Administrator

Administrator

የማላዊ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ገብተዋል ያላቸውን 238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው  ሊመልስ መሆኑን አስታውቋል። ስደተኞቹ በማላዊ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኙ እስር ቤቶች ታስረው እንደቆዩ ተገልጿል።
የአገሪቱ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ስደተኞቹ የማላዊን ሕግ በመተላለፍ ወደ አገሪቱ  መግባታቸውን ጠቅሷል።
የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሳጅን ፍራንሲስ ቺታምቡሊ፤ “238 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት በዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ድጋፍ የሚከወን ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ “አሁን ላይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ከዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት አቻዎቻቸው ጋር በማዚምባ እና ምዙዙ እስር ቤቶች የሚገኙ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የመለየት ስራ ሰርተዋል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዘንድሮው ዓመት ጥር ወር አንስቶ በሰሜኑ የማላዊ ክፍል ለመግባት ሞክረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የውጭ አገር ስደተኞች ብዛት 173 ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 142 ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የ”ማላዊ 24” ድረ ገጽ ዘገባ ይጠቁማል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የማላዊ ፖሊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የነበሩ 29 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር ማግኘቱን ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ገልጾ ነበር። የጅምላ መቃብሩ የተገኘው ከማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ በስተሰሜን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሚዚምባ አካባቢ ነበር።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የቀድሞ የማላዊ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ልጅ የሆኑት ታዲኪራ ማፉብዛ፣ በጥቅምት 2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ውለው  የነበረ ሲሆን፣ ከእርሳቸው ጋር ሰባት ሰዎችም ታስረው ነበር። ይሁን እንጂ  ታዲኪራ ላይ የቀረቡት የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰውን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል ክሶች ባለፈው ረቡዕ፣ ከ19 ወራት በኋላ ውድቅ ተደርገው፣ ተከሳሹ ነጻ መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡
ማላዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚሸጋገሩ ስደተኞች ሁነኛ የመተላለፊያ መስመር እንደሆነች ይነገራል።

አንድ የአይሁዶች አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
አይሁዶች በአንድ ክፉ-አጋጣሚ የሆነ እርኩስ (እኩይ) መንፈስ ሲገጥማቸው፣ ያን መንፈስ ለማባረር ሦስት ነገሮች ያደርጋሉ ይባላል፡፡
አንደኛ- ወደ አንድ ጫካ ይሸሹና አንድ ልዩ ቦታ ይመርጣሉ፡፡
ሁለተኛ -እሳት ያነዳሉ፡፡
ሦስተኛ -ፀሎት ይደግማሉ፡፡
ይህንን ሲያደርጉ ያ እርኩስ መንፈስ ይሸሻል፡፡ ይጠፋል፡፡
አንድ አይሁዳዊ የዕምነት ሰው ከዕለታት አንድ ቀን እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ሰው ሦስቱን ህግጋት ያውቅ ስለነበር፣ ቶሎ ብሎ  ወደ ጫካ ይሄድና ቦታ ይመርጣል፡፡
እሳት ያነዳል፡፡
ቀጥሎም ይፀልያል፡፡ ይደግማል፡፡
እርኩስ መንፈሱ በንኖ ሄደ፡፡ ድራሹ ጠፋ፡፡
ሌላ ጊዜ አንድ ሌላ የዕምነት ሰው እንደዚሁ እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ሰው ሦስቱን ህግጋት ለመፈፀም ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡
ምቹ ቦታ ይመርጣል፡፡
መፀለይና መድገም ያለበትን ያሰላስላል፡፡
እሳት ማንደድ ግን አልቻለበትም፡፡
ያም ሆኖ እሳቱን ሳያነደድ ፀለየ፡፡ እርኩስ መንፈሱ ድራሹ ጠፋ፡፡
ሦስተኛው የዕምነት ሰው እንደዚሁ ከዕለታት አንድ ቀን እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡
ይሄኛው፤ ቦታውን ያውቃል፡፡
እሳት ማንደድ አይችልም፡፡
የሚደገመውን ፀሎትም አይችልም፡፡ ሊያስታውሰው አልቻለም፡፡ ያም ሆኖ ቦታውን በመምረጡና ወደዚያ በመሄዱ እርኩስ መንፈሱ ተሰወረ፡፡
የመጨረሻው የዕምነት ሰው እንደሌሎቹ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡
ይሄ ሰው ግን፤ ቦታውን አያውቀውም፡፡
እሳት ማንደድም አያውቅም፡፡
የሚደገመውን ፀሎትም አያውቀውም፡፡
ምን እንደሚያደርግ ሲያሰላስል ቆይቶ እንዲህ አለ፡-
“በቃ፡፡ ከዚህ ቀደም እርኩስ መንፈስ ያጋጠማቸው ሦስት የዕምነት ሰዎች ታሪክ ልናገር” አለ፡፡
የሦስቱን ሰዎች ታሪክ ተናገረ፡፡
የነሱ ታሪክ መነገሩ በቂ ሆነ! እርኩስ መንፈሱ ድራሹ ጠፋ፡፡
***
 ታሪኩ መነገሩ በቂ መሆኑን የሚያምኑና ታሪክ ለመናገር የሚችሉ ሰዎች ማግኘት መታደል ነው፡፡ እርኩስ መንፈስን ለማጥፋት ቦታ መምረጥ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸው እሰየው ነው! እርኩስ መንፈስን ለማግለል ፀሎት መድገም የሚችል ሰው ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ እርኩስ መንፈስ ለማጥፋት እሳት ማጥፋት የሚቻለው ሰው ማግኘት የሚችል ብልህ ሰው መኖሩን ማወቅ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ሦስቱንም ማግኘት በማይቻልበት ቦታ የሦስቱን ታሪክ የሚናገር ሰው ማግኘት አገር ማዳን ነው፡፡ እነማን ምን ሰሩ?  እነማን ምን አደረጉ? እነማን የት ዋሉ? ታሪክ የሚናገር ሰው መኖር አለበት፡፡ እርኩስ መንፈስን ያስወግዳል፡፡ “ፃዕ እርኩስ መንፈስ!” የሚል ሰይጣንን ከየውስጣችንም ሆነ ከየአካባቢያችን የሚያወጣ ደጋሚ ያስፈልገናል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውና በጣም ድንቅ የሚባሉ የዘመናችንን መጻሕፍት (ለምሳሌ እንደ Clashes of Civilizations /የሥልጣኔዎች ግጭት እንደ ማለት፣) ያሉ፤ የፃፈውና በፖለቲካ ትንተና ባለሙያነቱ የሚታወቀው ሳሙኤል ሀንቲንግተን፣ የመደብ ፖለቲካ እያበቃ ሲሄድ ሀይማኖት እናም ባህል የግጭት ማትኮሪያ ነጥብ ይሆናል ይለናል፡፡ ቀጥሎ፤ “የአንድ አገር ህዝብ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያለው እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ድርጅቶችና አስተማማኝ የፍትህ አካላት (ፍርድ ቤቶች) ሊኖሩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ውጤቱ የባሰ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መግባት ነው” ይላል፡፡ ሀገራችን የተረጋጋ ህልውና ይኖራት ዘንድ ዲሞክራሲ ያሻታል ሲባል፣ ያንን የሚተገብሩ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ያላቸው ተቋማት ያሻታል  የማለት እኩሌታ ነው፡፡ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ሲባልም ሀሳዊ-ዲሞክራሲያዊ (Pseudo-democracy) አለና ነው፡፡ አንድም በምሪት የሚሄድ ዲሞክራሲ (guided democracy) አለና ነው፡፡ የሚያማምሩ ዕቃዎች ስናይ በዐይናችን እንደምንማረክ፣ ውሎ አድሮ ግን በአገልግሎት ላይ ውለው ስናይ ከቶም ዕድሜ የሌላቸው ሆነው ስናገኛቸው እንደሚቆጨን ሁሉ፤ በመልካም ሀረጋትና ስሞች የሚጠሩ እንደ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ኮሙኒኬሽን፣ ኮሚሽን፣ ሚኒስቴር፣ ባለስልጣን፣ ኤጀንሲ፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፣ ዲሞክራሲያዊ መንግስት፣ ኮከብ አምራች፣ ሀቀኛ ካድሬ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ራእይ፣… ያሉ አያሌ መጠሪያዎች ተግባሪዎቻቸው በሌሉበት እንዲያው መጠሪያዎች ናቸው፡፡ የአራዳ ልጆች “የቻይና ሶኬት ስትገዛ፣ የሚይዝልህ ጩሎ አብረህ ግዛ” የሚሉት አባባል መንፈሱ ይሄው ነው፡፡ ተግባራዊነት ምኔም ወሳኝነት አለው፡፡ አፈፃፀምም አልነው ተግባራዊነት፤ “አንተ ዘፈን አልከው፣ እኔ ስልት ያለው ጩኸት አልኩት” ሁሌም ትርጉሙ ያው ነው እንዳሉት መምህር ያለ ነው፡፡
ምንም አይነት ጉዳይ ይሁን ምን፣ ምንም ዓይነት ለውጥ ይሁን ምን፣ ምንም ዓይነት ስያሜ ይሰጠው ምን፣ መለኪያው ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታው ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-አገር የሆነ አገዛዝ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ነው፡፡ ይህንን የሚናገሩ ታሪክ ተራኪዎች፣ አይጥፉ፡፡ የሚናገሩ አፎች አንጣ፡፡ የሚፅፉ ብዕሮች አይንጠፉ፡፡ “ላምህ ባትታለብ እንኳ፤ እምቧ ትበልልህ” ማለት ይሄው ነው፡፡ በፖለቲካዊ- ኢኮኖሚኛ “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ” ማለትም ነው፡፡

