Administrator

Administrator

 አንድ ብልህ ንጉስ በከተማው ውስጥ ሦስት አዋቂዎች ነን እያሉ ህዝቡን ይመክራሉ፤ ያወናብዳሉ የሚባሉ ሰዎችን በተራ በተራ ጠርቶ ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፡፡
የመጀመሪያው አዋቂ እንደገባ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡-
“ህዝቡ ይውረድ ይውረድ እያለ እያስቸገረኝ ነው፡፡ እኔ ግን በስልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ፡፡ ምን ባደርግ ይሻላል?”
አንደኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ እርሶን የመሰለ ደግ ንጉስ ይውረድ ያለ ህዝብ ከእንግዲህ ሊታመን አይገባውም፡፡ ይልቁንም ሊቀጣ ይገባዋል፤ ስለዚህ ለመቀጣጫ ከህዝቡ መካከል ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን በአደባባይ ይቅጧቸው፡፡ ያኔ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” ሲል መለሰ፡፡
ሁለተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቡ ያላንተ መኖር አንችልም፤ ለዘላለም ቆይልን እያለ አስቸገረኝ፡፡ እኔ ግን ስልጣኔን ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ ኑርልን የሚለኝ እውነቱን ይሁን ውሸቱን ለማወቅ ተቸግሬያለሁ፤ ምን ትመክረኛለህ?”
ሁለተኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ ይህን ህዝብ አይመኑት፤ ይኑሩልን ሲል ይሙቱ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማወቅ ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን አስጠርተው በአደባባይ ቢቀጡ ማታለሉን ትቶ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” አለ፡፡
በመጨረሻም ሦስተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቤ ይውረድም አይለኝም፡፡ ይኑርም አይለኝም፡፡ ዝም ብሎ እየተገዛ ነው፡፡ የልቡን ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሦስተኛው አዋቂም፤
“ይህን ህዝብ አይመኑት፡፡ ይኸኔ ሴራ እየጎነጎነ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ተጠሪ ናቸው የሚባሉትን ሽማግሌዎች አስጠርተው ሸንጎ ፊት ቢያስገርፏቸው የተዶለተችው በሙሉ ትጋለጣለች፡፡”
ከዚህ በኋላ ንጉሱ ህዝቡ እንዲጠራ አዋጅ አስነገረና፤ ህዝብ ሲሰበሰብ እንዲህ አለ፤
“እነዚህን ሦስት አዋቂዎች አስጠርቼ ህዝቡ ይጠላኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ ይወደኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ መውደዱንም መጥላቱንም አልነግር አለኝ ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ምን ታስባላችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ህዝቡም መክሮ ሲያበቃ በተወካዩ በኩል መልስ ሰጠ፡፡ ተወካዩ የአገር ሽማግሌ፤
“ንጉስ ሆይ፤ ከህዝቡ ጋር ስንመክር አንድ እልባት ላይ ደረስን፡፡ እነዚህ ሦስት አዋቂዎች በተለያየ ጊዜ ስለ እርሶ ጠይቀናቸው የመለሱልን መልስ ’ንጉሱን አትመኗቸው’ የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም በወዲህም ወገን በወዲያም ወገን፤ መተማመን እንዲጠፋ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሊቀጡልን ይገባል” አሉ፡፡
ንጉሱም፤
“እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ፤ ስለሆነም ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ያም ሆኖ ለእናንተ አንድ ምክር ልምከራችሁ፡፡ ሁልጊዜ ተነጋገሩ፡፡ ተመካከሩ፡፡ ግልፅ ሁኑ፡፡ ጥፋት ስታገኙ ጥፋተኛውን ቅጡ፤ ንጉስ ያልፋል መንግስት ይለወጣል፤ ሁሌም ነዋሪው ህዝብ ነው” ሲል ነገራቸው፡፡
***
ብልህ ንጉስ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የአገር አዋቂዎች ማጣት መረገም ነው፡፡ የሚመካከር ህዝብ መላ ያገኛል፡፡ ችግሩን የማይፈታ ህዝብ በሽታውን እንደደበቀ ህመምተኛ ነው፡፡ ግልፅነት ሲኖር እውነት ወደ አደባባይ ትወጣለች፡፡ ግልፅነት ከመሪዎችም፣ ከምሁራንም፣ ከህዝብም የሚጠበቅ ፍቱን ወርቅ ነው፡፡ ግልፅነት ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ ከሆነ ሌላውን ወገን መሸፈኛ፣ የተንኮል ጭምብል ይሆናል እና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ግልፅነት አለቃ ምንዝሩ የሚተችበት መሳሪያ ብቻ ተደርጎ አንዱን ንፁህ፣ አንዱን አዳፋ፣ አንዱን ቀና፣ ሌላውን ጎልዳፋ ብሎ ለመፈረጅ፤ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ ግልፅነት ሁሉም ላይ የሚሰራ፣ ለሁሉም የሚያገለግል መርህ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
ግልፅነት ከብልጥነት መለየት አለበት፡፡ ግልፅ ነኝ ማለት ድብቅነትን መሸፋፈኛ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አዋቂ ሳይሆኑ የወቅቱን መፈክር በማንበብ ብቻ አዋቂ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት አይደለም፡፡ ከስህተት ሳይማሩ ከስህተት የተማሩ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት ከቶ አይደለም፡፡ በአፍ ቅቤ፣ በልብ ጩቤ ይዞ መቅረብ ግልፅነት አይደለም፡፡ “ብቅል ለመበደር የምትሄድ ብቅል ያላስቀመጠችውን ምን ሴት ትባላለች! ትላለች” እንዲሉ፤ አንዱ ካንዱ ላይሻል ነገር፣ ጥፋተኛ እራሱን እንከን-የለሽ አድርጎ ሌላውን ጥፋተኛ ሲወቅስ፤ ያኛውን አጋልጦ እራሱን ሸሽጓል እና ግልፅነት እሱ ዘንድ የለም፡፡ የግልፅነት ስርአት ሁሉን-አቀፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእሙናዊው ተግባር የፈለቀ መሆን አለበት፡፡ ግልፅነት ከሁሉ አስቀድሞ እውነተኝነት መጠየቁ ለዚህ ነው፡፡
የአስተዳደግ ጉድለት፤ የአስተዳደር ጉድለትን ያስከትላል፡፡ እራሱ በወጉ ሀላፊነት ያልተረከበ፣ እራሱ እድገቱን ያላግባብ የወሰደ፤ እራሱ ሹመቱን በኢርትኡ መንገድ የነጠቀ ሰው ስርአት ያለው አስተዳደር ለማስፈን ይቸግረዋል፡፡ ይልቁንም “ብልጥ ሌባ የቆጮ መቁረጫ ትሰርቃለች” እንደሚባለው፤ ከቆጮውም ይልቅ መቁረጫውን ይዟልና ህግ አውጭውም፣ ፈራጅም፣ ገምጋሚም አስገምጋሚም፣ ሰብሳቢም፣ መራጭም፣ ሆኖ ሁሉን ከእፍታው ይጨልፋል፡፡ ጠያቂ የለበትምና ልቡም እጁም አያርፍም፡፡ ሙስናን ለማስፋፋት ቅርብ ሆነ ማለት ነው፡፡ የአገርና የግለሰብን ጥቅም ያደበላልቃል፡፡ የተማረረን ከተማረ በላይ ያደርጋል፤ ባለሙያነትንና ባለእውቀትነትን ከአፋዊ ችሎታ በታች ያያል፡፡ ይህን መሳይ ድርጊት ሁሉ የመልካም አስተዳደር አለመምጣት መርዶ ነው፡፡ ያ በፈንታው የዲሞክራሲን በር ይዘጋል፡፡ የሰላምን ውጋጋን ይጋርዳል፤ የፍትህን ሚዛን ይነጥቃል፡፡
በተለይ እጅግ ወቅታዊ የሆኑትን፤ የሀገርም ሆነ የአገርና አገር ጥያቄዎችና ችግሮች በዲሞክራሲያዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አፍጦ የመጣበት ሰአት ነው፡፡ የችግር ቅደም-ተከተልን ጥያቄ (prioritization) ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሁኔታና ከተጎራባች አገሮቿ እንዲሁም ከሉላዊ እንቅስቃሴና መስተጋብር (global action and interaction) ጋር አጣጥሞ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ ለአቻ ቦታ አቻ ሰው መድቦ መራመድ ከወደቁ ወዲያ ከመንፈራገጥ ማዳን ብቻ ሳይሆን እስከ ፍልሚያ ሜዳ ያለውን ጎርበጥባጣና ኩርንችታማ ጎዳና ለመጥረግ በቅጡ ያግዛል፡፡ ጦርነት የሰላማዊ መንገድ መሟጠጫ እንጂ መነሻ መሆን በጭራሽ የለበትም፡፡ አለመዘናጋት ግን ሁሌም ወሳኝ ነው፡፡
የጥንቱ የጠዋቱ ሼክስፒር በሀምሌት ውስጥ “ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም፣ አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!” (ፀጋዬ ገብረመድህን እንደተረጎመው) ያለውን አለመርሳት ደግ ነው፡፡
ረጅም መንገድ አለብኝ ብሎ በርካታ ስንቅ የጫነ ሰው፤ ስንቁን ቅርብ ቦታ መጨረስ የለበትም፡፡ በትንሽ እንቅፋትም መውደቅ የለበትም፡፡ ነገ ሰፊ የምርጫ ትግል ያለበት የዛሬ አዘገጃጀቴ “የሚወጋ ጦር ከእጅ ሲወጣ ያስታውቃል” አይነት መሆን አለበት፡፡ የብዙዎችን ተሳትፎና ድጋፍ በጠዋት ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ መፎካከር ለማሸነፍ ብቻ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ነገም እንደዛው መሆኑን አውቆ መጓዝ ያሻል፡፡ መጋቢ ጅረቶች ሁሉ ወደ ወንዝ ለመቀላቀልና የአገር ሃይል ለመሆን እንደሚችሉ አጢኖ፤ ጊዜ መውሰድ አቅጣጫ ማግኘት ያሻዋል፡፡ ጊዜያዊ የሀገር ጉዳዮችን ከዘላቂ ፍሬ ነገሮች አነፃፅሮ አንዱ በሌላው እንዳይጋረድ ደህና አደርጎ ማስተዋል የሁሉም ድርጅቶች አጓጓዝ መሆን አለበት፡፡
ዳምኖም አጉረምርሞም ላይዘንብ እንደሚችል ሁሉ፣ ዘንቦም ሙሉ ጥጋብ ላይሆን እንደሚችል፣ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከህዝብ ያልመከሩበት፣ ህዝብን ያላሳተፉበት አካሄድ መሰረት-የለሽ ፒራሚድ ነው፤ ብዙ እድሜ የለውም፡፡ በአጭር ጊዜ ፈተና ይዳከማል፡፡ አዋቂዎቹን እንደፈተሸው ብልህ ንጉስ፣ ጠያቂ የመጣ እለት በአደባባይ መጋለጥ ይከተላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በቅንጣት ጥያቄ ግዙፍ ሀጥያት ይታያል፡፡ የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል የሚባለው እንግዲህ ያኔ ነው!

   • በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር ፍ/ቤት አልቀረቡም ተባለ
                 • አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ


        በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በአዋጁ ድንጋጌ መሰረት በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችም  እንዲነሱ ጠይቋል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ፣ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው የነበሩ 19 እስረኞች፣ “የተሃድሶ ስልጠና” ከወሰዱ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ከእስር መለቀቃቸው ተዘግቧል፡
ኢሰመኮ ላለፉት 10 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ በመከታተል፣ በአፈፃፀሙ ላይ ያሉ ጥሰቶችንና ክፍተቶችን ሲመረምር የቆየ ሲሆን፤ ግኝቶቹም በተከታታይ ሪፖርቶች  ታትመዋል፡፡
ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን በተመለከተ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም  ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በክልሉ በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን አስታወቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በአዋጁ የተያዙ እስረኞችን መፍታት፣ ወደ መደበኛ የህግ ማስከበር አሰራር መመለስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ  የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ በአፅንዖት አሳስቧል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታሰሩት ግለሰቦች  መካከል  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለውና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል አቶ ካሳ ተሻገርን የመሳሰሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች  ይገኙበታል።
በፌደራል መንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተባባሰ የመጣውን ግጭት ተከትሎ፣ ባለፈው ዓመት ሃምሌ መጨረሻ ላይ  በአማራ ክልል ለ6 ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የሚታወስ ሲሆን፤ ፓርላማው የመጀመርያው የስድስት ወራት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት ማራዘሙ ይታወቃል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል፣ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ ከሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ በተጨማሪ አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ  ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አቶ የሺዋስ አሰፋ “ሁከት በማነሳሳት” መጠርጠራቸውን አንድ የቤተሰብ አባል መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ፣ ህዳር 30 የተጠራው ሰልፍ አስተባባሪ ነበሩ የተባሉት አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ  መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  


• ፕሮዱዩሰር የዘፋኙን ሥራ ያቀላል፤ ጫና ይቀንሳል
         • የትም ቢሆን ለእኔ ተብሎ የሚደረግ ሸብረብ የለም
         • አብዛኞቹ ሥራዎች እኔን ለምለምን ይመስላሉ


       ባለፈው ሳምንት ዕትማችን ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከድምፃዊት ለምለም ሃይለሚካኤል ጋር ያደረገችው ጣፋጭ ወግ የመጀመሪያ ክፍል ለአንባቢያን የደረሰ ሲሆን፤ ቀጣዩ ወጋቸው ደግሞ እነሆ እንደሚከተለው ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ድምጻዊቷ በአዲሱ አልበም ውስጥ ስለተካተቱት ሥራዎች፣ ስለ ዝነኝነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ”ማያዬ” ስለተሰኘው የአልበሙ መጠሪያ ዘፈኗ፣ ስለ ቤተሰቦቿና የወደፊት ዕቅዷ በስፋት ታወጋለች፡፡ አንብቡት ትወዱታላችሁ፡፡


