Administrator

Administrator

  ሁለት ታሪኮች አሉ፡፡ ተመሳሳይም የሚለያዩም፡፡ አንደኛው የቡልጋሪያውያን ጋቭሮቮዎች ታሪክ ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡
የቡልጋሪያው ታሪክ እንዲህ ነው፣
በስግብብነታቸው ይታወቃሉ ከሚባሉት ጋቭሮቮዎች አንደኛው ብዙ ብርቱካን ይዞ እየበላ ወደ ሰፈሩ ይመጣል፡፡ የመንደር ጓደኞቹም ዘመዶቹም ብርቱካን መብላቱን አይተዋል፡፡ ከነሱም መካከል ብርቱካን ያላቸው አሉ፡፡ ሆኖም ሲበሉ ያያቸው ስለሌለ የራሳቸውን ብርቱካን ደብቀው ከእሱ ብርቱካን እንዲያካፍላቸው ጠየቁት፡፡ አጅሬም እንደነሱ ጋቭሮቮ ነውና፤
“አልሰማችሁም እንዴ ጎበዝ? እዚያ ወዲያ እሩቅ ከሚታየው መንደር እኮ ብርቱካን በነፃ እየታደለ ነው፡፡ እኔም ያመጣሁት ከዚያ ነው፡፡”
የሰፈሩ ጋቭሮቮች ብርቱካን ይታደላል ወዳላቸው ቦታ ነቅለው መሮጥ ጀመሩ፡፡ በየመንገዱ ያገኙት ህዝብም ሲጠይቃቸው ብርቱካን በነፃ እንደሚታደል ይናገራሉ፡፡ የሰማው ላልሰማው እየነገረ አገሩ በሙሉ ብርቱካን ወደሚገኝበት መንደር በሩጫ እየጎረፈ ሄደ፡፡
ይሄኔ ያ በመጀመሪያ በነፃ ይታደላል ብሎ የዋሸ ጋቭሮቭ ነገሩ አጠራጠረው፡፡ ሲያይ የህዝቡ ቁጥር ይብስ እየጨመረ ሄዷል፡፡ ስለዚህ፤
“አሀ! ይሄ ነገር እውነት ይሆን እንዴ?” ብሎ እራሱን ጠይቆ፣ ወደዚያው በፍጥነት መሮጥ ጀመረ፡፡
***
የኢትዮጵያው ታሪክ ደግሞ እንዲህ ነው፡፡
በአንድ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ሌባ ንብረት ዘርፎ ይሰወራል፡፡ ንብረቱ የተዘረፈበት ለመንግሥት ያመለክታል፡፡ መንግሥት ለህዝቡ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ “የገባችሁበት ገብታችሁ ይህን ሌባ ፈልጋችሁ አምጡ!” ብሎ፡፡ ስለሆነም ህዝቡ በሙሉ ሌባ ፍለጋ ተሰማራ፡፡ ሌባው ግን አልተገኘም። በመካከል አንድ በመልክም በቁመትም ልክ ያንን ሌባ የመሰለ ሰው ከባላገር ይመጣል፡፡ ህዝቡ ሮጦ ይህን ሰው ይይዘዋል፡፡ ሰውየው “እባካችሁ በመልክ ሌባውን መስያችሁ ነው እንጂ እኔ ሌባ አይደለሁም፡፡ ምንም የሰረቅኩት ነገር የለም” አለ፡፡ የሚያምነው ጠፋ፡፡ የማርያም ጠላት አደረጉት፡፡ ጩኸቱ በዛበት፤ “ሌባው አንተ እራስህ ነህ! ዛሬ ቀን ብታምን ይሻልሃል! እኛን በጭራሽ ለማታለል አትችልም፡፡ ይልቅ ተናገር!” እያሉ አፈጠጡበት፡፡ ያም ሰውዬ በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤
“አሁን ይሄ ሁሉ ህዝብ እንዴት ይሳሳታል? በፍፁም አይሳሳትም፡፡ … እኔ እራሴ መስረቄን እረስቼው ይሆናል እንጂ!” በመጨረሻም “አዎ እኔ ነኝ” ብሎ አመነና ወደ ወህኒ ወረደ፡፡
***
በቡልጋሪያም ሆነ በኢትዮጵያ ወይም በሌላ አገር ህዝብ ህዝብ ነው፡፡ የቡድን ስሜት የቡድን ስሜት ነው፡፡ አንድ አቅጣጫ ይዞ ያንኑ ቦይ ተከትሎ መፍሰስ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም፡፡ አንድም በመጭበርበር፣ ወንዝ ፈጥሮ፣ ወንዝ ሆኖ ሊጎርፍ ይችላል፡፡ አንድም ትእዛዝ አክብሮ፣ በታዛዥነት እየፈሰሰ ግለሰቦችን እየተጫነ፣ አንዴ መውረድ ወደጀመረበት አሸንዳ በጀማ ይጓዛል፡፡ ላቁምህ፣ ልገድብህ ቢሉት በእጄ አይልም፡፡ የመንገኝነት ስሜት (Herd instinct) በበጎም በክፉም ሊነዳ የሚችል ብርቱ ስሜት ነው፡፡  ልዩ ጥንቃቄ የሚፈልግ አደገኛ ቡድናዊ ደመ-ነብስ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ አገር ባህላዊ ህብሩ፣ ኢኮኖሚያዊ ትግግዙ፣ ጎሳዊ ትስስሩና አገራዊ አንድነቱ ቋጠሮው በጠበቀበትና ውስብስብ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ፤ የእያንዳንዱ ቀልጣፋ ግለሰብ ወይም ደፋር ቡድን ፍላጎት፤ የብዙሃኑን ፍላጎት የሚቃኝና የሚመራበት ሁኔታ ሀያል ነው፡፡ ግለሰቦች፤ ቡድኖች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና ማህበራት አዋሹን ህዝብ ወዳፈተታቸው አቅጣጫ ለመውሰድ በማባበልም፣ በመደጎምም፣ በማታለልም፣ በማዘዝም፣ በማስፈራራትም ቦይ ለመቅደድ መጣጣራቸው አይቀርምና የመንገኝነት ጉዳይ አጠያያቂና አደገኛም ሊሆን ይችላል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሁሉም የህዝብን ችግርና ብሶት መሰረት ያደረገ ቋንቋ አንግቦ ይነሳል፡፡ አንደበተ-ቀናው፣ ዲስኩር የሚዋጣለት በቀላሉ ይደመጣሉ፡፡ የእኛ ህብረተሰብ የተራኪና አድማጭ ህብረተሰብ (Story-teller society) ነው፡፡ ደህና ተናጋሪ ካገኘ አዳምጦ ወደ ማመን እንጂ መርምሮ ወደ መረዳትና ተንትኖ ወደ መቃወም ገና ሙሉ በሙሉ የተሸጋገረ አይደለም፡፡ በግሉ አስቦ፣ በግሉ መርምሮ፣ በግሉ ለራሱ የሚቆም ጥቂት ነው፡፡ መብቱን ለማስከበር የሚራመደው ገና ጎረቤትና ጎረቤት ተያይቶ፣ እነ እገሌ ምን አሉ ተባብሎ፤ ነው፡፡ ስለዚህም የነቃ ይቀድመዋል፡፡ ጮሌ እንዳሻው ይነዳዋል፡፡ አንደበተ-ቀና ያሳምነዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የዞረ ዕለትም ያው ነው፡፡ ሲገለበጥም እንደዚያው ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ደመ-መራራ ነው፡፡ የተከተለውን ሊያባርረው፣ የካበውን ሊንደው፣ ያከበረውን ሊንቀው ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ በማህበረሰቡ ዘንድ የመንገኝነት ስሜት መሪ ሚና መጫወቱን አለመዘንጋት ነው፡፡
ይህን የመንገኝነት ስሜት የሚመራ ሁሉ የተቀደሰ ዓላማ አለው ለማለትም አይቻልም፡፡ “ሆድ ዕቃው የተቀደደበት እያለ ልብሱ የተቀደደበት ያለቅሳል” ይሏልና፡፡ ስለዚህም እውነተኛውን ከሀሳዊው፣ ዋናውን ከትርፉ፣ ኦርጅናሌውን ከአስመሳዩ፣ ምርቱን ከግርዱ ለይቶ፣ አይቶ መጓዝ የሚያስፈልግበት ሰዓት ነው፡፡ ኤሪክ ሆፈር የተባለው ፀሐፊ፤ “አብዛኞቹ የቅዱስ ሰው ምርጥ ሃሳቦች ከሃጢያተኝነት ልምዱ ያገኛቸው ናቸው።” ያለውን አለመዘንጋት ነው፡፡ የወቅቱ መዞሪያ-ኩርባ (Turning point) መቼና የት እንደሆነ የማያይ ቡድን ወይም ፓርቲ እንደ እቴቴ ሽረሪት ድር ራሱን በራሱ ተብትቦ፣ ራሱን በራሱ ውጦ ለባላንጣው ሲሳይ የሚሆን ነው፡፡ ትንሽ መንገድም ቢሆን በሚያግባባቸው አቋም አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ቡድኖች ሲነጋ በቀኝ ጎናቸው ሊነሱ ይችላሉ። ለመንቃት በርትቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ዳተኝነትን ማስወገድና የቤት ስራን መስራት ያስፈልጋል፡፡ “ሰነፍ ይፀድቃል ወይ ቢለው፣ ገለባ ይበቅላል ወይ አለው” እንዳለው ገለባ ሆኖ ላለመቅረት ማለት ነው፡፡
ዛሬም የሦስት ምክሮች ዘመን ነው- ስለዚህ ባንድ በኩል “ዝግጅት! ዝግጅት!  አሁንም ዝግጅት!” ማለት ተገቢ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ፅናት! ፅናት! አሁንም ፅናት!” ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ምክር አዲስ እንዲወለድ የሚጠቅመውን ያህል ነባሩ በቀላሉ እንዳይፈረካከስ ይጠቅማልና የጠንካራ ድርጅት መሰረት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን የመበታተን ሥጋት እንደ ሀገር ችግር ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንዲት ነብሰጡር ሴት ጎረቤቷ በምትወልድበት ቀን ልውለድ ብትል እንደማይሆንላት ሁሉ፤ የፖለቲካ ድርጅቶችም የራሳቸውን ዕድሜና ብቃት፤ የማፍሪያና የማዘርዘሪያ ከዚያም ለፍሬ መብቂያ ጊዜ አይተው ብቻ ነው መነሳት ያለባቸው፡፡ ሌላው ከሚቀድመን ተብሎ ሳይጠነክሩ የሚሰራ ስራ የብልህ መንገድ አይደለም፡፡ የማያስተማምን ውህደት በሰም የተጣበቀ ጥርስ መሆኑን መርሳትም አይገባም፡፡ “ዛሬ የትላንትና ተማሪ ነው” እንዳለው ቶማስ ፉለር፤ ትላንትን ማሰብ የተማሪውን አስተማሪ እንደማወቅ ይሆናል፡፡ ማሰብ፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ነው፡፡ “ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል” እንዲሉ የሞተ ነገር ላይ መነታረክ ያልሞተውን ነገር እንዳናይ ያደርገናል፡፡ ሳያስቡ መጓዝ መፈክርን ያስነጥቃል፡፡ ሳያስቡ መጓዝ የተገኘን እድል በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፡፡ ባገኙት ድል ክፉኛ አለመፈንደቅ ብልህነት ነው፡ በደረሰ ጊዜያዊ ሽንፈትና ችግር የመጨረሻ የመንፈስና የአካል መፈረካከስ ድረስ መውረድም ደካማነት ነው-”የሚደኸይ ጉሮሮ ሁሌ ጣፋጭ ነገር ይመኛል” እንዲል መጽሐፍ፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሽኩቻ፤ ከመሰነጣጠቅ ለበያቸው ሲሳይ ከመሆን መቼ ይሆን የሚወጡት? የሚለው ጥያቄ ዛሬም አለ፡፡ ዛሬም ከመከፋፈል፣ ዛሬም ከመጠላለፍ እንዳይወጡ የሚያደርጋቸው የመርገምት አዙሪት ያው እንደተለመደው የት/ቤት፣ የአፈር ፈጭ አብሮ አደግነት፣ የመጠፋፋትና የአውቅሁሽ ናቅሁሽ ፖለቲካ ይሆን? “በቅርብ ያለ አማች ወፍጮ ላይ ይቀመጣል” የሚሉት ዓይነት ማለት ነው።