 አንድ ሰው አንዲት በጣም የሚወዳት ሴት ዘንድ ሄዶ “ዛሬ የት ውዬ እንደመጣሁ ታውቂያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡
ሴትዮይቱም፤ “የት ዋልክ የኔ ጌታ?” ትለዋለች፤ በፍቅር ቃና፡፡
ሰውዬው፤
“አንድ ጫካ ሄጄ፣ በእኔ ላይ ሸፍተው ከነበሩት ደመኞቼ ጋራ ተዋግቼ፣ ድባቅ መትቻቸው መጣሁ፤ በሙሉ ጨረስኳቸው” ይላታል፡፡
ሴትዮይቱ፤ “እንዲህ ነው እንጂ የኔ ጀግና! እኔ አንተን የወደድኩህ ለዚህ ለዚህ ታላላቅ ገድልህ ስል አይደል!” ትለዋለች፡፡
ሌላ ቀን ወደ ወዳጁ ዘንድ ሲመጣ፤ “ዛሬስ የት ሄጄ እንደመጣሁ ታውቂያለሽ?” ይላታል፡፡
“የት ዋልክልኝ የኔ ጀግና?”
“አንድ ጫካ ሄጄ፤ በእኔ ላይ ያደሙ ሽፍቶች አግኝቼ ጉድ አደረግኳቸው፡፡ አንድም ሳይቀረኝ ድምጥማጣቸውን አጥፍቻቸው መጣሁ!” ሲል ይፎክርላታል፡፡
ሴትዮይቱም፤ “እንዴ! የዛሬ ወር እዚያ ጫካ ሄደህ ድባቅ እንደመታሃቸው ነግረኸኝ አልነበር? ደግሞ ዛሬ ከየት መጡ?”
ሰውየውም ደንግጦ፤ “አይ ያኛው ሌላ ጫካ ነው!” ይላታል፡፡ ሴትየዋ ታዝባው ዝም ትላለች፡፡ ተጨዋውተው ይለያያሉ፡፡
ደሞ በሌላ ጊዜ ሲያገኛት፤ “ምነው ጠፋህ?” ትለዋለች፡፡
“ምን እባክሽ ወደ ጫካ ሄጄ ጠላቶቼን አንድ በአንድ ስለቅማቸው ውዬ፣ ድል በድል ተጎናጽፌልሽ መጣሁ፡፡ የመንደራችን ሰው ሁሉ “ጉሮ ወሸባዬ! እንዲያ እንዲያ ሲል ነው ግዳዬ!” እያሉ ነው ወዳንቺ የሸኙኝ፡፡”
ሴትየዋም ግራ በመጋባት፤ “እንዴ ባለፈው ጊዜ እዚያ ጫካ ሄጄ አሸንፌ መጣሁ አላልከኝም?” አለች ጥርጣሬዋ በግልጽ እየተነበበባት፡፡
“አ…ጫካው…ልክ ነሽ ያው ነው፡፡ ግን ጠላቶቼ፣ ….ሽፍቶቹ… ሌሎች ናቸው…”
ልቧ አልተቀበለውም፤ ግን ዝም ትለዋለች፡፡
አንድ ስድስት ወር አልፎ ሌላ ጊዜ መጣና፤
“እንደምን ከረምሽ? እኔ ጫካ ሄጄ ስንት ሽፍታ ዘርፌ ስመጣ፣ አንቺ የት ጠፋ ብለሽ እንኳ አልፈለግሽኝም?” ይላታል፡፡
ወዳጁም፤ “እንዴ ያንተ ጠላቶች አያልቁም  እንዴ? ይኸው በመጣህ ቁጥር ዘረፍኳቸው፤ ድባቅ መታኋቸው፣ ለቀምኳቸው ትለኛለህ?” ስትል የምሯን ተቆጥታ ትጠይቀዋለች፡፡
እሱም፤ “አይ እነዚህ የኔ ጠላቶች ሳይሆኑ የህዝቡ ጠላቶች ናቸው!” ይላታል፡፡
ሴትየዋ ጉራውና ውሸቱ በቅቷታልና፤ “በል ከዛሬ ጀምሮ እኔ ዘንድ ድርሽ እንዳትል፡፡ በየቦታው እየሄድክ እየቀበጣጠርክ ስላስቸገርክ፣ ቆርጦ-ቀጥል የሚል ስም እንዳወጡልህ ያልሰማሁ እንዳይመስልህ” ብላ በሯን ዘግታበት ወደ መኝታዋ ትሄዳለች፡፡ እሱም ተስፋ ቆርጦ ይወጣል፡፡
ሰነባብቶ አስታርቁኝ ብሎ የነፍስ አባትዋን አማላጅ ይልክባታል፡፡ ሴትየዋም ለነፍስ አባትዋ “ከእንግዲህ ወዲያ ከእሱ የምታረቀው፤ ይህን መዋሸቱን እንዲተው፤ ጠበል የሚረጩት ከሆነ ብቻ ነው!” ትላለች፡፡ የነፍስ አባትዋ በሃሳቧ ተስማምተው ሰውየው ዘንድ ሄደው፣ የውሸት ሰይጣኑንን እንዲያርቅለት ዳዊት ደግመው፣ ፀበል ከረጩ በኋላ፤ “በል ልጄ፤ አንድ ነገር ልንገርህ “ብልጥ ዋሾ፤ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ” ብሎ ይፀልያል!” አሉት፡፡
***
ከውሸትና ከዋሾ ይሰውረን ማለት የፀሎቶች ቁንጮ ነው፡፡ ከእርግማኑ አድነን እንደማለት ነውና፡፡  ስለ ዲሞክራሲ ውሸት፣ ስለ ሹም-ሽር  ውሸት፣ ስለ ሰላም ውሸት፣ ስለ ፍትህ ውሸት፣ ስለ ውስጠ-ፓርቲ ትግል ውሸት፣ ስለ ድል ውሸት፣ ስለ ታሪክ ውሸት፣ ስለ ዲፕሎማሲ ውሸት… ከመናገር ይሰውረን፡፡
የአንድ ሀገር የፖለቲካ ሂደት፤ ከተራ ቅጥፈት እስከ መረጃ ክህደት፤ ድረስ ከሄደ፤ እየዋለ እያደር “ሦስት የውሸት አይነቶች፡- ውሸት፣ የተረገመ ውሸትና ስታቲስቲክስ ናቸው” እንደሚባለው ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡
ልብ ብለን ካየነው ደግሞ፤ ማናቸውም የሀገራችን ፖለቲካ፤ አንዴ ውሸት፤ አንዴ እውነት እየተቀየጠ የሚመረትበት ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ አልፍሬድ ፔንሰን እንዳለው፤ “አይኑን በጨው ታጥቦ፤ ሽምጥጥ የሚያደርግን ቀጣፊ  ፊት ለፊት ሙሉ በሙሉ በመጋፈጥ ይፋለሙታል፡፡ ከፊል እውነት ያለበትን ውሸት ግን መዋጋት አስቸጋሪ ነው፡፡”
እርግጥ ነው፤ ውሸትን ለማጋለጥ መቻል ሌላው መታደል ነው፡፡ ለአገርና ለህዝብ ትልቅ አስተዋጽኦ አለውና፡፡ በ1950ዎቹ በአንጎላና ኬፕ ቬርዲ ዋና የፖለቲካ ተዋናይና የነጻነት ታጋይ የነበረውና እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ሲፋለም የወደቀው አሚልካር ካብራል ስለ ታማኝነት ሲናገር፤ “ከህዝባችን ምንም ነገር አንደብቅ፡፡ ምንም አይነት ውሸት አንዋሽ፡፡ የተዋሹ ውሸቶችን እናጋልጥ፡፡ ችግሮችን አንሸፋፍን፡፡ ስህተቶችን ቀባብተን ትክክል አናስመስል፡፡ ለህዝቡ የስራችንን መልካም መልካሙን ብቻ አናውራለት፤ ውድቀታችንን አንደብቀው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድል በቀላሉ ይገኛል ብለን አናስብ” ይለናል፡፡
የአሜሪካ ልብ ወለድ ደራሲና ጋዜጠኛ ኖርማን ሜይለርም፤ “በየቀኑ ጥቂት ጥቂት ውሸቶች የትውልድ ሀረጋችንን እንደምስጥ እየበሉ ያመነምኑታል፡፡ በጋዜጣ ህትመት ውጤት ትናንሽ ተቋማዊ ውሸቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚያ ላይ የቴሌቪዥን አስደንጋጭ ሞገድ ይጨመርባቸዋል፡፡ ከዚያ ደግሞ የስሜትን ስስ-ብልት የሚያማስሉና የሚያታልሉ የፊልም ሰሌዳዎች ይደመሩበትና ሙሉ ውሸት ይሆናል” ይለናል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን እዋሽ ነበር ብሎ የሚያስብ ሰው፤ የባላንጣዎቹን እውነት መቀበል አዳጋች ይሆንበታል” እንዳለው፤ ሀያሲው የጋዜጣ አዘጋጅ ሜንከል፤ ብዙ እውነቶች ከውሸት ጎራ ተደምረው ሲወገዙ ማየትም ያዘወተርነው ፍርጃ ነው፡፡
በተጨማሪም፤ እንደሚታወቀው በየአገሩ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የመዋሸት ፍቃድ የተሰጣቸው ብቸኛ ፍጡራን የሚመስሉበት ጊዜም አለ፡፡ “አገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የሀገር መሪዎች ለሀገሪቱ ደህንነት ሲሉ ይዋሹ ዘንድ ይፈቀድላቸው ይሆናል” እንዲል ፕላቶ፤ የጆሯችን ግዱ ያንን ማዳመጥ የሆነበት ወቅት አንድና ሁለት የሚባል አይደለም፡፡
ይህ የሆነው በአገራችን የፖለቲካ አየር ውስጥ እስከዛሬም ጠፍቶ ያለ አንድ ዋና ነገር አሁንም የጠፋ በመሆኑ ነው፡፡ ትናንት የተናገሩትን አሊያም የዋሹትን፣ ዛሬ አለማስታወስ እናም በተደጋጋሚ መዋሸት፡፡ መቅጠፍ፡፡ ማንም አይጠይቀኝም፣ ወይም ልብ- አይልም ብሎ መኩራራት፡፡ ይሄ ደግሞ ለዋሺም ለተዋሺም ጎጂ ባህል ነው፡፡ ውሎ አድሮም ህዝብ  ያልኩትን አያስታውስም አሊያም ለሱ ስል ነው የዋሸሁት ወደሚል ንቀትና ተአብዮ፣ ብሎም ወደ አምባገነንነት ሊመራ ችላል፡፡ “የረባ የማስታወስ ችሎታ የሌለው ሰው ከመዋሸት ቢታቀብ ይሻላል” የሚለው ገና በ15ኛው ክ/ዘመን ፈረንሳይ አገር የተነገረ ማስጠንቀቂያ ቢኖርም፣ እስከዛሬም ኢትዮጵያ የደረሰ አይመስልም፡፡
ያልሆንነውን ነን፣ ያላደረግነውን አደረግን ብለን መዋሸትና ራስን መገበዝ ፍፃሜው አያምርም፡፡
አንድ ልዑል መቃብር ላይ እንደተፃፈው ጥቅስ ማለት ነው፤
“ጀግና ነው ይሉታል ሣንጃ ሳይሞሸልቅ  
ጨዋ ነው ይሉታል ማላውን ሳይጠብቅ
ይህ ያገሩ ልዑል፣ ያገር ሙሉው ግዛት
በህይወቱ እያለ፣ አገር ምድሩ ጠልቶት፣
እዚያም እሰማይ ቤት-
ገነት ፍትህ ነሳው፣ ፊቱን አዞረበት፡፡”
እንዳንባል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ቢያንስ “ብልጥ ዋሾ፣ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ ብሎ ይፀልያል የሚለውን አባባል አትርሳ” የሚለውን አለመዘንጋት ደግ ነው፡፡
ማርክ ትዌይንም በምፀት፣ “ውሸት መፀለይ አይቻልም፤ ያንን ደርሼበታለሁ” የሚለው ውሸት ከልብ የማይመነጭ መሆኑን ሲያስረዳን ነው፡፡ የማይዋሽ የፖሊቲካ ሰው ይስጠን!



