Administrator

Administrator

Monday, 02 March 2015 10:03

የስኬት ጥግ

ዕድል ከሰማይ እንደ መና አይወርድም፡፡ አንተ ትፈጥረዋለህ እንጂ፡፡
ክሪስ ግሮሰሪ
በየቀኑ አንድ የሚያስፈራህን ነገር አከናውን፡
ያልታወቀ ሰው
ሁሉም ዕድገቶች እውን የሚሆኑት ከምቾት ቀጠና ውጭ ነው፡፡
ማይክል ጆን ቦባክ
ነጋችንን እውን እንዳናደርግ የሚገድበን ብቸኛው ነገር ዛሬአችን ላይ ያለን ጥርጣሬ ነው፡፡
ፍራንክሊን ዲ.ሩዥቤልት
የስኬት ምስጢር የለውም፡፡ የዝግጅት፣ ተግቶ የመስራትና ከውድቀት የመማር ውጤት ነው፡፡
ኮሊን ፖል
የስኬትን ቀመር ልሰጥህ አልችልም፡፡ የውድቀትን ቀመር ልሰጥህ ግን እችላለሁ፡- ሁሉን ሰው ለማስደሰት መሞከር ነው፡፡
ኸርበርት ባያርድ ሰዎኝ
ሰባት ጊዜ ወድቀህ በስምንተኛው ቁም፡፡
የጃፓኖች አባባል
ማለም ከቻልክ ታደርገዋለህ፡፡
ዋልት ዲዝኒ
ስኬታማ ለመሆን የስኬት ፍላጎትህ ከውድቀት ፍርሃትህ መብለጥ አለበት፡፡
ቢል ኪዝቢ
የስኬት ምስጢር ማንም የማያውቀውን አንድ ነገር ማወቅ ነው፡፡
አሪስቶትል አናሲስ
“አይሆንም” ያሉኝን ሰዎች አመሰግናቸዋለሁ። በእነሱ የተነሳ ነው ራሴ የገባሁበት፡፡
አልበርት አንስታይን
ህልሞችህን አንፅ፤ ያለዚያ ተቀጥረህ የሌሎችን ህልም ታንፃለህ፡፡
ፍራህ ግሬይ
የስኬት ጎዳና እና የውድቀት ጎዳና ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ኮሉን አር.ዴቪስ

Monday, 02 March 2015 09:30

የጀግንነት ጥግ

ድልን ጠብቅ፤ ድልም ታደርጋለህ፡፡
ፕሪስተን ብራድሊ
(አሜሪካዊ ቄስ)
አሸንፋለሁ ብለህ ካሰብክ ታሸንፋለህ፡፡ ድል ለማድረግ እምነት ወሳኝ ነው፡፡
ዊሊያም ሃዝሊት
(እንግሊዛዊ ወግ ፀሐፊና ሃያሲ)
በምርጫው ለተሸነፉት ሁሉ አዝናለሁ፡፡ ይሄ እኔ የማውቀው ተመክሮ አይደለም፡፡
ማርጋሬት ታቸር
(የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር)
 ድል ሺ አባቶች አሉት፤ ሽንፈት ግን ወላጅ አልባ ምስኪን ነው፡፡
ጆን ፊትዝገራልድ ኬኔዲ
(የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
የሰው ልጅ ትልቁ ድል ራሱን ድል ማድረግ ነው፡፡
ጆሃን ሔይንሪክ ፔስታሎዚ
ተመልከቱ፤ ድል አድራጊው ጀግና መጣ!
       ጡሩንባው ይነፋ፤ ከበሮው ይመታ!
ቶማስ ሞሬል
(እንግሊዛዊ የመደብ ልዩነት አቀንቃኝ)
መደበኛ ጦር ካላሸነፈ ይሸነፋል፡፡ ሽምቅ ተዋጊ ካልተሸነፈ ያሸንፋል፡፡
ሔነሪ ኪሲንጀር
(አሜሪካዊ ፖለቲከኛና ዲፕሎማት)
ሽንፈትን መቀበል የሚችል አንጀት ካለህ አታሸንፍም፡፡
ቪንስ ሎምባርዲ
(አሜሪካዊ የእግር ኳስ አሰልጣኝ)
አስቤው የሆነ አይደለም፡፡ ጀልባዬን አስጠሙብኝ፡፡
ጆን ፊትዝገራልድ ኬኒዲ
(እንዴት ጀግና ሊሆን እንደበቃ ሲጠየቅ የመለሰው)
ዓለም በደስታ ብቻ የተሞላች ብትሆን ኖሮ ጀግንነትንና ትዕግስተኛነትን አንማርም ነበር፡፡
ሔለን ከለር
(አሜሪካዊ ፀሐፊና መምህር)
ድፍረት የተስፋ ፍሬ ነው፡፡
የፊሊፒኖች አባባል
ለሰው ልጅ አንዳች ድል እስክታመጣ ድረስ ሞትን ተጠየፍ፡፡
ሆራስ ማን
(አሜሪካዊ የትምህርት ባለሙያ)

