Administrator

Administrator

 ዮናስ ታረቀኝ ይባላል፡፡ በጀርመን ባህል ማዕከል የቤተ መፃህፍትና የመረጃ ሃላፊ ነው፡፡ ከአስር በላይ የተለያዩ መጻሕፍትን ከጀርመንኛና ከእንግሊዝኛ በመተርጎም ለአንባቢ ማድረሱን ይናገራል፡፡ በቅርቡ ለንባብ በበቃውና በጀርመን ባህል ተቋም ሙሉ ድጋፍ በታተመው “ሠላሳዎቹ” የተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች መድበል ላይ ከሃሳብ ማመንጨት እስከ ማስተባበር ድረስ ተሳትፏል፡፡ በአጭሩ የፕሮጀክቱ መሪ ነበር፡፡ ለዮናስ ታረቀኝ “ሠላሳዎቹ” በተሰኘው የአጫጭር ልብወለዶች መድበልዙሪያ አንዳንድ ጥያቄዎችን ላቀርብለት እንደምፈልግ ስነግረው ምንም ሳያቅማማና ለደቂቃ ማሰብ ሳያስፈልገው ፈጣን ምላሹንበመስጠቱ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ከዚያም በላይ ግን ሥራዎቻቸው በመፅሐፉ የተካተተላቸው ደራስያንም የመጠየቅና ሃሳባቸውንየመግለጽ እድል ያገኙ ዘንድ ያቀረበልኝ ሃሳብ አስደምሞኛል፡፡ እውነቱንም ነው፡፡ በዚህ መሰረት በቀጣይ ሳምንታት ከጥቂቶቹጋር ቆይታ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ለዛሬ ግን ከደራሲና ተርጓሚ ዮናስ ታረቀኝ ጋር በ“ሰላሳዎች” መድበል ዙሪያ ያደረግነውን አጭር ቃለ ምልልስ እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡



           “ሠላሳዎቹ” የተሰኘውን የአጫጭር ልብወለዶች መድበል የማሳተም ሃሳቡ እንዴት ተጠነሰሰ? መቼና በማን ?
የጀርመን ባህል ማዕከል ባለፉት  አስርት ዓመታት በሀገራችን ውስጥ የንባብ ባህል እንዲዳብር የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፡- ወርሃዊ የመጽሐፍ ውይይቶች (በአካልም በኦንላይንም)፣ ሀገር አቀፍ የንባብ ፌስቲቫሎች (አዲስ አበባ ታንብብ፣ ኢትዮጵያ ታንብብ)፣ የተረት ሳምንት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ በየቤተ መጻሕፍቱ ከደራሲያን ጋር  የሚደረግ የንባብና የልምድ ማካፈል (ንባብን ባህላችን እናድርግ በሚል መርህ ስር)፣ በንባብ ለህይወት የመጽሐፍ አውደ ርዕይ ላይ በመሳተፍ ደራሲያንን ከታዳሚያን ጋር የማገናኘትና የማስፈረም እንዲሁም በተለያዩ ስነ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት የማካሄድ መርሃ ግብሮችን ማከናወን፣ የጀርመን ደራሲያንን ስራ በንባብ፣ በውይይት እንዲሁም ስራዎቹ እንዲታተሙ በማድረግ ማስተዋወቅ የመሳሰሉት ይገኛሉ። “ሠላሳዎቹ” የእነዚህ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውጤት ነው።  ገፊ ምክንያቶቹ፣ አሁን ሀገራችን ውስጥ ባለው ሁኔታ መጽሐፍ ማሳተም እጅግ ፈታኝ መሆኑ፤ የሀገራችን ወጣት ጸሐፍት የህትመት ብርሃን እንዲያገኙላቸው የሚፈልጓቸው ርዕሰ ጉዳዮች ምንድናቸው? ምን ያሳስባቸዋል? ስለምን መጻፍ ይፈልጋሉ? ይህንንስ እንዴት ባለ ስነ ጽሑፋዊ ለዛ ያቀርቡታል? የሚሉ ጥያቄዎች፤ እንዲሁም እጅግ በጣም በጥቂቱ ቢሆንም የኢትዮጵያዊ ወጣት ስራዎችን ቢያንስ ወደ ጀርመንኛ አፍ መልሶ ለጀርመን ማህበረሰብ የማቅረብ ፍላጎቶች ናቸው። መነሻ ሃሳቡን እኔ ያነሳሁት ቢሆንም እንዲዳብር በማድረግ የተሳተፉ ወዳጆቼ ብዙ ናቸው። የጀርመን ባህል ተቋም ደሞ ተቀብሎትና አምኖበት፣ በጀት መድቦ የተካሄደ ነው።    
ጸሃፊዎቹ ካልተሳሳትኩ አዳዲሶች ናቸው--- በአጭር ልብወለድ ሥራዎቻቸው  የምናውቃቸው ጸሃፍት አልተሳተፉም ብዬ ነው? ሆን ብላችሁነ ነው?
ጽሑፎቹን ለመሰብሰብ የታሰበው በውድድር መልክ ስለነበር፣ መስፈርቶች መውጣት ነበረባቸው። ስለዚህ አንዱ ያደረግነው የዕድሜ ገደብ ማስቀመጥ ነው። ይኸውም ከ18 እስከ 35 ዓመት የሚል ነበር፤ ከ-እሰከው ትንሽ ሰፋ ያለ ቢሆንም፡፡ ስለዚህ ምንም አንኳን ጥቂት ከዚህ በፊት የታተሙ ስራዎች የነበሯቸው ጸሐፍት ቢኖሩም፣ አብዛኛዎቹ አዳዲሶች ናቸው። እድሉን መስጠት የፈለግነውም በተቻለ መጠን ለጀማሪና አዳዲስ ጸሐፍት ነበር። ዋናው ትኩረታችን የነበረው ግን ያቀረቡት ስራ አዲስነት ላይ ነበር።   
ልምድ ከሌላቸውና ከጀማሪ  አዳዲስ ጸሐፍት ለህትመት ብቁ የሆኑ  ታሪኮችን  በቀላሉ ማግኘት አያስቸግርም ?  አድካሚስ አይሆንም ?
የማይታወቅና ልምድ የሌለው ጸሐፊ ለህትመት የሚበቃ ምርጥ ስራ ሊያቀርብ አይችልም የሚል እምነት የለኝም። ብዙ “ዋው” ያስባሉን፤ እጃችንን አፋችን ላይ ያስጫኑን፣ ከዚህ በፊት የማናውቃቸው ጸሐፍት ስራዎችን አንብበናል። እነዚህን ስራዎች ያቀረቡልን ግን ሳይደክሙ አልነበረም። ልምድ ደሞ ያለ ድካም አይገኝም። ወደ እኛ ጉዳይ ስመጣም ተመሳሳይ ነው።  መጀመሪያ እድሉን መስጠት ነው የፈለግነው፣ በራሳቸው ተማምነው ስራዎቻቸውን የላኩትን በሙሉ አድንቀን ነው የተቀበልነው። በውድድሩ መስፈርት (ለምሳሌ የተመጠነ የገፅ ብዛት) እና ሌሎችም፣ በዳኞች በተቀመጠ ስነ ጽሑፋዊ መመዘኛ መሰረት ከቀረቡልን 103 አጫጭር ልቦለድ ታሪኮች ውስጥ በዳኞች መካከል ከተካሄደ የከረረ ውይይት በኋላ 30 አጫጭር ልቦለዶችን ብቻ ማውጣት፣ ማድከሙ አይቀሬ ነው። የተመረጡት 30 ስራዎች እንዳሉ አይደለም ለህትመት የበቁት። ለጸሐፍቱ ከስራዎቻቸው በመነሳት ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ጎኖች የተዳሰሱበት፣ መሻሻል የሚኖሩባቸው ነገሮች የተመለከቱበት፣ መሰረታዊ የስነ ጽሑፍ ጉዳዮች የተጠቆሙበትና ልምዶች የተካፈሉበት፣ የሁለት ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል። በመቀጠል ፀሐፍቱ ከተሰጣቸው ስልጠና በመነሳት ጽሑፎቻቸውን መልሰው እንዲያዩ፣ እንዲያሻሸሉ፣ እንዲጨምሩ እንዲቀንሱ ሰፊ እድል እንዲሰጣቸው ተደርጓል። በመጨረሻም ከአርታኢያቸው ጋር በመሆን ለሕትመት ብቁ እስኪሆን ድረስ ተግተዋል። አርታኢውም በጣም ለፍቷል። ጥያቄህ አያደክምም ወይ አልነበር? ቀላል ያደከማል!
ታሪኮቹን ለማሰባሰብ ምን ያህል ጊዜ ፈጀባችሁ? በማሰባሰብ ሂደቱ የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምን ነበሩ?
በትክክል ካስታወስኩ ወደ ሁለት ወር ገደማ የወሰደ ይመስለኛል። የሰበሰብነው በኢሚይል እንዲላክ በማድረግ ስለነበር፣ ብዙ ተግዳሮት አልገጠመንም። አልፎ አልፎ ግን መስፈርቱን የማያሟሉ ጽሑፎችና መስፈሩትን የማያሟሉ ጸሐፍት ያጋጥሙን ነበር።
የተለያዩ ጸሃፍት የፈጠራ ሥራዎች በጋራ መውጣታቸው ፋይዳቸው ምንድን ነው?
አንዱ እንደ ቡፌ የተለያየ ጣዕም መፍጠር መቻላቸው ነው። ብዙም ባይሆን ከአዲስ አበባ ውጪ የሚኖሩ ጸሐፍትም የተካተቱበት ነው። ይህ በራሱ የሚሰጠው ነገር ያለ ይመስለኛል። ቀጥታ ከዚህ ጋር መያያዝ ባይኖርበትም፣ በጸሐፍቱ መካከል መተዋወቅና ግንኙነት መፍጠር መቻሉም መልካም ነው ብዬ አስባለሁ። ምናልባት የ“ሠላሳዎቹ” መድበል የህትመት ዋጋ በጀርመን ባህል ተቋም በመሸፈኑ እንጂ፣ አሁን ባለው የህትመት ዋጋ መናር የተለያዩ ጸሐፍት ዋጋውን እየተጋሩ፣ በጋራ ስራዎቻቸውን ማውጣት ቢችሉ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።  
እስቲ  “በሠላሳዎቹ” የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ውስጥ የተካተቱት ታሪኮች ምን እንደሚመስሉ በአጭሩ ጠቅልለህ ንገረን ?
እዚህ ላይ አርታኢው ቴዎድሮስ አጥላው በመጽሐፉ ላይ በመግቢያነት ካሰፈረው ጽሑፍ በላይ ሊያሳይልኝ የሚችል ስለማይኖር እሱኑ እንዳለ ብጠቅስ  ይሻላል።   
‘’በዚህ ሠላሳዎቹ ባልነው ስብስብ ከተካተቱት ሥራዎች አብዛኞቹ የደራሲዎቹን ወይም ድርሰቶቹ የተጻፉበትን ዘመን መንፈስ የሚወክሉ ናቸው። ደራሲዎቹ በጦርነት፣ በጥላቻ፣ ከሥር በመነቀል፣ በመካካድ፣ በአደጋዎች፣ በጭካኔ ድርጊቶች፣ በምንትነት መቃወስና በመሳሰሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት ከተፈጠረው የወል ድባቴ፣ የወል ትሮማ ያመለጡ አይመስሉም። ፊት ለፊት ባይኾንም በሥራዎቻቸው እነዚህን ለመግለጥ ወይም ለማምለጥ የሞከሩም ይመስላሉ። ለሕትመት በመረጥናቸው ሠላሳዎቹም ኾነ በተቀሩት ታሪኮች ውስጥ ሞት፣ የመኪና አደጋ፣ መካካድ፣ መወስለት፣ ድህነት፣ ኀዘን ጎልተው የሚሰሙ ድምጾች ናቸው። ከሁልዮ ኮርታዛር ዝነኛ አገላለጽ ብንዋስ፤ እነዚህ ሠላሳዎቹ የዚህን ዘመን መንፈስ በየራሳቸው መቃን ቀንብበው ያስቀሩ ሠላሳ “ፎቶግራፎች” ሲኾኑ፣ መድበሉ ደግሞ ጥየቃ ለመጣው አንባቢ እንግዳ የቀረበ አልበም ነው። (እንግዳው ፎቶዎቹ መሐል ራሱን መፈለጉ፣ አንዳንዴም ማግኘቱ አይቀርም።
በስልት ረገድ፣ ከተረኮቹ አንዳንዶቹ ለግል ማስታወሻነት የቀረበ አጻጻፍ አላቸው።የስሜትና የሐሳብ ጥልቀቶቻቸው ከምናብ የተፈጠሩ/የተቀመሩ ሳይኾን በአብዛኛው ከጸሐፊው/ተመክሮ የተቀዱ ያስመስሏቸዋል። ደግሞ አሉላችሁ፡-  በሥነ ልቡና እና በሥነ አእምሯዊ ሰብአዊ ጣጣዎች ላይ የተመሠረቱ፤ስለዚህም በይነዲሲፕሊናዊ ንባብን በተለይም ሳይኮአናሊሲስን የሚጋብዙ። ከጽንሰ ሐሳብ ለመዛመድ እንኳን ባይጻፉ፤ ግጭቶቻቸው፣ ጭብጦቻቸው፣የገጸባሕርያታቸው ጠባያትና ድርጊያዎቻቸው የሥነጽሑፍንና የሌሎች ሙያዎችን ጽንሰ ሐሳቦች በመፈከሪያነት የሚጣሩም አሉባቸው። ኢምክኑያዊ ፍርሓት፣ የአእምሮ ጤና እክል፣ ድባቴ፣ መርሳትና መዘንጋት፣ በራስ እጅ የማለፍ ግፊት፣ ኤዲፐሳዊ ምስቅልቅል፣… በአርእስተ ጉዳይነት ገንነውባቸው የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ሙያዎችን በማናበቢያነት ይጋብዛሉ። ‘’
እስቲ ታሪኮቹን ስታሰባስቡ ከጠየቃችኋቸው መስፈርቶች ሦስቱን ብቻ ጥቀስልኝ.....?
አንዱ እድሜ ነው፤ ቀደም ብዬ ጠቅሼዋለሁ። ሌላው የገፅ መጠኑ ከአምስት ያላነሰ፣ ከአስር ያልበለጠ የሚለው ነው። አንድ ሰው ለውድድር ማቅረብ የሚችለው አንድ ስራ ብቻ ነው የሚልም ነበረበት።
በመድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ታሪኮች ውስጥ አንተ በግልህ የወደድከውና በቀዳሚነት የምታስቀምጠው የትኛውን  ነው?  ደራሲውን ሳትጠቅስ ርዕሱን ብቻ ልትነግረኝ ትችላለህ----?
በዳኝነቱ ውስጥ ባልሳተፍም እኔም ስራዎቹን የማንበብ እድሉ ነበረኝ። አጋጣሚ ሆኖ ወደ ጀርመንኛ እንዲተረጎሙ በዳኞች የተመረጡት ሦስት ስራዎች እኔም ይበልጥ የወደድኳቸው ናቸው። “የክራሩ ክር”፣ “ኩኩ ሉሉ” እና “የማልረሳው መረሳት”።  
ከዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አጭር ልብወለድን ጨምሮ ጠብሰቅ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ተዳክመዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ በዚህ ሃሳብ ትስማማለህ?
ሁልጊዜም ዘመን የራሱ መልክ አለው። የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት ከኛ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተጽዕኖው ሁለንተናዊ መሆኑን ልንክደው አይቻለንም። ስለዚህ መፍትሄ የሚሆነው መገዳደር ሳይሆን፣  ይህንን ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ እንዴት አድርጌ ነው እኔ ለምሰራው ጉዳይ የምጠቀምበት፣ ምን አይነት ኦዲየንስ ነው ያለው፣ ወዘተ የሚለው ነው መታሰብ የሚኖርበት። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚወጡ የስነ ጽሑፍ ስራዎች በህትመትም በዲጅታልም እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ሰራዎቻቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያወጡ ቆይተው፣ ምርጥ ምርጥ ስራዎችን ወደ ህትመቱ ገበያ ያመጡ ብዙ ጸሐፍት አሉ።  ስለዚህ በእኔ በኩል መዳከም ሳይሆን ዲጂታል ሚዲያው በሚፈልገው መልኩ የስነ ጽሑፍ ስራ ቅርፁንም ሆነ አቀራረቡን እየቀየረ ነው በሚል መውሰድ ይሻላል ባይ ነኝ።     
በዚህ መድበል ዝግጅት ውስጥ የጀርመን ባህል ተቋም ሚና ምንድን ነው?
ከጽንሰቱ ጀምሮ እስከ ውልደቱ የባህል ተቋሙ ኃላፊነት ነበር። በሃሳብም ሆነ በገንዘብ።


