Administrator
ሁሉ ፈረስ ላይ ልውጣ ካለ፣ ገደሉን ማን ሊያሳይ ነው?
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “ሱካርና ወተት የልጆች ማሳደጊያ።” በሚለው ጽሁፋቸው፤ ስለ አንድ ሽማግሌ ሰውና ስለ አንዲት ልጅ በሚል፤ በመስኮብ የሚነገር አንድ ተረት እንዳለ ይናገራሉ።
በመስኮብ አገር ሦስት ሴቶች ልጆች ያሉት አንድ ሽማግሌ ነበረ። አንዲቱ በመልኳና በጥበብዋ እጅግ ስመ ጥሩ ናት፤ አንድ ቀን ወደ ገበያ ሲወጣ፡-
“ልጆቼ ሆይ፤ ከገበያ ምን ገዝቼላችሁ ልምጣ?” አላቸው። ሁለቱ ልጆቹ “ጌጥ ገዝተህልን ና” አሉት፡፤ አንዲቱ ግን፤ “እኔ ምንም አልፈልግም። ነገር ግን የምመክርህን ምክር ስማኝ” አለችው። ለጊዜው ነገሩ ከበደው፤ ነገር ግን ልጁ እጅግ ብልህ መሆኗን ያውቃልና “እሺ ይሁን ንገሪኝ” አላት። “ወይንማውን በሬ ወደ ገበያ አውጥተህ ስትሸጥ ዋጋ ንገረን ያሉህ እንደሆነ፣ የንጉሡን ግራ አይን አምጡና በሬውን ውሰዱ በላቸው” አለችው።
እርሱም በገበያ ተቀመጠና “የበሬውን ዋጋ ንገር?” ሲሉት፤ ልጁ እንደመከረችው፤
“የንጉሡን ግራ አይን አምጡና ውሰዱት” ይል ጀመረ።
ይህንም ወሬ ንጉሡ ሰሙና፤
“እጁን ይዛችሁ አምጡልኝ!” ብለው አዘዙ።
ሽማግሌውም በቀረበ ጊዜ “ንጉሥ ሆይ፤ እንደዚህ ያደረገችኝ ልጄ ናትና ማሩኝ እያለ ይለምን ጀመረ። ንጉሡም ይህን በሰሙ ጊዜ “ሔደህ ልጅህን አምጣትና እምርሃለሁ” አሉት።
ሽማግሌው እያዘነና እየተንቀጠቀጠ ሄዶ ልጁን ይዞ ወደ ንጉሡ ቀረበ። ንጉሡም ልጅቱን ባዩዋት ጊዜ፤ “ለበሬው ዋጋ የንጉሡን ግራ ዓይን አምጡና ውሰዱ በላቸው ብለሽ ለአባትሽ የመከርሽው ስለምን ነው?” አሏት።
“ንጉሥ ሆይ አልቀጣሽም ብለው ይማሉልኝና እነግርዎታለሁ” አለች።
“አልቀጣሽም!” ብለው ማሉላት።
“ንጉሥ ሆይ፤ ድኃና ጌታ ተጣልተው ወደርሶ የመጡ እንደሆነ በቀኝ የቆመውን ጌታውን ብቻ ያያሉ እንጂ በግራ የቆመውን ድኃውን አያዩም፤ ስለዚህ መቼም ግራ ዓይንዎ ሥራ ካልያዘ ብዬ ነው” አለቻቸው።
ንጉሡም የልጅቱን ንግግር ሰምተው እጅግ አደነቁ። ወዲያውም ወንድ ልጃቸውን ጠርተው “ልጄ ሆይ፤ በመልክና በእውቀት ከርሷ የምትሻል ሴት የለችምና እርሷን አግብተህ መንግሥቴን ይዘህ ኑር” አሉት። ልጁም እርሷን አግብቶ እርሱ ንጉሥ፣ እርሷ ንግሥት ተብለው ኖሩ።
***
በተናገረው ነገር ዕምነት ያለው ብልህ ህዝብና በኃይል የማያምን መሪ፣ ኃላፊና አለቃ ለማግኘት አለመቻል መርገምት ነው። ይህ አለመቻል በተደጋጋሚ ዕውነትነቱ ታይቷል። ይህ እየሆነ እያዩ ምክር አለመቀበል ደግሞ የባሰው አባዜ ነው።
ቮልቴር እንዳለው፡-
የክፉ ገዢ ጦስ፣
ስም ነው ክፉ ጥላ፣ የቀን ሌት መጋኛ
ስም ዕዳ ያለበት
እንቅልፍ አይወስደውም
ቢተኛም ባይተኛ።
አንዳንድ ጊዜ ገዢዎችና መሪዎች የተናገሩት በተግባራዊ ዕውነታ በተጨባጭ ቢፋለስና ቢረክስም እንኳ፤ ጉዳዩን መርምረው በተቃና መንገድ አገርን ፓርቲንና የሥራ ኃላፊነትን ከመምራት ይልቅ እኔ ያልኩት ከሚፈርስ፣ የኔ ዝናና ስም ከሚጎድፍ የቀረው ይቅር ማለት ይቀናቸዋል። ለዚህም ነው አጋጣሚንና ሁኔታዎችን ተገን በማድረግ፣ ለተቃና ጥያቄ፣ የተዛባ መልስ፤ ለቀላል ጥያቄ ውስብስብ ምላሽ፤… መስጠትን እንደ ልዩ ዘዴ መቁጠር የነጋ ጠባ ትዝብታችን እየሆነ የመጣው።
የኢኮኖሚ አቅም ግንባታንም በተመለከተ የዘመቻ ባህል መቀነስ አለበት ሲባል፣ ሲነገር ሲዘከር ኖሯል። የሚሰማ የለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ከአንድ ሰሞን ግርግርና ዘራፍ ዘራፍ የተለየ እርምጃ ከሌለ፤ እንደ ጧት ጤዛ መሆን ነው። ጥሞና ያለው፣ ከጀርባው ማናቸውም ዓይነት ጥንስስና እኩይ ዓላማ የሌለው፣ ክንዋኔ ብቻ ነው ወደፊት የመጓዝ መሠረት። ተግባራዊ ጽናቱና ጥረቱ በሌለበት፤ በጀማ፣ በኮሚቴ፣ በሸንጎ ላይ ዲስኩር ማድረግ ብቻ፤ እንኳንስ ትላልቅ ፅንሰ-ሀሳቦችን ማስረፅ አፍአዊ ሂደት ከመሆን አይታለፍም። በየጊዜው አድገናል ተመንድገናል በሚል ዜማ ድግግሞሽ ብቻ የዕውነቱ ብልጽግና አይመጣም። ይብሱንም አንድ አዛውንት፤ “ይህን ሁሉ ያወራህልንን በአይናችን የምናየው ማንኛችን እንሆን? እኛ ነን አንተ?” እንዳሉት እንዳያሰኝ ያሰጋል።
ከቶውንም፤”አልቀጣህም ብለው ይማሉልኝና ዕውነቱን እነግርዎታለሁ” የሚል ህዝብም ሆነ፤ “አልቀጣም!” የሚል የበላይ ባለበት ንፍቀ-ክበብ፤ የዲሞክራሲ አየር እንደማይነፍስ አሌ የሚባል ነገር አይደለም። የምህረት አድራጊና የምህረት ተቀባይ ግንኙነት መኖር የዲሞክራሲ ዋስትና አይሆንም። ይልቁንም የበላይና የበታች፣ የአዛዥና የታዣዥ ቁርኝት ነው። እኔ በነፃነት እናገራለሁ የሚል ህዝብና ነፃነትና መብትህን አከብራለሁ የሚል የበላይ ይኖር ዘንድ ነው የረዥሙ ዘመን ትግል ሁሉ መጠንጠኛ። ይህን የሚገድብ ሁኔታ፣ ማስፈንጠሪያ፣ ለበጣ፣ ትዕዛዝ ወዘተ-- ዛሬም ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ ዘላቂ ፈውስ አይደሉም።
አጋጣሚን በመጠቀም የሩቅም ሆነ የቅርብ ግላዊ ጥቅምን ለማግኘት መሯሯጤ በህዝብ ዘንድ አይታወቅም ብሎ መገመትም ፍፁም የዋህነት ነው። እንዲህ ያለ ተግባር ከተፈጸመ ግመል ሰርቆ ማጎንበስ ብቻ ሳይሆን፤ ግመሏም እንሽላሊት ናት ብሎ እንደ መሟገት ይሆናል። የህዝብ አደራ እንደ ዩኒቨርሲቲ ማሟያ ኮርስ አይደለም። ስለሆነም የህዝብን አደራ ለግል ህይወት ማሻሻያ፣ ለግል የሩቅ ጊዜ ምኞት ማሳኪያ፤ ለማድረግ መጣር በቀላሉ የማይስተሰረይ ኃጢአት ነው። ያስጠይቃል፤ ያስቀጣል፤ ዋጋ ያስከፍላል። አተርፍ ባይ አጉዳይ ያደርጋል። የገብሬልን መገበሪያ የበላ፤ በገብሬል በገብሬል! ሲል ይገኛል እንዲሉ፤ ብዙም ሳይርቁ መጋለጥ አለ።
እንዲህ ያለው እኩይ ተግባር የህዝቡን የረዥም ጊዜ ግብና የዕድገቱን ዋስትና ያኮላሻል። የህዝብ አደራ የሥልጣን ጥም መወጫ አይደለም። የወንበር ፍቅር ማሞቂያም አይደለም። የግል ዝና ማካበቻ አይሆንም። የፖለቲካ ሽኩቻ ማድሪያ ሊሆንም አይገባም። የጀብደኝነት ወሸነኔም ዘመን አይደለም። የውስጥ-አርበኝነት የበግ ለምድም ሊሆን ከቶ አይችልም። የህዝብ አደራ የዳተኝነትና የዐድር ባይነት መሸፈኛም አይደለምና፣ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱን መገንዘብ ያስፈልጋል።