Monday, 02 March 2015 09:23

የፀሃፍት ጥግ

ኃይለኛ መፅሃፍ ለመፃፍ ኃይለኛ ጭብጥ መምረጥ አለብህ፡፡
ሔርማን ማልቪሌ
ግሩም አድርገህ እስካረምከውና እስካሻሻልከው ድረስ ትርክምርኪ ብትፅፍ ችግር የለውም፡፡
ሲ.ጄ.ቼሪ
ታሪኩ ረዥም መሆን ስላለበት አይደለም፡፡ አጭር ለማድረግ ረዥም ጊዜ ስለሚወስድ ነው፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶርዩ
በህይወትህ ውስጥ ሌሎች ነገሮች ካሉህ - ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ ውጤታማ የሥራ ቀን - እኒህ ሁሉ ከምትፅፈው ጋር መስተጋብር በመፍጠር ድምር ውጤቱ እጅግ የበለፀገ ይሆናል፡፡
ዴቪድ ብሪን
በእኔ ልምድ እንዳየሁት፣ ታሪኩን አንዴ ከፃፉ በኋላ መግቢያውንና መጨረሻውን ሰርዞ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ እኛ ደራሲያን አብዛኞቹን ውሸቶችቻችንን የምንጨምረው መግቢያውና መዝጊያው ላይ ነው፡፡
አንቶን ቼኾቭ
እስካሁን ስኬታማ የሆንኩት ምናልባት ሁልጊዜም ስለድርሰት አፃፃፍ ምንም እንደማላውቅ በመገንዘቤና ማራኪ ታሪክን በሚያዝናና መንገድ ለመተረክ በመሞከሬ ብቻ ነው፡፡
ኢድጋር ራይስ ቡሮውስ
መጀመሪያ መሪ ገፀባሪህ ምን እንደሚፈልግ እወቅ፤ ከዚያ ዝም ብለህ እሱን ተከተለው!
ሬይ ብራድበሪ
ፀሐፊ የሚሰራበት አብዛኛው መሰረታዊ ጥሬ ነገር የሚገኘው ከ15 ዓመት ዕድሜ በፊት ነው፡፡
ዊላ ካተር
አዝናለሁ፤ የሳይንስ ልብወለድ ፀሃፊዎች ከምር ምንም ነገር አያውቁም፡፡
ፊሊፕ ኬ.ዲክ
በግጥም ውስጥ ገንዘብ የለም፤ በገንዘብም ውስጥ ግን ግጥም የለም፡፡
ሮበርት ግሬቭስ
ሰዎች ጥሩ ፅሁፍ ማግኘት አይገባቸውም፤ በመጥፎው ሲበዛ ደስተኞች ናቸው፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
ለዓመታት ምንም ሥራ ሳልጨርስ ነው የቆየሁት፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ጨርሰህ ስታወጣ ትችት አይቀርልህም፡፡
ኢሪካ ጆንግ
ሌሎች ካንተ መስማት ስለሚፈልጉት ነገር ለማሰብ አትሞክር፤ አንተ ማለት ስላለብህ ጉዳይ ብቻ አስብ፡፡ እሱ ነው አንተ መስጠት ያለብህ አንድና ብቸኛ ነገር፡፡
ባርባራ ኪንግሶልቨር