  ኢትዮ ቴሌኮም ፤ በ2016 በጀት ዓመት የደንበኛ ብዛትን በ8.3% በመጨመር 78 ሚሊዮን፣ አጠቃላይ ገቢውን ደግሞ 90.5 ቢሊዮን ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው በ2016 በጀት ዓመት የደንበኞቹን ብዛት 78 ሚሊዮን ለማድረስ ያቀደ ሲሆን፤ በሞባይል 7.5% በመጨመር 74.74 ሚሊዮን፣ በሞባይል ዳታና ኢንተርኔት 24% በመጨመር 41.17 ሚሊዮን እንዲሁም የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኛ  36.3% በመጨመር 842.8 ሺህ በማድረስ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠንን 71 % ለማድረስ ማቀዱን አመልክቷል፡፡  የቴሌብር ደንበኞች ቁጥርን ደግሞ  በ28.5% በመጨመር 44.1 ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱም ተጠቁሟል፡፡
ኩባንያው ገቢን ከማሳደግ አኳያ ከመደበኛ የቴሌኮም ገቢ ምንጮች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ
አገልግሎቶችን በማካተት የዲጂታል አገልግሎቶችን፣ አዳዲስና የተሻሻሉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ
አገልግሎቶችንና የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖችን ለገበያ በማቅረብ፤ የቴሌብር ተደራሽነት፣ አገልግሎት
አይነቶችና የአጋሮችን ቁጥር በማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል እንዲሁም የደንበኛ
እርካታን፣ ቆይታንና ታማኝነትን በማሳደግ የ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ የገቢ መጠንን 90.5 ቢሊዮን
ብር ለማድረስ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ይህም ከዘንድሮው በጀት አመት በ19.4% የሚልቅ  ይሆናል ተብሏል፡፡
ኩባንያው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በውድድር ገበያው የኩባንያችን ህልውና የሆኑትን ደንበኞች  በአገልግሎቶቻችን በማርካትና ከኩባንያችን ጋር ረዥም ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የአገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ የመረጡትን የአገልግሎት አይነት መጠቀም እንዲችሉ በማድረግ ተደራሽነትን የማሳደግ፣ የድህረ-ሽያጭ አገልግሎቶችን በማሻሻል እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትን የኔትዎርክ ዴንሲቲ የሚያሳድጉና የደንበኞችን ተሞክሮ ለማሻሻልና እርካታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሰፊ የኔትዎርክና የሲስተም ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስራዎች ይከናወናሉ፡፡
”የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ የውድድር ገበያውን ታሳቢ ያደረገና ኩባንያችን የደረሰበትን ደረጃና የኢንዱስትሪውን ለውጥ በማገናዘብ ካለፈው ዓመት ስትራቴጂ አፈጻጸም ግብዓት በመውሰድ፣ የተለያዩ ዳሰሳዎችን በማከናወን በውድድር ገበያው በሁሉም መስክ መሪነቱን በማስቀጠል የሀገራችን የቴሌኮም ዘርፍ የማህበረሰባችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዲኖረው ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፤” ብሏል ኢትዮ ቴሌኮም፡፡