መቼም ቢሆን መቼ የህዝብ አደራ በግልጽ፣ የህዝብን ጥቅም ማስከበሪያ ኃላፊነት ነው።
በአግባቡ ካልያዙት፣ ዙፋኑን ካገኘ በኋላ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ “ምነው ይሄን ዘውድ የሰጡኝ ዕለት ማጥለቂያ እራስ ባይኖረኝ ኖሮ?” እንዳለው ንጉሥ መፀፀቻ ይሆናል። በአንጻሩ መደረግ የሚገባውን ነገር በጥሞና ማስተዋል፣ የሂደትና ክንዋኔውን የወደፊት ችግሮችና እንቅፋቶች ከወዲሁ መለየት ያሻል። ምክንያቱም በተነሱት ግላዊ ጉዳዮች ላይ ልብና ልቦናን ከተከሉና ጥቅምን ብቻ ላሳድድ ካሉ፤ እንደ ንጉሱ ከግራና ከቀኝ ላሉ ወገኖች አድሏዊ መሆን አይቀርምና፤ “ግራ ዐይንዎ ስራ አልያዘም ብዬ ነው” ብሎ እሚያሳይ ሰው መኖር አለበት። “ሁሉም ፈረስ ላይ ልውጣ ካለ፣ ገደሉን ማን ሊያሳይ ነው?” ማለትም ይኼው ነው።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኢትዮጵያና ሶማሊያ ድርድር አላካሄዱም አሉ
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም ፋቂ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሁለት ወራት በፊት በቱርክ አመቻችነት ድርድር አላካሄዱም ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ባለፈው ረቡዕ ሃምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በኳታር ዶሃ የሶማሊያ ዲያስፖራ ኮንፈረንስ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ “አል አረቢ አል ጃዲድ” ከተሰኘ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።
“ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር አላካሄድንም። ነገር ግን እነርሱ አሁን እያደረጉ ካሉት አደገኛ አካሄድ እንዲመለሱ የሚያሳምን ንግግር ነው በእኛ በኩል የተደረገው። ከሶማሌላንድ ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንዲያቋርጡ ነግረናቸዋል፡፡” ብለዋል፤ ሚኒስትሩ ለዜና አውታሩ።
“ከኢትዮጵያ ጋር ድርድሮች አልተደረጉም። ያደረግናቸው ውይይቶችም እንደ ድርድር የሚቆጠሩ አይደሉም” ነው ያሉት አህመድ፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን ስምምነት “ሕገ ወጥ” ሲሉ ያጣጣሉት የሶማሊያው ሚኒስትር፤ “ኢትዮጵያ ወራሪ አገር ነች። መሬታችንንና አገራችንን ማስከበር አለብን። ስምምነታቸው ሕገ ወጥ በመሆኑ፣ መሬት ላይ መተግበር የለበትም” ሲሉም በሃይለቃል ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለዜና አውታሩ፣ ሁለቱ አገራት ድርድር አላደረጉም ቢሉም፤ ከወራት በፊት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ ድርድር እንደሚያደርጉ የሚገልጽ መረጃ በቀድሞው ትዊተር (ኤክስ) ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር። ይህን መረጃ ግን ብዙም ሳይቆይ ከገጹ ያስወገደው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በምትኩ “የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቱርክ አደራዳሪነት ለሚደረገው ንግግር አንካራ ገብተዋል” ሲል መግለጹ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ቀደም ብለው ወደ ቱርክ አቅንተው የነበር ሲሆን፣ የሶማሊያው አቻቸው እርሳቸውን ተከትለው መግባታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የተካሄደውን ይህን ውይይት ተከትሎም፣ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም፣ አገራቱ ልዩነታቸውን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ “በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ” ልዩነታቸውን ለመፍታት ሁለተኛውን ዙር ድርድር፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 2 ቀን 2024 ዓ.ም በአንካራ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነበር፣ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን የገለጹት።
እ.ኤ.አ. በ2011 ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሞቃዲሾን መጎብኘታቸውን ተከትሎ፣ የጸጥታ ሃይሎች በማሰልጠንና የልማት ዕርዳታዎችን በማቅረብ ቱርክ፣ የሶማሊያ መንግስት የቅርብ አጋር ሆናለች። ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ከስምምነት ላይ ከደረሱ ከወር በኋላም፣ ቱርክና ሶማሊያ የ10 ዓመት የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
"አዘቦት"
የዩንቨርሲቲ ተማሪ ነው፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ይጽፋል፣ ሞጋች ነው፣ የውይይት ባሕሉ ድንቅ ነው፣ መጻሕፍት ቆንጆ አድርጎ መተንተን ያውቅበታል፣ ምልከታውን እወድለታለሁ...ሌላም ሌላም! አሁን ደግሞ "አዘቦት" የተሰኘ የአጭል አጭር ታሪኮችን/Post card stories ይዞልን ቀርቧል።
የት ማግኘት እንችላለን? ቢሉ በእጅ ስልክዎ፥ #afro read app የሞባይል መተግበሪያ ላይ በ50 ብር ብቻ ሸምተው ማንበብ ይቻላል!
Sirak Wondemu ን በሀሳብ አግዙት፤ አንብቡለትም፤ በሀሳብ የሚያምን ትሁት ወንድማችን ነው፤ ዕድሜው ከእኔ ብዙ ቢያንስም ስራዎቹ ትልቅ እንደሆኑ እመሰክራለሁ፤ በእኔ ይሁንባችሁ አንብቡት ትወዱታላችሁ! ሰሞኑን በሰፊው እመለሳለሁ።
መልካም ዕድል ለታናሽ ወንድማችን!