ሮክስቶን በ1ቢ.ብር የመኖርያ አፓርትመንቶች እየገነባ ነው


         የጀርመኑ ሪልእስቴት ሮክስቶን ኢትዮጵያ፤ ታዋቂዋን ተዋናይት፣ የሚዲያ ባለሞያና ግንባር ቀደም የአረንጓዴ ልማት ተሟጋች አርቲስት አምለሰት ሙጬን፣ የከፍታ አፓርትመንቶች ብራንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን ሰሞኑን  አስታውቋል፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሪልእስቴት ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው ሮክስቶን ኢትዮጵያ፤ በመዲናዋ  ሲግናል አካባቢ በ1 ቢሊዮን ብር  በጀት ከፍታ በአዲስ አበባ የተሰኘ የመኖሪያ አፓርትመንቶች እያስገነባ ሲሆን አፓርትመንቶቹ ከ30 ሚሊዮን ብር እስከ 150 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ  ተብሏል፡፡
አርቲስት አምለሰት ሙጬ የከፍታ አፓርትመንቶች አምባሳደር ሆና መመረጧን አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የሮክስቶን ኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮችና አርቲስቷ በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የስምምነት ፊርማም ተፈራርመዋል፡፡  
 አርቲስት አምለሰት ሙጬ በብራንድ አምባሳደርነት የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያት አረንጓዴ ዓለምን ለመፍጠር በሚደረጉ ሁለንተናዊ ተሳትፎዎች ላይ እውቅናዋን ተጠቅማ የተለያዩ ንቅናቄዎችን ማሳካት በመቻሏ ነው ያለው ሮክስቶን ሪልእስቴት፤ ከዚህ በተጨማሪም አርቲስቷ ያላት ሰብዕና፣ ቁርጠኝነትና ትልልቅ ራዕዮቿ በሙሉ ድምፅ እንድትመረጥ አድርገዋታል ብሏል።
 አርቲስት አምለሰት አምባሳደርነቷን አስመልክቶ በሰጠችው ማብራሪያ፤ “ዘላቂነት ካለው የሪልእስቴት ልማት ኩባንያ ጋር አብሬ በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከፍታ፤ አዲስ አበባን የሚያምር ገፅታ በማላበስ፣ አረንጓዴነቷን በማስቀጠል የተፈጥሮ ሀብትን ለትውልድ እያስቀጠለ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው። በተጨማሪም እኔ እራሴ በከፍታ አፓርትመንት የቤት ባለቤት በመሆኔ  ኩራት ይሰማኛል፡፡” ብላለች፡፡
 ለብራንድ አምባሳደርነቷ ምን ያህል እንደተከፈላት ከጋዜጠኞች የተጠየቀችው አምለሰት፣ የክፍያውን መጠን ለመናገር ፈቃደኛ ሳትሆን የቀረች ሲሆን ይልቁንም፤ ”አንድ ቤት የሚሰጡኝ ይመስለኛል፤ፔንትሃውስ ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡” ስትል በቀልድ ተናግራለች፡፡
ከኩባንያው ጋር ለመሥራት የተስማማሁት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑና በህንጻዎቹ ዲዛይን ላይ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ በማንጸባረቁ ነው ብላለች - አርቲስት አምለሰት፡፡
የሮክስቶን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሚስተር ዲትሪክ ኢ. ሮጄ ስለ አምለሰት በብራንድ አምባሳደርነት መመረጥ ሲናገሩ፤ “አርቲስት አምለስት ባላት የግል ማንነት ከፍታ የያዘውን የዘመናዊነትና የአካባቢ ጥበቃ ተነሳሽነት ለብዙ ደንበኞቻችን ለማሳየት ወሳኝና ተመራጭ እንስት ናት። በአስገራሚ ሰብዕናዋና ከማህበረሰቡ ጋር ባላት ጠንካራ ትስስር፣ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ ከፍተኛ ስለሆነ ከፍታ አፓርትመንቶችን በማስተዋወቅ እንዲሁም አዲስ ነገሮችን በጋራ የመፍጠር ራዕያችንን ታሳካለች ብለን እናምናለን፡፡” ብለዋል፡፡
 የሮክስቶን ኢትዮጵያ  ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አድያምሰገድ ኢያሱ በበኩላቸው፤ “አርቲስት አምለሰት ሙጬ ብራንድ አምባሳደራችን በመሆኗ በጣም ደስተኞች ነን። አምለሰት የእኛን የልህቀት፣ የጥራትና የማህበራዊ ሀላፊነት እሴቶች የምትጋራ መልካም ሰብዕና ያላት ድንቅ አርቲስት ናት። ለድርጅታችን ትልቅ ሀብት እንደምትሆንና ወደምንፈልጋቸው ደንበኞቻችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እንድንደርስ ትረዳናለች ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
  ሮክስቶን ሪልእስቴት በጀርመን የተመሰረተ በግንባታው ዘርፍ ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ የሪልእስቴት ገንቢና የኢንቨስትመንት ድርጅት ሲሆን፤ በጀርመን ስፔንና ፖርቹጋል በየተለያዩ ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡   