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በጣም ጨካኝ ሹም ነበረ ይባላል፡፡ ይሄው ሹም በትንሽ በትልቁ ይቆጣል፡፡ ይገርፋል፡፡ ያስገርፋል፡፡ ሲያሻውም ይገድላል፡፡ አገር ይፈራዋል፡፡ ሰው ሲሽቆጠቆጥለት የማየትን ያህል የሚያስደስተው ነገር የለም፡፡
ወደ ቤቱ እንኳ በጊዜ ገብቶ ሚስቱ፤
“ዛሬ እንዴት ዋልክ?” ስትለው፤
“አንቺ ምን አለብሽ ሰው አትገርፊ፣
አታስገርፊ፣ አትገይ አታስገድይ
ቤትሽ ተኝተሽ ትበያለሽ፤ እኔ ላቤን አፍስሼ ያመጣሁትን ትቦጠቡጫለሽ!” ይላታል፡፡
“በነገራችን ላይ የአቶ እገሌ ልጅ ታሠረ ሲሉ ሰማሁ፡፡ አውቀሃል?”
“አዎን አውቄያለሁ፡፡ እኔ ሳላውቅ የሚሆን ነገር የለም አላልኩሽም?”
“ውይ ትንሽ ልጅ እኮ ነው፡፡ 15 ነው 16 ዓመቱ!”
“አዎ! እሥር ቤት እንዲቆይ ወሰንን”
“ምን ብላችሁ ወሰናችሁ?”
“ለአቅመ አዳም እስኪደርስ ይቀመጥና ሲያድግ እንገርፈዋለን ብለን ወስነናል”
“ውይ እንዴት ክፉ ናችሁ! አሁን ከእናንተና ከልጁ ማ ቀድሞ እንደሚሞት በምን ይታወቅና ነው እንዲህ የምትጨክኑት?”
“ስለ ነገ አርቀሽ ካላሰብሽ ምን ሠርተሽ ትኖሪያለሽ? ጠዋት የሆነውን ሳልነግርሽ? አንድ የህግ ት/ቤት ሄጄ ህግ መማር እፈልጋለሁ ብላቸው፤ ዲሬክተሩ አይቻልም!” አሉኝ
“ለምን አሉ?”
“አንተማ ፈርደህ ጨርሰሃል!” አሉኝ፡፡
“ይሄዋ እቅጩን ነገሩህ!”
“ዕውነትሽን ነው፡፡ ፈርጄ አለመጨረሴን ያሳየሁዋቸው አሁን እና እሥር ቤት ጐራ ብዬ ተሰናብቻቸው ስመጣ ነው!” ብሎ ሳቀ፡፡
                                         *    *    *
ሀገራችን ብዙ ለከት የለሽ ጭካኔ አይታለች፡፡ “ግፉ በዛብኝ እራሴን እገላለሁ” ያሉትን ተበዳይ፤ “እሱንም እኛ ከፈቀድንልህ ነው” ካሉት መሪ “ብዙ ቦታ አትፍጁ፤ አንድ ላይ ቅበሩ” እስካሉ መሪ ድረስ፤ ሰው ጤፉ ጭካኔ አይተናል/ታዝበናል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የሚወራው ስለ ህዝብ ነው፡፡ ስለ ሀገር ሉዓላዊነት ነው፡፡ ስለ ሀገራዊነት ነው ስለ አንድነት ነው፡፡ ስለ ዕድገትና ብልፅግና ነው፡፡ የተሻለ ኢኮኖሚ ስለማምጣት ነው፡፡ ስለ ፍትሕ ርትዕ ነው፡፡ ህዝብ የፈለገውን መሪ እንዳገኘ ነው፡፡ ለውጥ በየቀኑ እየመጣ እንደሆነ ነው፡፡ ለውጥ ግን መሠረታዊ መሆን እንዳለበት በቅጡ የተናገረም፣ የተገበረም አልታየም፡፡
“ለውጥ አምፖል የመለወጥ ጉዳይ መሆኑ አብቅቷል፡፡ ይልቁንም ዓለምን ሙሉውን የመለወጥ፣ ሙሉን የማብራት ጉዳይ ነው” ትለናለች ናዎሚ ክላየን፡፡
አንድም አንድ አምፖል ቀይሮ መፎከር አሳሳች ስለሆነ፤ አንድም ደግሞ ቢያንስ የተሻለ አምፖል መሆን አለመሆኑ አለመታወቁም ነው፡፡ በመጨረሻም ዘላቂና አስተማማኝ ለውጥ ለማግኘት ለዋጩ ብቻ ሳይሆን ተለዋጩ ህዝብ ይሆነኛል ማለት ስላለበት ነው፡፡
ተጠቃሚውም አረጋጋጩ እሱ ነውና፡፡ ይህንን ህዝብ ተኮር መርህ ስንቶች ተመራጮች ከልባቸው አስበውበት፣ ምን ያህልስ ይታገሉለት ይሆን? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ በምርጫ ፉክክር ውስጥ አሯሯጭ የሚባል አለ እንዴ? የቅስቀሳ የአየር ጊዜ ምን ያህል የነገ ማንነትን ጠቋሚ ይሆን?
“ካልታዘልኩ አላምንም” ያለችው ሙሽሪት፣ ይፈረድባት ይሆን? እስከዛሬ ምን ያህል ያማሩ ፕሮግራሞችን አይተናል? እኒያን ፕሮግራሞች ስንቶች ከልብ ደከሙባቸው? ምን ያህል ህዝብ ልብ ውስጥ ገቡ/ኖሩ? የተቀሰቀስነውን ያህል ነቅተን ይሆን? ከጠዋቱ ጭቅጭቅ፣ ንትርክና፣ መፈነካከት ውስጥ መግባት በረከሰባት አገራችን ምን ያህል ተወዳዳሪ ይሳካለት ይሆን? ነው ወይስ ስትታጭ ያጣላች፤ በሠርጓ ታጋድላለች ይሆን አካሄዱ? እስቲ ለነገ ያብቃን ለፍሬ - ግብሩ!


የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ መንግስታት ምላሽ አልሰጡም
የአሜሪካ መንግስት ዘገባው አስቂኝ አልቧልታ ነው ሲል አጣጥሎታል
ተጠርጣሪ ሆኖ የተጠቀሰው የሱዳን መንግስትም ዘገባው የውሸት ፈጠራ ነው ብሏል

     ከረዥም ጊዜ ውዝግብ በኋላ እ.ኤ.አ በ2012 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት ደቡብ አፍሪካዊቷ ዱላሚኒ ዙማ ላይ፣ በዚያው ሰሞን እዚሁ  አዲስ አበባ ውስጥ ግድያ ሊፈፀምባቸው ነበር በሚል አልጀዚራ ሰሞን ዘገበ፡፡
የግድያ ሴራው ጠንሳሾች ማንነትንና መነሻ ሰበቡን በግልጽ ያልዘገበው አልጀዚራ፣ ሱዳን ተጠርጣሪ እንደነበረች ጠቅሶ ሴራው ለደቡብ አፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎች ድንገተኛ ነበር ብሏል፡፡
ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል ዘገባውን በተመለከተ የተሰነዘረ ምላሽ የለም፡፡ የአፍሪካ ህብረትም፤ በአልጀዚራ የተላለፈውን ዘገባ አይተነዋል ከማለት ውጭ፣ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ኮሚሽነሯ የስራ ሃላፊነታቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እያከናወኑ ናቸው በሚል መግለጫ ያወጣው የአፍሪካ ህብረት፤
የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ተቋም፤ የህብረቱ መሪዎችና ተወካዮችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያካሂደውን ስራ እናደንቃለን፤ እንደአስፈላጊነቱም ከደቡብ አፍሪካ መንግስትና ከሌሎች የህብረቱ አባል አገራት ጋርም በትብብር ይሰራል ብሏል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ሊንዳ ግሪንፊልድ ግን፣ ዘገባውን የሚያጣጥል ቀጥተኛ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የግድያ ሴራ ተጠንስሶ ነበር የሚለው መረጃ ከየት እንደመጣ አይታወቅም፤ ቁም ነገር የሌለው ቧልት ነው ብለዋል - ሃላፊዋ፡፡
በአልጀዚራ ዘገባ ውስጥ የግድያ ሴራ ተጠርጣሪ ሆኖ የተጠቀሰው የሱዳን መንግስትም፤ ዘገባው የውሸት ፈጠራ ነው በማለት እንዳስተባበለ ሱዳን ትሪቢዩን ገልጿል፡፡ የግድያ ሴራን የሚያክል ወንጀል ያለ ጠንካራ መነሻ ሰበብ እንደማይጠነስስ የገለፁ የሱዳን መንግስት ባለስልጣናት፤ “ኮሚሽነሯን ለመግደል ሱዳን ምን መነሻ ሰበብ ይኖራታል?” በሚል ዘገባው ጤናማ አእምሮ ላለው ሰው ትርጉም የሚሰጥ አይደለም ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግስት እና ኮሚሽነሯ በጉዳዩ ላይ ምንም አለማለታቸው አስገራሚ ነው ሲሉ፣ የሱዳን ባለስልጣናት መናገራቸውንም የሱዳን ትሪቡን ገልጿል፡፡

