Administrator

Administrator

ባለፈው ሳምንት የብራሰልስ/የቤልጂየምን ብርድ ለመቋቋም ሬስቶራንት ፍለጋ ዞረን፣ አንዲት መካከለኛ ሬስቶራንት አግኝተን እየተረጋጋን ሳለን ነበር ጽሁፌን ያቆምኩት። ከዚያው እንቀጥላለን።
በነገራችን ላይ ከዛ በፊት ስላጋጠሙኝ ሁለት ነገሮች ልንገራችሁ።
1ኛው/ አንድ ወጣት ሚኒባስ ላይ አግኝቶኝ ተዋወቀንና፣ “የኛ ሰው በአሜሪካ አልቆ ነወይ፤ የኛ ሰው በብራሰልስ የጀመርከው?” ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “አይደለም ባለኝ የውጪ ማስታወሻ ላይ ተጨማሪ ስላገኘሁ ነው። ከዚህ ቀደም የሄድኩበትን ማስታወሻዬ ላይ ስላሰፈርኩት የት ይሄድብናል? ዕድሜውን ይስጠን እንጂ እናነበዋለን” አልኩት። “እንዲህ ከሆነማ ሁልጊዜ በየአገሩ በወሰዱህ አሪፍ ይሆንልን ነበር” አለ።
“ኢትዮጵያዊ የሌለበት ቦታ ከወሰዱኝ ነው ጉዱ!”
“ኢትዮጵያዊ የሌለበት ቦታ ፈጽሞ የለም! ጨረቃ ላይም አለ” አለኝ ኮስተር ብሎ፤ ነገር -ዓለሙ ገርሞኛል።
“እዛስ በምንም መንገድ ለመሄድ የምችል አይመስለኝም” ስለው፤
በጣም ፍርጥም ብሎና በተመስጦ፤ “ግዴለህም ነቢይ፤ አንድ ቀን ዲቪ ይደርስሃል!” አለኝና የመጨረሻ አሳቀኝ። ወጣቱ ከታክሲው ወርዶ ሲሄድ በማያዩ አይኖች እያየሁት ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄው ዲቪ መሆኑ ገረመኝ። የሐሳባችን ውሱንነት ሀሳብ ውስጥ ከተተኝ። ገጣሚ ፀጋዬ ገ/መድህን መንፈሴ ውስጥ ገባ- በከርሞ ሰው በኩል።
“… ምኞቴ እንደ ጉም መንጥቃ
ተስፋዬ እንደ ጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ ለርስታቸው ሳላበቃ
የኔ ነገር በቃ በቃ!!”
2ኛው/ አጋጣሚ
እንደዚሁ ታክሲ ውስጥ ነው። ልጆች ሲጨዋወቱ፤
አንደኛው “አይዞህ እኔ አሜሪካ ስሄድ፣ እኔ ነኝ ያለ ስኒከር፣ እልክልሃለሁ!!” ደሞ ትንሽ ተጫውተው፣
“እኔ አሜሪካ ስሄድ የቀወጠ ጃኬት እልክልሃለሁ!!” ይለዋል። እንዲሁ እያለ “እኔ አሜሪካ ስሄድ”ን ቀጠለ። “እኔ አሜሪካ ስሄድ…” ብሎ እንደገና ሊጀምር ሲል ጓደኝዬው አቋረጠውና፤
“ቆይ ኧረ፤ እኔ አሜሪካ ስሄድ፣ ይህን እልክልሃለሁ፣ ይሄን እሰድልሃለሁ የምትለው፣ እኔ ዋሊያ ነኝ፤ ቀይ ቀበሮ ነኝ… ወይስ መለስ ነኝ፤ ወደ አሜሪካ የማልሄደው?”
“አይ!! አንተ እንኳን ወደ አሜሪካ የምትሄደው ወይ “ከቦሌ ዲሲ” የሚሠራ ሚኒባስ ጀምሮ ወያላው “ዲሲ! ዲሲ!” እያለ ሲጠራ ካጋጠመህ፤ አለበለዚያ ኢትዮጵያ ራሷ ዲቪ ሲደርሳት ነው!” አለውና ተሳሳቁ።
ሦስት ነገር ገረመኝ። አንደኛው ሚኒባስ ላይ ሆነው የሚኒባስን እድገት አስበው ከቦሌ ዲሲ ስለሚለው ሚኒባስ ማሰባቸው ነው። ሁለተኛው መለስን እንደ ብርቅዬ እንስሳ ሲጠቅሰው፤ እንኳን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ መሥሪያ ቤት ዘበኛም የሚያወራ አለመምሰሉ ነው። ሦስተኛው ለኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ዲቪ መመኘታቸው ነው።
***
የሬስቶራንቱ ዋጋ አስፈሪ አይደለም። ሁለት ትላልቅ ሳንድዊች መጣልን። እርቦን ስለነበር እየተስገበገብን ሳንበላ አልቀረንም። ሁለታችንም የምንበላው አትክልቱንም፣ ስጋውንም ከውስጥ እየቦጠቦጥን ነው። ገርበብ ብለን ቀና ስንል አብሮኝ የሚመገበው ተጓዥ ወዳጄ፡-
“እኔ የምልህ?” አለ
“እ!”
“ይሄ ምግብ በሁለት ሳህን ለምን መጣ?”
“እንዴት በሁለት ሣህን?”
“ይሄው አንደኛው ሳህን” አለና ምግቡ የቀረበበትን ሳህን አሳየኝ።
ቀጥሎ ደግሞ!
“ይሄው ሌላው ሳህን” ብሎ ሁለተኛውን ሳህን አሳየኝ። ሁለተኛው ሳህን ብሎ ያሳየኝ አንድ ጥርብ እንጨት ሁለት ላይ ተሰንጥቆ ማህሉ ስጋና አትክልት የተደረገበት የሚመስለውን ትላልቅ ዳቦ ነው ለካ። ዕውነትም ሁለታችንም ዳቦውን እንደ ዳቦ ሳይሆን እንደ ምግብ ማስቀመጫ ነው ያየነው- ሳናውቀው።
በጣም ተሳሳቅን።
ለማንኛውም ከርሃብ እፎይ ብለን ቢራችንን መጠጣት ቀጠልን። “እስቲ እንግዲህ ደግሞ ሌላ ቢራ ቤት ዘወር ዘወር ብለን እንመልከት” አለኝ ጓደኛዬ። ከፈለና ወጣን። እዚያው የብርድ ግግር ውስጥ ጥልቅ አልን። ጀመረን ብርዱ። ግን እንደ መጀመሪያው አይደለም። “ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል” ወደሚለው አንድረስ እንጂ ብርዱን የመልመድን፤ መንገድ መንገዱን ጀምረነዋል።
የዚያን ዕለት በቤልጂየም አንድ ያስገረመን ነገር ፀጥታው ነው። ሰው ወዲያ ወዲህ አይልም። ቀኑ ቅዳሜ ነው። መቼም ሰው በቅዳሜ ምድር እቤቱ ክትት አይልም የሚለው የኢትዮጵያ አዋዋል ግምታችን እዚህም ተከትሎን መጥቶ ነው መሰለኝ። ብቻ ጭር ጭው ብሏል። ያ ስንመጣ ነው።
አሁን ግን ቢራ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ማለት ስንጀምር ሰው ማየት ጀመርን።
“ምናልባት የምሳ ሰዓት ቢሆን ነው ጭር ያለው” አልኩት ለጓደኛዬ።
ጓደኛዬም- “ነው ብለህ ነው? ሁሉም፣ እንዲህ ክትት እስከሚል ድረስ deserted (ሰው የት ይሄዳል) ይሆናል ብለህ ነው ታዲያ?”
እናም- “ይመስለኛል። ሌላ ምን ምክንያት ትሰጠዋለህ ታዲያ? በብራሰልሱ የስብሰባ ፕሮግራማችን ላይ እንኳ በደምብ ብታስተውለው ቅዳሜና እሁድን በጥንቃቄ ነው የዘለሏቸው። ስለዚህ የእረፍት ቀንነቱን ኮስተር ብለው ቢያምኑበት ነው”