ESX ወደ ሥራ ለመግባት ተጨማሪ 625 ሚ ብር ያስፈልገዋል
                      

       ዘመን ባንክ 47.5 ሚሊዮን ብር በኢትዮጵያን ሴክዊሪቲ ኤክስቼንጅ ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ሴክዊሪት ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለመግባት 625 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል ተብሏል።
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በዘመን ባንክ ዋና መሥርያ ቤት  በተፈረመው የኢንቨስትመንት ውል  መሰረት ዘመን ባንክ በኢትዮጵያን ሴክዊሪቲ ኤክስቼንጅ 5% ድርሻ መያዙ ተረጋግጧል። የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ዘበነ እንደተናገሩት፤ ኢኤስኤክስ ገዢና ሻጭን፤ ፈላጊና ተፈላጊን የማገናኘት ሥራ የሚያከናውን ሲሆን፤ የካፒታል ገበያው እንዲያድግና የአገር ኢኮኖሚ እንዲቀየር በማገዝ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተነግሯል፡፡ የዘመን ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ በኢኤስኤክስ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ሲወስን የባንኮችን የኢንቨስትመንት ገደብ ባማከለ መንገድ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘበነ፤ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያለውን የገበያ ስርዓት በኢትዮጵያ እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት በአርአያነት እንደሚከተሉን አምናለሁ ያሉት የባንኩ ሥራ አስፈፃሚ፤ የሴክዊሪቲ  ኤክስቼንጅስ መዋቅር መዘርጋቱ ተቋማት ወደ ገበያ እንዲወጡና ሃብት መፍጠር እንዲችሉ መንገድ  እንደሚያመለክታቸው ተናግረዋል፡፡
”ዘመን ባንክ ከESX ጋር ተባብሮ ለመሥራት ኢንቨስት በማድረግ ከመጀመሪያዎቹ  አንዱ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን፤ የካፒታል ገበያ መስፋፋት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፎች ላይ ለውጥ ያመጣል፣ ስለዚህም በዚህ አስደሳች ጉዞ ውስጥ በመቀላቀላችን ተደስተናል።” ብለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ኩባንያዎች፤ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙም ሆነ ሲስፋፉ አክሲዮኖቻቸውን ይሸጥላቸዋል። ዋናው አገልግሎቱም አዲስ ለሚመሠረቱም ሆነ ለነባር ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን መፍጠር ነው ተብሏል፡፡
የESX ዋና ሥራ  አስፈፃሚ ዶክተር ጥላሁን እሸቱ ካሳሁን በበኩላቸው፤ መ/ቤታቸው የካፒታል ገበያን ለማስተዋወቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ይገልፃሉ። ፈጣን የንግድ መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ፣ አዳዲስ ሠራተኞችን በመቅጠርና የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት  የዘመን ባንክ ኢንቨስትመንት መምጣቱን አመሥግነዋል። የኢትዮጵያን ሴኪዮሪትስ ኤክስቼንጅ በ900 ሚሊየን ብር ካፒታል ለመገንባት መታቀዱን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ዶክተር ጥላሁን እሸቱ፤ ባለፈው ሁለት ዓመት ውስጥ ሃምሣ በመቶ ጊዚያቸውን የወሰደው ስለ ካፒታል ገበያው የማሳመን፤ የማስረዳትና የማስተዋወቅ ስራ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
መንግስትና ሌሎች አጋር ተቋማት እስከ  25 % ድርሻን በመግዛታቸው 225 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የገለፁት ስራ አስፈፃሚው፤ የተቀረውን 625 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመሙላት ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትና ኩባንያዎች እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ከባህርማዶ የፋይናንስ ተቋማት ለመሰ ብሰብ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ብለዋል። አጠቃላይ ሂደቱም መንግስትና የግሉ ዘርፍ አንድ ላይ መሥራት እንደሚችሉ ማሣያ እንደሚሆንም ዶ/ር ጥላሁን ጠቁመዋል፡፡”ከ10 ሚሊየን እስከ 150 ሚሊየን ብር ኢንቨስት በማድረግ የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲ ኤክስቼንጅስ ድርሻን መግዛት ይቻላል። በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 30 ባንኮችና 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አብረውን እንዲሰሩ  እንፈልጋለን“ ብለዋል፤የESX ዋና ሥራ  አስፈፃሚው፡፡



  “በጊዜ ግቡ” በሚል መሪ ቃል ዘመናዊ የመኖሪያ አፓርታማዎችን እየገነባ ለቤት ፈላጊዎች የሚያስረክበው ጀምበሮ ሪል እስቴት፤ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ጋር በመተባበር ለዲስፖራ ማህበረሰብ አባላት ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችን በልዩ ቅናሽ ሊሰጥ መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ ከትላንት በስቲያ ጥር 2 በስካይላይት ሆቴል የቤት ሽያጩን አስመልቶ ከኢትጵያ ዲያስፖራ ማህበር ጋር ተፈራርሟል። ጀምቦሮ ሪል እስቴት ቦሌ ቡልቡላ የሚገኙ ግንባታቸው 70 በመቶ የተጠናቀቁ ቤቶችን እንዲሁም  በተለምዶ ሳር ቤት በሚባለው ቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ በቀጣዩቹ 3 ዓመታት ተገንብተው የሚጠናቀቁ ቅንጡ የኪሩ አፓርትመንት 400 ቤቶችን ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በልዩ ቅናሽ ማቅረቡን በፊርማ ሥነ-ስርአቱ ላይ ያስታወቀ ሲሆን የቦሌ ቡልቡላዎቹ 100 ቤቶች በ15 በመቶ የሳር ቤቶቹ 400 ቤቶች ደግሞ በ10 በመቶ ልዩ ቅላሽ ለዲያስፖራ ማህበር አባላት መቅረባቸውን የጀምቦሮ ሪል እስቴት ተወካይ አቶ ዮናስ ውብሸት ተናግረዋል።  
ጀምበሮ ሪል እስቴት ከገነባቸውና እየገነባቸው ካላቸው ስድስት ያህል ፕሮጀክቶች ሶስቱን ማስረከቡን አስታውቆ፣  በቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ የተጀመረውና ግንባታው 20 በመቶ ላይ ደረሰው ኪሩ አፓርትመንት፣ ከ5ሺህ በላይ  በሆነ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ፣ 30 ወለሎች ያሉትና ሰባ ወለል ያለው የመኪና ማቆሚያ እንዲሁም 5 ወለል ደግሞ ለአለም አቀፍ ብራንድ ሱቆች የተዘጋጀና 1 ሺህ ካሬ ሜትር አረንጓዴ ስፍራ ያለው ቅንጡ አኗኗር ለሚፈልጉ የመጀመሪያ ምርጫ የሚሆን ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር በ2001 ዓ.ም የተቋቋመና በስሩም ከ10 ሺህ በላይ አባላትን ያቀፈ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ማህበሩ ለዲያስፖራው መብትና ጥቅም መከበር ከፍተኛ ስራ እየሰራ ስለመሆኑም በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙትና የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ቅድስት ልዑል ሰገድ ተናግረዋል። የሁለቱም ቅናሾች በኢትዮጵያ ብር  ሲሆን የቡልቡላው ለ3 ወር የሳርቤቱ ለአንድ ወር የሚቆይ ቅናሽ ስለመሆኑም ተብራርቷል።