 - ነዋሪዎች ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ሰግተዋል


          በአማራና ትግራይ ክልሎች የ”ይገባኛል” ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ውጥረት መንገሱ ተገለፀ። ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የትግራይ ሃይሎች ወደ እነዚሁ አዋሳኝ አካባቢዎች መጠጋታቸው ነው ውጥረቱን የፈጠረው።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪ በአካባቢው ከአማራ ክልል ዞኖች በአንጻራዊነት የተሻለ መረጋጋት እንዳለ ይገልጻሉ። ይሁንና እርሳቸው “የህወሓት ታጣቂ” ያሉት የትግራይ ሃይል አደጋ መጋረጡን ጠቁመዋል።
“ይኸው ሃይል በጠለምትና በዋልድባ አካባቢ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው” ያሉት እኚሁ ነዋሪ፣ በቅርቡ “ሰሜን ጎንደርና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖችን በሚያገናኘው፤ አዲአርቃይ ወረዳ፣ አሊ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ‘ዱሃር ግዛና’ የሚባል ስፍራ ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ጥቃት 15 ንጹሃን መገደላቸውንና 3 ሰዎች መቁሰላቸውን ጠቁመው፤ ከጥቃቱ ተጎጂዎች መካከል ታዳጊ ሕጻናት እንደሚገኙበትም አስረድተዋል።
ከጥቃቱ ባሻገር፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ከ500 በላይ ከብቶችና 300 ፍየሎች በትግራይ ሃይሎች መዘረፋቸውን ነው የገለፁት።
ነዋሪው “ጥቃቱን አድርሰዋል” ያሏቸው ታጣቂ ሃይሎች መቀመጫቸው እንዳባጉና መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪው፤ “ሃይሉን የሚመሩት ወርቂ ዓይኑ የተባሉ ጄኔራል” መሆናቸውን አመልክተዋል። የታጣቂ ሃይሉ ብዛት ከ250 እስከ 300 ድረስ እንደሚገመትና “አርሚ 11” ተብሎ እንደሚጠራም አመልክተዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የትግራይ ሃይሎች ትጥቅ ሳይፈቱ መቅረታቸው የደህንነት ስጋት ጋርጦብናል የሚሉት ነዋሪው፣ “አሁንም ለሌላ ጥቃት እየተዘጋጁ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የሰሜኑ ጦርነት እንዳያገረሽ ስጋት አለን።” ብለዋል።
በራያ አካባቢ፣ ቀደም ሲል አላማጣ ከተማ ይኖሩ እንደነበርና አሁን ግን ተፈናቅለው ኮረም እንደሚገኙ የነገሩን አቶ አማረ ደሳለኝ የተባሉ መምሕር፣ የጸጥታውን ሁኔታ ሲያብራሩ፣ “በየትምሕርት ቤቶች የትግራይ ታጣቂዎች ገብተዋል። ሕዝቡ ተገቢውን ማሕበራዊ አገልግሎት እያገኘ አይደለም።” ብለዋል። በእነዚሁ ትምሕርት ቤቶች ውስጥ ታጣቂዎቹ የቡድን መሳሪያ ጭምር ይዘው መስፈራቸውንና መንግስታዊ ተቋማት ከስራ ውጭ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ አንድ የባለ ሶስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪ በትግራይ ሃይሎች መገደሉን ተከትሎ፣ በነጋታው ከቀብር ስነ ስርዓቱ በኋላ በአላማጣ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን የተናገሩት አቶ አማረ፤ በሰልፉ የተሳተፉ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ በእነዚሁ ሃይሎች ወረቀት መበተኑን  ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የራያ አካባቢ በአማራ ክልልም ሆነ በትግራይ አስተዳደር ስር አለመሆኑንና መደበኛ አስተዳደር አለመኖሩን በማመልከት፣ ሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እየከወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
“ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወደ ቆቦ ተጉዞ ነበር። ሆኖም መጠለያ አላገኘም። በቂ ዕርዳታ ከመንግስት አልቀረበለትም። ይህንን ተከትሎ ወደ አላማጣ ለመመለስ ተገድዷል። አንዳንድ በትግራይ ሃይሎች የሚታደኑ ግለሰቦች ከአላማጣ ሸሽተው ቆቦ ከትመዋል።”  ሲሉ ነዋሪው ጠቁመዋል።
ኮረም፣ ኦፍላ፣ ራያ አላማጣና አላማጣ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የራያ አካባቢዎች የትግራይ ሃይሎች እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ አማረ፣ ኮማንድ ፖስት በማወጅ የአማራ ክልል ግለሰቦችን ትጥቅ ከማስፈታት ባለፈ፣ የፌደራል መንግስቱ የሰጠው ተጨባጭ መልስ እንደሌለ ተናግረዋል።
ከወራት በፊት በፌደራል መንግስቱ፣ የራያ አላማጣ ነዋሪዎችን እንዲያወያዩ የተላኩት የአገር መከላከያ ሰራዊት አዛዦች፤ ከትግራይ ክልል ተፈናቃዮች እንደሚመጡ፣ የአማራ ክልል በራያ ያደራጀው የመንግስት መዋቅር እንደሚፈርስና በሕዝቡ ምርጫ መሰረት አዲስ የጋራ አስተዳደር እንደሚዋቀር መግለጻቸውን አቶ አማረ አውስተዋል።
አዲሱ አስተዳደር አሳታፊ የሆነ መዋቅር እንደሚኖረውና መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ጸጥታ እያስከበሩ ሪፈረንደም እንደሚደረግ ከአወያዮቹ መገለፁንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ቃል የተገባው ጉዳይ ተግባራዊ ከመሆን ይልቅ የትግራይ ታጣቂዎች የ”ይገባኛል” ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አልፈው ቀድሞም በአማራ ክልል አስተዳደር ስር ወዳሉ አካባቢዎች እየገቡ መሆናቸውን አቶ አማረ  አስታውቀዋል።
ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016  ባለው ጊዜ፣ በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተመሰረቱ “ሕገወጥ” ያሏቸው አስተዳደሮች ሊፈርሱ፣ ተፈናቃዮች ደግሞ ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ከፌደራሉ መንግስት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረው ነበር።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በበኩሉ፣ «ህወሓትና ግብረ አበሮቹ» ያላቸው አካላት፣ የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሱባቸውና ሰሞኑን በሃይል ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበርም መጠየቁ ይታወቃል።
በሌላ በኩል፤ ከሳምንታት በፊት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ፤ “የፌደራል መንግስት የህወሓት ታጣቂዎችን በወረራ ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እንዲያደርግና በተደጋጋሚ ወረራ እየተፈጸመበት ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጠው ህዝብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ” አሳስቦ ነበር።
እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ የፌደራሉ መንግስት የሰጠው ይፋዊ መግለጫም ይሁን ማሳሰቢያ የለም።



የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ፣ የኤርትራ ወታደሮች በኢሮብ ወረዳ 23 ትምሕርት ቤቶችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ  የወረዳው ትምሕርት ጽ/ቤት ጠቁሟል።
በወረዳው የትምህርት ፅህፈት ቤት ስር ከሚታወቁና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩት መካከል፣ አንድ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙባቸው 23 ትምህርት ቤቶች ከ3 ዓመት በላይ በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መቆየታቸው ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።
ከትምሕርት ቤቶቹ  ባሻገር፣ መምሕራንና ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅ እንዳልቻለ ተነግሯል።
በወረዳው አንጻራዊ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በመጪው ሐምሌ ወር ለሚሰጠው አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ታውቋል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በቂ የትምሕርት ቁሳቁስ አቅርቦት በሌለበት ለፈተና በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የዕገዛ እጃቸውን እንዲዘረጉ የወረዳው ትምሕርት ፅህፈት ቤት ጥሪውን አስተላልፏል።
ጦርነቱ ብዙ ነገሮች እንዳሳጣቸው የተናገሩ ተማሪዎች፤ አሁን በወረዳቸው ትምህርት ቤት የኢንተርኔት አቅርቦት ጨርሶ እንደሌለ ጠቁመዋል። በተጨማሪም የውሃ፣ የመብራት፣ የትራንስፖርትና የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት እንደሌለ ጠቅሰው ይህም በቴክኖሎጂ ታግዘው ከሚፈተኑ ተማሪዎች ጋር ተፎካካሪ ለመሆን አዳጋች እንደሚያደርግባቸው ነው የገለፁት።
እንዲያም ሆኖ፣ አሁን የተገኘው ዕድል እንዳያመልጣቸው ለመፈተን  በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተማሪዎች ተናግረዋል።
መምሕራን በበኩላቸው፣ በወረዳው ያሉት ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የክልሉና የፌደራል መንግስት ትምህርት ሚኒስቴር ዕገዛ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።
የኢትዮጵያ መንግስት፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት፣ በኤርትራ ወታደሮች ቁጥጥር ስር የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ነፃ እንዲወጡ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ፣ በኢሮብ ወረዳ የትምሕርት መሰረተ ልማት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መውደሙ የትግራይ ቴሌቪዥን ዘገባ ያመለክታል።