   በወሲብ ንግድ ላይ በተሰማሩ ሴቶች ላይ የሚደርሰው አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ተገለፀ፡፡
ይህን የገለፀው “እልልታ ውሜን አት ሪስክ” የተባለው በሴተኛ አዳሪዎች ላይ  ትኩረት አድርጎ  የሚሰራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ይህንን ጥቃትና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የወሲብ ንግድ በምን መልኩ መቀነስ እንችላለን በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር ከትላንት በስቲያ  ሀሙስ ሀምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በኔክሰስ ሆቴል የግማሽ ቀን ዎርክ ሾፕ ያካሄደ ሲሆን፤ በወርክ ሾፑ ላይ የፍትህ አካላት፣ የፖሊስ ተወካዮች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሚዲያ አካላትና የህግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
 በእለቱ ወቅታዊውን የወሲብ ንግድ ሁኔታና በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴተኛ አዳሪዎችን  የተመለከተ ጥናት የቀረበ ሲሆን፤ ሴቶች ወደዚህ አስከፊ ህይወት እንዲገቡ ከሚያደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የትዳር መፍረስ፣ የአቻ ግፊት የቤተሰብ ፍቺና ሞት፣ ሥራ ማጣት፣ በስራ ቦታዎች የሚደርሱ ጫናዎችና፣ በስራ ቦታዎች ተያዥ ማጣት በዚህ የወሲብ ንግድ ላይ ከ13 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ለጋ ታዳጊዎች እንደሚገኙበት በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ይህ የወሲብ ንግድ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋና መልኩን እየቀያየረ መምጣቱን ያመለከተው ጥናቱ፤ የወሲብ ንግዱ ቀድሞ አልቤርጎ ውስጥ ይፈፀም የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በየጎዳናው፣ በመኪና ውስጥ፣ በበይነመረብ፣ በእንግዳ ማረፊዎች፣ በት/ቤቶች አካባቢና በተለያዩ ቦታዎች እንደሚፈፀም አብራርቷል፡፡
በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማራች አንዲት ሴት በአማካይ በቀን ከሶስት ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት እንደምታደርግ ያመለከተው ጥናቱ፤ ለዚህ የወሲብ ንግድ መስፋፋት የመጠጥ ቤቶች ቁጥር እንደ አሸን መፍላት፣ ልቅ የሆኑና ሴቶችን ወደዚህ ስራ የሚገፋፉ ማስታወቂያዎች መበራከት፣ የወሲብ ንግድን ሳይለፉ ገንዘብ ማግኛ መንገድ አድገው የሚሰብኩ ህገወጥ ደላሎችና ኤጀንሲዎች መብዛትና ሌሎችም ምክንያቶች ተገልጸዋል፡፡
የህግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ሜሮን አራጋው በዎርክሾፑ ላይ ባቀረቡት ጥናት እንዳብራሩት በህጉ የተቀመጡ የሴት ልጅ ጥቃት መከላከያ ህጎች በአግባቡ አለመተግበር፣ የግንዛቤ እጥረትና ሌሎችም ምክንያቶች ተደራርበው የወሲብ ንግድ እንዲስፋፋ ብሎም በዚህ ሥራ የተሰማሩ ለጋ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፤ የፍትህ አካላት፣ ፖሊስ፣ ሚዲያውና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ ተቀናጅተው ካልሰሩ ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰና እየተስፋፋ እንደሚቀጥል አሳስበዋል፡፡



      - ንግድ ሚኒስቴር በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ ሪልእስቴቱ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ እንዲጠራና ዳግም ወደ ስራ እንዲገባ አደርጓል
       - አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በባለአክሲዮኖች አብላጫ ድምፅ ተመርጠው በድጋሚ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነዋል


         አክሰስ ሪልእስቴት አክሲዮን ማህበር፣ ከቤት ገዥዎች ጋር የነበረውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ሂደት ውስጥ መግባቱንና የንግድ ሚኒስቴር በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ሪልእስቴቱ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ስብሰባ እንዲጠሩና ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ በሰጠው መመሪያ መሰረት፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም አጠቃላይ የባለአክሲዮኖች ስብሰባ በመጥራት፣ አዲስ ቦርድ በመምረጥና ህጋዊ ሁኔታዎችን በማሟላት ዳግም ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ሪል እስቴቱ በዚህ ዕለት ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔም፣ የቀድሞውን የአክሲዮኑን ቦርድ ስብሳቢ አቶ ኤርሚያስ አመልጋን በአብላጫ ድምፅ በድጋሚ የቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መርጦአቸዋል ተብሏል።
ለ12 ዓመታት መፍትሄ ሳያገኝ የከረመው የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዥዎች ጉዳይ በአዲሱ ቦርድ መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ባለአክሲዮኖቹና ቤት ገዥዎች ተናግረዋል።

