማግኘት ቢችሉ ችግሩን ለማቃለል ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ህሙማኑ ወደ ህክምና ተቋማት ቢሄዱ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ይችላሉ? በአገራችን ምን ያህል ተቋማትስ አሉ?
በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች የህክምና ተቋማት አሉ፡፡ ለአዕምሮ ጤና ችግር ህክምና የሚሰጡ ማለት ነው፡፡ አስተኝቶ ለማከም ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ በአጠቃላይ የግሉንም፣ ወታደራዊ የህክምና ተቋማትን ጨምሮ ከ700 የማይበልጡ አልጋዎች ናቸው ያሉን፡፡ ይህ ደግሞ ከችግሩ አንፃር ኢምንት ነው፡፡ ስለዚህም ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ የሚገባን መከላከሉ ላይ ነው፡፡ ያለበለዚያ ውጤት የለውም፡፡ እኛ ሃኪሞች ወደ ህክምና ተቋማት የመጡልንን ጥቂት ዕድለኞች ማከም ላይ ብቻ ተወስነን መቅረት አይገባንም፡፡ ሁላችንም መከላከሉ ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል፡፡

Saturday, 15 November 2014 11:00

ኢቦላ - የዛሬ 38 ዓመት

ቤልጂየማዊው ፒተር ፒዮ የኢቦላ ቫይረስን ለመጀመሪያ ጊዜ ከመረመሩና ለቫይረሱም ስያሜ ከሰጡ ሳይንቲስቶች አንዱ ነው፡፡ በቅርቡ  ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የሰጠውን ቃለመጠይቅ ለጋዜጣው በሚመች መልኩ አቅርበነዋል መልካም ንባብ፡፡
“እሼ እዛው ነዋሪ ገበሬ ነው፡፡ ሞቅ ይለዋል! አንዱ ገንዘብ ሰጥቶ ምግብ በሳህን አርጎ ሂድ ወደሚስትህ ይለዋል፡፡
ይሄዳል፡፡ ግን በጨለማ በቀጭኑ ድንጋያማ የዘሙቴ መንገድ ሲሄድ ገንዘቡ ይጠፋዋል፡፡ ሳህኑን መሬት አስቀምጦ ገንዘብ
ፍለጋ ይመለሳል፡፡ ገንዘቡ የለም፡፡


ያኔ የኢቦላ ቫይረስ እንዴት እንደታወቀ ንገረኝ?
እ.ኤ.አ በ1976 በመስከረም ወር በአንዱ ቀን የሳቤና አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪ የነበረ ሰው በወቅቱ ዛየር በሚባለው በአሁኑ አጠራር ኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከሚገኝ አንድ ሃኪም በጥንቃቄ የተላከ የደም ናሙና ወደ ቤልጂየም ይዞልን መጣ፡፡ የደም ናሙናው በዛየር ያምቡኩ በተባለ ቦታ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ከነበሩ የቤልጂየም መነኮሳት የኣንዷ ነበር፡፡ መነኩሲቷ በማይታወቅ ህመም እየተሰቃየች የነበረ ሲሆን የደም ናሙናው ሲላክልንም ቢጫ ወባ ሊሆን ይችላል በሚል ግምት ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ የሚካሄደው እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነው፡፡ ያኔ እንዴት ነበር?
ቫይረሱ ምን ያህል አደገኛ እንደነበር አናውቅም ነበር፡፡ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሰራበት ላቦራቶሪም ቤልጂየም ውስጥ አልነበረም፡፡ የምንሰራው የተለመደውን ነጭ ጋውንና ጓንት አድርገን ነበር፡፡
የመነኩሲቷ የደም ናሙና ከቢጫ ወባ ጋር ግንኙነት ነበረው?