“ናዋዥ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ለንባብ በቃ
በደራሲ እያዩ ዳኛው የተሰናዳውና “ናዋዥ” የተሰኘው አዲስ የግለ ታሪክ መፅሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ መፅሐፉ በዋናነት በደራሲው የግል ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊያን በሱዳንና በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚያደርጉትን አስከፊና አስቸጋሪ የስደት ህይወት የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ነዋሪነቱን በጀርመን ያደረገው ደራሲ እያዩ ዳኛው፤ መፅሐፉ ከደቡብ ጎንደር ክምር ድንጋይ እስከ ጣሊያን የወደብ ከተማ ትራፓኒ የዘለቀውን የስደትና የውጣ ውረድ ጉዞ የሚዳስስ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
“ናዋዥ”፤ደራሲው ልጅነቱን የአፍላ ወጣትነቱን፣ የኢትዮጵያውያንን የስደት ኑሮ፣ በሱዳንና በሰሃራ በረሃ ለማቋረጥ ስደተኞች የሚከፍሉትን መስዋዕትነት እንዲሁም በመንግሥት አልባዋ ሊቢያ የነበረውን ኑሮና በሜድትራንያን ባህር የሚያጋጥምን ፈተና ያስቃኛል፡፡
በ470 ገፅ የተቀነበበው “ናዋዥ”፤ የግለ ታሪክ መፅሐፍ በ500 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
የሌሊሳ ግርማ “ደማቆቹ” በገበያ ላይ ዋለ
የዓለማችንን ምርጥና ስመጥር የአጭር ልብወለድ ድርሰቶችን ትርጉም የያዘው “ደማቆቹ“ የተሰኘ መድበል በገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ ከአሥራ አራት በላይ ደራስያንን ሥራዎች ያካተተ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አርነስት ሄሚንግዌይ፣ አየን ራንድ፣ ገብርኤል ጋርሺያ ማርኩዌዝ፣ አንቷን ቼኮቭ፣ ናጂብ ማህፉዝ፣ ማርጋሬት አትዉድና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በ254 ገጾች የተቀነበበው መድበሉ፤ አሥራ ስድስት የተለያዩ ርዝመት ያላቸውን የገናና ደራስያን ሥራዎች ያካተተ ነው፡፡ “ደማቆቹ” የተሰኘውን መድበል በዋናነት የሚያከፋፍለው የጃፋር መጻሕፍት መደብር ሲሆን፤ በ400 ብር ለገበያ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዚህ መጽሐፍ ተርጓሚ ከዚህ ቀደም “የንፋስ ህልምና ሌሎች ታሪኮች”፣ “አፍሮጋዳ” ፣ “መሬት-አየር-ሰማይ”፣ “የሰከረ እውነታ”፣ “እስቲ ሙዚቃ”፣ “ነጸብራቅ” እና “ይመስላል ዘላለም” በሚሉ የአጭር ልብወለድና የመጣጥፍ ስብስብ ሥራዎቹ በአንባቢያን ዘንድ ይታወቃል፡፡
ደራሲ ሌሊሳ ግርማ፤ ላለፉት ረዥም ዓመታት፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አጭር ልብወለዶችንና ወጎችን በአምደኝነት በመጻፍም የሚታወቅ ትጉህ የብዕር ሰው ነው፡፡
ምርኮኛው ባለቅኔ
“ባጠቃላይ፣ እናርጅና እናውጋ፣ ጌራወርቅ ሞጋች፣ አመራማሪ፣ ገሳጭና አስደማሚ ዐሳቦችን በምናቡ ሸምኖ በማቅረብ
ውስብስቡን ኑባሬንና ልቡናችንን ባላየነው አድማስ በርብረን እንድንገነዘብ ያደረገበት ሸጋ መድበል ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ
በኪነት ሚዛን የከያኒውን ክህሎት መስክረን፣ ያለ ንፍገት ሥሙን በደማቅ ቀለም እንድንጽፍ የሚገፋ ነው፡፡--
እናርጅና እናውጋ (2015) በጌራወርቅ ጥላዬ የተጻፈ የግጥም መድበል ነው፡፡ መድበሉ መልከ ብዙ የሕይወት ገጾች በወርድና ቁመታቸው የተፈተሹበት ነው፡፡ በመድበሉ ውስጥ የቀረቡ ግጥሞች አጀንዳና ድምጸት መልከ ብዙ መሆኑ ደግሞ የገጣሚውን አቅም በግልፅ ያሳያል፡፡ ይህ ማለት፣ የጌራወርቅ ግጥሞች እንደ አንዳንድ ጥቂት ገጣሚያን ሥራዎች በተመሳሳይ ድምጸት ሥር የወደቁ፣ በተመሳሳይ ጭብጥ (recurrent subject) ዙሪያ የሚሽከረከሩ አይደሉም፡፡
በእናርጅና እናውጋ የገጣሚው የቋንቋ ባለሟልነት፣ የምሰላ ክህሎት፣ የገለጻ ጠቢብነትና የምናብ ጥልቀት ተንፀባርቋል፡፡ በመድበሉ ውስጥ የቀረቡት ግጥሞች ምት ልክ ሆኖ መገኘትም ዜማው ስሙር እንዲሆን ረድቷል፡፡ ቀጥለው የቀረቡት ጥቂት ስንኞች ይህን ሐተታ በዋቢነት ያስረግጣሉ፡
እንደ ደብር መርገፍ፣ እንደ ጸናጽሉ
ወዲህ ወዲያ ብዬ፣ ወዳንቺ ተመለስኹ
አፈር ለሚበላው ላፈር ጦም እያደርኹ፡፡
እህል ውኃ ከወሰደኝ፣ ካፍሽ አፋፍ የነጠቀኝ፣
ቢመልሰኝ ላንቺ ማጀት …
ልሣለምሽ እንደ ደብር፣ ልስገድልሽ እንደ ታቦት፤
በዐይኔ ቅንድብ አመልክቼ፣ በአኮቴት ሥመለከት፣
ካድባር - ካውጋር፣ ሳውጠነጥን ያንቺን ሕይወት …
መኖርሽ በኗሪሽ ውስጥ ጠፍቶ አየሁት፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 21)
ወይዘሪት እምዬ! መሆንሽ ምን ነውሳ …?
ቀባሪ እንዳጣ ሬሳ፣ በሰው እንደተረሳ፣
ዳዋ እንደወረሰው እንደ ገበሬ ማሳ፤
ምላሱ ከላንቃው እንደተጣበቀ፣
ገላው እንደልብሱ በላዩ እንዳለቀ፣
በወንጭፍ ድንጋይ ምት እንደተሰበረ እንደበኩር እሸት፣
ሞት እንደተጸየፋት፤ ኑሮ እንዳቀለላት፤ ደካማ አሮጊት፣
ጎታታ፣ ዳተኛ፣ እንደጉፋያ ከብት፣
በሚታየኝ ኹነት፣ ይሁን ያንቺ ሕይወት?
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 22-23)
ማሳ ሲሆን እንቅልፋችን፣
ስንፍናችን ፍሬ አፍርቶ፤
ኩራት ሲሆን ብልግናችን፣
ትዕቢታችን አፍ አውጥቶ፤
ገድል ሲሆን ውርደታችን
ታ’ምር አይሆን ውድቀታችን፡፡
ለፍቅር ልብ ባንረታ፣
እንደ በሬ ጥልን ጠምደን፣
ለጦርነት ስንበረታ፤
ቀን ይነሣል፤ ዘመን ወድቆ፣
ሲደናበር ጊዜ ቃዥቶ፡፡
ለከንቱ አውድማ፣
… በባዶ ባድማ፤
ስንደክም ለሥጋ፣
ክረምት አልፈን በጋ፤
ነፍሳችን ብንገፋው፣ አድርገን እንዳይሆን
ካልተፈጠረ አነስን፣ ከሞተ ሰው ሳይሆን፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 94)
ጌራወርቅ ሥጋና ደምን ዘልቀው ስሜትን የሚሸነትሩ ቅኔያትን በመከየን የተካነ ልኂቅ ነው፡፡ የሐዘን ትካዜው የነፍስ ቅኝትን ያደፈርሳል፡፡ የፀፀት ኑዛዜው ልብ ያደማል፡፡ የፍቅር እንጉርጉሮው ማዕበሉ ያላጋል፡፡ የቁጭት እሮሮው ረመጡ ያጋያል፡፡ የኂስ ሾተሉ ኅሊና ያቆስላል፡፡ የመፃኢው ጊዜ ትንቢቱ በፍርሃት ያርዳል፡፡ ደም አንተክታኪ ሽለላው ፍም ያስጨብጣል፡፡
ጌራወርቅ ከሌሎች ባለቅኔዎች በበለጠ የውበት ምርኮኛ ነው፤ የፍቅር ተማላይ፡፡ የውበት ምርኮኛነቱ በሴት ቁንጅና ይገለጣል፡፡ በግጥሞቹ ውስጥ በምናብ ሥሎ ያቀረባቸው ሴቶች በአካል ቁመናቸው አምሣለ አማልክት ናቸው፡፡ ባለቅኔው በፍቅር ምርኮ ልደርላችሁ፣ ሠልጡኑብኝ የሚላቸው፣ ክሱት ምግባራቸውን እያወሳ የሚያወድሳቸው ሴት ገጸባሕርያትም እንከን የለሽ ሰብዕናን የተሸለሙ ናቸው፡፡ የሚከተሉት ስኝኞች ለእዚህ ዐሳብ ዋቢነት የቀረቡ ናቸው፡
የሚያስፈራስ! እንደመሸበር
የሚያስፈራስ! እንዳለማፈር
የሚያስፈራስ! እንደ ሲኦል መንገድ
አንቺን ለይቶ! ዐይቶ! አለመውደድ፡፡
ዐይንሽ አስደንባሪ፣ አፍንጫሽ አቀበት
ይጥላል ከንፈርሽ የጥርሶችሽ ውበት፤
መልክሽ እንቆቅልሽ ባገር የሚፈታ!