        አንድ በጣም ጥንቁቅና የንሥር ዐይን አለው የሚባል የጉምሩክ የኬላ ተቆጣጣሪ፣ ኬላ ተሻግሮ የሚመጣ አንድ ከባድ መኪና ያያል፡፡ ሹፌሩን ተጠራጠረው፡፡ ስለዚህ እንዲወርድ ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ ሹፌሩ ወረደ፡፡ ኬላ ተቆጣጣሪው ሹፌሩን ፈተሸ፡፡ ከዚያ መኪናውን መበርበር ጀመረ፡፡
 ወንበሩን አንስቶ ስሩን አየ፡፡ ኪሶቹን ፈተሸ፡፡ የጎማ ማስቀመጫዎችን አገላብጦ አየ፡፡ ምንም የኮንትሮባድ እቃ አላገኘበትም፡፡ ስለዚህ ምንም ጥርጣሬው ባይለቀውም እያመነታ እንዲያልፍ ፈቀደለት፡፡በሚቀጥለው ሳምንት ያው ሹፌር በኬላው በኩል አቋርጦ መጣ፡፡ ያም ተቆጣጣሪ ዛሬስ አያመልጠኝም ብሎ ውስጥ ውጪውን ከፋፍቶ በረበረ፡፡ አንዳችም የኮንትሮባንድ ዕቃ አላገኘበትም፡፡ በዓመት ውስጥ ባሉት ሳምንታት በሙሉ ያ ሹፌር ይመጣል፡፡
 በመጣ ቁጥር ተቆጣጣሪው ሙሉ ፍተሻ ያደርግለታል፡፡ በኤሌክትሮኒክ መፈተሻ ዘዴ - በኤክስሬይ መመልከቻ፣ ውሃ ውስጥ በድምፅ ሞገድ አማካኝነት በሚፈተሽበት በሶላር መሳሪያ ጭምር አጥብቆ ይፈትሸዋል፡፡ ሹፌሩ ግን በየሳምንቱ ማለፉን ቀጥሏል፡፡ ተቆጣጣሪው የበለጠ ይጠረጥራል፡፡ የበለጠ ይፈትሸዋል፡፡ ሆኖም ምንም በሚሥጥር የጫነው ነገር አልተገኘም፡፡ በየጊዜው ያለፍቃዱ የይለፍ ምልክት መስጠት ብቻ ሆነ ምርጫው፡፡ከዓመታት በኋላ ተቆጣጣሪው ጡረታ መውጪያው ጊዜ ደርሰ፡፡ ያ ሹፌር እንደልማዱ ከባድ መኪናውን እያምዘገዘገ መጣ፡፡ተቆጣጣሪው ሹፌሩን እንዲወርድ ጠየቀውና ከመኪናው ራቅ አድርጎ ወሰደው፡፡ ከዚያ “የኮንትሮባንድ እቃ የምታሻግር ሰው መሆንህን በደምብ አውቄያለሁ፡፡ ለመካድ ብለህ አትጨነቅ አደራህን፡፡ በጭራሽ አትሞክረው፡፡ ዋናው ነገር እኔ ይሄን ሁሉ ዓመት ፈትሼ ፈትሼ  ምንም ነገር ሳላገኝብህ መቅረቴ ነው፡፡ አሁን የጡረታ መውጫዬ ሰዓት ደረሰ፡፡ ስለሆነም ይህን ሥራ ለቅቄ መሄዴ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አንተ ምንም ብትሰራ የኔ ማወቅ ከእንግዲህ ፋይዳ የለውም፡፡ ሆኖም በጣም ረቂቅ የፍተሻ ስራ አዋቂ ነው እየተባልኩ ከአንዴም ሁለቴ የምስጉን ሰራተኝነት ሽልማት ያገኘሁ ነኝ፡፡ የሚገርመው ግን የአንተን የኮንትሮባድ ስራ በጭራሽ ልደርስበት አልቻልኩም፡፡ እንደው ለህሊናዬ ብለህ ምን ዕቃ እየጫንክ እንደምታልፍ እባክህ ንገረኝ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ሹፌሩም የሚገርም መልስ ነው የሰጠው፡-
“ከባድ መኪና እያመጣሁ እሸጣለሁ፡፡ አንተ ውስጡን ትፈትሽና ራሱን ከባድ መኪናውን ግን ታሳልፍልኛለህ ጥሩ ፈታሽ ነህ፡፡”
****
የኮንትሮባንድ ዕቃ በመፈለግ ዋናውን ከባድ መኪና ስናሳልፍ ብዙ ዘመን አልፏል፡፡ በሀገራችን ዋናው እያለ ጥቃቅኑን ነገር ካላየን ስንል በርካታ ግዙፍ እንከኖች ያመልጡናል፡፡ ዐይናችን በጥቃቅኖቹ ነገሮች እየታወረ ትልቁን ነገር እንስተዋለን፡፡
በቅርንጫፉ ላይ ስንንጠላጠል ዋናው ግንድ ላይ እንዴት እንውጣ፣ ማ ይውጣ ስንል ጀንበር ትተኛለች፡፡ ዋናው ኩባያ እንዳይጠየቅ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ላይ ማተኮር ውጤት ተኮር አያሰኝም፡፡ ዋና ባለሥልጣን እያለ ተከታዮ ላይ ማነጣጠር ደግ አይደለም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካን ሙሉ ስዕል ሳናይ ኢትዮጵያ ብቻ ነጥለን፣ አሊያም ኤርትራን ብቻ ነጥለን ለመመልከት መጣር አንዳች የተለከፈ ደም በተወሰነ ያካል ክፍል ብቻ ይዘዋወራል ብሎ እንደማሰበ  ይሆናል፡፡ (an infected blood, an infected body እንደተባለው ነው፡፡) መላውን አካል ራቅ ብሎ ማየትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ አንዳንዴ የአገር ጉዳይ እንደውሃ ቅብ ስዕል ራቅ ብለው ካላዩት ፍንትው ብሎ ዐይን አይገባም፡፡ ሆኖም ከሩቅ አስተውለው ሲያበቁ ቀርቦ ለመዳሰስ ካልደፈሩ ደግሞ አጉል ነው፡፡ “የሩቁ የሚሳልበትን  የቅርቡ አርሶ ይበላ” ይሏልና፡፡የአፍሪካ “ኩታ - ገጠም አገሮች ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፆች ናቸው የሚባለውን ያህል፣ የየአገሩ ባለስልጣናትም “አብ ሲነካ ወልድ ይነካ” የሚለውን ዓይነት ናቸው፡፡ ኃያላኑም ቢሆኑ ከትላንት ወዲያ በቀጥታ ቅኝ አገዛዝ፣ ትላንት በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ዛሬ በኢኮኖሚ ትብብር/በግሎባላይዜሽን፣ አሊያም በስፖንሰርነት “እየተንከባከቡ” (globalized babysitting) ግዙፏን አፍሪካ ሸንሽኖ በመልክ በመልክ፣ አለያም በአቀማመጥ አቧድኖ ድህነቷን “ለማስታመም” ሌት ተቀን ይባዝናሉ፡፡ አፍሪካ ግን “ዛር ነው በሽታዋ” እንደተባለው ነች፡፡

ካገሩ ልጆች በቀር የሚያድናት ያለም አይመስል፡፡ የአፍሪካ አገሮች የየግል ኪሳቸውን ሲፈትሹ ዋናውን የኮንትሮባንድ ከባድ መኪና ይዞ የሚገባውን ሰውዬ የአለማየት ዕዳቸውን እንደተሸከሙ ይኖራሉ፡፡ ባለሥልጣናቱ በሙስና ከመበልፀግ የራቀ ርእይ ሳይኖራቸው፣ የዲሞክራሲ፣ የሰላምና የፍትህ መፈክር ይዘው “ረዥም ዘንግ ባይመቱበት ያስፈራሩበት” ማለቱን እንደ ኑሮ ዘዴ ኮርተውበታል፡፡ ሲመች በጅምላ ሳይመች በችርቻሮ መቸብቸብ ነው ነገረ-ሥራቸው ሁሉ፡፡ የአፍሪካ ተጎራባች አገሮች ችግር እንደተስቦ ከአንዱ ወደ አንዱ ተዛማች ነው፡፡ ሆኖም አንዷ የአፍሪካ አገር በጦርነት ስትለበለብ ሌላዋ የአፍሪካ አገር “በርጩማ የምታሰራ እንጨት እሳት ላይ ባለው እንጨት ትስቃለች”  እንደሚባለው ተረት ነው፡፡ የሙስና ሆነ ሌላ ዓይነት የምዝበራ ተግባር ላይ የተሰማ የሚመዘበረው ነገር በጣመው ቁጥር ትኩረቱ የግል  እርካታው ላይ ነውና (ሙስናዊ ውጤት - ተኮርነት እንዲሉ) እታያለሁ፣ ከዛሬ ነገ ይነቃብኛል፣ የሚል ሥጋት አይኖረውም፡፡ ሀገር ቁልቁል ባደገች ቁጥር በገዛ አበሳዋ ተተብትባ ስታቀረቅር እኔን አታየኝም በሚል በኮንትሮባንድ ከባድ-መኪና የሚጓዘው ሹሬር ቁጥር እየበዛ ሲሄድ “ኬላው ተሰበረ!” እያለች ከመዝፈን በስተቀር አስተዋይ ዜጋ ለመፍጠር የምትችል አገር አይኖረንም፡፡ ከቶውኑም ጥቃቅኑን ኪስ እየፈተሸ ሲውል ዋና ኪስ የማያይ ዐይን አገር ያስጠቃል፡፡ በየትናንሾቹ ሙልሙል “ድሎች” (ውጤቶች) ሹሙኝ ሸልሙኝ ሲል ትልቁን የሀገር ዳቦ አሰርቆ ሲያበቃ እንዳማረበት ሰው አደባባይ ወጥቶ ሲቆም ማስቀየሙን የማያስተውል በርካታ ነው፡፡ “አጥንት የሚግጥ፣ መጋጡን እጂ የጥርሱን ማግጠጥ አያይም” የሚባለውም የዚህ ብጤው ነው፡፡

 አንባቢ ርእሱን ሲያነብ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? እንደሚል እርግጠኛ ነኝ። ያለፉትን ስልሳ ስምንት አመታት የመረጥኩት በምን ምክንያት እንደሆነ በአጭሩ በመግለፅ ፅሁፌን እጀምራለሁ።
ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት መስርታ ሀገር ማስተዳደር የጀመረችው ኃይለስላሴ ስልጣን ከያዙበት ከ1923 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ብል ብዙ የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ - ከ1848 እስከ 1983 ዓ.ም.” ብለው በሰየሙት መፅሀፋቸው ውስጥ የኃይለስላሴን ዘመነ መንግስት በሁለት ከፍለው በማብራራት በጣም ጥሩ የሚባል ግንዛቤ እንድናገኝ አድርገውናል። የመጀመሪያው ከ1923 ዓ.ም. እስከ  ከ1948 ዓ.ም. ያሉት 25 አመታት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከ1948 ዓ.ም. እስከ ከ1967 ዓ.ም. ያሉት 19 አመታት ናቸው። እንደ እሳቸው አገላለፅ በመጀመሪያው 25 አመታት ውስጥ ንጉሱ የሀገር ምስረታ(Nation building) ስራ ላይ ተወጥረው ነበር ያሳለፉት። ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት በመፍጠር የሀገር ምስረታ ስራውን በሚገባ ተወጥተውታል የሚል እምነት አለኝ።


 ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1967 ዓ.ም. መባቻ ድረስ ግን በዘመኑ የነበረው የፊውዳል ስርዐት ወቅቱ ግድ የሚሉ መሻሻሎችን (ለምሳሌ የመሬት ስሪት) ተቀብሎ ተገቢ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦችን ማምጣት ስላልቻለ ሀገሪቷን ለእርስ በርስ ሽኩቻና ምስቅልቅል የዳረገ መሆኑን ማስረጃ በተደገፈ መልኩ አብራርተዋል። ከላይ ያቀረብኩትን የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴን ሙያዊ ትንተና መሰረት በማድረግ ነው የመጀመሪያዎቹን 25 አመታት፤ ማለትም  ከ1923 ዓ.ም. እስከ  ከ1948 ዓ.ም. ያሉትን አመታት ትቼ፣ ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2016 ዓ.ም. ድረስ ያሉትን 68 አመታት በወፍ በረር ለመዳሰስ የሞከርኩት።


እኔ የትምህርት መሰረቴ የተፈጥሮ ሳይንስ፤ ቴክኖሎጂና የማህበራዊ ሳይንስ ድብልቅ ቢሆንም (ማስተርሴን MBA ሰርቻለሁ)፤ የስራ ልምዴ ወደ ቴክኖሎጂው የሚያደላ  በመሆኑ ከዚህ በታች ያቀረብኩትን ትንተና ከወፍ በረርነት በጠለቀ መልኩ ማቅረብ ባለመቻሌ አስቀድሜ አንባቢን ይቅርታ እጠይቃለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በታች ባነሳኋቸው የታሪክ አጋጣሚዎች  በመመርኮዝ የተሳሳትንባቸው ናቸው ብዬ በለየኋቸው ጉዳዮች ላይ አተኩሬ ለማብራራት የሞከርኩት የትኛውንም አካል ለመውቀስ ሳይሆን፤ ለወደፊቱ ያለፉ ስህተቶቻችንን በማረም ይህቺን ሰው፤ ትክክለኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስርዓት ማግኘት ባለመቻሏ በድህነት ውስጥ የምትዳክረውን አገራችንን ከድህነት ለማውጣት እንችል ዘንድ በማሰብ ነው።


ከዚህ በታች ያለውን ትንተና ከማቅረቤ በፊት ጉዳዩን ከምን አቅጣጫ አይቼ፤ ወይም ምን ሞዴል ተጠቅሜ እንደሆነ ግልፅ ማድረግ አለብኝ። በዚሁ መሰረት የተጠቀምኩት “ጆን ሮቢንስንና” እና “ዳሮን አኬ ሞግሉ” የተባሉ የመፅሀፍ ደራስያን በጋራ “Why Nations fail” በሚለው መፅሀፋቸው ውስጥ ያነሱትን ፅንሰ-ሀሳብ ነው። ሁለቱ ደራስያን በመፅሀፋቸው ውስጥ እንዳብራሩት፤ የተለያዩ የአለም ሀገራት በታሪክ ሂደት ውስጥ የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች(ፀሀፊዎቹ “Junctions” የሚል ስም የሰጡት) ያጋጥማቸዋል፤ እነኚህ የታሪክ አጋጣሚዎች ሀገራቱ በኢኮኖሚ እንዲያድጉ ወይም እንዳያድጉ ምክንያት ይሆኗቸዋል። በነሱ አባባል “Inclusive Political Institutions” እና  “Inclusive Economic Institutions” እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነው ኢኮኖሚያቸው ያድጋል፤ ወይም “Extractive Political Institutions” እና “Extractive Economic Institutions” እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነው ኢኮኖሚያቸው ባለበት ይረግጣል፤ ወይም አያድግም፤ የሚል ትንተና ሰጥተዋል። እኔ “Inclusive” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል “አካታች” ያልኩት ሲሆን፤ “Extractive” የሚለውን ቃል ደግሞ በቀጥታ “በዝባዥ” በሚለው ቃል ምትክ በኦፐሬሽናል ወይም በተግባራዊ ትርጉሙ “ወገንተኛ” በማለት “Inclusive Political Institution” እና “Inclusive Economic Institution” ያሉትን “አካታች የፖለቲካ ተቋም” እና “አካታች የኢኮኖሚ ተቋም” ያልኳቸው ሲሆን፤ “Extractive Political Institutions” እና “Extractive Economic Institutions” ያሉትን ደግሞ “ወገንተኛ የፖለቲካ ተቋም” እና “ወገንተኛ የኢኮኖሚ ተቋም” ብያቸዋለሁ።


ለዚህ አባባላቸው ማሳያ እንዲሆን ብለው በተለያዩ ሀገራት የተፈጠሩትን የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አንስተው ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው ወይም ውድቀታቸው እንዴት ምክንያት እንደሆኑ አብራርተዋል። ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ሀገራት መሀከል ፈረንሳይና ጃፓን ይገኙበታል። በ1789 ዓ.ም የተካሄደውን የፈረንሳይ አብዮት እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ (Junction) ወስደው ተንትነውታል። በዚህ አብዮት ምክንያት በፈረንሳይ ሀገር የፊውዳል ስርዓት ተገርስሶ የካፒታሊዝም ስርዓት የተጀመረበት ወቅት ሲሆን፤ እንደነጆን ሮቢንሰን አባባል “አካታች የፖለቲካ ተቋማት” እና “አካታች የኢኮኖሚ ተቋማት” እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኖ ሀገሪቱ በሂደት በኢኮኖሚ ልታድግ ቻለች፤ ከራሷም አልፋ ለጎረቤት ሀገራትም ተረፈች ብለዋል። ጃፓን በታሪኳ የሜይጂ ማሻሻያ(Meiji restoration) በመባል የሚታወቀውና በ1868 ዓ.ም የተካሄደውን የታሪክ አጋጣሚ(Junction) አሳልፋለች። ጃፓን ከሜይጂ ማሻሻያ በፊት ለ500 አመታት ሀገሪቱ ለውጪው አለም ሙሉ በሙሉ በሯ ዝግ ነበረ። ከሜይጂ ማሻሻያ በኋላ ግን ሀገሪቱ ለውጪው ዓለም እራሷን ክፍት በማድረጓ ምክንያት ንግድ፤ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተስፋፉ። ይህ የታሪክ አጋጣሚዋም አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኖ በሂደት ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ልታድግ በቃች። በመፅሐፉ ውስጥ የተጠቀሰችው ሌላ ሀገር ኢትዮጵያ ስትሆን፤ የኃይለስላሴና የደርግ መንግስታት አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት መገንባት ስላልቻሉ፣ ሀገሪቱን ከድህነት ማውጣት አለመቻላቸውን አብራርተዋል።