     ዐድዋን ጨምሮ በተለያዩ ጦርነቶች በመዝመትና በነገሥታት መናገሻነቱ የሚታወቀው ታሪካዊው የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ባለዕዳ በሚያደርግ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ምንጮች ገለፁ፡፡
ደብሩ ‹‹ዳዊት ወንድሙ›› በተባለ የሕንፃ ሥራ ተቋራጭ በማሠራት ላይ የሚገኘው ባለአራት ፎቅ የንግድ ማዕከል ሕንፃ፣ በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. በውስን ጨረታ በወጣ ማስታወቂያ መሠረት በሰበካ ጉባኤውና በልማት ኮሚቴው ጥምር የጋራ ስብሰባ ለአሸናፊው ድርጅት ተወስኖ የኮንትራት ውሉም በብር 61‚234‚885.02 ጠቅላላ ወጪ ተፈጽሞ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ አማካሪ ድርጅቱም የተቀጠረው በግልጽ አሠራር ተለይቶ መሆኑን፣ ተናግረዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የደብሩ አስተዳደር በዲዛይን ክለሳ ሰበብ የግንባታ ዋጋውን ከዕጥፍ በላይ በማናር የሥራ ውሉን መቀየሩ ተመልክቷል፡፡ የቀድሞውን አማካሪ መሐንዲስ በማሰናበትም ‹‹የዲዛይን ክለሳና ተያያዥ ሰነዶች ፍተሻ በማስፈለጉ›› በሚል ሰበብ ያለምንም ግልጽ መመዘኛና ውድድር በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በተቀጠረው ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ለተደረገው የፕላን ማሻሻያ 80‚500 ብር የተከፈለ ሲኾን የግንባታ ወጪውም ከ170 ሚልዮን ብር በላይ ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡
የኮንስትራክሽንን ሕጉን በመጣስ ያለጨረታ የተሰጠው ‹‹የፕላን ማሻሻያ››ና የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሀገረ ስብከቱ ባልፈቀደው ‹‹የተከለሰ ዲዛይን›› መቀጠሉ የተገለጸው ግንባታ፣ ከ80 ሚልዮን ብር ያላነሰ የወጪ ልዩነት ቢታይበትም እንደጭማሪ የተጠቀሱት የአሳንሰርና የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች የተጠቀሰውን ወጪ ምክንያታዊ እንደማያደርጉት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሕንፃው ከጠቅላላ ሥራው በሢሦ ደረጃ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት  ወጪው ከ25 ሚልዮን ብር በላይ መድረሱ፣ ሥራው በማዕከል ከተፈቀደው ውጭና በተለየ ውል እየተካሔደ መኾኑን ያረጋግጣል ብለዋል - ምንጮቹ፡፡
የደብሩ ይዞታዎች በኾኑ ኹለት ሕንፃዎች ላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት የደብሩ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሜን አዲስ አበባ ዲስትሪክት ጋራ ያደረገው የኪራይ ውል የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ የጣሰ እንደኾነ የደብሩ ሠራተኞች ያስረዳሉ፡፡ የደብሩ አስተዳደር በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ከባንኩ ጋር በፈጸመው የዐሥር ዓመት የኪራይ ውል፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቅርንጫፍ እና መሀል ፒያሳ ቅርንጫፍ ለመክፈት ብር 12 ሚልዮንና ብር 28 ሚልዮን በድምሩ ብር 40 ሚልዮን እንዲከፈለው መስማማቱ ታውቋል፡፡