አልነበረውም፡፡ ህመሟ ከቢጫ ወባና ከታይፎይድ ጋር ግንኙነት ከሌለው ምን ሊሆን ይችላል በሚል ጥረታችንን ቀጠልን፡፡ ከተላከው ናሙና ላይ ቫይረሱን ለመለየት አይጦችንና ሌሎች የላብራቶሪ እንስሳቶችን ወጋናቸው፡፡ ለብዙ ቀናት በእንስሳቶቹ ላይ ምንም አይነት ለውጥ ስላላየን ምናልባት ናሙናው ሲመጣ በቅዝቃዜ እጦት ተጎድቶ ሊሆን ይችላል ብለን አስበን ነበር፡፡ በኋላ ግን እንስሳቱ ተራ በተራ መሞት ሲጀምሩ ናሙናው ገዳይ ነገር እንዳለው አረጋገጥን፡፡
ከዚያስ ምን አደረጋችሁ?
በትንሽ ጊዜ ውስጥ ሌላ የመነኩሲቷን ደም የያዘ ናሙና መጥቶልን በኤሌክትሮን ማይክሮስኮፕ ለመመርመር ስንዘጋጅ፣ የአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ናሙናውን ከፍተኛ ጥንቃቄ ወዳለበት እንግሊዝ ወደሚገኝ ላቦራቶሪ እንድንልከው መመሪያ ሰጠን፡፡ ነገር ግን አለቃዬ የፈለገው ነገር ቢሆን ስራችንን ማጠቃለል አለብን ብሎ ስላመነ ናሙናውን አልላክነውም፡፡ በወቅቱ አለቃዬ ናሙናውን ለመመርመር ሲቀበል እጁ በጣም ይንቀጠቀጥ ስለነበር፣ ከናሙናው ወደ መሬትና ወደ አንዱ ባልደረባችን እግር ላይ  ፈስሶ ነበር፡፡ ሆኖም ጓደኛችን ጠንካራ ቆዳ ጫማ አድርጎ ስለነበር ምንም አልተፈጠረም፡፡
በመጨረሻ የቫይረሱን ምንነት አወቃችሁ?
አዎ፡፡ ለመመርመር ብዙ ጊዜ የፈጀበን ቫይረስ ትልቅና ረዘም ያለ መስሎን ነበር፡፡ ቫይረሱ ከቢጫ ወባ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ይልቁንም በ1960ዎቹ  ጀርመን ማርበርግ ውስጥ ብዙ የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ህይወት ከቀጠፈው ማርበርግ ቫይረስ ጋር የሚመሳሰል ነበር፡፡
ስጋት አልፈጠረባችሁም ነበር?
ስለ ማርበርግ ቫይረስ ምንም አላውቅም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተማሪዎቼን ስለዚያ ወቅት ስነግራቸው ስለ ድንጋይ ዘመን የማወራላቸው ይመስላቸዋል፡፡ ላይብረሪ ሄጄ የቫይሮሎጂ አትላስ ላይ ማየት ነበረብኝ፡፡
የእኛ ውጤት በታወቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲዲሲ ባወጣው መረጃ ማርበርግ እንዳልሆነ ነገር ግን ተመሳሳይነት ያለው ቫይረስ እንደሆነ ገለፀ፡፡ በወቅቱ ያምቡኩና በአቅራቢያ ባሉ ቦታዎች ብዙ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ነበር፡፡
ወደ ዛየር ከሄዱት ሳይንቲስቶችም አንዱ ነበርክ አይደል?
አዎ፡፡ የሞተችውን መነኩሲት ጨምሮ ትንሽ ሆስፒታል ከፍተው ይሰሩ የነበሩት ቤልጂየሞች ስለነበሩ የቤልጂየም መንግስት ባለሙያ ለመላክ ሲወስን ወዲያው ፈቃደኝነቴን ገለፅኩ፡፡ ያኔ 27 አመቴ ነው፡፡ የወጣትነት ዘመን ጀብድ በለው፡፡
እንዴት ደፈርክ?
ከዚህ በፊት በአለም ያልታየ ገዳይ በሽታ የምናክም ቢሆንም ቫይረሱ ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች እንደሚተላለፍ አናውቅም ነበር፡፡ ጋውንና ጓንት እንዲሁም ሞተርሳይክል አሽከርካሪዎች የሚያደርጉትን መነፅር ብቻ ነበር የምንጠቀመው፡፡ ኪንሻሳ የገዛሁትን የጋዝ ማስክ ደግሞ በሙቀቱ ምክንያት ማድረግ አልችልም ነበር፡፡ ያስፈራኝ የነበረው ነገር የደም ናሙና ስወስድ የደም ንክኪ ተፈጥሮ በበሽታው እንዳልያዝ ነበር፡፡
ግን በበሽታው ከመያዝ  አመለጥክ?