     አንጋረ ፈላስፋ መፅሐፍ ላይ እንዲህ ይላል፡- “አንድ ንጉስ ለህዝቡ፤ ‘ዘመን እንደ ምን አለች?’ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ህዝቡም፤ ‘ዘመን ማለት አንተ ነህ፤ አንተ ሰላማዊ ስትሆን ሰላማዊ ትሆናለች፤ አንተ የከፋህ እንደሆነ ትከፋብሀለች’ ሲሉ ለንጉሱ መለሱለት።”
ምንም እንኳን ዘመንን የሚያበጀው እሱ ፈጣሪ ቢሆንም፤ ሰው መልካም ከሆነ በመልካም ስራው ፈጣሪውም የተሻለውን ይሰጠዋል። ንጉስ ዳዊት ባደረገው ነገር ሁሉ ተፀጽቶ በእንባ እያለቀሰ ፈጣሪውን በመለመኑ፣ ፈጣሪም ይቅር ባይ አምላክ ነውና ይቅር ብሎትም አልቀረም፤ “ከልጅ ልጅህ እወለዳለሁ” በማለት ትልቅ ፀጋን ሰጥቶታል። በቃሉም መሰረት ከድንግል ማርያም ተወልዶ የዓለምን ሀጢያት ሁሉ ደምስሶ ወደ ዘላለም ሕይወት እንድንገባ አድርጎናል። ሰው ወደ መልካም ነገር ከተጠጋ ጠማማውን ያቀናል።
ህዝቡ ማንን ይመስላል? መሪውን! መሪው ማንን ይመስላል? ህዝቡን! ጥሩ መሪ፤ ጥሩ ተመሪ ህዝብ ያመጣል። ጥሩ ህዝብ፤ ጥሩ መሪን ያስገኛል። ከላይ “ዘመን አንተን ትመስላለች” እንዳሉት፣ መሪ ጉልበትን ሳይሆን ጥበብንና እውቀትን መላበስ አለበት። እንደ ጥበበኛው ኢትዮጵያዊ ዮቶር መሆንን ያሻል። ዮቶር ለሙሴ ስርዓትን አስተማረ። የዛሬን አያድርገውና ለካ እኛ ኢትዮጵያዊያን የአስተዳደር ጥበብን ገና በዓመተ ዓለም ዘመን ጀምሮ የታደልን ነበርን! “መሪነት ህዝብን ብቻ ሳይሆን እራስንና ቤተሰብንም በአግባቡ መምራት ነው” የሚሉ በርካቶች ናቸው። መሪነት ከስር ከመሰረቱ መጀመር፣ “በትንሹ የታመነ ለትልቁ ይታመናል” እንደሚባለው ሁሉ፣ እራሱን መምራት የቻለ አካባቢውንም ሆነ ሌሎች ሀላፊነቶችን መሸከም ማስተዳደር ይችላል። አንዳንድ የድርጅትም ሆነ የሌላ አመራሮች፣ ሰራተኛ ቁጭ ብድግ ስላለላቸው ብቻ የመሩና የተከበሩ ይመስላቸዋል።… በስርዓቱ ያስተዳደሩም እየመሰላቸው በዚህ ባህሪያቸው ይቀጥላሉ።
…”ዘመን አንተን ትመስላለች” እንደተባለው፣ ቤተሰብም ሆነ መስሪያ ቤት፣ ሀገርም ጭምር የሚመራውን ይመስላል። መንግሥት የሚመራው ህዝብ ድሀና ደካማ ከሆነ፣ የዚያ አገር መንግሥት በሌሎች ሀገራት እይታ ደካማ ነው። መንግሥት በህዝቦቹ ላይ የቱንም ያህል ሃያልና አምባገነን ቢሆንም፣ በሌሎች ዘንድ ደካማነቱ አይሸፈንም። ጠንካራና በኢኮኖሚ የፈረጠመ ሀገርና ህዝብ ያለው ደግሞ ተፈሪና ተከባሪ ነው። “ሥርዓት ከሌለው ብዙ ህዝብ ይልቅ ሥርዓት ያለው ጥቂት ህዝብ ይበልጣል” ያሉት ባልሳሳት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ይመስሉኛል፡፡
ለምሳሌ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በደካማ አስተሳሰባቸው ላይ ደካማ ህዝብና ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ይዘው፣ ግን ደግሞ በሀብት የበለጸገ ሀገር ይዘው እድሜ ልክ እርዳታ ተቀባይ ለማኝ ሆነው ይኖራሉ። እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር በተለያየ ማዕድን የበለፀገ፣ ለግብርና አመቺ፣ ለኢንዱስትሪም ምቹ ቢሆንም፣ ጠንካራ የስራ ልምድና ባህል ባለመኖሩ፣ እንኳን ለነገ ይቅርና ለዛሬም የሚሆን የዕለት ጉርስ የሌለው ህዝብ ነው።
ከድህነታችን የባሰው ደግሞ ደካማ አስተሳሰባችን ነው። በጎሳና በብሄር ተከፋፍለን እርስ በርስ መታኮስና መገዳደል፣ አንዱን ጥሎ ሌላው መንግስት ለመሆን በጦርነት ሀገሩን ማተራመስ፣ ህዝብን ለስደትና ለርሀብ መዳረግ፣ በራሳችን ሃብት የገነባውን ማቃጠልና ማውደም የእለት ተዕለት ስራችንና ልዩ መታወቂያችን አድርገነዋል…።
ስልጣን ያለው መንግስትም ስልጣኑን በራሱ ዘመድ፣ ጎሳ፣ ብሄር ብቻ ወንበሩን በማጥለቅለቅ በብልሹ አሰራርና በሙስና በመዘፈቅ ይታወቃል። ሌላውን ጎሳና ብሄር በመጨቆን የራስን ወገን ብቻ ተጠቃሚ በማድረግ፣ ሌላው የሀገሩ ገጸ በረከት ተካፋይ ሳይሆን ምፅዋተኛ እንዲሆን በማድረግ የአፍሪካ መንግስታት የተካኑ ናቸው። “ለምን!?” ብሎ የሚጠይቅን በመግደል እንዲያም ሲል በማሰርና በመደብደብ ለስደት በመዳረግ እነሱ ብቻ በሀገሩ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ይሆናሉ። የባለስልጣኖች ከህግ በላይ መሆን፣ የሀገር ገንዘብ ማባከን፣ የነሱ ልጆችና ቤተሰቦች ከሀገር  ወጥተው በአውሮፓና በአሜሪካ በውድ ትምህርት ቤት እንዲማሩ መደረግ፣ እነሱ በህዝብና በሀገር  ሀብት የቅንጦትና የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ፤ ሌላው በሀገሩ እንደ  ስደተኛ የቁም እስረኛ ሆኖ ነፃነቱን ተገፎ እንዲኖር በማድረግ፣ ህዝቡን ለአመፅና ለመንግስት ግልበጣ እንዲነሳሳ ያደርጉታል። ይህ የአፍሪካ መሪዎች የሚታወቁበት መለያ ታርጋ ቁጥራቸው ነው።
ምርጫ በመጣ ቁጥር የተፎካካሪ (ተቃዋሚ) ፓርቲዎች ደጋፊዎችን በማሰር፣ በመደብደብ፣ ለስደት በመዳረግና በመግደል የሚጀምረው የምርጫ ቅስቀሳ፣ ኮሮጆ በመስረቅና ድምፅ አጭበርብሮ “አሸንፌያለሁ”     በሚል የአምባገነናዊ ንግግር ይደመደማል። በዚህ የተነሳ ለተወሰነ ወራት ወይም ዓመታት “ድምፄን ተነጥቄያለሁ” በሚል ሌላኛው ተፎካካሪ ሃይል ጦርነት ይጀምራል። በዚህ የተነሳ የሚጀመረው ጦርነት ህዝብን ለስደትና ለረሀብ እንዲሁም የአማፅያኑን ጎሳ በማሳደድ ይቀጥላል። በዚህ ሁኔታ አፍሪካ ጥገኛ የሆኑ ደካማ መንግስታትን ተሸክማ አሁንም ድረስ እየተጓዘች ትገኛለች። ለምሳሌ ያህል ደቡብ ሱዳንን፣ ዋናዋ ሱዳንን፣ ሱማሌን ወዘተ የመሳሰሉት ሀገራትን መመልከት በቂ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት የምትደመር እየሆነች መጥታለች፡፡
እናም “ዘመን አንተን ይመስላል” እንዳሉት፣ እውነትም ዘመን መሪውን እንደሚመስል የደቡብ አፍሪካን መሪ ኔልሰን ማንዴላን ለዚህ አባባል መጥቀስ ይቻላል። ዘመን እሱን መስላ አገሩን ለተሻለና ህዝብ ለመረጠው መሪ በማስረከብ ወይም “እኔ እዚህ ጋ በቃኝ ሌላ ሰው ደግሞ ሀገሩን ይምራ” በማለት ሰላምና የተረጋጋ ሀገርና ህዝብ መፍጠር ይቻላል። “ዘመን አንተን ይመስላል” ማለት ይህ ነው  እንግዲህ።
(ከጋሻው ሙሉ “ሹመት እና ቁመት” መፅሐፍ የተቀነጨበ)


Saturday, 29 July 2023 11:26

ከራስህ ጀምር!

 በዌስት ሚኒስትር አቤይ፣ በአንድ የአንጀሊካን ጳጳስ መቃብር ላይ ተከታዮ ሃሳብ ሰፍሯል፡፡ ወጣትና ነፃ ሳለሁ፣ ምናቤ ገደብ አልነበረውም፤ ዓለምን ስለመለወጥም አልም ነበር፡፡ ዕድሜዬ እየገፋና ብልህ እየሆንኩ ስመጣ፣ ዓለም እንደማይለወጥ ተገነዘብኩ፡፡ እናም እይታዬን አጥብቤ፣ አገሬን ብቻ ለመለወጥ ወሰንኩኝ፡፡ እሱም ግን አልሆነም፡፡
የዕድሜዬ ማምሺያ ላይ፣ ሁሉን ትቼ ቤተሰቤን ለመለወጥ ተነሳሁ-የራሴን የቅርብ ሰዎች፡፡  ግን እሱም አልተሳካም፡፡
አሁን የሞት አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ፣ ድንገት እንዲህ ስል አሰብኩ፡- መጀመሪያ ራሴን ለውጬ ቢሆን ኖሮ፣ በእኔ አርአያነት ቤተሰቤን ለመለወጥ እችል ነበር፡፡  ከእነሱ መነቃቃትና መበረታታት ተነስቼ ደግሞ፣ አገሬን መለወጥ እችል ነበር፤ ከዚያም ማን ያውቃል ዓለምን ሳይቀር ልለውጥ እችል ነበር፡፡
(ምንጭ፡- “Chicken soup for the soul” የተሰኘው መፅሃፍ )

ግድግዳን በጀርባ ተደግፎ በዝግታ ቁጢጥ እንደ ማለት 'ስኳት' እና በክርን መሬት ላይ መላ ሰውነትን በመደገፍ የሚሰራው 'ፕላንክ' የተሰኙት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዓይነቶች የደም ግፊትን ለመቀነስ ከሚረዱ መንገዶች መካከል ተመራጭ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ።

ለዘመናት ያህል በዋናነት መራመድ፣ መሮጥ እና ብስክሌት መጋለብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ የተሰጡ ምክሮችም መሻሻል እንዲደረግባቸውም የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎች እየተናገሩ ነው።

የብሪታንያ ‘ጆርናል ኦፍ ስፖርትስ ሜዲሲን’ ይህንን አዲሱን ግኝት ከሰሞኑ አሳትሟል።

በ16 ሺህ ሰዎች ላይ በተደረገው ሙከራ ሁሉም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች የደም ግፊትን እንደሚቀንሱ አመልክተዋል።