         ኤልያስ መልካ አንቺን ከ“ሚሚነት” ወደ “ለምለምነት” ለመቀየር ሲያደርግ የነበረውን ጥረት እያወጋሽኝ ነበር ጨዋታችንን በይደር ያቆየነው።  እስቲ ከዚያው እንቀጥል----
መልካም! እንዳልኩሽ በተለያዩ ሂደቶች እኔ ከሚሚ ወደ ለምለም ከተቀየርኩና እሱ ላይ እርግጠኛ ከሆነ በኋላ ደግሞ ለለምለም ምን አይነት ዘፈን ይሰራ፣ በለምለም ምን ዓይነት መልእክት ማስተላለፍ ይቻላል፣ ለምለም እንዴት ነው የምትዘፍነው? አልበሟ ምን ይሁን? ወዘተ-- በሚሉ ጉዳዮች ላይ ብዙ ሙከራዎች (ኤክስፐርመንቶች) ስንሰራ የቆየንባቸው ጊዜያት ናቸው- አምስቱ ዓመታት። ሦስቱን ስራዎች እየሰራን ሳለ ታዲያ  ኤልያስ መልካ ጤናው እየታወከና እየደከመ ሲመጣ፣ ሌሎች ቦታዎች ሄጄ መስራት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ነው ወንደሰን ይሁብን ያገኘሁት። ከወንደሰን ጋር ከተገናኘን በኋላ የመጀመሪያውን ነጠላ ዜማዬን ሰራሁ።
የትኛውን ማለት ነው?
“ገዳም” የሚለውን ሥራ ማለቴ ነው። እሱን ስራ ወስጄ ለኤልያስ አሳየሁት። ቆንጆ እንደሆነ ነገረኝ። እናም በዚህ መልኩ እንደምችል ነገረኝ ማለት ነው።
ወንደሰን ይሁብ ምን አይነት ባለሙያ ነው?
ኦኦ! በጣም ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ከፍተኛ የሥራ ፍላጎት ያለው አስደናቂ ልጅ ነው፤ ወንድወሰን። ከኤልያስ ጋር የቆየሁበትና ከወንድወሰን ጋር የቆየሁበት ጊዜ ይለያያል። እዚህ በጣም ፍጥነት አለ። አልበሜን ከዚህ ልጅ ጋር ብሰራ የሚል ስሜት አደረብኝና፣ “ወንዴ፤ አልበሜን አብረን ብንሰራ ምን ይመስልሃል?” አልኩት። እሱም በደስታ ተቀበለኝ፤ ከዚያም በአራት ዓመታት ውስጥ ሰርተን ጨረስን ማለት ነው። እውነት ለመናገር እንደፍጥነታችን አራት ዓመት ላይፈጅ ይችል ነበር። እኔ በመሃል ወለድኩ፤ ኮሮና ገብቶ እንቅስቃሴ ተገደበ። በዚህ በዚህ ምክንያት አራት ዓመት ፈጅቶ ይኸው ለአድማጭ ቀርቧል። ከኤልያስ ጋር የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን “ማያዬ”ን፣  “ከፍቶኝ”ን እና ኦሮምኛውን “ውሊሊ”ን ነው የሰራነው። ቀሪዎቹ ከወንድወሰን ይሁብ ጋር የተሰሩ ናቸው። ወንድወሰን የአልበሙ ፕሮዱዩሰርም ነው። በነገራችን ላይ በአብዛኛው የፕሮዱዩሰር ሚና በግልጽ አይታወቅም ወይም በደንብ አልተነገረም። ምናልባት በፊት እነ አበበ መለሰ፣ ይልማ ገብረአብና አበበ ብርሃኔ ፕሮዱዩስ ያደርጉ ነበር። ይሄ ማለት ራስሽ ግጥም መርጠሽ ዜማ መርጠሽ፣ አልበሙ እንዲህ ይሁን ብለሽ ነው የምትሰሪው። ይሄ የማላውቀው ስለሆነ ከባድ ነበር። ስለዚህ ወንድወሰን ይህንን ሁሉ አድርጎ ነው አልበሙ ለውጤት የበቃው። ፕሮዱዩሰር ሥራ ያቀላል፣ ጫና ይቀንሳል። ከዚያ ባለፈ ሙያን ለባለሙያው መስጠትም ተገቢ ነው። ወንደሰን በዚህ የተካነ ስለሆነ 8 ሙዚቃዎችን መርጦ፣ ግጥሞቹን ግማሹን ጽፎ፣ ግማሹን አፅፎ ነው የሰራልኝ። በዚህ አጋጣሚ በጣም  ነው የማመሰግነው። ለሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ልጅ ነው።
ከዘፈኖችሽ ሁሉ አብልጠሽ የምትወጂው የትኛውን ነው? በእርግጥ ሁሉም ልጆቼ ናቸው እንደምትይኝ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ከጣት ጣት ይረዝማል እንደሚባለው፣ አንድ ምረጭ ብትባይስ?  እኔ ለምሳሌ የብዙ ሚስቶችን መቃተትና ለትዳራቸው የሚከፍሉትን መስዋዕትነት የሚያንጸባርቀውን “እንዳትጠላው” የሚለውን ዘፈን ነው የበለጠ የወደድኩት፡፡ አንቺስ ምን ትያለሽ?…
በነገርሽ ላይ “እንዳትጠላው” የተሰኘውን ግጥምና ዜማ የሰራልኝ ሀብታሙ ቦጋለ ነው። በጣም ጎበዝና ሀሳብ ያለው ገጣሚ ነው። እኔ ከሀብታሙ ጋር በመስራቴ ደስተኛ ነኝ። ሀብትሽ በ90ዎቹ ወርቃማ ሙዚቃዎች ላይ ዳሰሳ ተደርጎ ቢጠና፣ አብዛኛዎቹ የእሱ ናቸው፡፡ እኔ በጣም ነው የምወደው። እዚህ ሙዚቃ ላይ ልክ አንቺ የተሰማሽ  አይነት ስሜት እኔም አለኝ። የኔም ያንቺም የሁላችንም ህይወት ነው። ሲጀመር የተሰራበትም መንገድ እንደገለጽሽው ነው። እኔ ለበዓል ሰራተኛዬ ሄዳብኝ፣ ጠዋት ሲደውልልኝ መወልወያ ይዤ ቤት እየወለወልኩ ነበር። ደውሎ “ሊሊ የሆነ ዘፈን  ሰራሁልሽ” አለኝ። ሀብታሙ ሲነግርሽ ሀሳቡ ነው ከዜማው ቀድሞ የሚገባሽ። ሲነግረኝ፤ “እኔ አሁን ኤግዛክትሊ እዛ ሁኔታ ውስጥ ነኝ፤ ቤቴን ቤቴን እያልኩ ነው፤ ጨርስና ደውልልኝ” አልኩት። ማታ ሙዚቃውን ጨርሶ ልኮልኝ ካዳመጥኩት በኋላ፣ ”ሳላውቅ ብዙ ነገር አጫውቼሃለሁ እንዴ?” ነው ያልኩት። በዚህ ብቻ ሳይሆን በአልበሙ ውስጥ ባሉ በአብዛኞቹ ዘፈኖች ውስጥ ራሴን አገኘዋለሁ። በስሜት እጋራቸዋለሁ። ዘፈኖቹን ከዚህኛው ያኛው ይበልጣል አልልሽም። “ማያዬ” ለኔ ማመስገኛዬ፣ ሁሉን መመልከቻዬ ማለት ነው። “ማያ” ሁለተኛ ልጄ ናት። በውስጡ ትልቋ ልጄ “አና” አለች። ማያዬ ስል መስታወቴ፣ አይኔን ባይኔ ያየሁባቸው ልጆቼ፣ የፈጣሪን ድንቅ ስጦታ ያየሁበት ነው። ሙዚቃው ፆታው ተባዕት ነው። ነገር ግን እኔ የምዘፍንበት ስሜት የተለየ ነው። ይሁን እንጂ አድማጭን ሙዚቃውን በእኔ አይን እዩልኝ አልልም። ሁሉም እንደየስሜቱና መረዳቱ ሊያጣጥመው ይችላል። በአጠቃላይ አብዛኛዎቹ ሥራዎች እኔን ለምለምን ይመስላሉ።
እንግዲህ  ከወንድወሰን ጋር ጓደኝነቱም ስላለን አብረን ብዙ ጊዜ እናሳልፋለን። የኔም ስራ ሳይኖር ስቱዲዮ ቁጭ ብዬ ሲሰራ እያየሁ እናወራለን፣ እንወያያለንና ከዚህ አንፃር፣ ሃሳቤን ፍላጎቴን ተረድቶኝ ይሆናል እኔን የሚመስሉ ሃሳቦች የተፃፉት እላለሁ። እኔ አንድ ለምለም ነኝ፤ በአንድ አይነት የማህበረሰብ ስነልቦና ውስጥ ስታድጊና ስትኖሪ ስሜቶችን ትጋሪያለሽ። ስለዚህ አብዛኛው በአልበሙ የተነሱ ሃሳቦች የኔም ሃሳብ ናቸው ብዬ አምናሁ።
በአዲሱ አልበምሽ ጎጃምንም አሽሞንሙነሽል፣ ኦሮሚኛም አለ፣ የሙዚቃ ቡፌው በስፋት ነው። ኦሮሚያ ተወልደሽ ከዚያ ወደ መሃል አገር መጣሽ፣ በስራሽ ምክንያት ብዙ የአገሪቱን ክፍሎች ተዘዋውረሽ አይተሻል። ታዲያ ያንቺ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?
ኢትዮጵያ ለኔ ላንቺ እንደሆነቺው ናት። ስለ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከኔ የበለጡና የላቁ ሰዎች ብዙ ብለዋል። የእኔን ኢትዮጵያ ስለጠየቅሽኝ ግን፤ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ራስን መሆን ነው። በስራ አጋጣሚ በተለያዩ የሀገሬ ክፍሎችም ውጪም ሄጄ ብዙ ነገር የማየት የመታዘብ ዕድል አግኝቻለሁ። ሰው በዚህ ደረጃ እንዴት አገሩ ይናፍቀዋል? እዚህም ሆነሽ ስለ ኢትዮጵያ ሲዘፈን፣ ሌላ አገር ሆነሽ አገርሽ እንደሚናፍቅሽ አይነት ስሜት ይሰማሻል። ስለዚህ ኢትዮያዊነት ለኔ ማንነቴ በራስ መተማመኔም ነው። ኢትዮጵያዊነት ሰው መሆንና ቀና ብሎ መሄድ ነው ለኔ። ኢትዮጵያን ተዘዋውሬ ሳይ ብዙ አንድ አይነትና እንደገና ብዙ ልዩነትም አለ። ያ ልዩነትም ይመስለኛል ኢትዮጵያዊነትን ውብ የሚያደርገው። ሁሉም አንድ አይነትና ወጥ ሲሆን  አሰልቺ ነው። ኦሮሚያ ላይ ተወልጄ አማራ ስሄድ ብዙ ደስ የሚሉ አዳዲስ ባህሎችን አይቻለሁ። መቀሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሄድ፣ ወላይታ ስሄድ፣ ቦረናን ስቃኝ አንድ አይነትም ልዩነትም አይቻለሁ። ውብና ድንቅ ነገሮች። የሰዎችን ፍቅር፣ ሩህሩህነት አይቻለሁ። ፍቅርና ሩህሩህነታቸውን የሚገልጹበት ቋንቋ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ግን ሁሉም ሩህሩህና ፍቅር ናቸው።