አዎ፡፡ በእርግጥ በአንድ አጋጣሚ ከፍተኛ ትኩሳት ፣ የራስ ምታትና ተቅማጥ ይዞኝ በቃ ተያዝኩ ብዬ ከክፍሌ ሳልወጣ፣ ለቀናት እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር አሳልፌያለሁ፡፡ በኋላ ግን እየተሻለኝ መጣ፣ የታመምኩት በጨጓራ ኢንፌክሽን ነበር፡፡ በህይወት ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች የተሻለው ነው፡፡ ሞት ሲመጣ በአይንህ ታየዋለህ፤ ነገር ግን ለመዳን እድል አለ፡፡
ለቫይረሱ ስያሜ ከሰጡት ተመራማሪዎች አንዱ አንተ ነህ፡፡ ለምን ኢቦላ ተባለ?
ስያሜው በተሰጠበት ምሽት የተመራማሪ ቡድኑ አንድ ላይ እየተወያየ ነበር፡፡ ቫይረሱ በተከሰተበት በያምቡኩ መሰየሙ ቦታውን እስከ ወዲያኛው ያገለዋል ብለን አመንን፡፡ እናም አሜሪካዊው የቡድኑ መሪ  በአቅራቢያችን በሚገኘው ወንዝ ይሰየም አለ - ፊትለታችን ከተንጠለጠለው ካርታ ላይ የኢቦላን ወንዝ ተመልክቶ፡፡ ነገር ግን የተሰቀለው ካርታ ትንሽና የተዛቡ ነገሮች ነበሩበት፡፡ ኢቦላም በአቅራቢያ የሚገኝ ወንዝ እንዳልሆነ ብናረጋግጥም ስያሜው ግን ኢቦላ እንደሆነ ቀረ፡፡
ለቫይረሱ መዛመት የቤልጂየም መነኩሲቶች ድርሻ አለበት ይባላል...
በወቅቱ መነኩሲቶቹ በሚሰሩበት ሆስፒታል ለነፍሰጡር ሴቶች የቫይታሚን ክትባት ይሰጡ ነበር፤ ነገር ግን የመርፌው ንፅህና የተጠበቀ አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ነፍሰጡሮች በቫይረሱ እንዲያዙ አድርገዋል፡፡ በቅርቡ በምእራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ሆስፒታሎች የመጀመሪያውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
ከያምቡኩ በኋላ ላለፉት ሰላሳ አመታት ኤድስ ላይ አተኩረህ ሰርተሃል፡፡ ኢቦላ አሁን አዲስ ስጋት ሆኗል፡፡ የአሜሪካን ሳይንቲስቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው ሊጠቁ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ወረርሽኙ በዚህ ደረጃ ትጠብቀው ነበር?
በፍፁም አልነበረም፡፡ እንዲያውም ተቃራኒ ነበር፡፡
ኢቦላ እንደ ወባና ኤድስ ችግር ፈጣሪ አልነበረም፤ ምክንያቱም ሲከሰት የነበረው በጣም በተወሰኑ ገጠራማ አካባቢዎች ነው፡፡ ባለፈው ሰኔ ወደ ትላልቅ ከተሞች መግባቱን ስሰማ ከወትሮው የተለየ ነገር እንደተፈጠረ ገባኝ፡፡ በተመሳሳይ ወር የድንበር የለሹ የሀኪሞች ቡድን ስጋቱን ከገለፀ በኋላ እጅግ አሳሰበኝ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ምላሹን የሰጠው ዘግይቶ ነው፡፡ ለምንድን ነው?