የኢህአዴግን መንግስት በትንታኔያቸው ውስጥ ያላካተቱበት ምክንያት መፅሀፉን ለመፃፍ ቅድመ ዝግጅት የተደረገው በኢህአዴግ የመጀመሪያ አመታት አካባቢ ስለሆነ ነው የሚል የራሴን ግምት ሰጥቻለሁ። ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት ሀገራት በተጨማሪ ከተለያዩ ክፍለ አለማት ለማሳያነት የቀረቡ በርካታ በኢኮኖሚ ያደጉም ሆነ ያላደጉ ሀገሮች ተካተውበታል። ሌላው እነ ጆን ሮቢንሰን ያነሱት ነጥብ ወገንተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት የነገሱበት ሀገር በሚወስዱት የተሳሳተ ርምጃዎች ሀገሪቱ ከአንድ ችግር ወደ ሌላ ችግር ውስጥ እየገባች ከ “Vicious circle” ውስጥ መውጣት እንደሚቸግራት ሲገልፁ፤ አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማቷ ሊገነቡ የቻሉ ሀገራት በበኩላቸው፤ በተለያዩ ወቅቶች የሚወስዱት ተገቢነት ያለው ርምጃ ሀገሪቱን ከዕድገት ወደ ዕድገት እያሸጋገረ እንደሚሄድ አስረድተዋል፤ ይህንንም እውነታ “Virtuous circle” ብለው ሰይመውታል።
እስቲ ደግሞ አሁን ወደሀገራችን ኢትዮጵያ መለስ ብለን የተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችን (Junctions) በመመርመር የተፈጠረውን ሁኔታ ለመቃኘት እንሞክር። ሚዛናዊነቴን ላለማጣት ስል በሀገራችን ያለፉትና አሁን ያሉት መንግስታት፤ ማለትም ከዓፄ ኃይለስላሴ መንግስት እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይ አሕመድ መንግስት ድረስ፤ ሁሉም የራሱ ጠንካራና ደካማ ጎን አለው። ለጠንካራ ጎናቸው ሁሉንም እያመሰገንኩ፤ እኔ የማተኩረው መሻሻል ይኖርባቸዋል ብዬ በለየኋቸው ነጥቦች ላይ ነው። የትኛው መንግስት ከየትኛው በምን ይሻላል የሚለውን ጥያቄ ለታሪክ ባለሙያዎች ትቼ፤ በኔ እምነት ባለፉት 68 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ 6 የታሪክ አጋጣሚዎችን (Junctions) አሳልፋለች የሚል እምነት አለኝ። የታሪክ አጋጣሚዎቹ ምን ፈየዱላት የሚለውን በቅደም ተከተል እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
የጃፓን መልካም ትብብር፡
ጃንሆይ(ኃይለስላሴ) በስልጣን ዘመናቸው ከሚመሰገኑበት ነገር አንዱ በውጪ ግንኙነት ወይም በዲፕሎማሲ አዋቂነታቸው ነው። የዚህ ማሳያ አንዱ ከጃፓን መንግስት ጋር የነበራቸው የቅርብ ግንኙነት ነበር። ለዚህ ርዕሳችን ይጠቅመን ዘንድ በኃይለስላሴ ዘመን የነበረውን የፖለቲካ ሽኩቻ እዚህ ላይ በአጭሩ ላንሳ። “ረዥሙ የኃይለስላሴ የስልጣን ጉዞ” የሚል ርዕስ ባለው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መፅሀፍ ውስጥ በግልፅ እንደተብራራው…፤ በንጉሱ የስልጣን ዘመን ወቅት ሁለት ትላልቅ ተቃራኒ የፖለቲካ አመለካከት የነበራቸው ቡድኖች በስራቸው ነበሩ። የመጀመሪያው የፊውዳል አመለካከት ያላቸው፤ ለውጥ የማይፈልጉ የመሬት ከበርቴ ቡድን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የተማረ፤ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበረውና ለውጥ ፈላጊ ቡድን ነበረ። እንደ አምባሳደር ዘውዴ ረታ አባባል፤ ኃይለስላሴ በግላቸው ወይም በልባቸው የተራማጁን ወይም ለውጥ ፈላጊውን ወገን የሚደግፉ ቢሆንም፤ የመሬት ከበርቴውን ፊውዳል ቡድን ከተተናኮሉት ያለውን ሀብትና ስልጣን ተጠቅሞ ሊያጠፋቸው ወይም ቢያንስ ከስልጣን ሊያወርዳቸው እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ያለተራማጁ ወገን ዕውቀት፤ ስራና ድጋፍ ሀገር መምራትና መገንባት እንደማይችሉም በደምብ ያውቃሉ። (እዚህ ላይ አንባቢ ልብ እንዲለው የምፈልገው ነጥብ፣ ተራማጅ ወይም ለውጥ ፈላጊ የተባለው ቡድን ኃይለስላሴ ራሳቸው አውሮፓና አሜሪካ ልከው እንዲማሩ ካደረጉ በኋላ በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ መድበዋቸው ይሰሩ የነበሩ እንደ ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድና አቶ ከተማ ይፍሩን የመሰሉ ፕሮፌሽናል ሰዎች ስለነበሩ፣ አምባሳደር ዘውዴ ኃይለስላሴ በግል ወይም በልባቸው ተራማጅ ወገኑን ይደግፋሉ ያሉትን አባባል ትክክለኛነት ሚዛን እንዲደፋ ያደርጋል።) በመሆኑም ሁለቱን የማይታረቅ ቅራኔ ያላቸውን ቡድኖች አቻችለው(compromise እያደረጉ) ነበር የስልጣን ዘመናቸውን የገፉት።
አፄ ኃይለስላሴ ከላይ የተጠቀሰውን ከጃፓን መንግስት ጋር የነበራቸውን የቅርብ ወዳጅነት ተጠቅመው በ1940ዎቹ አመታት መጨረሻና  በ1950ዎቹ አመታት መጀመሪያ ላይ ጃፓኖቹን ”የናንተ ሀገር በስልጣኔ ያደገች ናት፤ የመንግስት አገዛዝ ስርዓታችን ደግሞ የሁለታችንም ንጉሳዊ ነው፤ በመሆኑም የናንተ ሀገር ባደገችበት መንገድ ሀገሬ እንድታድግ ሙያዊ እገዛ አድርጉልኝ” ብለው ጃፓኖቹን ጠየቋቸው። ከዚያም ጃፓኖቹ ምንም ሳያቅማሙ በጃንሆይ ሀሳብ ተስማምተው አንድ የባለሙያ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ። ለጥናት የተላከው የባለሙያ ቡድን ጥናቱን በዝርዝር አካሂዶ ብዙ ገፅ ያለው ሪፖርት ካዘጋጀ በኋላ ለጃንሆይ አቀረበ። የሪፖርቱ ፍሬ ሀሳብ “ወደፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የፖሊሲ ሪፎርም ፐሮፖዛል ከመግባታችን በፊት መወሰድና መስተካከል የሚገባቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስላሉ እነሱን ለማስተካከል የሚከተሉት ዝርዝር አስተዳደራዊ ርምጃዎች መወሰድ አለባቸው” የሚልና መወሰድ ያለበትን ዝርዝር ያካተተ ሪፖርት ነበር። ጃንሆይ ሪፖርቱ ከቀረበላቸው በኋላ እሺ ወይም እምቢ ሳይሉ ለረዥም ጊዜ አቆዩት። ምክንያቱም ይወሰዱ የተባሉት አስተዳደራዊ ርምጃዎች ቢወሰዱ ስርዓቱን፤ በተለይም ለውጥ የማይፈልገውን የመሬት ከበርቴ ስልጣንና ጥቅም በቀጥታ የሚጎዳ በመሆኑ  ጃንሆይ ለህይወታቸውና ለስልጣናቸው በጣም የሚያሰጋ ሆኖ ስላገኙት በጃፓኖቹ የተሰራውን ጥናት ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ግልፅ በሆነ አነጋገር የጥናቱ ተግባራዊነት የደም ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ ስለተገኘ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። ከዚያም ጃፓኖቹ ብዙ ጊዜ ጠብቀው መልስ ሊያገኙ ባለመቻላቸው “ያቀረብነው የአስተዳደራዊ ሪፎርም ተግባራዊ ካልሆነ ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የፖሊሲ ሪፎርም ፕሮፖዛል ስራ መግባት አንችልም፤ እኛ ደግም ሀገራችን ትፈልገናለች” ብለው ወደሀገራቸው ተመለሱ።


ይህን ታሪክ ከቅርብ ጊዜ በፊት ለአንድ ጓደኛዬ ሳጫውተው፤ “አዎን ልክ ነህ፤ ይሄንን ታሪክ እኔም አውቀዋለሁ፤ በወቅቱ ጃፓን ያቀረበችው ሀሳብ በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት ቢያገኝ ኖሮ ጃፓኖቹ ሁለቱን ሀገራት በኮንፌደሬሽን እስከማዋሀድ የሚደርስ ፍላጎት ነበራቸው” ሲል አጫወተኝ። አንድ የታላቅ ወንድሜ የህይወት ዘመን ጓደኛ ደግሞ(ለአርባ ሰባት አመታት በጓደኝነት ከኖሩ በኋላ ሞት ነው የለያያቸው።) ይህንን ፅሁፍ አንብብልኝ ብዬ ሰጥቼው ካነበበ በኋላ “ጃፓኖች ለምን ይሄን ያህል እኛን ሊረዱን ፈቃደኛ እንደሆኑ ታውቃለህ?” አለና “አሜሪካ ጃፓንን በአቶሚክ ቦምብ ሂሮሺማና ናጋሳኪ ላይ መትታ ጃፓን በትልቅ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት የጃፓንን መንግስት 5 ሚሊዮን ዶላር ረድቷል፤ ይህን ውለታ ቆጥረው ነው ከላይ ያጫወትከኝን አቋም የወሰዱት” አለኝ። አይገርምም? በዚያን ዘመን የነበረችዋ ኢትዮጵያ፣ በዚያን ዘመን የነበረችዋን ጃፓን የመርዳት አቅም ነበራት ማለት ነው! ሌላ አንድ ነገር ልጨምርላችሁ። ሰሞኑን ደግሞ ለአንድ የኮንሰልተንሲ ኮንትራት ስራ ወደ ቢሾፍቱ ሄጄ ነበር። በመንገድ ላይ ለስራ ባልደረቦቼ ይህንን ታሪክ ሳጫውታቸው አንዱ ጓደኛዬ “ይገርማል! በወቅቱ ጃፓኖቹ ሁለቱን ሀገራት በኮንፈደሬሽን ለማዋሀድ አስበው ነበር ነው ያልከኝ?” አለና፤ “እኔ የማውቀው እንግሊዝና አውስትራሊያ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በኮንፈደሬሽን አንድ ላይ እንደነበሩ ነው” አለኝ። የእንግሊዝና የአውስትራሊያ አይገርምም! ምክንያቱም የአውስትራሊያ ህዝብ ማለት፤ አቦሪጂኖችን ሳይጨምር፤ በዋነኛነት በስደት ከእንግሊዝ ሀገር የሄደ ህዝብ ማለት ነው።(አካሄዳቸው ራሱ የሚገርም ታሪክ አለው።አቦሪጂኖች የእንግሊዝ ህዝብ ወደአውስትራሊያ ሄዶ ከመስፈሩ በፊት እዚያው አውስትራሊያ ውስጥ ይኖር የነበረ ባለሀገር(Indegenous) ህዝብ ነው።) ጃፓኖች ግን ከእኛ ጋር ምንም የደም ትስስር ሳይኖራቸው፣ እንደ አንድ ሀገር አብሮ ለመኖር ማሰባቸው ምን ያህል መልካም ነገር ቢያስቡልን ነው አያስብልም?


በእኔ እምነት በታሪካችን ከተከሰቱት ትልቅ የታሪክ አጋጣሚዎች መሀከል ይህ ክስተት አንዱና ትልቁ ነው ባይ ነኝ። ትልቅ እጥፋት(turning point) ይሆነን ነበር። ውሳኔው ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ ከባድ ውሳኔ ነበር ባይ ነኝ። ሀገራችንም ቀደም ብላ እስካሁን ያልሞከረችው የካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ ትገባ ነበር ማለት ነው። የካፒታሊዝም ስርዓት የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም፣ ሁሉም ያደጉ የአለም ሀገራት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል “ቅይጥ ኢኮኖሚ” በሚል ስም ተከትለውት ያደጉበት ስርዓት መሆኑ ይታወቃል። አሁን ዞር ብዬ ሳወዳድራቸው የጃፓኖቹን ምክር ተግባራዊ የማድረጉ ውሳኔ ከላይ እንደገለፅኩት የደም ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም፤ እንደ ስልሳ ስድስቱ አብዮት ውጤቱ በተለያዩ መንገዶች አሳዛኝ ይሆን ነበር የሚል ግምት የለኝም። በመሆኑም ጥናቱ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ እንደ እንግሊዝና ጃፓን ንጉሳዊ ስርዓቱ ለምልክት እንዲኖር ተደርጎ(ጃንሆይም ህይወታቸውን ሳያጡ ብቻ ሳይሆን ከስልጣንም ሳይወርዱ፤ (የፊውዳሉ ቡድን ከሚፈጥረው ጫና ከተረፉ ማለቴ ነው)) የፖለቲካ ስልጣኑ ተራማጅ አስተሳሰብ ባላቸው የተማሩ ወገኖች(በእነ ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሐብተወልድ) እጅ ስለሚገባና ስርዐቱ ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ስለሚቀየር የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እምብዛም አስቸጋሪ አይሆንም ነበር ባይ ነኝ።                                        
ወቅቱ የሚጠይቀውን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት በራሳችን እውቀት ተጠቅመን መወሰድ ያለበትን እርምጃ አልወሰድንም፤ በራሳችን መውሰድ ያለብንን እርምጃ ለመውሰድ ዕውቀቱና ጥበቡ ካነሰን ደግሞ የሰውን ምክር(የጃፓኖቹን ማለቴ ነው) ሰምተን፤ ለራሳችን እንዲመቸን(customize) አድርገን ተግባራዊ ማድረግ አልቻልንም። ስለዚህ በድህነታችን እንድንቀጥል ምክንያት የሆነን ነገር እራሳችን መረጥን። በመሆኑም አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት ለመፍጠር የሚያስችል ሌላ ታሪካዊ አጋጣሚ (Junction) መጠበቅ ግድ ሆነብን። ጃንሆይም ውሎ አድሮም ቢሆን የፈሩት አልቀረላቸውም፤ ስልጣንና ህይወታቸውን በአሳዛኝ መንገድ አጡ፤ ጦሱም ለእነኛ የተማሩና ተራማጅ አስተሳሰብ ለነበራቸው ባለስልጣኖቻቸውም ተረፈ።
የኤርትራ    ፈደሬሽን    መፍረስ፡                                 
ኤርትራ ለ60 አመታት በጣሊያንና በእንግሊዝ ከተገዛች በኋላ የተባበሩት መንግስታት የሀገሪቷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን የውሳኔ ሀሳብ እንደያቀርቡ አምስት ሀገራት የሚገኙበት ኮሚቴ አቋቋመ። ሀገራቱም ኖርዌይ፤ ጉዋቴማላ፤ ፓኪስታን፤ ደቡብ አፍሪካና በርማ ነበሩ። ሀገራቱም በጉዳዩ ላይ ተወያይተውበት በድምፅ ብልጫ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፈዴሬሽን እንድትወሀድ የውሳኔ ሀሳብ አቀረቡ። በዚሁ መሰረት በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ በ1945 ዓ.ም. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፈደሬሽን ተዋሀደች። በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ መሰረት፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ከተወሰነ በኋላ ጥቂት ጊዜያት ቆይቶ የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር ወዳድ ኤርትራውያን ጋር ውስጥ ውስጡን በመነጋገር ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ሰፊ የፖለቲካ ስራ ተሰራ።