መዋቅራዊ አሠራርንና የሌሎችን የሥራ ሓላፊነት በማናለብኝነት በመጣስ እየተፈጸመ ነው በተባለው የገንዘብ ብክነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛ ተጠያቂ የተደረጉት የደብሩ አስተዳዳሪ፣ የቢሮ ሠራተኞችንና ባለሞያዎችን በዛቻ ቃል በማሸማቀቅ እንደሚወቀሱ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የሕዝብ ሀብት የኾነችው ቤተ ክርስቲያን ‹‹በልማት እየተመካኘ ተገቢ ባልኾነ የሥራ ሒደት በዕዳ እንዳትዘፈቅ፣ የሠራተኛው የሥራ ዋስትናም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ›› ሲሉ ያሳሰቡት የደብሩ ሠራተኞችና ምእመናኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ታሪካዊውን ደብር የሚታደግ ፈጣንና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ተማፅነዋል፡፡
ከመስከረም ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የደብሩ አስተዳዳሪ በመሆን የተሾሙት መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃን ስለጉዳዩ በስልክ አነጋግረናቸው፤ ‹‹የምእመናን አቤቱታ እንድትቀበሉና ይህን ጉዳይ እንድትመረምሩ ሥልጣን የሰጣችኹ ማን ነው?›› በማለት በአካል ካልኾነ በቀር በስልክ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልኾኑ በመግለጻቸው ቀጠሮ ለመያዝ ስንሞክር ስልኩን ጆሮአችን ላይ በመዝጋታቸው ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የፓትርያርኩን እገዳ ተቃወሙ›› በሚል ርእስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የቀረበው ዘገባ የስም ማጥፋት ዘመቻ መኾኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ገለጸ፡፡
የአዲስ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጋራ በመተባበር የየአድባራቱን የሰንበት ት/ቤቶች የሥራ አመራር የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ሰብስቦ የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስና የመምሪያው ምክትል ሓላፊ በተገኙበት የሥራ አመራር እንደሰጣቸው መምሪያው በደብዳቤው አስታውሷል፡፡ ይኹን እንጂ በጋዜጣው ላይ በቀረበው ዘገባ÷ ዓላማው በውል ባልታወቀ ኹኔታ፣ በወቅቱ ያልተባለና ኾን ተብሎ የተቀነባበረ የስም ማጥፋት ዘመቻ በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አመራር ላይ እንደተፈጸመ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡
ማደራጃ መምሪያው አያይዞም ‹‹የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የበላይ አመራርና የበታች አካላት ለማለያየት፣ ከዚህም ጋራ መንግሥታችን ለምርጫው በሰላም ዙሪያ በሚሠራበት ወቅት ሕዝብን ለመበጥበጥ እንዲሁም ወጣቱ የሰላም ተልእኮውን በአግባቡ እንዳይወጣ ለማድረግ›› ኾን ተብሎ እንደተቀነባበረ ገልፆ ‹‹የሃይማኖቱን ተከታዮች በእጅጉ አሳዝኖናል›› ብሏል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በዕለቱ ስላደረጉት የግማሽ ቀን ውይይት የስብሰባውን ተሳታፊዎች በምንጭነት በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