ለምሳሌ ኦሮሚያ ሆነሽ ቦረናና ባሌን የሚያመሳስለው፣ የሚያለያየው ነገር አለ። ባሌ ተወልደሽ ወለጋ ብትሄጂ፣ ኦሮሚያ ኦሮሚያ ነው፤ ግን  የሚለያይ በርካታ ነገር አለ። ነገር ግን ብዝሃነት (ዳይቨርሲፊኬሽን) በራሱ የኢትዮጵያ መልክ ነው። ይህንን በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት የማታገኚባቸው ቦታዎች ይኖራሉኮ!! በእርግጥ ኬንያ ሄደሽ አንድን ኬንያዊ ብትጠይቂው፣ የእኔን አይነት መልስ ሊሰጥሽ ይችል ይሆናል። ኢትዮጵያዊነት ለኔ ግን በቃ ማንነቴ፤ ነጻነቴ ነው። በራስ መተማመኔ፤ የተቀረፅኩበት ሰብዕናዬ ጭምር ነው።
በአልበሙ ብዙ መልዕክቶች ተላልፈዋል። ለምሳሌ “አስከትዬ” የተሰኘው ዘፈንሽ በገፉት ንፁህ ፍቅር መፀፀትን የሚያንፀባርቅ ነው፣ ስለ ልጅነት ፍቅር ያቀነቀንሽው አለ። ስለ ጎጃም የተዘፈነው “ደገምገም”  ወዝወዝ የሚያደርግም ነው። ሀሳቡም ድንቅ ነው። ነገር ግን “ከፍቶኝ” የተሰኘው ዘፈንሽ ላይ
ከፍቶኝ የቆየ አይመስለኝ
ባይኖር አለሁ የሚለኝ
ምክንያት ሆነልኝ ከላይ
ዘመን እራሴን እንዳይ
ጊዜ ጊዜማ ጊዜ
ሲሆን የባለ ጊዜ
ወትሮም በዓለም የፀና
የታል ሰው ሆኖ ጀግና።…
 እያለ በሚቀጥለው ዘፈንሽ…በተለይ “ጊዜ ጊዜማ ጊዜ ሲሆን የባለጊዜ” የሚለውን ሀረግ ሰዎች ብዙ ጊዜ “ተረኛ ባለጊዜ” እየተባለ ከሚነገረው ከወቅቱ ፖለቲካዊ አውድ ጋር ሊያያይዙት ይሞክራሉ። እስቲ የአንቺን አስተያየት ንገሪኝ። በዘፈኑ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ምንድን ነው? “ባለጊዜስ” ማነው?
ቅድም የገፉት ፍቅር ላይ ፀፀትን የሚገልፀው “አስከትዬ የተሰኘውን ዘፈን ስናይ፣ ሰው በትዝታ ወደ ኋላ ይሄዳል። በህይወትሽ ውስጥ የምታደርጊያቸው እውነታዎች ይኖራሉ። እናም ተከትለውሽ ይመጣሉ። ከህሊና መሸሽ አይቻልምና እስከ ህይወትሽ መጨረሻ የሚከተልሽ ነው። ነገር ግን ያንን ጉዳይ ከላይ ከላይ ትክጅዋለሽ። አጥፍተሸ ህሊናሽ እያወቀ እንኳን ስትጠየቂ፤ “ኧረ ይሄ አልሆነም በጭራሽ“ እያልሽ ትከራከሪያለሽ። ጭንቅላታችን ውስጥ ያለው ድብቁ የአዕምሮ ክፍል እየቀሰቀሰ ያስታውስሻል። ያንን ነገር በይቅርታ ማጠብ ተገቢ ነው። እንኳን አጥፍተሸ ክርስቶስ እንኳን ሳያጠፋ ይቅርታን አስተምሮናልና ይቅርታ ማለት ይገባል። ይህንን ዘፈን ወንድወሰን ሲሰጠኝ በጣም ብዙ ጊዜ የተሞከረ ዜማ ነው። በጣም ብዙ ሰዎች ሰርተውታል። እኔ በይቅርታ የማምን ሰው ነኝ። ያጠፋሁትንም አሽሞንሙኜና አለባብሼ የማልፍ አይነት ሰው አይደለሁም። በይቅርታ ስለማምን ዘፍኜዋለሁ እወደዋለሁም። ስለጊዜና ባለጊዜ ያነሳሽው… ላንቺ “ባለጊዜ” ማነው ላልሺኝ ባጭሩ ስመልስልሽ፣ ለእኔ ባለጊዜ ትልቁ ሃያል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ለኔ የሰው ባለጊዜ የለም።
ጊዜ ጊዜማ ጊዜ
ሲሆን የባለ ጊዜ
ወትሮም በዓለም የፀና
የታል ሰው ሆኖ ጀግና!... የሚለው ሃረግ የጊዜ ባለቤትና ጌታ ፈጣሪ መሆኑን ነው የሚያሳየው። ከፖለቲካ አንፃር ያነሳሽው----ባለጊዜ ምናምን ተብለው የሚለጣጠፉ የመንደር ወሬዎች ይኖራሉ፤ እሱ ለእኔ አይገባኝም። ሰው በፈጣሪ በተሰጠውና በተፈቀደለት ጊዜ የሚያደርገውን ነገር፣ የማድረግ ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጥረት ነው። ጊዜንም የሚገድበው ባለጊዜው እግዚአብሔር ነው። እኔ ከዚህ አንፃር ነው ሙዚቃውን የምረዳው። ሰዎች ግን  እንዳልኩሽ ከፈለጉት አንፃርና ዕይታ ሊተረጉሙት ይችላሉ። ቅድም ሙዚቃን እኔ ባየሁት አይን እዩልኝ አልልም  ብዬሽ የለ… ልክ እንደዛ ማለት ነው።
ለምለም የልጆች እናት ናት። ብዙ የቤተሰብም ሆነ የስራ ሃላፊነት አለባት። በእነዚህ ሃላፊነቶች ውስጥ አልፎ በሥራ ስኬታማ ለመሆን የትዳር አጋር ከጎን መቆም አለበት።  የለምለም የትዳር አጋር ደጋፊና አጋዥ ነው ወይስ …?
እውነት ለመናገር በዚህ ዙሪያ ብዙ መናገር አልፈልግም። በእርግጥ በድጋፍ ደረጃ ቤተሰቦቼ በእጅጉ ይደግፉኛል። ከዚያ ደግሞ የልጆቼ አባት ቤተሰቦች በጣም አጋዥና ደጋፊዎቼ ናቸው። ስራዬን ይወዳሉ፣ ልጆቼንም በጣም ነው የሚወዷቸው። እግዚአብሔር ይመስገን የድጋፍ ችግር የለብኝም። ከጓደኛም ከቤተሰብም ከሁሉም በኩል ጥሩ ድጋፍ የሚደረግልኝ ዕድለኛ ሰው ነኝ። በዚህ ስራ ውስጥ አላገዘኝም የምለው አካል የለም። ልጆቼ እንኳን ስራ ስወጣ የት እንደምሄድ ያውቃሉ። በዚህች ትንሽ እድሜያቸው “ማሚ ዛሬ ይሄኛውን ጫማ አድርገሽ ሂጂ” ብለው ይበልጥ እንዲያምርብኝ የሚጥሩ ናቸው። ይሄ መቼም መታደል ነው። አስቢው…አና ስድስት፣ ማያዬ ሦስት ዓመታቸው ነው። በአጠቃላይ የድጋፍ ችግር የለብኝም። አንድ ስራ በሰራሁ ቁጥር የሀገሬ ልጆች ደውለው፣ በርቺ ቆንጆ ነው እያሉ ያበረታቱኛል፤ የድጋፍ ሀብታም ነኝ። ከትዳርሽ ከባልሽ ወይም ከልጆችሽ አባት የምትፈልጊው ድጋፍ ብዬ የማስበው ሥነ ልቦናዊ (ኢሞሽናል) ድጋፍ ነው። ለአንድ አርቲስት ሊሰጠው የሚገባ ድጋፍ አለ ብዬ አምናለሁ። ያ ድጋፍ ኢሞሽናል ድጋፍ ነው። ይህን ደግሞ ብዙ ጊዜ ላታገኚው ትችያለሽ። በብዙ ምክንያቶች። እኔ ከ”የኛ” ያገኘሁት ትልቁ ነገር ደግሞ ለምለም ያለድጋፍ እንዴት መቆም ትችላለች የሚለውን ነው። ለምለም ድጋፍ ኖራት አልኖራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፋ እንዴት መቆም ትችላለች የሚለውን በራስ መተማመን በ”የኛ” ውስጥ ሳለሁ በበቂ ስልጠና ገንብቼአለሁ፡፡ ያም ሆኖ ሰው ነኝ፤ ሰው ደግሞ ደካማ ጎኖችም አሉት። እኔም ችግር ሲያጋጥመኝ መፍትሄ ፍለጋ ወደ ሰው እሄዳለሁ። በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ ሆኜ አሻግሬ የምመለከተው እግዚአብሔርን ነው። እግዚአብሔርን ተመልክተሽ ደግሞ የምታጭው ነገር የለም።
አንድ ሰው የህዝብ ሲሆን፣ ታዋቂ ዝነኛ ሲሆን ብዙ ነገሩ ምስጢር አይደለም። አለባበሱ፣ አመጋገቡ፣ ውሎው፣ የፍቅር ህይወቱ ሁሉ አደባባይ ይወጣል። ከዚህ አንፃር ዝናን የምታማርሪበት የግል ነጻነትን - ፕራይቬሲን የምትናፍቂበት ጊዜ አለ?