ይህንን የፖለቲካ አካሄድ በሚገባ የተረዱ፤ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ቢደረግ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ቀድመው ያወቁ፤ የወደፊቱ የፖለቲካ አካሄድ እንደራዕይ ፍንትው ብሎ የታያቸውና በንጉሱ የመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ተራማጅ ባለስልጣናት የሁኔታው አካሄድ አልተዋጠላቸውም። በመሆኑም ለንጉሱ፤ “ጃንሆይ ይሄ ፌዴሬሽኑን አፍርሶ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር የመቀላቀሉ እርምጃ ለመንግስትም ለሀገርም አይበጅም፤ የረዥም ጊዜ መዘዝ ይዞብን ይመጣብናልና ቢቀርብን ይሻላል፤ ማለትም የተባበሩት መንግስታት በወሰነው መሰረት ኤርትራ በፌዴሬሽን ብትቀጥል ይሻለናል” የሚል ጊዜውን የጠበቀና በሳል ምክር አቀረቡ። ይሁን እንጂ ጃንሆይ እነኚህን በትምህትና በልምድ ላይ የተመሰረተ ብስለትና አርቆ አስተዋይነት የተላበሱ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሀሳብ መደገፍ ሲገባቸው ፌዴሬሽኑን የማፍረስ ሀሳባቸውን ገፉበት። ንጉሱ ሀገር ወዳድ ከሚባሉት ኤርትራውያን ጋር ውስጥ ለውስጥ የፖለቲካ ስራ ሰርተው ከጨረሱ በኋላ በ1953 ዓ.ም. ፌዴሬሽኑን አፍርሰው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል አደረጉ። ከቅልቅሉ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እንደግብፅ አይነቶቹ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሁኔታዎች ተመቻቹላቸው። በመጀመሪያ ጀብሐን ቀጥሎም ሻዕቢያን አደራጅተው “የነፃነት” ትጥቅ ትግሉ ጀመረ። የኛም የኢትዮጵያውያን የሰሜኑ የ30 ዓመታት የጦርነት ገፈት ቀማሽነት ታሪክ አብሮ ተጀመረ።   በኔ ግምት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ትቀጥል ወይስ አትቀጥል የሚለው ጥያቄ ትልቅ አጀንዳ የነበረበት የ1953 ዓ.ም. ዘመን ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ ወይም መንትያ መንገድ(Junction) ላይ የደረስንበት ጊዜ ነበር። በዚህን ወሳኝ ወቅት ሀገሪቷ መከራ በበዛበት መንገድ እንድትገፋ ወይም በተሻለ መንገድ እንድትሄድ የሚያደርጋት በጣም ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ወቅት ነበር። የተማሩት ተራማጅ ቢሮክራቶች ንጉሱን በመከሩበት መንገድ፤ ማለትም ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት በወሰነው ውሳኔ መሰረት በፌዴሬሽን እንድትቀጥል ማድረግ ሲገባን፤ በተሳሳተ መንገድ በኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል በመደረጉ ከፍተኛ ስህተት ፈፀምን። ንጉሱ ይሄንን ሲወስኑ ሀገርን ከመውደድና ከመወገን አንፃር በቀናነት ያደረጉት ነው ብዬ ባምንም፤ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂያዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ከመሆኑ አንፃር ስመዝነው የውሳኔ ስህተት የተፈፀመ ይመስለኛል።

በመጨረሻም ኤርትራ መገንጠሏ ላይቀር ሀገሪቷ ሰላሳ አመት በፈጀ ጦርነት ቁም ስቅሏን አየች። የእነኚያ ተራማጅና በሳል የንጉሱ ባለስልጣናት ወርቃማ ምክር ተግባራዊ ባይሆንም በጊዜ ሂደት ዕውነተኛነቱ ተረጋገጠ። በዚሁ አጋጣሚ አንድ ታሪክ ላንሳ። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የምናደርገው ጦርነት እየተካሄደ እያለ ሶማሊያ በ1956 ዓ.ም. በቶጎ ውጫሌ በኩል ሀገራችንን ወረረች። በዚህም ደም አፋሳሽ ጦርነት መካሄዱ በታሪክ ተዘግቧል። ይህ ጦርነት እራሱን የቻለ የታሪክ መፅሀፍ የሚወጣው ቢሆንም፤ እኔ እዚህ ጋ ያነሳሁት ሀገራችን አንድ ጦርነት ማካሄድ አልበቃ ብሏት በአንድ ጦርነት ላይ ሌላ ጦርነት ተደርቦባት ባልጠና የኢኮኖሚ ወገቧ ሁለት ጦርነቶችን የተሸከመችበት የታሪክ ወቅት እንደነበረ ለማስታወስ ነው። የ1956 ዓመተ ምህረቱ የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት በተነሳ ቁጥር ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶምን አለማንሳት የታሪክ ሚዛናዊነትን ማዛነፍ ይመስለኛል። ከአዲሱ ትውልድ ጋር ለማስተዋወቅ ያህል ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም በደርግ የስልጣን ዘመን መባቻ ላይ የደርጉ ዋና ሊቀመንበር ሆነው ለአጭር ጊዜ ከሰሩ በኋላ በሀሳብ ወይም በአቋም ከደርግ ባለስልጣናት ጋር መስማማት ባለመቻላቸው፣ ደርግ ሊይዛቸው ቤታቸው ሲመጣ የእራሳቸውን ህይወት ያጠፉ የኢትዮጵያ ስመ-ጥር ጀነራል ነበሩ። ስመ-ጥር ካስባላቸው ታሪኮች አንዱ በ1956 ዓ.ም. ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ከባድ ጦርነት ወቅት በፈፀሙት ጀብዱ ነው። በታሪክ አንደሚታወቀው፣ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ይመራ የነበረው በጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም ሲሆን፤ ቶጎውጫሌ ላይ በተደረገው ከባድ ጦርነት የኛ ጦር ካሸነፈ በኋላ ጀነራል አማን ጦራቸው ወደ ሶማሊያ ዘልቆ በመግባት ሞቃዲሾን ለመያዝ ቢያስቡም ከንጉሱ “የጠላት ጦር ከወሰናችን ከወጣ ተመለስ” የሚል ትዕዛዝ ስለደረሳቸው መመለሳቸው በሰፊው ይነገር የነበረ ታሪክ ነው።


የ1953 ዓ.ምህረቱ የጀነራል መንግስቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ
በ1953 ዓ.ም. እነጀነራል መንግስቱ ንዋይ የሞከሩት የመንግስት ግልበጣ ሙከራ በታሪክ የሚታወቅ ነው። በመሰረቱ የሚሊታሪ መፈንቅለ መንግስት አካታች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት በመፍጠር ሀገሪቷን ወደ ትክክለኛ የዕድገት መስመር ያመጣል የሚል እምነት ባይኖረኝም፤
1ኛ - የእነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ዋና ቅራኔ ከፊውዳል ስርዓቱ ጋር ስለነበረ የፊውዳል ስርዓቱን አፍርሰው በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን ወደ ካፒታሊዝም ስርዓት የማስገባት ሂደት ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ስለነበረ፤
2ኛ - እነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ከተራማጁና ለውጥ ፈላጊው የንጉሱ ባለስልጣናት፤ ማለትም ከነጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሀብተወልድ ጋር በአመለካከት ተመሳሳይ ስለሆኑ በጋራ ሀገሪቷን ወደ ትክክለኛ የዕድገት መስመር ሊያስገቧት ይችሉ የነበረበት ዕድል ነበር የሚል ግምት ስላለኝ፤
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ(Junction) ወስጄዋለሁ። ለዚህም ጥሩ ማስረጃነት ከእነጀነራል መንግስቱ ንዋይ ጋር በማበር ከመፈንቅለ መንግስቱ ዋና አስተባባሪዎች አንዱ የነበረው ሌ/ኮሎኔሌ ወርቅነህ ገበየሁ የሚባል ግለሰብ ነበር። ይህ ሰው በጣም አስተዋይ፤ ቆፍጣና፤ ተራማጅ አስተሳሰብ የነበረውና በዘመኑ የፀጥታ ፅ/ቤት ኃላፊ የነበረው ይገኝበታል። አቶ ብርሀኑ አስረስ “የታህሳሱ ግርግር” የሚል ርዕስ በሰጡት መፅሀፋቸው ውስጥ “የዚህ ሰው ታታሪነትና ችሎታ ታይቶ የንጉሱ የቅርብ ባለሟል የመሆን ዕድል አግኝቶ ነበር” ብለዋል። ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ንጉሱ በሀገሪቱ ላይ የፖለቲካ ለውጥ እንዲያደርጉ ለመምከር ቢጥርም ሰሚ ጆሮ ማግኘት ባለመቻሉ፣ በሂደት ወደ መፈንቅለ መንግስት ጠንሳሹ ቡድን ውስጥ መቀላቀሉን አብራርተዋል። የመንግስት ግልበጣው ከከሸፈ በኋላ በሀገሪቱ ላይ ነገሮች እየተባባሱ መሄድ ቀጠሉ። በአንድ በኩል የሰሜኑ የእነሻዕቢያ ጦርነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመሬት አስተዳደሩ ከፊውዳል ስርዐት አለመላቀቁ ችግሮች እየተባባሱና እየተወሳሰቡ ለመሄዳቸው ምክንያት ሆኑ።