    በአለም ባንክ እና በሌሎች አለማቀፍ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው በሚል የባንኩ የውስጥ መርማሪ ቡድን ያወጣውን ሪፖርት ባንኩ በትኩረት ተመልክቶ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጠው ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ፡፡
ባንኩ በበኩሉ፤ መርማሪ ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት ላይ የተጠቀሱ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች በር የሚከፍቱ በርካታ የአሰራር ችግሮች እንደሌሉበት ገልጾ፣ ጥናቱ እንደገና ሊከለስ ይገባል ብሏል፡፡ የአለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የመርማሪ ቡድኑን ሪፖርት ለመገምገምና የማኔጅመንቱን ምላሽ ለማሰማት በትናንትናው ዕለት ስብሰባ አድርጓል፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች ለአለም ባንክ የአፍሪካ ምክትል ፕሬዚደንት በላከው ደብዳቤ እንዳለው፣ የባንኩ ገለልተኛ የተጠያቂነት ስልት መርማሪ ቡድን በጉዳዩ ዙሪያ ባደረገው ምርመራ በኢትዮጵያ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ የሚያደርገውን የራሱን ፖሊሲ እንደሚጥስ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት፤ በአለም ባንክ ፕሮጀክቶችና በኢትዮጵያ መንግስት የመልሶ ማስፈር ፕሮግራም መካከል የአሰራር ግንኙነት እንዳለ ማረጋገጡንና ይህም የአለም ባንክ ለነባር ህዝቦች መብቶች መከበር የቆመውን የራሱን ፖሊሲ እየጣሰ እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ማስታወቁንም አክሎ ገልጧል፡፡
መርማሪ ቡድኑ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማስፋፋት ዓላማ ያላቸውንና በአለም ባንክ፣ በእንግሊዝ መንግስት የአለማቀፍ ልማት ድርጅት፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በሌሎች ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ከጋምቤላ ክልል ስደተኞች የቀረበለትን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ባደረገው ማጣራት፣ የአለም ባንክ በፕሮጀክቶቹ ውስጥ ለሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት አደጋዎች ይህ ነው የሚባል ትኩረት እንዳልሰጠ ማረጋገጡን የሂውማን ራይትስ ዎች አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጀሲካ ኢቫንስ ገልጸዋል፡፡
የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶች አካሄድ ማስተካከል የሚችልበት ዕድል አለ ያሉት ጀሲካ ኢቫንስ፣ ባንኩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ የሆኑ ስደተኞችን የመብቶቻቸው ተጠቃሚ የማድረግ ሃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል፡
ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች በማሳካት ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገቧ፣ አገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ እና የአገር ውስጥ ገቢ እድገት እያሳየች መሆኗን ያመላክታል ያለው የእንግሊዝ መንግስት በበኩሉ፣ ይህም የአገሪቱን ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ የሚሰጠውን እርዳታ ከመሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ስራ ፈጠራና ራስን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ለማዞር እንዳነሳሳው ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ የእግሊዝ መንግስት የእርዳታ አቅጣጫ ለውጡ ለኢትዮጵያ በሚሰጠው የገንዘብ መጠን ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድርና በኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ለእንግሊዝ መንግስት ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡

*በርካታ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፉበታል

ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ የፊታችን ሰኞና ማክሰኞ ትምህርታዊ ፌስቲቫል ያካሄዳል፡፡ “የትምህርት እድልን በተቀናጀ መንገድ ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተማሪዎችን ማገናኘት” በሚል መሪ ቃል በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ በሚካሄደው ትምህርታዊ ፌስቲቫል ላይ በርካታ የውጭ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲና ፍራንክሊን ዩኒቨርሲቲ፣ የህንዱ አቻርያ ኢንስቲቲዩት፣የቱርኩ ኦካን ዩኒቨርሲቲ፣ የካናዳው ብሮንስቶን አካዳሚ፣ የማሌዢያው ማሌዢያ የትምህርት ማዕከል፣ የጣሊያኑ ካቶሊካ ዩኒቨርሲቲ፣ የኡጋንዳው ቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ፣ የስዊዘርላንዱ ሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የቆጵሮሱ ግሪኒ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ፣ የደቡብ አፍሪካው ጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚገኙበት የኮሌጁ የሚዲያ አስተባባሪ አቶ ቶፊቅ ሁሴን ገልጸዋል፡፡
በሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ አስተባባሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ትምህርታዊ ፌስቲቫል ቀጣይነት እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን የሌሎች አገራት ዩኒቨርሲቲዎችም በየተራ ፌስቲቫሉን ያዘጋጃሉ ተብሏል፡፡ የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ተማሪዎችን በማገናኘት ልምድ ማለዋወጥና በስኮላርሺፕ ሂደት ላይ ደላሎች የሚሰሩትን አሻጥር በማስቀረት፣ የየአገራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርታቸው ብልጫ ላላቸው ተማሪዎች በቀጥታ የትምህርት እድል እንዲሰጡ ለማድረግ እንደሆነ አቶ ቶፊቅ ተናግረዋል፡፡  
የፊታችን ሰኞና ማክሰኞ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት በሚካሄደው ፌስቲቫል፤የአገራችንም ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን ፌስቲቫሉ አገራችን ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የምታደርገውን ጥረት በማገዝ በእውቀት የበለፀገ ማህበረሰብን ለማፍራት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ የልምድ ልውውጦች፣ የፓናል ውይይቶችና መሰል ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በስፍራው ተገኝተው እንዲጎበኙት ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ጋብዟል፡፡

በአስር አመት ውስጥ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለሆኑ 800 ወንድና ሴት ተማሪዎች የነፃ ትምህርት ዕድል የሚያስገኘው የማስተር ካርድ ስኮላር ፕሮግራም ትናንት በይፋ ተጀመረ፡፡ በ100 ወጣት ወንድና ሴት ተማሪዎች የተጀመረው የነፃ ትምህርት ዕድል፤ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ  ተማሪዎች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ሆኖ ጥሩ የትምህርት ፍላጐት ያላቸውንና ጐበዝ ተማሪዎችን ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክልሎችና ከአዲስ አበባ አስተዳደር በማሰባሰብ የነፃ ትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገው ተብሏል፡፡  
Forum for African women education (FAWE) በተባለው ድርጅት በተጀመረው የነጻ ትምህርት እድል ፕሮጀክት በአስር ዓመት ውስጥ ተጠቃሚ የሚሆኑት 800 ወጣቶች ሲሆኑ 600 ያህሉ ሴት ተማሪዎች ናቸው፡፡ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች በውጭ አገር ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ሊያጋጥማቸው እንደሚችልም ተገልጿል፡፡