ሆኖም በግድግዳ ላይ የሚደረግ ስኳት እና ፕላንክ ከኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን የደም ግፊትን እንደሚቀንሱ ነው መረዳት የተቻለው።

እነዚህ ‘ኢሶሜትሪክ’ ተብለው የሚጠሩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ጡንቻዎችንም ሆነ መገጣጠሚያዎቻቸውን ሳያንቀሳቅሱ የጡንቻን ጥንካሬ የሚገነቡ ናቸው።

ፕላንክ ከፑሽ አፕ ጋር በተወሰነ መልኩ ይመሳሰላል።

ወለሉን በክርንዎት በመደገፍ ሰውነትዎን ቀጥ አድርገው የሚዘረጉበት እንቅስቃሴ ሲሆን የሆድ ጡንቻዎችን ያጠነክራል።የግድግዳ ስኳት ለመሥራት ደግሞ ሰውነትዎን ከጀርባ ግድግዳ ላይ ያስጠጉ።

ከዚያም ከግድግዳው ወለል 60 ሴንቲሜትር ቁጢጥ በማለት ከጀርባዎ ሸርተት ይላሉ። በመጨረሻም መቀመጫዎ ወለሉ ላይ ሳያርፍ ቁጢጥ የሚሉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዓይነት ነው።

ስኳት እና ፕላንክን የመሳሰሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ከኤሮቢክ እንቅስቃሴዎች በተለየ መልኩ በሰውነታቸውን ላይ የሚያሳርፉት የተለየ ጫና (ተጽእኖ) መኖሩንም የጥናቱ ፀሐፊ የካተንርበሪ ክራይስት ቸርች ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ጄሚ ኦድሪስኮል ያስረዳሉ።

“እነዚህን የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እሠሩ ሳያቋርጡ ለሁለት ደቂቃ ያህል የሚቆዩ ከሆነ፣ በጡንቻዎች ውስጥ ያለውን ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምሩታል። ከዚያም ሲዝናኑ በሰውነትዎ ውስጥ ድንገተኛ የደም ዝውውርም ያስከትላል” ይላሉ።

“ይህም በሰውነትዎ ውስጥ ያለውን የደም ዝውውር የሚጨምር ሲሆን፣ ነገር መተንፈስ እንዳለብዎ አይርሱ” ይላሉ።
ስኳት

ከፍተኛ የደም ግፊት በደም ስሮች፣ በልብ እና ሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ጫና በመፍጠር እንደ የልብ ድካም እና ስትሮክ ላሉ የጤና ችግሮች ያጋልጣል።

ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ መድኃኒት ይሰጣቸዋል።

ከዚያም በተጨማሪ በአኗኗር ዘይቤያቸው ላይ ለውጥ በማምጣት ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ፣ የአልኮል መጠጦችን እንዲቀንሱ፣ ማጨስን እንዲያቆሙ እና አዘውትረውም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ግለሰቦች የደም ግፊት ችግር ባይኖርባቸውም በየአምስት ዓመቱ እንዲመረመሩ ይመከራሉ።

በዋነኛው የደም ቧንቧ (አርተሪ) ውስጥ ያለው የደም ግፊት የሚለካው በሚሊሜትር ሜርኩሪ ወይም በምህጻረ ቃሉ ኤኤምኤችጂ በሚባል ነው።

ከ130/85 ሚሊሜትር ኤችጂ በታች ያላቸው ሰዎች ጤናማ ሲሆኑ ከ140/90 ሚሊሜትር ኤችጂ በላይ ደግሞ ከፍ ያለ መሆኑንም ጥናቱ ያሳያል።
ፕላንክ እየሰራች ያለች ግለሰብ የካተንበሪ ክራይስ ቸርች ዩኒቨርስቲ እና የሌስተር ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ለሁለት ሳምንታት ያህል እና ከዚያ በላይ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የቆዩ 15 ሺህ 827 ሰዎችን መረጃ አጥንተዋል።

እንዲሁም ከጎሮጎሳውያኑ 1990 እስከ 2023 ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተደረገባቸው 270 የክሊኒክ ሙከራዎችን መርምረዋል።

ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በኋላ ባለው የእረፍት ጊዜ ያለው የደም ግፊት በምን ያህል እንደቀነሰም ግኝታቸውን ይፋ አድርገዋል።

    4.49/2.53 ሚሊሜትር ኤችጂ እንደ ሩጫ ወይም ብስክሌት መንዳት ካሉ የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በኋላ መቀነስ አሳይቷል።
    4.55/3.04 ሚሊሜትር ኤችጂ ደግሞ እንደ ክብደት ማንሳት ባሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በሠሩ ሰዎች ላይ መቀነስ ታይቷል ።
    6.04/2.54 ሚሊሜትር ኤችጂ መጠን መቀነስ የኤሮቢክስ እና የክብደት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ባጣመሩ ላይ መታየቱም ሰፍሯል።
    4.08/2.50 ሚሊሜትር ኤችጂ መጠን መቀነስ ደግሞ ያሳየው ፈጣን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና አጫጭር እረፍቶችን ባጣመረው ‘ሃይ ኢንተንሲቲ ኢንተርቫል’ በተሰኘው እንቅስቃሴ ነው።
    ከፍተኛው 8.24/4 ሚሊሜትር ኤችጂ መጠን መቀነስ የተመዘገበው አይሶሜትሪክ በተሰኙት በጡንቻ በሚሠሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ማለትም እንደ የግድግዳ ስኳት እና ፕላንክ በሰሩ ሰዎች ላይ ነው።

ምንም እንኳን እነዚህ በአንጻራዊነት የቀነሱበት መጠን አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ኦድሪስኮል፣ ሆኖም የአንድን ሰው ለስትሮክ ተጋላጭነት እንደሚቀንሱም ያስረዳሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና መመሪያ አዋቂዎች በሳምንት ለ150 ደቂቃ ያህል መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ወይም 75 ደቂቃ ከበድ ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ጡንቻን የሚያጠናክሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲሰሩ ይመክራል።

በተጨማሪም ለሁለት ደቂቃ ያህል የግድግዳ ስኳት ወይም ሁለት ደቂቃ በየመሃሉ በማረፍ አራት ጊዜ ፕላንክ በሳምንት ሦስት ጊዜ እንዲሰሩ ዶ/ር ኦድሪስኮል ይመክራሉ።

የብሪታንያ የልብ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ለልብ ጤና ጥሩ እንደሆኑ እና የልብ እና የደም ዝውውር በሽታዎችን እስከ 35 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችልም ይናገራል።

“የሚያስደስቷቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ ስፖርት በመሥራት ስለሚቀጥሉ የደም ግፊትን አመጣጥኖ ለመቀጠል ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ሲሉም የፋውንዴሽኑ የልብ ህመም ከፍተኛ ነርስ የሆኑት ጆአን ዊትሞር ያስረዳሉ።

በተጨማሪም እንደ ጨው መቀነስ፣ ጤናማ ክብደትን መጠበቅ እና የታዘዘን መድኃኒት ሳያስተጓጉሉ መውሰድ የመሳሰሉ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ነርሷ ይናገራሉ።

የደም ግፊታቸው መጠን የሚያስጨንቃቸው ሰዎችም የጤና ባለሙያዎችን በማማከር ለእራሳቸው እና ለሁኔታዎች ተስማሚ የሆነውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አይነትን በተመለከተ ምክር እንዲጠይቁም ምክራቸውን ለግሰዋል።

•  የኮሎኔሉ ታሪክ - ከመጽሐፍ አዟሪነት እስከ  የጦር አዛዥነት

ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን አንስቶ በአራት መንግሥታት ውስጥ ያለፉትና ከመጻህፍት አዟሪነት እስከ ከፍተኛ የጦር አዛዥነት የደረሱት ኮሎኔል ፈቃደ ገብረየሱስ የጻፉት “የኔ መንገድ“ የተሰኘ ግለ-ታሪክ (ኦቶባዮግራፊ)፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በግዮን ሆቴል ግሮቭ ጋርደን ተመርቋል፡፡