(አንባቢን እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምፈልገው ከላይ እንደገለፅኩት የመፈንቅለ መንግስቱ ተዋናዮችን ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ ግምት ውስጥ አስገብቼ ነው እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ(junction) የወሰድኩት። ይሁን እንጂ ከመፈንቅለ መንግስቱ ተዋናዮች በስተጀርባ በሀገሪቷ ላይ ሊሰራ የታሰበ ሴራ ይኑር አይኑር እኔ የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ይህ የታሪክ አጋጣሚ ወደተሻለ መንገድ ሊወስደን የሚችልበት ዕድል ነበረው ብዬ ስል ትንተናዬ በማውቀው ልክ መሆኑን ነው።)  

                                                                    በዚህ ውስብስብ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ሆነንም ቢሆን በ50ዎቹ መጨረሻና በ60ዎቹ መጀመሪያ አመታት በሀገሪቷ ውስጥ እያቆጠቆጠ የነበረው ዘመናዊ እርሻ “Mechanized farming” እና የግል ኢንዱስትሪ ማበብ ለሀገሪቷ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ ነበር። በግሌ የማውቀው ታሪክ በ60ዎቹ አመታት መባቻ ላይ ከሀሮማያ እርሻ ኮሌጅ በዲግሪ እንደተመረቁ የሽርክና ኩባንያ (Share company) በመመስረት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ወስደው በቀጥታ ወደሜካናይዝድ እርሻ ስራ የገቡ ምሩቃን እንደነበሩ አስታውሳለሁ። እንዳለመታደል ሆኖ በመጨረሻ የዘመኑ የሜካናይዝድ እርሻ ተዋናዮች ድካም፤ ጥረትና የስራ ተነሳሽነት በ66ቱ አብዮት አፈር በላ።  (በዚያ ዘመን የነበረውን የብልፅግና ተስፋና አንዳንድ የአተገባበር ችግሮችን በተመለከተ ትክክለኛ ታሪክ መሰረት በማድረግ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።)
(ይቀጥላል)

የአሜሪካና የእንግሊዝ ወታደራዊ ሃይል በየመን የሁቲ አማፂያን ወታደራዊ ተቋማት ላይ ከባድ ጥቃት መፈፀማቸው ተገለፀ፡፡
የዓይን እማኞች ጥቃቱን፤ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ለሮይተርስ ያረጋገጡ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳት ጆ ባይደን ከትላንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በቡድኑ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይሉ አስጠንቅቀዋል። “እነዚህ የታለሙ ጥቃቶች አሜሪካና አጋሮ በሰራተኞቻችን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን እንደማይታገሱና የአማፅያኑ የበመርከቦችን ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያደናቅፉ እንደማይፈቅዱ አሳስበዋል፡፡
 ከቀዶ ህክምና በኋላ በገጠማቸው ኢንፌክሽን ለህክምና በሆስፒታል የሚገኙት የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን ባወጡት መግለጫ፤ ከትላንት በስቲያ በአሜሪካና እንግሊዝ ጥምረት የተሰነዘረው ጥቃት፣ ድሮኖችን ባሊስቲክና ክሩዝ ሚሳይልን እንዲሁም ራዳርና የአየር መቆጣጠሪያን ጨምሮ የሁቲ አማፅያን ወታደራዊ አቅሞች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አንድ የሁቲ ባለስልጣን የተፈፀመውን የአየርና የባህር ጥቃት አስመልክቶ ሲናገሩ፤ በዋና ከተማይቱ ሰነአ እንዲሁም በሰአዳና ዳማር ከተሞች “ወረራ” መፈፀሙን አረጋግጠው ጥቃቱ “የአሜሪካን - ፅዮናውያንና ብሪታንያ ወረራ” በሚሏቸው ወገኖች፡፡የዓይን እማኞች ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ የአሜሪካና አጋሮቿ ጥቃት ያነጣጠረው ከሰንአ አየር ማረፊያ አጠገብ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ያለው ወታደራዊ ስፍራ፣ በሆዲይዳህ የሚገኘው የሮውቲ የባህር ሃይል ሰፈር እንዲሁም በሃጃ ግዛት የሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎችን ነበር፡፡
አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት የሁቲ አማፂያን፣ ከሰሞኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት በቀይ ባህር ላይ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ከሚፈፅሙት የድሮንና ሚሳይል ጥቃቶች እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን አሜሪካም ቡድኑ በቀይ ባህር ላይ ጥቃት ከመፈፀም እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋ ተዘግቧል። ሆኖም የአማፂ ቡድኑ አሻፈረኝ ብሎ ጥቃቱን አጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል። ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ የሁቲ አማፅያን  በቀይ ባህር 27 መርከቦች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን በዚህም 15 በመቶ የሚሆነው የዓለም የንግድ መርከብ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ተጠቁሟል፡፡  ከትላንት በስቲያ አሜሪካና እንግሊዝ በቡድኑ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ የቡድኑ መሪ፤ አሜሪካ በላይ የአፀፋ እርምጃ እንደሚወስዱ  ዝተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመግለጫቸው የሁቲ ጥቃት በቀጥታ የአሜሪካ መርከቦችን ያለመ ነው ብለዋል፡፡የአሜሪካ ሪፐብሊካን ኮንግረስ አባላት በአማፂው ቡድን ላይ የተወሰደው እርምጃ ከመዘግየቱ በቀር በአዎንታዊ ጎኑ ተቀብለውታል፡፡ አንዳንድ የዲሞክራት ኮንግረስ አባላት በበኩላቸው አሜሪካ ሌላ የአስር ዓመት ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከትላንት በስቲያ በየመን ላይ የተፈፀመው ጥቃት የሁቲ አማፅያን በቀይ ባህር ላይ ከፍተኛ የተባለውን ጥቃት ከሰነዘሩ ጥቂት ቀናት በኋላ የተከናወነ ነው የተባለ ሲሆን አማፅያኑ ወደ ደቡባዊ ቀይ ባህር የተኮሷቸውን 21 ድሮኖችና ሚሳይሎች የአሜሪካና የእንግሊዝ ባህር ሃይል መትተው ለመጣል መገደዳቸው ተዘግቧል፡፡



Monday, 08 January 2024 19:51

ሠሚ አልባ ጩኸት !

እኛ ስንከፋ ፤
ምድሩን ቆርቆር
አንገት ደፍተን ቆፈር ቆፈር ...
ጌቶች ሲከፋቸው ፤
እኛን ኮርከም ኮርከም
በ፩ ላይ ወግነው ፥ ከፀሀይ ከሀሩሩ ጋር ።
አቤት ብንል ለ “ ማ “ ?
አካላችን ቀልጦ
ተስፋችን ተውጦ ፤
እንባና ደማችን በ፩ ጅረት ሲፈስስ
ባመንነው መዶሻ አናታችን ሲፈርስ ።
ይግባኝ ብንል ለ “ ማ “
ሠማዩ እንዲታረስ ፤
ዳኛው ችሎት መጥቶ በንጉሱ ፈረስ ።
የአብፀጋ ተመስገን /maddbn

•  በ4 ወራት ውስጥ ከ15 ሺ በላይ ቤት ፈላጊዎችን መዝግቧል


በአራት ወራት ውስጥ 15 ሺህ 388 ቤት ፈላጊዎችን መመዝገቡን ያስታወቀው  ኪ  ሀውሲንግ ፋይናንስ ሶልሽን፤ በዛሬው ዕለት ከ6 ሰዓት ጀምሮ በዲ ሊኦፖል ሆቴል ባካሄደው ዕጣ የማውጣት ሥነሥርዓት 60 ቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት አድርጓል፡፡

በዕጣ ከወጡት 60 አፓርተመንት ቤቶች  ውስጥ ሰላሳው ባለ ሦስት መኝታ  ክፍል፣ ሃያ አንዱ ባለሁለት  መኝታ ክፍል ሲሆኑ፤ ዘጠኙ ደግሞ ደግሞ ባለ አንድ መኝታ ክፍል መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ዕጣ የወጣላቸው አፓርትመንቶች በፒያሳ፣ በጋርመንትና  በሀያት የሚገኙ ሲሆኑ፤ ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸዉ ያለቀላቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኪ ሀውሲንግ፤ በአስር አመት ውስጥ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ቤቶችን ገንብቶ ለቤት ፈላጊዎች ለማስረከብ ዕቅድ እንዳለው  አስታውቋል።

ኪ ሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ባለፈው ነሀሴ ወር የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች በ77 ሺ 280 ብር ቅድመ ቁጠባ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ሞዴል ፕሮጀክት ማስተዋወቁ አይዘነጋም፡፡

Thursday, 04 January 2024 00:00

“የእኔ ሽበት”

“የእኔ ሽበት” እና ሌሎች ግጥሞች” በተሰኘ ርዕስ  በመጽሐፍ ያሳተመው፡፡ የወላለዬ ወለቶት ከያዟቸው ምሥጢራት ባሻገር የመጽሐፉ ዲዛይን፣ መልክአ ፊደል እና ኅትመቱ በዓይነቱ ልዩ የሚባል ነው፡፡ በጃፋር መጽሐፍት ያገኙታል፡፡