እኔ እስካሁን የግል ነፃነቴን (ፕራይቬሲዬን) ለማንም አሳልፌ አልሰጠሁም። የምኖረው የራሴን ሕይወት ነው። ሰፈር ብትመጪ ሁሉም ሰው የሚውለውን አዋዋል ነው የምውለው። ቤቴ ውስጥም የትም ቢሆን ለምለም ታዋቂ ስለሆነች ተብሎ የሚደረግ የተለየ ሸብረብ የለም። በተቻለኝ መጠን መጥፎና ክፉ ቦታ ላለመዋል ጥረት አደርጋለሁ፡፡ በማህረሰቡ ይሄ ክፉ ነው ተብሎ የሚነገር፣ እኔም ክፉ ነው ብዬ የማምንበት ቦታ ላይ አልገኝም። ከዚህ በተረፈ ሰፈር ብትመጪ ባለሱቁ መሃመድም ሌሎቹም ፊት ለፊት ያሉትን ብትጠይቂያቸው ያውቁኛል።
ዝነኛም ሆነሽ እንደኛ ነው የምትኖሪው ማለት ነው…?
ምን ልልሽ ፈልጌ ነው መሰለሽ… ሱቅም ሄጄ የምገበየው እራሴ ነኝ። ወፍጮ ቤት ሄጄም እህል የማስፈጨው እኔው ነኝ። በርበሬና ሽሮ ቤት ውስጥ ነው የማዘጋጀው። የምሬን ነው የምልሽ። እንጀራ ጋግሬ መብላት የጀመርኩት ገና አዲስ አበባ እንደመጣሁ በኪራይ ቤት ትንሿን ምጣድ ገዝቼ ነው፡፡ ለራሴ መጋገር እየቻልኩ ለምንድነው ገዝቼ የምበላው?...አንዳንዴ ታዋቂነት ይጫንሽና ኑሮሽን በአግባቡና በነፃነት እንዳትኖሪ ትደረጊያለሽ። ለመሆኑ ገና እኔ ምን ሰርቼ ነው ፌመስ የምትይው? ሰው እኮ መጀመሪያ  በኢኮኖሚ ራሱን መቻል አለበት፡፡ በሁለት እግሩ ተደላድሎ መቆም ይኖርበታል፡፡ እኔ ገና በኢኮኖሚ ራሴን ሳልችልና ሳልደላደል፣ ፌመስ የሚል ታፔላ እላዬ ላይ እንደመረብ ተጥሎ፣ እየተንደፋደፍኩ አላስመስልም።  እኔ አስመስዬ የምኖረው ኑሮ የለም። እናት ስሆን በትክክል እናት ነው የሆንኩት። የቤት እመቤት ስሆን በቃ በትክክል የቤት እመቤት ነኝ። ቤቴ ብትመጪ ፌሙ ይህን ይፈልጋል ብዬ የምኖረው ህይወት የለም። እኛ አገር ፌመስነት የሚተረጎምበት መንገድ ራሱ ትክክል አይደለም። በውጪው አለም በጣም ትልልቅ የምትያቸው አክትረሶች ለልጆቻቸው ምግብ ያበስላሉ።
እኔ ገና ጀማሪ ሙዚቀኛ ነኝ። ሙዚቃዬ መሸጥ እንኳን የጀመረው ገና አሁን ነው’ኮ። ዘጠኝ አመት ለፍተሽ የሚከፈልሽ ገንዘብ’ኮ ከወጪ ቀሪ የአንድ አመት የቤት ኪራይ እንኳን አይሸፍንም። ታዲያ የትኛው ዝና ነው የሚያመጻድቀኝ። እርግጥ የቤት ሰራተኛ አለኝ፤ ግን እራሴም በደንብ ነው የምሰራው፤ እና ፕራይቬሲን የሚያስናፍቅ፣ የሚያስጨንቅ ዝና የለም። አለቀ።
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪን የሰራሽበት የቴአትር ሙያ ላይ ምን እያሰብሽ ነው? ወደ ትወናው የመምጣት እቅድ የለሽም?
እኔ ቴአትር መስራት በጣም ነው የምገፈልገው። ስለምወደው ነው የተማርኩትም። ”የኛ“ ፕሮጀክት ያን ጊዜ ያዝ ስላደረገን፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ ለመስራት አንችልም ነበር። እስካሁን “ትመጣለህ ብዬ” እና “አንድ ጀግና” የተሰኙ ፊልሞች ፕሮዱዩስ አድርጌያለሁ፤ ከጓደኛዬ ከመሳይ ተፈራ ጋር፡፡ ከቅድመ-ፕሮዳክሽን ጀምሮ ስክሪፕት ላይ ሁሉ ተሳትፌ በደንብ ሰርቻለሁ፡፡ በመተወን ደረጃ ትልቁ ሰራሁት የምለው “ሀገር ማለት” ቴአትርን ነው። ከዚህ በኋላ ግን ልጆችም እያደጉ ሲሄዱ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ራሴ ቴአትር ፅፌ ለመተወን ሀሳብ አለኝ።
እንጠብቃለን! እኔ በግሌ እጠብቅሻለሁ--
አልቀርም፤ ጠብቂኝ።
አልበምሽ ተወዳጅ ይሆን ዘንድ  ጥረት እንዳደረግሽ ይገባኛል። አሁን ላይ እንደማንኛውም አድማጭ ቁጭ ብለሽ ስታዳምጪው ይሄ ቢስተካከል፣ ይሄ ቢሆን ያስባለሽ እንከን አግኝተሻል?
ይሄ ቢሆን ቢስተካከል ያልኩት ነገር በደንብ አለ። እንዳልሽው አልበሙን እንደማንኛውም አድማጭ በትልቅ ስፒከር አስከፍቼ ቁጭ ብዬ ሳዳምጠው፣ የተወሰኑ እንከኖችን አይቻለሁ፤ ግን አሁን ይሄ ነው  ይህ ነው ብዬ  መግለጽ አልፈልግም። አልበሙ በጣም  ቆንጆ የሆነበትንም ክፍል ይበልጥ እንድረዳ አድርጎኛል ማዳመጤ።
ከሴት ድምፃዊያን ማንን ታደንቂያለሽ?
በጣም ብዙ ሰው ነው የማደንቀው።
አንድ ጥሪ ብትባይስ?
አንድ ጥሪ ብለሽ ካስገደድሽኝ ልጥራ። አስቴር አወቀን በጣም ነው የምወዳት፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የእሷ አልበሞች ስብስብ በካሴት እቤት አለ። አስቴርን ሳዳምጥ ነው ያደኩት። ሙዚቀኛ ከታች ተነስቶ አድጎ አድጎ ብቁ ሲሆን ማን ይመስላል ብባል? አስቴር አወቀን ነው የምለው። የመጀመሪያ ካሴቷንና የመጨረሻ አልበሟን ስትከፍቺ፣ ያልኩሽን ሂደት ትመለከቻለሽ። እኔ በጉሮሮ የመተወን ብቃት የማደንቃት ግሩም  ድምፃዊት አስቴር አወቀ ናት።
“ጣይቱ” የተሰኘው ዘፈናችሁ ላይ አስቴር አለችበት፡፡ አብረሻት ስትዘፍኚ አድናቆትሽን አልገለጽሽላትም?
በጣም ነው የገለጽኩላት። አብራን ስትሰራ ደስተኛ ከመሆኔ የተነሳ ምን ላድርግልሽ? ምን ላቀብልሽ? ምን ልሁንልሽ? እያልኩ በቃ “አሽከሯ” ነው መሆን የፈለግኩት። (ሳ….ቅ….) ያኔ ሁሉም ጥግ ጥግ እየሆነ ማልቀስ ብቻ ነበር፡፡ ብቻ እድለኞች ነን። እንዳጋጣሚ እዛ ጣይቱ ዘፈን ላይ የገባችበት እንጉርጉሮ በኔ ድምፅ ነበር የሠራችው እና “እምዬ ምንሊክ እምዬ ምንሊክ የሚለው ማነው”? አለች “እኔ ነኝ” ስላት “ጎበዝ ጎበዝ” ብላኝ ሄደች።
በአልበምሽ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ ታታሪ ሙያተኞችን የምታመሰግኝበት ጊዜ እነሆ…    በጣም አመሰግናለሁ። የአልበሙን ፕሮዲዩሰር ወንደወሰን ይሁብን ፣ አንጋፋዎቹ አበጋዝ ክብረወርቅን፣ ኤልያስ መልካን (ነፍስ ሄር) ሰለሞን ሃይለማርም፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ አንተነህ ወራሽ፣ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ)፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ ብስራት ሱራፌል፣ ጥላሁን ሰማው፣ እሱባለው ይታየው፣ ዘርአብሩክ ስማው፣ ታምሩ አማረ፣ አዲስ ፍቀዱ፣ ብሩክ ተቀባ---እነዚህ ሁሉ አልበሙ አልበም ሆኖ እንዲወጣ ትልቅ አበርክቶት ያላቸው ናቸውና አመሰግናለሁ። ለነበረን መልካም የሥራ ቆይታ በእጅጉ አመሰግናለሁ።
ቤተሰቦቼን፣ ወላጆቼን፣ ዘመዶቼን፣ ጓደኞቼንና አድማጮቼን ሁሉ አመሰግናለሁ። ስማቸውን ዘርዝሬ አልጨርስምና አመሰግናለሁ። የልጆቼ አባት በጣም ጥሩ ሰው ነው። ልጆቼ ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ እድል ስለሰጣቸው በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ። አንቺም ከፈረንሳይ ሀያት ድረስ ተጉዘሽ መጥተሽ ይህን የመሰለ ቆይታ እንድናደርግ ስለፈቀድሽ በእውነት አመሰግናለሁ። ለከያንያን ማደግና መታወቅ ለሩብ ክፍለዘመን በትጋት አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው አንጋፋው አዲስ አድማስ ጋዜጣንና የዝግጅት ክፍሉን ባልደረቦች አመሰግናለሁ። ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ነው፤ በለምለም አቅም የሆነ አንድም ነገር የለም፤ የተደገፍኩት እግዚአብሔር ዙሪያዬን በበረከቱና ጥበቃው እዚህ አድርሶኛልና ክብር ምስጋና ይግባው እላለሁ። አመሰግናለሁ።