አንደበትሽ ቅኔ ግጥም በአንድምታ!
ልብሽ የመለኮት ምሥጢር የሚረታ!
አትገኝም እንጂ በዕድሜ ልክ ሱባዔ፣
አንቺን ያገኘ ነው፣ ፍቅር ማስመስከሪያ! የገነት ጉባኤ፡፡
ታምኖ እንደኖረ በጌታው ቤት ሲኖር
ለንጉሡ አስከሬን እንደሚሞት አሽከር፤
አልታደለም እንጂ አንቺን ሰው ሊያፈቅር!
አልመጠነም እንጂ ሰው አንቺን ለማፍቀር!
ተመርጦ! ተለይቶ! አንቺን ሰው ቢያፈቅር?!
ለጥላሽ ይሞታል እንኳን ላፍሽ ከንፈር፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 92-93)
እንኮይ የእንኮይ መሥክ መሣይ አበቄለሽ
ንጋት እያየሁሽ እጠላለሁ ሲመሽ፤
ወተት፣ ያጓት ፍሬ በሚያስንቀው ጥርስሽ
ሳልጠጣው፣ ሳልጎርሰው ብገድፍ በፈገግታሽ
ምን - ትዋብ? ስላቸው፣ ተዋበች እያሉ
ባርብ አፈር አልኩኝ ለቁንጅናሽ ቃሉ፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 102)
ዘቢብ - ዕጣን - ጧፍ ነው የደጅሽ አምኃ
አልማዝ የሚፈሰው ቀለመ ወርቅ ውኃ፡፡
አፍሽ ሥላሣየኝ የልብሽን ጸዳል
ገዳሙ፣ ገዳሙ ልበልሽ ሥራውባል
የሽፋልሽ ጽድቀት ከኃጢያት ያነጻል
የወደደሽ ወዶ ከሞት ይታረቃል፡፡
(ጌራወርቅ፣ 2015፡ገጽ 103-104)
እናርጅና እናውጋ እንደ ሀገር የተጣባንን ክፉ ደዌ በጥልቀት የሚዳስሱ፣ የዘመኑን መልክ የሚያሳዩ ግጥሞች የቀረቡበት መድበል ነው፡፡ በመድበሉ ገጣሚው የተንሻፈፈ አመለካከታችንን ኮንኖ፣ የእዚሁ እኩይ አመለካከታችን ዳፋ መጥፎ መሆኑን ነግሮናል፡፡
ባጠቃላይ፣ እናርጅና እናውጋ፣ ጌራወርቅ ሞጋች፣ አመራማሪ፣ ገሳጭና አስደማሚ ዐሳቦችን በምናቡ ሸምኖ በማቅረብ ውስብስቡን ኑባሬንና ልቡናችንን ባላየነው አድማስ በርብረን እንድንገነዘብ ያደረገበት ሸጋ መድበል ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራ በኪነት ሚዛን የከያኒውን ክህሎት መስክረን፣ ያለ ንፍገት ሥሙን በደማቅ ቀለም እንድንጽፍ የሚገፋ ነው፡፡
***
ከአዘጋጁ፦መኮንን ደፍሮ ልብ ወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር እና የማስተርስ ድግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ፍልስፍና አስተምሯል፡፡ ጸሐፊው ወደ ፊት ለህትመት የሚበቁ የተለያዩ የልብ ወለድ፣ የኢ-ልብ ወለድ እና የግጥም ሥራዎችን አዘጋጅቷል፡፡
ዝክረ - ነቢይ መኮንን
የእኛ ሰው በአሜሪካ
ከአዘጋጁ
አንጋፋው ገጣሚ ነቢይ መኮንን በአዲስ አድማስ ላይ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተነባቢነት ካስገኙለት ሥራዎቹ
መካከል “የእኛ ሰው በአሜሪካ” የተሰኘው ተከታታይ የጉዞ ማስታወሻው ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ነቢይን
በምናስታውስበት “ዝክረ- ነቢይ መኮንን” አምድ ላይ ህዳር 4 ቀን 1997 ዓ.ም የወጣውን “የእኛ ሰው በአሜሪካ” ለዛሬ
በድጋሚ አቅርበነዋል፤ ሥራዎቹን ለማስታወስ፡፡
የዚህን ሳምንት የእኛ ሰው በአሜሪካ በማጠናቀር ላይ ሳለሁ አንድ የዘወትር አንባቢያችንና ወዳጃችን የሚከተለውን ግጥምና ማስታወሻ ላከልኝ፡፡ እነሆ፡-
Gone are the days of youth
Upon torture, imprisonment & death;
Blurred were your futures
Along with the reachable skies
All these mess in your twenties
Withstanding the hardships;
Blocked were your Global trend
Darkening the bright cloud
Damn! The Ideological blade
That made y’r wisdom unfinished;
Lost are the ‘Jolly Jacks’
Along with their ‘bell-bottoms’
Except some within the states;
We are lucky having mirror
Which reveals us the Global sphere;
Kindness, despite all these
Feeding knowledge for the freed ones
Tikimt 22/97- by Bahiru Jemal
Dear Nebiy,
I dedicate the untitled poem exclusively for you & y’r passed away campus & prison – mates and also for your colleagues (friends) who live abroad.
Dear Nebiy,
I was extremely & uniquely touched by your travel story series on Tikimt 20,97 That’s why, I consider you as a mirror b/n your times & ours. But due to the holy month – Ramadan & some busy staff I was unable to contribute for so long. Any-way, I will keep in touch!
Wishing you all the best
ይሄ ወዳጃችን አብዛኛውን ጊዜ በእንግሊዝኛ መፃፍ ይቀናዋል፡፡ ግጥሙንም ማስታወሻውንም ከላይ እንዳያችሁት ነው የላከው፡፡ በግርድፉና በፍጥነት ለመተርጎም በመሞከር ለአንባቢያን እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡
ገና በለጋ እድሜ አለፉ እኒያ ቀናት
በሥቃይ በግርፊያ፣ በእሥራትና ሞት፡፡
ነበር ጭጋጋማ - ደብዛዛ ነገአችሁ
ሰማይ ርቆ ላይርቅ እየኖረ አብሯችሁ፡፡
ለግላጋው እድሜያችሁ፤ ገና ሃያን ሳይዘል
ላያችሁ አለቀ ያ ሁሉ ምስቅልቅል!
አላንበረከከ፤ አልፈታችሁ ገና
አልበገራችሁም መከራና ጫና፡፡
ብሩህ ሰማያችሁ ፊት-ገፁ ጨፍግጎ
ዓለም-አቀፍ ጉዞው እርምጃችሁ ታጥሮ
መንገዱ ተዘጋ፣ ዳመናው ታውሮ!!
ለአበባችሁ መርገፍ
ለጠቢባን ቅጭት - ለጥበብ መጨንገፍ
እኩዩ ምክንያት፤
ይረገም! ያ ሾተል፣
የአስተዋይ ሾተላይ፣ ያ የርዮት ስለት፡፡
ይረገም!