 - የወባ በሽታ ላይ የሚመክር ጉባኤ እየተካሄደ ነው


          የወባ በሽታ በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክልል፤ የአምራቹን ወጣትና  የሕጻናትን ሕይወት በመቅጠፍ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ።  በሽታው የሕልውና ስጋት ወደ መሆን ተሸጋግሯል ያሉት አዲስ አድማስ  ያነጋገራቸው  የክልሉ ነዋሪዎች፣ በበሽታው ተጠቂ የሆኑ ሕሙማን የህክምና አገልግሎት ባገኙበት በሁለትና በሦስት ቀናት ልዩነት ውስጥ እንደገና የበሽታው ምልክት ይታይባቸዋል ብለዋል። መድኀኒቱም የመፈወስ አቅሙ አናሳ እንደሆነ ተናግረዋል። በተደጋጋሚ ለበሽታው በመጋለጣቸው የተነሳ በአቅም ማነስ ሕይወታቸውን የሚያጡ ነዋሪዎች ቁጥርም ከቀን-ወደ ቀን እያሻቀበ መምጣቱ ተነግሯል።  
የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም፤ ወጣቶች፣ ሕጻናት እንዲሁም አምራቹ ገበሬና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በሽታው ሕይወታቸውን እያጡ እንደሆነ ከአካባቢው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቦንጋ ከተማ አገልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው የገብረጻዲቅ ሻዎ ሆስፒታል የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ፤ በአብዛኛው ሕጻናት በበሽታው ተጠቂ ሆነዋል። ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ከአንድ መቶ ታካሚዎች መካከል ሠላሳ ያህሉ የወባ በሽታ ተጠቂዎች እንደሆነም ታውቋል። የሕጻናት በሽታ የመቆጣጠር አቅም አናሳ በመሆኑ ለአዋቂዎች የተበጀውን መድኀኒት መስጠት ቀላል አለመሆኑን የሚገልጹት የጤና ባለሙያዎች፤ በማስታገሻ መልክ የሚወስዱት መድኀኒት እንጂ በዶዝ የተዘጋጀላቸው መድኀኒት ባለመኖሩ የተነሳ ሕጻናትን መፈወስ ከአቅም በላይ እንደሆነ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል፤ በገጠር አካባቢዎች የጤና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች፣ በቂ የመድኀኒት አቅርቦት እያገኙ አይደለም ተብሏል።
በአካባቢው የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ እንዳይራባና የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ የሚያስችል የኬሚካል ርጭት መስተጓጎሉን ያመለከቱት መረጃዎች፤ በተወሰኑ አካባቢዎች እንጂ በሁሉም ቦታዎች የኬሚካል ርጭት እንዳልተከናወነ ይጠቁማሉ።
በርካታ ሕሙማን መድኀኒት ጀምረው በማቋረጣቸው፣ እንዲሁም የክልሉ የጤና ቢሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ በሽታው ስርጭት፣ መከላከልና ስለ መድኀኒት አወሳሰድ እንዲሁም በጥንቃቄ አወሳሰድ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ያለመፍጠሩ የበሽታው ስርጭት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።   
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ በወባ ሥርጭትና መከላከል ላይ የሚያተኩርና ለስድስት ወር የሚዘልቅ ልዩ ዘመቻ ለመጀመር በሚዛን አማን ከተማ ትላንት አርብ ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የምክክር መድረክ ከፍቷል፡፡   
በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ባለስልጣናት፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የተለያዩ በወባ መከላከያ ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ተዘግቧል። በጉባኤውም የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ውይይቶችና ተግባራቶች ይከናወናሉ ተብሏል።

 አንድ ብልህ ንጉስ በከተማው ውስጥ ሦስት አዋቂዎች ነን እያሉ ህዝቡን ይመክራሉ፤ ያወናብዳሉ የሚባሉ ሰዎችን በተራ በተራ ጠርቶ ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፡፡
የመጀመሪያው አዋቂ እንደገባ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡-
“ህዝቡ ይውረድ ይውረድ እያለ እያስቸገረኝ ነው፡፡ እኔ ግን በስልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ፡፡ ምን ባደርግ ይሻላል?”
አንደኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ እርሶን የመሰለ ደግ ንጉስ ይውረድ ያለ ህዝብ ከእንግዲህ ሊታመን አይገባውም፡፡ ይልቁንም ሊቀጣ ይገባዋል፤ ስለዚህ ለመቀጣጫ ከህዝቡ መካከል ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን በአደባባይ ይቅጧቸው፡፡ ያኔ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” ሲል መለሰ፡፡
ሁለተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቡ ያላንተ መኖር አንችልም፤ ለዘላለም ቆይልን እያለ አስቸገረኝ፡፡ እኔ ግን ስልጣኔን ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ ኑርልን የሚለኝ እውነቱን ይሁን ውሸቱን ለማወቅ ተቸግሬያለሁ፤ ምን ትመክረኛለህ?”
ሁለተኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ ይህን ህዝብ አይመኑት፤ ይኑሩልን ሲል ይሙቱ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማወቅ ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን አስጠርተው በአደባባይ ቢቀጡ ማታለሉን ትቶ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” አለ፡፡
በመጨረሻም ሦስተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቤ ይውረድም አይለኝም፡፡ ይኑርም አይለኝም፡፡ ዝም ብሎ እየተገዛ ነው፡፡ የልቡን ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሦስተኛው አዋቂም፤
“ይህን ህዝብ አይመኑት፡፡ ይኸኔ ሴራ እየጎነጎነ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ተጠሪ ናቸው የሚባሉትን ሽማግሌዎች አስጠርተው ሸንጎ ፊት ቢያስገርፏቸው የተዶለተችው በሙሉ ትጋለጣለች፡፡”
ከዚህ በኋላ ንጉሱ ህዝቡ እንዲጠራ አዋጅ አስነገረና፤ ህዝብ ሲሰበሰብ እንዲህ አለ፤
“እነዚህን ሦስት አዋቂዎች አስጠርቼ ህዝቡ ይጠላኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ ይወደኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ መውደዱንም መጥላቱንም አልነግር አለኝ ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ምን ታስባላችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ህዝቡም መክሮ ሲያበቃ በተወካዩ በኩል መልስ ሰጠ፡፡ ተወካዩ የአገር ሽማግሌ፤
“ንጉስ ሆይ፤ ከህዝቡ ጋር ስንመክር አንድ እልባት ላይ ደረስን፡፡ እነዚህ ሦስት አዋቂዎች በተለያየ ጊዜ ስለ እርሶ ጠይቀናቸው የመለሱልን መልስ ’ንጉሱን አትመኗቸው’ የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም በወዲህም ወገን በወዲያም ወገን፤ መተማመን እንዲጠፋ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሊቀጡልን ይገባል” አሉ፡፡
ንጉሱም፤
“እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ፤ ስለሆነም ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ያም ሆኖ ለእናንተ አንድ ምክር ልምከራችሁ፡፡ ሁልጊዜ ተነጋገሩ፡፡ ተመካከሩ፡፡ ግልፅ ሁኑ፡፡ ጥፋት ስታገኙ ጥፋተኛውን ቅጡ፤ ንጉስ ያልፋል መንግስት ይለወጣል፤ ሁሌም ነዋሪው ህዝብ ነው” ሲል ነገራቸው፡፡
***
ብልህ ንጉስ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የአገር አዋቂዎች ማጣት መረገም ነው፡፡ የሚመካከር ህዝብ መላ ያገኛል፡፡ ችግሩን የማይፈታ ህዝብ በሽታውን እንደደበቀ ህመምተኛ ነው፡፡ ግልፅነት ሲኖር እውነት ወደ አደባባይ ትወጣለች፡፡ ግልፅነት ከመሪዎችም፣ ከምሁራንም፣ ከህዝብም የሚጠበቅ ፍቱን ወርቅ ነው፡፡ ግልፅነት ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ ከሆነ ሌላውን ወገን መሸፈኛ፣ የተንኮል ጭምብል ይሆናል እና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ግልፅነት አለቃ ምንዝሩ የሚተችበት መሳሪያ ብቻ ተደርጎ አንዱን ንፁህ፣ አንዱን አዳፋ፣ አንዱን ቀና፣ ሌላውን ጎልዳፋ ብሎ ለመፈረጅ፤ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ ግልፅነት ሁሉም ላይ የሚሰራ፣ ለሁሉም የሚያገለግል መርህ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
ግልፅነት ከብልጥነት መለየት አለበት፡፡ ግልፅ ነኝ ማለት ድብቅነትን መሸፋፈኛ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አዋቂ ሳይሆኑ የወቅቱን መፈክር በማንበብ ብቻ አዋቂ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት አይደለም፡፡ ከስህተት ሳይማሩ ከስህተት የተማሩ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት ከቶ አይደለም፡፡ በአፍ ቅቤ፣ በልብ ጩቤ ይዞ መቅረብ ግልፅነት አይደለም፡፡ “ብቅል ለመበደር የምትሄድ ብቅል ያላስቀመጠችውን ምን ሴት ትባላለች! ትላለች” እንዲሉ፤ አንዱ ካንዱ ላይሻል ነገር፣ ጥፋተኛ እራሱን እንከን-የለሽ አድርጎ ሌላውን ጥፋተኛ ሲወቅስ፤ ያኛውን አጋልጦ እራሱን ሸሽጓል እና ግልፅነት እሱ ዘንድ የለም፡፡ የግልፅነት ስርአት ሁሉን-አቀፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእሙናዊው ተግባር የፈለቀ መሆን አለበት፡፡ ግልፅነት ከሁሉ አስቀድሞ እውነተኝነት መጠየቁ ለዚህ ነው፡፡
የአስተዳደግ ጉድለት፤ የአስተዳደር ጉድለትን ያስከትላል፡፡ እራሱ በወጉ ሀላፊነት ያልተረከበ፣ እራሱ እድገቱን ያላግባብ የወሰደ፤ እራሱ ሹመቱን በኢርትኡ መንገድ የነጠቀ ሰው ስርአት ያለው አስተዳደር ለማስፈን ይቸግረዋል፡፡ ይልቁንም “ብልጥ ሌባ የቆጮ መቁረጫ ትሰርቃለች” እንደሚባለው፤ ከቆጮውም ይልቅ መቁረጫውን ይዟልና ህግ አውጭውም፣ ፈራጅም፣ ገምጋሚም አስገምጋሚም፣ ሰብሳቢም፣ መራጭም፣ ሆኖ ሁሉን ከእፍታው ይጨልፋል፡፡ ጠያቂ የለበትምና ልቡም እጁም አያርፍም፡፡ ሙስናን ለማስፋፋት ቅርብ ሆነ ማለት ነው፡፡ የአገርና የግለሰብን ጥቅም ያደበላልቃል፡፡ የተማረረን ከተማረ በላይ ያደርጋል፤ ባለሙያነትንና ባለእውቀትነትን ከአፋዊ ችሎታ በታች ያያል፡፡ ይህን መሳይ ድርጊት ሁሉ የመልካም አስተዳደር አለመምጣት መርዶ ነው፡፡ ያ በፈንታው የዲሞክራሲን በር ይዘጋል፡፡ የሰላምን ውጋጋን ይጋርዳል፤ የፍትህን ሚዛን ይነጥቃል፡፡
በተለይ እጅግ ወቅታዊ የሆኑትን፤ የሀገርም ሆነ የአገርና አገር ጥያቄዎችና ችግሮች በዲሞክራሲያዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አፍጦ የመጣበት ሰአት ነው፡፡ የችግር ቅደም-ተከተልን ጥያቄ (prioritization) ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሁኔታና ከተጎራባች አገሮቿ እንዲሁም ከሉላዊ እንቅስቃሴና መስተጋብር (global action and interaction) ጋር አጣጥሞ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ ለአቻ ቦታ አቻ ሰው መድቦ መራመድ ከወደቁ ወዲያ ከመንፈራገጥ ማዳን ብቻ ሳይሆን እስከ ፍልሚያ ሜዳ ያለውን ጎርበጥባጣና ኩርንችታማ ጎዳና ለመጥረግ በቅጡ ያግዛል፡፡ ጦርነት የሰላማዊ መንገድ መሟጠጫ እንጂ መነሻ መሆን በጭራሽ የለበትም፡፡ አለመዘናጋት ግን ሁሌም ወሳኝ ነው፡፡
የጥንቱ የጠዋቱ ሼክስፒር በሀምሌት ውስጥ “ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም፣ አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!” (ፀጋዬ ገብረመድህን እንደተረጎመው) ያለውን አለመርሳት ደግ ነው፡፡
ረጅም መንገድ አለብኝ ብሎ በርካታ ስንቅ የጫነ ሰው፤ ስንቁን ቅርብ ቦታ መጨረስ የለበትም፡፡ በትንሽ እንቅፋትም መውደቅ የለበትም፡፡ ነገ ሰፊ የምርጫ ትግል ያለበት የዛሬ አዘገጃጀቴ “የሚወጋ ጦር ከእጅ ሲወጣ ያስታውቃል” አይነት መሆን አለበት፡፡ የብዙዎችን ተሳትፎና ድጋፍ በጠዋት ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ መፎካከር ለማሸነፍ ብቻ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ነገም እንደዛው መሆኑን አውቆ መጓዝ ያሻል፡፡ መጋቢ ጅረቶች ሁሉ ወደ ወንዝ ለመቀላቀልና የአገር ሃይል ለመሆን እንደሚችሉ አጢኖ፤ ጊዜ መውሰድ አቅጣጫ ማግኘት ያሻዋል፡፡ ጊዜያዊ የሀገር ጉዳዮችን ከዘላቂ ፍሬ ነገሮች አነፃፅሮ አንዱ በሌላው እንዳይጋረድ ደህና አደርጎ ማስተዋል የሁሉም ድርጅቶች አጓጓዝ መሆን አለበት፡፡
ዳምኖም አጉረምርሞም ላይዘንብ እንደሚችል ሁሉ፣ ዘንቦም ሙሉ ጥጋብ ላይሆን እንደሚችል፣ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከህዝብ ያልመከሩበት፣ ህዝብን ያላሳተፉበት አካሄድ መሰረት-የለሽ ፒራሚድ ነው፤ ብዙ እድሜ የለውም፡፡ በአጭር ጊዜ ፈተና ይዳከማል፡፡ አዋቂዎቹን እንደፈተሸው ብልህ ንጉስ፣ ጠያቂ የመጣ እለት በአደባባይ መጋለጥ ይከተላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በቅንጣት ጥያቄ ግዙፍ ሀጥያት ይታያል፡፡ የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል የሚባለው እንግዲህ ያኔ ነው!

   • በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር ፍ/ቤት አልቀረቡም ተባለ
                 • አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ


        በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በአዋጁ ድንጋጌ መሰረት በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡ ኮሚሽኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችም  እንዲነሱ ጠይቋል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ፣ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው የነበሩ 19 እስረኞች፣ “የተሃድሶ ስልጠና” ከወሰዱ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ከእስር መለቀቃቸው ተዘግቧል፡
ኢሰመኮ ላለፉት 10 ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ በመከታተል፣ በአፈፃፀሙ ላይ ያሉ ጥሰቶችንና ክፍተቶችን ሲመረምር የቆየ ሲሆን፤ ግኝቶቹም በተከታታይ ሪፖርቶች  ታትመዋል፡፡
ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን በተመለከተ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም  ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በክልሉ በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሳሳቢ መሆናቸውን አስታወቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ በአዋጁ የተያዙ እስረኞችን መፍታት፣ ወደ መደበኛ የህግ ማስከበር አሰራር መመለስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ  የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ በአፅንዖት አሳስቧል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታሰሩት ግለሰቦች  መካከል  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለውና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል አቶ ካሳ ተሻገርን የመሳሰሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች  ይገኙበታል።
በፌደራል መንግሥትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተባባሰ የመጣውን ግጭት ተከትሎ፣ ባለፈው ዓመት ሃምሌ መጨረሻ ላይ  በአማራ ክልል ለ6 ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የሚታወስ ሲሆን፤ ፓርላማው የመጀመርያው የስድስት ወራት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት ማራዘሙ ይታወቃል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል፣ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ ከሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ በተጨማሪ አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ  ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አቶ የሺዋስ አሰፋ “ሁከት በማነሳሳት” መጠርጠራቸውን አንድ የቤተሰብ አባል መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ፣ ህዳር 30 የተጠራው ሰልፍ አስተባባሪ ነበሩ የተባሉት አቶ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ ባለፈው ረቡዕ  መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  


• ፕሮዱዩሰር የዘፋኙን ሥራ ያቀላል፤ ጫና ይቀንሳል
         • የትም ቢሆን ለእኔ ተብሎ የሚደረግ ሸብረብ የለም
         • አብዛኞቹ ሥራዎች እኔን ለምለምን ይመስላሉ


       ባለፈው ሳምንት ዕትማችን ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከድምፃዊት ለምለም ሃይለሚካኤል ጋር ያደረገችው ጣፋጭ ወግ የመጀመሪያ ክፍል ለአንባቢያን የደረሰ ሲሆን፤ ቀጣዩ ወጋቸው ደግሞ እነሆ እንደሚከተለው ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡ በዚህ ቃለ መጠይቅ ድምጻዊቷ በአዲሱ አልበም ውስጥ ስለተካተቱት ሥራዎች፣ ስለ ዝነኝነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ”ማያዬ” ስለተሰኘው የአልበሙ መጠሪያ ዘፈኗ፣ ስለ ቤተሰቦቿና የወደፊት ዕቅዷ በስፋት ታወጋለች፡፡ አንብቡት ትወዱታላችሁ፡፡