“እስቲ እናያለን” አለ ጓደኛዬ።
አንድ ሬስቶራንት ገባን። ቤቱ ከቅድሙ ተለቅ ያለና ግርማ-ሞገሱም ገዘፍ ያለ ነው።
“ቢራ” አልኩኝ።
“ምን ዓይነት ቢራ?” አለ አስተናጋጁ።
“እንግዲህ ገና በስም አናውቀውም- ቅድም የጠጣነው “ሜዝ” ይሁን “ሜስ” በደንብ አላወቅነውም እንጂ እሱን ብናዝ ጥሩ ነው” አልኩኝ።
“Do you have some light beer?” አለ ጓደኛዬ። (ቀለል ያለ ቢራ አላችሁ እንዴ? እንደ ማለት ነው)
“We have many types of birr! Something like 400 what do you want?...”
(ብዙ ነው ያለን! 400 ገደማ የተለያዩ ዓይነት ቢራዎች አሉን፤ የትኛውን ፈለጋችሁ?)
“የሰማያቱ ያለህ!” አልኩኝ በሆዴ። 400 ዓይነት ቢራ?!
ጥቂት ቆየት አለና ጠየቀን። “Shall I bring you maes?” (ሜስ የሚባለውን ላምጣላችሁ? ማለቱ ነው)
እንግድነታችን ገብቶታል።
“አዎን” አልኩኝ ወዲያውኑ!
“ይቺ ከላፍቶ ክፍለ ከተማ የማትበልጥ ከተማ እንዲህ ትጫወትብን?” አለ ጓደኛዬ። ተሳሳቅን።
“ምን ታደርገዋለህ? ሁሉም ነገር እንዳገሩ እንድትሆን ይወስንሃል”
“This is maes!” (ይኸው “ሜስ”!) አለ አስተናጋጁ። ድምፁ ውስጥ ያለው ልበ-ሙሉነት ሲታይ፤ ራሱ የጠመቀው ነው የሚመስለው።
“ራሱ ነው!” አልኩኝ አንዴ ተጎንጭቼ። እየተጎነጨን ጨዋታ ያዝን።
ተጨዋውተን፣ ጠጣጥተን ስናበቃ ወደ ሆቴላችን ሄደን አራተኛውን ጓደኛችንን፤ከፍራንክፈርት ዘግይቶ የሚመጣውን ማለት ነው፤ ልናገኘው አስበን መንገድ ጀመርን።
እኔ ሁሌ የምከራከርበት “ሁሉ አገር አዙሪት አለው” የሚል ሙግት አለኝ። አንዳንድ ወዳጆቼ አይቀበሉኝም። እኔ የናዝሬት ልጅ ነኝ። የናዝሬት ልጆች፣ ናዝሬት አዙሪት አለ ብለን እናምናለን። አዙሪት ማለት እንዲህ ነው።
ወደ አንድ ምንም ከዚህ ቀደም አይታችሁት ወደማታውቁበት ቦታ ሄዳችኋል እንበል። ባንዱ ቅያስ ሄዳችሁ ስታበቁ ተመልሼ ያንኑ ቅያስ አገኛለሁ ብላችሁ ስትመጡ፣ ምኑም ምኑም ያንን ቅያስ የሚመስል አንድ መንገድ ታገኛላችሁ። በእርግጠኝነት “ጎሽ አገኘሁት!” ብላችሁ ትገቡበታላችሁ። ትንሽ እንደሄዳችሁ ፍፁም ያንኑ ቅያስና መንገድ የሚመስል ታገኛላችሁ። ሊዞርባችሁ ይጀምራል። ትመለሳላችሁ። በቃ የአዙሪቱ ቀለበት ውስጥ ገባችሁ ማለት ነው። ያደረጋችሁት ምልክት የጠፋችሁ ይመስላችኋል። ሰው ልጠይቅ ብላችሁ አላፊ- አግዳሚ መማተር ትጀምራላችሁ። አንዱን አግኝታችሁ፡-
“እባክህ አንድ ነገር እርዳኝ?” ትሉታላችሁ። ደግ ሰው ከሆነ “ምን ልርዳህ? ምን ፈለግህ?” ይላል።
“እንዲህ እንዲህ የሚባል ቦታ ነበር የምፈልገው። ከዚህ ምን ያህል ይርቅ ይሆን?”
“ It is right behind you…or it is right in front of you there, across the road” ይላችኋል።
(ይኸው ከጀርባህ’ኮ ነው ያለው…ወይ ያው ፊት ለፊትህ መንገዱን ተሻግሮ’ኮ ነው)
ብሎ ወጣቱ ይጠቁማችኋል። ይሄ ዐይናችሁ ስር እያለ የሚጋርድባችሁ፤ ሲያዞር ሲያንቀዋልላችሁ የሚውለው ነገር ነው እንግዲህ “አዙሪት” የሚባለው። ቅድም እንዳልኩት በናዝሬት ልጅነት የማውቀው አዙሪት የቅያሶቹ መመሳሰል፣ የቤቶቹ ቅርፅና ዕድሜ አንድ መሆን፣ ከጠራራዋ የናዝሬት ጸሐይ ጋር ተደምሮ ናላ ይነካል፤ ብዥ-ድንብር ያደርጋል። ብዙ ሰው ይዞርበታል። ያ ነው እንግዲህ አዙሪት የሚሆነው። በተጨማሪም እንደ አገሬው እምነት “ቆሌዋ ሳትወድድህ ስትቀር ነው” የሚባለውም አለው። ያ በመጠኑ ወደ ዕምነታዊው አቅጣጫ ያመራናልና ለሌላ ጊዜ ልተወው።
ከሬስቶራንቱ ተመልሰን ወደ ሆቴላችን በሰላም እንዳንገባ የቤልጅንግ አዙሪት በዬት በኩል! ዞረን እዛው! ሄደን ሄደን እዛው! ብዙ ከተንገላታን በኋላ
“ያው ሆቴላችን!” አለ ወዳጄ።
በራሳችን ሳቅን። ልክ ወደ ሆቴላችን ልንገባ ስንል ከኋላችን አንድ ድምጽ ጓደኛዬን ጠራው።
ጓደኛዬ ዘወር አለ። የሚያውቀውን ሰው አግኝቶ ነው ብዬ እኔ በቀስታ ወደፊት ሳመራ ጓደኛዬ ጠራኝና፤ “ና እንጂ አትተዋወቁም እንዴ?” ብሎ መተዋወቅ ወደ አለብኝ ሰው በአይኖቼ አመላከተኝ።
ሰውዬውን በአካል አግኝቼው ባላውቅም ብዙ ቦታ አይቼዋለሁ። በቴሌቪዥንማ ሁሌ አለ።
ተጨባበጥን። ከሀገራችን የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች አንዱ ነው! ከጓደኛው ጋር ነው።
ጓደኛዬ በመገረም፤ “እንዴ እዚህ ነው እንዴ ያላችሁት?” አለና ጠየቀው።
“አዎ እዚሁ ሰንብተናል፤ ለስብሰባ መጥተን ነው” አለ መሪው
“ትቆያላችሁ?”
“የለም ዛሬ ማታ ወደ እንግሊዝ እሄዳለሁ። እዚያ አንድ ቀን አድርና ለአንድ ሳምንት አሜሪካ እሄዳለሁ”
“ምን ለመስራት ነው የምትሄዱት?”
“ያው lobby ለማድረግ ነዋ!” (ለመቀስቀስ ማለቱ ነው።)
ከተለያየን በኋላ ጓደኛዬ፤ “የዓለም ጠባብነት አይገርምህም። ከእነዚህ ሰዎች ጋር እዚህ እንገናኛለን ብለህ ታስባለህ አሁን?!” እውነትም እኛ ኢትዮጵያ ጥለናቸው የመጣን መስሎን ነበር፤ ለካ እነሱ ናቸው ጥለውን የመጡት።
“The world is a village nowadays man!`”
(ዛሬ ጊዜ ዓለም እንደ መንደር ጠባለች ወዳጄ!) የነገ ፕሮግራማችን ብራሰልስን በአስጎብኚ እየዞሩ ማየት ነው። የነገ ሰው ይበለን።
***
(አዲስ አድማስ፤ ሚያዝያ 1 ቀን 1997 ዓ.ም)