 ምሁራን በ”ብሄርተኝነት” መፅሀፍ ላይ የፓናል ውይይት አካሄዱ



          በዶ/ር በብርሃኑ ሌንጂሶ የተደረሰው “ብሔር-ተኝነት” የተሰኘው መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በዓድዋድልመታሰቢያ፣ ፓን አፍሪካ አዳራሽ የተመረቀ ሲሆን። በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ታድመዋል።
በምረቃቱ ሥነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ጽሑፍ ያቀረቡት ደራሲ፣ መምሕርና የሚዲያ ባለሙያ አቶ ታጠቅ ከበደ ከደራሲው ጋርስለነበራቸው የልጅነት ትውስታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።
 መጽሐፉ በኢትዮጵያ ስለሚስተዋሉ የብሔረተኝነት ዓይነቶች የሚቃኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታጠቅ፣ ከመጽሐፉ የተወሰኑ ጥቅሶችን በንባብ አቅርበዋል።
በመጨረሻም “ብሔር-ተኝነት” መጽሐፍ በአሁኑ ወቅት የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር እያካሄደ ለሚገኘው ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በግብዓትነት የሚያገለግሉ ምክረ ሃሳቦችን ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡
ደራሲው ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ የብሔረተኝነት ብየና አወዛጋቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ የብየናውን ሁለት ተቃራኒ ጎኖች በስፋት አብራርተዋል። “የብሔርተኝነትን ጥሩ ጎን ካጎለበትነው፣ ጥቅም አለው” ያሉት ደራሲው፣ መጽሐፉ ብሔረተኝነትን ከስሜት አላቅቆ በሚዛኑ ለማየት እንዲያግዝ በማሰብ  እንዳዘጋጁት ተናግረዋል።
ብርሃኑ (ዶ/ር) ስለ ብሔርተኝነት ምሳሌ ሲያቀርቡ፣ “በተለምዶ ‘የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ’ የምንለው የነገስታት ታሪክ ውስጥም የብሔረተኝነት ቀለም ይስተዋላል” ብለዋል።
“መጽሐፉን ለማዘጋጀት ወደ አምስት ዓመት ገደማ ፈጅቷል” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት  ደራሲው፤ “በምረቃው ዕለት በሁለት ነገሮች ደስተኛ ሆኛለሁ። አንደኛ አድዋ መታሰቢያ መመረቁ ነው። ምክንያቱም በዓለም ላይ የዕውነተኛ አገራዊ ብሔረተኝነት ቢፈለግ፣ ከዓድዋ ውጭ የለም። ሁለተኛው ደግሞ፣ በመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ የተገለጸው ሃሳብ ከአገራዊ ምክክሩ ጋር ተገናኝቷል።” በማለት አስረድተዋል።
በመጨረሻም፣ የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢ “በወጣቶች ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ” ላሏቸው፣ በሁሉም ክልሎች ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች እንደሚውል በማስታወቅ ደራሲው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአትሌት ደራርቱ ቱሉና ከሌሎች የክብር እንግዶች ጋር በመሆኑ መጽሐፉን መርቀዋል። አቶ አገኘሁ ከምረቃው አስከትለው ባደረጉት ንግግርም፣ “ጎንደርን የሚያውቅ...ፎገራን የሚያውቅ ነው” በማለት ደራሲውን ሲያሞካሹ፤ “ከእኔ በላይ ጎንደርን ያውቀዋል. . .የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ የተሳሰርን ነን” ብለዋል።
ለደራሲውና ቤተሰባቸው መልካም ምኞታቸውን የገለጹት አቶ አገኘሁ፣ መጽሐፉ ከሶስዮሎጂ ባሻገር፣ የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎችን እንደሚነካ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የመጽሐፉን ይዘትና የኢትዮጵያን አገራዊ ገጽታም በንግግራቸው ዳስሰዋል።
“እኛ ያለነው እንደ እኛ ክፋት ሳይሆን እንደ ሕዝቡ ቸርነት ነው” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት አቶ አገኘሁ፣ “የአሁኖቹ ልሂቃን ወይ በታሪክ ተወቃሽ ወይም ተመስጋኝ እንሆናለን” ሲሉ አመልክተዋል።
አቶ አገኘሁ ስለ አገራዊ ምክክሩ አጠቃላይ ገለጻ ሰጥተው፣ ከመጽሐፉ ጋር ያለውን ግንኙነት በመጥቀስ ንግግራቸውን አሳርገዋል።
በመጽሐፉ  ላይ የፓናል ውይይትም የተካሄደ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የሕግ መምሕሩ ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ መንግስቱ አሰፋ (ዶ/ር) እና ዕውነቱ ሃይሉ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ።
“ብሔር-ተኝነት” መጽሐፍ በአማርኛና ኦሮሚኛ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የአማርኛው መጽሐፍ በ5 ክፍሎችና በ15 ምዕራፎች የተዋቀረ ነው። የኦሮሚኛው መጽሐፍ ደግሞ፣ በ16 ምዕራፎች የተቀነበበ ነው።
ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጄሶ  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ናቸው።   

  ከዕለታት አንድ ቀን አሦች በግዛታቸው ላይ ከፍተኛ ቅሬታና መከፋት ተሰማቸው። አንዱ አሣ ሌሎችን በአጠገቡ የማሳለፍ ፍቃደኝነት አላሳይ አለ። ሁሉ በዘፈቀደ ወደ ግራ ወደ ቀኝ፣ ሽቅብ ቁልቁል ያለሥርዓት ይምዘገዘጋል፤ ውሃውን ያደፈርሳል። በሰላም በቡድን ሆነው ለመቆም በሚሞክሩት መካከል እየሰነጠቁ ማቋረጥና አንዳችም ይቅርታ አለመጠየቅ ተለመደ። የሌሎችን መንገድ ዘግቶ መቆም ተዘወተረ። ጠንካሮቹ ደካሞቹን በጭራቸው እየገረፉ ማለፍ እንደደግ ባህል ተቆጠረ። ጭራሽ አልፈው ተርፈውም ትልልቆቹ ትንንሾቹን ዐይናቸውን እንኳ ጨፈን ሳያደርጉ መዋጥ መሰልቀጥ ጀመሩ።
“ኧረ ህግና ሥነ-ስርዓት የሚያስከብርልን ንጉሥ ይኑረን?” ይላል አንደኛው አሣ።
ሁለተኛው አሣ፤
“ኧረ እስከመቼ ነው እንዲህ ሥርዓተ-አልባ ሆነን የምንኖረው?” ይላል።
አዛውንቱ አሣ ቀጠለ።
“ለመሆኑ እንዲህ ኃይለኛው ደካማውን እያጠቃ ጠቅላላ ማህበረ- አሣው ሳይከባበር አንዱ አንዱን እያንጓጠጠ፣ አንዱ ሌላውን እየሸነቆጠ፣ ሌላው ሌላውን ቁልቁል እያየና እየበጠበጠ፣ እንዴት ሊዘልቅ ነው። ህብረተ-አሣው ህልውናውን ለማስጠበቅም ሆነ መብቱን ለማስከበር አንድ መላ መፍጠር ይገባዋል። አለበለዚያ እንዲህ መላ ቅጣችን ጠፍቶና ኑሯችን ተመሰቃቅሎ ልንዘልቀው አንችልም” አለ።
ከዚያም ሁሉም በአንድ ድምጽ፤
“የንጉሥ ያለህ! ሥነ-ስርዓት የሚያስከብር ንጉሥ ያለህ!” አሉና ጮሁ።
በመካያው “ለምን የራሳችንን ጥሩ ንጉሥ አንመርጥም?” ተባባሉ። በዚህም መሰረት አንድ ውሃውን እንደልቡ በፍጥነት እየሰነጠቀ የሚጓዝ፣ ደካሞች ከመርዳት ወደኋላ የማይል መሪ መረጡ። በጣም ረጅም ቁመት፣ ስል ጥርስ ያለውና ካፉና ካፍንጫውም ረዥም-ሹል ቅርፅ ያለው ነው። በባህሩ ዳርቻ አሳዎቹ ሁሉ ተሰልፈው ሳሉ መሪው አሳ በጭራው እንዲንቀሳቀሱና የሩጫ ውድድር እንዲያደርጉ ነገራቸው። ሁሉም መሮጥ ጀመሩ። ርቀው ሄዱ።
መሪው አሣ እንደቀስት እየተወረወረ ሄደ። ከሱም ጋር ጨረር አሣ፣ አምባዛ፣ ሻርክ፣ ኢል ወዘተ እየተከታተሉ በረሩ። ፍላውንደር የተባለው ጠፍጣፋ አሳ ሁሉን ቀድሜ አሸንፋለሁ የሚል ተስፋ ነበረው። ግን አልተሳካለትም።
በዚህ መካከል በድንገት ጩኸት ተሰማ፤
“በእሽቅድምድሙ ትንሿ ብርማ አሣ ቀደመች! ትንሿ ብርማ አሣ ቀደመች!” አለ የጩኸቱ ድምጽ።
ጠፍጣፋው ቁጠኛና መቀደም የማይሻው ፍላውንደር እጅግ ወደ ኋላ ቀርቷል። በጣም ተናዷል። ከሱ ወደ ኋላ መቅረት የትንሿ መቅደምና አንደኛ መውጣት  ነው ያበገነው። “ማነው የቀደመው?” እያለ በንዴትና በቁጣ ጠየቀ።
“ትንሿ ብርማ አሣ ናታ! ትንሿ ብርማ አሣ!” የሚል ምላሽ ከግራም ከቀኝም አገኘ።
“ይቺ ራቁቷን ያለችው? ወይኔ ፍላውንደር” እያለ ዛተ፤ “በጊዜ በልቻት ቢሆን ኖሮ እንዲህ ጉድ አልሆንም ነበር!” አለ፤ ፍላውንደሩ በቅናት።
ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፤ በዚህ ጥፋቱ ምክንያት ምንጊዜም ሲንቀራፈፍ በቀላሉ የሚበላ አሣ እንዲሆን ተፈርዶበታል።
***
በራሱ መንቀራፈፍ ሳይቆጭ የሌላው መቅደም ንዴት ላይ የሚጥለው ለራሱም፤ ለሌላውም ለሀገሩም የማይበጅ ነው። ከዚያ የሚከፋው ደግሞ፤ ከዚህ ቀደም አጥፍቼው ቢሆን ኖሮ ዛሬ እንዲህ አልሆንም ነበር የሚል በጭካኔ የተሞላ ፀፀት ነው። እንደህ ያለ ፀፀት ከትላንቱ ክፋቱና ውጤቱ ያልተማረ ሰው ፀፀት ሲሆን፤ አድሮ የሚገጥመው ውጤትም ከትላንቱ የከፋ ውጤት መሆኑ አይቀሬ ነው። ጊዜያዊ ማታለልን እንደዘለዓለማዊ ስትራቴጂ የሚያስብ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ነው”። የፖለቲካን ችግር ኢኮኖሚያዊ ምላሽ በመስጠት፣ ለኢኮኖሚያዊ ችግር ፖለቲካዊ ምላሽ በመስጠት፤ ፍፁም ፖለቲካዊ ለሆነው ጥያቄ የዲፕሎማሲ ጭምብል መድፋት፣ ፍፁም ዲፕሎማሲዊ ለሆነው ጥያቄ ደግሞ፣ ልምድ የፖለቲካ ምላሽ ማላበስ፣ የአገር-ውስጡን ችግር ፣ ለዓለም-አቀፉ፣ የዓለም አቀፉን ለመንደሩ መፍትሔ መስጠት፤ “የሆድን በሆድ ይዞ! ሰባኪ ምላስ መዝዞ” እንደሚባለው ያለ አቋራጭ ይሆናል። ለየችግሮቻችን የምናቀርበው መፍትሔ ከተጨባጩ እውነታ በራቀ ቁጥር፤ ማንኛውንም ምንም ሳንጨብጥ አገርም ውልቅ የምትቀርበትና ኩም የምትልበት ሁኔታ ውስጥ እንዳትገባ መጠንቀቅ ተገቢ ነገር ነው።
“ለብልህ ጀምርለት አይስተውም፤ ለሞኝ በግልጽ ንገረው አይገባውም” ነው፤ ነገራችን ሁሉ።
ከቶውንም በበር ሲያቅት በመስኮት፤ በመስኮት ሲነቃ በፊት ለፊት በር፤ ፍላጎትን የማስፈፀም ፖለቲካዊ መንገድ፤ ረጅም ጎዳና የሚያስኬደን አይደለም። ባሁኑ ጊዜ በማናቸውም የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ዘመናዊ ዘዴ ጥንት የእጅ-አዙር አገዛዝ ይባል እንደነበረውያለ ነው፤ ለማለት ይቻላል።
አንዳንዶች “ፖለቲካ የመዋሸት ጥበብ ነው (መቦጥለቅ ነው) ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ “ፖለቲካ ራሱ ውሸት አይደለም ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ሌሎች ደግሞ “”ፖለቲካ የማሳመኛ ዘዴ ነው። ውሸት አይደለም። ውሸት የሚመጣው የማሳመኛ ዘዴ ሁሉ ሲያልቅ ነው” ይላሉ። ቶማስ ማን የተባለው ጀርመናዊ ፀሐፊ ደግሞ “ፖለቲካና የፖለቲካ ዕምነትን እጠላለሁ። ምክንያቱም ሰዎችን ዕብሪተኛ፣ ቀኖናዊ፣ ግትርና ጨካኝ ያደርጋቸዋል” ይለናል።
ለማንኛውም በሀገራችን “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ” ማለት ደግ ጸሎት ነው። ዲፕሎማሲውም ያው ነው፡፡ ኦስትሪያዊው ጸሐፊ ካርል ክራውስ “ዲፕሎማሲ ማለት ተደራዳራሪዎቹ አገሮች ንጉሦቻቸው መሄጃ-መላወሻ ሲያጡ (Checkmated) እንደሚባለው፣ የሚያጋጥሙበት የቼዝ ጨዋታ ነው” ያለውን ዓይነት ይመስላል። የተሻለ ቼዝ እንዲያጋጥመን እንመናለን።
መቼም ሀገራችን ዕድሜዋ በረዘመ ቁጥር የመነጋገሪ አጀንዳዋ እየበዛና እየተወሳሰበ ይሄዳል። የዲሞክራሲ መስፈን አጀንዳ፣ የዕድገት መኖር አለመኖር አጀንዳ፣ የውጪ ዕርዳታ መኖር አለመኖር አጀንዳ፣ የፖለቲካ ዕውነት መሆን አለመሆን አጀንዳ፣ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት አለመስፋት አጀንዳ፣ የዲፕሎማሲ መሳካት አለመሳካት አጀንዳ፣ የአገራዊ ምክክር ገለልተኛ የመሆን ያለመሆን አጀንዳ፣ ግጭት መቆም አለመቆም አጀንዳ፣ የፖለቲካ እሥረኞች መፈታት አለመፈታት አጀንዳ፣ የውጪ አገር አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ዝም ማለት አለማለት አጀንዳ፣ ….ቃለ-መጠይቅ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የእንደ-ፓርቲ አስተያየት፣ እንደ-ግል አስተያየት…ወዘተ ከዚያም የመረጃ እጥረት ከሌለ በስተቀር… የሰሚ ስሚ እንደሰማነው…እኔ እስከማውቀው ድረስ… ራሱ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል እስኪነግረን ድረስ ለጊዜው ይሄው ነው።… እኔ መረጃ እንደደረሰኝ… ስህተት ካለ እናስተካክላለን… የሚባለው ያ ነበር ግን ምን ያደርጋል ይሄ ሆነ ወዘተ… ማለት ብቻ ይሆናል ውጤቱ።
ነገሩ ሁሉ እቅጩነት ያለው መልስ ሳያገኝ፣ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሳይሰጠው፣ መሰንበት ባህሉ ሆነ። ብቻ የማታ ማታ
“አይጢቱ ድፍን ቅል ውስጥ ወለደች” ቢለው
“በምን ገብታ?” ብሎ ገርሞት ጠየቀው።
“እኸ! ጉዱ ምን ላይ ነው?” ብሎ ጨረሰው፤ የሚለው ምሳሌ ዓይነት እንዳይሆን ያሰጋል።



 እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ብሔራዊ  ምክክር ማድረግ በርካታ ፋይዳዎችን  ያስገኛል፡-

1.  የግጭት አፈታት፡- አገራዊ  ውይይቶች ወይም ምክክሮች  የረዥም ጊዜ ቅሬታዎችንና ግጭቶችን ለመፍታት መድረክ ይፈጥራሉ፤ በተለያዩ ቡድኖች መካከል እርቅን ለማውረድ ያስችላሉ፡፡            

2.  ሁሉን አካታች  አስተዳደር፡- አገራዊ  ምክክሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ፣ ሁሉን አቀፍና  ወካይ  የአስተዳደር መዋቅሮች እንዲፈጠሩ ያግዛሉ፡፡

3.  ህጋዊነትና መተማመን፡- እንዲህ አይነት ውይይቶች የፖለቲካ ሂደቶችንና ተቋማትን ህጋዊነት በማጎልበት በህዝቡ መካከል መተማመንን ይፈጥራሉ፡፡

4.  የፖሊሲ ቀረጻ፡- መጠነ-ሰፊ አመለካከቶችን ለመሰብሰብ እድል ይሰጣሉ፣ ይህም ሁሉን አቀፍና  ውጤታማ ፖሊሲ ለመቅረጽ ያስችላል፡፡

5. ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር፡- ብሔራዊ ውይይቶች መከፋፈልን ለማስወገድና የአገር አንድነት ስሜትን ለመፍጠር እንዲሁም የጋራ ዓላማን ለማጎልበት ይረዳሉ።

የተሳኩ  አገራዊ  ምክክሮች - ጥቂት አብነቶች፡

1.  ቱኒዝያ፡

   - ዳራ፡- እ.ኤ.አ ከ2011 አብዮት በኋላ ቱኒዚያ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችና  ማህበራዊ መከፋፈል ገጠማት።

   - ሂደት፡-  የሠራተኛ ማኅበራት፣ የአሰሪዎች ማኅበራትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ያቀፈው የቱኒዚያ አገራዊ  ምክክር  ኳርተር ውይይቱን አመቻችቷል።

ውጤት፡- ውይይቱ አዲስ ህገ መንግስት እንዲፀድቅ፣ የቴክኖክራት መንግሥት እንዲመሰረትና ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ አድርጓል። ኳርተሩ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ላበረከተው አስተዋጽኦ  የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸልሟል።

   - የተቀሰሙ  ትምህርቶች፡- አካታችነት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎና የጋራ መግባባትን መፍጠር ላይ ማተኮር ለስኬታማነቱ ወሳኝ ነበሩ፡፡


2.  ደቡብ አፍሪካ፡

   - ዳራ፡- እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአፓርታይድ ሥርዓት ማብቃት፣ አገሪቱ  ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትሸጋገር ዘንድ ግድ አደረገው፡፡

   ሂደት፡-  የደቡብ አፍሪካ ዲሞክራሲያዊ  ኮንቬንሽን (CODESA) በአገሪቱ የሚገኙ  የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ አሰባሰበ፡፡

   - ውጤት፡- አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲረቀቅና እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም  በአገሪቱ የመጀመሪያው የመድብለ ብሄር  ምርጫ እንዲካሄድ በር የከፈተ ሲሆን፤ ይህም  ኔልሰን ማንዴላን ወደ ፕሬዚዳንትነት መንበር  አምጥቷል፡፡

   - ቁልፍ ትምህርቶች፡- ለውይይት ቁርጠኛ መሆን፣ ስምምነት ላይ መድረስና  የወደፊት  የጋራ  ራዕይ መፍጠር  ለስኬታማነቱ ወሳኝ ጉዳዮች  ነበሩ።

3.  የመን (እ.ኤ.አ ከ2013-2014)

   - ዳራ፡- የአረብ አብዮትን ተከትሎ የመን ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ተለመች፡፡

   - ሂደት፡- ብሔራዊ የውይይት ኮንፈረንስ (ኤንዲሲ)፤ በአገሪቱ የሚገኙ  የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪል ማህበረሰብን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ሌሎች ቡድኖችን ያካተተ ነበር።

