Administrator

Administrator

መኖሪያ ቤታቸውን በ15 ቀን ውስጥ እንዲለቁ ታዘዋል

 “እኔ ሣላውቅ በስሜ በታተመ መፅሃፍ ሃሳቤን ተዘርፌያለው” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ፤ መብቴን ለማስከበር በፍ/ቤት ክስ እመሰርታለሁ አሉ፡፡ መሐመድ ሀሰን በተባለ ፀሐፊ አማካኝነት “የዳኛቸው ሃሳቦች” በሚል ርዕስ ታትሞ በ80 ብር እየተሸጠ ነው የተባለው መፅሃፍ፤ ላለፉት 7 ዓመታት በተለያዩ የስልጠና መድረኮች፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጦችና መፅሄቶች ያቀረቧቸው ሃሳቦች መሆናቸውን የጠቆሙት ምሁሩ፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ “ትንታኔ” የሚል ቁንፅል አረፍተ ነገሮችን እየጨመረ ሃሳቦቼን ገልብጦ አትሞታል ሲሉ ከሰዋል፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ያሉት ሃሳቦች በሙሉ በ7 አመታት ውስጥ የተናገርኳቸው ናቸው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ግጥሞቹ ሳይቀሩ የራሳቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ መፅሃፉ በግልፅ የኔን ሃሳብ በመዝረፍ የተዘጋጀ ነው የሚሉት ዶ/ሩ፤ “ከህግ ባለሙያዎች ጋር ተማክሬ በፍ/ቤት ካሣ እጠይቅበታለሁ፤ ይህን መሰል የሃሳብ ዝርፊያ እንዳይፈፀምም ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡”
መፅሀፉ የታተመበት ማተሚያ ቤት አይታወቅም የሚሉት ምሁሩ፤ የኔን ፎቶግራፍ ለጥፎ፣ ‹የዳኛቸው
ሃሳቦች› ብሎ ማውጣት ትልቅ ወንጀል ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ዶ/ር ዳኛቸው፤ የራሳቸውን መፅሃፍ ለማሳተም ከአሳታሚዎች ጋር ተዋውለው እንደነበር ጠቁመው የዚህ መፅሀፍ በስማቸው መውጣት ሊያሳትሙ ባቀዱት መፅሃፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡በሌላ በኩል ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መባረራቸውን ተከትሎ ላለፉት 7 ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ሰጥቷቸው ይኖሩበት የነበረውን መኖሪያ ቤት በ15 ቀን ውስጥ ያለባቸውን 3300 ብር ውዝፍ እዳና የመብራትና ውሃ አገልግሎት ክፍያ ፈፅመው እንዲለቁ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባለፈው ግንቦት 28 በፃፈላቸው ደብዳቤ ያስታወቀ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ያስተማሩበትንና የምርምር ስራዎች የሰሩበትን ወደ 56 ሺህ ብር ክፍያ ቢፈፀምላቸው እዳቸውን ከፍለው መልቀቅ እንደሚችሉ ጠቁመው የተሰጣቸው የጊዜ ገደብም በቂ አለመሆኑን ገልፀዋል - ለዩኒቨርሲቲው በደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

በጎተራ የሚገነባው መንደር 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል
           ሲኖማርክ የተባለው የሪልስቴት አልሚ ኩባንያ፤ በኢትዮጵያ ትልቁን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። ኩባንያው በ4 ቢሊዮን ብር ወጪ ጎተራ አካባቢ ሊያስገነባው ያቀደው የሪልስቴት መንደር “ሮያል ጋርደን” የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 20 ወለሎች ያሏቸው 14 ህንፃዎች እንደሚኖሩት የኩባንያው ማርኬቲንግ ማኔጀር አቶ ተስፋዬ ገ/የሱስ ተናግረዋል፡፡
ጥራታቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኢትዮጵያውያን የማቅረብ አላማ
እንዳለው የገለጸው ኩባንያው፣ የሪልስቴት መንደሩ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትና የንግድ ዞን እንደሚኖረውና አገር በቀሉ ሳባ ኢንጂነሪንግ በግንባታው ንደሚሳተፍበት አስታውቋል፡፡ሪል እስቴቱ የሚያስገነባቸው ህንፃዎች የየራሳቸው ሁለት ሁለት ሊፍቶች፣ ጀነሬተርና የውሃ ማጣሪያ ማሽኖች የሚኖራቸው ሲሆን የሪልስቴት መንደሩ ግንባታ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡ የቤቶቹ ዋጋ የፊታችን ሰኞ ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ሲኖማርክ ሪልስቴት ላለፉት 7 አመታት በቻይናና በሌሎች አገራት የተለያዩ ታላላቅ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ በማከናወን የሚታወቀው የቻይናው ሲንቹዋን ሄንግያንግ
ኢንቨስትመንት እህት ኩባንያ ነው፡፡