አንድ በሠፈር ውስጥ በጀግንነቱ የታወቀ ሰው አለ። አንድ ጠዋት የሠፈሩ ሰው ተሰብስቦ ቤቱ ይመጣል።
“ምነው በጠዋት ምን እግር ጣላችሁ ጎበዝ?” ሲል ጠየቀ።
የሠፈሩ ሰዎች ተወካይ፤
“ምን መሰለህ ጀግና ሆይ! በአካባቢያችን ያሉ ጠላቶቻችን መንደራችንን ዙሪያዋን ሊያቃጥሉ እያደቡ ነው። ነጋ ጠባ ስብሰባ የሚያካሂዱት በእኛው ላይ ነው። ሰላይ እየላክን የሚመጣው ወሬ በጣም ግራ የሚያጋባ፣ የሚያሰጋ ነው። እንዲያው ምን ይሻላል ልንልህ ነው የመጣነው?” ሲሉ አስረዱ።
ጀግናውም፤
“እስቲ ጊዜ ወስጄ ላስብበት ይላቸዋል”
ሰዎቹ አመስግነውት ሄዱ።
በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሰው ወደ ጀግናው ይሄዳሉ።
“እነዚህ ጎረቤቶቻችን እየተዘጋጁ ነው። እንዴት እያደረግህልን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ።
“እያሰብኩበት ነው። አንድ ቀን እንዋጋለን። በለስ የቀናን ዕለት እናሸንፋለን አይዟችሁ” ብሎ ይመልስላቸዋል።
ሰዎቹ በየሳምንቱ እየተመላለሱ “ዝግጅትህ ምን ደረሰ? ተሳካልህ ወይ?” ይላሉ። እሱም “እየተዘጋጀሁ ነው፤ አይዟችሁ” ይላል።
እንዲህ እንዲህ ሲባል ስድስት ወራት ያህል እንዳለፈ፤ አንድ ማለዳ ሰዎቹ ከመምጣታቸው በፊት ጀግናው ወደ ቤታቸው ይመጣል። ሁሉም ተደናገጡ። ስንቅም አዘጋጁ ሳይለን፣ ወደ ጦርነት እንሂድ ሊለን ነው እንዴ፤ በሚል ክፉኛ ስለሰጉ ሁሉ ነገራቸው ተረባብሿል።
“ምነው ጌቶቼ የተደናገጣችሁ ትመስላላችሁ? ስትመኙት የነበረው ጦርነት  ሲቃረብ ትሸበራላችሁን?” ሲል ጠየቀ።
ተወካዩ አዛውንትም፤
“ኧረ የለም። ያስደነገጠን ጦርነቱ አይደለም። አለመዘጋጀታችን ነው።”
“እኔን ተዘጋጀህ ወይ ስትሉኝ አልነበረም?”
“መሪያችን በመሆንህ፤ ይህን አድርጉ፣ በዚህ በዚህ ተዘጋጁ ትለናለህ ብለን ስንጠብቅ ነበር”
“አሁን የመጣሁት እሱን ልነግራችሁ ነው”
“እሺ የምትሰጠንን መመሪያ ሁሉ እንፈጽማለን”
“እንግዲያው ወደ ጎረቤታችን ሂዱና እንዴት ልታስተዳድሯቸው እንደምትፈልጉ ንገሯቸው”
ሁሉም አነጋገሩ ግራ ገብቷቸው፤
“ይህን እንዴት ለማድረግ እንችላለን። ጠላቶቻችን ሆነው ከመሬት ተነስተን እንግዛችሁ ብንላቸው ይቀበሉናል?”
ጀግናውም፤
“ከሦስት ቀን በፊት ጀምሮ ከጠላቶቻችን ጋር ስዋጋ ነበር። ድንገት ሄጄ ባላሰቡት ቀንና  ሰዓት ድምጥማጣቸውን አጥፍቻቸዋለሁ። አሁን ሁሉም ለኔ ገብረዋል። መመሪያ ስጠን ስላሉኝ ሰዎች እልካለሁ ብያቸዋለሁና ቶሎ ሂዱ”አላቸው።
“ለኛም የማትገመት ሆንክብንኮ? ነገርህ ሁሉ ያልታሰበ ሆነ?” ብለው በመገረም ጠየቁት።
“መሪ በተጠበቀበት መንገድ አለመምጣቱ የተለመደ ነው- ተገቢም ነው ለማንም ቢሆን። ድሉ የሚጀምረውም ከዚያ ነው” አላቸው።
***
ሮበርት ግሪን የተባለ ጸሐፊ “አርባ ስምንቱ የስልጣን ህግጋት” በተባለው መጽሐፉ፤ “ሌሎችን ምንጊዜም ልብ የሚያንጠለጥል ሽብር ውስጥ ክተታቸው። በተጠበቅኸው መንገድ የአለመሄድህን ዘዴ በየልባቸው ዝራ። ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ድርጊት የማወቅ የማይነካ ጥምና ሱስ ያለባቸው ፍጡራን ናቸው። በተጠበቅኸው መንገድ ከሄድክላቸው ድርጊትህን በቀላሉ ይቆጣጠሩታል። ስለዚህ ሁኔታውን ገልብጠህ አስቀምጠው። ሆነ ብለህ በተጠበቀው መንገድ የማትሄድ ሰው ሁን። ነገረ-ሥራህ የማይታወቅ፤ ተለዋዋጭ ጠባይ የምታሳይ ከሆንክ፤ ሰዎች ግራ-ይጋባሉ። ሚዛናቸውን ይስታሉ። ሲጨነቁ ይውላሉ። ድርጊትህ ምን እንደሆነ ሲመራመሩ ራሳቸውን ይጨርሳሉ። እያደርም ሽብር ይፈጥርባቸዋል” ይላል። በኢትዮጵያ የአመራር መድረኮች ይህን ፈሊጥ የሚጠቀሙ አያሌ መሪዎች፣ ኃላፊዎች፣ ሥራ-አስኪያጆች ወዘተ  አይተናል። መሪውም ተመሪውም በዚህ ሰንሰለት ተሳስረው ይኖራሉ። ሰብሳቢና ተሰብሳቢ በዚህ መንገድ ተቆልፈው ይገኛሉ። ድንገተኛ እርምጃና ያልተጠበቀ መንገድን መጠቀም ሌላውን ግራ ያጋባል። ጥንት “የመወቃቀስ  ጉባዔ” “የመመካከሪያ ሸንጎ” የነበረው፤ ቆይቶ ወደ “ሂስና ግለ-ሂስ”፤ እጅግ ሰነባብቶ ደግሞ “ግምገማ” ወደተባለ ደረጃ ተሸጋገረ። የስብሰባ አውጫጪኝ፤ በተጠበቀው መንገድ አለመሄድን እንደ ሁነኛ ዘዴ ሥራ ላይ ሲያውል ተመልክተናል። በተሰብሳቢው ላይ የፈጠረውን ሽብር ግን ቤቱ ወይም ልቡ ይቁጠረው። “ቅርበት ከቀረጥ አያድንም” እንዲሉ አውጫጭኙ ወገንንም አይምርም። ስለዚህ ሥጋትና-ሽብር-ተኮርነቱ ከሰብሳቢዎቹ በስተቀር የሁሉም የጋራ ሀብት ነው።
ከሞላ ጎደል መሪዎች እንደ ናፖሊዮን ቦናፓርት፤ “የመጨረሻው ከፍተኛ አደጋ የሚደርሰው በድል ወቅት ነው” የሚለውን አባባል ሳያምኑበት አይቀሩም። ስለዚህ አንድ ድል በተጎናፀፉ ቁጥር መንታ ስጋት ይወርራቸዋል። አንድም ከባላንጣ፣ አንድም ከወገን። ስለዚህም እከሌ ከእከሌ ሳይሉ ጅራፋቸውን ያጮሁበታል። አንዳንዴም ጅራፉ ለህዝቡ ይተርፋል። ምነው ቢሉ፤ የጅራፉን ጩኸት የሰሙ ትናንሽ አለቆችና ባለሥልጣናት በየጉያቸው የያዙዋትን ትናንሽ አለንጋ እያወጡ ወደ ህዝቡ (ዜጋው) ይሰነዝራሉና ነው። ይሄኔ ሥጋቱ ለአገር ይሆናል።