   - ውጤት፡- ሂደቱ በግጭት ቢቋረጥም፣ የአስተዳደርና የልማት መርሆችን የሚገልጽ ሁሉን አቀፍ  ሰነድ ማዘጋጀት ተችሏል፡፡

   - ቁልፍ ትምህርቶች፡- ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎና ክልላዊና ሃይማኖታዊ ችግሮችን  መፍታት ወሳኝ ነው፣ ምንም እንኳን ውጫዊና ውስጣዊ ግጭቶች አሁንም ከፍተኛ ፈተናዎችን ሊደቅኑ ቢችሉም፡፡


ኢትዮጵያ ከዚህ የምትማረው----

1.  አካታችነት፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ብሔረሰቦችና የተገለሉ ማህበረሰቦችን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው ቡድኖች ውክልናና ድምጽ እንዲኖራቸው ማድረግ።

2.  የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎ፡- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተጽእኖና ተአማኒነት በመጠቀም ሽምግልናና ውይይትን ማመቻቸት።

3.  በመግባባት ላይ ማተኮር፡- ውጤቶቹ በሰፊው ተቀባይነት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ፣ ከአብላጫ ድምጽ  ይልቅ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር አልሞ መሥራት፡፡

4.  ግልጽ ዓላማዎች፡- ግልጽ ዓላማዎችንና የውይይት ሂደቱን ትኩረትና አቅጣጫ ለመጠበቅ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት።

5.  ግልጸኝነት፡- በተሳታፊዎችና በህብረተሰቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ለመገንባት፣ በመላ የውይይት ሂደቱ  ግልጸኝነትን ማስጠበቅ፡፡

     6. አለም አቀፍ ድጋፍ፡- አገራዊ ውይይቶችን የማመቻቸት ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ  አካላት ድጋፍና ምክር መጠየቅ፤ ሂደቱ በአገር ውስጥ የሚመራና በባለቤትነት የሚቀጥል መሆኑን በማረጋገጥ።

ከእነዚህ አብነቶች  በመማር አገራችንም  የግጭቶቿን መንስኤዎች የሚፈታና ለወደፊት ሰላማዊና የብልጽግና መንገድ የሚከፍት ጠንካራና ውጤታማ አገራዊ የውይይት ሂደት መፍጠር ትችላለች። በዚያ መንገድ ላይ ነው ያለነው ብለን እንገምታለን፡፡ የተጀመረው አገራዊ ምክክር ይሳካ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ፣ በርበራ ወደብ በኩል ነዳጅ ለማስገባት መስማማቷን የበርበራ ከተማ ከንቲባ አብዲሽኩር መሃሙድ ሃሰን ተናግረዋል። ከንቲባው ይህንን የተናገሩት የሶማሌላንድ የነጻነት በዓል በአዲስ አበባ የሶማሌላንድ ኤምባሲ በተከበረበት ወቅት ነው።
አብዲሽኩር፤ ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርት የምታስመጣበትን ወደብ ወደ በርበራ እንደምትቀይር ያብራሩ ሲሆን፣ የገቢ ምርቶቿንም ለማስገባት ወደቡ ዝግጁ መሆኑን  ጠቅሰዋል።
ከንቲባ አብዲሽኩር መሃሙድ ንግግር ያደረጉት 33ኛው ዓመት የሶማሊላንድ የነጻነት በዓል ባለፈው ማክሰኞ  ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሶማሌላንድ ኤምባሲ በተከበረበት ወቅት ነው። እንደ ”በርበራ ታይምስ” ዘገባ፤ በዚህ ክብረ በዓል ላይ የኤምባሲው ባለስልጣናት፣ የሶማሌላንድ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ፖለቲከኞችና የፓርላማ አባላት ታድመዋል፡፡
ከንቲባው “ተደርጓል” ያሉት ስምምነት መቼ በትክክል  ወደ ስራ እንደሚገባ የገለጹት  ነገር የለም። እስካሁን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሌላንድ መንግስታት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል።
በስምምነቱ መሰረት፣ ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ ወደብ ስትሰጥ፤ ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና ትሰጣለች።
ይሁንና ሶማሊያ ስምምነቱን “ሉዓላዊነቴን የሚጻረር ነው” ስትል ክፉኛ መኮነንዋ አይዘነጋም፡፡ ሶማሌላንድ ከሶማሊያ ራሷን ገንጥላ ነጻነቷን ያወጀችው ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም. ላይ ነበር።

 ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭት በማገርሸቱ ሳቢያ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን  አስታውቋል። በኢትዮጵያ የኮሚቴው ቡድን መሪ ኒኮላስ ቮን አርክስ እንደተናገሩት፣ ኮሚቴው በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑ ሃይሎች ጋር በመገናኘት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕጎችን እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ እየወተወተ  ይገኛል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት፣ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ያደናቀፈ  ሲሆን፤ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ማሰራጨት ፈታኝ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አለመረጋጋቱ፤ የትግራይ ክልል ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው ተጽዕኖ ሕዝቡ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ተጠቁሟል።
“ችግሩን ለመፍታት በተወሰኑ አካባቢዎች እየተንቀሳቀስኩ ነው” ያለው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ከ100 በላይ የጤና ተቋማት ዕርዳታ ማሰራጨቱን ጠቁሟል፡፡
 ከእነዚህም ውስጥ በአማራ ክልል ለ62 የጤና ተቋማት፣ በኦሮሚያ ክልል ለ17፣ በትግራይ ክልል ለ20 እና በሶማሌ ክልል ለ6 የጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን  ኮሚቴው በድረ ገጹ  ባሰራጨው መረጃ ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ፣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የጤና እንቅስቃሴዎች አስተባባሪ ሲላስ ሙካንጉ፤ “በተለያዩ አካባቢዎች በግጭትና ጥቃት የተጎዱ ዜጎች ያሉበት ችግር አሳሳቢ ነው።
የሪፈር ስርዓት በመቋረጡ፣ ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት የሚያሻቸው ዜጎች ተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት አልቻሉም።” ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን፣ ታች ጋይንት ወረዳ፣ የእናት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ዲበኩሉ፣ በጸጥታ ሃይሎች መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል።  ”የአባላቱ እስራት የፖለቲካ ስብራታችን አንድ ማሳያ ነው” ብሏል፤ እናት።
ፓርቲው ሰሞኑን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ፤ አቶ ሰለሞን ዲበኩሉ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው የታሰሩት ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር። በአሁኑ ወቅት ሰብሳቢው በላይ ጋይንት ወረዳ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ እንደሚገኙ ነው ፓርቲው የጠቆመው።
አቶ ሰለሞን የታሰሩበትን ምክንያት የጸጥታ ሃይሎቹ እንዳልነገሯቸው እናት ፓርቲ በመግለጫው አትቷል። እስካሁን  የተመሰረተባቸው ክስ እንደሌለም ተጠቁሟል፡፡
 የአባላቱን እስራት “የፖለቲካችን ስብራት አንድ ማሳያ ነው” ያለው  ፓርቲው፤ “ትግላችን ሰላማዊ በመሆኑ መንግስት አባላቶቻችንን እያሳደደ ማሰሩን ያቁም” ሲል አሳስቧል።
የፓርቲው ሕግና ሥነ ስርዓት ክፍል ሃላፊ አቶ ዋለልኝ አስፋው ባለፈው ሰኞ  ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘው፣ ግራር ሰፈር ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ታስረው፣ በነጋታው ከእስር መፈታታቸው ከእናት ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ አድማስ የእናት ፓርቲ አመራሮችን በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ከሳምንታት በፊት እናት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር ባወጣው መግለጫ፤ በስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ለዚህ ውሳኔው ያቀረበው ምክንያትም፤ “ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ የለም” የሚል ነው።


የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21- 27 ቀን 2016 ዓ.ም ለሰባት ተከታታይ ቀናት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በአዲስ አበባ ያካሂዳል፡፡

 በነገው ዕለት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የመክፈቻ ሥነስርዓቱ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚከናወን ታውቋል፡፡

በዚህ የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ ከየወረዳው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ከ1700 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

”ይህ መድረክ ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ብዙም ባልተሄደበት ሁኔታ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እኩል የመምከር መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተሄደበት እርቀት ማሳያ ነው፡፡ የሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታችና አሳታፊ መሆን አንድ ማሳያም ነው፡፡“ ብሏል- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሚያከናውነው በዚህ  የምክክር ምዕራፍ፣ ከ2500 በላይ ተወካዮችን ተሳታፊ  እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡

ለሰባት ቀናት በተከታታይ የሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ፣ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት እንደሚከናወኑበት ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡ ይኸውም፡- በዚህ እርከን ላይ የሚገኙ ተሳታፊዎች በውይይትና በምክክር የአጀንዳ ሃሳቦችን ያመጣሉ፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ፣ ያደራጃሉ እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፤ በመጨረሻም የሂደቱ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ - ተብሏል፡፡

መርሃ ግብሩ፤ ኮሚሽኑ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን የያዙ አጀንዳዎችን በህዝባዊ ውይይት የሚሰበስብበት ምዕራፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይነት ኮሚሽኑ ተመሳሳይ መርሃግብሮችን በክልሎች ከተማ አስተዳደሮች እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፈው መልዕክት፤ ኢትዮጵያውያን የሚደረገውን የምክክር ሂደት ፋይዳ በመረዳት ዝግጅት እንዲያደርጉና በንቃት እንዲሳተፉ የጠየቀ ሲሆን፤ ለሂደቱ ስኬት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