በ653 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ የተመረቀው፣ የኮሎኔሉ የቀድሞ አለቆችና የደርግ ዘመን ከፍተኛ የጦር አዛዦች፣ ቤተሰቦችና ወዳጆች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች በታደሙበት ደማቅ  ሥነስርዓት ነው፡፡


የመጽሐፍ አዟሪነት ዘመናቸውን በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ ያወሱት ኮሎኔል ፈቃደ፤ “እኔ መጽሐፍ ስነግድ እነሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስን፣ አቤ ጉበኛን፣ ክቡር ደራሲ ሚካኤል ከበደን በአካል አውቃቸው ነበር፡፡” ብለዋል፡፡

ከአጼ ኃይለሥላሴ ጋር ድንገት መንገድ ላይ ተገናኝተውም መጽሐፍ እንደሸጡላቸው ደራሲው በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ አስታውሰዋል፡፡

“የኔ መንገድ“ የተሰኘውን የኮሎኔል ፈቃደ ገብረየስ ግለታሪክ መጽሐፍ፣ የአርትኦት ሥራ ያከናወኑት ታዋቂው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላና ጸሃፊና የሥነጽሁፍ ባለሙያ የሆነው ባዩልኝ አያሌው ሲሆኑ፤ ሁለቱም ስለመጽሐፉ አጫጭር ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል - በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ፡፡

የኮሎኔል ፈቃደ የቀድሞ አለቃ የነበሩትና የደርግ ዘመን ከፍተኛ የጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ ጨመዳና ሌሎችም በመድረኩ ላይ ስለ ባለታሪኩ የሚያውቁትን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡


ኮሎኔል ፈቃደ ከዚህ ቀደም አራት ያህል መጻሕፍት ለንባብ አብቅተዋል፡፡  አምስተኛውንና አዲሱን  “የኔ መንገድ“ የተሰኘ ግለታሪክ ለምንና እንዴት እንደጻፉት በመጽሐፉ መግቢያው ላይ እንዲህ ያስረዳሉ፡-

“አንዳንድ ወዳጆቼ “ለምን የህይወት ታሪክህን አትጽፍም?“ ሲሉኝ፣ “እኔ ምን ታሪክ አለኝ?“ እያልኩ ነገሩን ጉዳዬም ሳልለው ቆየሁ፡፡ አንድ ቀን ጠዋት አንደኛው ልጄ ብስራት ፈቃደ በጨዋታ መሃል ድንገት “ጋሼ የህይወት ታሪክህን ግን ለምን አትጽፍም? በሕይወት እያሉ እኮ ታሪካቸውን የሚጽፉ ጥቂቶችና የታደሉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ እኮ ልጆቻቸው ናቸው የሚጽፉላቸው“ አለኝ፡፡ እኔም “ምን ታሪክ አለኝና እጽፋለሁ? ልጻፍ ብልስ አስር ገጽስ መጻፍ እችላለሁ እንዴ?“ ብዬ መለስኩለት፡፡ “ግለ ታሪክህን ስትጽፍ እኮ ያንተን ታሪክ ብቻ አይደለም የምትጽፈው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘሃቸውን ሰዎችንና ድርጊቶች እንዲሁም ገጠመኞች ጭምር እንጂ፡፡  አንተ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ስታጫውተን ልብ እንዳልኩት ብዙ ህይወት አሳልፈሃል፡፡ በዚህ ሂደትም ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝተሃል፡፡ የሚገራርሙ ገጠመኞችም አሉህ፡፡ ብዙ ሰውም የሚጽፈው  እኮ ይህንኑ ነው፡፡ ለማሳተም እንኳን ብትቸገር አዘጋጅቶ ማስቀመጡ አንድ ነገር ነው፡፡“ ብሎ የምመልሰውን ለመስማት በአንክሮ ተመለከተኝ፡፡ የምመልሰው ባጣ “እስቲ ላስብበት“ ብዬው ጨዋታችንን ቋጨን፡፡--” በዚህ መንገድ ነው በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቃው መጽሐፍ የተወለደው፡፡

የራሳቸውን ታሪክና ከህይወታቸው ጋር የተገናኙ የሌሎች ሰዎችን እንዲሁም ገጠመኞችን ታሪኮች ያካተቱበትን ይህን መጽሐፍ ለምን “የኔ መንገድ“ እንዳሉት ሲገልጹም፤

 “--ሁሉም ሰው የራሱ የተለየ ታሪክ አለው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የተጓዘበት የህይወት ልምዱ የአንዱ ከሌላው ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ልክ እንደ እጃችን አሻራ ያንዱ ከሌላው ጋር በምንም አይመሳሰልም፡፡ አሁን ላይ የዕድሜዬ ቆጣሪው 69ኛው ዓመት ላይ ያሳያል፡፡ በዚህ ረጅም ዓመታት እኔ የተጓዝኩበትና የመጣሁበት መንገድ፣ የኖርኩበትና ያለፍኩበትም የህይወት ልምድ እንዲሁ ከሌላው የተለየ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመጽሐፌን ርዕስ ”የኔ መንገድ” በማለት የሰየምኩት፡፡--” ብለዋል፡፡

ከመጽሐፉ አርታኢዎች አንዱ የሆነውና የቀድሞው የአዲስ አድማስ የረዥም ጊዜ ጸሐፊ በምረቃው ሥነስርዓት ላይ በሰጠው ሙያዊ አስተያየት፣ የምዕራፎቹ ስያሜዎች ጠሪ ናቸው ብሏል፡፡ ጥቂቶቹን ለማሳያ ያህል፡- “ከኢህአፓ ጋር መርካቶ ተዋወቅን“፣ “ባድመ ግንባር ላይ ያገኘሁት ጎረቤቴ“፣ “አይ ጨበራ ጩርጩራ ፓርክ“፣ “የሞስኮ ጎረምሶች አንቆራጠጡን“፣ “የባዳ ዘመዳችን - መወለድ ቋንቋ ነው“፣ “አባባ ጃንሆይን መንገድ ላይ አገኘኋቸው”፣ “የተነፋው ጎማ ተነፈሰ” ወዘተ ይገኙባቸዋል፡፡ አርታኢው እውነት ብሏል፤ጠሪ ናቸው፡፡

“የኔ መንገድ“ ግለታሪክ መጽሐፍ ለአገር ውስጥ በ600 ብር፣ ለውጭ አገራት በ25 ዶላር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

ዘገባዬን ደራሲው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ በተጠቀሙበት የሲ.ሲ. ኮልተን አባባል ልቋጭ፡፡ እንዲህ ይላል፡-

 “ደራሲ መሆን ሦስት ችግሮች አሉት፡፡ ለህትመት የሚመጥን ጽሁፍ መጻፍ ፤የሚያሳትሙ ቅን ሰዎች መፈለግ፤ የሚያነቡትን አስተዋይ ሰዎች ማግኘት፡፡”