በአንድ በኩል የድርጅቱ የአፍሪካ ቢሮ ብቃት ባላቸው ሳይሆን በፖለቲካ ሹመኞች የተሞላ ነው፡፡
በሌላ በኩል ጄኔቫ ያለው የድርጅቱ ዋና ቢሮ በበጀት ቅነሳ ምክንያት ችግር ያለበት ሲሆን በተለይ ደግሞ የድንገተኛ ወረርሽኞች ዲፓርትመንቱ በጣም የተዳከመ ነው የተዳከመ ነው የተጎዳ ነው፡፡ ከነሐሴ ወር በኋላ ግን ድርጅቱ የመሪነት ሚናውን መጫወት ጀምሯል፡፡
በዛየር የመጀመሪያው ወረርሽኝ ሲከሰት የሆስፒታሎች የንፅህና መጓደል አስተዋፅኦ አድርጎ ነበር፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ነገር ነው ያለው፡፡ ሉዊ ፓስተር “ሁሉም ነገር ያለው ባክቴሪያና ቫይረስ ላይ ነው” ብሎ ነበር፡፡ በዚህ ትስማማለህ?  
በጣም እስማማለሁ! ኤችአይቪ አሁንም አለ፡፡ ለንደን ውስጥ ብቻ በቀን አምስት ግብረሰዶማውያን በቫይረሱ ይያዛሉ፡፡ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ባክቴሪያዎች መድሀኒት የመቋቋም አቅማቸው እየጨመረ ነው፡፡ በባክቴሪያና በቫይረስ ላይ አሸናፊነትን ለመቀዳጀት ገና ብዙ ይቀረናል፡፡
 በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እውነት ብዙ እንድሰራ ያበረታታኛል፡፡ ለዚህም ነው በአለም ላይ ያሉ ሀያላን ለምእራብ አፍሪካ አገራት በቂ እርዳታ እንዲያደርጉ የተቻለኝን እያደረግሁ ያለሁት፡፡

በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዓለም ስጋት በሆነው ኢቦላ ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት የፊታችን ረቡዕ በግዮን ሆቴል ይካሄዳል፡፡
 የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ህዝባዊ ወይይት ላይ የኢቦላ ቫይረስ ምንነትና የመተላለፊያ መንገዶቹ እንዲሁም ስርጭቱ፣ ምልክቶቹ፣ የመጋለጫ መንገዶችና የቁጥጥር ዘዴዎቹን አስመልክቶ የጤና ባለሙያዎች ገለፃ እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡
የምዕራብ አፍሪካ አገራትን በተለይ ላይቤሪያና ሴራሊዮንን ክፉኛ ያጠቃው የኢቦላ ቫይረስ ወደ አገራችን እንዳልገባ ያስታወቀው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ  ላይ በሰዓት 1ሺ ሰዎችን መመርመር የሚያስችል ዘመናዊ መሣሪያ እንደተከተለና በድንበሮች አካባቢም ባለሙያዎች መድቦ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

ቁርስ አለመመገብ
ቁርሳቸውን የማይመገቡ ሰዎች በደማቸው ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ይህም ለአንጎል መድረስ ያለበትን ንጥረ ነገር በማስቀረት አንጎል በተገቢው ሁኔታ እንዳይሰራ ያደርገዋል፡፡
ከመጠን በላይ መመገብ
ከመጠን በላይ መመገብ የአንጎል የደም መተላለፊያ ቧንቧዎችን ያደድራቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአዕምሮን ኃይል ይቀንሳል፡፡
ማጨስ
ሲጋራ ወይንም ሌሎች አደገኛ ዕፆችን ማጨስ በርካታ የአንጐል ችግሮችን ከማስከተሉም ሌላ አልዚመር ለተባለ የአዕምሮ ህመም ሊያጋልጥም ይችላል፡፡
ከፍተኛ የስኳር ፍጆታ
ከፍተኛ የስኳር ፍጆታ፤ አንጎል ፕሮቲኖችንና የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳያውል ያሰናክላል፡፡ ይህም አንጎል አስፈላጊ ንጥረነገሮች እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡
 ጭንቅላትን ተሸፋፍኖ መተኛት
በመኝታ ሰዓት ጭንቅላትን በአንሶላ፣ በፎጣ ወይም በብርድልብስ ተሸፋፍኖ መተኛት የካርቦንዳይኦክሳይድ ክምችትን ይፈጥራል፡፡ ይህም በአንጎላችን ውስጥ ያለውን የኦክስጅን ክምችት ይቀንሳል፡፡ በዚህ ምክንያትም አንጎላችን ለአደጋ ይጋለጣል፡፡