         ኤልያስ መልካ አንቺን ከ“ሚሚነት” ወደ “ለምለምነት” ለመቀየር ሲያደርግ የነበረውን ጥረት እያወጋሽኝ ነበር ጨዋታችንን በይደር ያቆየነው።  እስቲ ከዚያው እንቀጥል----
መልካም! እንዳልኩሽ በተለያዩ ሂደቶች እኔ ከሚሚ ወደ ለምለም ከተቀየርኩና እሱ ላይ እርግጠኛ ከሆነ በኋላ ደግሞ ለለምለም ምን አይነት ዘፈን ይሰራ፣ በለምለም ምን ዓይነት መልእክት ማስተላለፍ ይቻላል፣ ለምለም እንዴት ነው የምትዘፍነው? አልበሟ ምን ይሁን? ወዘተ-- በሚሉ ጉዳዮች ላይ ብዙ ሙከራዎች (ኤክስፐርመንቶች) ስንሰራ የቆየንባቸው ጊዜያት ናቸው- አምስቱ ዓመታት። ሦስቱን ስራዎች እየሰራን ሳለ ታዲያ  ኤልያስ መልካ ጤናው እየታወከና እየደከመ ሲመጣ፣ ሌሎች ቦታዎች ሄጄ መስራት እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ነው ወንደሰን ይሁብን ያገኘሁት። ከወንደሰን ጋር ከተገናኘን በኋላ የመጀመሪያውን ነጠላ ዜማዬን ሰራሁ።
የትኛውን ማለት ነው?
“ገዳም” የሚለውን ሥራ ማለቴ ነው። እሱን ስራ ወስጄ ለኤልያስ አሳየሁት። ቆንጆ እንደሆነ ነገረኝ። እናም በዚህ መልኩ እንደምችል ነገረኝ ማለት ነው።
ወንደሰን ይሁብ ምን አይነት ባለሙያ ነው?
ኦኦ! በጣም ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ከፍተኛ የሥራ ፍላጎት ያለው አስደናቂ ልጅ ነው፤ ወንድወሰን። ከኤልያስ ጋር የቆየሁበትና ከወንድወሰን ጋር የቆየሁበት ጊዜ ይለያያል። እዚህ በጣም ፍጥነት አለ። አልበሜን ከዚህ ልጅ ጋር ብሰራ የሚል ስሜት አደረብኝና፣ “ወንዴ፤ አልበሜን አብረን ብንሰራ ምን ይመስልሃል?” አልኩት። እሱም በደስታ ተቀበለኝ፤ ከዚያም በአራት ዓመታት ውስጥ ሰርተን ጨረስን ማለት ነው። እውነት ለመናገር እንደፍጥነታችን አራት ዓመት ላይፈጅ ይችል ነበር። እኔ በመሃል ወለድኩ፤ ኮሮና ገብቶ እንቅስቃሴ ተገደበ። በዚህ በዚህ ምክንያት አራት ዓመት ፈጅቶ ይኸው ለአድማጭ ቀርቧል። ከኤልያስ ጋር የአልበሙ መጠሪያ የሆነውን “ማያዬ”ን፣  “ከፍቶኝ”ን እና ኦሮምኛውን “ውሊሊ”ን ነው የሰራነው። ቀሪዎቹ ከወንድወሰን ይሁብ ጋር የተሰሩ ናቸው። ወንድወሰን የአልበሙ ፕሮዱዩሰርም ነው። በነገራችን ላይ በአብዛኛው የፕሮዱዩሰር ሚና በግልጽ አይታወቅም ወይም በደንብ አልተነገረም። ምናልባት በፊት እነ አበበ መለሰ፣ ይልማ ገብረአብና አበበ ብርሃኔ ፕሮዱዩስ ያደርጉ ነበር። ይሄ ማለት ራስሽ ግጥም መርጠሽ ዜማ መርጠሽ፣ አልበሙ እንዲህ ይሁን ብለሽ ነው የምትሰሪው። ይሄ የማላውቀው ስለሆነ ከባድ ነበር። ስለዚህ ወንድወሰን ይህንን ሁሉ አድርጎ ነው አልበሙ ለውጤት የበቃው። ፕሮዱዩሰር ሥራ ያቀላል፣ ጫና ይቀንሳል። ከዚያ ባለፈ ሙያን ለባለሙያው መስጠትም ተገቢ ነው። ወንደሰን በዚህ የተካነ ስለሆነ 8 ሙዚቃዎችን መርጦ፣ ግጥሞቹን ግማሹን ጽፎ፣ ግማሹን አፅፎ ነው የሰራልኝ። በዚህ አጋጣሚ በጣም  ነው የማመሰግነው። ለሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ልጅ ነው።
ከዘፈኖችሽ ሁሉ አብልጠሽ የምትወጂው የትኛውን ነው? በእርግጥ ሁሉም ልጆቼ ናቸው እንደምትይኝ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን ከጣት ጣት ይረዝማል እንደሚባለው፣ አንድ ምረጭ ብትባይስ?  እኔ ለምሳሌ የብዙ ሚስቶችን መቃተትና ለትዳራቸው የሚከፍሉትን መስዋዕትነት የሚያንጸባርቀውን “እንዳትጠላው” የሚለውን ዘፈን ነው የበለጠ የወደድኩት፡፡ አንቺስ ምን ትያለሽ?…
በነገርሽ ላይ “እንዳትጠላው” የተሰኘውን ግጥምና ዜማ የሰራልኝ ሀብታሙ ቦጋለ ነው። በጣም ጎበዝና ሀሳብ ያለው ገጣሚ ነው። እኔ ከሀብታሙ ጋር በመስራቴ ደስተኛ ነኝ። ሀብትሽ በ90ዎቹ ወርቃማ ሙዚቃዎች ላይ ዳሰሳ ተደርጎ ቢጠና፣ አብዛኛዎቹ የእሱ ናቸው፡፡ እኔ በጣም ነው የምወደው። እዚህ ሙዚቃ ላይ ልክ አንቺ የተሰማሽ  አይነት ስሜት እኔም አለኝ። የኔም ያንቺም የሁላችንም ህይወት ነው። ሲጀመር የተሰራበትም መንገድ እንደገለጽሽው ነው። እኔ ለበዓል ሰራተኛዬ ሄዳብኝ፣ ጠዋት ሲደውልልኝ መወልወያ ይዤ ቤት እየወለወልኩ ነበር። ደውሎ “ሊሊ የሆነ ዘፈን  ሰራሁልሽ” አለኝ። ሀብታሙ ሲነግርሽ ሀሳቡ ነው ከዜማው ቀድሞ የሚገባሽ። ሲነግረኝ፤ “እኔ አሁን ኤግዛክትሊ እዛ ሁኔታ ውስጥ ነኝ፤ ቤቴን ቤቴን እያልኩ ነው፤ ጨርስና ደውልልኝ” አልኩት። ማታ ሙዚቃውን ጨርሶ ልኮልኝ ካዳመጥኩት በኋላ፣ ”ሳላውቅ ብዙ ነገር አጫውቼሃለሁ እንዴ?” ነው ያልኩት። በዚህ ብቻ ሳይሆን በአልበሙ ውስጥ ባሉ በአብዛኞቹ ዘፈኖች ውስጥ ራሴን አገኘዋለሁ። በስሜት እጋራቸዋለሁ። ዘፈኖቹን ከዚህኛው ያኛው ይበልጣል አልልሽም። “ማያዬ” ለኔ ማመስገኛዬ፣ ሁሉን መመልከቻዬ ማለት ነው። “ማያ” ሁለተኛ ልጄ ናት። በውስጡ ትልቋ ልጄ “አና” አለች። ማያዬ ስል መስታወቴ፣ አይኔን ባይኔ ያየሁባቸው ልጆቼ፣ የፈጣሪን ድንቅ ስጦታ ያየሁበት ነው። ሙዚቃው ፆታው ተባዕት ነው። ነገር ግን እኔ የምዘፍንበት ስሜት የተለየ ነው። ይሁን እንጂ አድማጭን ሙዚቃውን በእኔ አይን እዩልኝ አልልም። ሁሉም እንደየስሜቱና መረዳቱ ሊያጣጥመው ይችላል። በአጠቃላይ አብዛኛዎቹ ሥራዎች እኔን ለምለምን ይመስላሉ።
እንግዲህ  ከወንድወሰን ጋር ጓደኝነቱም ስላለን አብረን ብዙ ጊዜ እናሳልፋለን። የኔም ስራ ሳይኖር ስቱዲዮ ቁጭ ብዬ ሲሰራ እያየሁ እናወራለን፣ እንወያያለንና ከዚህ አንፃር፣ ሃሳቤን ፍላጎቴን ተረድቶኝ ይሆናል እኔን የሚመስሉ ሃሳቦች የተፃፉት እላለሁ። እኔ አንድ ለምለም ነኝ፤ በአንድ አይነት የማህበረሰብ ስነልቦና ውስጥ ስታድጊና ስትኖሪ ስሜቶችን ትጋሪያለሽ። ስለዚህ አብዛኛው በአልበሙ የተነሱ ሃሳቦች የኔም ሃሳብ ናቸው ብዬ አምናሁ።
በአዲሱ አልበምሽ ጎጃምንም አሽሞንሙነሽል፣ ኦሮሚኛም አለ፣ የሙዚቃ ቡፌው በስፋት ነው። ኦሮሚያ ተወልደሽ ከዚያ ወደ መሃል አገር መጣሽ፣ በስራሽ ምክንያት ብዙ የአገሪቱን ክፍሎች ተዘዋውረሽ አይተሻል። ታዲያ ያንቺ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?
ኢትዮጵያ ለኔ ላንቺ እንደሆነቺው ናት። ስለ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከኔ የበለጡና የላቁ ሰዎች ብዙ ብለዋል። የእኔን ኢትዮጵያ ስለጠየቅሽኝ ግን፤ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ራስን መሆን ነው። በስራ አጋጣሚ በተለያዩ የሀገሬ ክፍሎችም ውጪም ሄጄ ብዙ ነገር የማየት የመታዘብ ዕድል አግኝቻለሁ። ሰው በዚህ ደረጃ እንዴት አገሩ ይናፍቀዋል? እዚህም ሆነሽ ስለ ኢትዮጵያ ሲዘፈን፣ ሌላ አገር ሆነሽ አገርሽ እንደሚናፍቅሽ አይነት ስሜት ይሰማሻል። ስለዚህ ኢትዮያዊነት ለኔ ማንነቴ በራስ መተማመኔም ነው። ኢትዮጵያዊነት ሰው መሆንና ቀና ብሎ መሄድ ነው ለኔ። ኢትዮጵያን ተዘዋውሬ ሳይ ብዙ አንድ አይነትና እንደገና ብዙ ልዩነትም አለ። ያ ልዩነትም ይመስለኛል ኢትዮጵያዊነትን ውብ የሚያደርገው። ሁሉም አንድ አይነትና ወጥ ሲሆን  አሰልቺ ነው። ኦሮሚያ ላይ ተወልጄ አማራ ስሄድ ብዙ ደስ የሚሉ አዳዲስ ባህሎችን አይቻለሁ። መቀሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሄድ፣ ወላይታ ስሄድ፣ ቦረናን ስቃኝ አንድ አይነትም ልዩነትም አይቻለሁ። ውብና ድንቅ ነገሮች። የሰዎችን ፍቅር፣ ሩህሩህነት አይቻለሁ። ፍቅርና ሩህሩህነታቸውን የሚገልጹበት ቋንቋ የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ግን ሁሉም ሩህሩህና ፍቅር ናቸው።
ለምሳሌ ኦሮሚያ ሆነሽ ቦረናና ባሌን የሚያመሳስለው፣ የሚያለያየው ነገር አለ። ባሌ ተወልደሽ ወለጋ ብትሄጂ፣ ኦሮሚያ ኦሮሚያ ነው፤ ግን  የሚለያይ በርካታ ነገር አለ። ነገር ግን ብዝሃነት (ዳይቨርሲፊኬሽን) በራሱ የኢትዮጵያ መልክ ነው። ይህንን በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት የማታገኚባቸው ቦታዎች ይኖራሉኮ!! በእርግጥ ኬንያ ሄደሽ አንድን ኬንያዊ ብትጠይቂው፣ የእኔን አይነት መልስ ሊሰጥሽ ይችል ይሆናል። ኢትዮጵያዊነት ለኔ ግን በቃ ማንነቴ፤ ነጻነቴ ነው። በራስ መተማመኔ፤ የተቀረፅኩበት ሰብዕናዬ ጭምር ነው።
በአልበሙ ብዙ መልዕክቶች ተላልፈዋል። ለምሳሌ “አስከትዬ” የተሰኘው ዘፈንሽ በገፉት ንፁህ ፍቅር መፀፀትን የሚያንፀባርቅ ነው፣ ስለ ልጅነት ፍቅር ያቀነቀንሽው አለ። ስለ ጎጃም የተዘፈነው “ደገምገም”  ወዝወዝ የሚያደርግም ነው። ሀሳቡም ድንቅ ነው። ነገር ግን “ከፍቶኝ” የተሰኘው ዘፈንሽ ላይ
ከፍቶኝ የቆየ አይመስለኝ
ባይኖር አለሁ የሚለኝ
ምክንያት ሆነልኝ ከላይ
ዘመን እራሴን እንዳይ
ጊዜ ጊዜማ ጊዜ
ሲሆን የባለ ጊዜ
ወትሮም በዓለም የፀና
የታል ሰው ሆኖ ጀግና።…
 እያለ በሚቀጥለው ዘፈንሽ…በተለይ “ጊዜ ጊዜማ ጊዜ ሲሆን የባለጊዜ” የሚለውን ሀረግ ሰዎች ብዙ ጊዜ “ተረኛ ባለጊዜ” እየተባለ ከሚነገረው ከወቅቱ ፖለቲካዊ አውድ ጋር ሊያያይዙት ይሞክራሉ። እስቲ የአንቺን አስተያየት ንገሪኝ። በዘፈኑ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ምንድን ነው? “ባለጊዜስ” ማነው?
ቅድም የገፉት ፍቅር ላይ ፀፀትን የሚገልፀው “አስከትዬ የተሰኘውን ዘፈን ስናይ፣ ሰው በትዝታ ወደ ኋላ ይሄዳል። በህይወትሽ ውስጥ የምታደርጊያቸው እውነታዎች ይኖራሉ። እናም ተከትለውሽ ይመጣሉ። ከህሊና መሸሽ አይቻልምና እስከ ህይወትሽ መጨረሻ የሚከተልሽ ነው። ነገር ግን ያንን ጉዳይ ከላይ ከላይ ትክጅዋለሽ። አጥፍተሸ ህሊናሽ እያወቀ እንኳን ስትጠየቂ፤ “ኧረ ይሄ አልሆነም በጭራሽ“ እያልሽ ትከራከሪያለሽ። ጭንቅላታችን ውስጥ ያለው ድብቁ የአዕምሮ ክፍል እየቀሰቀሰ ያስታውስሻል። ያንን ነገር በይቅርታ ማጠብ ተገቢ ነው። እንኳን አጥፍተሸ ክርስቶስ እንኳን ሳያጠፋ ይቅርታን አስተምሮናልና ይቅርታ ማለት ይገባል። ይህንን ዘፈን ወንድወሰን ሲሰጠኝ በጣም ብዙ ጊዜ የተሞከረ ዜማ ነው። በጣም ብዙ ሰዎች ሰርተውታል። እኔ በይቅርታ የማምን ሰው ነኝ። ያጠፋሁትንም አሽሞንሙኜና አለባብሼ የማልፍ አይነት ሰው አይደለሁም። በይቅርታ ስለማምን ዘፍኜዋለሁ እወደዋለሁም። ስለጊዜና ባለጊዜ ያነሳሽው… ላንቺ “ባለጊዜ” ማነው ላልሺኝ ባጭሩ ስመልስልሽ፣ ለእኔ ባለጊዜ ትልቁ ሃያል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ለኔ የሰው ባለጊዜ የለም።