   አምስት ዓመት እጅግ ርቆብን… “ጥንት ዘመን” የሚሆንብን ለምንድነው? ወሬ በዛ። የሚታይ ነገር በዛ። ስንቱን አስታውሰን እንችለዋለን? አምስት ዓመት “የጥንት ታሪክ” ከሆነብን፣ 2ሺ ዓመት ምን ልንለው ነው?
ያኔም እስር ቤቶች ነበሩ። እስረኞችን መጠየቅና በምህረት መልቀቅም፣… ያኔ በጥንት ዘመን ነበር። ንጉሦችና ባለስልጣናት ያስራሉ፤ ምህረት ይሰጣሉ። ሕዝብ ለእስረኞች ምህረት የመስጠት ስልጣን ሲያገኝ ደግሞ አስቡት።
በእርግጥ፣ የሕዝብ ምህረት በነጻ አይገኝም። ሕዝብን ማስደሰትና ተወዳጅነትን ማትረፍ የቻለ እስረኛ ግን ምህረት ይደረግለታል። ከእስር ቤት ይወጣል።
የጥንት ዘመን እስረኞች በጣም እድለኞች ናቸው? ሕዝብ አይረሳቸውም?
ይረሳቸዋል። አንዳንዴ ግን ያስጠራቸዋል።
ወደ ስታዲዮም ይጋብዛቸዋል።
በግጥሚያ ትዕይንት እንዲሳተፉ ይፈቅድላቸዋል።
ብቃታቸውን በአደባባይ እንዲያሳዩ ሜዳውን ይሰጣቸዋል።
ትጥቅ ያሟላላቸዋል።
ስታዲዮሙ ከአፍ እስከ ገደፉ በተመልካች ሕዝብ ይጥለቀለቃል። ግጥሚያ ለማየት፣ አሸናፊዎችን ለማድነቅ እና  ለጀግኖች ምህረት ለመስጠት ነው የሕዝቡ ፍላጎት።
በእርግጥ፣ የግጥሚያ ወይም የፍልሚያ ትዕይንት ማለት፣… በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አይደለም።
ከ1500 ዓመት በፊት ነው ዘመኑ። የግሪክ የስፖርት ውድድሮች በሮም ዘመነ መንግሥት ወደ ውጊያ ተለውጠዋል። ጨዋታ ቀርቷል።
 ግጥሚያ ግጥሚያ ነው። ፍልሚያ ከምር ፍልሚያ ነው። የፍልሚያ ጨዋታ አይደለም። ሶስት ነጥብ ለማስመዝገብ የሚካሄድ ኳስ መጫወት አይደለም-ያኔው የጥንቱ ፍልሚያ። የዛሬማ ቀልድ ነው።
ኳስን መምታትና ማከባለል ይቻላል። ተጋጣሚን መጎሸም ግን አይቻልም። መግጨት ይቅርና ልብስ መጎተት ክልክል ነው። አሸናፊዎቹም ተሸናፊዎቹም አንዳች ጭረት ሳይነካቸው ጨዋታቸውን ጨርሰው ለደርሶ መልስ ይዘጋጃሉ። የሳምንት ደሞዛቸውን እየተቀበሉ።
የጥንቱ ስታዲዬም ለጨዋታ የተገነባ አይደለም።
የጥንቱ ግጥሚያ የምር ውጊያ ነው።
በጦር በጎራዴ፣ በመዶሻና በመፍለጫ የሞት ሽረት ነው ፍልሚያው።
የእስር ቅጣቴን ለመጨረስ ግማሽ ዓመት ብቻ ነው የቀረኝ፤ ፍልሚያና ምህረት ይቅርብኝ የሚል ሰው ይኖራል።
ነገር ግን ምህረት ለማግኘት የሞት ሽረቱን እንዲፋለም ህዝብ ከወሰነ የግድ ወደግጥሚያው ይገባል። ህዝብ ከወደደውና ከፈለገው ማምለጫ የለውም።
እስረኞቹ፣… አንዳንዶቹ ጨካኝ ወንበዴዎች፣ አንዳንዶቹ ጊዜ የከዳቸው ባለስልጣናት፣ ገሚሶቹ የከተማ ወረበሎች፣ ገሚሶቹ ከባለስልጣን ጋር ተጣልተው የታሰሩ ምስኪኖች ቢሆኑም፣ በፍልሚያው ሜዳ ላይ ግን ሁሉም ያው ተጋጣሚዎች ናቸው።
ጥሎ የማለፍ ገድሎ የመዳን ነው ፍልሚያው።
ተጋጥሞ ያሸነፈ በህይወት ይተርፋል፤ በምህረት ከእስር ይለቀቃል። ህዝብ ከወደደ ምን ይሳነዋል? ሕዝብ ከእስር የፈታው ሰው ንጉሥ አያስረውም።
ሕዝብ አብዝቶ የወደደ እንደሆነ ነው ችግሩ። ከሌሎች ተጋጣሚዎች ሁሉ እጅግ የላቀ ጀግና፣ በአንድ ጊዜ ከንጉስ የበለጠ ዝነኛ ይሆናል።
ህዝቡ ያብድለታል።
ከዓይናቸው እንዳይርቅ ይሳሱለታል።
ይደገም ይደገም ብለው ይዘምሩለታል።
ሌሎች እስረኞች ወደ ግጥሚያ ሜዳ ሲገቡ፣ ተወዳጁ እስረኛ አሁንም ይፋለማል። ካሸነፈ፣ ተወዳጅነቱ ይጨምራል።
አሁንም ይደገም፤ ከነብር ከአንበሳ ጋር ይጋጠም፤ ይደገም…ይላል ህዝቡ። አይጣል ነው። እጅግ የተወደደ እስረኛ፣ ከፍልሚያ ሜዳ በህይወት የመውጣት እድል የለውም።