ተገዥዎች ከገዢዎች የሚማሩት ብዙ ነገር ነው። ከዚህ ውስጥ በድንገት አቅጣጫ መቀየር፣ ያልታቀደ የሚመስል ንግግር መናገር፤ ሰው በታቀደ መንገድ ሲሄድ እነሱ ባልታቀደ መንገድ መሄዳቸውና የመሳሰሉት ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው።
ታዋቂው የቼዝ ተጫዋች ቦቢ ፊሸር ከዓመታት በፊት ተጋጣሚውን ሩሲያዊ ስፖስኪን ባልተጠበቀ መንገድ ሲረታው፤
“የፊሸር ልዩ ማሸነፊያ ዘዴ ምርጥ የሚባለውን መንገድ መፈለጉ ብቻ ሳይሆን፤ አብሮት የሚጫወተውን ሰው የሚረብሽና የሚያሸብረውን ጠጠር ማንቀሳቀሱ ነው” ተብሎለት ነበር።
ጥበቡ ይሄው ነው። ይሄ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ማህበራትና በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊያስተውሉት የሚገባ ጥበብ ነው። ብልህ ከአሸናፊም ከተሸናፊም ይማራል፤ እንዲል!
አለቆቹ አሳቻ መንገድ በመረጡ ቁጥርና ኃላፊዎቹ ያልተጠበቀ ዘዴ በተጠቀሙ ቁጥር ግራ እሚጋባው ህዝብ ሚሥጥሩና ጉዳዩ ላይ የሚደርሰው ከመሸ ነው። የነቃ ሲቪል ማህበረሰብ የመሪዎቹን አካሄድ ያስተውላል። የነቃ ሲቪል ማህበረሰብ የአለቆቹን አካሄድ ለመቆጣጠር የፈጠነ እይታና ንቃትን በየጊዜው ያዳብራል። የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ሙስናን ያስተውላል፤ ይዋጋል። ጊዜያዊ ዘዴን ከዘላቂ እስትራቴጂ ለይቶ ያያል። ከሁኔታዎች ፍጥነት ጋር ይራመዳል። አለበለዚያ “ሌባ ሀሙስ ጨፍሮ፣ ውሻ አርብ ይጮሃል” እንደሚባለው ይሆናል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ፣ አልሸባብና አይኤስ ኢትዮጵያውያንን መመልመላቸው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ተናገሩ፡፡ ቃል አቀባዩ ይህንን የተናገሩት ለቪኦኤ ሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው።  
“ኢትዮጵያ ጠንካራ የመረጃ አሰባሰብና የቡድኖቹን እንቅስቃሴ የማክሸፍ ብቃት ስላላት፣ ቡድኖቹ ድንበር ዘለል ጥቃት ይፈጽሙብኛል ወይም የጸጥታ ስጋት ይፈጥሩብኛል” የሚል ስጋት እንደሌላት ነቢዩ መናገራቸው በዘገባው ተገልጿል። በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቅንጅት በሚቆጣጠሯቸው የሶማሊያ አካባቢዎች ከአልሸባብ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የኢትዮጵያ የጸጥታ መዋቅር ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በሶማሊያ የፑንትላንድ ግዛት ባለስልጣናት፣ ተራራማ በሆነው አል ሚስካድ አካባቢ ከአይኤስ ጋር ወግነው የሚዋጉ ኢትዮጵያውያንን መማረካቸውንና መግደላቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡  
በሃምሌ ወር የፑንትላንድ የጸጥታ ሃይሎች፤ “ከኢትዮጵያ፣ ከማላዊና የመን ታጣቂዎች ጋር አብሬ በመሆን ተዋግቻለሁ” በማለት የተናገረ፣ አንድ ዛንዚባራዊ የአይኤስ ታጣቂ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም አስታውቀው ነበር።
የፑንትላንድ የቀድሞ የስለላና የፖሊስ አዛዥ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል አብዲ ሀሰን ሁሴን፤ ከአይኤስ ጋር የሚዋጉ የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር ከ500 እስከ 600 እንደሚገመት ለሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ጠቁመዋል፡፡ ይህ አሃዝ በይፋ ያልተረጋገጠ ቢሆንም፣ “ከተዋጊዎቹ መካከል ኢትዮጵያውያን ግን ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል” ብለዋል፤ ብርጋዲየር ጄኔራል አብዲ።
የቀድሞ የአልሸባብ አባል የነበረው ኦማር መሐመድ አቡ አያን፤ ወጣቶችን ለመሳብ የቡድኑን ፕሮፓጋንዳ ወደ አማርኛ የሚተረጎም አንድ ኢትዮጵያዊ ሰባኪ ከእርሱ ጋር ይሰራ እንደነበር ተናግሯል።
ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለመመልመል የሚያደርጓቸውን ሙከራዎች በጥብቅ እንደሚከታተል መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡


ዶላር ከአዲስ አበባ ገበያዎች ጠፍቷል

መንግስት መዋቅራዊ ችግሮችን ካልፈታ በስተቀር የብር የመግዛት አቅምን ማዳከም ዘላቂ ለውጥ እንደማያመጣ ተገለጸ፡፡ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡ አንድ የምጣኔ ሃብት ምሁር፣ ከሰሞኑ የወጡት የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ “የሚጣረሱ ነገሮች አሉ” ብለዋል።
የምጣኔ ሃብት ምሁርና በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ማሕበር ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር)፣ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን አስመልክተው ሲናገሩ፤ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ጥንካሬን መፍጠር ዋነኛው ዓላማ ሲሆን፤ በተጓዳኝም ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚ በመገንባት ኢንቨስትመንትን ማዘመንና የንግድ ስርዓቱን ቀልጣፋና ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ፣ ምርት፤ ምርታማነትና የምርት አቅምን መጨመር፣ የመንግስት ተቋማትን አቅም ማሻሻል ተጨማሪ ዓላማዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ብዙ ነገር ተነካክቷል ያሉት ምሁሩ፤ “ማሻሻያው በተለይ ትኩረቱ ያጠነጠነው በምንዛሬ ማሻሻያ ላይ ነው።” ብለዋል፡፡
“እስካሁን ማኔጅድ ፍሎቲንግ ሬት (ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ የሚገባበት የውጭ ምንዛሬ ስርዓት) ነበር። ሰዎች በፈለጉት መጠን ከባንክ በነጻነት ምንዛሬ አያገኙም ነበር። አሁን ግን ገበያ መር የምንዛሬ ስርዓት (ፍሎቲንግ ኤክስቼንጅ ሬት) እንዲሆን ተደርጓል። ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ጣልቃ ገብነት ይቀራል” ሲሉ ተናግረዋል።
አሁን በወጡት የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ የሚጣረሱ ነገሮች እንዳሉ ጣሰው (ዶ/ር) ያመለክታሉ። “አንደኛ ጠንካራ የፊስካል ፖሊሲ ይኖረናል። መንግስት የራሱን አቅም ያጠናክራል፤ገቢውን ያሻሽላል እያለ ነው። እነዚህ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ነገሮች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
 ሌሎቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ‘የማሻሻያ ማዕቀፍ’ ተባሉ እንጂ በአንድም በሌላም መልክ ይህንን ለውጥ ለማጠናከር የወጡ መሆናቸውን ምሁሩ  ይጠቁማሉ። “መንግሥት ራሱ ፈቅዶ ያወጣው ነው? ወይስ በጫና የመጣበት ነው? የሚለው በአንድ በኩል የሚታይ ነው” ሲሉ የሚሞግቱት እኚሁ ምሁር፤ መንግስት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ረዥምና ሰፊ ጊዜ የወሰደ ድርድር ስለማድረጉ አውስተው፤ “መንግስት በተወሰነ መልኩ አሁን የወሰዳቸውን እርምጃዎች ላለመውሰድ ፈራ ተባ ሲል ቆይቶ፣ በመጨረሻም ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እጁን ሰጥቷል -- በግልጽ ባይናገረውም።” ብለዋል።
አክለውም፤ “መንግሥት በራሴ ማሻሻያ ‘አደረግሁ’ ይበል እንጂ አብዛኛዎቹ ማሻሻያዎች በተለምዶ የአይኤምኤፍ ‘የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ’ (Washington Consensus) ተብለው የሚታወቁ የፖሊሲ እርምጃዎችን ነው፣ መንግስት እንዲቀበላቸው የተደረጉት። ከፖሊሲዎቹ መካከል፣ ወደ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርዓት መምጣት አንደኛው ነው። ሁለተኛው የማዕከላዊ መንግስት የታክስና የወጪ ፖሊሲ ለውጥ (fiscal policy reform) ነው። ሦስተኛው በወለድ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ አስተዳደር (interest rate based monetary framework) ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ሦስት ጊዜ ከዶላር አንጻር የብር የመግዛት አቅምን እንዳዳከመች የሚያወሱት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፤ የመጀመሪያው በደርግ የሚመራው መንግስት ወድቆ ኢሕአዴግ መንበረ ስልጣኑን ሲቆጣጠር፣ አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ “Structural Adjustment Program (SAP)” በተባለው መርህ መሰረት፣ ኢትዮጵያ የንግድ ሚዛኗን ለማስተካከል፣ የወጪ ንግዷንም ፈር ለማስያዝ የብር የመግዛት አቅምን አውርዳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  
እ.ኤ.አ. በ2010 በተወሰነ ፐርሰንት እንዲቀንስ ለማድረግ ተመሳሳይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ በ2010 ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ይህ እርምጃ መቀጠሉን ምሁሩ በአንክሮ ያብራራሉ። እርምጃው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ አካል በመሆን፣ የምንዛሬ ስርዓቱ በገበያ እስከሚወሰን ድረስ ተብሎ ቀስ በቀስ የመግዛት አቅሙ እንዲወርድ ተደርጎ እንደነበር ጣሰው (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
“እነዚህን እርምጃዎች ተከትሎ ኤክስፖርታችን አመርቂ ለውጥ አላመጣም። የምንልከው የግብርና ውጤቶችን  ነው። እነዚህ ምርቶች ደግሞ የገንዘብ የመግዛት አቅምን በማውረድ የሚያድጉ አይደሉም። ዋጋቸውም በዓለም አቀፍ ገበያ ነው የሚወሰነው። ለዋጋ ወጥ አለመሆን (price volatility) የተጋለጡ ናቸው” የሚሉት ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር)፤ “ምርቶቻችን የተሻሉ ተወዳዳሪዎች ሆነው የዓለም አቀፍ ገበያ ላይ አልተገኙም። በዚያ ምክንያት የኤክስፖርት ገቢያችን አልጨመረም። ጭማሪም ካለ፣ የአገር ውስጥ ምርታችን ጥሩ በሆነበት፤ በዓለም አቀፍ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ በሚንርበት ጊዜ ነው እንጂ ያን ያህል በተደረጉ የማዳከም እርምጃዎች ጠንከር ያሉ ለውጦች አይታዩም” ብለዋል።