ጊዜ ጊዜማ ጊዜ
ሲሆን የባለ ጊዜ
ወትሮም በዓለም የፀና
የታል ሰው ሆኖ ጀግና!... የሚለው ሃረግ የጊዜ ባለቤትና ጌታ ፈጣሪ መሆኑን ነው የሚያሳየው። ከፖለቲካ አንፃር ያነሳሽው----ባለጊዜ ምናምን ተብለው የሚለጣጠፉ የመንደር ወሬዎች ይኖራሉ፤ እሱ ለእኔ አይገባኝም። ሰው በፈጣሪ በተሰጠውና በተፈቀደለት ጊዜ የሚያደርገውን ነገር፣ የማድረግ ነፃ ፈቃድ ያለው ፍጥረት ነው። ጊዜንም የሚገድበው ባለጊዜው እግዚአብሔር ነው። እኔ ከዚህ አንፃር ነው ሙዚቃውን የምረዳው። ሰዎች ግን  እንዳልኩሽ ከፈለጉት አንፃርና ዕይታ ሊተረጉሙት ይችላሉ። ቅድም ሙዚቃን እኔ ባየሁት አይን እዩልኝ አልልም  ብዬሽ የለ… ልክ እንደዛ ማለት ነው።
ለምለም የልጆች እናት ናት። ብዙ የቤተሰብም ሆነ የስራ ሃላፊነት አለባት። በእነዚህ ሃላፊነቶች ውስጥ አልፎ በሥራ ስኬታማ ለመሆን የትዳር አጋር ከጎን መቆም አለበት።  የለምለም የትዳር አጋር ደጋፊና አጋዥ ነው ወይስ …?
እውነት ለመናገር በዚህ ዙሪያ ብዙ መናገር አልፈልግም። በእርግጥ በድጋፍ ደረጃ ቤተሰቦቼ በእጅጉ ይደግፉኛል። ከዚያ ደግሞ የልጆቼ አባት ቤተሰቦች በጣም አጋዥና ደጋፊዎቼ ናቸው። ስራዬን ይወዳሉ፣ ልጆቼንም በጣም ነው የሚወዷቸው። እግዚአብሔር ይመስገን የድጋፍ ችግር የለብኝም። ከጓደኛም ከቤተሰብም ከሁሉም በኩል ጥሩ ድጋፍ የሚደረግልኝ ዕድለኛ ሰው ነኝ። በዚህ ስራ ውስጥ አላገዘኝም የምለው አካል የለም። ልጆቼ እንኳን ስራ ስወጣ የት እንደምሄድ ያውቃሉ። በዚህች ትንሽ እድሜያቸው “ማሚ ዛሬ ይሄኛውን ጫማ አድርገሽ ሂጂ” ብለው ይበልጥ እንዲያምርብኝ የሚጥሩ ናቸው። ይሄ መቼም መታደል ነው። አስቢው…አና ስድስት፣ ማያዬ ሦስት ዓመታቸው ነው። በአጠቃላይ የድጋፍ ችግር የለብኝም። አንድ ስራ በሰራሁ ቁጥር የሀገሬ ልጆች ደውለው፣ በርቺ ቆንጆ ነው እያሉ ያበረታቱኛል፤ የድጋፍ ሀብታም ነኝ። ከትዳርሽ ከባልሽ ወይም ከልጆችሽ አባት የምትፈልጊው ድጋፍ ብዬ የማስበው ሥነ ልቦናዊ (ኢሞሽናል) ድጋፍ ነው። ለአንድ አርቲስት ሊሰጠው የሚገባ ድጋፍ አለ ብዬ አምናለሁ። ያ ድጋፍ ኢሞሽናል ድጋፍ ነው። ይህን ደግሞ ብዙ ጊዜ ላታገኚው ትችያለሽ። በብዙ ምክንያቶች። እኔ ከ”የኛ” ያገኘሁት ትልቁ ነገር ደግሞ ለምለም ያለድጋፍ እንዴት መቆም ትችላለች የሚለውን ነው። ለምለም ድጋፍ ኖራት አልኖራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፋ እንዴት መቆም ትችላለች የሚለውን በራስ መተማመን በ”የኛ” ውስጥ ሳለሁ በበቂ ስልጠና ገንብቼአለሁ፡፡ ያም ሆኖ ሰው ነኝ፤ ሰው ደግሞ ደካማ ጎኖችም አሉት። እኔም ችግር ሲያጋጥመኝ መፍትሄ ፍለጋ ወደ ሰው እሄዳለሁ። በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ ሆኜ አሻግሬ የምመለከተው እግዚአብሔርን ነው። እግዚአብሔርን ተመልክተሽ ደግሞ የምታጭው ነገር የለም።
አንድ ሰው የህዝብ ሲሆን፣ ታዋቂ ዝነኛ ሲሆን ብዙ ነገሩ ምስጢር አይደለም። አለባበሱ፣ አመጋገቡ፣ ውሎው፣ የፍቅር ህይወቱ ሁሉ አደባባይ ይወጣል። ከዚህ አንፃር ዝናን የምታማርሪበት የግል ነጻነትን - ፕራይቬሲን የምትናፍቂበት ጊዜ አለ?
እኔ እስካሁን የግል ነፃነቴን (ፕራይቬሲዬን) ለማንም አሳልፌ አልሰጠሁም። የምኖረው የራሴን ሕይወት ነው። ሰፈር ብትመጪ ሁሉም ሰው የሚውለውን አዋዋል ነው የምውለው። ቤቴ ውስጥም የትም ቢሆን ለምለም ታዋቂ ስለሆነች ተብሎ የሚደረግ የተለየ ሸብረብ የለም። በተቻለኝ መጠን መጥፎና ክፉ ቦታ ላለመዋል ጥረት አደርጋለሁ፡፡ በማህረሰቡ ይሄ ክፉ ነው ተብሎ የሚነገር፣ እኔም ክፉ ነው ብዬ የማምንበት ቦታ ላይ አልገኝም። ከዚህ በተረፈ ሰፈር ብትመጪ ባለሱቁ መሃመድም ሌሎቹም ፊት ለፊት ያሉትን ብትጠይቂያቸው ያውቁኛል።
ዝነኛም ሆነሽ እንደኛ ነው የምትኖሪው ማለት ነው…?
ምን ልልሽ ፈልጌ ነው መሰለሽ… ሱቅም ሄጄ የምገበየው እራሴ ነኝ። ወፍጮ ቤት ሄጄም እህል የማስፈጨው እኔው ነኝ። በርበሬና ሽሮ ቤት ውስጥ ነው የማዘጋጀው። የምሬን ነው የምልሽ። እንጀራ ጋግሬ መብላት የጀመርኩት ገና አዲስ አበባ እንደመጣሁ በኪራይ ቤት ትንሿን ምጣድ ገዝቼ ነው፡፡ ለራሴ መጋገር እየቻልኩ ለምንድነው ገዝቼ የምበላው?...አንዳንዴ ታዋቂነት ይጫንሽና ኑሮሽን በአግባቡና በነፃነት እንዳትኖሪ ትደረጊያለሽ። ለመሆኑ ገና እኔ ምን ሰርቼ ነው ፌመስ የምትይው? ሰው እኮ መጀመሪያ  በኢኮኖሚ ራሱን መቻል አለበት፡፡ በሁለት እግሩ ተደላድሎ መቆም ይኖርበታል፡፡ እኔ ገና በኢኮኖሚ ራሴን ሳልችልና ሳልደላደል፣ ፌመስ የሚል ታፔላ እላዬ ላይ እንደመረብ ተጥሎ፣ እየተንደፋደፍኩ አላስመስልም።  እኔ አስመስዬ የምኖረው ኑሮ የለም። እናት ስሆን በትክክል እናት ነው የሆንኩት። የቤት እመቤት ስሆን በቃ በትክክል የቤት እመቤት ነኝ። ቤቴ ብትመጪ ፌሙ ይህን ይፈልጋል ብዬ የምኖረው ህይወት የለም። እኛ አገር ፌመስነት የሚተረጎምበት መንገድ ራሱ ትክክል አይደለም። በውጪው አለም በጣም ትልልቅ የምትያቸው አክትረሶች ለልጆቻቸው ምግብ ያበስላሉ።
እኔ ገና ጀማሪ ሙዚቀኛ ነኝ። ሙዚቃዬ መሸጥ እንኳን የጀመረው ገና አሁን ነው’ኮ። ዘጠኝ አመት ለፍተሽ የሚከፈልሽ ገንዘብ’ኮ ከወጪ ቀሪ የአንድ አመት የቤት ኪራይ እንኳን አይሸፍንም። ታዲያ የትኛው ዝና ነው የሚያመጻድቀኝ። እርግጥ የቤት ሰራተኛ አለኝ፤ ግን እራሴም በደንብ ነው የምሰራው፤ እና ፕራይቬሲን የሚያስናፍቅ፣ የሚያስጨንቅ ዝና የለም። አለቀ።
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪን የሰራሽበት የቴአትር ሙያ ላይ ምን እያሰብሽ ነው? ወደ ትወናው የመምጣት እቅድ የለሽም?
እኔ ቴአትር መስራት በጣም ነው የምገፈልገው። ስለምወደው ነው የተማርኩትም። ”የኛ“ ፕሮጀክት ያን ጊዜ ያዝ ስላደረገን፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ ለመስራት አንችልም ነበር። እስካሁን “ትመጣለህ ብዬ” እና “አንድ ጀግና” የተሰኙ ፊልሞች ፕሮዱዩስ አድርጌያለሁ፤ ከጓደኛዬ ከመሳይ ተፈራ ጋር፡፡ ከቅድመ-ፕሮዳክሽን ጀምሮ ስክሪፕት ላይ ሁሉ ተሳትፌ በደንብ ሰርቻለሁ፡፡ በመተወን ደረጃ ትልቁ ሰራሁት የምለው “ሀገር ማለት” ቴአትርን ነው። ከዚህ በኋላ ግን ልጆችም እያደጉ ሲሄዱ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ራሴ ቴአትር ፅፌ ለመተወን ሀሳብ አለኝ።
እንጠብቃለን! እኔ በግሌ እጠብቅሻለሁ--
አልቀርም፤ ጠብቂኝ።
አልበምሽ ተወዳጅ ይሆን ዘንድ  ጥረት እንዳደረግሽ ይገባኛል። አሁን ላይ እንደማንኛውም አድማጭ ቁጭ ብለሽ ስታዳምጪው ይሄ ቢስተካከል፣ ይሄ ቢሆን ያስባለሽ እንከን አግኝተሻል?
ይሄ ቢሆን ቢስተካከል ያልኩት ነገር በደንብ አለ። እንዳልሽው አልበሙን እንደማንኛውም አድማጭ በትልቅ ስፒከር አስከፍቼ ቁጭ ብዬ ሳዳምጠው፣ የተወሰኑ እንከኖችን አይቻለሁ፤ ግን አሁን ይሄ ነው  ይህ ነው ብዬ  መግለጽ አልፈልግም። አልበሙ በጣም  ቆንጆ የሆነበትንም ክፍል ይበልጥ እንድረዳ አድርጎኛል ማዳመጤ።
ከሴት ድምፃዊያን ማንን ታደንቂያለሽ?
በጣም ብዙ ሰው ነው የማደንቀው።
አንድ ጥሪ ብትባይስ?
አንድ ጥሪ ብለሽ ካስገደድሽኝ ልጥራ። አስቴር አወቀን በጣም ነው የምወዳት፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የእሷ አልበሞች ስብስብ በካሴት እቤት አለ። አስቴርን ሳዳምጥ ነው ያደኩት። ሙዚቀኛ ከታች ተነስቶ አድጎ አድጎ ብቁ ሲሆን ማን ይመስላል ብባል? አስቴር አወቀን ነው የምለው። የመጀመሪያ ካሴቷንና የመጨረሻ አልበሟን ስትከፍቺ፣ ያልኩሽን ሂደት ትመለከቻለሽ። እኔ በጉሮሮ የመተወን ብቃት የማደንቃት ግሩም  ድምፃዊት አስቴር አወቀ ናት።
“ጣይቱ” የተሰኘው ዘፈናችሁ ላይ አስቴር አለችበት፡፡ አብረሻት ስትዘፍኚ አድናቆትሽን አልገለጽሽላትም?
በጣም ነው የገለጽኩላት። አብራን ስትሰራ ደስተኛ ከመሆኔ የተነሳ ምን ላድርግልሽ? ምን ላቀብልሽ? ምን ልሁንልሽ? እያልኩ በቃ “አሽከሯ” ነው መሆን የፈለግኩት። (ሳ….ቅ….) ያኔ ሁሉም ጥግ ጥግ እየሆነ ማልቀስ ብቻ ነበር፡፡ ብቻ እድለኞች ነን። እንዳጋጣሚ እዛ ጣይቱ ዘፈን ላይ የገባችበት እንጉርጉሮ በኔ ድምፅ ነበር የሠራችው እና “እምዬ ምንሊክ እምዬ ምንሊክ የሚለው ማነው”? አለች “እኔ ነኝ” ስላት “ጎበዝ ጎበዝ” ብላኝ ሄደች።
በአልበምሽ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ ታታሪ ሙያተኞችን የምታመሰግኝበት ጊዜ እነሆ…    በጣም አመሰግናለሁ። የአልበሙን ፕሮዲዩሰር ወንደወሰን ይሁብን ፣ አንጋፋዎቹ አበጋዝ ክብረወርቅን፣ ኤልያስ መልካን (ነፍስ ሄር) ሰለሞን ሃይለማርም፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሀብታሙ ቦጋለ፣ አንተነህ ወራሽ፣ አህመድ ተሾመ (ዲንቢ)፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ ብስራት ሱራፌል፣ ጥላሁን ሰማው፣ እሱባለው ይታየው፣ ዘርአብሩክ ስማው፣ ታምሩ አማረ፣ አዲስ ፍቀዱ፣ ብሩክ ተቀባ---እነዚህ ሁሉ አልበሙ አልበም ሆኖ እንዲወጣ ትልቅ አበርክቶት ያላቸው ናቸውና አመሰግናለሁ። ለነበረን መልካም የሥራ ቆይታ በእጅጉ አመሰግናለሁ።
ቤተሰቦቼን፣ ወላጆቼን፣ ዘመዶቼን፣ ጓደኞቼንና አድማጮቼን ሁሉ አመሰግናለሁ። ስማቸውን ዘርዝሬ አልጨርስምና አመሰግናለሁ። የልጆቼ አባት በጣም ጥሩ ሰው ነው። ልጆቼ ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ እድል ስለሰጣቸው በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ። አንቺም ከፈረንሳይ ሀያት ድረስ ተጉዘሽ መጥተሽ ይህን የመሰለ ቆይታ እንድናደርግ ስለፈቀድሽ በእውነት አመሰግናለሁ። ለከያንያን ማደግና መታወቅ ለሩብ ክፍለዘመን በትጋት አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው አንጋፋው አዲስ አድማስ ጋዜጣንና የዝግጅት ክፍሉን ባልደረቦች አመሰግናለሁ። ይህን ሁሉ ያደረገው አምላክ ነው፤ በለምለም አቅም የሆነ አንድም ነገር የለም፤ የተደገፍኩት እግዚአብሔር ዙሪያዬን በበረከቱና ጥበቃው እዚህ አድርሶኛልና ክብር ምስጋና ይግባው እላለሁ። አመሰግናለሁ።