       ጆቫጎ የተሰኘው አለማቀፍ የመንገደኞች የሆቴል ቀጠሮ አስያዥ ድረገጽ ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ፣ ወደ ውጭ አገራት የሚጓዙና በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንገደኞችን በተመለከተ የሰራውን ጥናት ይፋ ማድረጉን ሜል ኤንድ ጋርዲያን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡በውጭ አገራት የሚኖሩ ትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የጠቆመው ጥናቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ በርካታ መንገደኞች የሚመጡባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ናቸው ብሏል፡፡  ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ጎብኝዎች ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት ከፍተኛ እንደነበር የገለጸው ጥናቱ፣ እ.ኤ.አ በ2010 በድረ ገጹ አማካይነት በኢትዮጵያ የሆቴል ቀጠሮ ያስያዙ መንገደኞች 468 ሺህ እንደነበሩና ይህ ቁጥር በ2013 ወደ 681 ሺህ ከፍ ማለቱን ገልጾ፣ ቁጥሩ እስከ 2017 ከ1.2 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ያለውን ግምት አስቀምጧል፡፡ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በድረገጹ አማካይነት የሆቴል ቀጠሮ ካስያዙ መንገደኞች፣ በከፍተኛ ርቀት ላይ የተገኘው የጃፓኗ ቶክዮ ከተማ መንገደኛ እንደነበርና ቀጠሮውን ያስያዘው በ10ሺህ 89
ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ሆኖ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ በድረገጹ በኩል ቀጠሮ አስይዘው ወደተለያዩ አገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን መንደገኞችን በተመለከተም፣ ኢትዮጵያውያን መንገደኞች በብዛት የሚሄዱባቸው አገራት ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ አይቬሪኮስት፣ ጅቡቲና የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ ናቸው ብሏል ጥናቱ፡፡
በአገር ውስጥ የሚደረገውን የመንገደኞች ዝውውር በተመለከተም፣ አዲስ አበባ ከአገሪቱ ከተሞች በአገር ውስጥ መንገደኞች መዳረሻነት ቀዳሚነቱን መያዟንና ከመንገደኞቹ መካከል 13 በመቶ ሽፋን እንዳላት የገለጸው ጥናቱ፤ ጎንደር በ10 በመቶ፣ ላሊበላ በ9 በመቶ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን እንደያዙ ጠቁሟል፡፡ ከሃገር ውስጥ ጎብኝዎች 6 በመቶ የሚሆኑት ሃዋሳን ምርጫቸው አድርገዋል  ብሏል፡፡ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በመጓዝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች 60 በመቶውን ሲይዙ፣ የሃዋሳ ነዋሪዎች 2 በመቶ፣ የተቀሩት የአገሪቱ ከተሞች ደግሞ 38 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሏል፡፡

     በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን÷ ከሙስና እና ብልሹ አሠራር መንሰራፋት፣ ከመልካም  አስተዳደር እና ፍትሕ ዕጦት፣ ከአስተምህሮ እና ሥርዐት መጠበቅ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በየሰንበት ት/ቤቶች መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ እንደቀጠለ ነው፡፡
በሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት÷ ሌቦች እየተበራከቱ፣ ጎጠኝነት እየተስፋፋ፣ በመናፍቅነታቸው የተወገዱ ግለሰቦች ተመልሰው እየተቀጠሩና አስተምህሮውን እየተፈታተኑ መሆናቸውን ሰንበት ት/ቤቶቹ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ሕገ ወጥ ሰዎችን አልደግፍም›› የሚለው ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ፤ ካህናት ሙሰኞች ናቸው  ብሎ ንደማያምን ጠቁሞ፤ ‹‹ሰዎችን ሰረቃችሁ ለማለት ማስረጃ ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡በሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የሚመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ ባለፈው ማክሰኞ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ጋር በሀገረ ስብከቱ ይፈፀማል በተባለው ብልሹ አሠራር ላይ ያካሄዱት ውይይት ባለመግባባት ተቋጭቷል፡፡ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በማጋለጣቸው ‹‹የፖሊቲካ ድርጅቶች ደጋፊዎች እና ሁከት ቀስቃሾች ናቸው፤ ፓትርያርኩን ይቃወማሉ›› በሚል እየታሰሩ እንደሆነ በውይይቱ ላይ የተናገሩት የሰንበት ት/ቤቶቹ፤ በሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አሠራሩን የተቃወሙ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው ክሥ እንደተመሠረተባቸው፤ ካህናትም የንስሐ አባት እንዳይኾኗቸው በደብዳቤ መመሪያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡በሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት የሚመኩና የጥቅም ትስስር ያላቸው የአድባራትና የገዳማት ሓላፊዎች ከሦስት እስከ አራት ሺሕ ብር ያልበለጠ ደመወዝ እየተከፈላቸው ውድ ዋጋ ያላቸውን መኪኖችን እንደሚነዱና ቤት እንደሚገዙ ጠቁመው ገንዘቡ ከየት እንደመጣ ሊጣራ ይገባዋል ብለዋል። ሀገረ ስብከቱ የሙዳዬ ምጽዋት ቆጠራ በካሽ ካውንተር እንዲከናወን ማድረጉን ቢደግፉም በፐርሰንት አከፋፈል፣ በቦታ እና በሕንፃ ኪራይ፣ በሠራተኞች ቅጥርና ዝውውር ረገድ በጥቅም ትስስር የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ፤ በየአጥቢያው የሚታየው የጎጠኝነት መከፋፈል መፍትሔ እንዲያገኝ
አበክረው ጠይቀዋል፡፡ ሰንበት ት/ቤቶቹ ለዘረዘሯቸው በርካታ ችግሮች  ምላሽ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ሰዎችን ሰረቃችሁ ለማለት ማስረጃ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ‹‹ካህናት ሙሰኞች ናቸው ብለን አናምንም፤ መኪና ቢኖራቸው ቪላ ቤት ቢኖራቸው ደስ ይለናል፡፡ ካህናት የሀብት ችግር አለባቸው እንጂ ታማኞች ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል፤ ከሙዳይ ምጽዋት ጥገኝነት ይልቅ በልማት ሥራ መሠማራት እንደሚመረጥም አብራርተዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሠራተኛ ቅጥር እየተፈጸመ ያለው በውድድር እንደሆነና ለውጡ ባይጠናቀቅም መጀመሩ መልካም ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በቤተ ክርስቲያን ጎጠኝነትን ጨምሮ ሙስናን በሁለንተናዊ ገጽታው መዋጋት ይገባል ብለዋል፡፡