አክለውም፤ “እ.ኤ.አ. 2018 ላይ ኤክስፖርታችን ከGDP (አገራዊ ጥቅል ምርት) አንጻር ያለው ድርሻ 8 ነጥብ 2 በመቶ ነበር። እ.ኤ.አ. 2022/2023 አካባቢ ወደ 6 ነጥብ 7 አሽቆልቁሏል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ የአገሪቱ የገቢ ንግድ መጠን 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። ኤክስፖርት የጨመረው ግን በ590 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ከእነዚህ ቁጥሮች በመነሳት የንግድ ሚዛን ጉድለቱ “ጠብቧል፣ አልጠበበም?” የሚለውን መረዳት ይቻላል፤ አልጠበበም። እንዲያውም እየሰፋ ሄዷል።” ሲሉ ያስረዳሉ።
 “በኢኮኖሚው ያለው አብዛኛው ችግር መዋቅራዊ ችግር ነው፤ እርሱን ማስተካከል እንጂ የብር የመግዛት አቅምን በማዳከም የሚመጣ ለውጥ ለጊዜው አይታየኝም።” የሚሉት  የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ያገኘውን ድጋፍና ብድር የያዘ ተጨማሪ በጀት፣ በቅርቡ ለፓርላማ አቅርቦ እንደሚያስጸድቅ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ባለፈው ረቡዕ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸውን በማሳያነት ጠቅሰው “ማባበያ ነው፤ ብለዋል።
“በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት 2018 ላይ የተደረገው የመግዛት አቅምን ማዳከም፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ነው ያመጣው። የሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ እየጨመረ መጥቷል፤ምክንያቱም እኛ አምራች አይደለንም፤ለብዙ ዕቃዎች በገቢ ንግድ ላይ ጥገኛ ነን። አሁንም ይህ የማዳከም ሂደት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋና የኑሮ ውድነት መናርን ይዞ ይመጣል።” ሲሉ ተችተዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ሚኒስትሩ “ይጸድቃል” ያሉት ተጨማሪ በጀት ለዝቅተኛ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች ለሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ እንዲሁም ለነዳጅ፣ ዘይት፣ ማዳበሪያና መድኃኒት ድጎማ እንደሚውል ተነግሯል። ጣሰው ታደሰ (ዶ/ር) ግን የድጎማውን ዘላቂነት በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት፡፡
“ብዙ ጊዜ እነ አይኤምኤፍ ድጎማን ትኩረት አድርገው ድጋፍ አይሰጡም። የሚመጣውን ቀውስ የመንግስት ባለስልጣናት ያውቁታል። በሰው ዘንድ ያለውን ድንጋጤ ለማርገብ ካልሆነ በስተቀር፣ አንደኛ ድጎማ ቢሰጥም አብዛኛው ሰው የኑሮ ውድነትን መቋቋም አይችልም። የኑሮ ውድነቱ ጫፍ ላይ ደርሷል። ድጎማው እስከ መቼ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ፖሊሲውም ግልጽ አይደለም። በአንድ ሌሊት የተሰራ የፖሊሲ ማዕቀፍ ይመስላል። ድጎማውም ጊዜያዊ ‘ነው’ ነው የሚለው። በተወሰኑ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ድጎማ ‘እንሰጣለን’ ይላል። መሰረታዊ በሚባሉት ላይ ማለት ነው። በቅርብ ወራት ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሲፈጠር ያንን ለማስታገስ እንደ ነዳጅ፣ መድሐኒት፣ ማዳበሪያና የመሳሰሉ አስፈላጊ ምርቶች ላይ ድጎማ እንደሚደረግ ተገልጿል። አነስተኛ ገቢ ላላቸው መንግስት የደመወዝ ጭማሪ ያደርጋል። መንግስት በሴፍቲኔት ለታቀፉ ሰዎች ድጋፍ ‘አደርጋለሁ’ ነው ያለው። ምን ያህል በመቶ ድጎማ ይደረጋል? ስለሚለው በዝርዝር አልወጣም። ሁለተኛው ‘ጊዜያዊ’ ማለቱ ግልጽ አይደለም። ድፍን ነው። እስከ መቼ እንደሆነ አልገለጸም። የዋጋ ንረቱ ለብዙ ዓመታት እየቀጠለ ከሄደ፣ የመንግስት አቅጣጫ ምን ይሆናል? በዘላቂነት ድጎማ ለመስጠት አቅም አለው ወይ? አቅምም ስለሌለው ነው ‘ጊዜያዊ’ ተብሎ የተቀመጠው።” በማለት አብራርተዋል።
በሌላ በኩል፣ ዶላር ከአዲስ አበባ ገበያዎች መጥፋቱን ብሉምበርግ የዜና አውታር ዘግቧል። በውጭ ምንዛሬ ግብይቶች የዶላር ዕጥረት የተፈጠረው፣ “የብር ምንዛሬ ይበልጥ ሊዳከም ይችላል በሚል ግምት ሰዎች ዶላር መደበቅ በመጀመራቸው” መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ የጥቁር ገበያ መንዛሪዎች አንድ ዶላር በ115 ብር ለመግዛት ዝግጁ መሆናቸውን እንደተረዳ የጠቀሰው ብሉምበርግ፤ ነገር ግን አብዛኛዎቹ መንዛሪዎች ዶላር የሚመነዝር ሰው እንዳጡ መናገራቸውን ጠቁሟል።
ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2027 እስከ 2028 ባለው ጊዜ ውስጥ ከውጭ ዕዳ ሽግሽግ የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የብድር እፎይታ ያስፈልጋታል ብሏል። ድርጅቱ ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ጉድለት እንደሚኖርባትም አስታውቋል። ይሁን እንጂ የመንግስት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወርና የብድር መክፈያ ጊዜን የማራዘም ሁኔታዎች፣ የገንዘብ ጉድለቱን ወደ 10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወርደው ድርጅቱ አመልክቷል።
መንግስት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ያስታወቀው ባለፈው እሁድ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲሆን፤ ከዚያ ቀደም ብሎ ብሔራዊ ባንክ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በወለድ ተመን ላይ ወደተመሰረተ የገንዘብ ስርዓት እንደሚሸጋገር ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