ወደቀ በጊዜው ከነወረት ስሙ
‘ጆሊጃክ’ አለፈ፣ ከ’ነቤል ቦተሙ’
ተረፈ-ጆሊጃክ በወሬ ሊነገር
አሜሪካ ሄዶ ከሰፈረው በቀር፡፡
ታድለናል ግና፣ እኛ አለን መስተዋት
ዓለምን የሚያሳይ፣ እኛኑ እሚከስት
ምን ቢከፋ አባዜው፣ መከራ እንግልቱ
አለ መስተዋቱ
ደግነት ያደለው፣ ካኖረው በወቅቱ
ያየውን የሚያሳይ በሩህሩነቱ
እውቀት የሚመግብ፣ ነፃ ለወጡቱ!!
ጥቅምት 22/97
እኔ፣ የፍሎሪዳው ወዳጄ እና ፍንዳታዋ ወንድሙ አንድ ሆቴል ተቀምጠን ከቢራው እየደጋገምን ሳለ እኛም እየሞቀን፣ ውይይታችንም እየሞቀው፣ እየደመቀ መጣ፡፡
“ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ጋዜጣ የለም አልሽ፣ ፍንዳታ?” ብዬ ጠየቅኋት፡፡
“ያለ ስለማይመስለኝ፡፡ እኔ እዛ እያለሁ ጥቂት ናቸው ያነበብኳቸው፡፡ እነሱም በጣም ተራ ናቸው”
“‘ተራ’ ስትይ ምን ማለትሽ ነው?”
“በቃ ምንም የሚጥም ነገር አጣበታለሁ”
“ባንቺ ግምት ብቁ የሚመስልሽ ጋዜጣ ምን መምሰል አለበት?”
“ሙድ ያለው መሆን አለበት፡፡ ስልህ፣ አለ አይደል Ethics ነገሩን (ሥነ-ምግባሩን) የሚጠብቅ፣ ደሞ Professional የሆነ (ሙያዊ ብቃት ያለው) ደሞ Design (አጠቃላይ ቅርፀ-ተውህቦ) ያስፈልገዋል፡፡ ንገራቸው የምታውቃቸው ካሉ በእናትህ፡፡ በጣም ሙድ- ያለው Design ያድርጉበት…”
ወዳጄ ታላቅ ወንድሟ እንደገና ትእግስቱ አለቀ፡፡ “ምን ’ሙድ ያለው፣‘ ’ሙድ ያው‘ ትላለህ? በትክክል ወይ በአማርኛ ወይ በእንግሊዝኛ ተናገር፡፡ ዝም ብለህ መካከል ቤት እየዳከርክ አታደናግር”
ፍንዳታዋ አቋርጣው እንዳልሰማ ቀጠለች፡፡
“እዚህ አገር ያየሁዋቸው ጋዜጦች ሁሉ ብታያቸው ያላቸው ዲዛይን ነፍ ነው (በርካታ ነው) ማለቴ መዓት አይነት ዲዛይን ነው ያላቸው፡፡”
“ግንኮ ፍንዳታ፤… ሥነ ምግባርም፣ ሙያዊ ብቃትም፣ ቅርፃዊ ጥራትም በኢትዮጵያ ደረጃ ያላቸውም ያሉ ይመስለኛል፡፡ ግን እንዳልሺው ለብዙ ጊዜ ብዙ ጋዜጣ ካላነበብሽ እድገቱም፣ ጥራቱም፣ ደረጃውም በቀላሉ ሊታዩሽ አይችልም፡፡ አንቺ ብቻ አይደለሽም ብዙ ትላልቅ ሰዎች አጋጥመውኛል በአሜሪካ፡፡ አንድ ጊዜ የፈረጁትን ነገር እንደያዙ ያሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ They are stuck in time ለማለትም ይቻላል፡፡ (ያኔ ከሚያውቁት ጉዳይ ጋር ተቆራኝተው አሁንም እንደዚያው የሚያስቡ)
ለማንኛውም እሺ፤ ለማውቃቸው አዘጋጆች እነግርልሻለሁ፡፡ እስቲ ከዚህ ትንሽ ወጣ ያለ ጥያቄ ልጠይቅሽ?”
“fine!” (መልካም ቀጥል፤ ማለቷ ነው)
“ለመሆኑ እዚህ ከመጣሽ ለቤተሰብ ሳንቲም ልከሽ ታውቂያለሽ?”
“አዎን… ግን ተጠንቀቅ ነቢይ፣ ወንድም ጋሼ እንዳይቀየምህ?” አለች፣ ሽርደዳዊ ሳቅ እየሳቀች፡፡
“ለምን ይቀየማል…”
ወንድም ጋሼ ጣልቃ ገባ በተራው፡፡
“ምን መሰለህ? ሁሌ እቺ ፍንዳታ ምን የምትለው ነገር አላት መሰለህ? ‘እነ ወንድም ጋሼ ይሄን ያህል አመት ኖረው የረባ ገንዘብ ሳይልኩ እኛ ‘ዲቪ’ዎቹ እናት አባታችንን በደምብ አድርገን Handle እናደርጋቸዋለን’ (እንንከባከባቸዋለን) እያለች ስትሞጣሞጥ አንድ ጊዜ ተጋጭቻት ነበር”
“ታዲያ እውነት አይደለም እንዴ?” አልኩት ነገሩን ለማስረገጥ፡፡
ይሄኔ ፍንዳታዋ ጣልቃ ገብታ፤
“እውነት ነው እንጂ -- Let me read you the fashionable poem about ‘Findata’. I don’t know the poet; ግን ሙድ ያለው ግጥም ነው፡፡ (ስለፍንዳታ የተገጠመ የአሁን ጊዜ ግጥም ላንብብላችሁ፡፡ ገጣሚውን አላውቅም) I have it here (ይቻትላችሁ) አለችና አንዲት የተጣጠፈች፣ ብዙ ጊዜ ያገለገለች የምትመስል ወረቅ አወጣችና ማንበብ ጀመረች፡-
ነባር - ነባሮቹ፣
“Oldie’s እና Senior” እየተባባሉ
አገረ-አሜሪካ አናስገባም አሉ፡፡
“እኔ በሱዳን ነኝ፣ እኔ በድንበር ነኝ
የዲቪ አደለሁም፣ ከነሱ አትደባልቁኝ”
እያሉ ቢኩራሩም፤
ወደ አገር ቤታቸው፣ ዱዲ ቤሳ አልላኩም፡፡
’ዲቪና ፍንዳታ‘ ተብሎ ሲታማ
’የማያድግ ጥጃ‘ ተብሎ ሲታማ
’ድክሞ ነገር ነው‘ ተብሎ ሲታማ
’ፖለቲካ አይገባው‘ ተብሎ ሲታማ
’አይማር አያድግ‘ ተብሎ ሲታማ
’ወጣት ዱሮ ቀረ‘ ተብሎ ሲታማ
አባቱን አሻረ የፈነዳውማ!!
ቤት ሰራ ለእናቱ ሳይሰርቅ ሳይቀማ፡፡
ሌት ተቀን ፈጋና በላብ በጉልበቱ
የዶላርን ምሥጢር አሳየ ለስንቱ”
ፈርማ የማይነበብ
መታሰቢያነቱ፡- ለተኛው አንጋፋና ዐይኑን ለገለጠው ፍንዳታ ቢሆን ብለን ሦስታችን ተስማማን፡፡
ፍንዳታዋ አንብባ ስትጨርስ እኔ አጨበጨብኩኝ፡፡ ፍንዳታዋ የቀኝ አውራ ጣቷን ቀስራ፤
“Thank you m-a-n!” አለች (አመሰግናለሁ ወዳጄ፤ እንደማለት)
ወዳጄ ፊት ላይ ግራ የመጋባት መንፈስ ነው የማነብበው፡፡ ምናልባት ፍንዳታዋ ያነበበችውን ግጥም በጥሞና አድምጬ ከማድነቅ ጀምሬ በማጨብጨቤም ጭምር ስለደገፍኩ ይሆን ግራ-ገብ መንፈስ የታየበት፡፡ በበኩሌ ፍንዳታ ሆና፣ የአሜሪካ ወግ ታክሎባት፣ ከኢትዮጵያ ባገኘችው የወረደ ነው በሚባለው የትምህርት ደረጃ መሰረቷ አንፃር፣ እንዲህ ለግጥም ስሜት ያዳበረች ወጣት ፍሎሪዳ ውስጥ ማግኘቴ፣ ልዩ ስሜት ነው የጫረብኝ፡፡ አንድ በጣም ግር ያለኝ ነገር ግን የፍንዳታዋ ታላቅ ወንድም ወዳጄ ግጥሙን ከእኔው እኩል እንደ አዲስ የሚሰማ መምሰሉ ነው፡፡ ይህንን ግርታዬን ላጠራ ወደ ወዳጄ ዞሬ፣
“ይህንን ግጥም ሰምተኸው አታውቅም ነበር ወይ?” አልኩት፡፡
“በጭራሽ” አለ ፍርጥም ብሎ፡፡
“ለምን?”