ሩስያ መጠነ ሰፊ ወረራ ልታደርግብን ትችላለች ብለዋል

   በሩስያ በሚደገፉት የዩክሬን አማጽያን እና በመንግስት ጦር መካከል ባለፈው ረቡዕ የከፋ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ፣ ፕሬዚደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ የጦር ሃይላቸው ከሩስያ ሊቃጣ ከሚችል የተደራጀ መጠነ ሰፊ ወረራ አገሪቱን ለመከላከል በተጠንቀቅ እንዲቆም ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን አማጽያን ጋር በመተባበር በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ጥቃት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለአገሪቱ የፓርላማ አባላት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ጦራቸው ከአማጽያኑ የሚቃጣበትን ጥቃትና ከሩስያ ጋር በሚያዋስኗት ሁሉም የድንበር አካባቢዎች ሊፈጸምበት ከሚችለው ሰፊ ወረራ አገሪቱን ለመከላከል በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የዩክሬን አማጽያን ባለፈው ረቡዕ ማሪንካ ከተማን ለመቆጣጠር ባደረጉት ሙከራ፣ ከመንግስት ጦር ጋር በከባድ የጦር መሳሪያዎች የታገዘ አስከፊ ግጭት መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱም ግጭቱ ሩስያና አማጽያኑ በአገሪቱ ላይ ቀጣይ የተደራጀ ወታደራዊ ጥቃት እንደሚሰነዘር የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ገልጧል፡፡
ዩክሬንና የኔቶ አባል አገራት የሆኑ አጋሮቿ፣ በአገሪቱ ምስራቃዊ አካባቢዎች የሚገኙ ሁለት ግዛቶችን ከፊል አካባቢዎች ይዘው ለሚገኙት አማጽያን የጦር መሳሪያዎችንና ወታደሮችን በመላክ ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲሉ ሩስያን በተደጋጋሚ ሲከሱ መቆየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም፣ መጠነኛ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውንና፣ ባለፈው ረቡዕም አስከፊ የተባለው ግጭት መከሰቱን ገልጧል፡፡ ምዕራባውያን አገራት ሩስያ በሰላም ስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ሃላፊነቶቿን አልተወጣችም ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ ወታደሮቿን ከዩክሬን ግዛት ማስወጣትና ለአማጽያኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን ማቆም አለባት ማለታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ሩስያ በበኩሏ፤ ግጭቱን እንደገና የቆሰቆሰችው ዩክሬን ናት፣ ይህንንም ያደረገችው በቅርቡ በሩስያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይጣል አይጣል የሚለውን ይወስናል ተብሎ በሚጠበቀው የአውሮፓ ህብረት ላይ ጫና ለማሳደር በማሰብ ነው ብላለች፡፡
ፕሬዚዳንት ፖሮሼንኮ በአሁኑ ወቅት 9ሺህ ያህል የሩስያ ወታደሮች ድንበር ጥሰው ገብተው በግዛታችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ቢሉም፣ ሩስያ በበኩሏ መሰረተቢስ ውንጀላ ነው ስትል የፕሬዚዳንቱን ንግግር ማጣጣሏን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 5 በመቶውን ለወታደራዊ በጀት የመደበችው ዩክሬን፣ በቀጣዩ አመትም በወታደራዊ በጀቷ ላይ ጭማሪ ልታደርግ እንደምትችል ፕሬዚዳንት ፖሮሼንኮ ለፓርላማ አባላቱ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገመንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት በዚህ ሳምንትም ያገረሸበት ሲሆን  የአገሪቱ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ዳግም መራዘሙን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ምርጫን ለማከናወን አያስችልም በሚል ምርጫውን እንዲያራዝሙ ከአፍሪካውያንና ምእራባውያን መንግስታት ጫና ሲደረግባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፣ ምርጫው እንዲራዘምና በመጪው ነሃሴ ወር መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
ከአገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ የሆኑት አጋቶን ሩዋሳ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ አምባገነን መሪ ስለሆኑ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ሁኔታው ሳይሻሻል፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ሳይመረጥና የግል ሚዲያው ላይ የሚደረገው ጫና ሳያበቃ በአገሪቱ ምርጫ ሊከናወን አይችልም ብለዋል፡፡ የብሩንዲ ምርጫ ከዚህ ቀደም እንዲራዘም በተወሰነው መሰረት፣ የፓርላማ ምርጫው ትናንት፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ደግሞ በሰኔ ወር መጨረሻ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱና በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ዜጎች መሞታቸውን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ብሩንዲያውያንም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገመንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት በዚህ ሳምንትም ያገረሸበት ሲሆን  የአገሪቱ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ዳግም መራዘሙን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ምርጫን ለማከናወን አያስችልም በሚል ምርጫውን እንዲያራዝሙ ከአፍሪካውያንና ምእራባውያን መንግስታት ጫና ሲደረግባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፣ ምርጫው እንዲራዘምና በመጪው ነሃሴ ወር መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
ከአገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ የሆኑት አጋቶን ሩዋሳ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ አምባገነን መሪ ስለሆኑ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ሁኔታው ሳይሻሻል፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ሳይመረጥና የግል ሚዲያው ላይ የሚደረገው ጫና ሳያበቃ በአገሪቱ ምርጫ ሊከናወን አይችልም ብለዋል፡፡ የብሩንዲ ምርጫ ከዚህ ቀደም እንዲራዘም በተወሰነው መሰረት፣ የፓርላማ ምርጫው ትናንት፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ደግሞ በሰኔ ወር መጨረሻ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱና በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ዜጎች መሞታቸውን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ብሩንዲያውያንም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