....ስንወለድ የሚበጠሰው ከእናታችን ጋር የተያያዝንበት እትብት ውጪ ከአባታችን የተያያዝንበት  ሁለተኛ እትብት አለ የሚል ፍልስፍና ነው የመጽሐፌ አዕማድ።

በሦስት መንገድ ለማየት ሞክሬአለሁ። አባት ማጣት፤ አባት ማምለክ እና አባት መጥላት በሚሉ ምዕራፎች። ከዱር እንስሳ አንበሳን አጠናሁ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይስሀቅ ያቆብን ትቶ ኤሳውን መባረኩን አመጣሁ ከዛ...

...ሦስተኛ ፊልሞችን እንደ ዋቢ መጻሕፍት ተጠቅሜ በትንታኔ ደገፍኩት። ወጥ ልቦለድ ነው። 215 ገጽ ይረዝማል። postmodern ሲሆን፤ ስነ-ልቦና ከልብ-ወለድ ጋር ዝምድና እንዳለው ያሳየሁበትም ስራዬ ነው።

 ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ጥበቃ፣ ቅርስ፣ ታሪክ እና ባህል ዙሪያ ሲሰራ የቆየ ኢትዮጵያዊ የጉዞና ጉብኝት ጋዜጠኛ ነው። ከዚህ ቀደም "የመንገድ በረከት"፣ "ጎንደርን ፍለጋ"፣ "ሀገሬን" እና "ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች" የተባሉ መጻሕፍትን አሳትሞ ለአንባቢያን አድርሷል።

የተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም "መንገድ ዐይኑ ይፍሰስ..." የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ የተለያዩ አካባቢዎችን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ትረካዎች ይዟል።

Wednesday, 31 July 2024 07:05

የዘላለም ጥግ

 የህይወታችን ዓላማ ደስተኛ መሆን
ነው።
ዳላይ ላማ
 የምትኖረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤
በትክክል ከኖርከው ግን አንዱ በቂ ነው።
ማ ዌስት
 ገንዘብና ስኬት ሰዎችን አይለውጡም፤
የነበረውን ብቻ ነው የሚያጎሉት።
ዊል ስሚዝ
 ስለ ህይወት ለመጻፍ መጀመሪያ አንተ
ራስህ መኖር አለብህ።
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
 እኔ ትችት እወዳለሁ። ጠንካራ
ያደርግሃል።
ሌብሮን ጄምስ
 በእውነቱ እራስህ የምትናገረውን
ከመስማት ብዙም አትማርም።
ጆርጅ ክሉኒ
 ህይወት ብስክሌት እንደ መጋለብ ነው።
ሚዛንህን ለመጠበቅ መጓዝህን መቀጠል
አለብህ።
አልበርት አንስታይን
 ለህይወት በጣም ጤናማው ምላሽ
ደስተኝነት ነው።
ዴፓክ ቾፕራ
 እያንዳንዱ ቅፅበት አዲስ ጅማሮ ነው።
ቲ.ኤስ.ኢሊዮት
 ማለም ስታቆም መኖር ታቆማለህ።
ማልኮልም ፎርብስ


የተለያዩ ወጎችንና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ የምትታወቀው ደራሲ ሕይወት እምሻው፤ ‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ›› የተሰኘ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ መጽሐፍ ለተደራሲያን ልታቀርብ ነው።

መጽሐፉ የፊታችን  ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. አራት ኪሎ በሚገኘው ኢክላስ ሕንፃ፣ ዋልያ መጽሐፍ መደብር ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ የጥበብ አፍቃሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል፡፡

‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ››፤ 27 አጫጭር ታሪኮች የተካተቱበትና በ208 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤  በ300 ብር ለገበያ  እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

ደራሲዋ ከዚህ ቀደም ‹‹ባርቾ›› ፣ ‹‹ፍቅፋቂ›› እና ‹‹ማታ ማታ›› የተሰኙ የወግና የአጫጭር ታሪኮች መጽሐፍትን ለተደራሲያን ማቅረቧም ይታወሳል፡፡