“አላነበበልኝማ!”
ፍንዳታዋ ለዚህ መልስ ይኖራታል በሚል ፊቴን ወደሷ መልሼ በጠያቂ አይን አፈጠጥኩባት፡፡
“Well, I haven’t had an opportunity like this” (እንዲህ ያለ አጋጣሚ አልነበረኝም)
“ምን ማለት ነው ይሄ?” አለ ታላቋ ትንሽ ረገብ ብሎ፡፡ ምናልባት በሆዱ ’መቼም ወንድም ጋሼ አይሰማኝም ብዬ ነው ማለቷ አይቀርም‘ ብሎ ሳይገምት አይቀርም፡፡
ፍንዳታዋ ቀጥላ፣
“You know Nebiy, till today, I also didn’t know ወንድም ጋሼ appreciates poetry let alone write one!” (አየህ ነቢይ እኔም እስከዛሬ ድረስ ወንድም ጋሼ ግጥም መጻፍ ቀርቶ ማድነቁን አላውቅም ነበር፡፡)
“እንዴ ታላቅና ታናሽ ወንድምም ተጠፋፍታችኋላ? ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ገጣሚና ፀሃፊ-ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በአንደኛው ቴያትሩ ላይ ’ከመርገምት ሁሉ የከፋው መርገምት፣ ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት‘ ይላል፡፡ እናንተ አብራችሁ እየኖራችሁ የተጠፋፋችሁበት ክፍተት አስገርሞኛል”
“እንግዲህ መገናኛችን አንተ ሆንክ ማለት ነው”
እኔም፤
“የፍንዳታዋ ነገር ያስገረመኝኮ ከምንጫወተው ጨዋታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ግጥሙን በቦታው ማስገባቷ ነው፡፡ በጣም rare ነው (አንዳንዴ ብቻ የሚከሰት) እንደዚህ ጨዋታና ግጥም ግጥምጥም የሚልበት ሁኔታ፡፡ ሁኔታዎች ቢመቻቹላችሁ ሁለታችሁ የምትገናኙበት ቦታ አለ፡፡ ፍፁም የሆነ ውህደትም ባይሆን እንደልብ የሚያወራጭ ድንበርና የጋራ ሜዳ አላችሁ፡፡ አንተም የፓብሎ ኔሩዳን ግጥም ላክልኝ፡፡ አንቺ ደግሞ ይቺን ስለፍንዳታና ስለነባሩ የአሜሪካ ስደተኛ በተናፅሮ የተፃፈች ግጥም አመጣሺልኝ፡፡ ይሄ እንግዲህ የእናንተ የመንታዎቹ የግጥም ባላባሊቾዎች መገናኛ ነጥብ ነው፡፡ እኔ ደግሞ እንደ ሦስተኛ ቅርንጫፍ ብጨመር ብዬ የላክልኝን የፓብሎ ኔሩዳን ግጥም ተርጉሜ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ ቆይተን እናነበዋለን”
“ኦ ምንም ቆይተን ምናምን ማለት የለም፣ ‘የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ’ ነው፡፡ አሁኑኑ ታነብልናለህ፤ በቃ ታነብልናለህ” አለና አፋጠጠኝ፡፡
ፍንዳታዋም፤
“እኔም ከወንድም ጋሼ ጋር ነው አቋሜ - Read us, while the discussion is still fresh m-an” አለች፡፡ (ውይይቱ ገና ትኩስ እያለ አሁኑኑ ብታነብልን ነው እሚሻለው)
እቺ ፍንዳታ ብዙ ጊዜ ቆይተው እንግሊዝኛውን እንደሚያውገረግሩትና እንደሚያወላክፉት አበሾች አይነት አይደለችም፡፡ ጥሩ እንግሊዝኛ አቀነባበርና ፍሰት ያለው አድርጋ ማውራት ትችልበታለች፡፡ በጣም ነው የምትገርመው፡፡ ያው ሌላው ስደተኛ ፈሊጥ እንዳለው ሁሉ፣ ሴቶች ጸጉራቸውን ካንዱ ወገን ወደ ሌላው በአንገታቸው ጎተት እንደሚያደርጉት አይነት፣ እሷም በወንድ ኩራት፣ ሪቫኗን በጭንቅላቷ ንቅናቄ ካንዱ ወደሌላው ወንጨፍ እያደረገች- “ማን” (man) የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ሚ-ያ-ን ብላ በቄንጥኛ ጎተት ታደርገዋለች እንጂ ጤና እንግሊዝኛ ትናገራለች፡፡
ወዳጄ በተጨማሪ ስለግጥም ንባቡ ማጠናከሪያ ሰጠ፡-
“በዛ ላይ ነቢይ አንተ ስታነበው ድምፅህ ውስጥ የሆነ ቃናና ለዛ አለው፡፡ ትዝ ይልሃል ዱሮ-‘ድምፁን እንዳልረሳው በናትህ ድገምልኝ‘ ስልህ፡፡ ’ድምፁን ነው እንጂ!‘ እልህ አልነበረም?”
ትንሽ አሽኮረመመኝ፡፡ አንዳንዴ አድናቆትን በፊት ለፊት መቀበል ባለመልመዳችን የተነሳ፣ ፊታችን ስማችን ሲነሳ አንዴ ጣራ አንዴ ምድር እያዩ መሽኮርመም ይቀናናል፡፡ በጣም የሚቸግር እንቅስቃሴ እንድናሳይ ያደርገናል- ያላለቀ ንድፍ ስዕል ያስመስለናል፡፡ ለዚህ ነው አበሻ ’እፊቱ ስለሆነ አይደለም!‘ ብሎ እሚጀምረው፡፡
አሜሪካ ግን እንደዛ አይደለም ያፋጥጣሉ፡፡
አነበብኩላቸው፡፡
ስጨርስ ፍንዳታዋ አጨበጨበች፡፡ ወዳጄም fantastic! (ድንቅ ነው) አለና፤
“ይገርማል የዱሮ ነገራችንን እንደገና ቀሰቀስክብኝ፡፡ እዚህ ከመጣሁ እንደዚህ አይነት ምሽት አምሽቼኮ አላውቅም ባባትህ!”
“ኦ እንዲያውም አንድ ነገር አስታወስከኝ፡፡ እኛ እዛ ሞተሃል እያልን ስናማህ እንዴት ተረፍክ? አልነገርከኝም’ኮ”
“ታሪኩ ረጅም ነው፡፡”
“ግዴለም ባጭሩ ንገረንና እኔም ብዙ ሳይመሽብኝ ወደ ሆቴሌ ልሂድ!”