 አሸናፊው ሮቦት 3.5 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል

    በሮቦቲክስ መስክ የተሰማሩ 24 የአለማችን ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ያመረቷቸው ሮቦቶች የተሳተፉበትና 3.5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚያስገኘው የዳርፓ የሮቦቶች ውድድር ትናንትና ዛሬ በአሜሪካ እየተካሄደ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአሜሪካው መከላከያ ቢሮ ፔንታጎን ድጋፍ በሎሳንጀለስ አቅራቢያ በመከናወን ላይ በሚገኘው በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ሮቦቶች አደጋን የመቋቋም ብቃታቸውን የሚያሳዩ አስቸጋሪ ተግባራትን እንዲፈጽሙ በማድረግ አሸናፊው ይለያል ተብሏል፡፡
ሮቦቶቹ እንዲያከናውኗቸው ከተመደቡላቸው ስምንት ተግባራት መካከል፡- መኪና መንዳት፣ በር መክፈትና ማለፍ፣ ግድግዳ መብሳት፣ በደረጃዎች ላይ መወጣጣት የሚገኙበት ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ የሚገለጽ ሌላ ለየት ያለ ተልዕኮም እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡
እያንዳንዱ ሮቦት እነዚህን ስምንት ተግባራት ለማከናወን ሁለት ሙከራዎች የሚሰጡት ሲሆን ፈጥኖ ተግባራቱን በተሳካ ሁኔታ ማከናወንም ለአሸናፊነት በመስፈርትነት ከተቀመጡት ነጥቦች አንዱ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጊል ፕራት እንዳሉት፣ የዘንድሮው ውድድር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአስር እጥፍ አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት የሮቦቲክስ ዘርፍ ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ለውድድሩ የቀረቡ ቢሆንም፣ የመጀመሪያውን ማጣሪያ አልፈው ለፍጻሜ የደረሱት፣ 24 መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ፣ የደቡብ ኮርያ፣ የጃፓን፣ የጀርመንና የጣሊያን ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል፡፡  

  ከአለማችን ታላላቅ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አምራች ኩባንያዎች ተርታ የሚሰለፈው የጃፓኑ ሻርፕ ኩባንያ፣ በያዝነው የፈረንጆች አመት  ብቻ 1.45 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ እየደረሰበት ካለው ኪሳራ ለማገገም ደፋ ቀና ማለቱን የቀጠለው ሻርፕ፣ በዘንድሮው አመት  1.45 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ይደርስበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጃፓኑ ኮዮዶ ኒውስ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው ገልጧል፡፡
ኩባንያው ባለፈው አመት 222 ቢሊዮን የጃፓን የን መክሰሩን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአምናው ኪሳራው ባለፉት አራት አመታት ከደረሱበት ኪሳራዎች በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልጧል፡፡ ኩባንያው ባለፉት አመታት ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረገው በተለያዩ አለማቀፋዊና ውስጣዊ ምክንያቶች መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህም መካከል የምርቶች ሽያጩ መቀነሱ፣ የገበያ ውድድሩ ከፍተኛ መሆኑና የወጪዎች መብዛት ይጠቀሳሉ ብሏል፡፡ ሻርፕ ባለፈው አመት በአለም ዙሪያ ከሚገኙ 49 ሺህ ሰራተኞቹ መካከል 10 በመቶውን ከስራ እንደቀነሰና ከእነዚህም መካከል 3ሺህ 500 የሚሆኑት በጃፓን ይሰሩ የነበሩ መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የማይመለሱ 4 ነገሮች፡- ከአፍ የወጣ ቃል፣ የተወረወረ ቀስት፣ ያለፈ ህይወት እና የባከነ ዕድል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ለማቀድ መስነፍ ለመውደቅ ማቀድ ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል
ማለም ብቻ በቂ አይደለም፤ መምታት አለብህ፡፡
የጣሊያኖች አባባል
መሬት ላይ እሾህ ከበተንክ ባዶ እግርህን አትሂድ፡፡
የጣሊያኖች አባባል
ሁልጊዜ የምትሰጥ ከሆነ ሁልጊዜ ይኖርሃል፡፡
የቻይናውያን አባባል
በአንድ እጅህ ሁለት እንቁራሪቶችን ለመያዝ አትሞክር፡፡
የቻይናውያን አባባል
የተጠበሰች ዳክዬ መብረር አትችልም፡፡
የቻይናውያን አባባል
አበቦች በያዛቸው እጅ ላይ መዓዛቸውን ይተዋሉ፡፡
የቻይናውያን አባባል
ጠብ ከፈለግህ ለጓደኛህ ገንዘብ አበድረው፡፡
የቻይናውያን አባባል
የምላስ ብዕር፣ የልብ ቀለም ውስጥ መነከር አለበት፡፡
የቻይናውያን አባባል
የአንድ ዓመት ብልጽግና ከፈለግህ እህል ዝራ፤ የ10 ዓመት ብልጽግና ከፈለግህ ዛፎች ትከል፤ የ100 ዓመት ብልጽግና ከፈለግህ ሰዎችን አልማ፡፡
የቻይናው ያን አባባል
የአንድ ሰዓት ደስታ ከፈለግህ አሸልብ፤ የአንድ ቀን ደስታ ከፈለግህ ሃብት ውረስ፤ የዕድሜ ልክ ደስታ ከፈለግህ ሰዎችን እርዳ፡፡
የቻይናውያን አባባል