 ምሁራን በ”ብሄርተኝነት” መፅሀፍ ላይ የፓናል ውይይት አካሄዱ



          በዶ/ር በብርሃኑ ሌንጂሶ የተደረሰው “ብሔር-ተኝነት” የተሰኘው መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በዓድዋድልመታሰቢያ፣ ፓን አፍሪካ አዳራሽ የተመረቀ ሲሆን። በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ታድመዋል።
በምረቃቱ ሥነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ጽሑፍ ያቀረቡት ደራሲ፣ መምሕርና የሚዲያ ባለሙያ አቶ ታጠቅ ከበደ ከደራሲው ጋርስለነበራቸው የልጅነት ትውስታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል።
 መጽሐፉ በኢትዮጵያ ስለሚስተዋሉ የብሔረተኝነት ዓይነቶች የሚቃኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታጠቅ፣ ከመጽሐፉ የተወሰኑ ጥቅሶችን በንባብ አቅርበዋል።
በመጨረሻም “ብሔር-ተኝነት” መጽሐፍ በአሁኑ ወቅት የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር እያካሄደ ለሚገኘው ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በግብዓትነት የሚያገለግሉ ምክረ ሃሳቦችን ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡
ደራሲው ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ የብሔረተኝነት ብየና አወዛጋቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ የብየናውን ሁለት ተቃራኒ ጎኖች በስፋት አብራርተዋል። “የብሔርተኝነትን ጥሩ ጎን ካጎለበትነው፣ ጥቅም አለው” ያሉት ደራሲው፣ መጽሐፉ ብሔረተኝነትን ከስሜት አላቅቆ በሚዛኑ ለማየት እንዲያግዝ በማሰብ  እንዳዘጋጁት ተናግረዋል።
ብርሃኑ (ዶ/ር) ስለ ብሔርተኝነት ምሳሌ ሲያቀርቡ፣ “በተለምዶ ‘የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ’ የምንለው የነገስታት ታሪክ ውስጥም የብሔረተኝነት ቀለም ይስተዋላል” ብለዋል።
“መጽሐፉን ለማዘጋጀት ወደ አምስት ዓመት ገደማ ፈጅቷል” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት  ደራሲው፤ “በምረቃው ዕለት በሁለት ነገሮች ደስተኛ ሆኛለሁ። አንደኛ አድዋ መታሰቢያ መመረቁ ነው። ምክንያቱም በዓለም ላይ የዕውነተኛ አገራዊ ብሔረተኝነት ቢፈለግ፣ ከዓድዋ ውጭ የለም። ሁለተኛው ደግሞ፣ በመጽሐፉ የመጨረሻ ምዕራፍ የተገለጸው ሃሳብ ከአገራዊ ምክክሩ ጋር ተገናኝቷል።” በማለት አስረድተዋል።
በመጨረሻም፣ የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢ “በወጣቶች ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ” ላሏቸው፣ በሁሉም ክልሎች ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች እንደሚውል በማስታወቅ ደራሲው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአትሌት ደራርቱ ቱሉና ከሌሎች የክብር እንግዶች ጋር በመሆኑ መጽሐፉን መርቀዋል። አቶ አገኘሁ ከምረቃው አስከትለው ባደረጉት ንግግርም፣ “ጎንደርን የሚያውቅ...ፎገራን የሚያውቅ ነው” በማለት ደራሲውን ሲያሞካሹ፤ “ከእኔ በላይ ጎንደርን ያውቀዋል. . .የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ የተሳሰርን ነን” ብለዋል።
ለደራሲውና ቤተሰባቸው መልካም ምኞታቸውን የገለጹት አቶ አገኘሁ፣ መጽሐፉ ከሶስዮሎጂ ባሻገር፣ የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎችን እንደሚነካ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የመጽሐፉን ይዘትና የኢትዮጵያን አገራዊ ገጽታም በንግግራቸው ዳስሰዋል።
“እኛ ያለነው እንደ እኛ ክፋት ሳይሆን እንደ ሕዝቡ ቸርነት ነው” ሲሉ ንግግራቸውን የቀጠሉት አቶ አገኘሁ፣ “የአሁኖቹ ልሂቃን ወይ በታሪክ ተወቃሽ ወይም ተመስጋኝ እንሆናለን” ሲሉ አመልክተዋል።
አቶ አገኘሁ ስለ አገራዊ ምክክሩ አጠቃላይ ገለጻ ሰጥተው፣ ከመጽሐፉ ጋር ያለውን ግንኙነት በመጥቀስ ንግግራቸውን አሳርገዋል።
በመጽሐፉ  ላይ የፓናል ውይይትም የተካሄደ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የሕግ መምሕሩ ታደሰ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ መንግስቱ አሰፋ (ዶ/ር) እና ዕውነቱ ሃይሉ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ።
“ብሔር-ተኝነት” መጽሐፍ በአማርኛና ኦሮሚኛ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የአማርኛው መጽሐፍ በ5 ክፍሎችና በ15 ምዕራፎች የተዋቀረ ነው። የኦሮሚኛው መጽሐፍ ደግሞ፣ በ16 ምዕራፎች የተቀነበበ ነው።
ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጄሶ  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ናቸው።   

Page 13 of 721