   የአንድ ቅኔ ት/ቤት ተማሪዎች ቅኔ የሚዘርፉበት ዕለት ነው፡፡ ከየደብሩ፣ ከየቅኔ ት/ቤቱ ሁሉ አንቱ የተባሉ ሊቆች ተጠርተው መጥተዋል፡፡ ተማሪዎች ምን ያህል እንደተማሩና እንደረቀቁ ለማዳመጥና ለመመዘን፣ እግረ-መንገዳቸውንም የእነሱ ዘመነኛ የሆኑት የቅኔ መምህር ምን ያህል እንዳስተማሩ በማየት ከራሳቸው ጋር ሊያነፃፅሩ ነው፡፡ በተማሪዎቹ መካከል ፉክክር እንዳለ ሁሉ በመምህራኑም መካከል የእኔ እሻል እኔ እሻል ውድድር አለ፡፡ በጥንቱ የቅኔ ትምህርት ይትባህል አለቃ እገሌ ዘንድ የተማረ፣ መምህር እገሌ ዘንድ ቅኔ የዘረፈ መባል ብዙ ስምና ክብር አለው፡፡ (በዘመናችን ሲታሰብ ዶክተር እከሌ የተባለ፣ ፕሮፌሰር ጋር ነው ያጠናሁት እንደማለት ነው፡፡ ወይም ዛሬ “የዚህ School of thought “ ተከታይ ነኝ እንደሚባለው፣ “የዚህ ደብር ተከታይ ነኝ” እንደማለትም ይሆናል)
ከተማሪዎቹ መካከል አንድ ኃይለኛ ተማሪ አለ፡፡ መምህሩ ሳይቀሩ ይፈሩታል፡፡ ታዲያ የዚያን ዕለት መምህሩ በበኩላቸው፣ ችሎታቸውን ለማሳየት ያህል ቅኔውን ሲዘርፉት፣ አንድ ላላ ተደርጎ ሳይረገጥ መነበብ ያለበት “ታምሪሃ” (የተዓምር ድርጊት) የሚል ቃል፣ የኔታ እርግጥ አድርገው ‘ታምሪሃ!’ ብለው ያነባሉ፡፡ ይሄኔ ያ ጎበዝ ተማሪ “የኔታ ልመልስዎት” ይላቸዋል፡፡ የኔታ አፍረውም ተናደውም ቢሆን፣ ምሬታቸውን ዋጥ አድርገው ሲያበቁ፣ “እሺ የእኔ ልጅ፤ መልሰኝ” አሉ፡፡ “‘ታምሪሃ’ አይጠብቅም ያላሉት” ይላቸዋል፡፡ የኔታም አላልተው በድጋሚ ይወርዱታል፡፡
በነዚያ ሁሉ ታዋቂ መምህራን ፊት ተማሪያቸው ስህተት ስላገኘባቸው በጣም ተናደዋል፡፡ ስነሥርዓቱ ሁሉ አለቀና እንግዶቹ ሁሉ ተሸኙ፡፡
የየኔታ ቤት አፋፍ ላይ ነው፡፡ የጎበዙ ተማሪ ቤት ታች ሜዳው ላይ ነው፡፡ ለተማሪው የየኔታ ቤት ቁልጭ ብሎ ካፋፍ ይታየዋል፡፡ የኔታ ጠዋት ማለዳ ተነስተው እደጃቸው ካለው የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጠው አርጩሜ መልምለው፣ በጋቢያቸው ሸፍነው ይዘው ቁልቁል ሲወርዱ ተሜ ያስተውላቸዋል፡፡
ት/ቤት እንደተለመደው የኔታ ተማሪዎቹ ቅኔ እንዲዘርፉ ሲመሩ፤ ሳያውቁ ያሉት አስመስለው የትላንትናውን “ታምሪሃ” የሚል ስህተት በመድገም ረግጠው አነበነቡት፡፡ ተሜ ግን እንደ ትላንቱ “ልመልስዎት” ሳይላቸው ጭጭ አለ፡፡ የኔታ ትንሽ እንደመናደድ ብለው አሁንም ያችን “ታምሪሃ” ረገጥ አድርገው ተናገሯት፡፡ ተሜ አሁንም ጭጭ! የኔታ በጣም ተናደዱና ጮክ ብለውና በጣም ረግጠው “ኧረ ታምሪሃ”! አሉ፡፡ ተሜ አቀርቅሮ እረጭ፡፡ የኔታ ትዕግሥታቸውን ጨርሰው፤
“አንተ፤ አትመልሰኝም እንዴ?” ሲሉ ጠየቁት በኃይለ-ቃል፡፡
ተማሪው ሲመልስ፤
“አይ የኔታ፤ ይቺ እንኳ ውስጠ-ወይራ ናት!” አላቸው፡፡
ውስጠ-ወይራ ታሪካዊ አመጣጧ ይሄ ነው፡፡
***
በረዥም ጊዜ ታሪካችን ውስጥ በሀገራችን የሚካሄድ ብዙ ውስጠ-ወይራ ነገር አለ፡፡ ስህተት የሚሰራ ሞልቷል፡፡ ስህተት እያየ ውስጠ-ወይራ ናት ብሎ ጭጭ የሚልም አንድ አገር ነው፡፡ የትላንቱን ቂም ለመወጣት እንደየኔታ አውቀው ተሳስተው “አትመልሰኝም ወይ?” የሚሉም አያሌ ናቸው፡፡ በስህተት ከማፈርና መናደድ፤ ብሎም ለአርጩሜ ከመዘጋጀት ይልቅ፣ ስህተትን ለማረም ዝግጁ መሆን ቢችሉ፣ አገራችን ከስንት ህመም በዳነች ነበር፡፡ ይህ ድክመት በሁሉም የህይወት መስክ ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ በተለይ ግን በፖለቲካው መድረክ ላይ ተሰማርተው የተንቀሳቀሱም ሆኑ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ለአካለ- ትግል ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የሚታይባቸው መሰረታዊ የድክመት ጠባይ አለ፡- ፖለቲካዊ ሸፍጥ፣ ስቶ ማሳሳት (Disinformation)፣ አድርባይነት፣ አስመሳይነት (Hypocracy)፣ ባዶ ሜዳ ዛቻ፣ ዕብጠት፣ ፖለቲካዊ አክራሪነት፣ መቻቻልን ከሽንፈት መቁጠር፣ እኔ የሌለሁበት ማሕበር ጥንቅር ብሎ ይቅር ማለት፣ ማጋለጥ፣ ማጋፈጥ፣ ለጠላት አሳብቆ ማስመታት፣ ታክቲካል ግንኙነትንና ጡት-መጣባትን አለመለየት፣ ህጋዊ ትግል፣ ዲፕሎማሲንና ህቡዕ ትግልን (Clandestine struggle) ወይ አጥርቶ አለማወቅ፣ አሊያም አንዱን ከአንዱ ጋር ማምታታት፣ እርስ በርስ  እየተሻኮቱ አገርንና ህዝብን እርግፍ አድርጎ መርሳት፣ መሸመቅ፣ ያታግላል በሚል ምክንያት ብቻ አዲስ መፈክር ማውጣት ወዘተ…
እንግዲህ ከነዚህ በአንዱ፣ በጥቂቱ ወይም በሁሉም የተነሳ እስካሁን የሚታየው የትግል ስልት ሁሉ ውስጠ-ወይራ አለበት፡፡ “ጠጅ የለመደች ገንቦ፣ ያለ ጠላ አታድርም” እንዲሉ መልኩ ይለዋወጥ እንጂ በውስጠ-ወይራ የማያምን ፓርቲ፣ ማህበር፣ ድርጅት፣ መሪ፣ ካድሬ፣ ታጋይ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ እርግጥ መጠቅለያው ይለያያል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በማህበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ “ውስጠ-ወይራ” እንደማይጠፋ ሁሉ በየፓርቲው ፕሮግራም፣ በየቡድኑ ታክቲክና ስትራቴጂ፣ በየስምምነት ፊርማው፣ በየጋራ ግንባር ውይይት ውስጥ ሁሉ በገዛ ወገን ላይ ሳይቀር “ውስጠ-ወይራ” አለች፡፡
ብዙ ህይወት የጠፋባቸው፣ ብዙ ቁርሾ የተፈራባቸው፣ ለዘመናት የማይሽሩ የሚባሉ ቁስሎች የተፈጠሩባቸው፤ አመታትን አይተናል፡፡ በነዚህ ውስጥ “ከሰራነው ስህተት እራሳችንን ለማረም የቻልን ስንቶች ነን?” ብሎ የጠየቀ ሰው የሚያገኘው መልስ ግን  እጅግ መንማና ቁጥር ነው፡፡ ወደ አለፉት ስህተቶቻችን መለስ ብለን እንድናይ የሚያግዘን አንድ ፍቱን መሳሪያ አለ፡፡ ታሪክን በፅሁፍ ማስቀመጥ፡፡ ትንሽም ይሁን ትልቅ ታሪክ ፅፎ ማስቀመጥ፡፡ ሁሉ በሚዋሃድበት ጊዜ የሚጣረሰው ተዋዶ፣ የተሳሳተው ታርሞ አንድ ቀን ሙሉ ታሪካችን አደባባይ ይወጣል፡፡
ቶማስ ኤዲሰን “ከሰራኋቸው ኤክስፔሪመንቶች ሁሉ ውጤት አግኝቻለሁ! ሁሉም ስህተት ናቸው፡፡ ይህ ግን ትልቅ ድል ነው፡፡ እስካሁን ድረስ እንኳን 138 እኔ ባሰብኩት መንገድ የማይሰሩ መንገዶች መኖራቸውን ተምሬአለሁ፡፡” ይለናል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ድክመቶች እስካሉ ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን እጣ-ፈንታ ከወዲሁ መናገር የሚያዳግት አይሆንም፡፡ ጊዜያዊ  አሸናፊ ብቅ ይላል፡፡ ይኸው አሸናፊ አንድ ሰሞን ያለፈውን ሲረግም፣ አንድ ሰሞን መጪውን እቅዱን ሲያስተዋውቅ ይከርማል፡፡ ከዚያ “ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፣ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ” እንደተባለው ተረት ይሆናል ነገሩ ሁሉ፡፡ ከዚያ ስለእኔ ተሰብሰቡ፣ “በእኔ እመኑ” “እኔ ቀናዒ” (እኔ ቀናተኛ አምላክ ነኝ) እያለ ሰውን ሲያፈጋ ይቆያል፡፡ ሰነባብቶ የአሸናፊነት ሰንጠረዥ ላይ ያለው ጠቋሚ-መስመር እንደገና ማሽቆልቆል ይጀምራል፡፡ ሌላው ባለ ጊዜ ደግሞ ለሌላ ጊዜያዊ አሸናፊነት፣ ያንኑ ማንነቱን፣ ያንኑ ውስጠ-ወይራውን እንደያዘ መድረኩ ላይ ብቅ ይላል፡፡ ቀለበታዊ ሂደቱ ይቀጥላል፡፡ “እራሱን የማይገዛ፣ አገር አይገዛ” የሚባለው ተረት የዋዛ አይደለም፡፡ እራስን መመርመር፣ ማረም፣ ስህተትን መቀበል፣ መሳሳትን በሰው ፊት ማመን፣ በጋቢው የተሸሸገውን ወይራ ለመስበርም ሆነ፣ ወደፊትም ከነጭራሹ ከዛፉ ተቆርጦ እንዳይመለመል ለማድረግ፣ ወሳኙ እርምጃ ነው፡፡ አለበለዚያ “ከእትብት ጋር የወጣ አመል፤ ከከፈን ጋር ይቀበራል” ማለት ብቻ ይሆናል ቋንቋችን፡፡

Page 10 of 665