“መልካም”
ታላቁ ከያኒ ነቢይ መኮንን የተዘከረበት ምሽት
ታላቁን ሁለገብ ከያኒና የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረውን ነቢይ መኮንንን ለማክበርና ለማመስገን ታልሞ የተዘጋጀው፣ “ዝክረ ነቢይ መኮንን”፣ ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት በዋቢሸበሌ ሆቴል፣ የኪነት አድናቂዎችና የጥበብ ቤተኞች ይገኙበታል በታደሙበት በውበትና በድምቀት ተከናውኗል።
አዲስ አድማስ ባዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ጋዜጠኞችና ደራስያን እንዲሁም የሥነ-ጽሁፍ ባለሙያዎች ስለነቢይ መኮንን የሚያውቁትን መስክረዋል- ገጠመኞቻቸውን አጋርተዋል።
አንጋፋው የማስታወቂያና ፊልም ባለሙያ አርቲስት ተስፋዬ ማሞ፣ መድረኩን በጥበባዊ ለዛ እያዋዛ የመራውና ያጋፈረው ሲሆን፤ እርሱም በወዳጅነት ለረዥም ዓመታት ስለሚያውቀው ነቢይ መኮንን በየአፍታው ለታዳሚው አውግቷል- መድረኩንም በራሱ በነቢይ ግጥሞች አድምቆታል። ተስፋዬ ለምሽቱ ታዳምያን ካቀረባቸው ግጥሞች መካከል ነቢይ በ1997 ዓ.ም ወደ አማርኛ የተረጎመው የገጣሚ አንድሬ ቼዲድ ግጥም ይገኝበታል። “ይታያችሁ” ይላል ርዕሱ።
ይታይችሁ
ይታያችሁ እስቲ…
ያ ሰፊ ውቅያኖስ፣ እንደ ፅጌ ደርቋል፤
እንደ አበባ ጠውልጓል።
የዛፉም ቅርንጫፍ ከችሮ በድኗል
የወፍ ማረፊያ እንኳን፣
መሆን አቅቶታል።
ይታይችሁ ግና፤
ከአድማስ ወዲያ ማዶ፤
ሞት ከስቶ ገርጥቶም
የሟችን ትንሳኤ፣
ዳግም ሲያለመልም!
በዚህ “ዝክረ- ነቢይ” መርሃ ግብር ላይ ነቢይ መኮንን ብቻ አይደለም የተከበረውና የተዘከረው። ከዓመታት በፊት ህይወቱ ያለፈው ባለራዕዩና የአዲስ አድማስ ጠንሳሹ አሰፋ ጎሳዬም በትላልቅ ሃሳቦቹና እውን በሆኑ ሥራዎቹ፤ እንዲሁም በውብ ሰብዕናስ ተደጋግሞ ተነስቷል- ተወድሷልም። ነቢይን ሲያነሱ አሰፋ ጎሳዬን አለማንሳት አይቻልም። ሁለቱም የአዲስ አድማስን እንቁዎች ነበሩ። ነቢይን፣ አሰፋን፣ አዲስ አድማስን ብዙዎች በአንድ ላይ ነው የሚያውቋቸው።
ለዚህም ነው ስለነቢይ ለመናገር መድረክ ላይ የወጣው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ፣ መግቢያው ላይ በስፋት ስለ አሰፋ ጎሳዬ ያወሳው ትዝታዎቹን ያነሳው። በቅጡ ተዘጋጅቶ የመጣበት ጉዳይ በመሆኑ ግን ወደ ነቢይ በቀላሉ ለመሸጋገር አልከበደውም። እናም እርሱ የሚያውቀውን ነቢይ መኮንን ለታዳሚው አስተዋውቋል”… ነቢይ በጣም ሰው ይወዳል፣ የተማረ ነው፣ መሃይም ነው ሳይል አጠገቡ ካለው ጋር ያወራል፣ ይጫወታል፣ የምታስቡትን ይጋራል። ይሄ የአንድ ትልቅ ደራሲ ባህርይ ነው። … ነቢይ ሲተርክልህ ጥሩ የማድመጥ ብቃት ያስፈልግሃል… ከፍተኛ ኢነርጂ ከሌለህ… ወራጅ ነው የምትሆነው…. ይበዛብሃል…. ይጠልቅብሃል…. የመገንዘብ አቅምህ እዚያ ጋ ካልደረሰ፣ ትፋታለህና ጥሩ አድማጭ መሆን ይፈልጋል…” ብሏል።
ዘነበ ወላ፤ ነቢይ በደርግ ዘመን ያሰቃዩትና የገረፉት እንዲሁም በወህኒ ቤት ዓመት በእስር ያጉሩት ባለስልጣናት ላይ ቂም እንዳልያዘና አንዳንዶቹን ሲያገኛቸውም እንደሚወራቸው በመግለፅ፤ “ነቢይ በጣም ይቅር ባይና ሆደ-ሰፊ ነው” ሲል አድናቆትን ቸሮታል። እውነቱን ነው። ዘነበ ጥሩ አስተውሏል። ነቢይ እንኳን የደርግ ሹመኞችንና ገራፊዎችን ቀርቶ ራሱን ሥርዓቱን- ደርግን ሲረግምና ሲያወግዝ ተሰምቶ አይታወቅም። ነቢይ ማለት በአጭሩ በየሳምንቱ በአዲስ አድማስ ላይ ሲጽፋቸው የኖራቸው ርዕሰ አንቀጻት ማለት ነው። (ከዚህ የተለየ ነቢይ እኔ በበኩሌ አላውቅም) ፅንፈኝነትና ጨለምተኝነት አያውቀውም። እርግማንና ውግዘት ውስጥ የለበትም።
ሁሌም ብሩህና ተስፈኛ ነው- ነቢይ መኮንን። ግጥሞቹም በአብዛኛው የሚያንፀባርቁት ብሩህ ተስፈኝነትን ነው።
ወደ ዝክረ-ነቢይ መኮንን እንመለስ። ሌላው በመርሃ ግብሩ ላይ ምስክርነቱን የሰጠው ደግሞ የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ነበር። በነገራችን ላይ ጥበቡ ዘንድ ደውዬ በዝግጅቱ ላይ ስለነቢይ እንዲናገር ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ፡- “እርሱ በተጠራበት ሁሉ ሲሄድ አይደል እንዴ የኖረው፤ ኧረ እመጣለሁ፤ ይኼ የሁላችንም ሃላፊነት ነው።” የሚል ርዕስ ነበር። ጋዜጠኛ ጥበቡ ነቢይን በሁለት መልኩ ነው አንስቶ ያስታወሰው፣ ያከበረው፣ ዘከረው። አንደኛው ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነ ነው። ሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ ላይ ከህልፈቱ በፊት በተናዘዘው መሰረት፣ ስዕሎቹን ከጀርመን ሙኒክ ወደ አዲስ አበባ የማስመጣት ፕሮጀክት ተቀርጾ ነበር።
ስዕሎቹን ለማስመጣት ሎቢ ይደረግ ነበርና ለዚያ ዝግጅት ተካሂዶ ነበር። ታዲያ የዝግጅቱ ጥሪ ላይ የሚለው “ገጣሚና ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ” ነበር። ይኼኔ ሰዓሊያኑ እነ በቀለ መኮንንና እነ እሸቱ ጥሩነህ ለገብረክርስቶስ መቅደም ያለበት ሰዓሊነቱ ነው በሚል “ሰዓሊና ገጣሚ” መባል አለበት ብለው መከራከራቸውን ያስታውሳል፣ ጋዜጠኛ ጥበቡ። በዚህ የተነሳ ቤቱ ለሁለት ተከፈለ፣ “ገጣሚነቱ ነው የሚቀድመው ወይስ ሰዓሊነቱ” በሚል። በዚህ መሃል አሁን በህይወት የሌለውና በሥነ-ግጥም ላይ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ያደረገው የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያው ብርሃኑ ገበየሁ፤ “እንደውም ገብሬ ሙዚቀኛ ነው፣ ዘፋኝ ነው” ብሎ ግጥሞቹን በዜማ ማቅረብ ጀመረ። ከዚያ ደግሞ ነቢይ መኮንን የተለየ ሃሳብ ማቅረቡን ይገልፃል- ጥበቡ።
“እናንተ ገጣሚም በሉት ሰዓሊም በሉት ሙዚቀኛም በሉት… ገብረክርስቶስ ደስታ ግን የሳይንስ ሰው ነው” ብሎ ስዕሎቹን ከሳይንስ አንፃር ተነተናቸው። ለምሳሌ፡- ቀራኒዮ… የኢየሱስን ስቅለት በደም ብቻ የሳለውን…በማንሳት ሳይንስ ነው፤ የባዮሎጂ ባግራውንድ ስላለውነው…አለ። ባዮሎጂ ስለተማረ የኢየሱስ ክርስቶስን ስዕል በደሙ ነው የሳለው… ብሎ በማስረጃነት አቀረበ። ከዚያ ደግሞ የባህር ቅርድዶች የሚለው ግጥም… አንድ ድንጋይ አንስተን የሆነ ባህር… ወይም ውሃ ላይ ስንወረውር… እንደዚህ የሚሄዱ ሞገዶች አሉ…. ስለነሱ የገጠመው… የሳይንስ ሰው መሆኑን ነው የሚሳየው… በሚል ግጥሞቹን…. ስዕሎቹን ከሳይንስ አንፃር በደንብ ተነተናቸው…. ሲል አውግቷል። ይኼም ራሱ ነቢይ የኬምስትሪ ተማሪ፣ ኬሚስት ስለነበር… ሁለቱ…. ነቢይና ገብረክርስቶስ በጣም የሚያይዝ የራሳቸው ባክግራውንድ… ከሳይንስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያሳየበት ነውና… በዚያ ዝግጅት የገብረክርስቶስ ስዕሎች ወደ አገር ቤት እንዲመጡ በጣም ትልቅ አስተዋፅኦ ካደረጉ……. (እነ በቀለ መኮንን ጨምሮ) አንዱ መሆኑን በማውሳት፣ ብዙም የማይታወቀውን የነቢይን አበርክቶ አጉልቶ አሳይቷል- ጥበቡ- በለጠ።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በዚህ ብቻ አላበቃም። ነቢይን ከአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅነቱ አንፃርም ያበረከተውን አስተዋፅኦ አፅንኦት ሰጥቶ አንስቶታል። ጥበቡም እንደ ዘነበ ሁሉ ታዲያ፣ አሰፋ ጎሳዬን ከአዲስ አድማስና ከአጠቃላይ የጋዜጠኞች ህትመት ጋር አያይዞ አውስቶታል- አወድሶታል። አስገራሚው ግጥምጥሞች ሁለቱ የአዲስ አድማስ እንቁዎች በዚህች ምሽት በአንድ ላይ መዘከር መወደሳቸው ነው። በዕቅድ ሳይሆን በአጋጣሚ፤ በአዘጋጆቹ ፍላጎት ሳይሆን በተናጋሪዎቹ የልቦና ፈቃድ! ግሩም ነው በዝክረ- ነቢይ መርሃ ግብር ስለነቢይ የተናገሩትና የመሰከሩት ሁለቱ ብቻ አልነበሩም። ሰዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንን፣ የሥነ-ፅሁፍ ባለሙያው ባዩልኝ አያሌው።
ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ልጅ- ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የፊዚክስ ፕሮፌሰሩና የነቢይ ወዳጅ ዶ/ር ሙሉጌታ…፣ አንጋፋው ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ… ገጣሚ ነቢይን ከታዳሚዎቹ ጋር በህብረት ዕፁብ ድንቅ ነው። የነቢይ ነፍስ በሃሴት ጮቤ ትረግጣለች ብዬ አምናለሁ የአሰፋም ጭምር።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ሃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ሃላፊዎች በሙስናና በሃብት ምዝበራ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሃላፊዎች መካከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሀብታሙ አበበ እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ታምራት ታገሰ ይገኙበታል።
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ለአንድ የዩኒቨርስቲው የፋይናንስ ቡድን መሪ የ790 ቀናት አበል እንዲሁም ለሌላኛው የፋይናንስ የቡድን መሪ ደግሞ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ የ1,469 ቀናት (1,056,854 ብር) አበል እንደተከፈላቸው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በዩኒቨርሲቲው የሀብት ምዝበራ ላይ አተኩሮ በሰራው የምርመራ ዘጋቢ ፊልም ላይ ማቅረቡ ይታወሳል።
በተጨማሪም የዩኒቨርስቲው ፋይናንስ ሳያውቅ 1.4 ቢሊዮን ብር ለኦክስጅን ማምረቻ በሚል በህገወጥ መንገድ መንቀሳቀሱንና ፍቃድ የሌለው የኮንስትራክሽን ድርጅት ግንባታውን እንዲሰራ ያለ ጨረታ እንደተሰጠው በምርመራ ውጤቱ ተገልጿል። በዚህ የተነሳ ዛሬ አመራሮቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል::
አራተኛው ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ
ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለአራተኛ ጊዜ በትናንትናው ዕለት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል። የ15 ኪሎሜትር የሩጫ ውድድርን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ስፖርታዊ ፍልሚያዎች ተደርገዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒሰቴር የስፖርት ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በውድድሩ ላይ ተገኝተዋል። መነሻውን ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ባደረገው ውድድር ብርቱ ፍልሚያ እንደታየበት ለማወቅ ተችሏል።
ሚኒስትር ደኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት "እንደኬሮድ መሰል የሩጫ ውድድሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። በዚህ ውድድር ያሸነፋችሁ እና የተወዳደራችሁ አትሌቶች ጠንክራችሁ ቀጥሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ምስጢሩ ሕብረ ብሔራዊ አትሌቶችን ማግኘቱ ነው። በሁሉም አቅጣጫ እንደእነዚህ ዓይነት ውድድሮች መካሄድ ይኖርባቸዋል።" በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም ለኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር አዘጋጆች ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
የኬሮድ የስፖርት እና የልማት ማሕበር ቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ተሰማ አብሽሮ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች እና ተወዳዳሪ አትሌቶች በውድድሩ በማሳተፋቸው ምስጋናውን ገልፆ፤ "ኬሮድ ሩጫ በቡታጅራ፣ ወራቤ እና ሆሳዕና በተለያዩ ክልሎች ላይ ውድድሩን ለማዘጋጀት ዕቅድ አለው። የኬሮድ ዓላማ ሰላምን መስበክ ነው። ሕብረተሰቡ ሊደግፈን ይገባል።" ሲል ተናግሯል። የፓሪስ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለሆኑ አትሌቶች መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
በአንድ ኪሎሜትር የዊልቸር ውድድር በሴቶች፤ አንደኛ አብነት ጌትነት የወርቅ ሜዳልያ እና 5 ሺህ ብር፣ ሁለተኛ እምነት ከበደ የብር እና 3 ሺህ ብር፣ ሶስተኛ ሰዓዳ አብደላ የነሐስ ሜዳልያ እና 2 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ሆነዋል። በወንዶች ውድድር ደግሞ፣ አንደኛ አቡበክር ጀማል የወርቅ ሜዳልያ እና 5 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ ዳዊት ዮሴፍ የብር ሜዳልያ እና የ3 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ዳንኤል ዲባባ የነሐስ ሜዳልያ እና የ2 ሺህ ብር ሽልማት ተሸላሚዎች መሆናቸው ታውቀዋል።
በ15 ኪሎሜትር የሴቶች ሩጫ ውድድር አንደኛ መብርሂት ግደይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወርቅ ሜዳልያ እና የ100 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ መቅደስ ሽመልስ በግል የብር ሜዳልያ እና የ50 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ኑኖ ሻንቆ ከኦሮሚያ ፖሊስ የነሐስ ሜዳልያ እና የ25 ሺህ ብር ተሸላሚዎች ለመሆን በቅተዋል። በወንዶች ደግሞ፣ አንደኛ ጨምዴሳ ደበላ በግል የወርቅ ሜዳልያ እና የ100 ሺህ ብር፤ ሁለተኛ ዘነበ አየለ ከዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብ የብር ሜዳልያ እና 50 ሺህ ብር እና ሶስተኛ ጂግሳ ታደሰ በግል የነሐስ ሜዳልያ እና 25 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
እንዲሁም አሸናፊ አትሌቶች ለወከሏቸው የስፖርት ክለቦች የዋንጫ ሽልማት ከውድድሩ የክብር ዕንግዶች እጅ ተቀብለዋል።
"ለኢትዮጵያ ሰላም እሮጣለሁ" በሚለው የዘንድሮው የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በተጨማሪነት የሕዝባዊ ሩጫ ውድድር እንደተካሄደና ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡ ተሳታፊዎች ሜዳልያ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።