 ባለፈው ሳምንት እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን ይዘን ለጥቂት ቀናት እረፍት ወደ ሃዋሳ ተሻግረን ነበር- ለመዝናናት። እንደሚታወቀው ሃዋሳ ከአገራችን ምርጥ ከተሞች ተጠቃሽ ናት፡፡
አየሯ ምቹ ነው፡፡ ውብ መልክአ ምድር የታደለች ናት፡፡ በሃይቆች ተከባለች፡፡ በዚያ ላይ እንደ ኃይሌ ሪዞርት ዓይነት ባለ 4 ኮከብ ምርጥ  ሆቴሎች ታንጸውላታል፡፡ ቢያንስ ሁለት ሆቴሎች እንግዶቻቸውን በመኪና ከአየር ማረፍያ  እንደሚቀበሉና  እንደሚሸኙ  አይተናል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች እንደሚኖሩ እንገምታለን፡፡
በዚህች አጭር ማስታወሻዬ፣ እኔና መላው ቤተሰቤ በሃዋሳው ኃይሌ ሪዞርት የቀናት ቆይታችን የገጠመንንና ያስተዋልነውን ለመመስከር እወዳለሁ፤ ሊመሰከርለት   ይገባልና፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም የኃይሌ ሪዞርቶች በእንግዳ አቀባበላቸውና መስተንግዶአቸው የሚታሙ አይደሉም፤ ይልቁንም ለብዙዎቹ የአገራችን ሆቴሎች በአርአያነት የሚጠቀሱ  እንጂ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደው በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን ብዙ የተለፋበት ነው፡፡ ልብ በሉ፤ ኃይሌ በብቃት የሰለጠኑ የሆቴል ባለሙያዎች በአገሪቱ  እንደሌሉ ሲገነዘብ መፍትሄ ነው ብሎ የወሰደው እርምጃ፣ የሆቴል ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም መክፈት ነው፡፡ ለዚህ ነው አሁን 10 በሚደርሱ ሪዞርቶቹ ተመሳሳይ (ደረጃውን የጠበቀ) የእንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ ማቅረብ የቻለው፡፡ እርግጠኛ ነኝ የራሱን የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ለማሟላት የከፈተው የሆቴል ማሰልጠኛ ተቋሙ፣ የአገርንም የሆቴል ባለሙያ  እጥረት ይቀርፋል፡፡ ኃይሌ ሲከፍተውም ለአገርም ጭምር አስቦ እንጂ ለራሱ ሆቴሎች ብቻ እንደማይሆን መገመት ይቻላል፡፡
ወደ ኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ ስንመጣ፣ ከህንጻው አሰራርና ህንጻው ካረፈበት መልክአ ምድር ይጀምራል - ውበቱና መለያው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄና በዕውቀት መሰራቱን መመስከር ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሆቴሉ ሰራተኞች የተሰጣቸው ሥልጠና ቀላል እንዳልሆነ መስተንግዷቸውና አገልግሎት አሰጣጣቸው ይናገራል፡፡
የመስተንግዶ ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጠቅላላ የሆቴሉ ሠራተኞች (የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎቹ፣ የእድሳትና ጥገና ሰራተኞቹ፣ ሴኩሪቲዎቹ እንዲሁም ሃውስ ኪፐሮቹና አትክልተኞቹን ጨምሮ) እንግዶችን አይተው በዝምታ አያልፉም፤ ወዳጃዊ የአክብሮት ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ግራ የገባው ወይም አንዳች ነገር የቸገረው እንግዳ ከገጠማቸው ከመቅጽበት ደርሰው ለመርዳት ይተጋሉ፡፡
በሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ እስካላችሁ ድረስ በፈገግታ የተሞላ የአክብሮት ሠላምታ የማይሰጣችሁ አንድም ሠራተኛ አታገኙም። በዚህም የተነሳ ፈፅሞ ባይተዋርነትና እንግድነት  አይሰማችሁም፤ የሆቴሉ እንግዳ ብትሆኑም። ባለፋችሁ ባገደማችሁ ቁጥር ፈገግታና ሰላምታ በሽበሽ ነው፤ በኃይሌ ሪዞርት፡፡ ምግቡም ቢሆን ግሩም ነው፤ ጣዕሙ--ዓይነቱ---መጠኑ አጥጋቢ ነው፡፡
በመስተንግዶው፣ በምግቡ ወይም በመኝታ ክፍል አገልግሎቱ አሊያም በሌላ ቅር ከተሰኛችሁ ደግሞ መፍትሄው ቀላል ነው፤ ከናንተ የሚጠበቀው ቅሬታችሁን ለቅርብ ሃላፊ ማቅረብ ብቻ ነው። አትጠራጠሩ፤ ፈጣን ምላሽ ታገኛላችሁ። ያውም አጥጋቢ ምላሽ፡፡
አሁን ይህችን ማስታወሻ ለመከተብ ሰበብ የሆነኝን አንድ የኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ አስገራሚ ገጠመኝ ላጋራችሁ፡፡ ነገሩ የተከሰተው የመኝታ ክፍላችንን ተከራይተን እንደገባን ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ ባላወቅነው ምክንያት (ምናልባት ተዘንግቶ ሊሆን ይችላል) ወደ መኝታ ክፍላችን ስንገባ  የተለመደው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ሳይደረግልን ቀረ፡፡ በሆቴሉ አሰራር መሰረት ወደ ክፍላችን ስንገባ፣  የፍራፍሬ ጭማቂዎች ሊቀርብልን ይገባ ነበር- የእንኳን ደህና መጣችሁ የቤቱ ግብዣ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ቅሬታችንን በቀጥታ ለሆቴሉ አስተዳደር አቀረብን።
ቅሬታችን ታዲያ እንደ ብዙዎቹ የአገራችን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት  ጆሮ ዳባ ልበስ አልተባለም። ወዲያው ነው ምላሽ የተሰጠን፡፡ በሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተፃፈና የተፈረመ የይቅርታ ደብዳቤ - የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ከተሞላ  ቅርጫት ጋር መኝታ ክፍላችን ድረስ መጣልን፡፡ ይቅርታና ካሣ እንደማለት ነው፡፡
ከሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእንግሊዝኛ የተፃፈልንን የይቅርታ ደብዳቤ (ለኢትዮጵያውያን በአማርኛ ቢሆን ይመረጥ ነበር)  በግርድፉ ተርጉሜ ታነቡት ዘንድ  ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የሃዋሳው ኃይሌ ሪዞርት አስተዳደር፣ ለቅሬታችን ለሰጠን በአክብሮት የተሞላ ፈጣን ምላሽ  በራሴና በቤተሰቤ ስም ከልብ ላመሰግንና ላደንቅ እወዳለሁ። ከዚህ በኋላ እኔና ቤተሰቤ፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ ቁጥር አንድ ምርጫችን እንደሚሆን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ እንደ ሩጫው ሁሉ፣ በሆቴል ኢንዱስትሪውም ሪከርድ እየሰበረና ታሪክ እየሰራ መሆኑን እያስተዋልን ነው! ለራሱም ለአገሩም፡፡ ሌሎች የአገራችን ሆቴሎችና በአገልግሎት ዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ  ከኃይሌ ሪዞርት ብዙ ሊማሩ እንደሚችሉ ሳልጠቁም አላልፍም። እነሆ ደብዳቤው፡-
ለውድ ወ/ሮ ሃና ጎሳዬ፡-
በኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ ቡድን ስም፤ ለገጠማችሁ ችግር ልባዊ ይቅርታ ልጠይቅ እወዳለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለተከሰቱት አጠቃላይ የአቀባበል ክፍተቶች ይቅርታ እንጠይቃለን፤ እርስዎ ከጠበቁን በታች በመሆናችንም በጣም አዝነናል። በመሆኑም፤ ይህ ሁኔታ ዳግም እንደማይከሰት ልናረጋግጥልዎ እንፈልጋለን፡፡
በሁኔታው በእጅጉ እያዘንኩ፤ ይህችን ትንሽዬ የፍራፍሬ ግብዣ ይቀበሉኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ። በሃይሌ ሪዞርት ሀዋሳ ባደረጋችሁት ቆይታ ሊፈጠርባችሁ የሚችለውን የተዛባ ምስል ለማንጻት ላደርግ የምችለው ትንሹ ነገር ይህ ነው።
የዋና ሥራ አስኪያጁ ስምና ፊርማ

Page 12 of 726